You are on page 1of 4

ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን፡ የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ!

Posted on December 21, 2018 by Astemhro Ze Tewahdo

የትንሣኤ ሙታን (Mystery of resurrection from the dead) ትርጉም


ትንሣኤ የሚለው ቃል ተንሥአ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን መነሣት ማለት ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን ማለት የሙታን መነሣት ማለት ነው፡፡ ይህም ተለያይተው በተለያየ ስፍራ ይኖሩ የነበሩ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው መነሣት፣
ከሞት በኋላ በነፍስና በሥጋ ሕይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያው ሞት ምክንያት የተለያዩት ነፍስና ሥጋ በመጨረሻው ዘመን ዳግመኛ የሚኖራቸው ኅብረት ትንሣኤ ሙታን ይባላል፡፡ ሙታን በመጨረሻው ቀን
ዳግመኛ በማይሞት ሥጋ ሕያዋን የሚሆኑበት አምላካዊ ጥበብ ትንሣኤ ሙታን ይባላል፡፡ ይህ የሙታን መነሣት ሁኔታ በሰው ልጅ አእምሮ ሊደርስበትና ሊታወቅ የማይችል ረቂቅ ጥበብ ስለሆነ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን
ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ምስጢር ተስፋ የምናደርገው ሲሆን ክርስቶስ ዳግመኛ ከመጣ በኋላ ለሚኖረው ዘላለማዊ ሕይወት መጀመሪያ ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን በአዳምና በልጆቹ ላይ የተፈረደው የሞት ፍርድ ለመጨረሻ
ጊዜ የሚጠፋበት ነው፡፡

ሞት ምንድን ነው?
ሰው ከመሬት የተሠራ ሥጋና ዘላለማዊት ነፍስ ያለው ፍጡር ነው፡፡ ሰው አራት ባህርያተ ሥጋ (አፈር፣ እሳት፣ ነፋስና ውኃ) እንዲሁም ሦስት ባህርያተ ነፍስ (ለባዊት፣ ነባቢት፣ ሕያዊት) ያለው ፍጡር ነው፡፡ ዘላለማዊ ሆኖ
በገነት እንዲኖር የተፈጠረው ሰው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመሻሩ ሞት መጣበት፡፡ በሃይማኖታዊው ትርጉም ሞት ማለት የሥጋና የነፍስ መለያየት ነው (ያዕ 2፡26 ማቴ 10፡28 መዝ 30፡5 ሉቃ 23፡46 ሐዋ 7፡59 ራዕ
6፡9)፡፡ ሞት ተዋሕደው የሚኖሩት ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ነፍስ ከእግዚአብሔር እስትንፋስ የተገኘች ናትና ወደ እግዚአብሔር፣ ሥጋ ደግሞ ወደ ተገኘበት ወደ መሬት የሚሄድበት ሁኔታ ነው፡፡ በሳይንሳዊ ትርጉሙ ደግሞ
ሞት ማለት ለሕይወት መቀጠል አስፈላጊ የሆኑት ሕዋሳት ሥራ ማቆም ነው፡፡ በሌላ በኩል ሁለተኛ/ዳግመኛ ሞት የሚባለው ከእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር መንግስት መለየት (ወደ ዘላለም ቅጣት መግባት) ነው፡፡

የትንሣኤ ሙታን የብሉይ ኪዳን ማስረጃዎች


ትንሣኤ ሙታን አስቀድሞ ነቢያት ያስተማሩት ተስፋ ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ‹‹በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነሣሉ እኩሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ እፍረትና ጉስቁልና›› (ዳን 12፡2) በማለት
የሙታን ትንሣኤ መኖሩን ተናግሯል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ‹‹ሙታን ሕያዋን ይሆናሉ ሬሳዎችም ይነሣሉ በምድርም የምትኖሩ ሆይ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም›› (ኢሳ 26፡19)
ብሎ በመጨረሻ ያንቀላፉት ሁሉ እንደሚነሱ በትንቢቱ አስተምሯል፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ሕዝቅኤል ‹‹ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ። ጅማትም
እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ›› (ሕዝ 37፡1-10) በማለት ሙታን
እንደሚነሱ አብራርቶ ተናግሯል፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም እንዲሁ ‹‹ብዙ መከራና ጭንቀት አሳይተኸኛልና ተመልሰህ ሕያውም አደረከኝ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኝ›› (መዝ 70፡20) በማለት ስለ ምስጢረ
ትንሣኤ ሙታን ዘምሯል፡፡

