You are on page 1of 38

የቦሎቄ ሰብል አመራረት መመሪያ: ደቡብ ኢትዮጵያ ተኮር

አዘጋጅ

ዋለልኝ ወርቁ (ዶ/ር)

የተዘጋጀዉ

በካናዳ ዓለም-አቀፍ የምግብ ዋስትና ምርምር ፈንድ በሚደገፈዉ


"የጥራጥሬ ሰብል ቴክኖሎጅወችን ማስፋፋት ለምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና
በደቡብ ኢትዮጵያ" በተባለዉ ፕሮጀክት እገዛ ነዉ

ሰኔ 2007 ዓ.ም.

I-:sJlIhr: GZiUt l.... lta;.t If..~rrm::f. ~ IDRClcRDI


ru:~,·~",'tI4W'.I::.r~
Utu.r~;:~,~.::J:Jlt
rsrsrv'
~t1'(E~·1'1·,:o.Pltf.,(~lf''f1
ማዉጫ

ርዕስ ገጽ

ማዉጫ-----------------------------------------------------------------------------ii
የሠንጠረዥ ማዉጫ ------------------------------------------------------------iv
የስዕል ማዉጫ ------------------------------------------------------------------v
1. መሰረታዊ መረጃዎች---------------------------------------------------------1
1.1 አጠቃላይ -----------------------------------------------------------1
1.2 ቦሎቄን ማምረት የሚያስገኘዉ ጠቀሜታ ---------------------3
1.3 ምርታማነት -------------------------------------------------------4
1.4 የቦሎቄን ምርት የሚቀንሱ ማነቆዎች -------------------------4
1.5 ለቦሎቄ ተስማሚ ስነ-ምኅዳር -----------------------------------6
2. የቦሎቄን ምርታማነት ማሳደጊያ የአመራረት ዘዴዎች -----------------7
2.1 የተሸሻሉ ዝርያወችን መጠቀም ---------------------------------7
2.2 ጥራት ያለዉ ዘር መጠቀም ------------------------------------12
2.3 የማሳ ዝግጀት ----------------------------------------------------13
2.4 የአዘራር ዘዴና የዘር ምጣኔ -----------------------------------14
2.5 የዘር ወቅት ------------------------------------------------------15
2.6 ማዳበሪያ አጠቃቀም --------------------------------------------16
2.7 አረም ቁጥጥር --------------------------------------------------17
2.8 ተባይ ቁጥጥር --------------------------------------------------18
2.9 በሽታ ቁጥጥር --------------------------------------------------22
2.10 ምርት ስብሰባ -------------------------------------------------23

ii
ርዕስ ገጽ

2.11 ምርት ክምችት ----------------------------------------------24


3. የአመራረት ዘይቤ -------------------------------------------------------25
3.1 ለብቻ መዝራት -----------------------------------------------25
3.2 አሰባጥሮ መዝራት -------------------------------------------25
3.3 አፈራርቆ መዝራት ------------------------------------------30
4. ምንጮች -----------------------------------------------------------------31

iii
የሠንጠረዥ ማዉጫ

ሠንጠረዥ ገጽ

1፡ የቦሎቄና የበቆሎ የንጥረ ምግብ ይዘት በንጽጽር ---------------------- 3


2፡ ለሀገር ዉስጥ ፍጆታና ለዉጭ ገበያ የሚሆኑ በደቡብ
ኢትዮጵያ በተለያየ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋሉ ዝርያዎች--------------- 8

iv
የስዕል ማዉጫ

ስዕል ገጽ
1፡ የቦሎቄ አምራች አካባቢዎች በኢትዮጵያ ------------------------------------2
2: በደቡብ ክልል ከፍተኛ ቦሎቄ አብቃይ አካባቢዎች ለቦሎቄ የዋለ
መሬት በ2005 ዓ.ም. -----------------------------------------------------2
3፡ የቦሎቄ ምርታማነት በተለያየ ደረጃ ------------------------------------------5
4፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚታወቁት ዝርያዎች መካከል፤ ፍሬዎቹ
በቀለምና በመጠን ይለያያሉ ---------------------------------------------10
5፡ ዉስን ቀጥተኛ (ግራ) እና ኢዉስን ቀጥተኛ (ቀኝ) ዝርያዎች ለብቻ
ተዘርተዉ ------------------------------------------------------------------11
6፡ ኢዉስን ሀረጋማ ዝርያወች ሲመረቱ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤
የአደጋገፍ ስልቶች (ግራ)፣ በተዘረጉ ገመዶች ላይ (መካከል)
እና በሶስትዮሽ በተተከሉ ረጅም እንጨቶች ላይ (ቀኝ)---------------11
7፡ ርቀቱን ጠብቆ በመሰመር የተዘራ ቦሎቄ በምርምር ማሳ (ግራ) እና
በገበሬ ማሳ (መካከል)፤ርቀቱን ሳይጠብቅ በአግባቡ ያልተዘራ
ቦሎቄ በገበሬ ማሳ (ቀኝ)------------------------------------------------15
8፡ ሕያዉ ማዳበሪያ ከፎሰፎረስ ማዳበሪያ ጋር ጥሩ ዉጤት
ያስገኛል፤ በተመረጠ የህያዉ ማዳበሪያ ታሽቶ የተዘራ ዘር
ከፎስፎረስ ማዳበሪያ ጋር (ግራ)፣ በተመረጠ የህያዉ ማዳበሪያ
ታሽቶ የተዘራ ዘር ያለ ፎስፎረስ ማዳበሪያ (መካከል) እና
በሕያዉ ማዳበሪያ ታሽቶ ያልተዘራ ዘር ያለ ፎስፎረስ
ማዳበሪያ (ቀኝ) ---------------------------------------------------------17
9፡ ቆራጭ ትል ------------------------------------------------------------------19

v
ስዕል ገጽ

10፡ የቦሎቄ አገዳ ትል የተጎዳዉ አገዳ ሲሰነጥቅ የሚታይ ሲሆን


ጉዳቱም ከፍተኛ ነዉ --------------------------------------------------20
11፡ የጓይ ትል -------------------------------------------------------------------21
12፡ በክሽክሽ የተጎዳ የቦሎቄ ሰብል--------------------------------------------21
13፡ የቦሎቄ ነቀዝ ----------------------------------------------------------22
14፡ የቦሎቄ ዋግ (ግራ)፤ አንተራክኖስ (መካከል) እና ባክቴሪያል
ብላይት (ቀኝ) በሽታወች ------------------------------------------------23
15፡ አብረዉ የተዘሩ ዉስን ቀጥተኛ (ግራ) እና ኢዉስን ከፊል ሀረጋማ
(ቀኝ) የቦሎቄ ዝርያወች ከበቆሎ ጋር በአንድ ጊዜ በመዝራት
ተሰባጥረዉ ---------------------------------------------------------------27

16፡ በቆሎና ቦሎቄ አንድ ለአንድ (ግራ) እና አንድ ለሁለት (ቀኝ)


በሆነ አቀማመጥ በስብጥር ተዘርተዉ ---------------------------------28
17፡ በአግባቡ ያልተሰባጠረ አዘራር ለቦሎቄዉም ሆነ ለበቆሎዉ አይበጅም-29
18፡ የበቆሎዉን የታች ቅጠሎች በማንሳት በቅብብሎሽ ለሚዘራዉ ቦሎቄ
ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል፤ ቦሎቄ የበቆሎ ቅጠል ተነስቶ
ሲዘራ (ግራ) እና የበቆሎ ቅጠል ሳይነሳ ሲዘራ (ቀኝ) ---------------30

vi
1. መሰረታዊ መረጃዎች

1.1 አጠቃላይ
ቦሎቄ በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ተፈላጊ ሰብል ነዉ፡፡
በዓለማችን በአንደኛ ደረጃ የሚገኝ ተመራጭ የጥራጥሬ ሰብል ሲሆን
በሀገራችን ደግሞ ከባቄላ ቀጥሎ በሁለተኛነት ይገኛል፡፡ በአትዮጵያ
ዉስጥ በኦሮምያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች በስፋት ይመረታል (ስዕል
1)፡፡ የሀገር አቀፍ የቦሎቄ ምርት አስተዋጽኦቸዉም ኦሮምያ ክልል 51
በመቶ፣አማራ ክልል 24 በመቶ እና ደቡብ ክልል ደግሞ 21 በመቶ
ነዉ፡፡ በደቡብ የሀገራችን ክልል ደግሞ በአንደኛ ደረጃ በስፋት የሚመረት
የጥራጥሬ ሰብል ነዉ፡፡ በአብዛኛዉ የደቡብ ክልል አካባቢወች ቦሎቄ
የሚመረት ሲሆን ሲዳማ፣ ወላይታና ጋሞ ጎፋ ዞኖች ከፍተኛዉን ድርሻ
ይይዛሉ (ስዕል 2)፡፡ በዚህ ክልል ቦሎቄ ለብቻና በስብጥር ይመረታል፡፡

1
-
_,.,~dOt
-,~.....",.

