You are on page 1of 19

በትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት

የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የአሰለጣጠን ችግር ለመቅረፍ


የተዘጋጀ የዳሰሳ ጥናት

ግንቦት 2009 ዓ.ም


አዲስ አበባ
1.መግቢያ
የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የትራንስፖርቱ ዘርፍ የኢኮኖሚውን ዕድገት በማስቀጠል የደጋፊነት
ሚናውን በላቀ ሁኔታ እንዲወጣ የሚያስችሉ የተለያዩ ውጥኖችን በመያዝ ለተግባራዊነታቸው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
መጠነ-ሰፊ የትራንስፖርት ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ የቴክኒክ ብቃት በመምራትና በማስተባበር፤ ለከተማዋ የትራንስፖርት
ዘርፍ መሻሻል ከፍተኛ ደረጃ ያለው የምክር አገልግሎትና በጥናት የተመሰረተ ሃሳብ በማቅረብ እና ዘርፉ በስትራቴጂያዊ
ዕቅድ እንዲመራ በማድረግ የከተማችንን የትራንስፖርት ሥርዓት አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ወጪ ቆጣቢና
አካባቢያዊ ተስማሚነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ማስቻል የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የትኩረት አቅጣጫ
ነው፡፡ ጽ/ቤቱ በአሁኑ ወቅት የሚታዩትን የትራንስፖርት ተግዳሮቶች በማስወገድ ለአዲስ አበባ ከተማ ዘላቂ የሆነ የከተማ
ትራንስፖርት ሥርዓት ዕድገት ጽኑ መሠረት ለመጣል የታለሙትን ነባርና በቀጣይ የሚጀመሩትን አዳዲስ የትራንስፖርት
ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን የመቅረፅ፣ የማከናወንና የማስተባበር ጉልህ ሃላፊነት የተጣለበት አካል ነው፡፡

በዚህ ረገድ የከተማውን የትራንስፖርት አገልግሎት ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የተጀመሩትን የፈጣን አውቶቡስ ትራንዚት
ፕሮጀክቶችን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኙትን የከተማ አውቶቡሶች፣ ሌሎች በዘርፉ የሚሳተፉ አዳዲስ
የመንግስት ተቋማትንና የግል የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ማህበራትን ማበራከትና የትራንስፖርት አገልግሎቱን
በማቀናጀት የሚፈለገውን ጠቀሜታ እንዲያስገኙ የማድረግ ስራ ያከናውናል፡፡ በተለይም የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስና
ፍሰቱን ለማሻሻል በከተማዋ በሚገኙ የመንገድ መጋጠሚያዎችና አጠቃላይ የመንገድ መረቡ ላይ መጠነ-ሰፊ ጥናት
በማካሄድና ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ የትራፊክ ፍሰቱንና ደህንነቱን ማሻሻል ከመቼውም ጊዜ በተለየ
ሁኔታ በጽ/ቤቱ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

ስለሆነም እነዚህንና ሌሎች የዘርፉን ቁልፍ ጉዳዮች በመለየት፣ የችግሮቹን መንስኤዎች በጥልቀት በመረዳት እና አገልግሎት
አሰጣጡን ደረጃ በደረጃ በማሻሻል የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት እውን እንዲሆን ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ የመንገድ
ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ የትራንስፖርት ባለስልጣን፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን እና
የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትን በማቋቋም ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል፡፡

ተቋማት መንግስት የነደፋቸውን ፖሊሲዎችንና ስትራተጂዎችን ከመፈጸም አኳያ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዘርፉ
የተሰማሩት የመንግስት ተቋማትም ሆኑ የግል ተቋማት የማስፈጸም አቅማቸውን እንዲያጎለብቱና በትራንስፖርት ሴክተሩ
አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሴክተሩንም ወደ ላቀ
ደረጃ ለማሳደግ ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ተቀናጅቶ መስራት ወሳኝ ነው፡፡

ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ በስሩ ያቋቋማቸውን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ወደ ሥራ በማስገባት በትራንስፖርት ዙሪያ የሚታዩትን
በርካታ ችግሮች ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በጽ/ቤቱ ተቋቁመው ካሉት የሥራ ክፍሎች አንዱ
የትራንስፖርት አገልግሎት የሥራ ክፍል ነው፡፡ የሥራ ክፍሉ በትራንስፖርት ዙሪያ የሚታዩትን ችግሮች በጥናት በመፈተሽ
የመፍትሔ ሃሳቦችን ለሚመለከተው ባለድርሻ አካላት በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
2.የጥናቱ አስፈላጊነት
ይህን ጥናት ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ተገቢውን
አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን አደረጃጀት በመፍጠር ብቃት ያላቸው አሽከርካሪዎችን ለማፍራት የሚያስችል
አሰራር መኖሩን፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም ጥናት
አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡

2.1.የጥናቱ ዘዴ
ይህ ጥናት የተካሄደው የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ መረጃዎችን በመሰብሰብ ሲሆን፡-

የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች፡- እነዚህ መረጃዎች የተሰበሰቡት የስልጠና አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ የአሽከርካሪ
ማሰልጠኛ ተቋማት ዳይሬክተሮች፣ ከክፍለ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከተገልጋዩ
ህብረተሰብ (ሰልጣኞች) ጋር ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና በቃሊቲ የአዲስ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ማዕከል
በአካል በመገኘት የነባራዊ ሁኔታ ቅኝት በማድረግ መረጃዎችንና የተለያዩ አስተያየቶችን በመሰብሰብ ሲሆን፣

የሁለተኛ ደረጃ መረጃዎች፡- ለአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን
የተዘጋጁ ማኑዋሎችና የአሰራር መመሪያዎች፣ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የጥናት ሰነድ፣
የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ አሰጣጥ የጥናት ሰነድ እንዲሁም የሌሎች አገሮች የአሽከርካሪ የስልጠና አሰጣጥ
ተሞክሮዎችን የሚዳስሱ ከድረ-ገጽ የተገኙ መረጃዎች ለጥናቱ የሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ተደርገው ተወስደዋል፡፡
2.2. የጥናቱ ወሰን
ይህ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት በዘርፉ ብቁ አሽከርካሪዎችን ለማፍራት
የሚያስችላቸው አደረጃጀት፣ አሰራርና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩትን መሰረታዊ ችግሮች ማጥናት እና የመፍትሄ
ሃሳብ መጠቆምን የሚያካትት ነው፡፡

