You are on page 1of 57

• የትምህርት

ጥናትና ምርምር ስልጠና


ህዳር 5 2016 ዓ.ም
የስልጠናው ዓላማ
• መምህራን ስለተግባራዊ ጥናትና ምርምር ጽንሰ ሀሳብ ለማስገንዘብ፤
• የተግባራዊ ጥናትና ምርምር የአካሄድ ዘዴዎችን ለማሳወቅ፤
• በት/ቤቱ ያሉ ጥቃቅን ችግሮች በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ለመፍታት፤
• ለመምህራን አጠቃላይ የሆነ ስለተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሙያዊ እውቀት ለማዳበር፡፡
የትምህርት ጥናትና ምርምር ምንነትና ፅንሰ ሀሳብ
ብዙ ምሁራን ለጥናትና ምርመር የተለያዩ ሆኖም ግን ተቀራራቢ ሀሳብ
ያላቸው ትርጉሞችን ይሰጣሉ፡፡ "Research" የሚለው የእንግለዚኛ
ቃል የመጣው "Recherch’e" ከሚለው የፈረንሳይ ቃል ሲሆን
ትርጉሙም መፈተሸ /Travel through or survey/ ማለት ነው፡፡
ይህም ማለት በዘፈቀደ የሚሰራ ሳይሆን በሳይንሳዊ መንገድ በመከተል
መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ወደ አንድ መደምደሚያ
የሚያደርስ መሳሪያ ነው፡፡
በአጠቃላይ ምርምር ሳይንሳዊ ዘዴን መሰረት አድርጎ ማህበራዊ፣
አካበቢያዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ወይም
በተለያዩ መስኮች አዳዲስ ንድፈ ሀሳቦችን ወይም እውቀት ለማፍለቅ
ወይም የአንድን ፕሮግራም፣ፖሊሲ፣ አዲስ ምርት፣ የአሰራር ዘዴና
ሌሎች ነገሮች በተጠቃሚዎች ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ለማወቅ
በሰዎች ወይም በሌሎች ማናቸውም ነገሮች ላይ የሚካሄድ ተግባር
ነው፡፡
የትምህርት ጥናትና ምርምር ባህርያት
• የትምህርት ጥናትና ምርምር ሳይንሳዊ ዘዴን በመከተል የትምህርት
ባለሙያዎች ለችግሮቻቸው ቋሚና ዘላቂ መፍትሄ የሚፈልጉበት መንገድ
ነው፡፡ ይህንን ተጨባጭ ለማድረግ የትምህርት ጥናትና ምርምር
ባህርያት ከዚህ ቀጥለው ቀርበዋል፡፡
• የትምህርት ጥናትና ምርምር ስራ ችግሮችን በመፍታት ላይ ያተኮረ
ነው፡፡
• የትምህርት ጥናት ምርምር የሚከናወኑ አንድ ችግር በሌሎ መልስ
የማግኛ ዘዴዎች በሚገባ ተሞክሮ መልስ ካልተገኘ ነው፡፡ በቀላሉ
መልስ ላልተገኘላቸው ችግሮች መልስ ይፈልጋል፡፡
• የትምህርት ጥናትና ምርምር የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ በአጋጣሚ ወይም
በዘፈቀደ የሚመራ ሳይሆን ችግርን ከመለየት አንስቶ አዋጭ መንገድን
እስከማመልከት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ይከናወናል፡፡
• የትምህርት ጥናትና ምርምር አስፈላጊነት
• የትምህርት ጥናትና ምርምር የተከሰተ ችግር መፍትሄ ለመሻት
ለማስወገድ እንዲሁም የሰው ልጅን የማወቅ ጉጉት ለማርካት፣ አዳዲስ
የእውቀት ዘርፎችን ለማፍለቅ፣ የጎደለ መረጃን ለማሟላትና አዳዲስ
ግኝቶችና ንድፈ ሀሳብን ለመፍጠር ይረዳል፡፡
• በትምህርት መስክ ስንመጣ በመማር ማስተማሩ የግብዓት፣ የሂደትና
የውጤት በርካታ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ በተማሪዎች፣ በመምህራን
በስርዓተ ትምህርት፣ በት/ቤት በማስተማሪያና በመማሪያ
ቁሳቁሶች/ግብዓቶች/ ወዘተ. . . ዙሪያ ከቢሮ ጀምሮ እስከ ት/ቤት
ድረስ በርካታ ችግሮች በየዕለቱ ይከሰታሉ፡፡
የትምህርት ጥናትና ምርምር ዘርፎች
የትምህርት ጥናትና ምርምር ይዞት ከሚነሳው ዓላማ ወይም ግብ አንፃር በሶስት
ይከፈላል፡፡ እነዚህም
ሀ/ ገምጋሚ ጥናትና ምርምር
ለ/ ተግባራዊ ጥናትና ምርምር
ሐ/ መሰረታዊ ጥናትና ምርምር በመባል ይታወቃሉ፡፡
ሀ/ ገምጋሚ ጥናትና ምርምር
• ይህ የምርምር ዓይነት የሚያተኩረው በአንድ በተወሰነ ቦታ የሚከናወን
ወይም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለ ፕሮግራም፣ፖሊሲ፣ፕሮጀክት፣ መስሪያ
ቤት ወይም ደንብ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነና እንዳልሆነ ምላሽ
ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ላይ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ከሚካሄድበት አካባቢ
አንፃር ያለውን ተገቢነትና ፋይዳ በመገምገም ለሚኖረው ቀጣይነት ወይም
መቋረጥ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘት
ይረዳል፡፡
ለ/ ተግባራዊ ጥናትና ምርምር
• ተግባራዊ ጥናትና ምርምር አፋጣኝ መፍትሄ ለሚፈልጉና በስራ ሂደት
ፊት ለፊት ለሚታዩ አካባቢያዊ ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሄ ለማምጣት
ያለመ የመስክ ጥናት አንዱ አካል ነው፡፡
• በተጨባጭ በሚከሰቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ላይ የሚያተኩርና የችግሮችን
መንስኤ በመለየት መፍትሄ ለማግኘት የሚጥር የምርምር ዓይነት ነው፡፡
ይህ ሲባል ግን ተግባራዊ ምርምርና መሰረታዊ ምርምር የማይገናኙ
ናቸው ማለት አይደለም እንዲያውም ተደጋጋፊዎች ናቸው፡፡
ሐ/ መሰረታዊ ጥናትና ምርምር
• ይህ ምርምር የሚካሄደው በቀጥታ ችግርን ለመፍታት ሳይሆን የሰውን
ልጅ የእውቀት ጥማት ለማርካት በአእምሮ ውስጥ ለሚጉላሉ ጥያቄዎች
መልስ ለመሻት አዳዲስ ቲዎሪዎችን ለማፍለቅና ከነበረው የእውቀት
ደረጃ ላይ ሌሎች አዳዲስ የእውቀት ጠብታዎችን ለመጨመር ነው፡፡
የትምህርት ጥናትና ምርምር ርዕስ አመራረጥ
• የጥናትና ምርምር ስራ የመጀመሪያው ተግባር የጥናቱን ርዕስ መምረጥ
ነው፡፡ የጥናቱን ርዕስ ለመምረጥ ደግሞ ስለሚጠናው ጉዳይ በቅድሚያ
በቂ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም
ማንኛውም ጥናትና ምርምር ለማካሄድ የሚፈልግ ሰው በመጀመሪያ
ደረጃ የጥናት ርዕስ ምንጮችን ለይቶ ማወቅና ተፈላጊ የጥናት ርዕስ
በመምረጥ የጥናቱን ግኝት፣ ተቀባይነትና ጠቀሜታ ከወዲሁ ማመቻቸት
ይኖርበታል፡፡ ማንኛውም አጥኚ በጥናትና ምርምር ርዕስ ምንጭነት
ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ሶስት ዋና ዋና ምንጮች አሉ፡፡
እነሱም፡-
• ሀ/ አጥኚው በስራ ሂደት የተገነዘባቸው ችግሮችና ያካበታቸው ተሞክሮች
• ለ/ አንዳንድ ንድፈ ሀሳቦች በጥናት ላይ ቢመሰረቱም በቀጣይ ጥናቶች
እንዲደረግባቸው ሲጠቆም
• ሐ/ የተዛማጅ ፅሁፎች ቅኝት ናቸው፡፡
እነዚህ ሶስቱ ዋና ዋና የጥናት ርዕሰ ምንጮች በሚከተለው መልኩ ያብራራሉ፡፡
• ከልምድ የተደረሰባቸው አጨቃጫቂና አጠራጣሪ ድምዳሜዎች
• የምርምር ባለሙያዎች ቀጣይ ጥናት እንዲደረግባቸው ከሰጧቸው አስተያየቶች
• በቂ ገለፃና ማብራሪያ ያልተሰጠባቸው ፅንሰ ሀሳቦች
• ድጋሜ ፍተሻ የሚጠይቁ ንድፈ ሀሳቦች
• ቀደም ሲል ከተከናወኑ የጥናትና ምርምር ሪፖርቶች
• በዕለት ተዕለት የመማር ማስተማርና ማህበረሰባዊ መስተጋብሮች ከሚገጥሙን
እውነታዎች
• የቴክኖሎጂ ለውጥና የህብረተሰቡ ዕድገት የሚያስከትሏቸው ተፅዕኖዎች ወዘተ. . .