---
0 __

ስዕል 1፡ የቦሎቄ አምራች አካባቢወች በኢትጵያ


(ምንጭ፡ Alemu et al. 2009, cited in IFPRI, 2010)
20000
ለቦሎቄ የዋለ መሬት (በሄክታር)

16000

12000

8000

4000

0
ሲዳማ ደቡብ ወላይታ ሀድያ ከፋ ጋሞ ጎፋ ዳዉሮ ስገን
ኦሞ ሕዝቦች
ዞን

ስዕል 2: በደቡብ ክልል ከፍተኛ ቦሎቄ አብቃይ አካባቢዎች ለቦሎቄ የዋለ መሬት
በ2005 ዓ.ም. (ምንጭ፤የኢትዮጵያ ማዕከላዊ የስታቲሰቲክስ ድርጅት፤ 2005 ዓ.ም.)

2
ቦሎቄ የያዛቸዉ ንጥረ ምግቦች ለጤናማና የተሟላ አመጋገብ አስተዋጽኦ
ያበረክታሉ፡፡ ይኸዉም በመጀመሪያ ደረጃ ከፍተኛ ፕሮቲንና ጥሩ የንኡስ
ንጥረ ምግብ ክምችት ስላለዉ ነዉ (ሠንጠረዥ 1)፡፡ ከፕሮቲን ይዘቱም
ጋር በተያያዘ ቦሎቄን "የድሃ ስጋ" የሚል ስም የሚሰጡት አሉ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የፕሮቲን ስሪቱ በብርዕ ሰብሎች ጉድለት
የሚገኝባቸዉን የፕሮቲን አካላት በማካካስ ስለሚረዳ ነዉ፡፡ ስለዚህ
የበቆሎና የስራስር ሰብሎች ምግብ በሚዘወተርበት የደቡብ አትዮጵያ
አካባቢወች ቦሎቄ ለተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ
ያደርጋል፡፡

ሠንጠረዥ 1፡ የቦሎቄና የበቆሎ የንጥረ ምግብ ይዘት በንጽጽር

ንጥረ ምግብ ቦሎቄ* በቆሎ*


ካርቦሃይድሬት 57.8 75.0
ፕሮቲን 22.9 8.5
ስብ 1.6 3.0
አሰር (ፋይበር) 4.0 2.2
ማዕድናት 3.6 1.3
*ቀሪዉ ዉሃ ነዉ

1.2 ቦሎቄን ማምረት የሚያስገኘዉ ጠቀሜታ


1. አጭር የመድረሻ ጊዜ ያላቸዉን ዝርያዎች በመጠቀም በአንድ የሰብል
ወቅት ሁለት ጊዜ ማምረት ያስችላል
2. ለምግብ ፍጆታነት ከመዋሉም በላይ ተሸጦ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ
ለገበሬዉ ያስገኛል
3. ከፍ ያለ የፕሮቲን ይዘት ስላለዉ የተመጣጠነ አመጋገብ እንዲኖር
ያግዛል
4. በአስተዳደግ ባህርይዉና በሚፈልገዉ ጊዜ አመችነት የተነሳ ከሌሎች
ሰብሎች ጋር ተሰባጥሮ ሊመረት ይችላል
3
5. ረጅም ጊዜ የሚፈጁ ሰብሎች በዝናብ እጥረት ምክንያት በተሰናከሉ
ጊዜ ተተኪ ሆኖ ሊመረት ይችላል
6. ለዉጭ ገበያ ቀርቦ የዉጭ ምንዛሪ ያስገኛል፤በዚህም ከጥራጥሬ
ሰብሎች ዋናዉን ድርሻ ይይዛል፡፡

1.3 ምርታማነት
የአገራችን ገበሬዎች ብሔራዊ አማካይ የቦሎቄ ምርት በሄክታር 1. 26
ቶን (12.6 ኩንታል) ሲሆን የደቡብ ክልል ደግሞ 1.14 ቶን (11.4
ኩንታል) ነዉ (ስዕል 3)፡፡ የዓለም አቀፍ አማካይ ምርት ደግሞ 0.80
ቶን በሄክታር (8 ኩንታል) ነዉ፡፡ ነገር ግን የተሻሻሉ የአመራረት
ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም የአገራችን ገበሬወች የቦሎቄን ምርት
በአማካይ ወደ 2.5 ቶን (25 ኩንታል) በሄክታር ማሳደግ ይችላሉ፡፡
በተስማሚ ስነ ምህዳርና በተስተካከለ አመራረት የቦሎቄ ምርታማነት
በሞዴል ገበሬዎች እስከ 3.2 ቶን (32 ኩንታል) በሄክታር ሊደርስ
እንደሚችል ታይቷል፡፡

1.4 የቦሎቄን ምርት የሚቀንሱ ማነቆወች-


የቦሎቄን ምርት ከሚቀንሱ ችግሮች መካከል የሚከተሉት በዋናነት
ይጠቀሳሉ፡-
 ወቅቱን ጠብቆ አለመዝራት
 መሬቱን በደንብ አለማረስ
 የዘር መጠኑን አለመጠበቅ
 በወቅቱ አለማረም
 በቂ የተባይና የበሽታ ቁጥጥር አለማድረግ
 የተሻሻሉ ዝርያወችን አለመጠቀም
 እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉትን ግብአቶች በተሟላ መልኩ
መጠቀም አለመቻል
 የአፈር ለምነት ማጣት
 የዝናብ እጥረት
4
 የጎተራ ተባዮች እና
 በሚመለከታቸዉ አካላት የሚሰጠዉ ትኩረት በንጽጽር አናሳ
መሆን

2.5
ምርት በቶን ከአንድ ሄክታር

1.5

0.5

0
ኢትዮጵያ-አማካይ ደቡብ ክልል- ዓለም አቀፍ- በተሻሻለ አመራረት
አማካይ አማካይ የሚገኝ-አማካይ

ስዕል 3፤ የቦሎቄ ምርታማነት በተለያየ ደረጃ፤(አንድ ቶን አስር ኩንታል ነዉ)

5
1.5 ለቦሎቄ ተስማሚ ስነ-ምኅዳር

ቦሎቄ ከቆላ ጥራጥሬ ሰብሎች የሚመደብ ሲሆን ሞቅ ያለ የአየር ጸባይ


ያላቸዉ አካባቢወች ይስማሙታል፡፡ አማካይ የአየር ሙቀት መጠናቸዉ
ከ 18 እስከ 24 oC የሆኑ አካባቢዎች ለቦሎቄ ምርት ተመራጭ ናቸዉ፡፡

ቦሎቄን አሲዳማ (ኮምጣጣ) ባልሆኑና ዉሃ በማያቁሩ ማሳወች ላይ በጥሩ


ሁኔታ ማምረት ይቻላል፡፡ የአፈሩ ኮምጣጣነት ከ 6.5 እስከ 7.5 ቢሆን
ተመራጭ ሲሆን ከ 5.0 ማነስ ወይም ከ 8.0 መብለጥ የለበትም፡፡

በኢትዮጵያ ከ1000 እስከ 2000 ሜትር ከፍታና ከ 500 እሰከ 1100


ሚ.ሜ. የዝናብ መጠን ባላቸዉ አካባቢወች ቦሎቄን ማብቀል ይቻላል፡፡
በዕድገቱ ወቅት ከ 300 እስከ 400 ሚ.ሜ. ዉሃ ይፈልጋል፡፡ ቦሎቄ
የዉሃ እጥረትም ሆነ ብዛት በጣም ይጎዳዋል፡፡ የዉሃ እጥረት በተለይ
በአበባዉ ጊዜና ፍሬዉን በሚሞላበት ጊዜ ያጋጠመዉ እንደሆነ ከፍተኛ
የሆነ የምርት መቀነስ ይከሰታል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ጊዜያት አፈሩ ዉስጥ
ያለዉ ዉሃ ከ 50 በመቶ እንዳያንስ በማድረግ የምርት መቀነስን
መከላከል ይቻላል፡፡ በተመሳሳይም ዉሃ እንዳይተኛ የማፋሰሻ ቦዮችን
በመቅደድና ዉሃ የማይቋጥር ማሳ በመጠቀም በተረፈ ዉሃ ምክንያት
የሚከሰተዉን ጉዳት መከላከል ይቻላል፡፡

6
2. የቦሎቄን ምርታማነት ማሳደጊያ የአመራረት
ዘዴወች

2.1 የተሸሻሉ ዝርያወችን መጠቀም

የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ አንዱ


የተመሰከረለት አማራጭ ነዉ፡፡ ይሄ አማራጭ አሁን በመገኘት ላይ ባለዉ
ዝቅተኛ ብሔራዊ አማካይ ምርትና የተሻሻሉ የአመራረት ሂደቶችን
በመከተል ሊገኝ በሚችለዉ ምርት መካከል ያለዉን ክፍተት ለመሙላት
ጉልህ ድርሻ አለዉ፡፡

የቦሎቄ ሰብል በአስተዳደግ ባህርይ የሚለያዩ ብዙ የተሻሻሉ የዝርያ


አማራጮች አሉት (ሠንጠረዥ 2)፡፡ ከተሸሻሉ ዝርያዎች የሚፈለገዉን
ዉጤት ለማግኘትም ገበሬዎች ትክክለኛ የዝርያ ምርጫ ማድረግ
ይገባቸዋል፡፡ ተገቢዉን ዝርያ ለመምረጥ መታየት ያለባቸዉ ነጥቦች
የሚከተሉት ናቸዉ፡-

