You are on page 1of 4

ምስጢረ ሥጋዌ: ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው!

Posted on November 2, 2018 by Astemhro Ze Tewahdo

ምስጢረ ሥጋዌ (Mystery of incarnation) “ቃል ስጋ ሆነ… በእኛም አደረ” በሚለዉ የወንጌል ቃል ላይ የተመሰረተ ታላቅ የክርስትና ሃይማኖት ምስጢር ነዉ (ዮሐ 1፥14)። ይህ ምስጢር አምላካችን የእግዚአብሔር
ልጅ፣ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል በሥጋ በመወለዱ (ሰው በመሆኑ) አምላክ ሰው የሆነበት፣ ሰው አምላክ የሆነበት ልዩ ምስጢር ነው፡፡ የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት
ከመጣበት ሞት የዳነበት ምስጢር ነው፡፡ በተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን ‹‹ተዋሕዶ›› የሚለውን ስያሜ ያገኘችበት እኛም “ክርስቲያን” የተባልንበት ምስጢር ነው፡፡ ሰማያዊው “ነገረ እግዚአብሔር” ለሰው ልጅ የተገለጠው
በዚህ ምስጢር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ምስጢረ ሥጋዌ ታላቅነት ሲናገር “የተነገረውን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ፣ ይህንን ለመላእክት
አላደረገውምና፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 62፡4)

የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት


ወልደ እግዚአብሔር፣ ወልደ ማርያም (የእግዚአብሔር አብ ልጅ፣ የድንግል ማርያም ልጅ) ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት፡፡ የመጀመሪያው (ቀዳማዊ) ልደት ዘመን ከመቆጠሩ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሔር
ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ከሰው አእምሮ በላይ በሆነ ምሥጢር (አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ) የተወለደው ልደት ነው (መዝ 2፥7 መዝ 109፥3 ምሳ 8፥25)፡፡ ሁለተኛው (ደኀራዊ) ልደቱ ደግሞ ዓለም ከተፈጠረ
አዳም ከበደለ ከአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ የተወለደው ልደት ነው (ገላ 4፥4 ኢሳ 7፥14 ኢሳ 9፥6 ዘፍ 3፥15 ፤18፥13 ፤ 12፥8 ፣ መዝ 106፥20)፡፡ ዘመን የማይቆጠረለት፣
በቅድምና ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረ፣ ዓለምንም በአምላክነቱ የፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አካላዊ ቃል መለኮታዊ አካሉን፣ መለኮታዊ ባሕርይውን ሳይለቅ በተለየ አካሉ ንጽሕት፣ የባሕርያችን መመኪያ ከምትሆን
ከድንግል ማርያም በሥጋ በተወለደ ጊዜ አምላካዊ አካልና ባሕርይን ከሰው አካልና ባሕርይ ጋር ያለመጠፋፋት፣ ያለመቀላቀል ተዋሐደ እንጅ አካሉም ባሕርይውም አልተለወጠም፡፡

ሊቁ አባታችን ቅዱስ ፊሊክስ የጌታችንን ቀዳማዊና ደኀራዊ ልደቱን በተናገረበት አንቀጽ “ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው በኋላ ዘመን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ያደረ እርሱ ነው፤
እርሱ ሰውም ቢሆን አንድ አካል፣ አንድ ገፅ፣ አንድ ባሕርይ ነው” በማለት ሁለቱን ልደታት አስተምሯል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ፊሊክስ 38፡10 በተጨማሪም ቅዱስ ናጣሊስ “ከእግዚአብሔር አብ በተወለደው በቀዳማዊ
ልደቱ የእግዚአብሔር አብ ልጅ ነው፤ ከድንግል በተወለደው በደኃራዊ ልደቱ የሰው ልጅ ሆነ፡፡ እርሱ አንዱ በመለኮት ከአብ ጋር አንድ የሚሆን የሚተካከል ፍጹም አምላክ ነው፤ እርሱ ብቻ ከድንግል በተወለደው ልደት በሥጋ
ከሰው ጋር አንድ የሚሆን ፍጹም ሰው ነው፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ናጣሊስ 46፡3-4)

አምላክ ለምን ሰው ሆነ?