የትንሣኤ ሙታን የሐዲስ ኪዳን ማስረጃዎች


በሐዲስ ኪዳንም እንዲሁ ስለትንሣኤ ሙታን ጌታችን በወንጌል ሐዋርያትም በመልእክቶቻቸውና በስብከታቸው አጽንተው አስተምረዋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን
የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ››(ዮሐ 5፡ 28-29) በማለት ሙታን ለክብርና ለአሳር እንደሚነሱ አስተምሯል፡፡ ስለነገረ
ምጽአቱ በተናገረበት ክፍልም ‹‹የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ
እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል›› (ማቴ 25፡31-32) ብሎ ስለሙታን መነሳትና ስለመጨረሻው ፍርድ ነግሮናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው
መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።›› (1ኛ ቆሮ 15፡52) በማለት የሰው ልጅ በማይበሰብስ ሥጋ እንደሚነሳ
በመልእክቱ ጽፎታል፡፡

ለጊዜው ከሞት የተነሱ ሰዎች


ነፍሳቸው ከሥጋቸው ከተለየች በኋላ በቅዱሳን ጸሎት፣ በጌታችን ተዓምራት ለጊዜው ከሙታን የተነሱ ሰዎች የትንሣኤ ሙታን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የእነርሱ መነሳት ነፍስና ሥጋ ዳግመኛ መዋሐድ እንደሚችሉ ያሳያሉና፡፡
በብሉይ ኪዳን ለጊዜው ከሙታን የተነሡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው ብላቴና (1ኛ ነገ 17፡ 21) እና ነቢዩ ኤልሳ ያስነሣው ብላቴና (2ኛ ነገ 4፡18)፣ በነቢዩ ኤልሳ አጽም የተነሳው እስራኤላዊ ሰው (2ኛ ነገ 13-20) ይገኙበታል፡፡
ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ ያለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዘመነ ሥጋዌው የመበለቲቱን ልጅ (ሉቃ 7፡11)፣ የኢያኢሮስን ልጅ (ሉቃ 8፡49)፣ አልዓዛርን (ዮሐ 11፡1-44) እና የኢየሩሳሌም ቅዱሳንን (ማቴ
27፡50) ከሞት አስነስቷል፡፡ የሐዋርያት አለቃ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስም ጣቢታን ከሞት አስነስቷል (ሐዋ 9፡ 36)፡፡ የእነዚህ ሁሉ ትንሣኤ ግን ዳግመኛ መሞት የነበረበት ጊዜያው ትንሣኤ ነበር፡፡

ዘላለማዊ ትንሣኤ
መድኃኒዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለአዳም በገባው ቃልኪዳን መሠረት: በአይሁድ እጅ መከራ መስቀልን ከተቀበለ በኋላ ነፍሱን በራሱ ስልጣን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ዐርብ በ11 ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
መስፍኑ ጲላጦስን አስፈቅደው ከመስቀል አውርደው ዮሴፍ ራሱ ባሰራው መቃብር በንጹህ በፍታ ገንዘው ቀብረውት ገጥመው ሲሄዱ ጸሐፍት ፈሪሳውያንና መስፍኑ በመቃብሩ ላይ ማኅተማቸውንና ጠባቂዎችን አኖሩ
(ማቴ 27÷57-66 ማር 15÷42 ሉቃ 23÷50 ዮሐ 19÷38-42) ፡፡ በሦስተኛው ቀን እሑድ በእኩለ ሌሊት መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በታላቅ ኃይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ ይጠብቁ የነበሩ
ጠባቂዎችም ደንግጠው ተበታተኑ በመቃብሩ ዙሪያ ቅዱሳን መላዕክት ታዩ (ማቴ 28÷1-15 ማር 16÷11-15 ሉቃ 24÷1-43 ዮሐ 20÷1-25 1ኛ ቆሮ 15-1 ሮሜ 6÷9-15)፡፡ ለሰው ልጆች ዘላለማዊ ትንሣኤ በኩር
የሆነው የክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ ከክርስቶስ ትንሣኤ ቀጥሎ ዘላለማዊ ትንሣኤን የተነሣችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ የድንግልም ትንሳኤ ዘላለማዊ ስለሆነ እንደሌሎች ሰዎች የመጨረሻውን ትንሣኤ
አልጠበቀችም፡፡ በመጨረሻው ቀን ሁላችን የምንነሳው ትንሣኤ እንዲሁ ዳግመኛ ሞት የሌለበት ዘላለማዊ ትንሣኤ ነው፡፡

