You are on page 1of 140

ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ።

ብላ ካለኝ እንደአባቴ በቆመጠኝ።

ጌጥ ያለቤቱ ቁምጥና ነው።

ደሀ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ ንጣት በገደለው።

የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም።

አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ።

ሲተረጉሙ ይደረግሙ።

ቀስ በቀስ፥ ዕንቁላል በእግሩ ይሄዳል።

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር።

ሰው እንደቤቱ እንጅ እንደ ጉረቤቱ አይተዳደርም።

እግዜር የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አይድርም።

የጎረቤት ሌባ፥ ቢያዩት ይስቅ ባያዩት ያጠልቅ።

ሥራ ከመፍታት ልጄን ላፋታት።

%
ዓባይ ማደሪያ የለው፥ ግንድ ይዞ ይዞራል።

የእስላም አገሩ መካ የአሞራ አገሩ ዋርካ።

ተንጋሎ ቢተፉ ተመልሶ ባፉ።

ወዳጅህ ማር ቢሆን ጨርስህ አትላሰው።

እግርህን በፍራሽህ ልክ ዘርጋ።

አልሸሽም ዞር አሉ።

ትከሻው ካበጠ ዝንጅሮም አንበሳ ይሆናል።

ገበታ ለአዋቂ ወሬ ለጠያቂ።

እዚያም ሄደሽ በላሽ፣

እዚህም መጥተሽ በላሽ፣

ሰው ታዘበሽ እንጂ ሆድሽን አልሞላሽ።

ጅብን ሲቀርቡ በአህያ።

ስም ከመቃብር በላይ ይውላል።

መንገድ የምታውቅ አይጥ ከፈረስ የበለጠ ትሮጣለች።

%
ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል።

ልፋ ያለው በሬ ቆዳው ለከበሮ ይወጠራል።

ንዝንዝ ጭቅጭቅ አደርባይ ያሰኛል፣

ወይንም ገድሎ መሄድ ወይም ሰምቶ መቻል።

ጥንት አባቶቻችን ተጋዳይ ነበሩ፣

ጥንት እናቶታችን ተጋዳይ ነበሩ፣

ጥንት ወንድሞቻችን ተጋዳይ ነበሩ፣

እህቶቻችንም ተጋዳይ ነበሩ፣

እኛን ያፈዘዘን ምን ይሆን ነገሩ?

ጐበዝ ይሙት ፈሪ ይኑር ቢሻው፣

አተላ መሸከም ይችላል ትከሻው።

ከላይ ከደጋው ላይ ቦታ ደልድለናል፣

ቢሆን እንሠራለን ባይሆንም ይቀራል።

ስግብግብ አንዱ ያንቀው አንዱ ይወድቀው።

ለአፈኛ ሰው ገደልም ሜዳ ነው።

አሽሟጣጭ ዝናብ ወንዝ ዳር ያካፋል።

መካኑ ብዙ ነው በሮም በሶሪያ፣


ወላድ እጅግ አየሁ በኢትዮጵያ።

የዘሩት ሁሉ አይበቅልም፣ የወለዱት ሁሉ አያድግም።

በመስከረም የሚቆስል እግር በሰኔ ዝምብ ይወረዋል።

የባዳ ሞኝ ከዘመድ እኩል፣ የዘመድ ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ ይላል።

ሞት ይቅር ይላሉ፣ ሞት ቢቀር አልወድም፣

ድንጋዩም አፈሩም ከሰው ፊት አይከብድም።

ሥጋ እበላ ብዬ የቆረጥኩትን፣

ላሳያችሁ መጣሁ እኔማ ጣቴን።

በጎዣም ያካፋል በሸዋ ፀሐይ፣

በጎንደር ደመና መቅረቱ ነው ወይ?

በባቡር ተጉዘን ምንድን ነው ቅልውጡ?

ግብፆች ለአበሻ ደግሰው ላይሰጡ።

አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም።

ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል።

ነገር ከሥሩ ውኃን ከጥሩ።

%
እብድ ቢጨምት እስከ እኩለ ቀን ብቻ ነው።

ሰው ጥራ ቢሉት እራሱ መጣ።

የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል።

ቀንድ የገባበት ጅራት አይቀርም።

በሬ ካራጁ ይውላል።

ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ።

ማን ቢስምሽ ማሞጥሞጥሽ።

ሞኝና ወረቀት የያዙትን አይለቁም።

የነብር ጅራት አይዙም ከያዙም አይለቁም።

ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ።

የምናውቃትን ክምር ገለባ አለበሷት።

ሞኝ ይስቃል፣ ብልህ ያለቅሳል።

ባሰበችው ቀርቶ ባሰበው ካዋላት፣

እኔ ምን እላለሁ እናንተው ቅበሯት።


%

ስልብ ሎሌ በጌታው ምንትስ ይፎክራል።

ለዚሁም ትዳሬ ይቆጡኛል ባሌ።

ሳይከካ ተቦካ።

ማርና ወዳጅ በልኩ ነው።

እብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል።

አንጀት ዳብሣ የማታበላ ሴት፣

በክረምት የሚያፈስ ቤት፣

ሴቷንም መፍታት፣

ቤቱንም ለእሳት።

በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ።

እሷ ሳትነሳ ልታቋቁም ሔደች።

ሳይተርፋት አበድራ ሳትቀበለው ሞተች።

እየሰማ የሞተ እያየ ይቀበራል።

ሰው በሰው፣ ቅቤ በጨው።

%
ስትሠራ ውላ አበላሸችው ባተላ።

ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ።

ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል።

ሲታጠቡ እስከ ክንድ ሲታረቁ እስከ ሆድ።

እሳት ቢዳፈን የጠፋ ይመስላል፤

ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል።

ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው።

አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ።

ከጅብ የተጠጋ ፈረስ ኋላውን አያይም።

ሴትና ዶሮ ሳያብድ አይውልም።

ይሆናል ያሉት መድኃኒት ዓይን አጠፋ።

የሚዳቋ ብዛት ለውሻ ሠርግ ነው።

በፈረስ የፈለጉት በእግር ይገኛል።

ለዳኛ አመልክት እንዲሆን መሠረት።


%

ባለቤት ያከበረው አህያ በቅሎ ይለውጣል።

እንጀራ ከባዕድ መከራ ከዘመድ።

ይብራና ይብራ ተጣሉ በሰው ሽምብራ።

ደጃቸውን ሳይዘጉ ሰው ሌባ ይላሉ።

ድኃ ተበድሎ ማሩኝ ይላል ቶሎ።

የሚያልፍ ዝናም አይምታህ፣

የሚሞት ሽማግሌ አይርገምህ።

ጅብና እህል ሳይተዋወቁ ይኖራሉ።

እንቅልፍ ታበዢ ከነብር ትፋዘዢ።

እንጨት ካልነሱት እሳት አይጠፋም።

የገበያ ሽብር ለቀጣፊ ይመቻል።

በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ።

የተሾመ ይሟገቱለታል በተሻረ ይመሰክርበታል።

%
ደባልና ሹመት አለሰበብ አይሄድም።

ክረምትና ልጅ ሲጠሉት ያከብራል።

ከተረገመ በቅሎ የተባረከ አህያ ይሻላል።

ለከርሞ የሚያብድ ዘንድሮ ሱሪውን ከፍ ከፍ ያደርጋል።

ቅቤ አንጣሪዋ እያለች፣

ጎመን ቀንጣሽዋን ምች መታት።

የአንተን የሚመስል እኔም አለኝ ቁስል።

ባይቸኩሉ እንቁላል ይሄዳል በእግሩ።

ግርግርታ የሌባ ደስታ።

ሁሉም ያልፋል እስኪያልፍ ያለፋል፣

ድኃ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል።

የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል።

ምቀኛ ጠላቱን ይተክል፤ ራሱን ይነቅል።

ያየ ቢሄድ የሰማ ይመጣል።

%
የተነቃነቀ ጥርስ ሳይወልቅ አያርፍም።

ከባዕድ እየጐረስክ ወደዘመድህ ዋጥ።

ሰዎች ሁሉ አብደው እኔ ጤነኛ ከሆንኩ እብዱ እኔ ነኝ።

ለስሶ ፍትፍት አሳይቶ እበት ያጐርሷል።

የክፉ ልጅ እናት ሁለት ጊዜ ታዝናለች።

ያልወለደ አጋድሞ አረደ።

ያምራል ብሎ ከተናገሩት ይከፋል ብሎ የተውት።

የዝንጀሮ መነኩሴ የሰንበሌጥ አንካሴ።

የዘላን ጦመኛ ከጥጃ ጓዳ አታግቡኝ ይላል።

ውሻ ካልቀበጠ ጅብ አይበላውም።

ለአንተ የተባለ እንጀራ ሌላ አያገኘውም ሻግቶ ይቀራል እንጂ።

የወታደር ቁም ነገረኛ ባመቱ ድኃ።

በገዛ ሀገራችን በገዛ ወንዛችን፣

ማዕዘኑ እንደሆነ ሞልቷል ባገራችን።


%

ነፍስ ብትታመም ፍሪዳ አረዱላት፣

በከንቱ ነው እንጂ ሥጋ ላያድናት።

ለጠጁ ነበረ ብቸና መሄዴ፣

ዲማ ሥጋ አላጣም ታረዱ ዘመዴ።

ሻኛ ትከሻ ላይ ተቀምጦ ይወፍራል።

-- የጉጂ ተረትና ምሳሌ

ደግነት የሚቆየውን ያህል ክፋት አይቆይም

-- የጉጂ ተረትና ምሳሌ

ከባዕድ ቆንጆ ቤት የራስ ጎጆ ይሻላል

-- የጉጂ ተረትና ምሳሌ

እውነት ከጠፋበት ሥፍራ ይልቅ

ሰው ከሞተበት ሥፍራ መኖር ይሻላል።

-- የጉጂ ተረትና ምሳሌ

ይህች ጠጋ ጠጋ ዕቃ ለማንሳት ነው።

-- የከንባታ ተረትና ምሳሌ።

ሚዳቋ ሐምሌ ትዝ ሲላት በጥር ትንቀጠቀጣለች።

-- የከንባታ ተረትና ምሳሌ።

%
ከጉንዳን ቤተሰብ ትልቁ ትንሽ ነው።

-- የከንባታ ተረትና ምሳሌ።

ለሁሉም የመጣ ችግር እንደ ሠርግ ይቆጠራል።

-- የከንባታ ተረትና ምሳሌ።

ቀድሞ የጎመራ እህል አይበረክትም

-- የከንባታ ተረትና ምሳሌ።

ምላሰኛ ጦረኛን ያባርራል።

-- የከንባታ ተረትና ምሳሌ።

መጥፎን የወለደ ሞቶም አላረፈ።

-- የቸኻ ተረትና ምሳሌ።

ምንም የማይጮህ ወፍ ሲጮህ ጫካን ያደነቁራል።

-- የቸኻ ተረትና ምሳሌ።

ይሉኝታ የፈራ እራሱን ጎዳ።

-- የቸኻ ተረትና ምሳሌ።

ትንሽ ችግር ይድረስብህና

የሚወድህንና የሚጠላህን እወቅ።

-- የቸኻ ተረትና ምሳሌ።

ቀንድ ሊያበቅል የወጣ አህያ ጆሮውን ጥሎ መጣ።


-- የቸኻ ተረትና ምሳሌ።

ችኩል እግር ከዘንዶ ጉድጓድ ይገባል።

-- የወላይታ ተረትና ምሳሌ።

ብዙ ትዕግስት የጊደር ወተት ያስጠጣል።

-- የወላይታ ተረትና ምሳሌ።

እስኪበስል የማያደርስ ረሀብ እስኪበርድ አያደርስም።

-- የወላይታ ተረትና ምሳሌ።

ማለዳ በመጋዣ መንገድ የሔደ፣

ማታ ሰንጋ ፈረስ ቢጭኑ አይደረስበትም።

-- የወላይታ ተረትና ምሳሌ።

እንዶድ በገርነቱ ውሃ ወሰደው።

-- የወላይታ ተረትና ምሳሌ።

ዘንዶ ለሆዱ ሲል በሆዱ ይሄዳል።

መሞገስ የፈለገ ይሙት፣ መሰደብ የፈለገ ሚስቱን ይፍታ።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ሳይደርስ ያገባ ሲደርስ ይፈታል።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

%
የሞተ ሰው ሠርጉ ሦስት ቀን ነው።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

የፍየል ዓይን ቅጠል ላይ የጎረምሣ ዓይን ልጃገረድ ላይ።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ለሞኝ ወተት ጥሬው ማር ኮምጣጣው ነው።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ከልጅ ጋር የዋለ ሽማግሌ ሞቶ ተገኘ።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ነገር ፈላጊ ከሆንክ ከግቢህ ውስጥ ቤት አከራይ።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ውኃ እንዲጠብቅ የተቀጠረ አሽከር ድንጋይ የሚያቀብለው ቀጠረ።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ለራስ ያሉት ገንፎ አይቀጥንም።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ሥጋ ለማያውቅ ሣንባ ስጡት አገዳ ለማያውቅ ሣር ስጡት።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ወተት ያጣ አሬራ ጠጣ።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ


%

ከበሽታ መዳን ከሙሽርነት ይቆጠራል።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ዕቃ እንደባለቤቱ ነው።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ቁጣ የቀደመው ፀፀት ተረፈው።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

መለመን በሽታ ነው ለምኖ ማጣት ሞት ነው።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

አልሞት ያለችዋን አሮጊት ልጅ አሸክሟት።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ሥራ ያጣ የአንበሣ ጥርስ ነቀሰ።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

