You are on page 1of 9

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

በአገር ውስጥ የወቅት ሥራ ሠራተኛ የሥራ ስምሪት


የአፈጻጸም መመሪያ

ሚያዝያ 2006 ዓ.ም


አዲስ አበባ
መ ግ ቢ ያ

ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት አገልግሎት ዋነኛ ዓላማ ሥራ ፈላጊ እንደፍላጎቱና ችሎታው ሥራ


እንዲያገኝ መርዳት ሲሆን፣ አሰሪም ለሥራው ብቁ የሆነ ሠራተኛ እንዲያገኝ እገዛ ማድረግ ነው፡፡

ሆኖም ወቅታዊ የሥራ ዕድል በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የወቅት ሥራ ሠራተኛ ተዘዋውሮ


የሚሰራበትና ተጠቃሚ የሚሆንበት እና አሠሪው በተለይ በእርሻና በአግሮ-ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ
ዘርፍ የሚያስፈልገውን የወቅት ሥራ ሠራተኛ የሥራ ወቅቱን ጠብቆ በመቅጠር ለሥራ
የሚያሰማራበት ግልጽና ወጥነት ያለው አጋዥ የአሰራር ሥርዓት ባለመኖሩ ሁለቱም ወገኖች
ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡

በዚህም የተነሳ አሠሪው የሚያስፈልገውን የወቅት ሥራ ሠራተኛ በጊዜ ማግኘት ባለመቻሉ


የምርት ብክነትን ከማስከተሉም ባሻገር በአገሪቱ የልማት ሥራ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ
ተስተውሏል፡፡

ስለዚህ ግልጽና ወጥነት ያለው የወቅት ሥራ ሠራተኛ ምልመላና ስምሪት የአሰራር ሥርዓት
በመዘርጋት የአሠሪውን የሰው ኃይል ፍላጎት በወቅቱና በጥራት ለማሟላት እንዲሁም የሠራተኛን
መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ብሎም የአገሪቱን የልማት ሥራ ለማፋጠን የሠራተኛና ማህበራዊ
ጉዳይ ሚኒስትር በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 170 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን
መመሪያ አውጥቷል፡፡

1. አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ “በአገር ውስጥ የወቅት ሥራ ሠራተኛ የሥራ ስምሪት የአፈጻጸም መመሪያ”


ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ዓላማ

የወቅት ሥራ ሠራተኛንና አሠሪን ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማገናኘት የሚያስችል


አጋዥ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የዘርፉን የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት በማጣጣም
የሥራ ስምሪትን ማቀላጠፍ እና የምርት ብክነትን መታደግ ነው፡፡

3. ትርጓሜ

በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-

1/ “አዋጅ” ማለት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 /እንደተሻሻለው/ ነው፣

2/ “ሚኒስቴር”፣“ሚኒስትር”፣“አሠሪ”፣“ሠራተኛ“፣ “ድርጅት”፣ “የሥራ ሁኔታ” እና “ክልል”


ማለት በአዋጁ አንቀጽ 2 የተሰጣቸው ትርጓሜ ይኖራቸዋል፣

1
3/ “ሰው” ማለት ማንኛውም የተፈጥሮ ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፣

4/ “የወቅት ሥራ” ማለት በእርሻ ወይም በአግሮ-ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ዘርፍ የአሠሪው ቋሚ


ሥራ ሆኖ በየዓመቱ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በተለመደው ጊዜ እየተደጋጋመ የሚሰራ ሥራ
ነው፣

5/ “የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ” ማለት ሥራና ሠራተኛ ማገናኘት” በሥራና
ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2001 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 እና
8 የተሰጣቸው ትርጓሜ ይኖራቸዋል፣

6/ “አግባብ ያለው ባለሥልጣን” ማለት በክልል የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕጎችን የማስፈጸም
ኃላፊነት የተሰጠው አካል ነው፣

7/ ማንኛውም በወንድ “ጾታ” የተገለጸው አነጋገር ሴትንም ይጨምራል፡፡

4. የተፈጻሚነት ወሰን፣

ይህ መመሪያ በወቅት ሥራ ሠራተኛ የሥራ ስምሪት ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

