You are on page 1of 5

የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ

የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት

"ከመጋረጃ በስተጀርባ" ተውኔት ተምሳሌታዊ ውክልና አስረጂነት ላይ የተዘጋጀ ሂሰዊ ትንተና

ለ Critics ኮርስ ማሟያነት የተሰናዳ

በ፡-

1. ያሬድ መኮንን

2. ሚኪያስ ግርማ

3. ሙሉቀን አረጋ

4. ሰርካለም ጌታነህ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ምስጋና

በቅድሚያ ወጥተውና ወርደው ከመጋረጃ ጀርባ ተውኔት በብዙ ድካም አዘጋጅተው ለተውኔት አፍቃሪያን ለእይታ
ያቀረቡ ደራሲው ቶፊቅ ኑሪ፣ አዘጋጁ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ ተዋንያኑ ይገረም ደጀኔ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ሳጅን መኮንን
ንጉሴ፣ አንዷለም ደጀኔ፣ ኢየሩሳሌም ኃይለ ኢየሱስ፣ ብሩክ ምናሴና ፅዮን ዳኛቸው እንዲሁም የመድረክ ዝግጅት
ባለሙያዎቹ በላይ ኪዳኔ፣ ለማ ጸደቀና ዘውዱ ገ/ማርያም፣ የመብራት ስርጭት ባለሙያው ወርቁ ታምራት፣ የድምጽ
ስርጭት ባለሙያዎቹ ሬድዋን አወልና አምሳሉ ጌታቸው፣ የቁሳቁስና አልባሳት ባለሙያዎቹ የትም ወርቅ በቃሉና
አሰለፈች እንግዳ እንዲሁም ሌሎች በዚህ ተውኔት ዝግጅት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ባለሙያዎች
ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ይህንን ተውኔት አዘጋጅቶ ለተመልካቹ ለእይታ ለማቅረብ ያሳለፏቸው ውጣ ውረዶች በርካታ
መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ከዚህ ተውኔት የተሻለ ስራ ለማቅረብ መትጋትም ይጠበቅባቸዋል፡፡

መግቢያ

ሀገር ፍቅር ቴአትር ከምስረታው ጀምሮ ለዘመናት በየጊዜው ተምሳሌታዊ ስልትን የሚከተሉ ተውኔቶችን በማቅረብ
ይታወቃል፡፡ ለእይታ ቀርበው የተመልካቹን ቀልብ ከሳቡ ተወዳጅ ተምሳሌታዊ ውክልና ካላቸው ተውኔቶች መካከል
በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ የመጀመሪያው ተምሳሌታዊ ተውኔት የሆነውና በቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ተጽፎ
የተዘጋጀውና ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ከጀመረበት 1928 ጣልያን አገራችንን ለቃ እስክትወጣ እስከ 1933 በአገራችን
በታየው ፖለቲካዊ ሁነት ላይ ጭብጡን ያደረገው ̎አፋጀሽኝ̎ ቴአትር ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌሎችም በርከት ያሉ ተምሳሌታዊ
ተውኔቶች በዚሁ በአገር ፍቅር መድረክ ላይ ለተመልካች ቀርበው የተመልካቹን የቴአትር ጥም ማርካታቸው የሚታወስ
ነው፡፡ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በአሁኑ ወቅት ለእይታ ካበቃቸው ተውኔቶች መካከል ከመጋረጃ ጀርባ ቴአትር አንዱ ነው፡፡
ይህ ጽሁፍም ከመጋረጃ ጀርባ ተውኔቱ ተምሳሌታዊ ውክልና አስረጂነት አንጻር ሂስ ያደርገዋል፡፡

ጥቂት ስለ ከመጋረጃ ጀርባ ተውኔት

ከመጋረጃ ጀርባ በቶፊቅ ኑሪ ተደርሶ በዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ አዘጋጅነት በአገር ፍቅር ቴአትር ለእይታ የበቃና
የቧልታይ ዘውግና የተምሳሌታዊ ውክልና ስልትን (Symbolic Representation style) አጣምሮ የያዘ ተውኔት ነው፡፡ ይህ
ተውኔት በ 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትርና ጥበባት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተጽፎና በዶ/ር ተሻለ አሰፋ
ተዘጋጅቶ፤ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተልኮ ቢገመገምም፤ በወቅቱ በነበረው ቢሮክራሲና በተዋንያን የሥነ-ምግባር
ጉድለት፣ ለእይታ ሳይበቃ የቆየው ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ዘውትር እሁድ ከቀኑ በ 8፡00 በሀገር ፍቅር ቴአትር
ለዕይታ በመቅረብ፣ ብዙ ተመልካቾችን በማስተማርና በማዝናናት ላይ የሚገኝ ተውኔት ነው፡፡

ተምሳሌታዊ ውክልና የቴአትር አቀራረብ ስልት ምንድነው ?

