You are on page 1of 20

አዋጅ ቁጥር----------፪ሺ፲፪ ዓ/ም

የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ

የአካባቢ መራቆትንና የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን በመከላከል፣ የውኃ ሀብትን በማጎልበትና


የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ የመሬት የማምረት አቅም ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ
እንዲተላለፍ እና በዚህም ለእርሻ ሥራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር በማስፈለጉ፤

የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለሥራ
ዕድል ፈጠራ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ይቻል ዘንድ ቀደም ሲል የተጀመሩትን የተፋሰስ ልማት
ሥራዎች ማስቀጠል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከፍተኛ የሰው ጉልበትና የገንዘብ ወጪ
ተደርጐባቸው እንዲለሙ የተደረገ ቢሆንም ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ የተፋሰሱ ተጠቃሚዎች
በባለቤትነት ስሜት ተረክበው የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚያስተዳድሩበት የርክክብ፣ የአጠቃቀም፣
የአጠባበቅና የተጠያቂነት አሠራር ማስፈን ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፤

የማኅበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች ያለሙትን ሀብት ለማስተዳደር፣ ለመጠቀምና ለመጠበቅ


የሚችሉበትን ሁለንተናዊ አቅም ማሳደግ በማስፈለጉ።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ፶፭/፩/ እና /፪/ (ሀ)


መሠረት የሚከተለው ታውጇል።

ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌዎች

፩/ አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ የማኅበረሰብ ተፋሰሶች፣ ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር ፪ሺ፲፪ ዓ/ም
ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

1
፪/ ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ

፩/ ”ሚኒስቴር” ማለት የግብርና ሚኒስቴር ነው።

፪/ “ማኅበር” ማለት በጋራ ፍላጐት ተነሳስተው በዚህ አዋጅ መሠረት የተደራጁና የተመዘገቡ
የማህበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች በአባልነት የታቀፉበት አካል ነው።

፫/ “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ማለት ነው።

፬/ “የማህበረሰብ ተፋሰስ” ማለት ወደ አንድ መልከዓ ምድራዊ አቅጣጫ የሚፈስሱ የገጸ


ምድርና የከርሰ ምድር ውኃዎች የሚያካልሉትን አካባቢ የሚያካትት፣ አነስተኛ ተፋሰስ
ሆኖ አማካኝ ስፋቱ ከ 500 ሄክታር የማይበልጥ የመሬት ክፍል ነው፡፡

፭/ “የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት” ማለት በማህበረሰብ ተፋሰሱ ክልለ ውስጥ የሚገኘውን


የአፈር፣ የውሃ እና የዕጽዋት ሀብት ለመጠበቅና ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚረዱ
ተግባራትን አቀናጅቶና አጣጥሞ ማከናወን ማለት ነው፡፡

፮/ “የማህበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች” ማለት በማህበር ተደራጅተውም ይሁን ሳይደራጁ


ተፋሰሱ በመልማቱ ምክንያት የሚፈጠረውን ሃብት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ
የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለት ነው፡፡

፯/ “የወል ይዞታ” ማለት በተጠቃሚዎች ስምምነት በሚተዳደር ተፋሰስ ውስጥ በግል፣


በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ያልተያዙ ይዞታዎች እና
የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ ይዞታነት የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች በመሥራት
አልምተው እንዲጠቀሙበት በመንግሥት የተሰጣቸው የገጠር መሬት ነው።

፰/ “ልዩ ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች” ማለት በማኅበራዊ፣ በጤና ወይም


በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ምክንያት መብታቸውን ለመጠየቅና ለማግኘት ችግር
የሚገጥማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።

፱/ “የተፈጥሮ ኃብት ተቋም” ማለት ተፋሰሱ በሚገኝበት አካባቢ ወይም ወረዳ የተፈጥሮ
ኃብትን ለመንከባከብ፣ ለማልማትና አጠቃቀሙን ለመወሰን የተቋቋመ መንግሥታዊ
ተቋም ነው።

2
፲/ “ተሳትፎ” ማለት በውሳኔ ሊነኩ በሚችሉ ሃብቶች ላይ ባሕላዊ ወይም ሕጋዊ መብት
ያላቸው ሰዎች በውሳኔ ሰጪነት ሂደት ውስጥ የመሳተፍ መብት ማለት ነው።

፲፩/ “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት አንቀጽ


፵፯(፩) የተመለከተው ማንኛውም ክልል ሲሆን የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ
አስተዳደሮችን ይጨምራል፡፡

፫/ የፆታ አገላለጽ

በዚህ አዋጅ ውስጥ በወንድ ፆታ የተደነገገው ለሴት ፆታም ያገለግላል።

፬/ የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ አዋጅ በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

ክፍል ሁለት
ስለ ተፋሰስ ዕቅድና ልማት

፭/ የተፋሰስ ዓይነቶች

፩/ በዚህ አዋጅ መሠረት እውቅና የተሰጣቸው ተፋሰሶች የማኅበረሰብ ተፋሰስና ዋና ተፋሰስ


ናቸው።

፪/ የማንኛውም የማህበረሰብ ወይም ዋና ተፋሰስ ስፋት ወይም መልክዓ-ምድራዊ ወሰን በአንድ


ውስን አካባቢ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት በአንድነት ለማልማትና ብቃት ባለው መንገድ
ለመንከባከብ አመች ወይም ተመጣጣኝ ሆኖ የተከለለ መሆን አለበት።

፮/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ

፩/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ አማካይ ስፋት ፭፻ ሄክታር ሆኖ እንደ አካባቢው መልክዓ-ምድራዊ