ማን አሳደገው እንጂ ማን ወለደው አይባልም።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

የሠረቀች ዓይን አስቀድማ ታለቅሳለች።

-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

የነገረ አጥቶ የተነገረው አገኘ።


-- የአደርኛ ተረትና ምሳሌ

የቁማር ገበያ እጅግ ተፋፍሞ፣

ሀገሬ ተበላች ሕዝቧ ከዳር ቆሞ።

ጎጆየን አፍርሷት ቁንጮዋን ይዛችሁ፣

መቼም ቤት አልሰራም እናንተ እያላችሁ።

ጠጅ መስሎን ነበረ ሲከፈት ምርጊቱ፣

ጠላ ነው መልሱ ከነበረበቱ።

ማድጋውን ሁሉ ታስቆጥራላችሁ፣

አለቃችሁ እንጂ ማን ወሰደባችሁ።

ምንም ሳይቸግረው ተቀምጦ በተድላ፣

እንዴት ሲሮጥ ሄዶ ይሞታል በዱላ።

ማን አመጣብኝ ስል ገርሞኝ መሸለሉ፣

ለካስ አሁን ገባኝ አንድ ነው ክልሉ።

መለስ ቀለስ ብላ አየችው ቀሚሷን፣

ረሳችውና ባፈር መለወሷን።

ሰውን ሰው ናቀው፣

የራሱን ሳያውቀው።

%
ዳኛ ሲገኝ ተናገር፣

ውኃ ሲጎድል ተሻገር።

ሐሰተኛ በቃሉ፣

ስደተኛ በቅሉ።

መዋቀስ፣

መራከስ።

አባት ካልሞተ ልጅ አዋቂ አይባልም።

ሲደላኝ አቅፋታለሁ፣ ሲከፋኝ እገፋታለሁ።

እንኳንስ በአህያ ቢጭኑህ በውሻ፣

ቀን ከተሰበረ አያድንም ጋሻ።

ንቡን እሽ በለው አስጠጋው ከገደል፣

ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል።

አንድ ዘመን አለ የተልወሰወሰ፣

ወይ ጠርቶ አላረፈ ወይ አልደፈረሰ።

ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ናት ይሏታል።

ለሙን መሬት ትተው ጋራውን አረሱ፣

የዛፍ ዘር ሳይጠፋ እንቧጮ አነገሱ።


%

አባይ ከደፈረሰ፣

ባለጌ በርኖስ ከለበሰ፣

አባይም አያሻግር፣

ባለጌም አያናግር።

ቢታዘዝ ነው እንጂ ከላይ ተዠመዱ፣

እሾህ ይወጋል ወይ? በጫማ ተሄዱ።

ከእግር ነጣ ነጣ፣ ከእጅ ነጣ ነጣ፣

እንዲያ እንዲያ እያለ ነው ቁምጥና እሚመጣ።

ሲጠርጉ ከመኖር የድሩን ዝግንትል፣

ከሥቃይ ለማረፍ ሸረሪትን መግደል።

ጠላ መጠንሰሱን አላውቅም እያለች፣

ጠጅ እንደምን አውቃ ትበጠብጣለች።

ሞፈር ዘመት አርሶ ምን ይጠቀማል ሰው፣

ጦጣና ዝንጀሮ ማልዶ ተቀመሰው።

እደግ እደግ ብለን ያሳደግነው ቀጋ፣

ይላል ቀና ጐንበስ እኛኑ ሊወጋ።

አርግልን ያልንህን አረክልን ለካ፣

በነካካው እጅህ እኒህንም እንካ።


%

ሲሆን ተከናነብ ሳይሆንም ልበሰው፣

አያደገድግም እንዳንተ ያለ ሰው።

ከስቼ ቢያዩኝ ጅማት ለመኑኝ።

ያበደውን በሬ ቀንዱን ይዘው አሸንፈው።

ድንጋይ ሲጸና ሲቀል ጥብጣቡ፣

እያንጠበጠበ ይቆረቍራል አለቱ።

የደረቀ ምንጭ ይጮኻል፣

ያልሞላ ገንቦ ይምቦጫቦጫል።

ዋርካ በሌለበት ብሳናው አድባር ነው።

ምን ይጐዳል ቢሞት የመጋዣ ልጅ፣

አንድ በቅሎ ሲጠፋ ያሳዝናል እንጅ።

ክፉ ሳይናገር ሞት ይፈታል አገር።

ዱለቱን የበሉት ቄሱ፤ እማሆይ ፈርስ አገሱ።

አውልቀው ወንድሜ አውልቀው ሱሪህን ምን ያደርግልሃል፣

ስንት አዕላፍ ሴት ውስጥ አንቀው ይገድሉሃል።

%
ወንድሙን ሲገድሉት ወንድሙን ካልከፋው፣

አቅርቡለት ልብሱን የወንድሙን ሱሪ ደሙ እንዲከረፋው።

የዝንጀሮ ንጉስ ራሱ ይከምር ራሱ ያፈርስ።

ምድር በወለደች ነደደች።

ሰርቆ ከማሰብ እጅን መሰብሰብ።

ሰውን ሰው ናቀው፣ የራሱን ሳያውቀው፣

ተመውጣቱ ዓለምን ዞሮ መምጣቱ።

ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ።

ገበያ ቢያመቻት፣ ልጇን አስማማቻት።

ያፍ ዘመድ ከገበያም አይገድ።

ላሳር የጣፈው፣ ቢነግድ አይተርፈው።

ተሰብሮ ቢጠገን፣ እንደቀድሞው አይሆን።

የጉም ሌባ ጉሙ ሲለቅ የት ትገባ?

ዋቢ ያለው ያመልጣል፣ ዋቢ ያጣ ይሰምጣል።


%

ዳኛም ይመረምራል፣ ጣዝማም ይሰረስራል።

ለመራመድ ያቃታት እግር ለእርግጫ ተነሳች።

ባንቺ ኑሮ ባንቺ ንብረት 7 ውሻ 7 ድመት።

አበቅቴ ሲቆጠር ብሰማ እንደዋዛ፣

ምን ያለ ዘመን ነው ተውሳኩ የበዛ።

ምን ዕዳ ቢቆለል አይጨነቅ እሱ፣

መከፋፈል ያውቃል በሰላ ምላሱ።

ወጥ በጣም እወዳለሁ ዳጎስ እንዲል ጎኔ፣

አነካክቶ መብላት አይሆንልኝ እኔ።

አፍና ቅብቅብ ሁልጊዜ አያበላም።

ፍሬ ፍሬ ላይ ቆሞ ጎተራ ይሞላል።

የአቦን ፍየል የበላ ይለፈልፋል።

ውል ያዋውላል ታንኳ ያሻግራል።

ውሃ ብሎ ነበር አገኘን ወይ አጣ?

አገር ጥም ቆረጠው ደሙን እየጠጣ።


%

ፍየል ብትመነኩስም መቀነጣጠሷን አትተውም።

እባብ ለሆዱ ሲል በሆዱ ይሔዳል።

የሚያልፍ ውኃ አደረገኝ ድኃ።

ዐመልህን በጉያ፣ ስንቅህን ባህያ።

የኋላ ኋላ አይቀርም ዱላ።

ጊዜ አለው ለሰው እድሜ ካላነሰው።

ለቤት ሳንቃ፣ ለሰው አለቃ።

ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም።

በየገደሉ መቀደስ የተኛውን ሰይጣን መቀስቀስ።

የሰው ልጅና ምስማር አጥብቀው ካልመቱት አይፀናም።

በአህያ ላይ ሞፈር በፈረስ ላይ ቀንበር፣

እኛም የፈራነው ይኽንኑ ነበር።

ገረዴ ሄዳ በድንገት፣

አሽክሬ ሆና ወጥ ቤት፣
የምበላው ሳይጠይቀኝ፣

ሥራ ሰርቶ አስጨነቀኝ።

ፍርድ ልበስ የኔ ጌታ፣

አሽከር አስነሳኝ ከገበታ፣

እንኳንስ ለኔ ለሰው፣

ለእሳት እራት አለው።

ፍቅር ደገደገ ምነው ከሣ?

በጽልሁት በቀለ ነቀርሣ፣

ማን ባመጣልኝ እምነት፣

እሱ ነበር መድኃኒት።

ትንሽ ቤት ሰራሁ እንዳቅምኛ፣

ሁለት ሦስት ሰው የሚያስተኛ፣

አላስገባ አለችው ያችው ጠባ፣

ሰው በሰው ላይ እየገባ።

ሞኞች ላኩትና ሞኙን ሞኞች አገር፣

ሞኞች አይጠይቁት ሞኞም አይናገር።

ዘመን ሲበላሽ አይጥ መጥረቢያ ይቆረጥማል።

ዋሾና ስንቅ እያደር ይቀላል።

እስቲ ጥራኝ ጫካው አረ ጥራኝ ዱሩ፣


ለአንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ።

ተናጋሪ ሲያመርት ሰሚ ያከማቻል።

በሩቅ ሲያዩት አህያ ፈረስ ይመስላል።

ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል።

ድንጋይ ውኃ ውስጥ ስለኖረ ዋና አይለምድም።

የማታ አፍ ከበረት ይሰፋል።

አድመው ቢነሱ አፈረሰው እሱ።

ሲዋቀር ያልበጀው ሲማገር እሳት ፈጀው።

አንቱው ትተረጎሙ፣ አንቱው ትደረግሙ።

አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው።

አዋጅ በአዋጅ የደበሎ ቅዳጅ፣

ዳማ ሲሄድ ዳማ፣

ሌላ ባለጋማ፣

ሌላ ባለጭራ፣

ይመጣል በተራ።
%

ሰው ሙዝ ቢሆን ተልጦ ቢበላ፣

ውስጡ በተጣለ ላዩ በተበላ።

ግፍ የሌለበት ጠላ ያለብቅል ይበስላል።

በወጉ ለማድረቅ ሳይቃጠል እህሉ፣

ማመሱን ሲያውቅበት በረጋው አመሉ።

ውሽልሽል ነው አልጠበቀም ዕርቁ፣

አውድማው ይለቅለቅ በሮቹም አይራቁ።

ምነው አምና በሞትኩ እንዲያ እንዳማረብኝ፣

የማንም ደላጎ ሣይጫወትብኝ።

በላይ እንጨት ስበር፣ ካሣም ውኃ ቅዳ፣

መንገድ እየመራህ ባመጣኸው ዕዳ።

አግብቶ ማሸከም ይህን የኛ ቀንበር፣

ወንድማማች ሆኖ የከዳውን ነበር።

አያፍር አይጨነቅ ስፖርቱ ገብቶታል፣

መገለባበጡን ጥሩ ተክህኖታል።

ምን አዚም ዞረብን ውልክፍክል አልንሳ?

ጎበዝ አለቅን እኮ ሆነን እንደ እሬሣ።


%

እኒያስ መስጠታቸው እርሱስ መቀበሉ፣

ከነልቡ ነው ወይ? አረ ልብ በሉ።

እንዴት አደርጋለሁ ብዬ ስጨነቅ፣

እያደር ይቀላል ዐባይና ስንቅ።

እኔ ከተፈጠርኩ አልጠጣሁም ጠጅ፣

አባቴ በጠጣው ያዞረኛል እንጂ።

አራዳ ለኪራይ ቤት የፈለጋችሁ፣

ዘማለች ምናልባት በውል እያያችሁ።

ዘማለች እያልን ምክር እየናቁ፣

ምን ይጠቀማሉ እየገቡ ቢያልቁ።

አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ባሰብሽ።

የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ።

የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ።

ደሀ እስኪለብስ ሸንጐ ይበተናል።

ባለጌ ተጣሪ ወይ ባዩን ያባልጋል።

%
አባት የላት አያት አማራት።

የቆየ ከሚስቱ ይወልዳል።

አሌ ብሎ የተረታ፣ መሐል አገዳውን የተመታ።

የቡና ቀዝቃዛ፣ የሹም ፈዛዛ።

የጎበዝ ዱዳ፤ ባመቱ ምድረ በዳ።

ያልወለደ አይነሳ፤ የሽንብራ ማሣ።

አትኩራ ገብስ፤ ጎመን ባቆየው ነፍስ።

የገዳይ ምልክቱ ደም በጣቱ።

የእንቢተኛ መድኃኒቱ ዳኛ።

ከቆረበች ባሰች።

እካስ ያለ ታግሶ እፀድቅ ያለ መንኩሶ።

የአባት ዕዳ ለልጅ፣ የአፍንጫ ዕድፍ ለእጅ።

ተመርመር ይገኛል ነገር።

%
ክረምትና ጊዜ የማያወጡት ምስጢር የለም።

ማገር ላያቀብሉ ቤት አስፋ ይላሉ።

የክብር አወዳሽ የሽንብራ ቆሎ ያሽ።

ሰውን ሰው ናቀው፣

የራሱን ሳያውቀው።

ሲያረጁ

አምባር ይዋጁ።

አታላይ ከታች ሲሉት ከላይ።

የቀድሞ ሰዎች በሕልማቸው፣

መጭውን ሁሉ ገልጦላቸው፣

ያላዩት የለም ተሆነው፣

ሁሉ እንዳለሙት ነው።

ሞት ገበሬ ነው በእውነት፣

እሰው ቤት ኗሪ ስዋትት፣

ያስደንቀኛል በተግባሩ፣

አፈር አርሶ መኖሩ።

አንተ የአውድማ ቀራተኛ፣

ተጠንቀቅና ነቅተህ ተኛ፣


ታስወድሳለህ ምርትህን፣

ያፍሰዋለና አትመን።

አባት ልጁን ተጣልቶት፣

በጣም አዝኖ ረግሞት፣

ይታረቀዋል አሁን፣

እረግሞት አይቀርም።

እዚያ ላይ ሆኖ ቢጠራኝ፣

ወይ እንዳልለው ድምጥ የለኝ፣

ባልሰማ እንጅ ነው ዝምታዬ፣

አቤት!አቤት!ጌታዬ።

ያባቴን አገር ደጋውን፣

አስከልክየው ነበር ሣሩን፣

አበሉኝ አሉኝ ዘመዶቼ፣

እርሻ ማረጌን ትቼ።

አምና ኩዳዴን መኰደድ፣

አክፍሎት አለ በግድ፣

የሰው ሁሉ መጎጃው

በማማት እንጂ ነው።

የእየሩሣሌም ነጋዴ፣

ጣለበት አሉ ወንበዴ፣

ለገንዘቡማ ማን አዘነ፣
አወይ ነፍሱን ያዳነ።

ያደኩባትን መሬት፣

ማነው ደጋ ናት ያለት፣

ልናገር እኔ የማውቃት፣

አገሬ ጋራ ናት።

እኔን ፍረድ ቢሉኝ ሞት በደለኛ ነው፣

አንድ ሰው ለምስል ቆሞ በቀር ምነው!

ጆሮዬ እየሰማ እያየሁት ባይኔ፣

ሣቅ ነው የገደለኝ መች አጣሁት እኔ።

በጣም አደነቅሁ ስትሠራው ባይ፣

ለካስ ይህ ገላችን አፈር ኖሯል ወይ?

