You are on page 1of 11

የጌታችን በዐለ ልደት መቼ? ለምን?

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ

መድኃኒታችን የተወለደበት ቀን ይታወቃልን? የልደት በዐል የሚከበርበት ቀንስ

በምዕራባውያንና በእኛ ቤተክርስቲያን ለምን ተለያየ? የእኛ ቤተ ክርስቲያን ልደትን ለምን

ታኅሣሥ ፳፱ ታከብራለች? ምዕራባውያንስ የልደትን በዐል ለምን December 25

ያከብራሉ?

ምዕራባውያን የጌታን ልደት ከእኛ ሁለት ሳምንት ያህል ቀድመው December 25 (በእነርሱ

አቆጣጠር ታኅሣሥ ፳፱) ያከብራሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ

ታኅሳስ ፳፱ ቀን ታከብራለች። የዚህ ልዩነት መንሥኤ ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ቤተ

ክርስቲያን ልደትን በዚህ ቀን ለማክበሯ መሠረቷ ምንድን ነው? ምዕራባውያንስ

መሠረታቸው ምንድን ነው? ከሁለቱስ የትኛው ቀዋሚና ትክክል ሆኖ ይታያል? በመጀመሪያ

የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዐለ ልደትን የምታከብረው ታኅሣሥ ፳፱ ቀን የሆነበትን

ምክንያት ካየን በኋላ ምዕራባውያኑ በዐለ ልደትን የሚያከብሩበትን ቀን ምንጭና የትመጣ

በአጭሩ እንዳስሳለን።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ

ካለመገለጹ የተነሣ ትክክለኛውን ቀን ለማግኘት ታሪክን ተከትለው ብዙ የደከሙ አሉ።

ከዚሁም የተነሣ ዕለተ ልደቱን በተመለከተ የቀናት ልዩነቶች ተከሥተዋል። ሆኖም ግን ምንም

እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ቀኑን ይህ ነው ብሎ በግልጽ ባይናገርም አመልካች የሆነ ፍንጭ


ሳይሰጥ ግን አልቀረም። ይህንን ለመረዳት በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ አንድ ከቁጥር ፰-፲፬

የተጻፈውን መመልክት ያስፈልጋል።

«በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ።

ሚስቱም ከአሮን ልጆች ወገን ነበረች። ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበር... እርሱም በክፍሉ ተራ

በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። በዕጣንም

ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ

ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ ፍርሃትም ወደቀበት:: መልአኩም እንዲህ አለው፦

ዘካርያስ ሆይ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፣ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ

ትወልድልሃለች፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ ተድላና ደስታም ይሆንልሃል፣ በመወለዱም

ብዙዎች ደስ ይላቸዋል»ሉቃ፩፥፭፤፰-፲፬

በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ አመልካች (ጠቋሚ) ነገር እናገኛለን፡፡

ሆኖም ይህን አሳብ ፈልፍሎ ለማግኘት ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃልና አሳብ ጋር ተዛምዶ

ሊብራራና ሊተረጎም ያስፈልገዋልና ነገሩን በጥንቃቄና በማስተዋል መከታተልን ይጠይቃል፡፡

ዋናው አመልካች ፍሬ ነገር መልአኩ ገብርኤል ለዘካርያስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መወለድ

ያበሠረበት ቀን በዕብራውያን ዘንድ «በዐለ ሥርየት» ተብሎ ይከበር የነበረው ቀን መሆኑ

ነው፡፡ ሥርየት የሚባለው በዐል በዕብራውያን አቆጣጠር በሰባተኛው ወር ማለትም

በታስሪን (በጥቅምት) አሥረኛ ቀን የሚውል ታላቅ በዐል ነበር። ይኸውም በዐል በኦሪት ሕግ

«በሰባተኛው ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን ራሳችሁን አስጨንቋት። ያገር ልጅም በእናንተ

መካከል የተቀመጠ እንግዳም ሥራ አትሥሩበት፤ በእግዚአብሔር ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ

ትነጻላችሁ። ታላቅ ሰንበት ይሆንላችኋል...» ተብሎ የታዘዘበት ታላቅ በዐል ነበር።/ዘሌዋ.፲፮፥

፳፱-፴፤፳፫፥፳፯/፤/ዘኍ.፳፱፥፯-፲፩/
በዚህ በዐል ቀን ሊቀ ካህናቱ የተቀደሰ ተክህኖውን ለብሶ ወደ መቅደስ ይገባል።

በእግዚአብሔር ፊት ባለው መሠዊያ የእሳት ፍህም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል። እንዳይሞት

የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለው መክደኛ (ማስተሥረያ) ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር

ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። ዘሌዋ.፲፮ ፥ ፲፪-፲፫። እንዲሁም ካህኑ ለማስተሥረይ ወደ

መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ መጀመሪያ ለራሱ፣ ከዚያም ለሕዝቡ ሁሉ አስተሥርዮ እስኪወጣ

ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሌላ ማንም ሰው አይኖርም ነበር። ዘሌ፲፮፥፲፯። እንግዲህ

ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ እነዚህ ድርጊቶች መፈጻማቸውን ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ

ገልጾአቸዋል። «እርሱም (ዘካርያስ) በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል ወደ ቤተ

መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ

ነበር።» ይላል። ስለዚህ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ቀን የተጠቀሰው ሥነ ሥርአት

በሚፈጸምበት በበዐለ ሥርየት ቀን ሲሆን ይህም በዕብራውያን አቆጣጠር በጥቅምት ፲ኛ

ቀን ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ቀን በተለየ ሁኔታ ጌታችን ለተወለደበት ቀን ታሪካዊ

የአኀዝ መነሻና የመሠረት ድንጋይ መሆኑን ጠቁሞ አመልክቶአል ማለት ነው።

ይህ ዘካርያስ የተበሠረበት ቀን የአይሁድ በዐለ ሥርየት የዋለበት በዕብራውያን የዘመን

አቆጣጠር ጥቅምት አሥረኛ ቀን መሆኑን ብዙ ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች

መተርጉማን ገልጸው እናገኛለን። ለምሳሌም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ማር ዮሐንስ ወንጌለ

ሉቃስ ምዕራፍ አንድን ሲተረጉሙ ሰፋ ባለ ሐተታ ገልጸውት እናገኛለን። የኢትዮጵያ

መተርጉማንም በተወራረስው የሊቃውንት ትርጓሜ «ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ»

ከሚለው ላይ በታሪክ ሲያትቱ «የጥቅምት ጨረቃ ሠርቅ ባደረገች በአሥር ቀን ነው፣

ዕለቱም ዕለተ ዮሴፍ (በዐለ ሥርየት)ነው፣… ተሰብስበው ይጸልያሉ፣ ወበይእቲ ዕለት

አሕምምዋ ለነፍስክሙ (በዚያች ዕለት ራሳችሁን ታዋርዳላችሁ) እንዲል» ብለው

አስረድተዋል። (ትርጓሜ ወንጌል፣ ገጽ. ፫፻፳፬)


እስከዚህ ድረስ ዘካርያስ ዮሐንስን እንደሚወልድ የተበሠረበት ቀን በዐለ ሥርየት በሚባል

በዕብራውያን አቆጣጠር ታስሪን (ጥቅምት) አሥር ቀን ለመሆኑ የተገናዘበበትን

ትምህርታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ አይተናል። አሁን ደግሞ ይህ ቀን ከኢትዮጵያ የቀን

አቆጣጠር ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት እንደሆነና መቼ ላይ እንደሚያርፍ እንመልከት።

በዕብራውያን አቆጣጠር በዐለ ሥርየት የዋለው በጨረቃ አቆጣጠር ጥቅምት አሥር ቀን ስለ

ነበር ይህንን ወደ ኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መልሶ ዕለቱን ለማግኘት ወደ ዘመን አቆጣጠር

