You are on page 1of 27

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የከፍተኛ ባለሙያዎች ብቃት ምዘና እና


ማረጋገጫ አፈፃፀም ረቂቅ መመሪያ

ግንቦት፣ 2014 ዓ.ም. | አዲስ አበባ


መግቢያ
የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው በሀገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ
ይገኛል፡፡ በዚሁ ኢንዱስትሪ ልማት ላይ የሰው ኃይል ትልቁን ሚና የሚጫወት ሲሆን የተለያዩ
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በማንኛዉም ግንባታ የጥራት ጉድለት ከሚያስከትሉ ምክንያቶች ውስጥ
ዋነኛው ባለሙያዎች ኢንዱስትሪው በሚፈልገው የብቃት ደረጃ ላይ ያለመሆናቸው ነው፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ዘርፉ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ
ባለሙያዎች በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን በመፈለጉ እና ባለሙያዎቹ በአለም አቀፉ ገበያ
ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የመመሪያው መውጣት ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ሚና
የሚጫወተውን የሰው ሀይል ልማትን ለመምራት የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል እንደማይሆን
በመታመኑ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 ማብራርያ
ላይ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሙያ ብቃት
ደረጃ ምዘና እና ማረጋገጫ ስታንዳርድ ለማስፈፀም እና በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ
የተሰማራውን የሰው ኃይል ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ በምዘና መረጋገጥ እንዳለበት ታሳቢ
በማድረግ ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡
ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
1. አጭር ርዕስ
ይህ መመርያ “በኮንስትራክሽን ዘርፍ የከፍተኛ ባለሙያዎች ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ
አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር -------- /2014” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
2. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውሰጥ፣

1. “ኢንስቲትዩት” ማለት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ነው።


2. “የኢንስቲትዩት በላይ ኃላፊ” ማለት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወይም ም/ዋና
ዳይሬክተር ነው።
3. “ኮንስትራክሽን ዘርፍ” ማለት ከመሬት በታች እና በላይ የሚከናወኑ የምህንድስና
መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ በቋሚ ንብረቶች፣ በአገልግሎቶችና በመሳሪያዎች
የሚታገዙ የጉልበት ሥራዎች ጭምር ሆኖ በህንጻ እና በሌሎች መሰረተ ልማት
ግንባታ ሥራዎች የማልማት፣ የማስፋፋት፣ የመገጣጠም፣ የመጠገን፣ የማሻሻል፣
የመቆፈር፣ የማወላለቅ፣ የማፍረስ እና የማማከር ተግባር ነው።
4. “ኢንዱስትሪ” ማለት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለበት ኢንዱስትሪ ነው።
5. “የሙያ ደረጃ” ማለት በኢንስቲትዩቱ የሚዘጋጅ አንድ ባለሙያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ
ውስጥ በሚገባ ጊዜ ሊኖረው የሚገባ የብቃት እና ክህሎት ዝግጅትን የሚገልጽ ሰነድ
ነው።
6. “የብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ስርዓት” ማለት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ አንድ
ባለሙያ በትምህርት ዝግጅት ወይም/እና በስራ ልምድ የሙያ ደረጃው
የሚጠይቀውን ብቃት አሟልቶ መገኘቱን የሚፈተሽበት ስርዓት ነው፡፡
7. “የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት” ማለት በሙያ ብቃት ምዘና ሥርዓት
ተመዝኖ ብቁ ለሆነ የሙያ ባለቤት ለብቁነቱ ምስክር የሚሆን በኢንስቲትዩቱ
የሚሰጥ ህጋዊ ማስረጃ ነው።
8. “ከፍተኛ ባለሙያ” ማለት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ከዚያ በላይ
የትምህርት ዝግጅት ያለው ባለሙያ ነው።
9. “ተመዛኝ” ማለት በኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን የብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ
ለመውሰድ ምዝገባ ያካሄደ እና ምዘናውን መቀመጥ እንደሚችል በኢንስቲትዩቱ
የተረጋገጠ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማራ ከፍተኛ ባለሙያ ነው።
10. “የምዘና መሣሪያ” ማለት በኢንስቲትዩቱ ከተዘጋጀው የሙያ ደረጃ ሰነድ የሚቀዳ
ተመዛኞችን ለመመዘን አገልግሎት ላይ የሚውል ነው።
11. “የምዘና መሳሪያ ቋት” ማለት የተዘጋጀው የምዘና መሳሪያ ተሰብስቦ በኢንስቲትዩቱ
የሚቀመጥበት ነው።
12. “የምዘና ፓኬጅ” ማለት ከምዘና መሳሪያ ቋት ውስጥ የሚውጣጣ እና ተመዛኞችን
ለመመዘን አገልግሎት ላይ የሚውል የጥያቄ ስብስብ ነው።
13. “የምዘና ማዕከል” ማለት በኢንስቲትዩቱ የተፈተሸ እና የተረጋገጠ ለሙያ ብቃት
ምዘና፣ ተመዛኞች ምዝገባ ለማካሄድ እና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት
አገልግሎት ላይ የሚውል ቦታ ነው።
14. “የሙያ ማህበራት” ማለት ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ጋር በተገናኘ የተመሰረቱ ማህበራት
ናቸው።
15. “ከፍተኛ ትምህርት ተቋም” ማለት በሃገሪቱ የትምህርት ስርዓት ውስጥ እውቅና
ያገኙ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ትምህርቶችን በዲግሪ እና ከዚያ በላይ የሚሰጡ
የመንግስት እና የግል ተቋማት ናቸው።
16. “መመልመያ መስፈርት” ማለት በኢንስቲትዩቱ አማካኝነት ለምዘናው የሚመለመሉ
ባለሙያዎች እና የሚዋቀሩ ኮሚቴዎች የሚመለመሉበት መስፈርትን የያዘ ሰነድ
ነው።
17. “ኮሚቴ” ማለት የባለሙያዎችን ብቃት ምዘና በተሳካ እንዲካሄድ በኢንስቲትዩቱ
አማካኝነት ለተለያየ ዓላም የሚሰየም ኮሚቴ ነው፡፡
18. “የቅድመ-ምዘና ሂደት” ማለት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ተሰማርተው
ያሉ ወይም ለመሰማራት የሚፈልጉ ከፍተኛ ደረጃ ባለሙያዎች የብቃት ምዘና
ለመዉሰድ የሚያደርጉት የምዝገባ ምዕራፍ ሲሆን ለኢንስቲትዩቱ ድግሞ የሙያ
ብቃት ምዘና ለማካሄድ የሚረዳ የዝግጅት ምዕራፍ ማለት ነዉ።
19. “የምዘና ሂደት” ማለት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ተሰማርተው ያሉ
ወይም ለመሰማራት የሚፈልጉ ከፍተኛ ደረጃ ባለሙያዎች ብቃታቸው የሚመዘንበት
ምዕራፍ ነው።
20. “የድህረ-ምዘና ሂደት” ማለት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ተሰማርተው ያሉ
ወይም ለመሰማራት የሚፈልጉ ከፍተኛ ደረጃ ባለሙያዎች የክህሎት ብቃት
ማረጋገጫ ምዘና/ፈተና ከወሰዱ በኋላ የምዘና ውጤት የሚገለጽበት፣ የሙያ ብቃት
ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የሚሰጥበት እና ተመዛኞች በውጤቱ ቅሬታ ካላቸው
ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበትና የሚስተናገድበት ምዕራፍ ነው።
21. “ግለ ግምገማ ማረጋገጫ” ማለት ተመዛኙ የሙያ ብቃት ምዘናውን ከመውሰዱ
አስቀድሞ ራሱን ለመገምገም የሚሞላው ቅጽ ነው።
3. የጾታ አገላለጽ

