Professional Documents
Culture Documents
Garlic Production Manua
Garlic Production Manua
አመራረት
©EIAR, 2019
ኢግምኢ ፤ 2012
Website: http://www.eiar.gov.et
Tel: +251-11-6462633
Fax: +251-11-6461294
P.O. Box: 2003
Addis Ababa, Ethiopia
ማዉጫ
መቅድም iii
መግቢያ iv
የነጭ ሽንኩርት ተክል 1
ተስማሚ የአየር ንብረትና አፈር 2
የተሻሻሉ ዝርያዎች 3
ቅድመ-ምርት እንክብካቤ 4
ምርት አሰባሰብና ድህረምርት አያያዝ 7
በሽታዎች 8
ተባዮች 13
የተባይ አሰሳ 16
የፀረ-ተባይ አጠቃቀም 17
i
ምስጋና
ii
መቅድም
አዘጋጆቹ
iii
መግቢያ
ነጭ ሽንኩርት በኢትዮጵያ ደጋና ወይናደጋ አካባቢዎች ከሚመረቱ የአትክልት ሰብሎች
አንዱ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተዉ በ2008
ዓ.ም 1.08 ሚሊዮን ኩ/ል በላይ ነጭ ሽንኩርት በ11845 ሄ/ር መሬት ላይ 1.5 ሚሊዮን
በሚበልጡ አርሶአደሮች በአነስተኛ ማሳዎች ላይ አምርተዉታል፡፡ ነጭ ሽንኩርት ከበርበሬ
ጋር ተፈጭቶ ወይም ብቻዉን ተከትፎ ምግብ ዉስጥ እየተጨመረ ለምግብ ማጣፈጫነት
ይዉላል፡፡ በተጨማሪ ፀረ-ፈንገስና ፀረ-ባክቴሪያ ንጥረነገር በዉስጡ ስላለዉ ለበርካታ
በሽታች ማስታገሻነት ያገለግላል፡፡ ይህ ሰብል ጠቀሜታዉ በርካታ ስለሆነ በህዝቡ ዘንድ
በከፍተኛ ደረጃ ይፈለጋል፡፡ ስለዚህ በተለይ በደጋማ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚኖሩ አርሶአደሮች
ጥሩ የገቢ ምንጭ ነዉ፡፡ እንዲሁም ነጭ ሽንኩርት ጠቀሜታዉ አለምአቀፋዊ በመሆኑ
በጥራትና በብዛት ቢመረት ወደሌሎች ሀገሮች ተልኮ የዉጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ ይችላል፡፡
iv
የነጭ ሽንኩርት ተክል
የነጭ ሽንኩርት ተክል ቅጠል፣ ሽልቅጠል፣ ኩርት፣ ግንድና ስር አሉት (ምስል 1)፡፡ ግንዱ
በኩርትና በስር መካከል የሚገኝ በጣም አጭር አካል ሲሆን ኩርት፣ ሽልቅጠልና ቅጠል
ወደላይ ስር ደግሞ ወደታች ያበቅላል፡፡ የነጭ ሽንኩርት ተክል የሚራባዉ በክፍልፋይ
ኩርቶች ሲሆን አንድ ኩርት እስከ 20 የሚደርሱ ክፍልፋዮች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡
የኩርት ቆዳ ቀለም ነጭ ወይም ወይንጠጅ ሲሆን ነጭ የቆዳ ቀለምና በቁጥር አነስ ያሉ
(ከስድስት እስከ ስምንት) ትልልቅ ክፍልፋይ ኩርቶች ያሉት ዝርያ በገበያ ተፈላጊ ነዉ፡፡
ቅጠል
ሽልቅጠልል
ኩርት
ስር
ምስል 1. የነጭ ሽነኩርት ተክል ክፍሎች
1
ተስማሚ የአየር ንብረትና አፈር
ነጭ ሸንኩርት ቅዝቃዜና ዉርጭ የመቋቋም ችሎታ አለዉ፡፡ ቅዝቃዜ ለኩርት ምስረታና
እድገት አስፈላጊ ነዉ፡፡ ስለዚህ ደጋማ የሀገራችን ክፍሎች ዋነኛ የነጭ ሽንኩርት አምራቾች
ናቸዉ፤ የደጋ ነጭ ሽንኩርት ኩርትም ትልልቅ ነዉ፡፡ ነጭ ሽንኩርት በወይናደጋም