ሀ. አካባቢዉን መላመድ መቻል

አንድ ዝርያ ምርታማ ለመሆን የአካባቢዉን የአፈር፣ የዝናብና ሌሎች


የአየር ጸባይ ባህርያትን ተላምዶ ማደግ ይገባዋል፡፡የተለያዩ አካባቢወች
ደግሞ በእነዚህ ባህርያት ይለያያሉ፡፡ ስለዚህ ዝርያወች በሚፈለጉበት
አካባቢ ወይም በሌላ ተመሳሳይ አካባቢ ከተደረጉ የግምገማ ዉጤቶች
ተነስቶ አካባቢዉን ተላምደዉ በተገቢዉ ሁኔታ ማደግ የሚችሉ
ዝርያዎችን መለየት ይገባል፡፡ ቦሎቄ በአጠቃላይ ከሁለት እስከ አምስት
ወር የሚፈጅባቸዉን ዝርያወች ይይዛል፡፡ ለምሳሌ አጭር የዝናብ ወቅት
ላላቸዉ አካባቢወች ይህንኑ ወቅት ተጠቅመዉ በቶሎ መድረስ የሚችሉ
ዝርያዎች ተመራጭነት ይኖራቸዋል፡፡ ኢዉስን ሀረጋማ ዝርያወች ረዥም
7
የዕድገት ዑደት ስላላቸዉ ለማምረት ረዘም ያለ የዝናብ ስርጭት ያላቸዉ
አካባቢወች ያስፈልጉታል፡፡

ሠንጠረዥ 2፡ ለሀገር ዉስጥ ፍጆታና ለዉጭ ገበያ የሚሆኑ በደቡብ ኢትዮጵያ


በተለያየ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋሉ ዝርያዎች
የዝርያ ለምርት የዘር ሰብሉ የዕድገት ዋና የ100 የዘር
ስም የወጡበት መጠን የሚፈጅበት ባህርይ አግልግሎት ዘሮች ቀለም
ጊዜ በኪ. ግ. ጊዜ (ቀን) ክብደት
(እ.ኤ.አ1) (ግራም)
ሳሪ-1 2011 70-80 90-110 ኢዉስን ለሀገር ዉስጥ 17.3 ክሬም
ቀጥተኛ ፍጆታ
ሀዋሳ 2008 70-80 85-110 ኢዉስን ከፊል ለሀገር ዉስጥ 21.5 ጥቁር
ዱሜ ቀጥተኛ ፍጆታ ቀይ
ኢባዶ 2003 90-100 90-110 ዉስን ቀጥተኛ ለሀገር ዉስጥ 44.5 ቀይ
ፍጆታ ዥንጉር
ጉር
ኦሞ-95 2003 70-80 95-110 ኢዉስን ከፊል ለሀገር ዉስጥ 17.9 ጥቁር
ሀረጋማ ፍጆታ ቀይ
ናስር 2003 70-80 85-95 ኢዉስን ከፊል ለሀገር ዉስጥ 20.9 ጥቁር
ሀረጋማ ፍጆታ ቀይ
ቀይ 1974 70-80 90-110 ኢዉስን ከፊል ለሀገር ዉስጥ 20.5 ጥቁር
ወላይታ2 ሀረጋማ ፍጆታ ቀይ
አዋሽ-1 1990 70-80 85-100 ኢዉስን ከፊል ለዉጭ ገበያ 17.5 ነጭ
ሀረጋማ
አዋሽ- 1999 70-80 85-100 ኢዉስን ከፊል ለዉጭ ገበያ 17.3 ነጭ
መልካ ሀረጋማ
1
‚ እንደ ኤዉሮፓዉያን አቆጣጠር፤ 2‚ ከቀይ ወላይታ በስተቀር ሁሉም የተሻሻሉ ዝርያወች ናቸዉ

ለ. ከፍተኛ ምርት የመስጠት አቅም

አንድን አካባቢ ተላምደዉ ማደግ ከሚችሉት ዝርያዎች መካከል ከፍተኛ


ምርት የሚሰጠዉን ዝርያ በመለየት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል፡፡
ምክንያቱም ዝርያዎች በተፈጥሮ ባገኙት ባህርይ ምክንያት በምርታማነት
ይለያያሉ፡፡ በተጨማሪም እንደየአካባቢዉ ተጨባጭ ሁኔታ የሚመረጠዉ
ዝርያ ሌሎች ተጨማሪ ተፈላጊ ባህርያት እንዲኖሩት ማድረግ ይቻላል፡፡

8
ለምሳሌ ድርቅን የመቋቋም አቅም ፡፡ በዝርያ ግምገማ ወቅት የተጠቃሚ
ገበሬወች ተሳትፎ ተፈላጊዉን ዝርያ ለመምረጥ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ሐ. በሽታና ተባይን የመቋቋም ችሎታ

ዝርያዎች በሽታና ተባይን በመቋቋም ባህርያቸዉ ይለያያሉ፡፡ አንዳንዶቹ


በከፍተኛ ደረጃ መቋቋም ሲችሉ ሌሎቹ ደግሞ በመቋቋም ችሎታቸዉ
መካከለኛ፣ ዝቅተኛ ወይም አቅም አልባ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በተቻለ
መጠን የሚመረጡ ዝርያወች በሚፈለጉበት አካባቢ ያሉ የበሽታና የተባይ
ችግሮችን መከላከል የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ዝርያወች
በሽታና ተባይን መቋቋም የሚችሉ ከሆነ፡-

 ለጸረ በሽታና ጸረ ተባይ መድሃኒቶች የሚወጣዉን ወጭ


ያስወግዳል
 ለአንዳንድ የበሽታ ዓይነቶች ለምሳሌ እንደ ቦሎቄ ዋግና
አንትራክኖስ ያሉ በሽታወች ተቋቋሚ ዝርያወችን መጠቀም ዋነኛ
አማራጭ በመሆኑ

መ. ዝርያዎች ያላቸዉ ተቀባይነት

አንድ ዝርያ በአካባቢዉ ተቀባይነት ካለዉ ጥሩ የገበያ ዋጋ ስለሚኖረዉ


ለገበሬዉ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ለዝርያ ተቀባይነት አስተዋጽኦ
ከሚያደርጉ ባህርያት መካከል የዘሩ (ፍሬዉ) ቀለም መጠንና ጣዕም፣
ለመብሰል የሚፈጀዉ ጊዜ፣ ከምርቱ የሚሰራዉ ምግብ ጥራት እና
የመሳሰሉትን ይይዛል፡፡ ቦሎቄ ለዉጭ ገበያ ወይም ለአካባቢ ፍጆታ
(ለሀገር ዉስጥ) ተብሎ ሊመረት ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ
ገበሬዎች ለምርት የሚመርጧቸዉ ዝርያዎች ገዥ ደንበኞቹ
የሚፈልጓቸዉን ባህርያት ያካተቱ መሆናቸዉን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡
የቦሎቄ ዝርያወች ካለቸዉ የአስተዳደግና የአቋም ልዩነቶች በተጨማሪ
በዘር ባህሪያት ልዩነታቸዉ ይታወቃሉ (ለምሳሌ ስዕል 4)፡፡

9
ሀዋሳ ዱሜ ኢባዶ ኦሞ-95
ሣሪ-1

ናስር ቀይ ወላይታ አዋሽ-1 አዋሽ-መልካ


ስዕል 4. በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚታወቁት ዝርያዎች መካከል፤ ፍሬዎቹ በቀለምና
በመጠን ይለያያሉ፡፡

ሰ. የአመራረት ዘይቤዉ

ቦሎቄ ለብቻዉ ከመመረት በተጨማሪም ተስማሚ የእድገት ባህርያት


ስላሉት ከሌሎች ሰብሎች ጋር በስብጥር ሊመረት ይችላል፡፡ ለሁለቱም
የአመራረት ዘዴዎች ተስማሚዉን ዝርያ መጠቀም አስፈላጊ ነዉ፡፡ ዉስን
ቀጥተኛና ኢዉስን ቀጥተኛ ዓይነቶች ቦሎቄን ለብቻ በስፋት ለማምረት
አመች ናቸዉ (ሰዕል 5)፡፡ ኢዉስን ሀረጋማ ዓይነቶችን ለብቻ ለመዝራት
ግን ድጋፍ አስፈላጊ ነዉ (ሰዕል 6)፡፡ አብሮ ከበቆሎ ጋር በስብጥር
በሚዘራበት ጊዜ ተገቢዉን ዝርያና የአስተዳደግ ባህርይ መጠቀም ይገባል
(ክፍል ሦስትን ይመልከቱ)፡፡

10
በአሁኑ ጊዜ ሀዋሳ ዱሜና ናስር የተባሉት ባለ ቀይ ዘር የተሻሻሉ
ዝርያዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ገበሬወች ተቀባይነት እያገኙ ነዉ፡፡

ገበሬወች ሊገነዘቡት የሚገባዉ ነገር ቢኖር የተሻሻሉ ዝርያወችን


ሲጠቀሙ የተሻሻሉ የአመራረት ዘዴዎችን በቅንጅት አብረዉ መጠቀም
ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ የተሻሻሉ ዝርያወችን መጠቀም ብቻዉን
ለሚፈለገዉ ዉጤት አያበቃም፡፡

