You are on page 1of 6

ከአስቸኳይ የህክምና አገልግሎት በኋላ ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች የሚሰጥ

የህክምና አገልግሎትን በተመለከተ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣በጤና


ሚኒስቴር፣በፌዴራል ፖሊስ፣በህክምና ተቋማት፣በኢትዮጵያ
የምግብ፣የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና በመድን
ፈንድ አገልግሎት መካከል የተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ

ታህሳስ/2014

መግቢያ

1
በተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005 አንቀጽ 27 መሠረት የግልም ሆኑ የመንግስት
የሕክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች እስከ 2,000 /ሁለት ሺህ/ ብር ነፃ ህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ
በተደረገው ጥረት በአሁኑ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ከተቋማት ጋር በተደረገው ግምገማ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ነገር ግን ከአስቸኳይ ህክምና አገልግሎት በኋላ ተኝተውም ሆነ በተመላላሽ ህክምና በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት
የደረሰባቸው ተጎጂዎች ህክምናውን በራሳቸው ወጪ አገልግሎት አግኝተው ተመላሽ ብር(ተገቢ ካሳ) በኢንሹራንስ
ኩባንያዎች ወይም በመድን ፈንድ አገልግሎት እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር መጠየቅና ማግኘት እንደሚችሉ በአዋጅ
የተሰጣቸው መብት ቢሆንም በተጎጂዎች ግንዛቤ እጥረት እና ተቋማት ለዚህ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት
በተፈለገው መጠን ውጤታማ ነው ማለት አይቻልም፡፡
በሌላ መልኩ ተጎጂዎች የተሻለ ህክምና ከፍለው አገልግሎት ለማግኘት እና በኋላ ተመላሽ ለመጠየቅ አቅም
የሌላቸው ስለሚበዙና አዋጁም ሲወጣ ተሽከርካሪዎች የ 3 ኛ ወገን መድን ሽፋን እንዲገቡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት
በ 3 ኛ ወገን ላይ ለሚያደርሱት አደጋ ተገቢውንና ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ታሳቢ ተደርጎ የወጣ ስለሆነ
በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ በመንግስትም ሆኑ በግል የህክምና ተቋማት አስቸኳይ ህክምና አገልግሎት ካገኙ በኋላ እስከ
40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና
ማህበራዊ ችግር ለመፍታትና ይህንንም አሰራር አንድ ወጥ በሆነ መልኩ ወደ ክልሎች ለማውረድ በማስፈለጉ
በኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ በጤና ሚኒስቴር፣በፌዴራል ፖሊስ፣በህክምና ተቋማት፣በኢትዮጵያ የምግብ፣የመድሀኒትና
የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና በመድን ፈንድ አገልግሎት መካከል የጋራ ስምምነት ሰነድ ማዘጋጀት
አስፈልጓል፡፡

1 የስምምነቱ አላማ
ሁሉም የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ህክምና አገልግሎት በኋላ የተሻለ ህክምና ግልጋሎት እንዲያገኙ
ቁልፍ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውና በጋራ የሚፈጽሟቸው ስራዎች ላይ የተቀናጀ አሰራርና ቅልጥፍና
እንዲኖርማድረግ፡፡
የህክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ለሚሰጡት ሕክምና ተገቢውን ተመላሽ ብር እንዲያገኙ እና
የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎችን ለመርዳት በተነሳሽነት እንዲሰሩ በተቋማቱ መካከል የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር
በማድረግ አዋጁን በተገቢው መንገድ ተፈፃሚ እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡

2 የስምምነቱ አስፈላጊነት
1.የህክምና ተቋማት የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎችን እስከ 2,000 /ሁለት ሺህ/ ብር ድረስ በነፃ ካከሙ በኋላ ህክምናው
እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ በመነጋገር ለመቀጠል በተነሳሽነት እንዲሰሩ ወጪያቸውን የሚያስመልሱበትን
አሰራር መዘርጋት በማስፈለጉ፣
2.በስምምነቱ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን ለመፍጠር፣
3.አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ጉዳዮችን በመነጋገር እልባት እንዲያገኙ ለማስቻል ናቸው፡፡

