You are on page 1of 2

መስቀል️⤵️

የመስቀል ትርጉም፦ መስቀል ማለት በመንፈሳዊ (ግብራዊ) ትርጉሙ ፦ መከራ ማለት ሲሆን አካላዊ /ፊደላዊ
ትርጉሙ ደግሞ የተመሳቀለ ተ ን የሚመስል ማለት ነው ።

መስቀል ቅድመ ክርስትና፦ መስቀል በስቅለት ተቀጥተው ከሚሞቱ ወንጀለኞች ታሪክ ጋር የተያያዘ ታሪክ
ነበረው ። መስቀል ቅድመ ክርስቶስ በምድረ አሕዛብ የታወቀ የክፉዎች መስቀያ ፣ መከራ ስቃይ እንዲበዛበት ፣
ውርደት እንዲሰፍንበት የፈለጉትን ሰው በሞት መቅጣት አልበቃቸው ፣ ትኩሳታቸውን አላበርድላቸው ስላለ
ሞቱ አይበቃም እና የስቃይ ሞት ይሙት ብለው የፈረዱበት ሰው አሰቃይቶ በውርደት ሞት ለመግደል
ሮማውያን እና ሌሎች መሰል አሕዛብ ለፍርድ መሣሪያነት ይጠቀሙበት ነበር ። መምለክያነ ጣዖት የሆኑት
የአሕዛብ የምድር አምላክ እንዳይቆጣ ፣ የክፉ ሰው ደም እንዳይነካው ብለው በመስቀል ላይ ይቀጡ ነበር ይባላል
። ለነሱ ስለ መሰላቸው ነው እንጂ ያ ሰው የሚቀበረው ከተፈጠረበት ምድር ላይ በመሆኑ ክፉውንም
ያስተማረው ሰይጣን በመሆኑ በሞቱ አብረው ነው የሚኖሩት ። አይሁድም ከአሕዛብ ያን ባህል ወርሰው ሟቹን
ለማሰቃየት በመስቀል ሰቅለው ይገድሉት ነበር ። በሮማውያን ተገዝተው የአሕዛብን ሥርዐት ሥርዐታቸው
እስኪያደርጉ ድረስ ከመስቀል ይልቅ በድንጋይ ውግረት ይቀጡ ነበር ። ዘዳ 21 ፥ 21-23 ፤ ኢያ 10 ፥ 26 ። የሐዋ
7 ፥ 58 ።

የመስቀል ሞት የውርደት ሞት ነው ። ክርስቶስ እኛን ያከብር ዘንድ በመስቀል ሞተ ። ፊል 2 ፥ 8 ፤ ዕብ 12 ፥ 1-


2።

የኃፍረት ሞት ነው ። ክርስቶስ የዓለምን ኃፍረት ይጋርድ ፣ የተዋረዱትንም ያከብር ዘንድ ስለ መጣ በመስቀል


ላይ ሞተ ። በመስቀል ተሰቅሎ የሚሞት የተረገመ ነበር ። ገላ ፥ 3-13 ።

ክርስቶስ ግን መርገመ ሥጋችንን እና መርገመ ነፍሳችንን ይሽር ዘንድ በመስቀል ላይ ሞተ ። ክርስቶስ


በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ሞትን ገድሎ ፣ ጥልን ገድሎ ለሰው ልጆች ሕይወትን አድሎ በትንሣኤው ብርሃን
በመገለጡ መስቀል የድል ፣ የሕይወት ፣ የክብር ፣ የነጻነት ፣ የአሸናፊነት ግርማ ሆነ ።

ሰዎች ክርስቶስን ወንጀለኛ ነው ለማለት በአደባባይ ከወንጀለኞች መካከል ሰቀሉት ። እርሱም መጽሐፍ
“ተኈለቈ ምስለ ጊጉያን” «ከበደለኞች ጋር ተቈጠረ» ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ በመስቀል ከነፍሰ ገዳዮች ጋር
ተሰቀለ ። ነገር ግን የሰው ልጆች በሱ (በእርሱ) ከወንበዴዎች መካከል መሰቀል ከማኅበረ አጋንንት ወጡ ።
ከማኅበረ መላእክትም ተጨመሩ ። በመሆኑም የመስቀሉ ቃል የሕይወት መልእክት ሆነ ። 1 ቆሮ 1 ፥ 17-25 ፤
ቈላ 1 ፥ 19-20 ።

