You are on page 1of 4

የሰበር መ/ቁ 43514

የካቲት 25 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ

መንበረፀሐይ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- አዲስ አበባ አስተዳደር ፍትህና ሕግ ጉዳዮች ቢሮ ነ/ፈጅ ፍቅርተ አጅበው ቀረቡ፡፡

ተጠሪዎች፡- 1. የፌዴራል አገር ውስጥ ባለስልጣን ዐ/ሕግ ተፈራ አጥላው ቀረቡ

2. ብንዮማ ኃላ.የተ.የግል ማህበር - በሌለበት የሚታይ ነው፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ጉዳዩ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 መሠረት መቃወሚያን ለማቅረብ ስለሚችሉ ወገኖቼን

የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ 1 ኛ ተጠሪ ከአሁኑ 2 ኛ ተጠሪ ለሚፈለገው እዳ

በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ወረዳ 3 ቀበሌ 32 ቁጥሩ 1244 የሆነው ቤት በድርጅትነት እንዲሸጥ እና

እዳው እንዲከፈለው ባቀረበው አቤቱታ እንዲሸጥ የታዘዘው የቤት ቁጥር 1244 የሆነው በመንግሥት

በአዋጅ ወርሶ የሚያስተዳድረው ቤት ስለሆነ ለ 2 ኛ ተጠሪ እዳ የመንግሥት ቤት ተሸጦ ሊከፈል

አይገባም 2 ኛ ተጠሪም በዚህ በተጠቀሰው ቤት የሚታወቁ ስላልሆኑ ቤቱ በእዳ እንዳይሸጥ አመልካች

ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ በአመልካች በኩል

የቀረበውን መቃወሚያ የአመልካች አስተዳር መዋቅር አካል የሆነው የወረዳ 03 ቀበሌ 32 መስተዳድር

ጽ/ቤት አቅርቦ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን አቤቱታ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት መጋቢት 10 ቀን

1994 ዓ.ም ውድቅ ማድረጉን፣ ይህም በአንድ በፍርድ ባለቀ ጉዳይ ላይ አመልካች በድጋሚ አቤቱታ

ማቅረቡ ከሥነ ሥርዓቱ ውጩ መሆኑን በምክንያትነት በመጥቀስ የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ

1
አድርጓል፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ

የስር ፍርድ ቤትን ውሣኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቷል፡፡ የአሁኑ የሠበር አቤቱታ የቀረበውን ይህንኑ የበታች

ፍርድ ቤቶችን ውሣኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ነገረ ፈጅ የካቲት 09 ቀን 2001 ዓ.ም በተፃፈ ሁለት ገጽ የሠበር አቤቱታ በበታች

ፍርድ ቤቶች ውሣኔ ላይ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽማል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው

አቀርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጨሩ፡ አመልካች የራሱን ሕጋዊ ሰውነት ያለውና በህጉም ሥልጣን የተሰጠው

ሆኖ እያለ የስር ፍርድ ቤቶች የአመልካቹ አስተዳደር መዋቅር አካል የሆነው የወረዳ 03 ቀበሌ 32

መስተዳድር ጽ/ቤት በክርክሩ ተቃሙሞ አቅርቦ ተቀባይነት አላገኘም በሚል የአመልካችን

የመቃወሚያ አቤቱታውን ውድቅ ያደረጉት አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 13(1(ሀ)ን አዋጅ ቁጥር

2/1995 አንቀጽ 29 እንደተሻሻለ (አዋጅ ቁጥር 4/2000)ን የሚፃረር እና የመንግሥትን ቤት ያላግባብ

ለግለሰብ እዳ መሸፈኛ ያደረገ መሆኑን በመዘርዘር በጉዳዩ የተሠጠው ውሣኔ እንዲሻር ዳኝነት

መጠየቁን የሚያሣይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ሊታይ ይገባዋል ተብሎ የ 1 ኛ

ተጠሪ ነገረ ፈጅ ነሐሴ 26 ቀን 2001 ዓ/ም በፃፉት ሁለት ገጽ የማመልከቻ መልሳቸውን ሲሠጡ 2 ኛ

ተጠሪ በተደረገለት ጥሪ መሠረት ባለመቅረቡ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ተደርጓል፡፡ የአመልካች ነገረ

ፈጅ በበኩላቸው ታህሳስ 23 ቀን 2002 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ በ 1 ኛ ተጠሪ ነገረ ፈጅ በኩል

በቀረበው መልስ ላይ የመልስ መልሳቸውን ሠጥተዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር

ከሠበር አቤቱታው መነሻ ለሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ

በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም አመልካች መቃወሚያ ውድቅ የተደረገው

ባግባቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሆኖ አግኝቶታል፡፡

ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአመልካች መቃወሚያ ውድቅ የተደረገው የአመልካች

አስተዳደር አካል የሆነው የወረዳ 03 ቀበሌ 32 አስተዳደር ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ ተቃውሞ አቅርቦ

2
ተቀባይነት ካጣ በኋላ አመልካች በጉዳዩ ላይ ተቃውሞ ማቅረቡ በፍርድ ባለቀ ጉዳይ በድጋሚ አቤቱታ

ማቅረቡ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 5 ድንጋጌን ያላገናዘበ ነው በሚል ነው፡፡

በመሠቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(1) መሠረት ባንድ ጉዳይ ሁለተኛ ክስ ወይም

