You are on page 1of 3

ወልድ በራሱ ህይወት እንዲኖረው ከአብ ተሰጥቶታል ማለት ምን ማለት ነው?

ሙስሊም ወገኖች ኢየሱስ በባህርዩ ከአብ እንደሚያንስ ለማሳየት ከሚጠቀሙባቸው ሙግቶች መካከል “ወልድ ህይወትን የተቀበለው
ከአብ በመሆኑ ለሕላዌው ጅማሬ አለው” የሚለው ሙግት አንዱ ነው። ይህንን ሙግት ለማጠናከር ደግሞ የሃ 5፡26 ን እንደ ማስረጃ
ይጠቅሳሉ፤ ክፍሉ እንዲህ ይነበባል፡

“አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና”

በርግጥ ይህ ክፍል ኢየሱስ ህያውነቱን ከጊዜ በኋላ ከአብ እንደተቀበለ የሚያሳይ ነውን?

መጽሃፍ ቅዱስን ቆርጦ ማንበብ ለከፋ የስህተት ትምህርት ይዳርጋል፤ በመሆኑም አንድን ጥቅስ ለመመልከት
የተጻፈበትን ሙሉ አውድ አስቀድሞ ማሰስ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ዮሃ 5፡26 ኢየሱስ በዚያ ምእራፍ ውስጥ በብዙ
ቁጥሮች ካደረገው ዘለግ ያለ ንግግር ክፍል ነው፤ ስለዚህ ትርጉሙን ለመረዳት ኢየሱስ የተናገረው ምን እንደሆነና ለምን
እንደተናገረው ማየት ያስፈልጋል። ክፍሉን በዚህ መሰረት ለማየት ከሞከርን “ወልድ ህይወትን የተቀበለው ከአብ በመሆኑ
ለሕላዌው ጅማሬ አለው” የሚለውን ድምዳሜ በጭራሽ እንዳንይዝና በተቃራኒው ወልድ ራሱ ከአብ እኩል መሆኑን እንድናምን
የሚያስግድድ ክፍል መሆኑን እንረዳለን። እንዴት? የሚል ጠያቂ ቢኖር ምክንያቶቼ የሚከተሉት ናቸው፡

1) ዮሃ 5፡26 ራሱ አብ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታል ይላል እንጂ አብ ለወልድ ህይወት ሰጥቶታል
አይልም። ስለዚህ በራሱ ህይውት አለው ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ ከመመለስ በፊት በግርድፉ
ምደምደም አይቻልም። ወልድ በራሱ ህይወት አለው የሚለውን ይህንን ንግግር ለመረዳት ደግሞ ወደጥቅሱ
የመጀመሪያ አንጓ መምጣት ይኖርብናል። ይህም ኢየሱስ በራሱ ያለው ህይወት ልክ እንደራሱ እንደ አብ
እንደሆነ ይነግረናል። በአብ በራሱ ያለው ህይወት ምንድነው? ጅማሬ ያለው ነውን? አይደለም! ስለዚህ ይህ
ክፍል ኢየሱስ ከአብ ህይወት ተሰጠው ከሚለው ቀላል አመለካከት በላይ የሆነ ውስብስብ ሃሳብ የተሸከመ ክፍል
ነው ማለት ነው። የኢየሱስን አምላክነት የማያምኑት ወገኖቻችን “ሰጥቶታል” የሚለውን ቃል ብቻ ይዘው
መሟገቱ የማያዋጣቸውም ለዚህ ነው።
2) ይህ የዮሃ 5፡26 ንግግር ከቁጥር 18 የሚጀምር በመሆኑ ትርጉሙን ለማግኘት ከላይ ጀምረን ያለማቋረጥ ማንበብ
ይኖርብናል።
ከቁጥር 18 ቅደም ብለን ስናነብ ኢየሱስ በሰንበት በመፈወሱ ምክንያት አይሁድ ሊገድሉት እንደፈለጉና እርሱም
“አባቴ እስከዛሬ ይሰራል እኔም እሰራለሁ” ብሎ እንደመለሰላቸው እናነባለን (ዮሃ 5፡1-17)። ከዚህም የተነሳ
አይሁድ እርሱን ለመግደል የሚያበቁ ሁለት ምክንያቶች በኢየሱስ ላይ አግኝተዋል፤ 1 ኛ ሰንበትን መሻሩ ሲሆን
2 ኛ ደግሞ እግዚአብሄር አባቴ ነው ብሎ ራሱን ከአብ ጋር እኩል ስላደረገ ነበር (ቁጥር 8)። ለዚህ የግድያ
ፍላጎታቸው ነው ኢየሱስ ከቁጥር 19 ጀምሮ ያለውን ረዘም ያለ ምላሽ የሚሰጣቸው። በዚህ ምላሹ ውስጥም
በአብና በእርሱ መካከል ያለው ጥልቅ (Intimate) ፍቅር ምን ያህል የተግባርና የፈቃድ አንድነትን እንዳመጣ ነው
የሚናገረው። በዚህም መሰረት አብ ወልድን ስለሚወድደው የሚሰራውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ወልድም በምላሹ
ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይፈቅድም፤ ከሚወደው አባቱ ያየውን እንጂ። ይህ የኑባሬ መተናነስን ሳይሆን የግብር
መተናነስን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ አብ የሚሰራው ሁሉ የወልድም ስራ ነው፤ ለአብ የሚገባውም ሁሉ ለወልድ
ይገባዋል። ይህንን ከሚከተሉት ጥቅሶች በግልጽ እንመለከተዋለን።
 አብ ለሙታን ህይወትን እንደሚሰጥ ሁሉ ወልድም ህይወትን ይሰጣል (ቁጥር 21)፡ ኢየሱስ በዚህ ምንባብ ላይ
የእግዚአብሄርን ህይወትን የመስጠት ባህርይ የሚጋራ ሲሆን ቁጥር 24 ላይ ደግሞ በእርሱ የሚያምኑ ህያዋን
ሆነው እንደሚኖሩ ይናገራል። መጽሃፍ ቅዱስ ህይወትን የመውሰድና የመስጠት ስልጣን በእግዚአብሄር እጅ
ብቻ ያለ ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ ይነግረናል። የመግደልና የማዳን ችሎታ የአምላክ እንጂ የሰው አይደለም
(2 ነገ 5፡7)፣ እግዚአብሄር ብቻ ተግባር ኢየሱስ ከአብ ተመልክቶ እንደሚያደርገው ይናገራል። የአይሁድ
መምህራንም በዚህ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ፤ ለእነርሱ በእግዚአብሄር እጅ ብቻ ያሉ እና ለማንኛውም
ተውካዩ (ማለትም ልፍጡራን ነገስታትና ነቢያትም ጭምር) የማይሰጣቸው ሶስት ቁልፎች አሉት፤ እነርሱም፡
የዝናብ ቁልፍ (ዘዳ 28፡12)፣ የማህጸን ቁልፍ (ዘፍጥ 30፡22) እና የሙታን ትንሳኤ ቁልፍ (ሕዝ 37፡13) ናቸው።1

