You are on page 1of 2

ሰው ምንድን ነው ?

ሰው ማለት ነፋሳዊነት፣ እሳታዊነት፣ ውኃዊነት፣ መሬታዊነት ባሕርያት ያሉት በነፍስ ተፈጥሮውም ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት
የሆነች ነፍስ ያለችው ፍጥረት ነው፡፡ እንዲህ ብለን ግን የሰውን ተፈጥሮ ጠቅልለን መናገር አይቻለንም፡፡ ምክንያቱም ሰውን
ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ እጅግ ልዩ በሆነ መልኩ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮአልና፡፡ ስለዚህም ቅዱሳን አባቶች
እንዲህ ብለው ሰው ለሚለው ስያሜ ትርጓሜ ይሰጡታል፡፡

ከስጋ አንጻር

ሰው ከሥጋ አንጻር በባህርይው ከ አራቱ ባህሪያተ ሥጋ ማለትም ከ እሳት መሬት ውሃ እና ነፋስ የተፈጠረ በመሆኑ የጊዜ
ገብደ የተቀመጠለት የሚራብ የሚጠማ የሚደክም የሚዎድቅ የሚነሳ እንደሁም የሚሞት ባህርይ ያለው ፍጥረት ነው፡፡

መልክ (አርአያ) ማለትም ነው

መልክ (አርአያ) ማለት ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስል ዘንድ በተፈጥሮ የተሰጡት ባሕርያት ናቸው፡፡ እነዚህ ባሕርያት
ከሰው ፈጽሞ የሚወሰዱ አይደሉም፡፡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች መልክ (አርአያ) ለሚለው ቃል ትርጉም ሲሰጡ ሲለያዩ ይታያሉ፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘፍጥረትን በተረጎመበት ድርሳኑ ላይ መልክ (አርአያ) ማለት ለሰው በተፈጥሮ ፍጥረታትን
ለሚገዛበት ባሕርይው የተሰጠው ስያሜ ነው ይላል እርሱ (ሙሴ) በእግዚአብሔር መልክ ሲል በምድር ያሉትን ሁሉ ሰው
የሚገዛቸው መሆኑን የሚያመለክተን ነው፡፡ በምድር ላይ ከሰው በላይ የሆነ ፍጥረት የለውም ይላል፡፡

አምሳል ማለትም ነው

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እኛ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር መልክ(አርአያ) የመፈጠራችን ዓለማው እግዚአብሔርን እንደ
ችሎታችን መጠን እርሱን መስለን እንመላለስ ዘንድ ነው ይላል፡፡ ከዚህ ተነሥተን ምሳሌ (አምሳል) ስንል በተፈጥሮ የተሰጠንን
ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ ምሳሌ (አምሳል)ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር
ነው፣ ትሑትና የዋህ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ
ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም
የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል፡፡

ከነፍስ አንጻር

ሰው በነፍስ ተፈጥሮው ነጻ ፈቃድ፣ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታ እንዲሁም ሓላፊነት የሚሰማው ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡
በእነዚህ ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡ሰው ሰማያዊት አካል ስላለችው ረቂቁን ዓለም የመረዳት ችሎታ ሲኖረው
ምድራዊውም አካል ስላለው ምድራዊውም እውቀት አለው፡፡ ሰውን ከሰማያውያን መላእክትና ከምድራውያን መላእክት ጋር
ስናስተያየው ለሁለቱም ዓለማት እንግዳ እንዳልሆነ በሁለቱም ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮአዊ ባሕርይ እንዳለው፣
የሰማያውያንንም የምድራውያንንም እውቀት ገንዘቡ ያደረገ ፍጥረት መሆኑን ስናስተውል በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ
መፈጠሩን እንገነዘባለን ፡፡

