You are on page 1of 27

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ

የግንባታ ቦታ ሙያዊ ጤናና


ደህንነት ደንብ

01/2011

ጥር 2011ዓ.ም.
አዲስ አበባ

1
መግቢያ
በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉትን የግንባታ ስራዎች መምራትና ማስተዳደር ለከተማዋ
ኢኮኖሚያዊ እድገትም ሆነ ጤናና ደህንነት ጠቀሜታ እንዳለው ስለታመነበት፤

በግንባታስራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ጤናና ደህንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ላይ እየወደቀ


በመምጣቱና ይህንንም መቆጣጠርናስርዓት ማስያዝ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚና ማዘጋጃ ቤት
አገልግሎት አካላት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ፴፭/፪ሺ፬ ዓ.ም (እንደተሻሻለ) አንቀፅ ፹፬
በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህንን መተዳደሪያ ደንብ አውጥቷል፡፡

2
ክፍል አንድ
ጠቅላላ
1.አጭር ርዕስ

ይህ ደንብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ የግንባታ ስራ ሠራተኞች የጤናና


ደህንነት መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር ……/፪ሺ፲፩ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2.ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ የተለየ ትርጉም የሚያሰጠው ከልሆነ በስተቀር በዚህ መተዳደሪያደንብ መሰረት ፡-

1) ‹ ‹ ከተማ› › ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡


2) ቢሮ ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ነው፡፡
3) “ተወካይ"ማለት በሀገሪቱ ህግ መሰረት ከሚመለከተው አካል የውክልና ስልጣን
የተሰጠው ሰው ወይም ተቋምነው፡፡
4) “የግንባታ ግብዓቶች ማቀነባበሪያ(Bulk mixing plant)" ማለት ለግንባታ ስራ የተቀላቀለ
ምርት ጥቅም ላይ ለማዋል እቃዎችን በጅምላ ለማቀላጠፍ በሚያስችል የተቀናጁ
መሳሪያዎች, ወይም ተመሳሳይ መሳሪያዎች ማለት ነው::
5) "አሰሪ" ማለት የግንባታ ሥራው የሚከናወንለት ሰው ወይም ተቋምነው፡፡
6) "ብቃት ያለው ሰው" ማለት ለስራውየተሟላ አስፈላጊ ዕውቀት፤ ልምድ እና ክህሎት
ያለው ሰው ነው፡፡
7) "የኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጅ" ማለት የግንባታ ሂደቶችን በአስተባባሪነት እና በግብዓት
አቅርቦት ስራ ላይ የማስተባበር ፤የማሰራት፤እና የማስተዳደር ኃላፊነት ያለው ሰውነው፡፡
8) "የግንባታ ቦታ" ማለት የግንባታ ሥራው የሚካሄድበት ቦታ ነው፡፡
9) "የግንባታ ተቆጣጣሪ" ማለት በግንባታ ቦታ ላይ የግንባታ ስራዎችን በበላይነት
የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለው ግለሰብ ነው፡፡
10)‘ዋና ተቆጣጣሪ ‘ማለት የጤናና የደህንነት ስራዎችን በበላይነት የሚቆጣጠር ስው ነው፡፡
11)"የግንባታ ተሽከርካሪ" ማለት የግንባታ ሥራን ለማከናወን በግንባታ ቦታ ላይና ከግንባታ
ቦታ ውጭ ያሉትን ሰዎች ወይም ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ የሚያገለግል መኪናነው::
12)«የግንባታ ስራ» ማለት ከማናቸውም የኮንስትራክሽን ስራ ጋር የተያያዘ ሆኖ፡-
(ሀ) ሕንፃ ወይም ማንኛውም ተመሳሳይ መዋቅር ለመገንባት፤ ለመለወጥ፤ለማደስ፤
ለመጠገን; ወይም ለማፍረስ ወይም፤
(ለ) ማናቸውንም ድልድይ, ግድብ, ቦይ, መንገድ, የባቡር መስመር, የፍሳሽ ወይም
የውኃ መስመር ዝርጋታ, እና ማንኛውንም ተመሳሳይ የሲቪል ኢንጂነሪንግ መዋቅር
ወይም የሥራ ዓይነት ነው፡፡

3
13)"የኮንስትራክሽን ስራ ፈቃድ" ማለትበህግ አግባብ ካለው አካል የግንባታ ስራውን
ለመስራት የተሰጠ የፈቃድ ሰነድ ነው፡፡
14)"ስራ ተቋራጭ " ማለት የግንባታ ስራውን የሚያከናውን ተቋም ነው፡፡

15)"የማፍረስ ስራ" ማለት በሰው ኃይል ጉልበት, በማሽነሪ, ወይም በፈንጂዎች በመጠቀም
አንድን መዋቅር ወይም ክፍልን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የማፍረስ ስራ ነው፡፡
16)"ዲዛይን" ማለት ለሚሰራው የግንባታ ስራ ንድፎችን, ስሌቶችን, የንድፍ ዝርዝሮችንእና
ዝርዝር መግለጫዎችን የያዘ ሰነድ ነው፡፡
17)"የመሬት ቁፋሮ ስራ” ማለትከላይኛውን የአፈር ጠረጋ ጀምሮ እስከ ጥልቅ ቁፋሮ ድረስ
ያለውን የቁፋሮ ስራ የሚያጠቃልል ነው፡፡
18)"የጤና እና ደህንነት ፋይል" ማለት በዚህ መተዳደሪያ ደንብ የሚጠየቀውን ፋይል
ወይም ሌላ የጽሁፍ መረጃ የያዘ ሰነድ ነው::
19)"የጤና እና የደህንነት ዕቅድ" ማለት የሰራተኞችን ጤናና ደህንነት በስራ ቦታ ላይ
እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል የሚያሳይ በስራ ተቋራጭ የሚዘጋጅ ዝርዝር እቅድ ነው፡፡
20)"የእቃ ማንሻ" ማለት እቃዎችን ወደ ላይ እና ወደ ታች ለማጓጓዝ የሚረዳ መሳሪያ ነው፡

21)"የሰው ማመላለሻ" ማለት ሰዎችን ወደ ላይ እና ወደ ታች ለማጓጓዝ የሚረዳ መሳሪያ
ነው፡፡
22)"ስካፎልዲንግ" ማለት ጊዜያዊየሆነና ከፍባለ ቦታ ላይ ሰራተኞች ለስራ የሚንቀሳቀሱበትና
የስራ እቃዎቻቸውን የሚስቀምጡበትከእንጨት ወይም ከብረት የሚዘጋጅ መዋቅር ነው፡፡
23)‘’ የድጋፍ ሥራ (ሾሪንግ)’’ ማለት በአፈር ቁፋሮ ጊዜ ከጎን ያለው መሬት እንዳይናድ
ለመከላከል የሚሰራ ግንባታ ነው፡፡
24)"ጊዜያዊ ስራዎች" ማለት ዋናውን የግንባታ ስራ ለማከናወን የሚረዱ እና ግንባታው
ካለቀ በኋላ የሚፈርሱ ስራዎችንሁሉ ያጠቃልላል፡፡
25)በዚህ በመተዳደሪያ ደንቡ በወንድ ፆታ የተገለጸው የሴት ጾታንም ይጨምራል
26)“ሰው”ማለትየተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡
27)የጾታ አገላለጽ
በዚህ መመሪያ ውስጥ በወንድ ፆታ የተገለፀው የሴትንም ፆታ ያካትታል፡፡

3.የተፈጻሚነት ወሰን

ይህመተዳደሪያ ደንብበአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ በሚገነቡ ማናቸውም


ዓይነት ግንባታዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

4
ክፍል ሁለት

የባለድርሻ አካላት ተግባርና ኃላፊነት

4.የቢሮ ተግባርና ኃላፊነት


1) የግንባታ ሰራተኞች የጤናና ደህንነት አብይ ኮሚቴ ያቋቁማል፤በበላይነት ይመራል፤
ይቆጠጠራል፤
2) የግንባታ ሰራተኞች የጤናና ደህንነት አብይ ኮሚቴ በሚሰጣቸው ውሳኔዎች ላይ
የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፤
3) የዚህን መተዳደሪያ ደንብ አፈፃፀም ይከታተላል፤ይቆጣጠራል ችግር ሲኖር አጣርቶ
እርምጃ ይወስዳል፡፡

