You are on page 1of 13

www.abyssinialaw.

com

እንዴት ያለባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ የተላለፈን


ንብረት ማስመለስ፤ የተቋቋመን የመብት ገደብ
ማስነሳት ይቻላል?

ጥያቄዉ?
በዚህ ጽሁፍ መመለስ የምፈልገዉ ጥያቄ ቀላል ይመስላል፤ እንዴት ያለባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ
የተላለፈን ንብረት ማስመለስ፤ የተቋቋመን የመብት ገደብ ማስነሳት ይቻላል የሚለዉን ነዉ፡፡ ቀጥታ
ጥያቄዉን ወደ መመለሱ ከመሄዴ በፊት፤ ጥያቄዉ የሚመለከታቸዉ ሁኔታዎች ምን አይነቶቹን እንደሆነ
ግልጽ ላድርግ፡፡

ያለ ሙሉና ነጻ ፈቃድ ሲባል?


እንደሚታወቀዉ ንብረትን (የማይንቀሳቀስም ይሁን ልዩ ወይም ተራ የማይንቀሳቀስ) ለሌላ ሰዉ ዉልን
መሰረት አድርጎ ለማስተላለፍ የባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ባለቤቱ ፈቃዱን ሰጥቷል ነገር ግን
ፈቃዱ ሙሉ እና ነጻ አልነበረም የሚባለዉ የባለቤቱ ፈቃድ በስህተት ወይም በማታለል ወይም በሃይል
ተግባር ምክኒያት የተሰጠና በሕጉም መሰረት ዉሉ ፈራሽ ዉል ሲባል ነዉ፡፡ ባለቤቱ ፈቃዱን የገለጸዉ
ራሱ ወይም በወኪሉ በኩል ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ የባለቤቱ ፈቃድ ጉድለት አለበት፤
ነገር ግን ንብረቱ ተላልፎ ሊሆን ይችላል ወይም የመብት ገደብ ተቋቁሞ ሊሆን ይችላልና እንዴት ባለቤቱ
ንብረቱን ማስመለስ ገደቡን ማስነሳት ይችላል የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ባለቤቱ በምንም አይነት መልኩ ፈቃዱን ሳይገልጽ ከሆነስ?


በሁለተኛ ደረጃ የንብረት ማስመለሱና የመብት ገደቡን የማስመለስ ጥያቄ ሊነሳ የሚችለዉ
ከመጀመሪያዉኑ ባለቤቱ በምንም መልኩ ፈቃዱን ያልገለጸ ከሆነ ነዉ፡፡ ባለቤቱ ፈቃዱን ሳይገልጽ እንዴት
ንብረት ይተላለፋል ወይም መብት ይገደባል ለሚል ጥያቄ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሁኔታዎች መልስ
ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
www.abyssinialaw.com

1. አንድ ሰዉ ህጋዊ ባለቤት ሳይሆን ባለቤት እንደሆነ በማስመሰል ከሌላ ሰዉ ጋር በመዋዋል


ንብረቱን ሊያስተላልፍ ወይም የመብት ገደብ ሊያቋቁም ይችላል፡፡ ንብረቱ ተራ የሚንቀሳቀስ
ንብረት ከሆነ ይህን ለማድረግ ቀላል ነዉ፡፡ ንበረቱ የማይንቀሳቀስ ወይም ልዩ ተንቀሳቃሽ ቢሆንም
ይህን ለማደድረግ ቀላል ነዉ፡፡ ነገር ግን ሰነዶችን ፎርጅድ ማድረግ ሊጠይቅ ወይም የሌላ አካል
ትብብርን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ እነዚህ ሰነዶች ይህ ሰዉ ባለቤት መሆኑን የሚያሳዩ ወይም ንብረቱን
አስመልክቶ በባለቤቱ ስም ዉል የመዋዋል ስልጣን አንዳለዉ የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
2. ንብረቱን ያስተላለፈዉ ወይም የመብት ገደቡን ያቋቋመዉ ሰዉ የባለቤቱ ወኪል/እንደራሴ ሆኖ
ነገር ግን ንብረቱን ለማስተላለፍ ወይም የመብት ገደቡን ለማቋቋም ስልጣን የሌለዉ ከሆነ ወይም
ወኪል እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ቢኖርም እንኳ ይህ የእንደራሴነቱ ስልጣን ፈራሽ ወይም ዋጋ
አልባ ከሆነ ወይም ምንም እንኳ በአንድ ወቅት ስልጣን ቢኖረዉም እንኳ ይህ ስልጣኑ በኋላ
በባለቤቱ የተነሳ ወይም የተገደበ ወይም ጊዜዉ ያለፈበት ከሆነ፡፡

ከባለቤቱና ንብረቱ ከተላለፈለት ሰዉ ወይም መብቱ ከተገደበለት ሰዉ ዉጭ ሌላ ሰዉ ሊኖርም


ላይኖርም ይችላል?
ከላይ በተገለጹት ሁለት ሁኔታዎች ያለባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ ንብረት ሊተላለፍ ወይም መብት ሊገደብ
እንደሚችል አይተናል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ከባለቤቱን ንብረቱ ከተላለፈለት ሰዉ ወይም መብቱ
ከተገደበለት ሰዉ ዉጭ ሌላ ሰዉ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡ ጉዳዩ የማይንቀሳቀስ ንብረትን ወይም ልዩ
ተንቀሳቃሽ ንብረትን የሚመለከት ከሆነ፤ ከባለቤቱን ንብረቱ ከተላለፈለት ወይም መብቱ ከተገደበለት ሰዉ
ዉጭ ቢያንስ እነዚህን ንብረቶችን አስመልክቶ የሚፈጸሙ ዉሎችን የሚመዘግቡ፤ ወይም እነዚህን
ንብረቶች አስመልከቶ የባለቤትነት ማስረጃን የሚሰጡ፤ የመብት ገደብን የሚመዘግቡ፤ ማስረጃዎችን
የሚያረገግጡ መንግስታዊ ድርጀቶችንም ይመለከታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ንብረቱ የተላለፈዉ ወይም
መብቱ የተገደበዉ ከባለቤቱ ፈቃድ ወይም እዉቅና ዉጭ ከሆነ ተራ ተንቀሳቃሽ ንብረት ከሆን ይህን
ንብረት በስርቆት ወይም በአደራ ወይም በሌላ መልኩ ይዞታዉ ዉስጥ በማስገባት ያስላለፈ ሰዉን
ይጨምራል፡፡ ጉዳዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከት ከሆነ ራሱን የንብረቱ
ባለቤት በማስመሰል (በፎርጅድ ሰነድ) ወይም ራሱ ንብረቱን ለማስተላለፍ ወይም መብቱን ለማስገደብ
ስልጣን እንዳለዉ የሚያስብ ወይም የሚያስመስል ሰዉን ይጨምራል፡፡
www.abyssinialaw.com

