You are on page 1of 17

ሱባኤ

ሱባኤ ምንድን ነው ?

ሱባኤ በሰዋሰው ትርጉሙ "ሰባት"ማለት ሲሆን በመንፈስ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከ እዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ
ጋር እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው ፡፡

ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡

ለምሳሌ ፦ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፋ ፡ለጸሎት የሚተጉ ምዕመናን በቀን
ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥር ፋጹምነት ያመለክታል ፡፡ [ዘፍ 2፥2 , መዝ 118፥164 ] አንድ ሰው 7 ቀናት ቢጾም
"አንድ ሱባኤ ጾመ" ይባላል ፡፡

ሱባኤ መቼ ተጀመረ ?

የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመርያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት እንዳስተማሩት የቤተ
ክርስቲያናችን መዛግብት ያስረዳሉ በምላሹም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሥጋን ለብሼ ከ 5 ቀን ተኩል በኋላ አድንሃለሁ የሚለውን
ቃል ኪዳን የሰማው ሱባኤ በመግባቱ ነው፡፡

ሱባኤ ለምን ?

የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል ፡፡ በፈፀመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል
ይጸጸታል ፡፡በመጀመርያ ደፍሮ በሰራው ኃጥአት በኋላ ይደነግጣል ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ
የሚፈራረቅ ክስተት ነው ፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል ይተክዛል፡፡

ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ዓለም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና


የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር
የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባኤ ነው፡፡

1. እግዚአብሔርን ለመማጸን

ማንኛውም ሰው ሱባኤ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማፅኖ ሊኖረው ይገባል ፡፡ ምንም የምንጠይቀው (
የምንማፀነው) ነገር ሳይኖር ሱባኤ ብንገባ የምናገኝው መልስ አይኖርም ፡፡ ስለዚህ ሱባኤ ከመግባታችን በፊት ፦ሱባኤ
የምንገባው ለምንድን ነው ? በማለት እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ፡፡

2. የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶችና እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባኤ
የቅዱሳን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን ፤ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን ፤በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን
በረከት ለመሳተፋ ሱባኤ መግባት የነበረ ነው፡፡

የሱባኤ ዓይነቶች ?

1. የግል ሱባኤ ( ዝግ ሱባኤ) ፦ አንድ ሰው ብቻውን አመቺ ቦታ ማንም ሳያየው በግሉ የጸሎት በአቱን ዘግቶ በሰቂለ ኅሊና
ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው በኅቡዕ የሚፈፅመው ሱባኤ ነው ፡፡
2 .የማኅበር ሱባኤ ፦ ካህናት፣ምዕመናን፣ወንዶች፣ሴቶች ሽማግሌዎች፣ወጣቶች በአንድ ሆነው በቤተ ክርስትያንና አመቺ
በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚገቡበት ሱባዔ ነው፡፡

3 .የአዋጅ ሱባኤ ፦ በሀገር ላይ ድንገተኛ አደጋ ፤ ቸነፈር ጦርነት ሲነሳ እንዲሁም በማኅበረ ምዕመናን ላይ አስጊ የሆነ
መቅሰፋት ሲከሰት እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግስት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባኤ አይነት ነው፡፡

ቅድመ ዝግጅት

ሱባኤ ከመግባታችንም ሆነ ከገባን ግዜ እንዲሁም ከጨረስን በኋላ ምእመናን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባናል ፡፡

ሱባኤ ከመግባት አስቀድሞ

፩ በመጀመሪያ ሱባኤ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል ፡፡

፪ ሱባኤ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡

፫ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል ፡፡ሱባኤ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው።

፬ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡በቤተ ክርስቲያናችን በአብዛኛው ጊዜ ሱባኤ የሚገባው በአጽዋማት ወቅት በመሆኑ
ይህንን መለየት ነው ፡፡ምክንያቱም በጾም ወቅት ብዙ አባቶች ጸሎት የሚይዙበት ስለሆነ ጸሎታችን ከእነርሱ ጋር አብሮ
ያርግልናልና ነው፡፡ እዚህ ላይ በማንኛውም ጊዜ ሱባኤ አይያዝም ለማለት አይደለም በማንኛውም ጊዜ ፈተና ያጋጠመው ሰው
ሱባኤ ሊይዝ ይችላል።

በሱባኤ ጊዜ

ሀ. በጸሎት ሰአት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡
እንዲሁም ፊትን ወደ ምስራቅ መልሶ መቆም ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰቂለ ኅሊና ሆኖ መጸለይ ይገባል፡፡

ለ . በቅደም ተከተል መጸለይ ይገባል በመጀመርያ አአትብ ከሚለው ተጀምሮ አቡነ ዘበሰማያትን ጠቅሶ ጸሎተ ሐይማኖትን
መጨረስ ፡፡ስግዱ እና ስለ መስቀል በሚያነሳው ላይ እየሰገዱና እያማተቡ መጸለይ ፡፡ በማስቀጠል አቡነ ዘበሰማያት ፤መዝሙረ
ዳዊት ውዳሴ ማርያም ሌሎችንም ማስከተል ከዚያ 41 ጊዜ ኪራላይሶ ይባላል ፡፡

ሐ. በሱባኤ ግዜ ከተሐራሚው የሚጠበቀው ነገር ኃጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ለእያንዳንዱ በደል ማልቀስ ማዘን
ይገባዋል ፡፡

መ. በመጨረሻም ሱባኤ የገባው ሰው

ሱበዔውን ሳይጨርስ ወይም አቋርጦ ከማንኛውም ሰው ጋር ፈፅሞ መገናኘት የለበትም ፡፡

ከሱባኤ በኋላ

ላቀረብነው ተማፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል ፡፡ "ሱባኤ" የገባ ሰው ሁሉ ራዕይ ላያይ
ይችላል፡፡ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም ፡፡ ከሱባኤ በኋላ መጀመሪያ የምናገኝው የኅሊና
ሰላም ነው ፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው ፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባኤ ገብተን ያሰብነውን ካላገኝን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ
መጨረሻው ሰዓት በመማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡፡
ጾመ ፍልሰታ
ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞትና
ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ምስጢር ከነሐሴ 1-16 ድረስ ምእመናን በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት
የእርሷን አማላጅነት በሱባኤ ይማጸናሉ፡፡

ፍልሰታ ማለት ምን ማለት ነው

ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ
ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው ፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት
በእፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገርነው ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ
ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ እንደ ልጅዋ ሞታ መነሣቷን እና እርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት
ጾም ነው ፡፡

ምክንያተ ጾም

እመቤታችን ጥር 21 ቀን እረፍት በሆነበት እለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ እረፍት ይዘው
ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው <<ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ
ሰማይ አረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል>> እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡
አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች አረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን; ኑ
ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፋኒያ የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ
ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት
ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ
እመቤታችን ስለተማጸነ በተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች (ስንክሳር ዘጥር፡፡)

የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡
ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ
ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከእፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡
ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማእታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት <<በወርቅ
ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች>> እንዳለ፡፡ መዝ 44፡9

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ
ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ
ቆዩ፡፡ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም
እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና
በምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡

የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ
ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡
ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ <<በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ
የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ>> ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር
ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት
ይሆነው ዘንድ ሰበኗን - መግነዟን ሰጥታው አረገች፡፡

ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት እርሱም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር
እንዴት ይሆናል? አላቸው፡፡<<አንተ እንጂ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት
ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡ ቶማስም <<አታምኑኝም
ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ አርጋለች>> ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን
ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን - መግነዟን ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡

ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ ዓይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው በቀጣዩ ዓመት ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡
በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ
ረዳት ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ ዋና ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን እርገቷን
ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡

ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ
ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡

የእመቤታችን ከሞት መነሳት በመጸሐፍ ቅዱስ

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳርና ተአምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21
ቀን ዐርፋለች፡፡ እረፍቷን ቅዱስ ዳዊት ሲናገር <<አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት>> መዝ.136፡8
ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል
ቅዱስ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ከኖረች በኋላ ነብሷ ከሥጋዋ
ተለይቶ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን <<ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፡፡
የዜማም ጊዜ ደረሰ የቀረ ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ
ውበቴ ሆይ ነይ>> ሲል ስለ እመቤታችን በምሳሌ ተናግሮአል፡፡ መኃ 2፡1-13

ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት
በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ
የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡
ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ
ደርሷል ማለት ነው፡፡

ነቢዩ ዳዊት ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ ብሎ ስለ ሐዋርያት የተናገረው በዓለም ያለውን
መከራ ስድት ሲገልጽ ነው፡፡ /መዝ 18:4/ የዜማም ጊዜ ደረሰ ያለው የመከራን ጊዜ ነው፡፡ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ
ይጮሃሉ፣ ይዘምራሉም ተብሏል፡፡ መዝ 14፡13 የመከር ጊዜ ደረሰ የተባለው መከር የፍሬ ጊዜ በመሆኑ ክርስትና አፍርቷል
ማለት ነው፡፡ በለሱ ጐመራ ማለት ደግሞ በጐ ምግባረ ፍሬ ሳያፈሩ የነበሩ ሰዎች በጐ ምግባር መሥራት መጀመራቸውን
የሚያሳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ወይኖች አብበዋል፣ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል እንደተባለ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት
በሃይማኖት ማበብ መዓዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ እመቤታችን አረፈች፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የአማላክ እናት ድንግል ማርያም ለሐዋርያት እንደተገለጠች እኛንም እንድትገለጥልን እንድትባርከን
እንዲሁ ታላቁን የበረከት ድግስ ደግሳ ምዕመናንን ትጠባበቃለች፡፡ በዚህ ወቅት ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር መቅረብና
መንፈሳዊ ትሩፋትን ማድረግ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በዓለ ደብረ ታቦር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ስለሆነች ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋ መሳካት የሚያገለግሏት ከፍተኛ
ክብር ያላቸውና በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥርዓት የምታከብራቸው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ሥጋዌና የማዳን ሥራ ጋር
የተገናኙ ዘጠኝ ዓበይት በዓላት እና ዘጠኝ ንኡሳን በዓላት አሏት፡፡ ከእነዚህ የጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ በየዓመቱ ነሐሴ
13 ቀን የምናከብረው የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል (ማቴ. ምዕ.17፡1
ማር.9፡1፤ ሉቃ.9፡28)፡፡

በዚህ በዓል በተዋሕዶ የከበረ፣ አምላክ ሲሆን በፈቃዱ የሰውን ባሕርይ ያለመለወጥ የተዋሐደ ጌታ መለኮታዊ ክብሩ፣
የተዋሕዶው ፍጹምነት ይነገርበታል፣ የነቢያትና የሐዋርያት ምስክርነት ይተረጎምበታል፡፡ በባሕላዊ ገጽታው ይህ በዓል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት ‹መላጣ፣ ገላጣ›
ማለት ነው፡፡ ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለሆነ በዓሉ ‹‹ቡሄ››
ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበት
ዕለት ስለሆነ ‹‹የብርሃን በዓል›› (Transfiguration) ይባላል፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም ስለ ደብረ ታቦር በዓል
መንፈሳዊ መሠረትና ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እንዳስሳለን፡፡

በስድስተኛው ቀን ሦስቱን ሐዋርያት ይዞ ወደ ተራራ ወጣ

‹‹ደብረ ታቦር›› የሁለት ቃላት ጥምር ሲሆን ‹‹ደብር›› ማለት ተራራ፣ ‹‹ታቦር›› ደግሞ በናዝሬት አካባቢ በሰማርያ አውራጃ
በገሊላ ወረዳ የሚገኝ የረጅም ተራራ ስም ነው፡፡ የደብረ ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር
ርቀት የሚገኝ ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ 572 ሜትር ያህል ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ አስቀድሞ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦርና
አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” ብሎ ተናግሮ ነበር (መዝ. 88፥12)፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በዚህ ተራራ ላይ ብርሀነ መለኮቱን በመግለጡ ተራሮችም የፈጣሪያቸውን ተዓምራት በማየታቸው የነቢያት ትንቢት
ተፈጽሟል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሳራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነበር (መሳ. 4፥6)፡፡