ትንሣኤ ዘለክብር፡- የሚነሡት ጻድቃን የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያትን ሲሆን ሲነሡ ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው እንደ ፀሐይ እያበሩ ወንዶች የ30 ዓመት ጎልማሳ ሴቶች የ15 ዓመት ቆንጆ ሆነው ለዘላለም
በደስታ በሕይወት ለመኖር የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ (ራዕ 21÷1-5 ፤ 2ተኛ መቃ 13÷8-14) የ 30 ዓመትና የ15 ዓመት መባሉ አዳምና ሄዋን ሲፈጠሩ የ30 ዓመትና የ15 ዓመት ሆነው ተፈጠሩ
ብለው ሊቃውንት ከሚያስተምሩት ጋር በተመሳሳይ መልኩ ለሰው በሚገባ ቋንቋ ሙሉ ሰው መሆናቸውን ለማስገንዘብ እንጅ ከትንሣኤ በኋላ የሚቆጠር እድሜ ኖሮ አይደለም፡፡
እድሜ የሚቆጠረው በፀሐይ፣ በጨረቃ፣ በከዋክብት ነው፡፡ ከዳግም ምጽዓት በኋላ እነዚህ ሁሉ ፍጥረታት ስለሚያልፉ በማይቆጠር እድሜ እንኖራለን፡፡

ትንሣኤ ዘለኃሣር ፡-ይህን ትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች በዚህች ምድር ሳሉ እግዚአብሔርን ሲበድሉ በክህደት በምንፍቅና የሚኖሩ ትንሣኤ ልቡና ያላገኙ ሰዎች የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ ትንሣኤ ዘለኃሣር የሚነሡት ኃጥአን
ከቁራ ሰባት እጅ ጠቁረው የግብር አባታቸውን ሰይጣንን መስለው ለዘላለም ትሉ በማያንቀላፋበት እሳቱ በማይጠፋበት በገሃነመ እሳት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ (1ኛ መቃ 13÷9-11′ ማቴ 13÷-42)

ዳግም ምጽዓት
ዕለተ ምጽአት /ዳግም ምጽአት/ የምትባለው ዕለት ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ሆኖ ዳግመኛ ይመጣል፡፡ የተወጋ ጎኑን የተቸነከረ እጅና እግሩን እያሳየ ለጻድቃን ሊፈርድላችው ለኃጥአንና ለሰይጣን
ሊፈርድባቸው ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣባት ዕለት ናት (መዝ 49/50÷2-3′ ራዕ 22÷12)፡፡ ጌታችን በዓለም ፍጻሜ ዳግመኛ እንደሚመጣ በደብረ ዘይት ተራራ በሰፊው አስተምሯል፡፡ አመጣጡም ‹‹መብረቅ
ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፡፡››(ማቴ 24፡ 27) እንዳለው ለሁሉም በአንድ ጊዜ የሚታይ ነው፡፡ ከመምጣቱ አስቀድሞ ግን ብዙ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ የመምጣቱም
ነገር አስጨናቂ እንደሆነ ሲናገር ‹‹በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል››(ማቴ 24፡
30) በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።›› (ማቴ 16፡27) ጌታችን ስለ ነገረ ምጽዓት ሲናገር “ስለዚያች ቀንና
ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን የሚያውቃት የለም፡፡ በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ የሰው ልጅ አመጣጡ እነዲሁ ይሆናል፡፡” (ማቴ. 24፡
36) በማለት አስተምሯል፡፡ የዚህም ዓላማ የጌታ መምጫው ድንገት መሆኑን ለማስረዳትና ያችም ዕለት በአብ ልብ ታስባ እንደምትኖር (ሥላሴ በአብ ልብነት ያስባሉና) የሚያስረዳ
ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡ ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው ለአብ የሚታወቅ ከወልድ ግን የተሰወረ ሆኖ አይደለም፡፡ የተናገረው ራሱ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን፣
የተናገረበት አውድም ዳግመኛ ስለ ሚመጣበት ሰዓትና ዕለት ደቀመዛሙርቱ ጠይቀውት ሲመልስ መሆኑን ማስተዋል ከደካማ እይታ ሊሰውረን ይችላል፡፡ በተጨማሪም (ሉቃ 17፡28-30
ሉቃ 21፡34-36 ማቴ 25፡1-12 ሉቃ 12፡37-38 ዮሐ 14፡1-3 ሉቃ 12፡40 ማር 8፡38) ያሉት ነገረ ምጽአቱን ያስረዳሉ፡፡

