You are on page 1of 11

ማውጫ

ክፍል አንድ--- የእግዚአብሄር ቃል እውቀት

 በእግዚአብሄር ቃል የመሞላት ጥቅም


 በቃሉ እውቀት መኖር
 በቃሉ እውቀት ያልተሞላ ሰው ባህሪያት
 ተግባራዊ እይታ

ክፍል ሁለት--- ፀሎት

 ፀሎት ምንድነው
 ፀሎት ምን አይደለም
 የፀሎት ጥቅም
 እንዴት እንፀልይ
 ሳያቋርጡ መፀለይ
 የፀሎት የቃልና የእምነት ግንኙነት
 ተግባራዊ እይታ

ክፍል ሶስት--- በመንፈስ መመራት

 በመንፈስ መመራት ምንድነው


 የመንፈስ ቅዱስ ህብረት ከቅዱሳን ጋር
 የመንፈስ ፍሬ
 በመንፈስ የማይመራ ሰው ባህሪያት
 ተግባራዊ እይታ

ክፍል አራት--- ህብረት

 የህብረት ምንነት
 የጤነኛና ጤነኛ ያልሆነ ህብረት መገለጫዎች
 የጤናማ ህብረት ጥቅም
 ህብረት ያለማድረግ ጉዳቶች
 ከነማን ጋር ህብረት ላድርግ
 ከአስቸጋሪ ሰዎች ጋር ህብረት ማድረግ በእግዚአብሄር እይታ
 ህብረትና ፍቅር
 ተግባራዊ እይታ

ክፍል አምስት--- እግዚአብሄርን ማገልገል


 እግዚአብሄርን ማገልገል ምንድነው
 እግዚአብሄርን ለማገልገል ምን ያስፈልገናል
 ጥሩ አገልጋይ ማነው
 ፀጋዬን እንዴት ልወቅ
 ራእይ በአገልግሎት ውስጥ
ክፍል 1- የእግዚአብሄር ቃል እውቀት

የእግዚአብሄር ቃል ማለት ምን ማለት ነው?

በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሄር ቃል የሚለው ሃረግ የአምላካችንን ማንነት በሚያሳይ ሁኔታ የተለያዩ
ትርጉሞችን ይዞ ይገኛል። ከእነዚህም ውስጥ፦

1) እግዚአብሄር ነገሮችን የሚያጸናበት/ የሚሰራበት ቃል ፦ እግዚአብሄር እንዲሆኑ የሚፈልጋቸውን


ነገሮች ቃሉን በመናገር ወደመኖር አምጥቷቸዋል፤

 “በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤’’ (መዝ


33፡6)

 “እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ።” (ዘፍጥ 1፡3)

2) በነቢያት በኩል ወደሰዎች የሚላከው የእግዚአብሄር ቃል፦ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሄር
ነቢያትን ተጠቅሞ ቃሉን ወደህዝቡ አድርሷል፤

 “ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ


አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤በስሜም የሚናገረውን ቃሌን
የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ።” (ዘዳ 18:18-20)፣

 “ እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም። እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ


ውስጥ አኑሬአለሁ፤እነሆ ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና
ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ አድርጌሃለሁ አለኝ።” (ኤር1:9-10)

3) ኢየሱስ የእግዚአብሄር ቃል ተብሎ ተጠርቷል፦ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሄር እንደሆነ


ከምንረዳባቸው መንገዶች አንዱ በመፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄር ቃል ተብሎ መጠራቱ ነው፤

 “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም


እግዚአብሔር ነበረ።” (ዮሃ1:1 ) ፣

 “በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።


”(ራእይ19:13)

4) መፅሃፍ ቅዱስ ራሱ የእግዚአብሄር ቃል ተብሏል፦ እግዚአብሄር በመንፈሱ መሪነት በአገልጋዮቹ ሰዎች


እንዲፃፍ ያደረገው ቃሉ ራሱ የእግዚአብሄር ቃል መሆኑን ጌታ ኢየሱስ መስክሯል፦

 “እግዚአብሔር፦ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ


ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤እናንተ ግን፦ አባቱን ወይም እናቱን ከእኔ የምትጠቀምበት
መባ ነው የሚል ሁሉ፥አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም
የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ።” (ማቴ፣15:4-6)

 “ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ


የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል
የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ
የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?” (ዮሐ10:34-36)
በመፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል የሚለው ሃረግ ብዙ ፍቺዎችን የያዘ ቢሆንም በዚህ ምእራፍ ቁጥር 4 ላይ
የተጠቀሰውን የተፃፈውን የእግዚአብሔር ቃል ምንነትና ጠቀሜታ እናጠናለን።

የእግዚአብሄር ቃል እውቀት ምን ማለት ነው? (ቆላ3:16)

