You are on page 1of 5

ምስጢረ ጥምቀት፡ የክርስትና መግቢያ በር

Posted on November 23, 2018 by Astemhro Ze Tewahdo

ጥምቀት(Mystery of Baptism) የሚለው ቃል “አጥመቀ” (አጠመቀ) ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም በተከማቸ ውሃ ውስጥ መነከር፡ መዘፈቅ፡ ገብቶ መውጣት ማለት ነው። ምስጢረ ጥምቀት
በምስጢራዊ (በሃይማኖታዊ) ፍቺው በተጸለየበት ውሃ (ማየ ኅይወት) ውስጥ በሥላሴ (በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ) ስም ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ብሎ የመውጣት ሂደት ነው (ማቴ 28፡19)። ጥምቀት “የክርስትና
መግቢያ በር” ናት፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች ምስጢራት ስለሚቀድምና ለእነርሱም መፈጸም ቅድመ ሁኔታ ስለሆነ ነው፡፡ ጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት (ሀብተ
ወልድና ስመ ክርስትና) ምሥጢር ነው። ሰው ከሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ለመካፈል አስቀድሞ መጠመቅና ከማኅበረ ክርስቲያን መደመር አለበት፡፡ ስለዚህም ምስጢረ ጥምቀት ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት
እንዲሁም ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ የእምነታችን መሠረትም፣ የጸጋ ልጅነት የሚገኝበትም ምስጢር ነውና ከሁለቱም ይመደባል፡፡

የጥምቀት አመሠራረት
የምሥጢረ ጥምቀት መሥራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት “ጥምቀት” ነበራቸው፡፡ ይኸውም
እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ ይህም የእግዚአብሔርም
ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡ ሰውነታቸውን ከአፍአዊ
(ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት መንፈሳዊ ሥርዓት ነበር፡፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን የመሠረተው በሦስት መንገድ ነው። መጀመሪያ በተግባር ራሱ ተጠምቆ እንድንጠመቅ አስተምሮናል፤ አርአያም ሆኖናል (ማቴ 3፡13)፡፡ ሁለተኛም
በትምህርቱ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” (ማር 16፡16) እንዲሁም “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ 3፡3-6) በማለት ጥምቀት ለድኅነት አስፈላጊ
መሆኑን አስተምሯል፡፡ ሦስተኛም ለቅዱሳን ሐዋርያት በሰጣቸው ትዕዛዝ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 28፡19-20) በማለት
ምስጢረ ጥምቀትን መስርቶልናል። ይህንንም መሠረት በማድረግ ሃይማኖታቸው የቀና ቅዱሳን አባቶች “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት
መሠረተ እምነትን ደንግገዋል፡፡

የጥምቀት አስፈላጊነት
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ከተነሱት አባቶች አንዱ “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም” (ራእይ 20:6) የሚለውን የወንጌላዊው
ዮሐንስን አባባል በተረጎመበት የእግዚአብሔር ከተማ በሚለው መጽሐፉ ላይ “ፊተኛው ትንሣኤ” የተባለው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የምናገኝበት ጥምቀት እንደሆነ ገልጿል:: ክርስቶስን መሠረት ያደረገ እምነት ሁሉ
“ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ. 3፡3) የሚለው የጌታ ትምህርት መመሪያው ሊሆን ግድ ነው፡፡ ጌታችን እንዳስተማረውም ያለጥምቀት ድኅነት የለም፡፡ በምስጢረ
ጥምቀት በሚታየው አገልግሎት የሚገኘው የማይታይ ጸጋ ግን ብዙ ነው፡፡ የሚከተሉት በጥምቀት የሚገኙ የማይታዩ ጸጋዎች ናቸው::

ድኅነት: “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” (ማር. 16፡16)

የድኅነት ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንደተናገረው ዘላለማዊ ድኅነትን ለማግኘት የሚሻ ሁሉ ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት አምኖ መጠመቅ ግድ ይለዋል፡፡ ስለዚህም ጌታችን ከሙታን ከተነሳ
በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል›› (ማር 16፡16) በማለት በጥምቀት ድኅነት እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡ ከጌታ ከቃሉ የተማረ ቅዱስ ጴጥሮስ የመምህሩን ትምህርት መሠረት
አድርጎ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፤ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል የሰውነትን
እድፍ ማስወገድ አይደለም” ብሏል፡፡ (1ኛ ጴጥ. 3፡20-21)፡፡ ኖኅና ቤተሰቡ የዳኑበት ውኃ ምሳሌነቱ የጥምቀት መሆኑን ገልጾ አሁንም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ሁሉ በጥምቀት ድኅነትን እንደሚያገኙ በግልጽ
ቃል ተናግሯል፡፡ መዳን ስንል የእግዚአብሔርን መንግሥት ወርሶ የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆን ማለት ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሌሊት የትምህርት መርሐ ግብር
ትምህርቱን በተመስጦ ኅሊና በሰቂለ ልቡና ይከታተል ለነበረው ለኒቆዲሞስ የድኅነት በሩ ጥምቀት እንደሆነ ገልጾለታል “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ
ይችልም” (ዮሐ. 3፡5)፡፡ ይህ ታላቅ ቃልም ጥምቀት ለድኅነት አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል፡፡

ዳግም ልደት: “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም” (ዮሐ. 3፡5)