የሙታን አነሳስ
የሞትህ ተነሥ የሚል አዋጅ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ይታወጃል፡፡ ሦስት ረቂቃን ነጋሪት አሉ፡፡ ነጋሪት ሲባል ነጋሪት አይደለም የጌታ ትዕዛዝ ነው ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም
መለከት ከሰማይ ይወርዳልና (1ና ተሰ 4÷16) እንደተባለ የመጀመሪያው ረቂቅ ነጋሪት ሲመታ አውሬ የበላው ነፋስ የበተነው ያለቀው የደቀቀው ሁሉ ራስ በፈረሰበት ቦታ ላይ ይሰበሰባል (ያዕቆብ ዘሥሩግ ቁ.91)፡፡ ሁለተኛው
ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ አጥንትና ሥጋ ተዋሕደው ሳይንቀሳቀስ ትኩስ ሬሳ ይሆናል፡፡ አጥንትና ጅማቶች ከሥጋ ከደም ጋር ይያያዛሉ እስኪነሡ ያለመንቀሳቀስ ፍጹም በድን ይሆናሉ፡፡ ሦስተኛው ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ በቀዋሚ
አካል የምትናገር አንደበት ከራስ ጸጉራቸው ሳይከፈሉ በአርባ ቀን በእናቱ ማህጸን ደም ሆኖ የወረደው ጽንስ ሳይቀር በጎም ሆነ ክፉ ሥራቸውን ይዘው ይነሣሉ፡፡ በዳግም ትንሣኤ ሴቶች የ15 ዓመት ወንዶች የ30 ዓመት
(ሙሉ ሰው ሆነው) ሆነው ይነሳሉ፡፡ ሲፈጠሩም ሙሉ ሰው ሆነው የ15 እና የ30 ዓመት ሆነው ስለነበር በዚያው ሰውነት ይነሳሉ፡፡ በምድር ላይ ስንኖር እንዳለው በሚበሰብስ ሥጋ ሳይሆን ዘላለማዊ በሆነው ሥጋ ሁላችን
እንነሳለን፡፡

