You are on page 1of 1

በ/ኢ/ኦ/ተዋህዶ የደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ማኅበረ አማኑኤል ዘዲያቆናት የተቸገሩ አብያተ

ክርስትያናት መርጃ

"ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ" 2ኛ ነገ. 6:16

ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በብዙ ቋንቋ አገልጋይ ይብዛ የሚል መልካም ሀሳብን ሰበብ በማድረግ የዘር ፖለቲካ የተጫነው፣
በመንግሥት ድጋፍ የተደረገው ኢ-ሲኖዶሳዊ 'የኤጲስ ቆጶሳት ሲመት' እና በዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ በጥር 18 ቀን 2015
ዓ.ም በአስቸኳዩ ምልዐተ ጉባዔው ያስተላለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ከማኅበረ አማኑኤል ዘዲያቆናት የተቸገሩ አብያተ
ክርስትያናት መርጃ የተሰጠ መግለጫ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ላይ ለብዙ ዘመናት ከውስጥም ከውጪም ስርዓትዋን ለመናድና
አምልኮትዋን ለመበረዝ የተነሱ አጽራረ ቤተ ክርስትያን በመንግሥት መዋቅር በመደገፍ በተደራጀ መልኩ
በኦርቶዶክሳውያን ላይ ብዙ እልቂት፣ መከራና ስቃይ አድርሰዋል። ዛሬም በቤተክርስትያን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ
መልኩ መላው ህዝበ ክርስትያንን ያሳዘነና ያስቆጣ የመፈንቅለ ሲኖዶስ ሙከራ ተደርጓል። ይህ ጉዳይ በመንግስት
ይሁንታን ማግኘቱ ደግሞ ይበልጥ ያሳስበናል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖና ቤተ ክርስትያንን በመጣስ በህገወጥ መልኩ 'ኤጲስ ቆጶሳትን' የሾሙ እንዲሁም የተሾሙትን 25
'ኤጲስ ቆጶሳትን' ጨምሮ ህገ ቤተክርስትያንን መሠረት አድርጎ የቤተክርስትያንን ክብርና ልዕልና ለማስጠበቅ
የወሰነውን ውሳኔ በታላቅ አክብሮት እንቀበላለን።

እኛም ቤተክርስትያኒቱ በየጊዜው የምታወጣውን መመሪያና መግለጫዎች በአጽንኦት እየተከታተልን እንገኛለን።


ከቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ በኋላም የተባባሰው የብጹአን አባቶቻችን፣ የመነኮሳትና የቤተክርስትያኗ ኃላፊዎች ላይ
የሚደርሰው እስርና እንግልት ይበልጥ አሳስቦናል፤ አስጨንቆናል።

እንደታናሽ የቤተክርስትያን አገልጋይነታችን ካለአባቶቻችን ትዕዛዝ አንዲት ነገር ባለመፈጸም ቤተክርስትያናችንን


በመጠበቅ ላይ እንገኛለን። ቤተክርስትያኒቱ ላይ ከመንግሥት ጀምሮ በተለያዩ አካላት በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ
የሚደረጉ ማንኛውም ጥቃቶችንና ግፊቶችን የምንቃወም መሆኑን እናሳውቃለን።

ቀደምት ቅዱሳን አባቶቻችን በደም መስዋዕትነት ያቆዩዋት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን እኛም
የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የምናስመሰክርበት ሁነኛ ሰዓት ላይ የምንገኝ በመሆኑ እንደማንኛውም
የቤተክርስትያን ልጅ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዋጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።

መጽሐፍ "ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ" (2ኛ ነገ. 6:16) እንዲል ሁሉን ቻዩ ቅዱስ አማኑኤል
ከእኛ ጋር እንዳለ በማመንና ይህን ክፉ ጊዜ እኛንም ብጹአን አባቶቻችንንም በማጽናት እንዲያሳልፈን በጾምና በጸሎት
ዘወትር እንጠይቀዋለን። ይልቁንም ከመንጋው የተለዩትንም ተንሳሂ ልቦና ሰጥቶ ወደበረቱ እንዲመልስልን ጸሎታችን
ነው።

በመጨረሻም በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስትያን ውስጥ የሚገኘው ይህ አንጋፋ ማኅበር የቤተክርስታያኒቱ
የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በቀጣይ የሚሰጠው ማንኛውም ዓይነት መመሪያ ቢኖር በጥብዐት ለመፈጸም
ዝግጁዎች መሆናችንን እናሳውቃለን።

"ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስትያን እናምናለን"

ጥር ፳፬/፳፻፲፭

You might also like