2.3.የጥናቱ ዓላማ
አጠቃላይ ዓላማ
የዚህ ጥናት ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ አሽከርካሪዎችን ለማሰልጠን ፍቃድ ወስደው በሥራ ላይ የሚገኙ ተቋማት
በሥልጠና አሰጣጥ ዙሪያ በተጨባጭ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ በመዳሰስ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩትን መሰረታዊ
ችግሮችና ክፍተቶች በመለየት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚያስችል የመፍትሄ ሃሰቦችን ማቅረብ ነው፡፡
ዝርዝር ዓላማ

 የማሰልጠኛ ተቋማት የቢሮ አደረጃጀት ለተገልጋይና ለፈጻሚው በሚያመች መልኩ መደራጀቱን መገምገም፣

 የስልጠና ቦታው ለሰልጣኞች ምቹ መሆኑን እና ለስልጠናው የሚያስፈልግ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ መሟላቱን
መገምገም፣

 በተቋማቱ እየተሰጠ ባለው የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ስልጠና፣ የምዘና ሥርዓት ላይ ያሉ ክፍቶችን መለየት፣

 በማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰጡ ስልጠናዎች እንዳሉ ሆነው የንድፈ ሀሳብ እንዲሁም የተግባር ስልጠና በግላቸው
ሰልጥነው ለመፈተን ለሚፈልጉ ተገልጋዮች የስልጠና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት የስልጠና አመራጮችን
ማስቀመጥ፣

 የሌሎች አገሮች የአሽከርካሪ የስልጠና አሰጣጥና የምዘና ሥርዓት ተሞክሮዎችን በመዳሰስ ተገቢውን የማሻሻያ
ሃሰቦች ማቅረብ ነው፡፡
3. የማሰልጠኛ ተቋማት ነባራዊ ሁኔታ
የአንድን ተቋም አደረጃጀትና አሰራር ለማሻሻልና የአገልግሎት አሰጣጡን ተገልጋይ ተኮር ለማድረግ በነባሩ አደረጃጀት
የሚከናወኑ ተግባራትን እንዲሁም የነበሩን ዋና ዋና ችግሮችን መዳሰስ አስፈላጊ ነው፡፡ በከተማችን በአሁኑ ወቅት
የአሽከርካሪነት ፍቃድ ማውጣት ለሚፈልጉ ዜጎች የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና እንዲሰጡ የብቃት ማረጋገጫ
ተሰጥቷቸው በማሰልጠን ላይ የሚገኙ 66 የሚሆኑ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ማሰልጠኛ ተቋማቱ
ለከተማችን ነዋሪዎች የአሽከርካሪ የስልጠና ፍላጎት ለማሟላትና ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ወደ ተግባር የገቡ
ቢሆንም በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ሲታይ አብዛኞቹ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው ሊያስተካክሏቸው የሚገቡ በርካታ ጉድለቶች
አሉባቸው፡፡ በዚሁም መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የትራንስፖርት
አገልግሎት የሥራ ክፍል ጥናቱን በማካሄድ ከየክፍለ ከተሞቹ ናሙና በመውሰድ በቁጥር 38 ከሚሆኑ የአሽከርካሪ
ማሰልጠኛ ተቋማት በተዘጋጀው መጠይቅ መሰረት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የታዩ ክፍተቶች ዙሪያ መረጃዎችንና
አስተያየቶችን ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን በቃሊቲ የአዲስ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ማዕከል እንዲሁም የተግባር
ሥልጠና የሚሰጥባቸው ሥፍራዎችም ላይ የመስክ ምልከታ በማካሄድ በተለያዩ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰለጥኑ ሰልጣኞች
ከሰጡት በርካታ አስተያየቶች በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ችግሮችና ቅሬታዎች መኖራቸውን በጥናቱ ለመዳሰስ ተችሏል፡፡

በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት በኩል ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለባቸውን ችግሮች መፈተሽና ተቋማቱ
በተጨባጭ ያሉበትን ሁኔታ መዳሰስ በቀጣይ ችግሮቻቸውን ለይቶ ለመደገፍና በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉትን
ችግሮች ለመቅረፍ ስለሚያስችል ተቋማቱ ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ እንደሚከተለው ተዳሷል፡፡

3.1. የቢሮ አደረጃጀት

የተቋማት ዳይሬክተሮች የትምህርት ደረጃ እና ዓይነትን በሚመለከት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተመረቁ ሲሆን ከነዚህም
መካከል በህግ፣ በማኔጅመንት፣ በኢኮኖሚክስ፣፣ በታሪክ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ከተቋማቱ ፋሲሊቲዎች ጋር
ተያይዞ ወንበሮች፣ጠረጴዛዎች፣ የማስተማርያ ክፍሎች፣ የመጸዳጃ ክፍሎች፣የስልጠና ማኑዋሎችና መጽሐፎች፣ የኮሚፒዩተር
ማለማመጃ ክፍሎች እና ወርክሾፖችን ማየት ተችሏል፡፡

3.2. የአሽከርካሪዎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር አሰልጣኞች የትምህርት ደረጃ፣ ዓይነትና አፕሩቫል

ለአሽከርካሪዎች ለንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና በአውቶመካኒክ፣ አውቶሞቲቭ ኢንጅነሪንግ፣ኢንጅን ሰርቪስ፣ፓወር


ትሬይን፣ሜካኒካል ኢንጅነሪንግ፣አውቶኤሌክትሪክ እና ኤሌክትሮኒክስ የትምህርት ዓይነት የተመረቁ ሙያተኞች
በአሽከርካሪነት ስልጠና መሳተፍ እንደሚችሉ በአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ አሰራር መመሪያ ወስጥ ተቀምጧል፡፡
ሆኖም ግን በማሰልጠኛ ተቋማት በማሰልጠን ሙያ ላይ የሚገኙት አሰልጣኞች በአውቶ ኢንጅን ሰርቪስ ደረጃ 2፣ደረጃ
3፣በአውቶመከኒክ 10+3 ያጠናቀቁ እንዲሁም በአውቶመካኒክ ዲፕሎማ ያላቸው ሲሆኑ ሁሉም አሰልጣኞች አፕሩቫል
አላቸው፡፡
3.3. የማስተማርያ ተሽከርካሪዎች

የተቋማቱ የማስተማርያ ተሽከርካሪዎች በተቋማቱ ስም የተመዘገ የባለቤትነት መታወቂያ ደብተር (ሊብሬ ፣ሰሌዳ ቁጥር እና
በተቋሙ ስም ለስልጠና አገልግሎት ተብለው የተመዘገቡ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