የመጨረሻው ፍርድ
ሁሉም እንደየሠራው የሚያገኝበት የመጨረሻው ቀን ፍርድ አለ፡፡ ይህም ከጌታችን ምጽአትና ያንቀላፉት ሁሉ ከተነሱ በኋላ ይከናወናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ
የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል›› (ዮሐ 12፡48) በማለት ሰው በመጨረሻው ቀን የሰማው የእግዚአብሔር ቃል እንደሚፈርድበት ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ‹‹እኔ እላችኋለሁ፥
ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል›› (ማቴ 12፡36) ብሎ ዛሬ ለምንናገራቸው ከንቱ ነገሮች ሁሉ በዚያ በፍርድ ቀን መልስ የምንሰጥበት ይሆናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ
ስለመጨረሻው ቀን ፍርድ ሲናገር ‹‹ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ›› (ራዕ 20፡11-15) በማለት ሁሉም እንደ ሥራው
የሚከፈልበት ፍርድ መሆኑን መስክሯል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ሰለዚህ ቀን ‹‹መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና›› (2ኛ ቆሮ 5፡10)
ብሏል፡፡ እንዲሁም ለአቴና ሰዎች ‹‹ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል›› (ሐዋ 17፡31) በማለት እውነትን
መስክሮላቸዋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ስለዚች ቀን ‹‹እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና›› (መክ 12፡14) ብሏል፡፡ ገነትና ሲኦል ጊዜያዊ የነፍሳት
መቆያ ናቸው፡፡ መልካም የሠሩ ነፍሳት እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ በገነት ይቆያሉ፡፡ ክፉ የሠሩ ደግሞ በሲኦል ይቆያሉ (2ኛ ጴጥ 3፡13 ራዕ 21፡1-5 2ኛ ቆሮ 5፡1 2ኛ ጴጥ 1፡14 ፊልጵ 3፡20-21)፡፡ መንግስተ ሰማያትና
ገሀነመ እሳት፡ በመጨረሻው ፍርድ ጻድቃን ወደ መንግስተ ሰማያት፣ ኃጥአን ደግሞ ወደ ገሀነመ እሳት ይገባሉ (ማቴ 10፡28 ራዕ 20፡14-15 ራዕ 19፡20 ማር 9፡43)፡፡

ቀኝና ግራ
አባታችን አባ ሕርያቆስ እንደተናገረ ለመለኮት ቀኝና ግራ የለውም፡፡ ቀኝና ግራ የተባለውም ምሳሊያዊ ነው፡፡ ጻድቃን በቀኝ የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው፡፡ቀኝ ቅን ነው፡፡ ጻድቃንም
ለምግባር ለሃይማኖት ቅን ናቸው፡፡ ቀኝ ፈጣን ነው፡፡ ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ፈጣን ናቸው፡፡ ቀኝ ብርቱ ነው፡፡ ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ብርቱ ናቸው፡፡ ኃጥአን በግራ
የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው፡፡ ግራ ጠማማ ነው፡፡ ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመሥራት ጠማማ ናቸው፡፡ ግራ ዳተኛ ነው፡፡ ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመስራት
ዳተኞች ናቸውና፡፡ ቤተክርስቲያን ለምን አትሄዱም ሲሏቸው እዚህ ቦታ ደርሼ መጥቼ ደከመኝ ጸልዩ ሲባሉ ራሱ እግዚአብሔር ፍላጎቴን ያውቅ የለ ስገዱ ጹሙ ሲባሉ ምክንያት
አያጣቸውምና፡፡ ግራ ሰነፍ ነው፡፡ ኃጥአንም በምግባር በሃይማኖት በኩል ሰነፎች ናቸው፡፡ ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት አይችልም ኃጥአንም በምግባር በሃይማኖት በኩል ጠንከር ያለ ነገር
ሲገጥማቸው ደከመን ሰለቸን ብለው ይተውታል፡፡ ለኃጢአት ግን አይደክሙም ሌሊት ጨለማን ተገን አድርገው ሲዘርፉ ሲዘሙቱ ይዉላሉና፡፡

በጎችና ፍየሎች
ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ይመሰላሉ፡፡ ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ተመሰሉ ቢባል የበጎች ተፈጥሮ ከጻድቃን ሥራ ጋር የፍየል ተፈጥሮ /ግብር/ ከኃጥአን ጋራ ስለሚመሳሰል ነው፡፡ በጎች በደጋ እንጂ በቆላ
አይኖሩም፡፡ ተስማሚያቸው ደጋ ነው ጻድቃን በመከራ ሥጋ እንጂ በተድላ ደስታ ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን ክደው በምግባር ብልሹነት አይገኙም፡፡ ፍየሎች በቆላ እንጂ በደጋ አይኖሩም፤ ኃጥአንም በተድላ ደስታ
ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን በወርቅ በብር ይለውጣሉና፡፡

