Professional Documents
Culture Documents
November 30, 2018 Astemhro Ze Tewahdo Mystery of Eucharist)
November 30, 2018 Astemhro Ze Tewahdo Mystery of Eucharist)
ምስጢረ ቁርባን (Mystery of Eucharist) ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት አንዱ ነው፡፡ ሃይማኖታቸው የቀናና እውነተኛ የሃይማኖትን መንገድ ያቀኑ ቀደምት አበው (ሠለስቱ ምዕት) “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት
ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት (ከሁሉ በላይ በምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን)” ብለው የሃይማኖትን ድንጋጌ ያስቀመጡት በቅድስት ቤተክርስቲያን ምስጢረ
ምስጢራት (የምሥጢራት ሁሉ ማጽኛ ማኅተም) የተባለው ምስጢረ ቁርባን ስለሚፈጸምባት ነው፡፡ ይህም ምስጢር የሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን መክብባቸውና መፈጸሚያቸው ነው፡፡ የሰው ልጆች ድኅነትን
(የዘላለም ሕይወትን) የምናገኝበት፣ በክርስቶስ ቤዛነት ያገኘነውን ነፃነት በሥጋዊ ድካም በኃጢአት ስናሳድፈው ደግሞ ለዘለዓለም ሕያው ከሆነ መስዋዕት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እየተካፈልን፣ በድቅድቅ ጨለማ የተመሰለ
ኃጢአትን ድል አድርገን ለሰርጉ ቤት ለመንግስተ ሰማያት የተገባን የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡
በሁለት ተከታታይ የአስተምህሮ ጦማሮች ምስጢረ ቁርባንን የሚመለከቱ ዋና ዋና ጥያቄዎችን አጠር ካለ ማብራሪያ ጋር እናቀርባለን፡፡
ከአባታችን አዳም ጀምሮ የነበሩ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን በኃጢአታቸው ከእግዚአብሔር በተለዩ ጊዜ ሁሉ በግና ላምን የመሳሰሉ እንስሳትን በእምነት መስዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር፤ እግዚአብሔርም መስዋዕታቸውን
እየተቀበለ ይታረቃቸው ነበር፡፡ በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት የነበሩት ሁሉ በዚህ ሥርዓት አልፈዋል፡፡ አበ ብዙሐን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ለመሰዋት ወደ ሞሪያ ተራራ በሚወስደው ሰዓት የክርስቶስ ምሳሌ የሆነ ይስሐቅ
አባቱን አብርሃምን የጠየቀው ጥያቄና በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘው የአብርሃም ምላሽ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን መስዋዕት መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ያስረዳናል፡፡ በዘመነ ብሉይ መስዋዕቱ ምድራዊ፣
አቅራቢውም ምድራዊ ነው፡፡ ይስሐቅ እንደተለመደው የመስዋዕት በግ እንዳልተያዘ ባየ ጊዜ “አባቴ ሆይ…እሳቱና እንጨቱ ይኸው…የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?” በማለት ጠይቆት ነበር፡፡ በአብርሃም ህሊና የመሥዋዕቱ
በግ ይስሐቅ ነበር፡፡ ይሁንና መንፈስ ቅዱስ እንዳቀበለው “ልጄ ሆይ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል፡፡” በማለት መለሰለት፡፡ (ዘፍ. 22፡7-8) ለጊዜው እግዚአብሔር ያዘጋጀው (አብርሃምም ይስሐቅም የማያውቁት)
ንጹሕ የመሥዋዕት በግ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ከሰማይ ወረደ፣ በይስሐቅም ቤዛ መሥዋዕት ሆኖ ቀረበ፡፡ (ዘፍ. 22፡13) ይህ በይስሐቅ ፈንታ የተሰዋው ንጹሕ በግ የዓለም መድኃኒት የኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌ ነበር፡፡
ይስሐቅና አብርሃም ለጊዜው ሳይረዱት በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ሳይረዱት የመሰከሩለት እውነተኛው፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀው (ሰውን ለማዳን በባሕርያችን የተገለጠ) የመሥዋዕት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የነቢያት
ፍጻሜ፣ የሐዋርያት መጀመሪያ የሆነ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ መስክሮልናል፡፡ “ዮሐንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታችን ኢየሱስን አይቶ እንዲህ አለ ‘እነሆ የዓለሙን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፡፡ ከእኔ በፊት
የነበረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበርና፡፡” (ዮሐ. 1፡29-30) ስለ ሆነም የሐዲስ ኪዳን እውነተኛ መሥዋዕት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መሥዋዕትነቱም በይስሐቅ
ፈንታ እንደቀረበው በግ ለአንድ ሰው ወይም ለጥቂቶች ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ነው፡፡ መሥዋዕት የሆነውም እንደ ብሉይ ኪዳን መሥዋዕት በተደጋጋሚ ሳይሆን አንድ ጊዜ ነው፡፡ መሥዋዕቱም፣ መሥዋዕት አቅራቢውም፣
መሥዋዕት ተቀባዩም እርሱ ራሱ ሰው የሆነ አምላክ፣ ልዩ ሊቀ ካሕናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ምሥጢረ ቁርባን ማለት ከዚህ በታች በተብራራው መሰረት አንድ ጊዜ ስለ ዓለም ሁሉ ቤዛ መሥዋዕት ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ
ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም አካሉ እንሆን ዘንድ የምንካፈልበት፣ ከክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ የጸጋዎች ሁሉ አክሊል ነው፡፡ ደጉ አባታችን አባ ሕርያቆስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በተናገረው የቅዳሴ ማርያም አንቀጽ
ይህንን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፡- “ዛሬ በዚህች ቀን በፍቅርና በትሕትና ግሩም በሚሆን በዚህ ምሥጢር ፊት እቆማለሁ፡፡ በዚህም ማዕድና ቁርባን ፊት፡፡ መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ከርሱ ሊቀምሱ የማይቻላቸው በእውነት
ቁርባን ነው፡፡ በበግ በጊደርና በላም ደም እንደ ነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መሥዋዕት አይደለም፤ እሳት ነው እንጂ፡፡ ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዓመፀኞች ሰዎች
የሚበላ እሳት ነው፡፡” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 5-7)
በእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት (በምስጢረ ስላሴ) አምነው በክርስቶስ ደም የተዋጁና በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁ ምዕመናን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም
በመቀበል ምስጢረ ቁርባንን ይፈጽማሉ፡፡ ጌታም በቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› (ዮሐ 6፡54) ብሎ እንደተናገ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ ምዕመናን የዘላለም ሕይወት
አላቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት›› (1ኛ ቆር 11፡26) ብሎ እንደገለጸው የምስጢረ ቁርባን ተካፋይ የሆነ ሁሉ ስለ ቅዱስ
ቁርባን ትርጉም፣ አስፈላጊነት፣ አፈጻጸም …ወዘተ ማመንና ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡
ቅዱስ ቁርባን የዘላለም ሕይወት ያሰጠናል፡፡ ጌታችን በማይታበል አማናዊ ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ›› በማለት እንደተናገረ የተቀበልነው
ቅዱስ ቁርባን የሕያው አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ነውና የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆናችንን ያረጋግጣል፡፡ ዳግመኛም ቅርጫፍ ከግንዱ እስካልተለየ ድረስ ልምላሜ፣ ጽጌና ፍሬ ሕይወት ለዘላለም እንዲኖረው
ሁሉ ክርስቲያኖችም ጉንደ ሐረገ ወይን ከሆነው ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አለመለየታችንና በሕይወት መኖራችንን ቅዱስ ቁርባን ስንቀበል እናረጋግጣለን፡፡ (ዮሐ 6፡53፣ ሮሜ 11፡21-24) ሕያዋን የሚያደርጉንም
በውስጣችን ያደረው (የተዋሐደን) ሥጋ ክርስቶስና ደመ ክርስቶስ ናቸው፡፡ እርሱ የማይሞት የማይለወጥ ነውና ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ›› በማለት አረጋግጦልናል፡፡ (ዮሐ
6፡56)
ቅዱስ ቁርባን ሥርየተ ኃጢአትን ያስገኛል፡፡ አባቶቻችን ‹‹ሰው ሆኖ የማይበድል እንጨት ሆኖ የማይነድ የለም፤ ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም›› እንዲሉ ደካማና ስሑት የሚሆን ሰብአዊ ባሕርያችን ወደ ስህተት
ጎዳና ሲነዳንና ኃጢአት ሲያገኘን በደላችንን ለካህን ተናዝዘን፣ ቀኖና ተቀብለንና ንስሐችንን ጨርሰን በካህኑ ፈቃጅነት ቅዱስ ቁርባንን ስንቀበል የቀደመ ኃጢአት በደላችን ሁሉ እሳት ላይ እንደወደቀ ቅቤ ቀልጦ ጠፍቶ ነጻ
ያደርገናል፡፡ ‹‹ከጥምቀት በፊት የተሠራ ኃጢአት በጥምቀት ይሰረያል፤ ከጥምቀት በኋላ የተሠራ ኃጢአት በንስሐና በሥጋ ወደሙ ይሰረያል›› እንዳለ ፊልክስዮስ፡፡ የጌታ ሥጋና ደም ሥርየተ ኃጢአትን ያሰጣልና፡፡ ‹‹
ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡›› (ማቴ. 26፡28) ብሎ ባለቤቱ ራሱ አስረድቶናል፡፡ እንግዲህ እናስተውል ሥጋውን ከመቁረሱ ደሙን ከማፍሰሱ በፊት በአንጻረ ሕብስትና ጽዋ
ሥጋውንና ደሙን ባርኮ ሰጥቶናል፡፡ ይህም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የክርስቶስ አካል የሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ኃጢአትን የሚያስተሰርይ የጌታን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለምዕመናን የምትሰጥበት ሰማያዊ ሥርዓት
ነው፡፡ የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ እንዳትበድሉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤ የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፡፡” (1ኛ ዮሐ. 2፡1)
በማለት እንደመከረን በደካማ ባሕርይ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን በደል ብንፈጽም በንስሐ ተመልሰን የእግዚአብሔርን ማዳን የምናገኝበት ህያው ቃል ኪዳን የእግዚአብሔር የቸርነቱ መገለጫ የሆነ ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡
ማንኛውም ሰው በሃይማኖት ሆኖ ቅዱስ ቁርባንን ቢቀበል ሥርየተ ኃጢአትን ያገኛል፡፡ ከኃጢአት ቁራኝነት ነጻ ሆኖ ኅብረቱ ከሰማያውያን ቅዱሳን ጋር ይሆናል፡፡ ‹‹ኅብስቱ አንድ እንደሆነ እንዲሁም እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ
አካል ነን፡፡ ሁላችንም ከአንድ ኅብስት እንቀበላለንና›› በማለት ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ያረጋግጥልናል፡፡ (1ኛ ቆሮ 10፡17)
ቅዱስ ቁርባን የኃጢአት ልጓም ሆኖ ያገለግለናል፡፡ ክርስቲያን የጌታን ሥጋና ደም ሲቀበል የኃጢአት ልጓም ያገኛል፡፡ ሥጋው ለኃጢአት የሚጓጓና የሚሰነካከል እንዳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይጠብቀዋል፡፡ በሥጋውና
በደሙ የተዋሐደው አምላክ ኃጢአትን ተደፋፍሮ እንዳይሠራ ይወቅሰዋል፡፡ የኃጢአት ውጤት ሞት መሆኑን ያሳስበዋል፡፡ በአጠቃላይ ወደ ቅድስናና ጽድቅ የሚመራ መንፈሰ እግዚአብሔር ስለተዋሐደን ለጽድቅ ሥራ
የምንተጋ ለኃጢአት የምንሰቀቅ እንሆናለን፡፡ በቅዱስ ቁርባን ጸጋ እግዚአብሔርን ስለምንታደል ኃጢአትን እንጸየፈዋለን፡፡ ምክንያቱም በመንፈሳዊ ዕውቀት የምናድግበትና በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የምንበለጽግበት ምግበ
ሕይወት አግኝተናልና ነው፡፡ ‹‹የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፡፡ በእኔ የሚያምን ሁል ጊዜ ከቶ አይጠማም….ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜ እውነተኛ መጠጥ ነውና›› (ዮሐ 6፡35-45) እንዲል፡፡
መሥዋዕተ መልከጼዴቅ፡ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም በፊት የነበረ የእግዚአብሔር ካህን ነው፡፡ዘፍ 14፡18-21 ዕብ 7፡1 ከመልከጼዴቅ በኋላ የተነሡ ሌዋውያን ካህናት መሥዋዕትን የሚያዘጋጁት ከእንስሳት ነበር፡፡ ዕብ 10፡
4 መልከጼዴቅ ግን የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ራስ የክርስቶስ ምሣሌ ነበርና እንደ ሐዲስ ኪዳን ሥርዓት በንጹህ ስንዴና ወይን ያስታኩት ነበር፡፡ ይህንንም መሥዋዕት አድርጎ ያቀርብ ነበር፡፡ ‹‹የእንስሳትን መስዋዕት
አትሰዋ፤ ነገር ግን መስዋዕትህ በእግዚአብሔር ፊት ከንጹሕ የስንዴ ኅብስትና ከንጹሕ የወይን ፍሬ ይሁን›› እንዳለ ቀለሜንጦስ፡፡ መሥዋዕተ መልከጼዴቅ ለቅዱስ ቁርባን ምሳሌው ነበር፡፡ የመልከ ጼዴቅ ክህነትም ለኢየሱስ
ክርስቶስ ዘላለማዊ ክህነት ምሳሌ ነበር፡፡
የደብተራ ኦሪት ቁርባንና መሥዋዕት፡ ከ430 ዓመታት በኋላ ከግብፅ የወጡት እስራኤላውያን መሥዋዕትን እንዲያቀርቡ ታዘው ነበር፡፡ ዘሌ 12፡3-11 ይህ የበግ መሥዋዕት የሚቀርብበት የእስራኤል ፋሲካ የሥጋ ወደሙ
ምሳሌ ነበር፡፡በዕብራይስጥ ፋሲካ ማለት ‹‹አለፈ›› ማለት ነው፡፡ያለፈውም ቀሳፊው መልአክ ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን ክርስቶስ ‹‹ፋሲካችን›› ተብሏል፡፡ 1ኛ ቆሮ 5፡7 ‹‹በዓለ ትንሣኤ ፋሲካነ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ››
እንዲል፡፡
እስራኤል ከሞተ በኩር የዳኑበት በግ፡ ሕዝበ እስራኤል በእግዚአብሔር ኃይል በሙሴ መሪነት ከፈርዖን መዳፍ ነጻ የወጡት በግብፃውያን ላይ በታዘዘው ሞተ በኩር ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ሞተ በኩር የእስራኤልን ልጆች
እንዳያገኛቸው ‹‹ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ጠቦት እንዲያዘጋጁ፣ እስከ 14ኛው ቀንም እንዲጠብቁት፣ሲመሽም እንዲያርዱት፣ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን እንዲቀቡት፣ በእሳት
የተሠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ እንዲበሉ፣ የቀረውንም እንዲያቃጥሉት›› ታዘው ነበር፡፡ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ጠቦት ምክንያተ ኃጢአት የሌለበት የንጹሐ ባሕርይ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡
የበጉን ጥብሱን ብቻ እንደተመገቡ በእሳት የተመሰለ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ ለምንቀበል ለእኛ አብነት ለመሆን የምንበላውና የምንጠጣው ሥጋና ደም ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ነውና፡፡ ዘጸ 12፡46
ለእስራኤል የወረደው መና፡ ለእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ከደመና የወረደላቸው መና ጌታ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች ሲል የቆረሰው ሥጋና ያፈሰሰው ደም ምሳሌ ነው፡፡ መናው የተገኘው ከደመና
እንደሆነ ሁሉ ጌታም ሥጋና ነፍስን የነሳው ከቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ስለዚህ ደመናው ጌታ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነባት የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ ጌታም በዘመነ ስብከቱ ‹‹የሕይወት እንጀራ
እኔ ነኝ፡፡ አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው….እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምስጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው›› በማለት ለእስራኤል የወረደው መና
የሥጋውና የደሙ ምሳሌ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ዮሐ 6፡49-51
ይህም በቅዳሴ ሐዋርያትና በቅዳሴ እግዚእ ነው ያለው፣ በሌሎቹ ቅዳሴዎችም ይህን የመሰለ ጸሎት አለ፣ ከዚህ ቀጥሎ አያይዞ ካህኑ እየመራ፣ ሕዝቡ እየተከተለ “ሀበነ ንኀበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ
ጵርስፎራ…” እያሉ ይጸልዩበታል፡፡ ቀጥሎ ጸሎተ ፈትቶ አለ፣ ቄሱ ያን እየጸለየ እንደ ሥርዓቱ ሥጋውን ይፈትተዋል፡፡ ይህንንም ሲፈጽም ካህኑ እየመራ ሕዝቡ እየተቀበሉ አርባ አንድ ጊዜ እግዚኦታ (እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ)
ያደርሱበታል፡፡ ቀጥሎ ካህኑ “አአምን፣ አአምን፣ አአምን፣ ወእትአመን …እያለ ሥጋውን በደሙ” “ቡሩክ እግዚአብሔር አብ…ወብሩክ ወልድ ዋሕድ…ወቡሩክ መንፈስ ቅዱስ…”እያለ ደሙን በሥጋው ሦስት፣ ሦስት፣ ጊዜ
ይባርከዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በቅድሚያ ቀዳሾች ካህናት (ቅዱስ ሥጋውን ከሠራዒው ካህን፣ ክቡር ደሙን ከንፍቁ ካህን እጅ በዕርፈ መስቀል)፣ ቀጥሎ ሕዝቡ (ቅዱስ ሥጋውን ከሠራዒው ካህን፣ ክቡር ደሙን ከዲያቆኑ በዕርፈ
መስቀል) እንቀበላለን፡፡
10. ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ሊቀበል የሚገባው ማነው? ሕጻናትና ለአዛውንቶች ብቻ ናቸውን?
ለብዙዎች የክርስቶስ ሥጋና ደም ለሕፃናት፣ ለአረጋውያንና በደዊ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ለተያዙ ብቻ የተሰጠ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ግን ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙ የዘላለም ሕይወትን የሚያድል፣ ሥርየተ ኃጢአትን
የሚሰጥና ከዳግም ድቀት የሚጠብቅ ነው ካልን ይህ ጸጋና በረከት ደግሞ ዕድሜ፣ዘር፣ ቀለምና ጾታ ሳይለይ በስሙ ለሚያምኑ የሰው ልጆች ሁሉ የሚያስፈልግ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ጌታችን ኅብስቱን ከ13 ፈትቶ