የሰው ልጆች የእግዚአብሄርን ማንነት ወደማወቅ መድረስ የሚችሉት ቃሉን ሲያውቁ ብቻ ነው። ምክኒያቱም
እግዚአብሄር በቃሉ ውስጥ ከእርሱ ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል እንዲሁም ለህዝቡ ያለውን አላማና ለሰው
ልጆች ያለውን ፍቅር ገልጧል። አንድ ክርስቲያን በህይወት ዘመኑ ሁሉ ከአምላኩ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው
ከፈለገ ከቃሉ ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ሊኖረው ያስፈልጋል፤ ማለትም የየእለት እንቅስቃሴው የእግዚአብሄር ቃል
በሚያዘው መሰረት ይሆን ዘንድ መፅሃፍ ቅዱስን በየእለቱ ማንበብና ያነበበውን መኖር ይገባዋል። ሰው የህይወት
ምልልሱ በቃሉ መሰረት ሲሆን በእግዚአብሄር ቃል ተሞልቷል ይባላል።

1.1 በእግዚአብሄር ቃል የመሞላት ጥቅሞች

መፅሃፍ ቅዱስ ቃሉ በሙላት ይኑርባችሁ በማለት በግልፅ ይመክረናል(ቆላ3:16)። ይህ ቃል በሙላት


በውስጣችን ሲኖር እግዚአብሄርን እየመሰልን ለመኖር የሚያስችሉ የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጠናል። እነዚህም፦

ሀ) እግዚአብሄርን የማያከብሩ ሃሳቦችንና ሀጢአትን ለይተን ለመመከት ይጠቅመናል፦ ዳዊት


በመዝሙሩ፦ “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው።በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ
አታርቀኝ።አንተ እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።” በማለት እግዚአብሄርን እንዳንበድል ቃሉ በልባችን መኖር
እንደሚገባው ያሳስበናል። (መዝ 119:9-11)

ሃጢአት ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ህብረት በማበላሸት መልካም ኣገልጋዮች እንዳንሆን የማድረግ ሃይል አለው፤
ቃሉን ዘወትር የምናነብና የምንመገብ ከሆነ ግን የሃጢኣትን ምንነት፣ መገለጫዎቹንና እግዚአብሄርን መበደል
የሚያመጣውን መዘዝ ጠንቅቀን በማወቅ ጌታን በፍርሃት እናገለግላለን። በሃጢኣት ውስጥ ሆኖ የሚያገለግል
ሰው የእግዚአብሄር ክብር ከኣገልግሎቱ እንደሚሸሽ መፅሃፍ ቅዱስ በስፋት ይነግረናል (ሕዝ 44:10-16) ። ስለዚህ
ቃሉን መሞላት ጌታን እንዳንበድል ያደርገናል።

 ጥያቄ 1:1

 ሀ) የሚከተሉት ጥቅሶች በሃጢአት ውስጥ የሚኖሩ አገልጋዮች የሚገጥማቸውን ክፉ


ነገር ያሳያሉ። ጥቅሶቹን ካነበባችሁ በኋላ አገልጋዮቹ ምን የሚለውን የእግዚአብሄርን
ቃል እንደተላለፉና የበደላቸው ዋጋ ምን እንደሆነ ተንትኑ።

ዳዊት- 2ሳሙ ምእራፍ 11 እና 12 ሰሎሞን -1ነገ 11፡1-1 ፣ ሐናንያና ሰጲራ- ሃዋ 5:1-11

 ሕዝ 44:10-16 ን አንብቡና በሃጢአት ውስጥ የሚኖሩና የማይኖሩ አገልጋዮች


የሚኖራቸውን ልዩነት ተወያዩበት።

ለ) ጠላትን/ዲያቢሎስን ለማሸነፍ ይረዳናል፦ ሰይጣን የእግዚአብሔርን መንግስት ከሚዋጋባቸው


መንገዶች አንዱ ቅዱሳንን በተለያዩ መንገዶች በመሸንገል እና በማታለል ሃጢኣትን እንዲሰሩ በመፈተን ነው።
ጠላት ይህንን ሲያደርግ ቃሉን የተሞላ ሰው ሽንገላውን በቀላሉ ተረድቶ ራሱን ይጠብቃል። ኢየሱስ የዲያቢሎስን
ፈተና ያለፈውና ጠላቱን ያሸነፈው የእግዚአብሄርን ቃል በመጥቀስ በመሆኑ ለተከታዮቹም ትልቅ ምሳሌን
ትቶልናል፤(ማቴ 4፡3-11)።
 ጥያቄ 1.2