መግባት ግድ ይሆናል። ነገር ግን ወደዚህ የቀን አቆጣጠር ዝርዝር ብንገባ የያዝነውን ጉዳይ

እንዳያወሳስበው ዝርዝር ሐተታውን ትተን እንዲሁ ዕለቱ የሚውልበትን ብቻ እንመልክት።

በዕብራውያን አቆጣጠር ወርኀ ታስሪን (ጥቅምት) አሥር ቀን የዋለው በኢትዮጵያ አቆጣጠር

መስከረም ፳፯ ቀን ነበር። ይኸውም የጨረቃ የቀን አቆጣጠር ወደ ፀሐይ የቀን አቆጣጠር

ሲለወጥ የሚገኝ ነው። ይህም ማለት በጨረቃ አቆጣጠር ጥቅምት ፲ ቀን የነበረው በዐለ

ሠርቅ በፀሐይ የቀን አቆጣጠር መስከረም ፳፯ ቀን ነበር ማለት ነው።

ስለዚህ ዘካርያስ የተበሠረው መስከረም ፳፯ ቀን ሆኖ እናገኛለን። በዐሉ ወዲያው እንዳበቃ

ዘካርያስ ወደ ቤቱ ገባ፤ መጥምቁ ዮሐንስ ተፀነሠ። ቅዱስ ወንጌል «የማገልገሉ ጊዜ ሲፈጸም

ወደ ቤቱ ገባ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ፀነሠች» ሲል ያስረዳል። ቅዱስ ያሬድ ይህን መሠረት

በማድረግ ‹ወእምድኅረ ክልዔ መዋዕል ፀንሠት ኤልሳቤጥ ብእሲቱ - ከሁለት ቀንም በኋላ

ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሠች» ብሏል። ስለዚህ ዮሐንስ መጥምቅ የተፀነሠው መስከረም ፳፱

ቀን ነው ማለት ነው። መጥምቁ ዮሐንስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ጠራጊና በፊቱ

የሚሄድ መልእክተኛ መሆኑ በነቢያት ትንቢት ተነግሮ ቆይቶአል። ኢሳ ፵፣፫-፭ ፤ ሚል ፫፥፩።

እንደ ትንቢቱም ቃል ሁሉ ዮሐንስ ከፅንሠቱ ዕለት ጀምሮ በተፈለገው መንገድ ለጌታችን

ጎዳናውን እያቀና የሚሄድ የፊቱ መልእክተኛ ሆኖ ተገኝቶአል። ሉቃ.፩፥፸፮-፸፱ ፣ ዮሐ ፩፥፴-

፴፱። መጥምቁ ዮሐንስ የተፀነሠበትም ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማኅፀን

ለተፀነሠበትና ለተወለደበት ቀን ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው መነሻ አብነት ሆኖ ይገኛል

ማለት ነው።
እንግዲህ በዚህ ታሪካዊ ቁርኝትና ትስስር መሠረት ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛ ወሯ

ለዘካርያስ ያበሰረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ተልኮ

«ትፀንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ» በማለት መድኀኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምትፀንስና

እንደምትወልድ ነገራት። ይህም መጥምቁ ዮሐንስ ከተፀነሰበት ጊዜ (ከመስከረም ፳፱ ቀን)

አንሥቶ ሲቆጠር መጋቢት ፳፱ ቀን ይሆናል። መልአኩ እመቤታችንን ሲያበሥራት‹‹መካን

ትባል ለነበረችው (ለኤልሳቤጥ) ይህ ስድስተኛ ወር ነው» ሲል የተናገረው የፅንሠትዋን ጊዜ

የሚያመለክት አይደለምን? ሉቃ፩፥፴፮-፴፰ ። ስለዚህ መጋቢት ፳፱ ቀን ቃል ሥጋ የሆነበትና

በድንግል ማኅፀን የተፀነሠበት ዕለት ነው ማለት ነው። ከዚህ ከመጋቢት ፳፱ ቀን ጀምሮ

ወንድ ልጅ በእናቱ ማኅፀን የሚቆይባቸውን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት (፪፻፸፭ ቀናት)

ስንቆጥር ጳጉሜን ጨምሮ ዕለተ ልደቱ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ላይ ይውላል። ስለዚህም መጋቢት