በጎች እረኛቸው ባሰማራቸው ሥፍራ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ጻድቃንም እረኛቸው ክርስቶስ ባሰማራቸው በአንዲት ሃይማኖት ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ፍየሎች እረኛቸው ባሰማራቸው ቦታ ጸንተው እንደማይኖሩ ኃጥአንም እንዲሁ
በሃይማኖት ጸንተው መኖር አይቻላቸውምና፡፡ በጎች ጥቂት ሳር ካገኙ ተፋቅረው አብረው ይበላሉ ጻድቃንም ያለቻቸውን ተካፍለው ይኖራሉና፡፡ ፍየሎች ግን ሣር ቅጠሉ ሞልቶ ለሁላቸው ሲበቃ ሳለ ይጣላሉ፡፡ ኃጥአንም
ሀብት ንብረት ተትረፍርፎላቸው ለወገናቸው አያካፍሉም፡፡ ለገንዘብ ብለው እርስ በእርሳቸው ይጣላሉ ዘለው የሌላውን ሀብት ንብረት ለማግኘት ሲሉ የማይገባ ሥራ ይሠራሉና፡፡
የበጎች ላታቸው የተከደነ ሐፍረተ ሥጋቸው የተሸፈነ ነው፡፡ የጻድቃንም ኃጢአታቸው በሰው ዘንድ የተጋለጠ አይደለም፡፡ ኃጢአት ቢሰሩ ሌላ ሰው ሳይሰናከልባቸው ንስሐ ይገባሉ፡፡ የፍየሎች ላታቸው የተሰቀለ ሐፍረተ
ሥጋቸው የተጋለጠ ነው፡፡ የኃጢአተኞችም ሥራ በሰው ዘንድ የተጋለጠ ለሚሰሩት እኩይ ሥራ የማያፍሩ በየአደባባዩ ኃጢአትን የሚፈጽሙ ናቸውና፡፡ በጎች አቀርቅረው እንጂ አሻቅበው አያዩም ጻድቃንም ሁልጊዜ ዕለተ
ሞታቸውን በማሰብ ወደ አፈር እንደሚመለሱ እያሰቡ በትህትና ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ሀብት’ ንብረት’ ዕውቀት እያላቸው ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ ፍየሎች አሻቅበው ነው የሚያዩት አንገታቸውን ያንጠራራሉ
ኃጥአንም ደካማ ሆነው ሳሉ ብርቱ ነን ይላሉ ባገኙበት ሀብት ዕውቀት ይመካሉ ትዕቢተኞች ናቸው፡፡ ትሕትና በእነርሱ ዘንድ የበታችነት ምልክት ነው፡፡

ከበጎች ውስጥ አንዲቱ ተኩላ ቢነጥቃት ሁለተኛ ወደዚያ ቦታ ተመልሰው አይመጡም፡፡ ጻድቃንም እኩይ ሞት ከእነርሱ አንዱን ከወሰደ ነገም የእነርሱ ተራ እንደሆነ ተረድተው ከኃጢአት ሥራቸው በንስሐ ይመለሳሉ ወደ
እግዚአብሔር ይቀርባሉ፡፡ ፍየሎች ግን ከመካከላቸው ነብር አንዲቱን ቢወስድ ለጊዜው ደንብረው ይሄዳሉ፡፡ ኋላ ግን ተመልሰው እዚያው ቦታ ይመጣሉ ኃጥአንም ከመካከላቸው አንዱ ሳያስቡት በሞት ቢወሰድ ለጊዜው
ደንግጠው ከኃጥአት ሥራቸው ይታቀባሉ በኋላ ግን የሞተው ሰው ከህሊናቸው ሲጠፋና የዓለም ሁኔታ ሲማርካቸው ወደ ኃጢአት ግብራቸው ይመለሳሉና፡፡

የፍርድ ቀን ጥያቄዎች
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መጨረሻው የፍርድ ቀን ሲናገር ‹‹ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።
ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ
አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?
ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና
ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ
ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ
ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።›› (ማቴ 25፡34-46) በማለት ሰው በመጨረሻው ቀን
የሚጠየቀው እነዚህን ጥያቄዎች መሆኑን ተናግሯል፡፡ ይህም እምነት ያለ ምግባር ከንቱ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