3 የስምምነቱ አካላቶች
ኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ጤና ሚኒስቴር፣ፌዴራል ፖሊስ፣ህክምና ተቋማት፣የኢትዮጵያ የምግብ፣የመድኃኒትና የጤና
ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እና የመድን ፈንድ አገልግሎት ናቸው፡፡

4 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተግባርና ሀላፊነት

2
1.በደንበኞቻቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች በመንግስትም ሆነ በግል የህክምና ተቋማት እስከ ብር
2,000 /ሁለት ሺህ/ ድረስ ነፃ የአስቸኳይ ህክምና አገልግሎት ካገኙ በኋላ በመነጋገር የቀጠለውን የህክምና አገልግሎት
ወጪ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ ተመላሽ የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡
2.በደንበኞቻቸው ተሽከርካሪ የተጎዱ ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት ወጭ ከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር በታች ከሆነ
ቀሪውን የሞት እና የአካል ጉዳት ካሳ ውስጥ አካተው ለተጎጂው ወይም ለተጎጂው ቤተሰቦች የመካስ ግዴታ አለባቸው፡፡
3.በደንበኞቻቸው ተሽከርካሪ የተጎዱ ተጎጂዎች ከአንድ የህክምና ተቋም በላይ አገልግሎቱን ሊያገኙ ስለሚችሉ
የሚከፈለው (ተመላሽ) የሚደረገው ክፍያ የሁሉንም ተቋማት ወጪ በድምሩ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር መሸፈን
አለበት፡፡
4.ተጎጂው ህክምናውን ከጨረሰ ወይም ህይወቱ ካለፈ ደረሰኞች ከህክምና ተቋሙ ሲመጡለት በደረሰኞቹ መሰረት
የወጣውን ወጪ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ ተመላሽ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
5.የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂ በዱቤ ህክምና እያገኘ መሆኑን ተጎጂዉ ወይም ህክምና ተቋሙ ሲያሳውቀው በስሙ ፋይል
በመክፈት ለህክምና ተቋሙ ተመላሽ ለማድረግ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አለበት፡፡
6.በተራ ቁጥር 5 ላይ በተገለፀው መሠረት ለህክምና ተቋሙ የተጠየቀውን ክፍያ ሳይከፍል ለተጎጂው ወይም ለተጎጂ
ቤተሰብ ክፍያ መፈፀም የለበትም፡፡
7.ኢንሹራንስ ኩባንያው ለመንግስትም ሆነ ለግል ህክምና ተቋማት እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ ለሰጡት የዱቤ
ህክምና አገልግሎት ክፍያ ለመፈፀም ደረሰኞች እና ማስረጃዎች እንዲቀርቡለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡
8.የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ነፃ አስቸኳይ ህክምና አገልግሎት ካገኙ በኋላ ቀጣዩን እስከ አርባ ሺህ ብር ህክምና
ከኢንሹራንስ ካምፓኒዎች ወይም ከመድን ፈንድ አገልግሎት ጋር በመነጋገር መቀጠል እንደሚችሉ ለህብረተሰቡ
ግንዛቤ ይሰጣል፡፡
9.ለህክምና ተቋማት ተመላሽ ስለተደረጉ ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ የህክምና
ወጪዎች ሪፖርት በየወሩ ለመድን ፈንድ አገልግሎት ይልካል፡፡
10.ኢንሹራንስ ኩባንያው የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ
የህክምና ወጪ ከህክምና ተቋማት በሚቀርበው ደረሰኝ መሠረት ተመላሽ በኢንሹራንሱ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ
የሚከታተል ኃላፊ (focal person) በመመደብ ክትትል ያደርጋል ይህ ኃላፊም ኤጀንሲው በየወሩ በሚያዘጋጀው
ስብሰባ ላይ ሪፖርት ያቀርባል፡፡