ይመረታል፡፡ በአጠቃላይ ከፍታቸዉ ከባህር ወለል በላይ ከ1800 እስከ 2500 ሜትር፣
የሙቀት መጠናቸዉ ከ12 እስከ 24 ዲ.ሴ፣ እንዲሁም ከ600 እስከ 700 ሚ.ሜ ለ90 ቀናት
ስርጭቱ የተስተካከለ ዝናብ ያላቸዉ አካባቢዎች ለነጭ ሽንኩርት ተስማሚ ናቸዉ፡፡ ነገር ግን
የዝናቡ ወቅት ምርቱ ከሚደርስበት ሁለት ሳምንቶች ቀደም ብሎ የሚያቆም መሆን አለበት፡፡
ቀላልና ለም፣ ዉሃ የማያቁር፣ ቆምጣጤነቱ ከ6.0 እስከ 7.5 የሆነ አፈር ለነጭ ሽንኩርት
ተስማሚ ነዉ፡፡ ከባድ ጥቁር አፈር በዝናብ ወቅት ዉሀ ስለሚያቁርና በደረቅ ወቅት
ስለሚሰነጣጠቅ ኩርት እንዳያድግ ያግዳል፡፡ ነገር ግን ጥቁር ኮትቻ አፈር ላይ የመስኖ ዉሀን
በጥንቃቄ መጥኖ በማጠጣት ጥሩ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡ መጠነኛ ብስባሽ ያለዉ አፈር
ለተክሎች ተስማሚ ቢሆንም ብስባሽ የበዛበት አፈር ግን ተክሉ የተከፋፈሉ ሽልቅጠሎችና
ኩርቶች እንዲኖሩት ያደርጋል፡፡
2
የተሻሻሉ ዝርያዎች
አብዛኛዉ የነጭ ሽንኩርት ምርት በገበሬዉ እጅ ተጠብቀዉ በቆዩ ዝርያዎች የሚመረት ሲሆን
በደብረዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል አምስት ዝርያዎች ተሻሽለዉ ወጥተዋል፡፡ እነዚህም፣
ፀደይ
የኩርት ቆዳ ቀለም ነጭና ወይንጠጅ ድብልቅ (ግራጫ) ሲሆን መካከለኛ መጠን
ያለዉ ኩርትና ክፍልፋይ ኩርቶች አሉት፡፡ በአርሲ ከፍተኛ ቦታዎች በስፋት
ለረጅም ጊዜ እየተመረተ ያለ ዝርያ ነዉ፡፡
ቢሾፍቱ ነጭ
የኩርት ቆዳ ቀለም ከፀደይ ነጣ ያለ ሲሆን መጠኑ አነስተኛ ነዉ፡፡ ይህ ዝርያ ከፀደይ
በሳምንት ያህል ቀድሞ ይደርሳል፡
ኩሪፍቱ
የቆዳ ቀለሙ ነጭ ሲሆን ሽልቅጠሉ ወፍራምና ኩርቱም ትልልቅ ነዉ፡፡ ይህ ዝርያ
ከፀደይና ከቢሾፍቱ ነጭ ይልቅ ዘግይቶ ይደርሳል፡፡
ጨፌ
ኩርቱ ነጭ የቆዳ ቀለም አለዉ፣ የተክሉ እድገት ገዘፍ የሚል ሲሆን ትልልቅ ኩርቶች
ያፈራል፡፡ ለመድረስ በአማካይ 120 ቀን ይፈጅበታል፡፡
ሆለታ
የቆዳ ቀለሙ ነጭ ሲሆን ኩርቱ ትልልቅ ነዉ፡፡ ለመድረስ 128 ቀን የፈጅበታል፡፡
3
ቅድመ ምርት እንክብካቤ
የዘር መጠን
አንድ ሄ/ር መሬት ለመትከል የሚያስፈልግ የነጭ ሽንኩርት ዘር መጠን ኩርቶቹ
መካከለኛ ከሆኑ 8 ኩ/ል ትልልቅ ከሆኑ ደግሞ እስከ 12 ኩ/ል ይደርሳል፡፡
የዕረፍት ጊዜ
ለተከላ የሚዉል ኩርት በደንብ ደርሶ የተሰበሰበና መጋዘን ዉስጥ ከሁለት እስከ ሶስት ወሮች
የቆየ መሆን አለበት፡፡ የእረፍት ጊዜዉን የጨረሰ ኩርት መሀሉ ተሰብሮ ሲታይ ጉንቁሉ
ይታያል (ምስል 2) ሲተከልም ፈጥኖና ተመሳስሎ ይበቅላል፣ ይደርሳልም፡፡
ያጎነቆለ ኩርት
ÁÔ’qK Ÿ<`ƒ
ምስል 2. የእረፍት ጊዜዉን ጨርሶ መብቀል የጀመረ ኩርት
4
የኩርት መጠን
ለተከላ የሚዉል ኩርት በሚገባ ደርሶ የተሰበሰበ መሆን አለበት (ምስል 3)፡፡ ክፍልፋይ
ኩርት መጠን ከ1.5 ግራም እስከ 5 ግራም የሚመዝን መሆን አለበት፡፡ ትንንሽ ኩርቶች