ምስጢረ ሥጋዌ አምላክ ሰው የሆነበት ሰውም አምላክ የሆነበት ምስጢር ነው ስንል ‹‹አምላክ ለምን ሰው ሆነ?›› የሚለውን በመጻሕፍት ማስረጃነት መዳሰስ ያሻል፡፡ የእግዚአብሔርን ዕቅድ በሙሉ መርምሮ የሚያውቅ
ባይኖርም በቅዱሳት መጻሕፍት በተገለጠውና በሊቃውንት አስተምህሮ በተተነተነው መሠረት አምላክ ሰው የሆነባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ቤዛ ለመሆን (ኢሳ 64፥6 ኢሳ 53፥5 ዕብ 9፥26 ዮሐ 10፥15-18)
(‹‹የወደቁትን ያነሳ ዘንድ፣ በክብር ከፍ ያደርገን ዘንድ››)፣ አርአያ ለመሆን (ዘፍ 3፥12 4፥8 13፥3፣ መዝ 61፥4 ማቴ 11:29 2ኛ ጴጥ 2፥21)፣ ፍቅሩን ለመግለጥ (ሆሴ 14፥4) (ዮሐ 3፥16) (1ኛ ዮሐ 4፥19፣ ሮሜ 5፥8፣ ኤፌ
2፥4)፣ አምላክ መኖሩን ለመግለጽ (ሮሜ 1:19-20 ዮሐ 14:8-9 ዮሐ 1:18)፣ የሰይጣንን ጥበብ ለመሻር (ዕብ 2:9;14;15) እና እነዚህን የሚመስሉት ናቸው፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ አምላክ ለምን ሰው መሆን እንዳስፈለገው ሲያስረዳ “ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፤ ከሕይወት የተገኘ ሕይወት፤ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን ወደዚህ ዓለም የላከው ከእመቤታችን ከቅድስት
ድንግል ማርያም የእኛን ባሕርይ ይዋሐድ ዘንድ ጌትነቱንም ወደማወቅ ያደርሰን ዘንድ ነው፡፡” ብሏል፡፡ ዮሐ. 6፡55፣ ዮሐ. 11፡25፣ ገላ. 4፡4፣ ኤፌ. 2፡16፣ ሐዋ. 4፡12 (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ 15፡2)
ቅዱስ እለእስክንድሮስም “እግዚአብሔር ቃል ወደዚህ ዓለም ይመጣ ዘንድ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ሥጋን ይዋሐድ ዘንድ ምን አተጋው? በጨርቅ ይጠቀለል ዘንድ፣ በበረት ይጣል ዘንድ፣ ከሴት (ከድንግል) ጡት ወተትን
ይተባ ዘንድ፣ በዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ምን አተጋው? ሕግ አፍራሽ ጲላጦስ ይዘብትበት ዘንድ፣ በመስቀል ይሰቀል ዘንድ፣ በመቃብር ይቀበር ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ይነሣ ዘንድ ምን አተጋው? በፍዳ ተይዘን የነበርን እኛን
ያድነን ዘንድ፣ ለእኛ ብሎ አይደለምን?” በማለት አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት በአንክሮ ገልጾታል፡፡ ኢሳ. 7፡14፣ ፊልጵ. 2፡5-9፣ 1ኛ ቆሮ. 1፡21-25 (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ እለእስክንድሮስ 16፡2-3)

አምላክ እንዴት ሰው ሆነ?


ቅድመ ተዋሕዶ (ከተዋሕዶ በፊት) ሁለት ባሕርያት ሁለት አካላት ነበሩ፡፡ እነዚህም መለኮትና ትስብዕት (ሰው) ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ ፈጣሪ፣ በባሕርይ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ
ወልድ ሲሆን በሁሉም ቦታ ያለ፣ ዘላለማዊ፣ ከሁሉ በላይ የሆነ፣ ሁሉን የሚያውቅ፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል፣ ሁሉን የፈጠረ ነው፡፡ በአንጻሩ ትስብዕት (ሰው) ደግሞ አራት ባሕርያተ ሥጋ (ከአፈር፣ ከነፋስ፣ ከእሳትና ከውኃ
የተሠራ) እና ሦስት ባሕርያተ ነፍስ (ልባዊት፣ ነባቢት፣ ሕያዊት) ያለችው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሲሆን ውሱን፣ የሚደክም፣ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚታመም፣ የሚያንቀላፋ፣ የሚሞት ነው፡፡
ተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የመሆን ምስጢር ነው፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል ሲባል ረቂቅ መለኮት ርቀቱን ሳይለቅ፣ ግዙፍ ሥጋ ግዙፍነቱን ሳይለቅ ማለትም ግዙፍ ሥጋ ረቂቅ
መለኮትን ግዙፍ ሳያደርገው፣ ረቂቅ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ሳያረቀው በመጠባበቅ (በተዐቅቦ) ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ማለት ደግሞ መለኮት የእርሱ ያልሆነውን የሥጋ ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ፣
ሥጋም የእርሱ ያልሆነውን የመለኮት ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ቅዱስ ቴዎዶስዮስ “ከተዋሕዶ በኋላስ ሁለት ባሕርይ አንልም፤ እንደ ንጹሐን አባቶቻችን ክርስቶስ (መለኮትና ትስብእት) በአንድ
አካል ሁለተኛ የሌለው አንድ እንደሆነ እንናገራለን እንጂ፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶስዮስ 82፡37) ቅዱስ ቄርሎስም “የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ” በማለት አንድ አካል አንድ
ባህርይ መሆኑን ተናግሯል፡፡