በዚህ የአፈጻጸም መመሪያ በወንድ ጾታ የተገለጸው የሴትንም ጾታ ያካትታል።

4. የተፈጻሚነት ወሰን

ይህ መመርያ የሙያ ደረጃ በወጣላቸዉ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሙያዎች ውስጥ በተሰማሩ


ከፍተኛ ባለሙያዎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
ክፍል ሁለት
ተግባር እና ኃላፊነት
5. የኢንስቲትዩቱ ተግባር እና ኃላፊነት
1. በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ብቃት ይመዝናል፣
የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፤
2. በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ለሚገኙ ሙያዎች የሙያ ደረጃ ያዘጋጃል፣ በየጊዜው
ከኢንዱስትሪው ጋር በመተባበር ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ያሻሽላል፣ በተሻሻሉት
የሙያ ደረጃዎች መሰረት የምዘና መሣሪያዎችን በማዘጋጀት እና በመመርመር
ወቅታዊነት ባለው አግባብ እያሻሻለ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤
3. የተዘጋጁ የሙያ ምዘና መሳሪያዎችን ያጸድቃል፣ ሚስጢራዊነታቸውን ጠብቆ
ለምዘና ዝግጁ ያደርጋል፤
4. የብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ስርዓት አስፈጻሚ አካላት የሆኑትን የምዘና መሳሪያ
ዝግጅት ባለሙያ፣ የምዘና መሳሪያ አደራጅ ኮሚቴ፣ መዛኝ፣ የፈተና ገምጋሚ እና
ውጤት ሰጪ ኮሚቴ እና ሱፐርቫይዘር ይመለምላል፤ ይመድባል፤
5. በምዘና ሥራ ላይ የሚሳተፉ አካላት የሥራ ልምድ፣ የትምህርት ማስረጃ፣ ተገቢዉን
ስልጠና መውሰዳቸውን እና ልዩ ልዩ መረጃዎችን ወቅታዊነት በማረጋገጥ
ያደራጃል፤
6. በሙያ ብቃት ምዘና ሂደት ውስጥ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት
ጋር በመሆን መፍትሄ ይሰጣል፤ የተፈጠረ ክፍተት ካለ የማስተካከያ እርምጃ
ይወስዳል፤ በቀጣይ የምዘና ሂደት ላይ ማሻሻያ ያደርጋል፤
7. የምዘናውን ሂደት በተመለከተ ለሚነሱ ማንኛውም ቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ
ይሰጣል፤
8. ኢንስቲትዩቱ በሚያካሂደው የምዘና ስርዓት አልፈው ብቁ ለሆኑ ተመዛኞች የሙያ
ብቃት ምስክር ወረቀት ያዘጋጃል፤ ይሰጣል፤ ያድሳል፤
9. ለሙያ ብቃት ምዘና ስኬታማነት ከሚመለከታቸው አካል ጋር በመተባበር ይሰራል፤
10. የባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ስርዓትን በተመለከተ
ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ይሰራል፤
11. የተመዛኞችን መረጃ በዝርዝር በመረጃ ቋት አጠናቅሮ ይይዛል፤ ለሚመለከተው አካል
ሪፖርት ያደርጋል ወይም ያስተላልፋል፤
12. መመሪያውን በበላይነት ያስፋጽማል፤ አፈጻጸሙንም ይከታተላል፤ መመሪያውን
ጥሰው የሚገኙ የሙያ ብቃት ምዘና አስፈጻሚ አካላትን በዲስፕሊን ወይም
በመደበኛ ሕግ እንዲጠየቁ ያደርጋል፤

6. የኢንስቲትዩቱ የበላይ ኃላፊ ተግባር እና ኃላፊነት


ከላይ በአንቀጽ 5 ስር የተዘረዘሩት የኢንስቲትዩቱ ተግባር እና ኃላፊነት እንደተጠበቁ
ሆነው፣
1. የባለሙያዎች የሙያ ብቃት ምዘና ሂደትን በበላይነት ይመራል፤ ጥራቱን
ያስጠብቃል፤
2. ከባለሙያዎች የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጥ ስርዓት ጋር በተገናኘ ስትራቴጂክ
ግቦችን ለኢንስቲትዩት ያወርዳል፤ አፈጻጸሙን ይከታተላል፤

7. የሱፐርቫይዘር ተግባር እና ኃላፊነት


1. ሱፐርቫይዘሩ የተመደበበትን የምዘና መሳሪያ ዝግጅት፣ የብቃት ምዘና እና የፈተና
ግምገማ እና ውጤት አሰጣጥ ሂደት የተሳካ እንዲሆን እና በመመሪያው መሰረት
እንዲከናወን የቁጥጥር እና ክትትል ስራ ይሰራል፤ በሂደቱ ላይ ከሚመደቡ
ባለሙያዎች እና ከበላይ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል፤

2. ከሙያ ብቃት ምዘና ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ በሚያመቻቸው ማንኛውም መድረክ


መገኘት ይኖርበታል፤

3. የምዘና መሳሪያ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ የምዘና መሳሪያዎችን መርምሮና አረጋግጦ


ከምዘና መሳሪያ ዝግጅት ባለሙያዎች ጋር በመፈራረም ይረከባል፤

4. የምዘና መሳሪያዎችና ፓኬጆች ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ ለምዘና ዝግጁ


መሆናቸውን ያረጋግጣል፤ የምዘና መሳሪያው ፓኬጆች እና አስፈላጊ ሰነዶች ለመዛኝ
ተፈራርሞ ያስረክባል፤

5. ምዘናው ከመካሄዱ በፊት እና በሚካሄድበት ወቅት ከመዛኙ ጋር በመተባበር የምዘና


ክፍሉ አስፈላጊውን ግብዓት ማሟላቱን ያረጋግጣል፤ የተመዛኞችን ማንነት እና
ህጋዊነት በማረጋገጥ ወደ መመዘኛው ክፍል ያስገባል፤ ለተመዛኞች ከምዘናው
ሂደት ጋር በተገናኘ አስፈላጊውን ገለጻ ያደርጋል፤ ምዘናው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ
ድረስ የምዘናው አፈጻጸም በተገቢው ሁኔታና ጥንቃቄ መካሄዱን ይከታተላል፤

6. ምዘናው ከተጠናቀቀ በኋላ በተመዛኝ የተሞሉ የፈተና ወረቀቶችና ቅጾች


በሚመለከታቸው አካላት መፈረማቸውን መርምሮና አረጋግጦ በአዲስ ፖስታ
እንዲታሸጉ በማድረግ ከመዛኙ ጋር ተፈራርሞ ይረከባል፤

7. ምዘናው በተሰጠበት ዕለት ከመዛኙ የተረከበውን ለምዘና አገልግሎት ጥቅም ላይ


የዋሉትንም ያልዋሉትን የፈተና ወረቀቶች እና ቅጾች ከኢንስቲትዩቱ ጋር ተፈራርሞ
ያስረክባል፤

8. ሱፐርቫይዘሩ በበላይነት የመራውን የምዘና ሂደት የሚመለከት ዝርዝር ሪፖርት


በማዘጋጀት ለኢንስቲትዩቱ ያቀርባል፤

8. የምዘና መሳሪያ ዝግጅት ባለሙያ ተግባር እና ኃላፊነት

1. የምዘና መሳሪያ ዝግጅት ባለሙያ በመመሪያው ክፍል ሶስት/3 ላይ በተጠቀሰው


የምልመላ መስፈርት መሰረት የሚመደብ ባለሙያ ሲሆን ተመዛኞች
የሚመዘኑበትን የምዘና መሳሪያ ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀውን የመጨረሻ እና የተሻሻለ
የሙያ ደረጃ ሰነድ እና ተቁሙ የሚያስቀምጥለትን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ
ያዘጋጃል፤

