You are on page 1of 4

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የሰ.መ.ቁ. 231644

ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም

ዳኞች፡- 1. ብርሃኑ አመነዉ

2. ረታ ቶለሳ

3. በእዉቀት በላይ

4. ቀነዓ ቂጣታ

5. ኑረዲን ከድር

አመልካች፡……ሕጻን መቅደስ ሁሴን ተወካይ የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ - የቀረበ የለም

ተጠሪ፡………...1. አቶ ማንዴ መንግስቱ - ጠበቃ ጥበበስላሴ አበራ - ቀረቡ

2. አቶ አበራ ማሞ - የቀረበ የለም

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ይህ የጉዳት ካሳ ክርክር የተጀመረዉ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን
አመልካች የሥር ከሳሽ፣ የአሁን ተጠሪዎች የሥር ተከሳሾች ሆኖ ሲከራከሩ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ለዚህ
ችሎት ሊቀርብ የቻለዉ አመልካች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.03-
111282 በ25/8/2014 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ
እንዲታረምልኝ በማለት በማመልከቷ ነዉ፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ ከሳሽ በሥር ዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረበችዉ ክስ የ1ኛ ተከሳሽ (የአሁን 1ኛ
ተጠሪ) ንብረት የሆነዉ የሰሌዳ ቁጥር አማ-03-12387 የሆነዉ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና በ2ኛ
ተከሳሽ (የአሁን 2ኛ ተጠሪ) በ6/9/2010 ዓ.ም ከሳሽንና ሌሎች ሰዎችን አሳፍሮ ከደብረብርሃን ወደ
አጣዬ እየሄደ በጣርማ በር ወረዳ ሲና ቀበሌ ሲደርስ ከተፈቀደዉ ፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከሩ
ምክንያት ተገልብጦ በከሰሽ ግራ እጅ ትከሻዬ ላይ የአጥንት ስብራት የደረሰ በመሆኑ፣ የደብረብርሃን

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም
ሆስፒታል ቦርድ በሰጠዉ ዉሳኔ በከሳሽ ላይ ቋሚ የሆነ ጉዳትና ግራ ትከሻዋ መገጣጠሚያ አካባቢ
እንደፈቀደች ማንቀሳቀስ ማቃት 10٪ እንዳላት የገለጸ በመሆኑ፣ ተከሳሾች በአንድነት ኃላፊዎች
በመሆናቸዉ ብር 485496 እንዲከፍሉኝ በማለት ዳኝነት ጠይቃለች፡፡

1ኛ ተከሳሽ በዚህ ክስ ላይ ባቀረበዉ መልስ መኪናዉ የመድህን ሽፋን ስላለዉ ኢንሹራንስ ወደ


ክርክሩ እንዲገባልኝ፣ ጉዳቱ የደረሰዉ በ2ኛ ተከሳሽ ጥፋት መሆኑን የትራፊክ ፕላን ስላልቀረበ
ኃላፊነት የለብኝም፤ ግንኙነታችን የአጓዥና ተጓዥ በመሆኑ ተፈጻሚነት ያለዉ የንግድ ሕግ ነዉ፤
ጉዳቱም የደረሰዉ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በመሆኑ ኃላፊነት የለብኝም፤ ካሳ መክፈል
የለብኝም ይህ ካልሆነ የካሳዉ መጠን ብር አርባ ሺህ መብለጥ የለበትም፤ ከሳሽ እድሜዋ 13 ዓመት
ስለሆነ እየሰራች ገቢ ማግኘት ስለማትችል ጥያቄዋ ተቀባይነት የለዉም፤ የከሳሽ የመስራት ችሎታዋ
መቀነሱን የሕክምና ማስረጃዉ አያሳይም ጉዳቱ ሥራ የሚከለክላትም አይደለም፤ በንግድ ሕጉ
መሰረት ለደረሰዉ ጉዳት ካሳዉ ከአስር ሺህ መብለጥ የለበትም፤ ከሳሽ የተቋረጠባት ጥቅም
ባለመኖሩ ካሳ መከፈል የለበትም በማለት ተከራክሯል፡፡

2ኛ ተከሳሽ መጥሪያ ደርሶት መልስ ባለማቅረቡ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል፤ ክስ


የሚሰማበት ቀን በመቅረቱ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ታዟል፡፡ ጣልቃ ገብ ብሔራዊ የኢትዮጵያ
ኢንሹራንስ መልስ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ጠይቆ በመቅረቱ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል፤
ክስ በሚሰማበት ቀን ስለቀረ ጉዳዩ በሌለበት ታይቷል፡፡