3.4. በማሰልጠኛ ተቋማት የተሰጡ አስተያየቶች


 ተማሪዎቻችን ገና ትምርቱን ሳይጀምሩ የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ለማለፍ ክፍያ ይፈልጋል ብለው
ስለሚያስቡ ስልጠናውን በሙሉ ልቦና አይከታተሉም፣

 እድሜ የሚጠይቀው ቢስተካከል፣ የእድሜ ጉዳይ ከትምህርት ማስረጃቸው ጋር ቢታይ፣

 የክፍለ ሀገር መታወቂያ ቢፈቃድ፣

 ብዙ የመማሪያ ክፍልና ወንበር እንጠየቃለን ነገር ግን ለማስፈተን የሚፈቀድልን በጣም ጥቂት ተማሪዎችን ብቻ
ነው፣

 በአንድ የተሽከርካሪ ምድብ ስልጠና ጨርሰን በሌላ ምድብ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ሁለት ወርና ከዚያ
በላይ (75 ቀን መጠበቅ አለብን፤ መመሪያው ጥናት ቢደረግበት)

 የፈሳሽ የተሽከርካሪ ምድብ ስልጠና አልተፈቀደም፣

 ከትራንስፖርት ባለስልጣን ነው የመጣነው እያሉ ገንዘብ ለመቀበል የሚሞክሩ ሰዎች አሉ፣

 ተማሪ ማሰልጠኛ ተቋም ገብቶ ሳይማር በራሱ ሰልጥኖ መፈተን የሚችልበት መመሪያ የወጣ እንደሆነ ሰምተናል፤
የተሳሳተ ሀሳብ ስለሆነ ቢታሰብበት፣

 የህዝብ መንጃ ፍቃድ እያለን የአውቶ መንጃ ፍቃድ እንድናወጣ እንጠየቃለን፤ ትክክል አይደለም፣

 የቤተ መጻህፍት የማስተናገድ አቅም በሰልጣኞች ልክ 25 እንዲሆን ባንገደድ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰልጣኞች
ስለማይጠቀሙ፣

 የቃሊቲ አሰራር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ቶሎ ቶሎ ተፈታኞችን አያስተናግዱም፤ ወረፋ ይበዛል፣

 ጥሩ ስነ ምግባር የሌላቸውን ተማሪዎች የሚቀጣ መመሪያ ቢኖር፤ አንድ አንድ ተማሪዎች የትራንስፖርትን
ባለስልጣን እንደ መመኪያ በማድረግ ያስፈራሩናል፤ ይቆጡናል፣

 ተሰሚነት የለንም፤ የንግድ ቦታ ላይ ያለው ነው ጥፋተኛ የሚደረገው፤ አሰልጣኝ አይከበርም፣

 የማስፈተኛው የቀጠሮ ጊዜ ቀልጣፋ አይደለም፤ ረጅም ጊዜ ይወስዳል፣

 ውስን መኪና ነው የሚፈቀድልን፤ ነገር ግን ስልጠና የሚፈልግ ብዙ ሰው አለ፣


 የፈተና ቀጠሮ እና ውስን መኪና መፈቀዱ ህዝቡን በሙስና መንጃ ፍቃድ እንዲያወጣ አድርጎታል፤መንጃ ፍቃድ
ሳይኖረው የሚነዳ እንዲበዛ አድርጎታል

 የቅበላ አቅም ላይ ችግር አለ፡፡በአንድ ተሽከርካሪ አሥር ሰልጣኝ ይፈቀዳል፡፡ ሰልጣኞች ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላ
ከአሥሮቹ 2 ወይም 3 ሰልጣኞች የሚጠፉበት አጋጣሚ አለ፡፡ይህም የሆነበት ምክንያት ከረዥም ጊዜ በኋላ
ስለሚፈተኑ ነው፣

 በአውቶሞብል ለማሰልጠን ከ8-12 መቀመጫ ያለው ተሽከርካሪ ለምን እንጠየቃለን፡፡

3.4.1. በተወሰኑ ማሰልጠኛ ተቋማት የታዩ ጠንካራ ጎኖች


 በጥሩ የስልጠና ግብዓቶች (የተደራጀወርክ ሾፕ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን አሟልተው)
የሚያሰለጥኑ መኖራቸው፣

 የንድፈ ሀሳብ ፈተና ላላለፉ ሰልጣኞች የማብቂያ ስልጠና ክለሳ የሚሰጡ መኖራቸው፣

 የስነ-ምግባር ችግር ባላቸው አሰልጣኞች ላይ ምክር የሚለግሱና የማስተካከያ እርምጃ የሚወስዱ መኖራቸው፣

 በስነ-ምግባርም ሆነ በቴክኒክ ብቃታቸው የተሟሉ መምህራንና በቴክኒክ ብቁ የሆኑ የማሰልጠኛ ተሽከርካሪዎችን


በማቅረብ የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያከናውኑ ተቋማት መኖራቸውን ተገንዝበናል፡፡

3.4.2. ከተግባር ስልጠና ጋር ተያይዞ የተሰጡ አስተያየቶች


 በአንድ ተሸከርካሪ አስር ሰልጣኝ ነው የሚፈቀደው፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ በአንድ ተሸከርካሪ እስከ 30
ሰልጣኞች የሚሰለጥኑበት ሁኔታ አለ፡፡ በቂ የሆነ የማሰልጠኛ ተሽከርካሪ አለመኖር (የሰልጣኞች የተግባር ልምምድ
ላይ ተፅዕኖ ማምጣት) ፣

 የተግባር ስልጠና ሙሉውን አለማሰልጠን፡፡ ሰዓታቸውን ለልምምድ እንዳይጠቀሙ እና በተከታታይ ልምምድ


አድርገው ቶሎ ጨርሰው ለፈተና አለማቅረብ (የሰዓት መሸራረፍ አለ)፣

 የተግባር ስልጠናው በቂ የትራፊክ ምልክቶች፣የትራፊክ መብራቶች፣የመንገድ ዳር ቅቦች በሌሉበት ቦታ ላይ


በመሰጠት ላይ ነው፡፡ የተግባር ማሰልጠኛ ቦታው በጣም አይመችም፤ ጠባብ ነው፣

 ተሽከርካሪዎች ስለሚበዙ የመኪና ማቆሚያ የለም፣ የሰልጣኞች ማረፊያ ቦታ የለም፣

 ተጨማሪ የሰዓት ክፍያ እንጠየቃለን ፤ የተለየ ነው በሚል፣

 አሰልጣኞች ፈተና አለብን እያሉ የመቅረት ችግር አለ፤ የረጅም ጊዜ ቀጠሮ ይሰጡናል፣

 የተግባር ማሰልጠኛ ቦታው ወጣ ገባ ነው ለመለማመጃ አይሆንም፣ ጠባብ ነው ፣ ዝናብ ሲሆን ወዲያው


ይጨቀያል፣

 አንዳንድ ማሰልጠኛ ተቋማት የተግባር ማሰልጠኛ ቦታ ከማጣት የተነሳ በግላቸው ቦታ ፈልገው የሚያሰለጥኑበት
ሁኔታ አለ፣
 ሰልጣኞች የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት ቦታ የመሰናክል ቦታ ጭቃማ እና መኖሪያ አካባቢ መግቢያና መውጫ
አጠገብ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ከነዋሪዎቹ ጋር ውዝግብ እንደሚነሳና ምቹ አለመሆኑ፣ በቂ የማለማመጃ ጠርዝ
አለመኖሩ እና ለአደጋ ተጋላጭ መሆኑ ፡፡ ለምሳሌ አንፎ እና ኪዳነ ምህረት አካባቢ፣