አቀማመጥ ወይም የተፋሰስ ልማቱን ዓላማ ግምት ውስጥ በማስገባት መጠኑ ከፍ ወይም
ዝቅ ሊል ይችላል፡፡

3
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ ሥር በተደነገገው መሠረት የማኅበረሰብ ተፋሰሱ ከ፭፻
ሄክታር በላይ በሚሆንበት ጊዜ ይህንኑ እንደ አመችነቱ ከፋፍሎ ማልማትና መንከባከብ
ይቻላል።

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፪ የተደነገገው ቢኖርም በመከፋፈሉ ምክንያት የሚፈጠረው


ተፋሰስ ስፋት ከ፪፻ ሄክታር በታች ሊሆን አይችልም።

፯/ ዋና ተፋሰስ

፩/ ዋና ተፋሰስ የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ስብስብ ሲሆን ስፋቱ እስከ ፳ ሺህ ሄክታር ሊደርስ


ይችላል።

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ የተደነገገው ቢኖርም እንደ አካባቢው መልክዓ-ምድራዊ


አቀማመጥ ወይም ለአስተዳደር አመችነት ሲባል መጠኑ ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል።

፫/ ዋና ተፋሰሶች በወረዳው ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ወንዞችን መነሻ በማድረግ ይለያሉ።

፬/ ከዋና ተፋሰሱ ተለይተው የወጡትን የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ለማልማት ከላይኛው የተፋሰሱ


ክፍል በመጀመር ወደታችኛው በቅደም ተከተል መውረድ ያስፈልጋል።

፭/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፫ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ከራስጌ በታች ጎንና ጎን


ከሚገኙ የማኅበረሰብ ተፋሰሶች በቅድሚያ የሚለማውን የመራቆት ደረጃ፣ የሰው ሀይልና
ሌሎች

፰/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅት

፩/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅት የአሳታፊነት መርሕን የተከተለ መሆን አለበት።

፪/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት የማህበረሰብ ተፋሰስ የሚያለሙ አካላት
በቅድሚያ የማህበረሰብ ተፋሰስ ዕቅድ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡

፫/ ማኅበር ከመቋቋሙ በፊት የተፋሰስ ዕቀድ የሚዘጋጅ ከሆነ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፩ ንዑስ
አንቀጽ ፭ የተጠቀሰው ማኅበር መሥራች ኮሚቴ የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበሩን
ከማደራጀት ጎን ለጎን በሚመለከተው የተፈጥሮ ሀብት ተቋም በመታገዝ ዕቅዱን ማዘጋጀት
አለበት።

4
፬/ በሚዘጋጀው ዕቅድ ውስጥ የሚካተቱ ተግባራት የአካባቢ መራቆትንና የተፈጥሮ ሀብት
መመናመንን ለመከላከል፣ የውኃ ሀብትን ለማጎልበትና የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት
በመቀነስ የመሬት የማምረት አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ መሆን አለባቸው።

፭/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ልማት በሚታቀድበት ጊዜ መላ ተፋሰሱን ለማልማት የሚያስችል


ዝግጅት በማድረግ ከፊሉ ለምቶ ከፊሉ ሣይለማ እንዳይቀር ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ
አለበት።

፮/ ዋና ተፋሰስ የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ስብስብ በመሆኑ ለልማት ዕቅዱ ተፈፃሚነት ያመች


ዘንድ እንደ አስፈላጊነቱ በማኅበረሰብ ተፋሰስ ስፋት መጠን ተከፋፍሎ መዘጋጀት
ይኖርበታል።

፯/ በተፈጥሮ የተፋሰስና የአስተዳደር ድንበር ልዩነት በሚያሳይ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ላይ


የሚዘጋጀው ዕቅድ ሁሉንም የተፋሰስ ተጠቃሚ ማኅበረሰብ ያሳተፈ መሆን አለበት።

፰/ የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ዕቅድ አዘገጃጀት የአካባቢና ማኅበራዊ ዘላቂነት መርሕን


የተከተለ መሆን አለበት።

፱/ አንድ የማህበረሰብ ተፋሰስ በካርታ የተደገፈ የተሟላ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ሊኖረው ይገባል።

፲/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፱ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የማኅበረሰብ ተፋሰሶች የረጅም


ጊዜ ዕቅዳቸውን መሠረት ያደረገ ዓመታዊ ዕቅድ ሊዘጋጅላቸው ይገባል።

፲፩/ የሚዘጋጀው የማህበረሰብ ተፋሰስ ዕቅድ ተፋሰሱ የሚገኝነበትን አገራዊ ዋና ተፋሰሶች


ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት በማድረግ መዘጋጀት አለበት፡፡

፲፪/ በማኅበሩ የተዘጋጀው ዕቅድ ከአንድ ወረዳ በላይ ወሰን ተሸጋሪ ከሆነ ዕቅዱ ጉዳዩ
ለሚመለከታቸው ወረዳዎች ሁሉ ቀርቦ በወረዳዎቹ የተፈጥሮ ሀብት ተቋማት ስምምነት
መጽደቅ አለበት፡፡ ዝርዝሩ በደንብ ይወሰናል፡፡

፲፫/ በየአካባቢው የሚለዩ የማህበረሰብ ተፋሰሶች እና ዋና ተፋሰሶች አገራዊውን የልዩ መለያ


አሰጣጥ ሂደት ተከትለው ልዩ መለያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

5
፱/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ልማት

፩/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከላይኛው የተፋሰሱ አካል ተጀምረው ወደታችኛው


የተፋሰሱ ክፍል መውረድ አለባቸው።

፪/ ለሚለማው ተፋሰስ ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በመምረጥ በአግባቡ መተግበር


ያስፈልጋል።

፫/ የማኅበረሰብ ተፋሰሶች በተፋሰሱ ተጠቃሚዎች፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ


ድርጅቶች በሚቋቋሙ ፕሮጀክቶች ወይም በግለሰቦች ሊለሙ ይችላሉ።

፬/ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ዕቅድ በተፈጥሮ ተፋሰስና በአስተዳደር ወሰን መካከል ልዩነት ባለው
ቦታ ላይ የሚያርፍ በሆነ ጊዜ ዕቅዱ የሚተገበረው የአስተዳደር ወሰንን በመከተል ይሆናል፡፡

፭/ በተፋሰስ ልማት ሥራዎች ላይ ተባይና በሽታን ለመቆጣጠር የተቀናጁ የመከላከያ ዘዴዎች


ይተገበራሉ።

፮/ የማህበረሰብ ተፋሰስ አልሚዎች የሚገለገሉበትን ማናቸውም ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ወይም


መሠል ኬሚካላዊ ግብዓት የሚያገኙት ከመንግሥት ወይም ሕጋዊ ፈቃድ ከተሰጣቸው
ድርጅቶች ብቻ ይሆናል።

፯/ ማንኛውም ፀረ-ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ሁሉ በንብ እርባታ፣ በሰብልና


በአካባቢው ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ኬሚካሉን የሚያሰራጨው ሕጋዊ አካል ለኬሚካሉ
ተጠቃሚዎች በቂ ዕውቀት ማስጨበጥና ተገቢውን ወቅትና የአጠቃቀም ጊዜ መርጠው
ርጭቱን እንዲያካሂዱ ማድረግ ይኖርበታል።

፰/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፫ ስር የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ ኬሚካሎች


ካላቸው ጠንካራ መርዛማነት የተነሳ በዕፅዋትና በአካባቢው ላይ የሚያደርሱት ጉዳት
ከፍተኛ በመሆኑ በባለሙያ ድጋፍ እንዲረጩ ወይም በእርሱ የቅርብ ክትትል ጥቅም ላይ
እንዲውሉ መደረግና ቅሪቶቹም በወንዞች፣ በኩሬዎች፣ በጅረቶችና በሌሎች የውኃ አካላት
ላይ እንዳይጣሉ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል።

፱/ በማህበረሰብ ተፋሰሱ ክልል ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶች ደረጃቸውን የጠበቁና


የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያላለፈ መሆን አለበት።

6
፲/ የማህበረሰብ ተፋሰስ አልሚዎች ተፈጥሯዊ የግብርና ግብዓቶችን እንዲጠቀሙ
ይበረታታሉ።

ክፍል ሦስት
ስለማህበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር አመሠራረት

፲/ ስለማህበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር አመሠራረት

፩/ የማህበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች በማህበር የሚደራጁት የማህበረሰብ ተፋሰሱን


ለማልማት፣ ለማስተዳደር እና ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ
የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ነው፡፡

፪/ የማህበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች አግባብ ባላቸው ሕጐች መሠረት በማኅበር ይደራጃሉ።

፫/ ማኅበሩ በተፋሰሱ ተጠቃሚዎች ፍላጎትና ሙሉ ፈቃደኝነት መሠረት ይቋቋማል።

፬/ ማኅበሩ በማህበረሰብ ተፋሰሱ ስፋት ወይም ወሰን መሠረት መቋቋም አለበት። ሆኖም ግን
የማህበረሰብ ተፋሰሱና የአስተዳደር ወሰኖች የሚለያዩ ከሆነ ማኅበሩ የወረዳውን ወሰን
ተከትሎ መቋቋም አለበት፡፡ ዝርዝሩ በደንብ ይወሰናል፡፡

፭/ የማኅበሩ መመስረቻና መተዳደሪያ ደንብ ተፋሰሱን በባለቤትነት ይዘው እንዴት


እንደሚያለሙት፣ እንደሚያስተዳድሩትና እንደሚጠብቁት በዝርዝር የሚደነግግ ሆኖ
ተጠቃሚ ማኅበረሰቡ የመከረበትና ስምምነት ላይ የደረሰበት መሆን አለበት።

፮/ የሚመለከተው የወረዳ የተፈጥሮ ሀብት ተቋም ከሚመለከተው የማኅበር አደራጅ መሥሪያ


ቤት ጋር በመተባበር የማኅበር መሥራች ኮሚቴ እንዲደራጅ የማድረግ ኃላፊነት አለበት።

፯/ የተጠቃሚዎች ስምምነት በማኅበሩ መሥራች ኮሚቴ አማካኝነት ተረቅቆ በጠቅላላ ጉባዔ


አባላት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ መጽደቅ ይኖርበታል።

፰/ የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር መመስረቻና መተዳደሪያ ደንቦች በሚረቀቁበት፣ ለውይይት


በሚቀርቡበትና በጠቅላላ ጉባዔው ተመክሮባቸው በሚፀድቁበት ጊዜ አግባብ ያላቸው አካላት
መሥራች የኮሚቴ አባላትን የመደገፍ ኃላፊነት አለባቸው።

7
፱/ በዚህ አንቀጽ ንዑሰ አንቀጽ ፯ ለጠቅላላ ጉባዔው ቀርቦ የፀደቀው የተፋሰስ ተጠቃሚዎች
መመስረቻና መተዳደሪያ ደንቦች ፩ ቅጅ ተፋሰሱ ለታቀፈበት ቀበሌ/ዎች አስተዳደር ጽ/ቤት
እንዲያውቀው መላክ አለበት።

፲/ የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር አስፈላጊ መመዘኛ መስፈርቶችን አሟልቶ በመቅረብ


በክልሉ መንግሥት ሥልጣን ከተሰጠው አካል ሕጋዊ ሰውነት ያገኛል።

፲፩/ ከተፋሰሱ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብት ውጤቶች እንደ ሣር፣ ደን እና የደን ውጤቶች ወይም
መሰል የተፈጥሮ ሀብት ውጤቶች በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ተሽጠው ከተገኘው ገንዘብ ላይ
ለአባላት የሚከፋፈልና ለተፋሰሱ ልማት ዓላማ በማኅበሩ ስም በሚከፈት የባንከ ሂሳብ
ተቀማጭ የሚሆነው የገንዘብ መጠን በማኅበሩ የውስጥ ደንብ ይወሰናል።