ጥምቀትን ዳግም ልደት ያስባለው ከሥጋ ልደት የተለየ በመሆኑ ነው፡፡ በአዳምና በሔዋን ስህተት ምክንያት አጥተነው የነበረውን የልጅነት ጸጋ የምናስመልሰው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው፡፡ ዳግም ከሥላሴ
የምንወለደው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው፡፡ ጌታችን “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም” (ዮሐ. 3፡5) በማለት ለኒቆዲሞስ መናገሩን ልብ
ይሏል፡፡ ጌታችን እንደተናገረው ጥምቀት የልጅነትን ጸጋ የምናገኝበት ምሥጢር ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ታላቅ ምሥጢር መሆኑን እንዲህ ሲል አስተምሯል “ዳግመኛ
የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም” (1ኛ ጴጥ. 1፡23)፡፡ ይህ ቃል ጥምቀት የዘላለም ሕይወት እንደሚያሰጥ ያሳያል፡፡ ጌታችን በግልጽ ቃል እንደተናገረው የማይጠፋው የልጅነት ጸጋ የሚገኘው በውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ
በማድረግ በሚፈጸመው ገቢር እንጂ አንዳንዶች ከልቦናቸው አንቅተው እንደሚናገሩት ቃለ ወንጌልን በመስማት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን መንግስቱንም እንወርሳለን፡፡

ሥርየተ ኃጢአት: “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት” (ጸሎተ ሃይማኖት)

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ባወጡት አንቀጸ ሃይማኖት ላይ ካሰፈሩት አንቀጽ አንዱ በጥምቀት ሥርየተ ኃጢአት እንደሚገኝ “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት
እናምናለን” የሚለው ነው፡፡ እነዚህ አባቶች በቅዱስ መጽሐፍ የሰፈረውን በአንዳንድ የቤተክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች አማካይነት ወደ ቤተክርስቲያን ሾልኮ የገባን የስህተት ትምህርት ለማጥራት፣ እምነትን ለማጽናትና
ምእመናንን ከውዥንብር ለመታደግ አንቀጸ ሃይማኖትን ወስነዋል፡፡ ይህ የአበው ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ መሆኑን ከብዙ ማስረጃዎች የምንገነዘበው እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡ በድንቅ አጠራሩ
ለአገልግሎት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ይነጻ ዘንድ “አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ” መባሉን አስተውሉ (የሐዋ. ሥራ 22፡16)፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሣ ተሰብስበው ለነበሩት በትምህርቱ ልቡናቸው በተነካ ጊዜ “ምን እናድርግ?” ብለው ሲጠይቁት የመለሰላቸው “ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” ብሏቸው ነበር (የሐዋ. ሥራ 2፡37-38)፡፡ ይህ ታዲያ ከሌላ በረት ለመጡ በጎች እንጂ በበረቱ ተወልደው በበረቱ ላደጉት በጎች አይደለም፡፡ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” ማለቱ የእርሱን
የባሕርይ አምላክነት ለመግለጽ እና ዓለም እንዲቀበለው ለማስተማር እንጂ ጥምቀት መፈጸም የሚገባው በሥላሴ ስም መሆኑን ጌታችን ራሱ አስተምሯል (ማቴ 28፡19)፡፡ “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኃጢአት”
በሚለው ንባብ ውስጥ ያለችው “ስርየተ ኃጢአት” የምትል ‘ነባር’ ኃጢአትን አመላካች ሐረግ የምታመለከተው ካደጉና ከጎለመሱ በኋላ ተምረው፣አምነው፣አመክሮ (የፈተና ጊዜ) አልፈው ለጥምቀተ ክርስትና የበቁ ንዑሰ
ክርስቲያኖችን እንጂ ሕጻናትን ወይም ጥንተ አብሶን አያመለክትም፡፡

ክርስቶስን መምሰል፡ “ጥምቀት ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበትና በትንሣኤው የምንተባበርበት ነው” (ሮሜ 6፡3-4)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛ
በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ. 6፡3-4) በማለት በጥምቀት ክርስቶስን እንደምንመስለው ተናግሯል፡፡ ማጥመቅ በፈሳሽ ውኃ ነው፤ ጥልቅ ውኃ
በማይገኝበት ጊዜ ግን ውኃ በሞላበት ገንዳ ይፈጸማል፡፡ ይህም ካልሆነ ውኃ ቀድቶ የተጠማቂውን መላ አካል ውኃው እንዲያገኘው በማድረግ በእጅ እየታፈኑ ያጠምቁታል፡፡ በጥምቀት ጊዜ የተጠማቂው አካል በውኃ
እንዲጠልቅ መደረጉ “ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ. 6፡4) የሚለውን በገቢር ለመግለጽ ነው፡፡ እንዲሁም ተጠማቂው ከውኃ ውስጥ ብቅ ማለቱ “በጥምቀት ደግሞ ከሙታን
ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ” (ቆላ. 2፡12) ያለውን እንዲሁ በድርጊት ለማሳየት ነው፡፡

አጥማቂው ካህን “አጠምቀከ/ኪ በሥመ አብ አጠምቀከ/ኪ በሥመ ወልድ አጠምቀከ/ኪ በሥመ መንፈስ ቅዱስ” እያለ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያደረገ ድርጊቱን ሦስት ጊዜ መፈጸሙ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት አምኖ
መጠመቁን ለማጠየቅ ሲሆን እንዲሁም የጌታን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር አድሮ መነሳቱንና ተጠማቂዎችም ኋላ በትንሣኤ ዘጉባኤ “ንቃ መዋቲ” የሚለው አዋጅ ሦስት ጊዜ በሚታወጅበት ጊዜ በቀዋሚ አካል
በምትናገር አንደበት ከራስ ጠጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ከቁጥር ሳይጎድሉ ከሰውነታቸው ሳይከፈሉ ወንድ በአቅመ አዳም ሴት በአቅመ ሔዋን መነሳታቸውን ለማዘከር ነው፡፡ ስለዚህ ጥምቀት “ከክርሰቶስ ጋር ከሞትን
ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን” (ሮሜ. 6፡8) በሚለው የሐዋርያው ቃለ ትምህርት መሠረት ጥምቀት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበት በትንሣኤውም የምንተባበርበት ታላቅ
ምሥጢር ነው፡፡

