You are on page 1of 16

አንቀፅ

አንቀፅ ማለት አንድ ነጠላ ሀሳብን ለመግለፅ ሲባል በቁጥር አንድ ወይም ከአንድ የበለጡና የሀሳብ
ተዛምዷቸውን የጠበቁ ዓ.ነገሮች የሰፈሩበት የድርሰት ቅርፅ ነው፡፡ አንቀፅ ብዙውን ጊዜ አንድ ሀይለቃል
(መንደርደሪያ ዓ.ነገር) እና ከአንድ በላይ መዘርዝር ዓ.ነገሮችን ሊይዝ ይችላል፡፡

የአንቀፅ ቅርፆች /መልኮች/

የአንቀፅ ቅርፅ /መልክ / ማለት ዓብዩን ሃሳብ ወይም ሀይለቃሉን የሚይዘው መንደርደሪያ ዓ.ነገር
በአንቀፅ ውስጥ የት የት እንደሚገኝ የሚወስን ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት የአንቀፁ ሀይለቃል ወይም
መንደርደሪያ ዓ.ነገር ስፍራ አራት ቦታዎች ላይ ይገኛል፡፡ በሀይለ ቃሉ አንፃር ሌሎችን ዓ.ነገሮች ዝርዘር
ዓ.ነገሮች እንላቸዋለን ፡፡ ስለሆነም በሀይቃሉ የሚጀምር አንቀፅ ዝርዘር ይከተላቸዋል፡፡ ባጠቃላይ አንደ
አንቀፁ ሀይለቃል መገኛ ቦታ የዝርዝር ዓ.ነገሮች መገኛ ይወሰናል ማለት ነው፡፡

ሀ. ሀይለቃል በአንቀፅ መጀመሪያ ላይ ሲገኝ፡-ይህ ማለት የአንቀፁ ቅርፅ ከሰፊው ሀሳብ ወደ ጠባቡ
ወይም ወደ ዝርዝሩ ሀሳብ አቅጣጫ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ቅርፁም፡-

ሐይለቃል

ዝርዝር ዓ.ነገር

ምሰሌ፡- ሶፊያ አና ፅጌ መንታዎች ናቸው፡፡ እናታቸው ብርሀነ በተወለደች በአስራ ሶስት ዓመቷ
አግብታ በአስራስድስት ኣመቷ እነሱን ወለደች ፡፡ መንትዮዎቹ ከተወለዱ በኋላ አራት ቀን ብቻ ቆይታ
ሞተች፡፡ አባታቸው ተድላ የሚስቱ እሬሳ ሲወጣ አብሮ እንደወጣ የደረሰበት አልታወቀም፡፡ ስለዚህ
ሶፊያን ደብረሊባኖስ ገዳም መንኩሰው የሚኖሩ እማሆይ ጥሩነሽ የሚባሉ የእናቷ ታላቅ እህት ወስደው
ያሳድጓት ጀመር፡፡ በዚህ አንቀፅ ውስጥ ሀይለቃሉ በመጀመርያ ላይ ይገኛል፡፡ ሌሎቹ ሀይለቃሉን
የሚዘረዝሩ ዘርዛሪ ሀሳቦች ናቸው፡፡

ለ.ሀይ ለቃል በአንቀፅ መጨረሻያ ላይ ሲገኝ

ይህ ማለት የአንቀፁ ቅርፅ ከጠባቡ ሀሳብ ወደ ሰፊው ሀሳብ አቅጣጫ ይሄዳል ማለት ነው፡፡
ምሳሌ፡- እስክንድር እራሱን አከከ፡፡ ሰው ሰራሽ ጥርሱንም ወደውስጥ ገፋ አደረገ፡፡ ከሲራክ ባሻገር
መስኮቱን ዘልቆ ሩቅ ተመለከተ፡፡ አይኑ ከአድማስ ጋር ተጋጨ፡፡ የነበረው ተሰጦ እንደጉም በኖ ሲጠፋ
ታየው፡፡ አንድ ወይም ገፍ ቢል ሁለት ወር ስሙን የያዘው መፅሀፍ ታትሞ ሰው እጅ ገብቶ ሲነበብ
ለማየት የነበረው ተስፋ ይታየው የነበረው ጣፋጭ ኅይልም በሲራክ ክፋት ምክንያት ድንገት መጥፎ
ቅዠት ሆኖ ሲቀር ደብዛ ሲጠፋ፣ ሲጨልም ….የገራ ስሜቱ ከስሎ አመድ ሲሆን ታየው፡፡ ህይወት
መራራ ሆነችበት ሲራክን ከልቡ ጠላው፡፡ ልቡንበጦር ቢወጋው ምንኛ ደስ ባለው ነበር፡፡ የተሰመረበት
የመጨረሻው ዓ.ነገር የአንቀፁ ሀይለቃል ነው፡፡ ቅርፁም፡-

ዝርዝር ዓ.ነገር

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 1


ሐይለ ቃል

ሐ.ሀይለ ቃል በአንቀፅ መጀመሪያና መጨረሻያ ላይ ሲገኝ

ምሳሌ፡- ዮፍታሄ ለሁለተኛ ጊዜ ኤሊያስን ላይመለስበት ጥሎ የወጣው በእናቱ ምክንያት መተፈጠረው


ሀሜት ነበር፡፡ ቄስ ገበዝ ንጉሴና ወይዘሮ ማዘንጊያ የተጋቡት ስርዓት ተክሊል ደርሶላቸው ስጋዎ ደሙ
ተቀብለው ነበር፡፡ ሞት ቢለያቸውም ህጋቸው እንደፀና ይኖራል እንጂ መፍረስ መደምሰስ የለበትም፡፡
በለዘበ በረቀቀ ሲያቃጥል ጠቅ ሲያድርግ በሚያንቦገቡግ ቅስም በሚሰብር ውቃቢ በሚገፍ ቅኔ ሳይሆን
አልቀረም፡፡ በቅኔ መሰደብ ቀላል አይደለም፡፡ በተለይም በጥበቡ ከያኒው ታሽቶ ላደገው ብሩህ ለሆነው
ለዮፍታዬ የማይዋጥ ነገር ሆነ፡፡ በእናት ምክንያት የተጀመረው ሀሜት በልጅ ስደት ተፈፀመ፡፡ በዚህ
አንቀፅ ውስጥ በመጀመሪና በመጨረሻ የመጣው ዓ.ነገር የአንቀፅ ሀይለቃል ነው፡፡ ቅርፅም፡-

ሐይለቃል

ዝርዝር ዓ.ነገር

ሐይለቃል

መ. ሀይለ ቃል በአንቀፅ መካከል ላይ ሲገኝ ፡-ይህ ማለት ከዝርዝር ሃሳብ ወደ ሰፊ እንደገና ከሰፊው
ሀሳብ ወደ ዝርዝር ዓ.ነገሮቹ ይሄዳሉ፡፡

ምሳሌ፡- ‹‹ፊታውራሪ መሸሻ ሳይሸመግሉ ከስው ጋር ተጣልተው ካልተከሰሱ እሳቸው ከሰው በዘመድ
ይሁን በአካል ዳኛ ፊት ቆመው አየኋቸው የሚል ሰው አልነበረም፡፡ብዙ ጊዜ ከሰው አይጣሉም፤
ከተጣሉም ግን አከሰዋለሁ ከማለት እፋለመዋለሁ ማለት ይቀናቸዋል፡፡ ለዳኛ አቤት ማለት ደካማነትን
ወይንም ፈሪነትን አምኖ እርዳታ መለመን ነው›› ይሉ ነበር፡፡ ተመቶ ወይም ተሰድቦ ካሱኝ ከሚል
መትቶ ወይም ሰድቦ ካሳ የሚክሰውን የሚያከብሩ መሆናቸውን በማንም ዘንድ የታወቀላቸው ነበሩ፡፡
አገረ ገዢ ሆነው በዳኝነት ወንበር ይቀመጡ በነበረ ጊዜ እንኳ ተመቶ ላቤቱታ የመጣባቸውን ‹‹እጅ
የለህም ወይ››ተሰድቦ የመጣባቸውን አይን የለህም ወይ›› ይላል፡፡