2. ከሙያ ብቃት ምዘና ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ በሚያመቻቸው ማንኛውም መድረክ


መገኘት ይኖርበታል፤

3. በምዘና መሳሪያ ዝግጅት ወቅት የማንኛውንም መረጃ ምስጢራዊነት በጠበቀ እና


ከፍተኛ የስነምግባር መርሆዎችን በተከተለ መልኩ መሆን አለበት፤

4. ባለሙያው የምዘና መሳሪያውን አዘጋጅቶ እንዳበቃ የመሳሪያው ምስጢራዊነትን


በተጠበቀ መልኩ ኢንስቲትዩቱ ለመደበው ሱፐርቫይዘር ተፈራርሞ ያስረክባል፤
9. የምዘና መሳሪያ አደራጅ ኮሚቴ ተግባር እና ኃላፊነት

1. የምዘና መሳሪያ አደራጅ ኮሚቴ በመመሪያው ክፍል ሶስት/3 ላይ በተጠቀሰው


አግባብ የሚዋቀር ሲሆን በምዘና መሳሪያ ዝግጅት ባለሙያዎች አማካኝነት
ተዝጋጅቶ ከኢንስቲትዩቱ የምዘና ቋት ውስጥ የተቀመጡ የምዘና መሳሪያዎችን
ወይም ጥያቄዎች በማደራጀት ለምዘና ዝግጁ እንዲሆን ያደርጋል፤

2. ከኢንስቲትዩቱ የምዘና መሳሪያ ቋት ውስጥ ለአንድ ምዘና የሚያስፈልጉ ጥያቄዎች


በባለሙያ ወይም በኮምፒዩተር አማካኝነት በመታገዝ መምረጥ የሚቻል ሲሆን
በዋናነት በዚህ ኮሚቴ ክትትል እና ቁጥጥር ስር የሚካሄድ ይሆናል፤

3. ከሙያ ብቃት ምዘና ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ በሚያመቻቸው ማንኛውም መድረክ


መገኘት ይኖርበታል፤

4. የምዘና መሳሪያዎችን ለምዘና ዝግጅት በማድረግ ሂደት ወቅት የማንኛውንም መረጃ


ምስጢራዊነት በጠበቀ እና ከፍተኛ የስነምግባር መርሆዎችን በተከተለ መልኩ
መሆን አለበት፤

5. ኮሚቴው የምዘና መሳሪያውን ለምዘና ዝግጁ አድርጎ እንዳበቃ የመሳሪያው


ምስጢራዊነትን በተጠበቀ መልኩ ኢንስቲትዩቱ ለመደበው ሱፐርቫይዘር ያስረክባል፤

10. የመዛኝ ባለሙያ ተግባር እና ኃላፊነት


1. መዛኝ ባለሙያ በመመሪያው ክፍል ሶስት/3 ላይ በተጠቀሰው መሰረት የሚመደብ
ባለሙያ ሲሆን በምዘናው ወቅት የተመዛኞችን ምዘና ይመራል ወይም ፈተና
ይፈትናል፤

2. ለተመደበበት ምዘና መገኘት የማይችል ከሆነ ከሶስት ቀናት(3) ቀድሞ በስልክ


ወይም በአካል ተገኝቶ ለኢንስቲትዩቱ ማሳወቅ ይኖርበታል፤

3. ከሙያ ብቃት ምዘና ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ በሚያመቻቸው ማንኛውም መድረክ


መገኘት ይኖርበታል፤
4. ምዘናው ከመጀመሩ አስቀድሞ ለምዘናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ የምዘና መሳሪያ
ፓኬጅ እና ለምዘናው የሚያስፈልጉ ቅጾችን ከሱፐርቫይዘሩ ቆጥሮ፣ መርምሮ እና
ፈርሞ ይረከባል፤

5. መዛኙ እያንዳንዱ ተመዛኝ በምዘና ቦታ መያዝ የሌለበትን ምንም አይነት የመገናኛ


ወይም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አለመያዙን ማረጋገጥ ይኖርበታል፣

6. ለተመዛኞች ከምዘናው ጋር በተያያዘ ማወቅ ስለሚገባቸው ነጥቦት አጠቃላይ ገለጻ


ያካሂዳል፣ ከተመዛኝ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እና ማብራሪያ
ይሰጣል፤

7. በምዘናው ሂደት ውስጥ ምዘናውን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ክስተቶች በሚፈጠሩ ጊዜ


ከሱፐርቫይዘር ጋር በመተባበር ችግሮቹን ይፈታል፤

8. ተመዛኞች የምዘና ሂደቱን ሲያጠናቅቁ በጥቅም ላይ የዋሉትን የምዘና መሳሪያዎች


በትክክል በመፈተሽ እና ተመዛኞች በተዘጋጀው አቴንዳንስ ቅጽ ላይ መፈረማቸውን
በማረጋገጥ የተመዛኞችን የፈተና ወረቀት እና የመልስ መስጫ ቅጽ ከሱፐርቫይዘር
ጋር ተፈራርሞ ያስረክባል፤

9. አንድ መዛኝ በአንድ ቀን ውስጥ መመዘን የሚችለው እስከ አርባ/40 ተመዛኞችን


ብቻ ነው፣

11. የፈተና ግምገማና ውጤት ሰጪ ኮሚቴ

1. የተመዛኞች የፈተና እርማት ሂደት በባለሙያ ወይም በኮምፒዩተር አማካኝነት


መከናወን የሚችል ሲሆን ይሄን ሂደት በዋናነት ይህ ኮሚቴ የሚመራው ይሆናል፤
የሚዋቀረውም በዚህ መመሪያ ክፍል ሶስት/3 ላይ በተቀመጠው አግባብ መሰረት
ይሆናል፤

2. ኮሚቴው ከመዛኞች እና ሱፐርቫይዘሮች ተሰብስቦ የሚመጣውን የተመዛኞች የፈተና


ወረቀት ከሚመለከተው የኢንስቲትዩቱ የስራ ክፍል ወይም ተቁሙ ከመደበው
ሱፐርቫይዘር ፈርሞ ይረከባል፤ በተቀመጠው የፈተና መልስ አማካኝነት ያርማል፤
የተመዛኞችንም የፈተና ውጤት ምስጢራዊነትን በተጠበቀ መልኩ ለሚመለከተው
የስራ ክፍል ወይም ኢንስቲትዩቱ ለመደበው ሱፐርቫይዘር ተፈራርሞ ያስረክባል፤