የክርስቶስ አካል መሆን፡ “ጥምቀት የክርስቶስ አካል መሆናችን የሚረጋገጥበት ነው” (ገላ 3፡27)

በዘመነ ብሉይ የአብርሃም ወገኖች የአብርሃም ልጆች መሆናቸው ይረጋገጥ የነበረው በግዝረት ነበር፡፡ ግዝረት በኦሪቱ የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ እንዲጠፋ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ
ነበር (ዘፍ. 17፡14)፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በአምሳልነት ሲፈጸም የኖረው ግዝረት በዘመነ ሐዲስ በጥምቀት መተካቱን “በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣል ሰው ሰራሽ ያይደለ ግዝረትን
የተገዘራችሁበት፤ በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ” (ቆላ. 2፡11-12) በማለት አበክሮ ያስገነዝባል፡፡ ግዝረት ለሕዝበ
እግዚአብሔር የአብርሃም የቃል ኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደነበር ሁሉ ጥምቀት ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ
የሚገኘው ጸጋ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል፡፡ በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና” (ገላ. 3፡27) በማለት ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በጥምቀት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት የምንለብሰውና የክርስቶስ ተከታዮች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡

የጥምቀት አከፋፈል (ዓይነቶች)


የንስሐ ጥምቀት፡ የንስሐ ጥምቀት ልጅነትን ላገኙ ሰዎች ሕይወት ፈተና ለሚደርስባቸው ድካምና ጉስቁልና ፈውስ እንዲሆን የሚሰጥ ሊደጋገምም የሚችል የጥምቀት ዓይነት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ያጠምቀው
የነበረ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ማሳያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ዮሐንስ ጥምቀትን ያጠምቅ የነበረ ቢሆንም የዮሐንስ ጥምቀት ልጅነትን የሚያሰጥ ጥምቀት አልነበረም:: የዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር:: የዮሐንስ
ጥምቀትን አቅምንም ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል:: እድፍ ቆሻሻ የያዘው ልብስ በውኃ ታጥቦ ነጽቶ ሽቱ ይርከፈከፍበታል:: ገላም ሲያድፍ በውኃ ታጥቦ ጽዱ ልብስ ይለብሳል:: እንደዚሁም ሁሉ
የዮሐንስ ጥምቀት ተጠማቂዎቹ ኋላ በክርስቶስ ጥምቀት የሚሰጠውን መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በቅተው እንዲገኙ ከኃጢአት መለየታቸውንና ተለየን ማለታቸውን የሚገልጽ ምልክት ነበር:: ራሱም አንዲህ ሲል መስክሯል
“እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ …ከኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ግን በእሳት ያጠምቃችኋል..” (ማር 1፡4-8 ማቴ 3፡11 ሉቃ 3፡16 ሐዋ 19፡4)፡፡ በነቢዩ ሕዝቅኤልም ‹‹ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም
ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።
መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ›› (ሕዝ
36፡25-28) ተብሎ የተtነገረውም የንስሐ ጥምቀትን የሚያመለክት ነው፡፡

የልጅነት ጥምቀት፡ አስቀድመን በሥጋ ከእናትና አባታችን በዘር በሩካቤ እንደተወለድንና የሥጋ ልጅነትን እንዳገኘን ሁሉ በማየ ገቦ ስንጠመቅ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጌታችን “ከሥጋ
የሚወለድ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው” ብሎ ከማስተማሩ በፊት “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” በማለት (ዮሐ.3፥3 እና 6) በምሥጢረ ጥምቀት ሀብተ
ወልድና ስመ ክርስትና ስለመገኘቱ አስተምሯል፡፡ ሐዋርያውም በጥምቀት ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ አስመልክቶ ሲናገር “አባ አባት ብለን የምንጮኸበትን (የምንጣራበትን) የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና
ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈስ ጋር ይመሰክራል” ብሏል (ሮሜ.8፥15-16)፡፡ ጌታችንም ለተቀበሉት ሁሉ በስሙም ላመኑበት በጠቅላላው
የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አለመወለዳቸው ተገልጿል (ዮሐ.1፥11-13)፡፡ እንግዲህ እኛ
ክርስቲያኖች ሁለት ልደታት እንዳሉን እናስብ፡፡ ይኸውም መጀመሪያው ከሥጋ እናትና አባታችን የተወለድነው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር የምንወለደው ነው፡፡ ከተወለድን በኋላ እድገታችን በሁለቱም ወገን
መሆን ያስፈልጋዋል፡፡ ሰው ሥጋዊም መንፈሳዊም ነውና፡፡ ገላ 3፡26 ፡ ቲቶ 3፡5 ፡ 1ኛጴጥ 1፡23

የልጅነት ጥምቀት በምን ይፈጸማል?