5 የጤና ሚኒስቴር ተግባርና ኃላፊነት


1.ከአስቸኳይ ህክምና ውጪ ያለውን ህክምና የሚከታተል ሀላፊ (focal person) በመመደብ በየሆስፒታሉ አገልግሎቱ
በተገቢው መንገድ መሰጠቱን ይከታተላል፤ ችግር ሲኖር ማስተካከያ ይሰጣል እንዲሁም ይህ ሀላፊ (focal person)
የመድን ፈንድ አገልግሎት በየወሩ በሚያዘጋጀው ስብሰባ ላይ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
2.ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎዎች እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ ለተሰጠው የህክምና
አገልግሎቶች ሪፖርት በየወሩ ለመድን ፈንድ አገልግሎት ይልካል፡፡
3.የግልም ሆኑ የመንግስት የህክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ህክምና አገልግሎት በኋላ እስከ
40,000 /አርባ ሽህ/ ብር ድረስ ከመድን ፈንድ አገልግሎት እና ከሚመለከተው ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር በመነጋገር
የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጡ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ስራ ይሰራል፡፡
4.የግልም ሆነ የመንግስት ህክምና ተቋማት ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ ብር 40,000 ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች
ህክምና አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው እና የሰጡትን አገልግሎት ወጪ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ከመድን ፈንድ
አገልግሎት ገንዘቡን በህጋዊ ሰነድ ተመላሽ ማድረግ እንዳለባቸው ለህክምና ተቋማት ግንዛቤ እና መመሪያ ማውረድ
አለበት፡፡

3
5.የግልም ሆኑ የመንግስት የህክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ 40,000 /አርባ
ሽህ/ ብር ድረስ የህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና ሆስፒታሎቹ ለሰጡት አገልግሎት እና ላወጡት ወጪ በወቅቱ
ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና ከመድን ፈንድ አገልግሎት ተመላሽ እየተደረገላቸው መሆኑን ይከታተላል ችግር ካለም
ከተቋማት ጋር ሆኖ መፍትሄ እንዲያገኝ ይሰራል፡፡
6.መረጃ ያደራጃል እንዲሁም ያሳውቃል፡፡

6 የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተግባርና ኃላፊነት


1.የተሽከርካሪ አደጋ የደረሰበት ማንኛውም ሰው እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ህክምና አገልግሎት በመንግስትም ሆነ
በግል የህክምና ተቋማት እንዲያገኝ የተሽከርካሪ አደጋ መረጃ ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች የፖሊስ ሪፖርት አሰጣጥ
ስርአት በመዘርጋት በስሩ ባሉ መዋቅሮች ወደ ክልል እና ወደ ከተማ አስተዳደሮች ያወርዳል፡፡
2.የክልልና የከተማ አስተዳደር የፖሊስ ተቋማት ጉዳዩን አውቀውት ተገቢውን የአደጋ መረጃ ለተቋማት እንዲሰጡ
ግንዛቤ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
3.በመላው አገሪቱ ስለደረሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች ሪፖርት በየወሩ ለመድን ፈንድ አገልግሎት ይልካል፡፡
4.የተሽከርካሪ አደጋ መረጃ በትክክሉ ስለመሰጠቱ የሚከታተል ሙያተኛ (focal person)ይመድባል፡፡ ይህ ሙያተኛም
የመድን ፈንድ አገልግሎት በየወሩ በሚያዘጋጀው ስብሰባ ላይ በመላ አገሪቱ ስለተሰጡ የተሽከርካሪ አደጋ ሪፖርቶች
ሪፖርት ያቀርባል፡፡
5.በአዋጁ መሰረት ግዴታቸውን ያልተወጡ ተቋማትና ለተጎጂዎች ተገቢውን አገልግሎት ያልሰጡ ላይ በሚቀርበው
ጥቆማ መሰረት ምርመራ አጣርቶ ለህግ ያቀርባል፡፡

