You are on page 1of 5

አመሠራረት /ታሪካዊ አመጣጥ/

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንገድ ትራንስፖርት አጀማመር በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ
መኪና በ 1899 ዓ.ም ወደ ሀገር ውስጥ መግባትና በ 1928-1933 ዓ.ም በጣሊያን ወረራ ወቅት ከነበረው
የመንገዶች መስፋፋት ጋር የተያያዘ ሲሆን ጣሊያኖች አስተዳደራቸውን ለማስፋፋት በተለይም ደግሞ
የመከላከያ ኃይላቸውን ለማጠናከር እንዲረዳቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ መንገዶችን በመስራትና
ተሽከርካሪዎችን በማስገባት የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጎለብት አድርገዋል፡፡

በ 1933 ዓ.ም የጣሊያን ወራሪ ኃይል ተሽንፎ ከመጣ በኋላ የወራሪው ንብረት የነበሩት ተሽከርካሪዎች
ተወርሰው ለኢትዮጵያውያንና ለውጪ ዜጎች እንዲሸጡ በመደረጉ ለኢትዮጵያውያንና ለውጪ ዜጎች
እንዲሸጡ በመደረጉ ለኢትዮጵያውያንና የውጪ ሀገር ባሀብቶች በትራንስፖርት ንግድ ውስጥ በስፋት
ለመሳተፍ ምቹ ሁኔታን የፈጠረላቸው ሲሆን ውድድሩን በአሸናፊነት ለመውጣት ባደረጉትም ፉክክርም
የትራንስፖርት አገልግሎቱ እድገት አሳይቶ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ትራንስፖርትን በተመለከተ
በየወቅቱ የወጡ አዋጆችን መዳሰስ ስለትራንስፖርት አጀማመር የበለጠ ግንዛቤ ስለሚሰጥ እንደሚከተለው
በአጭሩ ቀርቧል፡፡

አዋጅ ቁጥር 11/1934፡- ይህ አዋጅ የመንገድ ትራንስፖርትን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣ አዋጅ ሲሆን
ዋና ትኩረቱም ስለተሽከርካሪ ማፃፍ የወጣ አዋጅ ነው፡፡

በወቅቱ የነበሩት ማዘጋጃ ቤቶች ተሽከርካሪዎችን እየመዘገቡ (እየፃፉ) ዝርዝሩን ለአገር ግዛት ሚኒስቴር
የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው አዋጁ ይገልፃል፡፡

አዋጅ ቁጥር 35/1935፡- ይህ ቀጥሎ የወጣው ሁለተኛ አዋጅ የየብስ ትራንስፖርት አዋጅ የሚባል ሲሆን ዋና
አስፈፃሚ አካል የሥራና መገናኛ ሚኒስቴር ነው፡፡ በወቅቱ ትራንስፖርትን ለመቆጣጠር ስድስት አባላት ያሉት
ቦርድ ተዋቅሮ ስራው ይካሄድ ነበር፡፡

በወቅቱ የሥራና መገናኛ ሚኒስቴር ይባል የነበረው መ/ቤት ከጣሊያን ወራሪ ኃይል የተረከባቸውን መጠነኛ
ተሽከርካሪዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎች ከ 1935-1943 ዓ.ም ሲያስተዳድር ቆይቶ በ 1944 ዓ.ም በታህሳስ ወር
ለተቋቋመው አክሲዮን ማህበር አስረክቧል፡፡
ይህ አዋጅ የሚያካትታቸው ድንጋጌዎች፡-

ስለተሽከርካሪ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ

ስለመኪና መንዳትና መንጃ ፈቃድ እንዲሁም

ጋሪዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ያካተተ ነበር

ይህ አዋጅ እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ አገልግሏል፡፡

የመንገድ ትራንስፖርት አስተዳደር /1960 - 1969/

በ 1960 ዓ.ም እንደገና በመንገዶች ላይ ጉዞንና ማመላለሻን (ትራንስፖርትን) ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 256
ወጥቶ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት

