You are on page 1of 4

ዕርገት: በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ

ዕርገት ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ “ዕርገት” የሚለው ቃል “ዐርገ”
ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ከታች ወደ ላይ መውጣት፣ ክፍ ከፍ ማለት፣ ማረግ ማለት ነው፡፡ ዕርገት
(Ascension) ሲባልም ማረግን፣ ከፍ ከፍ ማለትን፣ ወደ ላይ መውጣትን ያመለክታል፡፡ በዓለ ዕርገትም ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የነበረውን የማዳኑን ሥራ ጨርሶ ወደ ላይ መውጣቱና በቀደመ ክብሩ በአብ ቀኝ
መቀመጡ የሚከበርበት በዓል ነው፡፡ ለዚህም መሰረት እንዲሆን አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ የተሰበሰቡት ቅዱሳን አበው
“ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ…/ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ…” ብለው
ዕርገቱን በቅዱሳት መጻሕፍት ዋቢነት አስረግጠው ደንግገዋል፡፡

ዕርገቱ የትሕትና ሥራው የመፈጸሙ ምልክት ነው

አምላካችን ምሉእ በኩለሄ (ሁሉን የሞላ እና በሁሉም ቦታ የሚኖር) ነዉ። ስለዚህ ጌታችን በባሕርይው መውጣት መውረድ
የለበትም:: ወረደ ተወለደ ሲባል ፍጽም ሰው መሆኑን የትሕትና ሥራ መፈጸሙን ከመናገር ውጪ ከዙፋን ተለየ ማለት
እንዳልሆነ ሁሉ ዐረገ ወጣ ሲባልም ከሰማያዊዉ ዙፋኑ ተለይቶ ነበር ማለት አይደለም:: በምድር ላይ ሊሰራ ያለውን ሁሉ
መፈጸሙን ያመለክታል እንጂ:: እንዲሁም ጌታችን በዕርገቱ ምክንያት ከቤተክርስቲያን የተለየበት ጊዜ የለም። ነገር ግን ዕርገቱ
በሥጋዉ የተደረገዉን ዕርገቱን ያመለክታል። ይህም ዕርገት ቅዱስ ሥጋዉ በምድር የስበት ቁጥጥር (Gravitational force)
የማይዘው ለመሆኑ አስረጅ ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ አምላካዊ ስልጣኑን ያሳያል።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱ በምድር ላይ የሚሠራውን የትሕትና ሥራ የመፈጸሙ ምልክት ነው፡፡
ዕርገቱም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ/ በዕልልታና
በመለከት ድምፅ ላረገ ለአምላካችን፣ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና አቅርቡ (መዝ ፵፮፥፭፡፮)
እንዳለው በታላቅ ክብር እልልታና ምስጋና ነው፡፡ ጌታችን የድል ዕርገትን ያረገው ወደ ባሕርይ አባቱ ቀኝ ነው፡፡ በእርሱ ዕርገት
የጸጋ መንፈስ ቅዱስና የዳግም ምጽአት ተስፋዎች ተሰጥተውናል፡፡ የእርሱ ዕርገትም ለነፍሣችን ዕርገት /ለዕርገተ መንግሥተ
ሰማያት/ አርአያ ሆኖናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ክታቡ ይህንን ሲያስረዳ “ከዚያም
በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታችንን በአየር እንቀበለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን” (፩ተሰ. ፬፡፲፯)
ብሏል፡፡
እስከ ቢታንያም አወጣቸው
በዓለ ዕርገት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ከሚከበሩት በዓላት አንዱ
ነው፡፡ በዓሉ የሚውልበት ዕለት ሐሙስን (ከበዓለ ትንሣኤ አርባኛው ቀን) አይለቅም፤በዚህ መሠረት የዘንድሮው በዓለ ዕርገት
ግንቦት ፱ ቀን ፳፲ ዓም ይውላል ማለት ነው፡፡ የጌታችን ዕርገት ከትንሣኤ በኋላ በአርባኛው ቀን (በስድስተኛው ሐሙስ)
የሚከበረው ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ “ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር
እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው” (ሐዋ. ፩፡፫) በማለት የጻፈውን
መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም ይህንንትምሕርት ኪዳን ብላ ትጠራዋለች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶከተነሳ በኋላ ለሐዋርያት የነገራቸው መጽሐፈ ኪዳን ይባላል፡፡

