You are on page 1of 34

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

-
የቋንቋዎችና ሥነ ሰብዕ ፋካልቲ

-
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምርት ክፍል

ርዕስ

″በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ የስም አወጣጥ ቅየራ″


ይዘት ትንተና

ቤዛ አበራ

ግንቦት 2010 ዓ.ም


″በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ የስም አወጣጥ ቅየራ″
ይዘት ትንተና

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

የቋንቋዎችና ሥነ-ሰብዕ ፋካልቲ

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሁፍ ትምርት ክፍል

ቤዛ አበራ

ግንቦት 2010 ዓ.ም

አዲስ አበባ
ምስጋና
ከሁሉም አስቀድሜ ለዚህ ደረጃ ለማድረስ እና ለስራዎቼ ሁሉ መሳካት ለረዳኝ ለልዑል እግዚአብሔር ከፍ ያለ
ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህንን ጥናታዊ ጽሁፍ ከመጀመሪያ ጀምሮ ገንቢ አስተያየትና ምክሮችን በመለገስለዚህ ላበቃኝ
አማካሪዬ ለዶክተር ተስፋዬ ባዬ ልባዊ ምስጋናየን አቀርባለሁ፡፡ ትም ህርት ጀምሬ እስከምጨርስ ድረስ ለፍተውና ጥረው
ለዚህ ላበቁኝ ቤተሰቦቼ ምስጋናዬ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ለጥናታዊ ጽሁፍ አስፋላጊ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለረዱኝ እህት
ወንድሞቼ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በመጨረሻም ይህንን ጥናታዊ ጽሁፍ ከጀመርኩ ጀምረው በሀሳብ እየረዱኝ ከጎኔ
ላልተለዩኝ ጓደኞቼ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

I
አጠቃሎ

ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ማህረሰብ የሰዎችን ስም አወጣጥ እና
ቅየራ በሚል ርዕስ ትኩረት አድርጎ የቀረበ ሲሆን ዋና አላማ አድርጎ የተነሳውም ጥናቱም በተካሄደበት አካባቢ ነዋሪ
የሆነው ማህበረሰብ የስም አወጣጥና ቅየራ ስልት ምን እንደሚመስል ተንትኖ ማሳየት ነው፡፡ የጥናቱን አላማም ከግብ
ለማድረስ ቃለ መጠይቅና ሰነድ ፍተሻ ስራ ላይ ውለዋል፡፡ ጥናቱም በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፋፍሎ ቀርቧል፡፡ የጥናቱ
ውጤትም እንደሚያመለክተው ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ ነዋሪ የሆነው ማህበረሰብ ለልጆቻቸው ወይም ለሰዎች ስም
ሲያወጡና ሲቀይሩ መነሻ የሚያደርጉት የሚወልዱበትን ወቅት፣ ቤተሰባዊ ሁኔታ፣ የደረሰባቸውን ሀዘን፣ መልክ በአንድ
ወቅት የተፈጠረ መጥፎ ወይም ጥሩ ታሪክ በህይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ገጠመኞችና የሚከተሉትን
ሀይማኖት መሰረት በማድረግ እንደሆነ እና እነዚህ ስያሜዎችም የስም አውጪዎችን አመለካከታቸውን፣
አስተሳሰባቸውን፣ ፍልስፍናቸውን፣ ባህላቸውንና ምክንያታቸውን የሚጠቁም አድርገው ለሰዎች ስም እነደሚያወጡ
ከጥናት ውጤቱ መገንዘብ ተችሎዋል፡፡ ስሙም የባለ ስሙን እኔነት አሻራ እና ማንነትን ያመለክታል፡፡

II
ማውጫ
ምስጋና............................................................................................................................................................I
አጠቃሎ.........................................................................................................................................................II
ማውጫ........................................................................................................................................................III
ምዕራፍ አንድ.................................................................................................................................................1
1.1 የጥናቱ ዳራ....................................................................................................................................1
1.2 አነሳሽ ምክንያት.............................................................................................................................3
1.3 የጥናቱ አላማ.................................................................................................................................3
1.4 የጥናቱ ጠቀሜታ.............................................................................................................................4
1.5 የጥናቱ ወሰን..................................................................................................................................4
1.6 የጥናቱ ዘዴ.....................................................................................................................................4
1.6.1 የናሙና አመራረጥ ዘዴ.............................................................................................................4
1.6.2 የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ...........................................................................................................5
1.7 የመረጃ መተንተኛ ዘዴ.....................................................................................................................5
ምዕራፍ ሁለት................................................................................................................................................6
2.1 ንድፈ ሀሳባዊ ቅኝት...............................................................................................................................6
2.1.1 የስያሜ ምንነት..............................................................................................................................6
2.1.2 የስያሜ አጀማመር.........................................................................................................................7
2.1.3 የሰው ስም አወጣጥ ልማድ..............................................................................................................8
2.1.4 በስያሜ እና በተስያሚው መካከል ያለው ግንኙነት.............................................................................10
2.1.5 የስም ትርጉም ወይም ፍቺ ምንነት.................................................................................................11
ምዕራፍ ሶስት...............................................................................................................................................18
3.1 ቤተሰባዊ ሁኔታን መሰረት በማድረግ የወጡ እና የተቀየሩ ስሞች................................................................18
3.2 የማግኘት እና የማጣት መግለጫ ስሞች.................................................................................................21
3.3 የሀዘን መግለጫ ስሞች.........................................................................................................................23
3.4 መልክን መሰረት በማድረግ የወጡና የተቀየሩ ስሞች.................................................................................25
3.5 ታሪክን መሰረት በማድረግ የሚወጡ ስሞች............................................................................................26
3.6 መመኪያነትን መሰረት በማድረግ የወጡ ስሞች.......................................................................................28
3.7 ፀባይን ወይም ባህሪን መሰረት ያደረጉ ስሞች..........................................................................................30
3.8 የችግር መግለጫ ስሞች.......................................................................................................................32

III
ምዕራፍ አራት..............................................................................................................................................35
ማጠቃለያ....................................................................................................................................................35
ዋቢ መጽሐፍ.................................................................................................................................................1

IV
ምዕራፍ አንድ
መግቢያ

1.1 የጥናቱ ዳራ

ስያሜ አንድ ማህበረሰብ ተግባብቶ ለመኖር ቋንቋ እነደሚያስፈልገው ሁሉ ስያሜም የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ስያሜ
አመጣጡና አጀማመሩም የቋንቋ ብቸኛ ተገልጋይ ከሆነው ከሰው ልጅ ታሪክ እና ቋንቋ ተለይቶ አይታይም፡፡

ስየሜ በማንኛውም ማህረሰብ፣ በየትኛውም ሀገር እነዲሁም ለማንኛውም ነገር የሚ s ጥ ግላዊ ውክልና ነው፡፡ ስያሜ
ድሮም የነበረ፣ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር ዘላለማዊ ሀብት ነው፡፡ አገልግሎቱም አንዱን ነገር ማ l ትም ሰው፣ ቦታ፣
ቁስ ወዘተ የሚባሉ ነገሮች ተለይተው የሚታወቁበት ብቸኛና ጥቅል መጠሪያ በመሆን አንዱን ከአንዱ ለመለየት
የሚያገለግል ውክልና ነው፡፡ ይህን አስመልከቶ መላከ ብርሃን (2001÷10) እንደገለጸው ሰዎች ለልጆች ሆነ ለራሳው
የሚጠሩበትን ስም ለማውጣት ከአዳም እና ከሄዋን ጊዜ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በሀገሩ
ባህል፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት ረገድ ለልጁ የመጠሪያ ስምይሰይማል፡፡ሲሰይሙም ወቅቱን፣ የኑሮውን ገጠመኝ ተከትሎ
ወይም የልጁን የወደፊት እጣ ፋንታ ነጋሪ ሆኖ የሚሰየም ስም አለ፡፡

ይህን ሀሳብ ስንመለከት ለሰው ልጅ ስም ሲወጣ የተለያዩ ነገሮችን መሰረት እንዲያደርግ እና ስም የመጣው የሰው ልጅ
ከተፈጠረ ጀምሮ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ስም ማለት ህይወት ያላቸውም ሆነ ህይወት የሌላቸው ነገሮች የሚወከሉበት
ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላ l ፍ መጠሪያ ነው፡፡ ስም ለትልቅ፣ ለትንሽ፣ ለሰው፣ ለእንሰሳት ወዘተ እኩል በሆነ መልኩ
የሚሰጥ ነው፡፡ ይህን ሀሳብ አስመልክቶ ደስታ ተክለ ወልድ (1962፣ 183) እንደተገለጸው፡-

«ስያሜ ማለት የቦታና የአካል መጠሪያ ማንኛውም የሚታይና የማይታይ ሁሉ የሚጠራበትና የሚታወቅበት ስም
ይባላል፡፡ የባህርይ፣ የግብር፣ የአይነት፣ የመጠንና የመልክ ቁሳቁስ ወዘተ በማለት ፀሀይ፣ መሬት፣ ሰው፣ አየር፣ ጥቁር ወዘተ
በስም ፍቺ ተጠቅመው የሚጠሩ ናቸው» በማለት ገልጸውታል፡፡

ከላይ ከጥቅሱ መረዳት እንደሚቻለው ስያሜ ወይም የስም መጠሪያ የሚወጣው በአይናችን ለምናያቸው ወይም
በእጃችን ልንዳስሳቸው ለምንችላቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን በአይናችን ለማናያቸውና በእጃችን ለማንዳስሳቸው ነገሮች
ሁሉ የሚሰጥ መጠሪያ ነው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ነገሮች መጠሪያቸው ስም ወይም ስያሜ መሆኑን ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡

ይህን አስመልክቶ ዳኛቸው ወርቁ (1977፣ 40) የቃላት ስያሜ አይቶች በሚለው ርእስ ስር ጥቅል መጠሪያ የሚለውን
ሲገልጽ፡-

ለነገሮች መጠሪያ የሚወጣባላቸው እንደተገኘ ሳይሆን ስርዓትን ተከትሎ ጥቅል መጠሪያዎችና ስም አወጣጥ
ስርአታቸው ከተናጠል መጠሪያ ጋር ይመስላሉ፤ የቅርብ ዝምድናም አላቸው፤ በአብዛኛው የተናጠልም ሆነ
የጥቅል መጠሪያዎች ሁለት የስም አወጣጥ ስርአት አላቸው፡፡

1
ተናጠል መጠሪያ አንደኛው ክፍልፋዩን ለብቻ የሚታወቅበት ከሚለው አንጻር የሚወጣ ሲሆን ሁለተኛው
ደግሞ ጥቅል መጠሪያ ዋናው ዝርያ ወይም በውስጡ ሌሎችን ተዋላጆች አቅፎ የሚይዝ ሲሆን በዝምድና
የሚወጣ ነው፡፡ ስም እንደሚታወቀው አንድን ነገር ለመጥራት የምንጠቀምበት ነው፡፡

ከዘህ ሀሳብ መረዳት እንደሚቻለው ስሞች ጥቅል መጠሪያና የተናጠል መጠሪያ የሚሉ ነገሮች በውስጣቸው አጠቃለው
የሚይዙ ሲሆኑ ሁለቱም ተመሳሳይነት እንዳላቸው ያሳየናል፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ የሙህራኖች ሀሳብ የምንረዳው ስም ማለት አንድ ሰው ወይም አንድ ነገር እንደተፈጠረ ወይም
እንደተገኘ የሚሰጠው ስም መጠሪያ ነው፡፡ እንዲሁም ለነገሮች ማለትም ለእንሰሳት ለሰዎች እንዲሁም ለቦታዎች
ወይም ህይወት ላላቸው እና ህይወት ለሌላቸው ነገሮች ጥቅል መጠሪያ ነው፡፡ አንዱን ከአንዱ ለይተን የምናውቅበትና
የምንጠራባቸው የሚወጣው ስምም ዝም ብሎ በግምት ሳይሆን ስያሜ ለመስጠት የሆነ ነገራቸውን አይቶ
በመመርመር፣ በማስተዋል፣ ትኩረት በማድረግና ስርአትን ተከትሎ እንዲወጣላቸው ያስገነዝበናል፡፡

የሞረትና ጅሩ ወረዳ የወጣቶችና ስፖርት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑ ከአቶ አፈወርቅ ዘውዴ በተገኘው መረጃ
መሰረት የሞረትና ጅሩ ወረዳ በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ 24 ወረዳዎች አንዷ ናት፡፡ ከሀገራች ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ
በስተ ሰሜን 195 ኪ.ሜ ከዞኑ ማ l ትም ከደብረብርሃን 130 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ወረዳ ናት፡፡

የሞረትና ጅሩ ወረዳዎች የሚያዋስኗት በምስራቅ ባሶና ቦረና፣ በደቡብ ሳያደብርና ዋዩ፣ በምእራብ እንሳሮ፣ በሰሜን
መራቤቴና መንዝ ያዋስኗታል፡፡ ወረዳዋ በውስጧ የያዛቸው ቀበሌዎች 19 ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ የከተማ ሲሆኑ
አስራ ሰባቱ ደግሞ የገጠር ቀበሌዎች ናቸው፡፡

በ 2007 በነበረው የህዝብ ቆጠራ መሰረት የወረዳው ህዝብ ብዛት በከተማ 9,015 ሲሆን በገጠር የሚኖረው ህዝብ
83,922 ሲሆን በአጠቃላይ የህዝብ ብዛቱ 92,937 ነው፡፡ በወረዳው የሚኖረው ማህበረሰብ በአብዛኛው የአማራ
ብሄረሰብ ሲሆን የሚነገረው ቋንቋ በአብዛኛው አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነው፡፡ የወረዳው ህዝብም በአብዛኛው
የሚተደደረው በግብርና ስራ ላይ ሲሆን ጥቂት የሚባለው ማህበረሰብ በከተማ ሲሆን እነርሱም የሚተዳደሩበት በንግድና
በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ የወረዳው ህዝብም የሚያመርታቸው የአዝርዕት አይነቶች ጤፍ፣ ስንዴ፣
ገብስ፣ ባቄላ፣ ሽንብራ ፣ አተር፣ ጓያ፣ ምስር፣ በቆሎ ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡ አብዛኛው የወረዳው ህዝብም የኦርቶዶክስ
ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታይ ሲሆን በጣም ጥቂት የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት
ሀይማኖት ተከታዮች አሉ፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚኖረው በገጠር ሲሆን በአነስተኛ የሚኖረው ደግሞ በከተማ ነው፡፡

1.2 አነሳሽ ምክንያት


 ሰዎች ለልጆች ስም ሲያወጡም ሆነ ሲቀይሩ መሰረት የሚያደርጉት የተለያዩ ገጠመኞችንና ምክንያትን
በማስተዋል በጥናት አስደግፎ ታይቷል፡፡
 በአሁኑ ጊዜ ጥናት በሚካሄድበት አካባቢ ያለው ማህረሰብ ያለውን የስም አወጠጥ ስልት ምን እነደሚመስል
በማጥናት በጽሁፍ አስደግፎ ታይቷል፡፡
1.3 የጥናቱ አላማ

2
በዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ ለመዳሰስ የሚሞከረው አብይ አላማ ጥናቱ በሚካሄድበት አካባቢ ነዋሪ የሆነው ማህበረሰብ
የሰዎችን የመጠሪያ ስሞች አወጣጥ እና ቅየራ ስልት ምን እንደሚመስል በመተንተን ታይቷል፡፡ ንኡስ አላማው ደግሞ