 የእግዚአብሄር ቃል ጠላትን ለማሸነፍ እንደሚረዳ የሚያስተምሩ ሌሎች ክፍሎችን ከመፅሃፍ ቅዱስ


በመፈለግ አውጡና በህይወታችን በምን መንገድ ልንተገብረው እንደምንችል አስረዱ።

 ዘፍጥረት ምእራፍ 3 ላይ ያለውን ታሪክ አንብቡና አዳምና ሄዋን በሰይጣን የመታለላቸውና


የውድቀታቸው መንስኤ ምን እንደሆነ ተወያዩበት።

ሐ)በመንፈሳዊ ህይወታችን እንድናድግ ይረዳናል፦

የእግዚአብሄርን ቃል ዘወትር የምንመገብ ከሆነ ጌታ ወደሚፈልገው መንፈሳዊ ደረጃ ማደግና እግዚአብሄርን


የሚያከብር ህይወት ያለው አገልጋይ መሆን እንችላለን።( 2ጢሞ3፡17፣ 1ጴጥ2፡2-3)።

ስጋችን ለማደግና ለመጠንከር በተገቢው ሁኔታ መመገብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ መንፈሳዊ


ህይወታችንም ጌታ ወደሚፈልገው ደረጃ እንዲያድግና የእግዚአብሄር ክብር እንዲገለጥበት ቃሉን
በየእለቱ መመገብ ወይም ማንበብ አለብን።የትኛውም ክርስቲያን በህይወቱ ፍሬን እንዲያፈራ
ተጠርቷል፤ ይህ ፍሬ የሚገለጠው ደግሞ በእግዚአብሄር ቃል የተሞላ ሰው ላይ ነው። የእግዚአብሄርን
ቃል እየተመገበ በመንፈሳዊ ህይወቱ ያደገ ሰው የቃሉ ፍሬ በላዩ ላይ ይገለጣል፣( ዮሃ15፡16፣ መዝ1፡
2-3)። የመንፈስ ፍሬ የማይታይበት አማኝ የቃል ህይወቱን መመርመር አለበት።

 ጥያቄ 1.3

ገላ5፡22 ላይ የተቀመጡት የመንፈስ ፍሬ መገለጫዎች የእግዚአብሄርን ቃል ከመሞላት ጋር የሚያያዙበትን


መንገድ አስረዱ።

መ) በህይወታችን ስኬትን ይሰጠናል ፦

“የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም
አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም” (ኢያ1:8)።

ይህ ቃል እንደሚነግረን የእግዚአብሄርን ቃል የሚጠብቅ ሰው በህይወቱ ስከታማ ይሆናል። ምክንያቱም


እግዚአብሄር ለህይወቱ ያለውን ኣላማ ከቃሉ በመረዳት በጥንቃቄ ይጓዛልና ነው። የቃሉ እውቀት ከሆነ ግን
ኣላማውን ለመሳት ሰፊ እድል አለው። (መዝ 119፡105)

 ጥያቄ 1.4

ከመፅሃፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ የእግዚአብሄርን ቃል ጠንቅቀው በማወቃቸው ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን በማንሳት
ተወያዩ።

ሠ)ቃሉ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ላለ ሰው ተስፋን ይሰጣል፦በመጽሃፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ ብዙ


የእግዚኣብሄር ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ እግዚአብሄር ቃሉን በመላክ ተስፋቸውን ሲያድስ
እናነባለን። ይህ እግዚአብሄር ዛረም ለኣማኞች ተስፋን የሰጠው በቃሉ በኩል በመሆኑ በዚህ ቃል የተሞላ ሰው
በኣስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሲያልፍ ቃሉን በማሰብ ይፅናናል፣ተመልሶም በርትቶ ይቆማል። (ኤር15:16፣
ሮሜ15፡4፣እብ 7፡17-20)
ረ) የእግዚአብሄር ቃል ደስ ያሰኛል፦ እግዚአብሄር በቃሉ ውስጥ ማጽናናትን እና መልካም ምሪትን
ስላስቀመጠ የእርሱን ቃል የተሞላ ሰው ከህይወቱ ደስታን አያጣም። (መዝ119፡16፣140፣162፤ኤር15፡16)።

ሰ) ጠንካራ ያደርጋል፦ ክርስቲያን በሚኖርበት ዘመኑ ሁሉ ጠንካራና ፅኑ ለመሆን ይረዳው ዘንድ


የጌታን ቃል መመገብ አለበት፤ በእግዚአብሄር ቃል እውነት ላይ ህይወቱን የመሰረተ ሰው ጌታ እየሱስ
እንደተናገረው በማንኛውም ነውጥ ውስጥ ቢያልፍ በፅናት ቆሞ የማለፍ ችሎታ ይኖረዋል። (መዝ18፡30፣119፡
28፣38፣50)።