5.የአሰሪ ተግባርና ኃላፊነት


ማንኛውም አሰሪ ግንባታ በሚያከናውንበት ጊዜ የሚከተሉት ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡-
1) በግንባታ ቦታ የሚከሰቱ አደጋዎችን መረጃ በአግባቡ አደራጅቶ ይይዛል፤የግንባታ ስራው
ሲጠናቀቅ ለቢሮው ያስረክባል፤
2) ዋና ስራ ተቋራጭ ሞልቶ ያስገባው የጨረታ ሰነድ የዋስትና እና የደህንነት
እርምጃዎች ወጪዎችን ለመሸፈንየሚያስችል መሆኑን ማረጋገጥ፤
3) ዋና ሥራ ተቋራጭ የግንባታ ሥራውን በአግባቡ ለመፈፀም አስፈላጊ የሆነ የሰው ኃይል
፤ሀብት እና አስፈላጊውን የመድህን ዋስትናሽፋን ያለው መሆኑን ማረጋገጥ
4) በሁሉም ስራ ሰራተኞችና ስራ ተቋራጭ መካከል ሰላማዊ የስራ ግንኙነት መኖሩንና
የዚህ ደንብ ድንጋጌዎች መከበራቸውን ማረጋገጥ;
5) ስራው ከመጀመሩ በፊት ሁሉም ሰራተኞችና ስራ ተቋራጭ አግባብ ባለው አካል
የተመዘገቡና ፈቃድ ያላቸው መሆኑን መረጋገጥ፤
6) ከስራ ተቋራጭ ጋር ግንባታውን የሚመለከቱስራዎችን በተመለከተ
ህጋዊ ውል በሚፈራረምበት ወቅት የጤና እና የደህንነት ዕቅድ መኖሩን ማረጋገጥ
7) የዋናሥራተቋራጭየጤናአጠባበቅእናየደህንነትዕቅድከአማካሪ ድርጅትጋር
በመወያየትየትግበራውንእቅድማጽደቅ፤
8) የዋናውን ስራ ተቋራጭ የጤና አጠባበቅና ደህንነት ዕቅድ ለሁሉም ሰራተኞች፤
ተቆጣጣሪዎችና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ፎቶ ኮፒ አድርጎ መስጠቱን ማረጋገጥ
9) የዋናስራተቋራጩየጤናእናየደህንነትዕቅድለቁጥጥር ሲፈለግእንዲገኝማድረግ፤
10)እያንዳንዱሥራተቋራጭየጤናእናየደህንነትዕቅድበሥራላይመዋሉንማረጋገጥናችግሮች
ሲያጋጥሙ እርምጃበመውሰድ ማስተካከል ፤
11)ቢያንስ በየ 30 ቀናት ወቅታዊ የጤንነት እና ደህንነት የኦዲት ምርመራዎች

5
መካሄዳቸውን እና የፅሑፍ ማረጋገጫዎች በዋና ተቆጣጣሪ ለዋናው ስራ ተቋራጭ
ኦዲቱ በተደረገ በ7 ቀን ውስጥ መሰጠቱን ማረጋገጥ;
12)ስራ ተቋራጭ ለሰራተኞች ጤናእናደህንነት አስጊ በሆነ ሁኔታ ስራ እንዲሰራ
ሲያደርግ ማስቆምና የማስተካከያእርምጃ መውሰድ፤
13)ተጨማሪ ስራ እንዲሰራለት ካዘዘ የጤንነትና ደህንነት ወጪዎችን ጨምሮ
ተጨማሪውን ስራ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን መሸፈን፤
14)ከባድ አደጋ በግንባታ ቦታ ላይ ሲያጋጥም ለሚመለከተው የመንግስት አካል ወዲያውኑ
ማሳወቅ፤
15)በተለያየ ምክንያት በዚህ መተዳደሪያ ደንብ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት ካልቻለ ሌላ
ሰው መወከል ይኖርበታል፤
16)ከዚህ በላይ በተቀመጠው አንቀጽ …..ንኡስ አንቀጽ…….የተወከለ ሰው በዚህ መተዳደሪያ
ደንብ በአሰሪ ላይ የተመለከተው ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል፡፡
17)በግንባታ ቦታ ለሚከሰቱ የሞት፤ዘላቂ ወይም ጊዜያዊ የአካል ጉደት ለደረሰባቸው
ሰራተኞች ስራ ተቋራጩ አስፈላጊውን ካሳ መፈፀሙን ማረጋገጥ፤

6.የአማካሪ ተግባርና ኃላፊነት


ማንኛው አማካሪ ድርጅት፡-

1. የግንባታ ቦታ ደህንነት ከፌደራል፣ ከክልል እና ከአካባቢ ጥበቃ ኮዶች ጋር እንዲጣጣሙ


ያደርጋል፤

2. የሠራተኛ የሥራ ደህንነት መርሃ ግብሮችን ይቀርፃል፣

3. የሥራ ቦታ ደህንነት እና የሠራተኛውን የጤና እና ደህንነት አያያዝ በተመለከተ ቢያንስ


በ30 ቀን አንድ ቀን ምርመራ ያደርጋል፤

4. ሥራ ተቋራጭ የጤና እና የደህንነት እቅዶችን በተግባር ላይ እንዲያውል ግፊት


ያደርጋል፣ በተግባር ላይ ካልዋለም አስፈላጊ እርምጃ እንዲወሰድበት ያደርጋል፣

5. በግንባታ ቦታ የተከሰቱ አደጋዎችን መንስኤ ይመረምራል የምርመራውንም ውጤት


ለሚመለከተው አካል ሁሉ ያሳውቃል፣

6. ዋናው ሥራ ተቋራጭ የሚያቀርባቸውን የሠራተኛ የአደጋ ጊዜ መከላከያ መሳሪያዎችን


(PPE) መስፈርቱን የሚያሟሉ መሆናቸውን ይፈትሻል፣

6
7. ለሠራተኞች የጤና እና የደህንነት ስጋት የሚሆኑ የግንባታ ሥራዎችን እና ቦታዎችን
የሚጠቁም ምልክት ወይም በድምፅ የሚሰራ የአደጋ ማስጠንቀቂያ መሣሪያ
ማስቀመጡን ማረጋገጥ፣ ካላስቀመጠም እንዲያስቀምጥ ያደርጋል፣

8. ዋና ሥራ ተቋራጩ የሚጠቀምባቸውን በኤሌትሪክ የሚሰሩ መሳሪያዎች በትክክል


መቀመጣቸውን እና ለሠራተኞች አደጋ እንደማይፈጥሩ ያረጋግጣል፣

9. በጤና እና ደህንነት አጠባበቅ በተመለከተ ከዋናው ሥራ ተቋራጭ ጋር በጋራ ይሠራል፣

10. ዋናው ሥራ ተቋራጭ ያስገባውን የጤና እና ደህንነት ዋስትና ሽፋን ጊዜውን ጠብቀው
መታደሳቸውን ያረጋግጣል፣

11. የሚገነባው ግንባታ በአካባቢው ነዋሪዎች፣ በእንሰሳት እንዲሁም በአካባቢው ጤና ላይ


የሚያደርሰው ጉዳት መኖሩን እና አለመኖሩን ለሚመለከተው አካል ሁሉ ያሳውቃል፣

12. በግንባታ ቦታ ላይ የሚፈጠሩ የጤና እና የደህነነት አደጋዎች ላይ ከዋናው ሥራ


ተቋራጭ ጋር በመሆን ድጋሚ አደጋ እንዳይፈጠር የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል፡፡

13. ጊዜያዊ ሥራዎች ሲሰሩ ብቁ እና አስተማማኝ ሆነው የሚደግፉትን ወይም


የሚሸከሙትን ክብደት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲሸከሙ ወይም ድጋፍ እንዲሰጡ
አድርጐ ዲዛይን ማሠራት፣

7. የግንባታዎችን ዲዛይን የሚያዘጋጁ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት


7.1 ማናቸውም ዲዛይን ለማዘጋጀት ፈቃድ ያለው ተቋም ለሚያዘጋጀው ዲዛይን ብቃት
ያላቸውባለሙያዎች ያሉት ሆኖ የሚዘጋጀውም ዲዛይን ፡-

1. በጤና እና ደህንነት እቅድ ውስጥ የተካተቱትን የጤና እና የደህነነት መስፈርቶች


ያካትታል፣
2. በአሰሪ የቀረቡ የጤና እና የደህንነት ዝርዝሮችን ያካትታል፣

7.2 ማንኛውም ዲዛይን ለማዘጋጀት ፈቃድ ያለው ተቋም፡-

1) በግንባታ ቦታ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት


አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችል ዲዛይን ማዘጋጀት አለበት፣

7
2) በዲዛይን ችግር ምንያት አደጋ ቢከሰት ለተከሰተው አደጋ የመፍትሄ ሀሳብ ያቀርባል
ዲዛይኑንም በአፋጣኝ አሻሽሎ ያቀርባል፤
3) ለሠራተኛ ጤና እና ደህንነት አደገኛ የሆኑ የሥራ ጉዳዮችን እና የግንባታ ግብአቶችን
በዲዛይን ውስጥ ማካተት የለበትም፣
4) ጤና እና ደህንነት መሠረት አድርጐ ከተሰራው ዲዛይን ውጭ ስራ ተቋራጩ
የሚሰራቸውን ማንኛውንም ስራ ያስቆማል፣እና
3. የተሠራው የግንባታ ሥራ በዚህ ደንብ የተደነገጉትን የጤና እና ደህንነት መስፈርቶች
እና በሀገሪቱ ሌሎች ህጎች መሠረት የተሰራመሆኑ በማረጋገጥ ለአሰሪው የደህነነት
ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሁም ለስራ ተቋራጩ ቅጅ ይሰጣል፡፡
4. ውሉ ለጨረታ ከመውጣቱ በፊት የጤና እና የደህንነት መስፈርቶች በአስገዳጅነት
ያካትታል፣ እንዲሁም እንደተካተቱ አረጋግጦ ለአሰሪው በጽሁፍ ሪፖርት ያደርጋል፤
5. የአፈር ምርመራ ውጤት እና ግንባታው ምን ያህል ክብደት መሸከም እንደሚችል
ለአሰሪው ሪፖርት ያደርጋል፡፡
6. ጊዜያዊ ሥራዎች ሲሰሩ በግንባታው የመዋቅር ዲዛይን ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ
እንዳይፈጥሩ በቅርብ ሆኖ የስራ ተቋራጩን ያማክራል፣
7. ለጊዜያዊ ሥራ የተሰሩ ዲዛይኖች እና ስሌቶች በግንባታ ቦታ እንዲቀመጡ ያደርጋል
(መቀመጣቸውን) ያጋግጣል፡፡