 አንዳንድ የተግባር አሰልጣኞ ች እና ፈታኞች በልምምድ ላይ እና በፈተና ላይ ሰልጣኞች ላይ መጮህና በማስደንገጥ


ግራ ማጋባት፣

 አሰልጣኝ ከሰልጣኙ ጋር ቀጠሮ ከያዘ በኋላ ጠፍቶ ሰልጣኙ በግሉ የሚሰለጥንበት አጋጣሚ አለ፣

 ዋናው አሰልጣኝ አንዳንዴ በሚያውቃቸው የሰፈር ልጆች ሰልጣኝ እንዲሰለጥን ያደርጋል፣

 የትራፊክ መንገድ ላይ (ዋና መንገድ ላይ) በቂ የተግባር አነዳድ ስልጠና አይሰጥም፣

 የተግባር ስልጠና ላይ የቴክኒክ ብቃት ባልተሟላ አሽከረካሪ ማሰልጠን፡፡ለምሳሌ የእጅ ፍሬን፤ፍሬቻ፤ ክላክስ
በማይሰራ ተሽከርካሪ ስልጠና የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡ የተሽከርካሪ ፍተሻ አለ ሲባል ተሽከርካሪው ጋራዥ ይገባል፡፡
ተመልሶ ወዲያውኑ ይበላሻል፣

 ሰልጣኙን የተግባር ስልጠና ሳያሰለጥኑ አቴንዳንስ የሚያስፈርሙ አሰልጣኞች አሉ፡፡ ሰልጣኝ ቆይቶ ሲመጣ የ 3
ቀን አንዴ የሚፈርምበት አጋጣሚ አለ፡፡

 ለአካል ጉዳተኞች የአሽከርካሪነት ስልጠና መኖር አለበት፡፡ሰው እችላለሁ እያለ አትችልም በማለት የሰውን ሞራል
የሚሰብሩ አሰልጣኞች አሉ፡፡ አንድ አካል ጉዳተኛ የሆስፒታል የጤና ምርመራ አልፎ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ብቻ
መንዳት አይችልም የሚባልበት ሁኔታ አለ፣

 አንዳንድ አሰልጣኞች ሰልጣኞቻቸውን ከተግባር ልምምድ በኋላ ሰልጣኙ ይችላል አይችልም ብሎ መከታተል
የለም፡፡ ሰልጣኙ በአቋራጭ መንጃ ፍቃድ እንዲያገኝ ያበረታታሉ፣

 በአንዳንድ አሰልጣኞች ሰልጣኙ በአግባቡ ስልጠና ሳይሰለጥን ወደ ፈተና ግባ ማለትና ማስገደድ ይታያል፣

 የተግባር ስልጠና ላይ የተሽከርካሪ ፍተሻ ምን ምን ያካትታል ሲባሉ ጎማ ብቻ ነው የሚፈተሸው የሚሉ አሰልጣኞች


አሉ፣

 ብዙ ማሰልጠኛ ተቋማት አንድ ቦታ ላይ የተግባር ስልጠና ስለሚያሰለጥኑ ለብዙ ሰዓት ቆሞ መጠበቅ ፣ የቦታ
ሽሚያ አለ፡፡ አንፎ አካባቢ 11 ተቋማት በዛ ጠባብ ቦታ ላይ እንደሚያለማምዱ ለማየት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም
አንፎ መሐል መንገድ ላይ የመሰናክል ልምምድ ለደረቅ ተሽከርካሪ ለማጅ መሆኑ ለሰልጣኞቹም ሆነ
ለአሰልጣኞቻቸው ምቹ አለመሆኑ እና ለአደጋ ተጋላጭ መሆኑ ታይቷል፡፡

3.4.3. ከንድፈ ሀሳብ ስልጠና ጋር ተያይዞ የተሰጡ አስተያየቶች


 የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ሙሉውን አለማሰልጠን፡፡ (የሰዓት መሸራረፍ አለ)፣

 የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ትኩረት ሰጥተው በደንብ አለማስረዳት፣


 ተመሳሳይነት ያለው የማሰልጠኛ ማኑዋል አለመኖር እና ወጥነት ያለው ስልጠና አለመኖር፣

 የሥልጠና ሰዓት አለማክበር (የስልጠና መግቢያና መውጫ ሰዓት)፣

 በአንዳንድ ማሰልጠኛ ተቋማት የስነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው አሰልጣኞች አሉ፡፡ ሰልጣኙን አለማክበር፤ ፆታዊ
አድልዎ ማድረግ፣

 የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን አለመጠቀም፡፡ ለምሳሌ የተሟላ የተሽከርካሪ የተለያዩ ክፍሎችን ማሳያ ሞዴል ፤
በቪዲዮ የተደገፈ ምስል አለማሳየት፣

 የንድፈ ሀሳብ ፈተና በአንድ ማዕከል መሆኑ ተደራሽነትን ይቀንሳል፣

 አንዳንድ የማሰልጠኛ ተቋማት የሚገኙበት ቦታ መንገድ ዳር በመሆኑ የፀጥታ ችግር መኖሩ፣

 የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ከምዝገባ ጀምሮ በ3 ወር ያልቃል ተብሎ ከ3 ወራት በላይ መጉላላት፡፡

3.4.4. ከፈተና ጋር ተያይዞ የተሰጡ አስተያየቶች


የቃሊቲ አዲስ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ተቋም መፈተኛ ቦታ ለማለማመድ ችግር አለ፡፡ ከፈተና በፊት
ለመለማመድ የሚፈቀደው ለትንሸ ሰዓት ብቻ ነው፣