ስዕል 5፡ ዉስን ቀጥተኛ (ግራ) እና ኢዉስን ቀጥተኛ (ቀኝ) ዝርያዎች ለብቻ ተዘርተዉ

ስዕል 6፡ ኢዉስን ሀረጋማ ዝርያዎች ሲመረቱ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤የአደጋገፍ


ስልቶች (ግራ)፣ በተዘረጉ ገመዶች ላይ (መካከል) እና በሶስተዮሽ በተተከሉ ረጅም
እንጨቶች ላይ (ቀኝ)
ምንጭ፡ https://www.google.com.et/?gws_rd=ssl#q=climbing+bean+images)
11
2.2 ጥራት ያለዉ ዘር መጠቀም

ተፈላጊዉ ዝርያ ከተመረጠ በኋላ ተከታዩ ተግባር የዚህን ዝርያ ጥራት


ያለዉ ዘር ማዘጋጀት ነዉ፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ ከተመረጠዉ ዝርያ
የምንጠብቀዉን ዉጤት ማግኘት የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ጥራት ያለዉ
ዘርን መጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ያለዉ አስተዋጽኦ በአማካይ 15
እስከ 20 በመቶ ሊደርስ ይችላል፡፡ ጥራት ያለዉ ዘር የሚከተሉትን
መስፈርቶች ሊያሟላ ይገባዋል፡፡ እነዚህም፡-

ሀ. ከፍተኛ የብቅለት አቅም

የማይበቅል ዘር ለምርት ተግባር ሙሉ በሙሉ ዋጋ የሌለዉ ሲሆን


አነስተኛ የብቅለት አቅም ያለዉም ቢሆን ጠቀሜታዉ በጣም ዝቅተኛ
ነዉ፡፡ ዘሮች ከፍተኛ የመብቀል ሀይል እንዲኖራቸዉ፡-

 የእድገት ጊዜያቸዉን ጨርሰዉ የታጨዱና ሙሉ ፍሬ ያላቸዉ


ሊሆኑ ይገባል
 በነቀዝ፣ በሌሎች የጎተራ ተባዮችና በበሽታ ያልተጠቁ መሆን
አለባቸዉ
 በጎተራ ዉስጥ በአግባቡ ተጠብቀዉ የተቀመጡና ለረጅም ጊዜም
በጎተራ ዉስጥ ያልቆዩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
(ለተጨማሪ ነጥቦች 2.11ን ይመልከቱ)

ለ. ከበሽታ አምጭ ተህዋስያን የጸዳ መሆን

አንዳንድ የበሽታ ዓይነቶች ከአንድ የሰብል ወቀት ወደ ሚቀጥለዉ ከዘሩ


ጋራ ተቀላቅለዉ በሚገኙ ጥቃቅን ተህዋስያን አማካይነት ይሸጋገራሉ፡፡
ይህ እንዳይሆን ዘሩ ከእነዚህ ተህዋስያን ነጻ መሆን ይገባዋል፡፡

12
ሐ. ከአረም ዘሮች ነጻ መሆን

ዘሩ የአረም ዘሮች የተቀላቀሉበት ከሆነ ሁለቱም እኩል አብረዉ


ስለሚበቅሉ በሰብል እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ከመፍጠራቸዉም በላይ
እነርሱን ለመቆጣጠር ገበሬዉ ለከፍተኛ የገንዘብና የጉልበት ወጭ
ይዳረጋል፡፡

መ. ከሌላ ዝርያ ወይም ሰብሎች ዘር ጋር ያልተቀየጠ

ዘሩ ከሚፈለገዉ ሰብልና ዝርያ ሊሆን ይገባል እንጅ ከሌላ ጋር የተቀየጠ


መሆን የለበትም፡፡ ይህም የአመራረት አመችነትንና የገበያ ተፈላጊነትን
ታሳቢ በማድረግ ነዉ፡፡

የገንዘብ አቅም ከፈቀደና አቅርቦቱ በሚኖርበት ጊዜ የተመሰከረለት ዘር


ገዝቶ መጠቀም ተመራጭ ነዉ፡፡ ይሁን እንጅ ገበሬዎች ካመረቱት ምርት
ላይ ከላይ የተጠቀሱትን ሁኔታወች ታሳቢ በማድረግ ለዘር መጠቀም
ይችላሉ፡፡ በማንኛዉም መንገድ ቢሆን ለዘር የሚዉለዉ ቦሎቄ የብቅለት
መጠኑ ከ75 በመቶ ማነስ የለበትም፤ ከ 90 በመቶ በላይ ቢሆን
ተመራጭ ነዉ፡፡

2.3 የማሳ ዝግጀት

የቦሎቄ ማሳ ከሶስት እስከ አራት ጊዜ እንዲታረስ ይመከራል፡-


 የመጀመሪያዉ እርሻ ከቦሎቄ በፊት የተዘራዉ ሰብል እንደተነሳ
 ዘር ከመዘራቱ በፊት እንደ አፈሩ ሁኔታ ከሁለት እስከ ሶስት
ጊዜ ማረስ ያሰፈልጋል፡፡

13
2.4 የአዘራር ዘዴና የዘር ምጣኔ

በመስመር መዝራት በብተና ከመዝራት ተመራጭነት አለዉ፡፡ ምክንያቱም


በመስመር መዝራት የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት፡-
 ሰብሉ ማደግ ሲጀምር ኩትኳቶ፣ አረም፣ ኬሚካል ርጭትና
የመሳሰሉትን ተግባራት ለማከናወን አመች ነዉ
 ተክሎቹ በማሳዉ ላይ በተስተካከለ ስርጭት (ስዕል 7) ስለሚያድጉ
ዉሃና ማዕድናትን በተሻለ ዉጤታማነት ይጠቀማሉ
 የተሻለ ምርት ይሰጣል

በመስመር መዝራት ምንም እንኳን ተጨማሪ ጉልበት ቢጠይቅም


በንጽጽር የሚገኘዉ ጥቅም በብተና ከመዝራት የላቀ ነዉ፡፡

ቦሎቄ የሚዘራዉ መስመሮችን በ 40 ሳንቲ ሜትር በማራራቅ ሲሆን


ዘሮቹ ደግሞ በ10 ሳንቲ ሜትር ልዩነት ይቀመጣሉ፡፡

መስመር ለማዉጣት የተለየ መስመር ማዉጫ ካልተገኘ ቀጠን ያለ ድግር


መጠቀም በቂ ነዉ፡፡
በመስመር ዉስጥ ዘር የመዝራቱን ስራ ለማፋጠን በረጅም እንጨት ላይ
በየ 10 ሳንቲ ሜትር ምልክት አደርጎ መጠቀም ይቻላል፡፡ ረጅም ገመድ
ላይ በየ 10 ሳንቲ ሜትር ምልክት አበጅቶም በዚያዉ መሰረት ዘሮቹን
እየጣሉ መሄድ ይቻላል፡፡ ብቅለቱን አስተማማኝ ለማድረግ ሁለት ሁለት
ዘር ማስቀመጥ ወይም ዘር ለመቆጠብ አንድና ሁለት ዘር በማፈራረቅ
መዝራት ይገባል፡፡ አንድ ቦታ ላይ ሁለቱም ከበቀሉ አስከ ሁለት ሳምንት
ባለዉ ጊዜ ደከም ያለዉን መርጦ ማስወገድ ይገባል፡፡

በአማካይ ትንንሽ የዘር መጠን ላላቸዉ ከ 70-80 ኪሎ ግራም ዘር


ለአንድ ሄክታር የሚበቃ ሲሆን ትልልቅ የዘር መጠን ላላቸዉ ደግሞ ከ
90-100 ኪሎ ግራም ዘር ያስፈልጋል፡፡ ዘሩ ዝቅ ያለ የብቅለት ኃይል
የሚኖረዉ ከሆነ የዘር መጠኑን መጨመር ይገባል፡፡
14
አጠቃላይ የመዝሪያ ጥልቀት ከ 3 እስከ 6 ሳንቲሜትር ሲሆን
የመዝሪያዉን ጥልቀት እንደ አፈሩ የእርጥበት ሁኔታ መወሰን ይገባል፡፡
በዘር ወቀት ያለዉ እርጥበት አነስተኛ ከሆነና የላይኛዉ አፈር እርጥበት
አልባ ከሆነ የመዝሪያዉን ጥልቀት መጨመር ጥሩ ነዉ፡፡ አፈሩ በቂ
እርጥበት ካለዉ በአነስተኛ ጥልቀት መዝራት ይገባል፡፡

ስዕል 7፡ ርቀቱን ጠብቆ በመስመር የተዘራ ቦሎቄ በምርምር ማሳ (ግራ) እና


በገበሬ ማሳ (መካከል)፤ ርቀቱን ሳይጠብቅ በአግባቡ ያልተዘራ ቦሎቄ በገበሬ ማሳ
(ቀኝ)