የጥል ግድግዳ የወደቀበት የዕርቅ መሣሪያ ሆነ ። ኤፌ 2 ፥ 14-16 ።

መስቀል ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ፦ የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት መስቀል የእግዚአብሔር ኃይል ይገለጥበት
ጀመር ። ዕውራን መስቀሉን ሲዳስሱ ዐይናቸው በራ ። ሙታን በመስቀሉ ኃይል ሕይወት አገኙ ። በዚህ ጊዜ
የመሲሕ ገዳዮች ጻድቁን እንደ ገደሉ እንዳይ ታወቀባቸው በመስቀሉ የሚደረጉትን ተአምራቶች እንደ ጦር
ፈሩአቸው ። በመሆኑም ስሙን የሚጠሩትን ፣ በስሙ የሚሰብኩትን ፣ በስሙ ኃይል የሚያደርጉትን ሐዋርያት
እና ቤተ ክርስቲያን በእስራት እና በሞት ከፊታቸው እንዲወገዱ ጥረት ሲያደርጉ መስቀሉንም በስውር ቦታ
ጣሉት ። በተቻላቸው መጠን የገደሉትን መሢህ በክብር እንዳይገለጥ ጥረት አደረጉ ። ነገር ግን የክርስቶስ ክብር
ዕፀ መስቀሉም ቢቀበር አብሮ የማይቀበር ፣ ሐዋርያት ቢታሰሩ አብሮ በእስር ቤት የማይወሰን ፣ ቅድስት ቤተ
ክርስቲያንም በሰይፍ ብትመታ ስለት የማይዳፈረው መለኮታዊ ኃይል በመሆኑ ወንጌል እየሰፋ የመሢሕ
ምስክሮች ቍጥር እየጨመረ ሄደ ። በመስቀሉ ላይም የወሰዱት እርምጃ ለተወሰነ ጊዜ ሠምሮላቸው ነበር ።
ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ዕፀ መስቀሉ ከቤተ ክርስቲያን ፊት ተወስዶ ነበር ። ነገር ግነ የተሰቀለው ክርስቶስ
ሁል ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ፊት ነበር ። በኋላ ታሪክ እንደሚነግረን በንግሥት እሌኒ ጥረት የተጣለው መስቀል
ተነሣ ፣ የተሰወረው መስቀል ተገለጠ ፣ የጠፋው የድል አርማ መስቀል መጋቢት አሥር ቀን ተገኘ ። በቤተ
ክርስቲያንም በኢየሩሳሌም አሳንጻ በዚያ አስቀመጠችው ። መጋቢት 10 ቀን ዓቢይ ጾም ላይ ስለሚውል ክብረ
በዓሉ በቅዳሴ ቤቱ መስከረም 17 እን እንዲሆን ተወሰነ ። ስለዚህ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ስለኛ
የተሰቀለበት መስቀሉን መገኘት ምክንያት በማድረግ በመስቀሉ የፍርድ ጨለማውን እንዳራቀ ሁሉ በአዲስ
ዓመት ክረምቱ አልፎ የፀሐይ ዘመን በወሚመጣበት በመስከረም «መስቀሉን አበራ ፣ ሰማይንም በከዋክብት
አስጌጠ ፣ ከሁሉ ይልቅ ፀሐይን አሳየ (እንዲወጣ አደረገ) እያለች በቋንቋዋ = መስቀል አብርሃ በከዋክብት
አሰርገወ ሰማየ እም ኩሉሰ ፀሐየ አርአየ” እያለች ታከብረዋለች።

በንግሥት እሌኒ አድሮ መካነ መስቀሉን የገለጠውን ፣ መስቀሉን የኃይል ምንጭ ያደረገውን ፣ ለኛም ዘመኑን
ለውጦ ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋግሮ ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ የጠራ ሰማይ የተዋበች ፀሐይን እንድናይ
ያደረገውን አምላክ ቤተ ክርስቲያን ታከብራለች ። በመሆኑም በዚህ ዕለት የመስቀሉን መገኘት ምክንያት
በማድረግ ታላቅ በዓል እናደርጋልን ።

ዕፀ መስቀሉ በኢትዮጵያ

በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ማርያም መቀመጡን ታሪክ
ይመሰክራል ። በመሆኑም መስከረም 21 ቀን ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ግሸን ማርያም በመሄድ የመስቀሉን በዐል
በታላቅ ሥነ-በዓል ያከብራሉ ። ይህም ለሁላችን የታደለ ታላቅ በረከት በመሆኑ ደስ ሊለን ይገባል ።

You might also like