፳፱ ቀን የተፀነሰው ጌታችን ከኃጢኣት በቀር የሰውነትን ሥራ ሁሉ ፈጽሟልና ዘጠኝ ወር

ከአምስት ቀን በእናቱ ማኅፀን ቆይቶ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን በቤተልሔም ዘይሁዳ ተወለደ።

ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ከርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ

የታሪክና የትውፊት ማስረጃዎችን መሠረት አድርጋ የመድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን በዐለ

ልደት ታኅሣሥ ፳፱ ቀን በታላቅ ምስጋና ታከብራለች።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ታኅሣሥ ፳፱ ቀን መሆኑን ከጻፉ አበው መተርጉማንና

የሐሳበ ዘመን መምህራን መካከል የተወሰኑትን ከዚህ ቀጥሎእንመልከት።

፩ኛ. «ይቤ ወልደ መነኰስ፦ ውእቱ ተወልደ ለጸቢሐ ሠሉስ በሌሊት አመ እሥራ ወተስዑ

ለወርኃ ታኅሣሥ በተፍጻሜተ ሃምሳ ወኃምስቱ ምዕት ዓመተ ዓለም። -እርሱ ጌታችን ወደ

ማክሰኞ አጥቢያ በሌሊት በታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፭ሺሕ፭፻ ዓመተ ዓለም ሲፈጸም ተወለደ»

ይላል፡፡ (ማር ዮሐንስ መተርጕም፣ትርጓሜ ወንጌል ዘማቴዎስ ገጽ ፹፰) ፡፡


፪ኛ. «ይቤ ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ በሠላሳ ወሠለስቱ ዓመተ መንግሥቱ ለሄሮድስ…አመ

እሥራ ወተስዑ ለወርኃ ታኅሣሥ ተወልደ እግዚእ ኢየሱስ፡፡ ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ በሄሮድስ

በ፴፫ ዓመተ መንግሥት… በታኅሣሥ ፳፱ኛ ቀን ጌታ ኢየሱስ ተወለደ» ይላል።

፫ኛ. ይቤ ጊዮርጊስ ወልደ ዓሚድ ፦«ወኮነ ድሙረ ሃምሳ ወኃምስቱ ምዕተ ዓመት እስከ

ልደተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ… ወተፀንሠ አመ እሥራ ወተስዑ ለመጋቢት በዕለተ እሑድ።

ወተወልደ አመ እሥራ ወተስዑ ለታኅሣሥ በዕለተ ሠሉስ ።- እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

ልደት የተደመረው ቁጥር ፭ሺ፭፻ ዓመት ነው፡፡ መጋቢት ፳፱ ቀን እሑድ ዕለት ተፀነሠ፤

ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ማክሰኞ ዕለት ተወለደ›› ብሎአል። (ጊዮርጊስ ወልደ ዓሚድ፣ ገጽ.፲፯-፲፰)

፬ኛ. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ (፫፻፴-፫፻፸፮ዓ.ም.) ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ

ክርስቶስ ልደት በታኅሣሥ ፳፱ ቀን ያስተማረው ትምህርት በሳሂዲክ (Sahidic - የቅብጥ

ቋንቋ ጥንታዊ ዘዬ) ይገኛል። (Coptic Encyclopedia, p. 380)

፭ኛ. ዲድስቅልያ _አንቀጽ ፳፱፦«ቀዳሚ በዐል ዘውእቱ ዕለተ ልደቱ ለክርስቶስ አመ እሥራ

ወኃሙሱ ለታስዕ ወርኅ በኁልቆ ዕብራውያን ወበኀሳበ ግብፃውያን አመ እሥራ ወተስዑ

ለወርኃ ታኅሣሥ ዘውእቱ ራብዓይ ወርኅ ግበሩ፡፡ -የመጀመሪያው በዐል የክርስቶስ ልደት

ነው፡፡ ይኸውም በዕብራውያን አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር በ፳፭ኛ ቀን በግብፃውያን አቆጣር

በታኅሣሥ ወር በ፳፱ኛው ቀን ታደርጋላችሁ ተብሉ ተወስኖአል። ዲድስቅልያ፣ አንቀጽ ፳፱

ገጽ. ፴፯)