ኒቼ የተሰኘው የቴአትር ሊቅ ተምሳሌታዊ ውክልና በፈረንሳይና ሰሜን አሜሪካ ግጥሞች ውስጥ በተሰኘ መጽሐፉ
በ 197 ኛ ቅጂው ላይ ̎የተምሳሌታዊ ውክልና የአቀራረብ ስልትን ̎የድራማ ዓላማው የገሃዱን ዓለም እውነታ ወደ ተውኔቱ
ዓለም አምጥቶ ማሳየት ነው፡፡ ነገር ግን ተምሳሌታዊ ውክልና፤ ድራማ ሊደርስባቸው የማይችላቸውን ረቂቅና ምጡቅ
የሁኑ ሃሳቦችን ገጸ-ባህሪያት በአሳሳላቸው ረቂቅ ማንነት(identity) እንዲኖራቸው አድርጎ የሚያቀርብ የተውኔት
አቀራረብ ስልት ሲሆን እንደ ሀገር፣ ህዝብ፣ አራዊትና ግዑዝ ቁስ አካልን የመሳሰሉ ረቂቃንና ግዑዛን ፍጥረታት በአንድ
በኩል ሰው በሌላ በኩል ማንነታቸውን ሳይለቁ የሚሳሉበት የተውኔት ስልት ነው፡፡̎ በማለት ይገልጸዋል፡፡ ̎

በሌላ በኩል ረዳት ፕሮፌሰር ፈንታሁን እንግዳ የተውኔት ድርሰት አጻጻፍ ዘዴ መጽ|ሐፉ አራተኛ እትም ገጽ 139 ላይ፤
ተምሳሌታዊነትን ሲገልጸው አንድን ነገር ወክሎ የቆመ ከላዕላይ ትርጉሙ ባሻገር ያለው የአንድ ቃል፣ ጊዜ፣ ቦታ፣ ገጸ-
ባህሪ፣ ቁስ፣ ድርጊት፣ ወዘተ ታዕታይ(የታችኛው/ውስጣዊ) ትርጉሙ ማለት ነው፡፡ ተምሳሌት ከቁስ አካሉ ወይም ከረቂቅ
ሃሳቡ ባሻገር ያለው ህሊናዊ ትርጉሙ ነው ̎ በማለት ይገልጸዋል፡፡ እስቲ ከመጋረጃ ጀርባ ተውኔትን ከዚህ አንጻር ለማየት
እንሞክር፡፡

ከመጋረጃ በስተጀርባ ከጭብጣዊ ዳሰሳና ከሴራ አንጻር (Thematic and Plot Exploration)

ከመጋረጃ በስተጀርባ ተምሳሌታዊ ተውኔት እንደመሆኑ፤ ሁለት ሴራዎችን ይዞ የሚጓዝ ባለ አምስት ገቢር ተውኔት
ሲሆን፤ አንድ ወጥ የሆነ ጭብጥም የለውም፡፡ ከአምስቱ ገቢሮች ሦስቱ የተውኔቱ ክፍሎች የሚያጠነጥኑት (ገቢር
1፣3፣5)፤ ዋነኛ የተውኔቱ ክፍል በሆነውና የአገራችን ወቅታዊ ፖሊቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ ባተኮረው
የተውኔቱ ክፍል ላይ ነው፡፡ አንደተደራቢ ሴራ ሆኖ የቀረበው ጭብጥ ደግሞ በየቴአትር ቤቶች ያለውን የባለሙያዎች
የሙያ ስነ-ምግባር ለማሳየት የተሞከረበት የቴአትሩ ገቢር፤ (ገቢር ሁለትና በገቢር አራት) ነው፡፡