ሸ) የእግዚአብሄር ቃል አስተዋይ ያደርጋል፦ የጌታን ቃል የተሞላ አገልጋይ በውስጡ ከሚኖረው


የእግዚአብሄር ጥበብ የተነሳ ከሌሎች ይልቅ አስተዋይ እንደሚሆን መፅሃፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ (መዝ119፡98፣
130፣169)። ከዚህም የተነሳ የሰዎችን ችግር እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ለመፍታት፣ሰዎችን ለመምከር፣ እንዲሁም
በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ሆኖ ለማገልገል በምንም የማይተካ ጠቀሜታ አለው፤ (2ጢሞ3፡16፣ዘፀ18፡16) ።

ማጠቃለያ

እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር እና አላማ በሙሉ የገለጠው በቃሉ ውስጥ በመሆኑ ቃሉን የተሞላ
ሰው ከጌታ ዘንድ የታሰበለትን የህይወት አቅጣጫ በቀላሉ ማግኘት ይችላል። ከላይ ከተገለፁት የቃሉ
ጠቀሜታዎችም በተጨማሪ እግዚአብሄር ቃል አማኞችን በሌሎችም ብዙ መንገዶች ይጠቅማቸዋል።ለምሳሌ
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በገባው ተስፋ መሰረት፦ በቃሉ የሚኖር ሰው ኣብ እና ወልድ ከእርሱ ጋር ይኖራሉ፤
እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ያስተምረዋል (ዮሃ 14፡23፥26)፣ ልመናው ይደረግለታል (ዮሃ 15፡7)፣ እግዚአብሄር
ለራሱ ይቀድሰዋል (ዮሃ 17፡17፣ኤፌ5፡25፥27)። ስለዚህ ክርስቲያን የእግዚአብሄርን ቃል ለመሞላት ዘወትር
መትጋት ይኖርበታል።

 ጥያቄ 1.5

መዝሙር 119 ስለ እግዚአብሄር ቃል ጠቀሜታ ብዙ ያብራራል። ከዚህ ክፍል ውስጥ ከላይ ያልተዘረዘሩ የቃሉ
ጥቅሞችን በማውጣት ፃፉ።

1.2 በቃሉ እውቀት መኖር

መፅሃፍ ቅዱስ ቃሉ በሙላት እንዲኖርብን በ ቆላ 3፡16 ላይ ይነግረናል፤ ምክኒያቱም እርስ በርስ ለመማማርም
ሆነ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት ለማድረግ ቃሉ ወሳኝ ነው፤

“የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ።


በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።”
ከላይ በነበረው ንኡስ ርእስ እንዳነሳነው በእግዚአብሄር ቃል መሞላት ማለት ቃሉን ሸምድዶ መያዝ ማለት
ሳይሆን የህይወት ምልልሳችን በቃሉ መሰረት ሲሆን እንደሆነ ቆላ 3፡16 ያስረዳናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በዲያቢሎስ
ሲፈተን በውስጡ የነበረውን ቃል መሪው በማድረግ ለዲያቢሎስ ሃሳብ እንቢተኝነቱን አሳይቷል። በቃሉ የተሞላ
ሰው የተሞላውን ቃል በመኖር ክርስትናውን ያሳያል እንጂ ቃሉን አውቆ ብቻ ዝም አይልም። ፈሪሳውያን
መፃህፍትን በመመርመር የተካኑ በመሆናቸው ምክኒያት ቃሉን በልባቸው ይዘው ይኖሩ የነበረ በመሆኑ ክርስቶስ
ከየት እንደሚነሳ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፣ ጌታ በመጣ ጊዜ ግን እርሱ መሆኑን አላወቁትም ነበር። ስለዚህ ቃሉን
መሞላት ቃሉን ከመሸምደድ በእጅጉ የተለየ ነው።ከዚህ በመቀጠል በቃሉ ለመሞላት ምን ማድረግ እንዳለብን
እንማራለን።

ሀ) መፅሃፍ ቅዱስን ማንበብ፦ ሮሜ 15፡4 ላይ እንደተፃፈው የእግዚአብሄር ቃል በፅሁፍ የተቀመጠልን


በዚህ ዘመን ላለነው ለኛም ጭምር ትምህርት ይሆነን ዘንድ ነው። ስለዚህም ቃሉን በማንበብ መትጋት
ለህይወታችን ወሳኝ መሆኑን ቃሉ ያስተምረናል፤ (1ጢሞ4፡13)። እስራኤላውያን ከምርኮ በተመለሱ ጊዜ
ከሰሯቸው ነገሮች አንዱ ለዘመናት ርቀውት የነበረውን የእግዚአብሄርን ቃል ማንበብ ነበር፤(ነህ 8፡1-9)። በዚህ
ክፍል እንደምናነበው ህዝቡ የህጉን መፅሃፍ አስመጥተው ካስነበቡ በኋላ ከቃሉ ምን ያህል እንደራቁ ሲገባቸው
ማልቀስ ጀመሩ፤ እኛም እየተመላለስን ያለነው በጌታ መንገድ መሆን አለመሆኑን ማወቅ የምንችለው መፅሃፍ
ቅዱስን በቋሚነት ማንበብ ስንችል ብቻ ነው።ከዚህ የነህምያ መፅሃፍ ክፍል እንደምንረዳው ማንበብ ለማይችሉ
ወዳጆቻችን ጭምር ቃሉን በማንበብ ልንረዳቸው እንደሚገባን እንዲሁም ቃሉን በግል ብቻ ሳይሆን በህብረትም
ጭምር ማጥናት እንዳለብን ነው።