8.የሰራተኞች ተግባርና ኃላፊነት


ማንኛውምሰራተኛ በስራ ቦታው ላይ ፡-

1) ለጤናና ደህንነት መጠበቂያ የተሰጠውን መሳሪያ የመጠቀም፤


2) ለጤናና ደህንነቱ አስጊ በሆነ ቦታ ላይ እንዲመደብ ሲደረግ ይህንኑ በአፋጣኝ ለግንባታ
ቦታ የጤናና ደህንነት ንኡስ ኮሚቴ የማሳወቅ ግዴታ ያለበት ሆኖ፤
3) ከላይ በአንቀጽ 7(1) የተሰጠውን ጤናና ደህንነት መጠበቂያ ባለመጠቀሙ ምክንያት
ለሚደርስ አደጋ ኃላፊነቱን የሚወስድ ይሆናል፡፡

9.የዋና ሥራተቀራጭ ተግባር እና ኃላፊነት


9.1 ማንኛውም ዋና ስራ ተቋራጭ የግንባታ ስራ ከመጀመሩ 10 ቀናት በፊት፡-

1. ለስራው የሚያስፈልጉትን ሰራተኞች ዓይነትና ብዛት


2. በስራው ላይ ሊከሰቱ ይችላሉ ተበሎ የሚገመቱ አደጋዎችን ዓይነት
3. ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች እንዴት መከላከል እንደሚቻል፤ እና
4. ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰራተኞች የህክምና አገልግሎት መስጫና ሌሎች ለሰራተኞች
ጤናና ደህንነት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በዝርዝር የያዘ ሰነድ ለአሰሪና ለአማካሪ
ድርጅት ማቅረብይኖርበታል፡፡

9.2 ማንኛውም ዋና ስራ ተቋራጭ ግንባታ በሚያከናውንበት ጊዜ፡-

8
1. የጤና እና የደህንነት መረጃዎችን በግንባታ ቦታ ለሁለም ሠራተኛ፣ የግንባታ ቦታ
ጉብኝት ለሚያደርጉ፣ ለግንባታ ባለቤት ተወካይ እና ለግንባታ ተቆጣጣሪ በቀላሉ
እንዲያገኟቸው ክፍት እና ግልፅ የሆነ ቦታ ማስቀመጥ አለበት፣
2. ሥራውን ለሌላ ሥራ ተቋራጭ ከሰጠ፣
ሀ. የጤና እና የደህንነት ዝርዝር ሁኔታዎችን አማልቶ ሥራውን በብቃት እና
በኃላፊነት ለሚሰራ ንኡስ ስራ ተቋራጭ መስጠት ይኖርበታል፣
ለ. ንኡስ ስራ ተቋራጭ በግንባታ ወቅት ለሚተገብራቸው የጤና እና የደህንነት
እርምጃዎች በቂ የሆነ የገንዘብ መጠን መኖሩን ማረጋገጥ አለበት፣
ሐ. ንኡስ ስራ ተቋራጭ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በሰራተኛው ላይ ለሚደርሱ
የበሽታ፣ የሞት እና የአካል ጉዳቶች ዋስትና ለመስጠት የሚያስችሉት የህይወት
ዋስትና መድህን ሽፋን መኖሩን ማረጋገጥ አለበት፣
መ. ያዘጋጀውን የጤና እና ደህንነት ዕቅድ በግንባታ ቦታ ላይንኡስ ስራ ተቋራጭ
እንዲተገብርማድረግ እና ካልተገበረ እርምጃ መውሰድ፣

ሠ. በራሱ እና በንኡስ ስራ ተቋራጭ በተቋራጭ መካከል በጋራ በተወሰነው የጊዜ ገደብ


ውስጥ ንኡስ ስራ ተቋራጭ የጤና እና የደህንነት እቅድ መተግበሩን እና የግንባታ
ቦታውን ለሠራተኛ ምቹ ማድረጉንቢያንስ በየ30 ቀናት አንድ ጊዜ ኦዲት ያደርጋል፣

ረ. ከጤና እና የደህንነት ዝርዝር እቅዶች ጋር የማይጣጣም ወይም ለሠራተኞች ጤና


እና ደህንነት አስጊ የሆኑ የግንባታ ሥራዎችንያስቆማል፤እርምጃምይወስዳል፤

ሸ. በዲዛይን እና በግንባታ ሥራ ለውጥ ሲኖር ሥራው ጉዳት እንዳያደርስ በቂ የሆነ


የጤና እና የደህንነት መረጃዎችን መቅረባቸውን ያረጋግጣል፣

ቀ. በደህንነት እና ጤና ዝርዝር እቅዶች ላይ ከንኡስ ስራ ተቋራጭ ጋር በመወያየት


የትግበራ እቅድ ያደድቃል፡፡

3. የጤና እና የደህንነት እቅዶችን ለባለቤት ፎቶ ኮፒ አድርጎ ይሰጣል፣


4. የግንባታ ሥራ ሲጠናቀቅ የተሟላ የጤና እና የደህንነት መረጃዋችን ለባለቤቱ
ያስረክባል፣
5. ሁሉም በግንባታ ቦታ የሚሰሩት ሠራተኞች ለሚሰሩት ስራ በቂ የሆነ የጤና እና የአካል
ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ማቅረባቸውን ያረጋግጣል፣
6. የግንባታ ቦታ ጤናና ደህንነት እንዲጠበቅ የሙሉ ጊዜ ሥራ የሚሰራ የግንባታ ጤናና
ደህንነት ባለሙያ (Safety Officer) እና የሚያስተባብር ሥራ አስኪያጅ ይመድባል፣
7. የግንባታ ቦታ ጉብኝት ለሚያደርጉ አካላት የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን ያዘጋጃል፤
8. ማንኛውም የግንባታ ቦታ ለመጎብኘት የሚመጣ አካልና ሁሉም ሰራተኛ የደህንነት
መሳሪያ ሳይጠቀም ወደ ግንባታ ቦታው እንዳይገባ ይቆጣጠራል፤
9. የጤና እና ደህንነት ዕቅድ አፈፃፀም በየቀኑ ይገመግማል መረጃዎችን በአግባቡ መዝግቦ
ይይዛል፤

9
10. በግንባታ ቦታ የሠራተኞቹ ጤና እና ደህንነት እንዲጠበቅ፣በዚህ መተዳደሪያ ደንብ ላይ
የተደነገጉትን የጤና እና የደህንነት ድንጋጌዎችን እንዲከበሩ፤ የጤና እና የደህንነት
አጠባበቅ ስልጠና የሚሰጥ እና የግንባታ ቦታ ደህንነት እንዲጠበቅ የደህንነት መሀንዲስ
ይመድባል፡፡
11. አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮችን ቀድሞ መከላከል እና አደጋ ከደረሰ ወደ ህክምና ቦታ
በመውሰድ አስፈላጊውን ህክምና እንዲወስዱ ያደርጋል፡፡

10. የንዑስ ስራ ተቋራጭ ተግባርና ኃላፊነት


ማንኛውም ንዑስ ሥራ ተቋራጭ፡-

1. ዋናው ሥራ ተቋራጭ እና አሰሪው ተስማምተው ባፀደቁት የጤና እና ደህንነት ዝርዝር


እቅድ ላይ በመመርኮዝ ተስማሚ እና ግልፅ የሆነ የደህንነት እና ጤና እቅዶችን
ለዋናው ሥራ ተቋራጭ ያቀርባል፣

2. በአንቀፅ 1 ንኡስ አንቀጽ… ላይ ያቀዳቸውን የጤና እና የደህንነት መረጃዎች ሥራውን


ከጀመረ ቀን ጀምሮ በግንባታ ቦታ ላይ በተግባር ያውላል፣

3. የጤና እና የደህንነት ዝርዝር መረጃ የያዙ ፋይሎችን ግልፅ በሆነ የግንባታ ቦታ ላይ


ሁሉም ሠራተኞች፣ ጐብኝዎች እና ለአሰሪ ተወካይ ወይም ባለቤትበቀላሉ ሊያገኙ
በሚችሉበት ቦታ ማስቀመጥ አለበት፣

4. የጤና እና ደህንነት ዝርዝር እቅዶች በግንባታ ቦታ ላይ እንዲተገበሩ ከዋናው ሥራ


ተቀራጭ ከተመደበው ዋና ተቆጣጣሪ ጋር በጋራ መሥራት አለበት፣

5. በግንባታ ቦታ ለሚሠሩ ማንኛውም ሠራተኞች የጤና እና የደህንነት ስጋት የሚሆን


የሥራ አይነቶችን ለዋናው ሥራ ተቋራጭ ማሳወቀ አለበት፣

11.በግንባታ ወቅት በስራ ተቋራጭ የሚከናወኑ ልዩ ልዩ ስራዎችና


ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች
11.1. የማፍረስ ሥራ
11.1.1 በሰው ኃይል ወይም በማሽነሪ የማፍረስ ሥራ
የማፍረስ ሥራ ከመከናወኑ በፊት ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ፡-