1
D.A. Carson; The pillar New Testament commentary: The Gospel according to John: Page 344
ኢየሱስ ይህንን ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም የማይዘውን ለሙታን ህይወትን የመስጠት ቁልፍ እንደያዘ
ይናገራል።
 ሰዎች አብን እንደሚያከብሩት ወልድንም ያከብሩታል (ቁጥር 22 እና 23)። አሁንም ኢየሱስ ከተሰጠው
የፈራጅነት ተግባር የተነሳ ሰዎች ልክ እንደ አባቱ እንደሚያከብሩት ይናገራል። አሁንም ወደ ብሉይ ኪዳን ሄደን
ስንመለከት ይህንን አይነቱ ክብር ለእግዚአብሄር ብቻ የተገባ እንደሆነ (መዝ 29፡1፣ 96፡7)፣ እንዲሁም እስራኤልን
ወደ ምርኮ የመራት ይህንን ክብር ለጣኦታት የማጋራት አባዜ እንደሆነ እንመለከታለን። ነገር ግን ዮሃ 5፡26 ላይ
ይህንን ለእግዚአብሄር ብቻ የሚገባ ክብር ኢየሱስ በግልጽ ይጋራዋል። ይህንን ክብር የሚጋራበት ምክንያትም
ከአባቱ ከተቀበለው የፈራጅነት ተግባር የተነሳ ሲሆን ወልድን ልክ እንደ አብ የሚያከብር ሁሉ ወደዚህ ፍርድ
እንደማይመጣና ወደ ዘለአለም ህይወት እንደሚገባ፤ እንዲሁም ድምጹን የሚሰማ ሁሉ ቢሞት እንኳን
በህይወት እንደሚኖር ጨምሮ ይነግራቸዋል (ቁጥር 25)።

