You are on page 1of 35

1

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ኮርስ

ዓላማ
የትምህርቱ ዓላማ በ40 ቀንና በ80 ቀን ተጠምቀው ከእግዚአብሔር አምላክ ልጅነትን ያገኙ ክርስቲያኖች
ሁሉ የቤተ ክርስቲያናቸውን ሥርዓት በሚገባ አውቀውና ተረድተው በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን ያስተማረቻቸውንና የምታዛቸውን ሥርዓት በቅፅረ ቤተክርስቲያን ሆነ ከቅፅር ውጪ
እንደአስፈላጊነቱ እንዲፈፅሙ ማስጨበጥ ነው፡፡

የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት 5 ዋና ዋና ምዕራፎች አሉት፡፡

1. ህንፃ ቤተ ክርስቲያን
2. ሥርዓተ ቅዳሴ
3. ሥርዓተ ቁርባን
4. ሥርዓተ ገዳም፣ ስግደት እና ምጽዋት
5. ሥርዓተ ፀሎት፣ ምፅዋት፣ መዝሙር ያካተተ ነው፡፡

ምዕራፍ አንድ

ህንፃ ቤተ ክርስቲያን
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማለት ሥርዓት እና ቤተ ክርስቲያን ከሚሉ ሁለት የግዕዝ ቃላት የተመሠረተ
ነው፡፡ ትርጉማቸውንም እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

ሥርዓት፡- ማለት ሠርዕ ሠራ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ድንብ፣ አሠራር፣
መርሐ ግብር፣ መመሪያ ማለት ነው፡፡ ሥርዓት ለማንኛውም ሊከናወን ለሚችል ነገር ቅደም ተከተል
ነው፡፡ መጀመሪያና መጨረሻ፣ ልክና መጠን (ገደብ) ማዘጋጀት ነው፡፡

ሥርዓት መንፈሳዊ ትርጉሙ ቀደምት አበው ሐዋሪያት ለቤተ ክርስቲያን የሠሩት ህግ፣ ውሳኔ፣ ደንብ፣
መመሪያ ወይም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማለት ነው፡፡ 1ኛ ተሰሎንቄ 5÷14 ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን
ገስጹአቸው፡፡ ያዘኑትንም አረጓጓአው፡፡ ድፍረት የሌላቸውን አፅኑዋቸው፡፡ ለደካሞች ትጉላቸው፡፡

ሥርዓት ለምን ያስፈልጋል

1. ማንኛውም ሥራ ዘላቂ እንዲሁም ወጥ በሆነ መልኩ በሥርዓት ማስኬድ ይቻላል፡፡


ያለ ሥርዓት የሚሠራ ነገር ፍፃሜው አያምርም፡፡ እግዚአብሔር እንኳን ዓለሙን የፈጠረውና
የሚያስተዳደድረው በስርዓት ነው፡፡ ስለሆነም በቤተ ክርስቲያን የሚፈፀሙ አገልግሎቶች ሁሉ
ወጥ እና አንድ አይነት በሆነ ሁኔታ እንዲፈፀሙ ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሁሉም በአግባቡ
እና በሥርዓት ይሁን እንደተባለ አንድ ሀሳብ አንድ ልብ በመሆን አንድ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡
1ኛ ቆሮንቶስ 5÷40
2. የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማፅናት ያስችላል፡፡ ያለ አንድ አይነት ሥርዓት አንዱ ሲጀምር
አንዱ የሚጨርስ፣ አንዱ ሲዘምር ሌላው የሚያስተምር ከሆነ መለያዬት ያመጣል፡፡ ስለሆነም
ምዕመናን ሐዋሪያው እንደተናገረው የመንፈስ አንድነትን ለመጠበቅ አንድ ዓይነት ሥርዓት

2
ለቤተ ክርስቲያን ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ስንሆን አንድ ልብ እና አንድ ሀሣብ የሚያደርገን ሥርዓት
ነው፡፡ ኤፌ 4÷3፣ የሐዋ 4÷32 ፣ ሮሜ 15÷5-6
3. የቤተ ክርስቲያንን ምስጢራት በአግባቡ ለመፈፀም ይረዳል፡፡
ለምሣሌ ምስጢረ ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ፆም፣ ፀሎት …ወዘተ በማመን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆኑ
የአፈፃፀም እና የአተገባበር መንገድ (ሥርዓት) ያስፈልጋቸዋል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ዝርዝር አፈፃፀም
በስርዓት ውስጥ ይካተታል፡፡ ስለዚህ በአንዲት ርትዕትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት
ሥር ያሉ ሁሉ ይቺን አንዲት እምነት የሚፈፅሙት በአንድ አይነት ሥርዓት ነው፡፡
4. የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጥልቅ እና ምጡቅ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት
በመጠኑም ቢሆን ለመማር እና ለማስተማር ለማወቅ ሥርዓቱን ለመፈፀም የሚረዳ ነው፡፡

የሥርዓት ዓይነቶች

ሁለት ዓይነት የሥርዓት ዓይነቶች አሉ፡፡

1. የተፈጥሮ ሥርዓት
2. መንፈሳዊ ሥርዓት

የተፈጥሮ ሥርዓት

የተፈጥሮ ሥርዓት የሚባለው የሥነ ፍጥረት ፈጣሪ እግዚአብሔር ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በነፃ
ያደለው ለእያንዳንዱ የግል ፀጋ መለያና የአስተሳሰብ እንዲሁም የአኗኗር ስልት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ
ሁሉም አንድ አይነት ፀባይ እና ተፈጥሮ የሕይወት ስልት የለውም፡፡ ሁሉም የየራሱ ፀባይ አለው፡፡ ሰው
ልዩ ሥርዓት አለው፡፡ የእንስሳትም ሥርዓት ሌላ ነው፡፡ የአራዊትም ሥርዓት የተለየ ነው፡፡ ግዑዛን
ፍጡራን ሳይቀሩ በተፈጥሮ የተሰጣቸው ሥርዓት አለ፡፡

መንፈሳዊ ሥርዓት

በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ በእርሱ የሚዘጋጅ የመንፈስ ቅዱስ ውጤት ነው፡፡ ይህም በቅዱሳት መፃሕፍት
ላይ የተመሠረተ የመንፈሳዊ ሕይወት መመሪያ ነው፡፡ ሥጋዊ ሥርዓት የሥጋዊ መሪዎች ለሥጋዊ
ኑሮ መመሪያነት የተዘጋጀ ስለሆነ በስሩ ላሉ ተስማሚ ካልሆ በቀላሉ ሊሻሻልና ሊለወጥ ይችላል፡፡
ምንም አይነት ጊዜ የሚወስድ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ሥርዓት የተሰራው በብዙ መንፈሳዊ ጥረት ነው፡፡
ለሚደረገው ለውጥም ሆነ መሻሻል መንፈሳዊ አሰራርን ይጠይቃል፡፡

መንፈሳዊ ሥርዓት ከሰበካ ሰበካ ከሀገር ሀገር የሚለያይ ሳይሆን አንድ መሠረት ያለው ከአንድ ምንጭ
የተቀዳ አንድ ወጥ አንድ አይነት አምልኮመመሪያ ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ የጋራ ውሳኔ እንጂ
አንድ ግለሰብ (አንድ ካህን)፣ የአንድ ፓትርያርክ ወይም ኤጲስ ቆጶስ፣ ዲያቆን …ወዘተ ሥርዓተ
ቤተክርስቲያን መጨመርም መቀነስም አይችሉም፡፡ ከጊዜው እና ከምዕመናን የኑሮ ደረጃ አንፃር ሊታይ
መቀነስ፣ መሻሻል ወይም ፈፅሞ መለወጥ ያለበት ሆኖ ከተገኘ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ በኤጲስ ቆጶሳት
ጉባኤ አማካኝነት ይፈፀማል እንጂ እያንዳንዱ ካህንም ሆነ ምዕመን እንደመሰለው የተፃፈውን መቀነስ
ወይም መጨመር አይችሉም፡፡

3
ቤተ ክርስቲያን ማለት ምን ማለት ነው?

ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ቤተ እና ክርስቲያን ከሚሉት ሁለት የግዕዝ ቃላት የተገኘ ሲሆን


ትርጉሙም የክርስቲያኖች መኖሪያ ቤት ማለት ነው፡፡ የክርስቶስ ቤት የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ ቤት
የሚል ትርጉም አለው፡፡ በግሪክ አቅሌስያ ትባላለች የምርጦች ጉባዔ ማለት ነው፡፡

በዘይቤያዊ ፍች ቤተ ክርስቲያን ስንል 3 ትርጉም አለው፡፡

1ኛ. ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ተሰብስበን የምንስቀድስበት፣ የምንማርባትና ሌሎች ምሥጢራት


የምንፈፅምባት ናት፡፡ ይህች ቤት ጌታችን የክርስቶስ ቤተ ስላላት የክርስቶስ ቤት እንላታለን፡፡ ‘’ቤቴ
የፀሎት ቤት ትባላለች’’፡፡ በዘመነ ሐዲስ የማርቆስ እናት የማሪያም ቤት የመጀመሪያዋ የሐዲስ ቤት
ክረስቲያን ነበረች፡፡ ሐዋሪያት በዚህች ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ይፀልዩ ነበር፡፡

2ኛ. የክርስቲያኖች ስብስብ ነው፡፡ በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሁለትና ከዚያ በላይ
የሚኖራቸው ስብሰባ ቤተ ክርስቲያን ይባላል፡፡ ምክንያቱም በዚያ የአንድነት እምነት ውስጥ
እግዚአብሔር አለና፡፡ ማቴ 18÷20 ሁለት ወይም ሦስት ሆናችሁ በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ
በመካከላቸው እኖራለሁ፡፡

3ኛ. እያንዳንዱ ክርስቲያን፡- በእግዚአብሔር አንድነት እና ሦስትነት አምነው የተጠመቁ ክርስቲያኖች


የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች የክርስቶስ አካላት ናቸውና ቤተ መቅደስ ይባላሉ፡፡‘’ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ
የእግዚአብሔር መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?’’ 1ኛ ቆሮ
3÷16 ‘’የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣኦት ጋር ምን መጋጠም አለው፣ እኛ የሕያው
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና’’ 2ኛ ቆሮ 7÷16 እግዚአብሔር እንዲህ አለ ‘’በእነርሱ እኖራለሁ፣
በመካከላቸው እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ እንደተባለ‘’ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ማደሪያ ነንና ቤተ
ክርስቲያን ተብለን እንጠራለን፡፡

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ሥርዓት

እግዚአብሔር በባሕሪው ምልዐት የተነሳ የሌለበት ቦታ ባይኖርም ውስን ፍጥረታት እኛ ለህሊናችን


በሚስማማ ሁኔታ በውስን ቦታ እንድናመልከው አዝዞናል፡፡ ይህም ለእኛ መሰብሰቢያ ብቻ ሳይሆን
እርሱም በእኛ በረድኤት እና በፀጋ ላለመለየቱ የቃል ኪዳን ቦታ በመሆኑ ነው፡፡ እስራኤልን
በመካከላችሁ አድር ዘንድ መቅደሴን ስሩልኝ ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ ዘፀ 20÷9 ሰዎችምምህረትና ይቅርታ
ረድኤት እና በረከት ሲፈልጉ ወደዚህ ቦታ ይመጣሉ፡፡

የሐዲስ ኪደን ቤተ ክርስቲያን ያለ ሥርዓት አትተከልም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የኩነኔ አገልግሎት ለክብር
ሲሆን የፅድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና፡፡ 1ኛ ቆሮ 3÷7-11 ማንኛውም ቤተ ክርስቲያን
በተለያዬ ቅርፅ ቢሰራም 3 ክፍል አለው፡፡ ይህውም በንጉስ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ አምሳል ነው፡፡
ምክንያቱም ለብዙ ክርስትና እምነት ሥርዓት መሠረቷና ምሳሌው የብሉይ ኪዳን ሥርዓት ነው፡፡

4
የቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ክፍሎች

ቤተ ክርስቲያን ሦስት ክፍሎች አሏት፡፡

ሀ) ቅኔ ማህሌት

ለ) ቅድስት

ሐ) መቅደስ ናቸው፡፡

1. ቅኔ ማህሌት
ስያሜው ከግብሩ የተወረሰ ነው፡፡ ይህ ክፍል በቤተ ክርስትያን ከውጪ ወደ ውስጥ ሰንገባ
በመጀመሪያ የምናገኘው ክፍል ነው፡፡ መዘምራን ስብሐተ እግዚአብሄር፣ ማሕሌት እግዚአብሔር
የሚዘምሩበት ነው፡፡ በዚህ ክፍል (በሰሜን ምስራቅ) በኩል ቀሳውስት እና ዲያቆናት በመንፈቀ
ሌሊት እና በነግህ ሰዓታት ይቆሙበታል፡፡ ኪዳን ያደርሱበታል፡፡ በጥንተ ቤተ ክርስቲያን
ሥርዓት ሥርዓተ ጥምቀት ይፈፀምበታል፡፡ በምዕራብ አቅጣጫ መዘምራን የሚዘምሩበት ቅኔ
የሚቀኙበት ማህሌት ቆመው የሚያስቀድሱ ሲሆን ንፍቅ ዲያቆናት የአናጉንስጢስ መዘምራን
በዚህ ስፍራ ያስቀድሳሉ፡፡
በዚህ ክፍል በደቡብ ምሥራቅ በኩል የሚገኘው ቦታ የሴቶች መቆሚያ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን
ሥርዓት ወንድ እና ሴት አብረው መቆም ስለማይችሉ በመጋረጃ ይጋረዳል፡፡ ምሥራቅ
የካህናት፣ በሰሜን የወንዶች፣ በደቡብ የሴቶች መግቢ ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአራቱም
ማዕዘናት አቅጣጫዎች አራት ወይም ሦስት በሮች አሉዋት፡፡
2. ቅድስት
ቅድስት ማለት ቀጥተኛ ትርጉም የተመረጠ የተለየ ማለት ነው፡፡ ይክ ክፍል የሚገኘው በቤተ
ክርስቲያን ማዕከላዊ ቦታ ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ በስብከተ ወንጌል ሰዓት መምህራን ቆመው
የሚያስተምሩበት ክፍልም ነው፡፡ ካህናት መዕመናንን የሚያቆርቡበት ቦታ ነው፡፡ በተክሊልና እና
በቁርባን ለሚጋቡ ሙሽሮች ሥርዓተ ተክሊል የሚፈፀምበጽ ነው፡፡ በስቅለት ዕለት ሥርዓተ
ፀሎት ይፈፀምበታል፡፡ ካህናት ኪዳን ዘነግህ ያደርሱበታል፡፡ የማይቆርቡ ምዕመናን በዚህ ቦታ
ቆመው ማስቀደስ አይችሉም፡፡
3. መቅደስ
ስያሜው ከብሉይ ኪዳን ከቅድስተ ቅደሳን አሰያየም ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በዚህ
ውስጥ ህብስት ወደ አማናዊ ሥጋ መለኮት ወይኑ ወደ አማናዊ ደመ መለኮት በፀሎተ ቅዳሴ
የሚለወጥበት ሥርዓተ ቅዳሴ የሚመራበት ቅዳሴ ሥጋው እና ቅዳሴ ደሙ የሚፈተትበት ነው፡፡
መንበረ ታቦቱ እና ሌሎች ንዋየ ቅድሳት በዚህ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ክፍል ከርዕሰ
ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ዲያቆናት ድረስ ያስቀድሱበታል፡፡ ሥጋ ወደሙን ይቀበሉበታል፡፡
ወደዚህ ክፍል መግባት የሚችሉት ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ውጫዊ ክፍሎች እና አገልግሎታቸው