የተተከሉ እንደሆነ ተክሉ ቀጫጫ የሚመረቱትም ኩርቶች ትንንሽ ይሆናሉ (ምስል 3)፡፡
ሀ ለ
ምሰል 3. ሀ) በአግባቡ ደርሶ የተሰበሰበና ከክምችት በኋላ ጥሩ ይዞታ ያለዉ ኩርት
ለ) በምስል “ሀ” ከምንመለከተዉ ኩርት የተፈለፈሉ ክፍልፋይ ኩርቶች ሲሆኑ በአራት
መዕዘን ዉስጥ ያሉት መጠናቸዉ አናሳ በመሆኑ ለተከላ የማይዉሉ ናቸዉ፡፡
የተከላ ርቀት
ነጭ ሽንኩርት ከመተከሉ በፊት መደብና ቦይ ይዘጋጃል፡፡ የመደቡ ስፋት 20 ሳ.ሜ ሲሆን
የቦዩ ስፋት 40 ሳ.ሜ ይሆናል፡፡ ኩርቶቹ እንደወቅቱ እርጥበት መጠን መደቡ ሁለቱም ጎኖች
ጠርዝ ወይም መሰረት ተከትለዉ በመስመሮች መካከል 20 ሳ.ሜ በኩርቶች መካከል 10 ሳ.ሜ
ተራርቀው ይተከላሉ (ምስል 4)፡፡ ኩርቶቹ ከ3 እስከ 4 ሳ.ሜ. ጠልቀዉ (አናታቸዉ በአፈር
እስኪሸፈን) የሚተከሉ ሲሆን ወደጎን ተንጋደዉ ወይም ተዘቅዝቀዉ መተከል የለባቸዉም፡፡
3 5
ሀ ለ
ምስል 4 የመደብና ቦይ የተከላ ዘዴ ሀ) በቦዮች መካከል 40 ሳ.ሜ እና በመደብ ጠርዞች (በመስሮች) መካከል 20 ሳ.ሜ ለ)
በተክሎች መካከል 10 ሳ.ሜ ተራርቀዉ የተተከሉ ነጭ ሽንኩርት ተክሎች
ተከላ ወቅት
ተከላ ዝናብ ሲጀምር ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ ወር መጀመሪያ ሳምንታት ቢሆን
ይመረጣል፡፡ በመስኖ የሚታገዝ ወይም ሙሉ በሙሉ በመስኖ የሚመረት ከሆነ ከነሀሴ ጀምሮ
መትከል ይቻላል፤ ነገር ግን ምርቱ የሚደርስበት (የሚሰበሰብበት) ወቅት የዝናብ ወቅት
እንዳይሆን ማቀድ ያሻል፡፡
የማዳበሪያ ዓይነትና መጠን
የተጠና የማዳበሪያ መጠን መረጃ ባይኖርም እስካሁን ካለዉ ልምድ 200 ኪ.ግ ዳፕ
በተከላ ወቅት እንዲሁም በተጨማሪ 150 ኪ.ግ ዩሪያ ለሁለት ከፍሎ ግማሹን በተከላ
ወቅት ከዳፕ ጋር ቀሪዉን ግማሽ ደግሞ ኩርቶቹ ከበቀሉ ከአንድ ወር በኋላ መጨመር
ምርትን ያሳድጋል፡፡ ይህም 242 ኪ.ግ ቲ.ፒ.ኤስ እና 130 ኪ.ግ ዩሪያ ይሆናል፡፡ የአፈሩ
በተፈጥሮ ማዳበሪያ (በፍግ) የዳበረ ከሆነ ግን የማዳበሪያዉን መጠን መቀነስ ይቻላል፡፡
የመስኖ ዉሃ
ነጭ ሽንኩርት ከተተከለ በኋላ ተስተካክሎ እስኪበቅል በሳምንት ሁለት ጊዜ፣ ከዚያ በኋላ
እንደአየሩ ሁኔታና እንደአፈሩ አይነት ከ5 እስከ 10 ቀኖች ዉስጥ አንዴ ዉሃ መጠጣት አለበት፡፡
ይኸዉም ተክሉ ያደገ ፣ አፈሩ ቀላል (ጎንቦሬ)፣ አየሩ ደረቅ ከሆነ በየአምስት ቀኖች፣ ተክሉ በችግኝ
ደረጃ ካለ፣ አፈሩ ከባድ (መረሬ)፣ አየሩ ዳመናማ ከሆነ በየአስር ቀኖች ዉሃ መጠጣት አለበት፡፡
አረምና ኩትኳቶ
የነጭ ሽንኩርት ተክል ስሮች ከ30 ሳ.ሜ በላይ ጠልቀዉ ስለማያድጉ ቅጠሎቹም ሰፍተዉ ከስሩ
ያለዉን መሬት ስለማይሸፍኑ አረሞች አድገዉ ማዕድናትንና የፀሀይ ብርሃንን ይሻሙታል፡፡
ስለዚህ ከተከላ በፊት መሬቱ በደረቅና ፀሀያማ ወቅት ታርሶ ተከስክሶና የአረም ስሮች ድርቀዉና
ተጎልጉለዉ መዉጣት አለባቸዉ፡፡ ኩርቶቹ ተስተካክለዉ ከበቀሉ በኃላ ከሁለተኛዉ ሳምንት
