You are on page 1of 4

ቀሲስ መ/ር ሄኖክ ወ/ማርያም 

የወሊድ መቆጣጠሪያ መውሰድ ይቻላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወሊድ መቆጣጠሪያ ምን ይላል?

ከሰዎች ወቅታዊ ችግር አንጻር እንዴት ይታያል?

ተወዳጆች ሆይ በዚህ ርእስ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ሥርዐት እና ከሰዎች ወቅታዊ ችግር አንጻር በሰፊው እንመለከታለን፡፡ የወሊድ

መቆጣጠርያ መውሰድ ይቻላል ወይስ አይቻልም ብለን ስናስብ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር መለኮታዊ እቅድ እና ሐሳብ ብሎም የሰውን ልጅ

ዘር ከማስቀጠል ጋር ነው የምንጋጨው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር መውለድን ተቆጣጠሩ ሳይሆን በመውለድ ተባዝታችሁ ኑሩ ነው ያለን፡፡

እኛ ገና ያልተፈጠሩት ልጆች በወሊድ መቆጣጠሪያ ወደዚህች ምድር እንዳይመጡና ከእኛ አብራክ እንዳይወለዱ እንከላከላለን፡፡ ግን ልዑል

እግዚአብሔር ገና ሳንፈጠር አካላችን በእናታችን ማሕፀን ሳይሠራ፣ ነፍሳችን በሥጋችን ሳትዘራ ያውቀናል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ያልተሠራ አካሌን

ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ አካሌን ቀኖቼ ሁሉ አንድስ እንኳ ሳይኖር በመጽሐፍ ተጻፉ›› ያለው፡፡

ወዳጆቼ እግዚአብሔር በማሕፀን ሳንሠራ አካላችንን ያውቃል ያያል፡፡ /መዝ 139፣16/ እንዲሁም እግዚአብሔር እኛ ገና ለገና ሳይፈጠሩ

የወሊድ መቆጣጠሪያ ወስደን እንዳይወለዱ የምንከላከላቸውን ልጆች አስቀድሞ ሳይፈጠሩ እንደሚያውቃቸው በመጽሐፈ ኤርሚያስ ላይ

‹‹በሆድህ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ ስለዚህ እኛ መውለድ እየቻልን ግን በወሊድ መቆጣጠሪያ ይምከኑ አይምከኑ

የማናውቃቸው ልጆች በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት›› ብሎ በቡራኬ አዞናል፡፡ ግን

እጅጉን በሚያሳዝን ሁኔታ ዛሬ ልጆች እንደ ሸክም ተቆጥረዋል፡፡ እኛ አንወልድም እያልን በወሊድ መቆጣጠሪያ የምንከላከላቸው ልጆች

መካኖች መውለድ የሚመኟቸው ልጆች ናቸው፡፡ እኛ ለምለም ማሕፀን ይዘን ልጅ መውለድ አልፈልግም የምንለው መካኖች ዐሥር

በወለድኩበት የሚሉበት ማሕፀን ነው፡፡

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ደረጃ የወሊድ መቆጣጠሪያን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተቃወመው በይሁዳ ልጅ በአውናን ነው፡፡ ትዕማርን ያገባው

ዔር ክፉ ስለነበር አካሄዱም ከእግዚአብሔር መንገድ የወጣ ስለሆነ እግዚአብሔር ቀሠፈው ሞተ፡፡ ምስኪኗ ትዕማርም ያለ ባል ቀረች፡፡ ከዚያም

ለሟቹ ለዔር ወንድም ለአውናን በጋብቻ ተሰጠች፡፡ አውናንም እንደ ወንድሙ ክፉ ነበርና ያለውን ርስት ገና ለገና በሟች ወንድሙ ፈንታ

ለሚወልዳቸው ልጆች ላለማካፈል ብሎ በወቅቱ በነበረው የእርግዝና መከላከያ ዘዴ እና በነበረው ልምምድ ከትዕማር ጋር ሩካቤ ሥጋ ሲፈጽም

ዘሩን ከማሕፀንዋ ውጭ እያፈሰሰ እርግዝናን ይከላከል ነበር፡፡ ይህንን ተግባሩን መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ

ሆነበት፣ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው›› ይለናል፡፡ /ዘፍ 38፣10/ ወዳጆቼ አውናን በወቅቱ በነበረው ልምድ ባደረገው እርግዝና መከላከያ ዘዴ

እርሱም ዘርን ከማሕፀን ውጪ በማፍሰስ ቢጠቀምም ከእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቅሥፈትን አስተናግዷል፡፡