አለማዊው ጥናት እንደሚያስረዳው

ሰው ልብስ ሳይለብስ ዕራቁቱን ወደዚህ ዓለም የመጣ፣ ምንም የዘመኑ ዕውቀት የሌለው፣ ቀስ በቀስ በልምምድ ወደ ሥልጣኔ
የመጣ፣ ከአውሬ፣ ከፀሐይና ከዝናብ ራሱን ለማዳን በጫካ ከመኖር በዋሻ ወደ መኖር የጀመረ፣ በዋሻ ከመኖር ቤት ሠርቶ ወደ
መኖር፤ ከዕራቁትነት ወደ ልብስ መልበስ፤ በእንጨት ከመቆፈር በዶማ፣ በዶማ ከመቆፈር በበሬ ማረስ፣ በበሬ ከማረስ
በትራክተር ማረስ ያደገ፤ በእግር ከመሄድ በእንሰሳ መሄድ፣ ከዚያም በመኪና፣ በአውሮፕላንና ወደ ህዋ በመንኮራኩር መሄድ
የቻለ ሰው፣ አስደናቂ ፍጡር፣ ክቡር ፍጡር፣ እንደዚሁም አምላኩን በመታዘዝ መኖር ያልቻለ ደካማ፣ራሱን በራሱ ለማጥፋት
(በሚሠራቸው የጦር መሣሪያ) የጀመረ አሳዛኝ፣ እንደሆነ የሚጻፉለት ታሪኮቹያስረዳሉ፡፡

መንፈሳዊው(መጽሐፍ ቅዱሳዊው) ጥናት እንደሚያስረዳው

ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስንመጣ ሰው አስደናቂ የሆነ ጅማሬ ያለው፣ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ፣
ከፍጥረታት ሁሉ የላቀ ክቡር ፍጥረት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሰው ልጅ ላለው ጥያቄ ሁሉ መልስ የሚሆን
እንደያዘ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ በፈጠረበት መጽሐፍ ውስጥ በቃሉ እንዲህ በማለት የሚናገረውን
በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 1፡26-27 እንመልከት፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን
እንፍጠር፣ … እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፣ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፣ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው››
ይላል፡፡መጽሐፍ ቅዱሳችን በዚህ መልኩ የሰው ጅማሬ በእግዚአብሔር እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል፡፡ በመቀጠልም ስንመለከት
‹‹እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው ባረካቸውም፡፡
ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው›› (ዘፍ.5፡2) በማለት ሰው በእግዚአብሔር የተፈጠረ የእጁ ሥራ እንደሆነ
ያረጋግጥልናል፡፡

ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጠረ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እግዚአብሔር እንደ ሰው እጅ፣ እግር፣ ዓይን፣
ጆሮ… የመሳሰሉት ሁሉ አሉት ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ‹‹መልክና›› ‹‹ምሳሌ›› የሚለው አካልን የሚያመለክት ሳይሆን
አስተሳሰብን፣ እውቀትን፣ ሞራላዊ ሁኔታንና የማስተዳደር ችሎታን የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ብሎ
ከባረካቸው በኋላ ‹‹… ምድርንም ሙሉአት ‹ግዙአትም› …›› (ዘፍ.1፡28) በማለት የሚናገረው ሐሳብ ማስተዳደርን
ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ ፍጥረትን ከፈጠረ በኋላ፣ አዳምንና ሔዋንን የፍጥረት
ገዥ አድርጎ ኃላፊነት ሲሰጣቸው፤ በምዕራፍ ሁለት ላይ የገነት ጠባቂ አድርጎ እንደ አስቀመጣቸው ቃሉ ያሳየናል፡፡ሐዋርያው
ጳውሎስም በመልእክቶቹ ‹‹…እንደ እግዚአብሔር ምሳሌየተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ›› (ኤፌ.4፡21-24)፣ ‹‹….
የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል›› (ቆላ.3፡10) በማለት በኃጢአት ምክንያት ተበላሽቶ የነበረውን የእግዚአብሔር መልክ
በክርስቶስ በኩል መልሰው መልበስ (ማግኘት) እንዳለባቸው ለሁለቱም ከተማ አማኞች ያሳስባቸዋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳችን እግዚአብሔር የከበረ እንደሆነ ይነግረናል፤ ነብዩ ኢሳይያስ ሰውን የፈጠረበትን ምክንያት ሲናገርም እንዲህ
ይላል፣ ‹‹ለክብሬ የፈጠርኳቸው›› (ኢሳ.43፡7)፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ረዳት ፈልጎ ሳይሆን ለክብሩ እንደ
ፈጠረን ያመለክታል፤ እርሱን እያመለክን በኅብረት እንድንኖር ተፈጥረናል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 1፡12 ላይ
‹‹…እኛ ለክብሩ ምሥጋና እንሆን ዘንድ ነው›› በማለት በክርስቶስ እንደገና ለእግዚአብሔር ክብር የመፈጠራችንን ዓላማ
ያመለክተናል፡፡ ሰው ከከበረው እግዚአብሔር ጋር በኅብረት እንዲኖር ተፈጥሮአል፡፡

You might also like