የዚህም ታሪክ ምሳሌነቱ ባርቅ የጌታችን ሲሳራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ በአይሁድ
እያደረ አምላክነቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን አጋንንት ድል የማድረጉ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት
ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል (1ኛ ሳሙ.10፡3)፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ
ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ አይተዋል፡፡ አባታችን ኖኅም ይህንን ተራራ ‹‹መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡
የሐዲስ ኪዳን ወንጌል ጸሐፊያን ግን ‹‹ረጅም ተራራ፣ ቅዱስ ተራራ›› ከማለት በስተቀር ‹‹የታቦር ታራራ›› ብለው ስሙን
አልጠቀሱትም፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ክብሩን እንደገለጠና የዚህም ተራራ ስም ታቦር መሆኑን
ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ገልጠዋል፣ በትውፊትም ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ረጅም ተራራ
ደብረ ታቦር እያለ በድጓው አስፋፍቶ ጽፏል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ ነው፤ ሰው የሆነ ጌታ ነው፤ ሰው የሆነ ንጉሥ ነው፡፡ ጌትነቱና ንግሥናው በጸጋ
እንደከበሩ ቅዱሳንና፣ በኃላፊ ስልጣን እንደተሾሙ ምድራውያን ነገስታት በጊዜ የሚገደብ፣ ሰጭና ከልካይም ያለበት
አይደለም፡፡ አምላክነት፣ ጌትነት፣ ንግሥና የባሕርይ ገንዘቡ ነው፤ ከማንም አልተቀበለውም፣ ማንም አይወስድበትም፡፡
የድኅነታችን መሠረቱም የጌታችን ፍፁም አምላክ፣ ፍፁም ሰው መሆን ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔርሰ
ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር/ እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፣
በምድርም መካከል መድኀኒትን አደረገ” (መዝ. 72፡12) ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ ማዕከለ ምድር በተባለች በቀራንዮ ሰው የሆነ
አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ቤዛነት ዓለሙን ሁሉ አድኗልና፡፡ ይሁንና የጌታችን ነገረ ተዋሕዶ ለብዙዎች ለማመንና
ለመረዳት ይከብዳቸዋል፡፡
ዛሬም ድረስ በዚህ የተነሳ ብዙዎች ስለአንድ ክርስቶስ እየተነጋገሩ የተለያየና የነገረ ድህነትን ምስጢር በማወቅም ሆነ
ባለማወቅ የሚያዛቡ እምነቶች አሏቸው፡፡ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ወቅትም የተለያዩ
የአይሁድ ማኅበራት ስለ ጌታችን ማንነት ባለመረዳት አንዳንዱ ነቢይ ነው ሲል ሌላው ከዮሴፍ ጋር በተናቀች ከተማ
በናዝሬት ማደጉን አይቶ ይንቀው ነበር፡፡ ፍጥረታቱን ለሞት ለክህደት አሳልፎ የማይሰጥ ጌታ የአይሁድ ክህደት
ደቀመዛሙርቱንም እንዳያውካቸው ነገረ ተዋሕዶን (አምላክ ሲሆን ሰው የመሆኑን ድንቅ ምስጢር) በትምህርትም
በተዓምራትም ይገልጥላቸው ነበር፡፡ በትምህርት ነገረ ተዋሕዶን ካስረዳባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አንዱ በማቴዎስ
ወንጌል ምዕራፍ 16 ደቀመዛሙርቱን በጥያቄ ያስተማረበት ነው፡፡ ይህም ጥያቄ የጠየቀበት ቦታ ቂሣርያ ይባል ነበር፡፡
አባቶቻችን ይህን የጌታችንን ትምህርት ተስእሎተ ቂሣርያ (የቂሣርያ ጥያቄ) በማለት ይጠሩታል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳርያ ደቀመዛሙርቱን ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ቅዱስ
ጴጥሮስም ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ!›› ብሎ መሰከረ (ማቴ 16፡16)፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት
የመሰከረውን ምስክርነት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ይሰሙ ዘንድ፣ ከነቢያት (ሙሴና ኤልያስ) አንደበት ይረዱ ዘንድ፣
በተዓምራት የደነደነ ልባቸውን ይከፍት ዘንድ በተስእሎተ ቂሣርያ ቅዱስ ጴጥሮስ የሃይማኖት መሠረት የሆነውን የጌታችንን
ነገረ ተዋህዶ ከመሰከረ ከስድስት ቀን በኋላ አዕማድ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩትን ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስን ይዞ ወደ
ተራራ አወጣቸው (ማቴ 17፡1-10)፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠው ከተስእሎተ ቂሣርያ በ6ኛው ቀን
(ነሐሴ 13 ቀን) ነው፡፡ ተራራ የወንጌል ምሳሌ ናት፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፤ ከወጡት በኋላ ግን ከታች ያለውን ሁሉ
ሲያሳይ ደስ ይላል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፡፡ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅንና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ
ታሰኛለች፡፡

አንድም ተራራ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ተራራን በብዙ ጻዕር እንዲወጡት መንግስተ ሰማያትንም በብዙ መከራ
ያገኟታልና፡፡ (ሐዋ. 14፡22) አንድም ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ እንደተገለጠ በቤተ
ክርስቲያንም የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ይነገርባታልና፡፡ ተራራ መሠረቱ ከመሬት አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ፤
ቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር ሲሆን ራሷ (ክርስቶስ) በሰማይ ነውና፡፡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮቿ የተጠሩት ከምድር
(ከዓለም) ሲሆን ክብራቸው ግን በሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› እንዲል (ፊልጵ. 3፥20)፡፡
በዚህም መነሻነት ጌታችን በልዩ ልዩ ኅብረ አምሳል ለደቀመዛሙርቱ ነገረ ተዋሕዶውን አስረዳቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱም ዛሬ
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንደምታምነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ ሲሆን ሰው መሆኑን አመኑ፣
መሰከሩ፡፡

በፊታቸው ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ

ሦስቱ ሐዋርያት በተራራው ሳሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲጸልይ ሳለ መልኩ በፊታቸው ተለወጠ፡፡
ይህም የመለኮቱን ብርሃን ሲገልጥ ነው እንጂ ውላጤ/መለወጥ አይደለም፡፡ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” እንዳለ /ሚል
3፥6/ በእርሱ ዘንድ መገለጥ እንጂ መለወጥ የለም፡፡ ሦስት ክንድ ከስንዝር አካል ምሉዕ ብርሃን ሆኗል፡፡ ይህም አበቦች
ከአዕጹቃቸው እንዲፈነዱ ያለ መገለጥ ነው፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ፡፡ ልብሱም እንደ በረድ ጸዓዳ ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ
ነገረ ተዋሕዶን እንዲረዱ የተደረገ መገለጥ ነው፡፡ ሰውነቱን አልካዱም፣ አምላክነቱን ግን ተጠራጥረው ነበርና አምላክነቱን
ከሰውነቱ አዋሕዶ ነገረ ተዋሕዶን ገለጠላቸው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ32 ዓመት ከ6 ወር
ከ13 ቀን፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ በወርኃ ነሐሴ በዕለተ እሑድ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ጌታችን ብርሃንነት “በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ” “ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ” “እኔ
የዓለም ብርሃን ነኝ” “በሞት ጥላ መካከል ላሉ ብርሃን ወጣላቸው” እንዳለ ፀሐየ ጽድቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የሰው ልጆች የተስፋ ብርሃን፣ የእውቀት ብርሃን፣ የዓይን ብርሃን፣ የሕይወት ብርሃን የሆነውን ብርሃኑን ገለጠ፡፡
ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትንም ብርሃን ያለበሰ እርሱ ነው፡፡ ለመላዕክት፣ ለጻድቃን ለቅዱሳን ሁሉ የጽድቅ ብርሃንን ያደለ
የማይጠፋ ብርሃን እርሱ ነው፡፡ ለእርሱ ብርሃንነት ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከተራራው በወረደ ጊዜ የእስራኤልን ዐይን የበዘበዘ ገጸ
ብርሃን ምሳሌው ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ የብርሃን መገኛ ለቅዱሳን ብርሃንን የሚሰጥ የብርሃናት አምላክ፣ ሙሴን ብሩህ
ያደረገ፣ ለአባ አትናቴዎስም ብርሂት እድን (እጅ) የሰጠ ነው እንጂ፡፡ በቅዱሱ ተራራ ማደሪያውን ያደረገ አምላክ በዚህ
ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠ፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ «በፊታቸው ተለወጠ፣ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ» ሲል የክርስቶስ ፊቱ እንደ
ፀሐይ የበራው የብርሃኑም ኃይል ያንፀባረቀው የብሉይ ኪዳን መሪ እንደነበረው እንደ ሙሴ ፊት ብርሃን ያለ አይደለም፡፡
«ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ የፊቱ ቆዳ አንፀባረቀ፣ አሮንና እስራኤልም ይህንን ስላዩ ወደ እሱ ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ ተሸፈንም
እያሉ ጮኹ «ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ለእነሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ» ይላል (ዘፀ .34፡29-
30)፡፡ የሙሴ የጸጋ ነው፤ የክርስቶስ ግን የባህርይ ነው፡፡እንዲሁም «ብሩህ ደመና ጋረዳቸው» ያለው በሲና እንደታየው ያለ
አይደለም፡፡ በታቦር የታየው ብሩህ ደመና ነበር፡፡ በደብረ ሲና የተገለጠ የፍጡሩ የሙሴ ክብር ነበር፤ በደብረ ታቦር
የተገለጠው ግን የሕያው ባሕርይ የክርስቶስ ክብር ነው፡፡

ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴና ኤልያስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲነጋገሩ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደታዩአቸው ይነግረናል
እንጅ የተነጋገሩትን ዝርዝር አላስቀመጠልንም (ማቴ. 17፡3)። ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በትውፊት የከበሩ ናቸውና
ከቅዱሳን ሐዋርያት በቃል የተማሩትን የሙሴና የኤልያስ ምስክርነት አቆይተውልናል፡፡ ከሞተ ብዙ ዘመን የሆነውን ሙሴን
ከመቃብር አስነስቶ ቀጥሎም በእሳት ሠረገላ ያረገውንና በብሔረ ሕያዋን የሚኖረውን ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ
ያደረገበት ምክንያት እርሱ የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከመቃብር ተነሥቶ “እኔ ባህር
ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ
ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብሎ ስለጌታችን አምላክነት
ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ነቢዩ ኤልያስም ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት
ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለኝ ነኝ። እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ
እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” በማለት የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክሯል፡፡ ሐዋርያቱ “አንዳንዱ መጥምቁ
ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› ብለውት ነበርና (ማቴ.16፡14)፡፡ ቅዱስ
ሉቃስ በወንጌሉ ‹‹በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር›› ያለውም የነበራቸውን
ክብር ታላቅነት ያስረዳል፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሕግ/ከኦሪት ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ ከታላላቅ ነቢያት የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ለሙሴ “ጀርባዬንም
ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም” ተብሎ ነበርና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ከሙሴ ጋር ቃል በቃል በደመና
በሚነጋገርበት ጊዜ ነቢዩ ሙሴ ‹‹… ጌትነትህን (ባሕርይህን) ግለጽልኝ›› ሲል እግዚአብሔርን ተማጽኖት ነበር፡፡
እግዚአብሔርም ለሙሴ ‹‹በባሕርዬ ፊቴን አይቶ የሚድን የለምና ፊቴን ማየት አይቻልህም፡፡ … እኔ በምገለጽልህ ቦታ ዋሻ
አለና በብርሃን ሠረገላ ሆኜ እስካልፍ ድረስ በዋሻው ውስጥ ቁመህ ታየኛለህ፡፡ በባሕርዬ አይተህ ደንግጠህ እንዳትሞት
በብርሃን ሠረገላ ሆኜ እስካልፍ ድረስ ቀዳዳ ባለው ዋሻ እሠውርሃለሁ፡፡ በብርሃን ሠረገላ ኾኜ ካለፍሁ በኋላ እጄን
አንሥቼልህ ከወደ ኋላዬ ታየኛለህ እንጂ በባሕርዬ ግን ፊቴን ማየት አይቻልህም›› የሚል ምላሽ ሰጥቶት ነበር (ዘፀ.33፡13-
23)፡፡ ይህም በፊት የሚሔድ ሰው ኋላው እንጂ ፊቱ እንደማይታይ ጌታም በባሕርዩ አለመገለጡን ያስረዳል፡፡ ምሥጢሩም
አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም አምላክ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ በደብረ ታቦር በባሕርዩ እስኪገለጥለት ድረስ ሙሴ
በመቃብር ተወስኖ እንደሚቆይ ያጠይቃል፡፡ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ከሙታን ተነሥቶ ከዘመናት በፊት የተመኘውን
የአምላኩን ፊት ለማየት የታደለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተወለደውም በዚህች ዕለት ነው፡፡ ነቢዩ ኤልያስም “በኋለኛው ዘመን
ምስክሬ ትሆናለህ” የተባለው ትንቢትም በዚህች ዕለት ተፈጸመ፡፡

ስለምን ሁለቱን ከነቢያት ሦስቱን ከሐዋርያት አመጣ ቢሉ ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆኑን ሲያስረዳ ነው፡፡
በቤተክርስቲያን ነቢያት ያስተማሩት ብሉይ ኪዳንና ሐዋርያት የሰበኩት ሐዲስ ኪዳን ይነገራሉና፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትም፣
ሐዋርያትም እንደ ተገኙ ሁሉ ዛሬ በቤተክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይሰበካል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጽሙ ልዑካን
አምስት መሆናቸውም በደብረ ታቦር የተገኙትን ሙሴን፣ ኤልያስን፣ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ያስታውሱናል፡፡ ዘወትር
በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ደግሞ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው የጌታችን
የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡ አንድም ደብረ ታቦር የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡
፡ በሕግ በሥርዓት ያገቡ ሰዎችም፣ በንጽሕና በድንግልና በምንኩስና የአምላካቸውን ፈቃድ የሚፈጽሙ መናንያን፣
ባህታውያን፣ መነኮሳት አንድ ሆነው መንግስተ ሰማያትን እንደሚወርሷት ለማጠየቅ ከሕጋውያን ሙሴን ከደናግል ደግሞ
ኤልያስን አመጣ፡፡ ሙሴን ከመቃብር አስነስቶ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ በደብረ ታቦር ተራራ አብረውት እንዲገኙ
ያደረገው ደቀ መዛሙርቱ ሙሴ ነው ወይም ኤልያስ ነው በማለት ሲጠራጠሩ እንዳይኖሩ መለኮታዊ ትምህርት ለመስጠትም
ነው፡፡

ጴጥሮስም ‘በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው’ አለው

በዚያን ሰዓት ሦስቱ ሐዋርያት ማለትም ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና
ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ (ሉቃ 9፡32)። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ምስጢረ መለኮት፣ ማለትም የጌታ
በብርሃነ መለኮት ማሸብረቅና ልብሶችም እንደበረዶ ነጭ መሆን እንደዚሁም የእነዚህ የቅዱሳን የነቢያት መምጣት እና
ከጌታችን ጋር መነጋገራቸውን ከሰማ በኋላ “እግዚኦ እግዚእ ሠናይ ለነ ኃልዎ ዝየ/ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም
ነው/“አለ፡፡ ቅዱሳን ነቢያቱ የወትሮ ሥራቸውን እየሠሩ ማለትም ሙሴ ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣
ጠላት እያስገደለ፤ ኤልያስም ሰማይ እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናመ እያቆመ፤ አንተም አምላካዊ የማዳን ሥራን እየሠራህ
ገቢረ ተአምራትህን እያሳየህ፤ በዚህ በተቀደሰ ቦታ “በደብረ ታቦር” መኖር ለእኛ እጅግ መልካም ነው”፡፡ “ወእመሰ ትፈቅድ
ንግበር በዝ ሠለስተ ማኅደረ አሐደ ለከ ወአሐደ ለሙሴ ወአሐደ ለኤልያስ” አምላካዊ ፈቃድህስ ከሆነ በዚህ ተራራ ላይ
አንድ ለአንተ፤ አንድ ለሙሴ፤ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራ ብሎ ጠየቀ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› ሲል መናገሩም ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ
እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣
ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በደብረ ታቦር ለመኖር
መሻቱን ያመላክታል፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሦስት ጎጆ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ›› በማለት
የእርሱንና የሁለቱን ሐዋርያት ጎጆ ሳይጠቅስ አርቆ መናገሩ በአንድ በኩል ትሕትናውን ማለትም ‹‹ለእኛ›› ሳይል ነቢያቱን
አስቀድሞ ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን አለመጥቀሱን፤ እንደዚሁም ከጌታችን ጋር ለመኖር ያለውን ተስፋ ሲያመለክት፣ በሌላ
በኩል ደግሞ የቅዱስ ጴጥሮስን ድክመት ማለትም የክርስቶስን አምላክነት በሚገባ አለመረዳቱን ያሳያል፤ ጌታችንን በተራራ
ላይ በሰው ሠራሽ ቤት ይኖር ዘንድ ጠይቆታልና፡፡ጌታችንም ሐዋርያቱን ወደ ተራራው የወሰዳቸው ብርሃነ መለኮቱን
ሊገልጥላቸው እንጂ በዚያ ለመኖር አልነበረምና ቅዱስ ሉቃስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር የተናገረውን ‹‹የሚለውንም አያውቅም
ነበር›› በማለት ገልጦታል፡፡