ሀ/ ቤተልሔም፡- ማለት የእንጀራት ቤት ማለት ነው፡፡ ቤተልሔም ከቤተ መቅደስ በስተምሥራቅ በኩል
የሚሰራ ቤት ነው፡፡ ምሳሌነቱ ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ
ቦታ መግባት የሚችሉት ዲያቆናት እና ከድቁና በላይ ማዕረግ ክህነት ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ ቤት
ለቅዳሴ የሚቀርበው ህብስትና ወይኑ ይዘጋጅበታል፡፡ ክህናት እና ዲያቆናት ቅዳሴ በሚጀመርበት ጊዜ

5
ህብስቱን በመሰበ ወርቅ ወይኑን በፅዋ ከቤተልሔም ወደ ቤተ መቅደስ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ምሳሌነቱ
ጌታችን በቤተልሔም ተወልዶ በቀራንዮ የመሰቀሉ ምሳሌ ነው፡፡ ሉቃስ 2÷6-12 ማቴ 27÷45-30

ለ/ ግብር ቤት:- ለመስዋዕትነት የተመረጡ ስንዴ የሚሰየምበት ቤት ሲሆን ካህን ወይም መነኮሳት
መስዋዕቱን ይሰይማሉ፡፡ ያዘጋጃሉ፡፡

ሐ/ ዕቃ ቤት፡- ንዋየ ቅድሳት ማስቀመጫ ቤት ነወ፡፡ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉ ንዋየተ
ቅድሳት በክብር ሊቀመጡ ይገባል፡፡ ለሌላም አገልግሎት ማዋል አይቻልም፡፡ ቅጣትም ያመጣል፡፡ ዳን
5÷1-4 ዘፀ 30÷9

መ/ ቤተ ምርፋቅ (ደጀ ሰላም)፡- ምርፋቅ ማለት ፈለቀ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን የምግብ ቦታ
ወይም ዳስ ማለት ነው፡፡ ይህ ቦታ ከቤተ መቅደሱ በስተ ምዕራብ ይሰራል፡፡ ምዕመናን ለካህናት
የሚሆነውን ምግብ ይዘው ሲመጡ የሚያስቀምጡበትንና የሚመገቡበት ቦታ ነው፡፡ እንዲሁም
አገልግጋዮች ከሌላ ሩቅ ደብር ሲመጡ የሚያርፉበት ቦታ ነው፡፡ የገነት ምሳሌ ነው፡፡

ሠ/ ክርስትና ቤት፡- በ40 እና በ80 ቀን ሀብተወልድና ስመ ክርስትና ለመቀበል የሚመጡ ህፃናት ከሌላ
እምነት የተመለሱ ኢ አማንያን አምነው የሚጠመቁበት ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት ቤቶች ቤተ ክርስቲያን
ሲሰራ አብረው መሰራት ያለባቸው ናቸው ማለት ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን የሚሰሩ ማናቸውም ነገሮች ምሳሌነት ያላቸው ቢመለከቷቸው በራሳቸው ቃለ


እግዚአብሔርን የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡

ሀ/ ቅፅር ወይም የግቢው አጥር(ከለላ)፡-የሬደኤተ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው፡፡ ቅፅር ለቤተ መቅደስ ቤዛ፣
አምባ፣ ከለላ እንዲጠበቅ ነው፡፡ በቤተ መቅደስ ለተመሰለ የሰው አካል ቤዛ፤ አምባ ሆኖ ከፀበ አጋንንት
የሚጠብቀን ረድዔተ እግዚአብሔር ነው፡፡

ለ/አፅድ (ዕፅዋት)፡- በቤተ መቅደስ ዙሪያ ባለው በብዛት ተተክለው የሚገኙ ዕፅዋት አለ፡፡ የሰውን ልጅ
ከጥፋት የሚጠብቁ የዕልፍ አዕላፋት መላዕክት ምሳሌ ናቸው፡፡ እፅዋት በብዛት ሆነው እንደሚታዩት
ቅዱሳን መላዕክት በብዛት ሆነው ሰውንም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ይጠብቃሉ፡፡ በመንገድ ሁሉ ይጠብቁ
ዘንድ መላዕክት ስላንተ ያዛቸውል፡፡ እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሀል፡፡ መዝ 9÷11

ሐ/ ደወል (መንቅ)፡- ደወል ለመንፈሳዊ አገልግሎት መዋል የጀመረው በኖህ ዘመን ነው፡፡ ደወል ካህናት
ለአገልግሎት እንዲወጡ፣ ለመጥሪያነት ያገለግላል፡፡ ደወል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እራሱን የቻለ ሕንፃ
ተሰርቶለት የሚገኝ ሲሆን ይህም ደወል ቤት ይባላል፡፡ ደወል ቤተ ክርስቲያን አደጋ በሚደርስበት ጊዜ
ምዕመናንን ትሰበስብበታለች፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ ስርዓተ ቅዳሴን ለማሳወቅ፣ ፃኡ ንዑሰ ክርስቲን
በሚባልበት ጊዜ በእግዚኦታ ጊዜ፣ ዕርገት ሲወርድ ይደወላል፡፡ በንግስና ለሌሎች የተለያዩ አገልግሎቶች
ይውላል፡፡ ምሳሌነቱ የመጥመቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ ስብከት ነው፡፡ አንድ ቤተ ክርስቲያን አቅምና
ስፋት ሰንበት ትምህርት ቤት፣ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ቢሮዎችና የአብነት ትምህርት ቤት ይኖራሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያን ማድረግ ስለሚገባ እና ስለማይገባን

1. ማድረግ የማይገባን
በብሉይ ኪዳን ዘመን ነቢዩ ሳሙኤል ከህፃናቱ ጀምሮ የመቅደሱን ሥርዓት ያከብር
እግዚአብሔርንም ይፈራ ነበር፡፡ አፍኒን እና ፍንሐስ ስርዓተ አልበኞች ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር

6
ሳሙኤልን ለበለጠ ክብር አጨው፡፡ ሥርዓቱን ያላከበሩትን አፍኒንና ፊንሐስን በሞት ቀጣቸው፡፡
1ኛ ሳሙ 2÷12
 ጫማ አድርጎ መግባት አይፈቀድም፣ ዘፀ 3÷5
 የሚበላና የሚጠጣ ይዞ መግባት ክልክል ነው፤
 የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ለግል ጥቅም ማዋል ያስቀጣል፣ ዘፀ 30÷9
ት/ዳን 5÷23
 በቅፅረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መገበያየት እግዚአብሔር አይወድም፣ ማቴ 21÷13
 በማህበር ፀሎት ወቅት የግል ፀሎት ማድረግ አይፈቀድም፣
 ከቤተ መቅደስ ቅዳሴ አቋርጦ መውጣት አይገባም፡

2. ማድረግ የሚገባን
 የግል ንፅህናችንን መጠበቅ፣ ንፁህ ልብስ መልበስ ይገባናል፡፡ አቤል ንፀህ መስዋዕት
ስለአቀረበ እግዚአብሔር ተቀብሎታል፡፡ ዘፍ 4÷
 ነጠላን በመስቀል ምልክት አጣፍቶ መልበስ
 ማማተብ

ምዕራፍ ሁለት

ሥርዓተ ቅዳሴ

ቅዳሴ ማለት ቀደሰ፣ አመሰገነ፣ ባረከ፣ አከበረ፣ ለእግዚአብሔር መርጦ ሰጠ ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን
የቃሉ ትርጉም ማወደስ፣ መባረክ፣ ማመስገን ማለት ነው፡፡ በጠቅላላ ሥርዓተ ቅዳሴ ማለት የምስጋና
መርሐግብር (የምስጋና ሥርዓት) ማለት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ለምትፈፅምባቸው፣ በረከቷን ከምታካፍልባቸው አገልግሎቶች አንዱና


ዋነኛው ቅዳሴ ነው፡፡ ቅዳሴ ለፀሎት ጥያቄያችን መልስ የምናገኝበት፣ በዜማ እግዚአብሔርን
የምናመሰግንበት እና በሥጋ ወደሙ የምንታተምበት አገልግሎት ነው፡፡ ቅዳሴ፣ ትምህርት፣ ፀሎት፣
አምልኮትና ባርኮትን ያካተተ የሥርዓተ አምልኮ ክፍል ነው፡፡

የሥርዓተ ቅዳሴ አከፋፈል

 ሥርዓተ ቅዳሴ በ3 ይከፈላል፡፡

1ኛ. የዝግጅት ክፍል (ግብዓተ መንጦላዕት)፡- ይህ ክፍል ዋናው ክህን ቅዳሴውን ከመጀመሩ በፊት
በንዋያት ላይ የሚጸልየው ወደ መንጦላዕት ከመግባቱ አስቀድሞ የሚፀልየው የፀሎት ጊዜ ነው፡፡
በሥርዓቱ የተደነገገውን ፀሎት ከፈፀመ በኃላ ሁሉም ዝግጁ መሆናቸውን ካየ በኃላ ወደ ቅዳሴው
ይገባል፡፡ ፀሎቱ አልቆ ይህቺ ሰዓት ምን ያህል የምታስፈራና እስከሚለው ድረስ ያለው የዝግጅት ክፍል
ይባላል፡፡ ዋናው ቄስ ልብሰ ተክህኖ ከመልበሱ በፊት ከእርሱ የሚበልጥ ካህን (ጳጳስት) ካሉ አስባርኮ
ይለብሳል፡፡ ከሌለ ደግሞ ራሱ ባርኮ ይለብሳል ማለት ነው፡:

7
2ኛ. የትምህርት ክፍል፡-የትምህርት ክፍል የሚባለው ዋናው ካህን (ይህች ቀን መምን ያህል
የምታስፈራናት ብሎ ከሚጀምረው አንስቶ ዋናው ዲያቆን ፀልዩ በእንተ ሰላም እስከሚለው ድረስ ያለው
የትምህርት ክፍል ይባላል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የቅዱሳን ነቢያት ትንቢት፣ የሐዋሪያት መልዕክታት
እና የጌታችን ቅዱስ ወንጌል ይነበባል፡፡

3ኛ. የፍሬ ቅዳሴ ክፍል፡- ፍሬ ቅዳሴ የሚባለው ሠራዒው (ዋናው) ቀዳሽ ካህን አኮቴተ ቁርባን ዘ…
ብሎ ጀምረው ዋናው ዲያቆን "እትው በሰላም (በሰላም ወደ ቤታችሁ ግቡ ብሎ ህዝቡን
እስከሚያሰናብትበት ያለው የቅዳሴ ሰዓት ነው፡፡

በቅዳሴ የሚሰየሙ አገልጋዮች

በቅዳሴ የሚሰየሙ አገልጋዮች ቁጥራቸው 5፣7፣12፣24 ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሲሰየሙም

 ሠራዒ (ዋና) ካህን (ቅዳሴውን የሚመራው፣ የሚባርክ፣ የሚያቆርበው ነው፡፡


 ንፍቅ (ተጨማሪ) ካህን (ዋናውን ካህን ያግዛል፤ ለእርሱ የተመደበውን ያከናውናል፡፡
 ሠራዒ (ዋና) ዲያቆን (ደሙን የሚያቀብለው ይህ ነው፣
 ንፍቅ (ተጨማሪ) ዲያቆን (ለእርሱ የተመደበውን ይፈፅማል፣
 ሰሞነኛ (ፍሬ ሰሞን ተብሎ ይሰየማሉ፣ መብራት ያበራል፣ጥላ ይይዛል
 አምስት መሆናቸው፡- የአምስቱ አዕማደ ምስጢር ምሳሌ ነው፡፡
 ሰባት መሆናቸው፡- የሰባቱ ምስጢራት ወንጌል ምሳሌ ነው፡፡
 አስራ ሁለት መሆናቸው፡- የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ምሳሌ ነው፡፡
 ሃያ አራት መሆናቸው፡- የሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌ ነው፡፡

በሰማይ ባለው የእግዚአብሔር መቅደስ የሚያገለግሉት ሊቃነ ካህናት ቁጥራቸው ሃያ አራት ነው፡፡ ራዕ
4÷11

በሁሉም ቤተ ክርስቲያን የሚታየው ቁጥር ከላይ እንዳየነው አምስት ልዑካን ናቸው፡፡ ይህም በወንጌል
ተፅፎ ስለምናገኘው ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ከገለፀባት የደብረ ታቦር ምስጢር ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ከብሉይ ኪዳን ሙሴና ኤሊያስ፣ ከሐዋሪያት ጴጥሮስ፣
ዮሐንስና ያዕቆብ በተራራው መገኘታቸው ቤተ ክርስቲያን ብሉይም ሐዲስም የሚነገርባት ለመሆኗ
ነው፡፡

የደብረ ታቦር ተራራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነቢያት የሐዋሪያት የሕያዋን እና የሙታን አምላክ
መሆኑን የገለፀበት ነው፡፡ ከሙታን ሙሴን፣ ከሕያዋን ኤሊያስን ማምጣቱ ለዚህ ነው፡፡ ዛሬም በቅድስት
ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ሥርዓት የጌታችን አምላክነቱ፣ ስቅለቱ፣ ሞቱና ትንሳዔው ያደረጋቸው ድንቅ
ተአምራት ሁሉ የሚገለፅበት ነውና ደብረ ታቦር ይህ ሁሉ የተነገረባት ስለሆነች የመቅደሱ ምሥጢር
ምሳሌ ናት፡፡ በደብረ ታቦር ጌታችን አለ፡፡ በመቅደሱ የቃል ኪዳኑ ታቦት አብሮ አለ፡፡ እንደ ሙሴ እና
ኤሊያስ ሁለት ቀሳውስት አሉ፡፡ እንደ ሦስቱ ሐዋሪያት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ሦስቱ ዲያቆናት
አሉ፡፡ አምስቱ ልዑካን የሚባሉትም ቀዳሲን እነዚህ ናቸው፡፡

ከቤተልሔም ወደ መቅደስ

ቅዳሴ በሚገባበት ጊዜ ቀዳሽ ልዑካን ከቤተልሔም ተነስተው ወደ መቅደሱ ህብስቱን በመሰበወርቅ


ወይኑን በፅዋ አድርገው ይገባሉ፡፡ ይህም ምሳሌነቱ ከድህነታችን ጋር የተያያዘ ታላቅ ምሥጢር ነዉ፡፡

8
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ተወልዶ በቀራንዮ የመሰቀሉ ነገር ነው፡፡ ክህናቱ ከቤተልሔም
ሲመጡ በማዕጠንት እያታጠነ ደወል እየተደወለ ወደ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አስቀዳሻ ሁሉ ቦታውን ይዞ ቀጥ
ብሎ ይቆማል፡፡ ህዝቡም ዕለታቱ ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ሐሙስ ከሆነ "እምነ በሀ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
ሥርጉት አረፈቲሃ ወሥዕልት በእንቆጳዝዮን ረቡዕ፣ አርብና ቅዳሜ ከሆነ "መስቀል አብርሐ ከዋክብት
አሰርገዋስማ እምኩሉ ፀሐየ አርአየ ይባላል፡፡ እሁድ (ሰንበት) ኩሉ ዘገበረ ለፅድቅ ፃድቅ ዉእቱ
ወዘያከብር ሰንበተ ኢየበል ፈላሲ ዘገባ ሀበ እግዚአብሔር ይፈልጠኒቱእም ህዝቡ ይላሉ፡፡

