You are on page 1of 12

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የፕሮግራም ምዝገባና የዕውቅና ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የእውቅና አሰጣጥ ስርዓቱ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ
በማሰልጠን የተሰማሩ ተቋማትን በማብቃት ላይ ያተኮር ድጋፍ የሚሰጥና የሚያበረታታ የእውቅና አሰጣጥ
መዋቅር በመዘርጋት የተቋማትን የጥራት ደረጃ መመዘኛ መስፈርት ማስቀመጥና መዘርዘር አስፈላጊ
በመሆኑ፤

ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ አሟልተው እንዲገኙ


ችግሮቻቸውን ለይቶ በማወቅ ድጋፍ መስጠት እና የስኬታቸውን ደረጃ መገምገም፤ ከመስፈርትና መመዘኛ
በታች ለሚያሰለጥኑ ተቋማት የእርምት እርምጃ በመውሰድ ሰልጣኞች የጥራት ደረጃውን ካልጠበቀ
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አቅርቦት እንዲጠበቁ፣ የእውቅና ሰጪ አካልና ተቀባይ ተጠያዊነትን
ለማስፈን ግልጽ የሆነ የአሰራር ስርዓትን እውን ማድረግ በማስፈለጉ፣

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አዋጅ ቁጥር 954/2008 አንቀፅ 43/3 መሰረት ይህ መመሪያ
ወጥቷል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ ‘‘የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የፕሮግራም ምዝገባና የዕውቅና ፈቃድ


አሰጣጥ መመሪያ” ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ
የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፡
1. ‘ሚኒስትር' ማለት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ማለት ነው፡፡
2. ‘ኤጀንሲ' ማለት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 199/2003 የተቋቋመው ቴክኒክና ሙያ
ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ነው፡፡
3. ‘የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ' ማለት ማንኛውም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጥ
ተቋም በተቋሙ የሚሰጣቸውን ፕሮግራሞች በይፋ ለመጀመር የሚያስችል እና የዕውቅና ፈቃድ
ማስረጃ ማግኘት እስከሚጠበቅበት ጊዜ ድረስ የስልጠና ፕሮግራሙን እንዲጀምር የሚሰጥ ፈቃድ
ማለት ነው፡፡

1
4. ‘የእውቅና ፈቃድ' ማለት ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለሚሰጥ ተቋም ዕውቅና ለመስጠት
የሚደረግ የጥራት ማረጋገጫ ሂደት እና ኃላፊነት በተሰጠው የእውቅና ሰጪ አካል አስቀድሞ
የተቀመጡ መለኪያዎችን አሟልቶ መገኘቱን ሲያረጋግጥ የሚሰጥ ፈቃድ ማለት ነው፡፡
5. ‘ፕሮግራም' ማለት አንድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ስልጠና የሚሰጥበት የሙያ
ዘርፍ ነው፡፡
6. ‘የሙያ ደረጃ' ማለት በስራ ዓለም በሚገኙ ሙያተኞች የሚዘጋጅ የሙያ ደረጃ ሲሆን ሰዎች በስራ
ዓለም ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ሊኖራቸው የሚገባውን ብቃት የሚያመለክት ነው፡፡
7. ‘ደረጃ' ማለት አንድ ባለሙያ በስራ መደብ መስራት የሚጠበቅበትን የስራ ውስብስብነት ወይም
ክብደት መጠን የተቀመጡ ስራዎችን የአገር አቀፍ ብቃት ማዕቀፍ መሰረት አድርጎ በሙያ ደረጃ
በተቀመጡ የብቃት አሃዶች/unit of competence/ የሚመደብ ከ 1 እስከ 5 የተለየ ደረጃ ነው፡፡
8. ‘የእውቅና እድሳት' ማለት ትምህርትና ስልጠና የሚሰጥ ተቋም የተሰጠውን ዕውቅና በመጠቀም
ስልጠና ሲሰጥ ቆይቶ የተሰጠው የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ ምክንያት የተቋሙን ወይም የፕሮግራሙን
ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚታደስ እውቅና ማለት ነው፡፡
9. ‘የማሰልጠኛ ተቋማት' ማለት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጡ በፌዴራል መንግሥት፣
በፌደራል ደረጃ በግል፣ በውጪ ዜጐች የሚቋቋሙ እና በሌላ አገር ህግ በተቋቋሙ መንግሥታዊ
ያልሆኑ ድርጅቶች ሥር የሚተዳደሩ ማሰልጠኛ ተቋማት ማለት ነው።
10. ‘የልማት ድርጅት' ማለት በትብብር ሥልጠና ማዕቀፍ የሚሳተፉ ምርት ወይም አገልግሎት
ለመስጠት በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆነ አካል ወይም በግል የተቋቋሙ ድርጅቶች ሲሆኑ
ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችንም ይጨምራል።
11. ‘የሙያ ብቃት' ማለት የተወሰነ ሥራ ለማከናወን ለስራ መደቡ የሚገባውን እውቀት፤
ክህሎትና አመለካከት ይዞ መገኘትን እና ተግባራዊ ማድረግ መቻል ነው
12. ‘የሙያ ብቃት ምዘና' ማለት ተገቢው የሙያ ብቃት ላይ የደረሰ ስለመሆኑ የማረጋገጥ
ተግባር ነው፡፡
13. ‘የሥራ የገበያ ፍላጎት' ማለት ኢንዱስትሪው በሚፈልገው የሙያ ዘርፍ፣ ደረጃ፣ መጠንና
ብቃት ያለው ዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ተፈላጊ የሰለጠነ የሰው ሃይል ነው፡፡
14. ‘እውቅና ሰጪ አካል' ማለት የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጄንሲ ማለት
ነው፡፡
15. ‘እውቅና መሰረዝ' ማለት ከተፈቀደለት ህግና ደንብ ተላልፎ ሲገኝ እውቅናውን ማንሳት
ማለት ነው፡፡
16. ‘እውቅና ማገድ' ማለት ከመመዘኛ መስፈርት በታች ሆኖ የተገኘን ተቋም
እስከሚያስተካክል ሰልጣኞችን ከመቀበል ከ 3 ወር ላልበለጠ ጊዜ ማገድ ማለት ነው፡፡
17. ‘ግብዓት/input(s)/ ማለት በተቋማት ለአንድ ፕሮግራም የሚያስፈልጉ የማሰልጠኛ
መሳሪያዎችና ማቴሪያሎችን የሚይዝ ሆኖ በጥቅሉ ሰብዓዊና ቁሳዊን ያጠቃልላል፡፡