ዕርገቱም የተፈጸመው ስለ ምጽአቱ ባስተማረበትና ዳግም ይመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት በደብረ ዘይት ተራራ ነበር፡፡
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ይህንን “እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ
ወደ ሰማይም ዐረገ” (ሉቃ ፳፬፡፶) ብሎ በወንጌሉ እንዲሁም “በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም
ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው” ብሎ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፩፡፩፪ አስፍሮታል፡፡

በልደቱና በትንሣኤው የተገኙትና ለሰው ልጆች መልካሙን ዜና ያበሰሩት ቅዱሳን መላእክት በዕርገቱም ተገኝተው ለአስራ
አንዱ ሐዋርያት የዳግም ምጽአቱን ነገር አሳስበዋቸዋል፡፡ ቅዱስ ሉቃሰ ይህንን ሲገልጽ “እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር
ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥
ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ
እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው ” (ሐዋ ፩፡፲-፲፩) ብሏል። ቅዱስ ዮሐንስም እንደተናገረው እርሱ ዳግም ሲመጣ
ሐዋርያቱ ብቻ ያይደለ የወጉት ጭምር ያዩታል (ራዕ ፩፡፯)፡፡

ሐዋርያቱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ

የጌታችን ዕርገት በመርቀቅ /በርቀት/ ሳይሆን ቀስ በቀስ ሐዋርያት እያዩት በመራቅ /በርኅቀት/ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህንን
ሲያስረዳ “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው ” (ሐዋ ፩፡፱)
በማለት ገልፆታል፡፡ ይህም የሚያመለክተው የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ይዞት እንዳረገ ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ
በቅዳሴው “በአካል ወደ ሰማይ ባረግህበት ዕርገትህ ላይ” እንዳለው በአካል ነው ወደ ሰማይ ያረገው። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅም በቅዳሴው “በዚያች ሥጋ በመለኮት ኃይል ወደ ሰማይ ወደ ቀድሞ አኗኗሩ ዐረገ” ያለው ይህንን ለማመልከት
ነው፡፡ ይህንን ሲያብራራ “ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሔደ፣ ዛሬ
ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፡፡ ሥጋው አልተለወጠምና” በማለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሞቱና ከትንሣኤው አስቀድሞ በውኃ ላይ እንደተራመደ ሁሉ፣ በለበሰው ሥጋ ወደ ሰማይ ማረግም እንደሚቻለው
አስረድቷል /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ክፍል ፲፫ ምዕ.፥፹፯፡፲፪-፲፫/፡፡ ቅዱስ ሉቃስም “እያዩት ከፍ ከፍ አለ”
ማለቱ በእርግጥ ዕርገቱ በአካል እንደነበር ያስረግጥልናል፤ ምክንያቱም ሰው መለኮትን መመልከት አይችልምና ።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ስለ ጌታችን ዕርገት “በደብረ ዘይት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲመገብ እጁን በደቀ መዛሙርቱ ላይ
አኖረ፤ እያንዳንዳቸውንም ባረካቸው ከዚያም የእሳት ደመና ተቀበለው፤ ከእነርሱም ሰወረው፤ በጨርቅ የጠቀለሉት ይህ ሥጋ
በኪሩቤል ክንፎች ተጋረደ፤ በጒልበት ያቀፉት ይህ ሥጋ በእሳት ሠረገላ ተቀመጠ፤ በዚህ ዓለም የተራበና የተጠማ ይህ ሥጋ
እህል መብላት፤ ወይን መጠጥን ውሃም መጠጣት ወደ ማይሻበት ወደ አርያም ከፍታ ወጣ፤ በሊቀ ካህናቱ አገልጋዮችና
በጲላጦስ አደባባይ ራቁቱን የቆመ ይህ ሥጋ በምስጋና መብረቅ ተሸፈነ፤ በእሳት ደመናም ተጋረደ፤ ጉንጮቹን በጥፊ የተመታ
ይህ ሥጋ ከፍ ከፍ አለ” ብሏል፡፡