ጀምሮ እንደአረሙ እድገት በየሁለት ወይም ሶስት ሳምንቶች ማረምና መኮትኮት ያስፈልጋል፡፡
6
ምርት አሰባሰብና ድህረምርት አያያዝ
ምርት አሰባሰብ
እንደስህነምዳሩ፣ ወቅቱና ዝርያዉ ሁኔታ ነጭ ሽንኩርት ከተተለ በግምት ከአራት እስከ
አምስት ወሮች ዉስጥ ይደርሳል፡፡ ገበያንና የአየር ሁኔታን (ዝናብ እንዳያበላሸዉ) ግንዛቤ
ዉስጥ በማስገባት ቅጠሉ ወደቢጫነት መቀየር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ
እስኪደርቅ ድረስ መሰብሰብ ይቻላል፡፡ የአከባቢ ዝርያዎች በባህላዊ አሰራር 50 ኩ/ል በሄ/ር
ምርት ሲሰጡ የተሻሻሉ ዝርያዎች በዘመናዊ አሰራር በአማካይ 85 ኩ/ል ሊያመርቱ ሊሰጡ
ይችላሉ፡፡
ድህረምርት አያያዝ
ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ኩርቶች በቀላሉ ሳይበላሹ እንዲቆዩ ለማድረግ ለሳምንት ያህል ጥላ
ስር ማጠዉለግ ያስፈልጋል፡፡ ኩርቶች ሳይቆረጡ ጎንጉኖ ማንጠልጠል አለበለዚያም ከሽቦ
ወይም ከእንጨት በተሰራና አየርና ከፊል ብርሃን በሚገባ በሚንሸራሸርበት መጋዘን ለስድስት
ወራት ያህል ማቆየት ይቻላል፡፡
7
በሽታዎች
የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርት በፐርፕል ብሎች፣ ዳውኒ ሚልዲዉ፣ ኩርት
አበስባሽና በጥቁር ሻጋታ የሚጠቁ ሲሆን ነጭ ሽንኩርት ከነዚህ በተጨማሪ በነጭ ሽንኩርት
ዋግ ይጠቃል፡፡
የመከላከያ ዘዴዎች
በሽታው ዘር ወለድ ስለሆነ ከበሽታ ነፃ የሆነ የሽንኩርት ዘር በማምረት መጠቀም
ሰብልን አፈራርቆ መጠቀም
ዘርን አፕሮን ስታር በተባለ ኬሚካል 3 ግራም ለአንድ ኪ.ግ ዘር አሽቶ መዝራት
የበሽታው ምልክት ሲታይ ሪዶሚል የተባለ ኬሚካል 3 ኪ.ግ. በሄክታር በየሳምንቱ
መርጨት
8
ዳውኒ ሚልዲው (downy mildew)
ይህ በሽታ የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርትን፣ የአበሻ ሽንኩርትንና ነጭ ሽንኩርትን በማጥቃት
የምርትና የጥራት ጉድለት ያስከትላል፡፡ ይህ ችግር የመስኖ ውሀ በሚበዛበትና
በዝናብ ወቅት በተጠቀሱት ሰብሎች ላይ የላቀ ጉዳት እንደሚያስከትል ይታወቃል፡፡
የበሽታው ምልክቶች
በሽታው ሲጀምር ቅጠሉ ላይ ነጭ ነጠብጣብ መሳይ ይታያል
እነዚህ ነጠብጣቦች ቀስ በቀስ የብረት መልክ ዓይነት ምልክት ይታይባቸዋል
ዝናብና የመስኖ ውሀ ሲበዛ በሽታው በቀላሉ ስለሚስፋፋና የጥቃት መጠኑ
ስለሚጨምር ቅጠሎቹ የመቃጠል ምልክት ይታይባቸዋል:: የበሽታዉን ምልክቶች
በምስል 6 ይመልከቱ
የመከላከያ ዘዴዎች
ሰብልን ማፈራረቅ
ከበሽታው ነፃ የሆነ ችግኝ መትከል
የመስኖ ውሀ መጠንን ማሰተካከል
የሽንኩርት ማሳ ውሀ እንዳያቁር ጥንቃቄ ማድረግ
የበሽታው ምልክት ሲታይ ቬሪታ 2.5 ኪ.ግ በሄክታር ወይም ሪዶሚል የተባለውን
ኬሚካል 3 ኪ.ግ. በሄክታር በየሳምንቱ መርጨት
መከላከያ ዘዴዎች
ከበሽታው ነፃ የሆነ ሽንኩርት ኩርት ለዘር መጠቀም