2
18. ‘የስልጠና አሰጣጥ ሂደት/process(es)/ ማለት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና
ተቋማት የሚሰጡት ስልጠና ሰልጣኞችን ለስራ የሚያዘጋጅ እንዲሆን በስራ ገበያው ፍላጎት ላይ
ተመስርቶ በትብብር ስልጠና የተደገፈ ሲሆን ማለት ነው፡፡
19. ‘ዝቅተኛ መለኪያዎች ማለት በዚህ መመሪያ የተቀመጡ መስፈርቶች እና ፈቃድ ሰጪው
አካል የሚያዘጋጀው ስታንዳርድ ማለት ነው፡፡
20. ‘የሥራ አመራር ቦርድ ማለት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ በማስልጠኛ ተቋማት
ደረጃ የሚቋቋም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስርዓትን በበላይነት የሚመራ አካል ማለት
ነው፡፡
21. ‘ቅሬታ' ማለት በፕሮራም ምዝገባ፣ እውቅናና እድሳት ፈቃድ አሰጣጥ እና እውቅና እገዳና
ስረዛ ሂደትና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የሚቀርብ አቤቱታ ማለት ነው፡፡
22. ‘የአገልግሎት ክፍያ' ማለት ለፕሮግራም ምዝገባ፣ እውቅናና እድሳት ፈቃድ የሚከፈል
የአገልግሎት ክፍያ ነው፡፡
23. ‘የበላይ ኃላፊ' ማለት የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር
ማለት ነው፡፡
24. ‘አጣሪ ኮሚቴ' ማለት በኤጀንሲው የበላይ ኃላፊ ከሰራተኞች መካከል የሚቋቋም
የቀረበውን አቤቱታ የሚያጣራና የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ ማለት ነው፡፡
25. ‘ምትክ ፈቃድ' ማለት የእውቅና ፈቃዱ የጠፋበት ወይም የተበላሸበት የማሰልጠኛ ተቋም
በድጋሚ የሚሰጥ ፈቃድ ማለት ነው፡፡
26. ማንኛውም በወንድ ፆታ የተገለፀው አነጋገር ሴትንም ይጨምራል፡

3. የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ መመሪያ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሥርዓቱ ውስጥ በሚሳተፉ በፌዴራል መንግሥት አካላት፣
በፌዴራል ደረጃ በግል፣ በውጪ ዜጐች ለሚቋቋሙ እና በሌላ አገር ህግ በተቋቋሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ
ድርጅቶች ሥር የሚተዳደሩ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

ክፍል ሁለት
የኤጀንሲው ስልጣንና ተግባር፣ የማሰልጠኛ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት

4. የኤጀንሲው ስልጣንና ተግባር


1. ኤጀንሲው በፌዴራል መንግስት አካላት የሚቋቋሙ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ በፌዴራል ደረጃ በግል
ለሚቋቋሙ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ በውጪ ዜጎች ለሚቋቋሙ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ እንዲሁም በሌላ
አገር ህግ በተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስር የሚተዳደሩ ማሰልጠኛ ተቋማት እውቅና
ይሰጣል፡፡
2. የእውቅና አሰጣጥ ግልፅነት በተሞላበት አሰራር እንዲከናወን ያደርጋል፡፡