ልብሰ ተክህኖ

የእግዚአብሔር አገልጋዮች ካህናት በቤተ መቅደስ የተለየ ልብስ በመልበስ እንዲያገለግሉት ይወዳል፡፡
ስለዚህም የአለባበስ ሕግ አዟል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደነገረው አሮንና ልጆቹ ናዳብን፣ አብዩድ፣
አልዓዛር፣ ኢታምርን ለክህነት ከመመረጣቸው በኃላ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡፡ ዘፀ 25÷2-4
በመቀጠልም እግዚአብሔር የሚሠሩአቸው ልብሶች ምንምን እንደሆኑ ይዘረዝራል፡፡ ዘፀ 28÷40

ሀ) የካህናትና እና የዲያቆናት ልብስ


ካህንና ዲያቆን የሚለብሰው ልብሰ ተክህኖ ልዩነት አለው፡፡ የካህኑ ካባ ሲኖረው የዲያቆኑ ካባ
አይጨምርም፡፡ ግን በሁለቱም ልብስ ላይ አምስት ዘርፎች (ላንቃዎች) አሉት፡፡ ይህም የአምስቱ
ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ላንቃ የሌለው ልሙጥ የሆነም ካባ ይለብሳል፡፡ የተለያዩ
ቀለሞች ያሏቸው ልብሶች ቢለብሱም በዋናነት ነጭ ልብስ ይታዘዛል፡፡ የፀሎተ ሐሙስ ዕለት ግን ጥቁር
ልብሰ ተክህኖ እንዲለበስ ያዛል፡፡

ለ) አክሊል (ቆብ)

ካህናት በቅዳሴ ጊዜ አክሊል በማድረግ ያገለግላሉ፡፡ ክብር፣ ውዳሴ፣ ኃይል ልትቀበል ይገባሃል እያሉ
በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ፡፡ ራዕ 4÷11

ምሳሌነቱ ጌታችን የደፋው የሾህ አክሊል (የድህነታችን ምሳሌ) ነው፡፡ ሁለተኛ ወደፊት የሚጠብቀን
የድህነት ክብር ምሳሌ ነው፡፡ "ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፡፡ ወደፊት የፅድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፡፡" 2ኛ
ጢሞ 4÷8

ሐ) ሞጣሕት

ካህናት በቀሚስና ካባው ላይ የሚደርቡት ሞጣሕት ተብሎ ይጠራል፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደነበረው አሮን
በልብሰ ተክህኖ ላይ ኤፋዱን ይደርብ ነበር፡፡ ሞጣሕት ከትከሻ እስከ እግር ጫፍ ድረስ ይደርሳል፡፡
የረጅም መንግድ ቅርፅ አለው፡፡ ምሳሌነቱ ክርስትና ለረጅም የሃይማኖት ምሳሌ ነው፡፡

አስራ አራቱ ቅዳሴ

1. ቅዳሴ ሐዋሪያት፡- ይህ ቅዳሴ አባቶቻችን ሐዋሪያት በአንድነት የተናገሩት ነው፡፡


2. ቅዳሴ እግዚ፡- ይህ ቅዳሴ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋሪያት ከሞት ከተነሳ
በኃላ ያስተማራቸው ናቸው፡፡ ከሰባቱ ኪዳናት ውስጥ አንዱ ቅዳሴ እግዚ ነው፡፡
3. ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፡- የዚህ ቅዳሴ ደራሲ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ ወልደ
ነጎድጓድ ማለት የነጎድጓድ ልጅ ማለት ነው፡፡

9
4. ቅዳሴ ማሪያም፡- የእመቤታችን ቅዳሴ የደረሰው አባ ሕርያቆስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተደረሰ
ነው፡፡
5. ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት፡- ሠለስቱ ምዕት ማለት ሦስት መቶ አስራ ስምንት ማለት ነው፡፡
ቁጥራቸው የተጠራው ይህን ቅዳሴ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በአንድነት የተናገሩት አርዮስንና
ተከታዮቹን አውግዘው ሃይማኖትን አቅንተው ያባቶች ሐዋሪያትን ሥርዓት አፅንተው ከወሰኑ
በኃላ ነው፡፡
6. ቅዳሴ አትናቴዎስ፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው የእስክንድሪያው ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ
አትናቴዎስ ነው፡፡ እሱም በኒቂያ ጉባዔ ከ318ቱ ቅዱሳን አበው ጋር አርዮስን ያሳፈረው ነው፡፡
7. ቅዳሴ ባስልዮስ፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው የቂሣሪያ ኤጵስቆጶስ የነበረው የጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
ወንድም የሆነው ባስልዮስ ነው፡፡
8. ቅዳሴ ጎርጎርዮስ (ዘኑሲስ)፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው የኒሲስ ኤጵስቆጶስ የነበረው የቅዱስ ባስልዮስ
ወንድም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነው፡፡
9. ቅዳሴ ኤጴፋንዮስ፡- የቆጵሮስ ደሴት ሊቀጳጳስ ነው፡፡ ይህን ቅዳሴ የደረሰው ቅዱስ ኤጴፋንዮስ
ይባላል፡፡
10. ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው የቄስጥንጥንያው ኤጴስቆጶስ ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ ነው፡፡
11. ቅዳሴ ቄርሎስ፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው ንስጥሮስ በተወገዘበት የኤፌሶን ጉባዔ ከሁለት መቶ
ቅዱሳን አበው መካከል አንዱ የነበረው ቅዱስ ቄርሎስ ነው የደረሰው፡፡
12. ቅዳሴ ቅደስ ያዕቆብ (ዘሥሩግ)፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው የሥሩግ ኤጲስ ቆጶስ የነበረው ቅዱስ
ያዕቆብ ነው፡፡
13. ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው የእስክንድሪያ ኤጲስ ቆጶስ የነበረው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ
ነው፡፡
14. ቅዳሴ ጎርጎርዮስ ካልዕ፡- ይህን ቅዳሴ የደረሰው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ካልዕ ነው፡፡ ካልዕ መባሉ
ከመጀመሪያው ጎርጎርዮስ ሊለየው ነወ፡፡

ሦስቱ የዜማ ዓይነቶችና የሚቀደስባቸው ጊዜ

1. ግዕዝ
2. ዕዝል
3. አራራይ

ቅዳሴ ግዕዝ እና ዕዝል የሚደስባቸው ዕለታት ተለይተው የታወቁ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ፆም በሚሆንበት
ወራት በግል ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው ግዕዝ ይቀደሳል፡፡ በበዓላት ጊዜ ደግሞ ዕዝል ይቀደሳል፡፡
ዕዝል ወይም ግዕዝ መሆኑ የሚለየው ወንጌል ከመነበቡ በፊት "በወንጌል መረሐአነ" የሚለው ከተዜመ
ቅዳሴው ግዕዝ ነው፡፡ "ትፈሰሑ በእግዚአብሔር" ከተባለ ዕዝል ነው፡፡

ግዕዝ እና ዕዝል የሚቀደስበት ጊዜ

1. ከስብከት እስከ ዓብይ ፆም ዋዜማ - ዕዝል ይቀደሳል፤


2. ከዓብይ ፆም ዋዜማ እስከ ሆሣዕና - ግዕዝ ይቀደሳል፣
3. ከሆሣዕና እስከ ሰኔ 16 ድረስ - ዕዝል ይቀደሳል፡
4. ከሰኔ 17 እስከ መስከረም 25 - ግዕዝ ይቀደሳል፣

10
5. ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 - ዕዝል ይቀደሳል፣
6. ከህዳር 7 እስከ ስብከት - ግዕዝ ይቀደሳል፣

ከግዕዝ እና ከዕዝል ዜማ በተጨማሪ አራራየረ ዜማ አለ፡፡ ይህ ዜማ የሚቀደስበት የተወሰነ ጊዜ


የለውም፡፡ በግዕዝ እና በዕዝል ዜማ ጣልቃ ይዜማል፡፡ ግዕዝ በሚቀደስባቸው ወቅቶች በዓለ ንግስ ከሆነ
ዕዝል ይቀደሳል፡፡ እንደገና ማህሌት በተቆመ ጊዜ ምንግዜም ቅዳሴው ዕዝል ነው፡፡

በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ የምንጠቀምባቸው ንዋያተ ቅድሳት

1) ታቦት፡- ማለት ማደሪያ፣ መገለጫ፣መታያ ማለት ነው፡፡ ታቦት የእግዚአብሔር መገለጫ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከብሉይ ኪዳን ከወሰደቻቸው ንዋያተ ቅድሳት አንዱ ታቦት ነው፡፡ እግዚአብሔር አስርቱን
ትዕዛዛት በእጁ ጽፎ ያስቀመጠበትና ለሙሴ የሰጠው ቅዱስ ንዋይ ነው፡፡ በታቦቱ ላይ ፃሕሉን እና
ፅዋውን በማስቀመጥ እናከብርበታል፡፡ ዘፀ 34÷29

ታቦቱ የእግዚአብሔር ማደሪያነው፡፡ ያለ ታቦት መስዋዕት አይሰዋም፡፡በቅዳሴ ጊዜ ህብስቱ እና ወይኑ


ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ቄሱ ሥርዓተ ቅዳሴውን የሚያከናውነው ህብስቱን ሥጋ መለኮት መሆኑን እና
ወይኑን ወደ ደመ መለኮት የሚለውጠው በዚህ በታቦቱ ላይ ነው፡፡

2) መስቀል፡- ጌታችን እና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት ሰይጣን ድል


የተነሳበት የመዳናችን ዓርማ ነው፡፡ መስቀል ምዕመናንን እና ንዋያተ ቅድሳትን ለመባረክ

የመስቀል ዓይነቶች

1. የእጅ መስቀል፡- ይህ የእጅ መስቀል የክህነት ማዕረግ ያላቸው አባቶች ብቻ የሚይዙት ሲሆን
ምዕመናንን ለመባረክ ይጠቀሙበታል፡፡
2. የመፆር መስቀል፡- ይህ መስቀል ዲያቆናት በቅዳሴ ጊዜ የሚሰብኩበት ሲሆን በመጠኑም ከፍ
ይላል፡፡
3. ዕርፈ መስቀል፡- ዲያቆኑ ለምዕመናን ክቡር ደሙን የሚያቀብልበት ነው፡፡
4. እፀ መስቀል፡- ጌታችን የተሰቀለበት ትልቁ መስቀል ነው፡፡
5. የአንገት መስቀል፡- ምዕመናን በማህተባቸው አስረው በአንገታቸው በማድረግ ለጌታችን ያላቸውን
ፍቅር የሚገልጹበት ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን መስቀል የሚዘጋጅባቸው መሣሪያዎች እና ምሳሌያቸው

1. የእንጨት መስቀል፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ነው፡፡


2. የወርቅ መስቀል፡- ወርቅ ንፁህ እንደሆነ የጌታችን የንፅህና ምሳሌ ነው፡፡
3. የብር መስቀል፡- የአስቆሮቱ ይሁዳ በ30 ብር ጌታን መሸጡን ለማስታወስ ነው፡፡
4. የነሐስ መስቀል፡- የብሩህነቱ ምሳሌ ነው፡፡
5. የመዳብ መስቀል፡- የአማናዊ የደሙ ምሳሌ ነው፡፡ (መዳብ ቀይ ስለሆነ)
6. የብረት መስቀል፡- የተቸነከረበት እና ጎኑ የተወጋበት ምሳሌ ነው፡፡ (በአምስቱ ቅንዋተ
የመቸንከሩ ምሳሌ ነው፡፡

11
ለመስቀል ክብር የምንሰጠው ለምንድነው?

1. ክርስቶስ መስዋዕት ሆኖ እራሱን የሰዋበት እውነተኛ መንበር በመሆኑ፤


2. የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት፣ እኛ የዳንበት፣ የነፃነት አርማችን፣ የክርስቲያኖች አንድነት
የተመሠረተበት የድህነት አርማችን ስለሆነ፣
3. መስቀል መለኮታዊ ፍቅር የተገለፀበት ስለሆነ፣

መብራት

 መጽሐፈ ቅዱሳዊ ትውፊት ምሳሌነት አለው፡፡ በቀድሞ ጊዜ ለሙሴ ሥርዓት አድርጎ


ሰጥቶታል፡፡ ዘፀ 40÷2-4 የዘይት መብራት ነው፡፡ በአሁኑ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጠዋፍ
ነው፡፡
 መብራት በሚበራበት ወቅት በተለይ ቅዱሳት መፃሕፍት ማለትም መልዕክታት፣ ግብረሐዋሪያት
እና ወንጌል ሲነበብ ይበራል፡፡
 መቅረዝ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡
 መብራት (ብርሃን) የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡

መጎናፀፊያ

ትልቅና እና አራት ማዕዘን ያለው ባለገበር ከወርቀ ዘቦ የሚሠራ ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ መንበሩ የሚለብሰው
ለአከብሮተ ስጋ ወደም የሚለብስ ነው፡፡ ታቦት በወጣ ጊዜ የሚጎናፀፈው ነው፡፡

መንጦላዕት (መጋረጃ)

በሦስቱ የመቅደስ በር የሚጋረዱ ሁለት ክፍያ ያለው መጋረጃ ነው፡፡ በሁለት መከፈሉ ጌታ በተሰቀለ
ጊዜ መልዐኩ የቤተ መቅደስን መጋረጃ የመሰንጠቁ ምሳሌ ነው፡፡ ማቴ 27÷51 ስገዱ ሲባል ይከፈታል፡፡
ፃኡ ንዑስ ክርስቲያን ሲባል ይዘጋል፡፡ በመጀመሪያ መገለጡ ጌታ በሥጋ የመገለጡ ምሳሌ ነው፡፡ ፃኡ
ሲባል መዘጋቱ ኢአማንያን (የማያምኑ) ከእኔ ወግዱ ሲል ነው፡፡ ማቴ 25÷41 ዕርገት ሲወርድ መከፈቱ
አይሁድ ጌታን ሁሉ እንዲያው ብለው በገበያ ቀን ልብሱን ገፈው የመስቀላቸው ምሳሌ ነው፡፡ መዘጋቱ
ደግሞ በክብር የመነሣቱ ምሳሌ ነው፡፡

መንበር

መንበር ማለት የታቦቱ መቀመጫ ዙፋን ማለት ነው፡፡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከብረት ወይም ከእንጨት
ይሰራል፡፡ አገልግሎቱም በቤተ መቅደስ ታቦቱ ይቀመጥበታል፡፡ ፀሎት ይፀለይበታል፣ መስዋዕት
ይሰዋበታል፡፡ በመንበሩ ላይ በመደበኛነት የሚቀመጡት ንዋያተ ቅድሳት ታቦት፣ ሥዕለ ማሪያም፣ ምስለ
ፍቅሩ ወልዳ ሲሆን በቅዳሴ ጊዜ ስጋ ወደሙን ለመፈተት የምንገልገልባቸው ፃሕል፣ ጽዋ፣ ማሕፈድ፣
እርፈ መስቀል፣ መስቀል፣ እጣን ይቀመጡበታል፡፡ መንበሩን የሚዳስሱት እና የሚገለገሉበት ቀሳውስት
ናቸው፡፡ ዲያቆናት ግን ከበውት ይቆማሉ፡፡ምሳሌነቱ የእመቤታችን እና የጌታ ምሳሌ ነው፡፡ አንድም
የመንበረ ፀባኦት ምሳሌ ነው፡፡

