You are on page 1of 3

አብይ ጾም (ጾመ ሆዳዴ)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር በራሱ ፈቃድ
በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾመ። መጾሙ ግን ኃጢአት ሠርቶ ለስርየት፤ እሴት
ሽቶ ለበረከት አይደለም። ለምዕመናን አብነት ለመሆን ነው። አርባ ቀን መሆኑም ነቢያት አርባ ቀን
ጾመው ትንቢት የተናገሩለት እሱ መሆኑን ለማጠየቅ ነው። (ማቴ 4፥ 1-6)

አብይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ) ስምንት ሳምንታት ሲሆኑ የየራሳቸው ስያሜ አላቸው።

የመጀመሪያው እሁድ ( የካቲት 4 ቀን 2010 ዓም/Feb. 12, 2018)ዘወረደ


ይባላል። ዘወረደ መባሉ ጌታ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፤ ከድንግል ማርያም መወለዱንና
መሰቀሉን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሰንበት ነው። (ዮሐንስ 3፥1 ፤ መዝ 2፥11)

2ኛ እሁድ (የካቲት 11 ቀን 2010 ዓም/Feb. 18, 2018)ቅድስት ይባላል። ዛቲ


እለት ቅድስት ይእቲ። ይህች ቀን የተቀደሰች ናት፤ ያረፍኩባት ቅድስት ሰንበት ናት። ቅዱሳን ሁኑ፤
እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ በማለት የሰንበትን ቅድስና የሚያወሳ ምስጋና ለእግዚአብሔር
የሚቀርብበት እለት ነው።

3ኛ እሁድ (የካቲት 18 ቀን 2010 ዓም/February 25, 2018) ምኩራብ


ይባላል። ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ። በዚህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ
አይሁድ ምኩራብ መግባቱንና በምኩራብ የሚሸጡና የሚለውጡ ነጋዴዎችን በጅራፍ ገርፎ
በማስወጣት ቤተመቅደሱን ለማስከበሩ፤ እምነታቸው ከምግባር ጋር እንዲሆን የቤተመቅደሱ ፍቅር
ቅንዓት እንዲያድርባቸው ማስተማሩን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው። (ማቴ 21፥
12-13 ፤ዮሐንስ 2፥12-19 ፤ መዝ 68፥9)

4ኛ እሁድ (የካቲት 25, 2010 ዓም/March 4, 2018) መጻጉእ ይባላል።


አህይወ ኢየሱስ ለመጻጉእ። 38 ዓመት ሙሉ ሽባ ሆኖ የታመመውን መጻጉእን ጌታችን ያዳነበት፤
እውራንን ያበራበት፤ አንካሶች እንዲሄዱ ያደረገበት፤ አጋንንት ያደሩባቸውን አማኞች በቃሉ
መፈወሱን፤ ሙት ማስነሳቱን በማዘከር ምስጋና የሚቀርብበት ሰንበት ነው። (ዮሐንስ 5፥1-18፤
ማቴ 8፥1-37፤ ማር 7፥31-ፍፃሜ፤ ሉቃ 17፥ 19፤ ማቴ 9፥1)

5ኛ እሁድ (መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓም/March 11, 2018) ደብረዘይት ይባላል።


እምዘይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረዘይት ቀረቡ ሀቤሁ ኲሎሙ አርዳኢሁ በእለተ ሰንበት፤
ወይቤልዎ ነግረነ በምንት ይከውን ተአምሪሁ ለምጽአተከ ወለእልቀተ ዓለም። ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በደብረዘይት ተቀምጦ ሳለ በእለተ ሰንበት ደቀመዛሙርቱ ወደእርሱ ቀርበው የመምጣትህ
ምልክቱ፤ የዓለምስ ማለፍ ቀን መች ይሆናል ንገረን ብለው የጠየቁበት ሰንበት ነው። ጌታም
ለደቀመዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ሰማይ ከምድር ጋር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም፤
ከሐሰተኞች ነብያቶች ተጠንቀቁ፤ ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ በማለት ጌታ በደብረዘይት የዳግም
ምፅዓቱን ነገር ማስተማሩ ይነገርበታል፤ ነገሩስ እንደምን ነው ቢሉ ጌታችን ይህንን ዓለም ለማሳለፍ
ለሁሉም እንደየሥራው ለመክፈል በግርማ መንግሥቱ ይመጣል። (ማቴ 24፥1-50፤ ምር 13 ፥1፤
መዝ 49፥2፤ ቅዳሴ አትናቴዎስን ተመልከት)