3
3. እውቅና ለሚሰጣቸው ተቋማት አቅማቸውን ደረጃ በደረጃ እንዲያሳድጉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና
ስልጠና ስትራቴጂ በሚፈቅድ መልኩ ይደግፋል፣ ያበረታታል፡፡
4. እውቅና ለሚሰጣቸው ተቋማት እውቅና ያድሳል፣ ከመመሪያና መስፈርት ውጪ የሚሰሩትን ያግዳል፣
ይሰርዛል፡፡
5. በተቋማት እውቅና አሰጣጥ ዙሪያ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ያያል፣ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
6. እውቅና ለሰጣቸው ተቋማት የሚጠበቅባቸውን የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፍሉ ያደርጋል፡፡
7. ተቋማት እውቅና የጠየቁበት ፕሮግራም በሥራ ገበያ ፍላጎት ጥናት መሰረት መሆኑን ያረጋግጣል፤
8. የሠልጣኞችን ቁጥር፣ የሙያ ብቃት ምዘና ውጤት እና የመሳሰሉትን መረጃዎች ከማሰልጠኛ ተቋማት ይቀበላል፡፡
9. በዚህ አንቀፅ ንዑስ እንቀፅ (8) የቀረቡለትን መረጃዎች እንደአስፈላጊነቱ በህግ ወይም በሌላ አኳኋን እንዲገልጽ
ካልተገደደ በስተቀር በሚስጥር ሊይዛቸው ይገባል።
5. የማሰልጠኛ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት
1. የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መርሃ ግብር በአዲስ መልክ ለመጀመር ወይም ወደሚቀጥለው
ደረጃ ለማሳደግ እና ለማስፋፋት የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ እንዲሁም የፕሮግራሙን ቀጣይነት
ለማረጋገጥ የእውቅና ፈቃድ የማግኘት ግዴታ አለበት፡፡
2. ማንኛውም የማሰልጠኛ ተቋም ስልጠና መስጠት የሚችለው እውቅና ሰጪ አካሉ በሰጠው
የፕሮግራም ዓይነት፣ ደረጃና በተፈቀደለት የሠልጣኝ ብዛት ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡
3. የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ ወስዶ የተሠጠው ገደብ ሲጠናቀቅ የእውቅና ፈቃድ መጠየቂያ
ማመልከቻ ለእውቅና ሰጪ አካላት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
4. የእውቅና ፈቃድ የተሰረዘበት ማሰልጠኛ ተቋም ሠልጣኞች ስልጠናቸውን አግባብነት ባላቸው ሌሎች
ተቋማት እንዲከታተሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
5. የእውቅና ፈቃድ የተሰረዘበት ተቋም ፈቃድ በተሰረዘበት በአንድ (1) ወር ጊዜ ውስጥ የእውቅና
ፈቃድ እና ተያያዥ ሰነዶችን ለእውቅና ሰጪው አካል መመለስ አለበት፡፡
6. ማንኛውም ማሰልጠኛ ተቋም ፈቃድ ለማግኘት የአገልግሎት ክፍያ በቅድሚያ መክፈል ይኖርበታል፡፡
7. ሰልጣኞችን ኤጀንሲው በሚያወጣው ዓመታዊ የቅበላ መሰፈርት መሰረት መቀበል እና
የተቀበላቸውን ሰልጣኞች በምዘና ማብቃት እና ከስራ ጋር እንዲተሳሰሩ ድጋፍ ያደርጋል፤

ክፍል ሶስት

የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ


6. ለምዝገባ ፈቃድ የሚቀርብ ማመልከቻ ሊይዛቸው የሚገቡ መስፈርቶች
1. ማንኛውም የማሰልጠኛ ተቋም የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ ለማግኘት ፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻ ለእውቅና
ሰጪ አካላት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ(1) መሰረት የሚቀርበው ማመልከቻ የሚከተሉትን ማሟላት
ይኖርበታል፡፡

4
ሀ/ የተቋሙ ስምና ዋና አድራሻ፣
ለ/ የተቋሙ ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማ፣
ሐ/ የስልጠና ፕሮግራም ዓይነትና ደረጃ፣
መ/ የተቋሙ የአምስት ዓመት እቅድ፣
ሠ/ አግባብነት ካለው የመንግስት አካል የተሰጠ የኢንቨስትመንትና ንግድ/የበጎ አድራጎት ፈቃድ፣
ረ/ ለፕሮግራሙ የሚያስፈልጉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ግብዓቶችን በመስፈርቱ መሰረት አሟልቶ መቅረብ፣
7. የፕሮግራም ምዝገባ ማመልከቻ መገምገሚያ መስፈርቶች
1. ከትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ የተቋሙ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዓላማና አሠራርን
በተመለከተ