አንዳንድ ሰዎች አውናን የተቀሠፈው ዘሩን ከማሕፀን ውጭ በማፍሰሱ ሳይሆን ራስ ወዳድነት በተሞላው ክፉ ተግባሩ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህ

ግን ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ አውናን ዘሩን ከማሕፀን ውጭ በማፍሰሱ እርግዝና እንዳይፈጠር በፈጣሪ ሥራ ስለገባ እና ዘሩን ያለ ቦታው ስላፈሰሰ

ነው የተቀሠፈው፡፡ ወዳጆቼ አንድ ወንድ ከሚስቱ ጋር በሩካቤ ሥጋ ጊዜ ዘሩን ከማሕፀን ውጭ ቢያፈስ እና ሌላ ሰው ደግሞ ሚስቱን የእርግዝና

መድኃኒት ውሰጂ ብሎ ወይም ሚስቱ የእርግዝና መከላከያ ወስዳ በሩካቤ ሥጋ ጊዜ ግን ዘሩን በማሕፀንዋ ውስጥ ቢያፈስ ዘሩን ከማሕፀን ውጪ

ካፈሰሰው ሰው ጋር ልዩነቱ ምንድን ነው? መቼም ዘሩን ከማሕፀን ውጪ ያፈሰሰውን ኮንነን እንዲሁም ዘሩን የወሊድ መቆጣጠሪ በወሰደች

ሴት ማሕፀን ውስጥ ያፈሰሰውን ልክ ነው ልንል አንችልም፡፡ ዘሩን በማሕፀን ያፈሰሰውን ሰው ምናልባት ዘሩን በተገቢው ቦታ ማፍሰሱን ነው

የምናየው እንጂ ቀድሞ ዘሩ ልጅ እንዳይሆን የተጠቀሙትን የወሊድ መቆጣጠሪያ አናስብም፡፡ አውናን በራሱ የልምድ መንገድ እርግዝናን

ስለተከላከለ ተቀሠፈ፡፡ እኛ ደግሞ በሰው ሠራሽ ዘዴ እርግዝናን ብንከላከል ጥፋት አይደለምን?

ወዳጆቼ የትኛውንም የወሊድ መቆጣጠሪያ ስንጠቀም መድኃኒቱ የወንድና የሴቷን ዘር እንዳይዋሐድ፣ በማሕፀን ግድግዳ ላይ ጸንቶ

እንዳይቀመጥ እና እንዲመክን/እንዲፈርስ ያደርገዋል፤ ይህ ድርጊት ከአውናን በምን ይለያል? ይህን መሰል ድርጊት ፍትሐ ነገሥ

‹‹መጀመሪያው ግን ስለ ጋብቻ የሆነው መጀመሪያው ፈቃድ አስቀድመን እንዳስረዳን ዘርን ለመተካት ካልሆነ በቀር አይጸናምና፡፡ ዘርንና
የሚመስለውን ከማራቅ ጋራ እንግዲህ ሚስት ማግባት እርሱን የሚፈልጉት የማይገኝበት ትሆናለች፡፡ እንዲህ ከሆነ ለሚያገባ ሰው ሚስት

ማግባትን መተው ይገባዋል›› ይለናል፡፡ /ፍት.ነገ አንቀ 24÷927/ ይህ ማለት ዘሩን ከማሕፀን ውጪ እያፈሰሰ እና በሰው ሠራሽ መንገድ ልጅ

እንዳይወለድ የሚያደርግ ከሆነ ባያገባ ይሻላል ማለቱ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እኛ የሰው ልጆች ወደ ፊት እርግዝና መከላከያ እንደምንጠቀም አውቆ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ ላይ

‹‹ለተፈጥሯቸው ልጅ እንዳይገኝ እነሆ ይጥራሉ፡፡ ይሄስ ካሉት መታጣት ይከፋል፡፡ ይህም ክፋት ያሉት ይታጡ ዘንድ ነው፡፡ ይህም ዘርን አውጥቶ

በማይሆን ቦታ ስለማፍሰስ ይሆናል፡፡ ፅንስንም ስለ መከልከል ሥራይ በማድረግ ነው›› ብሎናል፡፡ ወዳጆቼ እዚህ ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ

‹‹ፅንስን ስለ መከላከል ሥራይ በማድረግ›› ብሎ የገለጠው አሁን ፅንስን ለመከላከል መድኃኒት ለምንውጥ እና መርፌ ለምንወጋ ሰዎች ቀድሞ