ከደመናም ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት’ የሚል ቃል መጣ

ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ
ሠመርኩ/ልመለክበት የወደድኩት ለምስጢረ ተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው እርሱንም
ስሙት/” የሚል ቃል መጣ፡፡ በዚህም የሥላሴ ምስጢር ለዓለም ለሦስተኛ ጊዜ ተገለጸ፡፡ እግዚአብሔር አብ ደመናን
ተመስሎ “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” እያለ፣ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም
ሰውም ሆኖ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነጭ ደመና ተመስሎ ተገልጸዋል፡፡ ስለዚህም ደብረ ታቦር ጌታችን ብርሀነ
መለኮቱን፣ ክብረ መንግስቱን የገለጠበት እንዲሁም የስላሴ አንድነትን ሦስትነት የተገለጠበት ብላ ቤተክርስቲያናችን
ታስተምራለች፡፡

የደብረ ታቦር በዓል ከዘጠኙ የጌታችን አበይት በዓላተ አንዱ ስለሆነ በቤተክርስቲያናችን ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ
ፍጻሜ ድረስ ማኅሌት ይቆማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ በዓሉ የደረሰው «ሰበሕኩከ በደብር በቅድመ ሙሴ ወኤልያስ
ነቢያት ምእመናኒከ» በታማኞችህ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ ፊት የባሕርይ ልጅነትህን መሰከርሁልህ›› የሚለው መዝሙር
በመዘመር ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ተሰጥቶት ይውላል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት ሃይማኖትን
የሚማሩ ናቸውና ለሐዋርያት ነገረ መለኮቱን የገለጠ አምላክ እንዲገልጥላቸው በዓለ ደብረ ታቦርን በተለየ ድምቀት
ያከብሩታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ ነጎድጓዳማ ድምጽ መሰማቱን የብርሃን ጎርፍም መውረዱን በማሰብ
በሀገራችን በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች የነጎድጓዱ ምሳሌ አድርገው ጅራፍ በማጮኽ፣ የብርሃን ጎርፍ ምሳሌ አድርገው ችቦ
በማብራት ያከብሩታል፡፡

አባቶቻችን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ በዓላትን በትምህርት ከማስተላለፍ ባሻገር ምሳሌነታቸውን በባሕላችን
ውስጥ እንድንይዘው በማድረግ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲገለጽ ያደርጋሉ፡፡ ይህን
የማይረዱ ሰዎች ግን ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በባሕላዊ ጨዋታ በመተካት በበዓለ ደብረታቦር፣ በቤተ ክርስቲያን
መሠረታዊውን ነገረ ተዋሕዶ ከማስረዳት ይልቅ ስለባሕል በመጨነቅ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን በዓለ
ደብረታቦር በዋናነት የነገረ ተዋሕዶ ማሳያ እንጅ የባሕል ትርኢት ማሳያ ቀን አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ ባሕል የሚያስፈልገው
ለሃይማኖተኛ ሕዝብ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ከምንም በላይ መሠረተ እምነቱን ጠንቅቆ
ሊያውቅ፣ ከመናፍቃንም ቅሰጣ ሊጠብቅ ይገባል፡፡ እኛም በዓሉን ስናከብር በምስጋና በመዘመር እንጂ ሌሎች ሃይማኖታዊ
መሠረት የሌላቸውን ባሕላዊ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር መሆን የለበትም፡፡

በአጠቃላይ በወንጌሉ ያመንንና በስሙ የተጠመቅን ክርስቲያኖች የደብረ ታቦርን በዓል ስናከብር ቅዱስ ጴጥሮስ “ለእኛ በዚህ
መኖር መልካም ነው” እንዳለው በደብረ ታቦር በምትመሰለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን የቤተ ክርስቲያናችን ሕግና
ሥርዓት አክብረን፣ በምግባር በትሩፋት አጊጠን፣ ሕገ ተፋቅሮን አስቀድመን መኖር በሥጋዊ ዓይን መከራ ወይም ድካም
መስሎ ቢታየንም ፍጻሜው ግን ዘለአለማዊ ሕይወት ስለሆነ በቤቱ ጸንተን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ መኖር መንፈሳዊ
ግዴታችን መሆኑ ማወቅ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ለቅዱሳን ሐዋርያት ነገረ ተዋሕዶውን በታቦር
ተራራ የገለጠ፣ ነቢያት ሐዋርያት የመሰከሩለት የጥበቡ ጸጋ ብዛት የማይታወቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ
ተዋሕዶውን አውቀን፣ ተረድተን ለሌሎች የምናስረዳበትን ጥበብ መንፈሳዊ ይግለጥልን፡፡ አሜን፡፡
አሸንድዬ
የፍልሰታ ለማሪያም ጾም መጠናቀቅን ተከትሎ ከነሐሴ 16-21 በተለይም በሃገራችን የሰሜኑ ክፍል የተለያዩ አከባቢዎች
በድምቀት የሚከበር በዓል አለ። ይህ በዓል በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ስያሜ ነው የሚታወቀው፡፡

በዋግ ኽምራ ደይ፣

አሸንድዬ፣

በትግራይ አሸንዳ፣

በቆቦ ሶለል፣

በአክሱም ደግሞ ዓይነ ዋሪ እየተባለ ይጠራል፡፡

በዓሉ ምንም እንኳን ከጊዜ ብዛት ባህላዊ ይዘቱ ጎልቶ ቢታይም ሃይማኖታዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ ስለ በዓሉ ጥንተ መሰረት
የሚያትተው የቤተክርስቲያን ታሪክ ይህን ይለናል፡፡