ናቸው፡፡
የትምህርት ጥናትና ምርምር ርዕስ የመምረጫ መስፈርቶች
• የትኛውም የጥናት ርዕስ መመረጥና መጠናት እንዳለበት ለመወሰን ይቻል
ዘንድ በመጀመሪያ ደረጃ ስለሚጠናው ጉዳይ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ማዳበር
አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ በጥናቱ ሊተኮርባቸው ወይም መልስ ሊሰጥባቸው
የሚገቡ ጉዳዮችን ለይቶ ማወቅና የጥናት ርዕስ ቀርፆ በተገቢው መንገድ
ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በትምህርትም ሆነ በሌላ ዘርፍ ያሉ አጥኚዎች
የጥናት ርዕስ ሲመርጡ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር
ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ ለማጥናት የሚፈልጉትን ርዕሰ ሲመርጡ የሚከተሉትን
የጥናት ርዕስ የመምረጫ ነጥቦች መጠቀም ይችላሉ፡፡
• የተመረጠው የጥናት ርዕስ ከአሁን በፊት ያልታየ ወይንም ያልተተኮረበት
ቢሆን ይመረጣል፣ ነገር ግን የተጠና ርዕስም ከሆነ በአዲሱ ጥናት አዲስና
የተለየ ነገር መጨመር አለብን፡፡
• የተመረጠው የጥናት ርዕስ ወቅታዊና ቢጠና ጠቃሚነቱ በጉልህ የሚታይ
መሆን ይኖርበታል፡፡
• ርዕሱ ጥናቱን የሚያካሂደውን ሰው የማወቅ ፍላጎትና ጉጉት ከማርካት ጋር
ተያይዞ ቢመርጥ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡
• ርዕሱ ጥናቱን የሚያካሂው ሰው የስልጠና መስክና የት/ት
ደረጃ ጋር ተዛማጅ ቢሆን ይመረጣል፡፡
• ጥናቱን ለማካሄድ የሚረዱ መረጃዎችና ዘዴዎች በተሟላ
ሁኔታ ሊገኙ መቻላቸውን የጥናቱ ርዕስ ከወዲሁ መጠቆም
አለበት፡፡
• ለጥናቱ የሚወጣው ወጪ ከአጥኚው የገንዘብ አቅም ጋር
እንዲሁም ከሚገኘው ውጤት ወይም ጥቅም ጋር መገናዘብ
አለበት፡፡
• ከጥናቱ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ አደጋዎችና መሰናክለኮች ሊኖሩ
እንደሚችሉ አስቀድሞ ገምቶ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
• ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ጊዜ የጥናቱን ርዕስ መሰረት
አድርጎ መታወቅ አለበት፡፡
የትምህርት ጥናትና ምርምር ርዕሰ አቀራረፅና አቀራረብ
• የተመረጠው የጥናት ርዕስ ትክክለኛነትና ተገቢነት ከላይ በተቀመጠው
መስፈርት ታይቶ ከተረጋገጠ በኋላ የጥናቱ ርዕስ ግልፅና አጠር ባለ መልኩ
መቀረፅና መቀመጥ አለበት፡፡ የጥናቱን ርዕስ ስናስቀምጥ የጥናታችን ስፋት
ከአጠቃላይነት ይልቅ የአጥኚውን እውቀት፣ ጊዜና ገንዘብ በመጠነ መልኩ
ውስን በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር በሚያደርግ ደረጃ ርዕሱን መቅረፅና
ማቅረብ ጥናቱን ግልፅ ከማድረጉም በላይ ለተቀባይነቱም ምቹ ሁኔታን
ይፈጥራል፡፡ የጥናቱን ርዕስ በጥያቄ ወይም በሀረግ መልክ ማስቀመጥ
ይቻላል፡፡
• ለምሳሌ፡-
• ተማሪ ተኮር አሳታፊ የማስተማር ስነ ዘዴን እንዴት ማጎልበት ይቻላል?
• የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት በአዲስ አበባ ያለበት ደረጃ፣
• የትምህርት ብክነት በትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ላይ ያለው ተፅዕኖ፣
• የተማሪዎች የሂሳብ ትምህርት አቀባበል ችሎታን የሚወስኑ ጉዳዮች ምን ምን
ናቸው?
ሀ/ የእንግሊዝኛ ትምህርት አሰጣጥ በአዲስ አበባ
ለ/ የእንግሊዝኛ ትምህርት አሰጣጥ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ
የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች
ሐ/ የእንግሊዝኛ ትምህርት አሰጣጥ በቂርቆስ ክ/ከተማ ስር በተመረጡ
ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች
ሌላው በርዕስ መረጣ ወቅት ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ አንድ ጥናት
መዳሰስ በሚገባው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር አድርጎ ርዕሱን
የመቅረጽ ተግባር ነው፡፡ ይህም ካልሆነ የጥናቱን ጠቀሜታ ያሳሳዋል፡፡
ስለዚህም ርዕሱ በተቻለ መጠን ጎላ ጎላ ያሉ ጉዳዮችን በሚያንፀባርቅ
ሁኔታ መቀረፅና መቅረብ ይኖርበታል፡፡
•የጥናትና ምርምር ክፍሎች
የጥናትና ምርምር ክፍሎች
• ምእራፍ አንድ
መግቢያ(Introduction)
• በዚህ ምእራፍ ውስጥ የሚካትታቸው ንኡስ ርዕስ አሉ እነሱም፡
1.1 የጥናቱ ዳራ(Back ground of the study)
• የጥናቱ ዳራ በሚገባ ባለመዘጋጀቱ ምክንያት ጥናቱ ተቀባይነት እንዳያጣ ዳራውን በጥንቃቄ
ማዘጋጀት ወሳኝነት አለው፡፡
ይህ የምርምሩ የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን ተመራማሪው ጥናቱ ስለምንና
ለምን መካሄድ እንዳለበት ለአንባቢው የሚያስተዋውቅበት የምርምሩን
አጠቃላይ ዳራ የሚገልፅበት ክፍል ነው፡፡ በመግቢያው ላይ
ተመራማሪው አጠቃላይ የመንደርደሪያ ሀሳብ በተዛማጅ ፅሁፍ የተደገፈ
ስለ ጥናቱ ማብራሪያና የማጠቃለያ ሀሳብ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡
የመንደርደሪያው ሀሳብ የጥናቱ መክፈቻ በመሆኑ አንባቢውን ሊስብ
የሚችል መሆን አለበት፡፡ የአንባቢውን ትኩረት ለመያዝና የምርምሩን
ስራ በተቻለ መጠን በሙሉ እንዲያነበው ለማስቻል
• ከባድና ሙያዊ ቃላት የታጨቁ አገላለፆችን ማስወገድ
• በቀላል ነገር ግን መልዕክቱን ሊያስተላልፍ በሚችሉ ቃላት መጠቀም
• አስፈላጊ ሲሆን ምሳሌና አስረጅ መጠቀምና
• የሚቻል ሲሆን መግቢያውን ከአንባቢው ህይወት ጋር ሊዛመድ
የሚችል ገጠመኝን በማንሳት መጀመር ጠቀሜታ አላቸው፡፡
1.2 የጥናቱ መነሻ ችግር ማብራሪያ(Statement of the problem )
• በጥናቱ ችግር ማብራሪያ ክፍል ተመራማሪው ያነሳውን ችግር ምንነት?
እስከአሁን በዚህ መልክ የተደረጉ ጥናቶች መኖር አለመኖራቸውን?