በመንፈስ ቅዱስ መገለጥ የጻፈልን ነው፡፡ ‹‹ሥራይ›› የሚለውን ቃል የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ›› ‹‹የሚዋጥ

መድኃኒት፣ የሚላመጥ፣ የሚጠጣ፣ የሚቀባ›› በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ስለዚህ ፅንስን ለመከላከል ሥራይ ወይም መድኃኒት መውሰድ/መዋጥ

የሚገባ እንዳልሆነ ነው፡፡

ተወዳጆች ሆይ እዚህ ላይ ልብ ልትሉት እና በአግባቡ ልትጠቀሙበት የሚገባው፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሠራችልን አጽዋማት እና

በዓላት ካወቅንባቸው በራሳቸው የወሊድ መከላከያም ናቸው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት እና በበዓላት ወራት እና ቀናት ከሩካቤ ሥጋ

የምንታቀብባቸው ስለሆኑ በትክክል ከተጠቀምንባቸው ልጆችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባሰብነው መልኩ እንወልዳለን፡፡ ችግሩ ግን

አጽዋማትንና በዓላትን እየሻርን ሩካቤ ሥጋ ስለምንፈጽም ልጅን በአናት በአናቱ ልንወልድ እንችላለን፡፡ አስኪ አስቡት የእርግዝና ወራት፣ ሰባቱ

አጽዋማት፣ የአራስነት ወራት፣ ዓርብ ረቡዕ፣ እሑድ ቅዳሜ፣ የሴቶች የወር አበባ ቀናት፤ እነዚህ ከታቀብንባቸው እና በፈቃድ ቀናት ሩካቤ ሥጋ

ብንፈጽም ‹‹ያለ ዕቅድ እና ድንገተኛ እርግዝና›› እያልን ከምንሳቀቀው ሰቆቃ ነፃ እንሆናለን፡፡

በዚህ መሃል መታወቅ ያለበት ሴት ልጅ ለመፅነስ እንቁላሎችዋ ዝግጁ የሚሆኑት ከወር አበባ ቀጥሎ ሦስት አራት ቀናትን አሳልፎ ያሉትን

ሳምንታት እና የወር አበባ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ ያሉት ሳምንታት ውስጥ ነው፡፡ እነርሱን ቀናት በሩካቤ ሥጋ ጊዜያችን ላናገኛቸው

እንችላለን፡፡ አጋጣሚው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንዳሰባችሁት ማለትም ‹‹አራርቆ፣ አቅምን አውቆ›› ለመውለድ አጽዋማቱ እና

በዓላቱ ቀናቱ ያግዟችኋል፡፡ መቼም በኑሮ ውድነት በቤት ኪራይ እሳትነት እየተለበለቡ ለሚኖሩት ቀላል ባይሆንም፡፡ ሌላው በጸሎት የታገዘ

እምነት ካለን የኑሮ አቅማችንን፣ የሥራ እና የገቢ ሁኔታችንን እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ልጅ ከወለድን በኋላ ቆይተን መውለድ ከፈለግን

የለመኑትን የማይነሳ ልዑል እግዚአብሔርን፣ ወለላይቱ እመቤት ድንግል ማርያምን ፅንስ እንዳይፈጠር መለመን እንችላለን፡፡ ጌታችን በቅዱስ

ወንጌል ላይ ‹‹ለሚያምን ሁሉ ይቻላል›› ያለው እንደዚህ ጽኑ እምነት ለሚጠይቅም ነገር ነውና፡፡ /ማር 9÷23/

ብዙዎች የወሊድ መከላከያን የሚጠቀሙት በአራት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ከኑሮ አቅም ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ይህም እኛ ያየነውን ችግር

ልጆቻችን አይተው ማደግ የለባቸውም በሚል እሳቤ ገና ላልተወለዱት ልጆች በማሰብ ነው፡፡ ሁለተኛው ልጅን አራርቆ ወልዶ ከማሳደግ አንጻር

ነው፡፡ በዚህ የልጆቻችን አሳዳጊ እኛ እንጂ እግዚአብሔር እንዳልሆነ የምናስብበት ነው፡፡ ሦስተኛው ልጅን ልክ እንደ እህል በቃኝ ከማለት ነው፡፡

አራተኛ ከማሕፀን ጋር በተያያዘ ሕመም እና ችግር ነው፡፡ አንዳንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያን ይጠቀሙና ልክ ልጅ መውለድ ሲፈልጉ በባንክ

