You are on page 1of 8

እዌጥን ዝንቱ ነገር በረድኤተ እግዚአብሔር

አድዋ የእኛ ነው!!

ገቢር ፩

ትዕይንት ፩

ቦታው ተራራማ ስፍራ ነው፤ ታራራው ላይ የተወሰኑ ጉብታዎች ይታያሉ፤ በጉብታዎች ውስጥ አስከሬኖች
አሉ፡፡ ኹለት ወንድ እና ኹለት ሴት በተራራው ላይ በድካም አርፈውበታል፡፡ ወጣቶቹ የመጡት ከተለያየ
አቅጣጫ ነው፡፡ተጓዥ መኾናቸውን አለባበሳቸው እና ያዘሉት ቦርሳ ያሳብቃል፡፡መድረክ ላይ ሲወጡ ተራርቀው
ነው ዝርፍጥ ያሉት፤ በተለያየ እንቅስቃሴ ድካማቸውን ሲያሳርፉ ይታያል፡፡

ወጣቶቹ ጉብታዎቹን ተደግፈው ይታሉ፡፡ ከሩቅ የቀረርቶ ድምጥ ይሰማል፤ ኃይለኛንፋስ ይነፍሳል፤ ንፋሱ ላይና
ቀረርቶው ላይ ተደርቦ “እም እምምም” የሚል ድምጥ ይሰማል፡፡ ድምፁ የሚተም ሰራዊት ድምጥ ነው፡፡

ኩስያ፡- በቃ?

ኦልያድ፡- ባዶ ድንጋይ! በቃ?

ሳሚራ፡- ይኼው ነው?

ስርጉት፡- ለዚኽ ነው?

ኩሲያ፡- ምኑ?

ስርጉት፡- ታሪክ ተብየው!!! እዚኽ ድረስ ያመጣኝ!

ሰሚራ፡- መኩሪያ ነው ተብዬ መልፋቴ ቆጨኝ!

ኦልያድ፡- ድንጋይ ብቻ ባዶ ድንጋይ … ቆይ ድንጋዩ ለእኔ ምኔ ነው?

ሰሚራ፡- መኩሪያነቱስ ምኑ ነው?

ስርጉት፡- በቅድሚያ እንተዋወቅ፡፡ (እጇን ትዘረጋለች)

ሰሚራ፡- ቦታው ያተዋውቃችኋል ተብዬ ነበረ፡፡

ኩስያ፡- ተራራው ያግባባችኋል ተብዬ ነበር፡፡


ኦልያድ፡- ድንቄም¡ አግባባን እኮ … ድንጋዩ አተዋወቀን እኮ¡ …

ኩስያ፡- ግን ላንተ ምንኽ ነው?

ኦልያድ፡- እርሱማ ታሪኬ ነው … ማንጠያቂ አደረገኽ? ግን ላንተ ምንኽ ነው?

ስርጉት፡- ማነው ያንተ ያደረገው? ይኼማ የእኔ ቦታ ነው!!

ሰሚራ፡- “በገዛ ዳቦዬ …” አሉ … እኔ ባለቤቷ ቆሜ የእኔ ነው የእኔ ነው ስትባባሉ ትንሽ


አታፍሩም?

ኩስያ፡- ለምን አፍራለኹ!! ያንተ ነው ተብዬ ነው የመጣኹት … ግን ባዶ ነው! ድንጋይ ብቻ፣


ብርድ ብቻ …

ስርጉት፡- በእርግጥ ባዶ ነው፡፡ ቢኾንም የኔ ቦታ ነው፡፡

ኦልያድ፡- ለምን ተብሎ የእኔ ነው፡፡

ስርጉት፡- ግን ምንድን ነው?

ኩስያ፡- እ ምንድን ነው?

ሰሚራ፡- ምን አለው?

ኦልያድ፡- እ …ኔንጃ ምንድ ነው?

ኩስያ፡- ምንታፈጣላጭችኹ … አላቅም

ስርጉት፡- ኧረ እኔ አላውቅም!!