፲፩/ ሰለተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር ዋና አባላት

ዕድሜያቸው ፲፰ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከሚከተሉት መስፈርቶች አንዱን


ካሟሉ በዚህ አዋጅ መሠረት የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር ዋና አባል ለመሆን መብት አላቸው፡

ሀ/ በተፋሰሱ ክልል ውስጥ የመሬት ይዞታ ያላቸውና ከዚሁ በሚገኝ ገቢ የሚተዳደሩ፣

ለ/ በተፋሰሱ ክልል ውስጥ የመሬት ይዞታ ባይኖራቸውም በዙሪያው ነዋሪዎች ከመሆናቸው


የተነሣ ከተፈጥሮ ሀብቱ ተጠቃሚዎች የሆኑ ወገኖች፤

ሐ/ ኗሪነታቸው በተፋሰሱ ክልል ውስጥ ባይሆንም መሬት ተከራይተውም ሆነ በሌላ ህጋዊ


መንገድ ከተፋሰሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች።

መ/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ የተደነገገው ቢኖርም በተፋሰስ ክልሉ ውስጥ የመሬት
ይዞታ ያላቸውና ዕድሜያቸው ከ፲፰ ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች በአሳዳሪያቸው አማካኝነት
በአባልነት ሊመዘገቡ ይችላሉ።

ሠ/ በዚህ አንቀጽ የተደነገጉትን መስፈርቶች አሟልተው የተገኙ ልዩ ትኩረት የሚያሻቸው


የኅብረተሰብ ክፍሎች የማኅበር አባል የመሆንና ማኅበሩ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ተካፋይ
የመሆን ሙሉ መብት አላቸው።

8
፲፪/ ከዋና አባልነት ስለመሰናበት

በአንቀጽ ፲፪ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ዋና አባል የሆነ ሰው ከሚከተሉት በአንዱ ምክንያት ከአባልነት


ይሰናበታል።

ሀ) አባሉ በማኅበሩ ውስጥ ለመቀጠል ፈቃደኛ ካልሆነ፣

ለ) በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የአባልነት ግዴታውን ሳይወጣ ሲቀርና የማኅበሩ


ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ሲያሳልፍ፣

ሐ) በአንቀጽ ፲፪ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች በጊዜ ሂደት ሳያሟላ ቀርቶ ሲገኝ።

፲፫/ ስለማኅበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር የክብር አባላት

፩/ የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር ለዓላማው ተፈፃሚነት የሚያግዙ ሆነው በተፋሰሱ አካባቢ


የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን የተፋሰሱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ያልሆኑትን ግለሰቦች፣ ድርጅቶች
ወይም ተቋማት በክብር አባልነት ሊቀበል ይችላል።

፪/ የክብር አባላት በተፋሰሱ ተጠቃሚዎች ማኅበር ውስጥ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ ወይም


በማናቸውም ጉዳይ ድምጽ የመስጠት መብት አይኖራቸውም።

፲፬/ የክብር አባላት ሚና እና ኃላፊነት

፩/ የክብር አባላቱ በራሳቸው ተነሳሽነት ወይም በማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ጥያቄ ስለተፈጥሮ


ሀብቱ ልማትና ጥበቃ ትምህርትና ምክር ይለግሳሉ፣ እንደዚሁም የቴክኒክ፣ የዓይነትና
የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፣

፪/ በተፋሰሱ ሥራ አመራር ኮሚቴ በሚቀርብላቸው ጥሪ መሠረት በጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባዎች


እንዲሳተፉ እና ሀሳብ እንዲሰጡ መድረክ ሊመቻችላቸው ይችላል።

፲፭/ ስለተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር ዩኒየን እና ፌደሬሽን

የማኅበረሰብ ተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበራት በዋና ተፋሰስ ደረጃ የተፋሰስ ተጠቀሚዎች


ማኅበራት ዩኒየን እንደዚሁም ከፍ ባለ ደረጃ ደግሞ ፌደሬሽን ሊያቋቁሙ ይችላሉ።

9
፲፮/ የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር አባላት መብት

በአንቀጽ ፲፪ መሠረት የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር አባል መሆኑ የተረጋገጠለት ማንኛውም


ሰው የሚከተሉት ዝርዝር መብቶች ይኖሩታል፡፡

፩/ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙትን የተፈጥሮ ሀብቶች በጋራ ወይም በግል የመጠቀም፣

፪/ በተፋሰስ ክልል ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተመለከተ በሚደረግ የማኅበረሰብ


ውይይት ላይ የመሳተፍ፣

፫/ አባል በሆኑበት ማኅበር እና በማህበሩ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ውስጥ የመምረጥም ሆነ


የመመረጥ፣

፬/ በማህበሩ ስር አባላት እንደየሙያቸውም ሆነ ፍላጎታቸው የተጠቃሚዎች ቡድን በመፍጠር


ተፋሰሱን በማይጎዳ ሁኔታ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ የመሰማራት።

፭/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፭ መሠረት ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎች” እንደ ንብ ማነብ፣


ወተት እና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበር እና ማቅረብ፣ እንስሳት ማድለብ፣ እንጨት ነክ
ያልሆኑ የደን ውጤቶች ማምረት እና ማቅረብ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ማምረት እና
ማቅረብ፣ የመኖ ልማት፣ እንዲሁም የተፋሰስ ልማቱን የማይጎዱ ተመሣሣይ ሌሎች
ሥራዎችን ያጠቃልላል።