ከዚህ በኋላ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰዉ ምስክሮችን በመስማትና የሰነድ ማስረጃ በመመርመር
ባሳለፈዉ ዉሳኔ በከሳሽ እና በተከሳሾች መካከል የአጓዥና የተጓዥ ግንኙነት ስላለ ተፈጻሚነት ያለዉ
የንግድ ሕግ ነዉ፤ 1ኛ ተከሳሽ አደጋዉ የደረሰዉ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መሆኑን በማስረጃ
አላስረዳም፤ ከግራ ቀኙ የሰዉ ምስክሮች ቃል መረዳት እንደሚቻለዉ አደጋዉ የደረሰዉ
በተሽከርካሪዉ ፍጥነት ምክንያት መሆኑን ያስረዱ በመሆኑ፤ በከሳሽ ላይ ለደረሰዉ ጉዳት አጓዥ
ኃላፊነት አለበት፤ ጉዳቱ የደረሰዉ በአጓዥ ጥፋት እንደሆነ የጉዳት ካሳ መጠን በንግድ ሕጉ
ከተመለከተዉ በላይ ሊያልፍ እንደሚችል የሚያመለክት በመሆኑ፣ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2102 (1) መሰረት
ተከሳሾች ለከሳሽ ለደረሰዉ ጉዳት ብር 70000 (ሰባ ሺህ) የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ፤ ጣልቃ ገብ
በመድህን ዉሉ መሰረት 15000 (አስራ አምስት ሺህ) ለከሳሽ እንዲከፍል፤ ቀሪዉን ብር 55000
(አምሳ አምስት ሺህ) ተከሳሾች በአንድነትና በነጠላ ለከሳሽ እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡

የሥር ከሳሽ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት እና የሰበር አቤቱታ
ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበች ቢሆንም ፍ/ቤቶቹ የቀረበዉን ቅሬታ በትዕዛዝ ዉድቅ በማድረግ
የሥር ፍ/ቤትን ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ቅር
በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ፡፡

የአሁን አመልካች በ13/11/2014 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ፡ በአመልካች ላይ የደረሰዉ አካል
ጉዳት በ2ኛ መልስ ሰጪ ተሽከርካሪዉን በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር የደረሰ አደጋና በአሽከርካሪዉ
ጥፋት ምክንያት የተፈጸመ ጉዳት መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ ጉዳዩ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 599
መሰረት ታይቶ ሊወሰን ሲገባዉ፣ በአመልካች ላይ የደረሰዉን ቋሚ የአካል ጉዳት ወደፊት
የመስራት አቅሟን መቀነስ ያላገናዘበ በርትዕ ብር ሰባ ሺህ የተወሰነዉ የካሳ መጠን

