You are on page 1of 4

አብይ ጾም: በገዳመ ቆሮንቶስ በዲያብሎስ 

ተፈተነ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ 30 ዓመቱ በማየ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል
ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ ይህም ጌታችን የጾመው ጾም ልዩ ልዩ
መጠሪያዎች አሉት። እንደ ነቢያት ስርዓት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ስለጾመ ጾመ አርብዓ (አርባ ጾም) ይባላል። ስሙ
መድኀኒት የሆነ ጌታ የነፍስ ቁስል የሆኑ ሦስቱን ዐበይት ኃጢአቶች (ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ) ድል ያደረገበት
በመሆኑ የድል ጾም፣ ጾመ ኢየሱስ በመባል ይታወቃል። የፍጥረት ሁሉ ጌታ፣ ልዑለ ባሕርይ፣ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ
ክርስቶስ የጾመው በመሆኑ ከሌሎች አጽዋማት ተለይቶ ዐቢይ (ታላቅ፣ ዋና) ጾም ይባላል። ለረዥም ጊዜ የሚጾም፣ ብዙ
መንፈሳዊ በረከት የሚገኝበት ጾም በመሆኑ ብዙ ምርት ከሚያስገኝ ሰፊ እርሻ ጋር በማመሳሰል ጾመ ሁዳዴ ይባላል።

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ስለዚህ የጌታ ጾም ሲጽፍ ‹‹ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ
ምድረ በዳ ወሰደው፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ›› በማለት ገልጾታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ፈታኝ ወደ
እርሱ የቀረበው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ይህንን የጌታችንን በዲያብሎስ መፈተንን ሊቃውንት
አባቶች ያመሰጠሩትን በመተንተን ታስተምራለች፡፡ እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ይህንን የሊቃውንትን ትምህርት
መሠረት በማድረግ የጌታችን በዲያብሎስ መፈተንና ድል ማድረጉ ለእኛ ያለውን መንፈሳዊ ትርጉም እንዳስሳለን፡፡
ይህንንም በሰባት ጥያቄዎች ሥር አቅርበነዋል፡፡

ፈታኙ ማነው?

ጌታችንን ለመፈተን ፈታኝ ሆኖ የቀረበው ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ነው፡፡ ይህ ፈታኝ በመጀመሪያ ራሱ ተፈትኖ የወደቀ
ስለሆነ የሰውን ልጅ መፈተን የባሕርዩ ነው፡፡ አዳምን ፈትኖ ያሳተው፣ ኢዮብንና ሌሎችን አባቶች የፈተነው፣ በበርካታ
ቅዱሳን ዜና ሕይወት በፈታኝነቱ የተገለጠው፣ ዛሬም መልካም የሚሠሩትን የሚፈትነው፣ ቅድስት ቤተክርስቲያንንም
በየዘመናቱ የሚፈታተናት ይህ ፈታኝ ነው፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አገላለፅ በቤተክርስቲያን ላይ ዝናሩን የጨረሰው
ነገር ግን ያላጠፋት ዲያብሎስ ነው ክርስቶስን የፈተነው፡፡ ዛሬም በክርስቶስ የምናምን ክርስቲያኖችን በልዩ ልዩ መንገድ
ይፈትነናል፡፡ ጌታችን በጾሙ ወራት ዲያብሎስን ድል ማድረጉን ያሳየን እኛም ኃይለ አጋንንትን የምናሸንፍበት ኃይል
ጾም፣ ጸሎት እና ስግደት መሆናቸውን ሲያስተምረን ነው፡፡ ፈታኙን ድል ነሥቶ ድል የማድረጊያ ኀይል የሚሆኑንን
ጾምን፣ ጸሎትንና ስግደትን ባርኮልናል።

ጌታችን ለምን ተፈተነ?