ቅዱስ ማርቆስ የጌታችንን ዕርገት በገለጸበት አንቀጽ “ጌታችን ኢየሱስም ከተነጋገራቸዉ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፥ በአባቱም
በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡” (ማር. ፲፮፡፲፱) ብሏል፡፡ “ወደ ሰማይ” የሚለው ቃል ወደ ሰማየ ሰማያት ማለት ነው ።
ይህም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሚሠራበት ወቅት በጸለየው ጸሎት ውስጥ እግዚአብሔርን “በውኑ
እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤
ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!” (፩ኛ ነገ. ፰፡፪፯) ብሎ በጸለየው ይታወቃል። “ዐረገ” የሚለውም ( መላእክት
አሳረጉት አላለም) በራሱ ኃይል ሥልጣንና ማረጉን ያሳያል፡፡ ከጌታችን በቀር በራሱ ኃይል ያረገ የለም። ሌሎች ቅዱሳን፡
ለምሳሌ ኤልያስ እና ሄኖክም ቢሆኑ እግዚአብሔር ዐሳረጋቸው እንጂ በራሳቸው ስልጣን ዐላረጉም።
ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ይህንን “የእግዚአብሔር ልጅ ግን ያለ መሰላል በሚንቦገቦግ የደመና ተን (ጉም)
ዐረገ፤ መለኮቱ ይተጋለታልና ወደ አየራትም ነጥቆታልና፤ ነገደ መናብርት ሊያሳርጉት አልመጡም ርሱ ራሱ በመለኮቱ ኀይል
አብን ተካክሎ በቀኝ በኩል ተቀመጠባቸው” ሲል ገልጾታል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም ስለ ዕርገት በተናገረበት አንቀጽ
“በራሱ ሥልጣን ተነሣ፤ ርሱን ያስነሣው ማንም አይደለም፤ በሚያርግም ጊዜ ማንም ርሱን ያሳረገ አይደለም፤ ኤልያስን
አስመልክቶ ዕርገቱ በጌታ አማካይነት የኾነ ነውና እንዲያርግ ያደረገው ጌታ ነው፤ ከዚኽም የተነሣ በሠረገላ እና በእሳት ፈረስ
የከበረ ሥነ ሥርዐት ተደረገለት (፪ኛ ነገ ፪፥፲፩)፤ ምክንያቱም ወደ ዐረገበት ቦታ በራሱ ማረግ አይቻለውምና፤ የጌታችን ግን
እንደተጻፈው ተለየ፤ ወደ ላይ ለመነሣት ምንም ዐይነት መንኰራኲር አላስፈለገውም፤ በአንድ ቦታ በተወሰነ ጊዜ የሚቀመጡት
ሰው በአጋዥ መውጣት ያስፈልገዋል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ብቻ ነውና፤ የእግዚአብሔር ልጅ ግን ራሱ እግዚአብሔር ነውና
መንኰራኲር አያስፈልገውም” በማለት የእርሱ ዕርገት በራሱ ስልጣን መሆኑን አብራርቶታል፡፡

በአብ ቀኝ ተቀመጠ

ጌታችን በዕርገቱ “በኣብ ቀኝ ተቀመጠ” መባሉ ለእግዚኣብሔር ግራና ቀኝ ፥ታችና ላይ ኖሮበት ሳይሆን ወደ ቀደመ ክብሩ
መመለሱን በስልጣን እኩል መሆናቸዉን የሚያስረዳ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ፪፡፯ “ነገር ግን የባሪያን
መልክ ይዞ በሰዉም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። እንደ ሰዉም ሆኖ ራሱን አዋረደ” የሚለዉ ቃል ጌታችን በሥጋዌው
ራሱን በፈቃዱ ዝቅ አደረገ እንጅ በክብር ከአብ ከመንፈስቅዱስ እንደማይለይ ያስረዳናል፡፡ በቤተክርስቲያን አስተምህሮ
መሰረት በአብ ቀኝ ተቀመጠ ማለት በሥልጣን አንድ መሆንን ያሳያል፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ዳንኤል በትንቢቱ “በሌሊትም ራእይ
አየሁ፤ እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ፤ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ
የዘለዓለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፡፡” (ዳን. ፯፡፲፫-፲፬) ሲል ተናግሯል፡፡

ስለዚህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ስንል በክብር በልዕልና ከአብ ጋር እኩል ነው ማለታችን
ነው። ይህም ከተዋሕዶ በፊት ደካማ፣ በደለኛ እና ውርደት ይስማማው የነበረው የእኛ ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ ጸጋን የሚያድል፣
እውነተኛ ፍርድን የሚያደርግ፣ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው እውነተኛ ፈራጅ አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ
ነው እንጂ በመለኮቱስ ከአብ ሥልጣን ዝቅ ያለበት የዐይን ጥቅሻ ያህል ጊዜ እንኳ የለም። “ቀኝ” የሚለው ቃል ኃይልን
ቅድስናን ወይም ክብርን የሚያመለክት ነው ። ኃይልን ከመግለፅ አኳያ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “የእግዚአብሔር ቀኝ
ኃይልን አደረገች” (መዝ. ፩፲፯፡፲፭) ሲል ተናግሯል፡፡ ክብርም ከመግለጽ አኳያ “ጻድቃንን በቀኙ ያቆማቸዋል” (ማቴ. ፳፭፡
፴፫) እንላለን፡፡ ስለዚህም “የእግዚአብሔር ቀኝ “ማለት የእግዚአብሔር ኃይል ፣ ጽድቅ ፣ ክብር ማለት ነው፡፡ ይህም በብዙ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ያህልም የሚከተሉትን ማየት ይቻላል፡፡

 ጌታ ጌታዬን፡- ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው። (መዝ. ፻፱፡፻)
 ከእንግዲህ ወዲህ የሰውን ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ አለው። (ማቴ ፳፮፡፷፬)
 እነሆ፥ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ። (ሐዋ ፯፡፶፮)
 ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ፣ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፡፡ (ዕብ ፩፡፫)
 በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ (ዕብ ፰፡፩)
 እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና፡፡ (ዕብ ፲፪፡፪)

የጻድቃንን ዕርገት ያስገነዝብ ዘንድ ዐረገ


የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤው በተስፋ ለምንጠብቀው ትንሣኤያችን አርአያ እንደሆነው ዕርገቱም ለዕርገተ ነፍሳችን፣
መንግሥተ ሰማያትን ለመውረሳችን አርአያ ምሣሌ ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የጻድቃንን ዕርገት ያስገነዝብ ዘንድ ዐረገ፡፡
ከእኛ የተዋሐደዉን ሥጋ በዕርገቱ ከአባቱ ቀኝ በእግዚአብሔርነቱ አስቀመጠው፡፡ እንግዲህ በዕርገቱ የእኛን ሥጋ ከመላዕክት
ሁሉ በላይ አክብሮ በሰማያት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አስተካክሎ ካስቀመጠውማ እንደምን እኛን መንግሥተ ሰማያትን
አያወርሰንም ሊባል ይችላል? (፩ተሰ. ፬፡፲፯) ክርስቲያኖች በሰማያት ስፍራ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር
አብረን እንደምንቀመጥ የጌታችን ዕርገት ያረጋግጥልናል። የጌታችን ዕርገት ዓይነ ልቡናችንን እሱ ወደ አለባት መንግስተ
ሰማያት ይመራል።

ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ሲል ይላል፡፡ “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ
በአለበት በላይ ያለውን ሹ፡፡ የላይኛውን አስቡ ፤ በምድር ያለውንም አይደለም። እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤
ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰወረች ናትና። ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ ያንጊዜ
እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ።” (ቆላ. ፫፡፩-፬)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዕርገቱ የተስፋ ቃል ኪዳን ሰጥቶ ነበር። ለምሳሌ “እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ
ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ፡፡” (ዮሐ. ፲፮፡፯) ብሏል፡፡ እርሱ
በአካል ስለሚለያቸው የሐዘን ሰሜት እንዳይሰማቸው የሚያጽናና መንፈስ እንደሚልክላቸው ከሞቱ አስቀድሞ “አብ
በስሜየሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ
ያሳስባችኋል”(ዮሐ ፲፬፥፮) ብሎ ነግሯቸዋል።

ከምድራዊ አስተሳሰብና ከስጋ መንፈስ እንዲላቀቁ “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ እናንተ ግን ኃይልን ከላይ
እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ሉቃ ፳፬፥፵፱ ብሏቸዋል። ይህንን ተስፋ በማመን ጌታችን ሲያርግ ወደ ሰማይ
ትኩር ብለዉ ይመለከቱ የነበሩት ደቀ መዛሙርት በሃምሳኛዉ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል። እኛም ዕርገቱን እያሰብን
ዓይናችንን ወደ ሰማይ እናነሳለን። የራሳችንንም ዕርገት ተስፋ እያደረግን ልባችንን ወደ ሰማያዊዉ ህይወት ከፍ ከፍ
እናደርጋለን። በክብር ያረገ አምላክ ከትንሣኤ ሙታን በኋላ ያለውን ዕርገታችንን የክብር ያድርግልን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

You might also like