3. ኮሚቴው የፈተና እርማት በሚያካሂድ ጊዜ የማንኛውንም መረጃ ምስጢራዊነት


በጠበቀ እና ከፍተኛ የስነምግባር መርሆዎችን በተከተለ መልኩ መሆን አለበት፤

12. የተመዛኝ ተግባርና ኃላፊነት


1. መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውም ግለሰብ ኢንስቲትዩቱ በሚያወጣው የምዘና
መርሃ ግብር መሰረት ለምዘናው የሚጠየቀውን ክፍያ እና አስፈላጊ ሰነዶች
ለኢንስቲትዩቱ በማቅረብ እና እንዲሞላ የሚጠየቃቸውን ቅጾች በመሙላት
መመዝገብ ይኖርበታል፤
2. የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ለመውሰድ የተመዘገበ ተመዛኝ ምዘናው
የሚሰጥበትን ቀንና ቦታ በኢንስቲትዩቱ ድረ-ገፅ፣ ማህበራዊ ሚድያ ወይም
ማስታወቂያ ሰሌዳ በትኩረት በመከታተል በተገለፀው ስፍራና ዕለት ምዘናው
ከመጀመሩ ሰላሳ/30 ደቂቃ አስቀድሞ መገኘት ይኖርበታል፤
3. በምዘና ስፍራው በሚገኝ ወቅት ተመዛኙ ይዞ መገኘት የለባቸውም ተብለው የተለዩ
ምንም አይነት የመገናኛ ወይም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ይዞ ባለመገኘት ተቁሙ
የሚያስቀምጠውን ህግ እና ደንብ ማክበር ይኖርበታል፤
4. የብቃት ምዘናው በሚካሄድበት ወቅት በመዛኙና ሱፐርቫይዘሩ ለተመዛኞች
ከምዘናው ሂደት ጋር በተገናኘ የሚሰጠውን ዝርዝር ማብራሪያ በትኩረት
መከታተል፤ በማብራሪያው ላይ ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ ካጋጠመው በአግባቡ
ለማብራሪያ ሰጪው ጥያቄ ማቅረብ ይኖርበታል፤
5. በምዘናው ወቅት ከመዛኙ የሚረከባቸውን የፈተና ወረቀት፣ ከፈተናው ውጪ
የሚቀርቡለትን የአቴንዳንስ እና የመሳሰሉትን ቅጽ በአግባቡ በመሙላት ለመዛኙ
ማስረከብ ይኖርበታል፤
6. ተመዛኙ በምዘናው ሂደት የሚፈጠርበት ቅሬታ ካለ መመሪያው የሚያስቀምጠውን
የቅሬታ ማቅረቢያ መንገድ በመከተል ማቅረብ ይችላል፤
ክፍል 3
ምልመላና ምደባ
13. የሱፐርቫይዘር ምልመላና ምደባ

1. በሱፐርቫይዘርነት የሚመደበው የኢንስቲትዩቱ ባለሙያ ሲሆን ስለ ምዘናው በቂ


እውቀት ያለው፣ ለኢንስቲትዩቱ ህግና ደንብ ተገዢ የሆነ እና በኢንስቲትዩቱ
የተዘጋጀውን መመልመያ መስፈርት የሚያሟሏ መሆን አለበት፤
2. የተሰማራበትን የምዘና ቁጥጥር ኃላፊነት በአግባቡ የመከታተል፣ የመገምገም እና
ሪፖርት የማድረግ ብቃት ያለው በተጨማሪም መልካም የሙያ ሥነ-ምግባር ያለው
ሊሆን ይገባል፤

14. የምዘና መሳሪያ ዝግጅት ባለሙያ ምልመላና ምደባ

1. የምዘና መሳሪያ ዝግጅት ባለሙያ ከዘርፉ የሙያ ማህበራት፣ ከከፍተኛ የትምህርት


ተቋማት እና ከሚመለከታቸው የፌደራል፣ ከክልል፣ ከከተማ አስተዳደር
ኮንስትራክሽን ቢሮዎች እና መንግስታዊ ከሆኑ የየልማት ድርጅቶች ይመረጣል፤
2. ለአንድ በጀት አመት የምዘና መሳሪያ ያዘጋጀ ባለሙያ ለቀጣይ ሁለት/2 ተከታታይ
አመታት በኢንስቲትዩቱ በሚካሄድ የምዘና መሳሪያ ዝግጅት ላይ መሳተፍ
አይችልም፤

15. የምዘና መሳሪያ አደራጅ ኮሚቴ ምደባ

1. ይህ ኮሚቴ ሁለት/2 አባላትን የሚይዝ ሲሆን የሚመደቡትም ከኢንስቲትዩቱ


ባለሙያዎች ውስጥ በኢንስቲትዩቱ የበላይ ኃላፊ አማካኝነት ነው፤

16. የመዛኝ ባለሙያ ምልመላና ምደባ

1. በመዛኝነት የሚመደበው የኢንስቲትዩቱ ባለሙያ ሲሆን ስለ ምዘናው በቂ እውቀት


ያለው፣ ለኢንስቲትዩቱ ህግና ደንብ ተገዢ የሆነ እና በኢንስቲትዩቱ የተዘጋጀውን
መመልመያ መስፈርት የሚያሟሏ መሆን አለበት፤
17. የፈተና ገምጋሚ እና ውጤት ሰጪ ኮሚቴ ምልመላና ምደባ

1. ይህ ኮሚቴ ሶስት/3 አባላትን የሚይዝ ሆኖ ከኢንስቲትዩቱ ሁለት ባለሙያ እና


ከዘርፉ የሙያ ማህበራት አንድ ባለሙያ በማካተት የሚዋቀር ይሆናል፤
2. ከዘርፉ የሙያ ማህበራት የሚመደቡት የኮሚቴው አባላት አስፈላጊው የትምህርት
ዝግጅት፣ የስራ ልምድ ያላቸው እና በኢንስቲትዩቱ የተዘጋጀውን መመልመያ
መስፈርት የሚያሟሉ መሆን አለባቸው፤
ክፍል 4

የሙያ ብቃት ምዘና ዝግጅትና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት

18. ቅድመ-ምዘና ሂደት


18.1. የሙያ ብቃት ምዘና መሳሪያ ዝግጅት

1. የምዘና መሳሪያ ኢንስቲትዩቱ በሚያዘጋጀው የመጨረሻ የሙያ ደረጃ ሰነድ እና


በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት በኢንስቲትዩቱ በሚመለመሉ የምዘና መሳሪያ
ዝግጅት ባለሙያዎች አማካኝነት ይዘጋጃል፤
2. የተዘጋጀዉ የምዘና መሳርያ በኢንስቲትዩቱ ቋት ዉስጥ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ
ተቀምጦ ለአንድ የምዘና በጀት ዓመት ጥቅም ላይ ይውላል፤
3. በምዘና ቋት ውስጥ የተቀመጡ የምዘና መሳሪያዎች ወይም ጥያቄዎች ኢንስቲትዩቱ
በሚያወጣው ዓመታዊ የምዘና መርሃ-ግብር መሰረት በምዘና መሳሪያ አደራጅ
ኮሚቴ አማካኝነት ለምዘና ዝግጁ ይደረጋሉ፤
4. የሙያ ብቃት ምዘና መሳሪያ ዝግጅት እና መሳሪያውን ለምዘና ዝግጁ የማድረግ
ስራ በዋናነት በሱፐርቫይዘር ክትትል ስር የሚከናወን ይሆናል፤

18.2. የተመዛኞች ምዝገባ

1. መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውም ግለሰብ ኢንስቲትዩቱ በሚያወጣው የምዘና