2.5 የዘር ወቅት


የዘር ወቅት በየአካባቢዉ እንደየዝናቡ ወቅትና እንደ አመራረት ዘይቤዉ
ይለያያል፡፡ ቦሎቄ በአንጻራዊነት በአጭር ጊዜ የሚደርስ በመሆኑ ለምሳሌ
በደቡብ ኢትዮጵያ በአንድ ማሳ ላይ ሁለት ጊዜ ማምረት ይቻላል፡፡
የመጀመሪያዉ የበልጉ ዝናብ እንደጀመረ በመጋቢት የሚዘራ ሲሆን
ሁለተኛዉ ደግሞ የመጀመሪያዉ ሰብል ከተነሳ በኋላ በሐምሌ ሊዘራ
ይችላል፡፡

በስብጥር ሲዘራም በአንዳንድ አካባቢ በቆሎ ከተዘራ በኋላ አራት ሳምንት


ያህል ዘግይቶ በግንቦት ሊዘራ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የበቆሎ ስብል
የመጨረሻ የእድገት ደረጃዉን ሲጀምር በቅብብሎሽ ከስሩ ሊዘራ ይችላል፡፡
ይሄዉም በነሐሴ ሊሆን ይችላል፡፡
በተለይ በበልግ ለብቻ በሚዘራበት ወቅት ዝናቡ እንደጀመረ መሆን
ይገባዋል፡፡

15
2.6 ማዳበሪያ አጠቃቀም

እንደሰዉና እንስሳት ሁሉ ተክሎችም በሚገባ አድገዉ ጥሩ ዉጤት


ማስገኘት እንዲችሉ በእድገታቸዉ ወቅት የተሟላ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ናይትሮጅንና ፎስፎረስን የመሳሰሉት ዓበይት ማዕድናት ተክሎች በስፋት
የሚፈልጓቸዉ ቢሆኑም በአፈር ዉስጥ ያላቸዉ ክምችት አናሳ በመሆኑ
ፍላጎታቸዉ አይሟላም፡፡ ስለዚህ ሰብሎች የተሟላ እድገት እንዲኖራቸዉ
ተጨማሪ ማዳበሪያ መስጠት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለቦሎቄ ሰብል ይሄንን
በሁለት ዓይነት መንገድ ማሟላት ይገባል፡፡

ሀ. ኬሚካል ማዳበሪያ
ቦሎቄ አፈሩን የማዳበር ጠባይ ቢኖረዉም እንደ አፈሩ ለምነት ሁኔታ
እስከ 100 ኪሎ ግራም ዳፕ እና እስከ 50 ኪሎ ግራም ዩሪያ በሄክታር
መጨመር ያስፈልጋል፡፡ ይሄንንም ለዘር በተቀደደዉ መስመር ላይ ከዘሩ
መስመር 2 ሳ.ሜ. ያህል አርቆ ከጎን መጨመር ነዉ፡፡

ለ. ሕያዉ ማዳበሪያ
ናይትሮጅን የሚባለዉን ማዕድን ተክሎች ከማናቸዉም በላቀ ሁኔታ
የሚፈልጉትና ለእድገታቸዉ ወሳኝ የሆነ ነዉ፡፡በተጨማሪም ይሄ ማዕድን
በቀላሉ በዉሃ በመታጠብና በትነት ስለሚባክን በአብዛኛወቹ የገበሬ
ማሳዎች ዉስጥ በበቂ መጠን አይገኝም፡፡ ይህም በመሆኑ ገበሬወች ጥሩ
የቦሎቄ ምርት ለማግኘት ኬሚካል ማዳበሪያ ከመጠቀም በተጨማሪ
ሕያዉ ማዳበሪያ መጠቀም ይገባቸዋል፡፡ ይሄም ከተፈጥሮ የማዳበሪያ
ዘዴዎች አንዱ ሲሆን በጥራጥሬ ሰብሎች ስር ተጣብቀዉ በሚያድጉ
በዓይን በማይታዩ ራይዞቢያ በሚባሉ ህያዉ ተህዋስያን ዓማካይነት
የሚከናወን ነዉ፡፡
እነዚህ ተህዋስያን ከቦሎቄ ስሮች ጋር ተጣብቀዉ በተመጋጋቢነት
ይኖራሉ፡፡ ተህዋስያኑ የሚኖሩትና ናይትሮጅን የማንጠር ስራቸዉን
የሚያከናዉኑት የሰብሉ ስር ላይ በሚፈጠሩ ድቡልቡል አካላት ዉስጥ
በመኖር ነዉ (ስዕል 8)፡፡ እነዚህ ተህዋስያን በስሩ ያሉት ሰብል
16
ከተህዋስያኑ የናይትሮጅን አቅርቦት ያገኛል፡፡ ተህዋስያኑ ዉጤታማ
እንዲሆኑ፡-
 በአፈር ዉስጥ በበቂ መጠን መገኘት አለባቸዉ
 ዉጤታማ የተሕዋስያን ዝርያ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ስለዚህ የቦሎቄዉን ዘር በተመረጠ ህያዉ ማዳበሪያ አሽቶ መዝራት
አስፈላጊ ነዉ፡፡ በተለይ ለቦሎቄ በሕያዉ ማዳበሪያ አሽቶ መዝራት እጅግ
አስፈላጊ የሚሆነዉ ማሳዉ ከዚህ ቀደም ለቦሎቄ ምርት ስራ ያልዋለ
ከሆነ ነዉ፡፡ የህያዉ ማዳበሪያ ተህዋስያን በሚገባ አንድ ጊዜ ከተጨመሩ
እንደ ኬሚካል ማዳበሪያ በየወቅቱ እንዲጨመሩ አያስፈልግም፡፡ ለረጅም
ጊዜ አፈር ዉስጥ በመቆየት ናይትሮጅን የማንጠር ስራቸዉን ማከናወን
ይችላሉ፡፡ የህያዉ ማዳበሪያን የግብርና ባለሙያወችን በማማከር በግዥ
ማግኘት የሚቻል ሲሆን ዝርዝር የአጠቃቀም መመሪያዉም ከማዳበሪያዉ
ጋር አብሮ ይሰጣል፡፡

ስዕል 8፡ ሕያዉ ማዳበሪያ ከፎሰፎረስ ማዳበሪያ ጋር ጥሩ ዉጤት ያስገኛል፤ በተመረጠ የህያዉ ማዳበሪያ
ታሽቶ የተዘራ ዘር ከፎስፎረስ ማዳበሪያ ጋር (ግራ)፣ በተመረጠ የህያዉ ማዳበሪያ ታሽቶ የተዘራ ዘር ያለ
ፎስፎረስ ማዳበሪያ (መካከል) እና በሕያዉ ማዳበሪያ ታሽቶ ያልተዘራ ዘር ያለ ፎስፎረስ ማዳበሪያ (ቀኝ)፡፡
(ምንጭ፡ ደምስ ዘዉዱ፣ 2008 እ.ኤ.አ.)

2.7 አረም ቁጥጥር

ከፍተኛ ምርት ለማግኘት የቦሎቄ ማሳ ከአረም ነጻ መሆን አለበት፡፡


ቦሎቄዉ ከተዘራ ከሁለተኛዉ ሳምንት ጀምሮ ማበብ እስኪጀምር ድረስ
17
ሁለት ጊዜ ማሳዉ መታረም አለበት፡፡ ቦሎቄዉ ከአበበ በኋላ ማረም
አይመከርም፡፡ ምክንያቱም አበባዉ እንዲረግፍ ስለሚያደርግና በሽታም
በሰብሉ ዉስጥ በፍጥነት እንዲተላለፍ ስለሚያደርግ ነዉ፡፡ቦሎቄን በእጅ
ማረም የተሻለ አማራጭ ሲሆን ኬሚካልም መጠቀም ይቻላል፡፡
የመጀመሪው አረም ቦሎቄው ከተዘራ ከ 2-3 ሳምንት ባለው ጊዜ
ውስጥ ሲደረግ ሁለተኛዉ ደግሞ እንደ ዝርያው እድገት ታይቶ አበባ
ከማበቡ በፊት ከተዘራ 4-5 ሳምንት ባለዉ ጊዜ ሊከናወን ይችላል፡፡

ቀለል ያለ ኩትኳቶ በመጀመሪያዉ የአረም ወቅት ማካሄድ አፈሩን


በማላላት ዉሀ እንዲሰርግ፣ አየር እንዲዘዋወርና አረምም ለማስወገድ
ስለሚጠቅም ጥሩ ነዉ፡፡ ኩትኳቶ ከተደረገ በቂ ዝናብ ባለበት ጊዜ መሆን
ይገባዋል፡፡