12
ፃሕል

ፃሕል የሥጋው ማስቀመጫ ነው፡፡ ይኸውም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናሀስ ከብረት የሚሰራ ነው፡፡ ምሳሌነቱ
ጌታ የተወለደበት የግርግም ምሳሌ እና ጌታ የመቃብሩ ምሳሌው ነው፡፡

ጽዋዕ

ጽዋዕ፡- የክርስቶስ ክቡር ደሙ የሚቀርብበት ቅዱስ ንዋይ ነው፡፡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ፣ ከነሀስ፣
ከብረት የሚሰራ ነው፡፡ ምሳሌነቱ የጌታ የመቃብሩ ምሳሌ ነው፡፡ አንድም መላዕክት ከጌታችን የፈሰሰውን
ደም ተቀብለው በዓለም ሁሉ የረጩበት የብርሃን ጽዋ ምሳሌ ነው፡፡

ዕርፈ መስቀል

የክርስቶስን ደም ለመቀበል የሚያገለግል የማንኪያ ዓይነት ሲሆን ጽዋው ከተሰራበት ቁስ የተሰራ ነው፡፡
በደሙ መያዣ በኩል ጎድጎድ ያለ ነው፡፡ ከእጁ አካባቢ መያዣዋ መስቀል ያለበት ነው፡፡ ይህም የሱራፌ
ጉጠት ምሳሌ ነው፡፡ የሱራፌ ጉጠት ፍም ይዞአል፣ እርፈ መስቀል የመለኮትን እሳታዊ ደም ይይዛል፣
የሱራፌ ጉጠት የያዘው ፍም የኢሳያስን ከንፈር ከለምፅ አድኗል፡፡ ደሙም ምዕመናንን ከኃጢአት
አድኗል፡፡ ኢሳ 6÷6-8

አውድ

አውድ ማለት አደባባይ ማለት ነው፡፡ በቁርባን ጊዜ ፃሕል የሚቀመጥበት ሰፋ ያለ ንዋይ ነው፡፡ ሥጋው
እንዳይነጥብ (እንዳይወድቅ) መጠበቂያ እና ሳፋ ጎላም ከበርም ብሎ የሚታይ ነው፡፡ እርሱም የሚሠራው
ከብረት፣ ከነሀስ፣ ከእንጨት ይሰራል፡፡

ምሳሌነቱም ፡- ጌታ የተፈረደበት የጲላጦስ አደባባይ ምሳሌ ነው፡፡

ማሕፈድ

የተመረጠ ጨርቅ የሚሰራ የሥጋውና የደሙ መሸፈኛ ነው፡፡ 5 ማሕፈንት አገልግሎት ይሰጥባቸዋል፡፡
አንደኛው ፃሕሉ ላይ ይነጠፋል፡፡ 3ቱ ህብስተ ቁርባኑ ይሸፈንባቸዋል፡፡ አንዱ የፅዋ መሸፈኛ ነው፡፡
ምሳሌነቱ ፡- ጌታ ሲወለድ በጨርቅ የመጠቅለሉ ምሳሌ ነው፡፡

፡- አንድም ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታ የገነዙበት ምሳሌ ነው፡፡

ጽንሐሕ

ጽንሐሕ እጣን ማጠኛ (ማሳረጊያ) ማለት ነው፡፡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከብረት፣ ከነሀስ ይሰራል፡፡ ዘዳ 30÷6-
10ምሳሌነቱ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ እጣኑ የሥጋ፣ ፍሙ የመለኮት፣ የወርቅ ዘንጉ የመለኮት
ምሳሌ ነው፡፡

መሶበ ወርቅ

ዲያቆኑ መስዋዕቱን ከቤተልሔም ወደ ቀራንዮ ወደምትመስለው ቤተ መቅደስ የሚወሰወድበት ነው፡፡


ከስንደዶ፣ከወርቅ ሊሰራ ይችላል፡፡ምሳሌነቱ

13
 መሶቡ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም የንፅህናዋ ምሳሌ ነው፡፡
 መሶቡ ውስጥ ያለው መና የአማናዊው የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡

መቁረርት ወይም ከሰኩሰት

ቆረ፣ ቀዘቀዘ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ማብረጃ ማለት ነው፡፡ አገልግሎቱ
ለምዕመናን የቅዳሴ ፀበል ማደያ ነው፡፡ እንዲሁም በቅዳሴ ጊዜ ካህኑ እጁን የሚያነፃበት (የሚታጠብበት)
ንዋይ ነው፡፡ ዘፀ 30÷17

ምሳሌነቱ ፡- ጲላጦስ "እኔ ከደሙ ንፁህ ነኝ" ብሎ የታጠበበት ምሳሌ ነው፡፡

ቃጭል (መረዋ)

ቃጭል በቅዳሴ ጊዜ የሚደወል እና ድምፅ የሚሰጥ ከብረት፣ ከመዳብ፣ ከነሐስ ይሰራል፡፡ በሚደወልበት
ጊዜ ቀዳሲያን ከቤተልሔም ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ፣ ፃኡ ንዑስ ክርስቲያን ሲባል፣ በእግዚኦታ ጊዜ፣
ድርባት ሲወርድ እንዲሁም በሰሞነ ሕማማት ጊዜም ለአገልግሎት ይውላል፡፡

ምሳሌነቱ ፡-“መንግስተ ሰማያት ቀርባለች እና ንሰሐነግቡ" ያለውን የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከትና በእግረ
መስቀሉ ተገኝቶ ያለቀሰው የዮሐንስ ወንገላዊው ምሳሌ ነው፡፡

ዣንጥላ

ከነጭ ወይም ወርቃማ ቀለም ካለው ጨርቅ ይሰራል፡፡ ከብረት፤ ከብር ይሰራል፡፡ አገልግሎቱ ታቦት ወደ
ዐውደ ምሕረቱ ሲወጣ፣ ካህናት መስዋዕቱን ለማክበር ወደ ቤተልሔም ሲወርዱና መሥዋዕቱን
አክብረው ከቤተልሔም ወደ ቤተ መቅደስ ሲወጡ እንዲሁም ወንጌል ሲነበብ ይዘረጋል፡፡ ይህም
ለመስዋዕቱ ለታቦቱ እና ለወንጌሉክብር ነው፡፤

ምሳሌነቱ ፡- እስራኤላዊያን በሲና ምድረ በዳ ሲጓዙ ይጋርዳቸው የነበረ ደመና ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም
ሙሴ ለእግዚአብሔር ፅላተ ኪዳኑን ሲቀበል የጋረደው ደመና ምሳሌ ነው፡፡

መቅረዝ

መቅረዝ፡- የመብራት ዕቃ የሻማ ማኖሪያ ማስቀመጫ ማለት ነው፡፡ ዘካ 4÷2

ምሳሌነቱ ፡- የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ የሚበሩት ሻማዎች ደግሞ የቅዱሳን መላዕክት ምሳሌ ነው፡፡

ድባብ

ድባብ እንጨቶች እንደ ምሶሶ ቆመውበላዩ ላይ ጨርቅ በመስፋት የሚሰራ ትልቅ ጥላ ነው፡፡ ላዩ
በነሐስ፣ በብር፣ በመሳሰሉት ይሰራል፡፡

ምሳሌነቱ ፡- እግዚአብሔር ለሙሴ ይገለጥለት የነበረ የግምደ ደመና ምሳሌ ነው፡፡

14
ሙዳይ

ሙዳይ ማለት መኖሪያ፣መጨመሪያ፣ መክተቻ ማለት ነው፡፡ ልዩ አገልግሎቱ የእጣን መሰቀመጫ


(ማቅረቢያ) ነው፡፡

ምሳሌነቱ ፡- ሙዳዩ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡

አትሮኖስ

ከእንጨትና ከብረት የሚሰራ መፃህፍት ሲነበብ የሚዘረጋበት ንዋይ ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ መፃሕፍት
ይነበቡበታል፡፡

ምሳሌነቱ ፡- የእመቤታችን ሲሆን መፃሕፍቱ የጌታ ምሳሌ ነው፡፡

ፍምሐም

ለማዕጠንት የሚሆነው እሳት የሚቀጣጠልበት ነው፡፡

ጉጠት

ፍም ማውጫ (ፀቅም የሚያዝበት) ነው፡፡

ፍሕም

ለእጣን ማጠኛ የምንጠቀምበት ነው፡፡

መፃሕፍት

በቅዳሴ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥበት ነው፡፡

በቅዳሴ ጊዜ የሚታወጁ አዋጆች

ዋና ዋና አዋጆች

1. ተንሥኡ ለፀሎት
2. ፀልዩ በእንተ እገሌ
3. ሥገዱ ለእግዝአብሔር

15
ተንሥዑ ለፀሎት (ለፀሎት ተነሱ)

15 ጊዜያት ያህል ሕዝቡን ለፀሎት ለማትጋት በዲያቆናቱ የሚተላለፉ ትዕዛዝ አዘል መልዕክት ነው፡፡
ሠራጊው ዲያቆን 12 ጊዜ ንፍቁ 3 ጊዜ ይናገራሉ፡፡ 12 መሆኑ የ12 ሐዋሪያት ምሳሌ ነው፡፡ 3 መሆኑ
የሥላሴ ምሳሌ ነው፡፡

በፀሎት ተነሱ ብሎ የተናገረው አዳም ነው፡፡ ጌታ 5ሺህ 5መቶ ዘመን ሲፈፀም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ
አድንሃለሁ ያለውን ይዞ ሲቆጥር ኖሯል፡፡ በኃላም ጌታ በዕለተ ዓርብ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ
ባለ ጊዜ የተናገረው ትንቢት ደረሰ፡፡ የጠቆጠረው ሱባዔ ተፈፀመ፡፡

 አዳም ተንስኡ ለፀሎት (ለፀሎት ተነሱ) አለ፣


 ነፍሳትም እግዚኦ ተሰሐለነ (አቤቱ እዘንልን፣ እራራልን፣ ይቅር በለን አሉ)፣
 ጌታም በአካለ ነፍስ ሆኖ ወርዶ ሠላም ለኩልክሙ (ሠላም ለሁላችን ይሁን) በሲኦል ባሉት
ነፍሳት ላይ ብርሃን ነዛባቸው፣
 ነፍሳትም ምሥለ መንፈስከ (እንደቃልህ ይደረግልን) ከመንፈስህ ጋር እንደቸርነትህ መጠን
ይቅር በለን ብለው ወጥተዋል፡፡

ፀልዩ በእንተ እገሌ (ስለ እገሌ ፀልዩ)

ይህ አዋጅ ሲተላለፍ የምንፀልየው ስለ ማህበራችን አንድነት፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ቤተ ክርስቲን፣ ስለ


መሪዎች፣ ስለ ሠራዊት ፣ ስለ ተጨገሩ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ተሰጥኦ ስለሌለ በለሆሳስ አቡነ ዘበሰማያት
መድገም ይገባናል፡፡

ስገዱ ለእግዚአብሔር በፍርሐት

በቅድስና ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ (መዝ 21÷21) ዲያቆን ስገዱ ለእግዚአብሔር ብሎ ሲያዜም
መስገድይገባል፡፡ ነገር ግን እንሰግዳለን ካልን በኃላ በመቀመጥ የሰገድን መስለን እረፍት የምንሻ ካለን
ይህ አግባብ አይደለም፡፡ መውደቃችን የሞት ምሳሌ ነው፡፡ መነሳታችን የትንሳኤ ምሳሌ ነው፡፡

በቅዳሴ ጊዜ ስንት ጊዜ እንሰግዳለን

በፀሎተ ቅዳሴ ጊዜ ልንሰግድ የሚገቡን ስግደቶች 4 ናቸው፡፡

1ኛ) ካህኑ ፀሎተ ንሰሓ ሲፀልይ (ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት ካህኑ በለሆሳስ የሚፀልየው ፀሎት ነው፡፡)

2ኛ) ዲያቆኑ ስገዱ ለእግዚአብሔር በፍርሀት ብሎ ሲያዝ ነው፡፡

3ኛ) የቆማችሁ ሰዎች እራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ ስገዱ ብሎ ሲያዘን (ለሁለተኛ ጊዜ ካህኑ ፀሎተ
ንሰሓ ሲል፣)

4ኛ) ድርገት ሲወርድ (ቅዱስ ቁርባን) ሊያቀብሉ ሲወጣ እጅ ነስተን እንሰግዳለን፡፡

ራስን ዝቅ ለማድረግ እጅ የምንነሳባቸው ቦታዎች

1. በፀሎተ ቅዳሴ መካከል ካህኑ ከመቅደስ ወጥተው በ4ቱም ማዕዘን ሲባርክ እራሳችንን ዝቅ
በማድረግ ቡራኬውን መቀበል ይገባል፣

16
2. ዲቆኑ በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ ብሎ አዋጅ ሲያሰማ አንገታችንን ሰበር
አድረገን ፀሎተ ንሰሓውን እንቀበላለን፣
3. ዲያቆኑ በሐዋሪያት ሰላምታ እጅ ተነሳሱ ብሎ አዋጅ ሲያዉጅ ሴቶች ሴቶችን ወንዶች ወንዶችን
ሁሉም በየፆታው እጅ ይነሱ ይገባል፣
4. ድርገት ወርዶ ሲመለክ (ሥጋ ወደሙ ሲመለስ) ጎንበስ ብሎ እጅ መንሳት ይገባል፣
5. ኦ ሥሉስ ቅዱስ ሲነበብ፣
6. ዲያቆኑ አድንኑ አርሰቲክሙ (በካህኑ ትባረኩ ዘንድ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ ብሎ ሲያዘን
ነወ፡፡

ሌላው የመጨረሻው ስግደት በፀሎተ ቅዳሴውም ይሁን በማንኛውም ጊዜ የፀሎታችን ፍፃሜ ሰግደን እጅ
ነስተን አቡነ ዘበሰማያት ደግመን ለላቱ ያለንን ሥርኣተ እናጠናቅቃለን፡፡

ፃኡ ንዑስ ክርስቲያን (የክርስቲያን ታናናሾች ዉጡ)

ዲያቆኑ ፃኡ ንዑስ ክርስቲያን ሲል ለመናፍቅነት ተመልሰው ገና ለጥምቀት እና ለቁርባን ያልደረሱ


በትምህርት እና በፀሎት ላይ ያሉ አዳዲስ አማኞች ከህዝቡ መካከል ወጥተው በዐፀድ ሆነው ቀሪውን
ሥርዓት ይከታተላሉ፡፡

የተቀመጣችሁ ተነሱ

ካህኑ ፀሎተ ቡራኬ ከጨረሰ በኃላ ዲያቆኑ ካህኑን ተከትሎ የሚናገረው ቃል ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ
ከደከመ፣ በደዌ፣ በእርግዝና በቀር የሚቀመጥ ስለማይኖር መልዕክቱ ልብን ከመዘንጋት እና ከመሳነፍ
መንቃትን ይመለከታለ፡፡

ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ

ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ማለት ምስጢራዊ ሕገ ወንጌልን በማመን እንድንፀና አንድም እመቤታችን


በአማላጅነቷ እንድናስባት አንድም ሀሳባችን በቤተ ክርስቲያን እንድያረፍ አንድም ጌታ የሚመጣው
በምሥራቅ ነውና ዳግም ምፅአቱን እንድናስብ ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘን እየተዘዋወረ እጅ ለመንሳት
የሚነገር አይደለም፡፡