የተገኙ ውጤቶች ምንድን ናቸው? ምን ያህል ይቃረናሉ? ካልተደጋገፉ
ለመለያየታቸው ምክንያቶቹ ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ምን ያህሉስ
ይስማማሉ? ተመራማሪው ከነዚህ ጥናቶች የተለየ ምን ለማድረግ
ፈልጓል? የሚጨመረው አዲስ ነገር ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች
ይነሳሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለማንሳትና በቂ ማብራሪያ ለማቅረብ
ተመራማሪው የተዛማጅ ስራዎች ዳሰሳ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ተመራማሪዎች በተቻለ መጠን የተዛማጅ ፅሁፍ ክለሳ ሲያካሂዱ እጥር
ምጥን አድርገው የችግሩን ምንነት በሚያጎላ መልኩ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሀሳባቸውን ወይም መላምታቸውን የሚደግፉ ወይም ያነሷቸውን
የምርምር ጥያቄዎች እነሱ በሚፈልጉት አቅጣጫ የሚረዷቸውን ብቻ
በመምረጥ ሳይሆን ተቃራኒ ሀሳቦችንና የጥናት ውጤቶችን የያዙ ተዛማጅ
ፅሁፎችን ማካተት ተገቢ ነው፡፡
1.3 መላምት (መሰረታዊ ጥያቄዎች)/Hypothesis(basic
Question)
መላምት ተመራማሪው ምርምሩን ለመተግበር ሲነሳ በመጀመሪያ አንዳንድ
ጥርጣሪያዊ ጥያቄዎችና መልሶች ወይም መፍትሄዎች ይሆናሉ ብሎ
የሚያስባቸው ናቸው፡፡ ምሳሌ የተማሪው የስነ ምግባር ጉድለት
መንስኤዎች፡-
• የቤተሰብ አያያዝ
• በትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ማምጣትና ተስፋ መቁረጥ ወዘተ. . .
• የሚሉት ለተማሪው የጠባይ መበላሸት ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ
ተብለው በመላምት መልክ ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ እነዚህም በጥናቱ ውስጥ
ሊረጋገጡ ወይም ሊሻሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ መላምት በጥያቄ ወይም
በአርፍተ ነገር መልክ ሊቀርብ ይችላል፡፡
ለምሳሌ፡- መላምት 1. ተማሪውን ረባሽ ያደረገው የቤተሰብ አያያዝና
አስተዳደር መበላሸት ነው ፡፡ (አርፍተ ነገር)
• መላምት 2. በተማሪው ጠባይ ላይ ተፅዕኖ ያደረገው የጓደኞቹ ግፊት
ይሆን?(በጥያቄ መልክ)
• እነዚህ በጥናቱ ውስጥ በተለያዩ ዘዴዎች መረጃዎችን በማሰባሰብ
መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የእነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች
መልስ ማግኘት የመላምቶችን እውነተኛነት ወይም ሀሰተኛነት ግልጽ
ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰውን መላምቶች ሁኔታ ብናይ
በሚከተሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች መልክ መመለስ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
• የትምህርት ውጤቱ ምን ይመስላል?
• የቤተሰቡ አያያዝና አስተዳደር ምን ይመስላል? ወዘተ. . .
• እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን ተመራማሪው መመለስ ከቻለ ለተማሪው
ጠባይ መበላሸት መንስኤ የሆነውን ነገር ማግኘት ይችላል፡፡ ስለዚህ
በምርምር አለም ተመራማሪው በጥናቱ ሂደት ውስጥ አጥጋቢ ምላሽ
ሊያገኝላቸው የሚገባው አብይ ነጥቦችና ጥያቄዎች እንዳሉ መረዳት
አስፈላጊ ነው፡፡
• ከላይ የተገለፁት መላምትና መሰረታዊ ጥያቄዎች ተመሳሳይ
አገልግሎ ያላቸው በመሆኑ አጥኝዎች ከሁለቱ አንዱን ብቻ
በመውሰድ ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ስለዚህ እኛም
በጥናታችን የሚመቸንን አቀራረብ በመምረጥ አንድም
በመላምት ወይም በመሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ መሰረት
አድርገን ምርምራችንን ልናካሂድ እንችላለን፡፡
1.4 የጥናቱ ዓላማዎች(Objectives of the study)
• የጥናቱ ዓላማ ተመራማሪው በምርምሩ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ
ሲጨርስ ጥናቱ ምን ሊያመላክተን እንደፈለገ የሚያሳይ ክፍል ነው፡፡
ተመራማሪው በምርምሩ ሂደት ለማድረግ ያሰበው፣ ለአንባቢው
ሊያሳያውና ሊነግረው የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች
መልስ የሚሻው በጥናቱ አላማ ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ የጥናቱ ዓላማ
ከምርምሩ ጥያቄዎች እና ወይም መላምቶች ጋር በቀጥታ መዛመድ
አለበት፡፡
ለምሳሌ፡- ተመራማሪው ያነሳው የምርምር ርዕስ "የተማሪዎችን
የፈጠራ ችሎ የሚያቀጭጩ የት/ቤት ውስጣዊ ሁኔታዎች"
በሚል ሆኖ የምርምር ጥያቄዎቹ
1. የማስተማር ስነ-ዘዴዎች የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታ
ለማሳደግ ያላቸው አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው?
2. መምህራን የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታ ለማሳደግ ያላቸው
አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው?
3. የመማሪያ ቁሳቁሶችና መፅሐፍቱ የተማሪዎቹን የፈጠራ ችሎ
ለማሳደግ የሚረዱ ናቸው?
የሚሉ ቢሆኑ የጥናቱ ዓላማዎች ደግሞ እንደሚከተለው ሊፃፉ
ይችላሉ፡፡
• የዚህ ጥናት ዓላማ
• የማስተማር ዘዴዎች የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታ ምን ያህል የማሳደግ ብቃት
እንዳላቸው ለማወቅ፣
• መምህራን የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታ ለማሳደግ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች
ምን ምን እንደሆኑ ለመለየትና
• የመማሪያ ቁሳቁሶችና መፅሐፍቱ የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎ ለማሳደግ
ያላቸው ብቁነት ምን ያህል እንደሆነ ለመገምገም ነው፡፡
• ተመራማሪው የጥናቱን ዓላማ ሲፅፍ እንዳለው ችሎታ መጠን ዘርዘር አድርጎ
ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይሁንና ምርምሩ ይዟቸው ከተነሳቸው ጥያቄዎች ወይም
መላምቶች ያፈነገጠ መሆን የለበትም፡፡
1.5 የጥናቱ አስፈላጊነት(Significance of the study)
• ተማራማሪው ምርምር ማካሄዱ ምን ፋይዳ አለው? ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት
ወጪ ሲደረግ ከምርምሩ የሚገኘው ውጤት ምን ጥቅም ይሰጣል? የሚል
ጥያቄ ይነሳል፡፡ ተመራማሪው ለዚህ የሚሆን መልስ መስጠት
ይጠበቅበታል፡፡ የዚህ መልሰ ነው የምርምሩ ጠቀሜታ፡፡
• ስለዚህ የምርምሩ ጠቀሜታ የምርምሩን ግብ ያመለክታል፡፡
ምርመር የሚካሄደው ለችግር መፍትሄ ለመሻት አዲስ
እውቀት ለማፍለቅ ወይም ፕሮግራችንና ፖሊሲዎችን
በመገምገም አዋጭነታቸውንና ቀጣይነታቸውን ለመወሰን
ነው፡፡ ምርምር የሚያስገኘው ፋይዳ በአግባቡ ሳይታወቅ
የሚካሄድ ከሆነ ጠቀሜታው ባዶ ነው፡፡ ተመራማሪው
ምርምሩን ለማካሄድ ለምን አስፈለገው? ምንድን ነው ጥናቱን
ለማካሄድ ያነሳሰው ጉዳይ? ባይጠና ምን ችግር ሊያመጣ
ይችላል? የምርምሩ ውጤት ለማን ይጠቅማል? ለተጠኝዎቹ