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም
የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2102 ድንጋጌ ያላገነዘበ በመሆኑ፣ የሥር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት
ያለበት ስለሆነ ተሽሮ ተገማች የሆነ የካሳ መጠን እንዲወሰንልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣በአመልካች ላይ ለደረሰዉ የአካል ጉዳት የደረሰዉ በአሽከርካሪ
ጥፋት እስከሆነ ድረስ በሥር ፍ/ቤቶች የተወሰነዉ የካሳ መጠን ተገቢ ነዉ ወይስ አይደለም?
የሚለዉን ነጥብ ለማጣራት ሲባል የሰበር አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪዎች መልስ
እንዲሰጡ ያዘዘ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በተጻፈ መልስ፡ ይህ ጉዳይ በይግባኝ
የቀረበለት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ.21642 በ14/6/2014 ዓ.ም በሰጠዉ ዉሳኔ
አሽከርካሪዉ ጥፋት ስለመሆኑ በማስረጃ አለመረጋገጡን በማመልከት የደረሰዉ ጉዳት በአጓዥ ጥፋት
አለመሆኑን በማረጋገጥ ፍርድ የሰጠ ስለሆነ አመልካች ችሎቱን ለማሳሳት ጉዳቱ የደረሰበዉ በአጓዥ
ጥፋት ነዉ በማለት ያቀረበችዉ ቅሬታ ተቀባይነት የለዉም፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በሰጠዉ ዉሳኔ
በንግድ ሕጉ አንቀጽ 597 (1) መሰረት ለአመልካች ብር 40000 (አርባ ሺህ) ሊከፈላት ይገባል
በማለት የወሰነ በመሆኑ፤ አመልካች ያቀረበችዉ ቅሬታ የማስረጃ ምዘና ጉዳይ ስለሆነ ቅሬታዋ
ዉድቅ ሆኖ የሥር ፍ/ቤት ዉሳኔ እንዲጸናልኝ በማለት ተከራክሯል፡፡ 2ኛ ተጠሪ የችሎቱ መጥሪያ
ደርሶት መልስ ባለማቅረቡ የጽሑፍ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል፡፡ አመልካች ያቀረበችዉ
የመልስ መልስ ባለመኖሩ ታልፏል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ከፍ ሲል የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ
የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም የሰበር አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ
አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡ እንደመረመርነዉ በ1ኛ ተጠሪ ንብረት በሆነዉ ተሽከርካሪ
በ2ኛ ተጠሪ ሲሽከረከር በደረሰዉ የመገልበጥ አደጋ ተሳፋሪ በነበረችዉ በአሁኗ አመልካች ላይ የግራ
እጅ ትከሻዋ ላይ ጉዳት የደረሰና ጉዳቱም መገጣጠሚያዋ አካባቢ እንደፈቀደች ማንቀሳቀስ ማቃት
10٪ እንዳላት ከሆስፒታል የቀረበዉ ማስረጃ እንደሚያመለክት የሥር ፍ/ቤት ዉሳኔ ያመለክታል፡፡
የሥር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን የሰዉ ምስክሮች በመስማት በደረሰበት ድምዳሜ በአመልካች ላይ
ለደረሰዉ የአካል ጉዳት የተሽከርካሪዉ አሽከርካሪ በሆነዉ በ2ኛ ተጠሪ ከተወሰነዉ ፍጥነት በላይ
በማሽከርካሩ በደረሰዉ የመገልበጥ አደጋ በአመልካች ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን በማረጋገጥ
በንግድ ሕጉ ከተመለከተዉ የካሳ መጠን በላይ መወሰኑን የዉሳኔዉ ግልባጭ ያሳያል፡፡

እንግዲህ የሥር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር በመስማት፣ የሰዉ ምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃ
በመመርመር፣ በአመልካች ላይ የደረሰዉን የአካል ጉዳት መጠን የአመልካች ሥራ ከመስራት አቅሟ
ላይ ያደረሰዉን ጉዳትና ተጽህኖ እና የአመልካች የእድሜ ደረጃ ከግንዛቤ በማስገባት፣ በርትዕ
ተጠሪዎች ለአመልካች ብር ሰባ ሺህ የካሳ እንዲከፍሉ መወሰኑን ማየት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ
በንግድ ሕጉ አንቀጽ 599 እና የፍትሕ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2090 እና 2091 ድንጋጌዎች ሥር
ከተመለከተዉ የካሳ መጠን አንጻር የሚነቀፍበት አግባብ የለም፡፡ የሥር ፍ/ቤት ፍሬ ነገር
የማጣራትና ማስረጃን መርምሮና መዝኖ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በሕግ በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት
የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃን መርምሮና መዝኖ የሰጡት ዉሳኔ ይህ ችሎት ከሚቀበል በቀር
የሚለዉጥበት የህግ አግባብ የለም፡፡ የአመልካች ቅሬታ የሥር ፍ/ቤት የሰጠዉ ዉሳኔ የህግ ስህተት
የተፈጸመበት መሆኑን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ይህ ችሎት በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80
(3) (ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 2 (4) (ለ) እና 10 (1) (መ) መሰረት ከተሰጠዉ

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም
ስልጣን አንጻር ሲታይ የአመልካች ቅሬታ የሥር ፍ/ቤቶች በሰጡት ዉሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ
ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን የሚያመለክት ባለመሆኑ ቅሬታዉ ተቀባይነት የለዉም ብለናል፡፡

ሲጠቃለል የሥር ፍ/ቤቶች ተጠሪዎች ለአመልካች እንዲከፍሉ የወሰኑት የካሳ መጠን መሰረታዊ
የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን የሚያመለክት ነገር ባለመኖሩ ተከታዩን ወስነናል፡፡

ዉሳኔ

1. የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.03-111282 በ25/8/2014 ዓ.ም


የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348
(1) መሰረት ጸንቷል፡፡
2. የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ፡፡
3. ግራ ቀኙ የሰበር ክርክሩ ያስከተለዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

መ/ዐ

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም

You might also like