የመጀመሪያው የተውኔቱ ጭብጥና ሴራ እቴሜቴ የተባለች ታማሚ እናትና አምስት ልጆቿ እንዲሁም እቴሜቴን
የሚያክመው ሃኪሟ የሚታዩበት የተውኔቱ ክፍል ሲሆን፤ በዚህ ክፍል በተምሳሌታዊ ውክልና የቴአትር አቀራረብ ስልት
ኢትዮጵያና የኢትዮጵያን ብሄሮች እንዲወክሉ ተደርገው የቀረቡ አራት ብሄሮችና ዳያስፖራዎች እንዲሁም
ምዕራባውያን በውክልና እንደ ገጸ-ባህሪያት ተስለው ቀርበዋል፡፡ የዚህ ክፍል ጭብጡም ራስን መሆን፣ አንድነት….ወዘተ
የሚል አንድምታ ሲኖረው፤ በዚህ ውስጥ የተለያዩየ የኢትዮጵያችን ባህላዊ፣ ፖሊቲካዊ፣ ማህበራዊና ታሪካዊ
አንድምታዎችን ለመዳሰስ እንዲሁም በተጠና መንገድና በአግባቡ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ የኢትዮጵያን ብሄሮች
እንዲወክሉ ተደርገው የቀረቡት 5 ገጸ-ባህሪያት ውክልናቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባው ከ 80 በላይ ብሄሮች ባሉበት አገር
ተውኔቱ አራት የተለመዱ ብሄሮችን ይዞ በመቅረብ ነው፡፡
ሁለተኛው ጭብጥ ለህዝቡ ተውኔት ለማቅረብ በልምምድ ላይ የሚገኙ ተዋንያንና ዳይሬክተርን ከመጋረጃው በስተጀርባ
ያላቸውን ህይወት የሚያስቃኝ ሲሆን፤ በከተማችን የተለያዩ ቴአትር ቤቶች ለሙያ የሚሠጥ አናሳ ክብርንና
ባለሙያዎች ወደ ቴአትር ቤት ሲመጡ ምን ፈልገው እንደሚመጡና ምን ዓይነት ባህሪና ስነ-ምግባር እንዳላቸው
የሚያሳየን የተውኔቱ ክፍል ነው፡፡ ይህ የተውኔቱ ክፍል ሁሉንም የፕሮዳክሽን ክሪው በጨረፍታ እንኳን የማይዳስስ
በመሆኑ ምሉዕነት የሚጎለው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከታሪክ አስተምሮ(Historical perspectives)

እዚህ ጋር በዋናነት ሁለት ነገሮችን ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንደኛ የማህበረሰቡን ታሪክ፣ በመቀጠልም የተውኔቱን ታሪክ፡፡
ከማህበረሰቡ ታሪክ አንጻር ከመጋረጃ በስተጀርባ ተውኔት ያለንበትን ክፍለ ዘመን ታሪክ መነሻ አድርጎ በፋርስ ኮሜዲ
ዘውግ ቅርጽ የቀረበ ተውኔት ነው፡፡ ተውኔቱ ያለንበት ዘመን በተምሳሌታዊ ውክልና ይዘት ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ የተውኔቱ
ታሪክ ከተውኔት ታሪክ አወቃቀር አንጻር ገባ ወጣ ሚታይበት ነው፡፡

ከማህበራዊ አተያይ አንጻር( Social-Discourse)

እዚህ ላይ ገጸ-ባህሪያቱ ግላዊና እርስ በእርስ ያላቸው ቁርኝት ተለይቶና ተጠንቶ የቀረበ ነው፡፡ ደራሲውም ሆነ
ዳይሬክተሩ አራቱን የገጸ-ባህሪ የአሳሳል ደረጃ በአግባቡ ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ ተዋንያኑም ያንን በትክክል
ተላብሰውታል፡፡ የገጸ-ባህሪያቱ ግንኙነትም በአግባቡ የተጠናና ምክንያታዊ ይመስላል፡፡ከማኅበራዊ አተያይ አንጻር
ለማንሳት የሚሞክረው በአገራችን የሚታየውን ህብረተሰባዊ እሳቤ ሲሆን፣ ይህም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ግብረ-ገባዊ
ይዘት አለው፡፡ የማህበረሰቡን እሳቤና አተያይ በሚገባና በተረዳ ነገር ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