እንዳስቀመጡት ገንዘብ አውጥተው የሚወስዱት ይመስል ልጅ መውለድ ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ በፈለጉት ጊዜ ልጅ መውለድ ሲያስቡ ልጅ እንቢ

ሊላቸው ይችላል፡፡ ልጆች ማለት ደግሞ መውለድ ሳንፈልግ የማንወልዳቸው፤ መውለድ ስንፈልግ የምንወልዳቸው አይደሉም፡፡ ልጆች በእቅድ

ሳይሆን በፈጣሪ ፈቃድ የሚወለዱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መዝሙረኛው ዳዊት ‹‹መካኒቱን በቤት የሚያኖራት፣ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት

የሚያደርጋት›› ያለው፡፡ /መዝ 113÷9/ እግዚአብሔር ሰዎችን ደስ ከሚያሰኝባቸው ሰማያዊ ስጦታዎቹ አንዱ ልጆች ናቸው፡፡

ከላይ የቤተ ክርስቲያናችንን መጻሕፍት አብነት አድርገን የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም እንደሌለብን አይተናል፡፡ እስኪ በርእሳችን የሰዎችን

ወቅታዊ ችግር ባገናዘበ መልኩ እንመልከት፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት አርግዛ በምጥ መውለድ ላትችልና በቀዶ ጥገና ልትወለድ ትችላለች፡፡ ይህቺ

ሴት በቀዶ ጥገና ከወለደች ዳግም ልጅ ልውለድ ብትል ቢያንስ ከአንድ ዓመት በላይ እስከ ሁለት ዓመት መቆየት አለባት፡፡ ይህም የሆነው በቀዶ

ጥገና ወቅት ሦስት የቆዳ ደረጃዋ ተቀዶ ነው ልጁ ከማሕፀንዋ እንዲወጣ የሚደረገው፡፡ በዚህ ቀዶ ሕክምና አገግማ ለመውለድ ሦስቱ

የማሕፀን የቆዳ ደረጃዎች በአግባቡ መዳንና መጠገን አለባቸው፡፡ ብዙዎች በቀዶ ጥገና ወልደው ስፌታቸው ኢንፌክሽን ይፈጥርና

ማሕፀናቸውና ስፌቱ በከፍተኛ ደረጃ ይቆስልባቸዋል፡፡ በዚህም ለማገገም እና ለመዳን ወራቶች ይፈጅባቸዋል፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ችግር
ከገጠማት ሴት ጋር በትዳር የሚኖረው ባል ስለ እውነት ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ከሩካቤ ሥጋ ርቆ ነው የሚኖረው ወይስ በችግር

ምክንያት የወሊድ መቆጣጠሪያ እየተጠቀሙ ነው? እንደዚህ ያለ ትልቅ ችግር ያለባት ሴት ንስሐ አባቷን ማማከር እና የንስሐ አባቷን

መፍትሔ ልትጠቀም ይገባታል፡፡ ምክንያቱም ነገ በቆሰለው፣ ባልጠገገው፣ በአግባቡ ባልዳነው ማሕፀንዋ ልጅ ብታረግዝ ለከፋና እስከ ሞት

የሚያደርስ ችግር ውስጥ ልትገባ ትችላለች፡፡

እዚህ ጋር አንድ የማውቃት ልጅ የገጠማትን ላንሳላችሁ፡፡ ልጅቷ በተፈጥሮ የማሕፀን ጥበት ስለነበረባት በቀዶ ጥገና በስንት ስእለት እና ጸሎት

ወለደች፡፡ በወለደች በስድስት ወሯ አረገዘች፡፡ ሁለተኛው እርግዝና እጅጉን ከባድ የሆነና በሕመም እና በሥቃይ የታጀበ ነበር፡፡ የመውለጃዋ

ወራት ሲቃረብ በድንገት ደም ይፈሳት ጀመር፡፡ ሆስፒታል ሄዳ ስትታይ በአፋጣኝ የማዋለጃ ክፍል ትገባለች፡፡ በሆነው ነገር ሐኪሞቹ እጅጉን

ተደናገጡ፡፡ ለካ ደሙ የሚፈሰው ቀድሞ ቀዶ ጥገና የተደረገለት ማሕፀን፣ አሁን በተፈጠረው ፅንስ ምክንያት ስፌቱ ወደ መፈታት ደርሶ ነው፡፡