ልጅነት የምታሰጠዋ ጥምቀት አንዲት ናት (ኤፌ 4፡4-5)፡፡ ነገር ግን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ልትፈጸም ትችላለች። የውሃ ጥምቀት በካህናት አማካኝነት በተጸለየበት ውሃ ውስጥ በሥላሴ ስም ተጠምቀን በመንፈስ ቅዱስ
ግብር ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ነው (ዮሐ 3፡3-6)፡፡ ጥምቀት በመርህ ደረጃ በውኃ የሚፈጸም ነው፡፡ ውኃው በጸሎት በተባረከ ጊዜ ልጅነትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሚያድርበት በእምነት ሆኖ በውኃ
የሚጠመቅ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ይወለዳል፡፡ ጥምቀት የእግዚአብሔር ቸርነት መገለጫ ነው፡፡ ማንም ሰው ደሃ እንኳ ቢሆን ቢያንስ ውኃ ይኖረዋልና በጸጋ ከእግዚአብሔር እንወለድ ዘንድ በውኃ መጠመቅ ይገባል፡፡
በውኃ መጠመቅ እየቻሉ መጠመቅን እንደተራ ነገር አድርገው የሚያቃልሉ ሰዎች ኤሳው እንዳቃለላት ብኩርና ባለማወቅ የእግዚአብሔርን ጸጋ ያቃልላሉ፡ በአንጻሩ ደግሞ በፍጹም ልብ የክርስትናን ትምህርት አምነው
ከመጠመቃቸው በፊት በሰማዕትነት የሚያርፉ ሰማዕታት እግዚአብሔር ባወቀ የልጅነትን ጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ወይም ከእሳት ይቀበላሉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማለት ደግሞ በውሃ ሳንጠመቅ እግዚአብሔር
በፍቃዱ ጸጋውን በመላክ የሚሰጠን ልደት ነው። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን ቅዱሳን ሐዋርያት የተጠመቁት ጥምቀት ነው (ሉቃ 3፡16 ፡ ሐዋ 1፡5 ፡ ሐዋ 2፡1-4 ፡ 1ኛ ቆሮ 12፡13)፡፡ ሦስተኛው የደም ጥምቀት ሲሆን ይህ
የሰማዕታት የጥምቀት ዓይነት ነው። የክርስትናን እምነት በመማር ላይ ሳሉ ወይም ተምረው ሳይጠመቁ ወይም ሁለቱንም ሳያውቁ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ብለው መሥዋዕት መሆናቸውን ተመልክተው “ኢየሱስ
ክርስቶስ እውነተኛ አምላክ ነው፤ የክርስቲያኖች እምነት እውነተኛ ነው” በማለት መስክረው በሰማዕትነት የሚሞቱ ሰዎች ደማቸው /ስቃያቸው/ በእግዚአብሔር ቸርነት እንደ ጥምቀት ይቆጠርላቸዋል። ልጅነትን ያገኙበታል፤
ኃጢአታቸውም ይሰረይላቸዋል።

ጥምቀት እንዴት ይፈጸማል?


ተጠማቂው ንዑሰ ክርስቲያን ከሆነ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርቶችን ተምሮ እምነቱ የተመሰከረለት መሆን አለበት። ሕጻናት የሆኑ እንደሆኑ ግን ለሕጻናቱ የክርስትና እናትና አባት ሊሆኑ የመጡት ሰዎች ስለሕጻናቱ
እምነት መስክረውላቸው እንዲጠመቁ ይደረጋል። በሚጠመቅበት ጊዜ በውሃ ውስጥ ሶስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማለት አለበት ፤ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምሳሌ ነውና። ተጠማቂው የሚጠመቀው በአብ በወልድና በመንፈስ
ቅዱስ ስም ነው (ማቴ 28 ፥ 19)። ተጠማቂዎች ባለትዳሮች ከሆኑና ቤተሰብም ካላቸው ሁሉም ተምረው አምነው በአንድነት መጠመቅ አለባቸው። ከተጠመቀ በኋላ መቁረብ (ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል)
ይገባል። ይህ ካልሆነ ጥምቀቱ ህያው አይሆንም።

እንዲያጠምቁ ስልጣን ያላቸው ከክህነት ደረጃዎች ውስጥ ኢጲስቆጶስና ቀሳውስት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማጥመቅ ስልጣንን የሰጠው ለአስራ አንዱ ሐዋርያት ብቻ ስለሆነ ነው (ማቴ
28፡19)፡፡ ዲያቆናት እንዲያጠምቁ አልተፈቀደላቸውም (ማቴ 28፡19 እና ፍት ነገ አንቀጽ 3)። ክህነት በሌለው ሰው የተከናወነ ጥምቀት እንደ እጥበት እንጂ እንደ ጥምቀት አይቆጠርም፡፡ በዚህ መንገድ “የተጠመቀ” ሰው
ልጅነት የምታስገኘዋን እውነተኛዋን ጥምቀት መጠመቅ አለበት፡፡ ጥምቀት በመድፈቅ ወይም በመንከር ነው እንጂ በመርጨት (በንዝሐት) አይፈጸምም፡፡ ምሳሌውን፣ ምስጢሩንና ሥርዓቱን ያፋልሳልና፡፡ ጥምቀት ማለት
መነከር ማለት ስለሆነ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን ያመለክታል፡፡ ስለዚህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ ውኃ ውስት ገብቶ በመውጣት ይከናወናል (ማቴ 28፡19)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም የተገለጠው
በመንከር የተከናወነው ጥምቀት ነው፡፡