መርሃ-ግብር መሰረት ለምዘናው የሚጠየቀውን ክፍያ እና አስፈላጊ ሰነዶች
ለኢንስቲትዩቱ በማቅረብ እና የምዘና ማመልከቻ ቅጽ በመሙላት በኢንስቲትዩቱ
ድህረ-ገጽ ወይም ኢንስቲትዩቱ በሚያመቻቸው የመመዝገቢያ ስፍራ በአካል ቀርቦ
ይመዘገባል፤ ከኢንስቲትዩቱ ለምዘናው መመዝገቡን የሚገልጽ የምዝገባ ቁጥር
ወይም እንደአስፈላጊነቱ የምዝገባ ካርድ ይሰጠዋል፤ ለመመዘን የሚመጣ አመልካች
የሚሞላው ቅጽ በዕዝል አንድ ላይ ተቀምጧል፤
2. በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚመዘኑ ሙያዎች እና ተመዛኙ በነዚህ ሙያዎች
ለመመዘን ሊኖረው ስለሚገባው ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት በዕዝል ሁለት ላይ
ተቀምጧል፤
3. ምዘና ለመውሰድ ተመዝግቦ ምዘናውን በተለያየ ምክንያት መውሰድ ያልቻለ
ተመዛኛ በዚህ ንዑስ አንቀጽ አንድ/1 ላይ የተገለጹትን አስፈላጊ ሰነዶች በማቅረብ
እና ከኢንስቲትዩቱ የሚቀርብለትን ቅጾች በመሙላት በድጋሚ መመዝገብ ይችላል፤
4. ተመዛኞች ማንኛውንም ምዘና ከመውሰዳቸው በፊት ዝግጁነታቸውን የሚያረጋግጥ
ግለ ግምገማ ማረጋገጫ ቅጽ እንዲሞሉ ይደረጋል፤
5. የተመዛኞችን ስም ዝርዝር፣ የምዘናውን ቀን እና ስፍራ የሚገልጽ ማስታወቂያ
ምዘናው ከሚካሄድበት አምስት/5 ቀናት ቀደም ብሎ በኢንስቲትዩቱ ደህረ-ገፅ፣
ማህበራዊ ሚድያ ወይም የኢንስቲትዩቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በመልቀቅ
ለተመዛኞች ጥሪ ይደረጋል፤

19. ምዘና ሂደት

1. ምዘና የሚካሄደው ኢንስቲትዩቱ በሚያዘጋጃቸው እና በኢንስቲትዩቱ እውቅና ባገኙ


የምዘና ጣቢያዎች ሲሆን እውቅና በሌላቸው ተቋማት የሙያ ብቃት ምዘና ማድረግ
አይቻልም፤ ቢደረግም የተመዛኞቹ ውጤት በኢንስቲትዩትችን ተቀባይነት
አይኖረውም፤
2. በተቀመጠው የምዘና መርሃ-ግብር መሰረት የምዘና መሳሪያዎች እና ሌሎች
ለምዘናው አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች እና ቁሳቁስ ምዘናው ወደ ሚካሄድባቸው ስፍራ
እንዲሰራጭ ይደረጋል፤
3. የሙያ ብቃት ምዘናው በፅሁፍ፣ በምልከታ፣ በስራ ላይ ምዘና፣ በሲሙሌሽን፣
በፕሮጀክት ወይም በቃለ-መጠይቅ የሚካሄድ ይሆናል፤
4. ምዘናው ከመጀመሩ አስቀድሞ ሱፐርቫይዘር እና መዛኝ በጋራ ሆነው ተመዛኞችን
ወደ ምዘና ጣቢያው በመቀበል ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ወይም የምዝገባ
ካርድ መያዛቸውን እና እያንዳንዱ ተመዛኝ በምዘና ቦታ መያዝ የሌለበትን ምንም
አይነት የመገናኛ ወይም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አለመያዙን እያረጋገጡ በማስገባት
በተገቢው የመፈተኛ ቦታ ያስቀምጣሉ፤
5. በመዛኙ አማካኝነት ከምዘናው ጋር በተያያዘ ለተመዛኞች አጠቃላይ ገለጻ ይሰጣል፤
6. መዛኙ ተመዛኞች በግልጽ በሚያዩት እና ጥርጣሬ በማይፈጥር መልኩ የምዘና
መሳሪያዎችን ከታሸጉበት ፖስታ በመክፈት ለተመዛኞች ይሰጣል፤ የምዘናው
መጀመርንም ይገልጻል፤
7. ተመዛኞች ምዘናው ከተጀመረ እስከ ሰላሳ/30 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ መግባት
የሚችሉ ሲሆን ወደ ምዘናው የገባ ተመዛኝ ምዘናው ከተጀመረ ቢያንስ ለአንድ
ሰዓት ያህል ምዘናው ላይ ሳይቆይ መውጣት አይችልም፤
8. ለምዘናው የተሰጠው ሰዓት እንደተጠናቀቀ መዛኙ ለተመዛኞች የምዘና ሰዓት
እንዳለቀ በመግለጽ ከተመዛኞች የፈተና ወረቀት እና ሌሎች ቅጾችን ይሰበስባል፤
9. መዛኙ የሰበሰበውን የፈተና ወረቀት እና ሌሎች ቅጾች ኢንስቲትዩቱ ለመደበው
ሱፐርቫይዘር ተፈራርሞ ያስረክባል፤
10. ሱፐርቫይዘር ከመዛኝ ተፈራርሞ የተረከበውን የፈተና ወረቀት እና ሌሎች ቅጾች
ለኢንስቲትዩቱ ወይም በኢንስቲትዩቱ ለተዋቀረው የፈተና ገምጋሚና ውጤት ሰጪ
ኮሚቴ ተፈራርሞ ያስረክባል፤

20. ድህረ-ምዘና ሂደት


1. እያንዳንዱ ተመዛኝ ያገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ ብቁ መሆን
አለመሆናቸውን የሚገልጽ ማስታወቂያ እጅግ ቢዘገይ በአምስት/5 የስራ ቀናት
ውስጥ በኢንስቲትዩቱ ድህረ-ገጽ፣ ማህበራዊ ሚድያ ወይም በኢንስቲትዩቱ እና
ምዘና በተካሄደበት የምዘኛ ጣቢያ በሚገኝ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የሚገለጽ ሲሆን
ለቀጣይ አምስት/5 የስራ ቀናት ሳይነሳ የሚቆይ ይሆናል፤
2. በውጤቱ ቅሬታ የሚኖረው ተመዛኝ በመመሪያው ክፍል ስድስት/6 ላይ
በተቀመጠው የቅሬታ አቀራረብ እና አፈታት አግባብ መሰረት ቅሬታውን
ለኢንስቲትዩቱ ማቅረብ ይችላል፤
3. ብቃቱ በምዘና የተረጋገጠ ተመዛኝ ባለሙያ የሙያ ብቃት ምስክር ወረቀት
በኢንስቲትዩቱ በአካል በመቅረብ እና የሚጠየቃቸውን አስፈላጊ ሰነዶች በማቅረብ
መውሰድ ይችላል፤
4. በኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን የሙያ ብቃት ምዘና ማለፍ ያልቻለ ተመዛኝ
ኢንስቲትዩቱ በሚኖረው የምዘና መርሃ-ግብር መሰረት ድጋሚ ምዝገባ በማካሄድ
ብቁ ሆኖ ከኢንስቲትዩቱ የሙያ ብቃት ምስክር ወረቀት እስኪያገኝ ድረስ ምዘናውን
መውሰድ ይችላል፤
5. አንድ በኢንስቲትዩቱ ብቁ ተብሎ የሙያ ብቃት ምስክር ወረቀት የወሰደ ባለሙያ
በየሶስት/3 አመቱ በኢንስቲትዩቱ ብቃቱን እያስመዘነ የምስክር ወረቀቱን ማሳደስ
ይጠበቅበታል፤
ክፍል 5