3) ስለዚህ አብ በራሱ ለሙታን የሚሰጠው ህይወት እንዳለው ሁሉ ወልድም በራሱ ለሚወዳቸው ሁሉ ህይወት
እንዲሰጣቸው ፈቅዷል (ቁጥር 26፡28)።
እንደምትመለከቱት ቁጥር 26 በሙሉ ምንባቡ አውድ ውስጥ ገብቶ ሲነበብ ስለኢየሱስ ስለ ኢየሱስ ህልውና
የሚናገር ሳይሆን በእርሱ ስላለው ለሰዎች ስለሚሰጠው እንደ አብ አይነቱ ህይወት የሚናገር ነው። በእርሱ
የሚያምኑ፣ ድምጹን የሚሰሙ፣ እንዲሁም አብ በሚከበረው ልክ የሚያከብሩት ሁሉ የዚህ በእርሱ ያለው
ህይወት ተካፋዮች ናቸው፤ ምክንያቱም አብ በራሱ ይህ ህይወት እንዳለውና ለሰዎች ህይወትን የሚሰጥ
እንደሆነ ሁሉ ኢየሱስም ይህ ህይወት በራሱ አለው፣ ለሚወድዳቸውና ድምጹን ለሚሰሙት ሁሉም ከፍርድ
ያመልጡ ዘንድ ይህንን ህይወት ይስጣቸዋል። ሃዋርያው ዮሃንስ በሌላም ስፍራ ተመሳሳይ ነገሮችን ስለ ኢየሱስ
ሲናገር ይታያል፤ ለምሳሌ የኢየሱስን ቅድመ ሕላዌነትና አምላክነት በዋሳበት በወንጌሉ መግቢያ ላይ “በእርሱም
ሕይወት ነበረች” (ዮሃ 1፡4) ሲለን በመጀመሪያው መልእክቱ መግቢያ ላይ ደግሞ “ህይወት ተገለጠ አይተንማል፤
እንመሰክርማለን፤ ከአብ ጋር የነበረውን ለእኛም የተገለጠውን የዘለአለምን ህይወት እናወራላችኋለን” (1 ዮሃ 1፡
2) በማለት ይነግረናል። በዮሃ 5፡26 ላይም ጌታ ኢየሱስ ይህንኑ ህይወት፤ ማለትም በእርሱ ያለውንና ልክ እንደ
አብ
ለሚያምኑበት ሁሉ የሚሰጠውን ህይወት እየተናገረ እንጂ ወገኖቻችን እንደሚሉት ኢየሱስ ህልውናው የሆነ
ሰአት ላይ የጀመረ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም።
ሰጥቶታል ማለት ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ይህ የወልድን የግብር መተናነስ (Functional
subordination) የሚያሳይ እንጂ ኢየሱስ በአብ መፈጠሩን የሚያስረዳ አይደለም እንላለን።2

ማጠቃለያ
እግዚአብሄር በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “እግዚአብሄርን በማን ትመስሉታላችሁ?” (ኢሳ 40፡18) እንዲሁም
“ተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?” በማለት እስራኤላውያንን ይወቅሳል።3 የእስራኤላውያን በምድር ሁሉ
የመበተንና የመፍረስ ዋና ምክንያት ስንመረምርም እግዚአብሄርን ከሌሎች ባእዳን አማልክት ጋር እኩል
በማድረጋቸው መሆኑን እንረዳለን። በሌላ በኩል ኢየሱስ ራሱን ከእግዚአብሄር ጋር በማስተካከሉ ሊገድሉት
እንዳሰቡ ዮሃንስ ያስነብበናል። ከቁጥር 19 ጀምሮ ያምናነበው ዘለግ ያለው የኢየሱስ ንግግርም ራሱን ከአባቱ ጋር
አስተካክሎ ይናገር እንደነበረ ማረጋገጫ ነው። ይህንንም ኢየሱስ ልክ እንደ አብ ለሚወድዳቸው ሁሉ ህይወትን
እንደሚሰጥ፣ ይህ አይነቱ ለሙታን የሚያካፍለው ህይወትም በራሱ እንዲኖረው ከአባቱ እንደተሰጠው፣
ድምጹን የሚሰሙና የሚያምኑበት ሁሉ ይህንን ህይወት እንደሚካፈሉ፣ ኢየሱስ ልክ እንደ አብ እንደሚፈርድ
እና አብ እንደሚከበረው ሁሉ እርሱም እንደሚከበር በመናገር ገልጦታል። ይህም ኢየሱስ እግዚአብሄር አባቴ
ነው ሲል ከአባቱ ጋር እኩል መሆኑን እየተናገረ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንጂ ኢየሱስ ፍጡር መሆኑን የሚያሳይ
አይደለም። ከዚህ ምንባብ ውስጥ ቁጥር 26 ን ብቻ መርጦ ኢየሱስ ለህልውናው ጅማሬ አለው ብሎ መፍረድም

2
Ibid, 340
3
ibid
መጽሃፉን አንብቦ እውነትን ለማወቅ ተነሳሽነት እንደሌለን ከማሳየቱ ውጪ የሚሰጠው ምንም ትርጉም
አይኖረውም።

You might also like