እንዴት ለፖሊሲ አውጭዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች? በምን
መልክ? ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥበት ክፍል የምርምሩ
ጠቀሜታ ነው፡፡
1.6 የጥናቱ ወሰን(Delimitation of the study)
የጥናትን ክልል መወሰን ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ሆኖ ይገኛል፡፡ በሚገባ
ከታሰበበት ግን አስቸጋሪነቱ ጎልቶ አይታይም፡፡ የአንድ ጥናት ርዕስ
በሚገባ ከተገለጸ በኋላ በርዕሱ ስለተገለፀው ጉዳይ የተለያዩ ገፅታዎች
በአንድ ጊዜ ማጥናት አስቸጋሪ ይሆን ይሆናል፡፡ የአንድን የትምህርት
ችግር ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለማጥናት ሲሞክር ምርምሩ ከጥልቀት
ይልቅ ስፋት ብቻ ስለሚኖረው እያንዳንዱ የችግሩ ነጥብ በቂና ጠንካራ
ምርምር ሳይደረግበት ይቀራል፡፡ ይህ እንዳይሆን የትምርት ባለሙያዎች
ያላቸውን ጊዜ፣ ገንዘብ፣ አቅም ፣ ችሎታ፣ አስፈላጊ መሳሪያዎችና
ግብዓቶች እንዲሁም ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስችላቸውን መረጃ
ለመሰብሰብ ያለውን አመቺነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የጥናታቸውን
ክልል መወሰን አለባቸው፡፡
ለዚህም አጥጋቢ መግለጫ የሚሰጠው በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር ነው፡፡
የሚከተሉትን ርዕሶች እንደምሳሌ ወስደን እንመልከት
• የመዋዕለ ህፃናትን ትምህርት ለማስፋፋት ያጋጠሙ ችግሮች
• ይህ ርዕስ ሰፊ በመሆኑ ብዙ ጊዜና ገንዘብ እንዲሁም ከፍተኛ ችሎታና
የምረምር ብቃት ይፈልጋል፡፡ በውስጥም የሚነሱ ጥያቄዎች ብዙ
ስለሚሆኑ ከዛም በላይ በውስጡ ብዙ ተለዋዋጮች ስለሚኖሩ
ለምርምር አመቺ አይደለም፡፡ የሚከተሉትን ርዕሶች ደግሞ
እንመልከት፡፡
• በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዋዕለ ህፃናትን ለማስፋፋር ያጋጠሙ
ችግሮች (በቦታ መከለል)
• በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1984 ዓ/ም ወዲህ መዋዕለ ህፃናትን
ለማስፋፋት ያጋጠሙ ችግሮች (በጊዜ መከለል)
• በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ መዋዕለ ህፃናት የሚያስተምሩ
መምህራን ችግሮች(በሁኔታ መከለል)
1.7 ጥናቱ ሲጠና ያጋጠሙ ችግሮች(Limitation of the study)
በጥናትና ምርምሩ ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን መዘርዘር
• ጥናቱ በሚደረግበት ወቅት የሚፈለገውን መረጃ በተሟላ ሁኔታ
በማግኘት በኩል በገንዘብ፣ በማቴሪያልና በጊዜ አንፃር ችግር
ሊያጋጥም ስለሚችል በጥናቱ ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን
መጥቀስ አስፈላጊ ነው፡፡
1.8 በጥናትና ምርምሩ የተካተቱ ሙያ ነክ ቃላትን መግለፅ(Key
words)
• በምርምሩ ውስጥ ቁልፍ የሆኑ ቃላት በምርምሩ አግባብ ምን
ትርጉም እንዳላቸው ቀድሞ የሚገለፅበት ክፍል ነው፡፡
1.9 የጥናቱ አወቃቀር
• ምርምሩ ስንት ክፍሎች እንዳሉትና በውስጣቸውም ምን ምን
ነገሮችን እንዳካተተ የሚገለፅበት ክፍል ነው፡፡
ምዕራፍ ሁለት
2.የተዛማጅ ፅሁፍ አዘገጃጀት(Related litreatures)
2.1 የተዛማጅ ፅሁፍ አስፈላጊነት ጥቅም
ተገቢና ጥሩ ትርጉም የሚሰጥ የምርምር ስራ የሚመዘነው
በጥንቃቄ በተቃደና በተዘጋጀ የጥናት ንድፍ ሲታገዝ ነው፡፡
ይህ ማከናወን የሚችለው በመጀመሪያ ደረጃ ከሚጠና ርዕሰ
ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የፅሁፍ ጥንቅር ሲኖሩ ነው፡፡
እነዚህም ከተለያዩ መፃህፍት፣ መፅሄቶች፣ ሰነዶች፣ የጥናት
ሪፖርቶች፣ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሀሳቦች ማጠናቀር
ይገባል፡፡ በሂደትም ተመራማሪዎች በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀትና
ግንዛቤ ያገኛሉ፡፡ የጥናቱን ንድፍ በአግባቡ ያዘጋጃሉ፡፡
እንዲሁም በመጨረሻ የጥናቱን ግኝቶች በጥንቃቄ ለመተርጎም
ያስችለዋል፡፡
• በአጠቃላይ ቀደም ሲል የተሰሩ ጥናቶችን ገምግሞና መርምሮ ተዛማጅ
ሀሳቦችን ማሰባሰብ የሚከተሉትን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድግ
ይጠቅማል፡፡
• የምርምር ርዕስን/ችግሮችን/ በአግባቡ ለመምረጥና ለመወሰን
• የጥናቱን መላምቶች ወይም መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመቅረጽ
• የጥናቱን ንድፈ ሀሳብ ለመወሰን
• ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስችሉ የጥናት ዘዴዎችን፣ የናሙና አመራረጥ፣
የመረጃ መሰብሰቢያና የአተናተን ስልቶች ለመወሰንና በአንፃሩ
ውጤታማ ያልሆኑ የአጠናን ዘዴዎችን ላለመድገም፣
• ቀደም ሲል በተካሄዱ ጥናቶች የሚታዩ የዕውቀት ክፍተቶችን
ለመሙላትና (ለማጥበብ) በጉዳዩ ላይ ሰፊና በቂ ግንዛቤ ለመጨበጥ
• የአንድን ጥናት ግኝት ለመገምገም ጥናቱን በሌላ ጊዜ፣ ቦታ ናሙና
በማካሄድ ተመሳሳይ ግኝት ላይ መደረሱን ለማወቅና ለመግለፅ፣
• በአንድ ባህልና አካባቢ የተደረገ ጥናት ውጤቱ ምን ያህል በሌሎች
አካባቢዎች ተግባራዊ መሆን መቻሉን ወይም አለመቻሉን ለመገንዘብ፣
• አጥኚው የራሱን ስራ ከሌሎች መሰል የምርምር ስራዎች ጋር አወዳድሮ
ለመገምም፣
• ከተለያዩ የመረጃ ምንጮቸ ጋር ለመተዋወቅ፣ የዕውቀት አድማስ
ለማስፋትና በምንም መልኩ አላስፈላጊ ድግግሞሽን ለማስወገድ
ይጠቅማል፡፡
• የተዛማጅ ፅሁፍ ምንጮች
• ለትምህርት ጥናትና ምርምር ስራ የሚረዱ ተዛማጅ ፅሁፎችን የተለያዩ
መፅሀፍት፣መፅሄቶች ጋዜጦች፣ ሰነዶች ወዘተ. . . ስናሰባስብ
የወሰድናቸው ሀሳቦች ጥቅሶች ከነምንጫቸው መያዝ ያስፈልጋል፡፡
ይኸውም የደራሲውን ስም፣ የፅሁን ርዕስ፣ የታተመበትን ቦታ፣
አሳታሚውን፣ የታተመበትን ጊዜና የመሳሰሉት በአግባቡ ተመዝግበው
መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡
2.2የተዛማጅ ፅሁፍ አዘገጃጀት ቅድመ ሁኔታዎች
ለማንኛውም የት/ት ጥናትና ምርምር ስራ ተዛማጅ ፅሁፎች ከተሰበሰቡ በኋላ
ለመዋስ የምንፈልጋቸውን ሀሳቦች ከመፃፋችን በፊት ልናስተውላቸውና
ቅድመ ዝግጅት ልናደርግባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ፡፡ እነዚህም
ሀ/ በቂ የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ
ለ/ እቅድ መስራት
ሐ/ ተዛማጅ ፅሁፎችን ማሳጠር እንጂ አለመቅዳት
ከተዛማጅ ፅሁፍ የሚወሰድ መረጃ አያያዝና የማስታወሻ አወሳሰድ
አጥኚዎች ከተዛማጅ ፅሁፍ ላይ ስለሚወስዷቸው መረጃዎችና ማስታወሻዎች
ትኩረት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት የተገኘው መረጃ በሌላ
ጊዜ ሲፈለግ ለማግኘት የበለጠ አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር
ይችላል፡፡ ይህም ሊከሰት የሚችለው የመረጃ አያያዝና የማስታወሻ አወሳሰድ
ዘዴዎች ስርዓት ያላቸውና የተሟሉ ባለመሆናቸው ነው፡፡
ምዕራፍ ሦስት
3. የጥናቱ አሰራር ዘዴ(Methodology of the study)
3.1.መረጃ ፣የጥናቱ ተሳታፊዎች ናሙና
መረጃ ምንድን ነው?