2
5. የወቅት ሥራ ሠራተኛ ጥያቄ ለማቅረብ መሟላት ያለበት ሁኔታ፣

የወቅት ሥራ ሠራተኛ ጥያቄ ለማቅረብ የሚፈልግ ማንኛውም አሠሪ እንደአግባቡ


የኢንቨስትመንት ወይም የንግድ ፈቃድ ማቅረብ አለበት፡፡

6. የወቅት ሥራ ሠራተኛ ጥያቄ ስለማቅረብ፣

1/ ማንኛውም አሠሪ የሚፈልገውን የወቅት ሥራ ሠራተኛ ከአካባቢው ማግኘት ካልቻለ


የሠራተኛ ፍላጎቱን ዝርዝር ሁኔታ (የሠራተኛ ብዛት፣ ሥራው የሚቆይበት ጊዜ፣ ወ.ዘ.ተ)
ጭምር ጥያቄውን ቅጥሩ ከሚፈጸምበት ጊዜ አንድ ወር አስቀድሞ በክልሉ ለሚገኘው
አግባብ ላለው ባለሥልጣን በዚህ መመሪያ በአንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 3 የተመለከቱትን
ማሟላት እንደሚችል በመግለጽ በጽሁፍ ማቅረብ አለበት፣

2/ ጥያቄው የቀረበለት አግባብ ያለው ባለሥልጣን ተፈላጊ የወቅት ሥራ ሠራተኛን ከክልሉ


ማሟላት የማይቻል መሆኑን ካረጋገጠ ሠራተኛው ከሚገኝበት ክልል አግባብ ያለው
ባለሥልጣን ጋር ግንኙነት በመፍጠር አሠሪው የሚፈልገውን ሠራተኛ ጥያቄው በቀረበለት
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፣

3/ የወቅት ሥራ ሠራተኛ የተጠየቀበት ክልል አግባብ ያለው ተፈላጊውን የሰው ኃይል በወቅቱ
ለማቅረብ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡

7. ክፍት የሥራ ቦታን ስለማሳወቅ፣

1/ ሠራተኛን ለወቅት ሥራ ከአንድ ከልል ወደ ሌላ ክልል አጓጉዞ ለመቅጠር የሚፈልግ


ማንኛውም አሠሪ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ለማውጣት በሠራተኛ ላኪ ክልል
ለሚገኘው አግባብ ያለው ባለሥልጣን በቅድሚያ ማሳወቅ አለበት፣

2/ የወቅት ሥራ ሠራተኛ ለመቅጠር የሚወጣ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ሥራው


የሚጠይቀውን ተፈላጊ ችሎታ፣ የደመወዝ መጠን፣ የሥራ ቦታና ጊዜ፣ ቀጣሪው ድርጅት
የሚሸፍናቸው ወጪዎች (መጠለያ፣ ምግብ፣ ንጽህ ውሃ፣ ሕክምና፣ትራንስፖርት፣
ወ.ዘ.ተ) በግልጽ የሚያመለክት መሆን አለበት፣

3/ የሚወጣው የክፍት ሥራ ቦታ ማስታወቂያ ምልመላው ከመጀመሩ በፊት ለአምስት የሥራ


ቀናት ግልጽና አማካይ በሆኑ ቦታዎች ላይ ተለጥፎ መቆየት ይኖርበታል፣

4/ አሠሪው የወቅት ሥራ ሠራተኛ ፍላጎት በብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች ማስታወቅ ካስፈለገው


ይህንኑ ለማድረጉ ለሠራተኛ ላኪው አግባብ ላለው ባለሥልጣን ማሳወቅ አለበት፡፡

3
8. ስለ ሥራ ፈላጊ ምዝገባ፣

1/ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 7 በሚወጣው ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ መሠረት