1) ከሁለት ወለል በላይ ያለን ግንባታ የሚያፈርስ ከሆነ ስራውን እንዴት እንደሚያከናውን
ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅቶ ማቅረብና ማፀደቅ፤

10
2) የኤሌክትሪክ፣ የስልክ እና የሌሎች መሠረተ ልማት መስመሮች ዝርጋታ መቋረጡን
ማረጋገጥ፣
3) ተገቢውን የሰው ኃይልና መሣሪያ ማዘጋጀት፣
4) የማፍረስ ስራውን የሚቆጣጠር በቂ ልምድና ክህሎት ያለው ባለሙያ ይመድባል፤
5) ከአንድ ወለል በላይ የሆኑ ህንፃዎች በሚፈርሱበት ወቅት ከጣሪያው በመጀመር
በየደረጃው መፍረስ ፣
6) የማፍረስ ሥራ ሲከናወን በአጐራባች ይዞታ ወይም ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርሰ
ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ፣
7) የማፍረስ ሥራ የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ተገቢውን የደህንነት መሣሪያ
መጠቀማቸውን ማረጋገጥ፣
8) በማፍረስ ሥራ ወቅት አቧራም ሆነ ሌላ ብናኝ አካባቢው እንዳይበከል ተገቢውን
መከላከያ መጠቀም፣
9) ከፍተኛ ክብደት ያላቸው ነገሮች በሚፈርስበት ወቅት መሬት ላይ ወድቀው ሌላ ጉዳት
እንዳያደርሱ መጠንቀቅ፣እና
10)የድጋፍ ግርግዳዎች በሚፈርሱበት ወቅት የመሬት መናድ እንዳይከሰት ተገቢውን
ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

11.1.2 በፈንጂዎች በመጠቀም ማፍረስ


በፈንጂዎች በመጠቀም በሚፈርስበት ወቅት ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ፡-

1) የፈንጅዎችን የፍንዳታ መጠን ከሚመለከተው ክፍል ማረጋገጥ፣


2) ፈንጂዎችን ከመጠቀማቸው 5 ቀናት በፊት በአቅራቢያው ላለው የፖሊስ ጽ/ቤት
ማሣወቅ፤
3) በአካባቢው በፈንጂው በሚፈጠረው ንዝረት ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችሉ ንብረቶች
መኖራቸውን ማጣራትና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣
4) ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ በአካባቢው ባሉት ንብረቶች ላይ ጉዳት ቢደርስ
የደረሰውን ጉዳት በመጠገን ወደ ነበሩበት መመለስ፤
5) በሚፈነዳበት ወቅት የድምፅም ሆነ የአቧራ ብክለት እንዳይኖር ተገቢውን ጥንቃቄ
ማድረግ፣
6) ፍንዳታውን የሚያከናውኑት ሠራተኞች ተገቢውን የደህንነት መሣሪያ መጠቀማቸውን
ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

11.2 የቁፋሮ ሥራ

በቁፋሮ ሥራ ወቅት ማንኛውም ስራ ተቋራጭ፡-

1) ሁሉንም የቁፋሮ ሥራዎች በተገቢው ባለሙያ መሰራቱን፣

11
2) የቁፋሮ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ቁፋሮ የሚካሄድበት ቦታ ከማንኛውም የመሠረተ ልማት
ዝርጋታ የፀዳ መሆኑን ፣
3) ዛፎች፣ ቋጥኖች ወይም ሌሎች ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮች ከቁፋሮው ቦታ
በቅድሚያ መወገዳቸውን፣
4) የግንባታ ቦታው አፈር በአግባቡ መጠናቱንና ተገቢው ጥንቃቄ መደረጉን፣
5) ሠራተኞች በአፈር መናድም ሆነ ጉድጎድ ውስጥ በመውደቅ ምንም ዓይነት ጉዳት
እንዳይደርስባቸውጥንቃቄ መደረጉን፣
6) ቁፋሮ ከመጀመሩ በፊት ቁፋሮ የሚካሄድበትን ቦታ ለይቶ መከለል፤
7) የሚቆፈረው ጉድጓድ 1.5 ሜ በላይ ከሆነ ለሠራተኛ መግቢያና መውጫ መሰላል
መዘጋጀቱንና መሰላሉ ከጉድጓዱ የላይኛው ጠርዝ ከ80 ሴ.ሜ በታች ዝቅ አለማለቱን፣
8) የሚቆፈረው ጉድጎድ ከ3 ሜ በላይ የሚቆፈር ከሆነ በ900 ከመቆፈር ይልቅ አግድም
(ስላይድ) አድርጐ መቆፈሩን ፤
9) የቁፋሮ ስራው በሚሰራበት ወቅት አፈሩ የመናድ ባህሪ ካለውና በአከባቢው ሌሎች
ግንባታዎችና የመሰረተ ልማት አውታሮች ካሉ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ግዜያዊ
የድጋፍ መዋቅር (shoring) መሰራቱን፤
10)ቁፋሮው በሚከናወንበት ወቅት በአከባቢው ስነ ምህዳር (ecology)፤ ታሪካዊ ቅርሶችና
ሌሎች ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ሀብቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ
መወሰዱን ፤
11)ተቆፍሮ የሚወጣው አፈር በየጊዜው ከግንባታ ቦታ ላይ መነሳቱን ማረጋገጥ
ይኖርበታል፡፡

11.3. ፎርም ዎርክ (Form work)


Formwork በምንጠቀምበት ጊዜ መደረግ ያለበት

1) ፎርም ዎርክ (Form work) ምንም አይነት ክፍተት ሳይኖረው በአግባቡ መገጠም
አለበት፣
2) የውስጠኛው የፎርም ዎርክ (Form work) ክፍል ንፁህ እና ምንም አይነት ወጣ ገባ
የሌለው መሆን አለበት፣
3) ፎርም ዎርክ (Form work) በሚፈታበት ጊዜ በቀላሉ ከመዋቅሩ ላይ እንዲላቀቅና አደጋ
እንዳያደርስ ለዚሁ አላማ የተዘጋጀ ማለስለሻ ዘይት መቀባት አለበት፤
4) ለስላብ የምንጠቀመው ፎርም ዎርክ (Formwork) ከሆነ ሁሉም በእኩል ደረጃ
መደርደር አለባቸው፣
5) የስላብ ፎርም ዎርክ (Formwork) ለመደገፍ የሚቆመው ቋሚ በቂ ጥንካሬ ሊኖረው
ይገባል፣
6) አርማታ (Concrete) በቂ ጥንካሬ እስኪኖረው ድረስ ፎርም ዎርክ (Form work)
መነሣት የለበትም

12
7) ፎርም ዎርክ (Formwork) መነሣት ያለበት የሚመለከተው ባለሙያ ሲፈቅድ ብቻ
ይሆናል፤
1. ፎርም ዎርክ (Form work) በሚነሣበት ወቅት አደጋ እንዳይፈጥር ተገቢውን ጥንቃቄ
መደረግ አለበት፡፡

11.4. ስካፎልዲንግ (Scaffolding)


Scaffolding ከእንጨት ወይም ከብረት የሚሠራ ጊዜያዊ መዋቅር ሲሆን
በScaffolding አጠቃቀም ወቅት የሥራ ተቋራጩ፡-
1) ተገቢውን ጥንካሬ ያላቸውን እንጨት ወይም ብረት መጠቀም አለበት፣
2) ከመሬት በላይ ከአምስት ወለል በላይ ለሆኑ ህንፃዎች የእንጨት Scaffolding መጠቀም
የለበትም፣
3) ከሦስት ሜትር ከፍታ በላይ ላለ Scaffolding ቢያንስ 1ሜ ከፍታ ያለው የመጠበቂያ
ከለላ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፣
4) ማንኛውም Scaffolding ከሚያንሸራትት ነገር እና ከፍሳሽ ነገሮች የፀደ መሆን አለበት፣
5) ከ10ሜ በላይ ከፍታ ባላቸው Scaffolding ላይ የሚሰሩ ሠራተኛች የወገብ ቀበቶ
ከScaffolding ጋር የተያያዘ መጠቀማቸውን ማረጋገጥ፣
6) ከ15ሜ በላይ ከፍታ ካለ ተገቢውን ከለላ መጠቀም፣
7) ሠራተኞች ተገቢውን የደህነነት መሣሪያ መጠቀማቸውን ማረጋገጥ፣
8) Scaffolding በተገቢው ሁኔታ የተገጠመ ወይም የተያያዘ መሆኑን ማረጋገጥ፣
9) የእንጨት Scaffolding ከሆነ ከአንድ ፕሮጀክት በላይ መጠቀም የማይቻል ሲሆን
የፕሮጀክቱ ጊዜ ረጅም ከሆነና የተለያዩ ወቅቶችን የሚያልፍ ከሆነ የእንጨቱ ጥንካሬ
በባለሙያ ተረጋግጦ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል፣
10)ለመቆሚያነት የሚያዘጋጀው ጣውላ ወይም ብረት በቂ ጥንካሬ ያለው፤ የማያንሸራትት
እና ስፋቱ ከ40 ሴ.ሜ ያላነስ መሆን አለበት፡፡

11.5. ተንጠልጣይ ስካፎልዲንግ (Suspended Scaffolding)

