You are on page 1of 3

ብሬክስሩ ትሬዲንግ ‹ባለራዕይ፣ ቅን፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድን ለመፍጠር የሚል ዓላማን ሰንቆ ቅን በተሰኘና አሥራ

ስድስት አባላት ባሉት ቡድን ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በዋናነት የሰብዕና ማጎልበቻ
ሥልጠናዎችን ለግለሰቦች፣ ለድርጅቶች፣ ለተቋማትና ለካምፓኒዎች እየሰጠ የሚገኝ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዜጎች
በተማሩበት መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ፣ የተፈጠሩበትንና የተጠሩበትን ዓላማ እንዲያውቁ፣ ከጥገኝነት መንፈስ
ተላቀው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመጣመር ፕሮግራሞችን ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ
ይገኛል፡፡ በድርጅቱ ሥራዎች ዙሪያ የማነ ብርሃኑ ሥራ አስፈጻሚውን አቶ አብዱልፈታህ ሁሴንን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሬክስሩ ትሬዲንግ መቼ ተቋቋመ? የተቋቋመለትስ ዓላማ ምንድነው?

አቶ አብዱልፈታህ፡- ድርጅታችን የተቋቋመው ታኅሣሥ 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ በተለያዩ ሙያ ውስጥ የሚገኙ 16
ኢትዮጵያውያን ‹ለአገራችን ምን እናበርክት› በሚል የመሠረቱት ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ከግል ሰብዕና ሥልጠና፣ ከንግድና
ከተለያዩ የቢዝነስ ሥራዎች አንፃር ከነበራቸው ልምድና ተሞክሮ በመነሳት ቅን፣ ባለራዕይ፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድ
ማፍራትን ታሳቢ በማድረግ የግል ሰብዕና ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ የሚገኘውን ድርጅቱን
መሥርተውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ የሚሰጠው የሰብዕና ሥልጠና በይዘት ምን ላይ ያተኮረ ነው?

አቶ አብዱልፈታህ፡- የግል ሰብዕና ሥልጠናው የሚሰጠው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች በሌክቸረርነት፣
በባንክና በተለያዩ መስኮች ልምድና የዳበረ ዕውቀት ባላቸው ምሁራን ነው፡፡ ሥልጠናው ረዥም ጊዜ ተወስዶበት ዝግጅት
ተደርጎበትና ሞጁሎች ተቀርፀውለት የሚሰጥ ነው፡፡ ሥልጠናው ሰዎችን ከማበረታትና ከማነሳሳት መንፈስ በዘለለ፣
መሬት ወርዶ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ እየተሰጠም ይገኛል፡፡ ሥልጠናዎቻችን የግለሰቦችን
የአዕምሮ ደረጃና የትምህርት ዝግጅት በሚመጥን መልኩ በግል ሰብዕና፣ በአዕምሮ ግንባታ፣ ኃያልነት፣ የመሪነትና የቡድን
ሥራ በመሳሰሉት ርዕሶች ለግለሰቦች፣ ለድርጅቶችና ለተቋማት በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የምትሰጡት ሥልጠና የዜጎችን ሕይወት ከመለወጥ አንፃር ምን አበርክቶ ነበረው?

አቶ አብዱልፈታህ፡- ድርጅታችን ላለፉት አራት ዓመታት ለ 41,000 ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ካምፓኒዎች
ሥልጠና የሰጠ ሲሆን፣ በዚህም ግለሰቦቹ የነበረባቸውን ከፍተት እንዲለዩ፣ ካለባቸው መጥፎ ልምድና አመለካከት
እንዲርቁ ከማድረግና ሰብዕናቸውን ከመቅረፅ አንፃር ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ሥልጠናችንን የተከታተሉ ሰዎች
በሕይወታቸው ላይ ያመጡትን ለውጥ ከቢዝነሳቸው፣ ከጤናቸው፣ ከአመለካከታቸውና ከተለያዩ መጥፎ ልማዶች
መውጣታቸውንና መሻሻል ማሳየታቸውን በቅርበት እንከታተላለን፡፡ የእኛን ሥልጠና ወስደው ሕይወታቸውን የቀየሩና
የራሳቸውን ቢዝነስ የጀመሩ በርካታ ወገኖችም አሉ፡፡ ሥልጠናችን ሰዎች የይቻላል መንፈስን እንዲያዳብሩና ወድቆ
መነሳት እንዳለ እንዲያውቁም የሚያግዝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሥልጠናችሁ ከትምህርት ሥርዓታችንና ከባህላችን ጋር ምን ያህል የተጣጣመ ነው?