የፈተና ጥያቄ ይደገማል ፤ የጥያቄዎቹ ምርጫዎች አወዛጋቢ መሆን፣

ከፈተና በፊት ለተፈታኞች መረጃ አለመስጠት፤ ለምሳሌ - ፈተናውን ለመጨረስ የሚፈጀውን ሰዓት፤ የጥያቄ ብዛት፣

ፈተና የሚፈትኑት ፈታኞች ትህትና የላቸውም፣ ይሳደባሉ፤ ይቆጣሉ፤ ያመናጭቃሉ፤ ያደናግራሉ፤ተፈታኞቹ ላይ


ጭንቀት ይፈጥራሉ፣

አሰልጣኞች በመቀራረብ ነው የሚሰሩት፡፡ የተቋማት አሰልጣኞች ከአዲስ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ተቋም
ፈተና ፈታኞች ጋር ልዩ ጥቅም ከመፈለግ የተነሳ እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ አለ፡፡ተፈታኝ ከማሰልጠኛ
ተቋም ለፈተና ብቁ ነው ተብሎ ወደ አዲስ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ተቋም ለፈተና ሲላክ የተግባር ፈተና
በሚፈተንበት ጊዜ ዛሬ አታልፍም፣ወድቀሃል ውረድ ፣የደህንነት ቀበቶ ካላሰርሽ በቃ ወድቀሻል የሚባልበት ሁኔታ
አለ፣

ተፈታኙ የተግባር ፈተና ላይ ስህተት የሰራበት ቦታ ሳይነገረው ወድቋል ተብሎ ይለጠፋል፡፡ ለዚህ ተጠያቂ የሚሆን
ማንም የለም፡፡ ተፈታኙ የተግባር ፈተና ላይ በትክክል ሰርቻለው በሚልበት ጊዜ ሰሚ ባለመኖሩ ለቀጣይ ፈተና
ብቻ ነው የሚቀርበው፣

አንዳንድ አሰልጣኞች የተቋማቸውን ሰልጣኞች ትተው ከሌላ ተቋም የመጣውን ሰልጣኝ የግል ጥቅም ከመፈለግ
የተነሳ ሰልጣኙን በማግባባት ለፈተና እናበቃለን ብለው የሚያሰለጥኑበት ሁኔታ አለ፡፡
4. የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች
በአለማችን በስልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሱ ከተሞች መካከል እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ስዊድን፣ ጀርመን፣ኖርዌይ ተጠቃሾች
ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀገራት የሚሰጠው የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ስልጠናና የምዘና ሥርዓት እንዲሁም የሚሰጡት
አገልግሎቶች በተመራጭ ቴክኖሎጂ የታገዙ በመሆናቸው ተገልጋዩ በቀላሉ በድረ-ገፆች መገልገል ይችላል፡፡ ዕጩ
አሽከርካሪዎች ለንድፈ ሀሳብ ፈተና የሚረዳቸውን መፅሓፍቶችን በቀላሉ ከድረ-ገፅ ማግኘት ይችላሉ፡፡

ከአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ስልጠናና የምዘና ሥርዓት ጋር ተያይዞ የእንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ስዊድን፣ጀርመን፣ ኖርዌይ
እና የኬንያ ሀገራት ተሞክሮዎች ተወስደዋል፡፡