እናስተውል

የሚነገረውን በጥንቃቄ እንድንሰማ ነው፡፡

ተሰጥዎ መልስ

ሕዝቡ ካህናቱን እየተከተሉ ተሰጥዎ በመመለስ ፀሎቱን መሳተፍ እንዳለባቸው ለማዘከር ነው፡፡

ዑደት

መጀመሪያ ቁርባኑ ከቤተልሔም ሲመጣ መንበሩን ይዞሩታል፣


በፀሎተ እጣን ጊዜ ዲያቆናቱ መብራት፣ መስቀል፣ መፃሐፍ ይዘው ካህኑ እያጠነ መንበሩን 3
ጊዜ ይዞራል፣
ስገዱ ከተባለ በኃላ

17
ከመቅደስ ውጪ (መልዕክታት ከመነበባቸው በፊት)
በወንጌል ጊዜ

ንባብ

ሠራዒው ዲያቆን የጳውሎስ መልዕክት ንፍቅ ዲያቆን የጴጥሮስን መልዕክትን ንፍቅ ቄስ


ግብረሐዋሪያትን በየተራ በ3ቱ ማዕዘናት ያነባሉ፡፡ አራተኛው ወንጌል ዲያቆኑ ለዕለቱ ተስማሚ
መልዕክት ያለውን ከንባቡ ጋር የሚዛመደውን የዳዊት መዝሙር (ምስባክ) ከዘመረ በኃላ ቄሱ ፊቱን ወደ
ምሥራቅ መልሶ ወንጌል ያነባል፡፡

ምሳሌነቱ፡-

አራቱ መፃሕፍት የአራቱ ወንዞች ምሳሌ ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት መነበባቸው አራቱ ወንዞች ከዕፅ
ሕይወት ሥር ፈልቀው ዙረው አጠጥተው አዝርዕትን፣ አትክልትን ከመድረቅ ወደ ለምለም፣ ወደ
ማበብ፣ ወደ ማፍራት እንደሚያደርሱ እነዚህም መፃሕፍት ሰውን ከኃጢያት መድረቅ ወደ ንሰሓ፣ ወደ
ትሩፋት፣ ወደ ክብር፣ ወደ ፍሬ ያደርሱታል፡፡

ምስባክ 5 ጊዜ መባሉ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌ ነው፡፡ ወንጌሉ ከተነበበ በኃላ ልዑካኑም
ህዝቡም በከበረ የወንጌል ቃል እናምናለን እያሉ ይሳለሙታል፡፡

ምሳሌነቱ፡- በዓለም ሁሉ የመሰበኩ ነው፡፡ መሸፈኑ ክብሩን ያመለክታል፡፡

በመቀደስ ማስቀደስ ጊዜ የሚደረግ ጥንቃቄ

 ህሊናን መሰብሰብ
 በፍቅርና በማስተዋል ማስቀደስ
 የሚነገረውን ቃል በጥንቃቄ መስማት
 ወሬ አለማውራት
 ቅዳሴ አቋርጦ አለመውጣት
 የግል ፀሎት አለማድረግ
 ትኩረት የሚስቡ ልብሶችን አለመልበስ (መከናነብ)
 ምግብ ወደ ውስጥ ይዞ አለመግባት
 ድምፅ ያላቸውን መሣሪያዎች ይዞ አለመግባት

ቅዳሴ በማስቀደስ የሚገኝ በረከት

ሀ) ከእግዚአብሔር በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንገኝበታለን፣

ለ) ከቅዱሳን ህብረት እንዲኖረን ያደርገናል፣

ሐ) ምሥጢራትን ለመካፈል ይረዳናል፣

18
ምዕራፍ ሦስት

ሥርዓተ ቁርባን
ቁርባን ማለት ቃሉ የሱርሱት ቃል ሲሆን ትርጉሙም ለአምላክ የሚቀርበውን መባ (እጅ መንሻ) ማለት
ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ስለኃጢአታቸው ሆነ ስለእግዚአብሔር ክብር ብለው የሚያቀርቡት
የእንስሳት ደም ቁርባን ይባላል፡፡

በሐዲስ ኪዳን ግን ቁርባን ማለት እግዚአብሔር እራሱን ከሰው ልጆች ጋር ለማስታረቅ መባ አምሀ
አደርጎ ያቀረበው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዮሐ 1÷29 "የአለም ኃጢአት
የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" በአጠቃላይ በሐዲስ ኪዳን ቁርባን ማለት የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም
ሥጋው እና ደሙ ነው፡፡

3.1 በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ቁርባን ምሣሌዎች

1. መስዋዕተ አቤል፡-

የአዳም ልጅ አቤል ንፁህ ባህሪይ እግዚአብሔር ንፁህ መስዋዕት ይገባዋል ብሎ ከበረት ከበጎቹ
መልካሙን ጠቦት እንከን የሌለበት በግ ማለት ቀንድ ያልነበረው፣ ጠጉሩ ያላረረውን፣ ጥፍሩ
ያልረዘመውን መርጦ አቅርቧል፡፡ ዘፍ 4÷17 ዘፍ 4÷4 ዕብ 11÷4

2. ስለይስሐቅ ፈንታ ለአብርሃም በእፅ ሳቤቅ ተይዞ የቀረበ በግ፡-

እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፡፡ እንዲህም አለው፡፡ አብርሃም ሆይ የምትወደውን አንድ ልጅህን


ይሰሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ አለው፡፡ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መስዋዕት
አደርገህ ሰዋው፡፡ ዘፍ 22÷1-2

አብርሃም ለዚህ ቃል ታዞ በሰተርጅና የወለደውን ይዞ ሄደ፡፡ እንጨትም ረብርቦ ይስሐቅን አጋድሞ


ሾተሉን ከአንገቱ አሳረፈው፡፡ እግዚአብሔርም የአብርሃምን የልቡን ውሳኔ አይቶ ተው ዓለም የሚድነው
በኃያሉ በእኔ በእግዚአብሔር ልጅ እንጂ በአንተ በደካማው ልጅ ደም አይደለምና ተው አለው፡፡ ወዲያው
አብርሃም ሽቅብ ቢያይ በግ በእፀ ሳቤቅ ተይዞ ወረደለት፡፡ ልጁን ፈትቶ በጉን ተቀብሎ ሰውቶታል፡፡
ምሳሌነቱ፡- ይስሐቅ የዘለአለም በግ የጌታ ምሳሌ ነው፡፡

3. ካህኑ መልከፃድቅ ለአብርሃም ያቀረበው ሕብሰትና ወይን ዘፍ 14÷18

4. ከግብፅ የወጡ እስራኤላውያን የሰውት በግ ዘፀ 12

3.2 የሥርዓተ ቁርባን አጀማመር (አመሠራረት)

ቅዱስ ቁርባን የመሠረተው እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሥርዓቱን የጀመረበት ዕለት የሥቅለት
ዋዜማ ፀሎተ ሐሙስ ነው፡፡ (ማቴ 26÷26) "ሲበሉም ሕብስቱን አንስቶ ባረከ፣ አከበረ፣ ለወጠ፣
ጽዋውንም ይዞ አክብሮ ለውጦ ትኩስ ደም አድርጎ ይህ ሥጋዬ ነው፡ ይህ ደሜ ነው ብሎ ሰጥቷቸዋል፡፡

19
አንድም ሕብስቱን አንስቶ ባረከ፣ ቆረሰ፣ ፈተተ፣ አስራ ሦስት አደረገው፣ አንዱን እርሱ በላው፡፡ አስራ
ሁለቱን ለሐዋሪያት ሰጣቸው፡፡ ይህ ለአብነት ነው፡፡ ዛሬ ክህኑ መጀመሪያ እራሱ ቆርቦ በኃላ ምዕመናንን
የሚያቆርበው ለዚህ ነው፡፡

3.3 መቁረብ ያለባቸው እነማናቸው?

ይህን ንዑስ ርዕስ ማንሳት ያስፈለገው ሥርዓተ ቁርባን የተሰራው ለማን እንደሆነ ለማስገንዘብ ነው፡፡
ለብዙ ሰዎች የክርስቶስ ሥጋና ደም ለሕፃናት፣ ለአረጋውያን፣ በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቁራኛ ለተያዙ ብቻ
የተሰጠ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ግን ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙ የዘላለም ሕይወት የሚያድል፣
ሥርየተ ኃጢያትን የሚያሰጥ እና ከዳግም ድቀት የሚጠብቅ ነው ካልን ይህ ፀጋና በረከት ደግሞ
ዕድሜ፣ ዘር፣ ቀለምና ፆታ ሳይለየው በስሙ ለሚያምኑ የሰው ልጆች ሁሉ የሚያስፈልግ ጥርጥር
የለውም፡፡

3.4 ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል የሚደረግ ዝግጅት

1. ከመቁረብ በፊት

ሀ. ኃጢያትን ተናዝዞ ይቅር በለኝ እያሉ ከኃጢአት ነፅቶ ልብን ከቂም በቀል ሰውነትን ከበደል ማራቅ
ይገባል፣

ለ. ቅዱስ ቁርባን የሚቀበሉ ሰዎች በጋብቻ ሥርዓት የሚኖሩ ከሆነ ከመቁረባቸው በፊት 3 ቀን ለሩካቤ
ሥጋ መከልከል አለባቸው፣

ሐ. ሥጋ ወደሙን ለመቀበል 18 ሰዓት ከእህል ውሃ ተከልክሎ በመፆም አፍን ምሬት እሰከሚሰማ


መፆም ይገባል፣ (ፍት. ነገ 13)

መ. ወንድ ልጅ (ዝንየት) ሕልመ ሌሊት ካገኘው በዚያን ቀን አይቆርብም፡፡ እንቅፋት ቢመታውና ቢደማ
እንዲሁም ቢነስረው መቀበል አይችልም፡፡ ይሔ ለካህኑም ለምዕመኑም የሚመለከት ነው፡፡

ሠ. በመቁረብ ዋዜማ ገላን መታጠብ የሚለብሱትን ንፁህ አድርጎ ማዘጋጀት ይገባል፣

ረ. ቅዳሴ ከመገባቱ በፊት አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን መገኘትና በሚገባ ቅዳሴውን ማስቀደስ፣ ቅዳሴ
ሲገባ ያልነበረ በመሐል የመጣ ሰው መቁረብ አይገባውም፣

ሰ. ሴት በወር አበባ ጊዜ መቁረብ አይገባትም፡፡ ከነፃች በኃላ ሰውነቷን ታጥባ ትቀበላለች፡፡እንዲሁም


በወሊድ ጊዜ (የመታረስ) እስከሚፈፀም ድረስ እስከ ህፃኑ ክርስትና ድረስ "ሴት ከወለደች 80 ቀን ወንድ
ከወለደች ከ40 ቀን ማለት ነው፡፡"

2 ከቆረቡ በኃላ

ሀ. ቆራቢው ሰው በጋብቻ ሥርዓት የሚኖር ከሆነ ከቁርባን በኃላ ሁለት ቀን ከሩካቤ ሥጋ መከልከል
ይገባል፣

ለ. ከቆረቡ በኃላ በዚያው ዕለት ወደ ፍርድ ቤት መሔድ መሟገት ክልክል ነው፣

20
ሐ. አብዝቶ መመገብ፣ መጠጣት፣ ጥፍር መቁረጥ፣ ፀጉር መላጨት፣ መሰገድ እና መንበርከክ፣ ምራቅ
መፍታት፣ በውሃ መታጠብ እና ከልብስ መራቆት ክልክል ነው፡፡

3.5 በሥርዓተ ቤተ ክርስተያን መቀበል የሚፈቀድላቸው እና መቀበል የሚከለከሉ

ሀ. ቅዳሴ ሲጀመር ያልነበረ ሰው ቅዳሴ ሲጀመር ያልነበረ ካህን፡- እነዚህ ሁለቱ ሊቀበሉ ሊያቀብሉ
አልተፈቀደላቸውም፣ (ፍት ነገ 12÷97)

ለ. ያላመኑ ሰዎች ሥጋ ወደሙ እንዳይቀበሉ መጠበቅና መቆጣጠር ያስፈልጋል፣ (ፍት ነገ 23÷44)

ሐ. በንሰሓ ላይ ያለ ሰው የንስሓ ጊዜውን ሳይፈፅም ለሞት የሚያበቃ ደዌ ቢታመም ሥጋ ወሰሙ


ከመቀበል አይከለከልም፡፡ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ከዳነም ንስሓውን እንዲጨርስ ይደረጋል፡፡ ፍት
13÷15

መ. ካልታመመ በቀር በንስሓ ላይ ያለ ሰው የተቀበለውን ቀኖና ሳይጨርስ መቀበል አይችልም፣

ሠ. ጋኔን የሚጥለው ሕመም ያለበት ሰው አረፋ የሚያስደፍቀው የሚያስተፋው ከሆነ ሥጋ ወደሙ


ለመቀበል አይከለከልም፡፡ (ፍት ነገ 13)

3.6 ሥርዓተ ቁርባን አፈፃፀሙ እና ቅደም ተከተል

ቅዱስ ቁርባን ካህናት፣ ሕፃናት፣ ደናግል፣ ሕዝባዊያን ምዕመናን ቤተ ክርስቲያን በሠራችላቸው ቅደም
ተከተል ጠብቀው ይቆርባሉ፡፡ ዋናው ቄስ ሥጋውን በእጁ ሲያቀብል ዋናው ዲያቆን በእረፈ መስቀል
ይቀበላል፡፡ የአቆራረብ ቅደም ተከተላቸው

1ኛ መቅደስ ውስጥ

ሀ) ሊቃነ ጳጳሳት
ለ) ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት
ሐ) ቆሞሳት
መ) ቀሳውስት
ሠ) ዲያቆናት
ረ) ክርስትና የሚነሱ
ሰ) የቀሳውስት ሚስቶች
ሸ) የዲያቆናት ሚስቶች
ቀ) መነኮሳት
በ) ምዕመናን ወንዶች እና ሴቶች

ከተቀበሉ በኃላ ቅዳሴ ጠበል ይጠጣል፡፡

21
ምዕራፍ 4

ሥርዐተ ገዳም፣ ሥግደት እና ምጽዋት


፬. ፩ ወደ ገዳም ሂዶ የመሳለም ሥርዓተ
ገዳም ማለት በቁሙ ደብር፣ የመነኮሳት ሰፈር፣ ምድረ በዳ፣ አባቶች ከሰው ተለይተው
የሚኖሩበት ቦታ ማለት ነው፡፡ ገዳማዊነት ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ
መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ››(ማቴ
፲፮ ፣፳፭ ) እንዳለ ጌታችን ይህንን አማናዊ ቃል መሠረት በማድረግ ቅዱሳን በጾም፣ በጸሎት፣
በስግደት፣ ክርስቶስ በዕለተ አርብ ለሰዎች ሲል የተቀበለውን መከራ እያሰቡ በማልቀስ መላ
ሕይወትን ለክርስቶስ የሚሰጥበት ሕይወት ነው፡፡
በእነዚህ መካናት የሚኖሩ ቅዱሳን አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ከማድረጋቸው የተነሳ
ከእግዚአብሔር ለቦታዎቻቸው ቃል ኪዳን የተገባላቸው የተቀደሱ ስለሆኑ ማንኛውም ሰው ወደ
እነዚህ ገዳማት ለመሳለም ሲሄድ ክርስቲያናዊ አለባበሱን መጠበቅ፣ የሚመገበውን ምግብም
የተመጠነና ከገዳሙ ሥርዓት ጋር የማይጋጭ፣ በዙሪያው በስውር በጸሎት የሚኖሩ ቅዱሳንንም
ላለመረበሽ በሚነጋገሩበት ጊዜ ድምጽንም መቀነስና የመሳሰሉትን ትውፊታዊና ሥርዓታዊ
ህግጋት መጠበቅ ይገባል፡፡ ወደ ገዳም የሚሄድ ሰው ከተቻለው ጥሬ፣ ዳቦ ቆሎና የመሳሰሉ
ደረቅ ምግቦችን ይዞ መሄድ ካልተቻለው ደግሞ እንጀራ ሊበላ ይችላል፡፡
በመሆኑም ወደ ገዳም ለመሄድ የሚያስብ ሰው ሁሉ ማሰብ ያለበት ነገር ቢኖር ወደ እነዚህ
ቦታዎች የመጣው በቅዱሳን ቃል ኪዳን ተጠቅሞ እግዚአብሔር ኃጢአቱን ይቅር እንዲለው
መለመን፣ ከኃጢአት በቀር እግዚአብሔር የልቡን መሻት እንዲሰጠው ሱባኤ የሚገባበት፣
ሥጋዊ ድሎት ትቶ ለመንፈሳዊ ነገር ትኩረት የሚሰጥበት፣በአርምሞ፣ በተመስጦ
ከምግብና መጠጥ ተቆጦቦ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋት የሚያሳልፍፈበት
ከእግዚአብሔር የሚገናኝበት መሆኑን አምኖ መሄድ ይኖርበታል፡፡