ተንጠልጣይ Scaffolding በሚጠቀሙበት ወቅትማንኛውም ሥራ ተቀራጭ፡-


1) ተንጠልጣይ Scaffolding የሚያንቀሳቅስው ባለሙያ ተገቢውን ልምድና ክህሎት ያለው
መሆኑን ማረጋገጥ፤
2) የማንጠልጠያ ገመዶች ተገቢውን ጥንካሬ እንዳላቸው ማረጋገጥ
3) ተንጠልጣዩ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ችግር የሚፈጥር ነገር እንዳይኖር ተገቢውን
ጥንቃቄ ማድረግ፣
4) ሠራተኞቹ ተገቢውን የደህነነት መሣሪያ መጠቀማቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

13
11.6. መሰላል
በግንባታ ሥራ ወቅት የምንጠቀመው መሰላል ከብረት ወይም ከእንጨት የተሠራ ሆኖ

1. ሁለቱ ቋሚዎች ቀጥ ያሉና በቂ ጥርንካሬ ያላቸው በቁመትም እኩል የሆኑ መሆን


አለባቸው፣
2. አግድም የሚደረደሩት እኩል ርዝማኔ ያላቸው፤ትይዩ የሆኑና በቂ ጥንካሬ ያላቸው
መሆን አለባቸው፣
3. በአግድም በሚደረደሩት መሀል የሚኖረው ርቀት ከ40ሴ.ሜ መብለጥ የለበትም፣
4. የመሰላሉ የታችኛው መቆሚያ የማያንሸራትት መሆን አለበት፣
5. መሰላሉ ላይ ምንም ዓይነት ልብስ ሊይዝ ወይም ቁስል ሊፈጥር የሚችል ነገር መኖር
የለበትም፣
6. በኤሌክትሪክ ስራ ወቅት የምንጠቀምባቸው መሰላሎች ኤሌክትሪክ ከማያስተላልፉ ቁሶች
የተሰሩ መሆን አለባቸው፡፡
7. መሰላሉ በሚቆምበት ወቅት ከሚደገፈው አካል በ300 መሆን አለበት፡
8. የእንጨት መሰላል በሚዘጋጅበት ወቅት እንጨቶችን ቀጣጥሎ መጠቀም አይቻልም፡
9. መሰላልን ለመወጣጫ አንጂ መሰላሉ ላይ ቆሞ መስራት አይቻልም

11.7 ክሬን (Crane)


ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ በሚገነባቸው ግንባታዎች ላይ ክሬን የሚጠቀም ከሆነ
የሚጠቀመው ክሬን፡-

1. በሙያው ብቃት ባለው ሰው የተከላ ንድፍ የተሰራለት እና የተተከለ መሆኑን፣


2. ተገቢው የአደጋ ግምገማ እና የአተገባበር ዘዴ መግለጫ የተዘጋጀ እና የተተገበረ
መሆኑን፣
3. ተገቢው የንፋስ ኃይል መለኪያ መሣሪያ የተገጠመለት መሆኑን፣
4. በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመና በአግባቡ ከጠንካራ መዋቅር ጋር የተያያዘ መሆኑን፤
5. በክሬን የሚነሳው የእቃ ክብደት ከክሬኑ የመሸከም አቅም ጋር የተመጣጠነ መሆኑን፤
6. ክሬኑ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ስር ሆኖ የሚከናወን ስራ አለመኖሩንና ምንም አይነት
የሚንሳቀስ ሰውም ሆነ እንስሳ አለመኖሩን፤
7. ብቃት ያለው ባለሙያ የተመደበለት መሆኑን እና
8. በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀስ 7 መሠረት የተመደበው ባለሙያ ለሥራው ብቁ መሆኑን
የሚያሳይ የጤና ምርመራ በማድረግ ማረጋገጫ ማቅረቡን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

14
11.8 የግንባታ ተሽከርካሪዎች እና ተንቀሳቃሽ የግንባታ ግብዓት
ማቀነባበሪያ
ማንኛውም ሥራ ተቀራጭ ሁሉም የግንባታ ተሽከርካሪዎችና ተንቀሳቃሽ ማቀነባበሪያዎች

1. ለሚሰራው ስራ የሚመጥን የግንባታ ንድፍ ያላቸው መሆኑን፣


2. ጥራት ባለው ሁኔታ የተሰሩ መሆናቸውን፣
3. ለታለመላቸው ሥራ ብቻ መዋላቸውን፣
4. በተሸከርካሪው ማኑዋል መሰረት ወቅታዊ እድሳት የተደረገላቸው መሆኑን ፤
5. አስፈላጊውን ትምህርትና ሥልጠና ወስዶና ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችል ባለሙያ
የሚንቀሳቀሱ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡

11.9 በግንባታ ቦታ ላይ ያሉ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ በኤሌክትሪክ ኃይል


የሚሰሩ ማሽኖችና የግንባታ መሣሪያዎች

ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ፡-

1. የግንባታ ሥራው ከመጀመሩ በፊትና በግንባታ ወቅት ሠራተኞችን ለኤሌክትሪክ አደጋ


የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ያለመኖራቸውን፣
2. በአካባቢው ያሉት የኤሌክትሪክ መስመሮች በግንባታው ምክንያት ምንም ጉዳት
የማይደርስባቸው መሆኑን፣
3. ሁሉም ጊዜያዊ የኤሌክትሪክ መስመሮች ብቃት ባለው ባለሙያ ንድፍ የተሰራላቸውና
የተዘረጉ መሆኑን፤
4. የኤሌክትሪክ ገመዶች ያልተላጡ እና የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ መሆኑን
5. ማንኛውም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀነሳቀሱ ማሽኖች ለዚሁ ሥራ በሰለጠኑና
ብቃታቸው የተረጋገጠ ባለሙያ የሚሠራባቸው መሆኑን እና ለማሽኖቹ አስፈላጊው
ክትትልና ጥገና የሚደረግላቸው መሆኑን፤እና
6. ሠራተኞች የሚጠቀሙባቸው የደህንነት መሳሪያዎች ኤሌክትሪክ የማያስተላልፉ
መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

11.10. በግንባታ ቦታ ላይ ያሉ ተቀጣጣይነት ባህሪ ያላቸው ፈሳሽ ነገሮች


አጠቃቀምና አቀማመጥ በተመለከተ

ማንኛውም ሥራ ተቀራጭ፡-

1. ተቀጣጣይነት ባህሪ ያላቸው ፈሳሽ ነገሮች በጥቅም ላይ ሲውሉ ወይም ሲቀመጡ አደጋ
በማያስከትሉና የሥራ አካባቢን በማይበክሉ መልኩ መሆኑን፣

15
2. በተከማቸበት ቦታ ከእሳትጋር የተያያዘ ሥራ እንዳይሰራ መከላከልና ይህንኑ የሚያሳይ
ምልክት ማስቀመጥ፣
3. ያሉበት መጋዘን ምቹ በሆነ ቦታ ላይ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ የተቀመጠ መሆኑን፣
4. ለአንድ ቀን ፍጆታ ብቻ የሚውል ከመጋዘን እንዲወጣ መደረጉን፣
5. ተቀጣጣይነት ባህሪ ያላቸው ፈሳሽ ነገሮች በጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ የደህንነት
ባለሙያ በቦታው ላይ መገኘቱን፤
6. በደንብ በተከደነ እቃ የተቀመጡ መሆኑንና ካለቀ መያዣው በአግባቡ የተወገደ
መሆኑን፣
7. በቆርቆሮ የታሸጉ ከሆኑ ፈሳሹ ሲያልቅ መያዣው እቃ በተገቢው መንገድ የተወገደ
መሆኑን እና
8. ምንም ዓይነት እሳት ሊያስነሱ የሚችሉና ተቀጣጣይነት ባህሪ ያላቸው ሌሎች ነገሮች
አለመኖራቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡

11.11. የውሃ አካባቢ

ማንኛውም ሥራ ተቃራጭ ግንባታው የሚከናወነው በውሃ ላይ ወይም ለውሃ ቅርበት ባለው


አካባቢ ከሆነ፣

1. በግንባታ ስራው ምክንያት ውሀው ሊበከል እንደማይችል ፤


2. ሰዎች ወደ ውሃ እንዳይወድቁ መከላከያ የተሰራ መሆኑን፣
3. የመስጠም አደጋ ሲያጋጥም የህይወት አድን ባለሙያ የተመደበ መሆኑን እና
4. በቂ ከመስጠም የሚከላከል መሣሪያ ለሠራተኞች የተዘጋጀ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት
አለበት፡፡

11.12. አጠቃላይ የግንባታ ቦታ አጠባበቅን በተመለከተ

ማንኛውም ሥራ ተቀራጭ የግንባታ ቦታውን ጥበቃ ቀጥሮ የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ
እንደተጠበቀ ሆኖ፡-

1. የግንባታ ግብዓቶች በሙሉ በአግባቡ የተቀመጡ መሆኑን፣


2. የግንባታ ተረፈ ምርቶች በአግባቡ የተወገዱ መሆኑን፣
3. የግንባታ ግብዓቶች የግንባታ ስራን በማያውክ መልኩ የቀመጡ መሆኑን፣
4. ግንባታ ላይ የማይውሉ ነገሮች በተገቢው ጊዜ የሚወገዱ መሆኑን፣
5. የግንባታ ተረፈ ምርት ወይም ፍርስራሽ ከከፍታ ቦታ ሲወገድ በተገቢው ጥንቃቄ
የሚወገዱ መሆኑን፣
6. የግንባታ ቦታው በአግባቡ የታጠረ መሆኑን እና
7. ከሥር ሰዎች የሚተላለፉበት ቦታ ላይ ከላይ ግንባታ የሚካሄድ ከሆነ ተገቢውን
መከላከያ የተገነባ መሆኑን የማረጋገጠ ኃላፊነት አለበት፡፡