በገዳመ ቆሮንቶስ የተፈተነው የሰውን ልጅ ለማዳን ሰው ሆኖ የመጣው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ነው፡፡ “አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን” ብለን እንድንጸልይ ያስተማረን፣ ወደ ፈተና በገባን ጊዜም በቅዱስ ስሙ፣
በህያው ቃልኪዳኑ ተማምነን “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር” ብለን ስንጠራው የሚመልስልን ሰው የሆነ አምላክ
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተፈተነ? የጌታችን መፈተን እንደሌሎች ቅዱሳን በፈተና በመጽናት ጸጋን ገንዘብ ለማድረግ
አይደለም፤ እርሱ የጸጋ ሁሉ ምንጭ (አስገኝ፣ ሰጭ) ነውና፡፡ ይልቁንስ የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ በሥጋ ሲኖር ፈተና
እንዳለበት ሊያስተምር እርሱ ተፈተነ፡፡ በባሕርዩ መፈተን የሌለበት አምላክ የሰውን ልጅ ፈተና ሰው ሆኖ ተፈተነ፡፡
በዚህም በሕይወታችን መፈተን እንዳለብን አስተማረን፡፡ እርሱ በፈጠረው ፍጡር (በዲያብሎስ) የፈጠረውን ፍጡር
(አዳምን) ለማዳን ተፈተነ፡፡ ጌታችን የተፈተነበት ዓላማ የሰው ልጅ የዲያብሎስን ፈተና እንዴት ድል እንደሚያደርግ
አብነት፣ አርአያ ሊሆን ነው፡፡ ፈጣሪ በፍጡር ለፍጡራኑ አብነት ሊሆነን በፈቃዱ ተፈተነ፡፡ እርሱ እጸድቅ አይል ጻድቅ፣
እቀደስ አይል ቅዱስ፣ እከብር አይል ክቡር ሲሆን ለሰው ልጅ አርአያ ሊሆን በተለየ አካሉ ባሕርያችንን ባሕርይው አድርጎ
በማስመሰል ሳይሆን በእውነት በዲያብሎስ ተፈተነ፡፡

ጌታችን መቼ ተፈተነ?

በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ፣ በገዳመ ቆሮንቶስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ከጾመ በኋላ በተራበበት ወቅት
ተፈተነ፡፡ እንዲሁ በሰው ልጅ ላይም ፈተና የሚመጣው አምኖ ተጠምቆ በጎ ምግባራትን መሥራት ሲጀምር ነውና
ይህንን ለማጠየቅ በዚህ ወቅት ተፈተነ፡፡ ክርስትና ከፈተና የምናመልጥበት (ሳንፈተን የምናሸንፍበት) መንገድ ሳይሆን
በፈተና ውስጥ አልፈን፣ ድል በማድረግ ከሥጋ ሞት በኋላ የዘለዓለም ሕይወትና ክብር የምናገኝበት ፍኖተ ጽድቅ
(የእውነት መንገድ) ነው።  ክርስቲያኖች ምግባር ትሩፋትን (ጾም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ስግደት) መስራት ሲጀምሩ ነው
ፈተና የሚበዛባቸው፡፡ ከቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ዜና ሕይወት (ገድል) እንደምንማረው ብዙዎቹ ቅዱሳን
በገድል በትሩፋት እያደጉ በሄዱ ጊዜ የዲያብሎስ ፈተና ዓይነትና ብዛት ይጨምርባቸዋል። ምንም ዲያብሎስ ፈተናውን
ቢያበዛ በገድል በትሩፋት የጸኑት በመስቀሉ ኀይል፣ በእግዚአብሔር ቸርነት ፈታኛቸውን ድል ይነሱታል። መፈተን የማደግ
እንጂ የመውደቅ ምልክት አይደለምና። በዚህ ወቅት የሥጋንና የዲያብሎስን ፈተና ለማለፍ ተግተው ልንጸልይ ይገባል፡፡
ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ ተብሎ ተጽፏልና፡፡

ጌታችን በየት ተፈተነ?