ስማኝ ልንገርህ አትስነፍ፣

ተው እየሠራህ እለፍ።

አታላይ ከታች ሲሉት ከላይ።

የሴት አገርዋ ባልዋ።

እህል ከበዩ ሰው ከገዳዩ።

ገብስ የእህል ንጉሥ።


%

የጦጣ ዘር አቀባይ የዝንጀሮ ጎልጓይ።

አህያ እንደምትታለብ፣

ከላሞች ፊት ትቅለበለብ።

ከተመቱ ማንጠርጠር፣

ጅብ ከሄደ ማጠር።

ቅን በቅን ከማገልገል

ፊት ለፊት ማውደልደው።

በሰም የተጣበቀ ጥርስ፣

ቢበሉበት አያደቅ፣

ቢስቁበት አያደምቅ።

ክረምቱን የፈጀ በጋ፣

ዕዳውን የፈጀ ዜጋ።

የውኃ ውኃ፣

ምን አለኝ ቀሐ!?

ሰው እንደነገሩት፣

በቅሎ እንዳሰሩት።

ወርቁን በሚዛን፣
እህሉን በላዳን።

በነፋስ አውታር ወጥሮ፣

በእሳት ዛንጅር አስሮ።

በጦር አንደበት፣

በፈረስ አንገት።

ነፍጥ ቢያጓር፣

የጌታውን ጎድን ይሠብር።

የወደዱትን ሲያጡ፣

የጠሉትን ቀላውጡ።

አንተ ግፋኝና፣

እኔ ስጋ ላይ እወድቃለሁ።

ወድደህ ከተደፋይ፣

ቢረግጡህ አይክፋህ።

ወድደው የዋጡት ቅልጥም፣

ከብርንዶ ይጥም።

ምላጮች ቢያብጡ፣

በምን ይበጡ!?

%
ብለው ግዛኝ ግዛኝ፣

ሊሸጠኝ አስማማኝ።

ቀን በበቅሎ፣

ማታ በቆሎ።

ብረት ካልፈላ፣

አይሳሳ።

ከመቃለል፣

መጠቃለል።

ገንፎ እፍ እፍ ቢሉህ፣

ሊውጡህ!