16
11.13.ማከማቻ (መጋዘን) በተመለከተ

ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ በግንባታ ቦታ ላይ፡-

1. ተገቢውን የመጋዘን ሠራተኛ የመመደብ፤


2. የሚመደቡት ሰራተኞች አስፈላጊው የደንብ ልብስ የተሟላላቸው መሆኑን፤
3. የሚዘጋጀው ማከማቻ (መጋዘን) ዝናብም ሆነ ጎርፍ ሊያስገባ የማይችል መሆኑን
4. የሚዘጋጀው ማከማቻ (መጋዘን) የተሰራበት ቁስ በእሳት በቀላሉ የማይቀጣጠል መሆኑን
5. በመጋዘኑ ውስጥ የሚሰራው የእቃ መደርደሪያ አስፈላጊውን ጥንካሬ ያለው መሆኑን
ማረጋገጥ
6. በመደርደሪያው ላይ የሚቀመጡ ዕቃዎች እንዳይናዱ ተገቢውን ከለላና ድጋፍ
የተደረገላቸው መሆኑን እና፣
7. የሚዘጋጀው ማከማቻ (መጋዘን) በአግባቡ የተከለለና፤ በቂ ስፋት ያለው እና ብርሀን
ሊያስገባ የሚችል፤ አየር እንደልብ የሚዘዋወርበት ንጽህናው የተጠበቀ የማዘጋጀት
ኃላፊነት አለበት፡፡

11.14. በግንባታ ቦታ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት መደረግ ያለበት ጥንቃቄ

ማንኛውም ሥራ ተቀራጭ በግንባታ ቦታ ላይ፡-

1. የእሳት አደጋ እንደይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ፣


2. ተቀጣጣይነት ባህሪ ላላቸው ነገሮች በቂና መቹ ቦታ ማዘጋጀት፣ እና
3. ዝግ በሆኑ አካባቢዎችና ሌሎች የእሳት አደጋ ሊከሰት በሚችሉባቸው ቦታዎች ላይ ያሉ
የኤሌክትሪክ መስመሮች በአግባቡ መከላከያ የተደረገላቸው መሆኑን እንዲሁም ምንም
ዓይነት ተቀጣጣይነት ባህሪ ያላቸው ነገሮች ወይም እሳት ሊያስነሱ የሚችሉ ነገሮች
አለመኖራቸውን ፣
4. ምቹና በቂ የእሳት ማጥፊያ በተገቢው ቦታ መኖሩን፣
5. በአንቀጽ ንዑስ አንቀጽ የተጠቀሰው የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ ብቃት
ባለው ባለሙያ በየጊዜው ፍተሻ የሚደረግለት መሆኑን፣
6. በቂ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ አጠቃቀም በቂ ሥልጠና
የተሰጣቸው መሆኑን፣
7. የእሳት አደጋ ሲከሰት በደንብ በሚታጥ ቦታ ከአደጋ ማምለጫ አቅጣጫ ጠቀሚ
ምልክት የተቀመጠ መሆኑን፣
8. በአደጋ ጊዜ የማምለጫ መንገዶች ጽዱና በቂ ስፋት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡

11.15 የመውደቅ መከላከያ

ማንኛውም ስራ ተቋራጭ፡-

17
1. የመውደቅ መከላከያ እቅድ የሚያዘጋጅ ብቁ የሆነ ባለሙያ ይመድባል፣
2. የተዘጋጀው እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋል፣ በአስፈላጊው ጊዜ እና ቦታ እንዲሻሻል
ያደርጋል፣
3. የመከላከያ እቅድ ተግባራዊነት ቀጣይነት እንዲኖረው አስፈላጊ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡

11.16 የዕቃ ማመላለሻ

የዕቃ ማመላለሻ ዕቃዎች ወደ ላይና ታች በሚመላለሱበት ወቅት ማንኛውም ሥራ ተቀራጭ፡-

1) በቂ ልምድና ክህሎት ያለው ባለሙያ የመመደብ፤


2) በጠንካራ ገመድ የተንጠለጠሉ መሆናቸውን የማረጋገጥ፣
3) ማመላለሻ ማሽኖቹ ከሚችሉት አቅም በላይ እቃ እንዳይጫን የማድረግ፣
4) በማመላለሻ ማሽኖቹ አካባቢ ሌሎች ሠራተኞች አንዳይኖሩ የማድረግ፣
5) ድንገት የገመድ መበጠስ አጋጥሞ አደጋ እንዳያደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ የማድረግ፤
6) ሠራተኞች ተገቢው የደህንነት መሣሪያ መጠቀማቸውን የማረጋገጥ፣
7) መሣሪያዎቹን በየወቅቱ እድሳት እዲደረግላቸው የማድረግ፣ እና
8) የዕቃ ማመላለሻ ማሽኖች ተገቢው ጥንካሬ እንዳላቸው የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርበታል፡

11.17. የሰው ማመላለሻ

የሰው ማመላለሻ ማሽኖች ሥራ ላይ በሚውሉበት ወቅት ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ፤

1. በቂ ልምድና ክህሎት ያለው ባለሙያ የተመደበ መሆኑን፤


2. የሰው ማመላለሻ ማሽኖች ተገቢው ጥንካሬ እንዳላቸው ማረጋገጥ፣
3. የማንጠልጠያ ገመዶች ጥንካሬን በየወቅቱ መፈተሽ፣
4. ማሽኖቹ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እንቅስቃሴውን የሚያውክ ነገር አለመኖሩን፤
5. ለመሣሪያዎቹ በየወቅቱ ተገቢውን ጥገና ማድረግ፣
6. ከማመላለሻ ማሽኖቹ አቅም በላይ ሰው እንዳይጫን ጥንቃቄ ማድረግ፣
7. የማመላለሻ ማሽኖቹ እስከ 1.5 ሜ ድረስ የተሸፈኑ መሆን አለባቸው፡፡
8. ማመላለሻ ማሽኖቹ በኤሌክትሪክ ኃልይ የሚሰሩ ከሆነ አማራጭ የኃይል ምንጭ
መዘጋጀቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡

11.18. የጣራ ሥራ

የጣራ ስራ ሲሰራ (ለመሥራት) ማንኛውም ስራ ተቋራጭ፡-

1. የጣራ ስራውን የሚሰሩ ሠራተኞች በአካል ብቁ የሆኑ አስፈላጊውን እውቀት እና ልምድ


ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ፤

18
2. ከፍተኛ የንፋስ ፋጥነት እና ከባድ ዝናብ ባለበት የአየር ጠባይ ሁኔታ ውስጥ
የሠራተኞች ደህንነት ስለማይጠበቅ የጣራ ሥራ ማስቆም፤

3. በጣሪያ ጠርዝ አካባቢ ለሚሰሩ ሠራተኞች የደህንነት ቀበቶ ወይም እሱን ሊተካ የሚችል
የደህንነት መጠበቂየ መሣሪያ ማቅረብ ፣

4. ለጣሪያ መውጫ የሚጠቀሙበት መሰላል፣ መተላለፊያ መንገዶች አስተማማኝ


መሆናቸውን እና በትክክል ከመዋቅሩ ጋር መያያዛቸውን ማረጋገጥ፣

5. ጉድለት ያለው የጣራ ሥራ ሲሰራ ብቁ እና አስተማማኝ የሆነ የመረማመጃ ጣውላ


ወይም መሰላል ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መዘጋጀቱን ማረጋገጥ፣

6. የሚሰበር የጣራ መዋቅር ያለው የግንባታ ሥራ ሲሰራ ቋሚ የሆኑ የአደጋ ማስጠንቀቂያ


ፅሁፍ በጣሪያው አቅራቢያ መቀመጡን፣ እና

7. የጣሪያ ቅንፎች ከጣሪያው ግድለት (slope) የሚጣጣሙ ሆነው አስተማማኝ እና


ጠንካራ በሆነ ድጋፍ መደገፋቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

11.19. የኮንክሪት ማቀነባበሪያዎች (bulk mixing plant)

ማንኛውም ስራ ተቋራጭ፡-
1) በኮንክሪት ማቀነባበሪያዎች በቂ እውቀትና ልምድ ያለው ባለሙያ መመደብ አለበት፣
2) በኮንክሪት ማቀነባበሪያዎችላይ ለሚመደቡ ሠራተኞች አደጋን ከመቀነስ አንፃር በቂ
ሥልጠና መስጠት አለበት፣
3) ኮንክሪት ማቀነባበሪያውን ከተመደበለት ባለሙያዎች ውጭ ማንም ሰው እንዳይነካ
ጥንቃቄ ማድረግ፣
4) አንድ የኮንክሪት ማቀነባበሪያ ማሟላት ያለበት መስፈርት አሟልቶ መገኘቱን
ማረጋገጥ አለበት፡፡
5) ኮንክሪት ማቀነባበሪያ የተገነባበት ቦታ በቀላሉ ተደራሽ የሆነ እና አደጋዎችን
ለመከላከል ምቹ መሆኑንማረጋገጥ አለበት፣
6) የሚጠቀማቸው የኮንክሪት ማቀነባበሪያዎች ጥራታቸው የተረጋገጠ መሆን አለበት፣
7) የኮንክሪት ማቀነባበሪያውን ወቅቱን የጠበቀ ጥገና በትክክለኛ ባለሙያ ማድረግ
አለበት፡፡