በዚህ አንቀፅ ውስጥ መሀል ላይ የተሰመረበት ዓ.ነገር የአንቅፁ ሀይለቃል ነው፡፡ ቅርፁም፡-

ዝርዝር ዓ.ነገር

ሐይለቃል

ዘርዝር ዓ.ነገር

አስተዋፅኦ/ ቢጋር/

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 2


አንድን ድርሰት መፃፍ ከመጀመራችን በፊት ሶስት ዋናዋና ተግባራትን እንከናውናለን፡፡ እነዚህም
ተግባራት፡-

1. ርእስ መምረጥ ርእስ መምረጥ፡- ለአንድ ፀሀፊ የመጀመሪያ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ፀሀፊው
በሚስበው መልኩ የተሰጠውን ርእስ ማደራጀት የፀሀፊው ተቀዳሚው ተግባር ነው፡፡
2. ርእስ ማጥበብ ወይም መወሰን፡- የሚፃፍበት ርእስ የሚፃፍበትን ዓላማ የሚያ ሟላ ወይም
ግብ የሚመታ መሆን አለበት ስለዚህ ልኩን ፣መጠኑን ወዘተ የሚመጥን መሆን ይኖርበታል፡፡
ምክንያቱም የሚፃፈው ድርሰት በጊዜ ፣ በቦታና በቃላት መጠን የሚወሰን በሆን አለበት፡፡
3. አስተዋፅኦ ወይም ቢጋር መንደፍ ፡- ቢጋር የሚለው ቃል ዋናውን ድርሰት በፅሁፍ ከማስፈር
በፊት አጠቃላይ የፅሁፉን አካሄድ የሚያሳየውን ዝርዝር እቅድ ወይም ንድፍ ይመለከታል
እንዲሁም ድርሰት ከመፃፉ በፊት የኀሳቡን ቅንጅት ለማየትና ለማስተካከል ፤ በተጨማሪም
መልእክትን ለማስተላለፍ ራሱን የቻለ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡ ይህ ከሆነ ድርሰቱ ከመፃፉ
በፊት በድርሰቱ ውስጥ መካተት ያለባቸውን ዋናዋና ፍሬ ነገሮች በቢጋር መልክ ማዘጋጀት
ለድረሰቱ ውጤታማነት አስፈላጊ ደረጃ ነው፡፡ ይህም የአስተዋፅኦ ወይም የቢጋር አነዳደፍ
የሚከተለውን ምስሌ መመልከት ይቻላል፡፡
ምሳሌ፡- ፀሀፊው ‹‹መስከረም ሲጠባ›› በሚል ርእስ ድርሰት ለመፃፍ አሰበና በቅድሚያ
የሚከተለውን አስተዋፅኦ ነደፈ፡፡
መስከረም ሲጠባ
1. አካባቢው አስደሳች ይሆናል
1.1 አበቦች ያብባሉ
1.2 የደፈረሱት ጅረቶች ይጠራሉ
1.3 በክረምት ተደብቀው የነበሩ አእዋፍ ብቅ ብቅ ይላሉ
1.4 ሰማዩ ይጠራል፤ ደመና ይወገዳል
2. ሰዎች መልካም ምኞታቸውን ይገልፃሉ፡፡
2.1. በዘፈን፣
2.2. ስጦታ በመለዋወጥ
2.3. እርስበርስ በመመራረቅና በመመሰጋገን
2.4. በአምልኮ ቦታዎች በመገኘትና ፈጣሪያቸውን በማመስገን፡፡

3. ተለያይተው የከረሙ ሰዎች ይገናኛሉ፡፡


3.1. ውሓ ሙላት ያለያያቸው ይገናኛሉ
3.2. በትምህርት ቤት መዘጋት የተለያዩ ተማሪዎች ይገናኛሉ፡፡
4. ሰዎች በአዲስ ዓመት አዲስ እቅድ ተልመው ለመተግበር ይዘጋጃሉ፡፡
4.1. ሰራተኛው የተሸለ ለመስራት ያቅዳል
4.2. ገበሬው የተሻለ ለመስራት ይዘጋጃል
4.3. ነጋዴው የተሻለ ለማትረፍ ያልማል
4.4. ተማሪው የተሸለ ውጤት ለማስመዝገብ ቃል ይገባል

ልቦለድ

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 3


ልቦለድ የገሀዱን አለም ተፈጥሮአዊና ማህበረሰባዊ እውነታ መሰረት አድርጎ ከደራሲ ምናባዊ የፈጠራ
ሐይል የሚመነጭ የስነፅሁፍ ስራ ነው፡፡ መነሻው እውናዊ ዓለም ይሁን እንጂ የሰው የእለት ተእለት
የኑሮ መልኮች በሚገኙበት ገሃዳዊ ሁናቴ ተወስደው እንደ ህይወት ታሪክ የሚዘግብበት ስራ ግን
አይደለም፡፡ የልቦለድ አለም የምናብ አለም ነው፡፡ የምናብ ዓለም በመሆኑም ይዞት የሚቀርበው ታሪክ
የገሀዱን ዓለም የሚመስል እንጂ እንዳለ የገሀዱ አለም እውነታ ባለመሆኑ እውነትነቱ በማስረጃ
ሊረጋገጥ የሚችልበት መንገድ ጨርሶ የለም፡፡

የልቦለድ አይነቶች

ሀ. ረጅም ልቦለድ፡- ረጅም ልቦለድ ስሙ እንደሚያመለክተው ረዘም ያለና በስድፅሁፍ የሚቀርብ


የፈጠራ ድርሰት ቅርፅ ነው፡፡ ረጅም በመሆኑ በሚያቀርበው ታሪክ ውስጥ በርካታ ገፀባህርያትን ማሳተፍ
ከመቻሉም በላይ የነዚህን ገፀባህርያት ህይወት ከልደት አስከ ሞት በሰፋትና በጥልቀት ለማሳየት በቂ
ቦታና ጊዜ አለው፡፡ በዚህ አይነቱ የፈጠራ ድርሰት ውስጥ በእውናዊ አለም ያሉ ሰዎችን
የሚያጋጥሟቸው ደሳታና ሀዘን ፍቅርና ጥላቻ ማግኘትና ማጣት ምኞታና ተሰፋ ባጠቃላይ የሰው ልጅ
እንቅስቃሴዎች ልዩ ልዩ አመለካከቶች ላዛ ባለው መንገድ እውን መስለው ይቀርባሉ፡፡

ለ. አጭር ልቦለድ ፡- አጭር ልቦለድ ስሙ እንደሚያመለክተው ቅርፁ አጭር የሆነ በስድ ፅሁፍ የሚቀርብ
የፈጠራ ድርሰት ነው፡፡ አጭር ልቦለድ ከ 10 ሺ ቃላት በታች የሚይዝ አንድ ዋንኛ ግብ ለማምጣት
የተዋቀረና ተውኔታዊነት የሚታይበት አጠር ያለ ትረካ ነው፡፡ አጭር ልቦለድ በአንድ ቅፅበት በአንድ
ነጠላ ሁነት ውስጥ የሚያልፍ አንድ ገፀባህሪ ላይ ያተኩራል፡፡ አጭር ልቦለድ በተወሰነ መቼት
የተቀረፁና አንድ ሁነት ወስጥ ገብተው በህሊናዊ ወይም በአካላው ድርጊት የሚሳተፉ አንድ ወይም
ጥቂት ገፀባህርያትን ይይዛል፡፡ ግጭት ወይም ተፃፃሪ ሀይላት ፍጭት የማንኛውም አጭር ልቦለድ
አምብርት ነው፡፡ በአጭር ልቦለድ ቅርፁ አጭር ከመሆኑ የተነሳ ጥድፊያ ፣ ነጠላ ውጤትና ቁጥብነት
ይታይበታል፡፡

የልቦለድ አላባዎች

በሁለቱም የልቦለድ አይነቶች ማለትም በአጭር ልቦለድ እና በረጅም ልቦለድ ውስጥ በመገኘት
ልቦለዶቹ ልቦለድ እንዲሆኑ የሚያደርጓቸው የልቦለድ አላባውያን ወይም ፍሬ ነገሮች በመባል
የሚታወቁት ታሪክ፣ ገፀባህሪ፣ መቼት፣ ግጭት፣ ትልም፣ አንፃር እና ጭብጥ ናቸው፡፡ እነዚህ
አላባውያን ምንነታቸውን ለማጥናት ሲባል ተለያይተው ይቅረቡ እንጂ በልቦለድ ውስጥ በተናጠል
የሚታዩ አይደሉም፡፡ ልቦለድ የሚኖረውም እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት አላባውያን ወይም ፍሬ ነገሮች
ተጣምረው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ እነዚህም የልቦለድ አላበውያን የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.ታሪክ ፡- ታሪክ የልቦለዱ መሰረት ነው፡፡ ልቦለዱን ከነበብን በኋላ ላላነበበ ሰው ስንገልፅ መጀመሪያ
እንደዚህ ሆነ ከዚያም እንደዚህ ሆነ ፣ በመጨረሻም እንደዚህ ሆነ ብለን የምንተርከው የልቦለድ ታሪክ
ይባላል፡፡ ታሪክ የጊዜ ቅደም ተከተልን መሰረት አድረገው በመቀናጀት የሚቀርቡትንና በገፀባህርያቱ
የሚፈፀሙ ድርጊቶችን ፣አነሳስ አካሄድና የመጨረሻ ውጤት የሚይዝ የልቦለድ ህይወት ወይም የመፃፉ
ሰበብና የህልውናው መሰረት ነው፡፡

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 4


2. ገፀባህሪ፡- ገፀባህሪ በገሀዱ ዓለም ያሉ ሰዎችን ወክለው በታሪኩ ወስጥ የሚንቀሳቀሱ በደራሲው
የተፈጠሩ የፈጠራ ሰዎች ናቸው፡፡ ‹‹በአንድ ልቦለድ ውስጥ ያለው ታሪክ የማን ነው›› ብልን
ስንጠይቅ ‹‹የአንነገሌ ታሪክ ነው›› የሚል መልስ እናገኛለን፡፡እነገሌ ተብለው የተጠቀሱት ደግሞ፤
በታሪኩ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ፤ ደራሲ የፈጠራቸው፤ የሚራቡ፣ የሚጠሙ፣ የሚያለቅሱ፣ የሚታረዙ፣
የሚደሰቱ ባጠቃላይ የገሀዱ ዓለም ሰዎች በምድር ላይ የሚሆኑትን ሁሉ የሚሆኑ የፈጠራ ሰዎቸ
ናቸው፡፡