ኩርቱ ከማሳ ላይ ከተሰበሰበ በኋላ በዝቅተኛ ሙቀትና ምዝን የአየር እርጥበት
ሥፍራ ማስቀመጥ
ምርቱ በመጋዘን ውስጥ በሚቀመጥበት ወቅት ሙቀቱ ከ30-32 ዲ.ሴ እንዲሁም
ምዝን የአየር እርጥበቱ ከ80 ፐርሰንት በታች መሆኑን ማረጋገጥ
በዘመናዊ መጋዘን መጠቀም ከተቻለ ለረጅም ጊዜ በዝቅተኛ ሙቀት (4 ዲ.ሴ)
ኩርቱን ማስቀመጥ
ስርና ኩርት አበስባሽ (bulb rot)
ይህ የኮረት አበስባሽ በሽታ እንደ ሌሎቹ በሽታዎች ሁሉንም የሽንኩርት ዓይነቶች (የፈረንጅ
ቀይ ሽንኩርት፣ የአበሻ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት) የሚያጠቃና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ
የፈንገስ በሽታ ነዉ፡፡ የሚተላለፈዉ በበሽታዉ የተበከለ ዘር በመጠቀም ወይም በበሽታዉ
በተበከለ አፈር ላይ በመትከል ነዉ፡፡ ሰለዚህ በዚህ በሽታ የተበከለ ማሳ ላይ ለረዥም
አመታት መቆየት ስለሚችል የበሽታውን የመከላከል ዘዴ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ
በበሽታዉ በተበከለ ማሳ ለረዥም ጊዜ ማንኛዉንም ሽንኩርት ማምረት አይቻልም፡፡
10
የበሽታዉ ምልክቶች
ይህ የሽንኩርትን ኩርትና ስር የሚያበሰብስ በሽታ ሲሆን ምልክቱ በቅጠል ላይ
ይታያል፡፡ ይኸዉም መጀመሪያ ቅጠሉን በግማሽ ወደቢጫነት ይቀይርና በቆይታ
ጠቅላላ ተክሉ ይሞታል፡፡
ተክሉ በሚነቀልበት ጊዜ የበሰበሰ ኩርትና ስር ይታያል (ምስል 8ሀ)፡፡
ኮረቱ ላይ ነጭ ጥጥ መሳይ የፈንገስ እድገት ይታይበታል
ከፍተኛ የአፈር እርጥበትና ለበሽታው ተስማሚ የአየር ፀባይ በሚኖርበት ወቅት
ሰብሉን ሙሉ በሙሉ የማበስበስና የማጥፋት አቅም አለው
በሽታው ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለ በኋላ ራሱን በአፈር ውስጥ ለማቆየት ጥቁር
የጎመን ዘር ፍሬ መሳይ የመራቢያ አካላቱ በተጠቃው ኮረት ዙሪያ ይታያሉ
(ምስል 8ለ)፡፡
እነዚህ የፈንገሱ አካላት በአፈር ውስጥ ለረጅም ዓመታት መቆየትና ሰብሉ
በሚተከልበት ወቅት በሽታ መፍጠር ይችላሉ፡፡
ሀ ለ
ምስል 8 በሽንኩርት አበስብስ የተጎዳ ነጭ ሽንኩርት (ሀ) ተክል (ለ) ኩርት
መከላከያ ዘዴዎች
የሽንኩርት ኮረት፣ ችግኝና ማሳዉ ከዚህ በሽታ ነፃ መሆናቸዉን ማረጋገጥ
የሽንኩርት ማሳን በሌሎች ሰብሎች በተደጋጋሚ ማፈራረቅ
በማሳ ዝግጅት ወቅት በሽታው ወደ ሌላ ማሳ እንዳይዛመት ጥንቃቄ ማድረግ
የመስኖ ውሀን መጥኖ መስጠትና ማሳው ውሀ እንዳያቁር ጥንቃቄ ማድረግ
የሽንኩርት ኮረት ከመተከሉ በፊት እስከ 45 ዲ.ሴ. በሞቀ ውሀ ውስጥ ለ25
ደቂቃ መዘፍዘፍ
አፕሮን ስታር (Apron star 42 WS) ሶስት ግራም ፀረ-ፈንገስ ዱቄት
በ10 ሚሊ ሊትር ዉሀ በጥብጦ አንድ ኪሎ ግራም የሽንኩርት ኩርት መለወስ
11
ማስገንዘቢያ
ከላይ የተጠቀሱትን ፀረ-ፈንገስ ኬሚካሎች ከመጠቀም በፊት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸዉን
ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ሀ ለ
ምስል 9. የነጭ ሽንኩርት ዋግ በሽታ ምልክቶች ሀ) ቅጠል ላይ የሚታይ ዝገት መሰል ሻጋታ
ለ) በዋግ ከተጠቁ ተክሎች የተሰበሰቡ ኩርቶች (ግራ) ካልተጠቁ ተክሎች የተሰበሰቡ ኩርቶች (ቀኝ)
መከላከያ ዘዴዎች
የተከላን ጊዜ ወደክረምት መጨረሻ ወይም በጋ ላይ ማድረግ
በበሽታው የማይጠቁ ተክሎችን በፈረቃ መዝራት የበሽታውን ጥቃት ይቀንሰዋል
በተከታታይ የሽንኩርት ዝርያዎችን አለመትከል
አረሞችን መቆጣጠርና ማሳውን በጥልቀት ማረስ
ቲልት 0.5 ሊትር በሄክታር ቅጠሉን በመርጨት
12
ተባዮች
የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርትና የነጭ ሽንኩርት በቅጠል ሰርሳሪ ዝንብ (leaf miner)፤ ሸረሪት
ድር የሚሰሩ ቅንቅኖች (spider mites)፤ ግንደ ቆራጭ (cut worms) የመሳሰሉ ተባዮች
አልፎ አልፎ በመከሰት መጠነኛ ጉዳት የሚያደርሱ ቢሆንም በሀገራችን ሽንኩርትን
በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃዉ ተባይ የፋሮ አንጥረኛ ወይም የሽንኩርት ትሪፕስ (onion
thrips) በመባል ይታወቃል፡፡
የፋሮ አንጥረኛ (onion thrips)
ይህ ተባይ የተለያዩ የሽንኩርት አይነቶችን (ቀይ ሽንኩርት፣ የሀበሻ ቀይ ሽንኩርት፣ ባሮ)
ያጠቃል፡፡ በነጭ ሽንኩርት ላይ ሽንኩርቱ ከበቀለበት ጊዜ ጀምሮ መውረር የሚጀምር
ቢሆንም እስከ ረጅም ጊዜ ጉዳት በማያደርስበት ደረጃ (የተባይ ቁጥር) ይቆያል፡፡
ምስል 10. (ሀ) በፋሮ አንጥረኛ የተወረረ የነጭ ሽንኩርት ቅጠል እና (ለ) የፋሮ አንጥረኛ
ጎልማሳ
13
የጉዳት ምልክቶች
ማንኛውም በተባይ የተወረረ ሰብል ዋናው የጉዳት ምልክት ተባዩ በአካል መኖር ነው፡፡
ስለሆነም ነጭ ሽንኩርት በፋሮ አንጥረኛ መወረሩን ለማወቅ የሽንኩርቱ ቅጠልና ሽልቅጠል
መጋጠሚያ ላይ ከፍቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ፋሮ አንጥረኛ ትንሽ ስለሆነ ሁሉም ሰው በዐይኑ
ሊያየው ስለማይችል አጉልቶ ለማየት የእጅ ሌንስ መጠቀም ይመከራል፡፡
በተጨማሪ ተክሉ ላይ የደረሰውን የጉዳት ምልክት መመልከት ሽንኩርቱ በፋሮ አንጥረኛ
መወረሩን ማወቂያ ሌላው መንገድ ነው (ምስል 10ለ))፡፡ ፋሮ አንጥረኛ ሲመገብ የቅጠሉን
የላይኛውን ቆዳ (epidermis) በመተው የውስጡን ህብረህዋስ እየፋቀ በማቁሰል የሚወጣውን
ፈሳሽ ይመጣል፡፡ ሳይጎዳ የቀረው የላይኛው ቆዳ ብርማ መልክ ይኖረዋል፡፡ እንዲሁም ቅጠሉ
ላይ የተባዩ እዳሪ ጥቁር ነጠብጣብ መስሎ ይታያል፡፡
የመከለከያ ዘዴዎች
ሽንኩርትን ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርበት ጊዜ አለማምረት
ከ2-3 አመታት ከሽንኩርት ነፃ የሆነን ማሳ መጠቀም
በቂ መስኖ (ከተቻለ ዝናብ መሰል (sprinkler) መስኖ መጠቀም