አምላክ ሰው የሆነው ያለመለወጥ (ዘእንበለ ውላጤ) ነው፡፡ ይህም በቃና ገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅ እንደተለወጠው ሳይሆን የመለኮትነቱ አካል፣ ባሕርይ ወደ ትስብዕት አካል፣ ባሕርይ ሳይለወጥ፣ የትስብዕትም አካል፣
ባሕርይ ወደ መለኮትነት ሳይለወጥ ነው በተዋሕዶ አምላክ ሰው፣ ሰውም አምላክ የሆነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ አምላክ መለወጥ የሌለበት መሆኑን ሲናገር “ሁሉን የፈጠረ ነው፤ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ፤ ሰውም
ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ እግዚአብሔር ቃል ነውና እርሱ መቸም መች አንድ ነው፤ የመለኮቱ ባሕርይ ወደ ሰውነቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤ የሰውነቱ ባሕርይም ወደ መለኮቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤
ደንግል ማርያም አንድ አካል ሆኖ ወለደችው እንጂ፤ ሰብአ ሰገልም አንድ ባሕርይ ሁኖ ሰገዱለት እንጂ፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ 60፡17)

የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ያለመመለስ (እንበለ ሚጠት) ነው፡፡ የሙሴ በትር እባብ ከሆነች በኋላ ተመልሳ በትር እንደሆነችው መመለስ (ሚጠት) የሌለበት ነው፡፡ ምስጢረ ተዋሕዶ የተፈጸመው ያለመቀላቀል (ዘእንበለ
ቱሳሔ) ነው፡፡ ይህም ወተትና ውኃ ሲቀላቀሉ ሌላ ሦስተኛ መልክ ያለው ነገር እንደሚሰጡት ሳይሆን መለኮትና ትስብዕት የተዋሐዱት በመጠባበቅ (በተዐቅቦ) ነው፡፡ ቅዱስ ሳዊሮስ ስለተዋሕዶ ምስጢር ሲናገር
“የምናምንባት ሃይማኖት ይህች ናት፤ መስሎ በመታየት በሐሰት አልተወለደም፤ ባሕርይን እውነት በሚያደርግ በከዊን ነው እንጂ፤ ይኸውም በተዋሕዶ እግዚአብሔርም ሰውም መሆን ነው፤ እርሱ ሰው የሆነ አምላክ
ነውና፡፡” በማለት አስረድቷል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ሳዊሮስ 84፡13)

የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ ያለማደር (ዘእንበለ ኅድረት) ነው፡፡ ሰይፍ በሰገባው፣ ዳዊትም በማኅደሩ እንደሚያድር መለኮትም በሥጋ ላይ አደረበት የሚል የንስጥሮስ ክህደት በተዋሕዶ ዘንድ የተወገዘ ነው፡፡ የመለኮትና
የትስብዕት ተዋሕዶ ልብስ በልብስ ላይ እንደሚደረበው ወይም እንጀራ በእንጀራ ላይ እንዲሚደራረበው ሳይሆን ያለመደራረብ (ዘእንበለት ትድምርት) ነው፡፡ የተዋሕዶ ምስጢር ሥጋና ነፍስ ተዋሕደው ኖረው በሞት ሰዓት
እንደሚለያዩትም ሳይሆን ያለመለያየት (ዘእንበለ ፍልጠት) ነው፡፡ ስለዚህም ነገር ሊቁ ቅዱስ አዮክንድዮስ “ሥጋ በሠራው ሥራ ሁሉ መለኮት አንዲት ሰዓት ስንኳን በማናቸውም ሥራ ከእርሱ እንዳልተለየ እናምናለን፤ ጌታችን
መድኃኒታችን ሰው በሆነ ጊዜ መለኮቱን ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ አንድ እንደ አደረገ እናምናለን፡፡ መለኮትም ከትስብእት ጋር ከተዋሐደ በኋላ ከሥራ በማናቸውም ሥራ አንድነታቸው ፈጽሞ አልተለየም፤ መለየት የለባቸውምና፤
ለመለኮት ጥንት እንደሌለው ከትንሣኤው በኋላ ለትስብእትም እንዲሁ ፍጻሜ የለውም፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ (ዕብ. 13፡8) )ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አዮክንድዮስ 44፡4-5)

የመለኮትና የትስብዕት ተዋሕዶ እንጨትና ዛቢያው (መቁረጫው) ተዋደው በኋላ እንደሚነጣጠሉትም ሳይሆን ያለመነጣጠል (ዘእንበለ ቡዐዴ) ነው፡፡ በዚህም አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር እጅግ ድንቅ ነው፤ ዓለምን
ከፈጠረበት ምስጢርም ይበልጣል ይላሉ ሊቃውንት፡፡ አምላክ በተዋሕዶ ሰው ስለሆነበት ምስጢር ቅዱስ መጠሊጎን ሲናገር “የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ዋሕድ ነፍስን ሥጋን ነስቶ ሰው ሆነ ባልን ጊዜም ስለዚህም ነገር ቢሆን
እነዚያ እንደሚያምኑ መቀላቀል የለበትም፤ የቃል ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ወደመሆን የሥጋ ባሕርይም የቃል ባሕርይን ወደመሆን አልተለወጠም፤ ሁለቱ ባሕርያት ያለመለዋወጥ ባለመቀላቀል ጸንተው ይኖራሉ እንጂ”
በማለት አረጋግጦልናል፡፡ (ዮሐ. 1፡1-18፣ ዮሐ. 3፡18፣ 1ኛ ቆሮ. 8፡6) (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ መጠሊጎን 43፡6)

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው!