አቶ አብዱልፈታህ፡- የምንሰጠው ሥልጠና የትምህርት ሥርዓቱንና ባህላችንን ታሳቢ ተደርጎ የተቀረፀ ከመሆኑ ባሻገር
ዜጎች በተማሩበትና በሠለጠኑበት ሙያ ውጤታማ እንዲሆኑና አዕምሯቸውን እንዲጠቀሙ በማገዝ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ማንም ያለ ምክንያት አልተፈጠረምና ዜጎችን እንዳይባክኑ እንሠራለን፡፡ በዚሁ መሠረት ሰዎች የተፈጠሩበትን ዓላማ
እንዲያውቁ፣ ማንነታቸውን በጥልቀት እንዲፈትሹና በተማሩበት ሙያ ውጤታማ እንዲሆኑ በሥልጠናችን
እንደግፋለን፡፡ ልጆች ከሕፃንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ዝንባሌያቸውን እንዲያውቁና እንዲረዱ፣ ነገ ለአገር መልካምና
የተሻለ የሚያበረክቱ ሆነው እንዲቀረፁ ለማስቻል በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ‹ፍቅር አስኳላ› የሚል ትምህርት ቤት ከኬጂ
ጀምረን በማስተማር ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ትምህርት ቤታችንም ልጆች አገራቸውን፣ ባህላቸውንና እሴታቸውን
እንዲያውቁና እንዲረዱ እያደረግን ሲሆን፣ በመማር ማስተማሩ ሒደትና ልጆች ላይ በምንሠራው ሥራም ከቦሌ ክፍለ
ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ዕውቅናና ሽልማት አግኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የምትሰጡት ሥልጠና በአገር ውስጥ የተወሰነ ነው ወይስ በውጭ አገሮችም ትሰጣላችሁ?

አቶ አብዱልፈታህ፡- የምንሰጠው ሥልጠና በአገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በኦንላይን የምንሰጣቸው


ሥልጠናዎች ስላሉን በተለያዩ አገሮች ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ለውጭ አገር ዜጎች እየደረስን እንገኛለን፡፡
በተጨማሪም በእስራኤልና በደቡብ ሱዳን ቢሮ ከፍተን የጤና መጠበቂያ ምርቶችንና ሥልጠናዎችንም በመስጠት ላይ
ስንሆን፣ በዚህም ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ትልቅ አበርክቶ በማድረግ ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ እየሰጠው ባለው ሥልጠና ሥራ አጥነትን በመቅረፍ ረገድ የተጫወተው ሚና ምንድነው?

አቶ አብዱልፈታህ፡- ድርጅታችን ሥራ አጥ ወጣቶችንና ወገኖችን ወደ ሥራ በማስገባት አምራች ዜጋ እንዲሆኑ


ከማስቻል፣ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር፣ የተለያዩ የአዕምሮና የሥነ
ልቦና ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ብዙ ወገኖች ከሥራ አጥነት እንዲወጡ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ነድፈን
በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶች ከጠባቂነት መንፈስ ተላቀው በአገር ግንባታ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ
እንዲያበረክቱ ለማስቻል፣ ከሴቶችና ከማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር 20 ሚሊዮን ወጣቶች ካሉባቸው ማኅበራዊ
ችግሮች ወጥተው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የስምንት ዓመት ፕሮጀክት ቀርፀን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ አካል ጉዳተኞች
በአገሪቱ የልማት ዘርፍ ተሳታፊና ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ በማድረግ ረገድም ድርጅታችን ፕሮግራሞችን ቀርፆ
በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የብሬክስሩ አጋር ድርጅቶች እነማን ናቸው? ከእነማንስ ጋር በቅርበት ይሠራል?

አቶ አብዱልፈታህ፡- ድርጅታችን ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል፡፡
ከተለያዩ ባንኮች፣ ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ
ሚኒስቴር፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በጥምረት በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡
ለአብነት ያህል ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ድርጅታችን በቅርቡ ለሠራተኞቻቸው የሦስት ቀናት ሥልጠና
ሰጥቷል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ላለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅታችን ሥልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣
ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋርም እንዲሁ የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት በተለያዩ መስኮች በቅንጅት
እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከሥልጠና ባሻገር የሚንቀሳቀስባቸው ሌሎች ዘርፎች ይኖሩት ይሆን?

አቶ አብዱልፈታህ፡- የዛሬ አራት ዓመት ድርጅታችን ብሬክስሩ ሲቋቋም ይዞት ከተነሳው ዓላማ አንዱ የሰብዕና ማጎልበቻ
የሥልጠና ማዕከላትን ወደ ዩኒቨርሲቲ የማሳደግ ራዕይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እሱን ለማሳደግ እየተንቀሳቀስን ሲሆን፣
ሌላው በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች በቅርቡ ይፋ የምናደርገውና የምንቀላቀለው የትራንስፖርት ዘርፍ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በትምህርቱ ዘርፍ ሕፃናት ልጆችን እየቀረፅን የምናበቃበት ‹‹ፍቅር አስኳላ›› ከኬጂ የጀመርን ሲሆን፣
ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እየሰጠን በአገር አቀፍ ደረጃ የምናሰፋውና የምናሳድገው ይሆናል፡፡ በሪል ስቴት ግንባታም
ከውጭ ካምፓኒዎች ጋር የጀመርነው የሙከራ ሥራ አለ፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በዳውሮ ዞን በሆቴልና በሎጅ
ሥራ ለመሰማራት የምናደርገው እንቅስቃሴም ተጠቃሽ ነው፡፡

You might also like