፮/ የተፋሰሱ ተጠቃሚ ሆነው ነገር ግን የማኅበሩ አባል ያልሆኑ ሰዎች በዚህ አንቀጽ ንዑስ
አንቀጽ ፬ እና ፭ የተደነገጉት መብቶች አይኖራቸውም።

፯/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፮ የተጠቀሱ ሰዎች በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ የተደነገገው
መብት በግል ይዞታቸው እና በማኅበረሰቡ ወይም በሕጋዊ አካል በተረጋገጠ የወል ይዞታ
ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል።

፲፯/ የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር አባላት ግዴታዎች

በዚህ አዋጅ መሠረት የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማኅበር አባል የሆነ ማንኛውም ሰው የሚከተሉት
ዝርዝር ግዴታዎች ይኖሩበታል፡፡

፩/ በተፋሰሱ ውስጥ በሚካሄድ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ የመሳተፍ፣

10
፪/ በተፋሰሱ ክልል ያሉትን ተፈጥሯዊና በልማት የተገኙ ሀብቶች ከውድመት የመጠበቅና
የመከላከል፣

፫/ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የሚወሰን የአባልነት ክፍያ የመክፈል፣

፬/ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በግል፣ በቡድንና በአጠቃላይ በሚከናወኑ የውይይት፣


የዕቅድ ዝግጅት፣ የጥበቃና የልማት ተግባራት ላይ የኑሮ ሁኔታቸውን በማይጎዳ መልኩ
ጉልበት ማዋጣትን ጨምሮ በንቃት የመሳተፍ፣

፭/ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መሠረተ ልማቶች፣ ተጠግነው


የዘወትር ጥቅም መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ማኅበሩ በሚያወጣው ፕሮግራም መሠረት
በጥገና ሥራ ላይ የመሰማራት።

፲፰/ የማኅበሩ አደረጃጀት

ማኅበሩ በዚህ አዋጅ የተሰጡትን መብትና ግዴታዎች ለመወጣት የሚከተሉት አካላት ይኖሩታል፡

፩/ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ፣

፪/ የሥራ አመራር ኮሚቴ፣

፫/ እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች ንዑሳን ኮሚቴዎች።

፲፱/ የጠቅላላ ጉባዔው ሥልጣንና ተግባር

ጠቅላላ ጉባዔው የማኅበሩ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ሲሆን የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት
ይኖሩታል፤

ሀ) የማኅበሩን ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ፣ የተፋሰስ ዕቅድና በጀት የማጽደቅ፤

ለ) የማኅበሩን የሥራ አመራር አካላት እና ሌሎች ንዑሳን ኮሚቴዎችን አባላት የመምረጥ


አና የመሻር፤

ሐ) የማኅበሩን መመስረቻ ጽሁፍ፣ መተዳደረያ ደንብና የውስጥ ደንብ የማጽደቅና የማሻሻል፤

መ) በማኅበር አባላት የሚከፈል የመዋጮና የቅጣት መጠንን የመወሰን፤

ሠ) በሥራ አመራር ኮሚቴው የሚቀርቡለትን የፋይናንስና የሥራ ክንውን ሪፖርቶች አዳምጦ


የመወሰን፤
11
ረ) ማኅበሩን እንደገና የማደራጀት ወይም የማኅበሩን ንብረት ማጣራትን የሚመለከቱ
ውሳኔዎችን የመወሰን፤

ሰ) የማኅበሩን ንብረቶች በማንኛውም መንገድ ማስተላለፍን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የመወሰን፤

ሸ) በማኅበሩ ውስጠ ደንብ መሠረት ከተወሰነ ዋጋ በላይ ያላቸውን ወይም ለማኅበሩ ከፍተኛ
ዋጋ ያላቸውን ውሎች የማጽደቅ፤

ቀ) በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአባላት መልቀቂያ ወይም ስንብትን በሚመለከት የሚቀርቡ


ውሳኔዎችን የማጽደቅ፤

በ) በሥራ አመራር ኮሚቴና በሌሎች ኮሚቴዎች የሚቀርቡለትን ማናቸውንም ጉዳዮች


የመወሰን።

፳/ የጠቅላላ ጉባዔው የአሠራር ሥነ ሥርዓት

፩/ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ መደበኛ ስብሰባውን በስድስት ወር አንድ ጊዜ ያካሂዳል። ሆኖም


ከማኅበሩ አባላት ውስጥ ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ከተደገፈ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ
ይችላል።

፪/ የጠቅላላ ጉባዔው ምልዓተ ጉባዔ የሚሆነው ከማኅበሩ አባላት መካከል ከግማሽ በላይ
የሚሆኑት በስብሰባው ላይ ሲገኙ ይሆናል።

፫/ ማናቸውም ጉዳይ የጠቅላላ ጉባዔው ውሣኔ ሆኖ ማለፍ የሚችለው በስብሰባው ላይ


በተገኙት የጉባዔው አባላት አብላጫ ድምጽ ሲደገፍ ነው። ሆኖም ድምጹ እኩል ከተከፈለ
ሰብሳቢው ያለበት ወገን የጉባዔው ውሳኔ ሆኖ ያልፋል።

፬/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፫ የተደነገገው ቢኖርም የመመሥረቻ ጽሁፍና መተዳደሪያ


ደንብ ለማጽደቅ ወይም ለማሻሻል፣ ማኅበሩን ለማፈረስ ወይም እንደገና ለማደራጀት
አንዲሁም ንብረት ለማጣራት የጠቅላላ ጉባዔው ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ያሰፈልጋል።

፳፩/ የሥራ አመራር ኮሚቴ

፩/ እያንዳንዱ ማኅበር ቁጥራቸው ከአምስት ያላነሰ ወይም ከአሥራ አንድ ያልበለጠ አባላት
ያሉት ሥራ አመራር ኮሚቴ ይኖረዋል።

12
፪/ የሥራ አመራር ኮሚቴው ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ፀሐፊ፣ ገንዘብ ያዥ፣
የተፋሰስ ልማት አስተባበሪ እንዲሁም ሌሎች አባላት ይኖሩታል።