፬. ፪ ክርስቲያናዊ አለባበስ

ቤተ ክርስቲያናችን ያስተማረችን ሰውነትን የሚሸፍን፤ ረጅም ቀሚስ እና ነጠላ መልበስ ነው፡፡


ወንድ የሴትን፤ ሴት ደግሞ የወንድን ልብስ ማድረግ ሕጉ ይከለክላል፤ (ዘዳ ፳፪፡ ፭)፡፡ “ሴት
የወንድን ልብስ አትልበስ ወንድም የሴትን ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ
በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፡፡” (ዘዳ.፳፪፡ ፭) እንደተባለ የአለባበስ ሥርዓትን ስንመለከት
ሥነምግባርን የሚገልፅ በመሆኑ ከክርስቲያናዊ አለባበስ ውጪ ከሆነ ሰውነትን የሚያዋርድ
ይሆናል፡፡
የሰው ልጅ በክብሩ በገነት ሲኖር፤ ልብሰ ብርሃንን /የፀጋ ልብሱን/ ሲገፈፍበትና ራቁቱን
መሆኑን ሲያውቅ ሰውነቱን ለመሸፈን ቅጠል ለብሷል፡፡ ሥልጣኔ ራቁት የሚያስኬድ ከሆነ
የሰውን ልጅ ክብር ይገፋል፡፡ ክርስቲያናዊ አለባበስን የሚጻረር ልብስ፤ይለብሳሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ
አለባበስ የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ትምህርተ ሃይማኖትን አለማወቅም ጭምር ነው እንደዚህ
መልበስ አይገባም፡፡ እንኳን የተቀደሰ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የሆነ የሰው ልጅ ሰውነት

22
እንስሣት እንኳ ሀፍረተ ሥጋቸውን ይሽፍናሉ። ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲሄዱ ቀርቶ በዚህ
ዓለም ሲኖሩ ለሥጋዊ ሥራ ባንክ፣ጤና ተቋም ና መሰል መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ሁሉ
ለአለባበስ ሥርዓት አላቸው።

፭. ፫ ሥርዓተ ስግደት
ስግደት ሰው አምልኮቱንና ተገዢነቱን ለመግለጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ግንባሩን መሬት በማስነካት
ለፈጣሪው ተገዢነቱን የሚገልጽበት ተግባር ነው። ስለዚህ ሥርዓተ ስግደትን ጠንቅቆ ማወቁ
መቼና እንዴት የስግደት ተግባር ማከናወን እንዳለብን ይረዳናል። ለክርስቲያኖች ዋና
መሠረታችን የእግዚአብሔር ቃል ነውና ስግደት በመጽሐፍ ቅዱስ ምን መሆን እንዳለበት እስቲ
እንመልከት፤ “……ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ….» ማቴ ፬:፲ ።
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት
ያስፈልጋቸዋል። ዮሐንስ ፬: ፳፪-፳፬
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትምህርት የስግደት ዓይነቶች ሦስት መሆናቸው በተለያዩ
መጻሕፍት ተብራርቷል። እነርሱም ሰጊድ፣ ከመሬት ወድቆ ግንባርን ምድርን አስነክቶ
መነሣት፤ አስተብርኮ ጉልበትን ምድር አስነክቶ መነሣት፤ አድንኖ ራስን ወደታች ዝቅ አድርጎ
እጅ መንሳት ናቸው። እንዲሁም ስግደት የአምልኮ፣ የፀጋና የአክብሮት ስግደት ተብሎ
ይለያል። እኛም የአምልኮ ስግደትን ለእግዚአብሔር እናቀርባለን፣ የጸጋ ስግደትን ደግሞ
ለቅዱሳን የምናቀርብ ሲሆን የአክብሮት ስግደትን ደግሞ ለታላላቆቻችንና ለሚገባቸው
እናቀርባለን፡፡
ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፣ እርሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ
ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፣ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱ ፯: ፮። ይህንን ሕያው
የሆነ የእግዚአብሔር ቃል መሠረት በማድረግ በታቦተ ሕግ ፊት እንሰግዳለን ስለዚህ ከመሬት
ላይ በግንባራችን ተደፍተን ለማን የት ማድረግ እንዳለብን ጠንቅቀን እንወቅ።

፭. ፬ ስለ ምጽዋት ሥርዓት
ምጽዋት የሚለው ሥርወ ቃል የግእዝ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ስጦታ፣ችሮታ፣ልግስና ማለት
ነው፡፡ምጽዋት፡-
• ምሕረት ነው ( ፍት ነገ አንቀጽ ፲፮ : ፻፳፭ ) ማቴዎስ ወንጌል ፭ :
ትርጓሜ
• ለአምላክ የሚሰጥ ብድር ነው ( ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤
በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል፡፡ ምሳ ፲፱ :
፲፯ )፣ ( ምጽዋትን የሚመጸውት ሰው ለእግዚአብሔር በማበደሩ ነው በእጁም የሚበቃ ገንዘብ
ያለው ፈቃዱን ያደርጋል፡፡ ሲራ ፳፱ : ፩ )
• ብልሆች ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ ነው (ሉቃ ፲፪ : ፴፫ )፣ ( ማቴ
፮ : ፲፱- ፳፩ )
• ሰው ለሰው ያለውን በጎ ፈቃድ የሚገልጥበት ክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር ዘርፍ ነው፡፡ ( ፪ኛ

23
ቆሮ ፰ : ፪ )
• ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ መ.ምሳሌ ፳፭ : ፳፩ የምጽዋት አስፈላጊነትና
ጥቅም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን ለማግኘት እንደምጽዋት
የሚጠቅም ነገር የለም።” እንዳለ የምጽዋት ጥቅሙ በብዙ
ወገን ነው። ለአብነት የሚከተሉትን እናያለን።

፩, ምጽዋት ከኃጢአት ታነጻለች፦ ማር ይስሐቅ <<ነዳያንን ውደድ፣ እነሱን ስለወደድህ የልዑል


እግዚአብሔርን ይቅርታውን ታገኛለህና” እንዳለው ነቢዩ ዳንኤልም “የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም
እንደሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፣ ኃጢአትህንም በጽድቅ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት
አስቀር”(ዳን ፬፥፳፯) በማለት እንደገለጸው ምጽዋት ኃጢአትን የምታስተስርይ የእድፈ ነፍስ
ሳሙና ናት።በትህትና መመጽወት በፍርድ ቀን ይቅርታን ያስገኛል። ይህንንም ማር ይስሐቅ
“ዝራዕ ምጽዋተ በትሕትና፤ ወተዓርር ምሕረተ በጊዜ ፍዳ - ምጽዋትህን በትህትና መጽውት
በፍርድ ቀን ይቅርታን ታገኛለህ” በማለት አብራርቶታል። ሰው በቅርብ ላለው ጓደኛው ከራራ
እግዚአብሔር አምላክም ስለፍቅር ሲል እርሱን ከሠራው ኃጢአት ይምረዋል።

፪, ምጽዋት በረከትን ታስገኛለች፦ ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሚሰጥ ሰው በፍጻሜ ዘመኑ እግዚአብሔር


ዋጋውን ያስብለታል፤ በመከራም በተሰነካከለ ጊዜ የሚድንበትን ረድኤት ያገኛል” እንዳለው
ምጽዋት የሚሰጥ ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ረድኤት በረከትን ያገኛል። ‘ስጥ ይሰጠሃል’
የሚባለውም ለዚህ ነው። “እስመ በረከት ትሄሉ ላዕለ ዘይሁብ ምጽዋት - በረከት ምጽዋትን
ከሚሰጥ ሰው ጋር ትኖራለች” እንደተባለው በረከት በሚመጸውት ሰው ላይ እንደምድጃ እሳት
ተዳፍና ትኖራለች። የተዳፈነ እሳት እንዳይጠፋ በረከትም ከሚመጸውት ሰው አትጠፋም። ብዙ
ሰው በመመጽወቱ ምክንያት የሚደኸይ የሚጎልበት ይመስለዋል። ምጽዋት ግን ገንዘቡን
ይባርከዋል፤ ያበረክተዋል እንጂ አያሳንሰውም፤ አያጎድለውም። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ
“ሰጥታችሁለት የተረፈውን እግዚአብሔር ሊያበረክትላችሁ ይቻለዋል፤ ለሁሉም ታተርፋላችሁ፣
በጎነት በመሥራት ታበዙታችሁ” (፩ቆረ ፰÷፰-፱) በማለት ያስተማረው። የሚያስተምር ሰው
እውቀቱ ይበዛለታል፣ መልካም የሚያደርግ ሰውም መልካምነት ይበዛለታል፣ የሚሰጥ ሰውም
ገንዘብ ይበረክትለታል። እኛ ያለንን ስንሰጥ እግዚአብሔር ያለንን አበርክቶ የሌለንንም ጨምሮ
ይሰጠናል።

፫, ምጽዋት ለሰማያዊ መንግሥት ታበቃለች፦ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ ለፍርድ


በመጣ ጊዜ የሚጠይቀንም የምጽዋት ጥያቄ ነው።” የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ
ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ
በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን
በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ
የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤
ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥

24
ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ
ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥
ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ
አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ?
ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ። እውነት
እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ
አደረጋችሁትይላቸዋል። በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥
ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥
ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥
ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ
ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን
አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ
ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም
ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ማቴ ፳፭፥ ፵፮) ተብሎ ተመዝግቦልናል።
ምግበ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ምግበ ነፍስንየተጠሙትን ቃለ እግዚአብሔር መመገብ፣ ስትየ
ሥጋን ብቻ ሳይሆን ጽዕመ ነፍስንም ማርካት... ምጽዋት ነው። ምጽዋት የሰማይ ቤትን
መሥሪያ ምድራዊ መሠረት ነው።

፬, ጸሎታችንን ቅድመ እግዚአብሔር ያደርሳል፦ ጾምና ምጽዋት የማይለያዩ አገልግሎቶች


ናቸው። ጾም ያለ ምጽዋት ምሉዕ አይሆንም። በኢሳይያስ ላይ አድሮ አምላካችን “እኔስ
የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን?” (ኢሳ ፶፰፥ ፮) ብሎ እርሱ የመረጠውን ጾም ሲናገር
ከዘረዘራቸው ውስጥ “እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ” (ኢሳ ፶፰÷ ፯) በማለት የተነገረለት
አንዱ ምጽዋት ነው። ምጽዋትን አድርጎ የሚጾም ሰውም “የዚያን ጊዜ ትጣራለህ
እግዚአብሔርም ይሰማሃል፣ ትጮሃለህ እርሱም እነሆኝ ይልሃል፤ “(ኢሳ ፶፰፥፰) በማለት
ከምጽዋት ጋር የሚጾምና የሚጸልይ ከእግዚአብሔር መልስ የሚያሰጥ እግዚአብሔርም
የሚቀበለው ጾም እንደሆነ ይናገራል።

፭, ምጽዋት መስጠት ለእግዚአብሔር መገዛት ነው:- ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና አምላካችን
ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ገንዘብ የሚገዛቸው እንዳሉ ገልጦ አስተምሯል። “ለሁለት ጌቶች
መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም
ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት
አትችሉም።”(ሉቃ ፲፮:፲፫) ። በማለት አስተምሯል። እዚህ ላይ ጌታችን በገንዘብ ጌታነት
የሚያምኑ፣ ለገንዘብ ሲሉ የሚዋሹ፣ የሚያታልሉ፣ ሰውን ከሰው የሚያጣሉ፣ ሰውን የሚገድሉ
አሉ። እነዚህ ሰዎች ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ማንንም ለመጉዳት አይመለሱም። ለገንዘብ ብለው
ሃይማኖታቸውንም የሚክዱ አሉ። ጌታችን ከላይ አተኩሮ የተናገረው ለሁለቱም እንገዛለን
የሚሉትን ነው። ለገንዘብ ሲሉ እየዋሹ ደግሞ እግዚአብሔርን እናመልካለን ይላሉ፣ ለገንዘብ

25
ሲሉ ሕንጻ እግዚአብሔርን
ክቡሩን ሰው እየገደሉ እግዚአብሔርን እናመልካለን ይላሉ፤ለእግዚአብሔር እንገዛለን ይላሉ፤
ለገንዘብ ሲሉ የክብር መገለጫቸውን ድንግልናቸውን እያጡ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን፣
ለእርሱም እንገዛለን ይላሉ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ነው ለሁለት ጌቶች
መገዛት አትችሉም ያለው። እኔ ያዘዝኳችሁን ትታችሁ ለገንዘብ እየተገዛችሁ ለእኔ ልትሆኑ
አትችሉም፤ ሲለን ነው። በአንድ ጊዜ ጻድቅም ኃጥእም መሆን አይቻልም። ብርሃንና ጨለማ
በአንድ ላይ አይኖሩም።

የምጽዋት ዓይነቶች
ምጽዋት የሚለው ሲነገር ለሕሊና የሚታይን የገንዘብ የምግብ የቁሳቁስ ስጦታ ነው፤ ነገር ግን
ምጽዋት በገንዘብና በዓይነት ስጦታ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ምጽዋት ካለው ነገር የሌለውን
ነገር መርዳት አስከሆነ ድረስ በሚቆጠርና በሚሰፈር ብቻ አይወሰንም፡፡ ደካሞችን በጉልበት
ያልተማሩትን በዕውቀት የሙያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት ምጽዋት ነው፡፡
(ሐዋ ፫: ፪-፲ ፣ (ማቴ ፳፭ : ፲፬-፴ )
የምጽዋት አፈጻጸም ሥርዓት
የምጽዋትን ምንነትና ጥቅም ተምረናል። ለማን እንደሚሰጥም ቀደም ባለው ትምህርታችን
አይተናል። የምጽዋት ምንነቱን ካወቅን፣ ጥቅሙን ከተረዳን፣ ለማን እንደምንሰጥም ግንዛቤ
ከወሰድን ቀሪው ትምህርታችን ‘እንዴት እንፈጽመው?’ የሚለው ነው። ስለ ምጽዋት
የተማርነው ትምህርትም ተምረን እንድናውቀው ብቻ ሳይሆን ተግብረን እንድንኖረውም ጭምር
ነው። ለመተግበርና ከበረከቱ ሱታፌ ለማግኘት ደግሞ ‘እንዴት እንፈጽመው’ ብለን
እንድንጠይቅ ያደርግናል። ምክንያቱም ምጽዋት መስጠታችን ብቻ ሳይሆን ምጽዋታችንን ዋጋ
እንዲኖረው አድርገን መስጠታችንም አስፈላጊ ስለሆነ ነው። እንደ አማኝ ምጽዋታችን ዋጋ
እንዲኖረው አድርገን ካልሰጠን ስጦታችን እንደ አንድ ዓለማዊ በጎ አድራጊ የሰብአዊ ድርጅት
ለተቸገሩት መለገስ እንጂ ሃይማኖታዊ ትሩፋት ሊያስገኝልን አይችልም። ይህም ማለት በምድር
የሰጠነው ምጽዋት ዋጋውም ምድራዊ ዋጋ የምንቀበልበት ይሆናል። ይህ ደግሞ ጊዜያዊ ዋጋ
ስለሆነ ዘለዓለማዊውን ሕይወት ለምንናፍቅ ለእኛ አይጠቅመንም። ስለዚህ ምጽዋታችን
ዘለዓለማዊ ዋጋን ያስገኝልን ዘንድ ‘የምጽዋት አፈጻጸም’ የሚለውን መማር አስፈላጊ ነው።
ስለዚህ ከዚህ
ቀጥሎ የምጽዋትን አፈጻጸም እናያለን። እንዴት እንመጽውት፦