ባህላዊ ሁነቶች አንጻር /Cultural Context/:- ከ Cultural Context አንጻር ከገጸ-ባህሪያቱ ስም አወጣጥ፣ አነጋገር፣
አስተሳሰብና ከ prop አጠቃቀም ጀምሮ፤ እስከ ድርጊታቸው ድረስ የተቀዱበትን ባህል በቀላሉ መረዳት ቢቻልም
በአግባቡ የተዋሃዱ ናቸው ማለት ግን አይቻልም፡፡

ሰየገጸ-ባህሪያት አሳሳል ከመጋረጃ በስተ ጀርባ ተውኔት

በከመጋረጃ በስተጀርባ ተውኔት በተምሳሌታዊ ውክልና የቀረቡ ገጸ-ባህሪያት የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. እቴሜቴ፡- ታማሚ እናት ተደርጋ የተሳለች ሴት ገጸ-ባህሪ ስትሆን ኢትዮጵያን እንድትወክል ተደርጋ ነው የተሳለችው፡፡
የቀደሙት ባሎቿ/የቀደሙት ነገስታት እና መሪዎች/ በፈጸሙባት ግፍ ታማሚ የሆነች፤ ልጆቿም እርስ በእርስ
የሚነካከሱባት እናት ሆና ተስላለች፡፡

2. ክብሮም፡- ከእቴሜቴ ልጆች አንዱ ተደርጎ የተሳለ ገጸ-ባህሪ ሲሆን፣ የተጋሩ/ትግሬ/ ብሄርን እንዲወክል ተደርጎ የተሳለ
ገጸ-ባህሪ ነው፡፡

3. መገርሳ፡- ሌላኛው የእቴሜቴ ልጅ ሲሆን ኦሮሞን እንዲወክል ተደርጎ የተሳለ ገጸ-ባህሪ ነው፡፡

4. ደምለው፡- ይህም ገጸ-ባህሪ የእቴሜቴ ልጅ ሲሆን ተምሳሌታዊ ውክልናው አማራን እንዲወክ ተደርጎ የቀረበ ገጸ-ባህሪ
ነው፡፡

5. ሙዲን፡- በተምሳሌታዊ ውክልናው ጉራጌን እንዲወክል ተደርጎ የተሳለ የእቴሜቴ ልጅ ገጸ-ባህሪ ነው፡፡

6. ሜሮን፡- ከውጪ አገር የምትመጣ የእቴሜቴ ልጅ ስትሆን ዳያስፖራውን እንድትወክል ተደርጋ የተሳለች ሴት ናት፡፡
7. ዶክተር ዊሊያም ጃክሰን፡- እቴሜቴን ለማከም ከውጪ የሚመጣ በተምሳሌታዊ ውክልናው ምዕራባውያንን የሚወክል
ገጸ-ባህሪ ነው፡፡

ገጸ-ባሪያቱ እርስ በእርስ ያላቸው መስተጋብር ስመለከት፤ አንዱ ከአንዱ ጋር ያላቸው የተጠናና ቀልብን የሚገዛ በእውነታ
ላይ የተመሰረተ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ግን Ethno-centric view ን በሚያንጸባርቅ መልኩ አንዱ ገጸ-ባህሪ
ሌላው ላይ ሲያቀርብ ተስተውሏል፡፡ ለአብነትም ደምለው ክብሮም ላይ፣ ክሮም መገርሳ ላይ ሲያነሱት የነበረውን
መጥቀስ ይቻላል፡፡

በከመጋረጃ በስተጀርባ ተውኔት ውክልናዎችን እናያለን፡፡ እነዚህ ውክልናዎች ግን ወጥነትና ቅቡልነት ይጎላቸዋል፡፡
የሚከተሉት በውክልና ወቅት ቢሟሉ ለተውኔቱ ሙላትን ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው፡፡

 እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሄሮች ከ 80 በላይ ሆነው ሳለ አራቱን ብቻ በውክልና በመውሰድ የኢትዮጵያን


ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችሮችን ይፈታሉ ብሎ ማቅረብ ሌሎቹስ ብሄሮች የሚለውን ጥያቄ ያጭራል፡፡