ማናቸውንም ዓይነት ሌላ ክርክር ማቅረብ አይቻልም በሚል የተደነገገው በሕግ ሥለጣን የተሠጠው

ማንኛውም ፍርድ ቤት ክርክሩን ተቀብሎ የመጨረሻ የፍርድ ውሣኔ ከሰጠ በኋላ ቀድሞ በፍርድ

የተወሰነው ክርክር ሥረ ነገር እና የተያዘው ጭብጥ አንድ ዓይነት ከሆነ በክርክሩ ላይ የነበሩት ወይም

ከተከራካሪዎቹ መብት ያገኙ ሶስተኛ ወገኖች በዚያው ነገር አቤቱታ ሲያቀርቡ ነው፡፡

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 መሠረት የመቃወሚያ አቤቱታ የሚቀርበው ደግሞ በተያዘ ወይም

በተከበረ ንብረት ላይ መብት አለኝ የሚሉ ወገኖች ሲሆኑ አቤቱታቸው የሚቀርበውም በፍርድ

አፈፃፀም ምክንያት ንብረታቸው እንዳይወሰድ ነው፡፡ መቃወሚያውን ማቅረብ የሚችሉትም

በንብረቱ ላይ መብት አለን የሚሉ ወገኖች ስለመሆናቸው ድንጋጌው ያሳያል፡፡

ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ራሱ የክርክሩ ተካፋይ ያልነበረ መሆኑን የስር ፍርድ

ቤትም የተገነዘበው ጉዳይ መሆኑን የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል፡፡ የስር ፍርድ ቤት አመልካችን የክርክሩ

ተካፋይ እንደነበር ሊቆጥር ይገባል ወደ ሚለው ድምዳሜ ሊደርስ የቻለው ተቃውሞ አቀርቦ

ተቀባይነት ያላገኘው የወረዳ 3 ቀበሌ 32 አስተዳደር ጽ/ቤት ከአመልካች ጋር የአንድ አሰተዳደር አካል

ነው በሚል ምክንያት ነው፡፡ በእርግጥ አመልካችና የወረዳ 3 ቀበሌ 32 አስተዳደር ጽ/ቤት መስተዳድር

በአንድ መንግሥታዊ አስተዳደር ስር የሚገኙ ሲሆን አመልካች እና ወረዳ 3 ቀበሌ 32 አስተዳደር

ጽ/ቤት የመስተዳድሩ የበታች መስሪያ ቤቶች ከሆኑት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱ አካላት የየራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት ስልጣንና ተግባር ያላቸው በተለያየ የሥልጣን

እርከን የሚገኙ ስለመሆናቸው ከአዋጅ ቁጥር 361/95 ይህንኑ መሠረት በማድረግ ከወጡት ህጐች

አዋጅ ቁጥር 2/1995 እና 4/2000 የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባ መስተዳድር

ወረዳ 3 ቀበሌ 32 አስተዳደር ጽ/ቤት ከአመልካች የተለየ ሥልጣንና ተግባር ያለው ሲሆን በተለየ

የሥልጣን እርከን የማገኘው አመልካች ወረዳ 3 ቀበሌ 32 አስተዳደር ጽ/ቤት ተቃውሞ አቅርቦ

3
ተቀባይነት ስላላገኘ ብቻ አመልካች የክርክሩ ተካፋይ ነበር ሊባል የሚችልበትን ሕጋዊ ምክንያት

አላገኘንም፡፡ አልካች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ ከሌሎች የአስተዳደሩ አካላት የተለየ እና

የራሱ የሆነ መብትና ግዴታ ያለው አካል በመሆኑ ሌሎች የአስተዳደሩ አካላት የክርክር ተካፋይ

መሆናቸው አመልካች በራሱ የሚያቀርበውን ክርክር የሚከለክለው አለመሆኑን ይህ ችሎት ከላይ

የተጠቀሱትን ሕጐች በመመርመር በመ/ቁጥር 37502፣45101 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት

አስገዳጅ የሆነ የሕግ ትርጉም ሠጥቶበታል፡፡ በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካችን

መቃወሚያ ውድቅ ያደረጉት አግባብነት ያላቸውን ህጐች ባግባቡ ሳይመለከቱና

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(1) እና 418 ድንጋጌዎች ስር የተመለከተውን የሕጉን መንፈስ ሳያገናዝቡ

በመሆኑ ድምዳሜው የአመልካችን መብቶችንና ጥቅሞችን የማስጠበቅና የመከራከር መብትን

ያጣበበ፣ መሠረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን

ወስነናል

ውሳኔ

1. በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 63693 መጋቢት 29 ቀን 2000 ዓ.ም ተሰጥቶ

በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመ/ቁጥር 37789 ሕዳር 30 ቀን 2001 ዓ.ም የፀናው ውሣኔ

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሠረት ተሽሯል፡፡

2. ጉዳዩ ቀደም ሲል በፍርድ አልቋል ሊባል የማይችል በመሆኑ አመልካች በጉዳዩ ላይ ቀደም ሲል

በተሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 መሠረት መቃወሚያ ማቅረብ ይችላል

ብለናል፡፡ በዚህም መሠረት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአመልካችን አቤቱታ ተቀብሎ

በጉዳዩ ላይ ግራ ቀኙን አከራክሮ ተገቢውን ውሣኔ ይስጥበት ብለናል፡፡

3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

You might also like