You are on page 1of 6

የሰበር መ/ቁጥር 43414

ታህሳስ 27 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሐጐስ ወልዱ

ሂሩት መለሰ

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- ወ/ሮ ፍቅር ፀደቀ - ጠበቃ ሀብታሙ ሙሉነህ ቀረቡ፡፡

ተጠሪ፡- የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ - ነገረ ፈጅ አለወንድ ካሴ ቀረቡ፡፡

መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ

ተጠሪ በአሁኗ አመልካች ላይ ሕዳር 26 ቀን 1998 ዓ.ም በመሠረተው ክስ መነሻ ነው፡፡ የክሱ ይዘትም፡-

በቀድሞው ወረዳ 21 ቀበሌ 19 ውስጥ የሚገኘውን ቁጥሩ 255 የሆነውን ቤት የአመልካች እናት ወ/ሮ

አምሳለ ማንያህላል ሰኔ 01 ቀን 1974 ዓ.ም በተፈፀመ የኪራይ ውል በወር ብር 160.00 (አንድ መቶ

ስልሳ ብር) ለመክፈል በመኖሪያ ቤት አገልግሎት ሊጠቀሙበት ከተጠሪ ተከራይተው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ

ተከራይዋ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የካቲት 08 ቀን 1996 ዓ.ም በተጻፈ የማመልከቻ

አመልካችና ሟች እናታቸው በቤቱ የተገለገሉበትን ውዝፍ የቤት ኪራይ እዳ በመክፈል ውል

በስማቸው እንዲዛወር ለኤንጂው አቤቱታ አቅርበው ውዝፍ የኪራይ እዳውን በመክፈል በስማቸው

ውል ፈጽመው በቤቱ እንዲገለገሉ ተፈቅዶላቸው በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ኪራይ ለመክፈልም ሆነ

ውል ለመፈፀም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፆ በተጠሪ እና በአመልካች እናት መካከል የተደረገው

የኪራይ ውል ፈርሶ በቤቱ ላይ የተገለገሉበትን ከጥቅምት 01 ቀን 1991 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 30 ቀን

1
1998 ዓ.ም ድረስ ያለው ውዝፍ የቤት ኪራይ ብር 13‚920.00 ፣ ወለድ በብር 6635.00 ተጨማሪ

እሴት ታክስ እስከ ታህሳስ 23 ቀን 1995 እስከ ህዳር 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ የለው ብር 846

በድምሩ ብር 21‚401.24 (ሃያ አንድ ሺህ አራት መቶ አንድ ብር ከሃያ አራት ሳንቲም) እንዲሁም

ቤቱን እስከሚያስረክቡ ድረስ ያለውን ኪራይ እንዲከፍሉና ቤቱን እንዲያስረክቡ ይወሰንለት ዘንድ

ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው፡፡ የአሁኗ አመልካችም በተከሳሽነት ቀርበው በሰጡት መከላከያ መልስ

ተጠሪ ክስ ለመመስረት መብት ወይም ጥቅም የሌለው መሆኑን ጉዳዩ በይርጋ የታገደ መሆኑን

የሚያሳዩ ነጥቦችን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት አንስተው የተከራከሩ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድም

የኪራይ ገንዘቡ ከመቼ እስከመቼ እንደሆነ ያልተጠቀሰ እና የዳኝነት ጥያቄው ስሌትም መሠረቱ

እንደማይታወቅ አከራካሪውን ቤትም ተጠሪ የሚያስተዳድረው ስለመሆኑ ያቀረበው ማስረጃ

አለመኖሩን ይልቁንም ቤቱን አመልካች እንደሚያስተዳድሩና ከተጠሪ ጋር የገቡት ውል አለመኖሩን

በሰኔ 01 ቀን 1974 ዓ.ም ተደረገ የተባለው ውልም በኃይል የተደረገና ፎርሟሊቲውን ያልጠበቀ

በመሆኑ በህግ ፊት እንደማይፀና ተጠሪ ከቤቱ ለማስውጣት በተለያዩ ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራራት

ስለአደረገ ይህንኑ ይዞታ በደጅ ለማቆየት ያህል ውል እንድፈጽም የጠየቅሁት ማመልከቻ ሀሳብን ብቻ

የሚገልጽ ፁሑፍ እንጂ እንደውል ሊቆጠር የሚችል አይደለም በማለት ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ሊሆን

ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም በአልካች በኩል

የቀረቡትን መከራከሪያ ነጥቦችን ውድቅ አድርጐ በተጠሪ እና በሟች አምሳለ ማንያህላል መካከል ሰኔ

01 ቀን 1974 ዓ.ም በቀድሞው ወረዳ 21 ቀበሌ 19 የቤት ቁጥር 255 የተደረውን የኪራይ ውል

በመሰረዝ አመልካች ቤቱን ለተጠሪ እንዲያስረክቡ ቤቱን ለተገለገሉበት ከጥቅምት 01 ቀን 1991

ዓ.ም እስከ ታህሳስ 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ ያለውን የሰባት ዓመት ከሦስት ወር ውዝፍ የቤት ኪራይ

እዳ በድምሩ ብር 13‚920.00(አስራ ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሃያ ብር) ክስ ከቀረበበት ከታህሳስ 06 ቀን

1998 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ 9(ዘጠኝ ከመቶ) እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ

ብር 846.40(ስምንት መቶ አርባ ስድስት ብር ከአርባ ሳንቲም) ለተጠሪ አመልካች እንዲከፍሉ ሲል

ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት

2
አቀርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ፀንቷል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ

የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስቀየር ነው፡፡

የአመልካች ጠበቃ የካቲት 04 ቀን 2001 ዓ.ም በፃፉት ሦስት ገጽ የሰበር አቤቱታ በበታች

ፍርድ በቶች ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚሉበትን ምክንያት ዘርዝረው

አቅርበዋል፡፡ ይዘቱም ባጭሩ ተጠሪ የቤት ኪራይ ውል ያለው ከአመልካች እናት ጋር በመሆኑ

እንዲሁም ከሕግና ከውል በሚመነጭ ምንም ዓይነት ግንኙነት ከአመልካች ጋር ሳይኖረው እና

በሚጠይቀው ሀብት ወይም ጥቅም ላይ መብት ያለው ስለመሆኑ ሳይረጋገጥ ክስ መመስረት አይችልም

ከሃያ ሶስት አመታት በኋላ የቀረበው ክስም በይርጋ ቀሪ ነው በሚል የቀረበው መቃወሚያ መታለፍ

ያላግባብ ነው የእናቴን እዳን እንድከፍል የተወሰነው ባግባቡ አይደለም በቤቱ ላይ የተሻለ መብት ያለኝ

አመልካች እንጂ ተጠሪ አይደለም በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲሻርላቸው ዳኝነት

መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አቤቱታው ተመርምሮም አመልካችን ሊያስገድዳቸው የሚችል ሕጋዊ

የኪራይ አለ ወይስ የለም?አለ ከተባለስ አመልካች የፍ/ብሕ/ቁጥር 2024(መ) ስር ያቀረቡት ክርክር

መታለፍ ባግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚሉትን ነጥቦችን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት

እንዲቀርብ ተደርጐ የተጠሪ ነገረ ፈጅ ታህሳስ 21 ቀን 2002 ዓ.ም በፃፉት ሁለት ገጽ ማመልከቻ

አከራካሪውን ቤት ተጠሪ የሚያስተዳድረው መሆኑን የአመልካች የግል ንብረታቸው ስለመሆኑ

ያቀረቡት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም ሆነ ካርታ ካለመኖሩም በተጨማሪ የስር ፍርድ ቤት

በአመልካች አውራሽና በተጠሪ መካከል የተደረገውን የኪራይ ውልና በአመልካች በጽፎና በፊርማ

ተረጋግጦ የቀረበውን ደብዳቤ መሠረት በማድረግ የሠጠው ውሳኔ ሕጋዊ ስለሆነ ሊፀና ይገባል በማለት

መልሳቸውን ሠጥተዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን

ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ

ለሰበር ችሎት ሊቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አኳያ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል፡፡