- ሰዎች ስማቸውን እንዲቀይሩ የሚያነሳሰሳቸውን ምክንያት ምን እንደሆነ በመለየት ተተንትኗል፡፡


- በመጀመሪያ የወጣላቸው ስም እና የተቀየረው ስም ያለው የትርጉም ልዩነት ተተንትኗል፡፡
- ስሞቹ ምንን መሰረት አድርገው እንደሚወጡ እና እንደሚቀየሩ በመለየት በየዘርፉ ተከፋፍሎ ተተንትኗል፡፡
1.4 የጥናቱ ጠቀሜታ

በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ የሰው ስም አወጣጥና ቅየራ የሚለው ጥናታዊ ጽሁፍ ሙሉ በሙሉ ተሰርቶ
ሲጠናቀቅ የሚኖሩት ጠቀሜታቸው፡-

- የማህበረሰቡን የሰው ስም አወጣጥ እና ቅየራ ምክንያት በማወቅ በታሪክ ቀርፆ ለማቆየት እና ከትውልድ
ትውልድ ለማስተላለፍ
- የሰው ስም አወጣጥ እና ቅየራ በሞረትና ጅሩ ወረዳ የማህረሰቡ ስልት ምን እነደሚመስል ታይቷል፡፡
1.5 የጥናቱ ወሰን

ይህ ጥናት በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ አካባቢ ነዋሪ የሆነውን ማህረሰብ የሰዎችን የመጠሪያ ስም አወጣጥና
ቅየራ ስልቱን በማጥናት መቃኘት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ሌሎቹን የስያሜ አይቶች እና ከመደበኛው ውጭ ያሉ የሰው
ስሞችን አይመለከትም፡፡ ምክንየቱም ካለው የጊዜ፣የገንዘብ፣የጉልበት፣የአቅም ውስንነትና እጥረት አኳያ ነው፡፡ ጥናቱ
በወረዳው ከሚገኙ 19 ቀበሌዎች መካከል በ 4 ቀበሌዎች የተሰራ ነው፡፡

1.6 የጥናቱ ዘዴ
1.6.1 የናሙና አመራረጥ ዘዴ

ይህ ጥናት አጥኝዋ በምቾት የናሙና አመራረጥ በመጠቀም በሞረትና ጅሩ ወረዳ ካሉ 19 ቀበሌዎች መካል በ 4
ቀበሌዎች ላይ በናሙናነት ተመርጠዋል፡፡ ምክንያቱም አጥኝዋ የምትኖርበት አካባቢ በመሆኑና በአቅራቢያው
መረጃዎችን ለማግኘት አመቺ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡

1.6.2 የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ

ይህ ጥናት ለማከናወንና ከግብ ለማድረስ ሁለት የመረጃ መሰብሰቢ መሳሪያዎች ስራ ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህም ቃለ
መጠይቅንና ሰነድ ፍተሻ ናቸዉ፡፡

ቃለ መጠይቅ

3
አለም እሸቱ (1992 ፣ 56) ቃለ መጠይቅ ተጠያቂው ከተጠያቂ ጋር በአካል ተገናኝተው በጽሁፍ ሳይሆን በቃለ ምልልስ
የሚሰጥበት ዘዴ ነው በማለት ገልፅዋል፡፡ በዚህ መሰረት አጥኝዋ በተጠቀሱት 4 ቀበሌዎች በመዘዋወር ስለ ሰው ስሞች
አወጣጥና ቅየራ ለማወቅ የሚያስችሉ ጥያቄዎች በማዘጋጀትና ከላይ በተጠቀሱት ቀበሌዎች በመዘዋወር ጥናቱ
የተካሄደበትን ነዋሪ የሆነውን ማህረሰብ የስም አወጣጥና ቅየራ ስልት የሚያውቁ ሰዎች ስለ ጥናቱ አላማ በማሳወቅና
በመግባባት መረጃ ለማሰባሰብ ተሞክሯል፡፡

1.7 የመረጃ መተንተኛ ዘዴ

ይህ ጥናት በአይነታዊ ጥናት የቀረበ ሲሆን በገለፃ ላይ በመመስረት ከተገኘው መረጃ መሰረት በማብራራት ተደራጅተው
በገለፃ መልክ ተተንትነዋል፡፡

4
ምዕራፍ ሁለት
ክለሳ ድርሳናት

በዚህ ምዕራፍ በዋናነት ሁለት ንኡሳን ርእሶች ተካተዋል፡፡ የመጀመሪያው የጥናቱ ትንታኔ ለመስራት አጋዥ እና መሰረት
የሆኑ ንድፈ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከጥናቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቀደምት ጥናታዊ ጽሁፎች
በመፈተሽ ከጥናቱ ጋር ያላቸው አንድነት እና ልዩነት የሚቃኝበት ክፍል ነው፡፡

2.1 ንድፈ ሀሳባዊ ቅኝት


በዚህ ርዕስ ስር ከጥናቱ ጋር ግኑኙነት ያላቸውን ንድፈ ሀሳቦች ተዳሰውበታል፡፡ እነርሱም፡ - የስያሜ ምንነት፣ የስያሜ
አጀማመር፣ የሰው ስም አወጣጥ ልምድ፤ በሰያሚዉ እና በተሰያሚው መካከል ያለውን ግንኙነት እና የስም ትርጉም
(ፍቺ) የሚሉት ጉዳዮች በዚህ ቅደም ተከተል ይቃኛሉ፡፡

2.1.1 የስያሜ ምንነት


ስያሜ በማንኛውም የሰው ልጅ ማህራዊ ግንኙነት ውስጥ የነበረ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ የሰው ልጅ ከህይወቱ
ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች አንዱን ከሌላው ለይቶ ለማወቅ ወይም ለነገሮች መለያና መታወቂያ እንዲሆን
ለተለያዩ ነገሮች ስያሜ ይሰጣል፡፡

ስያሜ የሚለውን ቃል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የአማርኛ መዝገበ ቃላት (2001፣122) ስያሜ
ማለት ስም ወይም መጠሪያ ወይም የመሰየም ጉዳይ ሲሆን አንድን ነገር ቦታ ወይም ሀሳብ የሚወክል ተግባር ነው፡፡

ከዚህ ሀሳብ መረጃ እንደምንረዳው ስያሜ ወይም ስም ማለት ለሰው ልጆች፣ለነገሮች ወይም ለቦታዎች ሁሉ መጠሪያ
የመፍጠር ተግባር እንደሆነ እና አንዱን ከሌላው ለይቶ ለማወቅ የመሰየም ወይም ስም የመስጠት ሂደት እንደሆነ ያሳያል፡፡

በተጨማሪም ተሰማ ሀብተ ሚካኤል (1951፣ 294) የስያሜን ምንነት ሲገልጽ “ስያሜ ማለት ለነገር በየአፈታቱ፣
ለሰው በየትውልድ መጠሪያ የመስጠት ወይም በክርስትና ወይም በህይወተ ስጋ በኖረበት ጊዜ እገሌ ተብሎ እዲጠራበት
ስምን እገሌ ብሎ መጥራት ነው” ይላል፡፡ በተጨማሪም ሲገልጽ “የሰው ስም ማ l ት የአንድ ሰው የመጠሪያ ስም፣
በየነፍሱ የሚጠራ b ት ከእናት ከአባቱ የወጣለት የግል ስም ነው፡፡ በማለት የሰውን ስም ምንነት ይገልጻል፡፡ ከዚህ ሀሳብ
እነደምንገነዘበው ስያሜ ለአንድ ሰው፣ ነገር በአጠቃላይ ከሰው ልጅ ህይወት ጋር ግንኙ n ት ላላቸው ነገሮች አንደኛው
ከሌላኛው ለመለየት የሚያስችል ስያሜ የማውጣት ወይም የመስጠት ሂደት ነው፡፡በስያሜ አማካኝነት የነገሩ እሱነት
እና ማንነት ተለይቶ የሚታወቅበት መለያው ነው፡፡ ይህ ለአንድ ነገር የሚሰጠው የሚገኘው ስያሜ ሂደት አማካኝነት
ሲሆን አገልግሎቱም አንድ ነገር ከሌላው ነገር ተለይቶ እንዲታወቅበት ማስቻል ነው፡፡በመሆኑም ስያሜ ለአንድ ነገር ስም
የማዉጣት ሂደት ሲሆን ጉዳዩ በቅርብ ጊዜ የተፈጠረ ሳይሆን ከሰው ልጆች ማህበራዊ ህይወት ጋር የተጣመረ ጥንትም
ጀምሮ የነበረ፣ አሁንም ያለ ወደ ፊትም የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የቀረቡትን ሀሳቦች መሰረት አድርገን የሰዎችን
ስያሜ ምንነት ስንመለከት ለሰዎች የሚሰጣቸው ከተለያዩ ቡድኖች መካከል አንዱን ሰው የሆነውን ፍጡር ብቻ ነጥለን
የምንጠራበት ማለት ነው፡፡

5
በአጠቃላይ ስም ማለት የተለያዩ ሰዎች፣ ቦታዎች እና ነገሮች የሚጠሩበት እና ተለይተው የሚታወቁበት ሲሆን
ጠቀሜታውም ጎልቶ የሚታየው በሰዎች ማህበራዊ እና ግላዊ ህይወት ውስጥ የሚገለገሉባቸው በርካታ ነገሮች አንዱን
ከሌላው ለይቶ ለማወቅ ማስቻሉ ነው፡፡ የስም ምንነት ስናስብ የሰው ስም፣ የቦታ ስም፣ የነገሮች ስም፣ የእንሰሳት ስም፣
የእጽዋት ስም … ወዘተ የሚሉትን ሰፊ ጉዳዮችን የሚያቅፍ ክፍል ነው፡፡

2.1.2 የስያሜ አጀማመር


ስያሜ በዚህን ጊዜ ተጀመረ ብለን በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም አጀማመሩን ግን ከሁለት አቅጣጫ ይታያል፡፡
የመጀመሪያ መለኮታዊ ስጦታ ተደርጎ ሲታይ፣ ለዚህ ማስረጃ ደግሞ በአለም ላይ በስፋት ተሰራጭቶ ያለውን መጽሀፍ
ቅዱስን ስንመለከት ኦሪት ዘፍጥረት (1፣1) እንደተገለጸው፡-

እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው ጨለማውን ሌሊት አለው፤ የብሱን ምድር
ብሎ ጠራው ውሃ ያለውንም ባህር አለው፡፡ ዘፍ (1፣1-8) እግዚአብሔር አምላክ ከምድር አራዊትና ከሰማይ
ወፎች ሁሉ ከመሬት አደረገ፣ በምን ስም እንደሚጠሯቸው ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፡፡ ዘፍ (12፡19-
20) አዳም ህያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደጠራው ህያው ሆነ፡፡ አዳም ለእንሰሳ ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎችም
ሁሉ፣ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፡፡

ከዚህ የምንረዳው የስያሜ አጀማመርን ገና ከሰማይና ምድር መፈጠር ጀምሮ በመለኮታዊ ሀይል እንደሆነ ያሳያል፡፡
ጀማሪውና አስጀማሪው እግዚአብሔር ሆኖ ተከታዩ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ሀሳብ አስመልከቶ ሳይንሳዊና
ተጨባጭ በሆነ ማስረጃ የሚያምኑ ሰዎች ወይም ወገኖች አይቀበሉትም፡፡ እንደነሱ አስተሳሰብ ስያሜ ከሰው ልጅ
ታሪካዊ አመጣጥ ከቋንቋ አፈጣጠር ጋር የጠበቀ ግንኙነትና ትስስር አለው ይላሉ፡፡ የቋንቋ አመጣጥ ታሪክም ከሰው ልጅ
ታሪክ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ለአሁኑ እድገትና ስልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰው በማምረትና ቋንቋ
መጠቀም በመቻሉ ነው፡፡

በተጨማሪም ዮናስ እና ሌሎች (1963፡4) እንደገለጹት፡-

የስያሜ አጀማመር ከቋንቋ አጀማመርና ከሰው ልጅ ታሪካዊ አመጣጥ ጋር ግኝት ለማሳየት የተለያዩ መላምቶች
ያቀርባል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት የመጀመሪያው መላምት ጥንታዊ ሰው ተፈጥሯዊ ነገሮች
የሚሰይሙት ተፈጥሯዊ ድምጾች በመቅዳት ወይም በመኮረጅ በአካባቢው ለሚገኙ ነገሮች ሁኔታዎች እና
ድርጊቶች ለስያሜ በቅቷል የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የሰው ልጆች ከባድ ነገር ለመስራት ለምሳሌ ድንጋይ
ለመፈንቀል፣ ግንድ ለማንከባለል፣ የመሳሰሉ ስራዎችን በሚሰሩበት ወቅት ምታዊ የሆኑ ድምጾችን ያሰማሉ፡፡
እንዲህ ያሉ ስራዎችን በሰሩ ቁጥር የስራው ጉልበት ፈላጊነት እና መተባበርን የተለያዩ ድምጾችን እየደጋገሙ
በመጥራት ከብዘ ጊዜ ልምድ በኋላ ድምጾች እና የስራዎችን አይነት በማዛመድ በዘመድ ብዛት ስያሜ አወጡ
በማለት ይገልጻሉ፡፡

ይህን ሀሳብ በተመለከተ ስያሜዎቹ ሰዎች እርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር አካባቢን ይበልጥ ለማወቅ ፍላጎትን
ለመግለጽ እና ለሚገባቸው ነገሮች ሁሉ ከቋንቋ አጀማመር ጋር አብሮ ስያሜ ይወጣ እንደነበረ ሲገልጽ ይታያል፡፡
በአጠቃላይ ስያሜ የተጀመረበት ጊዜን ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ስያሜ ከሰው ልጆች ጋር አብሮ እንደኖረ እና

6
ወደፊትም እነደሚኖር የሰው የአእምሮ አድመሱ እየሰፋ ሲሄድና በስልጣኔም ሆነ በማንኛውም እድገት ሲያሳይ ስያሜው
አብሮ ከፍልስፍናቸው ጋር የሚሄድ እንደሆነ እንገነዛባለን፡፡

2.1.3 የሰው ስም አወጣጥ ልማድ


የሰው ልጅ አንደኛው ለሌላኛው የመጠሪያ ስምን የሚየወጣው ምን ምን ጉዳዮችን መሰረት እንደሚያደርግ ለመጠቆም
ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ከተወለደ በኋላ ስም ይወጣለታል፡፡ ይህን አስመልክቶ የቀረቡ ማስረጃዎች
ደሳለኝ (1990፡12) ሰይፍ መታፈሪያን ጠቅሶ እንደገለጸው፡-

አንድ ስም ሲወጣ ልዩ ልዩ ምክንያቶች መነሻ አድርጎ ከዚህ ዋናው በህይወቱ ግንኙነት ለሰው ሁሉ አንድ
መጠሪያ ማስፈለጉ ነው፡፡ ስም የባለ ስሙን እኔነት አሻራ ይዞ የሚዞር ስለሆነ የሰው ልጅ ለሆነ ሁሉ እንደ
አስፈላጊነቱ ስለሚቆጠር ነው፡፡ ማለት ለሰው ልጆ ስም እና እኔነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ስሙም የሰዎች
የስም አውጭዎች የህይወት ብስጭት ወይም የህይወት ደስታ ወይም አንዳንዶች አስተያየት መግለጫ ነው
በማለት ገልጸዋል፡፡