ጠቃሚ ነጥቦች

 ሁልጊዜ መፅሃፍ ቅዱስን ስናነብ እግዚአብሄር እየተናገረንና እየመከረን እንደሆነ ማሰብ


አለብን።

 መፅሃፍ ቅዱስ በምድር ላይ አቻ የሌለው ባለስልጣን መፅሃፍ እንደሆነ እንጂ ከመፃህፍት


አንዱ አድርገን ማሰብ የለብንም። ህይወታችንን መቀየር የሚችል የእግዚአብሄር እስትንፋስ
ያለበት መሆኑን አምነን ማንበብ አለብን።

 ቃሉ የሚለውን ለማመንና ለመሆን በወሰነ ማንነት ማንበብ የቻለ ሰው ከመፅሃፍ ቅዱስ


ብዙ ይጠቀማል።

 መፅሃፍ ቅዱስን ሁልጊዜ በቋሚነት ማንበብ ይጠበቅብናል፣ቋሚ ያልሆነና ወጥነት የሌለው


የመፅሃፍ ቅዱስ ንባብ ውጤታማነት የለውም፤መፅሃፍ ቅዱስን ማንበብ ከየቀን ስራዎቻችን
ኣንዱ መሆን አለበት።

 አንድ ርእስ ማንበብ ከጀመርን እስከታሪኩ ማብቂያ ድረስ ለማንበብ መታገስ አለብን፣
ለምሳሌ የተራራው ስብከት በመባል የሚጠራውንና ከማቴዎስ ምእራፍ 5-7 ድረስ ያለውን
ክፍል ማንበብ ጀምረን ምእራፍ 6 ላይ ብናቆም ሙሉ ትምህርቱን ማግኘት አንችልም።
ስለዚህ መፅሃፍ ቅዱስን በእርጋታና በማስተዋል ማንበብ ይጠበቅብናል።

 በደከመንና እንቅልፋችን በመጣ ሰአት ለማንበብ መሞከር የለብንም፣ ይልቅ ኣእምሮኣችን


በንቃት የሚሰራበትን ሰአትና ፀጥ ያለ የማይረብሽ ቦታ መምረጥ አለብን።
 ቃሉ የህይወታችን መርህ በመሆኑ በእምነት ከማይመስሉን ሰዎች ጋር ለመከራከር በሚል
ሃሳብ ካነበብነው እድገት አይሰጠንም። ስለዚህ ቃሉን በክርክር ለማሸነፍ ማንበብ
የለብንም።

 በምናነብበት ጊዜ ሁሉ የቃሉን ፍቺ እንዲያበራልን ወደጌታ መፀለይ አለብን።

ለ)ያነበብነውን ማሰላሰል፦ ዳዊት በመዝሙሩ፦ ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፥ መንገድህንም እፈልጋለሁ።


በትእዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም (መዝ119፡15-16)። በማለት ቃሉን ማሰላሰል እንዳንረሳውና የጌታን
መንገድ ለመፈለግ እንደሚረዳን ይነግረናል።

ማሰላሰል ማለት አንድን ነገር ለረጅም ሰአት ደጋግሞ ማሰብ፣ አንድን ሃሳብ ይዞና ፀጥ ባለ ቦታ ላይ ሆኖ
ማውጣትና ማውረድ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ በጥልቀት ማሰብ የሚሉ ትርጉሞች አሉት። በእብራይስጥ ትርጉሙ
ደግሞ

ኣንድን ነገር በጥልቀት ማስተዋል መመልከት፣ በማስተዋል ማሰብ፣መናገር፣መጫወት የሚሉትን ትርጉሞች


ይይዛል። ስለዚህ የእግዚአብሄርን ቃል ማሰላሰል ማለት ለተወሰነ ሰአት አእምሮን ሰብስቦ ቃሉን ብቻ ማውጣትና
ማውረድ እንዲሁም እግዚአብሄር በዚያ ቃል ውስጥ ምን ሊናገረን እንደሚፈልግ ማሰብ ማለት ነው።

 እግዚአብሄር ኢያሱን ሲያዘው ለሙሴ የተሰጠውን ህግ ቀንና ሌሊት እንዲያስበው ተናግሮታል፤


(ኢያ1፡8) ምክንያቱንም የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በማለት ነግሮታል። ከዚህ
እንደምንረዳው ቃሉን ደጋግመን ባሰላሰልን ቁጥር በቃሉ ውስጥ እንድናደርገው ጌታ ያዘዘንን ነገር
ለማድረግ ራሳችንን እናስለምዳለን።