7 የህክምና ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት


1.የግልም ሆኑ የመንግስት የሕክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ለሰጡት የሕክምና አገልግሎትና ላወጡት
ወጪ ከመድን ፈንድ አገልግሎት እና ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሚያቀርቡት የሚከተሉት ህጋዊ ማስረጃዎች መሰረት
ወጪአቸውን ተመላሽ ማድረግ ይችላሉ፡-
1.1 ለአካል ጉዳት የሚቀርብ የወጪ ይመለስልኝ ጥያቄ ከሚከተሉት ደጋፊ ሰነዶች ጋር ተያይዞ መቅረብ አለበት፡-
ሀ.ህክምና መስጠት መጀመሩን ለሚመለከተው ኢንሹራንስ ወይም ለመድን ፈንድ አገልግሎት ማሳወቂያ ቅጽ መላክ
አለበት
ለ.ሐኪም መድኃኒት ያዘዘበት ማስረጃ
ሐ.መድኃኒት የተገዛበትና የሕክምና ወጪ ሕጋዊ ደረሰኝ
መ.የታካሚውን ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ
ሠ.የፖሊስ ሪፖርት
ረ.የወጪ መጠየቂያው ተጠቃሎ በህክምና አስተዳደሩ ተፈርሞ መላክ ይኖርበታል፡፡
1.2 ተጎጂዉ ህክምናዉን እየወሰደ እያለ ህይወቱ ካለፈ፡-
ሀ.ከላይ በቁጥር 1.1 ላይ ለአካል ጉዳት ለሚቀርብ የወጪ ይመለስልኝ ጥያቄ መቅረብ ካለባቸው ደጋፊ ሰነዶች
በተጨማሪ የሟቹን አሟሟት ሁኔታ የሚገልጽ የአስክሬን ምርመራ የሐኪም ማስረጃ መቅረብ
ይኖርበታል፣ማቹ የሞተበት የህክምና ተቋም የአስክሬን ምርመራ ከሌለ እና ወደ ሌላ የአስክሬን ምርመራ
ወደሚገኝበት የህክምና ተቋም አስክሬኑ እንዲመረመር ከተላከ የተላከበት ደብዳቤም አብሮ መያያዝ
ይኖርበታል፡፡

4
2. በተሽከርካሪ አደጋ የተጎዳን ሰው አስቸኳይ ህክምና አገልግሎት ከጨረሰ በኋላ በተመላላሽነትም ሆነ አስተኝተው
ተጎጂዉን እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ በተገቢው መንገድ የማከም ግዴታ አለባቸው፡፡
3. በተቋማቸው የሰጡት ሕክምና በቂ ካልሆነ ወደ ተሻለ ህክምና ተቋም በእነርሱ የተጠቀመውን የብር መጠን በመግለጽ
ሪፈር ማድረግ አለባቸው፡፡ሪፈር ያደረጉበትም ደብዳቤ ወደ ሚመለከተው ኢንሹራንስ ተቋም ወይም ወደ መድን
ፈንድ መላክ ይኖርበታል፡፡
4. ማንኛውም የሕክምና ተቋም ለሚሰጠው የተመላላሽነትም ሆነ ተኝቶ የመታከም አገልግሎት እንደጀመረ ለመድን
ፈንድ አገልግሎት ወይም ለሚመለከተው ኢንሹራንስ ኩባንያ በወቅቱ ሪፖርት ማድረግ አለበት፡፡
5.የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ህክምና ጉዳይ የሚከታተልና መረጃ ከተቋማት ጋር የሚለዋወጥ ባለሙያ (focal person)
የመመደብ ግዴታ አለባቸው፡፡
6. በየደረጃው ያሉ የህክምና ተቋማት አመራሮች፣ ሙያተኞችና ሰራተኞች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ እና ህክምና
እንዲሰጡ ማድረግ አለባቸው፡፡
7.በየደረጃው ያሉ የህክምና ተቋማት ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ ለተሽከርካሪ አደጋ
ተጎጂዎች መስጠትን በተመለከተ በየወሩ ሪፖርት ለመድን ፈንድ አገልግሎት መላክ እንዲሁም መስሪያ ቤቱ በየወሩ
በሚያካሂደው ስብሰባ ላይ መሳተፍም ይኖርባቸዋል፡፡

8 የኢትዮጵያ የምግብ፣የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን


ተግባርና ኃላፊነት
1. የግል የህክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ህክምናውን
መስጠት እንዳለባቸው ለግል ህክምና ተቋማት እና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ይኖርበታል፡፡
2.በየወሩ የግል የህክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር
ድረስ ስለሰጡት የህክምና አገልግሎት ሪፖርት እንዲልኩ ያደርጋል ችግሮችን በመለየት እንዲፈቱ ያደርጋል፡፡
3.የግል የህክምና ተቋማት ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ከአስቸኳይ ህክምና በኋላ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ
ህክምና እየሰጡ መሆኑን የሚከታተል ባለሙያ (focal person) ይመድባል፡፡ባለሙያውም በየወሩ በሚያዘጋጀው
ሪፖርት መገምገሚያ መድረክ ላይ ይሳተፋል፡፡
4.በስምምነቱ የተቀመጡ መብትና ግዴታዎች በግል ህክምና ተቋማት መፈፀማቸውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፡፡