በሃገራችን በኢትዮጵያ እጅግ በርካታ ጥንታዊያን በዓላትና ሥርዓቶች ይከናወናሉ አብዘኞቹ ደግሞ ከእስራኤላውያን የኦሪት
ሥርዓት የተወሰዱና በቀደመው ዘመን ሃገራችን ከእስራኤል ጋር በነበራት የሃይማኖትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አማካኝነት
የተወረሱ ናቸው፡፡ከእነዚህ ባህሎች ውስጥ ደግሞ የ "አሸንዳ " በዓል ነው፡፡ በዓሉን ልጃገረዶች በአማረ ልብስ ደምቀው
አሸንድዬ በሚባል የቄጠማ ጉንጉን ወገባቸውን አስረው ወደ ተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ በመጨፈር የሚያከብሩት ነው፡፡
ለመጠሪያውም አሸንዳ የሚለውን ስያሜ ያገኘው ወገባቸው ላይ ከሚያገለድሙት የቄጠማ አይነት ተክል ስም ተወስዶ ነው፡፡
በዓሉ ቤተ ክርስቲያናችን ዘንድ ሃማኖታዊ ይዘት ያለው ሲሆን የሚከበረውም ከነሐሴ 16 ምሮ እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ ነው፡
፡ የሻደይ በዓል ከኦርቶዶክስ ተዋሐዶ እምነት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው ሲባል፤ አጀማመሩ የእስራኤል መስፍን ከነበረው
ከዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ጋር በማስተሳሰር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻነት ስለሚሰጠው ነው፡፡ እንደዚሁም የደናግላን መመኪያ
ከሆነችው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ እና እርገት ጋር ተያይዞም ስለሚቀመጥ ነው፡፡ አሁን ላይም በዓሉ
በሚከበርበት አካባቢ በሚኖሩ የማሕበረሰቡ አባቶችና ሊቃውንት ዘንድ ጎልቶ የሚነገረውና የሚተረከው ይሄው ከእመቤታችን
ትንሣኤ ጋር የተያያዘው ታሪክ ነው፡፡ የበዓሉን አጀማመር ሥር መሰረቱ እንረዳ ዘንድ ሁለቱን ታሪኮች በጣም በአጭሩ አድርገን
እንመለከታለን።

የመስፍኑ ዮፍታሔ ታሪክ መ. መሳ 11 ቁ. 8

የታላቁ መጽሐፍ አንዱ ክፍል በሆነውና የእስራኤላውያን መሳፍንትን ታሪክ በያዘው መጽሐፈ መሳፍንት ላይ ስለ ዮፍታሔና
ስላጋጠመው ነገር እንዲሁም አሁን ስለምናወራለት በዓል መነሻ ምክንያት ይገልጻል፡፡ ዮፍታሔ ገለዓዳውያንን እየመራ ከአሞን
ልጆች ጋር ጦርነት ለመግጠም እንደተነሳና ወደዛም በሄደ ጊዜ ጠላቶቹን በእጁ ላይ ከጣለለትና ወደቤቱም በደህና ከተመለስ
ቀድሞ ሊገናኘው የሚወጣውን ለአምላኩ ለእግዚእብሔር መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ስዕለት ገብቶ ነበር፡፡ ዮፍታሄ ይህን
ሲል መጀመሪያ የሚያገኘውን ማንኛውም እንስሳ የሚቃጠል መስዋት እንደሚያደርገው አስቦ ነበር ነገር ግን እርሱ ወደ ቤቱ
በድል ሲመለስ ያለ ወትሮዋ በመጀመሪያ ወጥታ እየዘፈነች የተቀበለችው ሴት ልጁ ነበረች። ዮፍታሄም እርስዋንም ባየ ጊዜ
ልብሱን ቀድዶ፡፡ አወይ ልጄ ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር አፌን ከፍቻለሁና፥ ከዚያውም እመለስ ዘንድ አልችልምና በጣም
አዋረድሽኝ አስጨነቅሽኝም አላት፡፡ እርስዋም አባቴ ሆይ፥ አፍህን ለእግዚአብሔር ከከፈትህ፥ እግዚአብሔር በጠላቶችህ
በአሞን ልጆች ላይ ተበቅሎልሃልና በአፍህ እንደ ተናገርህ አድርግብኝ አለችው አባትዋንም ይህ ነገር ይደረግልኝ፤ ከዚህ ሄጄ
በተራሮች ላይ እንድወጣና እንድወርድ፥ ከባልንጀሮቼም ጋር ለድንግልናዬ እንዳለቅስ ሁለት ወር አሰናብተኝ አለችው፡፡ሁለትም
ወር ከተፈጸመ በኋላ ወደ አባትዋ ተመለሰች፥ እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት፤ እርስዋም ወንድ አላወቀችም ነበር፡፡
የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ
በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ፡፡ እዚህ ጋር ልብ ልንለው የሚገባው "እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት' ሲባል መስዋዕት
አድርጎ አርዶ ሰዋት ማለት ሳይሆን በድንግልናዋ እንዳለች ተለይታ እንድትኖር አደረጋት ማለት እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ
ክርስቲያን ያስረዳሉ፡፡ እናም ይህ ታሪክ ከተፈፀመበት ጊዜ አንስቶ በየአመቱ እየታሰበ መጥቶ አሁን ላይ በዓል ሆኖ ለመከበር
በቅቷል ማለት ነው፡፡ ይህም ታሪክ ደግሞ ወደ ሃገራችን በንግሥተ ሳባ ልጅ በቀዳማዊ ምኒልክ ምክንያት ታቦተ ጽዮንን ይዘው
ሲመጡ አብረው ከመጡት ሕዝበ እስራኤል ጋር አብሮ ሊገባ ችሏል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓልና አሸንዳ

የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለክተ ከላይ ከተቀመጠው ታሪክ በተጨማሪ በአካባቢው ሕዝብና በቤተ ክርስቲያን
ሊቃውንት ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሣው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ነው፡፡ ይኸውም
እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን ከ5500 ዘመን በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኃጢያት እሥራት ነጻ
እንደሚያወጣቸው ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ በሔዋን
ስህተት ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ በእርሷ ምክንያት ከኃጢያት ባርነት ነጻ የወጣባትና ወደ ቀድሞ ቤቱ ገነት እንዲመለስ
ምክንያት የሆነችው የሰው ልጅ መመኪያ የተባለች እመቤት፣ እንደማንኛውም ሰው የተፈቀደላትን እድሜ በምድር ከኖረች
በኋላ ሞተ ሥጋን እንደ ሞተች ከመጻሕፍት እንረዳለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከዚህ በኋላ በልጇ ሃይል
ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ አረጋለች፡፡

በፍልሰታ ወቅት በዓሉ መከበሩም ለሻደይ ተጨዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርዓያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም
አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፤ እንዲሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ
እንደሆነ ይነገራል በዓሉ በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው አስቀድሞ በዮፍታሄ ልጅ ታሪክና የዘላለማዊ ድንግልና ባለቤትና
መመኪያቸው በሆነች በእመቤታችን ድንግል ማርያም ምክንያት ነው፡፡ ልጃገረዶቹ ድንግልናቸውንም ለእርሷ አደራ እንደሚሉ
ይነገራል፡፡ ዕርገቷን በተመለከተም እመ አምላክ ስታርግ መላእክት በእልልታ፣ በሽብሸባና በዝማሬ ነጫጭ ልብስ ለብሰው
አጅበዋት ነበርና የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና በማሰብ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ደናግል ከቅዱሳን መላእክቱ
እንደተመለከቱት ባሕላዊ ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ የወቅቱ መታሰቢያ የሆነውን ለምለሙንና ከምድር
ሳሮች ሁሉ ረዘም ያለውን የሻደይ ቅጠል በወገባቸው