እነዚህ ለአብነት ተጠቀሱ እንጂ የልደተ ክርስቶስን ዕለት ታኅሣሥ ፳፱ መሆኑን የጻፉና የገለጹ

ሊቃውንትና ጸሐፊዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና

የግብፅ ኦርቶዶክስ (ኮፕት) ቤተ ክርስቲያን በዐለ ልደትን ታኅሣሥ ፳፱ ቀን የሚያከብሩት

በተረዳና በታወቀ ማስረጃና መሠረት ላይ ተመሥርተው ነው እንጂ እንዲሁ አይደለም።


የምዕራባዉያን የልደት በዐል ለምን December 25 ሆነ?

ምዕራባዉያን የጌታችንን በዐለ ልደት ለምን December 25 እንደሚያከብሩ የተለያዩ

አስተያየቶችና ምክንያቶች ይሰጣሉ። ከእነዚህም ጎላ ያሉት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።

አንደኛው ከዘመን አቆጣጠራቸው ጋር ለማዛመድ የተደረገ ሂደት ነው የሚል ነው::

ይኸውም ዲዮናስዮስ ኤክሲጀስ የተባለው የሮም መነኲሴ በ፭፻፳፭ ዓ.ም. በቫቲካኑ ጳጳስ

አነሳሽነት አዲስ የዘመን አቆጣጠር አዘጋጅቶ አቀረበ። «ታሪክን ተከትዬ ባደረግሁት ጥናት

መሠረት ክርስቶስ የተወለደው ከ ፩ ዓመተ ምሕረት በፊት ፯ ዓመት ቀደም ብሎ

(በ፭ሺሕ፬፻፺፫ ዓመተ ዓለም) ነው» የሚል አሳብ አቀረበ። በሁሉም የክርስትና ዓለም ጥቅም

ላይ ሲውል በነበረው የጋራ የዘመን አቆጣጠር መሠረት በዚያ ጊዜ በነበረው ዓመት በ፭፻፳፭

ዓ.ም. ላይ ፯ ዓመታትን ጨምሮ በአንድ ጊዜ ፭፴፪ አደረሰው። ሆኖም ይህ የኀሳበ ዘመን

ስሌቱ ስህተት ነበር። (የዘመን አቆጣጠርን በተመለከተ ወደፊት በሚወጣው የሐመር

መጽሔት ልዩ የመጽሐፍ ዕትም ላይ ሰፋ ብሎ በዝርዝር ስለሚወጣ በዚያ ላይ መመልከት

ይቻላል።) ስለዚህም ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ይህን አዲስ የዘመን አቆጣጠር

ስሌት ውድቅ በማድረግ በነበረው በጥንቱ የዘመን አቆጣጠር መጠቀማቸውን ቀጠሉ።

አዲሱ አቆጣጠር ግን አዲስ ዓመት የሚቀይረው በጥር ወር ሆነ። ለዚህም አንዱና ዋናው

ምክንያት በአውሮፓ ከባዱ የቅዝቃዜ ወቅት እያለ ቀና የፀሐይ ሙቀት እየመጣ የሚሄድበት

ወቅት ወርኀ ጥር በመሆኑም እንደ ሆነ ይነገራል። ስለሆነም የክርስቶስን በዐለ ልደት ከአዲሱ

ዓመት መጀመሪያ ጋር አንድ ለማድረግ ሲሉ በዐለ ልደቱን በ December 25 አደረጉት የሚል

ነው።

ሌላውና በብዙ ምሁራን ዘንድ የሚታመነው አሳብ ደግሞ December 25 የተመረጠበት

ምክንያት አውሮፓውያን ክርስትናን ከመቀበላቸው በፊት ያከብሩት ከነበረ የጣዖት በዓል

ዕለት የተገኘ ነው የሚለው ነው። ሮማውያን ከቄሣር ኦሬሊያን (275 ዓ.ም.) ጀምሮ የ «ኃያሏ
ፀሐይ» ("Sol Invictus": the Unconquered Sun) የአምልኮ በዓልን በዚሁ ቀን ያከብሩ

