You are on page 1of 2

የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ምን ማለት ነው??

ስለዚህ ጉዳይ ማውራትና እውነቱን ማወቅ ኢየሱስ ወይም እግዚአብሔር ቅር እንዲላቸው አያደርግም፡፡ ኢየሱስ ራሱ
እኮ አላፈረበትም፡፡ እንዳውም በግልፅ "ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ" ብሏል
(ዮሐ 20)፡፡ ደግሞ እውነቱን እንድናውቅ የሚፈልገውና "ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ
በሚወድ በእግዚአብሔር በመድሃኒታችን ፊት…" ያለን እግዚአብሔር ራሱ ነው (1ጢሞ 2)፡፡ የእውነተኛ እውቀት
ምንጭም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሃሌሉያ! ብዙ ሰዎች ስለጉዳዩ እውነቱን ማወቅ እና ማሳወቅ አልቻሉም፡፡ ስለመፅሐፍ
ቅዱስ ማወቅ ለሚፈልጉ ሌሎች ሃይማኖቶችም ትክክለኛ መረጃ አልሰጠናቸውም፡፡ የጌታ ቃል እንዲህ ይላል
"በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።
" (ኤፌ 1)፡፡ አምላክና አባት! ብዙ የመፅሐፍ ቅዱስ ቦታዎች ላይ እንደዛ ይላል፡፡ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ
አባት ነው ስንል ምንም ጥያቄ አይፈጥርም፡፡ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው ሲባል ግን ባለመረዳት
ምክንያት ግራመጋባት ይፈጥራል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ማለት ምን ማለት ነው?? ኢየሱስስ አምላክ
አይደለም ማለት ነው??

አምላክ ማለት የመፍጠር ሃይል ያለውና ለሞተ ነገር ህይወት መስጠት የሚችል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው የጌታ ቃል
"ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ
በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው።" የሚለው (ሮሜ 4)፡፡ የሌለውን መፍጠርና የሞተውን
የማስነሳት ሃይል መለኮታዊ ወይም አምላካዊ ማንነት ነው፡፡ ሮሜ 1 ላይም እግዚአብሔር አምላክ መሆኑ
የሚታወቀው በሃይሉ ፍጥረትን የፈጠረው እርሱ በመሆኑ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል "የማይታየው ባሕርይ
እርሱም የዘላለም ሃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና"፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔር ይህንን ሃይል ፍጥረትን ለመፍጠር ስለተጠቀመበት የፍጥረት ሁሉ አምላክ ነው፡፡ ፍጥረት በሱ
ሃይል ስለተፈጠሩ አምላካችን ይሉታል፡፡ ይህ ሃይል ፍጥረትን ከመፍጠር በተጨማሪ የሞተን ወደ ህይወት
ለማምጣት እግዚአብሔር ይጠቀምበታል፡፡ ከላይ ሮሜ 4 ላይ ያለው ቃል ያን ቢነግረንም አንድ ሌላ ቃል ልጨምር፡፡
"ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ
ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው
በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል" (ኤፌ 1)፡፡ እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት ሲያስነሳው
የተጠቀመው ጉልበት ወይም ሃይል አምላካዊ ሃይሉን ስለሆነ የኢየሱስ አምላክ እንዲባል ያደርገዋል፡፡

ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልፅ ለሰው ልጆች አባቴ ብቻ ሳይሆን አምላኬ ብሎ ያስተዋወቀው መቼ ነው?? ከሞት
ሲነሳ ነው፡፡ ዮሐ 20 ላይ፡፡ ከመስቀል በፊት የእግዚአብሔር አምላካዊ ሃይል በእርሱ ላይ በመፍጠር ወይም ከሞት
በማስነሳት ተደርጎ ስለማያውቅ አባቴ እንጂ አምላኬ ብሎ አላስታወቀንም ነበር፡፡ ከትንሳኤ በኋላ ግን እሱም ሆነ
ሐዋርያት በግልፅ የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ማለት ጀመሩ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና
አባት ተብሎ የሚነገረን ስፍራ ከኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ወይም ከትንሳኤ ሃይል ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ኢየሱስም አምላኬ
አምላኬ ብሎ የጠራው መስቀል ላይ ሊሞት ሲል ነው (ማቴ 27)፡፡ ሐዋርያት ደግሞ ለምሳሌ 1ጴጥ 1፡3 "ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት
ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ" ብሎ ስለ መነሳቱ አውርቶ የኢየሱስ ክርስቶስ
አምላክና አባት ይላል፡፡ 2ቆሮ 1 ላይ የኢየሱስ አምላክ ብሎ ሲነገረን በዛው ምዕራፍ "ሙታንን በሚያነሳ
በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን…" ይላል፡፡ ኤፌ 1 ላይ ሁለት ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት
ሲል ስለትንሳኤ፣ ሰማያዊ ስፍራና ሞቶ ስለመነሳቱ በሚናገርበት ምዕራፍ ነው ያን የተናገረው፡፡ 2ቆሮ 11 ላይ እንኳን
ጳውሎስ የኢየሱስ አምላክ ያለው በደማስቆ ሊገድሉት ፈልገው (ሐዋ 9) ግን ጌታ እንዳስመለጠው ሲናገር ነው፡፡

ስለኢየሱስ ሲናገር "ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ
ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።" (1ቆሮ 15) ይላል፡፡ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር የተገዛውና አምላኬ ያለው እግዚአብሔር
ሁሉን ለኢየሱስ ካስገዛለት በኋላ ነው፡፡ ኢየሱስ ሁሉ የተገዛለት መቼ ነው?? እግዚአብሔር ከሞት ሲያስነሳው ነው፡፡
ቃሉ እንዲህ ይላል "ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት ብሎ መሰከረ። ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት
ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አናይም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን
ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን
ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን።" (ዕብ 2 እና ኤፌ 1)፡፡ እኛ ሁሉ እንደተገዛለት አንይ እንጂ ለኢየሱስ ግን ሁሉ
ተገዝቶለታል፡፡ በሙታን ትንሳኤ ደግሞ እኛም ያንን እናያለን፡፡ ሃሌሉያ!!

ኢየሱስ አሁን አምላክ ነው ወይ?? የሚለውን ጥያቄ ለመመስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያለውን የኢየሱስ ማንነት ማወቅ
ያስፈልጋል፡፡ ስለራሱ ሲናገር "ትንሳኤና ህይወት እኔ ነኝ" ብሏል፡፡ አምላክ ካልሆነ ያንን ማለት አይችልም፡፡ "የመለኮት
ሙላት ሁሉ በሰውነቱ ተገልጦ ይኖራል" ማለት አምላክ ነው ማለት ነው (ቆላ 2)፡፡ አምላካዊ ማንነት አለው ማለት
ነው፡፡ "እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር
ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።" (ቆላ 1) ይላል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ
አድርጎታል፡፡ ህይወት ስለመስጠቱ እና ስለአምላክነቱ በአንድ ጊዜ የሚናገር አንድ ቃል አለ፡፡ እንዲህ ይላል
"የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤
እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም
ሕይወት ነው።" ሃሌሉያ! ኢየሱስ የተባረከ አምላካችን ነው፡፡ አሁን ሰዎች ህይወት ለማግኘት፤ ከሞት ወደ ህይወት
ለመሻገር ኢየሱስ ጋር ብቻ ነው መምጣት የሚችሉት፡፡ ምክንያቱም ትንሳኤ የሚሰጥ አዲስ ፍጥረት የሚያደርግ
አምላክ ነው፡፡ ሃሌሉያ!! ሃሌ…..ሉያ!! ሃሌሉያ! ሃሌሉያ!

Love by sharing
ቴሌግራም ለመቀላቀል t.me/Lovedface

እወዳችኋለሁ አከብራችኋለሁ, አማኑኤል ከበደ(@emanuellf) ከLovedface

ከእግዚአብሔር ጋር ጥልቅ ፍቅር ዲቮሽናል በየእለቱ

በየእለቱ አማርኛና እንግሊዝኛ ዲቮሽናል ቪዲዮዎች በዩቱዩብና ፌስቡክ እንዲሁም የፅሁፍ ዲቮሽናል በፌስቡክና
ቴሌግራም

You might also like