በሐዋርያት ሥራ ላይ “ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ
ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና (ሐዋ 8፡38-39)” በሚለው ቃል ውስጥ “ከውኃ ከወጡ በኋላ” የሚለው የሚያመለክተው ጃንደረባው የተጠመቀው ውኃ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ነው፡፡ “እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር
ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ
ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን (ሮሜ 6፡4-5 ቆላ 2፡12)” በሚለው ቃል ውስጥ መቀበር መቃብር ውስጥ መግባትን፣ ትንሣኤ ደግሞ ከመቃብር መውጣትን እንደሚያመለክት ጥምቀትም በውኃ ውስጥ ገብቶ
(በመነከር) መውጣትን ይጠይቃል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም (ቲቶ 3፡5)” እንዲሁም “አሁንስ ለምን
ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ (ሐዋ 22፡16)” ተብሎ ለሳውል በተነገረው ቃል ውስጥ “መታጠብ” ሰውነትን በሙሉ ነውና ጥምቀትም በመነከር ይከናወናል፡፡ በአራቱም ወንጌላት
የጌታችን ጥምቀትም በውኃ ውስጥ ገብቶ በመውጣት መሆኑ ተጽፏል፡፡ “ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም
ሲመጣ አየ (ማቴ 3፡16)” በሚለው ቃል ውስጥ “ከውኃ ወጣ” የሚለው የጌታችን ጥምቀት የተከናወነው በመነከር እንደነበር ያሳያል፡፡ መረጨት ወይም ማፍስስ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን አይጠይቅምና፡፡
በተጨማሪም በሥጋ መወለድ በእናት ማኅፀን ውስጥ ቆይቶ መውጣትን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ “ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድም” እንዲሁ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን (መነከርን) ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም
ነው ጥምቀት “ዳግመኛ መወለድ” የተባለው (ዮሐ 3፡3)፡፡

ስመ ክርስትና (የክርስትና ስም)


ስም አንድ ሰው ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት ነው። ሰው ከእናትና ከአባቱ ሲወለድ ስም እንደሚወጣለት ሁሉ በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድም ስም ይወጣለታል፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት
ስሞች ሊኖሩት ይችላል። አባትና እናት የሚያወጡለት ስም የተጸውኦ ስም ይባላል፡፡ በጥምቀት ጊዜ የሚወጣለት ስም ደግሞ የክርስትና ስም ይባላል፡፡ በጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ይገኝበታል፡፡ በክርስቶስ
የሚያምን ሰው ክርስቲያን ሲባል እምነቱ ደግሞ ክርስትና ይባላል። ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ወገን የሆነ ማለት ነው። በመሆኑም በክርስቶስ አምነን በሥላሴ ስም መጠመቃችንን የሚገልጸው ስም ስመ ክርስትና
ይባላል። ስያሜውም ተጠማቂው ከተጠመቀበት ዕለት ጋር ተያይዞ ሊሰየም ይችላል። በመንፈሳዊ አገልግሎት ስንሳተፍ ስመ ክርስትናችንን እንጠቀማለን፡፡ የክርስትና ስም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊት ያለው ነው፡፡ ይህም
እግዚአብሔር አብራምን አብርሃም፣ ያዕቆብን እስራኤል፣ ሰምዖንን ጴጥሮስ፣ ሳውልን ጳውሎስ እንዲባል እንዳደረገው ያለ ነው፡፡

ለጥምቀት የተወሰነ ዕድሜ


በሐዋርያት ስብከት ያመኑና በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሁሉ ይጠመቁ ነበር (የሐ ሥራ 16፡ 15 1ቆሮ 1፡15) ። በኋላ ግን ወላጆቻቸው ሊያስተምሯቸው ቃል እየገቡ ልጆቻቸውን ወንዶችን በአርባ ሴቶችን
በሰማንያ ቀናቸው ማጥመቅ ተጀመረ ። ለዚህም መሠረቱ የእስራኤል ልጆች በተወለዱ ወንድ በአርባ ሴት በሰማንያ ቀናቸው ወላጆቻቸው መባዕ (ስጦታ) ይዘውላቸው ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ በእስራኤልነት (የዜግነት)
መዝገብ እያስመዘገቡ የተስፋዋ ምድር ከነዓን ባለመብቶች (ወራሾች) ያደርጓቸው እንደነበረ ነው (ዘሌ 12፡1-10)፡፡ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ፣ ሔዋንም በተፈጠረች በ80 ቀኗ ወደ ርስታቸው ገነት እንደገቡ ሕጻናትም በ40
እና በ80 ቀናቸው ተጠምቀው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ወደሆነችው ወደ ቤተክርስቲያን ይገባሉ፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ህጻናት ወላጆቻቸው እንዲሁም ክርስትና እናት ወይም አባት ሃይማኖታቸውን ሊያስተምሯቸው ሃላፊነት ወስደው የክርስትና አባት ወይም እናት በተጨማሪ ቃል ገብተው ክርስትና በመነሳት
(በመጠመቅ) የወላጆቻቸውን ርስት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ።ከአርባ እና ከሰማንያ ቀን በኋላ የሚመጡ ተጠማቂዎች ግን ሃይማኖታቸውን ተምረው ካመኑ በኋላ በማንኛውም የዕድሜ ክልል መጠመቅ ይችላሉ ።
በሕይወት እስካሉ ድረስ መቸም ቢሆን ከመጠመቅ የሚያግዳችው ነገር የለም ።

የክርስትና አባትና እናት


በ40 እና በ80 ቀናቸው ለሚጠመቁ ሕጻናት ስለ እምነታቸው ባለው ነገር ሁሉ ኃላፊነት የሚወስዱ የክርስትና አባትና እናት እንዲኖራቸው ያደረጉት በ4ኛው መ/ክ/ዘ የነበረው የቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያው ኢጲስ
ቆጶስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ናቸው። ዓላማውም መንፈሳዊ ዝምድናን (አበ ልጅነትን) ማጠናከሪያ መንገድ ነው። በአበ ልጅነት የተዛመዱ ሰዎች በጋብቻ መዛመድ አይችሉም። በሥጋ የተዛመዱ ከ7ተኛ የዝምድና ሐረግ
በኋላ መጋባት የሚፈቀድ ሲሆን በአበ ልጅ ግን የተዛመደ ግን የቁጥር ገደብ የለውም (ፈጽሞ መጋባት አልተፈቀደለትም)፡፡ ይህም የሚያሳየው ከሥጋ ዝምድና ይልቅ ክብር የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ዝምድና መሆኑን ነው።