በተዋሕዶ የከበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡ ፍጹም አምላክነቱ አምላካዊ መስዋእትን ሲቀበል (ሉቃ. 2፡11)፣ ወጀቡን ጸጥ ሲያደርግ (ማቴ 8፡ 23)፣ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን ሲፈጥር (ዮሐ
9፡6)፣ ኃጢአትን በስልጣኑ ሲያስተሰርይ (ማር. 2፡5)፣ በተዘጉ ደጆች ሲገባ (ዮሐ 20፡26)፣ ውኃውን ወይን ጠጅ ሲያደርግ (ዮሐ 2፡1-11)፣ እንዲሁም በአብና በመንፈስ ቅዱስ፣ በመላእክት እና በሰዎች ምስክርነት (ማቴ. 3፡
16-17፣ ማቴ. 17፡5፣ ሉቃ 2፡11 ኢሳ 9፡6 ማቴ 2፡11) ታውቋል፡፡በእነዚህና በመሳሰሉትም ጌታችን እኛን ያከብረን ዘንድ ሰው ሆነ እንጂ ከአምላክነቱ ያልተለየ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ምስጢር ዘቅዱስ ቴዎፍሎስ “ሰው
ሆኖ ከድንግል ተወለደ፤ ከኃጢአት በቀር የኛን ሥራ ሁሉ በመሥራት መሰለን፤ ልዩ ድንቅ በሆነ ባሕርይ ሰው በሆነ ጊዜ በመታየቱ የሰውን ባሕርይ አከበረ፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎፍሎስ 69፡7)

ፍጹም ሰው መሆኑም እንዲሁ በግዕዘ ሕፃናት ሲወለድ (ማቴ. 2፡11)፣ በታንኳ ውስጥ ተኝቶ ሲያንቀላፋ (ማቴ 8፡23)፣ ምራቁን ወደ መሬት እንትፍ ሲል (ዮሐ 9፡6)፣ ሠርግ ቤት ተጠርቶ ሲሄድ (ዮሐ 2፡1)፣ በአጭር ቁመት፣
በጠባብ ደረት ተወስኖ በአንዲት ቤት ሲታይ (ማር. 2፡1)፣ ከትንሣኤ በኋላ ሲመገብ (ሉቃ 24፡42) እና በመሳሰሉት ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰው የሆነ አምላክ›› መሆኑን እናምናለን፣ እናውቃለንም፡፡ ቅዱስ
ኤፍሬም ሶርያዊ ይህንን ድንቅ ምስጢር “ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ፣ ቀዳማዊ ሆነ፤ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፤ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፤ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው
ሆነ፡፡” በማለት ገልጾታል፡፡ (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም)

ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው!


ቅዱሳት መጻህፍት በተዋሕዶ የከበረው ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የባሕርይ አምላክ መሆኑን ያረጋግጡልናል፡፡ ለምሳሌም ያህል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
“እርሱ ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው” (ሮሜ 9፡5) ብሎ ፍጹም አምላክነቱን ሲመሰክር ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ ደግሞ “እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው”
(1ኛ ዮሐ 5:20) በማለት የባህርይ አምላክነቱን አረጋግጦልናል፡፡ ትንሣኤውን ተጠራጥሮ የነበረው ቶማስም “ጌታዬ አምላኬም” ሲል መስክሮ (ዮሐ 20:28) የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ተናግሯል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም
በራዕዩ “ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ይላል” (ራዕ 1:8) በማለት ጌታችን “እኔ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” (ማቴ 22: 31) ያለውን አጠናክሮ አስፍሮታል፡፡
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጌታችንን ያለመለየት፣ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው የሆነ የባሕርይ አምላክ እንደሆነ ሲያስረዳ “የባሕርይ አምላክ እንደሆነ ቢነገርም በእውነት ሰው ሆኗል፤ አምላክ እንደመሆኑም ያውቀው ዘንድ የሚቻለው
ሰው የለም፤ ስለዚህም አብሲዳማኮስ ተባለ፤ ይኸውም ከሁለት አንድ የሆነ ማለት ነው፤ እርሱ አምላክ ነው፤ ሰው ነው” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ 54፡21)

የተዋሕዶን ምስጢር በምን እንመስለዋለን?