ከባለቤቱ ዉጭ ያሉ ወገኖች (ንብረቱ የተላለፈለትን ወይም መብቱ የተገደበለትን ጨምሮ) እና


የእዉቀት ደረጃቸዉ
ከባለቤቱ ዉጭ ያሉ ወገኖች እላይ የተገለጹት እና ንብረቱ የተላለፈለት ወይም መብቱ የተገደበለት ሰዉን
ጨምሮ፤ ጥያቄ የተነሳበትን ግብይት በቅን ልቦና ወይም ያለቅን ልቦና ያደረጉት ሊሆን ይችላል፡፡

1. ለምሳሌ በመጀመሪያ ግብይቱን ለማከናወን ሙሉ ስልጣን ኖሮት ነገር ግን ስልጣኑ በጊዜ ማለፍ
ምክንያት ወይም ባለቤቱ ስላነሳዉ ወይም ስለገደበዉ፤ ግብይቱን ሲያከናዉን ስልጣን የለለዉ ሆኖ
ነገር ግን ስልጣን እንደሌለዉ ወይም ስልጣኑ እንደተገደበ ወይም እንደተነሳ የማያዉቅና ማወቅ
የማይጠበቅበት ሰዉ በቅል ልቦና ነዉ ዉሉን የፈጸመዉ ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ሰዉ ዉሉን
የፈጸመዉ እያወቀ ወይም ማወቅ እየተጠበቀበት ሊሆን ይችላል፡፡
2. ሰዉየዉ የባለቤቱ እንደራሴ ሆኖ ነገር ግን እንዲህ አይነት ዉሎችን የመዋዋል ስልጣን ላይኖረዉ
ይችላል፡፡ ይህ ሰዉዬ ግን ስልጣኑ እንዲህ አይነት ዉሎችን ይጨምር አይጨምር የሚያዉቅ
ወይም ማወቅ የሚጠበቅበት ወይም የማያዉቅ እና ማወቅ የማይጠበቅበት ሊሆን ይችላል፡፡
3. ዉልን እንዲመዘግቡ ወይም ንብረትን እንዲመዘግቡ፤ የባለቤትነት ማስረጃን እንዲሰጡ ወይም
ማስረጃን እንዲያረጋግጡ የተቋቋሙ መንግስታዊ ተቋማት በቅን ልቦና ወይም ያለቅን ልቦና
የቀረቡትን ማስረጃዎች ሊያረጋግጡ ወይም ዉልን ሊመዘግቡ ይችላሉ፡፡
4. እንዲሁም ንብረቱ የተላለፈለት ወይም መብቱ የተገደበለት ሰዉ፤ ንብረቱን ያስተላለፈለት ሰዉ
ባለቤት ስላመሆኑ ወይም ስልጣን የሌለዉ ስለመሆኑ የማያዉቅና ማወቅ የማይጠበቅበት ወይም
የሚያዉቅ ወይም ማወቅ የሚጠበቅበት ሊሆን ይችላል፡፡

ጥያቄዉ ዘርዘር ሲደረግ


አሁን ታዲያ ጥያቄዉ በእነዚህ ሁኔታዎች ዉስጥ ባለቤቱ ንብረቱን ለማስመለስ ወይም የተቋቋመዉን
የመብት ገደብ ማስነሳት ቢፈልግ በምን አይነት ሁኔታዎች እና ገደቦች ይቻለዋል የሚል ነዉ፡፡ ጥያቄዉ
እነዚህን አስመልክቶ ያለዉ አግባብነት ያላቸዉ የኢትዮጲያ ሕጎች የትኞቹ ናቸዉ፤ ይዘታቸዉስ ምንድን
ነዉ? እንዲሁም በየትኞቹ ሁኔታዎች ነዉ ንብረቱን ለማስመለስ ወይም የመብት ገደቡን ለማስነሳት
ለንበረቱ መተላለፍ ወይም በመብቱ መገደብ ምክኒያት/መሰረት የሆነዉን ዉል ማፍረስ የሚቻለዉ ወይም
የሚገባዉ እና የማይቻለዉና የማይገባዉ? ንብረትን ለማስመለስ ወይም የመብት ገደብን ለማስነሳት
የሚቀርብ ክስን አስመልከቶ አግባብነት ያለዉ የይርጋ ዘመን የትኛዉ ነዉ? ንብረትን ለማስመለስ ወይም
የመብት ገደብን ለማስነሳት የሚቀርብ ክስን አስመልከቶ ገዢዉ ሕግ የዉል ሕግ ነዉ ወይስ የንብረት ሕግ
ወይስ የዉክልና ሕግ ወይስ አላግባብ የመበልጸግ ሕግ?
www.abyssinialaw.com

ጥያቄዉን ያስነሳዉ የሰበር ዉሳኔ


ይህን ቀላል የሚመስል ነገር ግን ብዙ አይነት ሴናሪዎችን ሊመለከት እና መልሱም እንደነገሩ ሁኔታ ሊለያይ
የሚችልን ጥያቄ እንድናነሳና እንድንፈትሽ ያስገደደን በሰ/መ/ቁ.48094 በግንቦት 10 ቀን 2002 ዓ.ም በእነ
ሙና እንድሪስ እና በኢትዮጲያ ልማት ባንክ ጉዳይ የተላለፈዉ የሰበር ዉሳኔ ስለሆነ ይህን ዉሳኔ ከዚህ
በታች ሙሉ ለሙሉ አስቀምጠነዋል፡፡
www.abyssinialaw.com