የሚመለከተው አሠሪ ሠራተኛው በሚገኝበት ክልል ካለው አግባብ ያለው ባለሥልጣን
ጋር በመተባበር ዕጩ የወቅት ሥራ ፈላጊ ምዝገባ ያካሄዳል፣

2/ የሚመዘገብ ዕጩ የወቅት ሥራ ፈላጊ መረጃ ለዚሁ በሚዘጋጀው ቅጽ መሠረት በተገቢው


ተሞልቶ መያዝ አለበት፡፡

9. eK W^}ኛ ምልመላ፣

1/ የወቅት ሥራ ሠራተኛ ምልመላ የሚካሄድበት ቦታ የክልሉ ሠራተኛ ላኪ አግባብ ያለው


ባለሥልጣን እና አሠሪው በሚስማሙበት ቦታ ይሆናል፣

2/ ለወቅት ሥራ የሠራተኛ ምልመላ የሚደረገው በዚህ መመሪያ በአንቀጽ 8 መሠረት


ከተመዘገቡት ዕጩ ሥራ ፈላጊዎች መካከል ነው፣

3/ የወቅት ሥራ ሠራተኛ ምልመላ የሚፈጸመው በአሠሪው ወይም አሠሪው በወከለው ሰው


ይሆናል፡፡

10. ስለ ቅጥር አፈጻጸም፣

1/ በዚህ መመሪያ በአንቀጽ 9 የተመለከተው ምልመላ እንደተጠናቀቀ በአሠሪ ወይም


በአሠሪው ተወካይ እና በሠራተኛው መካከል የሥራ ውል ይመሠረታል፡፡ የሥራ ውሉም
በአራት ኮፒ ተዘጋጅቶ ለላኪውና ተቀባይ ክልል አግባብ ላለው ባለሥልጣን፣ ለአሠሪው
እና ለሠራተኛው አንዳንድ ኮፒ እንዲደርሳቸው መደረግ አለበት፣

2/ አሠሪው የቀጠራቸውን የወቅት ሥራ ሠራተኞች ወደ ሥራው ቦታ ከማጓጓዙ በፊት


የእነዚህን ሠራተኞች መሠረታዊ መረጃ ለዚሁ በተዘጋጀው ቅጽ ላይ በመሙላትና
በፊርማው በማረጋገጥ በሠራተኛ ላኪ ክልል ለሚገኘው አግባብ ላለው ባለሥልጣን በሦስት
የሥራ ቀናት ውስጥ ማቅረብ አለበት፣

3/ ለወቅት ሥራ የተቀጠረ ሠራተኛ ከአሠሪው ወይም ከአሠሪው ተወካይ ጋር የሥራ ውል


ከተመሠረበት ቀን አንስቶ በአሠሪው እንደተቀጠረ ይቆጠራል፡፡ ሆኖም ይህ ድንጋጌ የሥራ
ውል ከተመሠረተ በኋላ በራሱ ፈቃድ በሥራ ቦታ ያልተገኘውን ወይም በራሱ ፈቃድ
ሥራ ያልጀመረውን ሠራተኛ አይመለከትም፣

4
4/ አሠሪው በዚህ መመሪያ መሠረት በተቀባይ ክልል ሥራ ቦታ ደርሰው ሥራ የጀመሩ
የወቅት ሥራ ሠራተኞች ዝርዝር መረጃ ለዚሁ በተዘጋጀው ቅጽ ላይ በመሙላትና
በማረጋገጥ ለሠራተኛ ላኪ እና ተቀባይ ክልል አግባብ ላለው ባለሥልጣን በአንድ ወር
ጊዜ ውስጥ ማሳወቅ አለበት፡፡