ሦስቱን ፈተናዎች በሦስት ቦታዎች ተፈተነ፡፡ አንዱን በገዳም፣ ሁለተኛውን በቤተመቅደስ፣ ሦስተኛውን ደግሞ በተራራ
(በቤተመንግስት) ተፈተነ፡፡ በገዳም ለሚኖሩ ባሕታውያን (መነኮሳት) አብነት ሊሆናቸው በገዳም ተፈተነ፡፡ በቤተመቅደስ
ለሚያገለግሉና ለሚገለገሉ ካህናትና ምዕመናን አብነት ሊሆናቸው በቤተመቅደስ ተፈተነ፡፡ በተራራ (በዓለም) ለሚኖሩ
አብነት ሊሆናቸው በተራራ ተፈተነ፡፡ በገዳም ሆነው በጾም በጸሎት የጸኑ ባሕታውያን ለመብቃት (ወደ ፍጹም
መንፈሳዊነት ለማደግ) ሲተጉ ይፈተናሉና ለእነርሱ አብነት ሊሆን በገዳም ተፈተነ፡፡ በቤተመቅደስ በእምነት ጸንተው
የሚኖሩ ካህናትና ምዕመናን ትሩፋትን ለመሥራት ሲተጉ ይፈተናሉና በቤተመቅደስም ተፈተነ፡፡ በቤተመንግስት
(በከፍታ) የሚኖሩ ባለስልጣናትና ዓለማውያን ለማመን፣ በጎ ምግባራትን ለመሥራት  ሲተጉ በዲያብሎስ ይፈተናሉና
በዚያም ተፈተነ፡፡

ፈተናዎቹስ ምን ነበሩ?

ጌታችን ሦስት ታላላቅ ፈተናዎችን ተፈተነ፡፡ ሦስቱንም እንደየአመጣጣቸው በትዕግስት ድል አደረጋቸው፡፡


የእስክንድሪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አባታችን ቴዎዶስዮስ ለአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ሳዊሮስ በጻፈው ጦማር
እንደተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሐደው ሥጋ ዲያብሎስን ድል ስለነሳው የእኛ ባሕርይም ከእርሱ የተነሳ
በዲያብሎስ ላይ መሰልጠን የሚችል ሆነ፡፡ “ጌታ ሰይጣንን ድል ቢነሣው የሚደነቅ ሥራ አይደለም፤ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ቀድሞ ድል ተነሥቶ የነበረ ሥጋን የተዋሐደ ባይሆን በባሕርይ ከእኛ ጋር አንድ በሚሆን ሥጋ እዳ በደል
ያልተገኘበት እርሱ በሥጋ መከራን የተቀበለ ባይሆን ኖሮስ መከራ መቀበሉ ባልተደነቀም ነበር፤ ሞትንም በሥጋው
ያጠፋው ባይሆን ኖሮ ሞትን የሚያሰለጥን ኃጢአት ባልጠፋም ነበር፤ የሞት ሥልጣንም ባልተሻረም ነበር፡፡” እንዲል
(ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶስዮስ 82፡7) ጌታችን ዲያብሎስን በተዋሐደው ሥጋ ሳይሆን በመለኮቱ ኃይል ብቻ ድል
እንዳደረገው አስመስለው የሚናገሩ ጌታችን በተዋሐደው ሥጋ ዲያብሎስን ድል ማድረጉን የሚክዱትን መናፍቃን
በገሰጸበት ትምህርቱ ቅዱስ ሳዊሮስም የደገኛውን የጎርጎርዮስን ትምህርት ጠቅሶ እንዲህ አለ፡ “ሰይጣን በገዳመ
ቆሮንቶስ በተፈታተነው ጊዜ ታገሠ፤ ግን ፈተናውን ሽቶ አይደለም፤ የሚፈታተን የዲያብሎስን ጦሩን ያጠፋ ዘንድ ነው
እንጂ፡፡ ዳግመኛ በመለኮቱ ኃይል ዲያብሎስን አልተዋጋውም፤ በሚታመም በሚሞት ሥጋ ድል አደረገው እንጂ፤
ዳግመኛም በዚህ ሥጋ ኃጢአት ወደዚህ ዓለም እንዳይመጣ በኃጢአት ምክንያት በሁሉ ላይ ሞት ተፈርዶአልና፤ በዚህ
ሥጋም የኃጢአት ፍዳ ጠፋ፣ ይህ ሥጋም ኃጢአትን ያለማ ዲያብሎስን ድል ነሳው አለ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ
ሳዊሮስ ምዕራፍ 85፡16-17)