ኦሊያድ፡- የኾነ ነገርማ አለው!! ይኼ ተራራ የእኔ ነው!

ኩስያ፡- የኾነ ምስጢር አለው!! … የእኔ ነው!

ስርጉት፡- ምስጢርማ የእኔ ነው!!

ሰሚራ፡- አትልፉ ምንም ይኹን ምንም የእኔ ነው !

ኦሊያድ፡- ማን ሰጥቶሽ?
ሰሚራ፡- አባቴ

ኩስያ፡- ለእኔም አባቴ ነው የሰጠኝ!

ስርጉት፡- የአባቴ ርስት ነው!

ኦሊያድ፤- የአባቴ ቅርስ ነው!

ሰሚራ፡- የአባቴ ታሪክ ነው!

ኩስያ ፡- የአባቴ እውነት ነው!

ሰሚራ፡- ምንድን ነው ምትቀባጥሩት!?

ኦሊያድ፡- ምንድን ነው ምትዘላብዱት?

ኩሲያ፡- ይኼ ተራራ ለእናንተ ምንም ነው … የእኔ ብቻ ነው፡፡

ኦሊያድ፡- ይኼ ተራራ ምናችኹም አይደል የእኔ ነው፡፡

ስርጉት፡- /እየሳቀች/ የእኔ ነው … አለዛ …

በህብረት፡- አለዛ ምን?

ስርጉት፡- ምስክር ይምጣ

ኦሊያድ፡- ይመስከራ!

ኩሲያ፤- መስካሪ ካለ ይመስክራ፡-

ሰሚራ፡- እነማ?

/ከተመልካች መኻል አንድ ሙዚቀኛ በጥላኹን ዜማ እየዘፈነ ይመጣል/

ዘፋኝ፡- ነበረ ነበረ ነበረ ነበረ

እውነት እስኪጠለሽ የጋራ ነበረ

የእኔ የእኔ ሳይኾን የእኛ ባሉት ሰዓት

የጋራ መክበሪያ በጋራ ያቆሙት


ነበረ ነበረ በህብረት ያፀኑት፡፡

ስርጉት፡- ማን ነኽ አንተ?

ዘፋኝ፡- ዘመን … ምስክር…

ኦልያድ፡- የጋራ ዘመንም የጋራ ምስክር የለንም፡፡

ኩስያ፡- የጋራ ነገር የለንም!

ሰሚራ፡- የጋራ አናውቅም!

ዘፋኝ፡- የጋራማ ሞልቷል አምላክ መች ነሳን

የፍቅር ርሃብ ነው የበታተነን

ስንለያይ ኁሉ ደስ ይለዋል

አንድነትን ማየት ኹሉም ይጠላዋል፡፡

ኦልያድ፡- ዝጋ …

/ዘፋኙን ገፈታትረው ሲጥሉት ሰቅጣጭ ጩኀት ይሰማል መድረኩን ጩኸቱ ሰይሞላዋል፡፡ የነፋሱ ድምጥ
ያይላል በነፋሱ ድምጥ ተደርቦ የመድፍ፣ የጠመንጃ፣ የጎራዴ መፏጨት ድምጥ ይሰማል፡፡ አራቱም ደንግጠው
በየጉብታው ይደበቃሉ፤ ጉብታው ተከፍቶ የአርበኛ ልብስ የለበሰ ይወጣል የሚወጡት በእየተራ ነው .. “አድዋ
ማለት”ን ያነበንባሉ/