ሀሰተኛ በቃሉ፤

ስደተኛ በቅሉ።

ሀሰተኛን ሲረቱ፤

በወንድሙ በእህቱ።

ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ አትሞትም።

ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣም።

ሁለት ባላ ትከል አንዱ ሲነቀል ባንዱ ተንጠልጠል።


%

ሁለት ቁና ሰጥቼ አንድ ጥንቅል።

ኃጢያት በንስሀ

በደል በካሳ።

ሄዳ ጉበት ይነሷታል፤

ታናሽ ታላቅ ስደዱልኝ አለች።

ሕመሙን የሸሸገ መድኃኒት የለውም።

ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው።

ሆድ ባዶ ይጠላል።

ሆድን በጐመን ቢደልሉት፤

ጉልበት በዳገት ይለግማል።

ሆድና ግንባር አይሸሸግም።

ሆዱን ያለ፤

ሆዱን ተወጋ።

ሆዳም ቢሸከም የበላ ይመስለዋል።

ሆዳም ሰው ፍቅር አያቅም።


%

ለወሬ የለው ፍሬ፤

ለአበባ የለው ገለባ።

ለቸኰለ ዋንጫ አስጨብጠው።

ለስሟ መጥሪያ ቁና ሰፋች።

ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው።

ለወዳጅና ለዓይን ትንሽ ይበቃዋል።

ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝለታል።

ለሞኝ ሰኔ በጋው፤

መስከረም ክረምቱ።

ለፈሪ ሜዳ አይነሱም።

ለሰባቂ ጆሮህን አትስጠው።

ለሰው ሞት አነሰው።

ለእብለት ስር የለው፤

ለእባብ እግር የለው።

%
ለብልህ አይነግሩም፤

ለአንበሳ አይመትሩም።

ለሞኝ ንገረው ምን ይስማ ብዬ፤

ለብልህ ንገረው ምን ይስተው ብዬ።

ለምሽት መብራት፤

ለመከራ ጊዜ ብልሃት።

ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ።

ለላም ቀንዷ አይከብዳትም።

ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ።

ለእግሩ የተጸየፈ ለቂጡ አስተረፈ።

ለእጅ ርቆ ለዓይን ጠልቆ።

ለሂያጅ የለውም ወዳጅ።

ለሰው ብትል ትጠፋለህ፤

ለእግዚአብሔር ብትል ትለማለህ።

ለቁንጫ ለምድ ያወጣል።

%
ለውጠኝ ባይ የሚሻለውን አውቆ።

ለዳኛ አመልክት እንዲሆን መሠረት።

ለደህና ሰው ውሸት ለጅብ እሸት።

ለንጉሥ ያልረዳ ከባሕር ያልቀዳ።

ለሆዴ ጠግቤ፤

ለልብሴ አንግቤ።

ለፈሪና ለንፉግ እያደር ይቆጨዋል።

ለጋስ ቢለግስ አበደረ እንጂ አይሰጥም።

ለዳባ ለባሻ ነገርህን አታበላሽ።

ለቀሊል ምስጢር በቀዳዳ አቆማዳ ጤፍ መቋጠር።

ለራስ ምታት ጩህበት፤

ለሆድ ቁርጠት ብላበት።

ለስሶ ፍትፍት አሣይቶ እበት ያጐርሷል።

ለውሽማ ሞት ፊት አይነጭለትም።

%
ለሴት ጠላ ለፈረስ ቆላ አይረባውም።

ለደህና ሰው ዋጋ አነሰው።

ሊያስቡት አይገድም።

ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው ፈጃት፤

እንዳትተወው ልጅዋ ሆነባት።

ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም።

ላፈ ግም አፍንጫ ድፍን ያዝለታል።

ላህያ ማር አይጥማትም።

ላም አለኝ በሰማይ ወተቷምን አላይ።

ላሊበላ አደራውን አይበላ።

ላም ነጂዋን እንጂ ጌታዋን አታውቅም።

ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ።

ላም ሲበዘበዝ ጭራዋን ያዝ።

ላይመራው አማሰነው።
%

ላይበላው አበላሸው።

ላንድ ብርቱ፤

ሁለት መድኃኒቱ።

ላምሳ ጋን አንድ አሎሎ ይበቃል።

ላይኛው ከንፈር ለክርክር፤

ታችኛው ከንፈር ለምስክር።

ላላወቀ ፎገራ ዱሩ ነው።

ላይሆን ዘመድ ገንዘቤን አልሰድ።

ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል።

ሌባ ቢያዩኝ እስቅ ባያዩኝ እሰርቅ ይላል።

ሌባውን ሌባ ሲሰርቀው እንዴት ይደንቀው።

ልጅ ካርጣጣ እህል ከዘበጣ።

ልጅ ያለናት፤

ቤት ያለጉልላት።

%
ልጅ በጡት፤

እህል በጥቅምት።

ልጅና ጥሬ አይተጣጣም።

ልጅ ያለ፤

ልጅ አከለ።

ልጅና ጦጣ ውሀ ይጠጣ።

ልጅ አይወልድ፤

እውነት አይፈርድ።

ልፋ ያለው በህልሙ ዳውላ ይሸከማል።

ልጡ የተራሰ መቃብሩ የተማሰ።

ልብ ካዘነ እንባ አይቸግርም።

ልብ ሳይዙ ነገር አያብዙ።

ሎሚና ትርንጐ ሞልቶ በአገልግልህ፤

እንቧይ ታሸታለህ የድኃ ነገርህ።

ሎሌና አሞሌ ካዘዙት ይውላል።

%
መልካም ወጥ እጅ ያስመጥጥ።

መጓጓት ያከሣል።

መሮጥ ሲበዛ ልብ ያፈርሣል።

መነዛነዝ ያመጣል መዘዝ።

መንገድ ከሀገር ልጅ፤

ስደት ከሹም ልጅ።

መሬት ሲያረጅ መጭ ያበቅላል።

መሰስ ሲል ምን ደስ ይል።

መሣሣል የጋራ ነው።

መቼ መጣሽ ሙሽራ፤

መቼ ቆረጠምሽ ሽንብራ።

መብረቅ የመታውን ወዘት አስተኛው።

መንገድ ሳለ በዱር፤

በቅሎ ሳለ በእግር።

መሬት በድንበር፤
ውበት በከንፈር።

መካር የሌለው ንጉስ፤

ያላንድ ዓመት አይነግስ።

ሚዳቋ ዘላ ዘላ ተምድር።

ማን ሊስምሽ፤

ታሞጠሙጫለች።

ማን ይንገር የነበረ፤

ማን ያርዳ የቀበረ።

ማን ያውቅ አገር፤

ማን ያጠብቅ ማገር።

ማቅ ያሞቃል፤

ሻሽ ይደምቃል።

ማጣትና ማግኘት ጆሮ ለጆሮ።

ማፈር ከሌለ ክብር የለ።

ማተብና አንገት፤

ክታብና ደረት።

%
ማሩን አምርሮ፤

ወተቱን አጥቁሮ።

ማረገ ቢስ፤

ራቱ ገሚስ።

ማሽላ ለማሽላ፤

ተያይዞ ቆላ።

ሜዳ መራመድ ሣታውቅ፤

መሰላል መውጣት ማን አስተማራት።

ምን ቢያርሱ፤

እንደጐመን አይጐርሱ።

ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ።

ምንም ቢከፋ ዘመድ፤

ምንም ቢጠም መንገድ።

ምንም ብታውቅ ከዳኛ ጋራ አትሟገት።

ምንም ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ።

ምን በእግሩ እየመጣ፤

በእጁ እንዳይመጣ።
%

ምን ቢነግሡ በእጅ አይካሱ።

ምን ያምጣ ድኃ፤

ምን ያግሣ ውሀ።

ምን ያስጠምዱ በዘጠና፤

ቤቱ አይተነ ቀጠና።

ምድር በአለቃ፤

ሰማይ በጨረቃ።

ምላጭን ምላጭ አይቆርጠውም።

ምንጃር ጤፍ ተወቃ ቢሉት፤

ሽንኰራ ሆኖ ዓይኔ ውስጥ እብቅ ገባ አለ።

ምጥ ለእናቷ አስተማረች።

ምርት ከአላባ፤

ግዳይ ለሰለባ።

ምሳሌ ሁሉ አንካሣ ነው።

ምስለኔ ሁን እንደኔ።

%
ምስክር ከተጠራ፤

መስዋዕት ከተሠራ።

ምቀኛ ጠላቱን ይተክል፤

ራሱን ይነቅል።

ምስክር ቢያድር ይለወጣል፤

ሽንፍላ ቢያድር ይመለጣል።

ምናልባት ቢሰበር አናት።

ምድር ሲደላደል፤

መሣ ሲታደል።

ምስር መዝራት ሙያ ማጣት አለ ጦጣ።

ምከረው ምከረው፤

እንቢ ካለ መከራ ይምከረው።

ሞት በአቤል ተስካር በሮቤል።

ሞኝ ሞኝ አያውቁብኝ ባይ።

ሞት ላይቀር ፍራት፤

አመል ላይቀር ቅጣት።

%
ሞት ሲደርስ ቄስ፤

ጦር ሲደርስ ፈረሰ።

ሞኝ የተከለው፤

ልባዊ አይነቅለው።

ሞኝና ውሀ፤

እንደወሰዱት ይሄዳል።

ሞኝ ቢቃጡበት የመቱት ይመስለዋል።

ሞኝ ሲናገር ብልህ ያደምጣል።

ሞኝ ካመረረ፤

በግ ከበረረ፤

መመለሻ የለውም።

ረጅሙን ባላማ፤

አጭሩን በጫማ።

ሩቅ አሳቢ፤

ቅርብ አዳሪ።

ሩቅ አገር ለውሸት ይመቻል።

ራስ ሳይጠና ጉተና።
%

ራስ ተላጭቶ ወለባ፤

ልባልባ ታጥቆ አዛባ።

ሮቃ የዝሆን አለቃ፤

ለምሣር አትበቃ።

ሠርቆ ከማሰብ፤

እጅን መሰብሰብ።

ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ።

ሰው ያመነ ውሀ የዘገነ።

ሰይጣን ለወዳጁ ድርብ ነው።

ሰምቶ ዝም፤

አይቶ ዝም።

ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል።

ሲምር ያስተምር።

ሲሸኝ ጢስ ወጋኝ።

ሲያጌጡ ይመላለጡ።
%

ሲያጣ እጅ ላፍ ይጠናል።

ሲስሟት ቀርታ ሲስቧት።

ሲበሉ የላኩት።

ሲያብል የተኛ ሲጠሩት አይሰማ።

ሲዋጥ በመረቅ።

ሲቀላውጡ ዓይን አፍጦ፤

ሲቆፍሩ አንፈራጦ።

ሲያልቅ አያምር።

ሲበላ ለሚከሣ፤

ሲመክሩት ለሚረሣ፤

ለዛ እህል ንሣ፤

ለዚያም ምክር ንሣ።

ሲያረጁ አምባር ይዋጁ።

ሲሱ ሲበላ ይታነቃል፤

ሐሰተኛ ሲናገር ይታወቃል።

%
ሲወርዱ ይዋረዱ።

ሲታጠቡ እስከ ክንድ፤

ሲታረቁ እስከ ሆድ።

ሲበዛ ሲበዛ ይገነፍላል።

ሲፈሩ አይከሱ፤

በቁጣ አያይሱ።

ሲሞቱ ገመድ፤

ሲገዙ ዘመድ አይታጣም።

ሲያይ የገባን ሲሰማ ቅብረው።

ሳትዋጋ ንገሥ ቢሉት ሳልዋጋ አልነግሥም አለ።

ሳይከካ ተቦካ።

ሳይርቅ በቅርቡ፤

ሳይደርቅ በእርጥቡ።

ሳይረቱ አይበረቱ።

ሳይተርፋት አበደረች፤

ሳትበቅል ሞተች።
%

ሳትቸገር ተበደረች፤

ሳትከፍል ሞተች።

ሳለቅስ ሳነባ ውል ሳሰማ፤

የሰጠኸኝ ሸማ በደጅህ ተቀማ።

ሳይቀደስ ያርዳል፤

ሳይታየው ይፈርዳል።

ሳይጠሩት አቤት፤

ሳይልኩት ወዴት።

ሳይሰበር ጥግን።

ሳይጣሉት የተጣላ፤

ሲርብ ያበላ አይረሳም።

ሳይገድሉ ጐፈሬ፤

ሳያስረግጡ ወሬ።

ሴት ያመጣው ጠብ አይበርድም።

ሴት ሲበዛ ጐመን ጠነዛ።

ሴት የወደደ ወደ ገሀነም እሳት ወረደ።


%

ሴትና ፈረስ ያቀረቡለትን ይቀምስ።

ሴትና ቄስ ቀስ።

ሴትና ዶሮ ሳያብድ አይውልም።

ስለጤሰ አይነድም፤

ስለዳመነ አይዘንብም።

ስንቅህን ባህያ፤

አመልህን በጉያ።

ስንቅ ያለው ጦም አያድር፤

ዋስ ያለው አይታሠር።

ስለት ድጉሱን ደባ ራሱን።

ስሙን ጠርቶ ራሱን ቆርቶ።

ስለ ፍቅር በስመ አብ ይቅር አለ ሰይጣን።

ስንዴ በጭምቅ፤

ባለጌ በጥብቅ።

ስም ይወጣ ከቤት፤
ይቀበል ጐረቤት።

ስንቅና ማህሌት እንደ ያዢው ነው።

ስደት ለወሬ ይመቻል።

ስለከሰሱ አይፈወሱ።

ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው።

ሥጋ ቀረ፤

ዕዳ ቀረ።

ሥጋ ለጥጋብ፤

አጥንት ለትካዜ።

ሥጋ ቁጠር ቢሉት ጣፊያ አንድ አለ።

ሥጋ ያማረው መረቅ የሸተተው፤

በበጐች መካከል ዝግ ብሎ ይተኛል።

ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል።

ሥራ ያጣ ጢስ ይሞቃል።

ሸማ በየፈርጁ ይለብሳል።
%

ሺኚ እቤት አያገባም።

ሸማ ማዋስ ለባላገር፤

በቅሎ ማዋስ ለወታደር።

ሹም ቢሞት አምሳ፤

የሹም ልጅ ቢሞት መቶ ታምሳ።

ሹምና ጥጥ እያደር ይከዳል።

ሹመት በተርታ፣

ሥጋ በገበታ።

ሺ በመከር አንድ በወርወር።

ሽማግሌና ስልቻ ሳይሞሉ አይቆሙም።

ሽበት እኖር ብዬ መጥቻለሁ አለ።

ሾላ በድፍኑ።

ቀባሪ በፈጣሪ።

ቀጥኜ ቢያየኝ ጅማት ለመነኝ።

%
ቀርቀሬ ወርጄ ማር ስልስ ማር ልክፈል።

ቀድሞ ሰኞን አለመሆን ነው።

ቀስ በመቀስ።

ቀን በበቀሎ ማታ በቆሎ።

ቀለም ሲበጠበጥ ብዕር ሲቀረጥ።

ቀን እስኪያልፍ፤

ያባትህ ባርያ ይግዛህ።

ቀን እንደ ተራዳ፤

ሌሊት እንደ ግድግዳ።

ቀን ተጣለው ሁሉ ይጥለው።

ቀሊል አማት ሲሶ በትር አላት።

ቁም እንደ ሳማ ቁርጥ እንደ ጫማ።

ቁራ ስሙን ይጠራ።

ቂል ያገኘው ፈሊጥ፤

ውሻ ያየው ሊጥ።
%

ቂል ሲረግሙት የመረቁት ይመስለዋል።

ቂል አይሙት እንዲያጫውት።

ቂም ቂም ያሰኝሽ እንደ ቄብ ዶሮ፤

ለመከራ ለአሣርሽ ኖሮ።

ቄስ ለኑዛዜ ፍቅር ለሚዜ።

ቅናት ጥናት አያገናኝ ከእናት ከአባት።

ቅቤ ይፍሰስ ከገንፎ አይለፍ።

በቅሎ ማሠሪያዋን በጠሰች ቢለው አሳጠረች አለ።

በጥባጭ ካለ ጥሩ አይጠጣም።

በሰማኒያ የተረታ ማህል አገዳውን የተመታ።

በዝሆን አፍ ቅርፊት።

በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት።

በባዳ ቢቆጡ በጨለማ ቢያፈጡ ምን ያመጡ።

%
በእጅ የያዙት ወርቅ ስለመዳብ አንድ ነው።

በቡሐ ላይ ቆረቆር።

በቃል ያለ ይረሣል፤

በመጽሐፍ ያለ ይወረሣል።

በካሣ የከበረ በአጓት ሰከረ።