1 ይህ ጉዳይ የተጀመረዉ በፊዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት ሲሆን አመልካቾች በተጠሪና በሥር


2 አንደኛ ተከሳሽ ላይ ባቀረቡት ክስ በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 6 ቀበሌ 13 ክልል ቁጥር
3 563 የሆነዉ ቤት ለከሳሾችና ለአንደኛ ተከሳሽ ከወላጆቻችን በዉርስ የተላለፈልን ንብረት
4 ሲሆን አቶ ጅላል አብዱልመናን የተባሉ ግለሰብ ከሁለተኛ ተከሳሽ ገንዘብ ሲበደሩ አንደኛ
5 ተከሳሽ አካለመጠን ባላደረሱት ወራሾች ላይ የተሰጠዉን የሞግዚትነት ሥልጣን መሠረት
6 አድርጎ የጋራ የዉርስ ንብረት የሆነዉን ቤት በመያዣነት ሰጥቷል፡፡ በአንደኛ ተከሳሽ
7 የተፈጸመዉ ተግባር ከፍ/ብ/ሕ/ቁ/300 እና 1266 አኳያ ሕገ-ወጥ ስለሆነ ሐምሌ 7 ቀን
8 1987 ዓ.ም እና ጥቅምት 16 ቀን 1987 ዓ.ም የፈረመዉ የመያዣ ዉል ፈራሽ ነዉ ተብሎ
9 እንዲወሰንና የቤቱንም ካርታ ሁለተኛ ተከሳሽ እንዲመልስ ይወስንልን በማለት
10 ጠይቀዋል፡፡

11 የከሳሾች ክስና ማስረጃ ለተከሳሾች ደርሶ መልስ እንዲሰጡ ታዞ አንደኛ ተከሳሽ ተጠርቶ
12 ባለመቅረቡ ጉዳዪ በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

13 ሁለተኛ ተከሳሽ (የአሁን ተጠሪ) ቀርቦ ለክሱ ምክንያት የሆነዉን ቤት በመያዣነት መያዙን
14 አምኖ ይህንን ለማድረግ የቻለዉ አንደኛ ተከሳሽ በቤተዘመድ ጉባዬ ዓማካይነት በ24/1/87
15 ዓ.ም የሞግዚትነት ሥልጣን ተሰጥቶት ፍ/ቤትም ቀርቦ በመጽደቁ ምክንያት እንደሆነና
16 የተሰጠዉም የሞግዚትነት ሥልጣን ሞግዚት በሆነላቸዉ ሰዎች ስም የሚንቀሳቀስም ሆነ
17 የማይንቀሳቀስ ንብረት በዋስትና ለመስጠት እንደሚችል በሰነዱ ላይ ስለተመለከተ
18 በመሆኑ ለአንደኛ ተከሳሽ በተሰጠዉ የሞግዚትነት ሥልጣን ላይ ተመስርቶ የመያዣ ዉል
19 መፈራረሙ በአግባቡ ስለሆነ የመያዣ ዉሉ የሚፈርስበት ምክኒያት የለም በማለት
20 ተከላክሏል፡፡

21 የፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤትም የመያዣ ዉሉ ሊፈርስ ይገባል ወይንስ አይገባም የሚለዉን


22 ጭብጥ መስርቶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የቤተዘመድ ጉባኤ አንደኛ ተከሳሽን ሞግዚት
23 አድርጎ የሾመዉ በ18/10/81 ዓ.ም ሲሆን ጥቅምት 11 ቀን 1987 ዓ.ም የሚግዚትነት
24 ሥልጣኑ ፍ/ቤት ቀርቦ ጸድቋል፡፡ በሞግዚትነት ማጽደቅ ዉሳኔዉም ላይ ከከሳሾች
25 መካከል አንደኛ እና ሁለተኛ ከሳሾች ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ የወጡ መሆኑ
26 ተመልክቷል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ሞግዚት በሆነላቸዉ ስም የተመዘገበ የሚንቀሳቀስም ሆነ
27 የማይንቀሳቀስ ንብረት በመያዣ ወይም ዋስትና ለመስጠት የተፈቀደለት ቢሆንም የመያዣ
28 ዉሉን በተፈራረሙ ጊዜ አንደኛ እና ሁለተኛ ከሳሾች ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥተዉ
www.abyssinialaw.com

29 የነበረ ስለሆነ ያለእነሱ ስምምነት የመያዣ ዉሉን መፈራረሙ የፍ/ቤ/ሕ/ቁ 1266ን


30 የሚጻረር ነዉ፡፡

31 በመሆኑም በወረዳ 6 ክልል የቤ.ቁ 563 ተመዝግቦ የሚገኘዉ የከሳሾችና የአንደኛ ተከሳሽ
32 የጋራ የዉርስ ሀብት ሆኖ እያለ አንደኛ እና ሁለተኛ ከሳሾች ስምምነታቸዉን ሳይሰጡ
33 በአንደኛ ተከሳሽ በኩል ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር የመያዣ ዉል የተፈጸመዉ የሕጉን ድንጋጌ
34 ባልተከተለ ሁኔታ ስለሆነ ጥቅምት 1987 ዓ.ም እና ሐምሌ 1987 ዓ.ም የተደረገ የመያዣ
35 ዉል ፈራሽ ነዉ በማለት ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡

36 የሥር ሁለተኛ ተከሳሽ የአሁን አመልካች በዉሳኔዉ ቅሬታ አድሮበት የይግባኝ ቅሬታዉን
37 ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቦ ፍ/ቤቱም በበኩሉ ግራ ቀኙን አከራክሮ አንድ ዉል
38 እንዲፈርስ ተዋዋይ ወገን ያልሆኑ ሦስተኛ ወገኖች ማቅረብ የሚችሉት በፍ/ብ/ሕ/ቁ/
39 1808(2) እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሠረት ነዉ፡፡ ዉል የማይረጋበት ምክንያት
40 ከቀረበት ጊዜ አንስቶ ከ2 ዓመት በኋላ የዉል ይሰረዝልኝ ክስ ሊቀርብ እንደማይችል
41 ጉዳቱ የደረሰበት ሰዉ አካለመጠን የደረሰ ሰዉ ከሆነ ክሱን ማቅረብ የሚገባዉ ሙሉ
42 በተደረገ በ2 ዓመት ጊዜ ዉስጥ እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810(1) ላይ ተደንግጓል፡፡ በተያዘዉ
43 ጉዳይ ከተራ ቁጥር 1-3 የተጠቀሱት መ/ሰጭዎች ዉሉ ሲደረግ ለአቅመ አዳም የደረሱ
44 መሆናቸዉ ከ4ኛ-7ኛ የተጠቀሱትም መ/ሰጭዎች ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ለአካለመጠን
45 የደረሱ መሆናቸዉ በመ/ሰጭዎች ያልተካደ በመሆኑ የዉል ይሰረዝልኝ ክሱ 2 ዓመት
46 ያለፈዉ መሆኑን ፍ/ቤቱ ተገንዝቧል፡፡ ስለሆነም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810(1) መሠረት የዉሉ
47 ይሰረዝልኝ ክሱ በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት ዉሳኔ ሠጥቷል፡፡

48 የሥር ከሳሾች /የአሁን አመልካቾች/ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዉሳኔ ቅሬታ አድሮባቸዉ
49 የይግባኝ ቅሬታቸዉን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረቡ ቢሆንም በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ
50 337 መሠረት ፍ/ቤቱ ይግባኙን ሳይቀበለዉ ቀርቷል፡፡

51 የሰበር አቤቱታዉ የቀረበዉ ይህንኑ በመቃወም ሲሆን አቤቱታዉ ተመርምሮ የአመልካች


52 የዉል ይፍረስልኝ ክስ በ2 ዓመት ይርጋ ቀሪ ሆኗል ተብሎ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት
53 መወሰኑ ለሰበር ቀርቦ መጣራት የሚገባዉ ሆኖ በመገኘቱ ይህ ችሎት አቤቱታዉ ለሰበር
54 እንዲቀርብ አድርጎ ተጠሪን በመጥራት ግራ ቀኙን አከራክሯል፡፡
www.abyssinialaw.com

55 በአጠቃላይ የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን በበኩላቸወን አቤቱታዉ ለሰበር


56 ያስቀርባል ከተባለበት ነጥብ አኳያ እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡

57 አንድ ዉል በሚመሰረትበት ጊዜ የችሎታ ወይንም የፈቃድ ጉድለት ያለበት ሆኖ


58 በሚገኝበት ጊዜ ችሎታ አልነበረኝም ወይንም ፈቃዴን በአግባቡ አልሰጠሁም በሚለዉ
59 ተዋዋይ ወገን ጠያቂነት ዉሉ ሊፈርስ እንደሚችል እንደዚሁም ዉሉ የተደረገበት ጉዳይ
60 ለሕግ ወይንም ለሞራ ተቃራኒ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜና የዉሉ አጻጻፍ ሥርዓትም
61 ባልተጠበቀ ወቅት ከተዋዋዮች ወገኖች መካከል ወይንም በዉሉ ጥቅም አለኝ በሚል 3ኛ
62 ወገን ዓማካይነት የዉል ይፍረስልኝ ጥያቄ ሲቀርብ ዉሉ ሊፈርስ እንደሚችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ
63 1808(1) እና (2) ላይ ተመልክቷል፡፡

64 የዉል ይፍረስልኝ ክስ ማቅረቢያ ጊዜዉን በተመከተም ዉሉ የማይረጋበት ምክኒያት


65 ከቀረበት ጊዜ አንስቶ በ2 ዓመት ዉስጥ ካልቀረበ በይርጋ ሊታገድ እንደሚችል
66 በፍ/ብ/ሕ/ቁ/1810 ላይ ተመልክቷል፡፡

67 በተያዘዉ ጉዳይ በፌዴራል መ/ደ/ፍ/ቤት ዉሉ ሊፈርስ ይገባል ተብሎ ዉሳኔ የተሰጠዉ


68 የጋራ ባለንብረቶች የሆኑት አንደኛ እና ሁለተኛ ተጠሪዎች ፈቃዳቸዉን አልሰጡም በሚል
69 ምክንያት ነዉ፡፡

70 በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 ላይ የተመለከተዉ የ2 ዓመት ይርጋ ጊዜ ተፈጻሚነቱ ዉሉ የማይረጋበት


71 ምክንያት ቀሪ በሚሆንበት ጊዜ ሲሆን ይህም የሚመለከተዉ ከአንደኛዉ ተዋዋይ ወገን
72 ችሎታ ወይንም ፈቃድ ጉድለት ጋር የተያያዘ በሚሆንበት ጊዜ ነዉ፡፡ ዉሉ ከችሎታ
73 ወይንም ከፈቃድ ጋር በተያያዘ ጉድለት አለበት በሚባልበት ጊዜ ይህንኑ መሠረት አድርጎ
74 ክስ የሚያቀርበዉ ወገን በ2 ዓመት ክሱን ካላቀረበ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 መሠረት በይርጋ
75 ቀሪ እንደሚሆን መገንዘብ ይቻላል፡፡

76 ነገር ግን በተያዘዉ ጉዳይ ዉሉ እንዲፈርስላቸዉ የጠየቁት አንደኛ እና ሁለተኛ


77 አመልካቾች ለዉሉ መፍረስ በምክንያትነት የጠቀሱት የጋራ የሆነዉን የዉርስ ሀብት
78 ለመሸጥም ሆነ በመያዣ ለመስጠት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1266 መሠረት የጋራ ባለሀብቶች
79 ስምምነት አስፈላጊ ሆኖ ሳለ የሥር አንደኛ ተከሳሽ ያለ እኛ ስምምነት የጋራ የዉርስ ሀብት
80 የሆነዉን ቤት ለሁለተኛ ተከሳሽ (ለአሁን ተጠሪ) በመያዣነት የሰጠ ስለሆነ ዉሉ ሊፈርስ
81 ይገባል በማለት ነዉ፡፡ አንደኛ እና ሁለተኛ አመልካቾች ተዋዋይ ወገን ካልሆኑ
www.abyssinialaw.com