3.ትልም/ሴራ/፡- በምክንያትና ውጤት የተሳሰሩ የሁነቶች ቅደም ተከተል ማለት ነው፡፡ ትልም የልቦለድ
ምሰሶ ነው፡፡ ልክ የሰውን ልጅ አጥንታቸው ደጋፏቸው አንደሚሄድ ሁሉ ትልምም ልቦለዱን
የሚደግፈው የጀርባ አጥንት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ትልም ዋንኛው ትኩረቱ ምክንያትና ውጤት ላይ
ነው፡፡ ምሳሌ ንጉሱ ሞተ፡፡ ከዚያም ንግሰቲቷ ሞተች ፡፡ ሲል ይህ ታሪክ ይሆናል፡፡ በንጉሱ ሞት
ምክንያት ንግስቲቷ ሞተች፡፡ ይህ ትልም ነው፡፡ ምክንያቱም ለሆነ ነገር መከሰት ምክንያት
ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ባጠቃላይ ትልም በሴራ የተሞላ ነው፡፡

4. ግጭት፡- በልቦለድ አለም የሚኖሩ ገፀባህርያት በታሪኩ ውስጥ በተፈጠረላቸው እርስ በርሳዊ ግንኙነት
የተነሳ በተለያዩ ምክንያቶች ቅራኔዎች ወይም አለመግባባቶች ሳቢያ የሚፈጠረው ፍጭት ወይም
ፈልሚያ ግጭት ይባላል፡፡ በሁለት ተፃራሪ ሀይላት መካከል በሚደረገው ትግል አንዱ ሌላውን ለማሸነፍ፣
አንዱ ሌላውን ለመጣል፣ሌላው ላለመሸነፍ ሲል፣ ላለመበለጥ ሲፍጨረጨር ይታያል፡፡ እግጭት ውስጥ
ሊገቡ የሚገባቸው ተፃራሪ ሀይላት ተመጣጣኝ ወይም አቻ መሆን አለባቸው ፤ ምክንያቱም
የሚሸነፈው ገና ከወዲሁ ከታወቀ ልብ ሰቀላ አይኖረውም፡፡ ግጭት መነሻ፣ እድገት፣ ልብ ሰቀላ፣
ርግበትና ልቅት ይኖረዋል፡፡ እነዚ የግጭት ደረጃዎች ወይም ባህርያቶች በመባል ይታወቃሉ፡፡

5. መቼት፡- የልቦለድ ገፀባህርያት እንደእውኑ አለም ሰዎች የመኖሪያ አካባቢ አላቸው፡፡ ይህም ቦታና
ጊዜን ይመለከታል፡፡ በልቦለድ አለማቸው የሚነቀሳቀሱና ታሪካቸውን የሚፈፅሙት ደራሲው በፈጠረው
የተወሰነ አካባቢ ሲሆን የሚኖሩበትና ታሪካቸውን የሚፈፅሙበት ታሪካዊ ጊዜ፣ ወቅት፣ እለትና ሰዓትም
ይኖራቸዋል፡፡ ይህ የገፀባርያቱ መገኛ ስፍራና ጊዜ ባንድነት መቼት ይባላል፡፡

6. ጭብጥ፡- ጭብጥ አንድ ልቦለድ ልያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ማለት ነው፡፡

7.አንፃር፡- ደራሲው የልቦለዱን ታሪክ የሚያቀርብበት የተራረክ አቅጣጫ ማለት ነው፡፡ አንፃር
የሚገልፀው ፅሁፉ ወይም ታሪኩ በየትኛው መደብ ቀርቧል የሚለውን ነው፡፡

ባጠቃላይ እነዚህ አላባዎች በረጅም ልቦለድ ውስጥ ረጅም፣ ሰፊና ብዙ ሲሆኑ በአጭር ልቦለድ ውስጥ
ደግሞ አጭር፣ ቁጥብና ጠባብ ናቸው፡፡

የቃል ክፍሎች

የአማርኛ የቃል ክፍሎች የንግግር ክፍሎች በመባል ይታወቃሉ፡፡ በዘመናዊ ምሁራን አመለካካት
የአማርኛ የቃል ክፍሎች በአምስት ይመደባሉ፡፡ እነሱም፡- ስም፣ ግስ ፣ቅፅል፣ መስተዋድድና ተውሳከ ግስ
ናቸው፡፡

1. ስም

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 5


ስም ፡- ስም ብለን የምንጠራቸው ብዙ ናቸው፡፡ መሳሌ፡- ሰው፣ እንሰሳት፣ ሙሀመድ፣ መፅፍ፣ አዲስ
አበባ፣ ዜና፣ ህልም፣ ጠረጴዛ ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡ ስሞች የተፅኦና የወል መጠሪያ በመባል በሁለት
ይመድባሉ፡፡ ስም በአረፍተ ነገር መዋቅር ውስጥ የሚከተሉት ባህርያት ይኖሩታል፡፡

ሀ. አብዢ ምእላድ ‹‹ኦችን›› ን የሚወስድ፡፡ ምሳሌ፡- ዶሮ/ ኦች-ዶሮች ፣ ሰው/ ኦች-ሰዎች፣


በሬ/ዎች--በሬዎች ወዘተ-

ለ. የዓ.ነገር ባለቤት በመሆን የሚያገለግል፡፡ ምሳሌ 1፡- ቶሎሳ ከብቶቹን አሰማራ፡፡ ባለቤት የሚለው ቃል
ቶሎሳ ነው፡፡

ሐ. የዓ.ነገር ተሳቢ በመሆን ያገለግላል፡፡ መሳሌ 1፡- ገመቹ ውሻውን መታው፡፡ ውሻውን የሚለው ቃል
ተሳቢ ነው፡፡

መ. አመልካች ወይም መጣኝ መጠንን የሚጠቁሙ ቃላትን የሚወስዱናቸው፡፡ ምሳሌ፡- እነዚያ ወወፎች፡፡
ምሳሌ 2. ሁለት ጠርሙስ ፣ አንድ ቤት ወዘተ… እነዚያ፣ ሁለት አና አንድ የሚሉት መጣኝ
መሰተዓምር ናቸው፡፡

ሰ. መጠንን፣ አይነትን፣ ባህሪን፣ የሚጠቁሙ ገላጮችን የሚወስዱ ናቸው፡፡

ምሳሌ፡- ጥሩ ሰው፣. ጥቁር በሬ፣ ረዥም ዛፍ ናቸው፡፡ የተሰመረባቸው ቃላት ገላጮች ናቸው፡፡
በቀድሞው ሰዋሰው ራሱን የቻለው ተውላጠ ስም በዚህ የቃል ክፍል ተካቷል፡፡

1. ቅፅል
ቅፅል የስም ገላጭ ከመሆን ተጨማሪ በጣም የሚል ቃል ጨምሮ የሚነገር ቃል ቅፅል ይባላል፡፡ ገላጭ
ወይም ቅፅል የምንለው ስምን ከተለያየ ባህርያት አንፃር ይገልፃል ፡፡ እሱም፡-
ሀ. ስምን ከመጠን እንፃር የሚገልፁ ቅፅሎች የሚባሉት፡- ረዥም ፣ ወፍራም፣ ቀጭን፣ አጭር ወዘተ
ናቸው፡፡ ምሳሌ አጭሩ ሰውዬ መጣ፡፡ የተሰመረበት ቃለ ቅፅል ነው፡፡
ለ.ስምን ከባህሪ አንፃር የሚገልፁ ቅፅሎች የሚባሉት፡-ብልህ፣ ደግ፣ የዋህ፣ ክፉ፣ አዋቂ ወዘተ ናቸው፡፡
ምሳሌ፡- ደጉ ልጅ መጣ፡፡ የተሰመረበት ቃል ቅፅል ነው፡፡

ሐ. ስምን ከመልክ አንፃር የሚገልፁ ቅፅሎች የሚባሉት፡- ቀይ፣ ቢጫ፣ ጥቁር፣ አረንጓዴ ወዘተ.. ምሳሌ፡-
ቀይ ክር እወዳለሁ፡፡ የተሰመረበት ቃል ቅፅል ነው፡፡

መ. ስምን ከሁኔታ አንፃር የሚገልጹ ቅፅሎች የሚባሉት ፡- ደጋማ፣ ቆላማ፣ አይናማ፣ ቡናማ፣ አሸዋማ፣
ገደላማ ወዘተ…. ምሳሌ. ገደላማ መሬት ነው፡፡ የተሰመረበት ቃል ቅፅል ነው፡፡

ሠ. ስምን ከቅርፅ አንፃር የሚገልፁ ቅፅሎች የሚባሉት ፡- ሞላላ፣ ክብ፣ ጠፍጣፋ፣ ሹል ወዘተ… ናቸው፡፡
ምሳሌ 1. ጠፍጣፋ ጠረጴዛ ምሳሌ 2. ሹል እንጨት የተሰመረባቸው ቅፅሎች ናቸው፡፡