ለመረጃ ምንጭነት የምንጠቀምባቸው ሰዎች ወይም ቁሳቁሶች በሁለት አበይት ክፍሎች
ይመደባሉ፡፡ እነዚህም ቀዳሚ እና ሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ይባላሉ፡፡
ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ አንድ ድርጊት ስለመከናወኑ በተግባር ተገኝተው ያዩ ወይም
የተሳተፉ ስለድርጊ የሚሰጡትን ቀጥተኛ አስተያየት ወይም ምስክርነት መሰረት
ያደረገ ነው፡፡
ምሳሌ፡- አጥኚው በፅሁፍ መጠይቅ፣ በቃለመጠይቅና በምልከታ የሚያገኛቸው
መረጃዎች ማለትም፡- የአይን ምስክሮች ቅርፃ ቅርፆች፣ ህገ መንግስት፣ ቃለ ጉባዔ፣
ፖሊሲዎች በግለሰቦች በራሳቸው የተፃፉ የህይወት ታሪኮቻቸው ወዘተ. .
ሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮች በአብዛኛው በምሁራን የተፃፉ ፅሁፎች፣ መፅሄቶች፣
መፃህፍት ወዘተ. . . ሲሆኑ ከቀዳሚ የመረጃ ምንጮች ለየት የሚያደርጋቸው ባህሪ
በየህትመቱ ውስጥ የተገለፁት ጉዳዮችና ክንውኖች በመረጃ አቅራቢ ቀጥተና
ምልከታ ተሳትፎና እማኝነት የተደረጉ አለመሆናቸው ነው፡፡
የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች፣ አስፈላጊነትና አመራረጥ
• ማናቸውም የት/ት ጥናትና ምርምር እንቅስቃሴ እንደምርምሩ
ባህሪ፣ ጥልቀትና ስፋት የራሱ የሆነ የመረጃ መሰብሰቢያ
መሳሪያዎችና ስልቶች ያስፈልጉታል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ
መሳሪያዎች ከአዘገጃጀት፣ ከአጠቃቀምና፣ መረጃዎችን
ከመተርጎም አንፃር ሲታዩ ከቀላል እስከ ውስብስብ የመረጃ
መሰብሰቢያ ዓይነቶች ውስጥ ሊፈረጁ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ
የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ ለታለመለት ዓላማ በሚገባ
እንዲያገለግል ከሚጠናው ጥናት ዓላማ ጋር ጥብቅ ቁርኝት
ያስፈልገዋል፡፡ ይህም ሲሆን ነው መሳሪያው ተፈላጊውን
አሃዳዊም ሆነ ሐተታዊ መረጃ ሊያስገኝ የሚያችለው፡፡
• የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች የሚፈለግባቸውን ተግባር እንዲወጡ ሁለት
መሰረታዊ ነጥቦች ማሟላት አለባቸው፡፡
• ሀ/ የመሳሪያዎቹ ተፈላጊውን መረጃ የመሰብሰብ አቅም መሟላት አለበት
• ለ/ መሳሪያዎቹ ተፈላጊውጀን መረጃ በትክክል መሰብሰብ መቻል አለባቸው
• በምርምር ሂደት እንደምርምሩ ዓይነት እንደሚጠናው ችግር ሁኔታ
እንደተመራማዊው ችሎታ፣ ተመራማሪው ምርምሩን ለማካሄድ እንዳለው
የገንዘብና የጊዜ መጠን፣ የስልጠና የፍልስፍና ሁኔታ ለመረጃ መሰብሰቢያነት
የሚያገለግሉ በርካታ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች አሉ ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ
የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ/ የፅሁፍ መጠይቅ
ለ/ የቃል መጠይቅ
ሐ/ ምልከታ
መ/ መዛግብት
ሠ/ የተለያዩ ፈተናዎች
ረ/ ቡድን ተኮር ውይይት
3.2 .የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች አዘገጃጀት(Data instrument)
• ሀ/ የፅሁፍ መጠይቅ
• በትምህርት፣ በሶሻል ሳይንስ፣ በጤና፣ በፖለቲካ ሳይንስ፣ በስነ ባህሪና በሌሎች በርካታ የምርምር
መስኮች ምናልባት ከሁሉም የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች የበለጠ ጥቅም ላይ የሚውለው የፅሁፍ
መጠይቅ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል የሚከተሉት በዋነኛነት ሊጠቀሱ
ይችላሉ፡፡
• ጊዜ ቆጣቢ ነው
• የመላሾችን ማንነት ስለማይገልፅ መላሾቹ አስተማማኝ መረጃ እንዲሰጡ ሊያበረታታቸው ይችላል፡፡
• ለሁሉም ተጠኚዎች አንድ ዓይነት ጥያቄ ያቀርብላቸዋል
• ከብዙ ሰዎች መረጃን ለመሰብሰብ ከሌሎች መሳሪያዎች ይልቅ ምቹነት ስላለው
• ሰዎችን በግንባር ለማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ የፅሁፍ መጠይቆችን በፖስታ ወይንም በኢሜል
በመላክ እንዲሞሉና አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በማድረግ መረጃ ለመሰብሰብ ስለሚያስችል
ነው፡፡
• የፅሁፍ መጠይቅ ሲዘጋጅ ሶስት መሰረታዊ እሳቤዎችን መሰረት በማድረግ ነው፡፡
• መላሾች ጥያቄዎችን በማንበብና በመረዳት መልስ መስጠት እንደሚችሉ በማመን፣
• መላሾች መረጃዎችን መሰረት አድርገው ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ስለሚገመት
• መላሾች መረጃውን በፈቃደኝነትና በሃቀኝነት እንደሚሰጡ መታመኑ ናቸው፡፡
የፅሁፍ መጠይቅ ሲዘጋጅ ከዚህ በታች የተቀመጡትን መመሪያዎች ታሳቢ
ማድረግ ይገባል፡፡
ሀ/ ጥያቄዎች ሲቀረፁ የጥናቱን ዓላማና መሰረታዊ ጥያቄዎች/መላምት/ ግብ
ለመምታት በሚያስችል ደረጃ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በአጭሩ ከጥናቱ ርዕስ
ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ብቻ መፃፍ ይገባል፡፡
ለ/ ጥያቄዎች በአጫጭር አርፍተ ነገሮችና በቀላል ቋንቋ መቅረብ
ይኖርባቸዋል
ሐ/ ጥያቄዎቹ በቅደም ተከተል መቀመጥ አለባቸው
መ/ ጥያቄዎቹ ግልፅና የማያሻሙ መልሶችን ለመስጠት የሚያስችሉ መሆን
ይገባቸዋል፡፡
ሠ/ ጥያቄዎች የፈተናነት ባህሪ ኖሯቸው መላሹን የሚያስጨንቁ ሆነው
መቅረብ አይኖርባቸውም፡፡
ረ/ መልስ ሰጪዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሊሰጡ የሚችሉትን የተሳሳተ
መልስ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ጥያቄዎች በመጠይቁ ውስጥ መካተት
አለባቸው፡፡
ሰ/ ስለመላሾች ፆታ፣ ዕድሜ፣ የት/ት ደረጃ፣ ስራ፣ የጋብቻ ሁኔታ የመኖሪያ አካባቢ
ወዘተ. . . አጭር መግለጫ መካተቱን ማረጋጥ