ከክርስትና አባትነትና እናትነትን የሚከለክሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም የሥጋ ዝምድና ያላቸው፣ የጋብቻ ዝምድና ያላቸው፣ ዕድሜያቸው ለማስተማር ለማሳመን ያልደረሰ፣ እምነት ትምህርት ችሎታ የሌላቸው፣ እምነታቸው
ከተጠማቂው ጋር ተመሳሳይ ያልሆነ ናቸው፡፡ የጾታ ሁኔታ በተመለከተ ወንድ ወንድን ሴት ሴትን ያነሣል እንጂ ወንድ ሴትን፡ ሴት ወንድን ክርስትና ማንሣት አይፈቀድላቸውም፡፡ የክርስትና አባትና እናት ክርስትና ያነስዋቸው
ልጆች በሥጋ ከወለድዋቸው ልጆች ሳይለዩ ሕጻናቱ ዕድሜያቸውም ለትምህርት ሲደርስ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት የማስተማር ግዴታ እንዳለባቸው ቃል ይገባሉ። በገቡት ቃል መሠረት በተግባር የመተርጎም
ኃላፊነት አለባቸው።
ማዕተብ (ክር) ማሰር
ማዕተብ የሚለው ቃል ዐተበ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አመለከተ ማለት ነው። ስለዚህ ማዕተብ ማለት ምልክት ማለት ነው። በሃይማኖት አምነው ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የሚሰጥ ምልክት
(መታወቂያ) ወይም ማኅተም ነው። ስለ ማዕተብ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል። በብሉይ ኪዳን የነበሩ አባቶች ለእምነታቸው መገለጫ ምልክት ነበራቸው። ለምሳሌ ለአበ ብዙኃን አብርሃም ግዝረት
ተሰጥቶት ነበር (ሮሜ 4፡13 ፡ ዘፍ 17፡9-14)። ማዕተብ ክርስቶስ በገመድ መታሰሩንና መጎተቱን የሚያስታውስ ምልክትም ነው፡፡ “ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን
ተቀብሎአልና (1ኛ ጴጥ 2:21)።” እንተባለ የክርስቶስን መከራ እናስብበታለን (ዮሐ 18፡12-24)

ማዕተብ በሦስት ዓይነት ቀለም መሆኑ የሦስትነት (የሥላሴ) ምሳሌ ነው። ሦስቱ ክሮች ደግሞ በአንድ ተገምደው መሠራታቸው የአንድነቱ ምሳሌ ነው። ክርስቲያን ማዕተብ በማሰሩ ስለ ክርስቲያንነቱ ሳያፍር
ይመሰክርበታል፤ አጋንንትን ድል ይነሣበታል፡፡ ተጸልዮበት ተባርኮ የሚታሠር ነውና ከቤተክርስቲያን በረከት ያገኝበታል፡፡ ማዕተብ ማሰርን ያስጀመረው ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ክርስቲያኖችን ከመናፍቃን ለመለየት
ማዕተብ ያስርላቸው እንነበር በመጻሕፍት ተጽፏል፡፡

የሚታይ አገልግሎት፤ የማይታይ ጸጋ


በምስጢረ ጥምቀት የሚታይ አገልግሎት ተጠማቂው ውሃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ሲል፤ ሥርዓተ ጸሎቱ ሲከናወን፤ ተጠማቂው ነጭ ልብስ ሲጎናጸፍ፣ ማዕተብ ሲያስር ወይም ሲታሰርለት ወዘተ. . .ነው፡፡ ይህም በዓይናችን
ልናየው የምንችለው ነው፡፡ በምስጢረ ጥምቀት የሚገኝ የማይታይ ጸጋ ደግሞ ውኃው ወደ ማየ ገቦነት ሲለወጥ፤ ተጠማቂው የእግዚአብሔር ልጅነትን ሲያገኝ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ፡ ንጸሕናን ቅድስናን ገንዘብ ሲያደርግ
ወዘተ. . . ናቸው፡፡ ምስጢረ ጥምቀትም በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚገኝበት ልዩ ምስጢር ነው፡፡

የጥምቀት ምሳሌዎች
አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሔዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው (ዘፍ. 14፡17) ፡፡ ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡
ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል (2ነገ. 5፡14)፡፡ ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው
ምሳሌ ነው፡፡

የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ. 7፥13)፡፡ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ
ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ
ነው እንጂ” (1ጴጥ. 3፥20) በማለት ገልጾታል፡፡ የጥፋት ውሃ በኖኅ ዘመን በበደላቸው ተጸጽተው ንስሓ ያልገቡ ሰዎችንና (ከኖኅና ቤተሰቡ እንዲሁም ለዘር እንዲቀሩ ከተደረጉት ፍጥረታት በቀር) በምድር የሚኖሩትን ሁሉ
ያጠፋው ማየ አይኅ(የጥፋት ውሃ) የጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ፤ ከጥፋት ውሃ የዳኑት ኖኅና ልጆቹ ፤ ከክርስቶስ ጎን ለጥምቀታችን በፈሰሰው ትኩስ ውሃ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደው ከፍርድ ለሚድኑ ምዕመናን
ምሳሌ ነው።

ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር (ዘፍ. 17፥9) “በሰው እጅ ያልተደረገ
መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል” (ቈላ. 2፥11)፡፡ ግዝረት ለጊዜው
ለእስራኤል ዘሥጋ መለያ ሲሆን ፤ ፍጻሜው ግን ሊመጣ ላለውና ለእሥራኤል ዘነፍስ ምዕመናን መክበሪያ ለሆነው ለጥምቀት ምሳሌ ነው ።