ነበር። December 25 የፀሐይ የልደት ቀን ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን በዚሁ ዕለትም

በመላዋ የሮም ግዛት ታላቅ አሕዛባዊና ጣዖታዊ የእምነት ሥነ ሥርዓታዊ ክብረ በዓል

ይፈጸም ነበር። ኋላ ሕዝቡ ክርስትናን እየተቀበለ ሲሄድ ከፍጡር የፀሐይ አምልኮና በዐል ወደ

እውነተኛው ፀሐይ (ፀሐየ ጽድቅ) ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ አምልኮ እንዲመለሱና የእርሱን

በዐለ ልደት እንዲያከብሩ ለማድረግ ይህንን ቀን መርጠዋል። ይህ አስተሳሰብ በዘመኑ በነበሩ

ጸሐፊዎች ተመልክቶአል።(W.P.Dawson "Christmas: Its Origins and Associations,"

London,1902). የፀሐይ አምልኮና ልማድ በተለይም በዚህ ቀን በሕዝቡ ይደረግ የነበረው

ጣዖታዊ የበዐል አካባበር ልማድ ብዙዎችን በቀላሉ ሊለቃቸው ስላልቻለ በዚሁ ቀን ላይ

የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዐል ማክበር ደካሞችን ከጣዖታዊ ልማድ ነፃ ለማውጣት

ይጠቅማል ብለው በማሰብ ያደረጉት ነው፡፡

ከዚሁ ጋር አብሮ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር በአገራችን ሕዝቡን ለማሳትና ጥንታዊትና

ሐዋርያዊት ከሆነችው ከኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖቱ ሰውን ለማናወፅ የጥፋት ሠራተኞች

የሆኑት የምዕራባውያን ተላላኪዎች ልደትን በእኛ አቆጣጠርና በዐል እናከብራለን ሲሉ

የመታየቸው ነገር ነው፡፡ እነርሱ ምንጫቸው አምባገነንና‹‹የክርስቶስ እንደራሴ ነኝ›› ይል

በነበረው በልዮን የተመሠረተው የሮማ ካቶሊክና ዘረኛ ጀርመናዊ በነበረው በማርቲን ሉተር

የተጀመረው ፕሮቴስታንት መሆኑ የታወቀ ነው:: እነዚህ ካቶሊካው ያንና ሉተራውያን ደግሞ

የልደትን በዐል የሚያከብሩት ከላይ እንደተገለጸው December 25 ነው፡፡ በዚያውም ላይ

ተሐድሶዎች ሉተራውያን በተለይ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የልደት በዐል መከበር የለበትም

እያሉ ብዙ ብጥብጥና ሁከት ሲፈጥሩ የነበሩባቸው ብዙ ዘመናት ነበሩ፡፡ በተለይ በእንግሊዝ

ፒዩሪታንስ የተባሉት የተሐድሶ ቅርንጫፎች የፖለቲካ ሥልጣን በያዙ ጊዜ በዐለ ልደትን «ሕገ

ወጥ» በዐል ነው ብለው በማወጃቸው ብዙ ደም አፋሳሽ ግጭት ተፈጥሯል:: (N. Doran,


"The Ups and Downs of Christmas," in "The National Magazine," London,
December 1857.)
ፕሮቴስታንቶች (ሉተራውያን) የልደትን በዐል መከበር እየተቀበሉ የመጡት ለሸቀጦች

ማሻሻጫ ሲባል የተፈጠረው ‹የገና አባት» ለገበያና ለንግድ ጥሩ መሆኑን ከተመለከቱ በኋላ

ነበር። ዛሬም ቢሆን ብዙዎቹ ምዕራባውያን ልደትን የሚያከብሩት ከሃይማኖታዊነቱ ይልቅ

በንግድ መሣሪያነቱ ሆኗል፡፡ ታዲያ በአገራችን ያሉ «ጥቁር ምዕራባዉያን» የልደትን በዐል

በእኛ በዐል ቀን እናከብራለን ለምን ይላሉ? በእርግጥ የእኛን አቆጣጠር አምነውበት ነው?