ስለ ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት

21. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አሰጣጥ እና እድሳት


1. ተመዝነው ብቁ ለሆኑ ተመዛኞች እጅግ ቢዘገይ በአስር የስራ ቀናት ውስጥ የሙያ
ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተዘጋጅቶ መሰጠት ይኖርበታል፤
2. ብቁ የሆነ ባለሙያ የምስክር ወረቀቱን በግንባር በመቅረብ ወይም በህጋዊ ወኪሉ
አማካኝነት በኢንስቲትዩቱ ተመዛኙ ማለፉ እና ማቅረብ ያለበት ሰነዶች
መቅረባቸው ተረጋግጦ መውሰድ ይችላል፤
3. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተመዛኙ በተመዘነበት የሙያ ዘርፍ
በተሳካ ሁኔታ ለመስራት አስፈላጊው ችሎታ፣ እውቀት ወይም ክህሎት እንዳለው
የሚገልጽ መረጃ እንጂ እንደ ስራ ፈቃድ አያገለግልም፤
4. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ህጋዊ ሆኖ የሚያገለግለው ከተሰጠበት
ቀን ጀምሮ ለሶስት/3 አመታት ሲሆን አንድ ተመዛኝ በየሶስት/3 አመቱ ተቋማችን
በሚያመቻቸው የሙያ ብቃት ምዘና ሂደት ውስጥ እየተመዘነ የሙያ ብቃት
ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቱን ማሳደስ ይኖርበታል፤

22. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ይዘት


1. የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሊያካትት የሚገባዉ አጠቃላይ ይዘትና መረጃ
በዕዝል ሶስት የተያያዘ ሲሆን የሚከተሉት ይዘት ይኖረዋል:-
1. የኢንስቲትዩቱ ስም እና አርማ
2. አጠር ያለ ስለ ኢንስቲትዩቱ የህግ መሰረት እና ዓላማ መግለጫ
3. የባለ ምስክር ወረቀቱ ባለሙያ ሙሉ ሥምና አንድ ጉርድ ፎቶግራፍ፣
4. የተመዘነበት የሙያ ደረጃ ዓይነት፣
5. ማረጋገጫ የተሰጠበት ቀን፣
6. የማረጋገጫው ህጋዊነት የሚያበቃበት ጊዜ፣
7. የኢንስቲትዩቱ ኃላፊ ስምና ፊርማ፣
8. የኢንስቲትዩቱ ክብ ማህተም፣
23. ስለ ምትክ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አሰጣጥ
1. ማንኛውም ምትክ ምስክር ወረቀት በአካል ቀርቦ የሚጠይቅ ተገልጋይ
የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት አለበት፤

ሀ. ማንነት የሚገልፅ መታወቂያ፣

ለ. አገልግሎት ክፍያ መፈፀም፣

ሐ. የተመዘነበት አመተ ምህረት፣ የሙያ ሥም፣ ደረጃ እና የኢንስቲትዩቱ


ሥም፣ በአገልግሎት መጠየቂያው ፎርም ላይ መሙላት እና፣

መ. ከሚኖርበት ወይም የምስክር ወረቀቱ ከጠፋበት አካባቢ ከሚገኝ የፖሊስ


ጣቢያ ምስክር ወረቀቱ የጠፋበት ስለመሆኑ የሚገልጽ ደብዳቤ ማቅረብ አለበት

2. በውክልና ለሚጠይቁ ባለጉዳች ከላይ በንኡስ አንቀጽ 23 ንኡስ አንቀጽ 1 ከ(ሀ-መ)


የተቀመጠው እንደተጠበቀ ሆኖ፡-

ሀ. ህጋዊ ውክልና ማስረጃ ዋናውንና ፎቶ ኮፒ፣

ለ. ተወካይ የታደሰ መታወቂያ እና

ሐ. ውክልና ከኢትዮጵያ ውጪ የተሰጠ ከሆነ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል


ማረጋገጥ አለበት።
ክፍል ስድስት

የቅሬታና ይግባኝ አቀራረብና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

24. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ


1. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት በኢንስቲትዩቱ የበላይ ኃላፊ የሚመደቡ ሲሆን ከሙያ

ብቃት ምዘና እና ማረጋገጥ ስርዓት ጋር በተገናኘ የሚቀርብ ማንኛውም ቅሬታ


የሚስተናገደው ለዚህ ኮሚቴ ይሆናል፤
2. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ከሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስራ ክፍል ጋር በቅርበት

እና በትብብር መስራት ይኖርበታል፤


25. ቅሬታ አቀራረብ
1. ማንኛውም ቅሬታ የሚያቀርብ ተመዛኝ ለቅሬታው መነሻ የሆነ ጉዳይ ከተከሰተበት ጊዜ
ጀምሮ በአምስት/5 ቀን ውስጥ ቅሬታው ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይኖርበታል፤
2. በሌሎች ማንኛውም በምዘና ጉዳይ ቅሬታ ካለው በአካል ወይም በጽሁፍ፣ በስልክና ኢ-
ሜይል በመሳሰሉት አማካኝነት ማቅረብ ይቻላል፤
3. ቅሬታው ለኢንስቲትዩቱ ከቀረበለት ከአምስት/5 የሥራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ምላሹን
መስጠት አለበት፤ ሆኖም የቀረበው ከአቅም በላይ ከሆነና አግባብነት ያለው ከሆነ
ቅሬታውን ተከታትሎ የመጨረሻው ውጤት ለቅሬታ አቅራቢው በአስር/10 የሥራ ቀናት
ውስጥ ማሳወቅ አለበት፤
4. በተመዛኝ ምዝገባ ምዘና እና ምስክር ወረቀት አሰጣጥ ላይ የሚቀርቡ ማንኛውም
ቅሬታዎች የሚስተናገዱት በኢንስቲትዮቱ ይሆናል፤
26. የይግባኝ አቀራረብ
1. ቅሬታ አቅራቢው በኢንስቲትዩቱ የተሰጠው ምላሽ ያላረካው ከሆነ ለኢንስቲትዩቱ የበላይ
ኃላፊ በአምስት/5 ተከታታይ የስራ ቀናት ውስጥ ይግባኝ ማቅረብ አለበት፤
2. የኢንስቲትዩቱ የበላይ ኃላፊ ይግባኙን መርምሮ በአምስት/5 የሥራ ቀናት ውስጥ
ውሳኔውን ለይግባኝ አቅራቢው ማሳወቅ ይኖርበታል፤
ክፍል ሰባት