11. ሠራተኛን ወደ ሥራው ቦታ ስለማጓጓዝ፣

1/ አሠሪው ሠራተኛን ከአንድ አካባቢ ወይም ክልል ወደ ሥራው ቦታ በሚያጓጉዝበት ወቅት


የሚከተሉት ሁኔታዎች መሟላታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፤

ሀ/ ሠራተኛን ለማጓጓዣ የሚያስችል አመቺ ትራንስፖርት መቅረቡን፣

ለ/ በየቦታው ሲታረፍ በቂ የማረፊያ ቦታ መኖሩን፣

ሐ/ እንዳስፈላጊነቱ የምግብ፣ የማደሪያ፣ የሕክምና አገልግሎት፣ ክትባት እንዲሁም


ሌሎች ሁኔታዎች መሟላታቸውን፤

2/ በሠራተኛ ላኪና ተቀባይ ክልል የሚገኝ አግባብ ያለው ባለሥልጣን በዚህ አንቀጽ ንዑስ
አንቀጽ1 የተመለከቱት መፈጸማቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡

12. የአሠሪው ግዴታና ኃላፊነት፣

በዚህ መመሪያ መሠረት አሠሪው ለወቅት ሥራ ሠራተኛ ያለበት ግዴታና ኃላፊነት


የሚከተሉትን ይጨምራል፣

1/ ለወቅት ሥራ ሠራተኛው መጠለያ፣ መብራት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እና የሕክምና


አገልግሎት በነፃ የመስጠት፣

2/ የወቅት ሥራ ሠራተኛው ወደ ሥራ ቦታ በሚጓጓዝበት ወቅትም ሆነ በሥራ ላይ


ለሚደርሰው አደጋ የኢንሹራንስ ሽፋን መስጠት፣

3/ የወቅት ሥራ ሠራተኛው ሥራ ከመጀመሩ በፊት፡-

ሀ/ ድርጅቱ ስለሚገኝበት አካባቢ፣ስለ ድርጅቱና ስለሥራው ሁኔታ፤

ለ/ የደመወዝ መጠንና የአከፋፈል ሁኔታ፤


ሐ/ የሥራ ቦታ፣

መ/ ሥራው የሚጀምርበትና የሚጠናቀቅበት ጊዜ፣

ሠ/ የአሠሪውና የሠራተኛው መብቶችና ግዴታዎች፣

5
ረ/ ከሥራው ጋር በተያያዘ የሠራተኛው ደህንነትና ጤንነት እንዲጠበቅ እና የሥራ
ላይ አደጋ እንዳይከሰት መወሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እና ስለመሳሰሉት
ጉዳዮች፣

የማሳወቅና መግለጫ የመስጠት፤

4/ ለወቅት ሥራ ሠራተኛው ከተመለመለበት አካባቢ ወደ ሥራው ቦታ ለማድረስ አመቺ


የመጓጓዣ አገልግሎት በነፃ የማቅረብ እንዲሁም ሥራው ሲጠናቀቅ ወደ ተመለመለበት
አካባቢ የመመለስ፣

5/ የወቅት ሥራ ሠራተኛው ምግቡን ራሱ የሚያዘጋጅ ከሆነ የሚዘጋጅበት አመቺ ቦታና


የምግብ ማብሰያ ዕቃዎችን የማቅረብ፣

6/ የወቅት ሥራ ሠራተኛው በጉዞ ወቅትም ሆነ በሥራ ቦታ የሞት አደጋ ወይም የሥራ ላይ


ጉዳት ሲደርስበት ጉዳት የደረሰበትን ሠራተኛ ወይም አስክሬን ወደ ቤተሰቦቹ የማድረስና
በአዋጁ መሠረት ተገቢውን የጉዳት ካሳ የመክፈል፣

7/ ለወቅት ሥራ ሠራተኛው በሥራ ውሉ መሠረት ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ የመፈፀም፣

8/ የወቅት ሥራ ሠራተኛን የሚመለከቱ መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ የመያዝና


ለሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ የማስተላለፍ፡፡

13.የሠራተኛው ግዴታ፣

ሠራተኛው በአዋጁና አዋጁን መሠረት አድርገው የወጡ መመሪያዎች እና በዚህ መመሪያ


መሠረት የሚወጡ የወቅት ሥራ ሠራተኞችን የሚመለከቱ የሥራ ደንቦች የማክበር ግዴታ
አለበት፡፡

14. የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ለወቅት ሥራ ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት
ስለመቻሉ