በቂ ማዳበርያ በትክክለኛ መጠንና ወቅት ተክሉ እንዲያገኝ ማድረግ ጠንካራና
ጤናማ ስለሚያደርገዉ ተባዩን የመቆቋም ችሎታዉ የተሻለ ይሆናል፡፡
አዲስ የሚተከል ሽንኩርት ቀድሞ ከተተከለዉ የነፋስ አቅጣጫ የተከተለ መሆን
የለበትም::
ከምርት ስብሰባ በኋላ የተክሉን ቅሪት ማጥፋት
ተባይ የሚቋቋሙ (ቅጠላቸዉ ዝርግ የሆነ) ዝርያዎች መጠቀም
ነጭ ሽንኩርት ለድርቅ ከተጋለጠ በቀላሉ በፋሮ አንጥረኛ ስለሚጠቃ ሰብሉን ውሃ
ማጠጣት ዋናው የፋሮ አንጥረኛ መከላከያ መንገድ ነው፡፡
በማሳው ውስጥና በማሳው ዙሪያ ያለን አረም ማረም
ተገቢውን የዘር መጠንና ንጹህ ዘር መጠቀም
የነጭ ሽንኩርቱ ማሳ በጣም ሰፊ ካልሆነ ከሽንኩርቱ ስር ገለባ መጎዝጎዝና ውሃ
ሲያጠጡ ሽንኩርቱን መርጨት ፋሮ አንጥረኛን ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡
ፀረ-ተባይ መጠቀም
ፀረ-ተባይ ለፋሮ አንጥረኛ ቁጥጥር መጠቀም እንደ መጨረሻ አማራጭ መወሰድ
አለበት፡፡ ምክንያቱም ተባዩ እንቁላሉን የቅጠሉ ህብረህዋስ (tissue) ውስጥ ስለሚጥልና
የሚመገበዉም የቅጠሉና የግንዱ መጋጠሚያ አካባቢ ተደብቆ ስለሆነ በንክኪ የሚሰሩ ፀረ-
ተባዮች አያገኙትም፣ አይገሉትም፡፡ ነገር ግን ሽንኩርቱ ከማኩረቱ በፊት የፋሮ አንጥረኛ
ቁጥር ከፍተኛ፣ ሽንኩርቱም ለድርቅ የተጋለጠ ከሆነና የአካባቢው አየር ሙቀት ከፍተኛ ከሆነ
ካራቴ፣ ዳይሜቶይት (ሮገር)፣ ወይም ሴሌክሮን የተባሉትን ፀረ-ተባዮች አምራቹ በሚሰጠው
የርጭት መጠን በፈረቃ መርጨት ተመጣጣኝ የምርት ጥፋትን ለመከላከል ይረዳል፡፡
14
ከላይ የተጠቀሱትን ዘዴዎች አቀናጅቶ መጠቀም፡፡
የእጽዋት ቅንቅን (spider mites)
ይህ ተባይ ነጭ ሽንኩርት ላይ አልፎ አልፎና ሽንኩርቱ ከደረሰ በኋላ የሚከሰት ተባይ ነው፡፡
ተባዩ የሸረሪት ቅርጽ፤ ስምንት እግሮችና ወደቢጫ የሚያደላ የሰውነት ቀለምና ሁለት ጥቁር
ቡናማ ነጠብጣቦች አሉት (ምስል 11)፡፡ ሲመገብም በሽንኩርቱ ቅጠል የላይኛው ገጽ ላይ ድር
በማድራት ከድሩ ሥር በመሆን ነው፡፡
የመካከያ ዘዴዎች
የእጽዋት ቅንቅን የሚከሰተው ሽንኩርቱ ከደረሰ በኋላ ስለሆነ ምንም ዓይነት ቁጥጥር
አያስፈልገውም፡፡ ባልደረሰ ሽንኩርት ላይ የሚከሰተው የውሃ እጥረት ሲኖር ስለሆነ
ነጭሽንኩርት ለውሃ እጥረት እንዳይጋለጥ ማድረግ ይገባል፡፡
15
የተባይ አሰሳና የፀረ-ተባይ አጠቃቀም
የተባይ አሰሳ
16
የፀረ-ተባይ አጠቃቀም
የፀረ-ተባይ መለያ (label)
ፀረ-ተባይ መርዝ ስለሆነ በአግባቡ መያዝና ጥቅም ላይ መዋል አለበት፡፡ ማንኛውም ፀረ-
ተባይ ተጠቃሚ ሰው ፀረ-ተባይ ከመግዛቱ፣ ከማከማቸቱ፣ ለርጭት ከማዘጋጀቱ እና ትርፍ
ፀረ-ተባይ ከማስወገዱ በፊት የፀረ-ተባዩ መያዣ ላይ ያለውን መለያ (label) ማንበብና
መረዳት ይኖርበታል፡፡ የፀረ-ተባይ መለያ ፀረ-ተባዩ እንዲሸጥና ጥቅም ላይ እንዲውል
መፈቀዱን የሚገልጽ ህጋዊ ማስረጃ ነው፡፡ ስለሆነም መለያውን ሳናነብና ሳንረዳ ቀርተን