ረ. ስምን ከወገን አንፃር የሚገልፁ ቅጥሎች፡- ኢትዮያዊ፣ ሱዳናዊ፣ ተርካዊ ወዘተ ናቸው፡፡

ምሳሌ 1. አሜሪካዊ ሰው ነው፡፡ ምሳሌ 2. ቱርካዊ ዜጋነው፡፡ የተሰመረባቸው ቅፅሎች ናቸው፡፡

3.ግስ

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 6


ግስ በዓ.ነገር መዋቅር ውስጥ መጨረሻ ላይ በመግባት ማሰሪያ አንቀፅ በመሆን ያገለግላል፡፡ ግስ አንድ
ዓ.ነገር መቋጨቱን ያሳያል፡፡ እሱም መጣ፣ ሄደ፣ በላ፣ ተኛ፣ ለበሰ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ የግስ አይነቶች
የተለያዩ ናቸው፡፡ እነሱም፡-
1 ተሸጋሪ ግስ፡- ይህ የግስ አይነት ድርጊቱ ከባለቤቱ አልፎ ወደ ሌላ አካል የሚሸጋገር ነው፡፡ እሱም
ሰበረ፣ አጠበች፣ ደበደበ ወዘተ
2. ኢ- ታሻጋሪ ግስ፡- ይህ የግስ አይነት ድርጊቱ በዛው በባለቤቱ ላይ የሚያልቅ ነው፡፡ እሱም፡-
አለቀሰ፣ ታመመ፣ ተኛች ወዘተ ናቸው፡፡
3. የመሆን ግስ ፡- የመሆን ግስ የምንለው ድርጊት ፈፃመው የሆነ ነገር መሄኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ተማሪ ነው ፣ ሀኪም ነው፣ ደግ ነው ወዘተ…
4. የመኖር ግስ ፡- ድርጊት ፈፃሚው የሆነ ቦታ መኖሩን የሚያሳይ ግስ ነው፡፡ እሱም፡- ቤት
ወስጥ ነው፣ ትምህርት ቤት አለ፡፡ ወዘተ ናቸው፡፡
ምሳሌ፡- ቶሎሳ ቤት ውስጥ አለ፡፡2. ገመቹ ላም አለው፡፡ የተሰመረበት ቃል ግስ ነው፡፡

4.ተውሳከ ግስ

ግስን የሚገልፅ ቃል ተውሳከ ግስ ተብሎ ይጠራል፡፡ በተውሳከ ግስ የቃል ክፍል ውስጥ ሊመደቡ
የሚችሉት ቃላት በቃላዊ ማንነታቸው እንጂ በሰዋሰዋዊ አገልግሎት መሆን የለበትም፡፡ ምስሌ 1.
ጫላ በሩጫ መጣ ፡፡ 2. ካሳ እሁድ ይመጣል፡፡ እነዚህ የተሰመረባቸው ቃላት በጥንታውያኑ የቃል
ክፍል አመዳደብ የተመደቡ ናቸው፡፡ በዘመናዊ የቃል ክፍል አመዳደብ ግን በቃላዊ ምንነታቸው ላይ
ብቻ የሚያተኩር መሆን አለበት፡፡ እነሱም፡- ቶሎ፣ ገና፣ ጅልኛ፣ ምንኛ፣ ክፉኛ ናቸው፡፡ ምሳሌ፡- ልጁ
ከፉኛ ታመመ፡፡ አስቴር ምንኛ ታሳዝናለች፡፡
5. መስተዋድድ

መስተዋድድ የሚከተሉትን ባህርያት ይገልፁታል፡፡ እነሱም፡-

-የራሳቸው የሆነ ፍቺ የሌላቸው

-በአእምሮ ውስጥ ምንም አይነት ምስል የማይከስቱ

-እንደሌሎቹ የቃል ክፍሎች ቃላትን የማይመሰርቱና የማይረቡ ናቸው፡፡ እነዚህም መስተዋድዶች


የሚባሉት፡ ከ፣ እንደ፣ ስለ፣ ወደ፣ ጋር፣ በ፣ ላይ ናቸው፡፡

ምሳሌ:- ካሳ ከወንድሙ ጋር መጣ፡፡ የተሰመረባቸው መሰተወድድ ናቸው፡፡

ሀረግ

ድምጾች በስርኣት ተቀናጅተው ቃላትን ፤ ቃላት ተቀናጅተው ደግሞ ሀረጋትን ይመሰርታሉ፡፡


በመሆኑም ለማንኛውም ሀረግ መሰረቱ ቃል ነው፡፡

የሀረግ አይነቶች

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 7


በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ የሀረጎች አይነት የሚወሰነው ለሀረጎች መሰረት ሆነው በሚገቡበት ቃላት
ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንዳየናቸው የቃላት ክፍሎች ሁሉ ሀረጎችም በአምስት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም፡- ስማዊ
ሀረግ፣ ቅፅላዊ ሀረግ፣ ግሳዊ ሀረግ፣ መስተዋድዳዊ ሀረግ እና ተውሳከ ግሳዊ ሀረግ ናቸው፡፡
1. ስማዊ ሀርግ፡- ይህ የሀረግ አይነት ከቃል የበለጠ፤ ከአረፍተ ነገር ያነሰ ሲሆን ስምን በመሪነት በመያዝ
ሌሎች አጅቢዎችን በመጨመር ሀረጉን ይመሰርታል፡፡ እነዚህ አጃቢዎች የሚባሉት ለሀረጉ ምሰረታ
የግድ አይደሉም ሊቀሩም ሊመጡምይችላሉ አይቀሬው አካል የሚባለው መሪው ቃል ስም ነው፡፡
ይህም መሪ የምንለው የሚገኘው በሀረጉ በስተቀኝ ነው፡፡
ምሳሌ 1፡- የትናንቱ ጫማ ምሳሌ 2፡- የጭቃው ቤት ምሳሌ 3፡- የገብስ ጠላ
የተሰመረባቸው ቃላት ሁሉ መሪ ስም ሲሆኑ ሌሎቹ አጃቢዎች ይባላሉ፡፡
2. ቅፅላዊ ሀረግ፡- የሀረግ አይነት ከቃል የበለጠ፤ ከአረፍተ ነገር ያነሰ ሲሆን ቅፅልን በመሪነት በመያዝ
ከሌሎች አጃቢዎች ጋር በመሆን ሀረጋቸውን ይመሰርታሉ፡፡ የዚህ ሀረግ መሪ በስተቀኝ ይገኛል፡፡
ለሀረጉ አይቀሬው አካል መሪው ቅፅል ሲሆን ሌሎቹ አጃቢዎች ሊቀሩም ይችላሉ፡፡
ምሳሌ 1፡- የሰው ክፉ ምሳሌ 2፡- የሴት ደግ ምሰሌ 3፡- የልጅ አዋቂ
የተሰመረባቸው ቃላት መሪ ቅፅል ናቸው ፡፡ ሌሎቹ ሀረጉን ሊያጅቡ የመጡ አጃቢዎች
ናቸው፡፡
3. ግሳዊ ሀረግ፡- የሀረግ አይነት ከቃል የበለጠ፤ ከአረፍተ ነገር ያነሰ ሲሆን ግስን በመሪነት በመያዝ
ከሌሎች አጃቢዎች ጋር በመሆን ሀረጋቸውን ይመሰርታሉ፡፡ የዚህ ሀረግ መሪ በስተቀኝ ይገኛል፡፡
ለሀረጉ አይቀሬው አካል መሪው ግስ ሲሆን ሌሎቹ አጃቢዎች ሊቀሩም ይችላሉ፡፡ የግሰዊ ሀረግ
አመሰራረት አንደየግሶቹ አይነት የተለያየ ነው፡፡ ይኸውም የግሰ አይነቶች የምንላቸው ተሻጋሪ ግስ፣
ኢ- ተሸጋሪ ግስ የመሆን ግስ እና የመኖር ግስ የምንላቸው ናቸው፡፡
ምሰሌ 1፡- እንጨት ሰበረ ምሰሌ 2፡- ክፉኛ ታመመ፡፡ ምሳሌ 3፡- መሬት አረሰ፡፡
ምሳሌ 4፡- እቤት ወስጥ አለ፡፡ ምሳሌ 5፡- ምሳውን በላ፡፡ እነዚህ የተሰመረባቸው ቃላት
ሁሉ የሀረጉ መሪ ግስ ሲሆኑ ሌሎቹ አጃቢዎች ናቸው፡፡
4. መስተዋድዳዊ ሀረግ፡- ይህ የሀረግ አይነት መስተዋድዶችን መሪ አድርገን እነሱ ላይ የተለያዩ
አጃቢዎች በመጨመር ትርጉማቸውን እያሰፋን ስንሄድ የሚመሰረት ነው፡፡ ይህ የሀረግ አይነት
መሪው በቀኝም በግራም ስለሚገኝ ሁለት መሪ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ መሰተዋድዶች ከሌሎች
የቃል ክፍሎች አንፃር ሲነፃፀሩ በቁጥር ያነሱ፤ በመሪያቸው ብቻ ሊቆሙ የማይችሉ ፤ መሙያን
የግድ የሚወስዱ፤ ሌሎች ቃላትን መመስረት የማይችሉ በመሆናቸው ሀረጋቸውን በመሪያቸው
ብቻ አያዋቅሩም፡፡ ምሳሌ 1፡- ወደ መናፋሻ
ምሰሌ 2፡- ከእህቷ ጋር ምሳሌ 3፡- ስለመጣ እነዚህ የተሰመረባቸው ሁሉ
የመሰተዋድዳዊ ሀረግ መሪ ቃል ናቸው፡፡ በምሳሌ ሁለት ላይ ሁለት መሪ እናገኛልን፤
እሱም ግራ መሪና ቀኝ በሪ በመባል ይጠራል፡፡
5. ተውሳከ ግሳዊ ሀረግ ፡- ይህ የሀረግ አይነት ተውሳከግስን በመሪነት በመያዝ ሀረጉን ያዋቅራል፡፡ የዚህ
ሀረግ መሪም በስተቀኝ ይገኛል፡፡ እነዚህም ተውሳከ ግሶች በቃላዊ ማንነታቸው ስንመለከታቸው
ከሌሎቹ የቃል ክፍሎች በቁጥር ያነሱ ናቸው፡፡ እነሱም ፡- ክፉኛ ፣ ገና፣ ቶሎ፣ ግምኛ ፣ ጅልኛ
የሚሉት ሲሆኑ እነዚህን በመሪነት በመያ ሀረጉን ይመሰርታል ማለት ነው፡፡ ምሰሌ 1. በጣም
ክፉኛ ምሳሌ 2. ዛሬ ገና
ምሰሌ 3. በፍጥነት ቶሎ የተሰመረባቸው ቃላት መሪ ተውሳከ ግስ ናቸው፡፡