በልጅ አመካኝቶ ይበላል አንጐቶ።

በሰበቡ መምሬ ተሳቡ።

በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ።

በየወንዙ ሃሌ።

በማያድሩበት ቤት አያምሻሹበት።

በበትሩ አይመታ፤

በዘመዱ አይረታ።

በፈረስ የፈለጉት በእግር ይገኛል።

በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ።

%
በትር ለገና ነገር ለዋና።

በሰም የተጣበቀ ጥርስ፤

ቢስቁበት አያደምቅ፤

ቢበሉት አያደምቅ።

በሁለት በትር አይማቱ፤

በሁለት ዳኛ አይሟገቱ።

በእለቱ ይወርዳል መዓቱ።

በቅሎ እንደ አሰጋገሩ፤

ሎሌ እንደ ነገሩ።

በምድር መጠቅጠቅ በሰማይ መጠየቅ።

በዋስ ያለ ከብት በጣት ያለ ቀለበት።

በሬ ተሽካሽኰ ከቀንበር፤

ገበሬ ተሸካኝኮ ከድንበር።

በጦም ቆሎ ፤

በዳገት በቅሎ፤

ቆሎም ይከካል፤

በቅሎውም ይነካል።

%
በውል ከሄደች በቅሎዬ፤

ያለ ውል የተበላች ቆሎዬ።

በርበሬ በገዛ እጅ ገዝቶ ይፈጃል።

በሰለ እንብላ ደረሰ እንዝራ።

በቅሎ ግዙ ግዙ አንድ ጨው ሊያግዙ።

በግ ባልበላሽ ትበይኝ አለ ጅብ።

በውሌ ደጃዝማች ባሌ።

በለፈለፉ ባፍ ይጠፉ።

በሰፈሩበት ቁና መሰፈር አይቀርም።

በምድር ብሠራ እባቡ መከራ፤

በዛፍ ብሠራ እረኛው መከራ፤

በሰማይ ብሠራ አሞራው መከራ፤

የት ውዬ ዬት ልደር ጌታዬ።

በሐምሌ ወጨፎ በሰኔ እርክፍካፎ።

በልቼ እንደ እንሰሳ ተኝቼ እንደሬሳ።

%
በሰው ቁስል እንጨት ቀርቅርበት።

በቂል ክምር ዝንጀሮ ይማታበታል።

በለምለም መላሴ ኰሸሽላ በላሁበት አለ አህያ።

በሴትና በውሃ የማይደርስ የለም።

በቤት ዘመድ ገናዥ በቄስ ናዛዥ።

በዓል ሽሮ የከበረ ጦም፤

ገድፎ የወፈረ የለም።

በገዛ ራሱ እባብ ጠመጠመ።

በጋለሞታ ቤት ሁሉ ይጣላበታል።

በበላህ ገብር በሰማህ መስክር።

በከብቱ የለገሠ በወለዱ የገሰሠ።

በእውር ይጠቃቀሷል፤

በደንቆሮ ይሾካሾኳል።

በጨው ደንደስ በርበሬ ይወደስ።

%
በሰው ምድር ልጅዋን ትድር።

በደል ዋና አጥታ ትኖራለች።

በወንድሜ ግንባር ደም አልይበት።

በሰኔ ካልዘሩ፤

በጥቅምት ካልለቀሙ፤

እህል የት ይገኛል በድንበር ቢቆሙ።

በዘጠና የለም ጤና።

በዝሆን ጆሮ ትንኝ።

በሰማይ የለም ጸጸት፤

በአባት የለም ቅጣት።

በቅሎ ማን አባትህ ቢሉት ፈረስ አጐቴ አለ።

በፋሲካ የተገዛች ባሪያ፤

ሁል ጊዜ ፋሲካ ይመስላታል።

በሰው ቡሃቃ ያቦካ፤

አሟጦ አይጋግርም።

ቢተኙ ነገር ያገኙ፤


ቢነሱ ነገር ይረሱ።

ቢሰጡኝ እነዳ፤

ቢነሱኝ እረዳ።

ቢጠረጥሩ፤

ጠጠር ይጥሉ።

ቢያብዱም ቢሞቱም፤

የአንዱን ነገር አያጫውቱም።

ባሪያ ቢያግዟት መጁን ደበቀች።

ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም።

ባይቸኩሉ እንቍላል ይሄዳል በእግሩ።

ባልፈሱበት ቂጥ አያፍሩበት።

ባንዱ ታዘብ፤

ባንዱ ተለዘብ።

ባልንጀራው ቢያጠቃው ወደ ሚስቱ ሮጠ።

ባለቤቱን ካልናቁ ውሻውን አይመቱ።

%
ባእድ ስር የለውም።

ባልነቃ ሰንጥቆ፤

ባልነበረ በርቆ።

ባለጌና ቆቅ በራሱ ያወራ።

ባልንጀራህ ሲታማ፤

የኔ ብለህ ስማ።

ባወጡት ዳኛ ቢረቱ፤

በቆረጡት በትር ቢመቱ።

ባልፈጠጥሽ በኖብሽ፤

ባልነበርሽ በርቆብሽ።

ባሪያ ቅቤ ወዶ፤

ማን ሊሸከም ነዶ።

ባቄላ ሣይሰበር መነኩሴ ሳይቀበር።

ባዳና ጨለማ አንድ ነው።

ባዋቂ ፊት መናገር መታገም።

ባመጣኸው ዳኛ፤
ትሆን አሣርኛ።

ባለቤት ያከበረው አህያ በቅሎ ይለውጣል።

ባፄ ይሙቱ የተከተረ፤

በስለት የተመተረ።

ባለቤቱ ካልጮኸ ጐረቤት አይረዳም።

ባለጌ የተመከረለት፤

ቁንጫ የተጠረገለት።

ባንድ ከፈጩ የለም እመቤት።

በፈሳ ይታፈሳል፤

በነጠር ይመለሳል።

ባገባቡ በደጃፉ ይገቡ።

ባለቤት ሲያፍር እንግዳ ይጋብዛል።

ባንድ ዙፋን ሁለት ንጉስ፤

ባንይ አፍ ሁለት መላስ።

ባላደራ ጮኸ በተራራ።

%
ባስተጋባ ከባሕር ሆዴ ገባ።

ቤት ያለሴት ከብት ያለበረት።

ቤተ ክርስቲያን ለማላጅ ገበያ ላርፋጅ።

ቤት ያለ አጥር ሰው ያለልብስ።

ቤት ከነጉልላቱ፤

ምድጃ ከነማዘንቱ።

ብልጥ ለብልጥ፤

ዓይን ብልጥጥ።

ብልጥ ዓይን አስቀድሞ ያለቅሳል።

ብርሌ ከነቃ፤

አይሆንም እቃ።

ብነጨው ፊቴን፤

ብመታው ደረቴን።

ብሎ ብሎ የዶሮ አንገት በምሣር።

ብርቅና ድንቅ፤

አለ ሳምንት አይደምቅ።
%

ተኩላ አንድ አንበሳ እጮኽ ብላ ተተረተረች።

ተሸፍኖ ቢተኙ ገልጦ የሚያወጣ ጌታ አለ።

ተቀምጦ የሰቀሉት ቆሞ ለማውረድ ይቸግራል።

ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ።

ተባለ ቀትር፣አትቀታተር።

ተናዞ ይሞቷል አሰይዞ ይሟገቷል።

ተናገር በከንፈሬ፤

ተቀመጥ በወንበሬ።

ተው ፈረሴን ለጉም ፤

አይዘነጉም ለሴትና ለጉም።

ተጦረኛ ሰው ስንቅ አይደባልቁም።

ተግደርዳሪ ጦም አዳሪ።

ተንጋሎ ቢተፉ ተመልሶ ካፉ።

ተዋጊ በሬህን ተናካሽ ውሻህን።


%

ተመመርመር ይገኛል ነገር።

ታከረሩት ይበጠሳል።

ታሞ የተነሣ እግዚአብሔርን ረሳ።

ትንሽ ቆሎ ይዞ ከአሻሮ ትጠጋ።

ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት።

ነገር በመልከኛ ጠላ በመክደኛ።

ነገር በዋስ፤

እህል በነፋስ።

ነገር በእርቅ፤

መንገድ በደረቅ።

ነገር አዳምጦ፤

እህል አላምጦ።

ነገር ሲጀመር፤

እህል ሲከመር።

ነገር ካወቂ፤
ብረት ከጠራቂ።

ነገር ካንሺው፤

ሥጋ ከጠባሺው።

ነገር ከግቡ፤

ጋሻ ከንግቡ።

ነገር ተሥሩ፤

ውሃ ከጥሩ።

ነገር ለበለጥ፤

ውድማ ለመለጥ።

ነገር ሲበዛ በአህያ አይጫንም።

ነገር በትኩሱ ጫዋታ በወዙ።

ነገር ከዋስ መላስ ከጥርስ።

ነገረኛ ሰው በቤቱ አይሞትም።

ነብር የሞተለት ፍየል ልጅዋን ትድራለች።

ነቢይ ባገሩ አይከበርም።

%
ነብር ሳይገድል ቆዳውን ይስማማል።

ነፋስ በተነሣ ጊዜ እሳት አይጭሩም።

ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል።

ኑሮ በዜዴ፤ አቶ ዘወልዴ።

ናዳ መጣልህ ቢሉት ተከናንቤአለሁ ልቀቀው አለ።

ንጉሥ አይከሰስ፣

ሰማይ አይታረስ።

ንጉስ አንጋሹን፤

ቤተ ክርስቲያን ቀዳሹን።

ንጉሥ በግንቡ ይታማል።

አባት ያበጀው፤

ልጅ ይበጀው።

አዬ ጉድን አታበላሽ፤

ለባሰ ቀን ይሆናል።

አላርፍ ያለች ጣት፤

አር ጠንቁላ መጣች።
%

አዋቂ ሲበዛ በሽተኛ ይሞታል።

አወቅሺ አወቅሺ ብሏት፤

የባሏን መጽሐፍ አጠበች።

አይነጋ መስሏት እቋት አራች።

አያ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ።

አንድ ጣት በቆማጣ ቤት ብርቅ ናት።

አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ።

አንድ አንድ ጊዜም በዋልድባ ይዘፈናል።

አንድ ቀን ቢስቱ ዓመት ይፀፀቱ።

አንድ ምስክር አያስደነግጥ፤

አንድ ዓይን አያስረግጥ።

አንድ ሲሻር፤

አንድ ይሾማል።

አንድ ሲናገር ሁሉ ይሰማል፤

ሁሉ ቢናገር ማን ይሰማል?
%

አንድ ወናፍ ሁለት አፍ።

አንደኛ ልብ አንድድ፤

ሁለተኛ ልብ አብርድ፤

ሶስተኛ ነገር ቀስቅስ፤

አራተኛ ጐራዴ መምዘዝ።

አንድ ዓመት በወዝ፤

አንድ ዓመት በደመወዝ።

አንዳይና በጎ ሄደች፤

በአንድ ዓይኗ እንቅልፏን ትፈጃለች፤

በአንድ ዓይኗ ጓዟን ትጠብቃለች።

አባት ካለ አጊጥ፤

ጀንበር ካለ ሩጥ።

አባይና ስንቅ እያደር ይቀላል።

አባቱን የጠላ የሰው አባት ይሰድባል።

አቦን አይጠምቅ፤

ፍልሰታን አይጥድ የለም።

አባይ ጠንቋይ ቤት ያስፈታል።


%

አባ ገምናኔ የለውም ቤትህ፤

ወረን ይላል ለመሸበትህ።

አብ ሲነካ፤

ወልድ ይነካ።

አለ አዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል።

አለዋንጫ አይስማት፤

አለቀንጠፋ አይስባት።

አለ እኩያ ጋብቻ ቆይ ብቻ።

አለ አባት ጐመን በጓት።

አለ አሽከር በቅሎ፤

አለ ወንድማማች አንባ ጓሮ።

አለ በለኝ ቀለቤን፤

ሞተ በለኝ ከፈኔን።

አለቃ ያውቃል፤

ድኃ ይጠይቃል።

አለ አንኰበር ሾላ ሜዳ አይገኝም።
%

አላ አንድ የላት ጥርስ በዘነዘና ትነቀስ።

አልቅትና ድኃ ውሀ ለውሀ።

አንበሳ ምን ይበላል ተበድሮ፤

ምን ይከፍላል ማን ተናግሮ?።

አንበሳ ሲያረጅ የዝምብ መጫወቻ ይሆናል።

አንበሳ የሰበረው፤

ንጉሥ የገደለው አንድ ነው።

አንበሳ የሰበረው ለጅብ ይተርፋል።

አንተም ሌባ እኔም ሌባ።

ምን ያጣላናል በሰው ገለባ።

አንገት ለምን ተፈጠረ አዙሮ ለማየት።

አህያ በሞተች በዓመቱ ᎐ር ᎐ር።

አህያ ለሰርዶ፤

ሰው ለመርዶ።

አህያ አታመኻብኝ ትበላኝ እንደሆነ እንድያው ብላኝ።


%

አህያ ጅብ፤ ለቅሶ ሄደች።

አህያውን ቢፈሩ ዳውላውን መቱ።

አህያም እንዳባቱ ይፈርጥጥ።

አህያ ላህያ ቢራገግ ጥርስ አይሳበር።

አህያና ጓያ በምስያ።

አህያ የለኝም ተጅብ አልጣላም።

አገር ላጣ ስሜን ምግብ ላጣ ጐመን።

አገር ጥሎ፤

ቁርበት ጠቅሎ።

አገር የሌለው ለጌታ አዳሪ፣

ማጭድ የሌለው ወራሪ።

አገርህ ወዴት ነው፤

ማርያም ውሀ፤

ዘመዴ ነሀ።

አገር አላት ይበሉኝ፤


መንደረ ማርያም ቅበሩኝ።

አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ፤

ተባልሽ ሆድ አትባባሽ።

አግኝቶ ከመዋረድ አጥቶ መ᎐ራት።

አፍ ሲያመልጥ ራስ ሲመለጥ አይታወቅም።

አፍና ቅብቅብ ሁል ጊዜ አያበላም።

አፍ ሲያርፍ ወዳጁን ያማል።

አፍ ያለው ጤፍ ይቆላል።

አፈኛ በአፉ፤

ኃይለኛ በመዳፉ።

አፍ ሲከዳ ከሎሌ ይብሳል።

አፉ ከኛ ልቡ ከወሬኛ።

አፍና እጅ፤

እጅና ፍንጅ።

አፍንጫን ቢመቱት ዓይን ያለቅሳል።


%

አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ።

አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች።

አይጠቅም ጠላ፤ ባልና ሚስት ያጥላ።

አይሆንም እንጂ ከሆነማ ከመጋዞ ምድር ይሻላል ጉልማ።

አይጽፍ ደብተራ ክንፍ የሌለው አሞራ።

አይበላ ዳኛ በእግት ይመረር።

አይቶ አጣ ቤት ጐመን የተቀቀለ ለት ሲያጨበጭብ ሲጨፍር ያድራል።

አይቡ ዳኛ ቅቤው መልከኛ።

አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን በያዝሽ።

አያጥብ ለባሽ አይረታ ከሳሽ አያርም አራሽ።

አያድን አገሬ ጐድን ያሰብር።

አጤ ከሞቱ በማን ይሟገቱ።

አጤን ይሻል ቀላጤ።

%
አጥብቆ ጠያቂ የናቱን ሞት ይረዳል።

አጥብቀህ ጐርሰህ ወደ ዘመድህ ዙር።

አመል ያሰወጣል ከማህል።

አካሄዱን አይቶ ጭብጦውን ቀማው።

አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል።

አርጂ ጥኑ ነው።

አዛኝ ቅቤ አንጓች።

አረምን መንቀል ስር ሳይሰድ ነው።

አማችና ጋሻ ካልሰጐዱት አይሆንም።

አሞራውም በረረ ቅሉም ተሰበረ።

አመስጋኝ አማሳኝ።

አዋጅ ቢነግሩ ልዩ ነው ምክሩ።

አስፍቶ ከማረስ ከተቀላቢው ማሳነስ።

%
አስቀድሞ ማመስገን ለማማት ይቸግራል።

አታበድር እንዳትቸገር።

አካል የወለደው፤

ዘመድ የወደደው።

አዎን ማለት መረታት፤

አለመመከት መመታት።

አዎን ባይ እንደከፋይ፤

አሌ ባይ ሞት ተቀባይ።

አዘዞ አንድም ተናዞ፤

አንድም ስንቅ ይዞ።

አደባባይ አይወድም አባይ።

አዳኝ ውሻ ጠጉር በአፏ በትር ትርፏ።

አደንጓሬ የእህል አውሬ።

አታላይ ከላይ ሲሉት ከታች ይላል።

አማች የበላው እሳት የበላው።

%
አተር መዝራት አቦ ብልሃት።

አማቻችን አፈኛ ቢመለስ ወደኛ፤