4.1. የእንግሊዝ አገር ተሞክሮ


በእንግሊዝ ከሚገኘው የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድ ማረጋገጫ ኤጀንሲ የሚከተሉት ተሞክሮዎች ተወስደዋል፡-
በእንግለዝ አገር የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ስልጠና ለመውሰድ የሚፈልግ ዕጩ አሽከረካሪ ዕድሜው ቢያንስ 17
ዓመት ከሞላው ለስልጠና ማመልከት ይችላል፡፡አሰልጣኞች ዕድሜያቸው ቢያንስ 21 ዓመት የሞላቸውና በአሽከርካሪነት የ3
ዓመት ልምድ ያዳበሩ እንዲሁም በአሽከርካሪ ብቃት ኤጀንሲ የተመሰከረላቸው የ45 ሰዓት ሙያዊ ስልጠናና ለ 22 ሰዓት
በግላቸው የተግባር ልምምድ ያደረጉ መሆን አለባቸው፡፡
ተፈታኝ የንድፈ ሀሳብ ፈተና ወስዶ ካለፈ ውጤቱ ለ 2 ዓመት ያገለግላል፡፡ ተፈታኙ በ2 ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የተግባር
ፈተና ካልወሰደ የንድፈ ሀሳብ ፈተና ደግሞ እንድወስድ ይገደዳል፡፡የንድፈ ሀሳብ ፈተናው ከ2002 እንደ አውሮፓውያን
አቆጣጠር ጀምሮ በቪዲዮ ወይም በኮምፒዩተር ላይ ተቀርጾ የሚለቀቁ በመንገድ ላይ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ የተለያዩ
ትዕይንቶችን ልክ እንደ ተመለከተ የኮምፒዩተሩን ማውዝ ተጭኖ እንዴት አደጋውን መከላከል እንደሚችል
ይፈተናል፡፡ለምሳሌ የመንገድ ዳር ምልክቶች ሲያጋጥሙ፣ እግረኛ ሲያቋርጥ፣ ፍጥነትና ርቀትን ማገናዘብ የማይችሉ ህፃናትና
አረጋውያን መንገድ ሲያቋርጡ፣ ረጃጅም ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ ሲያጋጥሙ፣ የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎች
ሲያጋጥሙ፣ብስክሌተኞችና ሞተረኞች ሲያጋጥሙ፣ መስቀለኛ መንገድ ላይ፣ ወዘተ ምን ማድረግ እንዳለበት ይፈተናል፡፡
የተግባር ፈተና በተለያዩ መንገዶች ላይ ረጅም ርቀት የሚሸፍን ሲሆን ዋና ፈታኝ አብሮት ይሆናል፡፡ የእጩ አሽከርካሪ
አሰልጣኝ በፈተና ጊዜ ከዋናው ፈታኝ ውጭ የፈተናውን ሁኔታ ለመታዘብ ከፈለገ ይፈቀድለታል፡፡
4.2. የአሜሪካ ዋሽንግተን እስቴት የባለሞተር ተሽከርካሪ ዲፓርትመንት
በአሜሪካ ዋሽንግተን እስቴት የአሽከርካሪነት ትምህርት የሚፈልጉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሆነው 16 ወይም 17
ዓመት የሞላቸው ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ውጪ የአሽከርካሪነት ትምህርት በሚሰጡ ትምህርት ቤቶች
ለአሽከርካሪነት ትምህርት ተመዝገበው መማር ይችላሉ፡፡ ሰልጣኙ ቤተሰቡን አስፈቅዶ በተዘጋው ስርዓተ ስልጠና መሰረት
የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠናውን መጨረስ ይኖርበታል፡፡ የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ክፍል ውስጥ 30 ሰዓት የትራፊክ
ደህንነት ትምህርት እንዲሁም 6 ሰዓት ስለ ተሽከርካሪ አነዳድ ስልጠና ይወስዳል፡፡ለተግባር ስልጠና የሚፈቀደው 50 ሰዓት
ሲሆን አስሩን ሰዓት በማታ ክፍለ ጊዜ ይሰለጥናል፡፡የተግባሩን ስልጠና ከወላጆች ጋር ወይም 5 ዓመትና ከዚያ በላይ
የማሽከርከር ልምድ ካለው አሰልጣኝ ጋር መሰልጠን ይችላል፡፡የተግባር ስልጠናው ላይ የሰልጣኙ ወላጅና ሰልጣኙ
በሀገርቷ የባለሞተር ተሽከርካሪ ዲፓርትመንት ሕግ መሰረት የሚታወቅ የስልጠና ስምምነት ይፈራረማሉ፡፡ የተግባር
ስልጠናው የትራፊክ መጨናነቅ በሌለባቸው መንገዶች ላይ እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው የተለያዩ መንገዶች ላይ
ረጅም ርቀት የሚሸፍን ስልጠና ይሰጠል፡፡ ስልጠናው ካለቀ በኋላ ፈተና ወስደው የመሸጋገሪያ መንጃ ፍቃድ
ይሰጣቸዋል፡፡ዕድሜያቸው 18 ዓመት ከሞላቸውና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምንም አይነት የትራፊክ ደንብ መተላለፍ
ቅጣት ከሌለባቸው መንጃ ፍቃዳቸው በቀጥታ ወደ ሙሉ መንጃ ፍቃድ ይቀየርላቸዋል፡፡
በአንጻሩ ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ጎልማሶች ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው ስልጠና የመውሰድ ግዴታ
የለባቸውም፡፡ በራሳቸው ሰልጥነው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ፈተና ካለፉ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ማግኘት ይችላሉ፡፡
በዋሽንግተን እስቴት መንጃ ፍቃድ ለማግኘት ሁለት አማራጮች እንዳሉ ለማየት የተቻለ ሲሆን አንደኛው ትምህርት ቤት
ተገብቶ የአሽከረካሪነት ትምህርት በመማር ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ በግል ራስን በማብቃት ነው፡፡
የንድፈ ሀሳብ ፈተና በኮምፒዩተር ላይ የሚሰጥ ሲሆን ከ40 የምርጫ ጥያቄዎች አንድ ዕጩ ተፈታኝ ለማለፍ 32 ጥያቄዎችን
በትክክል መመለስ ይኖርበታል፡፡ተፈታኝ የንድፈ ሀሳብ ፈተና ወስዶ ካለፈ ውጤቱ ለ 2 ዓመት ያገለግላል፡፡
የተግባር ፈተና በተለያዩ መንገዶች ላይ ረጅም ርቀት የሚሸፍን ሲሆን ዋና ፈታኝ ከተፈታኙ ጎን ሆኖ የፈተናውን ውጤት
ፈተናው በመካሄድ ላይ እያለ ይሞላል፡፡

4.3. የስዊድን አገር ተሞክሮ


በስዊድን የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ስልጠና ለመውሰድ የሚፈልግ ዕጩ አሽከረካሪ በማሰልጠኛ ተቋም ወይም
በግል መሰልጠን ይችላል፡፡ በግል የአሽከርካሪነት ስልጠና ለመውሰድ የፈለገ ሰልጣኝ በሚፈልግበት የተሽከርካሪ ምድብ
የማሰልጠን ብቃትና አፕሩቫል ያለውን አሰልጣኝ ፈልጎ መሰልጠን ይችላል፡፡አሰልጣኙም በስዊድን የትራንስፖርት ኤጀንሲ
የማሽከርከር ብቃቱ የተረጋገጠ መሆን አለበት፡፡ አሰልጣኙ የሚያሰለጥንበትን ተሽከርካሪ ሙሉ ኃላፊነት ይወስድና እራሱም
የ 5 ዓመት የማሽከርከር ልምድ ያለውና ዕድሜው 24 ዓመት የሞላው መሆን ይኖርበታል፡፡ በግል ስልጠና የፈለገ ሰልጣኝ
በአውቶሞቢል እንዲሁም ጠቅላለ ክብደቱ አስከ 3, 500 ኪሎ ግራም በሆነ ቀላል ተሽከርካሪ መሰልጠን ይችላል፡፡ሰልጣኙ
ከግል አሰልጣኙ በተጨማሪ በወላጆቹ አጋዥነት ስልጠና መሰልጠን ይችላል፡፡

ስልጠናውን በማሰልጠኛ ተቋም የሚሰለጥን ሰልጣኝ ለንድፈ ሀሳብ ስልጠና የሚረዳው ማኑዋል ከስልጠና
ማዕከሉ፤ከማሰልጠኛ ተቋሙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፤ ከቤተ መጻሕፍት፤ ከመጻሕፍት መደብር እንዲሁም ከድረ-ገፅ ማግኘት
ይችላል፡፡
የንድፈ ሀሳብ ፈተና በኮምፒዩተር ላይ ተፈትኖ ውጤቱን ወዲያው ማወቅ ይችላል፡፡ ማንበብ ካልቻለ አሳማኝ ምክንያት
አቅርቦ የፈተና ጊዜ እንዲራዘምለት በመጠየቅ የቃል ፈተና ወይም በአስተርጓሚ ፈተና እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ መፈተን
ይችላል፡፡ የተግባር ፈተና የማሰልጠኛ ተቋሙ በሚያቀርብለት ተሽከርካሪ መፈተን ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ በአገሪቱ
ከሚገኘው የትራንስፖርት አስተዳደር በመከራየት እንዲሁም በግሉ ባመጣው ተሽከርካሪ መፈተን የሚችልበት አማራጭ
አለው፡፡

በስዊድን የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ለ 2 ዓመት የሙከራ ጊዜ ይፈቀዳል፡፡በ 2 ዓመት የሙከራ ጊዜ ውስጥ
ከ3-4 ጊዜ የደንብ መተላለፍ ጥፋት ከፈጸመ እንደ አዲስ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ፈተና እንዲወስድ የሀገርቷ ሕግ
ያስገድዳል፡፡