ኬሚካል መጠቀም ካስፈለገ አላክሎር የተባለዉን መጠቀም ይቻላል፡፡


ኬሚካሉ ጊዜ ያላለፈበት መሆኑን ማረጋገጥና በአምራቹ ድርጀት
የተሰጡትን መመሪያወች ተረድቶ በተግባር ማዋል ያስፈልጋል፡፡

2.8 ተባይ ቁጥጥር


ሀ. ቆራጭ ትል

ቆራጭ ትል (ስዕል 9) ሰብሉን በለጋነት እድሜዉ ያጠቃል፡፡ ማታ ማታ


ከአፈር ዉስጥ በመዉጣት እጽዋቶቹን ከስራቸዉ ይቆርጣቸዋል፡፡ ቆራጭ
ትልን ለመከላከል፡-

 ጧት ጧት ማሳዉን በማየት ጉዳት የታየ እንደሆነ ትሎችን


ማስወገድ
 ከፍ ያለ የዘር መጠን መጠቀም

18
ስዕል 9፡ ቆራጭ ትል ምንጭ፡ http://www.infonet-biovision.org/default/ct/118/crops

ለ. የቦሎቄ አገዳ ትል

ይህ ተባይ የቦሎቄዉ የታች አገዳ ዉስጥ በመግባት በአገዳዉ ላይ ከፍተኛ


ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን በስሩ እድገት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል (ስዕል
10)፡፡ በተለይ ሰብሉ በለጋነት ጊዜዉ የሚጠቃ ሲሆን እድገቱ በተለያዩ
ችግሮች ለምሳሌ በድርቅ በሚጎዳበት ጊዜ ተጋላጭነቱ በእጅጉ
ይጨምራል፡፡

የቦሎቄ አገዳ ትልን ለመከላከልና ለመቋቋም፡-


 ዘሩን ጋዉቾ በተባለዉ ጸረ ተባይ ለዉሶ መዝራት
 ወቅቱን ጠብቆ በጊዜ መዝራት
 ሰብሉ የተሟላ እድገት እንዲኖረዉ የሚረዱ የአመራረት ዘዴወችን
መጠቀም፤ ለምሳሌ የአፈሩን ለምነት መጠበቅ፣የአፈር እርጠበትን
መጠበቅ
 ጨርሰዉ የተጎዱ ዕጽዋትን ከማሳዉ ማስወገድ
 ከበቀለ ከ 2 አስከ 3 ሳምንት ባለዉ ጊዜ ኮትኩቶ አፈር
ማስታቀፍ የተጎዱ ሰብሎች እንዲያገግሙ ይረዳል፤ በተለይ በቂ
እርጥበት የተገኘ እንደሆነ፡፡

19
ስዕል 10፡ የቦሎቄ አገዳ ትል የተጎዳዉ አገዳ ሲሰነጥቅ የሚታይ ሲሆን ጉዳቱም
ከፍተኛ ነዉ (ምንጭ፡ http://www.infonet-biovision.org/default/ct/118/crops)

ሐ. የጓይ ትል

የጓይ ትል (ሰዕል 11) በእሸትነት ጊዜ ወደ ፍሬ ከረጢቱ በመግባት


ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፤ ጓይ ትልን ለመቀነስ ወይም ለመቆጣጠር፡-
 የትሉን መከሰት በጊዜ ለማወቅ የማያቋርጥ ክትትል ማድረግ
 አነስተኛ ከሆነ ትሉንና የተጠቃዉን የፍሬ ከረጢት በእጅ
ማስወገድ
 ጥቃቱ ከፍ ያለ ከሆነ (በማሳው ውስጥ 10 በመቶ የሚሆነው
የቦሎቄ ተክል የጓይ ትል ከታየበት) እንደ ሳይፐርሜትሪን እና
ካራቴ ያሉ ጸረ ተባይ መደሃኒቶችን አንድ ጊዜ መርጨት
 ቦሎቄን ከበቆሎ ጋር አሰባጥሮ መዝራት

20
ስዕል 11፡ የጓይ ትል (ምንጭ፡ http://www.infonet-biovision.org/default/ct/118/crops)

መ. ክሽክሽ

ክሽክሽ የዕጽዋቱን ምግብ በመምጠጥ እድገታቸዉን ያቀጭጫል፡፡


በተለይ ቁጥራቸዉ ብዙ ከሆነ በሰብሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ
(ስዕል 12)፡፡

ክሽክሽን ለመቆጣጠር፡-

 ብዛታቸዉ ከፍተኛ ከሆነ (በማሳው ውስጥ ከ30-40 በመቶ በሚሆኑ


የቦሎቄ ተክሎች ላይ ክሽክሽ ከታየ) እንደ ፌነትሮታዮንና ዳያዚኖን
ያሉ ጸረ ተባይ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ስዕል 12፡ በክሽክሽ የተጎዳ የቦሎቄ ሰብል


(ምንጭ፡ http://www.infonet-biovision.org/default/ct/118/crops)
21
ሰ. የቦሎቄ ነቀዝ

የቦሎቄ ነቀዝ (ሰዕል 13) ቦሎቄን በመጋዘን ወይም በጎተራ ዉስጥ


ያጠቃል፡፡ ይህን ተባይ ለመቆጣጠር፡-

 ጎተራዎችን በሚገባ ማጽዳት


 ወደ ጎተራ የሚገባዉን ዘር በሚገባ ማድረቅ
 አዲስ የተመረተዉን ከቆየዉ ጋር ደባልቆ አለማስቀመጥ
 ፎስቶክሲን የተሰኘዉን ኬሚካል መጠቀም

ሰዕል 13፡ የቦሎቄ ነቀዝ


(ምንጭ፡ http://www.infonet-biovision.org/default/ct/118/crops)

2.9 በሽታ ቁጥጥር


ቦሎቄን ከሚያጠቁ ዋና ዋና በሽታዎች መካከል የቦሎቄ ዋግ፣
አንትራክኖስ እና ባክቴሪያል ብላይት ይጠቀሳሉ፡፡ በሽታዎቹ በአብዛኛዉ
የሰብሉን ቅጠል የሚያጠቁ ሲሆን በተለያየ ደረጃም የዘር ከረጢቱን ሊጎዱ
ይችላሉ (ስዕል 14)፡፡ እነዚህን በሽታወች ለመከላከል፡-

 ንጹህና በበሽታ ያልተጠቃ ዘር መጠቀም


 ቦሎቄን በአንድ ማሳ ላይ አከታትሎ አለመዝራት
 በሽታን የመቋቋም ባሕርይ ያላቸዉን ዝርያዎች መጠቀም
 እጽዋቶቹ በዝናብ በረጠቡ ጊዜ በማሳዉ ዉስጥ የተለያዩ ስራዎችን
ለመስራት አለመዘዋወር ስርጭቱ እንዳይባባስ ይረዳል
 አፈራርቆ መዝራት

22
ስዕል 14፡ የቦሎቄ ዋግ (ግራ)፤ አንተራክኖስ (መካከል) እና ባክቴሪያል ብላይት (ቀኝ)
በሽታወች
(ምንጭ፡ http://www.infonet-biovision.org/default/ct/118/crops፤
http://www.ipm.ucdavis.edu/PMG/r52101111.html)

2.10 ምርት ስብሰባ


ቦሎቄ አብዛኛዎቹ የዘር ከረጢቶች (ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት)
መድረቅ ሲጀምሩ መሰብሰብ መጀመር አለበት፡፡ ስብሰባዉ ሲጀመር የዘሩ
የእርጠበት መጠን ከ 16 በመቶ ማነስ የለበትም፡፡ ምክንያቱም በጣም
ከደረቀ የዘር ከረጢቱ ተከፍቶ ዘሩ መሬት ላይ ወድቆ ሊቀር ይችላል፡፡
እንዲያዉም ተመራጭ የሚሆነዉ ቀደም ብሎ ሰብስቦ ሰብሉ ከመወቃቱ
በፊት ለተጨማሪ ጊዜ አመች ቦታ ላይ እንዲደርቅ ማድረግ ነዉ፡፡
የምርት ብክነትን ለመቀነስ የዘር ከረጢቶቹ በቀኑ ሙቀትና ጸሀይ ክዉ
ብለዉ ከመድረቃቸዉ በፊት ስብሰባዉን ማለዳ ማከናወን ይመረጣል፡፡