ወይ እኛ እንሆን አሣርኛ።

አውቆ መተው፤

ነገሬን ከተተው።

አሰት ቢናገሩ ውቃቤ ይርቃል።

አትረፊ ያላት ወፍ በጥቅምት ትሞታለች።

አትግደርደሪ ጦምሽን እንዳታድሪ።

አሞራ ሲበሉ ስሙን ጅግራ ይሉ።

አደራ ቢሏቸው ይብሳሉ እሳቸው።

እንስራውን ጥላ ውሀ ወረደች።

እንዶድ በገርነቷ ውሀ ወሰዳት።

እንዳያማህ ጥራው፤

እንዳይበላ ግፋው።

እንደ ንጉሱ አጐንብሱ።


%

እንኳን ዘንቦብሽ፤

እንዲያውም ጤዛ ነሽ።

እንኳን ለቤቱ፤

ያተርፋል ለጐረበቱ።

እንደመረብ ሸፍኖ፤

እንደ እንቁላል ደፍኖ።

እንጀራ ከባእድ፤

መከራ ከዘመድ።

እንደ ልጅ በቀለበት፤

እንደ ድመት በወተት።

እንዳትበላ ለጐሟት፤

እንዳትሄድ ቀየዷት።

እንደቆጫት ተነስታ የሰው ልቅሶ አጠፋች።

እንደ አገሩ ይኖሩ እንደ ወንዙ ይሻገሩ።

እንደ ሰው ትመጪ፤

እንደ አውሬ ትሮጪ።

%
እንግዳ ፊት ወርቅ ኋላ ብር ኋላ ብረት።

እንጣጥ እንደ ፌቆ፤

ሙልጭ እንደ ሰብቆ።

እንጨት ካልነሱት እሳት አይጠፋም።

እንደ ውሀ ይፍሰስ፤

እንደ ጋጃ ይፈስ።

እንግዳና ሞት በድንገት ይመጣል።

እንኳን ያበሉት ገርፈው ሰደዱት።

እንዲያው ብትመለሺ፤

የገንፎ እንጨት ላሺ።

እንግዳ ደራሽ ውሀ ፈሳሽ።

እኔ እበላው ሳጣ፤

ልጄ ጥርስ አወጣ።

እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል።

እኔ የምሞት ዛሬ ማታ፤

እህል የሚደርሰው በፍልሰታ።


%

እኔ ልብላ አንተ ጦም እደር።

እባብ ግደል ከነበትሩ ገደል።

እባብ የልቡን አይቶ እግር ነሣው።

እባብ ያየ በሊጥ በረየ።

እብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል።

እብድ የያዘው መልክ አይበረክትም።

እሳትና ድኃ ሲነካኩት አይወድም።

እሳት የገባ ቅቤ።

እሳት ታየው ምን ለየው።

እሳት መጣብህ ቢሉት፤

እሣር ውስጥ ገብቻለሁ አለ።

እሳት ቢዳፈን የጠፋ ይመስላል፤

ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል።

እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጐበኘው።


%

እሳት ተበረበረው ሴት የበረበረው።

እሰር በፍንጅ ጣል በደጅ።

እሱ በእሱ ሥጋ በኩበት ጠበሱ።

እህል ላበደረ አፈር፤

ወርቅ ላበደረ ጠጠር።

እህል ሲጠፋ ወፍጮ ይሳላል፤

እህል ሲገኝ ወፍጦ ይደንዛል።

እህል ሲያጡ የእናት ልጅ ይጡ።

እህል ከበዩ፤

ሰው ከገዳዩ።

እርሟን ብታፈላ፤

አንድ ቁና አተላ።

እርቅ ቢፈርስ ከአስታራቂ ድረስ።

እርቅ ከወርቅ ዛላ ከምርቅ።

እርጥብ ሬሳ ደረቁን አስነሳ።


%

እርሻ ሲሉ ሞፈር ቁረጡ።

እርሾው ሲያምር ደቦው ያምር።

እርሷ ሰንፋ እራቷን ገንፎ አድርጋ ቢያጐርሷት ተኰሳት።

እራት የሌለው ቄስ ከልብ አይቀድስ።

እራት የሌላት ምሳ አማራት።

እራትና መብራት አማትና ምራት ሳይስማሙ መሬት።

እጅና አፍ አይተጣጡም።

እጅና ጭራ፤

አፍና እንጀራ።

እጅ ሲነድ ልብ ይንደድ።

እጅ እየታጠቡት ያድፋል፤

ልጅ እየነገሩት ያጠፋል።

እጅግ ስለት፤ይቀዳል አፎት፤

እጅግ ብልሃት ያደርሳል ከሞት።

%
እጄ ተበትር፤

አፌ ከነገር።

እጄን በጄ ቆረጥሁት።

እሺ፤ ይበልጣል ከሺ።

እሺ ባይ አክባሪ፤

እምቢ ባይ አቅላይ።

እሾህ በእሾህ ይነቀላል፤

ገንዘብ በገንዘብ ይመለሳል።

እሾህ አጣሪውን፤

ነገር ፈጣሪውን።

እናቱ የሞተችበትና፤

ውሀ የወረደችበት እኩል ያለቅሳል።

እኛ በአገራችን፤

ዳቦ ፍሪዳችን።

እኖር ባይ ተጋዳይ።

እናቷን አይተህ ልጅዋን አግባ።

%
እራት ቢንቁ አንድ እጅ ይለቃልቁ፤

ዳኛ ቢንቁ የተያዘ እህል ይወቁ።

እየቆራረጣችሁ አንበሳ ሄደ ነብሩም ሞተላችሁ።

ኤግዚአብሔርን ከማይፈራ ወዳጅ፤

እግዚአብሔርን የሚፈራ ጠላት።

እግዚአብሔር የተቆጣው በዝናብ አር መጣው።

እግር ሄዳ ሄዳ ሰገራ ጉዳጓድ ትገባለች።

እግር ቢያሳስት ከእንጋዳ አፍ ቢያሳስት ከእዳ።

እግርን ለጠጠር ደረትን ለጦር።

እገድል ያለ መጋኛ እበላ ያለ ዳኛ።

እጭን ያለ ኰርቻውን፤

እለምን ያለ ስልቻውን።

እሄድ ባይ ስንቅ ፈጅ።

እካስ ያለ ታግሶ፤

እጸድቅ ያለ መንኩሶ።

%
እጸድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጣል ቀረች።

እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል።

እከክ የሰጠ ጌታ ጥፍርን አይነሳም።

እውሻ ሆድ ቅቤ አያድርም።

እውነትና ንጋት እያደር ይገለፃል።

እዛው ሞላ እዚያው ፈላ።

ከሺ በቅሎና አንድ ፈረሰኛ፤

ከሺ ነፍጠኛ አንድ መልከኛ።

ከሺ ገበና አንድ ቀጣፊ ልበኛ።

ከሺ ዋቢ እራሱ ቆራቢ።

ከሺ ደብተራ፤

የቄስ ደንካራ።

ከሺ ሎሌ፤

አንድ ወሬ።

ከመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል።


%

ከመሞት፤መሰንበት።

ከመታገል፤መታደል።

ከመልካም ጠላ ክፉ ጠጅ፤

ከመልካም ወዳጅ ክፉ ልጅ።

ከመንግሥት ልብ ያዛል።

ከመነኮሰች ባሰች፤

ከተተኰሰች አነከሰች።

ከመሀይምን ጐረምሳ የተማረ አሮጌ።

ከመንር᎐ሴ ቤት ስስት፤

ከሸማኔ ቤት ቁቲት።

ከመንታ የተንጠለጠለች ወፍ፤

ሁለት ክንፏን ትነደፍ።

ከመቶ አምሳ ዳዊት፤

የልብ ቅንነት።

ከመምሩ፤ ደቀ መዝሙሩ።

%
ከመጠምጠም፤ መማር ይቅደም።

ከሚስቱ ጋር የቆረበ ከእግዚአብሔር ተማከረ።

ከምድር አይሰጡም ስንዝር።

ከምሳ የተለየ ደብተራ፤ ያደርጋል ሴራ።

ከማይናገር ከብቱን፤

ከማይራገጥ ወተቱን።

ከሞተ አቴቴ፤ ምን አለኝ ካማቴ።

ከሞተ አንበሳ፤ ያለ እንስሳ።

ከሞተ ወዲያ ማልቀስ ደንጊያ መንከስ።

ከሞተ ደጃዝማች፤ የቆመ ባላምባራስ።

ከሞኝ ሸክም ሞፈር ቀንበር ይቆረጥለታል።

ከላይ ከደፈረሰ ከታች አይጠራም።

ከእናት አትሻል ሞግዚት።

ከእጅ አይሻል ዶማ።


%

ከሹም አይጣሉም፤ ከግንብ አይታገሉም።

ከሻሽ የተከሳሽን ልብ ቢያውቅ ከቤቱም አይነሳ።

ከክፉ ባለእዳ ጐመን ዘር ይቀበሏል።

ከተማረ የተመራመረ።

ከባዕድ እየጐረስክ ወደ ዘመድህ ዋጥ።

ከጅብ ጐሬ ሸሽቶ ጅብ ዋሻ።

ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ።

ከልጅ አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት።

ከጦጣ የዋለ ጉሬዛ።

ከወፈሩ፤ሰው አይፈሩ።

ከራስ፤በላይ ንፋስ።

ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ።

ከለማኝ ለማኝ ቆሮንጮዬን ቀማኝ።

%
ከድኃ ከመበደር ከባለ ፀጋ መለመን።

ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል።

ከቀኑ ያለፈ ሥጋ መግማቱ አይቀርም።

ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ይደናገር።

ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ።

ከጠላት መሳም የወዳጅ መግመጥ ይሻላል።

ከቤት ዶሮ ሲገኝ ከውጭ ቆቅ ይያዛል።

ከነገሩ ጦም እደሩ።

ከባለጌ ጡጫ ከዳገት ሩጫ።

ከጨርቅ ነጩ፤

ከባሀ ልጩ።

ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤

ከሰው መርጦ ለሹመት።

ከድስት አፍላል፤

ከቅመም ድንብላል።
%

ከእህል ክፉ አጃ፤

ከሳር ክፉ ሙጃ፤

ከነገር ክፉ አንጃ።

ከሩቅ ዘመድ፤

የቅርብ ጐረቤት።

ከጠጅ ወዲያ አስካሪ፤

ከባለቤት ወዲያ መስካሪ።

ከዚህ የወደቀ ሬሳ ማን ያንሳ።

ከታዳጊ ጌታ ስግድድ ያለ ቦታ።

ከሰጪው፤ አስጪው።

ከቤተ ቀሊል ቤተ ቆማጣ ይሻላል።

ከቅርብ የወደቀ ከቁስል ይድናል።

ከጌታህ አትፎካከር፤ ከውሻህ አትቀዳደም።

ከቁንጫ መላላጫ።

ከባለቤት ያወቀ ቡዳ ነው።


%

ከንጉስ ላይ ሰው አይፈርድ፤

ከባሕር ላይ እሳት አይነድ።

ከብልህ ያለ ሞኝነት ተራራ ያህላል።

ከሳልስተኛ ይሻላል ትናንትና።

ከሰው ክፉ ደባል፤

ከጭነት ክፉ አላል።

ከውርርድ ላይ ውርርድ፤

ከነብር ላይ ስማርድ።

ከዘር የሚሰጡት አለ፤

አውድማ የሚነፍጉት አለ።

ከእንጨት አጥር የሰው አጥር።

ከባለቤት የዋለ እንቁላል አይሰበርም።

ከብት ሰማይ ይከፍት።

ከከብት አይቶ ፍፉ ማግባት፤

ከብቱ ቢያልቅ ሁለት ጥፋት።

%
ከጐተት እስከ ሽበት፤

ከልጅነት እስከ እውቀት።

ከጨለማ ዱር ከጕድጓድ ምድር።

ከብት አይወድም ገደል፤

ሰው አይወደም በደል።

ከእግዚአብሔር ወዲያ ፈጣሪ፤

ከባሌቤት ወዲያ መስካሪ።

ከወገብ በላይ ታቦት፤

ከወገብ በታች ጣዖት።

ከፊት ተወጣ ጆሮ፤

በኋላ የወጣ ቀንድ በለጠው።

ከባቄላ አይጠፋም ዲቃላ።

ከተመቱ ማንጠርጠር፤

ጅብ ከወሰደ አጥር ማጠር።

ከገበያ ሄዶ ማንቀላፋት፤

በአፋፍ ላይ ሆኖ ማንጠራራት።

ከዲዳ ላም ንዳ።
%

ከብዙ ጉልብት ጥቂት ብልሃት።

ከጥላ ያረፈ ከሞት የተረፈ።

ከዓርብና ሮብ በፊት ይህም ይፁም፤

ክፋ ነገር ከአፍ አያወጡም።

ከፍትፍቱ፤ ፊቱ።

ከዓይን ማየት የልብ ዕውቀት።

ከወገኑ የተለየ አንበጣ፤

ይሆናል ፌንጣ።

ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ፤

አብረህ ተወቀጥ።

ከተዘጋ ቤቴ ከተዳፈነ እሳቴ።

ከጥንት እስከ አጥነት።

ካፍ ከወጣ አፋፍ።

ካነጋገር ይፈረዳል፤

ካያያዝ ይቀደዳል።
%

ካይጥ ቤት ብቅል፤

ከውሻ ቤት ጠፍር።

ካህያ የዋለች ጊደር፤

ፈስ ተምራ መጣች።

ካስር ብልኮ ግማሽ እንጀራ።

ካልጠገቡ አይዘሉ፤

ካልዘለሉ አይሰበሩ።

ካረጁ አይበጁ።

ካላዋቂ ቤት እንግዳ ይዋኝበታል።

ካልተገለባበጠ ያራል።

ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም።

ካረገዘች፤ክታብ ያዘች።

ካልታረደ አይታይ ሰባቱ፤

ካልተናገረ አይታይ ብልሃቱ።

ካፍ የወጣ ከጥርስ የነጣ።


%

ካላዩም አይነድ ካልሰሙም አይቆጭ።

ካጭር ምከር፤

ከረጅም ውረር።

ካፍ የወጣ ቃል፤

ከእጅ የወደቀ እንቁላል።

ካረጁ መንገድ፤

ከመነኮሱ መውለድ።

ካገር ደጋ፤

ከመኝታ አልጋ።

ካጋም የተጠጋ ቁልቋል፤

ዘላለም ሲያለቅስ ይኖራል።

ካጉል ጥንቆላ፤

የሰው ልጅ መላ።

ካዋቂ ጠራቂ፤

ካጣቢ አድራቂ፤

ከሂያጅ ጠያቂ።

ካባቱ ፊት የሚናገር ልጅ አፉ ለምጣም ይሆናል።


%

ክዶ ከመሟገት፤

አምኖ መረታት።

ክፉ ሰው በከንፈሩ ያለቅሳል።

ክረምቱን የፈጀ በጋ፤

እዳውን የፈጀ ዜጋ።

ክፉ አሽከር እሰው ቤት ሲደርስ ወደ ኋላ ይቀራል።

ክፉ ነገር ከከርስ፤

ክፉ ሥጋ በጥርስ።

ኰሶ ሲጠጣ ስቅጥጥ፤

ወተት ሲጠጣ ሽምጥጥ።

ወደሽ ከተደፋሽ፤

ቢረግጡሽ አይክፋሽ።

ወግ አድራሽ ገበሬ፤ ይሞታል በሰኔ።

ወርቅና ጨው አስታራቂ ነው።

ወታደር ቢበድል ባላገር ይካስ።

%
ወልደው ሳይጨርሱ በሰው ልጅ አይስቁ።

ወንድ ባለ በዕለት፤

ሴት ባለች በዓመት።

ወዳጅ ሲጠላ ያረካክሳል።

ወይፈን ለገራፊ፤

ዓሣ ለጠላፊ።

ወልዶ አይሳምለት፤

ተናግሮ አይሳቅለት።

ወዶ የዋጡት ቅልጥም፤

ከብርንዶ ይጥም።

ወጥ ማን ያውቃል፤ ቀላዋጭ።

ወይ ጋሻ፤

ቀድሞ ቀረሻ።

ወርቅና ሰም ፈትልና ቀሰም።

ወፍ ዛፍ አይቶ፤

ወታደር ቤት አይቶ።

%
ወንዝ ለወንዝ እሯጭ ፤ የሰው በግ አራጅ።

ወንድ ልጅ አንድ ቀን እንደናቱ፤

አንድ ቀን እንደ አባቱ።

ወተት ለእንቦሣ፤

ሥጋ ለአንበሣ።

ወጥ ያጣ ዱባ።

ወዶ ገባ፤ ልብሱ ዳባ።

ወፍ እንደ አገሯ ትጮሃለች።

ወጭትና ሴት ሲከናነቡ ይሻላል።

ወልዶ አይስም፤

ዘርቶ አይቅም የለም።

ወይ ባልዘፈንሽ፤