ብቻ በብዙ ሥቃይ ወለደች፡፡ ወዳጆቼ እንደዚህ ያሉት እኅቶቻችን ችግራቸውን ከመጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ካሉበት እና ከገጠማቸው ችግር

አንጻር የንስሐ አባቶቻቸውም መፍትሔ እጅጉን ወሳኝ ነው፡፡

ስለ ወሊድ መቆጣጠሪያ ስናነሳ ተጠቃሚዎቹ ሴቶች ስለሆኑ እንጂ ወንዶችም የወሊድ መቆጣጠሪያ በመጠቀም ይታወቃሉ፡፡ አሁን ባለው

ተጨባጭ ሁኔታ ወንዶች በሁለት መልኩ ነው የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙት፡፡ አንደኛው ኮንዶም ሲሆን ሁለተኛው በእኛ ሀገር

እምብዛም ያልተለመደው የዘር ቱቦን ማስቋጠር ነው፡፡ ሳይንቲስቶች እንደ ሴቶቹ ለወንዶች በኪኒን መልክ የወሊድ መቆጣጠሪያ ለመፈብረክ

ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመን አልፏቸዋል፡፡ ቢሳካላቸው በወንዶችም በሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ አሁን ያለውን ከሰባት

ቢሊዮን በላይ የዓለማችን ሕዝብ ወደ አምስት ቢሊዮን ለመቀነስ ነው እየሠሩ ያሉት፡፡ ወዳጆቼ ነገ ምን እንደሚመጣ እና ምን እንደምንሰማ

ስለማይታወቅ ማወቅ እና መጠንቀቅ አይከፋም፡፡ የወሊድ መቆጣጠሪያ ምዕራባውያን ለእኛ አስበው ሳይሆን የዓለምን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ

የሚጠቀሙበት አንዱ ዘዴ ነው፡፡ በፊት እነርሱም፣ በተዘዋዋሪ በሦስተኛ ወገን የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት እያባሉን እያጋደሉን ሞተን

ሞተን አልቀንስ አላልቅ አልናቸው፡፡ አሁን ግን በድምጽ አልባ መሣሪያ፣ እኛን የሚጠቅም በሚመስል ግን በብዙ ነገር በሚጎዳን መንገድ በስውር

እየተዋጉን ነው፡፡

ስለ እውነት ከሆነ እኛ ኦርቶዶክሶች ገና አልወለድንም፣ አልበዛንም፡፡ የቀድሞ እናት አባቶቻችን በዛ አድርገው በወለዱት ነው አሁን ያለው

የኦርቶዶክሳውያን ቁጥር የሚሰላው፡፡ በሚያስደነግጥ ሁኔታ አሕዛብ ወደ አርባ ሚሊዮን ተጠግተዋል፡፡ በሕዝብ ብዛት በቅርብ ርቀት

እየተከተሉን ነው፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት በ 2007 ዓ.ም በሀገራችን የእምነት ተቋማት ያላቸውን የአማኞች ብዛት በተደረገው ጥናት እኛ
ኦርቶዶክሶች 43.5%፣ ሙስሊሞች 33.9%፣ ፕሮቴስታንት 18.6% /ሁሉንም አካቶ/፣ ባሕላዊ እምነት 2.6%፣ ካቶሊክ 0.7%፣
ሌሎች 0.7% እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ትንሽ በእኛ በኦርቶዶክሳውያን ላይ ያለው የቁጥር ማሻቀብ እንዳለ ሆኖ፡፡ ወዳጆቼ ከላይ ያለውን ወደ

ቁጥር ስንቀይረው የዛሬ አምስት ዓመት አርባ አምስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ገደማ ናችሁ ተብለናል፡፡ አሕዛብ ደግሞ ወደ አርባ ሚሊዮን

እንደተጠጉ ተነግሮናል፡፡ ጥናቱ ከተካሄደ ከአምስት ዓመት በኋላ እኛ ምን ያህል እንደሆንን በትክክል ባይታወቅም አሕዛብ ዱካችንን ሳይሆን

እግራችን ይዘው እየተከተሉን እንደሆነ እሙን ነው፡፡ አሕዛብ ልጆችን አብዝቶ በመውለድ እቅዳቸው ኢትዮጵያን የአሕዛብ ሀገር ለማድረግ

እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህ እቅዳቸው ይሳካላቸው ዘንድ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ተበጅቶላቸው ሁለት ሦስት በማግባት እንዲሁም