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 8


ዘይቤ ምንድን ነው

ዘይቤ ለአገላለፅ ትኩስነትና ጥንካሬ ለመስጠት ሲባል ከመደበኛው የቃላት ፍቺ ወይም የቃላት አደራደር ስርኣት
ይሁነኝ ብሎ ማፈንገጥ ነው፡፡ ዘይቤ አንድን ሁኔታ የሚገልፀው የቃላትንና የሀረጋትን ትርጉምና አገባብ
ከተለመደውና በውል ከታወቀው ወጣ ወይም ለየት በማድረግ ለሀሳብ ላቅ ያለ ደረጃ ለመስጠት ነው፡፡ ዘይቤ
የሚፈጥረውም አንድን ባህሪ ስሜት፣ ድርጊት፣ ሁኔታ ሰው ወይም እንሰሳ ከሌላ ነገር ጋር በማወዳደርእና
በማመሳሰል የአንድን ባህሪ ለሌላ በመስጠት ወይም በመለወጥ የአንድን ባህሪ በመለወጥና በመቅዳት እንዲሁም
በሌላ በመወከል ነው፡፡

ዘይቤዎች በአይነታቸው ብዙ ናቸው፡፡ አንድ አንድ ምሁራን 250 የዘይቤ አይነቶች አንዳሉ ይናገራሉ፡፡ነገር ግን
እነዚህን ዘርዝሮና ለይቶ የገለፀ እሰካሁን የለም፡፡ ብዙዎቹ እሰካሁን በጣም የተለመዱትና ዋናዋና የሚባሉት
ከአስራሁለት እሰከ አስራምስት የሚደርሱ ናቸው፡፡እነሱም ፡-

የዘይቤ አይነቶች

1. አነፃፃሪ ዘይቤ፡- ይህ የዘይቤ አይነት ነገሮችን ፣ሀሳቦችን ባህሪዎችንእና ድርጊቶችን በማነፃፀር ወይም
በማወዳደር የሚፈጠር ነው፡፡በዚህ የዘይቤ አይነት ሁለት ተነፃፃሪዎች ከተለያዩ ጎራዎች የመጡና
አብዛኛው የተለያዩ ባህርያት ያላቸው መሆን አለባቸው ፤ ነገር ግን የሚነፃፀሩበት አንድ የጋራ ባህሪ
ይኖራቸዋል፡፡ በአነፃፃሪ ዘይቤ እንዲጎላ ወይም እንዲደመቅ የተፈለገው ነገር ተገላጭ ሲባል ተገላጩን
አጉልቶ ወይም አተልቆ ወይም አድምቆ ለመግለፅ የሚገባው ደግሞ ገላጭ ይባላል፡፡ በተነፃፃሪዎቹ
መካከል መኖር ያለበት የጋራ ባህሪ ደግሞ ሰበበ ንፅፅር ይባላል፡፡ በዚህ የዘይቤ አይነት መነፃፃሪያው ቃል
እንደ፣ ይመስል እና ያህል የሚሉት ናቸው፡፡
ምሳሌ፡- አስቴር እንደጦጣ እየዘለለች ከመቀመጨዋ ተነስታለች ፡፡
ተገላጭ፡- አስቴር -- ገላጭ፡- እንደጦጣ-- የጋራ ሰበበንፅፅር፡- ሁለቱም መዝለላቸው ነው
ምሳሌ ሁለት፡- ገመቹ ጅብ ይመስል ሌሊት መሄድ ይወዳል፡፡
ተገላጭ ፡- ገመቹ -- ገላጭ፡- ጀብ------ሰበበ ንፅፅሩ ሁለቱም ሌሊት መሄዳቸው፡፡
2. ተለዋጭ ዘይቤ ፡- ይህ የዘይቤ አይነት የአንዱን ባህሪ ለሌላ በመስጠት የሚፈጠረ ነው፡፡ አንድን ሰው ፣
እንሰሳ ፣ተክል ወይም ግኡዝ ነገር ወይም አካል ወስዶ ለሌላው በመስጠት ሀሰቡን በጎላ ሁኔታና በምስል
ይገልፃል፡፡ ምሳሌ 1፡- አዶናይ ፀሀይ ነች፡፡ እዚህ ምሳሌ ላይ የፀሀይን በህሪ የወሰደቸው አዶናይ ነች፡፡
ምሳሌ 2፡- ካሳ አንበሳ ነው፡፡ ምሳሌ 3፡- አልማዝ ጊንጥ ነች፡፡
3. ሰውኛ ዘይቤ፡- ይህ የዘይቤ አይነት የሰውን ልዩ ልዩ ባህርያት ድርጊትና ችሎታ ሰው ላልሆነ ነገር
ለእንሰሳ ለግኡዝና ለተክሎች በመስጠት የሚፈጠር ነው፡፡ በዚህ የዘይቤ አይነት ሰው ያልሆኑ ነገሮች
ሲበሉ፣ ሲጠጡ፣ ሲያሥቡ ሲናገሩ ፣ሲጠማቸው ሲያዝኑ እና ስራን ሲሰሩ ይታያሉ፡፡ ሰውኛ ዘይቤ
ብዙውን ጊዜ በሶስተኛ መደብ ነጠላ ቁጥር ይጠቀማል፡፡
ምሰሌ 1፡- ምድር ጎዘጎዘች ቅጠል መንጣፏን
በጣም ደስ እንዲላት መኖሪያቸው ደን
ምሳሌ 2፡- ጸደይ ልትመጣነው ደገሰች አበባ
ቁንን ተሰናድታ አቀረበች ኮልባ
አደይም ጀመረች ቀይ ቀለም ትቀባ
በለስ ከተፍ አለች ሰውነቷን ታጥባ ፡፡ በዚህ ምሳሌ የተገለፀው የፀደይ ወራት ድምቀትን ፣
ልምላሜ፣ የአበቦች መፍካትና የወንዞች መጥራት ነው የተገለፀው፡፡