ከትንሣኤ በኋላ ያለው ሕይወት


ከትንሣኤ ሙታን በኋላ ስለሚኖረው ሕይወት ቅዱሳት መጻሕፍት ብዙ እውነታዎችን አስፍረዋል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን
እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን›› (1ኛ ቆሮ 15፡ 52) በማለት ሙታን የማይበሰበሱ ሆነው እንደሚነሱ በመልእክቱ ጽፎታል፡፡ ጌታችንም ትንሣኤ ሙታንን
የማያምኑ ሰዱቃውያን ለጠየቁት ጥያቄ ‹‹ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ
የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።›› (ሉቃ 20፡35) በማለት ከትንሣኤ በኋላ ማግባት መጋባት እንደሌለና ሰዎች እንደመላእክት ሆነው እንደሚኖሩ ነግሯቸዋል፡፡

ሙታን የማይነሱ ከሆነ…


ትንሣኤ ሙታን ከሌለ (ሙታን የማይነሱ ከሆነ) እምነታችን ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር ‹‹ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ
ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ
ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን›› (1ኛ ቆሮ 15፡ 12-19) በማለት አረጋግጦታል፡፡ በተጨማሪም ‹‹እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን
የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው?…እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ
የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ›› (1ኛ ቆሮ 15፡ 29-34) በማለት ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ድካማችን ሁሉ ከንቱ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ሳይሞቱ በብሔረ ሕያዋን ያሉትስ?


ነቢዩ ሚልክያስ ‹‹እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች
ይመልሳል››(ሚል 4፡5-6) ብሎ እንደተነበየው፤ ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ኢየሱስም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ
አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው››(ማቴ 17፡11-13) ብሎ እንዳረጋገጠው ከሰው ልጆች ሞትን የማይቀምስ አይኖርም፡፡ በዚያን ዘመን በምድር ላይ
ያሉትም ቢሆኑ፣ በብሔረ ሕያዋንም ያሉት ቢሆኑ እንዲሁ ሞትን ይቀምሳሉ፤ ሳይሞቱ ትንሣኤ ሙታን የለምና፡፡

መሐሪ የሆነው አምላክ ኃጥአንን በዘላለም ሞት ይቀጣልን?


ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስረዱት እግዚአብሔር ኃጥአንን በዘላለም ሞት ይቀጣልን፡፡ እግዚአብሔር ፈታሂ ነው፡፡ ክፉዎች ካልተቀጡ ግን ፍትህ እንዴት ይኖራል? እግዚአበሔር የኖኅ ዘመን ሰዎችን በኃጢአታቸው
ምክንያት የቀጣቸው መሐሪ ስላልሆነ ሳይሆን ፈታሂ ስለሆነ ነው (ዘፍ 7፡1)፡፡ በአዳም ላይ የሞት ቅጣትን የፈረደበትም እንዲሁ ፈታሂ ስለሆነ ነው፡፡ መሐሪ ስለሆነ ደግሞ ቤዛ ሆኖ አዳነው፡፡ ክፉዎች ካልተቀጡ እግዚአብሔር
እንዴት ፈታሂ ይባላል? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላቲያ መልእክቱ ‹‹አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥
በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት›› (ገላ 6፡7) እንዳለው በመጨረሻው ዘመን ሁሉም የዘራውን ያጭዳል::
እግዚአብሔር መሐሪም ፈታሂም ስለሆነ ጻድቃን የዘላለም ሕይወት ኃጥአን ደግሞ እንደሥራቸው የዘላለም ሞትን ያገኛሉ፡፡ ስለዚህ ‹‹የዘላለም ቅጣት ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር አይሄድም›› የሚለው አስተሳሰብ የዘላለም
ቅጣትን የሚያስቀር አይደለም፡፡