ሀ/ ማንኛውም ተቋም ሠልጣኞችን የሚቀበልበት ሥርዓት ሀይማኖት፣ ብሔርንና ፆታን መሠረት


ያላደረገ መሆን ይገባዋል፣
ለ/ ማንኛውም ተቋም ሠልጣኞችን የሚቀበለው ትምህርት ሚኒስቴር በየዓመቱ ወደ ቴክኒክና ሙያ
ትምህርትና ሥልጠና ለሚገቡ ሠልጣኞች ለየደረጃው የሚያስቀምጠውን የመቀበያ መስፈርት
መሰረት በማድረግ በፈቃድ ሰጪው አካል የተላለፉ ዝርዝር የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን የተከተለ
ይሆናል፣
ሐ/ ተቋሙ የምዝገባ ፈቃድ የሚጠይቅባቸው የፕሮግራም ዓይነት የአገሪቷን የሥራ ኃይል ገበያ ፍላጎትን
መሠረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል፣
መ/ ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ወገኖች ተጠቃሚ በማድረግ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ
ጉዳዮች እኩል የተሳትፎ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡
ሠ/ተቋሙ የሙያ ደረጃዎች እና ስርዓተ ትምህርትን፣ የአሰልጣኞች ብቃትን፣ የማሰልጠኛ ጥሬ
እቃዎችን፣ የስልጠና መሳሪያዎችን፣ ቁሳቁሶችንና የመርጃ መሳሪያዎችን በሙያ ደረጃ
የተቀመጡትን ዝቅተኛ መለኪያዎች የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል፣
2. የአስተዳደራዊ ሰነዶች፣

ሀ/ አካባባዊ የሥራ ገበያ ፍላጎት ጥናት ሪፖርት፣


ለ/ ስልጠና ሊሠጥባቸው በታሰበ ሁሉም ፕሮግራሞች ያሉ ወቅታዊ የኢትዮጵያ የሙያ ደረጃዎች
ሐ/ የንግድ ወይም የኢንቨስትመንት ፈቃድ (የመንግስት ተቋማትን አይመለከትም)፣
መ/ ተቋሙ ሥልጠናውን የሚሰጥበት ህንፃ/ካምፖስ በግል ንብረትነት የተያዘ ወይም በፍትሃ ብሔር ሕግ
አንቀጽ 1731 ወይም በማናቸውም በሕግ ፊት ሊጸና በሚችል ውል ለ 5 ዓመታት እንዲያገለግል
በኪራይ የተገኘ መሆን አለበት፣
ሠ/ የሥራ አመራር ቦርዱ አካላት አወቃቀር (በግልና በመንግስት ተቋማት መካከል ልዩነት ሊኖር
ይችላል)፣
ረ/ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሙ በሥራ አመራር ቦርድ ያለው ተቀባይነት፣

5
ሰ/ የአምስት አመት (5) ስትራቴጂካዊ እቅድ (ተቋማዊ የልማት እቅድ)፣
ሸ/ ለትብብር ስልጠና በአካባቢ ካሉ የልማት ድርጅቶች ጋር የተደረገ የመግባቢያ ስምምነት፤ የትብብር
ስልጠናን በተመለከተ ከተቋሙ ጋር በትብብር የሚሰራው የልማት ድርጅቶች አሰልጣኞችን ከራሱ
ተቋም ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህን በተመለከተም የእውቅና ፈቃድ የሚሰጠው አካል በተቋሙና
በልማት ድርጅቶች መካከል የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነትና አፈፃፀሙን በጥንቃቄ
መመርመር ይጠበቅበታል፡፡
ቀ/ ለፕሮግራሙ የሚሟሉ የስልጠና ማሽኖችና መሳሪያዎች በሙያ ደረጃው በተቀመጠው መሰረት
ሆኖ ለትምህርትና ስልጠናው የተገዙ ወይም የፈቃድ ጠያቂዉ ንብረት ስለመሆናቸው ማረጋገጫ
ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

3. የስርዓተ ትምህርት መስፈርቶች፣


1. አንድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ለሚያካሂደው ስልጠና ፕሮግራም በአግባቡ
የተቀረፀ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ስርዓተ ትምህርት ሊኖረው ይገባል፡፡ በዚህም መሰረት:-

ሀ/ የኢትዮጵያ የሙያ ደረጃን መሠረት ያደረገ ስርዓተ ትምህርት፣


ለ/ ስርዓተ ትምህርትን መሰረት ያደረገ የማሰልጠኛ ማስተማሪያና መማሪያ መሳሪያ
(TTLM)፤
ሐ/ እያንዳንዱ ሞጁል የተሟላ የሞጁል ዓላማ፣ የሞጁል ዲስክሪብሽን፣ የማሰልጠኛ
ዘዴዎችና የምዘና ዘዴዎች በግልጽና በዝርዝር የተዘጋጀለት መሆን አለበት፡፡
መ/ በሀገር ውስጥ ስልጠና ተሰጥቶበት የማይታወቅ ፕሮግራም ከሆነ የገበያ ፍላጎት
ያለው ለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፣ የሙያ ደረጃም ሊዘጋጅለት ፈቃድ
የሚሰጠው ይሆናል፡፡
ሠ/ አግባብነት ያላቸው የማሠልጠኛ ማቴሪያሎች (የማጣቀሻ መፃህፍት ኮምፒውተርና
የኢንተርኔት አቅርቦት፣ ቪዲዮ ቴፖች፣ ወዘተ…)
4. የሥልጠናና የድጋፍ ሠጪ ሠራተኞች

1. የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ሊኖራቸው በሚገባ ተቋማዊ መዋቅር መሰረት


በማድረግ ለእያንዳንዱ የሥራ ደረጃ የተቀመጡትን ተግባራት በአግባቡ ማከናወን የሚያስችል
የሙያ ብቃትና ልምድ ያላቸው በቂ የተቋሙ ሰራተኞች ሊሟሉ ይገባል፡፡