አግባብ ባለው ሕግ ፈቃድ ያለው ማንኛውም የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ በዚህ
መመሪያ መሠረት ለወቅት ሥራ ሥራና ሠራተኛን የማገናኘት አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡

6
15. ስለ ክፍያ አፈጻጸም፣

1/ አሠሪው በአካባቢው ያለውን የሥራ ገበያ ሁኔታ ያገናዘበ የደመወዝ መጠን ለሠራተኛው
መክፈል አለበት፣

2/ ለወቅት ሠራተኛ በወር ሁለት ጊዜ (በየ15 ቀን) የደመወዝ ክፍያ ሊፈጸም ይችላል፣

3/ የሠራተኛ ደመወዝ ክፍያ ሲፈጸም በሥራ ቦታና በሥራ ሰዓት መሆን ይኖርበታል፣
4/ ሠራተኛው ክፍያውን በፔሮል/በደመወዝ መክፈያ ሰነድ ፈርሞ እንዲቀበል መደረግ አለበት፣

5/ ከሠራተኛው ደመወዝ የሚቀነሱ ክፍያዎች በፔሮል/በደመወዝ መክፈያ ሰነድ ሊካተቱና


ሠራተኛው እንዲያውቀው መደረግ አለበት፣

6/ ሌሎች ክፍያዎች በአዋጁ እና በድርጅቱ የሥራ ደንብ መሠረት ሊከፈሉ ይገባል፡፡

16. የሥራ ውል ስለማቋረጥ፣

1/ ለወቅት ሥራ የተደረገ የሥራ ውል በውሉ የተወሰነው ጊዜ ወይም ሥራው ሲያበቃ


ይቋረጣል፣

2/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተው ቢኖርም በአዋጁ በተደነገጉ ሁኔታዎች


ምክንያት መሠረት የሥራ ውሉ ሊቋረጥ ይችላል፡፡

17. ስለ ቁጥጥር፣
አግባብ ያለው ባለሥልጣን በአዋጁ መሠረት በማንኛውም ወቅት የወቅት ሥራ ሠራተኛ
መብትና ደህንነት መከበሩን ቁጥጥር የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

18. ክልከላ፣
ከዚህ በታች የተመለከቱትን መፈጸም ክልክል ነው፤

1/ ማንኛውም ሰው ሥራ ፈላጊውን ለመቅጠርም ሆነ ለማስቀጠር ከሥራ ፈላጊው ላይ ገንዘብ


መቀበል፣

2/ አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ሥራና ሠራተኛን የማገናኘት አገልግሎት ለመስጠት


የሚያስችል የኤጀንሲነት ፈቃድ ሳይኖረው ለወቅት ሥራ ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት፣

3/ ማንኛውም አሠሪ አግባብ ላለው ባለሥልጣን ሳያሳውቅ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል


የወቅት ሥራ ሠራተኛ ለመቅጠር ማስታወቂያ ማውጣት፣ መመልመል ወይም መቅጠር፣

7
4/ የወቅት ሥራ ሠራተኛን የግል ሰነዶች እንደ መታወቂያ፣ የጤና ካርድና የመሳሰሉትን
መያዝ፡፡

19. ቅጣት፣
ይህንን መመሪያ የተላለፈ ማንኛውም ወገን ላይ በአዋጁ አንቀጽ 184 እና 185 ወይም
በሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2001 አንቀጽ 40 የተደነገጉት
ቅጣቶች ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡

20. የመተባበር ግዴታ፣

በዚህ መመሪያ በተደነገጉት ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው አካላት የመተባበር ግዴታ


አለባቸው፡፡

21. መመሪያው ስለሚሻሻልበት ሁኔታ፣

ሚኒስትሩ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ይህን መመሪያ ሊያሻሽል ይችላል፡፡

22. መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ፣

ይህ መመሪያ ከሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ---------------------------- ዓ.ም

---------------------------------

አብዱልፈታህ አብዱላሂ
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር

You might also like