የዚህ ሀሳብ አገላለጽ የሰው ልጅ ለአምሳያዎቹ የመጠሪያ ስምን የሚያወጣው አንዱን ከሌላው ለይቶ ለማወቅ የመጠሪያ
ስም የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ አስፈላጊነቱም አንዱን ከሌለው ለይቶ ለማወቅ የመጠሪያ ስም የግድ እንደሆነ
ይጠቁማል፡፡ የስምንም አወጣጥ ልምድ በተመለከተ የሰው ልጅ የግድ አስፈላጊ ዙሪያ ለሚያጋጥሙት ልዩ ልዩ ክስተቶች
ለምሳሌ ደስታ፣ ሀዘን፣ ችግር፣ መልካም ምኞት ወዘተ ስምን ከተሰያሚው እና ሰያሚው እውናዊ ህይወት ጋር እያጣመረ
እንደሚወጣ አክሎ ተገልጾአል፡፡

በተጨማሪም አበበ (1995፣11) ኢንሳይክሎ ብሪታኒካን ጠቅሶ እነደተገለጸው ማንኛውም ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ
ከተወለደ ስም ይወጣለታል፡፡ ይህ ስም በወላጅ ወይም በቤተሰብ አባል የሚሰጥ ነው፡፡ ሰሙም የሚወጣው ከእምነት፣
ከቤተሰብ ክብርና ደረጃ፣ ከህጻናት አጠቃላይ ሁኔታ ከተለያዩ የስም አውጪዎች ገጠመኝ አንጻር ነው ይላል፡፡

ከዚህ ሀሳብ መረዳት የሚቻለው ለስም አወጣጥ ልምድ የስም አውጭዎች የህይወት ገጠመኝ ወሳኝ መነሻዎች እንደሆኑ
ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም የሰዎች የመጠሪያ ስሞች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸው ጠቀሜታ የስነ ልቦናዊ ቅሬታን፣
የኑሮ ሁኔታን ባህሉን አመለካቱን በአጠቃላይ ህይወታዊ ልምዶችንም ስም ዋናው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህ የስም አወጣጥ
ልምድ እንደየ አካባቢውና እንደየ ሀገሩ ባህል፣ ቋንቋ፣ ተሞክሮ የተለያየ መልክ እንደሚኖረው ይጠቁመናል፡፡

በአጠቃላይ ስለ ስም አወጣጥ ልምድ አጠር ተደርጎ ሰታይ ሰዎች ላማወቅ የመጠሪያ ስም ያወጣሉ፡፡ የስም መውጣት
ሂደት ግን እንደየ አውጭዎች ገጠመኝ፣ ስሜት፣ እምነት ስነ ልቦነዊ ሁኔታ የተላየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ሲባል ለልጆች
ስም ለማውጣት ብዙ ሁኔታዎች ወሳኝ እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡

2.1.4 በስያሜ እና በተስያሚው መካከል ያለው ግንኙነት


በዚህ ርዕስ ስር ለማቅረብ የተፈለገው በአንድ የመጠሪያ ስምና የሰው ባለቤት ከሆነው ሰው ወይም ነገር መካከል ግንኙነት
መኖር አለመኖሩን ለመግለጽ ነው፡፡ ይህን ሀሳብ በተመለከተ ዮናስ እና ሌሎች (1966፣ 14) እንደገለጹት፡-

7
በአንድ ድምጽ ወይም በአንድ ቃል ድምጽ ወይም ቃሉ የሚያመለክተው ወይም የሚሰየመው ነገር መካከል
የባህርይ ግንኙነት የለም “ውሻ” የሚለው ድምፅ በዚህ ድምፅ ለምን ጠራው እንስሳት ውሻ በሚለው ፈንታ
“ብላ” ብንለው ውሻነቱን አይለውጠውም፤ ድመት ብንለው ድመት አይሆንም ለማንኛውም ነገር የሚሆን
ትክክል የምንለው መጠሪያ ወይም ተገቢ የምንለው ስም የለም፡፡

በአጠቃላይ ከምሁራን ሀሳብ የምንረዳው በወካዩና በተወካዩ መካከል ምንም አይነት ነገር የባህሪ ወይም የተፈጥሮ
ግንኙነት አለመኖሩንና ዘፈቀዳዊ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡

በሌላ በኩል ሙሉጌታ (1972፣ 1) ስያሜ እና ችግሩ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ጥናታዊ ጽሁፍ በስያሜና በተሰያሚው
መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ሲገልጽ፡-

በቋንቋ የሚሰራባቸው ስያሜዎች በመጀመሪያ ሲጠሩ ከሚያስተላልፉት ሀሳብ ወይም ከሚወክሉት ግዙፍ
ቁሳቁስ ወይም ድርጊት ወይም ሁኔታ የባህሪ ዝምድና ስላላቸው ከነሱ በቀር ሊሆን ባለመቻሉ አይደለም፡፡
እነደዚህ በመሆኑ ለአንድ ነገር የተለያዩ ስያሜዎች ሠተሰጥተውት እናያለን፡፡ ይህም በስያሜዎች እና
በተስያሚዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከመነሻው ሲታይ አጋጣሚያዊ እንጂ ስጋዊ አይደለም በማለት ገልጾአል፡፡

ይህ ሀሳብ የሚያስገነዝበው ለአንድ ነገር ሰዎች የሚሰጡት ስም ስሙ ከሚወጣለት ነገር ጋር ምንም አይነት የባህሪ
ግንኙነት የለውም፡፡ ሰዎች ወይም የስሙ አውጭዎች በአጋጣሚ ስለ ባለ ስሙ ወይም ነገሩ እና ስሙ ካላቸው ገጠመኝ
አንጻር የሚወጣበት ነው፡፡ ይህ እውነታም የሚታየው አንድ ነገር ሰዎች ካላቸው የግል ገጠመኝ አንጻር በተለያዩ ቦታዎች
የተለያዩ ስሞች ሰጥተውት ሲጠሩት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሰያሚው እና በተሰያሚው መካል ምንም አይነት ግንኙነት
ባለመኖሩ ሰዎች ስም ስለሚያወጡለት ነገር እንደ አጋጠማቸው የግል ገጠመኝ የተለያዩ ስሞች ለአንድ ነገር ሲሰጡ
ይስተዋላል፡፡ ይህ ጉዳይ ከፍ ሲል በሰሙና በተስያሚው መካከል ምንም አይነት ግንኙነት የለም የሚለውን ሀሳብ
ያጠናክራል፡፡ ይህ ሲባል የአንድ ነገር ስም ስለ ባለስሙ ምንም አይነት ነገር አይጠቁምም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም
ስለ ባለስሙ ማንነት በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ሁኔታ ወይም ስለ ስም አውጭዎች አንዳች የሆነ ስሜት የሚጠቁም
መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ በአጠቃላይ ከምሁራን ሀሳብ የምንረዳው በወካዩና በተወካዩ መካከል ምንም አይነት የባህሪ ወይም
የተፈጥሮ ግንኙነት አለመኖሩ እና ዘፈቀዳዊ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በተጨማሪም መላክ ብርሃን (2001፡ 10-11)
እንደገለጸው፡-

ስያሜ ለአንድ ነገር መለያ ወይም መታወቂያ ከመሆኑም በተጨማሪ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይገልጻል፡፡
አንድ ማህበረሰብ ተግባብቶ ለመኖር ቋንቋ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ስያሜም አስፈላጊ ነው፡፡ ቋንቋ ደግሞ ያለ
ስያሜ ብቻውን ሊያገለግል አይችልም፡፡ ለሰዎች፣ ለወንዞች፣ ለመንገዶ፣ ለተፈጥሮ ክስተቶች እንዲሁም
የመሬት ገጽታዎች የሚሰጡት ስያሜዎች ለመጠሪያነት ከማገለግለላቸው ባሻገር የህብረሰተቡን ባህል ታሪክ
የሚገልጹ ናቸው፡፡ የተለያዩ ብሄረሰቦች ደስታቸውን፣ ሀዘናቸውን፣ እምነታቸውን፣ልማዳቸውን እንዲሁም
ሌሎችን ሁነቶች ስም በመሰየም ይገልጻሉ፡፡

8
ከዚህ ሀሳብ መረዳት የሚቻለው ስያሜ የአንድን ማህበረሰብ እሴት፣ ባህል፣ ወግ እንዲሁም ሀዘን ደስታቸውን በሙሉ
የሚገልጹ አዳዲስ ነገሮች በገጠማቸው ቁጥር ስያሜዎችን በመስጠት ተግባብተው ከቋንቋው ጋር ግንኙነት ባለው መልኩ
የሚጠቀሙበት ስልት

ነው፡፡

2.1.5 የስም ትርጉም ወይም ፍቺ ምንነት


የስሞችዋነኛ አገልግሎት ለመጠሪያ ቢሆንም የተለያዩ ሰዎች የየራሳቸው የሆነ ትርጉም አላቸው፡፡ ይህም የስም
ትርጉም ስለ ስሙ ባለቤትና ስለ ስም አውጪዎች የሚጠቁመን ነገር አለ፡፡

ፀደቀ (1981፡ 28) የስሞችን ትርጉም እስሚዝን በመጥቀስ ሲገልጽ

“የሰው ስሞች አንድ ወጥ የሆነ መደብ ስሞች ሆነው በአጠቃላይ ሰብዓዊ ፍጡሮችን በመግለጽ በተደጋጋሚ ያገለግላሉ፡፡
የስያሜዎችን ማህበራዊ ሁኔታ ካሉበት አካባቢ ባህላዊ ገጽታዎች ጋር አገናዝበው የመግለጽ አቅማቸው ከፍተኛ ነው”
ይላል፡፡

የዚህ መረጃ ሀሳብ የሚያስገናዝበን የሰዎች የመጠሪያ ስሞች ትርጉም ያላቸው መሆኑን ነው፡ ይህ የአንድ ስም ፍቺ
የስሙን ባለቤት ምንነት ማለትም የስሙ ባለቤት ያለውን መልክ፣ ጸባይ፣ ተግባር ወዘተ እና የስም አውጭው ስም
ሲያወጡ የነበራቸውን የሀዘን፣ የደስታ፣ ሁኔታ፣ ፍላጎት ወዘተ ይገልጻል ማለት ነው፡፡ ይህም ሲባል የሰዎች የመጠሪያ
ስሞች ትርጉም የስም አውጨዎችን ስሜትና አጠቀላይ ሁለንተናዊ ስብእናን ይገልጻሉ፡፡ በተመሳሳይ የስም ምንነት
ደስታ ተክለወልድ/1962፣149/ ሲገልፅ፡-

“ስም የቦታና የአካል መጠሪያ ማንኛውም የሚታይ የማይታይ ነገር ሁሉ የሚጠራበትና የሚታወቅበት ነው፡፡” በማለት
ገልጾአል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት (2001፣
136) ሲገልጽ “ስም ለማንኛውም ነገር ሰው ቦታ የሚስጥ መጠሪያ ነው ይላል፡፡”

ከዚህ ሀሳብ የምንረዳው ነገር ስም በምድር ላይ ላለ ነገር ሁሉ ማለትም ረቂቅም ሆነ ተጨባጭ ነገሮች በሙሉ
ተለይተው የሚታወቁበት መሆኑም የሚያገለግለው ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን በርካታ ነገሮች ለሰዎች አንዱን ከሌላው
ለይቶ ለማወቅ ነው፡፡

ስም የሚወጣው በአይናችን ለምናያቸውና በእጃችን ልንዳስሳቸው ለማንችለው ነገር ሁሉ መሆኑን ከላይ የቀረቡት
ጥቅሶች ያመለክታሉ፡፡ ስለ ስም ስናስብ የሰው ስም፣ የቦታ ስም ፣የነገር ስም፣ የእጽዋት ስም፣ የእንሰሳት ስም ወዘተ
የሚሉትን የሚይዝ ሲሆን ይህ ጥናት ትኩረቱ በሰዎች ስም አወጣጥ ላይ ነው፡፡

የቀደምት ጥናቶች ቅኝት

ደሳለኝ (1990) “የሰው የተጽውኦ ስም አወጣጥ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርቧል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በሰሜን
ጎንደር ዞን በዳሎቻ ወረዳ አካባቢ ነው፡፡ በጥናቱ እንደተገለጸው የጥናቱን አላማ አድርጎ የተነሳው በሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪ

9
የሆነው የአማራ ህዝብ የሰዎች የመጠሪያ ስም አወጣጥ ልምዱ ምን እንደሚመስል ማጥናት ነው፡፡ ለጥናቱም
አነሳሽየሆነው ምክንያት የዚህ ማህበረሰብ የሰዎችን የመጠሪያ ስም አወጣጥ ምን እንደሚመስል ተንትኖ ማሳየት ነው፡፡
በዚህ መሰረት በጥናቱም የተገኘው ውጤት የሰሜን ጎንደር ዞን የዳሎቻ ወረዳ የመጠሪያ ስም አወጣጥ እና ስያሜ
ከሰዎች ህልውና ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጨባጭ እና ረቂቅ የሆኑ የተለያዩ ነገሮች የስያሜ ሂደት የአንድን ማህረሰብ
የተለያዩ ማህራዊ ገጠመኝ እና የእምነት ልማድ ልዩነት ሲከሰት አጋጣሚ ህብረተሰቡ ከሚከተላቸው የተለያየ ልምዶች
ሀይማኖታዊ ሁኔታ ስም አውጭዎች ካላቸው ገጠመኝ አንጻር ወዘተ አንደሚሰየመው ስምና በህብረተሰቡ ዘንድ
እንደሚሰጠው ትርጉም መረዳት ይቻላል፡፡ ለጥናቱ ደጋፊ የሆኑ መረጃዎችን በቃለ መጠይቅ የሰበሰበ ሲሆን ማጠቃለያ
ላይ እያንዳንዱ ሰው የሚከተለው የስም አወጣጥ ስርዓት እና ባህል እንደየወጉ እንደየ እምነቱ እንዲሁም ከስም አወጣጥ
ስርአት ጋር እንደየገጠመኞቻቸው የተለያዩ መሆናቸውንና ህብረተሰቡ የቀደምት እምነቱን ከነበረው ወቅታዊ ጉዳይ ጋር
ተዛማጅ በማድረግ እንደሚወጣ አመልክቷል፡፡

የዳሰለኝ ጥናታዊ ጽኁፍ ከእኔ ጥናታዊ ጽሁፍ ጋር የሚያመሳስለው በመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ አጠቃቀማቸው
ሁለቱም ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ መቅረባቸው የሁለቱም ጥናቶች አብይ ጉዳይ የሰው ስሞች አወጣጥ ላይ መሆኑ
ሲሆን የሚለያያቸው ደግሞ የደሳለኝለሰዎች ስም አወጣጥ ላይ ሲያተኩር ይህ ጥናታዊ ፅሁፍ ከስም አወጣጥ በተጨማሪ
የስም ቅያሬንም አብሮ ይመለከታል፡፡ ሌላው የሚለያያቸው ደግሞ ይዘውት ከተነሱት አላማ አንጻር ሲሆን የደሳለኝ
ጥናት ዋና አላማው የሰዎች የተጽውኦ ስም አወጠጥ ላይ ብቻ ሲሆን የዚህ ጥናት ዋና አላማ ደግሞ ከስም አወጣጥ
በተጨማሪ የስም ቅያሬንም የሚያነሳ መሆኑ ያለያያቸዋል፡፡