82 በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1808(1) መሠረት ዉሉ የችሎታ ወይንም የፈቃድ ጉድለት ያለበት ስለሆነ


83 ሊፈርስ ይገባል በማለት ሊጠይቁ የማይችሉ በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 ላይ
84 የተመለከተዉ የ2 ዓመት ይርጋ ጊዜ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት አይኖረዉም፡፡

85 በሌላ በኩልም በተሻሻለዉ የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 310 ላይ የተቀመጠዉን የይርጋ ጊዜ


86 በተመለከተም አካለመጠን ያላደረሰ ልጅ በሞግዚቱ ላይ የሚያቀርበዉ ክስ አስመልከቶ
87 ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን በዚህ ጉዳይ ግን ዉሉ ፈራሽ ነዉ የተባለዉ ከፍ ብሎ
88 እንደተጠቀሰዉ ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥተዋል በተባሉት አንደኛ እና ሁለተኛ
89 አመልካቾችን አስመልክቶ ስለሆነ ድንጋጌዉ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለዉ አይደለም፡፡

90 እንግዲህ ተጠሪ ያነሳዉ የይርጋ ክርክር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 እና የቤተሰብ ሕጉ የሚሸፈን


91 ባይሆንም የጋራ የሆነን ንብረት ለማስተላለፍ ወይንም በዋስትና ለመስጠት የሁሉንም
92 የጋራ ባለንብረቶች ስምምነት ማግኘት እንዳለበት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1266 ላይ የተመለከተ
93 ሲሆን ነገር ግን የጋራ ባለንብረት ከሆኑት መካከል አንደኛ እና ሁለተኛ ተጠሪዎች በመያዣ
94 ዉሉ ስምምነታቸዉን ያልሰጡ ስለሆነ ይህም ዉሉ ሕግን የሚጻረር መሆኑን
95 የሚያመለክት ነዉ፡፡ አንድ ዉል ሕግን የሚቃረን ነዉ በሚባልበት ጊዜ እንዲፈርስ ጥያቄ
96 መቅረብ ያለበት በ10 ዓመት ጊዜ እንደሆነ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 1845 መረዳት ይቻላል፡፡
97 አመልካቾች ክሱን ቀረቡት ደግሞ በሕጉ ላይ የተቀመጠዉ የ10 ዓመት ጊዜ ከማለፉ በፊት
98 ስለሆነ አቤቱታቸዉ በይርጋ የተጋደ አይደለም፡፡

99 ሲጠቃለልም የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአመልካቾች ክስ በ2 (ሁለት) ዓመት ይርጋ ቀሪ


100 ሆኗል ያለዉ ለጉዳዩ አግባብነት በሌለዉ ድንጋጌ ተመስርቶ በመሆኑ መሠረታዊ የሕግ
101 ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
www.abyssinialaw.com

እነ ሙና እንድሪስ እና ኢትዮጲያ ልማት ባንክ፡ የመጀመሪያ ደረጃ ግምገማ


የፍርድ ቤት ዉሳኔ በሁለት ወገኖች መካከል ያለን ሙግት ማን እንዳሸነፈ ለማወጅ ብቻ ተብሎ የሚጻፍ
አይደለም፡፡ እንደዛማ ቢሆን ኖሮ ሳንቲም ወደ ሰማይ ወርዉረን ጎፈር ከሆነ ከሳሽ ዘዉድ ከሆነ ደግሞ
ተከሳሽ አሸንፏል በማለት መወሰን ይችል ነበር፡፡ ይህ ያልሆነበት በብዙ ምክኒያቶች ነዉ፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ
ስለማይያያዝ በዚህ ጽሁፍ እነዚህን ምክንያቶች መዘርዘሩ አያስፈልግም፡፡ ቁም ነገሩ የፍርድ ቤት ዉሳኔ
ከሁለቱ ወገኖች መካከል ማን ምን እንዳገኘ/እንዳሸነፈ ከማስታወቅም በላይ ነዉ፡፡ በዉሳኔዉ ፍርድ ቤቱ
ተሸናፊዉን ወገን በማሳመን የዉሳኔዉን ፍትሃዊነት እና ትክክለኛነት እንዲሁም የሕግ መሰረት
የሚያስረዳበት ነዉ፡፡ ከዚህም አልፎ ለተመልካችም ቢሆን የዉሳኔዉን ትክክለኛነት ምክንያቱን
በማብራራት የሚያስረዳበትና ዉሳኔዉ አግባብነት ባላቸዉ ሕጎችና በጉዳዮ ፍሬ ነገሮች የተደገፈ መሆኑን
የሚያስረዳበት ነዉ፡፡ ከዘህ አንጻር የፍርድ ቤት ዉሳኔ እንደ ትእዛዝ ሳይሆን መጻፍ ያለበት፤ አንባቢን
ወይም ተመልካችን ለማሳመን ተብሎ ነዉ መጻፍ ያለበት፡፡ ዉሳኔዉ የሰበር ሰሚ ዉሳኔ ከሆነ ደግሞ ይህ
አባባል የበለጠ ተቀባይነት ያገኛል፡፡