ሸ/ ለጥያቄዎች የሚሰጡ መልሶች አጫጭር ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ምርጫ የሌላቸው
ጥያቄዎች አጫጭር መልስ ሊቀርብባቸው የሚችሉ ዓይነት ቢሆኑ የተሻለ ነው፡፡
የፅሁፍ መጠይቅ ሲዘጋጅ ሶስት አይነት አቀራረብ አለው
1. ዝግ ጥያቄዎች
ዝግ ጥያቄዎች ስማቸው እንደሚያመለክተው ተመራማሪው ለመላሾቹ ጥያቄዎችን
ይፅፍና ከጥያቄዎቹ ጋር ከሚገኙ አማራጮች መካከል የነሱን ሀሳብና እምነት
ሊያመለክት ወይም ሊወክል ይችላል ብለው የሚያስቡትን በመምረጥ
የሚመልሱበት ነው፡፡
2. ልቅ /ነፃ/ ጥያቄዎች
ልቅ ወይም ነፃ ጥያቄዎች ተመራማሪው ጥያቄዎቹን ብቻ ለመላሾች አቅርቦ መልስ
ከራሳቸው ለማግኝ የሚጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ በዚህ የጥያቄ ዓይነት ጥያቄውን
ተከትለው የሚቀርቡ አማራጮች የሉም፡፡ መላሾቹ ነፃ ሆነው በተነሳው ጥያቄ ላይ
የራሳቸውን አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና ወዘተ. . . ባሻቸው መንገድ
የሚገልጡበት በመሆኑ የመመለሻ ነፃነታቸው አይገደብም፡፡
3. ቅይጥ ጥያቄዎች
ቅይጥ ጥያቄዎች የሚባሉት ተመራማሪው ዝግና ልቅ ጥያቄዎችን
በማቀላቀል ሲጠቀም ነው፡፡ አንዳንድ የምርምር ርዕሶች በባህሪያቸው
የነዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን ለመጠቀም የሚያስገድድበት ወይም
የሚያስችልበት ሁኔታ አለ፡፡ በተቻለ መጠን እነዚህን ጥያቄዎች
መጠቀሙ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
ለ/ ቃለ መጠይቅ
ቃለ መጠይቅ በቃል የሚርብ የመጠይቅ ዓይነት ነው፡፡ ከፅሁፍ መጠይቅ
የሚለየው በመላሹና ቃለ መጠይቁን በሚያካሂደው ሰው መካከል የፊት
ለፊት የቃል ምልልስ በመኖሩ ነው፡፡ ጠያቂው ጥያቄዎቹን ለመላሹ
ያቀርባል፣ ያብራራል፣ ከመላሹ ጋር ፊት ለፊት ሆኖ የተቻለውን ያህል
መረጃ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል፡፡ መላሹ ደግሞ ለተጠየቀው ነገር
መልሱን በቃል ይሰጣል፡፡ ተመራማሪው ቃለ መጠይቁን እንደመረጃ
መሰብሰቢያነት ለመጠቀም ከወሰነ ከሚከተሉት ዓይነቶች በአንዱ፣
በሁለቱ ወይም በሁሉም መጠቀም ይችላል፡፡ እነሱም
1. ውስን ቃለ መጠይቅ
ተመራማሪው ለመላሹ የሚያቀርበው ጥያቄ ቀድሞ የተፃፈና ከዚያ ውጭ
የማይጨመርበት ሲሆን ለመልስ የሚሆኑ አማራጮችንም ያካትታል፡፡
ተመራማሪው የሚፈልገውን መረጃ ላገኝበት እችላለሁ ብሎ የሚያስበውን ጥያቄ
ቀድሞ በመወሰን መልሶቹ ደግሞ እነዚህ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ የሚገምታቸውን
ከጥያቄው ስር በመዘርዘር አሊያም ጥያቄዎችን በውስን መልሶች እንዲመለሱ
አድርጎ በማዘጋጀት ለተጠያቂዎቹ ያቀርብላቸዋል፡፡ መላሹም ከተሰጡት ውስን
መልሶች መካከል እየመረጠ ይመልሳል እንጂ እንደፈለገ ሊናገር አይችልም፡፡
በመሆኑም ጥያቄ እያነሳ ለመጠየቅ እድል አይሰጠውም፡፡
2. በከፊል ነፃ ቃለ መጠይቅ
ይህ ከነፃ የፅሁፍ ቃለ መጠይቅ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ከፊል ነፃ የተባለበት
ምክንያት መላሹ የራሱን ሀሳብ ለመስጠት ነፃ የሚያደርገውና በተወሰኑ
አማራጮች ተገድቦ የግድ ሀሳብን እንዳይገልፅ ማዕቀብ የሚያደርግበት
አይደለም፡፡ ሆኖም ጠያቂው ከተፃፈው ጥያቄ ወጣ እያለ ሌሎች ከዋናው ጥያቄ
ጋር ተዛማጅነት ሊኖራቸው የሚችሉ ጥያቄዎችን እያነሳ ለመጠየቅ እድል
አይሰጠውም፡፡
3. ነፃ/ልቅ/ ቃለ መጠይቅ
ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ነፃነትን ለመላሹም ለተመራማሪውም ይሰጣል፡፡
በዚህ ቃለ መጠይቅ ጠያቂው በሚጠይቀው ችግር ዙሪያ ጠቃሚ መረጃ
ያስገኙኛል ብሎ የሚያስባቸውን ጥያቄዎች በፈለገውና ለተጠያቂው ይመቻል
ብሎ ባሰበው መንገድ ማቅረብ የሚችልበት፣ ተጠያቂው ደግሞ ነፃና መልስ
ይሆናል ብሎ የሚገምተውን ያመነውን መረጃ የሚሰጥበት ነው፡፡ ነፃ ቃለ
መጠይቅ በአብዛኛው ጥያቄዎችን በወረቀት በመፃፍ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡
ቃለ መጠይቅ በጠያቂና በተጠያቂ መካከል የሚደረግ ግንኙነት እንደመሆኑ
መጠን ተፈላጊውን መረጃ ለማግኘት ጠያቂው ሊያደርጋቸው የሚገቡ ነገሮች
አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚገኘውን መረጃ ተአማሚነት፣ አስተማማኝነት
ትክክለኛነት በእጅጉ ይወስኑታል በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ ቃለ
መጠይቅ በሚካሄድበት ወቅት ሊደረጉ ከሚገቡ ነገሮች መካከል የሚከተሉት
ይገኛሉ፡፡
አለባበስ
አቀራረብ
• ገለፃ
• መልሱን መፃፍ ወይም በቴፕ አለመለዋወጥ
• የመላሹ ትኩረት ወደ ጥያቄው ማድረግ
• መጠይቁ አድካሚ መሆን የለበትም
• ምስጋና ማቅረብ
ሐ/ የምልከታ ዘዴ መረጃ ሰብሳቢው ሰው መረጃ ለመሰብሰብ ከሚፈለግባቸው
ተጠኝዎች ጋር ወይም አካባቢ በመሆን የሚያደርጉትንና የሚናገሩትን ነገር
በቅርበት ሆኖ እያየና እየሰማ በመመዝገብ መረጃ የሚሰጥበት ዘዴ ነው፡፡
ተመራማሪው ተጠኚዎቹ (እያወቁም ሆነ ሳያውቁ) በሚገኙበት ቦታ በመሆን
በዚያ ወቅት ምን እንደሚሰሩ፣ እንዴት እንደሚሰሩ፣ እርስ በእርሳቸው እንዴት
እንደሚገናኙ፣ ምን እንደሚናገሩ ወዘተ. . . ራሱን በሚመቸው፣ አስተማማኝና
ትክክለኛ መረጃ በሚያስገኝበት መንገድ መረጃ የሚሰበሰብበት ዘዴ ነው፡፡
• ተመራማሪው ምልከታን በሚጠቀምበት ወቅት የሚመለከተውን ነገር በሚገባ
መመዝገባ ይኖርበታል፡፡ ምዝገባ በሚያካሂድበት ጊዜ የሚከተሉትን የምልከታ
አመዘጋገብ አይነቶች መጠቀም ይችላል፡፡
1.የጊዜ ርዝማኔ ምዝገባ
• በዚህ የምልከታ አመዘጋገብ ዘዴ ተመራማሪው የሚመለከተውን ባህሪ
ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ በሴኮንድ ወይም በደቂቃ ወይም በሰዓት
ሊገልፅ ይችላል፡፡
2. የድግግሞሽ ቆጠራ ምዝገባ
• ተመራማሪው ፍላጎቱ አንድ ባህሪ ለምን ያህል ጊዜ እንደተከሰተ ማወቅ
ሳይሆን ምልከታው በተካሄደበት ወቅት ያባህሪ ስንት ጊዜ ተደጋግሞ