በሚወቃበት ጊዜ የዘር የእርጥበት መጠኑ ከ 14 በመቶ ባያንስ ጥሩ


ነዉ፡፡ ይኸዉም ዘሩ በጣም በደረቀ ጊዜ ለሁለት ስለሚፈረከስ ጥራቱ
የተጓደለ ይሆንና የገበያ ዋጋን ይቀንሳል፡፡

ዉቂያን እንደሰብሉ ብዛትና የቴክኖሎጅ አቅርቦት በተለያየ መንገድ


ማካሄድ ይቻላል፡፡

 አንድ ላይ እየመጠኑ ሰብስቦ ወይም በማዳበሪያ (ፕላሰቲክ


ከረጢት) አስገብቶ በዱላ በመምታት

23
 በተስተካከለ ወለል ላይ ወፍራም ፕላስቲክ ወይም ሸራ አንጥፎ
ላዩ ላይ ትራክተር በማስኬድና
 በመዉቂያ መኪና

2.11 ምርት ክምችት

ምርቱ በጎተራ በሚከማችበት ጊዜ ለተጨማሪ ጊዜ በማድረቅ የዘር


የእርጥበት መጠኑ ከ 11 በመቶ እንዳይበልጥ ማድረግ ተገቢ ነዉ፡፡
በደንብ ያልደረቀ እንደሆን ለጎተራ ተባዮችና በሽታወች መከሰት አመች
ከመሆኑም በላይ ዘሩም የምግብ ይዘቱን፣ ጣዕሙንና የብቅለት ኃይሉን
በአጭር ጊዜ ሊያጣ ይችላል፡፡ ዘር ጤንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ የዘሩ
የእርጥበት መጠንና የማስቀመጫዉ ሙቀት እጅግ ወሳኝ ናቸዉ፡፡ ብዙ
እርጥበት ያለዉ ዘር የተቀመጠ እንደሆነ በአጭር ጊዜ ሰብሉ በተባይና
በበሽታ ተጠቅቶ ጥራቱን ያጣል፡፡ በሞቃታማ አካባቢ በሚከማችበት
ጊዜም ምርቱ በአጭር ጊዜ ሊበላሽ ይችላል፡፡ የእርጥበት መጠኑ 13
በመቶ የሆነ ዘር መካካለኛ ሙቀት ባለዉ ማከማቻ (25 oC) የብቅለት
ኃይሉን ሳያጣ ለአንድ ዓመት ያህል መቆየት ሲችል 10 በመቶ ያለዉ
ደግሞ አስከ ሶስት ዓመት መቆየት ይችላል፡፡ በተጨማሪም ረዘም ላለ ጊዜ
ማከማቸት ሲያስፈልግ የጎተራ ተባዮችን የሚከላከሉና ለዚሁ አገልግሎት
ተብለዉ የተዘጋጁ ኬሚካሎችን ገዝቶ መጠቀም ይቻላል፡፡ ኬሚካሉ
የሚገዛዉ ለዚሁ ተግባር ፈቃድ ካላቸዉ አቅራቢወችና ስለአጠቃቀሙም
በቂ ማብራሪያ ከጽሁፍ መግለጫ ጋር ማቅረብ ከሚችሉ ድርጅቶች
መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በተጨማሪም የግብርና ባለሙያወችን እገዛ
መጠየቅ ይገባል፡፡

24
3. የአመራረት ዘይቤ

ከላይ እንደተጠቀሰዉ ቦሎቄ በአስተዳደግ ባሕርይና በአቋሙ ስለሚለያይ


የተለያየ የአመራረት ዘይቤ ለመከተል አመች ነዉ፡፡ ስለዚህ ለብቻ ወይም
በስብጥር ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሊመረት ይችላል፡፡

3.1 ለብቻ መዝራት


ቦሎቄን ለብቻ መዝራት የሚዘወተረዉ የተሻለ የመሬት ይዞታ ባላቸዉ
ገበሬወች ነዉ፡፡ በመካከለኛዉ የስምጥ ሸለቆ አካባቢወች ቦሎቄ በዚህ
መንገድ ይመረታል፡፡ በተጨማሪም ሰብሉ በሰፋፊ ማሳ ላይ በእርሻ
ማሳለጫ መኪናወች ታግዞ በሚመረትበት ጊዜ ለብቻ ይዘራል፡፡ ከላይ
በክፍል 3 የተጠቀሱትን ቴክኖሎጅወችንና ተሞክሮወችን ስራ ላይ
በማዋል ቦሎቄን ለብቻ በሚገባ ማምረት ይቻላል፡፡

3.2 አሰባጥሮ መዝራት


ቦሎቄ ከሌሎች ሰብሎች ጋር ተሰባጥሮ ሊመረት ይችላል፡፡ በደቡብ
አትዮጵያ ከበቆሎ፣ እንሰት፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ሙዝና እንዲሁም ከቡና ጋር
ተሰባጥሮ ይዘራል፡፡ በስፋት የሚታወቀዉ ግን ከበቆሎ ጋር ተሠባጥሮ
የሚዘራዉ ነዉ፡፡ ይሄ የአመራረት ዘይቤ በብዛት አነስተኛ የመሬት ይዞታ
ባላቸዉ ገበሬወች ይዘወተራል፡፡

አሰባጥሮ መዝራትን ተመራጭ የሚያደርጉ ምክንያቶች፡-


 ምርትን በመጨመር ዉስን መሬትን በተሻለ ዉጤታማነት
ለመጠቀም ያስችላል
 የምርት መዋዠቅን በማስቀረት በዚህ ምክንያት የሚከተለዉን
ለአደጋ ተጋላጭነት ይቀንሳል
 የሰብል በሽታና ተባዮችን የማሳ ዉስጥ ስርጭት ይቀንሳል
 የማዳበሪያ ወጭን ይቀንሳል

25
ምንም እንኳን አሰባጥሮ መዝራት ለገበሬዎች አዲስ ባይሆንም ስራዉን
ዉጤታማ ለማድረግ በምርምር የተደገፉ አሰራሮችን መከተል አስፈላጊ
ነዉ፡፡ ስለዚህ ይህን የአመራረት ዘይቤ የበለጠ ትርፋማ ለማድረግ ከላይ
በክፍል ሦስት ከተገለጡት በተጨማሪ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነጥቦች
ማስተዋል ይገባል፡፡

ሀ. ተሰባጥረዉ የሚዘሩትን ዝርያወች መለየት

አብረዉ የሚዘሩት ዝርያዎች ቢቻል የሚደጋገፉ ቢሆኑ የሚመረጥ ሲሆን


አንዱ በአንደኛዉ ላይ ጉዳት የሚያሰከትል ግን መሆን የለባቸዉም፡፡
ገበሬዎች አሰባጥረዉ ሲዘሩ አንዱ ዋና ሰብላችዉ ሲሆን ሁለተኛዉ
ደግሞ ተጨማሪ ጥቅም ለማስገኝት የሚገባ ተጓዳኝ ሰብል ነዉ፡፡ በቆሎና
ቦሎቄ ሲሰባጠሩ ዋናዉ ሰብል በቆሎ ነወ፡፡ ስለዚህ ስብጥሩ የዚህን ሰብል
ምርት እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ሀይለኛ
የቦሎቄ ዝርያወች እንዳይሰባጠሩ ይመከራል፡፡ ኢዉስን ሀረጋማ የቦሎቄ
ዝርያዎች በበቆሎዉ ላይ በመጠምጠም እድገቱን በማቀጨጭ የበቆሎዉን
ምርት ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ተሰባጣሪወቹ አብረዉ የሚዘሩ ወይም ስብጥሩ
በበቆሎ ለጋ ዕድሜ የሚደረግ ከሆነ ዉስን ቀጥተኛና ኢዉስን ቀጥተኛ
ዓይነቶች (ስዕል 15) ተመራጭ ሲሆኑ በቅብብሎሽ ለመዝራት ደግሞ
ኢዉስን ከፊል ሀረጋማና ኢዉስን ሀረጋማ ዝርያወችን በተጨማሪ
መጠቀም ይቻላል፡፡ በስዕል 15 እንደሚታየዉ ተሰባጣሪወቹ አብረዉ
በሚዘሩበት ጊዜ ኢዉስን ከፊል ሀረጋማ ዝርያወች እንኳን በበቆሎዉ ላይ
ጠንከር ያለ ተጽእኖ በማድረግ ምርቱን ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ ስብጥሩ
በቅብብሎሽ ከሆነ በቆሎዉ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ በተጽእኖ እንዳይጎዳ
ያደርገዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ተሻሽለዉ የወጡ እንደ ሀዋሳ ዱሜና ኢባዶ ያሉ ዝርያዎች


በንጽጽር ሲታዩ ገበሬዉ በተለምዶ ይጠቀምበት ከነበረዉ ቀይ ወላይታ
ተብሎ ከሚታወቀዉ ዝርያ ይልቅ ከበቆሎ ጋር በስብጥር በጣም የተሻለ
26
ምርት ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ ለስብጥርም ሆነ ለብቻ አመራረት የተሻሻሉ
ዝርያወችን መጠቀም ተመራጭ ነዉ፡፡

ሰዕል 15፡ አብረዉ የተዘሩ ዉስን ቀጥተኛ (ግራ) እና ኢዉስን ከፊል ሀረጋማ (ቀኝ)
የቦሎቄ ዝርያዎች ከበቆሎ ጋር በአንድ ጊዜ በመዝራት ተሰባጥረዉ

ለ. የስብጥሩን መጠን መወሰን

የዋናዉ ሰብል ለምሳሌ የበቆሎ ብዛት ወይም የዘር መጠን ለብቻ


ሲዘራ ከሚያስፈልገዉ መጠን ማነስ አይገባዉም፡፡ የቦሎቄዉ ብዛት ደግሞ
የዋና ሰብሉን ምርታማነት በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ ስለዚህ
የቦሎቄዉ መጠን ለብቻ ከሚዘራበት መጠን እስከ እኩሌታ ድረስ ዝቅ
መደረግ አለበት፡፡ ለብቻም ይሁን በስብጥር በማንኛዉም ቦታ ቢሆን
በማሳ ላይ ሊኖር የሚገባዉ የሰብል ብዛት የሚወሰነዉ አካባቢዉ ባለዉ
የዝናብ አቅርቦትና ያፈር ለምነት ላይ በመመርኮዝ ነዉ፡፡ በተጨማሪም
ስብጥሩ በቅብብሎሽ በሚሆንበት ጊዜ የቦሎቄዉን ብዛት ለብቻ ከሚዘራዉ
ማሳነስ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፤ ዋና ሰብሉ የደረሰበት የእድገት ደረጃ
ከተጽእኖ ዉጭ ስለሚያደርገዉ፡፡