የተዋሕዶን ነገር ጠንቅቀው የሚገልጹ ምሳሌዎች ባይገኙም ምስጢሩን ለሰዎች ለማስረዳት ያህል አባቶቻችን ያስተማሩንን ፍጹም ያልሆኑ ምሳሌዎች (ምሳሌ ዘየሐፅፅ፣ ከሚመሰልለት የሚያንስ ምሳሌ) እንጠቀማለን፡፡
የተዋሕዶ ምስጢር ከምሳሌዎች በላይ መሆኑን ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሲናገር “ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደ ሆነ፣ ከቅድስት ድንግልም መወለዱ እንዴት እንደ ሆነ አትጠይቀኝ፤ እርሱ በባሕርይው ከአብ
ተወልዶዋልና፤ ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ተወልዶዋልና አምላክ ነው፤ ሰውም ነው” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶጦስ 53፡16) ቅዱስ ኤፍሬምም “ከሕሊናት ሁሉ ለራቀ ለዚህ ድንቅ ምሥጢር
አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው፣ ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ፤ ከእርሷም እርሱ ፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤፍሬም 47፡2)
በማለት እንደተናገረው የተዋሕዶ ነገር ከምሳሌዎች በላይ እጅግ ድንቅ ነው፡፡እነዚህም ምሳሌዎች ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሥነ ፍጥረት የተገኙ ናቸው፡፡

ሙሴ ባያት ዕፀ ጳጦስ:- ሐመልማሉ የትስብእት ምሳሌ ነበልባሉ የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው ሐመልማሉ ነበልባሉን ሳያጠፋው በአንድነት ታይተዋል (ዘፀ 3:2)፡፡ አንዱ አንዱን ሳያጠፋ
እንደታዩ ሥጋ ከመለኮት ጋር ሳይጠፋፉ አንድ የመሆናቸው ምሳሌ ነው፡፡

በኢሳይያስ ፍሕም: ምሳሌነት ደግሞ እሳት የመለኮት ከሰል የሥጋ ምሳሌ ናቸው፡፡ እሳቱ ተለውጦ ከሰል ፤ ከሰሉ ተለውጦ እሳት አልሆነም፡፡ ሁለቱም ከሰል ከሰልነቱን እሳትም እሳትነቱን ሳይለቅ ተዋሕደው ፍሕም ሆነዋል
(ኢሳ 6:6)፡፡

የጋለ ብረት ምሳሌነት፡- አንድን ብረት ከእሳት ባስገቡት ጊዜ ብረትነቱን ሳይለቅ እሳቱም እሳትነቱን ሳይለቅ በብረቱ ቅርፅ ልክ እሳት ይሆናል፡፡ ይህንንም እሳትና ብረቱ ስለተዋሐዱ የጋለ ብረት ብለን እንጠራዋለን እንጂ ብረት
ወይም እሳት ብቻ ብለን አንጠራውም፡፡ ይሁንና ብረት እሳት ሲነካው በቀላሉ ስለሚቀጠቀጥ ይህ “ምሳሌ ዘየሐፅፅ” ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ስለዚህ ምሳሌ ሲናገር “በእግዚአብሔር ቃል በረቂቅ ባሕርይ የሆነውን ተዋሕዶ
አንካድ፤ ብረት ከእሳት በተዋሐደ ጊዜ ከእሳትም በመዋሐዱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ እንዲያደርግ፤ ብረት በመዶሻ በተመታ ጊዜ ከእሳት ጋር በአንድነት እንደሚመታ ግን ከመዶሻው የተነሣ የእሳት ባሕርይ በምንም በምን
እንዳይጎዳ ሰው የሆነ አምላክ ቃል በመለኮቱ ሕማም ሳይኖርበት በሥጋ እንደታመመ እንዲህ እናስተውል፡፡” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ 73፡12)
የሰው ነፍስና ሥጋ ውሕደት ምሳሌ፡- የሰው ልጅ ከእናቱ ማሕፀን ሥጋና ነፍስን ነስቶ ፅንስ ከሆነበት ቀን ጀምሮ ይህ ነፍስ ነው ይህ ሥጋ ነው ብሎ መለያየት እንደማይቻል ሁሉ ሥጋና መለኮትም ከተዋሕዶ በኋላ ይህ ሥጋ
ነው ይህ መለኮት ነው፤ ይህ ሥጋዊ ሥራ ነው ይህ መለኮታዊ ሥራ ነው ተብሎ መክፈል አይቻልም፡፡ ነገር ግን ነፍስና ሥጋ በሞት ስለሚለያዩ ይህም “ምሳሌ ዘየሐፅፅ” ነው፡፡