፫/ የኮሚቴው አባላት ስልጣንና ተግባር በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ይወሰናል።

፬/ የሥራ አመራር ኮሚቴው አባላት ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ግምት ውስጥ ያስገባ ሆኖ
ቁጥራቸው ከአባላቱ ቢያንስ ፴ በመቶ መያዝ ይኖርበታል።

፭/ የኮሚቴው ተጠሪነት ለጠቅላላ ጉባዔው ይሆናል።

፮/ የሥራ አመራር ኮሚቴው በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፰ ሥር የተዘረዘሩትን የማኅበሩን ጠቅላላ


ጉባዔ ውሳኔዎች በሥራ ላይ ከማዋል በተጨማሪ የሚከተሉት ተግባራትና ኃላፊነቶች
ይኖሩታል፡፡

ሀ) የጠቅላላ ጉባዔውን መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባዎች አጀንዳ በመያዝ ይጠራል፣


ይመራል፤

ለ) የማኅበሩን ፋይናንስና ንብረት ያስተዳድራል፣ ይጠብቃል፤

ሐ) የማኅበሩን የሥራ ዕቅድ፣ በጀትና የተጠቃሚዎች ስምምነት ረቂቆች አዘጋጅቶ


ለጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ያቀርባል፣ ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋል፤

መ) ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴና የበጀት ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔው ያቀርባል፤

ሠ) የማኅበሩን የዕለት ተዕለት ተግባራት ያከናውናል፣

ረ) በጠቅላላ ጉባዔው የሚሰጡትን ሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ያከናውናል።

፯/ ከሥራ አመራር ኮሚቴው አባላት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከተገኙ ኮሚቴው
ስብስባዎችን ሊያካሂድ እና ውሣኔዎችን በድምጽ ብልጫ ሊያሣልፍ ይችላል።

፳፪/ ንዑሳን ኮሚቴዎች

፩/ ማኅበሩ የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን እንደ አስፈላጊነቱ ያደራጃል።

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ መሠረት የሚቋቋሙት ኮሚቴዎች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት
ሳይወሰኑ የሚከተሉትን ያካትታሉ።

ሀ) የተፋሰስ ጥበቃና ቁጥጥር ኮሚቴ

13
ለ) የቅሬታ አፈታት ኮሚቴ

ሐ) የቁጥጥር ኮሚቴ

፳፫/ ማኅበሩ ከሌሎች አካላት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት

፩/ ከቀበሌ አስተዳደሩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር አስፈላጊውን ድጋፍ ማግኘት ይችላል።

፪/ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱም ሆነ ከሌሎች መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ካልሆኑ


ድርጅቶችና ማኅበራት ጋር የማኅበሩን ዓላማ እውን ለማድረግ የሚያግዙ ስምምነቶችን
ሊያደርግ ይችላል።

፫/ አንድን ውስን ሥራ በክፍያ ወይም ያለክፍያ ለማከናወን ከተለያዩ አካላት ጋር ሊዋዋል


ይችላሉ።

ክፍል አራት
የተፋሰስ ጥበቃ፣ አስተዳደርና አጠቃቀም

፳፬/ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አጠባበቅ፣ አስተዳደርና አጠቃቀም

፩/ የገጠር መሬት ባለይዞታ መብቶችና ግዴታዎችን አስመልክቶ የሌሎች ሕጎች ድንጋጌዎች


እንደተጠበቁ ሆነው ማንኛውም በተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ የግል ወይም የወል ባለይዞታ
እንደ መሬቱ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ የአፈርና ውኃ መጠበቂያ ሥራዎችን በመሥራትና
በመንከባከብ እንዲሁም በመጠገን የአፈር ክለትን በመከላከል የአፈርን ለምነት የመጠበቅ
ግዴታ አለበት።

፪/ ማንኛውም የግል ወይም የወል ባለይዞታ፡-

ሀ) በተፋሰሱ ውስጥ በተሠሩ የልማት ሥራዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ልቅ የእንስሳት


ስምሪትን የመቆጣጠርና የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት።

ለ) በተፋሰሱ ውስጥ በሚገኙት የመሬት ይዞታዎቹ ዳር ድንበር፣ በማሳው ውስጥና


በመንገዶች ዳር የደን፣ የመኖ ዛፎችንና አልሚ የእፅዋት ዝርያዎችን በመትከል፣
በመንከባከብና በመጠበቅ የአካባቢውን ለምነትና ጤንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት።
14
ሐ) በተፋሰሱ ውስጥ በሚገኙ የይዞታ መሬቶቹ አካባቢ ወንዞች፣ ምንጮች፣ የታከሙ
ቦረቦር ስፍራዎችና ውኃ አዘል መሬቶች ያሉ እንደሆነ እነዚሁ በአጠቃቀምና በአያያዝ
ሣቢያ ጉዳት እንዳይደርስባቸው እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በቂ የመከላከያ ርቀት
የመተው ግዴታ አለበት።

መ) በተፋሰሱ ውስጥ በሚገኘው ይዞታው ላይ የሚፈጠር ትርፍ የጎርፍ ውኃ ቢያጋጥም


ይኸው በሌሎች አጎራባች ማሳዎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል፣ ከሌሎች የሚመጣውንም
በማቀባበል ወደ ሰው ሠራሽ ወይም የተፈጥሮ መፋሰሻ ቦዮች እንዲፋሰስ የማድረግ
ግዴታ አለበት።

ሠ) በተፋሰሱ ክልል ውስጥ የሚገኝ ባለይዞታ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (መ) የተጣለውን
ግዴታ ለመወጣት ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ያጋጠመው እንደሆነ ይህንኑ
ለሚመለከተው የተፈጥሮ ሃብት ተቋምና ለማህበሩ ማሳወቅ አለበት፡፡