በእርግጥ የሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸዉ የሕግ ትርጎሞች በማንኛዉም የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅ
እንደሆነ የሚደነግግ አዋጅ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ድንጋጌ ብቻዉን የሰበር ሰሚዉ የሚሰጣቸዉ የሕግ
ትርጉሞች አስገዳጅ እንዲሆኑ አያስችልም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የአዋጅ ድንጋጌ የሚያስነሳዉ ጥያቄ፤
እንዴት ማስፈጸም ይቻላል የሚል ነዉ? አንድ ዳኛ ወይም ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠዉን የሕግ
ትርጉም ወደ ጎን በማለት ሌላ ትርጉም ቢሰጥ ይህ ቅጣትም ሆነ ሽልማትን ያልያዘን የአዋጅ ድንጋጌ
እንዴት ነዉ ማስፈጸም የሚቻለዉ? በእርግጥ ዳኞችን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመሾም በሚደረገዉ
ግምገማ፤ አንድ ዳኛ ምን ያህን የሰበር ዉሳኔን ያከብራል የሚለዉ አንድ የግምገማ ነጥብ ሊሆን ይችላል፡፡
ግን ይህን የአዋጁ ማስፈጸሚያ መንገድ አድርጎ መዉሰድ ያስቸግራል፡፡ ሁለተኛዉ የማስፈጸሚያ መንገድ
ፍርድ ቤቱ ወይም ዳኛዉ ከዚህ በፊት በሰበር የተሰጠዉን የሕግ ትርጉም ባለመከሉ የተነሳ ጥቅሙ
የተነሳበት ወገን በሚያቀርበዉ ይግባኝ ወይም የሰበር አቤቱታ ነዉ፡፡ በእርግጥ ይህ ከሆነ ከዚህ በፊት
ተቃራኒ ትርጉም የሰጠዉ ሰበር ችሎች ወይም ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ የበታች ፍርድ ቤት የሰጠዉን የሕግ
ትርጉም ዉድቅ በማድረግ የቀደመዉን የሕግ ትርጉም ሊከተለዉ ይችላል፡፡ ጥያቄዉ ታዲያ፤ ይህ የአዋጅ
ድንጋጌ ባይኖም እንኳ በይግባኝ ወይም በሰበር አቤቱታ ይህ ሊስተካከል ከቻለ አዋጁ በግልጽ የሰበር
የሕግ ትርጉሞች አስገዳጅ ናቸዉ ማለቱ የሚጨምረዉ አዲስ ነገር ምንድን ነዉ?

እንደ እኔ እምነት ሰበር ችሎቹ የሚሰጣቸዉ የሕግ ትርጉሞች ከሰበር በታች በሃገሪቱ ባሉ ችሎቶች
ተቀባይነት እንዲኖረዉ ለማድረግ የአዋጅ ድንጋጌ ብቻዉን በቂ አይደለም፡፡ እንደዉም የአዋጅ ድንጋጌም
www.abyssinialaw.com

ላይስፈልግ ይችላል፡፡ የቀደምን የፍርድ ዉሳኔን እንደ ሕግ ቆጥረዉ በሚከተሉ አገሮች ይህን እንዲያደደርጉ
የሚያስገድድ የተጻፈ ድንጋጌ የለም፡፡ ሰበር ችሎቱ የሚሰጣቸዉ የሕግ ትርጎሞች አስገዳጅነታቸዉ
የሚመነጨዉ መመንጨትም ያለበት ከዉጭ (ከአዋጅ ድንጋጌ) ሳይሆን ከዉስጥ ነዉ፡፡ ማለትም
ከራሳቸዉ የሕግ ትርጉሞች ወይም የሰበር ዉሳኔዎች ናቸዉ፡፡ ዉጫዊ ፋክተሮች አጋዥ ናቸዉ፡፡

የሰበር ሰሚ የሕግ ትርጉሞች አስገዳጅነታቸዉ የሚመነጨዉ ከራሳቸዉ ከዉሳኔዎቹ ነዉ ስንል ምን


ማለታችን ነዉ? እንደ እኔ እምነት ብዙ ነገር ለማለት ነዉ፡፡ አንደኛ ሰበር ችሎቱ ዉሳኔዉን ሲጽፍ እንዴት
ነዉ የሚጽፈዉ የሚለዉ ይወስነዋል፡፡ ከሁለቱ ወገኖች ማን እንዳሸነፈ ለመናገር ብቻ ነዉ? ወይስ ሌሎች
ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ የሕግ ትርጉም እንዲከተሉ ለማዘዝ ነዉ? ወይስ ሌሎች ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ
የሕግ ትርጉም እንዲከተሉ ለማሳመን ነዉ? መልሱ አንድ እና ሁለት ከሆነ ከሰበር ዉሳኔዉ የሚጠበቀዉ
ይዘት ዉስን ነዉ፡፡ ማን እንዳሸነፈ በግልጽ ካሳወቀና፤ ሌሎች ፍርድ ቤቶች እንዲከተሉ ማዘዝ የፈለገዉን
በግልጽ ካስቀመጠ በቂ ነዉ፡፡ ምክንያት ማቅረብም፤ ሆነ ለማሳመን ብዙ መጣር የለበትም፡፡ ነገር ግን
አላማዉ ሌሎች ፍርድ ቤቶችን እንዲሁም የሕግ ባለሙያዎችን እና ዜጎችን ማሳመን ከሆነ ከሰበር ዉሳኔዉ
የሚጠበቀዉ ይዘትና የጥራት ደረጃም ከፍ ይላል፡፡

1. የጉዳዩን ጭብጥ በግልጽና በትክክል ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡


2. የጉዳዮን ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች በትክክልና በሙሉነት ማስቀመጥ አለበት፡፡ ከሰበር ችሎቱና
ከተሟጋች ወገኖች ዉጭ ያሉ አካላት የጉዳዩን ሙሉ መዝገብ የማየት እድል የላቸዉም፡፡ ታትሞ
የሚወጣዉ ዉሳኔዉ እንጂ ሙሉ መዝገቡ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዉሳኔዉ ላይ ፍሬ ነገሮቹ
በትክክልና በሙሉነት መመዝገብ አለባቸዉ፡፡
3. በተመሳሳይ ምክንያት የጉዳዩ አመጣጥ በግልጽ መቀመጥ አለበት፡፡ ጉዳዩ የት ተጀመረ፡፡ ምን
አይነት መከራከሪያ ሃሳቦች ቀረቡ፡፡ ምን አይነት ዉሳኔ በታች ባሉ ፍርድ ቤቶች ተሰጠ፡፡ ማን
ይግባኝ አለ፡፡ ይግባኝ ለማለት የቀረበዉ ምክንያት ምን ነበር፡፡ በይግባኙ ላይ የተያዘዉ ጭብጥ
ምን ነበር፡፡ ምን አይነት መከራከሪያዎች ቀረቡ፡፡ ምን አይነት ዉሳኔ ተሰጠ፡፡
4. አሁንም በተመሳሳይ ምክንያት የሰበር አቤቱታዉን ማን አቀረበ፡፡ በአቤቱታዉ ላይ የቀረቡት
ምክንያቶች ምን ነበሩ፡፡ ለምን የሰበር አቤቱታዉ ተቀባይነት አገኘ፡፡
5. በሰበር ሂደቱ የተያዙት ጭብጦች ምንድን ናቸዉ፡፡ የቀረቡትን መከራከሪያዎች ምንድን ናቸዉ፡፡
እነዚህ መከራከሪያዎች በታማኝነት በትክክልና ሙሉ ለሙሉ ሊመዘገቡ ይገባል፡፡ የሰበር ችሎቱ
ዉሳኔ እና የሚያቀርባቸዉ ምክኒያችና አሳማኝነታቸዉ በከፊል የሚገመገመዉ ተሟጋች ወገኖች
ካቀረቧቸዉ መከራከሪያዎች አንጸር ነዉ፡፡
www.abyssinialaw.com