11.20 ለግንባታ ሥራ ሠራተኞች ሊሟሉላቸው የሚገቡ ነገሮች

ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ ደረጃውንና ንጽህናውን የጠበቀ፣

1. የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ ቦታና በዘርፉ በቂ እውቀትና ክህሎት ያለው ባለሙያ
መመደቡን፤

19
2. የባኞ (ሻወር) አገልግሎት፣
3. ንጹህና ለሁለቱም ፆታ የተለየ መፀዳጃ ቤት መኖሩን፤
4. ለሁለቱም ፆታ የተለየ የልብስ መቀየሪያ ክፍል፣
5. የተከለለ የመመገቢያና ማረፊያ ቦታ ፤
6. የምግብና የሻይ ቡና አገልግሎት መስጫ ቦታ እና
7. በካምፕ ውስጥ ለሚኖሩ ሠራተኞች ምቹ የመኖሪያ ቦታ መመቻቸቱን ማረጋገጥ
አለበት፡፡

12. በግንባታ ግብዓት ማምረቻ ቦታዎች ላይ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ


ማንኛውም የግንባታ ግብዓት አምራች ባለቤት
1. በግንባታ ግብዓት ማምረቻ ቦታ ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞች እንደ ስራው ዓይነት ከላይ
በግንባታ ቦታ ለሚሰሩ ሰራተኞች መደረግ ያለበት ጥንቃቄ በሙሉ ማድረግ አለበት
2. የግብዓት ማምረቻ ቦታዎች የማምረት ተግባሩ በሚጠናቀቅበት ወቅት በአግባቡ
መስተካከልና የተቆፈሩ ጉድጓዶች ካሉ መልሰው በመድፈንና በደንብ በመጠቅጠቅ
ለሚመለከተው ክፍል ማስረከብ ይኖርበታል፡፡

20
ክፍል ሦስት
የጤናና ደህንነትአብይና ንኡስ ኮሚቴዎችን
ስለማቋቋም

12.የደህንነትና ጤና ንኡስ ኮሚቴ


12.1.ስለተጠሪነትና የስራ ዘመን

1) የደህንነትና ጤና ንኡስ ኮሚቴ ተጠሪነቱ በቢሮ ስር ለሚቋቋመው አብይ ኮሚቴ


ነው፡፡
2) የደህንነትና ጤና ንኡስ ኮሚቴ የስራ ዘመን የተጀመረው የግንባታ ስራ
አስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡

12.2. የአባላት ስብጥር፤ብዛትና ኃላፊነታቸው

የደህንነትና ጤና ንኡስ ኮሚቴ አምስት አባላት የሚኖሩት ሲሆን ሁለቱ ከሠራተኛው አንድ
ከአማካሪ ድርጅት አንድ ከስራ ተቋራጭ እና አንድ ከአሰሪ ሆኖ ከአሰሪው የሚመደበው
በሰብሳቢነት የሚመራ ሲሆን ኮሚቴው ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ኃላፊነትና ተግባር ይኖሩታል፡፡

1) ለሰራተኞች በቂ የደህንነትና ጤናና መጠበቂያ መሳሪያ መቅረቡን ማረጋገጥ፤


2) ማንኛውም ሥራ ምን ያህል የሠራተኛውን ደህንነት ያረጋገጠ መሆኑን መከታተል፣
3) በወር አንድ ጊዜ ሥራዎችን መገምገምና ሪፖርት ማድረግ፣
4) ለዋናው ተቆጣጣሪ ከግንባታ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳይ ላይና አስፈላጊ በሆኑ
ሥልጠናዎች ዙሪያ ምክር መስጠት፣
5) ችግሮች ሲፈጠሩ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰዱ ለስራ ተቋራጩ ማሳወቅ፣
6) የማስተካከያ እርምጃ በወቅቱ መደረጉን መከታተል ካልተስተካከሉ ለባለቤቱ ማሳወቅና
አፈፃፀሙን መከታተል፤
7) ከላይ በአንቀጽ …ንኡስአንቀጽ…መሰረት የማየስተካከል ከሆነ ለቢሮው በማሳወቅ
የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ፤
8) በስራ ቦታ ላይየተከሰቱ አደጋዎችን መረጃ አጠናቅሮ በመያዝ የስራ ዘመኑ ሲጠናቀቅ
ለአብይ ኮሚቴው ማስረከብ ይኖርበታል፡፡

21
13.የግንባታ ሠራተኞች የጤና እና ደህንነት አብይ ኮሚቴ
በክፍለ ከተማው የኮንስትራክሽን ፅ/ቤት ኃላፊ የሚቋቋምና ከዚህ በታች የተጠቀሱት አባላት
የሚኖሩት የግንባታ ሠራተኞች አብይ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡

1. አንድ ከክፍለ ከተማው ኮንስትራክሽን ፅ/ቤት የሚደብ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣


2. አንድ ከክፍለ ከተማው ኮንስትራክሽን ፅ/ቤት የሚደብ የኮሚቴው አባል፤
3. አንድ ከክፍለ ከተማው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የሚወከል አባል፡
4. አንድ ከስራ ተቋራጮች ማኅበር የሚወከል አባል፣እና
5. አንድ ከአማካሪ ድርጅት ማኅበር የሚወከል አባል

13.1የአብይ የኮሚቴዉ ተግባርና ኃላፊነት

1) በክፍለ ከተማው አዳዲስ ግንባታ ቦታዎች ላይ የጤናና ደህንነት ጉዳይ ንኡስ ኮሚቴ ያቋ
ቁማል፤
2) የስራ ዘመናቸውን ከሚያጠናቅቁ ንኡስ ኮሚቴዎች የተረከባቸውን ፋይሎች አደራጅቶ
ይይዛል፤
3) ከፅ/ቤት ኃላፊ የሚመራለትን የስነምግባር ጥሰት ጉዳይ ያጣራል፤ የውሳኔ ሃሳብ ለፅ/ቤት
ኃላፊ ያቀርባል፤
4) ተፈጸመ የተባለውን የጤናና ደህንነት መተዳደሪያ ደንብ ጥሰት ክስ በዚህ ደንብ
ድንጋጌዎች እና ጥፋቱ በተፈጸመበት ጊዜ በስራ ላይ በነበሩ ሌሎች ህጎች መሰረት
ይመረምራል፤ለፅ/ቤት ኃላፊ ያቀርባል፤
5) በየግንባታ ቦታዎች ያጋጠሙ የጤናና ደህንነት አደጋዎች ይመረምራል የመፍትሄ ሀሳብ
ለፅ/ቤት ኃላፊ ያቀርባል፤እና
6) ግንባታ ቦታ በመሄድ ይከታተላል ርፖርት ለፅ/ቤት ኃላፊ ያቀርባል፤
7) በተለያዩ የስራ ቦታዎች የተከሰቱ አደጋዎችን መንስኤና ያስከተሉትን ጉዳት በመቀመር
ለዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሻሻልም ሆነ ለሌሎች ህጎች መነሻነት እንዲውል ለቢሮ
ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይልካል፤ እና
8) ከግንባታ ቦታ የጤናና ደህንነት ንኡስ ኮሚቴ የሚላክለትን ሪፖርት በመቀመር ለፅ/ቤት
ኃላፊ ያቀርባል፤

13.2የኮሚቴዉ ሰብሳቢና ፀሐፊ ኃላፊነትና ተግባር

13.2.1የኮሚቴዉ ሰብሳቢ ሃላፊነትና ተግባር


1) ኮሚቴዉን በበላይነት ይመራል፤
2) እርሱ በማይኖርበት ጊዜ ከአባላቱ ውስጥ ስብሰባውን የሚመራ ይወክላል፣
3) ኮሚቴዉ የሚመራበትን የሥራ መመሪያ ከኮሚቴዉ አባላት ጋር ያዘጋጃል፣
4) የደንብ ጥሰት ክሶችን ይቀበላል፣

22
5) ኮሚቴዉ የሚሰጠውን ውሣኔ ለቢሮው በጽሁፍ ወይም በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴ
እንዲደርሰው ያደርጋል፣
6) በኮሚቴዉ ውሳኔ የተሰጠባቸውን ጉዳዮች አፈፃፀም ይከታተላል፤
7) በዳኝነት አካል ሲጠየቅ የውሳኔውን ቅጂ ይሰጣል፣