ተዘራ ዘአማኑኤል (2006) “የስልጤ ማህረሰብ የማእረግ ስም አወጣጥ ስርአትና ፋይዳዊ ትንተና” በሚል ርዕስ ጥናት
አድርጓል፡፡ በጥናቱ ላይ እንደተጠቀሰው አላማ አድረጎ የተነሳው የብሄረሰቡን የማዕረግ ስም አሰጣጥ ን በመመርመር
ፎክሎራዊ የባህል ቅኝቱን ማሳየትና ይህ የማእረግ ስም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ ፋይዳ አሉታዊ እና
አወንታዊ ጎኖች ማሳየት፡ ጥናቱን ለማካሄድም ያልታቀደ ምልከታ እና ቃለ መጠይቅ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

በመሆኑም የማዕረግ ስም አሰጣጥ ከፎክሎር ዘውጎች ጋር ያለው ቀጥተኛ ግንኙነት ተዳስሷል፡፡ በዚህም መሰረት ስሞቹ
ለምን አይነት ሰው እንደሚሰጡ ያከናወኗቸው ተግባራት እና የሚሰጣቸው የማዕረግ አይነት ምን እንደሆነ ማህረሰቦቹ
ለስሞቹም አይነት አመለካከት እንዳለው ጭምር ተንትኖ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ ይህን አላማ ከግብ ለማድረስና ትክክለኛ
መረጃዎችን ለማግኘት ወይም ለመሰብሰብ አጥኚው ማዕረግ ከተሰጣቸው ግለሰቦች ጋር ተገናኝቶ ምልከታ በማካሄድ
ፎቶ ግራፍ በማንሳት እና ቃለ መጠይቅ በማድረግ ተገቢ መረጃዎችን መሰብሰብ ችሏል፡፡ በዚህ መሰረት በጥናቱ ውጤት
እንደተገለጸው አንድ ሰው ትላልቅ የሚባሉ ተግባራት ከስራ ወይም ከፈጸመ የማእረግ ስም እንደሚሰጠው እና
በማህረሰቡ ዘንድ እንደትልቅ አዋቂ እንደሚቆጠር ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም የተጣለበትን አደራ መወጣት
ካልቻለ ስሙን ሊነጠቅ እና ከማህረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እና ክብር ሊያጣ እንደሚችል በጥናቱ ውጤት ላይ
ተገልጾአል፡፡

በመቀጠልም በምዕራፍ ሶስት ላይ የማእረግ ስሞችን ምንነት ከተሰየሙበት ምክንያት አንጻር በአራት በመከፋፈል
መረጃውን ተንትኖ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ የማዕረግ ስሞች አከፋፈልም የተሰጡበትን ምክንያት በአስተዳደር ብቃት፣
በጀግንነት ብቃት፣ በሃይማኖት ጥንካሬ እና ለሴቶች የሚሰጡ ስሞች ላይ መሰረት እነደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

10
ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ ከተዘራ ዘአማኑኤል ጥናት ጋር የሚያመሳስለው ሁለቱም ጥናቶች ትኩረት አድረገው የተነሱት
በስያሜ ላይ መሆኑ እና ሁለቱም ለመጀመሪያ ድግሪ ማሟያ የቀረቡ መሆናቸው ነው፡፡ የተዘራ የጥናታዊ ጽሁፍ
አላማከግብ ለማድረስ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የማእረግ ስም ከተሰጣቸው ሰዎች ወይንም ግለሰቦች ጋር
መረጃውን በቃለመጠይቅ መሰብሰብ ያመሳስለዋል ስለዚህ በሌላ አነጋገር ከመረጃ መሰብሰብያ መሳሪያ አንጻርም
ይመሳሰላሉ ማለት ሲሆን ሁለቱም ጥናታዊ ጽሁፎች የሚያለያያቸው ደግሞ አላማቸው ነው፡፡ የተዘራ ጥናት አላማ
አድረጎ የተነሳው የስልጤ ማህረሰብ የማእረግ ስሞች አሰጣጥ ትንተና በመመርመር ፎክሎራዊ ቅኝቱን ማሳየት እና ይህ
የማእረግ ስም በማህረሰቡ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ ፋይዳ አሉታዊ እና አወንታዊ ጎኖች ማሳየት ሲሆን የዚህ ጥናታዊ
ጽኁፍ አላማ ደግሞ ጥናቱ በተካሄደበት ነዋሪ የሆነውን ማህረሰብ የሰዎችን የስም አወጣጥና ቅየራ ስልት ምን
እንደሚመስል ተንትኖ ማሳየት ነው፡፡ ሌላው የሚያለያያቸው የተዘራ ጥናት የማእረግ ስም ላይ ሲየተኩር የዚህ ጥናት
ትኩረት ግን የሰዎች ስም አወጣጥና ቅየራ ተንትኖ ማሳየት ነው፡፡ ከጥናቱ ውጤት አኳያ የተዘራ ጥናት የሚያሳየው አንድ
ሰው ትልቅ የሚባሉ ተግባራትን ወይም ገድላትን ሲሰራ የማእረግ ስም እንደሚሰጠውና በማህረሰቡ ዘንድ እንደ ትልቅ
እንደሚቆጠር በጥናቱ ግኝት ላይ ገልጾአል፡፡

ስለዚህ ሁለቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ከጥናቱ ውጤት አንጻርም ልዩነት እንዳላቸው መገንዘብ ተችሏል፡፡ ምክንያቱም የተዘራ
ጥናተዊ ጽኁፍ በማዕረግ ስሞች አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ ግን በሰዎች ስም አወጣጥና ቅየራ ላይ
ያተኮረ ነው፡ ከመረጃ መሰብሰቢያ አንጻርም ተዘራ ከቃለ መጠይቅ በተጨማሪ ምልከታን መጠቀሙ ከዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ
ጋር የመረጃ መሰብሰቢያ ልዩነትም ያመለክታል፡፡

ገብረስላሴ (2006) “በኩኃ ያሉ ሰፈሮች ስያሜ” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽኁፍ አቅርቧል፡፡ ጥናቱ አላማ አድርጎ የተነሳው
በእንድርታ ወረዳ ኩሃ ከተማ የሚገኙ ሰፈሮች ስያሜ መተንተን ነው፡፡ በዚህም መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች ስያሜ
የተሰጣቸው ሰፈሮች ስሞችን በስያሜያቸው መካከል ያለውን ግንኙነት ወይም ስያሜያቸውን ሊያገኙ የቻሉበት
ምክንያት ማለትም የቅርብ ጊዜ ስያሜአቸውን ደግሞ ለምን በቅርብ ሊሰየሙ እንደቻሉ እና የስያሜ ለውጥ ለምን
እንደፈለጉ በጥናቱ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡ መረጃ ለማሰባሰብ በዋናነት ቃለ መጠይቅ መጠቀሙን የገለጸ ሲሆን በተጨማሪ
ሰነድ ፍተሻንም ተጠቅሟል፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚጠቁመው በኩሀ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሰፈሮች ስያሜአቸውን
ያገኙበት ምክንያት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ሰፈሮች ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር፣ በአካባቢው በሚበቅለው
ተክል አንጻር፣ ከሰፈሩ ሰዎች ተግባራት ጋር በተያያዘ ሁኔታ እዲሁም ሌሎች የተለያዩ አጋጣሚዎችን መሰረት ያደረጉ
ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የሰፈር ስያሜዎች ሆነው ከማገለገላቸው ባሻገር የህብረተሰቡን ታሪክ፣ ባህል፣ ልማድ ወዘተ ለማንጸባረቅ
ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በጥናቱ ግኝት ላይ ገልጾአል፡፡

ይህ ጥናት ከገብረ ስላሰሴ ጥናት ጋር የሚያመሳስለው በመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች እንዲሁም ሁለቱም ጥናቶች
በስያሜ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው እና ሁለቱም ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ሆነው መቅረባቸው ነው፡፡ እዲሁም ሁለቱም
ጥናታዊ ጽሁፎች በስያሜ ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸው ያመሳስላቸዋል፡፡ ሁለቱን ጥናቶች የሚያለያያቸው ደግሞ የገብረ
ስላሴ ጥናት በኩሃ ከተማ ሰፈር ስያሜዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህ ጥናት ግን በሰው የመጠሪያ ስሞች አወጣጥና ቅያሬ
ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው የሚያለያያቸው ደግሞ ከአላማ አንጻር ሲሆ የገብረ ስላሴ ጥናት አላማ አድርጎ

11
የተነሳው በእንድርታ ወረዳ ኩሃ ከተማ የሚገኙ ሰፈሮችን ስያሜ መመርመር እና መተንተን ሲሆን ይህ ጥናት ደግሞ
አላማ አድርጎ የተነሳው የሰው ስሞችን አዋጣጥና ቅየራ መተንተን ነው፡፡

መሀመድ (1992) “በጉራጌ ዞን የቸሀ ወረዳ የማእረግ ስሞች አወጣጥ ይዘት ትንተና” በሚል ርዕስ ባደረግው ጥናት አላማ
አድርጎ የተነሳው የቸሀ ወረዳ የማዕረግ ስሞች በመተንተን ትርጉማቸውን ማመልከት እንደሆነ ገልጾአል፡፡ ጥናቱን
ለማድረግ ቃለ መጠይቅ እና ምልከታን በመረጃ ማሰባሰቢያነት ተጠቅሟል፡፡ በጥናቱ ውጤትም የገለጸው የጉራጌ ዞን
በቸሀ ወረዳ የማዕረግ ስም አወጣጥ እና የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግና ማህራዊ ተሳትፎን መሰረት ያደረገ እና በተለያዩ
መስኮች ባላቸው ውጤት እንዲሁም የዘር ሀረግ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በማጠቃለያው ላይ ለመግለጽ ሞክሯል፡፡
የመሀመድን ጥናት እና ይህን ጥናት የሚያመሳስላቸው ሁለቱም ጥናቶች በስያሜ ላይ ማተኮራቸው እንዲሁም ቃለ
መጠይቅን የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ አድርገው መጠቀማቸው እና ሁለቱም ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ሆነው
የቀረቡ መሆናቸው ነው፡፡

ሁለቱንም ጥናቶች የሚያለያያቸው ደግሞ የመሀመድ ጥናት በማእረግ ስሞች ስያሜ ላይ ማተኮሩ እና ይህ ጥናት ግን
አላማው አድረጎ የተነሳው ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ ነዋሪ የሆነውን የሰዎችን የመጠሪያ ስም አወጣጥ እና ቅየራ ስልት
ምን እንደሚመስል ተንትኖ ማሳየት ሲሆን የመሀመድ ጥናት ግን አላማ አድርጎ የተነሳው በጉራጌ ዞን በቸሀ ወረዳ
የማዕረግ ስሞች አወጣጥ ይዘት በመተንተን እና ትርጉማቸውን በማመልከት ማሳየት ነው፡፡ ከጥናት ውጤት አኳያም
ይለያያሉ፡፡

የመሀመድ ጥናት በጉራጌ ዞን በቸሀ ወረዳ የማዕረግ ስም አወጣጥ የማህረሰብን ባህል፣ ወግና ማህበራዊ ተሳትፎን መሰረት
ያደረገና በተለያዩ መስኮች ባላቸው ብቃት እና ውጤት እንዲሁም በዘር ሀረግ የተመሰረተ እንደሆነ በማጠቃለያው ላይ
ገልጾአል፡፡ የዚህ ጥናት ውጤት ደግሞ ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ የሰዎች የስም አወጣጥ እና ቅየራ የተለያዩ
ገጠመኞችንና ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ስሞችን እንደሚሰይሙ እና እንደሚ ቀይሩ በማሳየት የማህበረሰቡን
የስም አወጣጥ እና ቅየራ ልምድ ወይም ፍልስፍና ማሳየት ነው፡፡ በማእረግ ስሞችን እንዲሰይሙና እነዲቀይሩ በማሳየት
የህብረተሰቡን የስም አወጣጥና ቅየራ ልምድ ወይም ፍልስፍና ማሳየት ነው፡፡

ከላይ ከፍ ሲል የተዘረዘሩት የስያሜ ላይ የተዳረጉት ጥናቶች ከዚህ ጥናት ጋር የሚያመሳስላቸው ሁሉም ጥናቶች
በስያሜ ላይ ማተኮራቸው ሲሆን የሚለዩበት መሰረታዊ ጉዳይ ከላይ ከተዘረዘሩት ጉዳይ ደግሞ ይህ ጥናት በሰው ስሞች
አወጣጥና ቅየራ ላይ ሲሆን ከላይ ከተዘረዘሩት የተጽኦ ስም፣ የማእረግ ስም አወጣጥ እና የቦታ ወይም የሰፈር ስሞች
አወጣጥናየቦታ ወይም የሰፈር ስሞች አወጣጥ ላይ ማተኮራቸው ከዚህ ጥናት ጋር የሚለያዩበት መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡
ከእነዚህም ስራዎች ውስጥ ከዚህ ስራ ጋር ተቀራራቢነት ያለው የደሳለኝ ጓንጉል የሰው የተጽወኦ አወጣጥ ከሚለው ስራ
ጋር ነው፡፡

12
ምዕራፍ ሶስት
የመረጃ ትንተና

የሰው ልጅ አንዱን ከሌላው ለይቶ ለማወቅ እንዲቻል ለተለያዩ ነገሮች ስም ያወጣል፡፡ በመሆኑም ሰዎች አንዳቸውን
ከአንዳው ለመለየት ስያሜ ይሰጧቸዋል፡፡ ማንኛውም ሰው በሀገሩ ባህል በቋንቋው በሀይማኖቱ ረገድ ለልጅ መጠሪያ ስም
ይሰማል፡፡ የመጠሪያ ስም አወጣጥ እና ቅየራ እንደየ አካባቢው ገጠመኝ እና እንደየ ህብረተሰቡ ልምድ የተለያየ ነው፡፡
ስሞችን ሲያወጡና ሲቀይሩ በስሞቹ ውስጥ አንዳች ማስላለፍ የፈለጉት መልእክት ይኖራል፡፡

ስለዚህ የዚያን መህበረሰብ አመለካከት ታሪካዊ አመጣጥ የኑሮ ዘይቤ ማህበራዊ ደረጃ ወዘተ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡
ስለዚህ ማህበረሰቡ ለነገሮች ስያሜ ሲሰጥም ሆነ ሲቀይር አብሮ የሚያስተላልፈው መልእክት እንዳለው መረዳት
ይቻላል፡፡ ከዚህ በመነሳት የዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ አላማ ትኩረት በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ ያሉ ማህበረሰቦች
የሰዎች ስም አወጣጥና ቅየራ ስልት ምን እንደሚመስል መተንተን ነው፡፡ ይህ ጥናት በተካሄደበት አካባቢ የሰዎች ስም
አወጣጥ እና ቅየራ ምን እንደሚመስል ማየት ነው፡፡ ትንታኔው ትኩረት የሚያደርገው በጥናቱ ወሰን የሚነሱትን ስሞች
በየዘርፉ በመከፋፈል ከተለያዩ ምክንያቶች እና ሁኔተዎች አንጻር መተንተን ይሆናል፡፡