ረ) በተፋሰሱ ውስጥ በሚገኘው የይዞታ መሬቱ ውስጥ ወይም ዳር ድንበሮች ላይ ያለማቸው


ወይም የሚያለማቸው የደንና የእፀዋት ዝርያዎች በጥላቸውና በጠፈጠፋቸው ምክንያት
የተጎራባቹን ባለይዞታ የሰብል ምርትና ሌሎች መብቶች የሚጎዳ መሆን የለበትም።

ሰ) በተፋሰሱ ውስጥ በሚመለከተው አካል የፀደቀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ በሚኖርበት


ጊዜ መሬቱን በዕቅዱ መሠረት የማልማትና የመንከባከብ ግዴታ አለበት።

ሸ) በተፋሰሱ ውስጥ የእሳት ቃጠሎ እንዳይነሳ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ የመውሰድ


ግዴታ አለበት።

ቀ) በተፋሰሱ ውስጥ በሚገኙ ማሳዎቹና በአካባቢውው የሚገኙ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት


አካባቢውውን ለቅቀው እንዳይሰደዱ ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታ አለበት።

በ) በተፋሰሱ ውስጥ በሚገኙ የይዞታ መሬቶቹ ውስጥ ተክሎና ተንከባክቦ ያሳደጋቸውን


የደን ዛፎች፣ የመኖና አልሚ የእፅዋት ዝርያዎች አጠቃቀምን በተመለከት የደን ልማት
ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ተፈጻሚነት ይኖረዋል።

15
፳፭/ ስለ እንጨት፣ እንጨት ያልሆኑ የደን ውጤቶች እና ሣር አጠቃቀም

፩/ በተፋሰሱ ክልል ውስጥ በግል ወይም በወል ይዞታዎች ላይ የመጠቀም መብት ያላቸው
ሰዎች በእነዚህ ይዞታዎች ላይ የለሙትን ወይም የተተከሉትን ደረቅ እንጨት፣ ዛፍ፣
ቁጥቋጦ፣ ሣር እና እንጨት ያልሆኑ የደን ውጤቶች የመጠቀም መብት አላቸው።

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ ሥር ከተጠቀሱት ባለይዞታዎች ውጭ በተፋሰስ ክልል


ውስጥ የሚገኝ ማናቸውም ደረቅ እንጨት፣ ዛፍ፣ ቁጥቋጦ፣ እንጨት ያልሆነ የደን
ውጤት ወይም ሣር የማኅበሩ አባላት የጋራ ንብረት ስለሆነ፣ በማኅበሩ ውስጠ ደንብ
መሠረት ማኅበሩ ቆርጦ፣ አጭዶና ሰብስቦ መጠቀም ይችላል።

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ እና ፪ የተጠቀሱት ሀብቶች አጠቃቀም አቅርቦቱን ዘላቂነት


ባለው መንገድ ለመጠበቅ በሚያስችል አግባብ መፈፀም ይኖርበታል።

፳፮/ በተፋሰሱ ክልል ውስጥ ስለሚገኝ ድንጋይና አሸዋ አጠቃቀም

፩/ በአንቀጽ ፳፭ ንዑስ አንቀጽ ፩ ስር በሚገኙ ይዞታዎች ላይ የሚገኙት አሸዋ እና ድንጋይ


የመጠበቅ እና የመጠቀም ኃላፊነት የማዕድን ሥራዎች አዋጅ በሚፈቅደው መሠረት
የእነዚሁ ባለይዞታዎች ይሆናል።

፪/ በተፋሰሱ ክልል ውስጥ በታቀፈና የወል ወይም የመንግሥት ይዞታ በሆነ ሥፍራ ላይ
የሚገኝ ድንጋይና አሸዋ ንብረትነቱ የማኅበሩ ሲሆን የማዕድን ሥራዎች አዋጅ
በሚፈቅደው መሠረት ድንጋይና አሸዋውን ለተፋሰሱ ልማት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ እና ፪ ስር የተደነገገው ቢኖርም የድንጋይና አሸዋ አቅርቦቱን


ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀምና ለመጠበቅ እንዲቻል የአፈር ክለትን እንዳያስከትል
ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል።

፳፯/ በማህበረሰብ ተሰሱ ክልል ውስጥ ስለሚገኝ የውሃ ሀብት አጠቃቀም

በማህበረሰብ ተፋሰስ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የውሃ ሃብት አጠቃቀም የውሃ ሃብት አስተዳደር
አዋጅ በሚፈቅደው መሠረት ይሆናል::

16
፳፰/ ስለ ሥርዓተ ምሕዳር አገልግሎት ክፍያ

ከማኅበሩ አባላት ውጭ ተፋሰሱ በመልማቱ ምክንያት ተጠቃሚ የሆኑ አካላት ለተፋሰሱ ልማት
የሥርዓተ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ የመክፈል ግዴታ አለባቸው።

፳፱/ የሥርዓተ ምሕዳር ጉዳት ካሣ

በመሠረተ ልማት ግንባታ ወይም በሌላ ምክንያት በማንኛውም ሁኔታ በተፋሰሱ ወይም በተፋሰስ
ተጠቃሚዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት ላደረሱት ጉዳት ተመጣጣኝ ካሣ መክፈልና አካባቢውን
ተመጣጣኝ ወደ ሆነ ስነ-ምህዳር የመመለስ ግዴታ አለባቸው።

ክፍል አምስት
የተፋሰስ ማኅበረሰቡን የሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች
፴/ የተጠናቀቁ የተፋሰስ ሥራዎች ርክክብ