ስለተጠያቂነት

27. በሱፐርቫይዘር ላይ የሚያስከትለው ተጠያቂነት


1. በምዘና መሳሪያ ዝግጅት ሂደት ወቅት ሚስጢር ያወጣ፣ የተረከበውን የፈተና ፓኬጅ
እንዲጎድል ያደረገ፣ ምዘናውን እንዲወስድ በተቋሙ ያልተፈቀደለት ተመዛኝ እንዲመዘን
ያደረገ በከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ይቀጣል፤
2. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ አንድ/1 ከተጠቀሱት ውጪ ያሉትን ተግባርና ሃላፊነት
በአግባቡ ያልተወጣ ሱፐርቫይዘር ጥፋቱ በቀላል የዲሲፒሊን ቅጥት ይቀጣል፤
3. በዚህ መመሪያ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ ከተገኘ
በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ ይሆናል።
28. በምዘና ማሳሪያ ዝግጅት ባለሙያ፣ በምዘና መሳሪያ አድራጅ ኮሚቴ አባላት፣ በመዛኝ
እና በፈተና ግምገማና ውጤት ሰጪ ኮሚቴ አባላት ላይ የሚያስከትለው ተጠያቂነት
1. ሁሉም ከላይ የተዘረዘሩት አካላት በምዘና መሳሪያ ዝግጅት ሂደት ወቅት ሚስጢር ያወጣ፣
የተረከበውን የፈተና ፓኬጅ እንዲጎድል ያደረገ፣ ምዘናውን እንዲወስድ በተቋሙ
ያልተፈቀደለት ተመዛኝ እንዲመዘን ያደረገ በከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ይቀጣል፤
2. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ አንድ/1 ከተጠቀሱት ውጪ ያሉትን ተግባርና ሃላፊነት
በአግባቡ ያልተወጣ ሱፐርቫይዘር ጥፋቱ በቀላል የዲሲፒሊን ቅጥት ይቀጣል፤
3. አንድ መዛኝ በተቋሙ የምዘና አገልግሎት እንዲሰጥ ተመድቦ የማይመቸው መሆኑን
በተገቢው የጊዜ ገደብ ሳያሳውቅ ከቀረ፣ አንድ መዛኝ ለመመዘን በተመደበበት እለት በምዘና
ስፍራው በተገቢው ሰዓት ካልተገኘ፣ እንዲሁም ተቋሙ ለፓናል፣ የምዘና መሳሪያዎችን
ለማበልፀግ፣ ለተጨማሪ ስልጠና ወይም ለሌላ ውይይት ሲጠራው በተጠራበት ዕለት
የማይገኝ ከሆነ ከቀላል እስከ ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ይቀጣል፤
4. በዚህ መመሪያ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ ከተገኘ
በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ ይሆናል፤
29. በተመዛኝ ላይ የሚያስከትለው ተጠያቂነት
1. ሲኮርጅ ወይም ሲያስኮርጅ እጅ ከፍንጅ ከተያዘ፤ በምዘና ወቅት ከሱፐርቫይዘር ወይም
መዛኝ ጋር አንባጎሮ ከፈጠረ፤ በማንኛውም መንገድ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት
ወይም ለማስገኘት የሞከረ፤ ተገቢውን መረጃ ሳያሟላና ክፍያ ሳይፈፅም ለመመዘን የሞከረ
ከሁለት አመት እስከ አምስት አመት ጊዜ ድረስ ለምዘና እንዳይቀርብ ይታገዳል፤
2. በዚህ መመሪያ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ ከተገኘ
በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ክፍል ስምንት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

30. ያለ አድሎ አገልግሎት መስጠት


1. ከኢንስቲትዩቱ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡት ማንኛዉም አመልካቾች ሁሉ
በሃይማኖት፣ በዘር፣ በጾታ፣ በአካል ሰዉነት፣ በብሄር፣ በቀለምና በቋንቋ ምንም አድልዖ
ሣይፈጸም በጠየቁት አገልግሎት መሰረት በኢንስቲትዩቱ እኩል ይስተናገዳሉ፤
2. ኢንስቲትዩቱ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ስራዎች ትክክለኝነትና አድልኦ የሌለበት ተግባር
ስለመሆኑ ያለምንም ጥያቄ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፣ ከህዝብ ጋር ተገቢዉን ዉይይት
ያደርጋል፡፡
31. ክልከላ
1. መዛኝ የምዘና አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ ተመዛኝን መቆጣት፣ ማሸማቀቅ፣ መስደብ፣
ማንቋሸሽ ወይም ማንገላታት የተከለከለ ነው፤
2. መዛኝ የምዘና ቡክሌት ወይም ቅጻ ቅጽ ወይም ቼክሊስት የራስ ለማድረግ ይዞ መሄድ፣
የምዘና መሳሪያ መጣል፣ ከምዘና መሳሪያ መቅዳት የመሳሰሉትን ተግባራት መፈጸም
የተከለከለ ነው፤
3. ተመዛኙ ምዘናውን በቡክሌቱ ላይ በተጠቀሰው የመስሪያ ሰዓት ገደብ መሰረት ሰርቶ
ማጠናቀቅ፤ በቡክሌቱ ከተጠቀሰው የጊዜ ገደብ በላይ ምዘናውን ለመስራት መሞከር
የተከለከለ ነው፤
4. ተመዛኙ ቡክሌቱንና ሌሎች ምዘናውን የሰራባቸውን ወረቀቶች ከመፈተኛ ክፍል ይዞ
ለመውጣትና ለመውሰድ መሞከር የተከለከለ ነው፤
5. ተመዛኙ ክፍል ውስጥ ምዘናውን በሚሰራበት ጊዜ ከሌላ ተመዛኝ መኰረጅ /መቅዳት/
ወይም ከተፃፈ ወረቀት ላይ ወይም ከሲዲ /ፍላሽ ዲስክ/ ላይ ለመገልበጥ መሞከር ወይም
ለሌላ ተመዛኝ መልስ ማስኮረጅ የተከለከለ ነው፤
6. ተመዛኙ ወደ ምዘና ክፍል ሲገባ ስክሪፕቶ፣ እርሳስ፣ መቅረጫ፣ ላጲስ፣ መታወቂያ ካርድ
ከመሳሰሉት ውጪ መጽሀፍ፣ የተጻፈበትም ሆነ ንጹህ ወረቀት፣ ማስታወሻ ደብተር፣
ሲዲ፣ ፍላሽ ዲስክ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ /ሞባይል/፣ የፎቶ ግራፍ ካሜራና የተለያዩ
ስለታምና የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት ፈጽሞ የተከለከለ ነው፤
7. ለማንኛውም ምስክር ወረቀት እንዲረጋገጥለት ለሚፈልግ ተገልጋይ የተፋቀ፣ የተሰረዘ፣
የተደለዘ ወይም በትክክል ለማይታይ የሙያ ብቃት ምስክር ወረቀት ማረጋገጫ መስጠት
የተከለከለ ነው፡፡
32. የመተባበር ግዴታ
8. ማንኛውም የሚመለከተው ሰው ኢንስቲትዩቱ በዚህ መመሪያ የተሰጡትን ዓላማዎች
ለማሳካት በሚያደረገው እንቅስቃሴ የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡
33. ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው መመሪያዎች
9. ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረኑ መመሪያዎች ወይም ልማዳዊ አሰራሮች በዚህ መመሪያ
በተሸፈኑት ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖራቻም፡፡
34. መመሪያውን ስለማሻሻል
10. ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መመሪያውን ማሻሻል ይችላል፡፡
35. የተፈጻሚነት ጊዜ
11. ይህ መመሪያ ______ ቀን _____ ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