6. የሰበር ዉሳኔዉ ችሎቱ የተለያዩ የታች ፍርድ ቤቶች ከሰጧቸዉ የሕግ ትርጎሞች የተለየ ከተጠቀመ
ለምን የታች ፍርድ ቤቶች የሰጧቸዉ የሕግ ትርጉሞች ትክክል እንዳልሆኑ ማሳየት አለበት፡፡
እንዲሁም ሰበር ችሎቱ በተሟጋች ወገኖች የቀረቡትን መከራከሪያዎች እያንዳንዳቸዉን ለምን
እንደተቀበላቸዉና እንዳልተቀበላቸዉ በሚገባ ማስረዳት አለበት፡፡
7. የሰበር ችሎቱ የስር ፍርድ ቤቶችን ዉሳኔ የሚቀይር ከሆነ፤ የተለየ ትርጉም የሚሰጥ ከሆነ ለምን
የተለየ ትርጉም መስጠት እንዳስፈለገ ማስረዳት አለበት፡፡ እንደሚታወቀዉ የሰበር አቤቱታ
ተጨማሪ የይግባኝ መብት ወይም አማራጭ አይደለም፡፡ የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ የሕግ ስህተት
ማስተካከያ አማራጭ ነዉ፡፡ የሕግ ስህተት ሳይሆን መሰረታዊ የሕግ ስህተት ማሰተካከያ ነዉ፡፡
በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች የሰጧቸዉ የሕግ ትርጉሞች ስህተት መሆናቸዉን ማሳየት ብቻ በቂ
አይደለም፡፡ መሰረታዊ መሆናቸዉንም ማስረገጥ አለበት፡፡
8. በአዋጁ መሰረት አስገዳጅ የሆነዉ የሰበር ትእዛዙ ሳይሆን የሰበር ችሎቱ የሰጠዉ የሕግ ትርጉም
ነዉ፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የተረጎመዉን እና አስገዳጅ እንዲሆን ያሰበዉን አንድ ወይም ከዛ
በላይ የሕግ ትርጉም ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ አለበት፡፡
9. ከጉዳዩ ጋር የሚገኛኙ ከዚህ በፊት ዉሳኔ የተሰጣቸዉ የሰበር ዉሳኔዎች ካሉ እነሱን በዉሳኔዉ
ጠቅሶ ከጉዳዩ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰሉና እንደሚለያዩ፤ ያሁኑ የሕግ ትርጉም ከዚህ በፊት
ከተሰጡት እንዴት እንደሚሄዱ ማስረዳት አለበት፡፡
10. የዉሳኔዉ የተለያዩ ክፍሎች እርስ በርሳቸዉ የማይጋጩ፤ በግልጽ ቋንቋ የተጻፉ መሆን አለባቸዉ፡፡
11. ሰበር ሰሚዉ በዉሳኔዉ የሚጠቀምባቸዉን ሕጎችና ይዘታቸዉን እንዲሁም ትርጉማቸዉን
በሚገባና በትክክል ማስቀመጥ አለበት፡፡ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አርማለዉ በሚል እጅግ ቀላልና
ግልጽ ስህተት ሕግን በመለየትና በመተርጎም የሚሰራ ከሆነ ታማኝነቱን ይሸረሽረዋል፡፡
12. ሰበር ሰሚዉ በዉሳኔዉ ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት መሰራቱን ለማስረዳት ወይም አንድ ሕግ
እንዴት መተርጎም እንዳበት ለማሳየት የተለያዩ አማራጭ ትርጉሞች የሚኖራቸዉን የወደፊት
አንድምታና መዘዝ፤ እንዲሁም የተከተለዉ ትርጉም ከሕጉ አላማ ጋር አብሮ የሚሄድ ስለመሆኑ
ማስረዳት አለበት፡፡ ሕግን ለመተርጎም የቋንቋን እና የሎጂክ መመሪያዎችን ብቻ የሚከተል ከሆነ
ሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዴት ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተለየ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
13. ሰበር ችሎቱ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን በሚገባ ሲወጣ የሚያስተላልፈዉ መልእክት ዉሳኔዬን
በሚገባ አይቼ፤ በጣሙን አምኜበት፤ ብዙ ነገሮችን መዝኜ፤ ነዉ የሚል ነዉ፡፡ ማለትም ጉዳዩን
በሚገባ ከመርመሬ የተነሳ፤ ተመሳሳይ ጉዳይ ወደፊት ቢመጣልኝም እንኳ ተመሳሳይ ዉሳኔ እና
ትርጉም እከተላለዉ የሚል መልእክት ነዉ እያስተላለፈ ያለዉ፡፡ እነዚህን ነገሮች በሚገባ
www.abyssinialaw.com