እንደተከሰተ እየቆጠረ ሲመዘግብ የድግግሞሽ ቆጠራ ምዝገባ ይባላል፡፡
3. የግድብ ጊዜ ምዝገባ
• ተመራማሪው የሚመለከታቸውን ሰዎች ወይም ነገሮች በተወሰነ የጊዜ
ገደብ ውስጥ ለመመልከት የፈለገውን ባህሪ ስንት ጊዜ እንዳሳዩ መመዝገብ
ነው፡፡
4. ተከታታይ ምልከታ ተመራማሪው ይህን ዘዴ ሲጠቀም የሚያጠናው
ባህሪ ረዘም ላለ ጊዜ ይከታተለዋል፡፡
መ. መዛግብት
• ተመራማሪው ስላለፈም ይሁን ወቅታዊ ስለሆነ ጉዳይ መረጃ ለመሰብሰብ
ሲነሳ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ጠቃሚ ነገሮች መዛግብት በፅሁፍ መልክ
ከየቤተ-መጽሀፍቱ፣ ቤተ-መዛግብቱ ወይም ከሌሎች ቦታዎችና
እንደሁኔታውም ከግለሰቦች ሊገኙ የሚችሉ የመረጃ ምንጮች ናቸው፡፡
በዓይነታቸው ግልጽ የሆኑ ወይም ያልሆኑ፣ የህዝብ የሆኑ ወይም
ያልሆኑ፣ ወይም የግል ጉዳዮችን የያዙ የታተሙ ወይም ያልታተሙ
እንዲሁም ታሪካዊ ወይም ወቅታዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ደብዳቤዎች፣
የንግግር ረቂቆች፣ የግለሰቦች የዕለት ማስታወሻዎች፣ ቃለጉባኤዎች፣
አዋጆች፣ ደንቦች፣ህጎች፣ ዓመታዊ ዘገባዎች፣ የግል የህይወት ታሪኮች፣
ደረሰኞች የተማሪዎች የት/ት ውጤቶች፣ ያለፉ ፈተናዎች፣ ካርታዎች፣
ጆርናሎች፣ ጋዜጦች፣ መፃህፍት፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ፣ የተለያዩ
መ/ቤቶች ልዩ ልዩ ዘገባዎችና ሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች በፅሁፍ
መልክ ተዘጋጅተው የሚገኙ ሁሉ በመዛግብት ስር ይካተታሉ፡፡
ተመራማሪው አንድን መዝገብ ለመረጃ ምንጭነት ለመጠቀም በሚወሰንበት
ወቅት የትና እንዴት ሊያገኘው እንደሚችል በቅድሚያ ጠንቅቆ ሊያውቅ
ይገባል፡፡ ተመራማሪው መዛግብትን ለመጠቀም ሲነሳ እውነተኝነታቸውንና
ተአሚኒነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ መዛግብቱ ያልተበረዙ፣
ያልተከለሱ፣ ስህተት ያላጎደፋቸው ያልተዛቡ መሆናቸውን ከግለሰባዊነት
በፀዳ መልኩ ሊገመግማቸው የግድ ነው፡፡
ሠ. የተለያዩ ፈተናዎች
• መረጃ ለመሰብሰብ ከሚያግዙ በርካታ ዘዴዎች መካከል ፈተናዎች ጉልህ
ስፍራ ይዘው ይገኛሉ፡፡ ፈተና ማለት የተወሰኑ ጥያቄዎች ተዘጋጅተው
ወጥነት ባለው መንገድ የተፈታኞችን አእምሮአዊ ወይም ስነ ባህራዊ ሁኔታ
አስመልክቶ መረጃ ለመሰብሰብ የሚረዳ መለኪያ ነው፡፡ እዚህ ላይ ወጥነት
ሲባል ፈተናው ለጥናቱ ተሳታፊዎች የሚሰጠው በተመሳሳይ ሁኔታ ማለትም
በተመሳሳይ የጊዜ ገደብ፣ የአፈታተንና የአስተራረም መንገድ ፣ ተመሳሳይ
የመልስ አሰጣጥ መልክና መመሪያ ከተቻለም በተመሳሳይ ፈተኝ ወይም
ተቀራራቢ የአፈታተን ብቃት ባለቸው ሰዎች የሚካሄድ መሆኑን
ለማመልከት ነው፡፡
ረ. ቡድን ተኮር ውይይት
በቡድን ተኮር ውይይት የሚካሄደው በችግሩ ዙሪያ በቂ መረጃ ሊኖራቸው
ይችላሉ ተብሎ የሚታሰቡ ሰዎችን በመውሰድ በሚነሳው ጥያቄ ዙሪያ
በቡድን በመሆን እየተወያዩ መረጃ እንዲሰጡ ለማድረግ ሲሆን፣
ተሳታፊዎች እስከ 12 ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ዘዴ የቡድን ቃለ
መጠይቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ከቃለ መጠይቅ የሚለየው
ዋናው ነጥብ በርካታ ሰዎች በአንድ ጊዜ መሳተፋቸውና ጠያቂው
የተገደበ ሚና ያለው መሆኑ ነው፡፡
3.3.የናሙና አመራረጥ ዘዴዎች(Sampling method)
• ናሙና ስንል በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተነሳ የጥናቱን አካላይ አባላት
በሙሉ በመውሰድ በጥናታችን ተሳታፊ ለማድረግ ሳንችል ስንቀር
ወይም ማሳተፍ አስፈላጊ ሳይሆን ሲቀር ነገር ግን አጠቃላዪን ብንወስድ
ልናገኝ እንችላለን ብለን የምናስበውን መረጃ ሊሰጡን የሚችሉ
ሰዎች/ነገሮች/ ስርዓታዊና ተጠያቃዊ መንገዳችን የጥናቱ አካላይ ውስን
ክፍል ናቸው፡፡
• ጥናትና ምርምር በናሙና ወይም ያለናሙና ዘዴ በማካሄድ የመረጃ
አሰባሰብ ስራን ይከናወናል፡፡ ያለናሙና የሚካሄድ ጥናት ምርምሩ
የሚካሄድባቸውን ነገሮች ሙሉ በሙሉ በመውሰድ የሚደርግ የመረጃ
አሰባሰብ ዘዴ ሲሆን የናሙና አመራረጥ ዘዴ ግን በጥናቱ ውስጥ
ሊካተት የሚገባቸው ነገሮች ወይም ሰዎች ብዛት ያላቸው ሆነው
ሁሉንም ለማካተት በማይቻልበት ጊዜ ወካይ የሆኑ ቁጥሮችን ወስዶ
መረጃ ለማሰባሰብ የሚቻልበት ዘዴ ነው፡፡
የምርምር መረጃ ለመሰብሰብ ናሙና በሚመረጥበት ጊዜ የሚከተሉትን መንገዶች መከተል
ይገባል፡፡
• ጥናቱ የሚያቅፋቸውን ሰዎች ጂኦግራፊያዊ ክልሎች፣ ፆታ፣ ሀይማኖት፣ የት/ት ደረጃ
ስራ ወዘተ. . .
• ጥናቱ ከሚያቅፋቸው ሰዎች ውስጥ ናሙናዎችን መምረጥ ናቸው፡፡
• ለአንድ ለታቀደ ጥናት የናሙና ብዛት ምን ያህል መሆን አለበት? ለሚለው ሁሉን
የሚያግባባ የወጣ ደንብ የለም፡፡ ሆኖም ናሙናው በበዛ ቁጥር የጥናቱ አስተማማኝነት
የዛኑ ያህል ከፍተኛ ይሆናል፡፡
• በአጠቃላይ የናሙና ብዛት ለመወሰን የሚከተሉትን ሶስት ነጥቦች ማጤን ያስፈልጋል፡፡
• ጥናቱ የሚደረግበት ጉዳይ ባህሪ፣
• የምርምሩ ስፋት፣
• የሚፈለገው የጥናት መረጃ የትክክለኛነት ደረጃ ማወቅን ይጠይቃል፡፡
• የናሙና አመራረጥ ዘዴዎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡ እነሱም እኩል ዕድል
የሚሰጥ ናሙናና እኩል እድል የማይሰጥ ናሙና ናቸው፡፡
እኩል እድል የሚሰጥ ናሙና
• እኩል እድል የሚሰጥ ናሙና አመራረጥ ምርምሩ የሚያቅፋቸው ሰዎች ወይም
ሌሎች ምርምር የሚደረግባቸው ነገሮች በናሙናት የመመረጥ እኩል እድል
ይኖራቸዋል፡፡ የዚህ ዓይነት የናሙና አመራረጥ ዘዴ በአጋጣሚ የሚመረጥ
ናሙና ነው፡፡ በት/ት ምርምር በአብዛኛው ስራ ላይ የሚውሉ አራት ዓይነት
እኩል እድል ሰጪ የናሙና አመራረጥ ዘዴዎች አሉት፡፡ እነሱም
ሀ/ ተራ የእጣ ናሙና
• ተራ የእጣ ናሙና በሚወሰድበት ወቅት የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን
ተገቢ ነው፡፡
• ጥናቱ የሚያቅፋቸውን ሰዎች ወይም ሌሎች ነገሮች መለየት፣