ኢ/ር ታምራት ሙሉ

በኢፌድሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት

ዋና ዳይሬክተር
ዕዝል አንድ - በተመዛኙ የሚሞላ የምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ

አጠቃላይ የአመልካች መረጃ


1 ሙሉ ስም ከነ አያት
2 የትውልድ ቀን (ቀን/ወር/ዓመት)
ፎቶ
3 ጾታ
4 ዜግነት
አድራሻ
5
ክልል ________ ከተማ ________ ዞን/ክፍለ ከተማ _________ ወረዳ ________
6 ስልክ
7 ኢሜል
የትምህርት መረጃ
አድራሻ የትምህርት የትምህርት የተመረቁበት
የትምህርት ተቋም ስም
ሀገር ከተማ ደረጃ ዓይነት ዓምት
1
2
3
የስራ ልምድ መረጃ
አድራሻ የስራ
የመስሪያ ቤት ስም በተቋሙ የሰሩት ጊዜ
ሀገር ከተማ መደብ
1
2
3
ለመመዘን የሚፈልጉት ሙያ
1
በምዝገባ ቅጹ ላይ ያቀረብኩት መረጃ እውነተኛና እና ትክክለኛ መሆኑን ከዚህ በታች በፊርማዬ አረጋግጣለሁ።
የአመልካች ሙሉ ስም _________________________________
ቀን _________________
ፊርማ _______________
ዕዝል ሁለት - በኢንስቲትዩቱ የሚመዘኑ ሙያዎች እና ብቁ ለመባል የተቀመጡ መስፈርቶች

ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት መስፈርት


ተ.ቁ ሙያ
ከተመሳሳይ ዘርፍ ክሌላ ዘርፍ
ባችለር ዲግሪ በሲቪል
ስትራክቸራል ምህንድስና ማስተር ዲግሪ በስትራክቸራል
1
መሃንዲስ ባችለር ዲግሪ በስትራክቸራል ምህንድስና
ምህንድስና
ባችለር ዲግሪ በሲቪል
ማስተር ዲግሪ በጂኦቴክኒካል
2 ጂኦቴክኒካል መሃንዲስ ምህንድስና
ምህንድስና
ባችለር ዲግሪ በጂኦሎጂ
ባችለር ዲግሪ በሲቪል ማስተር ዲግሪ በሃይዌይ
3 ሃይዌይ መሃንዲስ
ምህንድስና ምህንድስና
ማስተር ዲግሪ በሃይድሮሊክ
ባችለር ዲግሪ በሲቪል
(ዋተር ሰፕላይ እና
ምህንድስና
ኢንቫይሮመንታል፣ ሳኒቴሽን
4 ሳኒታሪ መሃንዲስ ባችለር ዲግሪ በሃይድሮሊክ እና
ምህንድስና እና ተያያዝ የሆኑ
ዋተር ሪሶርስ እና ተያያዥ
እንደ ክላይሜት ቼንጅ እና
ፊልዶች
ዴቨሎፕመንት
ማስተር ዲግሪ በሃይድሮሊክ
ባችለር ዲግሪ በሲቪል
(ዋተር ሰፕላይ እና
ምህንድስና
ኢንቫይሮመንታል፣ ሳኒቴሽን
5 ሃይድሮሊክ መሃንዲስ ባችለር ዲግሪ በሃይድሮሊክ እና
ምህንድስና እና ተያያዝ የሆኑ
ዋተር ሪሶርስ እና ተያያዥ
እንደ ክላይሜት ቼንጅ እና
ፊልዶች
ዴቨሎፕመንት
ባችለር ዲግሪ በኮንስትራክሽን ማስተር ዲግሪ በኮንስትራክሽን
6 ኮንስትራክሽን ማናጀር ቴክኖሎጂ/ምንድስና እና ቴክኖሎጂ/ምንድስና እና
ማኔጅመንት ማኔጅመንት
ባችለር ዲግሪ በኮንስትራክሽን
ቴክኖሎጂ/ምንድስና እና ማስተር ዲግሪ በኮንስትራክሽን
ኳንቲቲ ሰርቬየር
7 ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ/ምንድስና እና
ወይም ኦፊስ መሃንዲስ
ባችለር ዲግሪ በሲቪል ማኔጅመንት
ምህንድስና
ባችለር ዲግሪ በኮንስትራክሽን
ማስተር ዲግሪ በኮንስትራክሽን
ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ/ምንድስና እና
8 ቴክኖሎጂ/ምንድስና እና
መሃንዲስ ማኔጅመንት
ማኔጅመንት
ባችለር ዲግሪ በሲቪል
ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት መስፈርት
ተ.ቁ ሙያ
ከተመሳሳይ ዘርፍ ክሌላ ዘርፍ
ምህንድስና
ባችለር ዲግሪ በሰርቬይንግ/
ጂኦማቲክስ ወይም ከተለያየ ማስተር ዲግሪ በሰርቬይንግ/
9 ሰርቬየር ትምህርት ቤት ቴክኒካል ብቃት ጂኦማቲክስ ወይም ተመሳሳይ
የያዙ ተመሳሳይ ፊልዶች እና ፊልዶች
ልምዶች
ማስተር ዲግሪ በላንድስኬፕ
10 ላንድስኬፕ አርክቴክት ባችለር ዲግሪ በአርክቴክቸር
አርክቴክቸር
11 አርክቴክት ባችለር ዲግሪ በአርክቴክቸር ማስተር ዲግሪ በአርክቴክቸር
ባችለር ዲግሪ በኤሌክትሪካ ማስተርስ ዲግሪ በኤሌክትሪካል
12 ኤሌክትሪካል መሃንዲስ
ምህንድስና ምህንድስና
ባችለር ዲግሪ በሜካኒካል ማስተርስ ዲግሪ በሜካኒካል
13 ሜካኒካል መሃንዲስ
ምህንድስና ምህንድስና
ባችለር ወይም ማስተር ዲግሪ
14 ኢንተሪየር ዲዛይነር ባችለር ዲግሪ በአርክቴክቸር
በአርክቴክቸር
ባችለር ዲግሪ በሲቪል
ምህንድስና
ማስተር ዲግሪ በማቴሪያል
ባችለር ዲግሪ በኮንስትራክሽን
ምህንድስና
15 ማቴሪያል መሃንዲስ ቴክኖሎጂ/ምህንድስና እና
ማስተር ዲግሪ በጂኦሎጂ
ማኔጅመንት
ምህንድስና
ባችለር ዲግሪ በጂኦሎጂ/
ጂኦሎጂ ምህንድስና
ዕዝል ሶስት - የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት

በኢ.ፌ.ድ.ሪ. የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚንስቴር

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት

የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት Professional Certificate of Competence


የኢትዮጵያ ዴደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የአስፈጻሚ Construction Management Institute by Virtue Vested in It by
አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ______ Definitions of Power and Duties of the Executive Organs of
አንቀጽ ______ ለኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት
Federal Democratic Republic of Ethiopia Proclamation Number
በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት ለአቶ/ወ/ሮ/ወ/ሪት
_____________ Article Mr./Ms. __________ Having Fully
_______________ ተገቢውን የብቃት ደረጃ በ ____________
Satisfied the Requirements Here by Registered and Licenced as
ሙያ አሟልተው ስለተገኙ ይሄ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር
____________.
ወረቀት ተሰቷል።
Authorized Person ______________
የኃላፊ ፊርማ ________________

ቀን _______________ Date ___________

You might also like