6ኛ እሁድ (መጋቢት 9 ቀን 20107 ዓም/March 18, 2018) ገብርሄር ይባላል።


በዚህ ቀን የሚዘመረው ጾመ ድጓ ገብርሄር ወገብር ምዕመን ገብር ዘአስመሮ ለእግዚአ። ጌታ
ላስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው፤ ስለታማኝ አገልጋይ ያስተማረውን የሚያዘክር
ምስጋና ይቀርብበታል። በእምነታቸውና በታማኝነታቸው ብቁ ሆነው የተገኙ የሚያገኙትን ዋጋ፤ ክፉና
ሀሴተኛ የሆኑ አገልጋዮች የሚጠብቃቸው መከራ በስፋት ይነገርበታል። ገብርሄር ማለት ደግና ታማኝ
አገልጋይ ማለት ነው። (ማቴ 25፥14-30፤ መዝ 39፥10)

7ኛ እሁድ (መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓም/March 25, 2018) ኒቆድሞስ ይባላል።


ኒቆድሞስ የጌታ ደቀመዝሙር ነው። ኒቆድሞስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን የአይሁድ አለቃና መምህር
ነው። ጌታችን ለኒቆድሞስ ሰው በስጋ ውልደት ብቻ ሳይሆን ከውሃና ከመንፈስ እንደገና በመወለድ
ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ ግድ ነው ብሎ የምስጢረ ጥምቀትን ነገር በስፋት ያስተማረበት
ትልቅ እለት ነው። (ዮሐንስ 3፥1-21፤ መዝ 16፥3፤ 1ና ዮሐንስ 4፥18 ፤ ሮሜ 7፥1)

8ኛ እሁድ (መጋቢት 23, 2010 ዓም/April 1, 2018) ሆሣዕና ይባላል። ይህ


ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየተመሰገነና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ
ወደኢየሩሳሌም የገባበት እለት ነው። መድኃኒትነቱን የተረዱ በጌትነትና በክብር፤ በውዳሴና በቅዳሴ፤
ሆሣዕና በአርያም እያሉ ሕፃናትና ሽማግሌዎች ምስጋና ያቀረቡበት ታላቅ በአል ነው። በልዋ ለወለተ
ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ፤ የጽዮንን ልጅ እነሆ ጻድቅ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያይቱና በውርንጭላይቱ ላይ
ተቀምጦ ወደአንቺ ይመጣል በሏት የሚለው የነብያት ትንቢት ተፈጸመበት። ይጠብቁት የነበረው
እውነተኛው መድኃኒት እርሱ መሆኑን ያሳየበት ታላቅ ሰንበት ነው። (ማቴ 21፥1-17፤ ማር
11፥1-10፤ ሉቃስ 19፥29፤ ዮሐንስ 12 ፥12 ፤ ት/ዘካርያስ 9፥9 ፤ 2ኛ ነገሥት 9፥13 ፤
ት/ኢሳይያስ 56፥7፤ ት/ኤርምያስ 7፥12፤ መዝ 8፥2)

ከሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ድረስ (መጋቢት 23, ቀን 2010 ዓም እስከ መጋቢት
30,ቀን 2010 ዓም/April 1-8, 2018) ያለው ሰባት ቀን ሰሙነ ሕማማት ይባላል።
በዚህ ሳምንት ውስጥ የጌታን መከራና ሞት የሚያስታውሱ ቅዱሳት መጽሐፍት ይነበባሉ። ስግደትም
በየተወሰነው ሰዓት ይሰገዳል። ልዩ ልዩ የፀሎት ስርዓትም ይካሄዳል። አዳም ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ
የኖረውን የመከራና የጨለማ ዘመን በማስታወስ መንበረ ታቦቱ በጥቁር መጐናጸፊያ ይሸፈናል።
ካህናቱም በዚሁ ሰሞን ለአገልግሎት የሚለብሱት ልብሰ ተክህኖም ጥቋቁር ነው። (ኢዩኤል 2፥21 ፤
ማቴ 21፥18 ፤ ሚክያስ 2፥ 3-13 ፤ኢሳያስ 50፥1 ፤ ሉቃ 13፥23 ፤ ዘፀዓት 19፥1 ፤ ኤርምያስ
17፥1 ፤ መዝ 41፥6)

እለተ ሐሙስ (ፀሎተ ሐሙስ)(መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓም/April 5, 2018)፤