የሥራና የመገናኛ ሚኒስቴር በመንገዶች ላይ አጠቃላይ ጉዞን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ስልጣን የነበረው
ሲሆን አስፈፃሚው አካል የመንገድ ትራንስፖርት አስተዳደር የሚባል መ/ቤት ነበር፡፡

አስተዳደሩ ራሱና ውክልና በሰጣቸው ማዘጋጃ ቤቶች አማካይነት፡-

የተሽከርካሪ ምርመራና ምዝገባ ማካሄድ

የመንጃ ፈቃድ መስጠትና ማደስ

ለንግድና የሕዝብ ማመላለሻ ማህበራትና ተሽከርካሪዎች ፈቃድ መስጠት የመሳሰሉትን ሥራዎች እስከ 1996
ዓ.ም ድረስ ሲያከናውን ነበር፡፡

በዚሁ ወቅትም የባለሞተርና ተሳቢ ተሽከርካሪ ምዝገባን፣ መንጃ ፈቃድን እና ትራፊክን የተመለከቱ ደንቦች
ወጥተው በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

በወቅቱም በትራንስፖርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ትርፍ በሚያገኙበት


መስመር ላይ ብቻ የሚሰሩ በመሆናቸውና ከመጠን በላይ ከመጫን ጋር በተያያዘ አደጋዎች በተደጋጋሚ
በመከሰታቸው ህብረተሰቡ ምቹና የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት አልቻለም ነበር፡፡
በመሆኑም በወቅቱ የነበረው መንግስት ችግሩን ለመፍታት በ 1952 ዓ.ም የሕዝብ ማመላለሻ ታሪፍን
በማውጣት ጣልቃ መግባት ጀመረ፡፡ በመቀጠልም በ 1960 ዓ.ም የመስመር ፈቃድንና የጉዞ ቁጥጥርን የሚመራ
የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር የሚባል መንግሥታዊ አካል ተቋቋመ፡፡ አስተዳደሩ በህግ ክፍል ማስታወቂያ
ቁጥር 362/61 በተሰጠው የሥራ ኃላፊነት መሠረት ራሱና ውክልና በሰጣቸው ማዘጋጃ ቤቶች አማካይነት
የተሽከርካሪ ምርመራና ምዝገባ፣ የመንጃ ፈቃድ መስጠትና ማደስ የመሳሰሉትን ስራዎች እስከ 1969 ዓ.ም
ድረስ ሲያከናውን ቆይቷል፡

የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን /1969 - 1984/

በ 1966 ዓ.ም ከተደረገው የመንግሥት ለውጥ በኋላ የደርግ መንግሥት በ 1969 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 107/69
የመንገድ ትራንስፖርት አስተዳደርን የሚተካ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መ/ቤት በአዋጅ ቁጥር ......
አቋቋመ፡፡ ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ፡-

የፍጥነት ወሰን ደንብ፣

የክብደት መጠን ደንብ እንዲሁም

የታሪፍ ደንብ ወጥቷል

በዚህ አዋጅ ውስጥ የተካተቱት መሠረተ ሀሳቦች

የነበሩት ማህበራት ፈርሰው የቀጠና አሠራር መተካቱን፣

የማንኛውም የንግድ ተሽከርካሪ ስምሪት በመንግሥት በተቋቋሙት ኮርፖሬሽኖችና ቀጠናዎች ስር መሆኑን፣

የተሽከርካሪዎች ስምሪት በመንግሥት በሚዘጋጀው የቀጠና ስምሪት ፕሮግራም መሠረት መሆኑን፣

የክፍያ ታሪፍ መንግሥት በሚወስነው ደንብ መሠረት መሆኑን የሚደነግግ ነበር፡፡

በመሆኑም በወቅቱ የነበረው አሠራር የነፃ ገበያ አሠራርን የማያስተናግድ ከመሆኑም በላይ የእዝ ኢኮኖሚን
የሚያራምድ ስለነበረ የትራንስፖርቱ ኢንዱስትሪ እንዳይስፋፋና እንዲቀጭጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡

በአጠቃላይ የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎትና ስምሪት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲውል


በመደረጉ አዋጁ መንግሥት ተሽከርካሪዎችን እየተቆጣጠረ በፈለገው ሁኔታ ለመምራት እንዲያስችለው
የሚያደርግና የትራንስፖርት ባለሃብቶች በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ያላቸውን የማዘዝ ስልጣን የሚጋፋ ነበር፡፡
በአጠቃላይም ያለፈው መንግሥት ይከተለው በነበረው የተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት የመንገድ
ትራንስፖርት ዘርፍ የአገሪቱንና የህብረተሰቡን ፍላጎት ሳያሟላ እንዲቀር ሆኗል፡፡

ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ዘርፉን በተሻለ
መልኩ ለማደራጀትና የተሟላ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት እንዲቻል የመንገድ ትራንስፖርት
ባለስልጣንን እንደገና ለማቋቋም አዋጅ ቁጥር 14/84 በማውጣት ቀድሞ የነበሩትን የተዛቡና ለእድገት አመቺ
ያልሆኑ መዋቅሮችንና አሰራሮችን በተስተካከለ መዋቅርና አሰራር እንዲተኩ ከማድረጉም በላይ ለዘርፉ
መጎልበት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡

የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን /1984 - 1997/

በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት በ 1983 ዓ.ም ስልጣን ከያዘ በኋላ በአዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት
በ 1984 ዓ.ም የመንገድ ትራንስፖርትን ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 14/84 የወጣ ሲሆን አስፈፃሚው አካልም
የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ነበር፡፡

የአዋጁ ዓላማ፡-

ቀልጣፋና ኢኮኖሚያዊ የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖርና በተመጣጠነ ሁኔታ እንዲዳረስ ማድረግ፣

የተሳፋሪው ሕዝብ ደህንነትና ምቾት እንዲሁም የሚጓጓዘው ጭነት በሚገባ መጠበቁንና የትራንስፖርት
አገልግሎት ሳይቋረጥ አስተማማኝ በሆነ ስርዓት ለተገልጋዩ ሕዝብ መድረሱን ማረጋገጥ ናቸው፡፡

በዚህ አዋጅ ውስጥ የተካተቱት መሰረተ ሀሳቦች

የንግድ የመንገድ ትራንስፖርት ሥራ ከመንግሥት ቁጥጥር ወጥቶ ራሱን የቻለ መሆኑን

ማንኛውም ሰው ለንግድ የመንገድ ማመላለሻ ሥራ ላይ መሰማራት የሚችል መሆኑን

በህዝብ የንግድ የመንገድ ማመላለሻ ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው በግል ወይም በማህበር ተደራጅቶ መስራት
መቻሉንና የመሳሰሉትን ያካተተ ነበር፡፡

አዋጅ ቁጥር 14/84 ከሽግግሩ ወቅት ጀምሮ ለ 13 ዓመታት በስራ ላይ የቆየ ሲሆን የአሰራር ክፍተቶችን
ለመዝጋትና እንደገና ለማሻሻል እንዲሁም ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆኑ ከተሞችን የመንገድ
ትራንስፖርት እንዲሁም የውሃና የባቡር ትራንስፖርትን ከፌዴራል መንግሥት ትራንስፖርት ጋር ማደራጀት
አስፈላጊ በመሆኑ ነባሩን አዋጅ ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 468/97 ሐምሌ 30 ቀን 1997 ዓ.ም ወጥቷል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 468/97 ትራንስፖርትን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ አስፈፃሚ የትራንስፖርት ባለሥልጣን
መስሪያ ቤት በአዲስ መልክ ተቋቁሟል፡፡

You might also like