3.1 ቤተሰባዊ ሁኔታን መሰረት በማድረግ የወጡ እና የተቀየሩ ስሞች


ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ከቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ የተለያዩ ውጣ ውረዶች ያጋጥሟቸዋል፡፡ ይህን ችግርም
በተለያየ ምክንያት ማስወገድ ይቻላል፡፡ ማለትም አንድ ሰው ችግሩን የሚልፍበት ምክንያት በመፈለግ ለችግሩ መፍትሄ
ይፈልጋል፡፡ ሰዎቹ ስሞች ለማውጣትና ለመቀየር መነሻ የሚያደርጋቸው ጉዳዮች የህይወት ገጠመኞቻውን የሚገልጽ
በመሆኑ ከገጠማቸው ችግር ጋር በማያያዝ ለወለዷቸው ልጆች ስም ሲያወጡና ሲቀይሩ ይታያል፡፡

ስለዚህም ወላጆች በህይወት ያጋጠማቸውን የተለያዩ ችግሮች አስመልክቶ ችግሮቻቸውን ለመግለጽ የሚያስችሉ
ቤተሰባዊ ሁኔታን መሰረት በማድረግ ለልጆቻው የመጠሪያ ስም ሲየወጡላቸው እና ሲቀይሩ ይታያል፡፡ ይህንንም
በማስልከት ከተጠኝዎች ቤተሰብ፣ ከራሳቸው ከተጠኝዎች እና ከአካባቢው ከሚገኙ ታሪክ አዋቂ ከተባሉ ሰዎች በቃ
ለመጠይቅ የተሰበሰበውን ወይም የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ትንታኔው ይቀርባል፡፡

1. ያሳብነህ

″ያሳብህ″ በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን ከመለወለዱ ጀምሮ ህመምተኛ በመሆኑ በየፀበሉና
በየሀኪም ቤቱ እሱን ይዘው ቤተሰቡ ይሰቃዩ ነበር፡፡ ስለዚህ ቤተሰቦቹ ሊሞትብን ነው እያሉ በሀሳብ ይማረሩ ነበር፡፡
ቤታቸውንም ትተው ወደ ራቅ ወዳለ ቦታ እሱን ጸበል ለማስጠመቅ እንዲሁም ለማሳከም በየሀገሩ ቢመዘር ብዙ ስቃይና
መከራን አሳልፈዋል፡፡ ያሳብነህ ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ከህመሙ ተፈወሰ፡፡

ያሳብነህ የመጀመሪያ ልጅ ከመሆኑ የተነሳ ወላጆቹን በተለያዩ የቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ያሉ ስራዎችን የሚያግዝ
እሱ ነበር፡፡ ከዚህም ቤታቸው ጫካ ውስጥ ስለነበር በከብት ጥበቃ እና በአዝመራ ጥበቃ የተለያዩ አራዊቶችን አዝመራውን
እንዳይበሉበት በመጠበቅ በፍርሃትና በሰቀቀን እየተሸማቀቀ ያደገ ህጻን ነው፡፡ እንዲሁም ወደ ቤት በሰአት ስለማይመጣ

13
እናት እና አባቱ ሁልጊዜ ነው ስጋት፣ ሀሳብ፣ ፍርሃት ወዘተ ስለሚድርባቸው አንተ የተፈጠርከውን ለሀሳብ ነው ቀደም
በህመም አሁን ደግሞ በአስተዳደግ መከራ የበዛብህ ነህ በማለት ያሳብነህ የሚል መጠሪያ ስም አወጡለት፡፡

ያሳብነህ አሁን ኢዮብ በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ የቀየረበት ምክንያት አንደኛ በልጅነቱ አያቱ ኢዮብ ይለው ስለነበርና
አሁን አያቱ በህይወቱ ስለሌለ እሱን ለማስታወስሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል
እየተማረ በነበረበት ሰአት እናት እና አባቱ በጠብ ምክንያት ሲለያዩ ትምህርቱን አቋርጦ ለስራ ወደ በረሃ በመሄድ ብዙ
ችግር ገጥሞታል፡፡

ሌለው ደግሞ እናት እና አባቱ ባለመስማማታቸው ከትዳራቸው ተፋቱ፡፡ ከዚያ በኋላ “ያሳብነህ” ከአባቱ ጋር መኖር
ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ በአባቱ እና በእናቱ አለመግባባት ምክንያት አባቱ ታስሮበት ነበር፡፡ በረሃብ በጥም በብቸኝነት
የመሳሰሉት ችግሮችን በትዕግስት አሳልፋቸው፡፡ በተጨማሪም ከጓደኞቹ ጋር ተጣልቶ በጣም አሰቃቂ ጥቃቶች
ተፈጽሞበት ከሞት ተርፏል፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ካሳለፈ በኋላ ያቋረጠውን ትምህርት መማር ጀመረ፡፡ ይህ ሁሉ
ስቃይና መከራ አሳልፎ ትምህርቱን መማር ሲጀምር ጎን ለጎን የሰንበት ትምህርትም መማር ጀመረ፡፡ የሰንበት ትምህርት
እየተማረ እያለ የኢዮብን ታሪክ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ አግኝቶ አነበበ፡፡ ይህን ታሪክ ካነበበ በኋላ ከኔ ጋር የሚተዳዳር
ባይሆንም የኔም ህይወት ትንሽ ውጣ ውረድ የበዛበት ስለነበር ያን ችግር ተቋቁሜ እዚህ ስለደረስኩ በማት ከመጽሀፉ
ቅዱስ ጋር አያይዞ ኢዮብ በሚል ስም ቀየረ፡፡ እንደ መጽሀፍ ቅዱስ ታሪክ መጽሀፍ ኢዮብ (1፡1) “ኢዮብ ማለት ብዙ
መከራ የደረሰበት፣ ታጋሽ፣ ትዕግስተኛና ብዙ ፈተናዎች ደርሰውበት ያሳለፈ” ማለት ሲሆን እሱም ከራሱ የህይወት ውጣ
ውረድ ጋር በማያያዝ ይህን ሁሉ ስቃይ አልፎ እዚህ ደረጃ ስለደረስኩ ብሎ “ኢዮብ” በሚል ስም ቀይሮታል፡፡

2. ጤናው

ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ፍላጎታቸው ተቃኝቶ፣ አላማቸው ተሳክቶ ጤናማ የሆነ ህይወት መኖር ምኞታቸው ነው፡፡
እንዲሟላላቸው ከሚፈልጓቸው ነገሮች አንዱ ፈጣሪ ጤናቸውን እንዲሰጣቸው የታመመ የቤተሰብ አባል ካለም
ምህረት እንዲያገኝ መመኘት ቀዳሚ ፍላጎታቸው ነው፡፡ ጤናው አባት ህመም የተነሳ ሁል ጊዜ ጭንቀት፣ መከራ፣ ሀዘን፣
ሀሳብ፣ ትካዜ ወዘተ ይበዛባቸውና ይጸናባቸዋል፡፡

ልጁ ከተወለደ ጀምሮ አባትየዉ አገግሞ ቀስ በቀስ ለውጥ እያሳየ እየተሻለው መጣ፡፡ ቤተቦቹም ማለትም እናትም
የባቤቷን መዳን ልጆች እና ሌላ ቤተ ዘመድም የአዳነን መዳን አምላካቸውን እየለመኑ በውስጣቸው ተስፋን ሰንቀው ነገን
እየናፈቁ የሚፈልጉት ነገር እንዲያሳካላቸው አምላካቸዉን ሲማጸኑና ሲጸልዩ ቀስ በቀስ በሂደትም የሚፈልጉት ነገር
ተሟልቶላቸው አባታቸው ከህመሙ ሙሉ በሙሉ ተፈወሰ፡፡

በዚህ ጊዜ የተወለደውን ልጅ “ጤናው” የሚል መጠሪያ ስም አወጡለት፡፡ “ጤናው” ማለት ከበሽታ መራቅ ጤና ማግኘት
መዳንን ወዘተ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ እናቱም አባትህ ከነበረበት በሽታ ተለቀቀ ተፈወሰ ዳነ ቤተሰቡም ጤና አደረ
በማለት ጤናው የሚል መጠሪያ ስም አወጣችለት፡፡

የጤናው ቤተሰቦች ስሙ የወጣበትን ምክንያት በተደጋገሚ ነግረውታል፡፡ ከዚያም መጀመሪያ ዘመናዊ ትምህርት ከመማሩ
በፊት የቆሎ ትምህርት ወይም መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እየተማረአደገ፡፡ በዚህ ምክንያት ስሙን ከመጽሀፍ ቅዱስ ታሪክ

14
ጋር በማያያዝ መቀየር ይፈልግ ነበር፡፡ ከዚያም ቤተሰቦቹን አማክሮ ከመጽሀፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር አያይዞ የስሙን ትርጉም
ለቤተሰቦቹ በማስረዳት ሳሙኤል በሚል ስም ቀይሮታል፡፡ ይህን ስም የመረጠበት ምክንያተ ፈጣሪው ለአባቱ መዳን
የጎደለውን አሟልቶ የተወለደውን አቃንቶ የጨለመውን ተስፋ አብርቶ ሁሉን ለማይሳነው አምላኩ የዋለለትንዉለታ
በማሰብ አባቴን ከሞት አትርፈህ በህይወት አኑረህ ቤተሰቦቼን ከጭንቀት ከሀዘን ከመከራ አውጥተህልናልና በማለት
ለአምላኩ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ሲል ሳሙኤል በሚል መጠሪያ ቀይሮታል፡፡ ሳሙኤል በመጽሀፍ ቅዱስ መጽሀፊ
ሳሙኤል ቀዳማይ (1፡20) “ሳሙኤል” ማለት በእግዚአብሔር የተሰማ ወይም እግዚአብሔር ሰማኝ ማረኝ አዳነኝ
ፈወሰኝ ማለት ነው፡፡

3.2 የማግኘት እና የማጣት መግለጫ ስሞች


ንብረት የማግኘት ፍላጎት የአብዛኛው ሰው ምኞት ነው፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ወላጆች ይህ ምኞት ሲሳካላቸው ከድህነት
ማጥ ወይም ወጥመድ ወጥተው ከብዙ አመት የሀብት መራቆት በኋላ ሀብት በማፍራት ላይ እያሉ ልጆች ከወለዱ ሀብት
በማፍራት ላይ መሆናቸውን ለመግለጽ ለልጆቻቸው የሀብት መግለጫ ስሞችን ሲየወጡና ሲቀይሩ እንመለከታለን፡፡
ስለዚህ ሀብት ማግኘታቸውን በኑሯቸው መሻሻላቸውን በቤት ውስጥ ሲቀይሩ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ሀብት
ማግኘታቸውን በኑሯቸወ መሻሻላቸውነ በቤት ውስጥ ደስታ መስፈኑን በልጆቻቸው ስም ምክንያት ይገለጻሉ፡፡

እነዚህን ሁኔታዎች ለመግለጽ የሚወጡ እና የተቀየሩ ስሞች ከተጠኝዎች ከእናት እና አባት እንዲሁም ከአካባቢው
ማህበረሰብ ቃለ መጠይቅ በማድረግ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት እንደሚከተለው የተለያዩ ስሞችን በመጥቀስ ቀጥሎ
በአስረጅዎች ተደግፎ ይቀርባል፡፡

3. ስንታየሁ

ስንታየሁ በጎ የሆነዉን እና መጥፎ የሆነውን ነገር ማየትን ያመለክታል፡፡ ይህ ስም ለወንድም ለሴትም ጾታ የሚውል ስም
ነው፡፡ በዚህ ጥናት ግን ጥቅም ላይ የዋለው ለሴት ነው፡፡ ይህ ስያሜ የተሰጣት ወላጆቿ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ
በየጊዜው የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሟቸው ቆይተው ማለትም የሀብት ችግር የጤና ችግር እንዲሁም የተመኙትን ሳያገኙ
በመቆየታቸው ለልጃቸው ስንታየሁ የሚል ስም አወጡላት፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ ልጅቷ ከተወለደች በኋላ ከህመማቸው
ተፈውሰው ያሳለፍትን የችግር የመከራ የስቃይ ውጣ ውረድ ወዘተ እያስታወሱ በስንቱ ስቃይና መከራ ተፈትነን ያንሁሉ
ነገር አሳልፈን ስንት መስዋትነትን ከፍለን እዚህ ደረጃ ደርስን ለማግኘት አበቃን ስለዚህ የመከራውንም ቀን አልፈን ለዚህ
ለደስታ ቀን ደረስን በህይወት ሲኖር የማይታይ ነገር የለም በማለት ለወለዷት ልጅ “ስንታየሁ” የሚል መጠሪያ ስም
አወጡላት፡፡

ስንታየሁ እናት እና አባቷ ቢሞቱም አካባቢዋነ ለቅቃ እባሏ ላይ እንደለመደች ቀረች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታገባ ሴት
ልዩ ክብር አላትና የወንድ እናት ወይም አማት ለልጇ ሚስት የሚሆን ስም ታወጣለች፡፡ ስለዚህ አማቷ “ዘመድ“ የሚል
ስም አወጣችላት፡፡ ዘመድ የሚለውም ስም ትርጉሙ ስጋዬ የቅርቤ የስጋ ክፋዬ ስጋዊ ዝምድና የሚል ሲሆን ከአሁን
ጀምሮ እና አባትሽም እኛ ነን አንችን እንደምራታችን ሳይሆን እንደ ልጆቻችን ነሽ የቃል ኪዳን ልጃችን ነሽ በማለት ስም
ወጥቶላታል፡፡ ከዚህ በኋላም በአካባቢዋ ማህበረሰብ ስንታየሁ ስም ቀርቶ ባሏም የባሏም ቤተሰቦች በሙሉ እንዲሁም
የአካባቢው ማህበረሰብ ዘመድ በሚለው ስም እየተጣራች ትገኛለች፡፡

15
4. ሀብቴ

ሀብቴ ከመወለዱ በፊት ቤተሰቦቹ መሬት የላቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ በረሀብ በድህነት በችግር ሲሰቃዩ ይኖሩ ነበር፡፡ ሀብቴ
ሲወለድ መሬት አገኙ ከዚህም በኋላ ሀብት አግኝተዉ ርሃብ ድህነት ችግር ጠፍቶ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን አሟልተው
የተመቻቸና ጥሩ ኑሮ መኖር ጀመሩ፡፡ ከዚህም የተነሳ አንተ እድለኛ ለምለም ልጅ ነህ ይህን መሬት እንድናገኝ ያደረገን
ያንተ እድል ነው በማለት ሀብቴ የሚል መጠሪያ ስም አወጡለት፡፡

ሀብቴ ማለት ትርጉሙ ንብረት፣ ስጦታ፣ ጌታ፣ ገንዘብ ሲሳይ ማለት ሲሆን የዚህ ስም መውጣት መሰረቱ ልጁ ሲወለድ
ሀብት በመገኘቱ የተሰየመ ወይም ስሙ የወጣ ሲሆን የተጠቀሙበትን ሀብት አገኘን ለማለት ነው፡፡

የደርግ መንግስት ተቀይሮ የኢህአዲግ መንግስት ቦታውን ሲይዝ አለፈልን አንድነት ጨቋኙ ቀረ ብለው የልጃቸውን ስመ
“ብርሃኑ” ወደ ሚል ቀየሩት፡፡ ስሙን ሲየወጡ መነሻ ወይም መሰረት ያደረጉት የልጃቸው ስም ከፖለቲካዊ ጉዳይ መሰረት
በማድረግ ነው፡፡ ብርሃኑ ማለት ደስታ ብስራት ከጨለማ ወደ ብርሀናዊ ህይወት ተሸጋገርን ነጻነት ሰፈነ በማለት ብርሃኑ
የሚል መጠሪያ ስም አወጡለት፡፡