የመጀመሪያው ፈተና በዚያው በገዳመ ቆሮንቶስ ሲሆን ፈተናውም ስስት ነበር፡፡ ዲያብሎስ ሥጋን የተዋሐደውን አምላክ
ኢየሱስ ክርስቶስን ተርቦ ቢያየው ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ›› በማለት
ፈትኖታል፡፡ ሁለተኛው ፈተና ደግሞ በቤተመቅደስ ሲሆን ፈተናውም ትዕቢት ነበር፡፡ ‹‹መላእክት ያነሱኃል ተብሎ
ተጽፏልና ራስህን ከመቅደስ ጫፍ ወርውር›› (መዝ 90፡11) ይህ ፈተና ከመጻሕፍት ጥቅስ ጠቅሶ የፈተነበት ነው፡፡
ሦስተኛው ፈተና ደግሞ በተራራ ጫፍ (በሰገነት) ሲሆን ፈተናውም የፍቅረ ንዋይ ነበር፡፡ ‹‹ወድቀህ ብትሰግድልኝ
የዓለምን መንግስታት ከብራቸውንም ሁሉ እሰጥሀለሁ›› በማለት ፈትኖታል፡፡ እነዚህ ፈተናዎች ዛሬም በክርስትና ያሉ
ዐበይት ፈተናዎች ናቸው፡፡ እኛም ጌታችንን አብነት አድርገን ሰይጣን በትዕቢት ቢፈትነን በትህትና፣ በስስት ቢፈትነን
በትዕግስት፣ በፍቅረ ንዋይ (ገንዘብን በመውደድ) ቢፈትነን በጸሊአ ንዋይ (ገንዘብን ባለመውደድ) ልናሸንፈው ይገባል፡፡

የተፈተኑት እሴቶች ምንድን ናቸው?


ለገዳማውያን አብነት ለመሆን የተፈተነው ፈተና የጽናት ፈተና ነው፡፡ የገዳማውያን ጾራቸው ስስት (መሳሳት) ነውና
በመጽናት ላይ ለሚመጣባቸው ፈተና አብነት ሊሆን ተፈተነ፡፡ ገዳማውያን እምነትን፣ እውቀትን፣ ጽናትን እንዲያሟሉ
ይጠበቅባቸዋልና፡፡ በቤተመቅደስ ለሚኖሩ ካህናት/በምዕመናን አገልጋዮች በብዛት የሚፈተኑ በትጋታቸው/እውቀታቸው
ነው፡፡ እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል እንደተባለ ክርስትናን ተምረናል አውቀናል በማለት መታበይ ስላለ የካህናት
ጾራቸው ትዕቢት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ መጽሐፍ ተጠቅሶ ፈተናው ይመጣልና ዲያብሎስም ከመጽሐፍ ጠቅሶ ፈተነው፡፡
በባለስልጣናት ዘንድ የሚፈተነው ደግሞ እምነት ነው፡፡ ጾራቸውም ፍቅረ ንዋይ ነውና፡፡ ወድቃችሁ ብታመልኩኝ በሀብት
ላይ ሀብት፣ በስልጣን ላይ ስልጣን እጨምርላችኋላሁ ብሎ ይፈትናል፡፡ የሀሰት አባት ነውና የሌለውን የራሱ አድርጎ
ይፈትንበታል፡፡ ስለዚህም ጌታችን ለሦስቱም አብነት ለመሆን ተፈተነ፡፡

የፈተናዎቹ መፍትሔስ ምን ነበር?