ከዘፈንሽም ባላሳፈርሽ።

ወዳጅ ይመጣ ከራያ፤

ጠላት ይወጣ ከጉያ።

ወንድ ለግርግርታ፤
ጋሻ ለመከታ።

ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባይ ቁጥጥ።

ወርች አሳልፎ ገራፊ፤

ዳኛ ሳለ ዘራፊ።

ወይዘሮና ሚዶ ገባርና ምሳር ትክክል ነው።

ዋንጫ በተርታ ሹመት በገበታ።

ዋቢ ያለው ያመልጣል፤

ዋቢ የሌለው ይሰምጣል።

ዋሽ ቢሉት እዋሻለሁ፤

ንፋስ በወጥመድ እያዛለሁ።

ዋና ከቤት፤ ጠበቃ ከዱለት።

ውሎ ውሎ ከቤት፤

ኑሮ ኑሮ ከመሬት።

ውሀ በብልሃት፤ ይቆላል በእሳት።

ውሀን መመለስ፤ ወደሌላ ማፍሰስ።

%
ውሀን የሚያናግረው፤ ደንጊያ ነው።

ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው።

ውሻ የጌታውን ጌታ አያውቅም።

ውሻ ከሊጥ ጦጣ ከጥጥ።

ውሻ ቢጠራ፤ቀን ቢቀጥሩ ደረሰ በእግሩ።

ውሻ ምን ትበያለሽ አለ ጌኛ፤

ቢበልግም እሌትም ባይበልግም አንቺን።

ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል።

ውሻ በበላበት ይጮሃል።

ውሽማዋን ብታይ ባሏን ጠላች።

ውሸትና ቅራሪ ሽምጥጥ ነው።

ውል ያውላል፤

ታንኳ ያሻግራል።

ውረድ ከማማ፤

ውጣ ከጫማ።
%

ውጣ ከቤት ተነቀል ከመሬት።

ውርርድ ቁም ነገር ይጋርድ።

ውትር ወትር ያነሣል በትር።

ውዝፍ ለሹም ጥንብ ለጅብ።

ዓባይ አንተ አየኸኝ ከደረት፤

እኔ አያሁህ በጉልበት።

ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል።

ዓባይን በጭልፋ።

ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል።

ዓሣ ጐርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፤

የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል።

ዓሣ በወንዙ ይታረዳል፤

የጨዋ ልጅ በቤቱ ይፈረዳል።

ዓሣ መብላት በብልሃት።

%
ዓሣ ለወጋሪ፤

ነገር ለጀማሪ

ዓይነ አፋር ልጃገረድ ከወንድሟ ታረግዛለች።

ዓይን ካላዩበት ግንባር ነው።

ዓይቡን ሲያዩት አጓቱን ጠገቡት።

ዓለም አታላይ፤

እንደበቅሎ ኰብላይ።

ዕንቁራሪት ዝሆን አህል ብላ ተሰንጣቃ ሞተች።

ዕድሜና መስተዋት አይጠገብም።

ዕርቅ አይፈርስ፤

ዓይን አይፈስ።

ዕወር ዕውርን ቢከተል ተያይዘው ገደል።

ዕውር ሲቀናጣ ዘንጉን ወርውሮ ፍለጋ ይገባል።

ዕብድ ቢጨምት እስከ እኩለ ቀን ነው።

ዘር ከልጓም ይስባል።
%

ዘሩ የጣቴ፤

ምድሩ የአባቴ።

ዘመድን የሚወጉበት ጦር ጅንፎው አይለቀቅም።

ዘመደ ብዙ ጠላው ቀጭን ነው።

ዘመዱን የሚያማ፤ ገማ።

ዘመድ ቢረዳዳ ምን፤ ችጋር ሊጐዳ

ዘመን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል።

ዘኬውን ሲቆጥር አነቀው ነብር።

ዘጠኝ ጠጥቶ አሥር የወደደ ዘጠኙ ተናደደ።

ዛር ልመና ሳይያዙ ገና።

ዝናብ ካልጣለ ሁሉ ቤት እንግዳ ካልመጣ ሁሉ ሴት።

ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም።

ዝናብ ሊጥል ሲል ይነፋፍሳል።

%
ዝናብ ሲያባራ ከዋሻ።

ዝናብ ከደመና፤

ነገር ከዋና።

ዝናብና ልጅ ሲጠሉ ያከብር።

ዝም አይነቅዝም።

ዝምብ ቢሰበሰብ ጋን አይከፍተም።

ዝንጀሮና ጥዋ ካፋ ነው የሚይዝ።

ዞሮ ዞሮ የዶሮ አንገት ከማሰሮ።

የሁለት ሀገር ሰደተኛ።

የሁለት፤ ዕዳ አፋይ።

የሆድ፤ መቀኛው አፍ ነው።

የሃብታም ልጅ ሲጫወት የድኃ ልጅ ይሞታል።

የሆድ ብልሃት የጋን መብራት።

የልጅ ነገር፤
ሁለት ፍሬ፤

አንድ ብስል አንዱ ጥሬ።

የልጅ ጥፉ በስም ይደግፉ።

የለመደች ጦጣ ሁል ጊዜ ሽምጠጣ።

የሎሌ አልቃሻ የሴት ቀዳሽ።

የለበሰ የማንንም ጐረሰ።

የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ።

የልጅ ተሟጋች በፊት ሰማይ ያያል ኋላ ምድር ያያል።

የልጅ ክፉ ድቃላ፤

የእህል ክፉ ባቄላ፤

የልብስ ከፉ ነጠላ፤

የቤት ከፉ ሰቀላ።

የልጅቷን ሥጋ በእናቷ ቅቤ።

የላጭን ልጅ ቅማል በላው።

የላሜ ልጅ ያውራዬ ውላጅ።

%
የልጅ ነገር ጥሬ በገል።

የልጅ ብልጥ እየቀደም ይውጥ።

የለመደ እጅ ጆሮ ክንድ ያስመታል።

የሌባን ጠበቃ፤

አደባልቀህ ውቃ።

የሌባን ሞኝ፤

በጐተራ ሥር ይገኝ።

የለመደ ፈረሠኛ ዛብን አይጨብጥል እርካብን አይረግጥ።

የመነ᎐ሴ ፈራጅ።

የመጠረቢያ ልጅ መዘለፊያ።

የመከራ ሎሌ መከራ መስሎ ይታያል።

የመንታ እናት፤

ተንጋላ ትሙት።

የመኰንን ልጅ አዘን ቢነግሩት አደን።

የመን᎐ሴ ሎሌ የክረምት አሞሌ።


%

የመታሰር ምልክቱ መያዝ፤

የመዳኘት ምልክቱ መያዝ።

የመዝሙር መጀምሪያው ሐሌታ የዘፈን መጀመሪያው እስክስታ።

የመኰንን ልጅ በከተማ የድኃ ልጅ በውድማ።

የሚጣፍጥ ምግብ ምንድር ነው ቢሉት፤ ሲርብ የበሉት።

የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ፤

የሚሞት ሽማግሌ አይርገምህ።

የሚፈታ ከተማ ነጋሪት ቢመቱ አይሰማ።

የሚመክተው ጋሻ የሚጠጋበት ዋሻ።

የሚበጀውን ባለቤት ያውቃል።

የሚያልቅ እህል ከሚያልቅ ዘመን ይጣላል።

የሚዛን አባይ ለእሳት፤

የዳኛ አባይ ለሰንሰለት።

የሚሸሹበት አንባ ሲሸሽ ተገኘ።

%
የሚሮጥበት ሜዳ የሚመጣበት ቀዳዳ የለውም።

የሚዳቋ ብዛት ለውሻ ሠርግ ነው።

የሚያድግ ልጅ አይጥላህ።

የሙት ቀናተኛ ሚስቴን አደራ ይላል።

የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ።

የምትጠባ ጥጃ አትጮህም።

የምትኰነንን ነፍስ ጐረቤት ያውቃታል።

የምትሄድ መበለት ᎐ራ ዙራ ትሰናበት።

የምስራች በቃሉ ምልጭ።

የምድሩን በአፍ የሰማዩን በመጽሐፍ።

የማይቻል ጠላት ስለወዳጅ ይቆጠራል።

የማያደርሱበትን አያኩም።

የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል።

%
የማሽላ ዘር ከነ አገዳው ቸር።

የማይመቱት ልጅ ቢቆጡት ያለቅሳል።

የማትረባ ፍየል አምስት ትወልዳለች።

የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል።

የሞተ ልጅ አንገቱ ረጅም ነው።

የሞተው ወንድምሽ፤

የገደለው ባልሽ፤

አዘንሽ ቅጥ አጣ፤

ከቤትሽም አልወጣ።

የሞተ አይከሰስ፤

የፈሰሰ አይታፈስ።

የሞኝ ዘመድ ያፍራል።

የባላገር ሥልጡን እጅ ይዞ ይጫወታል።

የበላ ዳኛ የወጋ መጋኛ።

የባለቤት ሰነፍ ቤቱን ያዋርዳል።

%
የባለቤት አዳይ ጦም ያሳድራል።

የቤት አመል ገበያ ይወጣል።

የባልቴት ወብራ የክረምት ብራ።

የበላን ሆድ ያውቃል የወጋን ክንድ ያውቃል።

የባለጌ ልጅ በመብል ያፍር በነገር ይደፍር።

የባእድ ፍቅር የውሀ ጌጥ አንድ ነው።

የበሬ ዳተኛ በማሀል ይተኛ።

የባለጌ ልጅ መንገድ ይፈጅ ነገር አይፈጅ።

የዝንብ ተላላ ከአንድ በሬ ደም ይቅርባታል።

የዘመድ ጥል የሥጋ ትል።

የዘነጋ ተወጋ።

የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ።

የዘመኑ ሰው መላሱ መንታ፤

አንዱ ለፍቅር አንዱ ለሀሜታ።


%

የዝሆን ክሳት የባለ ጸጋ ድህነት አይታወቅም።

የዘራ ምን ያመጣ? ፍሬና ፈንጣጣ።

የተነቃነቀ ጥርስ ሳይወልቅ አያርፍም።

የተናገሩት ሲጠፋ የወለዱት ይጥፋ።

የተሸሸገ ሆድ አይጠፋለትም።

የተበደለ ከነጋሽ፤ የተጠማ ከፈሳሽ።

የተገዘተች ነፍስ የተለጐመች ፈረስ።

የተማሪ ጋፍ መልክ ይገፍፍ።

የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው።

የተፈጠመ ያርፋል የተኛ ያኰርፋል።

የተጠራጠሩበት ድንጊያ ይጥሉት።

የት ላይ ተቀምጠሽ እግዚአብሔርን ታሚያለሽ።

የተማከሩት ዳኛ ያግዛል፤
የመተሩበት እጅ ይወዛል።

የተናካሽ ውሻ የጅብ መቋደሻ።

የተኛ አንበሳ አስነሳችው ላም ልሣ።

የትም ተወለድ አንኰበር እደግ።

የተረገዘ በሆድ፤

የታዛለ በለምድ።

የተራበ ከባቄላ፤

የተበደለ ከሰቀላ።

የተሾመ ይሟገቱለታል፤

በተሻረ ይመሰከርበታል።

የተልባ ስፍር የህልም እንጀራ።

የተቀማጭ አፍ ምላጭ።

የተናቀ ሠፈር ባህያ ይወረራል።

የቸኰለ አፍስሶ ለቀመ።

የቸገረው እርጉዝ ያገባል።


%

የቸገረው ዱቄት ከነፋስ ይጠጋ።

የእንጦጦ መምር ቢናገር በዓመት ያውም ሬት።

የእናት ሞትና የእግር እሳት እያደር ያቃጥላል።

የእናት ልጅ የጐን አሰጅ።

የእህት ልጅ ባይወልዱት ልጅ።

የእጅ ብልሃት ባርነት የአፍ ብልሃት ጌትነት።

የእብድ አሞራ ሲላ ደንገጡራ።

የእንጨት ምንቸት እርሱ አይድን ሰውን አያድን።

የእንጀራ እናት ምን አጠናሽ እንደ ጀማት።

የእህል ጌታ ፈርዛዛ የወርቅ ጌታ ቀበዝባዛ።

የሰው ሆዱን የወፍ ወንዱን የሚያውቅ የለም።

የሰው አገሩ ምግባሩ።

የሰው ቀላል ለራሱ ይቀላል፤


የልብስ ቀላል ባለቤቱን ያቀላል።

የሰው ቤት ሲቃጠል ቁያ ይመስላል።

የሰው አባቱ ሸማ የሸማ አባቱ እንዲያት ጥለት።

የሰው ልጅ በምን ይታፈራል? በወንበር አይደለም በከንፈር።

የሰው ታናሽ ይገዛል በግማሽ።

የሰከረ ሰው አወዳደቁ አያምርም።

የሰከረ ሲተፋ፤

የገደለ ሲደነፋ።

የሰለጠነ ሰይጠነ።

የስንዴ አራራ የቆንጆ መራራ።

የሴት አገሯ ባሏ።

የሰጠ ቢነሳ የለበት ወቀሳ።

የሰጡህን አትንሳ ያደረጉህን አትርሳ።

የሰዳጅ ለወዳጅ።
%

የሺ ምት ሰርግ ነው፤

የአንድ ሞት ጉዳት ነው።

የሹም ከርፋፋ አገር ያጠፋል፤

የአህያ ጀላፋ መስክ ያጠፋል።

የሺ ፍልጥ ማሠሪያው ልጥ።

የጠገበ አበደ።

የጠገበ ሰው ራቡን አያስብም።

የጠረጠረ ቤቱን አጠረ።

የጠጅ ቤት አዛዥ አተላ አጋዥ።

የጠሩት እንግዳ፤

እራቱ ፍሪዳ።

የጠላ ክፋቱ አለመገኘቱ፤

የልጅ ክፋቱ አለመከማቸቱ።

የጨረቃ ሂያጅ፤ የምስክር ፈራጅ።

የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል።


%

የጨዋ ልጅና ቅል፤ ተሰባሪ ነው።

የጫማ ጠጠር የእንጀራ ልጅ እያደር መቆርቆሩን አይተውም።

የነብርን ጅራት አይጨብጡም፤

ከጨበጡ አይለቁም።

የፈሩት ይደርሳል፤

የጠሉት ይወርሳል።

የጅብ እንግዳ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል።

የወደዱትን ቢያጡ፤

የጠሉትን ይቀላውጡ።

የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል።

የገንዘብ አሮጌ የአባት ባለጌ የለውም።

የቂል በትር ሆድ ይቀትር።

የፊት ወዳጅህን በምን ቀበርከው በሻሽ የኋለኛው እንዳይሸሽ።

የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታል።

%
የጋራ ወንጋራ።

የፈስ ማደናገሪያው ዳባ።

የደንቆሮ ልቅሶ መልሶ መልሶ።

የቀበጡ ለት ሞት አይገኝም።

የወደድሽው ቂጣ ሰተት ብሎ ወጣ።

የደመና ውሀ ጥምና የእናት በደል አይታወቅም።

የወታደር ፈዛዛ የእናት ነዝናዛ የለውም።

የገበያ ሽብር ለቀጣፊ በጀው።

የቀድሞ አርበኛ የቅምጥ ይዋጋል።

የቀማኛ የለው እጅ የበቅሎ የለው ልጅ።

የቆመ ሌባ የተቀመጠውን ይቀባ።

የቤት ቃጋ የሜዳ አልጋ።

የንጉሥ ቃል አንድ ይበቃል።

%
የዋስ ተሟጋች የቆማጣ ፈትፋች።

የወለደውን ቢስሙለት ያቀረበውን ቢበሉለት።

የቆጥን ስታይ የብብቷን ጣለች።

የክፉ ሰው ተስካሩ ያቅራል።

የራሷን አበሳ በሰው አብሳ።

የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ።

የነሐሴ ውሀ ጥሩ ነው የሚጠጣው የለም፤