ሀ/ የማሰልጠኛ ተቋሙን በበላይነት የሚመሩ ዲንና ምክትል ዲኖች ያላቸው ፕሮፋይልና የትምህርት
ደረጃና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ፣
ለ/ ለፕሮግራሙ የተመደቡ ተመዝነው የበቁና የማሰልጠን ስነ ዘዴ የወሰዱ አሠልጣኞችና ያላቸው
የትምህርት ደረጃ፣
ሐ/ የድጋፍ ሠጪ ሠራተኞች ዝርዝርና ያላቸው የትምህርት ደረጃ፣

6
መ/ የስልጠናና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የቅጥር ወይም ውል ስምምነት፣

5. የማሠልጠኛ ተቋማት አቅርቦትና መሰረተ ልማት

1. የማሠልጠኛ ተቋማት ህንፃዎች ከሚሰጡት የሙያ መስክ አንፃር ለስልጠና ተስማሚ እና ለአካል
ጉዳተኞች ምቹ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ የማሰልጠኛ ተቋም የሚከተሉትን
አቅርቦቶች ማካተት ይጠበቅበታል፡፡
ሀ/ ፀጥታ የሰፈነበትና ለስልጠና አገልግሎት ብቻ የሚውል ምቹ ግቢ ወይም ህንፃ፤
ለ/ የመማሪያ ክፍሎች፣ ወርክሾፖች፣ ላብራቶሪዎች፣ የኮምፒውተር ማዕከል/ክፍል፣
ሐ/ ለፕሮግራሙ የሚያስፈለጉ በቂ ቅጂ ባላቸው መፃህፍት የተደራጀ ቤተ
መጻሕፍት፣
መ/ በሚገባ የተደራጁ የኮምፒውተር ክፍሎች
ሠ/ ቢሮዎች /ለስልጠናና ለአስተዳደር ሰራተኞች/፣
ረ/ ዕቃ ግምጃ ቤቶች፣
ሰ/ የመፀዳጃ ክፍሎች፣ (የሴቶች እና የወንዶች ተለይተው)፣
ሸ/ በየወርክሾፑ የመጀመሪያ ሕክምና ዕርዳታ መስጫ፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ
መከላከያና መቆጣጠሪያ፣
ቀ/ አንድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ከ 500 ሜትር በላይ
የሚራራቁ ሁለት የማሠልጠኛ ቦታዎች ካሉት እንደ ሁለት ግቢ የሚቆጠር ሲሆን
እያንዳንዱ ግቢም ራሱን ችሎ እንደ ቤተመጻህፍት፣ ወርክሾፖችና በመሳሰሉት
አቅርቦቶች መደራጀት ይኖርበታል፡፡

2. ስልጠና የሚሰጥባቸው ወርክ ሾፖች በቂ ብርሃን የሚያገኙ መሆኑ፣ የሙቀት /ቅዝቃዜ/ ሁኔታ፣
እንዲሁም የወለሉ ክብደት የስልጠና ማሽኖችን የመሸከም ችሎታ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን
ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም የሚከተሉትን መሰረተ ልማት ያሟላ መሆን አለበት፡
ሀ/ የመኪና መንገድ መኖር፣
ለ/ የውሃ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት የተሟላ መሆን፣
ሐ/ የመሬቱ አቀማመጥ ለጎርፍ፣ ለከባድ ንፋስ፣ ለፍሳሽና ለመሳሰሉት የተጋለጠ
አለመሆን፣
መ/ ከስልጠናው ጋር ግንኙነት ከሌላቸው ሌሎች የምርት ወይም አገልግሎት መስጫ
ድርጅቶች የተለየ ቦታ መሆን፣
ሠ/ የማሠልጠኛ ተቋሙ ግቢም ሆነ የተቋሙ ሃብቶች ከአጠቃላይ ትምህርትም ሆነ ከከፍተኛ
የትምህርት ተቋማት ተለይተው ሙሉ ለሙሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራም
ብቻ ማዋል፣

7
8. የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ ስለመስጠት
1. እውቅና ሰጪው አካል የቀረቡለትን ማመልከቻ መርምሮ፡-

ሀ/ በአንቀፅ 7 ስር የተዘረዘሩት መመዘኛዎችን መርምሮ ተሟልቶ ሲገኝ በአንድ ደረጃ ለአንድ ጊዜ


ቅበላ የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ ይሰጣል፡፡
ለ/ መመዘኛዎቹን የማያሟላ ሆኖ ካገኘው የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ ጥያቄውን ውድቅ ያደርጋል፡፡
2. እውቅና ሰጪው አካል በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1(ለ) መሰረት የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ
ጥያቄውን ውድቅ ሲያደርግ ጥያቄው ተቀባይነት ያላገኘበትን ምክንያት ለአመልካቹ ወዲያውኑ
በጽሑፍ መግለፅ አለበት፡፡
3. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1(ለ) መሰረት የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ የተከለከለ አመልካች አስፈላጊ
የሆኑትን መመዘኛዎች በማሟላት እንደገና ማመልከት ይችላል፤
4. ፈቃድ ሰጪው አካል የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ የሰጣቸውን እና ፈቃድ የከለከላቸውን በተገቢ
ሚዲያ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡

ክፍል አራት
የእውቅና ፈቃድ መስጠት፣ ማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣

9. ለእውቅና ፈቃድ የሚቀርብ ማመልከቻ ሊይዛቸው የሚገቡ መስፈርቶች


1. ማንኛውም የማሰልጠኛ ተቋም በአንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1/ሀ መሰረት የፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ
ወስዶ የተሠጠው ጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ የእውቅና ፈቃድ ለማግኘት ፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻ
ለእውቅና ሰጪ አካል ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የሚቀርበው ማመልከቻ የሚከተሉትን ማሟላት
ይኖርበታል፡፡

ሀ/ የተቋሙ ስምና ዋና አድራሻ፣


ለ/ የተቋሙ ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማ፣
ሐ/ የስልጠና ፕሮግራም ዓይነትና ደረጃ፣
መ/ የተቋሙ የአምስት ዓመት እቅድ፣
ሠ/ አግባብነት ካለው የመንግስት አካል የተሰጠ የኢንቨስትመንትና ንግድ/የበጎ አድራጎት ፈቃድ፣
ረ/ ለፕሮግራሙ የሚያስፈልጉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ግብዓቶችን ዝቅተኛ መለኪያዎችን አሟልቶ
መቅረብ፣
10. የዕውቅና ፈቃድ መገምገሚያ መስፈርቶች
1. የተቀባላቸውን ሰልጣኞች በኤጀንሲው ዓመታዊ ዕቅድ በተቀመጠው መቶኛ መሰረት በምዘና
ብቃታቸው የተረጋገጠ ሰልጣኞች፤

8
2. በኤጀንሲው ዓመታዊ ዕቅድ በተቀመጠው መቶኛ መሰረት ብቃታቸው የተረጋገጠ ወደ ስራ የተሰማሩ
ሰልጣኞች፣
3. የተሻሻለ የሙያ ደረጃን (ካለ) ተከትሎ የተሻሻለ ስርዓተ ትምህርትና የማሠልጠኛ ማስተማሪያና
መማሪያ መሳሪያዎች፣
4. ተቋማዊ የልማት እቅድና አተገባበር፣
5. ስልጠና አጠናቀው የወጡ ባለሙያዎች ያሉበትን ሁኔታ የሚያሣይ የየድህረ ሥልጠና ጥናት ሪፖርት
6. ፈቃድ ባለው የሒሣብ ባለሙያ የተደረገ የኦዲት ሪፖርት፣
7. በአካባቢው ካለ ኢንዱስትሪ ጋር ለትብብር ስልጠና የተደረገ ከፕሮግራሙ ጋር ተዛማጅነት ያለው
የመግባቢያ ስምምነት ሰነድና አተገባበር፣
8. በተቋሙ ድጋፍ የተደራጁ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ብዛት፣ የተሰማሩበት የስራ ዘርፍና
ደረጃ የሚያሳይ መረጃ፣
9. የጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ/kaizen/ ስርዓት ትግበራ የሚያሳይ መረጃ፣
10. በድጋፍና ክትትል ወቅት የአካባቢው የሥራ ገበያ ፍላጎት፣ የክትትል ሪፖርቶች፣ ጥራት
ያለው የአመራር ስርዓት ሪፖርትን አስመልክቶ የተሰጡ ግብረ መልሶችና አመላካች መረጃዎች፤
11. የዕውቅና ፈቃድ ስለመስጠት
1. እውቅና ሰጪው አካል የቀረበለትን ማመልከቻ መርምሮ፡-

ሀ/ በአንቀፅ 10 ስር የተዘረዘሩት መመዘኛዎችን መርምሮ ተሟልቶ ሲገኝ ለሶስት (3) አመት


የሚፀና የእውቅና ፈቃድ ይሰጣል፡፡
ለ/ መመዘኛዎቹን የማያሟላ ሆኖ ካገኘው የእውቅና ፈቃድ ጥያቄውን ውድቅ ያደርጋል፡፡
2. እውቅና ሰጪው አካል በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 (ለ) መሰረት የእውቅና ፈቃድ ጥያቄውን ውድቅ
ሲያደርግ ጥያቄው ተቀባይነት ያላገኘበትን ምክንያት ለአመልካቹ በጽሑፍ መግለፅ አለበት፡፡
3. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 (ለ) መሰረት የእውቅና ፈቃድ የተከለከለ አመልካች የፈቃድ አስፈላጊ
የሆኑትን መመዘኛዎች በማሟላት እንደገና ማመልከት ይችላል
4. ፈቃድ ሰጪው አካል የእውቅና ፈቃድ የሰጣቸውን እና ፈቃድ የከለከላቸውን በተገቢ ሚዲያ ለህዝብ
ይፋ ያደርጋል፡፡