 ዳዊት በመዝሙሩ፦ አቤቱ፥ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ፤ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ
ነው። (መዝ119፡97) በማለት የእግዚአብሄርን ቃል ደጋግሞ ማሰብ የጌታን ድምፅ የመውደዳችን
ምልክት መሆኑን ይጠቁመናል። ሰው በአእምሮው እንዲመላለስ የሚፈቅደው ደስ የሚያሰኘውንና
ምቾት የሚሰጠውን ነገር እንዲሁም ትኩረቱን የሚስበውን ነው፣ ስለዚህ ቃሉን ማሰላሰላችን ቃሉን
መውደዳችንን እና ለቃሉ ያለንን አመለካከት ያሳያል።

 እንደገናም መዝሙረኛው ዳዊት በእግዚአብሄር ዘንድ ምስጉን ስለሚባለውና በሰነፎች ምክር


ስለማይሄድ ሰው ባህሪያት ሲናገር በቃሉ ደስ የሚለውና ህጉን የሚያሰላስል መሆኑን እንዲህ በማለት
ይተርካል፦ ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥
በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም
በቀንና በሌሊት ያስባል (መዝ1፡1፣2)። በመሆኑም ቃሉን ማሰላሰል እግዚአብሄርን ደስ ከሚያሰኙ
ባህሪያት አንዱ ነው።
የእግዚአብሄርን ቃል ማሰላሰል አይናችን ከጌታ መንገድ ላይ እንዳይነሳ ይጠቅመናል፤ እንዲሁም ቃሉን በቀላሉ
ማስታወስና መያዝ ያስችለናል።ያነበብነውን የእግዚአብሄርን ቃል ባሰላሰልነው ቁጥር ከማያሰላስሉት ሰዎች ይልቅ
የቃሉ መረዳት እና ምልልስ ይኖረናል። ስለዚህ ቃሉን ካነበብን በኋላ ደጋግመን ማሰላሰል ወሳኝ ነገር ነው።

ጠቃሚ ነጥቦች

 የጌታን ቃል የማሰላሰልን ጥቅም ጠንቅቀን ማወቅ አለብን፤ እንዲሁም ክርስቲያናዊውን ማሰላሰል


ከሌሎች የባእድ አምልኮ አስተሳሰቦች ጋር ማምታታት የለብንም።ቃሉን የምናሰላለው ልእለ
ተፈጥሮአዊ የሆነ ሀይልን ለማግኘት ሳይሆን ራሳችንን ከቃሉ አንፃር ለመመርመርና ከጌታ ጋር ጥብቅ
ግንኙነት እንዲኖረን ለማድረግ ነው።

 ቃሉን ማሰላሰል በቃሉ ደስ መሰኘታችንን ለጌታ የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው።

 ማሰላሰል የምንችለው ከቃሉጋር ጥብቅ ግንኙነት ሲኖረን ብቻ መሆኑን ማሰብ አለብን።

 ከምናነበው ክፍል የተወሰኑ ቁጥሮችን ወይም ኣንድን ታሪክ አውጥተን ማሰላሰል እንችላለን።
ለምሳሌ፦ ኤፌ 1፥5 ላይ ያለውን “በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ
ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።” የሚለውን ክፍል ይዘን እያሰላሰልን መዋል ይቻላል፣ እንዲሁም
1ሳሙ ምእራፍ 1 ላይ ያለውን ታሪክ በመውሰድ የታሪኩን ይዘት ማሰላሰል ይቻላል።

 ቃሉን ስናሰላስል የተለያዩ ጥያቄዎችን ለራሳችን ማንሳት እንችላለን፤ ለምሳሌ ቃሉ የተፃፈው ለማን
ነው? ለኔስ ምን ያስተምረኛል? በምን መልኩ ልተገብረው እችላለሁ? ለሌሎች ወዳጆቼ በምን መልኩ
ላካፍላቸው እችላለሁ? ወዘተ የሚሉ ጥያቀዎችን ማንሳትና መልሶቹን መፈለግ እንችላለን

 ቃሉን ለማሰላሰል የምንመርጠው ስፍራ ፀጥ ያለና ሃሳብ የሚበታትኑ ነገሮች የሌሉበት ቢሆን
ይመረጣል፤ በምናሰላስልበት ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያ፣ስልኮችና ሌሎች መፃህፍትን ከአጠገባችን ብናርቅ
ይመረጣል። እንዲሁም ብቻችንን የእግር ጉዞ እያደረግን፣ ትራንስፖርት ውስጥ ሆነን ወዘተ ማሰላሰል
ይቻላል።