3
አመልካች አከራካሪውን ቤት በተመለከተ የአውራሻቸው የግል ንብረት ስለመሆኑ ገልፀው

የሚከራከሩ ቢሆንም አከራካሪው ቤት የግል ንብረት ስለመሆኑ ያቀረቡት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም

ሆነ ካርታ የሌለ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ እንዲሁም የስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር መስከረም 11 ቀን

1983 ዓ.ም የፃፈው ደብዳቤም የሚያመለክተው በተክለሃይማኖት አውራጃ ቀበሌ 47 በውርስ ላገኙት

ቤት ደብተር እስኪሠጣቸው ድረስ ላሉበት ቤት ኪራይ እንዳይከፍሉ ለቂርቆስ አውራጃ አስተዳደር

ቀበሌ 19 ከነማ ጽ/ቤ መፃፉን እንጂ ለዚህ ክርክር መነሻ የሆነው ቤት በተመለከተ የአመልካች አውራሽ

የግል ቤት ነው በሚል የተሠጠ አለመሆኑን ስለመሆኑም ከክርክሩ ሂደት ተመልክተናል፡፡ በመሆኑም

በአከራካሪው ቤት ከተጠሪ የተሻለ መብት ያለኝ እኔ መሆኔ ተጠሪ ክስ ለመመስረት በቤቱ ላይ ጥቅም

ወይም መብት የለውም በማለት አመልካች ያቀረቡት ክርክር በስር ፍርድ ቤት መታለፉ ባግባቡ ሆኖ

አግኝተናል፡፡

ሌላው አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት ከተጠሪ ጋር በራሳቸው ስም ያደረጉት የኪራይ

ውል የለም በማለት ነው፡፡ ተጠሪ ደግሞ ለዚህ የአመልካች ክርክር የሚሠጠው መልስ ከአመልካች ጋር

በስማቸው የተደረገ የኪራይ ውል አለ በማለት ሳይሆን አመልካች ቤቱን ከተከራዩት እናታቸው ጋር

በቤቱ ላይ ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ እናታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ አመልካች የካቲት 08 ቀን 1996

ዓ.ም ለተጠሪ በፃፉት ደብዳቤ ውዝፍ እዳውን ከፍለው የቤቱ የኪራይ መብት በራሳቸው ስም

እንዲሆን ጠይቀው ተፈቅዶላቸው ኪራዩንም አልተዋዋሉም ውዝፍ የኪራይም ሆነ ቤቱን

የተገለገሉበትን ኪራይ አልከፈሉም በሚል ነው፡፡ አመልካች ደብዳቤውን መጻፋቸውን ሳይክዱ

ደብዳቤው የተፃፈው ተጠሪ አመልካች ቤቱን እንዲለቁ ስለአስፈራራቸውና የቤቱን ይዞታ በእጃቸው

ለማቆየት እንደሆነ ገልፀው ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ የአመልካች ክርክር መገንዘት የሚቻለው

በአልካችና በተጠሪ መካከል ከወ/ሮ አምሳለ ማንያህላል ሞት በኋላ የተደረገ የኪራይ ውል አለመኖሩን

ነው፡፡ የኪራይ ውልን ለማቋቋም በሕጉ የተለየ ፎርማሊቲ መከተል የማያስፈልግ ቢሆንም በተያዘው

ጉዳይ ግን አመልካች የቤቱ ኪራይ በራሳቸው ስም እንዲዞርላቸው ጥያቄ አቅርበው ተጠሪ ይህንኑ

ተቀብሎ አመልካች የኪራይ ውሉን እንዲገቡ ሲጠይቁ ፈቃደኛ አለመሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ

4
በጥያቄአቸው መሠረት የኪራይ ውል ገብተዋል ለማለት የሚያስችል አይደለም፡፡ በመሆኑም ተጠሪ

በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2968 መሠረት ላልተወሰነ ጊዜ የኪራይ ውሉን አድርጓል ሊባል የሚችለው ከሟች

እናት ከወ/ሮ አምሳለ ማንያህላል ጋር ነው ከሚባል በስተቀር በአመልካችና በተጠሪ መካከል በሕጉ

አግባብ የተቋቋመ የኪራይ ውል የለም፡፡ ስለሆነም የስር ፍርድ ቤት በአመልካችና በተጠሪ መካከል

የነበረውን ግንኙነት ከኪራይ ውል ግንኙነት አንፃር መመልከቱ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ሆኖም