13.2.2 የኮሚቴዉ ፀሐፊ ተግባርና ኃላፊነት

1) የስብሰባ አጀንዳና ቃለ ጉባዔ ይይዛል፤


2) የስብሰባቃለ ጉባዔ በአግባቡ እያዘጋጀ አባላቱ እንዲፈርሙበት ያደርጋል፣
3) አስፈላጊ መረጃዎች እና ሰነዶች እንዲገኙ በስብሰባ ወቅት ተሟልተው ያደርጋል፣
4) ኮሚቴዉ የተሟሉ ሰነዶች እና መዛግብቶች እንዲኖሩት ያደርጋል፣
5) ከኮሚቴዉ ሰብሳቢ በሚሠጠው መመሪያ መሰረት አጀንዳ ያዘጋጃል፤
6) የኮሚቴው አባልና ፀሐፊ ሆኖ ይሰራል፣
7) የጤናና ደህንነት መተዳደሪያ ደንብ ጥሰት ክስ የቀረበባቸውን ሰነዶች እና ለምርመራ
የተሰበሰቡ መረጃዎችን መዝግቦ ይይዛል፣
8) ውሳኔ የተሰጠባቸውንና ሌሎች ሠነዶችን መዝግቦ በጥንቃቄ ይይዛል፣

13.የግንባታ ሠራተኞች የጤና እና ደህንነት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ


በቢሮው ኃላፊ የሚቋቋምና ከዚህ በታች የተጠቀሱት አባላት የሚኖሩት የግንባታ ሠራተኞች
ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡

1. አንድ ከቢሮው የሚደብ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣


2. አንድ ከቢሮው የሚደብ የኮሚቴው አባል፤
3. ሁለት ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የሚወከሉ አባላት፣
4. አንድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም፤
5. አንድ ከስራ ተቋራጮች ማኅበር የሚወከል አባላል፣እና
6. አንድ ከአማካሪ ድርጅት ማኅበር የሚወከል አባል

14.የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዉ ስልጣንና ኃላፊነት

9) የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ከቢሮው የሚመደብ ይሆናል፡፡


10) በአብይ ኮሚቴው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ሰው ውሳኔው በደረሰው በአሥር የሥራ ቀናት
ውስጥ ይግባኝ ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ማቅረብ ይችላል፡፡
11)ከአብይ ኮሚቴዎች የሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርብለትን ይግባኞች ይመረምራል፤
የውሳኔ ሃሳብ ለቢሮ ኃላፊው ያቀርባል፡፡
23
12)የይግባኝ ሰሚኮሚቴ ውሳኔዎች በአብላጫ ድምጽ ይወሰናሉ፡፡
13)የይግባኝ ሰሚኮሚቴ ይግባኝ በቀረበለት በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
14)የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በይግባኙ ላይ የሚያስተላልፈውን ውሳኔ በጽሁፍ ለሁለቱም
ወገኖች እና ለቢሮው ውሳኔውን በሰጠ በ3 የሥራ ቀናት ውስጥ በፅሑፍ ያሳውቃል፡፡
15)የይግባኙ ቅጂ ለመረጃ እንዲሆን ለቢሮ ሀላፊ፣ ለኮሚቴዉ የሚሰጥ ሲሆን ሌላው
ተከራካሪ ወገን ለይግባኙ መልስ የመስጠት መብት አለው፡፡
16) ከክፍለ ከተማ አብይ ኮሚቴዎች የተረከባቸውን ፋይሎች አደራጅቶ ይይዛል፤

15. የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና ፀሐፊ ሥልጣንና ተግባራት፣

1. የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሥልጣንና ተግባር፣


ሀ) የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዉንን በበላይነት ይመራል፣

ለ) እርሱ በማይኖርበት ጊዜ ከአባላቱ ውስጥ ስብሰባውን የሚመራ በቢሮው እንዲወከል


ያደርጋል፣

ሐ) የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚመራበትን የሥራ መመሪያ ከኮሚቴ አባላት ጋር ያዘጋጃል፣

መ) ይግባኞችን ይቀበላል፣

ረ) የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚሰጠውን ውሣኔ ለተከራካሪ ወገኖች፣ ለቢሮው በጽሁፍ


ወይም በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፣

ሰ) በዳኝነት አካል ሲጠየቅ የውሳኔውን ቅጂ ይሰጣል፣

2. የይግባኝ ሰሚ የኮሚቴ ፀሐፊ ሥልጣንና ተግባርና ኃላፊነት

ሀ) የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባልና ፀሐፊ ሆኖ ይሰራል፣


ለ) የስብሰባ አጀንዳና ቃለጉባዔ እየያዘና በአግባቡ እያዘጋጀ አባላቱ እንዲፈርሙበት ያደርጋል፣

ሐ) አስፈላጊ መረጃዎች እና ሰነዶች በስብሰባ ወቅት ተሟልተው እንዲገኙ ያደርጋል፣


መ) የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የተሟሉ ሰነዶች እና መዛግብቶች እንዲኖሩት ያደርጋል፣

ሠ) ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሚሠጠው መመሪያ መሠረት አጀንዳ ያዘጋጃል፣

ረ) ይግባኝ የተጠየቀባቸውን ሰነዶች እና ለምርመራ የተሰበሰቡ መረጃዎችን በአግባቡ መዝግቦ


ይይዛል፣

ሰ) ውሳኔ የተሰጠባቸውንና ሌሎች ሠነዶችን በአግባቡ መዝግቦ ይይዛል፡፡

24
ክፍል አራት
የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ስርዓት
1) ማንኛውም የግንባታ ቦታ ሠራተኛ በንኡስ ኮሚቴ ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል ለፅ/ቤቱ
የጤናና ደህንነት አብይ ኮሚቴ በጽሑፍ በአምስት የስራ ቀናት ውስጥ ማቅረብ
ይኖርበታል፤
2) የፅ/ቤቱ የጤናና ደህንነት አብይ ኮሚቴ ቅሬታው በቀረበለት 5 የስራ ቀናት ውስጥ
ለፅ/ቤቱ ኃላፊ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፤
3) የፅ/ቤቱ የጤናና ደህንነት አብይ ኮሚቴ በንኡስ ኮሚቴ የተሰጠውን ውሳኔ
ሊያፀናው፣ ሊያሻሽለው ወይም ሙሉ በሙሉ ሊሽረው እና ሌላ የተለየ የውሳኔ
ሀሳብ ሊሰጥ ይችላል፣
4) የቢሮው ኃላፊ ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚቀርብለትን የውሳኔ ሃሳብ በሶስት የስራ
ቀናት ውስጥ በመመልከት ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ ሊያፀናው፤ በከፊል ሊያሻሽለው
ወይም ሙሉ በሙሉ ሊሽረው ይችላል ይህም የመጨረሻ ይሆናል፡፡
5) ከቢሮው ውሳኔ በኋላ ቅር የተሰኘ አካል ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት የመውሰድ
መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

25
ክፍል አምስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
14.ቅጣት

በሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር የዚህን ደንብ ድንጋጌዎች የተላለፈ


ማንኛውም ስራ ተቋራጭ ወይም አማካሪ ድርጅት በቢሮው አብይ ኮሚቴ፡-

1) እንደ ጉዳዩ ክብደት ጥፋቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ በሌላ ህጎች የሚያስጠይቀው


እንደተጠበቀ ሆኖ የስራ ተቋራጩን እስከ አንድ አመት በከተማው አስተዳደር ክልል
ውስጥ በየትኛውም ሌላ ግንባታ ላይ እንዳይሳተፍ ይታገዳል፣ ባለሙያውም
በኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ስነምግባር ደንብ መሰረት ተጠያቂ ይደረጋል።
2) ጥፋቱ ከቅጣቱም በሃላ ዳግም የተከሰተ ከሆነ በከተማው ውስጥ ተቋራጩ
እስከመቼውም እንዳይሰራ የሚታገድ ይሆናል፣ ባለሙያውም በኮንስትራክሽን
ባለሙያዎች ስነምግባር ደንብ መሰረት ተጠያቂ ይደረጋል።
3) እንደ ጉዳዩ ክብደት ጥፋቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ በሌላ ህጎች የሚያስጠይቀው
እንደተጠበቀ ሆኖ አማካሪው የግንባታ ቦታው ላይ እንዲቆጣጠር የመደበው ባለሙያ እና
የቅርብ ኃላፊው በኮንስትራክሽን ባለሙያዎች የስነ ምግባር ደንብ ተጠያቂ ይሆናሉ።
4) በቢሮው አብይ ኮሚቴ ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል ለቢሮው ኃላፊ በ 5 የስራ ቀናት ውስጥ
ቅሬታውን በጽሁፍ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
5) የቢሮው ኃላፊ የቀረበለትን ቅሬታ መርምሮ በአምስት የስራ ቀናት ውስጥ የመጨረሻ
ውሳኔ ይሰጥበታል ይህም የመጨረሻ ይሆናል፡፡
6) ከቢሮው ውሳኔ በኋላ ቅር የተሰኘ አካል ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት የመውሰድ መብቱ
የተጠበቀ ነው፡፡

16.የመተባበር ግዴታ፣
ማንኛውም ሰው ይህን ደንብ በማስፈጸም ረገድ የመተባበር ግዴታ አለበት::

17. ተፈፃሚነትስለማይኖረውሕግ
የዚህን ደንብ ድንጋጌዎች የሚቃረን ማንኛውም ሕግ ወይም የአሰራር ልማድ በዚህ
ደንብ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

18. መመሪያ የማውጣት ስልጣን፤


ኮንስትራክሽን ቢሮ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ መመሪያችን ሊያወጣ
ይችላል።

26
19. ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ ደንብ ከፀደቀበት ከ----- ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ---- ቀን ፪ሺ፲፩ ዓመተ ምህረት

ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ

27

You might also like