የወልደ እግዚአብሔር የተዋሕዶ ስሞች


የእግዚአብሔር ወልድ የተዋሕዶ ዋና ዋና ስሞች የሚባሉት አማኑኤል፣ ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ናቸው፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ከእኛ
ጋር ስለኖረ የወጣለት ስም ነው (ኢሳ 7፡14 ማቴ 1፡23)፡፡ ኢየሱስ ማለት ደግሞ መድኀኒት ማለት ነው፡፡ ደቂቀ አዳምን ሊያድን ሰው ሁኗልና ከእግዚአብሔርም በቀር መድኀኒት ሆኖ ዓለምን ሊያድን የሚችል የለምና (ኢሳ
45:20-24፤ሆሴ 13:4፤ቲቶ 1:3)፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ ማለት መሲህ፣ የተቀባ፣ ሹም፣ የተሾመ፣ ባለስልጣን ማለት ነው፡፡ የተቀባ የተሾመ ሲባል ግን ለእርሱ ቀቢ ሿሚ ኖሮት አይደለም ቀቢውም ሿሚውም ተቀቢውም
ተሿሚውም አንድ እርሱ ነው እንጂ (ዮሐ 4:25-30)፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለክርስቶስ ሲናገር “ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጡር አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የነበረ
ለዘላለሙ የሚኖር፤ ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነውና ስለርሱ ስንናገር ያልተፈጠረ ነው እንላለን፡፡ (መዝ. 102(101)፡ 25-27፣ ዕብ. 1፡1-14) ሰው ነው ያልነውም ስለ እኛ ባደረገው ተዋሕዶ ደካማ ባሕርያችንን ስለተዋሐደ
ነው” ብሏል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ 35፡2-3)

በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የተነሱ የኑፋቄ ትምህርቶች


በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ እጅግ ብዙ የኑፋቄ ትምህርቶች አሉ፡፡ እነዚህም ከጥንት ዘመን ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ መልካቸውን የሚለዋውጡ ናቸው፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢየሱስ “ሰው ብቻ ነው”
ብለው አምላክነቱን የካዱ፣ መለኮትነት የለውም፣ ሰው ብቻ ነው የሚሉ መናፍቃን ነበሩ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ “መለኮት ብቻ ነው” ብለው ሰውነቱን (ሰው መሆኑን) የካዱና ሰው መስሎ በተአምራት ተገለጠ የሚሉ
(ግኖስቲክስ) ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በእውነት ሰው የሆነ አምላክ ነው፤ ከሥጋዌ (ሰው ከመሆን) በኋላም መለኮት ከሥጋ ለቅጽበተ ዓይን እንኳ የተለየበት ጊዜ የለም፡፡ ጌታችን በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት
የአምልኮ ስግደትና ያቀረቡለት መብዓ ፍጹም አምላክነቱን ያሳየናል፡፡ ፍፁም አምላክ እንደመሆኑ ስግደትን፣ አምሐን ተቀበለ፤ ፍፁም ሰው እንደመሆኑም “ሕፃን” ተባለ፡፡ (ማቴ. 2፡9-11)

ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ የተነሱ “ልጅነት ተሰጠው” የሚል አስተሳሰብ ይዘው እርሱ ሲወለድ ሰው ብቻ ነበር፣ በጥምቀት ወቅት መለኮት አደረበት የሚል የስህተት ትምህርት ያስተማሩ መናፍቃንም ነበሩ፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በሥጋ ማርያም ሲወለድም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ መሆኑን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሰረበት አንቀጽ አስተምሮናል፡፡ (ሉቃ. 2፡32)
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘምን የተነሳው አቡሊናርዮስ ኢየሱስ ክርስቶስ “በሥጋ ሰው በነፍስ መለኮት” ነው በማለት አእምሮው መለኮት ነው የሚል የስህተት ትምህርት ሲያስተምር በቅርብ ዘመን የተነሳው ቶማሲየስ ደግሞ
“ሰው ለመሆን ሲል መለኮቱን ወሰነው/ተወው” የሚል ስህተትን ካስተማሩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በቤተክርስቲያን ታሪክ በምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ኑፋቄን ያስተማረው በቁስጥንጥንያ ጉባዔ የተወገዘው ንስጥሮስ ነው፡፡ ንስጥሮስ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ባህርይ ሁለት አካል ነው” በማለት የኅድረት
ኑፋቄን ሲያስፋፋ ነበር፡፡ ማርያም የወለደችው ሰው ነው፣ መለኮት አደረበት ብሎ ኅድረትን ያስተማረ እርሱ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን በወንጌሉ “ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” (ዮሐ. 1፡14) እንዳለ በስጋ ማርያም በተጸነሰ ጊዜም
ከአምላክነቱ ሳይለይ በእኛ ማደሩን መስክሮልናል፡፡ ቅዱስ አቡሊዲስ የኅድረት ትምህርት የተወገዘ መሆኑን ሲናገር “ክርስቶስ አምላክ ያደረበት ሰው እንደሆነ የሚናገር ቢኖር የተወገዘ ይሁን፤ አምልኮተ እግዚአብሔርን የዘነጋ ያ
ሰው የባሕርይ ገዥ ክርስቶስን ከተገዦች እንደ አንዱ አደረገው፡፡” ብሏል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አቡሊዲስ 42፡19 በዚያው ወቅት የተነሳው አውጣኪ ደግሞ “አንድ (ሦስተኛ) ባህርይ (የሰውና የመለኮት ቅልቅል)” የሚል
ፍልስፍናን ይዞ ብቅ አለ፡፡ አውጣኪ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋም ከመለኮትም የተለየ (የሁለቱ ቅልቅል) ሦስተኛ ባህርይ ያዘ” ሲል ክህደትን ሲያስተምር ነበር፡፡