5. ጥጋቡ

ጥጋቡ የሚለው ስም የወጣበት ምክንያት ከእሱ በፊት ሲወለዱ የነበሩት ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በግንቦትና በሰኔ ነበር፡፡
እነዚህ ወቅቶች ደግሞ እንደሚታወቀው የችግር ወራት ናቸው፡ ምክንየቱም የተዘመረው ያለቀበት የሚዘመረው
ያልደረሰበት ወቅት ከመሆኑም የተነሳ ነው፡፡ ጥጋቡ ግን የተወለደው በታህሳስ ወር ሲሆን ወራቱ የአዝመራ ወቅት የጥጋብ
ወቅት ሰብል የሚደርስትበና የመኸር ወቅት ርሃብ የሌለበት የደስታ ወቅት በመሆኑ በዚህ ወቅት የወለዱትን ልጅ “ጥጋቡ”
የሚል ስም አወጡለት፡፡

ጥጋቡ ለቤተሰቦቹ እና ለጓደኞቹ በጣም ቁም ነገረኛ ልጅ ነው፡፡ ከጎረቤት ልጆች ከወንዶችም ሆነ ከሴቶች ጋር በጣም
የሚቀራረብ እና ከስራ ሰአትና ከትምህርት ውጭ ያለውን ትርፍ ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር ያሳልፍ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን
ከሆነች ልጅ ጋር በጠዋት ተነስተው ወደ ትምህርት ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ልጅትዋ ትወደው ስለነበር የፍቅር ጥያቄ
አቀረበችለት “ጥጋቡ” ያቀረበችለትን ጥያቄ ስላልተስማማበት በጎድጓዳ ቦታ ላይ ሲደርሱ ጮሀ ደፈረኝ በማለት
ታሲዘዋች፡፡

በዚያም ነገሩ ወደ ፍርድ ቤት አመራ፡፡ በዚህ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲጠየቅ ለኔ ድርጊቱ አልፈጸምኩትም ነገሩ በህክምና
ይረጋገጥ ብሎ ክብረ ንጽህናዋ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በህክምና ሲረጋገጥ ምንም ሳይፈጠር በመገኘቱ እና ውሸት በመሆኑ
እናት አባቶቹ በነገሩ በመደነቅ አባቱ ቄስ ስለሆነ ከመጽኀፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር በማያያዝ “ዮሴፍ” የሚል መጠሪያ
አወጣለት፡፡

16
3.3 የሀዘን መግለጫ ስሞች
ሰዎች በህይወት ከሚየጋጥሟቸው በርካታ ገጠመኞች አንዱ ሀዘን ነው፡፡ ይህ ስሜትም በሰዎች መንፈስ ውስጥ
እንዲፈጠር የተለያዩ መክንያቶች ይኖራሉ፡፡ በሚያወጡላቸው የሀዘን ስሜት ለመግለጽ ከሚጠቀሟቸው አንዱ
ለሚወልዷቸው ህጻናት በሚያወጡላቸው የመጠሪያ ስሞች አማካኝነት ነው፡፡ የሀዘን መግለጫ ስሞች በህብረተሰቡ
የስም አወጣጥ ሂደት አንድ አይነት ስም ለማውጠት የሚከተሉት መነሻ ነው፡፡ ስሞቹም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ
የደረሰውን የሀዘን ሰሜት መግለጽ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ የሀዘን መግለጫ የሆኑ ስሞችን አወጣጥና ቅየራ በአካባቢው
ሰዎች፣ ከታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎች ከተጠኝዎች ቤተሰብ በመጠየቅ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ
እንደሚከተለው ማሰረጃ በማስደገፍ ትንታኔው ይቀርባል፡፡

6. ምትኩ

አባቱ በህመም ምክንያት ሲንገላታ እና ሲሰቃይ ኖሮ በአጋጣሚ ልጁ በተወለደ በመንፈቁ ወይም በስድስት ወሩ ከዚህ
አለም በሞት ተለየ፡፡ ከሱ በፊት ለእናቱና ለአባቱ ሌላ ልጅ የለም ምትኩ የበኩር ወይም የመጀመሪያ ልጃቸው ነው፡፡
በዚህም ምክንየት እናቱ ከአሁን በኋላ ሀላፊነት ተቀብለህ አባትህ የሚያደርገውን ሁሉ የምታደርግ አንተ ነህ አለኝ ታየ
ጉልበቴ የአባትህን ምትክ ነህ በማለት ምትኩ የሚል ለልጁ ስም አወጣችለት፡፡

ምትኩ ከመወለዱ ጀምሮ በበሽታ የሚሰቃይ ጸባዩ አስቸጋሪ ከሰው የማይስማማ ልጅ ስለሆነበት አናቱም በህመሙና
በጸባዩ ምክንያት በየታቦቱ ስለት ትሳል ነበር፡፡ እናቱም ምኞቷ ተስፋዋ ፍላጎቷ ሀሳቧ ተሟልቶላት ልጇ ከሚሰቃይበት
ህመም ተፈውሶ ጤነኛ ልጅ ስለሆነላት ታመሩ የሚል ስም እናቱ ቀይራ አወጣችለት፡፡ እናቱም አንዱን ልጇን የአባቱን
ምትክ ማረልኝ ጸሎቴን ሰማኝ ተስፋየ ለመለመ የፈጣሪን ታምር በአይኔ አየሁ በማለት ታምሩ የሚል ስም አወጣችለት፡፡
ስለዚህ ፈጣሪ ክዶኛል አንድ ልጄን ከህመሙ ፈውሶ ጤነኛ ሰው አድርጎልኛል፡፡ ስለዚህ ታምሩን በአይኔ አይቻለሁ በማለት
ታምሩ የሚል ስም አወጣችለት፡፡

7. ሰውነት

የሰውነት አባት መብራቱ ይባላል አቶ መብራቱ ሚስት አግበቶ እየኖረ እያለ ሚስቱ በአጋጣሚ በድንገትና ህመም
ምክንያት ከዚህ አለም በሞት ትለይበታለች፡፡ ከሞተች በኋላ ሌላ ሚስት አግብቶ እየኖረ ሳለ ሴት ልጅ ወለደ፡፡
የሞተችበትን ሚስት በጣም ይወዳት ስለነበር የሞተች ሚስቱን ማስታወሻ ነሽ በሌላ በኩል የእሷ ምትክ ነሽ በማለት
ሰውነት የሚል ስም አወጣላት፡፡ ሰውነት ማለት ትርጉሙ ስጋነፍስ መሆን ሰው አገኘሁ አካል ማለት ነው፡፡

ሰውነት እያደገች ስትሄድ ሰውነት የተባለችዉ የእንጀራ እናቷን ስም በመውረስ እንደሆነ በማወቋና እንዲሁም የሰውነት
ቤተሰቦች የልጃችን ስም ለምን ታነሳለህ ሞታም አታርፍ ወይ እኛን ሁል ጊዜ በሀዘን ቅስማችን እንዲሰበር ታደርጋለህ
በማለት ቅሬታ ስለ ተፈጠረ የልጁን ስም ማስረሻ ብሎ ቀየረው፡፡ ማስረሻ ማለት ከእንግዲህ ያለፈውን እንድረሳ
እንዳያስታሰዉስ በማለት ማስረሻ የሚል ስም ቀይሮ አወጣላት፡፡

17
3.4 መልክን መሰረት በማድረግ የወጡና የተቀየሩ ስሞች
የውበት መግለጫ ስሞች ለልጆቻው እንደሚያወጡላቸው መነሻ የሚየደርጓቸው ጉዳዮች ህጻናቱ ይዘውት የተወለዱትን
ማራኪ አካላዊ ቁመና የደም ግባት የመሳሰሉትን የሚገልጽ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህም ሁኔታዎች መሰረት በማድረግ
በህብረተሰቡ ውስጥ ከሌላው ነገር የተሻሉና የሚደነቁ የተለያዩ የአድናቆት መግለጫ ስሞች ለልጆቻቸው መጠሪያ
በመስጠት የልጃችን ተፈጥሮአዊ ውበት ለመግለጽ የሚያስችሉ ስሞችን ያወጡላቸዋል፡፡ ውበትን መሰረት አድርገው
የሚወጡ ስሞች አወጣጥ ከአባባቢው ከታሪክ አዋቂ አባቶች ከተጠኚዎች እና ከተጠኝች ቤተሰብ በመየጠቅ በተሰበሰቡ
ወይም በተገኙ መረጃ መሰረት እደደሚከተለው ይተነተናል፡፡

8. ካአንቺ ወዲያ

ከአንቺ ወዲያ ለቤተሰቦቿ አምስተኛ ልጅ ናት፡፡ ከሷ በፊት የተወለዱት ልጆች በመልካቸውቆንጆ አይደሉም፡፡ በሰፈሯ
ካሉት ጓደኞቿም በመልክ የምታምር ቆንጆ የሆነች ውብ ናት፡፡ከዚህም የተነሳ ሰዎች ከአንቺ የበለጠ ቆንጆ በዚህ ሰፈር
የለም ከአሁን ቀደምም አልተወለደም ብለው ከአንቺ ወዲያ የሚል ስም አወጡላት፡፡

ከአንቺ ወድያ እናቷ በልጅነቷ ስለሞተችባትና በቤት ውስጥ ያሉት ሁሉም ልጆች ከእሷ በላይ እና እራሳቸውን የቻሉ
ናቸው፡፡ቤት ውስጥም ያሉትን ትናንሽ ልጆች፤አባቷን እንዲሁም እንደ አጠቃላይ ትዳሩን የምትመራው እሷ ናት፡፡

በዚህም የተነሳ አባቷ አንቺን ባላገኝ ቤቴም ይፈታ ነበር እኔም በረሀብ እና በጥም እሰቃይ ነበር በማለት ፍትፍቴየሚል
መጠሪያ ስም ቀይሮ አወጣላት፡፡ ፍትፍቴ ማለት አጉራሽ፣ መጋቢዬ፣ አለኝታዬ፣ ጥጋቤ፣ ወዘተ የሚል ትርጉም
አለው፡፡ ስለዚህ ለእኔም ካንቺ የበለጠ የሚንከባከበኝ የውስጤን ስሜት የሚያዳምጥልኝ፣ የሚረዳልኝ፣
ረሀቤን የሚቆርጥልኝ፣ ጥሜን የሚያስታግስልኝ፣ የለም በማለት ፍትፍቴ የሚል መጠሪያ ስም አባቷ አውጥቶላት
በዚያ ስም እየተጠራች ትኖራለች፡፡

9. ጀሚላ

ይህ ስም በአብዛኛው በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ለሴቶች የተለመደ ስም ነው፡፡ ጀሚላ የሚለው ስምም
ትርጉሙ በቅዱስ ቁርዓን ቆንጆ በጣም የምታምር፣ ውብ የሚል ትርጓሜ ሲኖረው ከዚህም ጋር በማያያዝ ልጅቱን ከቤተ
ዘመድ ቆንጆ የምታምር እና ውብ ስለሆነች ወላጆቿም ከዚህ አንጻር አያይዘው “ጀሚላ” የሚል የመጠሪያ ስም
አወጡላት፡፡

ጀሚላ በመንፈሳዊ ህይወቷ በጣም ጠንካራ ሆና መንፈሳዊ ትምህርት እየተከታታለች ያደገች ናት፡፡ የአለም ኑሮ ሀጥያት
የበዛባት፣ አስቀያሚ፣ ለስጋ እንጂ ለነፍስ የማይመች ብላ ከዚህ አለም ራሷን አግልላ በመንፈሳዊ ቦታዎች የምትኖር ሴት
ስለሆነች “ፋጡማ” ብላ ቀየረች፡፡ “ፋጡማ” ያለችበት ምክንያት ራሷን አርቃና አግልላ የምትኖር ሴት ማለት ሲሆን
“ፋጡማ” ትርጉሙ አለም በቃኝ ብላ በሃይማኖታዊ ቦታዎች የምትኖር ብቁ ሴት ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፋጡማ
የሚለው ስም ከዚህ ታሪክ ጋር አያይዛ አውጥታ በዚህ ስም እየተጠራች ትኖራለች፡፡

18
3.5 ታሪክን መሰረት በማድረግ የሚወጡ ስሞች
ሰዎች ለልጆቻቸው ስም ለማውጣት መነሻ ምክንያት ከሚያደርጉት ነገር ውስጥ አንዱ ታሪክ ነው፡፡ አንድ ሰው በህይወት
ዘመኑ ሲኖር ሌሎችን ማህበረሰቦች የሚያጋጥሟቸው ክስተቶች በአንዳንድ ማህበረሰብ እየተውት የሚያልፍ አሻር
ወይም ታሪክ አለ፡፡ ይህም የጀግንነት፣ የወኔ፣ የሽንፈት፣ የደስታ፣ የመከራ ወዘተ ባህርያት ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ሊኖሩ
ይችላሉ፡፡

ወላጆችም የሚወልዷቸውን ልጆች ከእነዚህ ታሪኮች ጋር በማያያዝ ለልጆቻቸው ስም ያወጣሉ፡፡ እነዚህም ሰዎች
ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖራል፡፡ የስሞች ይዘት መልዕክትም እንደየወጡበት ምክንያት የተለያየ
ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ባለፉት ጊዜያት የተከሰቱትን ነገሮች አሁን ላይ ሆኖ ማስታወስ እንዲቻል እነዚህን ታሪክ መሰረት
አድርገው የሚወጡ ስሞች ታሪክን ለማስታወስ ይጠቀሳሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት በቃለ መጠይቅ አማካኝነት
ከአካባቢው ታሪክ አዋቂ ከሆኑ አባቶች፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከተጠኝዎች እና ከተጠኚዎች ቤተሰብ በተገኘው
መረጃ መሰረት በማስረጃ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

10. ባንች ጊዜ

ሰዎች በህይወት ዘመናቸው የተለያዩ ችግሮችና ውጣ ውረዶች እንግልት ይደርስባቸዋል፡፡ የባንች ጊዜ ቤተሰቦች ግፍና
መከራ ያጋጥማቸው ነበር፡፡ አባቷ ከበደ ይባላሉ፡፡ የከበደ ታላቅ ወንድሙ የእንጀራ ልጅ ነበረች፡፡ የእነ ከበደ ደግሞ ሽፍታ
ሆኖ የሚኖር ነበር፡፡ ለመንግስት እጅህን ስጥና ለህግ ተገዢ ሁን ምንም አትደረግ በማለት የሚቀርቡት ሰዎች አታለው
እጁን ለህግ እንዲሰጥ ካደረጉ በኋላ ክስ ተመሰረተበት፡፡

ይህ ሽፍታ የሆነው ሰው የከበደን የወንድሙን የእንጀራ ልጅ ሳትፈልግ አገባታለሁ እያለ ሁል ጊዜ ያሰቃያቸዋል፡፡ ሁል ጊዜ


ማታ ማታ እየመጣ ጨለማን ተገን አድርጎ በመሳሪያ እያስፈራራ ያስቸግራቸዋል፡፡ ከበደና በላቸው አንድ ላይ ቡና ሲጠጡ
ይመጣና እንደተለመደው አሰቃያለሁ ልጅቷን ይዤ እሄዳለሁ ሲል ሰክሮ ስለነበረ መሳሪያውን በመቀማት የእህታቸውን
ልጅ በራሱ መሳሪያ ገደሉት፡፡ በዚህ የተነሳ ታስረው ትዳራቸውም ተበትኖ ከሀገር ለቀው ለብዙ እንግልት ተዳረጉ፡፡ በዚህ
በችግር ወቅት የተወለደችውን ልጅ ከበደ የሚባለው ሰው ለልጁ “ባንች ጊዜ ከበደ” የሚል መጠሪያ ስም አወጣላት፡፡