ኦርቶዶክሳውያንን በገንዘብ እያማለሉ በማግባት በመውለድ ተጠምደዋል፡፡ እኛ ግን አንወልድም ብለን የሚዋጥ፣ የሚቀበር እና በመርፌ

የሚሰጠውን እንደ ሁኔታችን ወሊድን ለመከላከል እንጠቀማለን፡፡ እዚህ ላይ አንድ እውነታ አለ፡፡ እርሱም አብዛኞቹ በተክሊል እና በቅዱስ

ቁርባን የተጋቡት ምንም እንኳን መከላከያን መጠቀም የሚፈቀድ ባይሆንም እነርሱ ግን ይጠቀማሉ፡፡ የዚህ አንዱ ማሳያ አራርቀው

መውለዳቸው ነው፡፡

እኛ ግን በወሊድ መቆጣጠሪያ ተይዘን ልጅ ከመውለድ ተወስነን እንገኛለን፡፡ ወዳጆቼ እየሠራ ለሚወልድ ሰው የልጆቹ አሳዳጊ እግዚአብሔር

ነው፡፡ ነገር ግን እጁን አጣምሮ ተቀምጦ ከሥራ ዓለም ርቆ፣ እግዚአብሔር ያሳድግልኛል በማለት እየወለደ ለሚኖር ሰው ፈተና ሊሆንበት

ይችላል፡፡ እባካችሁ በተለይ አቅም ያላችሁ፣ ልጅ ወልዳችሁ ማሳደግ ያልከበዳችሁ ኦርቶዶክሳውያን ውለዱ ውለዱ….. ምክንያቱም አሁን

ቁጥራችን እያነሰ፣ ፈተናችን እየተግበሰበሰ ባለበት ሁኔታ ስለ እውነት እላችኋለሁ ለእግዚአብሔር የገንዘብ አሥራት ከምትሰጡ ወልዳችሁ

የልጅ አሥራት ብትሰጡ ትጸድቃላችሁ፡፡ በተለይ ሥርዓት ባለው እና ሕጉን በጠበቀ መልኩ ሩካቤ ሥጋ ፈጽማችሁ የምትወልዷቸው ልጆች
የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃዎች ናቸው፡፡ የቅርቦቹ ሉተራውያን እንደ እኛ ተዋልደው ሳይሆን ከእኛ ኮብልለው ነው አሥራ ዘጠኝ ሚሊዮን

ለመሆን የበቁት፡፡

የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የልጆችዋ ሕልውና በእኛ በመውለድ እና ባለመውለድ ላይ የተንተራሰ ነው፡፡ ለምሳሌ ብናይ በገጠር የአብነት ትምህርት

ቤቶች በተለያየ ችግር በመዘጋታቸው፣ ወላጆች ልጆቻውን ከመንፈሳዊ ይልቅ ዓለማዊ ትምህርት እንዲማሩ በማድረጋቸው ወደፊት ተተኪ

ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን እናጣለን፡፡ ወደ ፊት በቅዱስ ያሬድ እግር የሚተኩ ማሕሌታውያን እየቀነሱ ይሄዳሉ፡፡ በእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

እግር የሚተኩ የመጻሕፍት ሊቃውንት እየጠፉ ይመጣሉ፡፡ ይህ በቀትታ የሚጎዳው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን እና ሃይማኖታችንን ነው፡፡

እውነተኛውንና ቀጥተኛውን ሃይማኖትና እምነት ይዘን ከመውለድ መቆጠብ የለብንም፡፡ ከምዕራባውያን ስሕተት ልንማር ይገባል፡፡

ወዳጆቼ ልጆች የራሳቸው የሆነ ከእግዚአብሔር የሚሰጣቸው ሰማያዊ ዕድል አላቸው፡፡ የተባረኩ ልጆች የእኛን ችግር የሚያበዙ ሳይሆን

የሚፈቱ ናቸው፡፡ እኛ በልጆቻችን ዕድል እንጠቀማለን እንጂ እነርሱ በእኛ አይጠቀሙም፡፡ ምናልባት ለማሳደጉ ነው ዋጋ የምንከፍለው፡፡ ልጆች

በእኛ በኩል መጡ እንጂ የእኛ አይደሉም ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ስለሆነ እንውለድ እንውለድ ……..፡፡ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ

ናቸው፡፡ መዝ 127፣2-5

‹‹ትዳርና ሕገ ሩካቤ ችግሩ እና መፍትሔው›› ከሚለው በቅርቡ ከታተመው መጽሐፌ የተወሰደ፡፡


ሚያዝያ 20/8/12 ዓ.ም

አዲስ አበባ

You might also like