አመልካች ከተጠሪ ጋር የኪራይ ውል በሕጉ አግባብ ባያደርጉም በቤቱ የኪራይ ውሉ በስማቸው

እንዲዞርላቸው ከጠየቁበት ከየካቲት 08 ቀን 1996 ዓ.ም ጀምሮ መብት ሳይኖራቸው ቤቱን

በይዞታቸው ስር አድርገው ያለተጠሪ ፈቃድ የተጠቀሙበት ስለመሆኑ የተስተባበለ ጉዳይ አይደለም፡፡

ይህ ደግሞ በሕግ ኃላፊነትን የሚያስከትል ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2027፣2054 እና 2112

ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም አመልካች ቤቱን ያላግባብ

እስከተጠቀሙበት ድረስ በቤቱ ላይ ተጠሪ በአከራይነት የሚያገኘውን ጥቅም የማይከፍሉበት ሕጋዊ

ምክንያት የለም፡፡ በዚህ ጊዜ ተጠሪ ሊያገኝ ይችል የነበረው ጥቅምም በይርጋ የሚታገድ አለመሆኑን

ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑነም በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡

በዚህ መሠረት አመልካች ሊጠየቁ የሚገባው ቤቱን ራሳቸው ይዘው ከተጠቀሙበት ከየካቲት 08 ቀን

1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ ያለውን በቤቱ ላይ በኪራይ መልክ

የሚገኘውን ጥቅም መጠን ነው፡፡ አመልካች እናታቸው ለተጠቀሙበት ጊዜ ሊጠየቁ የሚችለው

የእናታቸው መብትና ግዴታ በሕጉ አግባብ የወረሱ መሆኑ ሲረጋገጥ እና በዚሁ የወራሽነት መብታቸው

የክርክሩ ተካፋይ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ ግን ይኸው ሥርዓት ተሟልቶ

አመልካች የተከሰሱ ስለመሆኑ የሚያሳይ ነገር የለም፡፡ ሲጠቃለልም በአመልካችና በተጠሪ መካከል

ከሕጉ አግባብ የተቋቋመ የኪራይ ውል በሌለበት ሁኔታ ክርክሩ የኪራይ ግንኙነትን መሠረት አድርጐ

በሥር ፍርድ ቤት መታየቱ ያላግባብ ሲሆን አመልካች ያላግባብ የተጠሪን ቤት ይዘው ለተጠቀሙበት

ጊዜ ብቻ ሊጠየቁ የሚገባ ሆኖ አግኝተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስኗል፡፡

ውሳኔ

5
1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 61819 ጥር 14 ቀን 1999 ዓ.ም ተሰጥቶ

በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 53107 ሕዳር 05 ቀን 2001 ዓ.ም የፀናው ውሣኔ

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሠረት ተሻሽሏል፡፡

2. አመልካች ቤቱን ለተጠሪ እንዲያስረክቡ ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል፡፡

3. አመልካች ለተጠሪ የሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ከየካቱት 08 ቀን 1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ

ታህሳስ 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ ያለውን በወር 160.00 (አንድ መቶ ስልሳ ብር) እየታሰበ

የሚመጣውን የሃያ ሦስት ወራት ጥቅም ብር 3680 (ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰማንያ ብር)

በዚሁ ገንዘብ መጠን ከታህሳስ 06 ቀን 1998 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ ህጋዊ ወለድ 9 (ዘጠኝ

በመቶ) እና በዋናው ገንዘብ የሚታሰብ ተጨማሪ እሴት ታክስ ነው ብለናል፡፡

4. የቤቱ ተከራይ የነበሩት ሟች ወ/ሮ አምሳለ ምንያህላል ለተጠሪ ያልከፈሉትን የውዝፍ

የኪራይ እዳ ተጠሪ ተገቢውን ወራሽ በሕጉ አግባብ ከስሶ ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግደውም

ብለናል፡፡

5. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

6. መስከረም 07 ቀን 2002 ዓ.ም ተሰጥቶ የበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ይፃፍ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

You might also like