“በአንቺ ጊዜ ከበደ” የሚለው ስም ትርጉም የሚሰጠው ከአባቷ ስም ጋር በአንድ ላይ ሲተረጎም ነው፡፡ ትርጉሙም ብዙ
ካሳለፉ የመከራ፣ የጭንቀት፣ የእንግልት ዘመን የአሁኑ ይባስ እጃችን በእጃችን ቆርጠን መቼም የማያልፍ መከራ እና ፀፀት
በማለት “በአንቺ ጊዜ ከበደ” የሚል የመጠሪያ ስም አወጣላት፡፡

በአንቺ ጊዜ ቤተሰቦቿ ከነበረባቸው የጭንቀት፣ የመከራ ዘመን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ያንን ነገር ሁሉ አልፈው አባቷም
ከታሰረበት ተፈቶ ከሟች ቤተሰቦች ጋርም ታርቀው በሰላም መኖር ሲጀምሩ ለልጃቸው ማለትም “ለባንቺ ጊዜ ከበደ”
ለተባለችው ልጅ “የምስራች” የሚል ስም ቀይሮ አወጣላት፡፡ መጥፎ የመከራ ጊዜ አልፎ ብርሃን ሆነ፣ ደስታ ሆነ ብስራት
ሆነ በማለት “ባንቺጊዜ” የሚለውን ስም “የምስራች ከበደ” የሚል ስም ቀይረው አወጡላት፡፡

19
11. መስታወት

መስታወት የተወለደችው የኢህደአዴግ መንግስትና የደርግ መንግስት ጦርነት ገጥመው ደርግ ተሸንፎ የኢህአዴግ
መንግስት ቦታውን በያዘበት ዘመን ነው፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ ደርግ ለቆ ኢህአዴግ ሲገባ ለተወለደችው ልጃቸው
የወቅቱን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ እና የወደፊቱ መንግስት ያላቸውን ግምት በማስመልከት “መስታወት” የሚል
የመጠሪያ ስም አወጡላት፡፡ ይህም ስም ትርጉሙ ብርሃን፣ ሁሉን አኩል የሚያሳይ፣ የማያዳላ፣ ጉድፍን በግልጽ የሚያሳይ
ወዘተ የሚል ትርጉም ሲሰጡት የሚመጣው መንግስትም እንደዚህ ይሆናል ብለው አወጡላት፡፡

መስታወት በተወለደች በ 10 አመቷ በጣም ጽኑ የሆነ የኩላሊት በሽታ አመማት አባቷም ሞቶ ነበረ፡፡ እናቷ አንድ
ወንድምና አንድ እህት ብቻ ነው ያላት ለመስታወት ማሳከሚያ የሚሆን በቂ ገንዘብ የላቸውም ነበር፡፡ ለማሳከሚያ ብዙ
ብር የሚፈጅ በመሆኑ በዚህ ምክንያት ብሩን ስላላገኙ መታከም አልቻለችም፡፡ ከዚህም እናቷ መስታወትን ይዘው ፀበል
ቦታ በመሄድ በየቦታው ገድለኛ በሚባለው ፀበል ሁሉ ይዘው እየዞሩ አባቶች ጸሎት እየደገሙ ፀበልን እምነት እየቀላቀሉ
እየሰጧት እሱን እየጠጣች በመስቀል እየተሻሸች በስንት ስቃይና መከራ ከህመሟ ዳነች፡፡

ከዚህም የተነሳ የቤተክርስቲያን አባቶች “በፀሎት” የሚል ስም አወጡላት፡፡ በጸሎት ማለት ከብዙ ጸሎትና ልመና ስቃይ
የፈጣሪ አዛኝነት የሚገለጽበት የፈጣሪ ጸጋና በረከት በሱ ፍቃድ የማይሆን የለም በማለት የፈጣሪዋን ምስጋናና ክብር
ከሚገልጽ ትርጉም አያይዘው “መስታወት” የሚለውን ስም በጸሎት ብለው የቤተክርስቲያን አባቶች ቀይረው አወጡላት
በዚህም ስም እየተጠራች ትኖራለች፡፡

3.6 መመኪያነትን መሰረት በማድረግ የወጡ ስሞች


መመኪያ መግለጫ ስሞችን ለልጆቻው የሚሰጦቸው አንድ መመኪያና አለኝታ እንዲሆናቸው በማሰብ አንዳንድ ሰዎች
ከሚኖሩበት አካባቢ የቤተሰብ ወይም የወገን እጥረት ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም ወላጆች ለሚወልዷቸው ልጆች የተለያዩ
ስሞችን ያወጣሉ፡፡ አንድ ሰው ልጅ ሲወልድ ጋሻ፣ መከታ፣ አለኝታ እና ጥላ ይሆነኛል በሚል መጠሪያ ስሞችን
ይሰይሙላቸዋል፡፡ ይህ ሲባል በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ወንድ ልጅ ጋሻ፣ መከታ፣ ትከሻ፣ ከለላ፣ ወንድም፣ አለኝታ ወዘተ
ይሆናል ብለው የመመኪያ ስም ያወጣሉ፡፡ ወላጆች የመመኪያነት መግለጫ ስሞችን የሚያወጡላቸው ለእነሱ ብሶትና
በደል መግለጫ ብቻ አይደለም፡፡ ከእነዚህም ከተጨማሪ ልጆች በደም በሚመሳሰሉት በስጋ በሚዛመዱት ዘመድ
አዝማዳቸው ሁሉ መከታ መሆናቸው ለመግለጽ ጭምር ነው፡፡ ይህ የአለኝታነት ስሜት ምኞት የሚመሰረተው በተለያዩ
ዘርፎች ዙሪያ ነው፡፡ ይኸውም ልጆች ሀብት አግኝተው የበላይ በመሆናው ባላቸው ጉልበት ልቆ በመገኘት ዘመድ የሚረዱ
የቤተሰብ አለኝታ እነዲሆኑ የመጠሪያ ስሞችን ያወጣሉ፡፡ ከዚህም ቀጥሎ የቀረቡትን ስሞች ይህን ስሜት መግለጫነት
ለሚወጡ ስሞች ምሳሌ ይቀርባሉ፡፡ በቃለ መጠይቅ ከታሪክ አዋቂ አባቶች፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከተጠኝዎች እና
ከተጠኚዎች ቤተሰብ በተሰበሰቡ መረጃዎች አማካኝነት መረጃ በማስደገፍ እነደሚከተለው ይቀርባል፡፡

12. ቁምላቸው

20
ቁምላቸው የተባለበት ምክንያት ወላጆች ሴት ልጅ እየወለዱ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ቁምላቸውን ወንድ ልጅ ስለወለዱ
መከታችን፣ መመኪያችን፣ አለኝታችን ነህ በማለት “ቁምላቸው” የሚል መጠሪያ ስም አወጡለት፡፡ ስለዚህ ለእህቶቹም
ሆነ ለእናቱ ለአባቱ በቤት ውስጥ ሌላ ወንድ ልጅ ስለሌለ መመኪያችን፣ አለኝታችን፣ ሁሉን ነገራችን ነህ በማለት
“ቁምላቸው” የሚል መጠሪያ ስም አወጡለት፡፡

“ቁምላቸው” ቁም ነገር የሌለው፣ አጭበርባሪ፣ ከንቱ መና ስለሆነ እንኳን ለልጆችን መከታ፣ አለኝታ፣ ጋሻ ሊሆን ቀርቶ
እኛን የሚያታልል፣ ከንቱ፣ የሚያሳድድ፣ አረመኔ፣ ልጅ ስለሆነባቸው “ደለለኝ” የሚል ስም ቀየሩለት፡፡ ቤተሰቦቹም
ፈጣሪን ምን በድለነው ነው በአንድ ልጃችን አለኝታችን፣ መከታችን፣ ጋሻችን፣ ጥላችን ብለን ያሰብነው አሳይቶ የነሳን
ያታለለን ወይም ባይሰጠን ለምን አሳይቶ ነሳን በማለት “ደለለኝ” የሚል ስም አወጡለት፡፡

13. አንጓች

“አንጓች” ስትወለድ ሴት ልጅ ቤት ውስጥ የለም ነበር፡፡ የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ እሷ ብቻ ነበረች የመጀመሪያ ልጅ


በመሆኗ ሌሎችን እስከምንወልድ ድረስ ሲጠማን አጠጫችን፣ ሲበርደን አልባሻችን፣ ሲከፋን አለኝታችን ናት በማለት
“አንጓች” የሚል መጠሪያ ስም አወጡላት፡፡

“አንጓች” ማለት ወዳጄ ነሽ፣ አጉራሼ፣ መጋቢዬ ወዘተ የሚል ስም ትርጉም ሰጥተዋታል፡፡ አንጓች ከልጅነቷ ጀምሮ አባቷ
ቃልኪዳን ይላት ነበር፡፡ ቃልኪዳን ያለበት ምክንያት ባለቤቱ በጣም ታማኝና ለባለቤቷ ያላት ክብርና አመለካከት ለየት ያለ
ስለነበር ማህተቤ፣ አለኝታዬ፣ ቃሌን አክባሪዬ፣ ለቃልሽ ታማኝ በማለት እሱም ለሚስቱ ያለው ከበሬታ፣ ፍቅር ለመግለጽ
ቃልኪዳን የሚል መጠሪያ ስም ለልጁ አወጣላት፡፡

ቃልኪዳን ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ሰዎች ሲስማሙ ነገሩን ለማጽናት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ይገባሉ፡፡
ሌላው ደግሞ ቃልኪዳን የተባለችበት ምክንያት 12 ኛ ክፍል ተማሪ እያለች በህመም ምክንያት ትምህርቷን አቋርጣለች፡፡
አንድ አመት በየሀኪም ቤቱና በየጸበሉ ስትዞር ከቆየች በኋላ ተሸሏት ትምህርቷን ቀጠለች፡፡ ከዚያም ለዩኑቨርሲቲ
መግቢያ ፈተና ስትመዘገብ ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ ስሟን “ቃልኪዳን” ብላ ቀየረች፡፡ ቃልኪዳን
ያለችበት ምክንያት አንደኛ ከአባቷ ጉዳይ ጋር አያይዞ፤ ሁለተኛ ለፈጣሪ ያላትን ፍቅር ለመግለጽ ማለትም ፈጣሪ
በገባልኝ ቃልኪዳን መሰረት የትም አይጥለንም በእኛ በሰዎች ልጀች እና በፈጣሪ መካከል ያለውን ዘላለማዊ ቃልኪዳን
ነው፡፡ ይኸውም እኔንም አልረሳኝም፡፡ አዳነኝ ያሰብኩት ተሳካልኝ ለፈጣሪ ክብር ምስጋና ይግባው ከአሁን ጀምሮ ለእሱ
ታማኝ ትዕዛዙን አክባሪ፣ ለህጉ ተገዥ ሆኜ ለመኖር በፈጣሪ ስም ቃል እገባለሁ በማለት “አንጓች” የሚለው ስም ተቀይሮ
ቃልኪዳን ብላ ብሄራዊ ፈተና ላይ ቀይራዋለች፡፡

3.7 ፀባይን ወይም ባህሪን መሰረት ያደረጉ ስሞች


ወላጆች ልጆቻቸውን ከወለዱ ጊዜ አንስቶ ለልጆቻቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ደህንነታቸውን በአትኩሮት መከታታል
የዘወትር ስራቸው ነው፡፡ የሚያደርጉትን ክትትል የህጻናትን ጸባይ ምን እንደሚመስል መገንዘብ ይችላሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ
ከልጆቻው የተገነዘቡት ጸባይን የሚገልጽ መጠሪያዎችን ያወጡላቸዋል፡፡ ህጻናቱ የሚያሳዩትን ሰናይ ስነ ምግባር መሰረት
በማድረግ ይህንን ሁኔታ የሚገልጽ መጠሪያዎች ያወጡላቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ህጻናት የሚያሳዩት የእልህ፣
የበጥባጭነት፣ የረብሻ ወዘተ ጸባይ በማስመልከት ልጆች ወደፊት ማንም የማይደፍራቸው ሀይለኛ የሁሉም የበላይ ነን

21
የሚሉ እና አስቸጋሪ ጸባይ የሚኖራቸው መሆኑን የሚገልጽ መጠሪያዎች ያወጡላቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አንዱ ህጻን
ተወልዶ እስኪያድግ ድረስ የተለያዩ ጸባይ ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ ባህሪ ያላቸውና ጥሩ ባህሪ የሌላቸው
ልጆችን በመገንዘብ እንደየ ባህርያቸው ስም ያወጡላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ህጻን ሲወለድ በቤተሰብ ውስጥ
የነበረውን ግንኑነት አስመልክቶ ለተወለደው ህጻን የጸባይ መግለጫ ስሞችን ያወጡላቸዋል፡፡ ጸባዩን ለመግለጽ ሲሉ
ሰዎች ለልጆቻቸው ባህሪ የሚያመለክት ስም ማውጣትና መቀየር የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህ ጸባይን ወይም ባህሪን
አመልካች ስለሆኑ ሰዎች ከአካባቢው ታሪክ አዋቂ አባቶች፣ ከአካባቢ ማህበረሰብ፣ ከወላጆች እና ከተጠኚዎች በቃለ
መጠይቅ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት በአስረጂ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

14. ትህትና

ልጅቱ በፀባይዋ ምስኪን ሰው አክባሪ የዋህ፣ ደግ፣ ትሁት፣ ሰው አክባሪ ለሰው ጥሩ አሳቢ የሆነች ልጅ ናት፡፡ ለቤተሰቦቿም
ሆነ ለጎረቤት ታዛዥ ራሷን ዝቅ የምታደርግ ከቤት ውስጥ ልጆችም ሆነ ከጎረቤት ልጆች ጋር በፍቅር የምትኖር ስለሆነች
“ትህትና” የሚል የመጠሪያ ስም ቤተሰቦቿ አወጡላት ስሟ የወጣላት ትንሽ ከፍ ብላ ነፍስ ማወቅ ስትጀምር ነው፡፡
ትህትና ቸር፣ ሰው አክባሪ፣ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ፣ ፀባያም ከሁሉ ስምሙ፣ አስተማሪ ረጋ የሚል ትርጉም አለው፡፡