ሀ) ከውዳሴ ከንቱ በራቀና በስውር ፦ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ
ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም”(ማቴ ፮÷፩) እንዳለው
ምጽዋት ስንሰጥ መስጠታችንን ሰው እንዲያውቅልንና፣ አውቆም <መጽዋቾች ናቸው፣
የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው፣ ቸርና ደግ ናቸው> ብሎ እንዲያከብረን፤ እንዲያመሰግነን አስበን
መስጠት የለብንም።ይህን

26
ካደረግን “ያለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም” እንደተባልነው የምንሰጠው
ምጽዋት ምድራዊ ዋጋ እንጂ ሰማያዊ ዋጋ አይኖረውም።

ለ) በትሕትና በንጽሕና መመጽወት፦ በእውነት ኃያልና ዘላለማዊ የሆነ አምላክ ከሰው ምጽዋትን
መውሰዱ ትሕትና ነው። ቅዱስ ዳዊት “ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፤ ዓለምም
በእርሷም የሚኖሩ ሁሉ “(፳፫፥፩) እንዳለው ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ነው። የምንሰጠውም
እርሱ የሰጠንን ነው። ስለዚህ “ከአንተ የተቀበልነውን ሰጠንህ”(፩ ዜና ፳፱፥፲፬) እንደተባለውከእኛ
የሆነ ነገር እንደሌለ ማወቅ አለብን።
ሐ) በደስታና በልግስና መስጠት፦ “የሚሰጥ በልግስና ይስጥ”(ሮሜ፲፪÷፰) እንደተባለው
እግዚአብሔር በቸርነቱ ከሰጠን ነገር ላይ ለሌሎች በማዘንና ስለእግዚአብሔር ብለን ስንመጸውት
ያለ ኀዘን፣ያለ መከፋት ያለ መጸጸት፣ በደስታ መስጠት አለብን።አንጋረ ፈላስፋ “እግዚአብሔር
ለአንተ እንደ ሰጠህ አንተም ስለ እግዚአብሔር ብለህ ፍሡሕ በሆነ ልብ ብሩህ በሆነ ዓይን
ለጋስ በሆነ እጅ ለድሀው ስጥ መጽውት” ያለውም ለዚህ ነው። “ አምላክህ እግዚአብሔር
በሰጠህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱ ቢደኸይ፥ ልብህን አታጽና፥
በድሀውወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ።”( ዘዳ ፲፭:፯) የተባለው በቸርነት መስጠት እንዳለብን
ያመለክታል። “ደስ ብሎት ደስ አሰኝቶ የሚሰጠውን ሰው እግዚአብሔር ይወደዋል።
እግዚአብሔር ከንቱ የሆነ ንፍገትን ይጠላል። ንፉግ ሰው ቅር እያለው ይሰጣል። ከሰጠ በኋላም
ያዝናል።” (ሲራ ፪÷፮) በማለት ከሰጠን በኋላ ማዘን መተከዝ አግባብ እንዳልሆነየሚገልጽ ነው።
እንዳውም የመጸወተ ሰው እግዚአብሔር ለዚህ ክብር ለመመጽወት ያበቃውን አምላኩን
ማመስገን ይገባዋል። ማር ይስሐቅ እንዳለው “ብትመጸውትም ደስ ይበልህ አቤቱ ለአንተ
ምስጋና ይገባል ብለህ እግዚአብሔርን አመስግነው። ሰጥተህ እንድሰጥ አድርገኸኛልና
አመሰግንሃለሁ በለው። “ ይላል። ስለዚህ ስንመጸውት ሁልጊዜ በብሩህ ገጽ ደስ እያለን መለገስ
ይገባናል።

መ) ምጽዋት ለመስጠት አለመቅጠር፦ ምጽዋት ይሰጥ ዘንድ ያሰበ ሰው ነገ ከነገ ወዲያ


እሰጣለሁ እያለ መዘግየት የለበትም። “የመዳን ቀን አሁን ነው” እንዲል መጽሐፍ ለመዳን
ምክንያት የሆነውን ምጽዋት የመስጠት ቀንም አሁን ነው። ከመስጠት ከዘገየን ለመዳንም
እንዘገያለን። በርሃብ ያሉ ሰዎችም በጉዳት ያልፋሉ። በርሃብ
ይሞታሉ።ከመስጠትበመዘግየታችንም እኛ በነፍስ ለመሞት ስንፈጥን ድሆች ደግሞ በርሃብ
ምክንያት በሥጋ ሞት ይፈጥናሉ። ስለዚሀ ለመመጽወት ጊዜ ቀጠሮ አያስፈልግም። ሲራክ
“ልመጸውት ብለህ ስታስብ ነገ ሣልስት አደርገዋለሁ ብለህ አትዘናጋ እግዚአብሔር የምክንያትን
ነገር አይቀበልምና”(ሲራ ፲፯÷፳፩) ሲል የተለያየ ምክንያት በመደርደር ምጽዋት
ከመስጠትመዘግየት እንደሌለብን አብራርቶታል። መጽሐፈ ምሳሌም “ለድሀም በጎ መሥራትን
ችላ አትበል። በእጅህ እንዳለ መጠን እርዳው እንጂ፤ ዛሬ ሂድ ነገ እሰጥሀለሁና ተመለስ
አትበለው መስጠቱ ሲቻልህ። ማግስት የምትወልደውን አታውቅምና” (ምሳ ፫÷ ፳፯) በማለት
አብራርቶታል።

27
ሠ) የበደሉንን ታግሶ መስጠት፦ ርኁሩኁ አምላካችን ፀሐይን ለኃጥአንም ለጻድቃንም ያወጣል።
ዝናቡንም እንዲሁ ለሁሉም ያዘንባል። ለሚበድሉትም ህጉን ለማይጠብቁትም፣ ትእዛዙን
ለማይፈጽሙትም ለሁሉም ምግበ ሥጋን ይመግባል። ይህ የእግዚአብሔር ቸርነቱን
የሚያመለክት ነው። እኛም ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን የበደሉንን ሁሉ
የሚያስፈልጋቸውን በማድረግ በመለገስ ማረጋገጥጠ አለብን።ሰው የበደሉትን ይቅር ብሎ በሰጠ
ጊዜ በልቦናው ጸጥታን
ጸጋ ክብርን ያገኛል። ላልበደሉት ከሚሰጠው ስጦታም በላይ ለበደሉት በይቅርታ የሰጠው ስጦታ
ዋጋው የበለጠ ዋጋ አለው። ስለዚህ ስንሰጥ የበደሉንን ታግሰንና ይቅር ብለን መስጠት አለብን።

ረ) ለለመነ ሁሉ አስተካክሎ መመጽወት፦ ጠቢቡ ሰለሞን “ለተቸገረ ሰው በጎ ነገርን ለማድረግ


አትከልክል፤ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” (ምሳ ፫፥ ፳፯) እንዳለው ዳግመኛም ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ “መጥቶ ለለመነ ሁሉ ርኅራኄ ማድረግ፥ ደሀውን ከባለ ጸጋ፥ ባለ ጸጋውን ከደሀ፥
አረማዊን ከክርስቲያን፥ ክርስቲያኑን ከአረማዊ ሳይለዩ ለተቸገረው ሁሉ
እንዲገባ ያስረዳል። ስለዚህ ጉዳይ ማር ይስሐቅም እንዲህ ሲል ያብራራል”በምትመጸውትበት
ጊዜ አስተካክለህ መጽውት እንጂ ይህ ይገባዋል ይህ አይገባውም አትበል። ይህ አይሁዳዊ ነው
ይህ ከሐዲ ነው አትበል። ይህ ነፍስ ገዳይ ነው አትበል። በባሕርይ ወንድምህ ነውና አእምሮ
አጥቶ ከሃይማኖት ተለየ እንጂ። ፈረሰኛም ቢለምንህ በዚያን ጊዜ ከነዳያን እንደ አንዱ ነውና
ስጠው እንጂ አታሳፍረው። ከለመነህ አትርፈህ ስጠው። ባለጸጋውን ለይተህ ለደሀ አትስጥ።
አስተካክለህ በመስጠትህ
ወደ በጎ ሥራ ለማቅረብ ትችላለህ። ከምጽዋት የተነሳ ስለሚገኝ ዋጋ ባለመለያየት መስጠት
ይገባል።” በማለት በዝርዝር አብራርቶታል።

ምጽዋት ስንሰጥ በመልካም ንግግርና በማክበርም መሆን አለበት።ሲራክ “ዝናም ዋዕይን


እንዲያቀዘቅዘው እንዲሁ ምጽዋት ደሀውን ደስ ያሰኘዋል። ክፉ ነገር ተናግሮ ከመስጠት በጎ
ነገር ተናግሮ መንሳት ይሻላልና። በምትሰጠው ሁሉ ክፉ ነገር አትናገር” በማለት የመልካም
ንግግር ምጽዋት ከገንዘብ ስለሚበልጥ የገንዘብ ምጽዋት ስለሰጠን በክፉ ንግግር ነዳያንን ማቁሰል
እንደማይገባን ያስረዳል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “ደሀ የዕለት ምግቡን እንጂ ሌላ አይሻምና።
ስለዚህ ቢኖርህ የምትሰጠውን ስጠው ባይኖርህ ስለምትሰድበው ፈንታ ከአለው ያድርስህ ብለህ
በፍቅር ስደደው” በማለት ይመክራል።
የምዕራፉ ማጠቃለያ ገዳም ማለት በቁሙ ምናኔ፣ ደብር፣ የመነኮሳት ሰፈር፣ ምድረ በዳ፣
አባቶች ከሰው ተለይተው የመኖሩበት ቦታ ማለት ነው፡፡ አማንያን ወደ ገዳማት ለመሳለም
ሲሄዱ ክርስቲያናዊ አለባበስን መጠበቅ፣ የሚመገቡት ምግብም የተመጠነና ከገዳሙ ሥርዓት
ጋር የማይጋጭ፣ በዙሪያው በስውር በጸሎት የሚኖሩ ቅዱሳንንም ላለመረበሽ በሚነጋገሩበት
ጊዜ ድምጽ መቀነስና የመሳሰሉትን ትውፊታዊና ሥርዓታዊ ህግጋት መጠበቅ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትምህርት ሦስት የስግደት ዓይነቶች አሉ፡፡ እነርሱም ሰጊድ፣
ከመሬት ወድቆ ግንባርን ምድርን አስነክቶ መነሣት፤ አስተብርኮ ፤ አድንኖ ናቸው። እንዲሁም

28
ስግደት የአምልኮ፣ የፀጋና የአክብሮት ስግደት ተብሎ ይለያል።
ሰው ምጽዋት ሲሰጥ ከውዳሴ ከንቱ በራቀና በስውር፣በትሕትና በንጽሕና ፣በደስታና በልግስና፣
ለመስጠትም አለመቅጠር፦ወዘተ ይገባል፡፡

ምዕራፍ አምስት
ጸሎትና መዝሙር
፭. የመዝሙርና የጸሎት ሥርዓት
፭.፩. የጸሎት ሥርዓት፡-
ጸሎት፡- ቃሉ ግእዝ ነው ሲሆን “ጸለየ” ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ጸሎት ማለት “ልመና”
ነው፡፡ ጸሎት ምስጋናም ነው ፣በአባታችን ሆይ ጸሎታችን ስምህ ይቀደስ ስንል ምስጋና ነው፡፡
የዕለት ምግባችንን ዛሬ ስጠን ስንል ደግሞ ልመና ነው፡፡ እንዲሁም ጸሎት ሰው ከልዑል
እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገርበት ነው፡፡ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፬ /

፭.፩.፩. ጸሎትን እንዴት መጸለይ ይገባል?

ሀ. በፍጹም እምነት መጸለይ ይገባል በፍጹም እምነት የምንጸልየውን ጸሎት እግዚአብሔር


ይቀበለዋል፡፡ እየተጠራጠርን የምንጸልየውን ጸሎት ግን እግዚአብሔር አይቀበለውም፡ ፡
“አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” /ማቴ. ፳፩
: ፳፪ እንደተባለ፡፡ ቅዱስ ያዕቆብም በመልእክቱ ‹‹ ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው ሳይነቅፍ
በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን
ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፣ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕር ማዕበል
ይመስላል፡፡ ሁሉት ሐሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ
ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው›› እንዳለው፡፡ያዕ ፩ : ፭-፰

ለ.ሀሳባችንን ሰብስበን አንድ ልብ በመሆን መጸለይ ይገባል ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት


የጰራቅሊጦስ ዕለት አንድ ልብ ሆነው
ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ /የሐ. ሥራ ፪: ፩-፬ እኛም ቅዱሳን አባቶቻችን
ሐዋርያትን አብነት በማድረግ በአንድ ልብ ልንጸልይ ይገባል፡፡

ሐ.በመፍራት ማለት ከልብ መጸለይ ይገባል ነቢዩ ሕዝቅያስ በመፍራትና ከልብ በመጸጸት ሆኖ
ስለጸለየ በዕድሜው ላይ አሥራ አምስት ዓመት ተጨምሮለታል፡፡ /፪ኛ ነገሥት ፳: ፩ - ፮/ኢሳ.