 ከተውኔቱ እንደምንረዳው ገጸ-ባህሪያቱ እርስ በእርስ አይተዋወቁም፡፡ አንተ ማነህ፣ አንተ ማነህ ሲባባሉ እናያለን ይህም
ማለት ላለፉት 3000 ዓመታት አብረው የኖሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች/ብሄሮች/ አይተዋወቁም እንደማለት ነው፡፡ ይህም
ትልቅ ታሪካዊና ማንነታዊ ተቃርኖን ይፈጥራል፡፡

 ሌላው የገጸ-ባህሪያቱ ውክልና/level of characterization/ ላይ ግድፈቶችና አላስፈላጊ ማጋነኖች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ


ትግሬው እኔ ያልኩት ካልሆነ፣ ኦሮሞው ቦቲ ማድረግ ጆሮ መኮርኮር፣ አማራው መነጫነጭ…….ወዘተ…

ከዝግጅት አንጻር

አርስቶትል የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ ስነ-ውበትን ሲተረጉመው አንድ ቁስ የተገነባበት/የተሰራበት/ ነገሮች መመጣጠን
ነው ይለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ከመጋረጃ በስተ ጀርባ ተውኔታዊ አወቃቀርና mise en scene/ everything on stage/
አመጣጥኖና አይነ-ግቡ አድርጎ ከማቅረብ አንጻር ስንመለከት…..ከ stage balance, movement, line and
composition አንጻር በተደጋጋሚ ግድፈቶችንና መድረኩን በአንድ በኩል ገልብጦ የማቅረብ ነገር በተደጋጋሚ
ተስተውሏል፡፡ አዘጋጁ አውቆም ይሁን ሳያውቅ፣ በማስተዋልም ይሁን ሳያስተውል በተደጋጋሚ የስነ-ዝግጅትን መርህ
በማፍረስና መድረኩ ሚዛኑን እንዲያጣ ሲሆን ተስተውሏል፡፡ ይህም ለሚመለከተው ሰው ውበትን አጥቶ
እንዲጎረብጠው ያደርገዋል፡፡

የመድረክ ግብዓት አጠቃቀም /Stage business and Props/፡- መድረኩ ላይ በተለያየ ቦታ የተቀመጡ ቁሳቁሶች
ያለምክንያት በአንደኛው የመድረክ ክፍል ተከምረው ይስተዋሉ ነበር፡፡ ምጣኔ ይጎላቸው ነበር፡፡ ይህም ለዓይናችን
ምቾትን ይነሳ ነበር፡፡

የመድረክ ሚዛን/Stage Balance/፡- ሁለት ዓይነት የ Stage Balance አሰራር አለ፡፡ ሚዛናዊ/symmetric/ እና
ኢሚዛናዊ/asymmetric/:: እንደሚታወቀው ሚዛናዊ symmetric stage balance፡፡ ዓይነ ግቡ ከመሆኑ አንጻር ከቤት
ውስጥ ቁሳቁሶች ጀምሮ ገጸ-ባህሪያት በአንድ በኩል በብዛት ተከምረው ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ደግሞ መድረኩን ወደ አንድ
በኩል ገልብጦታል፡፡

Movement ፡- በመርህ ደረጃ ገጸ-ባህሪያት በምክንያት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ነገር አንድ አንድ ገጸ-
ባህሪያት የሰውን ዓይንና ሃሳብ በሚሰርቅ መልኩ ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል፡፡ ምሳሌ- ሜሮን እግሯን በተደጋጋሚ
ታንቀሳቅስ ነበር፡፡

የመብራት ግብዓት/Stage Light:- ከመብራት አንጻር ለዓይን የሚስማማና ለኮሜዲ ዘውግ የሚመጥን መብራት
ሲጠቀም ተስተውሏል፡፡
የድምጽ ግዓት/Sound/፡- ከድምጽ አኳያ ተገቢ የሆኑ ድምጾች ለተገቢ ዕይታ ሲጠቀሙ አስተውለናል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ ከመጋረጃ ጀርባ ተውኔት ተምሳሌታዊ ውክልናን ይዞ የቀረበ ቴአትር ነው፡፡ እኛ እንደ ቡድን ከላይ
የተጠቀሱ ጥንካሬና ድክመቶችን በዚህ ቴአትር ውስጥ ተመልክተናል፡፡ ከኛ በኋላ ከመጋረጃ ጀርባ ተውኔት ላይ ሂስ
መሰንዘር የሚፈልግ ማነኛውም ሰው የራሱን ሂስ መስጠት ይችላል፡፡

You might also like