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት Page 9


4. እንቶኔ ዘይቤ ፡- ይህ የዘይቤ አይነት በአጠገብ የሌለን ሰው ወይም ሰው ያልሆነን ነገር በቅርብ እንዳለ፤
እንደሚሰማና መልስ አንደሚሰጥ በመቁጠር ፤ጥያቄ በመጠየቅ ፤ በመማፀን፣ በማወያየት፣በመውቀስ ፣
በማስተዛዘን ወይም በማሳሳቅ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ምሳሌ 1፡- አጫውተኝ እንጂ ተራራው
2፡- ምነው አዲስ አበባ ጭንቅሽ በዛ
3፡- አለቀሰ መውዜር አለቀሰ ስቅስቅ ብሎ እንደሰው
አልጋላይ ተኝቶ ትኋን እየላሰው
4፡- ተናገር አንተ ሀውልት አንተ አክሱም ያለህው
አስከ ዛሬ ድረስ ስንቱን ጉድ የያኸው ፡፡ ናቸው፡፡
5. ምስያ ዘይቤ፡- ይህ የዘይቤ አይነት አንድን ሀሳብ ፣ ሁኔታ፣ ባህሪ ወይም ተፈጥሮ በባህሪውም በቅርፅ
ተመሳሳይ ይሆናሉ ተብሎ የተገመተን ነገር አብሮ በማምጣት የፊተኛው የኋለኛውን ይበልጥ
እንዲያጎላውና እንዲያደምቀው ለማድረግ የሚገባ ነው፡፡
ምሳሌ 1፡- ዛፍን ማረቅ በለጋነት ልጅን መቅጣት በልጅነት፡፡
ምሳሌ 2፡- ጠዋት ብትታይም ፀሀይ ከፍ ብላ
የማታ የማታ እሷም አሽቆልቁላ
አይቀርም መጠለቋ አይቀርም መውረዷ
ብርሀኗን ሰውራ ከአይን መጋረዷ
ሰውንም ስናየው ሳለ በህይወቱ
እሸት ነው ለጋ ነው በወጣትነቱ
በጠዋቱ ጉዞ ምንም ቢበረታ
አይቀርም መድከሙ ሲመሽ ወደ ማታ፡፡ በዚህ ግጥም ሊገለፅ የተፈለገው የፀሀይ ብርሀን ወደ
ምሽት ሲደርስ መደብዘዙ የታወቀና ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው፡፡ ልክ እንደ ፀሀይዋ ሁሉ የሰው ጉልበት
እድሜም የማታማታ እንደፀሀይዋ መደብዘዙና እየደከመ እንደሚሄድ አመሳስሏቸዋል፡፡
6. ተምሳሌት ዘይቤ፡- ይህ የዘይቤ አይነት ዋና ባህሪው ውክልና ነው፡፡ አንድ ተጨባጭ ነገር ቦታ ወይም
ድርጊት ለሌላ ነገር በመቆም ያንን የሚወክለውን ነገር ወይም ጉዳይ አጉልቶና አድምቆ ያሳያል፡፡
ገጣሚያን ለሀሳባቸው ማንፀባረቂያ የፈጠራ ችሎታቸውንና የግል ምርጫቸውን በመመርኮዝ
ተምሳሌቶችን ያበጃሉ፡፡ እንደገጣሚው ምልከታ የተለያዩ ተምሳሌቶች ሊኖሩ ቢችሉም አይነታቸው
ከሶስት አይበልጡም፡፡ እነዚህም የታወቁት የተምሳሌት አይነቶች የሚባሉት፡-
6.1. ሁለንተናዊ ተምሳሌት፡-ይህ የተምሳሌት አይነት ውክልናው አለማቀፈ እውቅና ያለው
በመሆኑ በስነ ግጥም ውስጥ ሲገኙ ፍችውን ለመረዳት አዳጋች አይሆንም፡፡ ይኸውም
ለምሳሌ፡- አበባን ለፍቅርና ለውበት፤ ጨለማን ለድንቁርናና ለመጥፎ አጋጣሚ፤ ወርቅን
ለውድና ለክቡር ነገር፤ ተራራን ለማይገፋ ከፍተኛ ሀይል ተምሳሌት በማድረግ ወይም ውክልና
በመስጠት የሚመሰረት ነው፡፡
6.2. ተለምዷዊ ተምሳሌት፡- ይህ የተምሳሌት አይነት በአንድ ማህበረሰብ ወግና ልማድ እነዲሁም
የአኗኗር ስርአት ህይወታዊ ገጠመኝ መሰረትነት የሚፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ምድብ ውስጥ
የሚገኙ ተምሳሌቶች በማህበረሰብ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የኖሩ ህዝቡ በቀላሉ
የሚያወቃቸውና በልማዳዊ ስምምነት የተቀበላቸው ናቸው እነዚህ የተምሳሌት አይነቶች
የማህበረሰቡ አሻራ ይዘው የሚፈጠሩ በመሆናቸው ለልማዱና ለባህሉ በይተዋር የሆነ ሰው
በውል ሊረዳቸው አይችልም፡፡ ምሳሌ በኢትዮጵያ ጥቁር ልብስ ለሀዘን ፤ ነጭ ልብስ ደግሞ
ደስታን ይወክላል፡፡ በህንዶች የሀዘንና የትካዜ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለው ነጭ ልብስ
አንደሆነ ይነገራል፡፡
አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤትPage 10
6.3. ግላዊ ተምሳሌት፡- ይህ የተምሳሌት አይነት በደራሲው ምልከታና ምንባብ ለነገሮች የተለየ
ፍቺ በመስጠት የሚፈጠር ሲሆን የደራሲው አሻራ ለህይወትና ለተፈጥሮ ያለውን አተያይ
የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ በተጨማሪም ማህበረሰቡ በግል አመለካከቱ የሚሰጠው ውክልና ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ሙሽሮችን እርኩም በመንገድ ላይ ከአቋረጣቸው አድሜያቸው አጭር ነው
በማለት መወከል፤ አንዲትን ሴት ለመለመን ሽማግሌዎች ሲሄዱ ጥራጊ ይዛ ከወጣች ትዳሩ
አይሰምርም በማለት መወከል ፤ ባዶ እንስራ ካጋጠማቸውም ለመጥፎ አጋጣሚ በመወከል
የሚመሰረት የተምሳሌት አይነት ነው፡፡
7. አያዎ ዘይቤ፡- ይህ የዘይቤ አይነት ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦችን ወይም ዓ.ነገሮች ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ ላይ
ላዩን ሲመለከቱት እውነትነት የሌለው ከእውነታው ጋር የሚጣረስ ነገር የያዘ ይመስላል፤ጠለቅ ብልን
ስንመረምረው ረቀቅ ያለና እውነትነት ያለው መሆኑን የሚያመለክት ገፅታ አለው፡፡ ምሳሌ 1. የዝምታ
ሁካታ ምሳሌ 2. እያዩ አለማየት ምሳሌ፡-3 ህይወት ያለው በድን
8. ምፀት ዘይቤ፡- ይህ የዘይቤ አይነት አንድን ሀሳብ በተቃራኒ መልኩ የምናቀርብበት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-
አንድ ልጅ እናቱ ያስቀመጠቸውን ብርጭቆ አንስቶ ቢሰብር እሰይ የኔ ልጅ ስበረው ስትለው ልጁ
የእናቱን መንፈስ በማሰተዋል ፍቷን ስለሚረዳ ምን ማለቷ እንደሆነ በቀላሉ ያውቃል ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም አንድ ገጣሚ አንዱን ሰነፍ ሰው አንዲህ በማለት ይገጥምለታል፡፡ ደንስ ጎበዝ ደንስ ጀግና
ክርባትክን አውልቀውና
ሀሳብህን ልቀቀውና
ኮትክን ሸሚዝህን ጣልና
ርገጥ ጨፍር ደነስ ጀግና
9. ንቡር ጠቃሽ/ታሪክ ጠቃሽ/ ዘይቤ ፡- ይህ የዘይቤ አይነት አብዛኛውን ጊዜ አንድን የስነፅሁፍ ስራ
ወይም የኪነጥበብ ስራ ገለሰብ ወይም ድርጊት በግልፅ መጥቀስ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አንባቢው የደራሲውን
ገጠመኝ አንዲጋራ የሚጠይቅ ሲሆን ለተገላጩ ነገር በተዛምዶ ድምቀትና ጥልቀት የሚሰጥነው፡፡
የብዙ ደራሲያን ንቡርጠቃሽ ዘይቤ ቃሉ እንደሚያመለክተው የሚመሰረተው ከነበሩ ወይም ከኖሩና
በታሪክ ከታወቁ ሰዎች ፤ በታሪክ ከታወቁ አባይት ክንዋኔዎች፤ከመፅሀፍት ቅዱሳት፤ ከታወቁ መፃህፍት
፤ከከተማ ስሞች፤ከታላለቅ የኪነጥበብ ስራዎች ገፀባህርያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ምሰሌ፡- 1.የእዮብን
ትግስት ይስጥህ 2. ደግ እንደ ዮሴፍ 3. ተኮለኛ አንደ አያጎ 4. የቋራው ካሳ 5. ፍቅር አንደ
ሮሚዮና ጁሌት
10. በስመ ሀዳሪ ዘይቤ፡- በስመ ሀዳሪ ዘይቤ መኖሪያውን ጠርቶ ኑዋሪውን ፤ ኑዋሪውን ጠርቶ መኖሪያውን
የሚያሳይ የንግግር ስልት ነው፡፡ በአንድ አካል ወይም ቦታ ውስጥ የሚገኝን ወይም የሚኖርን ነገር
በመጥራት ስለተገኘበት ወይም ስልሚኖርበት መግለፅና መንገር ነው፡፡
ምሳሌ፡1 ንጉስ ለማለት ዘውድ ብሎ መጥራት 2. ዳኛው ፈረደብኝ ለማለት ወንበሩ አደላብኝ
ይባላል ፡፡ 3. የኢትዮጵያ ህዝብ ወይም መንግስት ተናገረ ለማለት ሲፈለግ ኢትዮጵያ ገለፀች ይባላል፡፡
11. አሊጎሪ ዘይቤ ፡- ይህ የዘይቤ አይነት ለረቂቅ ሀሳብ ፣ ባህሪ ወይም ድርጊት ተጨበጭነትን ሰዋዊነትን
በመስጠት የሚመሰረት ነው፡፡ እነዚህም ረቂቅ ነገሮች የሚባሉት፡-ጥበብ፣. ድንቁርና ፣ትህትና ፣
ቅንነት፣ ክፋት ፣ ትዝታ፣ የመሳሰሉትን አግዝፎና ተጨባጭ አድርጎ ሰዋዊ ባህሪ አላብሶ ሲናገሩና
አንዳንድ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ በማሳየት ሀሳብ ሲገለፅበት ይታያል፡፡ ምሳሌ፡- ፍርሀት የኛ ጌታ
ፍርሀት የገዛን እኛ የፍርሀት ሀገር ዜጋ
በፍርሀት ብቻ መቼም መውጫ መግቢያችን የተዘጋ
ያለንበትም ቤቱ ሁሉ መላው አየሩ ተነፈገ
በውስጡም ያለነው እኛ ሰውነታችን ጠወለገ፡፡