9 የመድን ፈንድ አገልግሎት ተግባርና ኃላፊነት


1.ባልታወቀ ተሽከርካሪ ለተጎዱ ተጎጂዎች የመንግስትም ሆኑ የግል ሕክምና ተቋማት ለሰጡት አገልግሎት እና ላወጡት
ሙሉ ወጪ እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ ተመላሽ ማድረግ አለበት፡፡
2.የ 3 ኛ ወገን መድን ሳይኖራቸው ወይም ሳያድሱ ጊዜ ያለፈባቸው ተሽከርካሪዎች ባደረሱት ጉዳት ተጎጂዎች
በመንግስትም ሆነ በግል የሕክምና ተቋማት ላገኙት የሕክምና አገልግሎት እስከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር ድረስ
ለህክምና ተቋሙ ተመላሽ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
3.ጉዳት የደረሰበት ተጎጂ የሕክምና አገልግሎት ወጪ ከ 40,000 /አርባ ሺህ/ ብር በታች ከሆነ የቀረውን ወጪ
እንደደረሰበት የጉዳት መጠን እና ሌሎች ለአካል ጉዳትና ለሞት ተጎጂዎች በሚሰላበት መሰረት ለተጎጂዎች ወይም
ለቤተሰቦቻቸው ቀሪውን የመካስ ግዴታ አለበት፡፡
4.ባልታወቀም ሆነ 3 ኛ ወገን በሌለው ተሽከርካሪ የተገጩ ተጎጂዎች በመንግስትም ሆነ በግል ሕክምና ተቋማት
የሚደረገው ሕክምና በአግባቡ መሰጠቱን ሙያተኞች (focal person) በመመደብ ቅርብ ክትትል ማድረግ አለበት፡፡
5.ከባለድርሻ አካላቶቹ ጋር በመሆን አፈፃፀሙን በየወሩ ሪፖርት ቀርቦ እንዲገመገም ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡

5
6.ስለ አገልግሎቱ ለህብረተሰቡ እና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ይሰጣል፡፡

10 የስምምነቱ አካላት የጋራ ኃላፊነት


1.ባለድርሻ አካላት ከአስቸኳይ ህክምና አገልግሎት በኋላ ለሚሰጥ ህክምና ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር::
2.ሁሉም በዚህ ስምምነት ላይ የተጠቀሱ ባለድርሻ አካላት በሰነዱ የተጠቀሱ ተግባራትና ሀላፊነቶችን ለመወጣት
የሚያስችል ግልጽ አቅጣጫና አሠራር በማስቀመጥ ይህ አሠራር እንዲጠናከር ማድረግ፡፡
3.ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር በአፈፃፀም ለሚፈጠሩ ችግሮች ልዩ ትኩረት በመስጠት
ችግሮችን በጋራ የመፍታት ሀላፊነት አለባቸው፡፡
4.በየወሩ በመሰብሰብ ስለ አገልግሎቱ በጋራ ግምገማ ያካሂዳሉ፡፡
5.በጋራ ስለአገልግሎቱ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ይሰጣሉ፡፡

11 የስምምነት ሰነዱ ስለሚሻሻልበት ሁኔታ


በዚህ የመግባቢያ ሰነድ መሰረት የተገባ ስምምነት ማስተካከያዎች ወይንም ማሻሻያዎች ወይንም ተጨማሪ ጉዳዮች
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ሊስተካከል ይችላል፡፡

12 ስምምነቱ የሚፀናበት ጊዜ
በዚህ መግባቢያ ሰነድ የተገባ ስምምነት በሚመለከታቸው አካላቶች ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

13 የስምምነቱ አካላት ስም እና ፊርማ


1. ስለ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የማህበሩ ሰብሳቢ----ስም……………………ፊርማ……………………
2.ስለ ጤና ሚኒስቴር------------------------------------ስም…………………….ፊርማ……………………..
3.ስለ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን-------------------------ስም……………………ፊርማ………………………
4.ስለ ህክምና ተቋማት----------------------------------ስም………………………ፊርማ…………………
5.ስለ የኢትዮጵያ የምግብ፣የመድኃኒትና
የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን----ስም……………………….ፊርማ……………………
6.ስለ መድን ፈንድ አገልግሎት------------------------ስም……………………….ፊርማ…………………...

You might also like