፩/ ማንኛውም የግል ወይም የወል ባለይዞታ በራሱ፣ በኅብረተሰቡ፣ በማኅበሩ ወይም ሥራውን
አጠናቀው በሚያስረክቡ መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች
የተከናወኑትን የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ቆጥሮ መረከብ አለበት።

፪/ ርክክብ ሲካሄድ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ጥራታቸው የተጠበቀ ስለመሆኑ የሚመለከተው


የወረዳ ተቋም ማረጋገጥ አለበት።

፴፩/ ስለማበረታቻ

፩/ በተፋሰሱ ክልል ውስጥ በግልም ሆነ በወል የተሰሩ የአፈርና ውኃ ልማትና ጥበቃ


ሥራዎችን እየጠገነ በአግባቡ በመንክባከብ በተፋሰስ ውስጥ የላቀ ውጤት ላስመዘገበ
ባለይዞታ የዕውቅና እና ማበረታቻ ሸልማት የሚሰጥበትን ሥርዓት ወረዳው ይዘረጋል።

፪/ በወረዳው ውስጥ ካሉት የማኅበራት የተሻለ የተፋሰስ ልማት ሥራ ላከናወነ ማኅበር


ወረዳው የዕውቅናና ማበረታቻ ሸልማት የሚሰጥበትን ሥርዓት ይዘረጋል።

17
፴፪/ ስለ ሥርዓተ-ፆታ እና ልዩ ትከረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች

፩/ በማናቸውም የተፋሰስ አስተዳደርና አጠቃቀም ሂደት ሚዛናዊ የፆታ ስብጥር መኖር


አለበት።

፪/ ሴቶችና ልዩ ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥቅም በሚያስገኙ በማናቸውም


የተፋሰሱ ልማት ተግባራት ሁሉ አቅማቸውና ሙያቸው በሚፈቅደው መጠን እኩል
የመሣተፍ ዕድል ይሰጣቸዋል።

፴፫/ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት

፩/ አግባብነት ያላቸውን ተቋማት በማስተባበርና አስፈላጊውን የሙያ ድጋፍ በመስጠት ይህንን


አዋጅ የማስፈጸም ኃላፊነት አለበት።

፪/ በክልሎችና በፌደራል መካከል የተፋሰስ ልማት አስተዳደርና አጠቃቀም የመረጃ ልውውጥ


ሥርዓት እንዲዘረጋ ያደርጋል።

፴፬/ የክልሎች ኃላፊነት

፩/ ክልሎች ይህንን አዋጅና ሌሎች ከተፋሰስ አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲሁም ከማኅበራት


አመሠራረትና አደረጃጀት ጋር ግንኙነት ባላቸው ሕጎች ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና ማኅበራት
እንዲመሠረቱ የመቀስቀስና ሕጎቹን የማስፈጸም ኃላፊነት አለባቸው።

፪/ ይህንን አዋጅና አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጣውን ደንብ ተከትለው ዝርዝር የአፈጻጸም


መመሪያ ያወጣሉ።

፴፭/ የተፈጥሮ ኃብት ተቋም ተግባርና ኃላፊነት

የሚመለከተው የተፈጥሮ ሃበት ተቋም ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሳይወሰን የሚከተሉት ተግባርና
ኃላፊነቶች አሉበት፡፡

ሀ/ የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ዕቅድ ዝግጅትን ይደግፋል፤ የተዘጋጁትንም መርምሮም


ያጸድቃል፡፡

ለ/ የተፋሰስ ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀምን ያስተባብራል፣ ይመራል፣ ይከታተላል፤

18
ሐ/ የማህበረሰብ ተፋሰስ ማህበር አባላት የተጠቃሚዎች ቡድን በመመስረት ገቢ በሚያስገኙ
ስራዎች ላይ እነዲሰማሩ ይደግፋል፣ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡

መ/ የዋና ተፋሰሰስ እና የማህበረሰብ ተፋሰስን ስፋት እንደ አካባቢው መልክዓ ምድራዊ


አቀማመጥ መሰረት በማድረግ ይወስናል፡፡

ክፍል ስድስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
፴፮/ ኃላፊነት

፩/ በዚህ አዋጅ ውስጥ የተደነገጉ ግዴታዎችን አለመወጣት የሚያስከትሉት ቅጣት በወንጀል


ሕጉና በሌሎች ሕጎች የተደነገጉ ቅጣቶች ተፈጻሚ ይሆናሉ።

፪/ በዚህ አዋጅ ውስጥ የተደነገጉ ግዴታዎችን አለመወጣት የሚያስከትሉትን አስተዳደራዊ


ቅጣት ዝርዝር አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጣው ደንብ ይወሰናል፡፡

፴፯/ የመሸጋገረሪያ ድንጋጌ

፩/ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የተቋቋሙ ማኅበራት በዚህ አዋጅ መሠረት አስፈላጊውን


ማስተካከያ ካደረጉ ተቀባይነት ይኖራቸዋል።

፪/ ቀደም ሲል በነበረው አሠራር የተቋቋመ የተፋሰስ ኮሚቴ የዚህን አዋጅ መውጣት ተከትሎ
በሚቋቋመው ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እስከሚተካ ድረስ ተቀባይነት ይኖረዋል።

፴፰/ የመተባበር ግዴታ

ማንኛውም ሰው ይህንን አዋጅ በማስፈፀም ረገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመተባበር ግዴታ


አለበት።

፴፱/ ደንብ የማውጣት ሥልጣን

ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ያወጣል።

፵/ ተፈፃሚነት ስለማይኖራቸው ሕጎች

19
ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማናቸውም አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም ልማዳዊ አሠራር በዚህ
አዋጅ ውስጥ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።

፵፩/ አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል።

አዲስ አበባ____________ ቀን ፪ሺህ፲፪ ዓ/ም

ሳሕለወርቅ ዘውዴ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት

20

You might also like