ፍትሐትና ተዝካር
ሰው በሥጋው ለጊዜው ቢሞትም በነፍስ ግን ሕያው ነው፡፡ ጸሎተ ፍትሐት በአፀደ ሥጋና በአፀደ ነፍስ በሚኖሩ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን የዕምነት አንድነት ይገልፃል፡፡ ነብዩ ሄኖክ ‹‹ህያዋን ለሙታን ሙታን ለህያዋን
ይጸልያሉ›› (12 ÷34) በማለት እንደተናገረው በአፀደ ነፍስ የሚገኙ ሙታን በአፀደ ስጋ ለሚገኙ እንደሚፀልዩ ሁሉ በአፀደ ስጋ ያሉትም በሞት ለተለዩት ይፀልዩላቸዋል፡፡ ይህም የክርስቲያኖችን አንድነት ይገልጣል፡፡ ጸሎተ
ፍትሐትም ሆነ ተዝካር (መታሰቢያ) ጸሎት እንጂ ድግስ አይደሉም፡፡ አንዳንዶች ሟች ፍርዱን ከተቀበለ በኋላ ጸሎት ምን ያደርግለታል እንደሚሉት አይደለም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐትም ጸሎት እደመሆኑ መጠን ኃጥያት
ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ ይቀርባል፡፡ ‹‹ኃጥአት የለብንም ብንል እራሳችንን እናታልላለን›› (ዮሐ 1፡8) በማለት ወንጌላዊው እንዳስተማረው ሐጥያት የለብኝም ፍትሐት አያስፈልገኝም ማለት የሚችል ሰው የለም፡፡

ተዝካር የሚለው ቃል ዘከረ አሰበ ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መታሰቢያ ማለት ነው። መታሰቢያውም የሚደረገው ለሙታን ሲሆን የሚቀርበውም በጸሎት፣ በመሥዋእት፣ በመብራትና በማዕጠንት
ነው። ስለተዝካር ጥበበኛው ሲራክ ‹‹ልጄ ለሞተ ሰው አልቅስለት እዘንለት፤ እደአገሩ ተዝካር አውጣለት ። የሞተ ሰውስ ዓረፈ ነገር ግን ነፍሱ ታርፍ ዘንድ ተዝካር አውጣለት ከዚህ በሁላ ለቅሶህን ተው›› (ሲራክ 38፡16)
በማለት በሃይማኖት ኖረው ለሞቱ ወገኖች ተዝካር ማውጣት ተገቢ መሆኑን ያመለክታል። ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ (ተዝካር) ለበረከት ነው›› በማለት ተናግሯል (ምሳ 10፡7)፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ቤት
ኖረው ላረፉ ወገኖች መታሰቢያን ማድረግ ለሚያደርገው ሰው በረከት ነው።

ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ከሌሎች አምስቱ አዕማደ ምስጢራት በመጨረሻ የሚገኝ ተስፋ ነው፡፡ ሌሎቹ አምነን የምንጠብቃቸው ወይም አምነን የምንፈጽማቸው ሲሆኑ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ግን አምነን ተስፋ
የምናደርገው ነው፡፡ በመጨረሻው ዘመን ክርስቶስ ዳግመኛ ይመጣል፤ ሙታንም እንደ ዓይን ጥቅሻ ፈጥነው ይነሳሉ፤ ለሁሉም እንደየሥራው ዋጋው ይከፈለዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ፍጻሜ ላይ ‹‹እነሆ፥ በቶሎ
እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ›› (ራዕ 22፡12) ብሎ እንደጻፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል፤ ለሁሉም እንደሥራው ዋጋውን ይከፍለዋል፡፡ ስለዚህ
ሃይማኖታቸው የቀና ቀደምት አበው ቅዱሳን በሃይማኖት ድንጋጌ ‹‹ዳግመኛም የሞቱ የጻድቃንና የኃጥአን ትንሣኤ እንዳለ እናምናለን᎓᎓ ሁሉ እንደ ሥራው ፍዳውን የሚቀበልበት የፍርድ ቀንም እንዳለ
እናምናለን᎓᎓›› በማለት እንዳስተማሩን እኛም ምስጢረ ሥላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን አምነንና ጠብቀን፣ ምስጢረ ጥምቀትንና ምስጢረ ቁርባንን አምነንና ፈጽመን፣ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታንን ደግሞ አምነንና ተስፋ
አድርገን እምነታችንን በአምስቱ አዕማደ ምስጢራት ላይ አጽንተን ዘላለማዊ ሕይወትን እንወርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡
This entry was posted in Uncategorized by Astemhro Ze Tewahdo. Bookmark the permalink [https://astemhro.com/2018/12/21/mystery_resurrection/] .

About Astemhro Ze Tewahdo


ይህ የጡመራ መድረክ (አስተምህሮ) የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡
View all posts by Astemhro Ze Tewahdo →

You might also like