ሁሉን የሚያውቅ ሁሉን የሚችል አምላክ በተለያየ መንገድ የመጡትን ሦስቱን ፈተናዎች እንደየአመጣጣቸው
መለሳቸው፡፡ በስስት የመጣውን በትዕግስት ድል ነሳው፡፡ ‹‹ይህንን ድንጋይ ዳቦ አድርግ›› በማለት የመጣውን ፈተና ‹‹ሰው
በእንጀራ ብቻ አይኖርም፣ በእግዚአብሔር ቃል እንጂ›› ብሎ መለሰለት (ዘዳ 8፡3)፡፡ ይህም ሰው ለሥጋ በሚመገበው
እንጀራ ብቻ ሳይሆን ለነፍስ ምግብ በሚሆነው ቃለ እግዚአብሔርን በመስማትም ጭምር ነው የሚኖረው ማለቱ ነው፡፡
በትዕቢት የመጣውን ፈተና ደግሞ በትህትና ድል ነሳው፡፡ ‹‹መላእክቱ በእጃቸው ያነሱሃል›› ተብሎ ተጽፏልና ራስህን
ወርውር ቢለው ‹‹ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፏልና›› (ዘዳ 6፡16) በማለት አሳፈረው፡፡ በዚህም
አእምሮአችን ረቂቅ፣ ማዕረጋችን ምጡቅ እያሉ በስጦታ በተሰጣቸው ስልጣን ለሚታበዩ የቤተመቅደስ ሰዎች ትህትናን
አስተማረ፡፡  በፍቅረ ንዋይ የመጣውን በጸሊዐ ንዋይ ድል ነሳው፡፡ ‹‹ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም
ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፏልና›› (ዘዳ 6፡13) በማለት መልሶታል፡፡ ነገስታት/ባለስልጣናት ቤታቸውን በከፍታ/በሰገነት
ሠርተው ለሀብትና ለሥልጣን ሲሮጡ በባዕድ አምልኮ ይፈተናሉና ይህንን ድል መንሻ ሠራላቸው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ከተፈተነባቸው ሦስት ፈተናዎች የምንገነዘበው
ፈታኝ የሚፈትነው በደካማ ጎን በመግባት መሆኑን ነው፡፡ የተራበውን በምግብ፣ ያወቀ የሚመስለውን በእውቀቱ፣
ሀብት/ስልጣን የሚወደውን ደግሞ በሀብት/በስልጣን ገብቶ ይፈትነዋል፡፡ በደካማ ጎን ለሚመጡት ፈተናዎች ድል መንሻ
የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ጌታችን ዲያብሎስን ካሳፈረባቸው ሦስት መንገዶች እናስተውላለን፡፡ ሦስቱንም ፈተናዎች
በመጻሕፍት ያለውን እውነት በመግለጥ ዲያብሎስን አሳፍሮታልና፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ  ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ዲያብሎስን ድል ከነሳው በኋላ ፈታኙ እንደራቀው መላእክቱም መጥተው እንዳገለገሉት ሲናገር ‹‹ያን ጊዜ
ዲያብሎስ ተወው፡፡ እነሆ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር›› (ማቴ 4፡11) ብሏል፡፡ እኛም ፈተናን ድል ስንነሳ
ዲያብሎስ (ፈታኝ) ይርቃል፤ መላእክት (ተራዳኢዎች) ይቀርቡናል፡፡ በመጨረሻም ጌታችን በዲያብሎስ ከተፈተነበት
ፈተና የምንማረው ፈተናን ድል ለመንሳት ጾምና ጸሎት መቅደም እንዳለበት ነው፡፡ የእምነት ጥሩር የእግዚአብሔር ዕቃ
ጦር ይህ ነውና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የመዳን ራስ ቁር፣ እምነት ጋሻ፣ የመንፈስም ሰይፍ የእግዚአብሔር ቃል
ነው›› (ኤፌ 6፡10-18) እንዳለው ከዲያብሎስ የሚመጣውን ፈተና ድል ለመንሳት ጽኑ እምነት፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደትና
ምጽዋት ያስፈልጋል፡፡

ፈታኝ ዲያብሎስን በገዳመ ቆሮንቶስ ድል ያደረገ፣ ለቅዱሳን ሁሉ ዲያብሎስን የሚያሸንፉበት ኀይል የሰጠ አምላካችን
እግዚአብሔር ለእኛም በጾማችን ወራት ከክፋት ሁሉ መራቅን እንዲያስችለን፣ የዲያብሎስንም ፈተና ድል
የምናደርግበትን ጥበብ መንፈሳዊ፣ ኀይል መንፈሳዊ ያድለን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።

You might also like