አስረው ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ ፤ እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ


በአንድነት ተሰባስበው በፍቅርና በሐሴት ያከብሩታል፡፡ከታሪኮቹ እንደምንረዳው በዓሉ የልጃገረዶች ነው፡፡
ወርኃ ጳጉሜን
ጳጉሜን የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው ፡፡ በግእዝ “ወሰከ
– ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ ምዕራባዊያኑ ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ቀን
አድርገዋታል፡፡ እኛ ግን የዓመት ተጨማሪ ወር አድርገናታል፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወርኃ ጳጕሜን የዓለም
ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ይህም ጳጉሜ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከክረምት ወቅት ወደ ጸደይ
መሸጋገሪያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ፣ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፣ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው
መሸጋገሪያ ነትና ነው፡፡ ጳጉሜ የክረምቱ ማብቂያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም በመጨረሻው ዘመን መከራ የሚበዛበት የዚህ
ዓለም ማብቂያ ናት፡፡ ወርኃ ጳጉሜ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የዝግጅት ጊዜ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ጻድቃል አዲሲቷን
ምድር (መንግስ ሰማያትን) ለመውረስ ተዘጋጅተው “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግስት ውረሱ”
የሚባሉባት ናት፡፡

በዚህም የተነሣ ብዙ ምእመናን በጾምና በጸሎት (በሱባዔ) ያሳልፏታል፡፡ በተለይም በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት
የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) መኾኑን በማመን ምእመናን የጸሎታቸውን ማረጊያ (ማሳረጊያ) መሆኑን በማመን
ከምንጊዜውም በበለጠ በእምነት ይጸልያሉ፡፡ ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት እንደማለት ሲሆን በክርስቶስ
ክርስቲያን የተባሉ ሁሉ ፀሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት የምእመናንን ልመና
መስዋእቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካችንን ምህረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት ዕለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ
ውኆች እንደሚባረኩ በሚረዳ ጽኑ እምነት ምዕመናን ወደ ወንዞች በመሔድና በሚዘንበው ዝናብ ይጠመቃሉ፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው ጾመ ዮዲት ነው፡፡
የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ
ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ (ዮዲ ፪፡-፪)፡፡
እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው
እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋት
በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባለቤቷ ምናሴ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖር ነበር:: በተፈጠረው ጥፋት
ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ
እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለጸላት (ዮዲ ፰፡፪)፡፡
ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡ ዮዲት ጠላቷን
ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን
ሰይጣንንና ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡ እና ከሚከበሩ በዓላት መካከል በየዓመቱ ጳጕሜን ፫ ቀን የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ
ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቅነቱ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ “ሩፋኤል” የሚለው የስሙ ትርጓሜ
“ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ” ማለት ነው፡፡ በሌላም መልኩ ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የዕብራይስጥ ሁለት
ቃላት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ “ሩፋ” ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን “ኤል” ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም
ላይ የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው:: ይህም “መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ አታስመርሩት” (ዘጸ.23÷20-
22) እንዳለው ነው፡፡ ታዲያ “ሩፋኤል” የሚለው በጥምረት “ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ” የሚለውን ይተካል፡፡ ቅዱስ
ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ስሙም ከሚካኤልና ከገብርኤል ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ “ከከበሩ
ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው
ልጆችን ይጠብቃቸዋል (ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ. 90÷11-13 ) ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡ (ሉቃ. 13፡6-9፣
ዘካ.1÷12) ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት
አንዱ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን በሚከተሉት ሰባት
አንኳር ነጥቦች ይገልጡታል፡፡

ፈዋሴ ዱያን፡ ሕሙማንን የሚፈውስ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ እየተመላለሰ ሲያስተምር ድውያነ ሥጋን በተአምራት
ድውያነ ነፍስን ደግሞ በትምህርቱ ይፈውስ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለሠላሳ ስምንት ዘመን በአልጋ ላይ የነበረውን መጻጉዕን ተነስተህ
አልጋህን ተሸክመህ ሄድ በማለት ከደዌው ፈውሶታል (ዮሐ ፭፡í-፲)፡፡ ማዳን (መድኃኒትነት) ለእርሱ የባህሪው ነው፡፡ የማዳንን
ጸጋ ለቅዱሳን ሰጥቷል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ድውያንን ሲፈውሱ የነበረው፡፡ ከቅዱሳን መላእክትም
ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኃጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የሚረዳ መልአክ ነው፡፡
“በበሽታ ዅሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ
ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖክ ፲፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ
ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል
ነው” እንዳለ ሄኖክ (ሄኖክ ፮፥፫)፡፡ ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው መልአክ ነው፡፡ ዛሬም ሁላችንን በአማላጅነቱ ከደዌ ሥጋ
ከደዌ ነፍስ ይፈውሰናል፣ ይጠብቀናልም፡፡

ፈታሔ ማኅፀን፡ ማኅፀንን የሚፈታ

በብሉያና በአዲስ ኪዳን ብዙ እናቶች ከመካንነት የተነሳ ሀዘን ጸንቶባቸው ቢቆይም ምንም የማይሳነው አምላክ እጅግ ድንቅን
ያደረጉ የተባረኩ ልጆችን ሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የይስሐቅ እናት ሣራ፣ የያዕቆብ እናት ርብቃ፣ የዮሴፍ እናት ራሄል፣
የሶምሶን እናት እንትኩን፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና፣ የመጥምቀ መለኮት የዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ፣ የድንግል ማርያም እናት
ሐና ይገኙበታል፡፡ እግዚአብሔር የመካኒቱን ማኅፀን ፈትቶ የተባረከ ልጅን የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ይህንንም ጸጋ ለቅዱሳን
መላእክት ሰጥቷል፡፡ ይህም ስልጣን ከተሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል አንዱ ነው፡፡

የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሾመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ ሴቶች
ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ፡፡ የይስሐቅን እናት
ሣራን፣ የሶምሶንን እናት (እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔ ማኅጸን የልዑል
እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ለነፍሰጡር ሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት
ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ (ኗ) በማኅፀን እያለ (ች) ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያ መልኩ /ኳ/ መሳል)
ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች
ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን
ያቀልላቸዋል፡፡ ሕጻናትን በእናታቸው ማኅፀን የሚጠብቃቸው እናቶችንም ከመፅነስ እስከ መውለድ የሚራዳቸው፣
የመካኖችንንም ማኅፀን የመፍታት ጸጋ የተሰጠው መልአክ ነው፡፡

ሰዳዴ አጋንንት፡ አጋንንትን የሚያሳድድ

ከጌታችን ሠላሳ ሦስት ታላላቅ ተአምራት ውስጥ አራቱ አጋንንትን ማስወጣት ነበሩ፡፡ ይህ ስልጣን ለቅዱሳን ሰዎችና መላእክት
በጸጋ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም በተሰጠው ስልጣን አጋንንትን የሚያሳድድ መልአክ ነው፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን
በሣራ (ወለተ ራጉኤል) ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል (ጦቢት ፫፥፰-
፲፯)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል “ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው”
ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖክ ፫፥፭-፯) ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ
አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው (ሄኖክ
፪፥፲፰)፡፡ ዛሬም ከእግዚአብሔር ተልኮ ለሰው ልጆች የተንኮልን፣ የጥላቻን፣ የመገዳደልን ሀሳብ እንዲያፈልቁ የሚያደርገውን
የመልካም ነገር ጠላት የሆነውን ጠላታችንን አስጨንቆ የሚያባርር መልአክ ነው፡፡
አቃቤ ኆኅት፡ የምሕረትን ደጅ የሚጠብቅ