ስለዚህ ፀባይዋ የዋህ ከመሆኑን ሰው አክባሪ አንገቷን የደፋች ከመሆኗ የተነሳ “ትህትና” የሚል ስም አውጥተውላታል፡፡
ትህትና እናቷ በልጅነት እድሜ ሞተችባት፡፡ ትህትና ከመወለዷ በፊት እናቷ በህመም ትሰቃይ ነበር፡፡ ትህትና በተወለደች
በ 8 አመቷ እናቷ በነበረባት ህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት ተለየች፡፡ እናቷ ጥላት ስለሞተች ልጅቷ ተጎሳቁላ፣
የሚንከባከባት ሳይኖር እንደምንም ሆና እየተሰቃየች አደገች፡፡ ከዚህም የተነሳ አባቷም ያ ሁሉ እንከብካቤ ቀርቶ ያች
አለም ለእኔም ሆነ ለአንቺ ጨለማ ከንቱ ሆነችብን በማለት “ቀረ አለም” የሚል ስም አወጣላት፡፡ “ቀረ አለም”
አለማችንን ተነጠቅን ከእንግዲህ ደስታ የለም ላትመለስ በዚህ አለም ጥላን ጠፋች፣ ከእንግዲህ ያለው ዘመን የመከራ ፣
የስቃይ፣ የሲኦል ሆነ የሚል ትርጉም ሲኖረው እኛም እንግዲህ በምድር ላይ ሆነን ጥሩ ደስታ የለም ደስታችን ላይመለስ
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተነጥቀናል በማለት “ቀረ አለም” የሚል መጠሪያ ስም አባቷ ቀይሮ አውጥቶላታል፡፡

3.8 የችግር መግለጫ ስሞች


የችግር መግለጫ ስሞች ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ደረጃ ያጋጠሙ ችግሮችን ይገልጻሉ፡፡ ግለሰባዊ ችግር ገላጭነታቸው
ሰዎች እንደሚያጋጥማቸው ችግሮች የተለያዩ ገጽታዎች ያሏቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ህጻናት ሲወለዱ እናቶች
ምጥ ጸንቶባቸው ስቃይ በዝቶባቸው ከሆነ እና ከብዙ ህመምና ስቃይ በኋላ በሰላም ከተገላለገለች ለሚወልዱት ህጻን
ችግር ገጥሟቸው እንደነበር የሚገልጽ መጠሪያ ያወጣሉ፡፡ እንዲሁም ህጻናት ከተወለዱ አንሰቶ በተለያዩ በሽታዎች
በተደጋጋሚ በመታመም በበሽታ የሚሰቃዩ ከሆነ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይድኑ ከሆነ የገጠማቸውን ችግር ለመግለጽ
የችግር መግለጫ ስሞችን ያወጡላቸዋል፡፡

22
የችግር መግለጫ ስሞችም እንደየግለሰቡ ችግር ገላጭነታቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ በመላው ማህበረሰብ ላይ
የደረሰባቸውን ችግር፣ ውድቀት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ረሃብና ድርቅ፣ ሰው ሰራሽ የሆኑ ጦርነት የመሳሰሉትን ማህበራዊ
ችግሮች ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም በመቀጠል የችግር መግለጫ ስለሆኑ ስሞች ከተጠኚዎች ቤተሰብ፣ ከአካባቢው ታሪክ አዋቂ
አባቶች ከአካባቢ ማህበረሰብ በቃለ መጠይቅ በተገኘው መረጃ መሰረት ማስረጃ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

15. ቢኒያም

የቢኒያም እናት ምጥ ይዟት በጨነቃት ጊዜ አዋላጅቱ አይዞሽ አትፍሪ ወንድ ልጅ ነው የወለድሽው አለቻት፡፡ እሷም
ጭንቁ በዝቶባት ስለነበር ቦኒኦኒ አለችው፡፡ ይህም ማለት የሀዘኔን፣ የጭንቀቴ፣ የመከራዬ ልጅ ማለት ነው፡፡ ወዲያው
እንደተገላገለች እናቱ አረፈች፡፡ አባቱም ቢኒያምን ያለ እናት ብቻውን ተሰቃይቶ አሳደገው፡፡ ልጁም አድጎ ለትምህርት
ሲደርስ ት/ቤት ገብቶ እየተማረ አደገ፡፡ ቢኒያም ያለ እናት ያደገ ሲሆን እንደ አባትም እንደ እናትም ሆኖ ያሳደገው አባቱ
ብቻ ነው፡፡ ልጁም ምነው ባልተፈጠርኩ ለእናቴ መሞት ምክንያት እኔ ነኝ የአባቴም መከራና ስቃይ እኔ ነኝ በማለት
ሁሌም በሀዘን በትካዜ ይኖር ነበር፡፡

ቢኒያም ስሙን የቀየረበት ምክንያት የ 8 ኛ ክፍል ተማሪ እያለ አባቱ በነበረበት ህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት
ተለየበት፡፡ የቢኒያም እናቱ በሱ ውልደት ምክንያት የተነሳ ሞታለች፡፡ እህትም ወንድምም የለውም፡፡ የብቸኝነት ኑሮ
አሰቃየው በዚህ ጭንቀት መከራ እንግልት የተነሳ ስሙን “ሰውመሆን” በማለት ቀየረው፡፡ ሰውመሆን ያለበት ምክንያት
መጀመሪያ በሱ የተነሳ እናቱ ህይወቷን አጣች በመቀጠል አባቱም እሱን በማሳደግ ደፋ ቀና ሲል ኖሮ በመሃል ሞተ፡፡ ችግሩ
ሳያልፍ እየተሰቃየ በሀዘን፣ በመከራ፣ በጭንቀት ሲሰቃይ እንደኖረ ሞተ፡፡ እሱም ያለ እናት፣ ያለ አባት፣ ያለ እህት፣ ያለ
ወንድም ብቻውን ስለቀረ ፈጣሪን ምን በድየው ነው እኔን በህይወቴ በእንዲህ ያለ ፈተና የሚያሰቃየኝ እኔ ምን አይነት
ፍጡር ነኝ ከንቱ የሆንኩ ሰው ለቤተሰቦቼ መሞት ምክንያት የሆንኩ ሰው በማለት ስሙን “ሰውመሆን” ብሎ ቀየረው፡፡

16. አበዛ

“አበዛ” በሚወለድበት ጊዜ እናቱ ሶስት ቀን አምጣ ነው የወለደችው፡፡ አበዛ ያለችበት ምክንያት ምነው ፈጣሪ ጣሬን፣
መከራዬን፣ እንግልቴን፣ ስቃዬን፣ ፈተነዬን አበዛህብኝ ምን አስቀይሜህ ነው በማለት የልጇን ስም “አበዛ” የሚል
የመጠሪያ ስም አወጣችለት፡፡

አበዛ ይህ ሁሉ መከራ፣ ስጋት፣ ስቃይ አልፎ ከህመሙ ተፈውሶ ሰላማዊ፣ ጤነኛ፣ በጎ አዳሪ ሰው ሆነ፡፡ ከዚህም የተነሳ
እናቱ “በጸጋው” የሚል መጠሪያ ስም አወጣችለት፡፡ በጸጋው ማለት ትርጉሙ በቸርነቱ፣ በምህረቱ፣ በሀዘኔታው፣ በበጎነቱ
በችሎታው ምንም የማይሳነው እግዚአብሔር በቃልኪዳኑ፣ በጸጋው ድህነት ምህረት አዘዘልን ማረን በማለት “በጸጋው”
የሚል ስም ቀይራ አወጣችለት፡፡

23
በአጠቃላይ የመጀመሪያው እና የተቀየሩ ስሞች ትርጉም

ተ.ቁ የመጀመሪየው ስም የስሙ ትርጉም የተቀየረው ስም የስሙ ትርጉም

1 ያሳብነህ ሀሳብ፣ ስጋት ኢዮብ ታጋሽ፣ ብዙ ፈተናዎች ያለፈ


2 ጤናው ዳነ፣ ተፈወሰ ሳሙኤል ሰማኝ፣ አዳነኝ
3 ስንታየሁ መከራና ደስታ ማየት ዘመድ የቅርብ ሰው
4 ሀብቴ ንብረት፣ ኢኮኖሚ፣ ሲሳይ ብርሃኑ ብስራት፣ ደስታ
5 ጥጋቡ ማግኘትን፣ ከችግር መላቀቅን ዮሴፍ አገልጋይ፣ የእግዚአብሔር ሰው
6 ምትኩ ተተኪ፣ ተረካቢ ታምሩ የሚያስደስት
7 ሰውነት ስጋና ነፍስ መሆንን ማስረሻ አለማስታወስን
8 ካአንቺ ወዲያ ባንቺ ያማረ የለም ፍትፍቴ አጉራሽ፣ መጋቢ
9 ጀሚላ የምታምር፣ ቆንጆ ፋጡማ ራሷን አግላ የመትኖር
10 ባንቺጊዜ ከጊዜ ሁሉ በአንድ ነገር የሚታወስ የምስራች ደስታ፣ ተድላ
የመከራ ጊዜ
11 መስታወት የማያዳላ፣ ሁሉንም በእል አይን በጸሎት በልመና
የሚያይ
12 ቁምላቸው መከታ፣ መመኪያ ደለለኝ አታለለኝ፣ አጭበረበረኝ
13 አንጓች አዛኝ፣ ሩህሩህ ቃልኪዳን እምነት፣ ቃል አክባሪ
14 ትህትና ሰው አክባሪ ቀረአለም የደስታ ዘመን የመከራ ዘመን ሆነ
15 ቢኒያም የሀዘን የመከራ የጭንቀት ሰውመሆን ከባድ መከራ የደረሰበት መሆኑን
16 አበዛ ከመጠን በላይ መከራ የበዛበት በጸጋው ፈጣሪ በቸርነቱ፣ በምህረቱ

ምዕራፍ አራት
ማጠቃለያ

ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ የሰዎች ስም አወጣጥ እና ቅየራ በሚል ርዕስ የቀረበ ነው፡፡ ዋና
አላማውም ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ ነዋሪ የሆነው ማህበረሰብ የሰዎችን የመጠሪያ ስም አወጣጥ እና ቅየራ ስልት
ወይም ልምድ ምን እንደሚመስል በትንታኔ ለማሳየት ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ አዘጋጅ ጥናቱ በተካሄደበት
አካባቢ ነዋሪ የሆነው ማህበረሰብ የዚህ ዘመን የሰው ስም አወጣጥና ቅየራ ስልት ምን እንደሚመስል ለማሳየትና በዚህ
ርዕስ ጉዳይ ዙሪያ ላይ ጥናት ለማድግ ለሚፈልጉ አጥኚዎች የመነሻ ሀሳብ ይሰጣል ብሎ በማሰብ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡

ስያሜ ከሰዎች ህሊና ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጨባጭ የሆኑ የተለያዩ ነገሮች የመጠሪያ ስም የማውጣት ሂደት ነው፡፡
አመጣጡ እና አጀማሩም የቋንቋ ብቸኛ ተገልጋይ ከሆነው ከሰው ልጅ ታሪክና ከራሱ ከቋንቋ አጀማመር ተነጥሎ
አይታይም፡፡

24
የስያነሜ ሂደት የአንድን ማህበረሰብ የተለያዩ ማህበረሰብ ገጠመኞችንና እምነትንና የተከተለ ነው፡፡ አንድ ማህበረሰብ
ከሌላው ማህበረሰብ የሚለይባቸው መንገዶች በርካታ ሲሆኑ ከነዚህም መካከል የስም አወጣጥ ልምዱ ነው፡፡ ይህ ጥናት
በተደረገበት አካባ ነዋሪ የሆነው ማህበረሰብ አባለት እንዳላቸው የግል የህይወት ገጠመኝ እንደሚከተሉት ሀይማኖት
የሰዎች የመጠሪያ ስሞች ያወጣሉ፡፡ በአንጻሩም የስያሜ ለውጦች ያደርጋሉ፡፡ ለሰዎች የሚወጡላቸው እና
የሚቀይሯቸው መጠሪያ ስሞች የስም አውጪዎን ስነ ልቦናዊ አስተሳሰብ፣ የተለያዩ ገጠመኞችን ለምሳሌ የደስታ፣
የሀዘን ወዘተ ስሜቶችን ከግምት የሚየስገቡ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ ስም አውጪዎችን ስሙን ላማውጣት እና
ለመቀየር መነሻ የደረጓቸዉ ምክንያቶች ይገልጻሉ፡፡ ይኸውም የአውጪዎች የስም አወጣጥ ስልት ተከትለው እንደየ
አውጭዎ የግል ገጠመኝ የተለያዩ ስልቶችን በማንጸባረቅ የህብረተሰቡን ጠቅላላ አስተሳሰብ፣ እምነት፣ ልምድ ወዘተ
መግለጫ ሆነው ያገለግላሉ፡፡

25
ዋቢ መጽሐፍ
መሀመድ አወል፡፡ (1992)፡፡ “በጉራጌ ዞን የቸሀ ወረዳ የማዕረግ ስሞች አወጣጥ” አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአማርኛ
ቋንቋና ስነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል፡፡ (ያልታተመ) ዲ.ማ.ፅ፡፡

መላከ ብርሃን፡፡ (2001)፡፡ የመጠሪያ ስሞች መዝገብ፡፡ አዲስ አበባ፣ ኤች ዋይ ኢንተርናሽናል የህትመት ስራ ድርጅት፡፡

ሙሉጌታ ስዩም፡፡ (1972)፡፡ ስያሜ እና ችግሩ፡፡ አዲስ አበባ፣ ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ቋንቋዎች
አካዳሚ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎች ኢንስቲቲዩት በተዘጋጀው የትርጉም ሴሚናር ላይ የቀረበ፡፡

መጽሀፍ ቅዱስ፡፡ (2000)፡፡ የብሉይና ሀዲ ኪዳን መጽሀፍ፣ የኢትዮጵያ መጽሀፍ ቅዱስ ማህበር፡፡

ተሰማ ሀብተ ሚካኤል፡፡ (1951)፡፡ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡ አዲስ አበባ፣ አርቲክስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡

ተዘራ ዘአማኑኤል፡፡ (2006)፡፡ “የስልጤ ብሄረሰብ የማዕረግ ስሞች አወጣጥና ፋይዳዊ ትንተና፡፡” አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣
የአማርኛ ቋንቋና ስነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል፡፡ (ያልታተመ) ዲ.ማ.ጽ፡፡

አለም እሸቱ፡፡ (1992)፡፡ መሰረታዊ የምርምረ ዘገባ አፃፃፍ፡፡ አዲስ አበባ፣ ንግድ ማተሚያ ቤት፡፡

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፡፡ (2001)፡፡ አማርኛ መዝገበ ቃላት አዲስ አበባ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ማተሚያ ቤት፡፡

ዮናስ እና ሌሎች፡፡ (1966)፡፡ አማርኛ በኮሌጅ ደረጃ፡፡ አዲስ አበባ፡ የልታተመ

ደስታ ተክለወልድ፡፡ (1962)፡፡ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡ አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡

ደሳለኝ ጓንጉል፡፡ (1990)፡፡ “የሰው የተፅውኦ ስም አወጣጥ”፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሁፍ
ትምህርት ክፍል፡፡ (ያልታተመ) ዲ.ማ.ፅ፡፡

ዳኛቸው ወርቁ፡፡ (1977)፡፡ የጽሁፍ ጥበብ መመሪያ፡፡ አዲስ አበባ፡ንግድማተሚያ ድርጅት፡፤

ገብረስላሴ ክፍሉ፡፡ (2006)፡፡ “በኩሓ ከተማ ያሉ ሰፈሮች ስያሜ ትንተና፡፡” አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአማርኛ ቋንቋና ስነ
ጽሁፍ ትምህርት ክፍል፡፡ (ያልታተመ) ዲ.ማ.ፅ
ፀደቀ ሱገቦ፡፡ (1981)፡፡ “የከምባተኛ ስሞች በከምባታ ብሄረሰብ”፡፡ አዲስ አበባ ዩኒርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋወች
ስነጽሁፍ ትምህርት ክፍል፡፡ (ያልታተመ) ዲ.ማ.ፅ፡፡

1
2

You might also like