የድኃ ነገር ፍሬ ነው የሚሰማው የለም።

የዓይን ህመም ክሱት ነው፤

የሆድ ህመም ልግም ነው።

የወርካ ልጅ ሳንቃ፤

የአለቃ ልጅ አለቃ።

የደላው ውሻ ማር ይቀላውጣል።

የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል።

የደላው ሙቅ ያኝካል።
%

የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ።

የቄስ ነጋዴ፤ ይሆናል ወንበዴ።

የወይፈን ሥልቻ ጤፍ ይቋጥራል ባቄላ ያፈሳል።

የወደቀን አንሳ፤

የሞተን አትርሳ።

የካህን አፋር፤

የአህያ ዕውር።

የነገር ወጡ፣ማዳመጡ።

የዋጋ ብልጥ ልብ ይግጥ።

የንጉሥ ሞት የፀሐይ እርበት።

የጐበዝ ዱዳ፤

ባመቱ ምድረ በዳ።

የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ።

የጁ ቄስ ቅኔው ቢጐድልበት ቀረርቶ ሞላበት።

%
የጐበዝ ልብ ከደረቱ።

የንጉስ እንግዳ አያድር ምድረ በዳ።

የረዘመውን በጦር፤

ያጠረውን በድግር።

የበሬ ዶሰኛ የሴት መላሰኛ አታምጣ ወደኛ።

የጐበዝ ሹም የህዳር ጉም ሀገር ይደረግም።

የራሷ ጊዜ አለቀሰች የሰው ጊዜ ሳቀች።

የክፉ ልጅ እናት ሁለት ጊዜ ታዝናለች።

የጉልበት ግማሽ አፍ ነው።

የፈረንጅ አሽከር ነጭ ለባሽ ሳህን አመላላሽ።

የፋክክር ቤት ሳይዘጋ ያድር።

የፋቂ ሰነፍ አንዱን ሳይፍቅ አንዱን ይወዝፍ።

የነብር ዓይን ከፍየል፤

የፍየል አይን ከቅጠል።

%
የደገመ ተረገመ።

ያልተነካ ግልግል ያውቃል።

ያልጫ ድንፋታ እንጀራ እስቲቀርብ።

ያልፋል እስኪያልፍ ያለፋል።

ያልጠረጠረ ተመነጠረ።

ያልበላኝን ቢያኩኝ አይገባኝም።

ያልወለደ አጋድሞ አረደ።

ያልሰማ ጆሮ ከጐረቤት ያጣላል።

ያይጥ ሞቷ የድመት ጨዋታ።

ያልታደለ ከንፈር ሳይሳም ያረጃል።

ያመኑት ፈረስ ጣለ በደንደስ።

ያፍ አማኝ ያደርጋል ለማኝ።

ያልጠሩት ሠርገኛ በትረኛ።

%
ያልገደለ ዘማች፤

ያልወለደ ሟች።

ያለው ይምዘዝ፤

የሌለው ይፍዘዝ።

ያልወለደ አይነሣ፤

የሽምብራ ማሳ።

ያባት ሞትን አይወዱ፤

ረጀቱን አይሰዱ።

ያገሩን ሠርዶ ያገሩ በሬ ያወጣዋል።

ያልሠጡት ተቀባይ፤

ያልጠሩት አቤት ባይ።

ያለሥፍራው የተሰበረ ሲጠግኑት አስቸጋሪ።

ያባይ ምልክቱ አንደበቱ፤

የጉዳይ ምልክቱ ሽልማቱ።

ያየ ቢሄድ የሰማ ይመጣል።

ያዩትን ቢያጡ ያላዩትን ይቀለውጡ።

%
ያንተን የሚመስል እኔም አለን ቁስል።

ያምራል ብሎ ከተናገሩት ይከፋል ብሎ የተውት።

ያበደች ጋልሞታ እናቷን ትመታ።

ያገው ልብ ዘጠኝ ስምንቱን አኑር አንዱን አጫወተኝ።

ያለወለደኩት ልጅ አባቴ ቢለኝ አፌን ዳባ ዳባ አለኝ።

የይጥቱ እላፊ ለምጣድ።

ያህያ ሥጋ ካልጋ ሲሉት ካመድ።

ያውቃል ብሎ ይሾሟል፤

ያምራል ብሎ ይሸልሟል።

ያቡነ ዘበሰማያት ጦር ሲወጋ እንጂ አይታይም ሲወረወር።

ያንዱ ቤት ሣይጠፋ ያንዱ አይለማም።

ያልታጣ ገበያ ጓያ ሸመታ።

ያለፊቱ አይቈርስ ያለቤቱ አይወርስ።

ያውሬ ሥጋ ለወሬ።
%

ያየሁ ላውራ ቢል የሰማሁ አውራ።

ያደረገችውን አውቃ በደረቷ ታጥቃ።

ያንካሳ ልብ ኢየሩሳሌም።

ያለ ባለቤቱ አይነድም እሳቱ።

ያደፈ በአንዶድ የጐለደፈ፤ በሞረድ።

ያኩራፊ ምሣ እራት ይሆነዋል።

ያባ ጐፍናኔ ቤቱ በሪድ።

ያወቀ ተጠነቀቀ፤ የዘነጋ ተወጋ።

ያገኘ ከራሱ ያጣ ከዋሱ።

ያመጣሁት ውሻ ነከሰኝ፤

ያነደድኩት እሳት ጠበሰኝ።

ያጓኑት ድንጋይ ተመልሶ ራስ ይመታል።

ያፍ ዘመድ በመንገድም አይገድ።

%
ያገር እድር፤

ለንጉሥ ያስቸግር።

ያንቺን አትበይ ገንዘብ ያለሽ፤

የሰው አትበይ ምግባር የለሽ።

ያለጐታ ደረባው ምንድነው።

ያተር ክምር የጭሰኛ ክብር።

ያበሬ ባላገደደ ያበሬ ገደል ባልገባ።

ያባት እዳ ለልጅ፤

ያፍንጫ እድፍ ለእጅ።

ያላዩት አገር አይናፍቅም።

ያብዬን እክክ ወደ እምዬ ለከክ።

ይበጃል ያሉት መድኃኒት ዓይን አጠፋ።

ይሆናል ብዬ ጐሽ ጠመድሁ ፤

የማይሆንልኝ ቢሆን ፈትቼ ሰደድሁ።

ይብራና ይብራ ተጣሉ በሰው ሽምብራ።

%
ይወደዋል ካሉ ይመክረዋል ፤

ይመክረዋል ካሉ ይመስለዋል አይቀርም።

ይምሰል አይምሰል ጠይብ እጁ ከሰል።

ይገርማል አህያ ከጅብ ይከርማል።

ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ።

ደፋርና ጪስ መውጫ አያጣም።

ደጃቸውን ሳይዘጉ ሰውን ሌባ ይላሉ።

ደባልና ሹመት፤አለሰበብ አይሄድም።

ደህና ሲታጣ ይመለመላል ጐባጣ።

ዱላ ይዞ ሌባ መጠየቅ።

ዱባና ቅል አበቃቀሉ አንድ ይመስላል፤ አበላሉ ለየቅሉ።

ዲያቆን ከዘፈነ፤

ፍየል ከቀዘነ አይድንም።

ዳኛ የወል ምሰሶ የመሃል።

%
ዳኛ ከፈረደበት መርከብ የተሰበረበት።

ዳኛ ምን ያደላ፤

ከተረታ ሊበላ።

ዳኛ ሰበር በእጁ ከበር።

ዳኛ ቢያጋድል በዳኛ፤

አህያ ቢያጋድል በመጫኛ።

ዳቦ ያለቅርፊት ጠላ ያለምርጊት።

ዳገት ሲወጡ ጥግ ጥጉን፤

ዳቦ ሲበሉ ልብ ልቡን።

ዳገት እርሙ፤ ሜዳ ወንድሙ።

ዳታም በሬ ሀብታም ነው።

ድኃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ እከክ ይጨርሰው ነበር።

ድኃ ጉልበቱን፤

ባለጸጋ ከብቱን።

ድኃ ተበድሎ፤

ማሩኝ ይላል ቶሎ።


%

ድኃ ከንቡ ይደላል።

ድኃ ባመዱ ንጉሥ በዘመዱ።

ድኃ ሲቀልጥ አመድ ይቀልጣል።

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር።

ድምጽና ቁንጫ ባዶ ቤት ይወዳል።

ድንቢጥ እንዳቅሟ በብርዕ ትታገም።

ድመት መንኩሣ አመሏን አትረሳ።

ድንኳን ገልጦ፤ ዙፋን አግጦ።

ድንኳን ያየ ባለጌ።

ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፤

ከቡሄ ወዲያ የለም ክረምት።

ዶሮ ብትታመም በግ አረደላት።

ዶሮ ጭራ ጭራ አወጣች ማረጃዋን ካራ።

%
ዶሮ ካልጫረ ድኃ ካልዘራ።

ዶሮ ሲሉ ሰምታ ሞተች ከጢስ ገብታ።

ዶሮ ከቆጥ በሬ ከጋጥ።

ጀርባዬን አሣከከኝ፤

ተንጠራርቼ ማከክ ተሳነኝ።

ጅራቷ ከደረሰን እናቷ።

ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ።

ጅብን ሲወጉ በአህያ ተጠግቶ ነው።

ጅብ እንደ ቁመቱ ልብ የለውም።

ጅብና እህል ሣይተዋወቁ ይኖራሉ።

ጅብ ካኰተኰተ፤

ሰው ከተከተተ።

ጅብ እንደባቱ ይዘርጥጥ።

ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ።

%
ጅብ ከላይ ውሀ ሲጠጣ፤

ታች ያለችውን አህያ አታደፍርሽቢኝ አለ።

ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው።

ጆሮውን ቢቆርጡት መስሚያው ይቀራል።

ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ።

ገበሬ አክባሪውን ይጠላል።

ገዳይ ቢያረፍድ ሟች ይገሰግሳል።

ገንዘብ ከእጅ ከወጣ ያመጣል ጣጣ።

ገላጋይ አጥቼ ግልግሌን በላኋት።

ጉንፋን የታመመ ውሻ፤

ልጅ ፍየል ይዞ የተደበቀ አይሰወርም።

ጉትቻ ለጆሮ ትንሽ ትመስላለች፤

ዛፈ ጐበዝ ትቆጠራለች።

ጉፋያ ከመብላት ጮማ መሸከም።

ጉድነሽ ያንኰበር ቅጠል፤


እያደር ትለበልቢያለሽ።

ጉልቻ ያለቀኝ አመድ ያጠለቀኝ፤

አላማኑኤል ማን ጠየቀኝ።

ጉልበት የሌለው ወንበዴ ትርፍ የሌለው ነጋዴ።

ጉልበት አለኝ የዝሆን አፍ አለኝ የመኰንን።

ጉዳይ የሌለህ ገበያ አትውረድ፤

ያንዱን ነገር ሰምተህ አትፍረድ።

ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ።

ጌታሁን እንደፈቃድህ ትሁን።

ጌታ ያዛል ውሀ ያነዛል።

ጌታ ለሎሌው ነጋዴ ላሞሌው።

ጌታዬ ያለበት እገመኝ።

ጌታዋን የምታምን ውሻ፤

ፍሪዳ ሲታረድ እወንዝ ወረደች።

ግረፍ ካአባት አትለፍ።


%

ግፍ ብናኝ ከብት ሲጠልቅ ድንጊያ ይዋኝ።

ግመል ሰርቆ ተጎንብሶ ሄደ።

ግንድ ለሺህ አይከብድ።

ግዛኝ ብለው ለመሸጥ አሰበኝ።

ግርግርታ ለሌባ ደስታ።

ጎልማሣ በቀለበት ላም አይማርክም፤

ሽማግሌ በቀለበት ነገር አይሳሳትም።

ጎሽ ለልጅዋ ትወጋ።

ጎልማሳ እንደበላ አንበሳ።

ጐመን በጤና።

ጐበዝ ፊት ሰማይ ሰማይ ያያል፤

ኋላ ምድር ምድር ያያል።

ጐባጣን ይቀብሩ እንደምግባሩ።

ጐኑ የኔ ቀኑ ሰኔ።
%

ጓሳና ድንግል ያላንድ ጊዜ አይበቅል።

ጠባቂ ያላት በግ ላቷ እደጅ ያድራል።

ጠንቋይ ለራሱ አያውቅም።

ጠላ ባለቤቱን አያውቅም።

ጠላ ከማቶት እንጀራ ከሌማት።

ጠላት ይቀባል ጥላት።

ጠጅ የሌለበት አበጋዝነት።

ጠጅ በብርሌ፤

ነገር በምሳሌ።

ጠጅ የወራት ወዳጅ።

ጠጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል።

ጠበቃና ቅል ባጠገብ ይውል።

ጠባ ለኪዳን መሸ ለቁርባን።

%
ጢቢብ ይበላል በገል።

ጠብ ያለበት ቤት ዶሮ ትሞት።

ጣጣ ፈንጣጣ።

ጣዝማ ሰርሣሪ ዳኛ መርማሪ።

ጥርስና ከንፈር ተደጋግፎ ያምር።

ጥምድ እንደበሬ፤

ቅኝት እንደ ገበሬ።

ጥቃት ከጥንብ ይገማል።

ጥቂት ያላት፤ እረፍት የላት።

ጥጃ ጠባ፤ ከሆድ ገባ።

ጥኑ ወዳጅ ጥኑ ጠላት ይሆናል።

ጥል ያለሽ ዳቦ።

ጥምጥም የሌለው መምህር፤

አጸድ የሌለው ደብር።

%
ጥቂት ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ።

ጥቂት ሽሮ ማታ ዶሮ።

ጥጋብ ቢያምርህ ጠላ፤

መግዛት ቢያምርህ ችላ።

ጦጣ ባለቤቱን ታስወጣ።

ጦጣ ተይዛ ትዘፍን።

ጦም ከማደር ዳቦ ቀርቅር።

ጦር ሲመጣ ዛቢያ ቆረጣ።

ጧት ከበላተኛ ማታ ከጦመኛ፤

እንደሽመላ በሁለት ይበላ።

ጨው ለራስህ ስትል ብትጣፍት ጣፍጥ፤

ባትጣፍጥ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል።

ጩኸት ለቁራ፤

መብል ለአሞራ።

ጭምት ሲሞት ልቡን፤

ንጉሥ ሲሞት ግንቡን።


%

ጮሌ ሲያረጅ መጋረጃ ይሆናል።

ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም።

ፈረስ የተፋው ኰርቻ ገልብጦ አየ።

ፈረሰኛ ሲሸሽ እግረኛ ምን ይቆማል።

ፈረሰኛ የወሰደው፤

እግረኛ አይመልሰው።

ፈስ ያለበት ቂጥ ዝላይ አይችልም።

ፈሪ ለእናቱ ይገባል።

ፈሪን ተውሀ ውስጥ ያልበዋል።

ፈርቶ ደንጊያ ቢጥሉ ጅብ ወጣ ከዱር።

ፈጥኖ መስጠት ኋላ ለመጸጸት።

ፈረንጆች እንደ መርፌ ፈትል ይገቡ እንደ ወርካ ይሰፉ።

ፉት ቢሉ ጭልጥ።

%
ፊት የተናገረን ሰው ይጠላው፤

ፊት የደረሰን ወፍ ይበላው።

ፊት ያሞጠሙጧል ኋላ ይፏጯል።

ፌንጣ ብትቆጣ እግሯን ጥላ ሄደች።

ፍየልም የለኝ ከነብር ምን አጣላኝ።

ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲያ።

ፍየሏን እንደ በግ።

ፍየል መንታ ትወልድ አንዱ ለወናፍ አንዱ ለመጽሐፍ።

ፍጥም አፍራሽ ቤተ ክርስቲያን ተኳሽ።

ፍርድ አያውቅ ዳኛ፤

ተገን አያውቅ እረኛ።

ፍጥም ያቆማል፤ እርቅ ይጠቀልላል።

ፀሐይ ብልጭ ወፍ ጭጭ ሲል።

ፀሐይ ያየውን ሰው ሳያየው አይቀርም።

%
ፀሎት በፍቅር ሃይማኖት በምግባር።

ጻድቃን ካልታቃጠሩበት ስፍራ ይገናኛሉ፤

ኃጥአን በተቃጠሩበት ይተጣጣሉ።

ጽድቅ ለመንኳሽ ቀኝ ለከሳሽ።

ጳጉሜ ሲወልስ ጐተራህን አብስ።

ንፅህና፣

ለሥጋ ለነፍስ ጤና

ሳይለፋ ያገኙት፣

ለቅፅበት።

ስትጠጣ አይተህ፣

ስትፈርም አንብበህ።

አንድ አይነድ፣

አንድ አይፈርድ።

ብዙ የሚያወራ፣

ጥቂት ይሠራ።

ቀዳሚ፣

ተጠቃሚ።
%

ሁሉም ያልፋል፣

እስኪያልፍ ያለፋል።

ውለታ፣

የልብ ትዝታ።

የስስታም አንድ ያንቀው፣

አንድ ይወድቀው።

You might also like