ለቤተክርስቲያን ሁለት መከፈል ምክንያት የሆነው ግን “ሁለት ባህርይ አንድ አካል” የሚለው የኬልቄዶናውያን ምንፍቅና ነበር፡፡ ይህ ኑፋቄ ከንስጥሮስ ትምህርት “ሁለት ባህርይ” የሚለውን ሀሳብ የወሰደ፣ የምዕራባውያኑ
አስተምህሮ፣ ለቤተክርስቲያን ሁለት መከፈል ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በ451 ዓ.ም በሊዮ እና በንግስቲቱ አስተባባሪነት የተዘጋጀው ጉባዔ እውነተኞቹ አባቶች ላይ መከራ በማድረስ ይህንን ኑፋቄ ተቀብሎ ስለተጠናቀቀ
ቤተክርስቲያናችን አትቀበለውም፡፡ ስሙንም “ጉባዔ አብዳን” ወይም “ጉባዔ ከለባት” ብላ ትጠራዋለች፡፡ ከእነዚህ ኑፋቄዎች ተርታ የሚመደበው በኢትዮጵያ ያለው “ጸጋና ቅባት” የሚባለው ነው፡፡ ይህም አልፎንሶ ሜንዴዝ
የተባለ ፖርቹጋለዊ በሸዋ እና በጎጃም ላሉ “ካህናት” ያስተማረው ሲሆን “ኢየሱስ በእናቱ ማሕጸን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ በጸጋ አምላክነትን (ቅባቶች: የባሕሪይ አምላክነትን ይላሉ) አገኘ” ይላሉ:: ይህም ምስጢረ
ሥላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን የሚያፋልስ ክህደት ነው፡፡

የተዋሕዶ አስተምህሮስ ምንድን ነው?


ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ የሆነ ሥግው ቃል ነው ብላ ታምናለች፤ ታስተምራለች፡፡ መለኮት ከቅድስት ድንግል ማርያም
ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በሥጋ ተወለደ፤ መለኮትና ትስብዕት የተዋሐዱት ያለመለወጥ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመለያየት፣ ያለመነጣጠል ነው በማለት ቅዱስ ቄርሎስ እንዳስተማረው ታምናለች፡፡ ቅድመ ዓለም ከአብ
የተወለደው ወልድ ድኅረ ዓለም በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደ በማለት አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር ተዋሕዶ ነው ትላለች፡፡ ይህም የኦርየታል አብያተ ክርስቲያናት አስተምህሮ
ነው፡፡ ይህንን ምስጢር ያመሰጠሩት ሊቃውንት ምስጢረ ሥጋዌን በሃይማኖተ አበው በብዙ መልኩ ገልፀውታል፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን ማየት ይቻላል፡፡

ስለተዋሕዶ ነገር ቅዱስ አትናቴዎስ “አሁንም በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ ሰምተህ ዕወቅ፤ አምላክ ብቻ ከሆነማ እንደምን በታመመ ነበር? ወይስ እንደምን በሰቀሉት ነበር? ወይስ እንደምን በሞተ ነበር? ይህ ሥራ
(ሕማም፣ ሞት) ከእግዚአብሔር የራቀ ነውና (ዘዳግ. 32፡40-49)፡፡ ሰው ብቻ ከሆነ በታመመ በሞተ ጊዜ ሞትን እንደምን ድል በነሣው ነበር? ሌሎችንስ በነፍስ በሥጋ እንደምን ባዳነ ነበር? ይህ ከሰው ኀይል በላይ ነውና
(1ኛ ቆሮ. 5፡13፣ ዕብ. 5፡1-4) ፡፡ እርሱ ታሞ ሞቶ ፍጥረቱን አዳነ፣ ሞትንም ድል ነሳ፤ ሰው የሆነ አምላክ ነውና” በማለት አስተምሮናል፡፡ (ሉቃስ 24፡5፣ ዮሐ. 5፡26-27፣ ሮሜ. 8፡3-4) (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ
ሐዋርያዊ 27፡6-8)