• ከላይ የተጠቀሱትን በተራ ቁጥር ዘርዝሮ መፃፍ፣
• የናሙናውን ብዛት መወሰን
• እጣ ማውጣትና እጣ የወጣላቸውን ናሙናዎች መመዝገብ ናቸው፡፡
ለ/ ምድብ የዕጣ ናሙና
• ጥናቱ የሚያቅፋቸውን ሰዎች የተለያየ ባህሪ ማለትም ወንድ ፣ ሴት፣ እድሜ፣ ወዘተ
የሚያመለክት መረጃ የሚፈልግ ከሆነ በምድብ የዕጣ ናሙና መጠቀም ተገቢ ይሆናል፡፡
• ምድብ የዕጣ ናሙና በሚወሰድበት ጊዜ
• ጥናቱ የሚካሄድባቸው ሰዎች ወይም ሌሎች ነገሮች መለየት፣
• የናሙናን ብዛት መወሰን፣
• ጥናቱ የሚካሄድባቸውን ሰዎች ወይም ሌሎች ነገሮች እንደየባህሪያቸው በቡድን መክፈል፣
• ከእያንዳንዱ ቡድን በተራ የዕጣ ናሙና አመራረጥ ዘዴ በተጠቀምንበት ስልት ናሙናዎቹን
መውሰድ ናቸው፡፡ ለቡድን ክፍፍሉ መነሻነት ከሚሆኑት ውስጥ
• የተለያየ ጂኦግራፊያዊ ክልል፣
• ገቢ
• ዕድሜ
• ስራ
• የት/ት ደረጃና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
• በዚህ ዓይነቱ የናሙና አመራረጥ ከእያዳንዱ ቡድን ተመሳሳይ ብዛት ያለው ናሙና ወይም
በየቡድኑ እንዳለው የስብስብ ብዛት በተመጣጣኝ ናሙናውን መውሰድን የሚያመለክት ነው፡፡
ሐ/ የቡድን ናሙና
• የቡድን ናሙና ብዙውን ጊዜ የሚያካሄደው ናሙና የሚወስድባቸውና ጥናቱ
የሚካሄድበት ጉዳይ በተበታተነ ሁኔታና በቀላሉ ለመድረስ በጊዜ፣ በገንዘብና
በሰው ኃይል አስቸጋሪ መሆኑ ሲታወቅ ነው፡፡ በቡድን የናሙና አመራረጥ
ግለሰቦች በተናጠል የሚመረጡ ሳይሆን የሚመረጡት ስብስቦች ናቸው፡፡
ምክንያቱም የሚመረጡት ስብስቦች አንድ ዓይነት ባህሪ ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡
• የቡድን ናሙና ሲመረጥ የሚከተሉትን ማጤን ይገባል፡፡ እነሱም፡-
• በጥናቱ የታቀፉተን ሰዎች ወይም ሌሎች ነገሮች መለየት፣
• የናሙናውን ብዛት መወሰን፣
• በጥናቱ የታቀፉት ሰዎች የሚገኙበትን ስብስብ መለየት፣
• ስብስቦቹን በዝርዝር በተራ ቁጥር መፃፍ፣
• በእያንዳንዱ ስብስብ ያሉትን ሰዎች ብዛት ማወቅ፣
• የሚፈለገውን የስብስብ ናሙና ብዛት ከአጠቃላይ የናሙና ብዛት ጋር ማካፈል፡፡
• የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት፣
በአንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ፡-
• 1000 መምህራን በጥናቱ ቢታቀፉ፣
• የናሙናውን ብዛት 200 ቢሆን፣
• እነዚህ መምህራን በት/ቤት ቢከለሉና 60 ት/ቤቶች ቢኖሩ፣
• የሚፈለገውን የስብስብ ናሙና ብዛት ከአጠቃላይ የናሙና ብዛት ጋር
ማካፈል፡፡ይህ ማለት ከ200 ናሙና ሲካፈል ለ60 ት/ቤት=3.33
• ከ60 ት/ቤቶች 3ቱን በመምረጥ መረጃ መሰብሰብ ይቻላል፡፡
• መ/ በስርዓት የተደራጀ የናሙና አመራረጥ
• በስርዓት የተደራጀ የናሙና አመራረጥ ሂደት፣
• ጥናቱ ያቀፋቸውን ሰዎች በዝርዝር ያለፊደል ተራ እንደተገኘ መመዝገብ፣
• የሚፈለገውን የናሙና ብዛት መወሰን፣
• የጠቅላላውን ሰዎች ብዛት ለናሙናው ብዛት ማካፈል፣
• ናሙናው የሚጀምርበትን ቁጥር ለመለየት ከ1 – 10 ካሉት ቁጥሮች
ውስጥ አንዱን በዕጣ ማውጣት፡፡ ለምሳሌ ጥናቱ ያቀፋቸው መምህራን
500 ቢሆኑና የሚፈለገው ናሙና ብዛት 50 ቢሆን የ500 መምህራን
ዝርዝር ተፅፎ ከሚገኝበት ሰንጠረዥ ውስጥ በዕጣ የወጣው ቁጥር 9
ቢሆን 9ኝን መውሰድና ቀጥሎ አስር በመደመር 19ኛውን፣
29ኛውም፣39ኛውን፣49ኛውን፣59ኛውን ወዘተ. . . በመውሰድ
ናሙናውን 50 እስኪሞላ ድረስ መቀጠልና ለጥናቱ በናሙናነት
የሚወሰዱትን ተሳታፊዎች መምረጥ ነው፡፡
እኩል እድል የማይሰጥ ናሙና
• በሚከናወነው የተግባራዊ ጥናትና ምርምር የሚታቀፉትን ሰዎች ወይም ሌሎች
ነገሮች ለመዘርዘር አንዳንድ ጊዜ ችግር ያጋጥማል፡፡ በዚህ ወቅት እኩል እድል
የማይሰጥ የናሙና አመራረጥ ዘዴን ለመጠቀም ሁኔታው ያስገድዳል፡፡ ዋና ዋናዎቹ
እኩል እድል የማይሰጡ የናሙና አወሳሰድ ዘዴዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ/ የአጋጣሚ ናሙና
• የአጋጣሚ ናሙና አወሳሰድ ዘዴ እንደ አመቺነቱ ከተገኘው ሰው ወይም ሌላ ጥናቱ
ከሚደረግበት ጉዳይ ላይ መረጃ የመሰብሰብ ዘዴ ስለሆነ ድክመቱ የጎላ የናሙና
አወሳሰድ ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ጉዳይ ላይ የአመቻቾችን አስተሳሰብ
ለመጠየቅ በድንገት የተገኘን አመቻች ቃለ መጠይቅ ማድረግ፣ ወይም በአንድ
ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች በማነጋገር ወይም ፈቃደኛ የሆኑትን ብቻ ቃለ መጠይቅ
ማድረግ የመሳሰሉትን ሁኔታዎች በመጠቀም መረጃ የመሰብሰብ ዘዴ ነው፡፡
ለ/ የታለመ ሁነኛ ናሙና
• የዚህ ዓይነቱ የናሙና አመራረጥ ዘዴ ጥናቱ ከሚከናወንባቸው ሰዎች ውስጥ
ይወከላሉ ተብለው የሚጠቀሱትን ሰዎች በመምረጥ መረጃ የመሰብሰብ ዘዴ
ነው፡፡
ምዕራፍ 4
4.መረጃ ትንተና(Data analysis)
• በዚህ ምዕራፍ ውስት የተለያዩ መረጃዎች ከተለያዩ አካላት የተገኙትን መረጃዎች
በቁጥር፤በፐርሰንት እና ዘርዘር ባሉ ሀሳቦች የተገኘውን መረጃ የምናስቀምይበት ነው፡፡
• ምሳሌ፡-/ር፣ር/መር ፣ ተማሪዎች፣፣75%፣ 50% ፣62.5% እና 37.5% በቅደም ተከተል
ምላሽ ሲሰጡ ውጤታማ ነው ያሉ መሰጡ ውጤታማ አይደለም ያሉ አካላት 25%፣
50% ፣37.5% 62.5% መምህራን፣ር/መምን፣ ተማሪዎች እና ባለሙያዎች በቅደም ተከተል
አስቀምጠዋል፡፡
ምዕራፍ 5.ማጠቃለያ፤መደምደሚያ እና የመፍትሄ
ሀሳቦች
5.1.ማጠቃለያ(Summary)

•በማጠቃለያ ሀሳብ ከመጀመሪያ ጀምሮ


የጥናቱን ሂደት ምን እንደሚመስል
ጠቅለል ያለ ሀሳብ የሚቀመጥበት ነው፡

5.2. መደምደሚያ(Conclusion)

•በዚህ ንዑስ እርዕስ ላይ የትናቱ


የመጨረሻ ውጤቱ ዘርዘር ባለ
መልኩ የሚቀመጥበት ነው፡፡
5.3. የመፍትሄ ሀሳቦች(Recommendation)

•በዚህ ንዑስ እርዕስ ላይ በተለያዩ የመረጃ


መሰብሰቢያ ዘዴዎች የተለዩ ችግር
ተብለው የተቀመጡትን ለመፍታት
የመፍትሄ ሀሳቦች የምናስቀምጥበት ተግባር
ነው፡፡
አመሰግናለሁ!!

You might also like