ቅዱሳን መላእክት የሰውን ልጅን ጸሎት ከምድር ወደ ሰማይ የእግዚአብሔርን ምህረት ደግሞ ከሰማይ ወደ ምድር የሚያደርሱ
መልእክተኛች ናቸው (ራዕ ፰፡፪)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም ስለራሱ ማንነት በሰጠው ምስክርነት “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ
ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” (ጦቢት
፲፪፥፲፭)፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሩፋኤል መዝገበ ጸሎት እና አቃቤ ኆኅት ይባላል፡፡ ከዚህ ጋርም በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት
ከተደረጉ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያደረገው ተአምር አንደኛው
ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሩፋኤል እንደ ተጻፈው በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ ክብር
በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ነበረች፡፡

ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ጠላት ዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፋ አሣ
አንበሪውን ቢያውከው ቤተክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጠች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች
ብዛትም በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ምእመናኑም ወደ ክብር ባለቤት
እግዚአብሔር በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ
“እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!” ባለው ጊዜ አንበሪው ጸጥ ብሎ ቆሟል፡፡ ምዕመናኑንም ከጥፋት
ታድጓቸዋል፡፡

መራኄ ፍኖት፡ መንገድ መሪ

ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር
በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ
ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ
ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡

ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች
ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ
በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ
ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ
በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም
የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት
ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡

“በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ (ዘጸ ፳፫፡፳)።”
ተብሎ ለመላእክት ሰውን መንገድ የመምራትና የመጠበቅ ስልጣን እንደተሰጣቸው የጦቢትን ልጅ ጦቢያን ከነነዌ የሜዶን
ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደምትባለው ሀገር ሲሄድ አዛርያስ (ቅዱስ ሩፋኤል) በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ
ሩፋኤል “መራኄ ፍኖት” (መንገድ መሪ) ይባላል፡፡ ጦቢያና አዛርያስ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ
ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ
መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው፤ ዓሣውን
እንዳትለቀው አለው፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል
ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን
አለው፡፡ ዛሬም በመንገዳችን እንዲመራን በጉዞአችንም ፈተና ሲገጥመን እንዲራዳን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን ሊልክልን
አምላካችን የታመነ ነው፡፡
መልአከ ከብካብ: ጋብቻን የሚባርክ መልአክ

የራጉኤል ልጅ ሣራ ሰባት ሰዎች አግብተዋት ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ አድረዋል፡፡ ይህንንም ከነነዌ ወደ ራጌስ
የመጣው የጦቢት ልጅ ጦቢያ ያውቅ ነበር፡፡ ለአዛርያስም “ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ
በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና
እፈራለሁ” አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል
የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም
የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን ያዘው ያልኩህ ለምን ይመስልሃል? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ
ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ
ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡
ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡

ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳየው ሚስቱ አድናን
“ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል” አላት ከዚያም ጋር አያይዞ “ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?” አላቸው፡፡ እነሱም
“ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን” አሉት፡፡ “ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት “እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ” አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል “የወንድሜ
ልጅ ነህን?” ብሎ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ
መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡

እራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን
በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ
የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት
አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን
ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት
በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ
አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኝቶ
በዶኪማስ ቤት የነበረውን ሠርግ ባርኮታል፡፡ የወይን ጠጅ ቢያልቅባቸውም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦ ቤቱን በበረከት
ሞልቶታል (ዮሐ ፪፡í)፡፡ ቅዱሳንም ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ ጋብቻን በጸሎታቸው ይባርካሉ፡፡ በመሆኑም የጦብያንና
የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ “መልአከ ከብካብ” ይባላል፡፡ ዛሬም በምልጃው ላመኑት ጋብቻን ይባርካል፣
ትዳርንም ያጸናል፡፡

ከሣቴ እውራን፡ ዓይነ ስውራንን የሚያበራ

ራጉኤልና ሐና የሣራንና የጦቢያን የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የአሥራ አራት ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ
ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡ የአሥራ አራት ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ
ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት
ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡
፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ
የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡ በምራቁ አፈር ለውሶ በደረቅ
ግንባር ላይ ዓይንን የሚሠራው እግዚአብሔር (ዮሐ ፰) በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አማካኝነት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን
በራለት፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ዛሬም በምልጃው ለሚያምኑት ሥጋዊ ዓይንና መንፈሳዊ ዓይንን (ዓይነ ልቡናን) የሚያበራ መልአክ
ነው፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት ወርኃ ጳጉሜን የእለተ ምጽአት መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡
በወርኃ ጳጉሜ የአሮጌውን ዘመን የኃጢአት ቆሻሻ በንስሃ አጥበን ከዕለተ ምጽዓት በኋላ ለምትገለጠው የእግዚአብሔር
መንግስት ምሳሌ ለሆነ አዲስ የምህረት ዓመት እንዘጋጅባታለን፡፡ የታደሉትም በፈቃድ ጾምና በሱባኤ እንደሚያሳልፏት
ይታወቃል፡፡ በወርኃ ጳጉሜን በገናንነት የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓል የአሮጌው ዘመን በዓላት መዝጊያ
ለአዲሱ ዘመን ርዕሰ አውደ ዓመት ለቅዱስ ዮሐንስ በዓልም መሸጋገሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የሊቀ
መልአኩን የቅዱስ ሩፋኤልን በዓል በማሰብ በወርኃ ጳጉሜ ውኆች እንደሚባረኩ በእምነት በመረዳት “ሩፋኤል አሳድገን
(እርዳን፣ ጠብቀን)” እያልን በሃይማኖት እንጠራዋለን፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን በመጽሐፈ
ጦቢት፣ በመጽሐፈ ሄኖክ፣ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በጻፈው አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፍና በድርሳኑ ላይ እንደተገለጠው
ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጸጋ ድውያነ ሥጋንና ድውያነ ነፍስን የሚፈውስ፣ የሚካኒቱን ማኅፀን የሚያለመልም፣ ሕጻናትንም
በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ የሚጠብቃቸው፣ የክፋት አባት የሆነውን ጠላት ሰይጣንን የሚያሳድድ፣ በመንገድ ያሉትን የሚመራ፣
ምህረትን ለሚሹ ፈጥኖ የሚደርስ፣ በጋብቻና በትዳር የሚፈተኑትን የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል
ጸሎትና አማላጅነት ልጅ በማጣት ለተጨነቁ መልካም ፍሬን፣ ለተወለዱት በሃይማኖት ማደግን፣ ለታመሙት ፈውስን፣
ለባለትዳሮች እግዚአብሔር የሚደሰትበት ትዳርን እንዲሰጥልን የሰራዊት ጌታ የአምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ
ይሁንልን፡፡

You might also like