ለሚከሰተው ማንኛውም ዓይነት ጉዳት አምራቹ ወይም ወኪሉ በሕግ ሊጠየቁ አይችሉም፡፡
የማንኛውም ፀረ-ተባይ መለያ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ እንዲጻፍ የኢትዮጵያ ሕግ ያስገድዳል::
በተጨማሪም መለያው ስር ምን ዓይነት የመከላከያ አልባሳት መጠቀም እንዳለብንና
ለውሃ አካላትና ለእንስሳት መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ በሥዕል መልክ እንዲቀመጥ ያዛል፡፡
17
ምስል 13. ትክክለኛ ያልሆነ አረጫጨት (በስተግራ) እና ትክክለኛ አረጫጨት (በስተቀኝ)
18
ለፀረ-ተባይ ርጭት የሚውሉ እቃዎችን ከቤት እቃዎች ይለዩ፤ እንዲሁም የርጭት
ሥራው እንደተጠናቀቀ ለዚሁ ሥራ የዋሉትን እቃዎች በሙሉ አጥበው ያስቀምጡ፡፡
በእጅ የፀረ-ተባይ ብጥብጥ አያማስሉ ወይም ዱቄት አይዛቁ/ አይፈሱ፡፡
ማንኛውንም ፀረ-ተባይ በራሱ/ኦሪጅናል እቃ ብቻ በማድረግ ህፃናትና እንስሳት
በማይደርሱበት ቦታ ቆልፈው ያስቀምጡ፡፡
አዲስ ፀረ-ተባይ ሲገዙ የተገዛበትን ቀን ጽፈው በፊት ከተገዙ ፀረ-ተባዮች በኋላ
አድርገው ይደርድሩ፡፡ ይህም በቅድሚያ መጠቀም ያለብዎት ቀደም ብለው የተገዙትን
ፀረ-ተባዮች ስለሆነ እነዚህን ፀረ-ተባዮች በቀላሉ እንዲያገኙ ይረዳዎታል፡፡
በሚረጩበት ጊዜ የፀረ-ተባይ መከላከያ አልባሳት ይጠቀሙ
አንድ ፀረ-ተባይ እጅግ መርዛማ ቢሆን መወሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች ወስደን
ከተጠቀምንበት አደገኛ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅተኛ መርዛማነት ያለው
ፀረ-ተባይ በግዴለሽነት ከተጠቀምንበት እጅግ አደገኛ ይሆናል፡፡ ይህም ማለት
የፀረ-ተባይ አደገኛነት በአጠቃቀምና መወሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች በመተግበር
ላይ ይወሰናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በርጭት ጊዜ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን
የመከላከያ አልባሳት መጠቀም ይኖርብናል (ምስል 13)፡፡
ኮፍያ
እጅጌ ሙሉ ሸሚዝ /ሹራብ፡- ይህ ልብስ የአንገት አካባቢን በደንብ መሸፈን አለበት
ረዥም (ቦላሌ) ሱሪ፡- እግርን ከፀረ-ተባይ ይከላከላል፡፡ ቁምጣ (አጭር ሱሪ)
አይጠቀሙ፡፡
ከፕላስቲክ የተሰራ እና ውሃ የማያሳልፍ የእጅ ጓንት፡፡ ከቆዳ ወይም ከጨርቅ የተሰራ
የእጅ ጓንት የፀረ-ተባዩን ውህድ ወይም ውሃ ምጎ/ መጦ ስለሚይዝ ከጥቅሙ ጉዳቱ
ይበልጣል፡፡
የፕላስቲክ ቦት ጫማ
የፕላስቲክ ወይም ዉሀ የማያሳልፍ የዝናብ ልብስ
የዐይን መነፅር (ጎግል)፣ የአፍ ጭምብል/ የመተንፈሻ ማስክ (aspirater)
19
ምስል 13 ትክክለኛ የመከላከያ አልባሳት ያልለበሰ (በስተግራ) እና
ትክክለኛ የመከላከያ አልባሳት የለበሰ (በስተቀኝ) ፀረ-ተባይ ረጪዎች
20
Note
ማስታወሻ፡-
Note
ማስታወሻ፡-