 በምናሰላስልበት ወቅት ግራ የሚያጋቡና ለመረዳት የሚቸግሩ ነገሮች ቢገጥሙን ማብራሪያዎችን


መጠቀምና ታላላቆችን ስለጉዳዩ መጠየቅ ልምዳችን ማድረግ አለብን።

 ቃሉን ማሰላሰል የተወሰነ የአእምሮ ልምምድ ይጠይቃል። ስለዚህ በየጊዜው አእምሯችንን ማሰላሰልንና
በአንድ ሃሳብ ላይ ማተኮርን ማሰልጠን ሊጠበቅብን ስለሚችል ይህንኑ በትእግስት መለማመድና
መፀለይ አለብን።

ሐ) ባነበብነውና ባሰላሰልነው ቃል ዙሪያ መፀለይ፦ የምናነበው የእግዚአብሄር ቃል ከጌታ ከራሱ የተሰጠን


መሆኑን ካመንን በዚህ በተሰጠን ቃል ዙሪያ ከሰጪው ከእግዚአብሄር መነጋገር ይኖርብናል። ጌታ በቃሉ ውስጥ
ያስቀመጠልንን ኣላማውን በየጊዜው ለመረዳት መፅሃፍ ቅዱስን በፀሎት ማንበብ ያስፈልገናል። እግዚአብሄር
በባህሪው ከልጆቹ ጋር ህብረት ማድረግ የሚፈልግ ኣምላክ በመሆኑ በቃሉ ዙሪያ መፀለያችንን የሚመለከተው
በየቀኑ በእኛ ላይ ያለውን ኣላማ የሚያሳውቅበት እና ከኛ ጋር የሚያወራበት መንገድ አድርጎ ነው። ብዙዎች
ያነበቡት ቃል በውስጣቸው የማያፈራው ቃሉን ስለማያሰላስሉትና ከጌታ ጋር ስለማይነጋገሩበት
(ስለማይፀልዩበት) ነው። በሚያነቡት ቃል ዙሪያ ተንበርክከው የማይፀልዩ ሰዎች ቃሉን የጌታ ፈቃድ ባልሆነ ጊዜ
ቦታና ሁኔታ ሁሉ ላይ በመጠቀም የስህተትና የክርክር መንስኤ ሲሆኑ ይታያሉ።
በአንፃሩ ቃሉን እያነበቡ የሚፀልዩ ሰዎች ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር የሚጠቅምን ነገር
ለማድረግ እግዚአብሄር እንደተጠቀመባቸው መፅሃፍ ቅዱስ ይነግረናል። ለምሳሌ ዳንኤል በነበረበት ዘመን
የኤርሚያስን ትንቢት በማንበቡና ሰባው የምርኮ አመት መፈፀሙን በመረዳቱ ወደ እግዚአብሄር በንሰሃ
በመጮሁ በዚህ ዘመን ላለነው ለእኛ ጭምር የሚሆንን ራእይ ተቀበለ፤ (ዳን9፡1-3)።

በሚቀጥለው ምእራፍ ስለፀሎት በሰፊው ይዳሰሳል።

 ጥያቄ1.6

 በቃሉ መሰረት መፀለይ የሚያስገኛቸውን ሌሎች ጥቅሞች መፅሃፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ
ግለፁ።

 ቃሉን መሰረት ኣድርጎ በመፀለዩ እግዚአብሄር እንደ ዳንኤል የተጠቀመበትን ሌላ ሰው ከመፅሃፍ


ቅዱስ ፈልጋችሁ አሳዩ።

መ) ያነበቡትን፣ያሰላሰሉትንና ከእግዚአብሔር ጋር በፀሎት የተነጋገሩበትን ቃል በህይወት ላይ


መተግበር፦ ይህ ደረጃ ብዙዎች የሚቸግራቸው ደረጃ ቢሆንም ከቃሉ ጋር ጊዜ ከሚያሳልፍና በእግዚአብሔር ቃል
ተሞልቻለሁ ከሚል ሰው የሚጠበቅ ዋና ነገር ነው። እግዚአብሔር ቃሉን የሰጠን ለህይወታችን ያለውን አላማ
ለእኛ ሊገልፅልን እንደሆነ ቀደም ባሉት ክፍሎች ተመልክተናል። ይህንን ቃል መተግበር ስንጀምር ጌታ በኛ ላይ
ያለው ኣላማ ይፈፀም ዘንድ ምቹ እንሆናለን። ስለዚህ ቃሉን በህይወት ላይ መተግበር ለክርስቲያን በጣም ወሳኙ
ክፍል ነው።