ከስቅለት በፊት ያለው ሐሙስ እለተ ሐሙስ ይባላል። በዚሁ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን የመስዋዕት ስርዓት ሠርቷል። ፀሎተ ሐሙስ አሮጌው ሕግ የተደመሰሰበት፤
አዲስ ስርዓት የተተከለበት፤ ዘላቂ ፈውስ የተገኘበት፤ እኩልነት የታወጀበት እለት ስለሆነ በከፍተኛ
መንፈሳዊ ስሜት ይከበራል። በዚሁ እለት ቅዳሴ መቀደስ እንዳለበት የቤተክርስቲያናችን ስርዓት
ያዛል። ከቅዳሴው ቀደም ብሎ ካህናቱ የምዕመናንን እግር በቤተክርስቲያን ውስጥ ያጥባሉ። ጌታችን
የጸሎተ ሐሙስ እለት ራሱን ዝቅ አድርጐ የሐዋርያትን እግር ተንበርክኮ በማጠብ ትህትናንም
ያስተማረበት እለት ነው። (ዮሐ 13 ፥1-18 ፤ ሉቃ 22፥19 ፤ ማቴ 26፥26 ፤ ማር 14፥2 ፤
መሣፍንት 19፥21 ፤ ዘፍጥረት 18፥4 ፤ 1ኛ ጢሞቲዎስ 5፥10)

ከእለተ ሐሙስ ቀጥሎ ያለው አርብ (መጋቢት 28 ቀን 20109 ዓም/April 6,


2018) ስቅለት ይባላል። በዚህም እለት የስቅለቱ ነክ የሆኑ ምንባባት ሁሉ ሲነበቡ ይውላሉ።
ስግደቱም ከሰሞኑ የበለጠ ነው። ሰርክ ሰዓት ሲሆን እያንዳንዱ ምዕመን በሰሙነ ሕማማት ውስጥ
የሠራውን ኃጢአት ወደካህኑ በመቅረብ ይናዘዛል። ካህናቱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠቡ ተጨማሪ
ፀሎትና ስግደት ለምዕመናኑ በመስጠት ፈጣሪያቸውን ይቅርታ እንዲጠይቁ ያዛሉ፤ ምዕመናኑም
ትዕዛዙን ተግባራዊ በማድረግ ከፈጣሪያቸው ይቅርታና ምህረትን እንዳገኙ ያምናሉ። በመጨረሻም
ንስብሖ ለእግዚአብሔር ሰቡሐ ዘተሰብሐ የሚለውን ምስጋና በማቅረብ ምዕመናኑ በደስታ መንፈስ
ተሞልተው ወደየቤታቸው ይመለሳሉ። ይህም በቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ በናፍቆት የሚጠበቅ
ታላቅ እለት ነው። (ዮሐ 19፥ 1-ፍፃሜ ፤ ማቴ 27፥1 ፤ ት/ሕዝቅኤል 22 ፥23 ፤ ት/ ዘካርያስ
11፥11 ፤ ት/ኢሳያስ 13 ፥1 ፤ ማቴ 27፥27 ፤ ዘፀዓት 12 ፥1)

በዓለ ትንሣኤ (መጋቢት 30 ቀን 2010 ዓም/April 8, 2018) ፤ ክርስቶስ ከሙታን


ተነሣ! በታላቅ ኃይልና ሥልጣን፤ ሰይጣንን አሠረው፤ አዳምን ነፃ አወጣው። ከዛሬ ጀምሮ ድስታና
ሰላም ሆነ ተብሎ የታወጀበት በዓለ ትንሣኤው ነው። ጌታችን ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን፤ ሞትን
በሞቱ ድል መንሣቱን፤ ሙስና መቃብርን ፤ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረት መጥፋቱን፤ በሞቱ
በመስቀሉ ያዳናቸውን በትንሣኤው ማስነሳቱን ፤ በዝግ ቤት ገብቶ በፍርሃት ለነበሩት ሐዋርያት
ሰላምን፣ እርቅን መስበኩን ቤተክርስቲያን በስፋት ታስባለች። ትንሣኤ ማለት መነሳት ፤ መቆም ማለት
ነው። ከበሽታ ድኖ መነሳት ትንሣኤ ነው፤ በተለይም ከሞትና ከመቃብር በሕይወት መነሳት ትንሣኤ
ይባላል። ሞቶ ከተቀበረ ከአራት ቀን በላይ የሆነውን አልዓዛርን ጌታችን በቃሉ አልዓዛር ሆይ ተነሳ
ወደ ውጭ ና ብሎ ከሞት በማስነሳት ከመቃብር አወጣው። ትንሣኤ ማለት ይህ ነው። ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም በተዋሐደው ሥጋ ከሞተና ከተቀበረ በኋላ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጐ
መነሳቱ አማናዊ እውነተኛ ትንሣኤ ይባላል። በአዳም ምክንያት ያመጣውንም ሞት ይሽር ዘንድ
በተዋሐደው ሥጋ ሞቶ ተቀበረ ከዚያም በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ። (ዮሐ 20፥1 ፤ ሉቃ
24፥1 ፤ ማቴ 28፥1 ፤ ማር 16፥1 ፤ መዝ 77፥65 ፤ ዮሐ 11፥43 ፤ ዮሐ 5፥9 ፤ 1ና ቆሮ 15፥20 ፤
የሐ ሥራ 2፥22)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
ከደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን

You might also like