12. የእውቅና ፈቃድን ስለማደስ


1. ማንኛውም የማሰልጠኛ ተቋም የእውቅና ፈቃዱ ከመጠናቀቁ ሶስት (3) ወር በፊት የእውቅና ፈቃድ
እድሳት ጥያቄ ማቅረብ አለበት፡፡
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የሚቀርበው ጥያቄ የሚከተሉትን ማሟላት ይኖርበታል፡፡

ሀ/ ተቋሙ በሚሰጠው ፕሮግራም በየዓመቱ የተመዘገቡ አጠቃላይ የሰልጣኞች ቁጥር፤


ለ/ በየዓመቱ የተቀባላቸውን ሰልጣኞች በኤጀንሲው ዓመታዊ ዕቅድ በተቀመጠው መቶኛ መሰረት
በምዘና ብቃታቸው የተረጋገጠ ሰልጣኞች፤

9
ሐ/ በኤጀንሲው ዓመታዊ ዕቅድ በተቀመጠው መቶኛ መሰረት በግልም ሆነ በቅጥር ብቃታቸው
የተረጋገጠ ወደ ስራ የተሳሰሩ ሰልጣኞች ብዛት፤
መ/ ለትብብር ስልጠና ከኢንዱስትሪ ጋር የተደረገ የመግባቢያ ሰነድ፣
ሠ/ በኤጀንሲው ዓመታዊ ዕቅድ በተቀመጠው መቶኛ መሰረት የትብብር ስልጠና በጥራትና በሽፋን
ያለው አፈፃፀም፤
ረ/ የጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ/kaizen/ ስርዓት ትግበራ የሚያሳይ መረጃ፣
ሰ/ የተሸጋገረና ሃብት የፈጠረ ቴክኖሎጂ ብዛት፤
ሸ/ የዕውቅና ፈቃድ እንዲሰጠው ወይም ቀደም ሲል እንዲታደስ ሲጠይቅ ለእውቅና ሰጪው አካል
ከአቀረበው ማመልከቻ ጋር ቀርበው የነበሩትን መረጃዎች፣ የስልጠና ግብዓቶች፣ ሂደቶች እና
ውጤቶች አሁን ያሉበት ደረጃ የሚገልፅ ሪፖርት፤
ቀ/ በህጋዊ ኦዲተር የተመረመሩ የመጨረሻዎቹን ሶስት ዓመታት የተቋሙ የሂሳብ ሪፖርቶች፤

13. የፕሮግራም ምዝገባ፣ እውቅና እና እድሳት ፈቃድ ምስክር ወረቀት መያዝ የሚገባው፡-
ሀ/ የተቋሙን ስምና አድራሻን፣
ለ/ የፕሮግራሙን ዓይነትና ደረጃ፣
ሐ/ የሰልጣኝ ብዛት፣
መ/ ትምህርትን ስልጠናው የሚሰጥበት ቦታ፣
ሠ/ ፈቃዱ የተሰጠበት ቀንና የሚያገለግልበት የጊዜ ገደብ፣
ረ/ ፈቃዱን የሰጠው የሥራ ሂደት ኃላፊ ስምና ፊርማ እና የፈቃድ ሰጪው አካል ማህተም፣ መያዝ
ይኖርበታል፡፡
14. እውቅና ስለሚታገድበት
1. እውቅና ወስዶ በማሰልጠን ላይ ያለ ማንኛውም ማሰጠልኛ ተቋም ከመመዘኛ መስፈርት በታች
እያሰለጠነ መሆኑ በክትትል ሲረጋገጥ፣
ሀ/ እስከሚያስተካክል ከማንኛውም ቅበላ ለሶስት (3) ወር ይታገዳል፡
ለ/ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1/ሀ የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ በስልጠና ላይ ያሉ ሰልጣኞችን
በተመለከተ በ 10 ቀናት ውስጥ መመዘኛውን በማሟላት ስልጠናውን እንዲያስቀጥል
ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡
2. የእውቅና ፈቃድ ሳይታደስ የተሰጠው ጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ እውቅና እስኪታደስ ከማንኛውም ቅበላ ለሶስት (3)
ወር ታግዶ ይቆያል፡
15. እውቅና ስለሚሰረዝበት
1. እውቅና ሰጪው አካል ከሚከተሉት ምክንያቶች በአንዱ ሊሰርዝ ይችላል፡፡
ሀ/ የፕሮግራም ምዝገባ፣ እውቅና ፈቃድና እውቅና እድሳት የተሰጠው በሀሰተኛ ማስረጃ ላይ ወይም
መሆኑ ሲረጋገጥ፤

10
ለ/ ፈቃድ ሰጪው አካል በአንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 1/ለ መሰረት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት
በማስጠንቀቂያ በተገለፀው የጊዜ ገድብ ጉድለቶችን ሳያስተካክል ሲቀር፤
ሐ/ እውቅና ሰጪው አካል በሚያደረርገው የመስክ ምልከታ የሚያገኛቸውን ጉደለቶችን
እንዲያስተካክል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶት በማስጠንቀቂያ በተገለፀው የጊዜ ገድብ ጉድለቶችን
ሳያስተካክል ሲቀር፤
መ/ በፕሮግራም ምዝገባ፣ በእውቅና ፈቃድና በእውቅና እድሣት ወቅት የታየ የመስፈርት ጥሰት፣
ሠ/ በየዓመቱ የሚወጣውን የመግቢያ መስፈርት ያልተከተለ የሠልጣኞች ቅበላ፣
ረ/ የእውቅና ፈቃድ ሳያገኝ በፕሮግራም ምዝገባ ፈቃድ ከአንድ ዙር በላይ ሰልጣኞችን ከተቀበለ፤
ሰ/ ማንኛውም እውቅና ያለው ፕሮግራም በየ 3 አመቱ ካልታደሰ፣
ሸ/ ተቋሙ ሲፈርስ ወይም ሥራውን ሲያቆም፤