ወ፩፡- አድዋ ማለት የጀግኖች የደም ጎራ

ለጥቁር ድል ብስራት የነፃነት ጮራ

ለነጭ የውድቀት የሽንፈት ስፍራ

ደም እንደጎርፍ ያፈሰስንበት

አጥንት እንደ አገዳ የሰበርንበት

ስጋችን የተመተረበት

ጉሮሮ የፈረጠቅንበት
የድል ብስራት ያወጅንበት

በእልፍ አእላፍ ሰማዕታት ደም

ድል የዘመርንበት ዓለም

አድዋ ማለት ጥልቅ ነው

የእኔ የእኔ የማንለው፡፡

ሴ፪፡- በእንዳ ኢየሱስ ጠላት በጥም ያረረበት

እጁን አንከርፎ የወጣበት

ሴት አናብስ እያገሳን

የጠላት አንገት እየቀነጠስን

የሮምን ጠሐይ ያጠለቅንበት

በሴት አንጀት የዋልንበት

የእኛ ነው … የእኔ አይደለም

የጋራ ነው የድል ቀለም

ከአድዋ ጫፍ የተከልነው

የድል ውሎ የጋራ ነው፡፡

ወ፫፡- አባ ዳኘው የዳኘበት

አባመላ ያወቀበት

አባ ነፍሶ የጣለበት

አባ ነጋ ያበራበት

አባ ሻንቆ ስንቱን አንቆ

አባ ጥመር ስንቱን ጣምሮ


አባ ቃኘው በስት ጥሮ

አባ ጎራው መድፉን አስሮ

ኧረ ስንቱ ኧረ ስንቱ የታየበት

እንዴት የእኔ የኛን እውነት፡፡

ሴ፬፡- /ቀረርቶ/

ጎራዴ መዞ ሲኼድ ከቤቱ

አወይ ሰው ፈጀ አለጭ እናቱ

አጣድፎ ገዳይ በያዘው ጣምራ

ባባቱ ወጥቷል ልጁም አይፈራ

ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ

አባት አስረካሽ ልጅ አይወለድ፡፡

ፎካሪ፡- ዘራፍ ዘራፍ

በሰፊው አውድማ የተበጠረው

ገለባው ኼደ ምርቱ የቀረው

አኹንም ዘራፍ ቅድምም ዘራፍ

ነጭ አንበርካኪ በበራፉ ሲያልፍ

ነጭ ሰው ገዳይ ባለ ጥሩንቡሽ

ወደዛ ኼዶ ወደዚኅ ሲሸሽ

ነጭ ሰው ገዳይ ፀጉረ ለሁጫ

ቆሞ ሚፈሳ እንደ ውርጫ

ጎራዴው በላጭ ስንጥቅ አክርማ


በጠላት ሬሳ ጆቢራ ጋባዥ በዓየር አውድማ

ግብር ሚያበላ ባየር ዳስ ጥሎ ሳተክል ካስማ

ጎበዝ ባገሩ ነፃነት ግብሩ

የአንበሳ ዶቦል አሉ ሲኮሩ

/ፉከራው ሲቀልጭ ወጣቶቹ ከየአሉበት ቀስ እያሉ መውጣት ይጀምራሉ፤ በሃፍረት ይተያያሉ ፎካሪዎቹ
ሲቀርቧቸው፤ በወኔ ይሰምጣሉ ይተቃቀፋሉ … በፉከራው ላይ ተደርቦ “የኛ” የሚል ዝማሬ ይዘምራሉ/

ዝማሬ፡- አድዋ አድዋ አድዋ

አድዋ የህብራችን ትኾናለች

አድዋ ቀለማችን ትኾናለች ትኾናለች ትኾናለች፡፡

አድዋ አድዋ አድዋ አድዋ

አድዋ በዓለም ታበራች

አድዋ ለጥቁር ብስራት ትኾናለች ትኾናች

አድዋ አድዋ አድዋ አድዋ

አድዋ መድመቂያችን ትኾናለች

አድዋ ቀለማችን ትኾናለች፡፡

/በህብረት እየዘመሩ ይሰናበታሉ፡፡/

መጋራጃ ይጣላል፡፡

እፌፅም ዝንቱ ነገር በረድኤት እግዚአብሔር


ከፍቃደ ማሪያም
የካቲት ፯ ቀን ፳፻ወ፲፫ ዓም
ዘመኑ ለማቴዎስ
አዲስ አበባ ኢትዮጲያ፡፡

You might also like