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤትPage 11


የሚለው ግጥም በአሊጎሪ ዘይቤ የተገለፀ ነው፡፡ በዚህ ውስጥም ፍርሀት የተባለውን ረቂቅ ነገር ሰዋዊ
ስራ ሲሰራ ይታያል፡፡
ግጥም ምንድን ነው
 ግጥም ማለት የስንኞችን መድረሻ ሆሄዎች ቤት እያስመቱ መናገር ማለት ነው፡፡
 ግጥም ምት ያለውና ምናባዊ የሆነ የብርቱ ስሜት መግለጫ ነው፡፡
 ግጥም በለሆሳስ የታወሱ ጠንካራ ስሜቶች ከውስጥ ገንፍሎ መውጣት ነው፡፡
 ግጥም ስሜት ነክ በሆነ ስልት የሚነግረን ቋንቋ ነው፡፡ ባጠቃላይ ግጥም እምቅ፣ ቁጥብ ፣ በትንሽ ቃል
ሰፊ መልእክትን ማስተላለፍ የሚችል ሙዚቃዊ ቃና ያለውና የጠበቀ ምትና ምጣኔ ያለው ነው፡፡
የግጥም አላባውያን ወይም ሙያዊ ቃል
የግጥም ሙያዊ ቃላት የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነሱም ፡-
1.ስንኝ፡- ሀረጎችን ያካተተ የግጥም አንድ መስመር ነው፡፡
ምሳሌ 1. አንበሳነው ጀግና ቁጣው አስበርጋጊ
የነፃነት አርማ የድል ፋና ወጊ፡፡ ይህ ግጥም ባለ ሁለት ስንኝ ነው፡፡
2. ሀረግ፡- በአንድ ትንፋሽ የሚነበብ የስንኝ ግማሽ መስመር ነው፡፡ ሀረጉ በስንኙ መጀመሪያ ካለ መነሻ
ሀረግ መስንኙ መጨረሻ ላይ ከላ መድረሻ ሀረግ ይባላል፡፡
ምሳሌ 1. አንበሳነው ጀግና/ ቁጣው አስበርጋጊ
የነፃነት አርማ/ የድል ፋና ወጊ፡፡ ይህ ግጥም ባለ አራት ሀረግ ነው፡፡
3. ቤት፡-በስንኝ መጨረሻ ላይ ያለው ቃል የመጨረሻ ላይ ያለው ቃል የመጨረሻ ሆሄ ወይም ድምፅ
ነው፡፡ በተራ ቁጥር ሁለት ላይ የተወሰደው የግጥም ቤት ‹‹ጊ›› ነው፡፡
4. ቤት መታ ፡- አንድ ስንኝ በምጣኔ ተሳክቶ ሲጨርስ ቤት መታ ይባላል፡፡ በተራ ቁጥር ሁለት ላይ
የተወሰደው የግጥም ምትና ምጣኔውን የጠበቀ በመሆኑ ቤት ይመታል፡፡
5. ቤት ደፋ፡- ግጥሙ ባለ ሁለት ስንኝ ከሆነ የሁለተኛው ስንኝ ቤት ከመጀመሪያው ጋር ተጣጥሞ
ሲጨርስ ቤት ደፋ ይባላል፡፡ በተራ ቁጥር ሁለት ላይ የተወሰደው ግጥም በተመሳሳይ ሆሄ መጨረሱ ቤት
ደፋ ይባላል፡፡ አሱም፡- ‹ጊ› የሚለው ነው፡፡
6. ቤት መምቻ ቃል፡- በተመሳሳይ ሆሄ ወይም ድምፅ በሚጨርሱ ስንኞች የተመሰረተ ግጥም
የመጀመሪያ ስንኝ የመጨረሻ ቃል ነው፡፡
ምሳሌ 1. አንበሳነው ጀግና ቁጣው አስበርጋጊ
የነፃነት አርማ የድል ፋና ወጊ፡፡ የተሰመረበት ቤት መምቻ ቃል ነው፡፡
6. ቤት መድፊያ ቃል፡- በተመሳሳይ ሆሄ ወይም ድምፅ በሚጨርሱ ስንኞች የተመሰረተ ግጥም የመጨረሻ
ስንኝ የመጨረሻ ቃል ነው፡፡
ምሳሌ 1. አንበሳነው ጀግና ቁጣው አስበርጋጊ
የነፃነት አርማ የድል ፋና ወጊ፡፡ የተሰመረበት ቤት መድፊያ ቃል ነው፡፡
8. አንጓ /አርኬ/፡- በአንድ አይነት ቤት የተደረደሩ ስንኞች ስብሰብ ሲሆን በአራት ነጥብ ይዘጋል፡፡
ምትና ምጣኔ
ምትና ምጣኔ እጅግ የጠበቀ ትስስር ያለቸው የግጥም አላባዎች ናቸው፡፡ ለግጥም ምት የምንለው
አንደልብ ትርታ ተደጋግመው በሚሰሙና በአንድ ትንፋሽ በሚነበቡ የቃላት ስብሰቦች መሀል ያለውን
የተወሰነ የጊዜ መጠን መጠበቂያ ስልት ነው፡፡ የግጥም ምት የሚመነጨው ሌሎቹ የምልዓቱ ማስገኛ
ክፍሎች ከሚኖራቸው ምጣኔ ነው፡፡ ስለዚህ ምጣኔ በተፈጥሮአዊ ቅንብርና በስርዓታዊ ትስስር
ግጥምን ህልው የሚያደርጉት ልዩ ልዩ ምልዓት ማስገኛ አላባዎች መጠን የሚወሰንበት ልኬታ ነው፡፡

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤትPage 12


ባጠቃላይ ምት የሚገኘው በሀረጋቱና በስንኞቹ ያሉት ቀለሞች ባላቸው ምጣኔ ነው፡፡ ስለዚህ ምጣኔ
ከተዛባ ምቱ ይዛባል፡፡ ምጣኔው ከተሰተካከል ምቱም ይስተካከላል፡፡

ተውኔት
ተውኔት ከኪነ ጥበብ ዘርፎች ማለትም ከስነ ፅሁፍ ከስነ ስዕል፣ ከሙዚቃ፣ከቅርፃቅርፅና ከፊልም አንዱ
ነው፡፡ ተውኔት ወይም ድራማ የሚለው ቃል የተገኘው ‹ዴራን›› ከሚለው የግሪክ ቃል ነው፡፡
ትረጉሙም ማድረግ ወይም መከወን ማለት ነው፡፡
የተውኔት አላባውያን
የተውኔት አላባውያን የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ገፀባህርያት ፡- በአንድ ተውኔት ውስጥ በፀሀፌ ተውኔቱ የሚፈጠሩ እና በተፈጠሩበት ተውኔት
ውስጥ የሚከናወኑት የስራ ድርሻ ያላቸው በገሀዱ አለም ሰውን መስለውና ሰውን ወክለው አንድ
ሰው በመናገርና የተለያዩ ተግባራትን በመፈፀም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ገፀባህርያት የሚናገሯቸው
ድርጊቶች ለአንባቢያን ሆነ ለተመልካቾች ሙሉ በሙሉ ግልፅ ናቸው፡፡
2. መቼት፡- በአንድ ተውኔት ውስጥ ድርጊቱ መቼ እንደተፈፀመ ጊዜውንና የት እንደተፈጸመ
ቦታውን ይገልፃል፡፡
3. ታሪክ፡- በአንድ ተውኔት ውስጥ በንግግርም ሆነ በገጸባህርያት በድርጊት የሚከናወነውን የአንድ
ተውኔት ታሪክ ነው፡፡ የተውኔት ታሪክ ሌሎችን አላባውያን ይይዛል ማለት ነው፡፡ ገጸባህርያት፣
መቼት፣ ትልምና ግጭት የሚፈጥሩት በአንድ ተውኔት ታሪክ ውስጥ ነው፡፡
4. ትልም፡- ሌላው የተውኔት አላባ ነው፡፡ ገጸባህርያት የሚፈፅሟቸው ድርጊቶች ምክንያትና
ውጤትን ተከትለው የሚካሄዱ አንደመሆናቸው ትልም በተውኔቱ ውስጥ የሚካሄዱትን ነገሮች
ምክንያትና ውጤት ያሳያል፡፡
5. ግጭት፡- በአንድ ተውኔት ውስጥ የሚገኘው ሌላው አላባ ግጭት ነው፡፡ በአንድ ተውኔት ውስጥ
ገፀባህርያት በሚያራምዱት ተግባር ወይም በሚያከናውኑበት ታሪክ እርስበርሳቸው ወይም ይህን
ላድርግ ወይስ አላድርግ በሚል በግል ከራሳቸው ጋር ይጋጫሉ፡፡ ማንኛውም የተውኔት ታሪክ ያለ
ግጭት ሊፈጠር አይችልም፡፡ ያለ ግጭት የሚፈጠር ታሪክ እንጂ የተውኔት ታሪክ አይሆንም፡፡