27
ሐ.የሰብሎቹን የተርታ አቀማመጥ መወሰን

የተሰባጣሪወቹ ሰብሎች አቀማመጥ ዉሃን፤ማእድናትንና የጸሀይ ብርሃንን


በብቃት ለመጠቀም የሚያስችላቸዉ መሆን ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም
ለመዝራት፤ ለአረም፤ ለአጨዳና ለመሳሰሉት ክንዉኖች የሰብሎቹ
አቀማመጥ አመች ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ አንድ መስመር በቆሎ ከአንድ
መስመር ወይም ከሁለት መስመር ቦሎቄ ጋር ተመራጭ እንደሆነ
ታይቷል (ስዕል 16)፡፡ አንድ መስመር በቆሎ ከአንድ መስመር ቦሎቄ ጋር
መዝራት ሁለቱንም ተሰባጣሪወች ለመኮትኮት የተሻለ ክፍተት ስለሚሰጥ
አመች ነዉ፡፡ በተለይ ስብጥሩ በቆሎዉ ከመኮትኮቱ በፊት ከተከናወነ
የአንድ ለአንድ የተርታ አቀማመጥ ተመራጭ ነዉ፡፡ ስብጥሩ ከታች
እንደተገለጸዉ በቅብብሎሽ የሚደረግ ከሆነ የአንድ ለሁለት አቀማመጥ
ከስብጥሩ የተሻለ የቦሎቄ ምርት ለማግኘት ይረዳል፡፡ በአግባቡ
ያልተሰባጠረ አዘራር ለስራ አመች ካለመሆኑም በላይ ለተሰባጣሪ ሰብሎቹ
እድገትም አመች አይደለም (ስዕል 17)፡

ስዕል 16፡ በቆሎና ቦሎቄ አንድ ለአንድ (ግራ) እና አንድ ለሁለት (ቀኝ) በሆነ
አቀማመጥ በስብጥር ተዘርተዉ

28
ስዕል 17፡ በአግባቡ ያልተሰባጠረ አዘራር ለቦሎቄዉም ሆነ ለበቆሎዉ አይበጅም

መ. ተሰባጣሪ ሰብሎቹ ምን ጊዜ እንደሚዘሩ ማወቅ

ተሰባጣሪዎቹ ሰብሎች በአንድ ጊዜ ወይም በቅደም ተከተል ሊዘሩ


ይችላሉ፡፡ ሰብሎቹ ለመድረስ የሚፈልጉት የጊዜ እርዝማኔ፣ የሚፈልጉት
የዝናብ መጠን እና የሰብሎቹ ተፈላጊነት የመዝሪያ ጊዜን ለመወሰን
ጠቃሚ ነጥቦች ይሆናሉ፡፡ ዋናዉ ሰብል በተቻለ መጠን ያለ ተጽእኖ
አድጎ ምርታማ እንዲሆን ስለሚፈለግ በሰብል ወቅት መጀመርያ ላይ
ይዘራል፡፡ በተጨማሪም ለመድረስ ረጅም ጊዜ የሚፈጁ ሰብሎች ቀደም
ብለዉ መዘራት ይኖርባቸዋል፡፡ ቦሎቄ በተነጻጻሪ አጠር ያለ የእድገት
እርዝማኔ ስላለዉ እንደሚከተለዉ አማራጮች ይኖሩታል፡-

 በቆሎ ለመድረስ ሲቃረብ በቅብብሎሽ ሊዘራ ይችላል


 በአንድ ላይ ከበቆሎ ጋር ሊዘራ ይችላል
 በቆሎዉ ከተዘራ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ሊዘራ ይችላል

ብዙ ገበሬወች ለበቆሎ ሁለተኛዉን ኩትኳቶ ሲያከናዉኑ (ከበቀለ ከአንድ


ወር ገደማ በኋላ) ቦሎቄን አሰባጥረዉ ይዘራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በቆሎ
ለመድርስ ሲቃረብ ይዘራሉ፡፡ በተለይ ቦሎቄዉ በአንድ ላይ ወይም ከወር
በኋላ ሲዘራ በዋናዉ ሰብል ላይ ተጽኖ እንዳያሳድር የዘር መጠኑን ዝቅ
ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
29
ቦሎቄዉ በቆሎ ለመድረስ ሲቃረብ በሚዘራበት ጊዜ ግን ዋናዉ የበቆሎ
ሰብል ከተጽዕኖ ዉጭ ስለሚሆን ለብቻ ሲዘራ የምንጠቀመዉን የቦሎቄ
የዘር መጠን መጠቀም ይቻላል፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚሰባጠረዉ ቦሎቄ
በአደገዉ የበቆሎ ሰብል ስር ስለሚያድግ በቂ የጸሃይ ብርሃን ስለማያገኝ
እድገቱ ደካማ ይሆናል፡፡ የበቆሎዉን የታች ቅጠሎች ማንሳት ይህንን
ተጽእኖ በመቀነስ በቅብብሎሽ ከሚዘራዉ ቦሎቄ የተሻለ ምርት ለማግኘት
ያስችላል (ስዕል 18)፡፡ የበቆሎዉን የታች ቅጠሎች (ከፍሬ መያዣዉ
በታች ያሉትን) ቦሎቄዉ ሙሉ በሙሉ ከበቀለ በኋላ ማንሳት የተሻለ
ነዉ፡፡

ሰዕል 18፡ የበቆሎዉን የታች ቅጠሎች በማንሳት በቅብብሎሽ ለሚዘራዉ ቦሎቄ ምቹ ሁኔታ
መፍጠር ይቻላል፤ ቦሎቄ የበቆሎ ቅጠል ተነስቶ ሲዘራ (ግራ) እና የበቆሎ ቅጠል ሳይነሳ
ሲዘራ (ቀኝ)

3.3 አፈራርቆ መዝራት


ቦሎቄን በአንድ ማሳ ላይ በድግግሞሽ መዝራት አይመከርም፡፡ ከዚህ
ይልቅ ከሌሎች ሰብሎች ጋር በፈረቃ መዝራት ተመራጭ ነዉ፡፡
ምክንያቱም የሰብሉን ለበሽታ፣ ተባይና አረም ተጋላጭነት በመቀነሰ
ምርታማነትን ለማሳደግ ስለሚረዳ ነዉ፡፡ ለምሳሌ እንደ በቆሎ፤ ስንዴ፤
ማሽላ፤ ድንች ከመሳሰሉት ሰብሎች ጋር አፈራርቆ መዝራት ለሁሉም
ሰብሎች ጠቀሜታን ያስገኛል፡፡

30
4. ምንጮች
1. በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የግብርና ሚኒስቴር. 2007 ዓ.
ም. የጥራጥሬ ሰብሎች ቴክኖሎጂ ፓኬጅ፤ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ.
2. ደምስ ዘዉዱ፤ 2008. እ.ኤ.አ. Growth, Yield and Nitrogen Fixation Response
of Soybean (Glycine max ) to Bradyrhizobium Inoculation and
Phosphorous Application. MSc Thesis. Hawssa University.
3. Food and Agriculture Organization (FAO). (2013). FAOSTAT.
Available at: http://faostat3.fao.org/download/Q/QC/E.
4. Infonet Biovision: Information on Pests: Available at:
http://www.infonet-biovision.org/default/ct/118/crops
5. International Food Policy Research Institute. 2010. Pulses Value
Chain Potential in Ethiopia: constraints and opportunities for
enhancing export.
6. Onwueme, T.C. and Sinha, T.D. 1991. Field Crops Production in
Tropical Africa. CTA, Ede, The Netherlands.
7. Raemaekers, R.H. 2001. Crop Production in Tropical Africa. Directorate
General for International Cooperation, Brussels, Belgium.
8. ረድኤት አበራ፤ 2015. እ.ኤ.አ Effect of Common Bean (Phaseolus
vulgaris L.) Genotypes Intercropped with Maize (Zea mays L.) on
Growth, Productivity and Iron and Zinc Contents of the
Component Crops at Halaba Special District, Southern Ethiopia.
MSc Thesis. Hawssa University.
9. ዋለልኝ ወርቁ፤ አጀቡ ኑርፈታና ዓለማየሁ ጫላ፤ 2006 ዓ.ም. አየር ንብረት ለዉጥ ተኮር
የግብርና ቴክኖሎጅወችና ተሞክሮወች፡ የስልጠና መመሪያ፤ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲና ኤስ
ኦ ኤስ ሳህል
10. ዋለልኝ ወርቁ፤ 2004 እ.ኤ.አ. Maize –Tef relay intercropping as affected by
maize planting pattern and leaf removal in southern Ethiopia. African
Crop Science Journal. 12(4) 359-367.
11. ዋለልኝ ወርቁ፤ 2014. እ.ኤ.አ. Sequential intercropping of common bean and
mungbean with maize in southern Ethiopia. Experimental Agriculture.
50:90-108.
12. የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፤ 1999 ዓ. ም. የሰብል ቴክኖሎጅወች
አጠቃቀም፡ አዲስ አበባ፡፡
13. የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ድርጅት፤ 2005 ዓ.ም. Agricultural Sample
Survey: Area and Production of Major Crops. Statistical Bulletin 532,
Addis Ababa.

31

You might also like