ኢየሱስ በ ሉቃ8፡5-15 ላይ እንዳስተማረው በቃሉ የሚኖር ሰው ብዙ ፍሬን ያፈራል። በዚህ ክፍል ላይ ሊያፈሩ
ያልቻሉትም ጭምር ቃሉ እንደሰሙ ነገር ግን በመልካም የተቀበሉት ብቻ እንዳፈሩ ተፅፏል።እንዲሁም በ ማቴ7፡
24-27 ላይ ቃሉን ሰምቶ የሚያደርግ ሰው በአለት ላይ ቤቱን እንደሰራ ሰው አድርጎ መስሎታል።

ያእቆብም በመልእክቱ ቃሉን ሰምቶ የማያደርግ በመስታወት ያየውን ፊቱን እንደሚረሳ ሰው ማንነቱን
እንደሚስት ይነግረናል፣ (ያዕ 1፡22-24)

ያእቆብ ቃሉን የሚያደርግ ሰው በስራው የተባረከ ይሆናል በማለት ያስተምራል፤ (ያዕ 1፡25) እንዲሁም መፅሃፍ
ቅዱስ ቃሉን የሚያደርግን ሰው እግዚአብሔር እንደሚሰማው ያስተምረናል፤(ዮሃ 9፡31)።

በዚህ ሁሉ ውስጥ የምንረዳው ነገር የእግዚአብሔርን ቃል አክብሮ ለመኖር የራስ ውሳኔና ፅናት ወሳኝ መሆኑን
ነው።

 ጥያቄ፦1.7

የእግዚአብሔርን ቃል መፈፀም የራስ ውሳኔን እና ፅናትን የሚጠይቅ መሆኑን የሚጠቁሙ ሌሎች የመፅሃፍ
ቅዱስ ትምህርቶችንና ታሪኮችን እያነሳችሁ ተወያዩባቸው።

1.3 በቃሉ እውቀት ያልተሞላ ሰው ባህሪያት

በእግዚአብሔር ቃል ያልተሞላ ሰው ህይወቱ በብዙ አቅጣጫ ከእግዚአብሔር አላማ በመራቁ ምክኒያት


የሚከተሉት መገለጫዎች ይኖሩታል፦
ሀ) ህይወቱ ሲመዘን የመንፈስ ፍሬ አይገኝበትም፦ ከቃሉ ጋር ቁርኝት የሌለው ሰው በህይወቱ ከሚስተዋሉ
ነገሮች መካከል አንዱ የመንፈስ ፍሬ መገለጫዎች የሆኑት ፍቅር፣ሰላም፣ደስታ፣ትእግስት፣በጎነት ወዘተ የሌሉበት፣
ቢኖሩበትም እንኳን ለይምሰል መሆኑ ነው። በምትኩ ደግሞ የስጋ ስራ መገለጫ የሆኑት ሃጢአቶች በተደጋጋሚ
የሚታዩበት ከሆነ ቃሉን የተሞላ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

ለ) ህይወቱ የተረጋና በእግዚአብሄር እቅድ መሰረት አይሆንም፦ የእግዚአብሄር ቃል ለሰው ልጆች የህይወት
ምሪት የሚሰጥ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው። ሰው በዚህ ቃል የተሞላ ምልልስ ከሌለው ከእግዚአብሄር አላማ ጋር
በቀላሉ ስለሚተላለፍ ህይወቱ የተረጋጋና ሰላም የሌለበት ይሆናል።

ከዚህም በተጨማሪ በቃሉ እውቀት ያልተገነባ ሰው ከላይ የተመለከትናቸውን በእግዚአብሄር ቃል የመሞላት


ጥቅሞች ስለሚያጣ ክርስትናው በተግባር ላይ ያልተመሰረተ እና የስም ብቻ ስለሚሆንበት ወደኋላ ሊያፈገፍግና
በመጨረሻም በክርስቶስ ያገኘውን ደህንነት መልሶ ሊያጣው ይችላል። በመሆኑም በእግዚአብሄር ቃል መሞላት
ለክርስቲያን በምንም ነገር ሊተካ የማይችል ነገር መሆኑን ጠንቅቀን ማወቅ ይጠበቅብናል።

 ጥያቄ 1.8፦

(ሆሴ4:4-10) ላይ ያለውን ክፍል አንብቡና ህዝቡ ለምን ጥፋት እንደተፈረደበት እንዲሁም ይህ ትንቢት በዚህ
ዘመን ላለነው ለኛ ምን ሊያስተምረን እንደሚችል ተወያዩበት።

ተግባራዊ እይታ

1፦ ከዚህ ምእራፍ ምን ጠቃሚ ትምህርት አግኝተናል?

2፦ ህይወታችን ከዚህ ምእራፍ አንፃር ሲመዘን ምን ይመስላል የእግዚአብሄርን ቃል ስለመሞላት


የነበረን እይታ እንዴት ነበር?

3፦ የእግዚአብሄርን ቃል ከመሞላት አንፃር በግል ሕይወታችን ምን መጨመር ይገባናል?

You might also like