ቅዱስ ኤራቅሊስም “እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንዲህ እናምናለን፡፡ መለየት መለወጥ የሌለበትን አንዱን ሁለት አንለውም፤ ሁለት ገዥ፣ ሁለት መልክ፣ ሁለት አካል፣ ሁለት ግብር፣ ሁለት ባሕርይ ነው አንለውም፤ እንደተናገርኩ
ሰው ሆነ እግዚአብሔር ቃል አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንጂ፡፡ ይህን ገልጠን እናስተምራለን፤ ቃልን ከሥጋ አንድ አድርገን አንዲት ስግደትን እንሰግድለታለን፡፡” በማለት የተዋሕዶ አስተምህሮ አንድ አካል አንድ ባህርይ
መሆኑን ገልጾታል (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ 48፡6-7)፡፡ ቅዱስ አፍሮንዮስም “እንግዲህ እንጠበቅ መለኮትንም ከሥጋ አንለይ፡፡…አንድ ጊዜ የጌትነቱን ነገር ይናገራል፤ አንድ ጊዜም የሕማሙን የሞቱን ነገር
ይናገራል፤ እግዚአብሔር ነውና የጌትነቱን ነገር ያስተምራል፤ የእግዚአብሔርም ቃል ነው፤ ሰውም እንደመሆኑ የሰውነቱን ነገር ይናገራል፤ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ፡፡” በማለት መለኮትና ትስብዕት ፍጹም መዋሐዳቸውን
አስተምሯል (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አፍሮንዮስ 51፡8-9)፡፡

አምላክ ሰው በመሆኑ ለመላእክትም ታያቸው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ስለዚህ ነገር ሲናገር “በስጋ ተወልዶ ለመላእክት ታያቸው፤ ሰው ሳይሆን አላዩትም ነበርና በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ተገባው ሰውንም ስለወደደ በምድር
ሰላም ሆነ አሉ፤ በአሕዛብም ዘንድ ተነገረ፤ በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ እንደሆነ ዓለም ሁሉ አመነበት፡፡ ብሏል፡፡ (ሉቃ. 2፡14፣ 1ኛ ጢሞ. 3፡16) ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቄርሎስ 79፡56 ቅዱስ ያዕቆብ
ዘሥሩግም “አገልጋይ ይሆን ዘንድ ወደ እዚህ ዓለም ከመጣ ከወልድ የተነሣ የአባቱ አገልጋዮች መላእክት እጅግ አደነቁ፤ በመለኮቱ ግን ማገልገል የለበትም፤ በወገቡ የታጠቀውን ማድረቂያ አይተው መላእክት አደነቁ፤ ስሙ
ከፀሐይና ከጨረቃ በፊት የነበረ እርሱ አገልጋይ ሆነ፡፡” በማለት የአምላክ ሰው መሆኑ በመላእክትም ዘንድ የተደነቀ መሆኑን ተናግሯል (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ 88፡9)፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ
ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ቅዱስ ዲዮናስዮስ እንደተናገረው “ሰው ከመሆኑ በፊት ሰው ከሆነም በኋላ ካንድ ወልድ በቀር የምናውቀው አይደለም፡፡” የሚል ነው፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዲዮናስዮስ 93፡2)

ምሥጢረ ሥጋዌ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርሰቶስ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል በተዋሕዶ መወለዱን የሚያስረዳ አምላካችን የሰይጣንን ተንኮል ያፈረሰበት የማይመረመር አምላካዊ
ጥበብ ነው፡፡ ጌታችን ሰው የሆነውም አባታችን አባ ሕርያቆስ “ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፤ ሳይወሰን ፀነስሽው፣ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማኅፀንሽ ተወሰነ” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 46) ብሎ
እንዳስተማረው ሰው ከመሆኑ የተነሳ ከአምላክነቱ ምንም ምን የጎደለበት የለም፤ ሰው ሲሆን በአምላክነት ወዳልነበረበት ዓለም የመጣ ሳይሆን እንደ አምላክነቱ በእቅፉ ወደተያዘች ዓለም የተጎሳቆለውን የሰውን ባሕርይ
በቸርነቱ ያከብር ዘንድ ከኃጢአት በቀር የሰውን ባሕርይ ተዋሕዶ ፍፁም ሰው ሆነ እንጂ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋዌውን ነገር በአግባቡ ያልተረዱ ብዙዎች ለእኛ ብሎ በፈቃዱ ያደረገው ቤዛነት “የመሰናከያ ዓለት”
ሆኖባቸው በክህደት ይኖራሉ፡፡ እኛ ግን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚመሰክሩት፣ አባቶቻችንም እንዳስተማሩን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ እናምናለን፣ እንመሰክራለንም፡፡ የወልድን ሥጋዌውን
ማመን የመዳናችን መሰረት ነውና፡፡

ወስብሃት ለእግዚአብሔር
This entry was posted in Uncategorized by Astemhro Ze Tewahdo. Bookmark the permalink [https://astemhro.com/2018/11/02/incarnation/] .

About Astemhro Ze Tewahdo


ይህ የጡመራ መድረክ (አስተምህሮ) የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡
View all posts by Astemhro Ze Tewahdo →

1 THOUGHT ON “ምስጢረ ሥጋዌ: ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው!”

Pingback: ምስጢረ ሥጋዌ: ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ ነው | ስምዓ ጽድቅ ሐዋርያዊ ኦርቶዶክስ ተሃድሶ

You might also like