ወይስ ሕዝቡን ለማታለልና ለማጭበርበር እንዲያመቻቸው? በመሠረተ እምነታቸው ከእኛ

ጋር አንድ ሳይሆኑ በቀን አቆጣጠር ብቻ እኛን ሊመስሉ አይችሉም:: ነገሩ በጎችን ለማጥመድ

የበግ ለምድ ለብሶ መምጣት በመሆኑ ልናስብበትይገባል።

እንግዲህ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አቆጣጠር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

ከተወለደ ይኸው ልክ ሁለት ሽሕ (፳፻) ዓመት ሆነው፡፡ ዓመተ ፍዳ አልፎ ዓመተ ምሕረት

(የምሕረት ዓመት) በሆነ ዘመን ላይ ስላለን በዐለ ልደቱን ስናከብር እግዚአብሔር ለእኛ

ያደረገልንን ታላቅ ውለታ በማስታወስ፣ የፈጸመውን ታላቅና ድንቅ ሰው የመሆን

(የተዋሕዶ) ምስጢር በማሰብና በመረዳት ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲህ ሲሆን በበዐለ ልደቱ

ተገኝተው «ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ - ክብር

ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ» እያሉ ካመስገኑ

ቅዱሳን መላእክት ጋር አብረን ደስ እያለን ምስጋናን ለአምላካችን ልናቀርብ ይገባናል።

ቅዱሳን መላእክት ለእኛ ለሰዎች የተደረገው መልካም ነገር አስደስቶአቸው ምስጋና ካቀረቡ

እኛ የድርጊቱ ባለቤቶች ምን ያህል ደስ ሊለንና ልናመሰግን ይገባን ይሆን? ስለሆነም

እግዚአብሔርን እንደማያውቁ እንደ አሕዛብ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፣ በዘፈንና

በጭፈራ፣ በዝሙትና በመዳራት፣ በአጠቃላይ ነፍስንና ሥጋን በሚያጎሰቁሉና ይህን ሁሉ

ቸርነት ያደረገልንን አባታችንን እግዚአብሔርን በሚያሳዝኑ ተግባራት ሳይሆን ለክርስቲያን

እንደሚገባ በቤተ ልሔም (በቅድስት ቤተ ክርስቲያን) በመገኘት ነገረ ልደቱን በማሰብ፣

በያሬዳዊ ዜማ ፣ ምስጋና ከሚያቀርቡ አባቶችና መዘምራን ጋር አብረን እናመስግን፡፡


የአምላካችንን ውለታና ፍቅርም በሕይወታችን ዘልቆ የታተመና በዓመት አንድ ጊዜ

በታኅሣሥ ፳፱ ቀን ብቻ ወይም በየወሩ በ፳፱ ቀን ብቻ ሳይሆን በልባችን ጽላት ሊቀረጽና

ሁል ጊዜም በየዕለቱ ልናስበው ይገባል። ሕይወታችንም ለአምላካችን የሚገዛና ለእርሱ ደስ

የሚያሰኝ ሊሆን ይገባዋል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ሐመር- ኅዳር/ታኅሣሥ ፳፻ ዓ.ም

ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ


ዋቢ ድርሳናት

* ወንጌል ቅዱስ፣ ከቀድሞ አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባቡና ትርጓሜው፣

ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. አዲስ አበባ፡፡

* አቡሻህር

* ማር ዮሐንስ መተርጕም፣ ትርጓሜ ወንጌል ዘማቴዎስ

* ዲድስቅልያ አንቀጽ ፳፱

* ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ

* ሃይማኖተ አበው፤ ዘቅዱስ አትናቴዎስ


* Coptic Encyclopedia, Volume 2, Macmillan Publishing Company, New
York, 1991.
* W. P. Dawson, "Christmas: Its Origins and Associations," London,
1902.
* N. Doran, "The Ups and Downs of Christmas," in "The National Magazine,"
London, December 1857.
* Koren, 57 ff.; R. J. Campbell, "The Story of Christmas," New York,
1934, 40.

You might also like