የተውኔት መዋቅር

የተውኔት ድርሰት በገቢርና በትእይንት እየተከፈለ ይዋቀራል፡፡ በተጨማሪም ቃለ ተውኔት፣ መራሄ


ተውኔት፣ ፀሀፌ ተውኔት፣ መነባንብ፣ ጎንታ እና መድረክ፣ የመሳሰሉት ተወኔቱን በማዋቀር
ይመሰርታሉ፡፡ እነዚህንም ምንነታቸውን ስንመለከት ፡-
1. ገቢር ፤- የታሪኩ አብይ ክፍል ነው፡፡ በአንድ ተውኔት እንደታሪኩ ስፋትና ጥበት አንድም ሁለትም
ከዚያም በላይ ገቢሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በተውኔት ውስጥ የሚኖሩ ገቢሮች ቁጥራቸው ይህን ያህል
ተብሎ አልተደነገገም፡፡እንደየዘመን የተውኔት አፃፃፍ ስልት መለያየት ቁጥራቸውም እንደሚለያይ
ይነገራል፡፡ ገቢሮች የተለያዩ ትዕይንቶች አሏቸው፡፡
2. ትዕይንት፡- ትዕይነት የገቢር ንኡስ ክፍል ነው፡፡
3. ቃለ ተውኔት፡- ገፀባህርያት ሀሳባቸውን የሚያስተላልፉበት ንግግር ማለት ነው፡፡
4. መራሄ ተውኔት፡- ተውኔቱን በመድረክ የሚመራው ሰው ወይም ባለሙያ ማለት ነው፡፡
5. ፀሀፌ ተውኔት፡- ይህ ማለት ተውኔቱን የሚፅፈው ባለሙያ ማለት ነው፡፡
6. መነባንብ፡- ይህ ማለት አንድ ተዋናይ በመድረክ ላይ የሚያቀርበው የብቻ ንግግር ነው፡፡

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤትPage 13


7. ጎንታ፡- ጎንታ አንድ ባለሙያ ሌሎች ታዳሚዎች እንደማይሰሙት በመቁጠር ሰዎችን የሚያማበት
ሂደት ነው፡፡
8. መድረክ ፡- ገፀባህርያት ታሪካቸውን የሚያቀርቡበት በታ ነው፡፡

የድርሰት አፃፃፍ አይነቶች


ጥሩ ድርሰት ለመፃፍ ከሁሉም በላይ የሚያስፈልገው የተስተክከለ አ.ነገር መፃፍ መቻል ነው፡፡ እንደ ድርሰቱ
አይነትና ልናስተላልፈው እንደፈለግነው መልእክት የአፃፃፍ ስልታችን ይለያያል ቀጥሎም የድረሰት አፃፃፍ
አይነቶች በአጭሩ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
1. ተራኪ ድርሰት፡- ተራኪ ድርሰት ሁኔታዎችን እንደ ስንሰለት የተያያዙትን ድርጊቶች እንዲህ
ሆነ እንዲህ ተደረገ ወዘተ በማለት የምንዘረዝርበት የደርሰት አይነት ነው፡፡ ድርሰቱም በትንሹ ጀምሮ እየተረከ
እየተነተነ እና እያደገ ወይም ስፋት እያገኘ የሚሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-ልጅ ካሳ ከእናታቸው ከእመት አትጠገብ
ወንደሰንና ከአባታቸው ከጌታው ሀይሉ በ 1811 ዓ.ም በቋራ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸውም ለትምህርት
እንደደረሰ አጎታቸው ደጃች ክንፉ በትምህርት እንዲያድጉ በማሰብ ወደ ገዳም ወሰዷቸው ፡፡ ከዚያ በኋላ
በተለያዩ ጦርነቶች ላይ ተሳትፈው አሸናፊ ሆኑ፡፡ በመጨረሳም በ 1837 ዓ.ም ንጉሰ ነገስት በኢትዮጵያ ሆኑ፡፡
2. አመዛዛኝ ድርሰት ፤- ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ተመሳሳይ ወይም ተቃራኒ ሀሳቦችን በሚገባ
ተመልክቶ ከራስ ሀሳብ ጋር አያይዞና አዋህዶ ለየብቻው እያነፃፅሩ በመግለፅ የምንፅፍበት የድርሰት አይነት ነው፡፡
ምሳሌ፡- በግል ማጥናት ወይስ በቡድን ማጥናት የሚለው ሀሳብ የራሱ ጥሩና ደካማ ጎኖች አሉት፡፡ በግል
ለማጥናት ትኩረትን ለማግኘትና ጊዜ የበለጠ ለመጠቀም ይረዳል፤ በቡድን ማጥናት ደግሞ ሀሳብን በጋራ
ለመካፈልና ያልገባን ለመረዳት ይጠቅማል፡፡
3. ስእላዊ ድርሰት፡- ይህ የድርሰት አይነት አንድን ሀሳብ በአእምሮ ውስጥ ምስል በሚከስት ቃላት
የሚፃፍ ነው፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ስእሎችን በመፍጠር እና እነሱንም የቅርብ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ
በማድረግ እንደሰሙት እንዳዩት፣ እንዳሸተቱት ወዘተ… አድርጎ በፅሁፍ መግለፅ የሚቻልበት ጥበብ ነው፡፡
ምሳሌ፡-
መድፍ ዷዷ!ዷ ዷዷዷ! ሲል በድንጋጤ ባነነና ከአልጋው ስር ሊገባ ዘሎ ተነሳ እለቱ ዘመን መለወጫ መሆኑን
ሲያስታውስ በእፎይታ ተመልሶ ጋደም አለ፡፡ ቆይቶም ጨለማውን በቁጥርና በቀስት ብርሀን ድል በማድረግ ላይ ያለውን
የግድግዳ ሰዓት ቀና ብሎ አየ፡፡ መንጋቱን በመረዳት የራስጌ መብራት አበራ ፡፡ ጠባቧ መኝታ ክፍሉ ዝብርቅርቋ ወቷል፡፡
አልጋው አጠገብ ቢቆም እንክርት ላይ የነበረው ፍም ሙቶ ቀዝቃዛ አመድ ብቻ ይታያል፡፡ አጎኑ ካለው ወንበር ላይ በጢስ
የተዥጎረጎረ ማንቆርቆሪያ የሻይ ጭላጭ ከውስጡ የሚታይ ብርጭቆና ስኳር የደረቀበት ማንኪያ ጉብ ጉብ ብለዋል፡፡
ወለሉ ላይ ደግሞ ቀንበጣቸው የተለቀመላቸው የለዘዙ ቅጠሎች ፣ የኮባቅጠል የመኪና የውስጥ አካል፣ የእርሳስ ንድፍ፣
ክላሰር፣ የቴፕ ክሮች አና የሲጋራ ቁራጭ ተበታትነዋል፡፡ ሲያያቸው መልሰው ያዩታል፡፡ እንደበታቸውን ሳይከፍቱ ‹‹
በልባቸው አንተ ብቸኛ ሰነፍ!›› እያሉ የሚያፈጡበት መሰለው፡፡ ከአይናቸው ለመሸሽ መብራት አጠፋ፡፡ አንሶላውን
ተከናንቦ ተኛ፡፡
4. አስረጅ/ገላጭ/ ድርሰት፡- ይህ የድርሰት አይነት አንድን ነገር እንዴት እንደተሰራ እንዴት
እንደተከናወነ ለማሳወቅ ወይም ለማስረዳት የምንጠቀምበት ፅሁፍ ነው፡፡ትኩረቱም መልእክቱን በተገቢው
ሁኔታ ለማስተላለፍ እንጂ ለቋንቋው ውበት እምብዛም አይጨነቅም፡፡ ሲጋራ ማጨስና ጫት መቃም በብዙ
ሰዎች ዘንድ የተጠሉ ተግባራት ናቸው፡፡ ምንም አይነት ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጠቀሜታም የላቸውም፡፡
ተጠቃሚዎችም ቢሆኑ የሚናገሩት ጎጂነታቸውን ነው፡፡ መቼ ነው ከነዚህ ሱሶች የሚላቀቀው በሚል ስሜት
ሲማረሩ ይደመጣሉ፡፡ ማንኛውም ሱስ ፈታኝና በአንድ ጊዜ ለማቆም አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙዎቹ ከገቡበት
በኋላ ለመውጣት ይቸገራሉ፡፡ ሲጋራ በማጨስና ጫት በመቃም ሱሶች የተጠመዱ ብዙ ወጣቶቸን አውቃለሁ፡፡

አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤትPage 14


አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤትPage 15


አርሲ ዩንቨርሲቲ አሰላ ልዩ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤትPage 16

You might also like