2. የእውቅና ፈቃድ የተሰረዘበት ማሰልጠኛ ተቋም ሠልጣኞች ስልጠናቸውን አግባብነት ባላቸው


ሌሎች ተቋማት እንዲከታተሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

3. የእውቅና ፈቃድ የተሰረዘበት ተቋም ፈቃድ በተሰረዘበት በአንድ (1) ወር ጊዜ ውስጥ የእውቅና
ፈቃድ እና ተያያዥ ሰነዶችን ለእውቅና ሰጪው አካል መመለስ አለበት፡፡

ክፍል አምስት
የፈቃድ አገልግሎት ክፍያ እና ቅሬታ አቀራረብ

17. የፈቃድ አገልግሎት ክፍያ


1. ማንኛውም ማሰልጠኛ ተቋም ፈቃድ ለማግኘት የአገልግሎት ክፍያ መክፈል ይኖርበታል፡፡
2. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት የአገልግሎት ክፍያ፡-
ሀ/ ለመኪና ነዳጅ፣
ለ/ ለባለሙያዎች ውሎ አበል፣
ሐ/ እንዲሁም ለፈቃድ ምስክር ወረቀትና ሌሎች ተመሳሳይ ወጪዎችን፣ ይሸፍናል፡፡
3. የአገልግሎት ክፍያ መጠንና የአከፋፈል ሁኔታ በደንብ ቁጥር 954/2008 አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀጽ
3 ስር በተጠቀሱት መሰረት የሚፈፀም ይሆናል፡፡
4. በደንብ ቁጥር ---/2008 አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀጽ 3 ስር የተዘረዘሩት ክፍያዎች በየፕሮግራሙ
የሚከፈል ይሆናል፡፡
5. ለፕሮግራም ምዝገባ፣ እውቅና ፈቃድ እና እውቅና እድሳት የሚጠይቅ የማሰልጠኛ ተቋም በቅድሚያ
በደንብ ቁጥር ---/2008 አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀጽ 3 የተወሰነውን የአገልግሎት ክፍያ ለኤጀንሲው
ፋይናንስ ወይም በአካውንት ቁጥሩ ገቢ በማድረግ ከፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻው ጋር ደረሰኙን
ማቅረብ አለበት፡፡
6. የአገልግሎት ክፍያው ለአገልግሎቱ የተከፈለ እንጂ ፈቃድ ለማግኘት ዋስትና አይሆንም፣

11
18. ቅሬታ አቀራረብ
1. ማንኛውም የማሰልጠኛ ተቋም ፈቃድ እንዲሰጠው ያቀረበው ማመልከቻ ውድቅ የተደረገበት፣
የእውቅና ፈቃድ የታገደበትና እና የተሰረዘበት ውሳኔው በደረሰው በ 30 ቀናት ውስጥ ውሳኔው
እንደገና እንዲታይለት ለእውቅና ሰጪ አካል የበላይ ኃላፊ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡
2. የእውቅና ሰጪ አካል የበላይ ኃላፊ አቤቱታውን መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ አጣሪ ኮሚቴ
ያቋቁማል፡፡
3. በአጣሪ ኮሚቴ የውሳኔ ሀሳብ መሰረት የእውቅና ሰጪ አካል የበላይ ኃላፊ አቤቱታው በቀረበ በ 30
ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፤ ውሳኔውም የመጨረሻ ይሆናል፡፡

ክፍል ስድስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
19. የመሸጋገሪያ ድንጋጌ
ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት የእውቅና ፈቃድ ተሰጥቶት እያሰለጠነ ያለ የማሰልጠኛ ተቋም የፈቃድ
ጊዜ ገደቡ እስኪያልቅ ድረስ በዚህ መመሪያ እንደተሰጠው ይቆጠራል፡፡
20. ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ሕጎች
ይህን መመሪያ የሚቃረኑ መመሪያዎች፣ አሰራርና ልማዶች በዚህ መመሪያ የተሸፈኑ ጉዳዮችን
በሚመለከት ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡
21. መመሪያን ስለማሻሻል
1. ይህን መመሪያ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 954/2008 አንቀፅ 43/3
መሰረት ሚኒስቴሩ ሊያሻሽለው ይችላል፡፡
2. ክልሎች ይህን መመሪያ መነሻ በማድረግ መመሪያ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡
22. መመሪያው የሚጸናበት ጊዜ
ይህ መመሪያ በሚኒስቴሩ ከወጣበት ቀን --------/2009 ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

12

You might also like