4.4. የጀርመን አገር ተሞክሮ


በጀርመን ዕጩ አሽከርካሪ ለአሽከርካሪነት ስልጠና ማሰልጠኛ ተቋም በመግባት ይሰለጥናል፡፡ ሰልጣኙ በቂ የንድፈ ሀሳብ
ስልጠና ከወሰደ በኋላ ፈተና በላፕቶፕ ኮምፒዩተር ላይ ይፈተናል፡፡ ተፈታኙ የትኛውን ጥያቄ እንደ ተሳሳተ የማየት ዕድሉ
ሰፊ ነው፡፡የመጀመሪያውን ፈተና ከወደቀ ከ14 ቀናት በኋላ ደግሞ መፈተን ይችላል፡፡
የተግባር ስልጠናው በተለያዩ መንገዶች ላይ ሆኖ ረጅም ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ አገር አቋራጭ መንገዶችንም ይጨምራል፡፡
የተግባር ስልጠናውን የሚሰጠው ከባለሞተር ተሽከርካሪ ዲፓርትመንት የተመደበ አሰልጣኝ ሲሆን ዕድሜው ከ30 ዓመት
ያላነሰ፤ ሕጋዊ መንጃ ፍቃድ ይዞ የ5 ዓመትና ከዚያ በላይ ልምድ ያለውና የደንብ መተላለፍ ጥፋት የሌለበት መሆን
አለበት፡፡
አንድ ሰልጣኝ ለተግባር ፈተና የሚያመለክተው፡-

 መሰልጠን ያለበትን መሠረታዊ የተግባር አነዳድ ስልጠና ከጨረሰ፣

 አሰልጣኙ ለተግባር ፈተና ብቁ ነው ብሎ ካረጋገጠለት፣

 የንድፈ ሀሳቡን ፈተና ቀድሞ ካለፈ፣

 ላመለከተበት የተሽከርካሪ ምድብ ዕድሜው በቂ ከሆነ ነው፡፡

በተግባር ፈተና ጊዜ ዕጩ አሽከረካሪ፣አሰልጣኙና ከትራንስፖርት የባለሞተር ተሽከርካሪ ዲፓርትመንት የሚመደበው ፈታኝ


አንድ ላይ ሆነው ፈተናው ይካሄዳል፡፡ በጀርመን አገር ፈታኞች ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ24 ዓመትና ከዚያ
በላይ ፤በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ወይም ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሆነው ቢያንስ የ 6 ወር
የፈታኝነት ስልጠና የወሰዱ መሆን አለባቸው፡፡
ለጀማሪ አሽከርካሪ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ለ 2 ዓመት የሙከራ ጊዜ ይፈቀዳል፡፡በ 2 ዓመት የሙከራ ጊዜ ውስጥ
የትራፊክ ደንብ ሳይጥስ እያሽከረከረ ብቃቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡
4.5. የኖርዌይ አገር ተሞክሮ
በኖርዌይ ዕጩ አሽከረካሪ የአሽከርካሪነት ስልጠና በማሰልጠኛ ተቋም እንዲሁም በግሉ መሰልጠን ይችላል፡፡ የስልጠና
አሰጣጡ ደረጃ በደረጃ ሲሆን ሰልጣኙ መጀመሪያ አሽከርካሪው ስለ አሽከርካሪ ስነ ምግባር፤የትራፊክ ሕጎችና ደንቦች ላይ
በቂ የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ይወስዳል፡፡ በመቀጠል በተግባር ስልጠናው ላይ ስለ መሰረታዊ የማሽከርከር ስልት ቴክኒካዊ
ስልጠና፣ በተለያዩ መንገዶች ላይ በትራፊክ ፍሰት ላይ የተመሰረተ የማሽከርከር ስልጠና ይወስዳል፡፡
የተግባር ስልጠና በሚሰለጥነበት ጊዜ የተለያዩ መስመሮች ላይ ሆኖ መጀመሪያ መደበኛ የትፊክ ፍሰት ባለባቸው መስመሮች
ላይ ከሰለጠነ በኋላ ቀጥሎ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ባለበት የጉዞ መስመሮች ላይ ይሰለጥናል፡፡የጉዞ መስመሩ ከ35-45 ኪሎ
ሜትር ይሸፍናል፡፡
የንድፈ ሀሳብ ፈተና ለአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድ ማረጋገጫ ጽ/ቤት አመልክቶ እዚያው ጽ/ቤት መፈተን ይችላል፡፡
ማመልከቻውን በመረጃ መረብ መላክ ይችላል፡፡ የንድፈ ሀሳብ ፈተና ከመፈተኑ በፊት የአይን ምርመራ ያደርጋል፡፡ፈተናውን
ከወደቀ ከ2 ሳምንት በኋላ ደግሞ መፈተን ይችላል፡፡
የተግባር ፈተና የትራፊክ ፍሰት ባለበት መንገድ ላይ ይፈተናል፡፡ የተግባር ፈተና ከወደቀ የወደቀበት ምክንያት ምን እንደሆነ
በጽሑፍ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡ ፈተናውን ከወደቀ ደግሞ ለመፈተን 4 ሳምንት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡

4.6.የኬንያ አገር ተሞክሮ


በኬንያ በየአመቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በህይወት መጥፋትና በንብረት ውድመት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡
በአገሪቱ የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ የትራፊክ አደጋን አስመልክቶ ከ90% በላይ አደጋ
የሚከሰተው በአሽከርከሪዎች ስህተት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህንን አስከፊ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ለአሽከርካሪዎች በቂ
የንድፈ ሀሳብና የክህሎት ስልጠና እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ለአሰልጣኞችና ለሰልጣኞች ስርዓተ ስልጠና በአገሪቱ
የትራንስፖርት ደህንነት ባለስልጣን ተቀርጾ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡
በኬንያ ለአሽከርካሪ አሰልጣኞች የሚፈቀደው ዕድሜ 23 ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኖ ስልጠናውን በሚፈልጉበት የተሽከርካሪ
ምድቦች ለ126 ሰዓት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ ለአንድ አሰልጣኝ ከ24 ሰልጣኞች በላይ ማስተማር
አይፈቀድለትም፡፡በማንኛውም የተሽከርካሪ ምድብ ለማሰልጠን አንድ አሰልጣኝ የ3 ዓመት የማሽከርከር ልምድ ያለው
መሆን አለበት፡፡
የማሰልጠኛ ተቋም ማናጀር በትምህርት ቢያንስ ዲፕሎማ ያለው/ያላት እንዲሁም የአሰልጣኝነት መንጃ ፍቃድ ያለው/ያላት
መሆን አለበት፡፡
ሰልጣኝ በቂ የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ከወሰደ በኋላ በማሰልጠኛ ተቋሙ የተዘጋጀለትን የንድፈ ሀሳብ ፈተና በየሳምንቱ
መጨረሻ ይወስዳል፡፡ በመጨረሻም የንድፈ ሀሳብ ፈተና ይወስዳል፡፡ፈተና ከወደቀ ከ21 ቀናት በኋላ መፈተን ይችላል፡፡
በተግባር ስልጠና ሰልጣኙ መጀመሪያ በትራፊክ ኮምፕሌክስ ውሰጥ የመሰናክል ስልጠና ከጨረሰ በኋላ የትራፊክ መንገድ
ላይ ስልጠና ይወስዳል፡፡
የተግባር ፈተና በሁለት ይከፈላል፡፡ መጀመሪያ በትራፊክ ኮምፕሌክስ የመሰናክል ፈተና ይወስዳል፡፡ቀጥሎ በተመረጠ
የትራፊክ መንገድ ላይ ይፈተናል፡፡የተግባር ፈተና ከወደቀ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ደግሞ መፈተን ይችላል፡፡
በተቀመጠው የጊዜ ገድብ ውስጥ ደግሞ ፈተና ካልወሰደ እንደ ጀማሪ ተመዝግቦ ስልጠናውን ይደግማል፡፡
የመፍትሄ ሃሳቦች
የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የሚከተሉት የመፍትሄ
ሃሳቦች ተቀምጠዋል፡፡

 የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሱፐርቭዥን ቡድን በመመደብ የተቋማት የንድፈ ሀሳብ
እና የተግባር ስልጠና አሰጣጣቸውን በአካል ተገኝቶ እንዲገመግሙ ቢያደርግ ጥሩ ነው፣

 ተፈታኞች በተግባር ፈተና ጊዜ በፈታኞች ስለሚረበሹ የፈተና ቦታ ቢፈተሽ ጥሩ ነው፣

 ሰልጣኞች ግርታ እንዳይፈጠርባቸው ስልጠና ሳይጀምሩ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና የሚወስዱበት ቦታ በቂ ግንዛቤ
ቢያገኙ፣

 በንድፈ ሀሳብ ፈተና ብዙ ተፈታኞች ስለሚወድቁ የንድፈ ሀሳብ ፈተና ትኩረት ተሰጥቶበት ቢፈተሽ፣

 ለሰልጣኞች በስርዓተ ትምህርቱ መሰረት ስልጠና የማይሰጡ፣ለስልጠናው አስፈላጊው ግብዓት የማያሟሉ፣ብቃት


ባለው አሰልጣኝ የማያሰለጥኑ፣ሰልጣኞችን በኮምፒዩተር አጠቃቀም ላይ በቂ ስልጠና ሰጥተው የማያበቁ
የማሰልጠኛ ተቋማትን በመለየት ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ፣

 የቴክኒክ ብቃታቸው ያልተረጋገጠና ችግር ያለባቸውን ተሸከርካሪዎች ለስልጠናና ለፈተና በሚያቀርቡ እንዲሁም
የሰልጣኝ ተሽከርካሪ ጥምርታን በመጠበቅ በማያሰለጥኑ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ተከታትሎ ተገቢውን እርምጃ
መውሰድ፣

 በማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰጡ ስልጠናዎች እንዳሉ ሆነው በግላቸው በማጥናት የንድፈ ሀሳብም ሆነ የተግባር
ፈተና ለመፈተን ለሚፈልጉ ተገልጋዮች አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር፣

 ለዕጩ አሽከርካሪዎች የተግባር ስልጠና ከማእከል በተጨማሪ በተመረጡ መንገዶች ላይ ብዙ ርቀት የሚሸፍን
የአነዳድ ስልጠና እንዲሰለጥኑና የተግባር ፈተናውም በእነዚሁ መንገዶች ላይ በተመራጭ ቴክኖሎጂ በመታገዝ
የሚሰጥበት አሰራር ቢኖር፣

 የተግባር ማሰልጠኛ ቦታዎች ለሰልጣኞች የሚመቹ እንዲሆኑ ሰፊና የትራፊክ ምልክቶች ያላቸው ቢሆኑ፣
ማጠቃለያ

በከተማችን የአሽከርካሪ ስልጠና አሰጣጥ፣ ብቃት ማረጋገጥና የፍቃድ አሰጣጥ አገልግሎቶች ዙሪያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ
በመረዳት እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን በመለየትና ከከተማው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለተገልጋዩ
ህብረተሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ በሆነ መልኩ በመስጠት የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ
ፍላጎት ማርካት ወሳኝ ነው፡፡ ከከተማው ዕድገት ጋር ተያይዞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ህብረተሰብ ቁጥርና ፍላጎት በከፍተኛ
ሁኔታ እየጨመረና አገልገሎቱ በተመራጭ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የማይሰጥ በመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚፈለገውን
ውጤት ለማምጣት አልተቻለም፡፡

በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና
ቁጥጥር ባለሥልጣን የአገልግሎት አሰጣጡ የሚሻሻልበት ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ወጥ የሆነ የክትትልና ቁጥጥር
ስርዓት በመዘርጋት አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የታዩ ችግሮችን መነሻ በማድረግና የቁጥጥር ስርዓቱን
በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በተለይ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትን የመፈፀም አቅም
በማሳደግ የዘርፉን ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ተቋማቱ ሙሉ አገልግሎት መስጠት ወደ
ሚችሉበት ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል፡፡
መረጃና አስተያየት የተሰበሰበባቸው የማሰልጠኛ ተቋማት ዝርዝር

ሴፍቲ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ኢትዮ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ቪው የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ብስራት የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ሰላም የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ቶፕ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

አሸተ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ደሩ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ኬቢ ኢንተርናሽናል የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ረቂቅ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ኦስሎ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ይሄነው ማስተዋል የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ህብረት አዲስ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ራሊ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ቢ-ኢንተርናሽናል የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ሮሆቦት የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ዲ. ኤም የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ፎርዊል የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ሳይን የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ሐሮት የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ምዕራፍ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም


ኦልካርስ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

አማስ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ሚሽከን የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ኤስ.ኬ.ኤስ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ፖራጎን የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ጋስፖ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ሀረግ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ባላንስ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ኬርቲና የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ጌትነት የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ተከዜ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ዳይናሚክ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

አመዩ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ሀሌሉያ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ላይን የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ናሂላ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

ኤ.ዜድ.ኬ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም

You might also like