29
፴፰: ፩-፭ / /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፬ ስለዚህ የሚጸልይ ሰው በማን ፊት እንደቆመ በማሰብ
በፍርሐትና በተመስጦ ከልብ በመሆን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡

መ. በጸሎት ጊዜ ቀጥ ብሎ መቆም በጸሎት ጊዜ ቀጥ ብሎ መቆም እንደሚያስፈልግ ሥርዓት


ተሠርቷል“በጽባሕ እቀውም ቅድሜከ ወአስተርኢ ለከ” /በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ
እታይሀለሁም/ /መዝ.፭ : ፫ እንደተባለ፡፡

ሠ. ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መጸለይ ይገባል ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ


ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ የተነገረለት ነውና ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ
መጸለይ ይገባል፡፡ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፬

ረ. በጸሎት ጊዜ መስገድ ይገባል ይኸውም ጸሎቱን ስንጀምርና ስንጨርስ እንዲሁም በጸሎት


ጊዜ ስግደትን ከሚያነሳ አንቀጽ ስንደርስ መስገድ ይገባል፡፡ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፬

ሰ. በትእምርተ መስቀል /በመስቀል ምልክት/ ማማተብ ይገባል ስናማትብም ከላይ ወደታች


ከግራ ወደ ቀኝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በማለት እንጀምራለን፡፡ በመስቀል አምሳል
የምናማትብባቸው ጊዜያትም ጸሎት ሲጀመር፣ሲጨረስና መስቀሉን ከሚያነሳ አንቀጽ ሲደረስ
ይሆናል፡፡ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ፲፬/

ሸ. ዐይኖቻችንን ወደላይ አቅንቶ መጸለይ ይገባል “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ “እንዲል


ሰማይ ዙፋኔ ነው ያለን አምላክ ጸሎታችንን በዘላለማዊ ዙፋኑ ለሚመለክ እግዚአብሔር
የምናቀርበው ልመና ጸሎት ነውና አይናችንን ወደ ላይ አቅንተን መጸለይ አለብን፡፡

ቀ. ለሌሎችም መጸለይ ይገባል ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሀገራችንና ለሌሎች ሰዎችም መጸለይ


ይገባል፡፡ ኤርምያስ ለሀገር ሰላም መጸለይ እንደሚገባ ‹‹በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና
ወደ እርስዋ ላስማረክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ ስለእርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ››
/ት.ኤር. ፳፱ : ፯ /፡፡ እንዳለ እኛም ታመው በየሆስፒታሉ፣ በየቤቱ ለሚገኙ ወገኖቻችን፣
በየማረሚያ ቤቱ ላሉ በአጠቃላይ በተለያየ ችግር ለሚንገላቱ ሁሉ መጸለይ ይገባል፡፡ ከሁሉም
በላይ ደግሞ ለአገር መጸለይ ይገባል፡፡ “ትድኑም ዘንድ እያንዳንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ” /ያዕ. ፭:
፲፮ /

፭.፩.፪. የጸሎት ጊዜያት


ልበ አምላክ ነቢየ ልዑል ቅዱስ ዳዊት “ስለ ጽድቅህ ፍርድ በቀን ሰባት ጊዜ
አመሰግንሃለው”/መዝ ፻፲፰ :፻፷፬ ብሎ እንደተናገረ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሰባት ጊዜ በየእለቱ

30
እንዲጸልይ ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡ ሰባቱ የጸሎት ጊዜያትም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ. በ፲ቱ ወ ፪ቱ /በነግህ ሰዓት
ለ. በ፫ቱ (ሦስት) ሰዓት
ሐ. በ፮ቱ (ቀን ስድስት) ሰዓት
መ. በ፱ቱ (ዘጠኝ) ሰዓት
ሠ. በ፲ቱ ወ ፩ዱ (አስራ አንድ) ሰዓት /በሠርክ/
ረ. በ፫ቱ (ሦስት) ንዋም /በመኝታ ጊዜ
ሰ. በ፮ቱ (ሌሊት ስድስት ) በመንፈቀ ሌሊት

ሀ. ጸሎተ ነግህ (ጠዋት)

. ቅዱስ ዳዊት “አምላኬ አምላኬ በማለዳ ወደ አንተ እገሰግሳለሁ” መዝ ፷፪


: ፲፩ እንዳለ ሌሊቱ አልፎ ቀኑ ሲተካ፣ ከመኝታችን ስንነሳ ምንጸልየው የጸሎት ዓይነት ጸሎተ
ነግህ ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚከተሉትን ምስጢራት እያሰብን መጸለይ ይገባናል፡፡
. ሌሊቱን አሳልፎ ቀኑን ስለተካልን እያመሰገንን ወጥተን እስክንገባ በሰላም ጠብቆ ውሎአችንን
የተባረከ እንዲያደርግልን እንጸልያለን።
. የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረበትም ሰዓት በመሆኑ ያንን እያሰብን እንጸልያለን፡፡
. ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በደል በጲላጦስ አደባባይ ለፍርድ
የቀረበበት ሰዓት በመሆኑ እንጸልያለን።

ለ. ጸሎተ ሠለስት (፫ቱ ሰዓት)

ከነግህ በመቀጠል የምንጸልየው ጸሎት ጸሎተ ሠለስት (የሦስት ሰዓት) ጸሎት ይባላል፡፡ ይህ
የጸሎት ጊዜ
. ሔዋን የተፈጠረችበት
., እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት የሰማችበት
. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሲል በጲላጦስ አደባባይ
የቆመበትና ፮፻፷፮ ግርፋት የተቀበለበት፡፡

ሐ. ቀትር (፮ቱ ሰዓት)


በዕለቱ እኩሌታ ላይ የምናገኘው ይህ ሰዓትም እንደዚሁ የጸሎት ጊዜ ነው፡፡
ይህም ጊዜ
. ሰይጣን አዳምን ያሳተበት
. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀለበ፡
. የቀን እኩሌታ በመሆኑ የፀሐይ ሙቀት የሚያይልበት የሰው ልጅ ለድካም

31
የሚዳረግበት በዚህም ምክንያት አጋንንት የሚበረታቱበት ጊዜ ነው።

መ. ተሰዓተ ሰዓት (፱ቱ ሰዓት)


ዘጠኝ ሰዓት ላይ አራተኛውን ጸሎት እናደርሳለን። በዚህ ጊዜ
. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ነጻ ለማውጣት በፈቃዱ ቅዱስ
ሥጋውን ከቅድስት ነፍሱ የለየበት ሰዓት ነው።
. ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱሰ ዮሐንስ ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ በ፱ ሰዓት
እንደሄዱበ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ሐዋ ፫: ፭

ሠ. ጸሎተ ሰርክ (በ፲ቱ ወ ፩ዱ ሰዓት)


. የጸሎት ሰዓት ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይላል፡፡”ጸሎቴን እንደ ዕጣን በፊትህ ተቀበልልኝ እጅ
መንሳቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን” (መዝ ፻፵ : ፪)

. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ከለየ
በኋላ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ቅዱስ ሥጋውን በአዲስ መቃብር ያኖሩበት ሰዓት ነው፡፡ (ማቴ. ፳፯ :
፶፯)

ረ. ጸሎተ ንዋም (የመኝታ ጊዜ ጸሎት)


. ይህ ጊዜ ቀኑን በሰላም አሳልፈን ለሌሊቱ ለዕረፍት የምንዘጋጅበት ነው፡፡በሰላም ላዋለን ፈጣሪ
በሰላም አሳድረን ብለን ራሳችንን በእምነት የምናስረክብበት ነው፡፡ እኛ ተኝተን የሚሆነውን
አናውቅም እርሱ ግን የማያንቀላፋ ትጉኅ እረኛ ስለሆነ ይጠብቀናል።
. ይህ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ ዛሙርቱን በጌቴሴማኒ ጸሎት
ያስተማረበት ሰዓት ነው፡፡
ሰ. መንፈቀ ሌሊት (እኩለ ሌሊት)
እኩለ ሌሊትም እንደ ቀናቱ የጸሎት ሰዓታት የተለያዩ ትርጉሞች አሉት ። ቅዱሰ ዳዊት
“መንፈቀ ሌሊት እትነሣእ ከመ እግነይ ለከ በእንተ ኵነኔ ጽድቅከ” “ስለ ጽድቅህ ፍርድ በእኩለ
ሌሊት አመሰግነህ ዘንድ እነሳለሁ” /መዝ ፻፲፰ :፷፪ በማለት ይህ ሰዓት ከእግዚአብሔር ጋራ
የሚነጋገርበት እንደሆነ ገልጿል፡፡
. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ዋሻ የተወለደበትሰዓት
ነው።
. ሞትን ድል አድርጎ በታላቅ ኃይልም የተነሳው በሌሊት ነው።

፭.፩.፫. ጸሎት አይነቶች


ሀ. የግል ጸሎት
የግል ጸሎት ማንኛውም ሰው ለብቻው የሚያደርገው ጸሎት ነው፡፡ ይህም በቤት፣ በት/ቤት፣
በቤተክርስቲያን እና በልዩ ልዩ ቦታዎች ለብቻችን ማድረግ ያለብን የጸሎት ዓይነት ነው፡፡

32
ለ. የቤተሰብ ጸሎት
ይህ የጸሎት አይነት የቤተሰቡ አባለት በጋራ ሆነው የሚያደርሱት ነው፡፡ በዚህም ጸሎት
ቤተሰባችንን እንዲጠብቅልን፣ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት እንዲኖረን በቤታችን በኑሯችን
እንዲሁም በልባችን ገብተህ ፍቅራችንን ባርክልን እያልን ስለቤተሰባችን መንፈሳዊና ሥጋዊ
ህይወት መሳካት እንለምንበታለን ፡፡

ሐ. የማህበር ጸሎት
በማህበር የሚደረግ ነው፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ሆናችሁ በስሜ ብትሰበሰቡ በመካከላችሁ
እገኛለሁ በማለት የተሰጠንን ተስፋ ለመቀበል የምናደርገው ጸሎት ነው::ማቴ ፲፰ : ለምሳሌ
በሰንበት ትምህርት ቤት የምናደርገው ፤በጸሎተ ቅዳሴ በሰርክ ጉባኤያት ብዙ ቦታዎች የሚደረግ
ክርስቲያኖች በኅብረት ሆነን የምንጸልየው በጣም አስፈላጊ ጸሎት ነው፡፡ ስለዚህ ዘወትር ለጸሎት
መትጋት ይኖርብናል። ጸሎት ያልጸለየ ሰው በባዶ ደብተር እንደማጥናት ቁጠሩት፣ ምንም
አያገኝም ከእግዚአብሔር
ጋርም አይገናኝም ማለት ነው፡፡

ምግብ ስንመገብ ስለምጸልየው


ምግብ ከመመገባቸው በፊት ሲጸልዩ የሚያሳይ ምስል ቢደረግ ምግብ ሲበላ ሁሉም ሰው
መጸለይ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ የምንጸልየው በቀን ሰባት ጊዜ ብቻ አይደለም እንደውም ከዛ በላይ
ነው ማለት ነው። ምግብ ሲበላ ደግሞ እራሱን የቻለ ጸሎት አለው፤ ምግብ ሲበሉ መጸለይ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ጸሎት ነው፡፡ ምግብ ከመብላታችን በፊት
የምንበላበትን እጅ እና ቁሳቁስ ማጽዳት ይኖርብናል፡፡ ንጹህ ከሆነ በኋላ ለምግብ ተቀምጠን
መጸለይ አለብን። በመጀመሪያ በማማተብ እንጀምራለን፣ ከዚያም አማትበን እንደጨረስን ለእኛ
የምንመገብውን የሰጠንን ቸር አምላክ አመስግነን ላጡት
እንዲሰጥልን ለምነን አባታችን ሆይ ብለን እንጸልያለን፡፡ የአባታችን ሆይ ጸሎት፡- ጌታችን
ያስተማረን ማንም ቢሆን ሲቆምና ሲቀመጥ፣ ሲተኛና ሲነሣ ፤ ሲበላም ሊጸልይ የሚችለው
አጭር የኅሊና ጸሎት ነው፡፡

፭.፪ የመዝሙር ሥርዓት


መዝሙር የሚለው ቃል ‹‹ዘመረ›› አመሰገነ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜው
ምስጋና ማለት ነው፡፡ መዝሙር በቤተ-ክርስቲያን የዝማሬ ሥርዓት መሠረት በዜማ የሚቀርብ
ምስጋና ነው፡፡ ምስጋና የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር ዓለማትን ከመፍጠሩ አስቀድሞ
ምስጋናው አልተጓደለበትም በባህርይው ይመስገን ነበር፡፡ ክብሩ በባሕርዩ ብቻ ተወስኖ
እንዳይቀር ስሙን እንዲቀድሱና ክብሩን እንዲወርሱ መላዕክትና ሰውን አስተዋዮች(ለባውያን)
እና አዋቂዎች(ነባብያን) አድርጎ
ፈጠራቸው፡፡ መዝሙር ከእግዚአብሔር የተሰጠ ጸጋ በመሆኑ ታላቅ መንፈሳዊ ኃይል አለው፡፡
መዝሙር ሕሙማንን የመፈወስ የተጨነቁ ሰዎችን የማረጋጋት ኃይል አለው፡፡ የእስራኤል

33
ንጉስ የነበረው ሳኦል በታመመ ጊዜ ልበ አምላክ ዳዊት ወደ እርሱ ዘንድ እየሔደ በገና
እየደረደረ ሲዘምርለት ሳኦል ከደዌው ይፈወስ ከጭንቀቱም ይረጋጋ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ
ተጽፏል፡፡ 1፩ኛ.ሳሙ ፲፮ : ፳፩ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በፊልጲስዮስ ወኀኒ ቤቱ መሠረቱ
እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ መንቀጥቀጥ አስከትሎ የወኀኒ ቤቱን ደጆች አስከፍቷል ያንንም ታላቅ
እሥራት አስፈትቷል፡፡ የሐዋ ሥራ ፲፮ : ፲፱- ፳፮
ሰዎች በገናንና መሰንቆን ለዝማሬ እንደሚቃኙ መንፈስ ቅዱስም ዘማሪያንን ይቃኛል፡፡ ለሰዎች
ዝማሬን ማስተማር የማይችሉ ለራሳቸው ብቻ የሚዘምሩ ልዩ ሀብተ መዝሙር የተሰጣቸው
ሰዎች አሉ፡፡ መዝሙር አስደሳች የድምጽ ቅላፄ የሚደመጥበት ጉባኤ ብቻ ሳይሆን
እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ መዝምሩ ፈጣሪያችንን፥ ቅድስት
ድንግል ማሪያምን እንዲሁም ቅዱሳኑን የምናመሰግንበት በመሆኑ በሥርዓት ልናቀርበው ይገባ፤
ስንጀምርም በጸሎት ሊሆን ይገባዋል። በህብረትም ለአገልግሎት ዝማሬን ስናቀርብ የድምጽ
አወጣጣችን፥ የሽብሸባችን፥ እንቅስቃሴያችን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቀ መሆን
ይኖርበታል።

የምዕራፉ ማጠቃለያ
. ጸሎት ቃሉ ጸለየ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲሆን ጸሎት ማለት ልመና ፤ ምስጋናም
ማለት ነው ።
. ጸሎት ስንጸልይ በፍጹም እምነት መጸለይ፤ ሀሳባችንን ሰብስበን በአንድ
,ልብ በመሆን መጸለይ፤ከልብ መጸለይ ፤ በጸሎትም ጊዜ ቀጥ ብሎ መቆም፤ ፊትን ወደ
ምሥራቅ መልሶ መጸለይ ፤ መስገድ ፤ ጸሎት ስንጀምር በትእምርተ መስቀል /በመስቀል
ምልክት/ ማማተብ ፤ዐይኖችን ወደላይ አቅንቶ መጸለይና ለሌሎችም መጸለይ ይገባል።
. ሰባት የጸሎት ጊዜያት አሉ። እነሱም:- ጸሎተ ነግህ፣ የቀን ሦስት ሰዓት ጸሎት፣ የቀትር
ጸሎት(ከቀኑ ፮ ሰዓት) ጸሎት፤ የሰርክ ጸሎት(ምሽት ፲ቱ ወ፩ዱ ሰዓት)፤ የምሽት ሦስት ሰዓት
ጸሎተ ንዋም እና የመንፈቀ
ሌሊት ጸሎት ናቸው።
. ሦስት የጸሎት ዓይነቶች አሉ። እነሱም የግል ጸሎት፤ የቤተሰብ ጸሎትና የማህበር ጸሎት
ናቸው።
. ምግብ በምንመገበብት ጊዜ ጸሎት እናደርጋለን።
. መዝሙር የሚለው ቃል ‹‹ዘመረ›› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜው ምስጋና
ማለት ነው፡፡

34
35

You might also like