ካልተወጣ ግን የሚያስተላልፈዉ መልእክት ተመሳሳይ ጉዳይ ወደ ፊት ቢመጣም በተመሳሳይ


መንገድ ላላየዉ እችላለዉ የሚል ነዉ፡፡ ታዲያ ባለቤቱ ያቀለለዉን አሞሌ ባለእዳ እንዴት
ይቀበለዋል፡፡

ከላይ በግልጽ ለማስቀመጥ እነዚህ ጉዳዮች የአንድ ሰበር ሰሚ ዉሳኔ እኔ በዉሳኔዉ የተካተተዉ የሕግ
ትርጉም የሚኖረዉን የአስገዳጅነት ደረጃ የሚወስኑ ናቸዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያሉ ዉጫዊና አጠቃላይ
የሕግ አመለካከቶች የሕግ ትርጉሙን አስገዳጅነት ሊያጠናክሩት ወይም ሊሽሩት ይችላል፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንጸር ሰበር ሰሚ ችሎቱ በእነ ሙና እንድሪስ እና የኢትዮጲያ ልማት ባንክ
መዝገብ የሰጠዉ ዉሳኔ የሚከተሉት ቅርጻዊ ጉድለቶች ታይተዉበታል፡፡

1. የሰበር አመልካቾች ብዙ ለመሆናቸዉ እነ ሙና እንድሪስ የሚለዉ አነጋገር ቢያመለክትም ስንት


ስለመሆናቸዉ የዉሳኔ መስመር ቁጥር 43 እና 44 እስኪደረስ ድረስ ግልጽ አይደለም፡፡
2. የቀን አጻጻፍ ዘይቤዉ ለምሳሌ በዉሳኔ መስመር ቁጥር 23 ላይ ብቻ እንኳን ወጥነት ይጎድለዋል፡፡
3. መስመር 36 ላይ የስር ሁለተኛ ተከሳሽ የአሁን አመልካች ይላል፡፡ ነገር ግን የስር ሁለተኛ ተከሳሽ
የአሁን መልስ ሰጪ እንጂ አመልካች አይደለም፡፡
4. ለምን ሰበር ችሎቹ የሰበር አቤቱታዉን ለመቀበል እንደወሰነ ግልጽ አላደረገም፡፡ በደፈናዉ ለሰበር
ቀርቦ መጣራት የሚገባዉ ሆኖ በመገኘቱ ነዉ የሚለን፡፡
5. በሁለቱም ወገኖች በሰበር ሂደቱ ያቀረቧቸዉ ክርክሮች ምን እንደሆኑ ግልጽ አይደለም፡፡ መስመር
55 ላይ በአጠቃላይ የክርክር ይዞታ ከላይ የተመለከተዉ ነዉ ይለናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ መስመር
በፊት ያሉት የዉሳኔዉ ክፍሎች መከራከሪያ ነጥቦቹን አያስቀምጡም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የሰበር
ችሎቱን ዉሳኔ እና የሕግ ትርጉም አግባብነት መገምገም አይቻልም፡፡
6. በመስመር 55 እና 56 አቤቱታዉ ለሰበር ያስቀርባል ከተባለበት ነጥብ አኳያ መርምረናል ይላል
ዉሳኔዉ፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ መስመሮች በፊት ያሉት የዉሳኔዉ ክፍሎች የተባለዉን ነጥብ
አያስቀምጡም፡፡
7. ከመስመር 70 እስከ 75 ባሉት በቁጥር 1810 ያለዉ የሁለት አመት የይርጋ ጊዜ ተፈጸሚ የሚሆነዉ
ለዉሉ ፈራሽ የሚሆነዉ ለዉሉ መፍረስ ምክንያቱ የችሎታ ወይም ፈቃድ ጉድለት ሲኖር ብቻ
እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ለዚህ ትርጉም የተሰጠ ምክንያት የለም፡፡
8. ከመስመር 85 እስከ 89 ባሉት ዉሳኔዉ ስለአዲሱ የቤተሰብ ሕግ ይመለከታል፡፡ ነገር ግን ይህ
ድንገተኛ ነዉ፡፡ ከዚህ በፊት ያሉት የዉሳኔዉ ክፍሎች ለምን የቤተሰብ ሕግን መጠቀም
እንዳስፈለገ ግልጽ አያደርጉም፡፡
www.abyssinialaw.com

9. በመስመር 95 እና 96 ሰበር ችሎቱ አንድ ዉል ሕግን የሚቃረን ነዉ በሚባልበት ጊዜ እንዲፈርስ


ጥያቄ መቅረብ ያለበት በ10 ዓመት ጊዜ እንደሆነ ከቁጥር 1845 መረዳት ይቻላል ይለናል፡፡
እንዴት/ለምን ለሚለዉ ምክንያት የለዉም፡፡
10. ከመስመር 99 እስከ 101 ባሉት ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት የተጠቀመዉ ድንጋጌ ለጉዳዩ አግባብነት
ስለሌለዉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተስርቷል ይላል፡፡ ይህ ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት የሕግ ስህተት
እንደሰራ እንጂ ይህ ስህተት መሰረታዊ ስለመሆኑ የሚያስቀምጠዉ ምክኒያት የለም፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሱት አስር ቅርጻዊ ዉስንነቶችና እና ጉድለቶች ብቻ የሰበር ችሎቱ በእነ ሙና እንድሪስ
እና የኢትዮጲያ ልማት ባንክ የሰጠዉ የሕግ ትርጉም አስገዳጅነቱ አጠያያቂ ነዉ፡፡ ከላይ በግልጽ
ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት የሰበር የሕግ ትርጉም አስገዳጅነት የሚመነጨዉ በአብዛኛዉ ከራሱ
ከዉሳኔዉ ነዉ፡፡

ይህ የሰበር ዉሳኔ ግልጽ አለመሆኑ እና ምክንያት አለማስቀመጡ ብቻ ሳይሆን ጉድለቱ እንደ እኔ እምነት
ብዙ የሕግ ስህተቶችን ፈጽሟል፡፡ እንደ እኔ እምነት ሰበር ችሎቱ የፈጸማቸዉ ስህተቶች መሰረታዊ
ናቸዉ፡፡ ከዚህ ቀጥሉ ባሉት ክፍሎች እነዚህን ስህተቶች ለመለየትና ለማብራራት ይሞከራል፡፡ እንዲሁም
ይህን ዉሳኔ እንደ መነሻ በጽሁፉ ርእስ የተነሳዉን ጥያቄ ለመመለስ ይሞከራል፡፡

(ይቀጥላል)

You might also like