የእስራኤል የኤርትራ ባህርን (ቀይ ባህርን) መሻገርም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፀ 14፡21 ። 1ቆሮ 10፡1) ። ሙሴ የክርስቶስ ፤ ባህሩን የከፈለባት በትር የመስቀል፤ ባህረ ኤርትራ የፍርድና የሲኦል ፤ በተከፈለው ባህር የተሻገሩት
እስራኤል በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ በጥምቀት ከእግዚአ ብሔር ተወልደው ባህረ ኃጢአትን የሚሻገሩ ምዕመናን ምሳሌ ነው ።ኢያሱ የዮርዳኖስን ባህር ክፍሎ እስራኤል መሻገራቸውም እንዲሁ የጥምቀት ምሳሌ ነው
(ኢያ 3፡14 4፡15) ። ኢያሱ የክርስቶስ ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት ፤ ዮርዳኖስን የተሻገሩ እስራኤል በክርስቶስ አምነው በመጠመቅ የዳኑ ምዕመናን ምሳሌ ነው። የዮሐንስ ጥምቀት (ማቴ 3፡1) የአማናዊት ጥምቀት ምሳሌ ነበር።
ዮሐንስ ህዝቡን የንስሓ ጥምቀት እያጠመቃቸው ከቆየ በኋላ ጌታ በሚመጣበት ጊዜ ግን እነሆ የእግዚአብሔር በግ በማለት ወደ ጌታ መርቷቸዋል ስለዚህ የዮሐንስ ጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ለአማናዊዉ የጌታ ጥምቀት
የሚያዘጋጅ ነው፡፡

ጥምቀት አንዲት ናት!


የልጅነት ጥምቀት አንዲት ናት፤ አትደገምም (ኤፌ 4፡5) “ኃጢአት በሚሠረይባት አንዲት ጥምቀት እናምናለን” እንዲል፡፡ ከወላጆቻችን በሥጋ የምንወለደው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ከውሃና ከመንፈስም
ከእግዚአብሔር የምንወለደውም (የምንጠመቀው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው ። የጥምቀት ምሳሌ የነበረው ግዝረት አንድ ጊዜ ብቻ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም አንድ ጊዜ ነው (ቆላ 2 ፥ 11)። ከጌታ ሥጋና ደም የምንሳተፍበት
ምሥጢር በመሆኑ ጌታም የሞተውና የተነሳው አንድ ጊዜ ነውና አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን (ሮሜ 6፡3)። በእኛ ቤተ ክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ በሌላ ሃይማኖት ገብቶ እንደገና ቢጠመቅ ወይም ከሌላ እምነት ተከታይ
ጋር ጋብቻ ቢመሠርት በንስሓ ከተመለሰ በኋላ መጽሐፈ ቄደር ተጸልዮለት ይጠመቃል። ይህ ግን ሁለተኛ ጥምቀት ሳይሆን የንስሓ ጥምቀት ይባላል። ከኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Churches) በቀር በሌላ
ማንኛውም ቤተክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ አምኖ የሚመጣ ሰው ቢኖር እንደገና ይጠመቃል።

የሕፃናት ጥምቀት
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕጻናትን በ40 እና በ80 ቀን ስታጠምቅ ምስጢራትን፣ ምሳሌዎችን፣ ትውፊትን እንዲሁም የጌታንና የሐዋርያትን አስተምህሮ መሠረት አድርጋ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም
እንደሚናገረው ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ኃጢአትበደል አለባቸው ብላ ሳይሆን ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምረው ፍቅሩን እያጣጣሙ እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋ
ልትሰጣቸው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ያውቃሉ ወይም አያውቁም ብላ አይደለም፡፡ የቤተሰቦቻቸውን እምነትና ፈቃድ ምስክር በማድረግ ነው እንጂ፡፡

1. አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ በ40 እና በ80 ቀናቸው ወደ ገነት መግባታቸው (ኩፋ 4፡9)፡፡
2. እስራኤል መስዋዕት ይዘው በ40 እና በ80 ቀን ወደ ቤተመቅደስ እንዲመጡ መታዘዛቸው (ዘሌ 12፡1-8)፡፡
3. በኦሪቱ ሕፃናትም አዋቂዎችም ተገርዘው የተስፋው ወራሾች ነበሩና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ 17፡1-5 ቆላ 2፡11-12)፡፡
4. በባህረ ኤርትራ የተሸገሩት ሕፃናትም ጭምር ነበሩና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (1ኛ ቆሮ 10፡1-2)፡፡
5. ወደ ኖኅ መርከብ የገቡት መላው ቤተሰብ ነውና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ 7፡1-17 1ኛ ጴጥ 3፡20-22)፡፡
6. ሕፃናት በማኅፀን ሳሉ መንፈስ ቅዱስ ከሞላባቸው ሲወለዱ እንዳይጠመቁ የሚከለክለቸው ምንድን ነው (ሉቃ 1፡15 ኤር 1፡4-5)፡፡
7. ሐዋርያትም ካስተማሩ በኋላ ቤተሰቡን ሙሉ ያጠምቁ ነበር (ሐዋ 10፡44-48 11፡13-14 16፡15 16፡43)፡፡
8. ጌታችንም “ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ…” ያለው ሕፃናትንም ይመለከታል (ዮሐ 3፡8)፡፡
9. ጌታችንም “ሕጻናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው” ብሏል (ማቴ 19፡14)፡፡

በአንዳንዶች ዘንድ የሕጻናት ጥምቀት ለዳግም ልደት ወይስ ለጥንተ አብሶ ስርየት? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በዚህ ላይ የጥንተ አብሶ ትርጉም ጋር በተያያዘ የተለያየ አመለካከት አለ፡፡ አንዳንዶች የሕጻናት ጥምቀት ጥንተ አብሶን
ለማጥፋትና ልጅነትን ለማግኘት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በጥንተ አብሶ ምክንያት የተጎዳውን የሰውን ባህርይ ለመጠገንና ልጅነትን ለማግኘት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ጥንተ አብሶ በክርስቶስ ጠፍቶልናል፤ የሕጻናት
ጥምቀት ለዳግም ልደት ብቻ ነው ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ሕጻናት ዳግም ልደትን ያገኙ ዘንድ መጠመቅ እንዳለባቸው ሁሉም ይስማማል፡፡

የሕጻናት ጥምቀት መብትን ይጋፋልን?