አንዱን ራሱ ተቀብሎ የቀረውን ያቀበላቸው 13ቱን ሕማማተ መስቀል ተቀብዬ አድናችኋለሁ ሲላቸው ነው፡፡ ሥጋዬን በልታችሁ ደሜን ጠጥታችሁ መንግስተ ሰማያት ትገባላችሁ ቢላቸው ከአይሁድ ትምህርት የተነሳ የሰው
ሥጋ እንዴት ይበላል ብለው ይፈሩ ነበርና አብነት ሲሆናቸው ቆርቦ አቆረባቸው፡፡
በማዕከለ ምድር በቀራኒዮ አደባባይ በመልዕልተ መስቀል ላይ የተሰዋው የመድኃኒት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለሚያምንበት ሁሉ የተሰጠ ምግበ ሕይወት መሆኑን
አስተምሯል፡፡ የአዳም ዘር የሆነ ሁሉ መንግስተ እግዚአብሔርን ይወርስ ዘንድ ከዚህ መንፈሳዊ አምኃ (ስጦታ) መካፈል ግዴታው ነው፡፡ ሰው አስቀድሞ የሚቀበለው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ አማናዊ መሆኑን አምኖ
ራሱን ሲመረምር፣ ንስሐ ሲገባና ከመምህረ ንስሐው ጋር ተማክሮ በሃይማኖትና በአትሕቶ ርዕስ ቢቀርብ ከቅዱስ ቁርባኑ አይከለከልም፡፡ 1ኛ ቆሮ 11፡29 ስለዚህ በክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ያመነ፣ ሃይማኖታዊ ምስጢር
የገባው፣ ንስሐ የገባና የተሰጠውንም ቀኖና በሚገባ የፈጸመ ሰው ዕድሜና ጾታ ሳይለይ ከምስጢረ ቁርባን መካፈል ይችላል፡፡
ስንዘጋጅም ወደ ልባችን የኃጢአት ሐሳብ እንዳያስገቡ አካለዊ ስሜቶቻችንን ሁሉ መግዛት፣ አካልን መታጠብና አቅም የፈቀደውን ንጹሕና ጽዱ (ነጭ) ልብስ መልበስ (ራዕ 6፡11)፣ ቁርባን በሚቀበሉበት ዋዜማ ቀለል ያለ
ምግብ መመገብና ለ18 ሰዓታት ከምግበ ሥጋ መከልከል፣ በትዳር ለሚኖሩ ከቁርባን በፊት ለ3 ቀናት ከቁርባን በኋላ ለ2 ቀናት ከሩካቤ መከልከል፣ ለወንዶች ህልመ ሌሊት (ዝንየት) ለሴቶች ደግሞ የወር አበባ (ወይም
በማንኛውም ምክንያት የሚደማ/የሚፈስ፣ ቁስል) ያላገኛቸው፣ ሴቶች ወንድ ቢወልዱ 40 ቀን ሴት ቢወልዱ ደግሞ 80ቀን የሞላቸው፣ በሚቆርቡበት ዕለት ቅዳሴ ሲጀመር ጀምሮ ተገኝቶ ማስቀድስ ናቸው፡፡
ይህ አዋጅ የሚታወጀው ከቅዱስ ሥጋና ከክቡር ደሙ ርቀን እንድንቆም ወይም ተመልካቾች ብቻ እንድንሆን ተፈልጎ ወይም እንዳንቆርብ ለማስፈራራት ተብሎ አይደለም፡፡ ንስሓ ገብተን፣ በምክረ ካህን ተዘጋጅተን
በንጽሕና ሆነን እንድንቀበል ነው ለማሳሰብ ነው እንጅ፡፡ የጌታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ከኃጢአት በንስሐ ሳይነጹ በድፍረት ቢቀበሉት ቅጣትን ያመጣልና፡፡ ጠላት ዲያብሎስ ግን ይህንን የካህኑን አዋጅ እያሳሰበና
እንደማስፈራሪያ እንድናየው እያደረገ “ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የበቃህ/ሽ አይደለህ/ሽም” ብሎ ከሥጋ ወደሙ እንድንርቅ ያደርገናል፡፡ የዚህ አዋጅ ዋና መልእክት ንስሓ ገብታችሁ፣ ከንስሓ አባታችሁ ጋር ተማክራችሁ ቅረቡ
የሚል ነው፡፡
ክፍል 2 ይቀጥላል፡፡
This entry was posted in Uncategorized by Astemhro Ze Tewahdo. Bookmark the permalink [https://astemhro.com/2018/11/30/eucharist1/] .
Enyew
on December 12, 2019 at 9:46 pm said:
keep it up
Like
Niguse Demeke
on September 21, 2020 at 11:46 pm said:
ወለተ ኪዳን
on December 30, 2020 at 3:36 am said:
ብዙ መማር እፈልጋለሁ
Like
ተክለ ዩሀንስ
on June 24, 2023 at 12:56 pm said:
መምህራን ሆይ በርቱልን
Like
Danat
on September 14, 2023 at 12:51 am said:
My favourite website as far. It is a great source for church assignments. And I’m also proud
Like