ጥምቀተ ክርስትና ሁል ጊዜ ተጠማቂው ተጠይቆ ላይፈጸም ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ተጠማቂው ህጻን የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ለህጻናት የሚያስፈልጋቸውን እናደርግላቸዋለን እንጂ ፈቅደዋል (አልፈቀዱም) በሚል
ግብዝነት ተይዘን ከጽድቅ ጉዞ እንዲለዩ አናደርግም፡፡ ይሁንና አንዳንዶች የሕጻናትን ጥምቀት መብተን መጋፋት አስመስለው ባለመረዳት ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ
ሆኖ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረው በኋላ በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎበታል፡፡ ይህም እፍታ ለአዳም የልጅነትን ጸጋ ያገኘበት ጥምቀቱ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ታሪክ በያዘው የኦሪት ዘፍጥረት
መጽሐፍ ላይ እግዚአብሔር ለአዳም የልጅነት ጸጋውን ከመስጠቱ በፊት እንደ ጠየቀው አይናገርም፡፡ ታዲያ እንዴት የሠላሳ ዓመቱ ጎልማሳ አዳም ያልተጠየቀውን ጥያቄ የአርባ ቀን ልጅ ጠይቁ ማለት ይቻላል? እግዚአብሔር
አዳምን አልጠየቀውም ማለት አስገደደው ማለት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሕጻናትን በቀጥታ እነርሱን አልጠየቀችም ማለት አስገድዳቸዋለች ማለት አይደለም፡፡ አዳም የኋላ ኋላ በፈቃዱ ፈጣሪውን ክዶ ልጅነቱን
እንዳጣ እንዲሁ የእግዚአብሔርን አባትነት ያልፈለጉትም አድገውም ቢሆን የመካድ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡

ማጠቃለያ
ምስጢረ ጥምቀት ከሥጋ የተወለደ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልዶ የእግዚአብሔርን የጸጋ ልጅነት የሚያገኝበት ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ ይህም ምስጢር ከሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ቀዳሚው ስለሆነ
“የክርስትና በር/መግቢያ” ይባላል፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢረ ጥምቀትን ራሱ ተጠምቆ አርአያ በመሆን፣ ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ መሆኑን በማስተማር፣ እንዲሁም ሐዋርያቱ
እንዲያጠምቁ በማዘዝ መስርቶልናል፡፡ በዚህም መሠረት በሥላሴ ስም የተጠመቀ ሰውም አምላኩ ክርስቶስ፣ እምነቱ ክርስትና፣ ማንነቱ ክርስቲያን፣ እናቱ ቤተክርስቲያን ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ
ቤተክርስቲያን ምስጢረ ጥምቀትን የእምነት መሠረት በመሆኑ ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት፣ ተፈጻሚ ምስጢር በመሆኑ ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን በመመደብ ታላቅ ቦታ ትሰጣለች፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ አምኖና
ተጠምቆ በቀናችው የሃይማኖት መንገድ ተጉዞ ዘላለማዊ ሕይወትን ይወርስም ዘንድ የሕይወትን ቃል ትመግባለች፡፡ በጥምቀት ከማይጠፋ ዘር የወለደን፣ በሞቱና በትንሣኤው እንመስለው ዘንድ ተጠምቆ ተጠመቁ ያለን
የቅዱሳን አምላክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀት የተሰጠንን የልጅነት ጸጋ ይጠብቅልን፤ ለዚህ ጸጋ ያልበቁትን ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግቢያ ያመጣልን ዘንድ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ
ይሁንልን፡፡
This entry was posted in Uncategorized by Astemhro Ze Tewahdo. Bookmark the permalink [https://astemhro.com/2018/11/23/baptism/] .

About Astemhro Ze Tewahdo


ይህ የጡመራ መድረክ (አስተምህሮ) የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡
View all posts by Astemhro Ze Tewahdo →

4 THOUGHTS ON “ምስጢረ ጥምቀት፡ የክርስትና መግቢያ በር”

ኖመ
on October 13, 2020 at 10:32 pm said:

ናመስግን ክብረት ይሃበልና

 Like

mintesinot zewdu
on April 18, 2021 at 5:21 am said:

ይህም ካልሆነ ውኃ ቀድቶ የተጠማቂውን መላ አካል ውኃው እንዲያገኘው በማድረግ በእጅ እየታፈኑ ያጠምቁታል ? ውሃ ውስጥ
ገብቶ ከመውጣት አይለይም::

 Like

yilkalyizengaw
on March 11, 2023 at 7:06 pm said:

ጽሁፍ አስተማሪ ነው።እግዜአብሄርቃለ ህይወት ያሰማልን።

 Like

ኤፍሬም
on March 29, 2023 at 4:12 am said:

ለምንድን ነው ህጻናት ሲጠመቁ ለምን ይላጫሉ?

 Like

You might also like