You are on page 1of 28

የጤና አገልግሎት አዋጅ

(ረቂቅ)
ህዳር 22 2010

0
መግቢያ
አዋጅ ቁጥር…. /2010
ስለ ጤና አገልግሎት የወጣ አዋጅ

ሀገር አቀፍ የጤና ክብካቤ አስተዳደር ስርዓት አወቃቀር ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እና ይህንን
አሰራር በአዲስ መልክ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ፤

ደረጃውን ባልጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲሁም ብቃትና ሙያዊ ሥነ-ምግባር በጎደለው የጤና ባለሙያ የቁጥጥር ጉድለት
ምክንያት በህብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር መከላከል እና መቆጣጣር በማስፈለጉ፤

ወጥነት ያለው የጤና ባለሙያዎች አስተዳደር ስርዓት በመተግበር የጤና አገልግሎትን ጥራት እና ተደራሽነት ለማሳደግ
እንዲሁም የጤና ሙያን የሚያጎለብት አሰራር መዘርጋት በማስፈለጉ፤

የታካሚን ወይም የጤና አገልግሎት ተጠቃሚን መብት ማእከል ያደረገ እና በጤና ተቋማት ተግባራዊ መደረግ የሚገባቸው
ዝቅተኛ ብሄራዊ መመዘኛዎችን እንዲሁም ሀገር አቀፍ የጤና አጠባበቅ ስርአቱን የሚደግፉ ተጓዳኝ የጤና ክብካቤ ጉዳዮችን
በህግ መደንገግ በማስፈለጉ፤

በሀይጅንና አካባቢ ጤና አጠባበቅ ጉድለት እና በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት በህብረተሰብ ጤና ላይ የሚደርስን ጉዳት
አንዲሁም ተያያዥ የሆኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የጎንዮሽ ጉዳቶች መከላከል እና መቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 55(1) መሰረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ
ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ “የጤና አገልግሎት አዋጅ ቁጥር------/2010” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ
1
የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፡-

1) “የጤና አገልግሎት” ማለት በህግ በተፈቀደለት የጤና ተቋም እና የጤና ባለሙያ የስራ ወሰን መሰረት የሚሰጥ
የጤና ማበልጽግ፣ የበሽታ መከላከል፣ ማከም እና መልሶ ማቋቋም አገልግሎት ነው፤
2) “የጤና አገልግሎት ተቋም” ማለት የጤና ማበልጸግ፣ የበሽታ መከላከል፣ ማከምና መልሶ ማቋቋም ሥራን የሚያከናውን
ማንኛውም የመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆነ ወይም የግል ተቋም ሲሆን የአምቡላንስና በቴሌኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ
አማካኝነት እና መሰል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጤና አገልግሎትን የሚሰጥ ተቋምን ያካትታል፤
3) “የሙያ ፈቃድ” ማለት የጤና አገልግሎት ወይም ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችን ለሚሰጥ የጤና ባለሙያ የሚሰጥ
የምስክር ወረቀት ነው፤
4) “የጤና ባለሙያ” ማለት የጤና አገልግሎት ለመስጠት ወይም የሰውን ጤና ለመጠበቅ አግባብ ባለው የጤና
ባለሙያ ተቆጣጣሪ አካል እንደ ጤና ባለሙያ የተመዘገበ ሰው ነው፤
5) ”የጤና ሙያ ደረጃ” ማለት የጤና ዘርፉን ፍላጎት ለማሳካት የሚችል ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት
የሚዘጋጅ የጤና ሙያ ወሰንና ዝርዝር ተግባር ነው፤
6) “የጤና ሙያ ሥርዓተ-ትምህርት” ማለት በሙያ ደረጃ ወይም የሥራ ወሰን ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ
የትምህርት ፕሮግራም ነው፤
7) “የክልኒካል ጤና ሙያ ትምህርት“ ማለት በቀጥታ ከህሙማን ጋር ግንኙነት በማድረግ የሚሰጡ የስልጠና
መስኮች ናቸው፤
8) “የጤና ባለሙያ የብቃት ምዘና” ማለት ከህሙማን ወይም ከጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጋር በቀጥታ
ተገናኝተው የጤና አገልግሎት ለሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጥ ቅድመ-ሥራ ፈተና ነው፤
9) “የጤና ባለሙያ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት” ማለት ቅድመ-ሥራ የብቃት ምዘና ፈተና ላለፉ
የጤና ባለሙያዎች የሚሰጥ ማረጋገጫ ነው፤
10) “የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ስልጠና”ማለት አንድ ባለሙያ በሥራው ላይ እያለ ሙያውን ሊያጎልብትና
ብቃቱን ሊጨምር የሚችል ከስራው ጋር ተያያዥነት ያለው ስልጠና ነው፤
11) “የጤና ሙያ ስነ-ምግባር” ማለት አንድ የጤና ባለሙያ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በሚወጣበት ጊዜ
ሊከተለው የሚገባ ሙያው የሚመራበት የሥነ-ምግባር መርህ ነው፤
12) “የሙያ ምዝገባ ፈቃድ ምስክር ወረቀት” ማለት የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ወይም ሌሎች ተዛማጅ
አገልግሎቶችን ለመስጠት እንዲችል ለጤና ባለሙያ የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡
13) “የማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ” ማለት መገናኛ ብዙሃንን፣ የውጭ ማስታወቂያን፣ የቴሌኮምን፣ የፖስታ፣
የኢንተርኔት ድረ ገፅ እና የፋክስ አገልግሎትን፣ ሲኒማን፣ ፊልምን፣ ቪዲዮን ወይም መሰል የማስታወቂያ ማሰራጫ
መንገድን ያጠቃልላል፤

2
14) “ጤና ነክ ቁጥጥር የሚደረግበት ተቋም” ማለት ማንኛውም የኅብረተሰብ መገልገያ ተቋም ሲሆን የትምህርት ተቋም፣
ማረሚያ ቤት፣ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል፣ የህጻናት ማቆያ፣ መዋዕለ ህፃናት፣ የህጻናት ማሳዳጊያ፣ የገበያ
ቦታ፣ የስፖርት ቦታ፣ የንግድ መኝታ ቤት፣ የመታሻ ማዕከል፣ የመዝናኛ ማዕከል፣ የህዝብ ማጓጓዣ፣ የጸጉር ቤትና
የውበት ሳሎንና ተቆጣጣሪ አካሉ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል የሚላቸውንም ይጨምራል፤
15) “ቆሻሻ” ማለት ከኢንዱስትሪዎች፣ ከእርሻ ቦታዎች፣ ከትምህርት ቤቶች፣ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከንግድ ስፍራዎች፣ ከጤናና
ጤና ነክ ተቋማት፣ ከመጸዳጃ ቤት ወይም ከሌሎች መሰል ተቋሞች የሚወጣና በሰው ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርስ
የሚችል ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማለት ነው፤

16) “የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ጉድለት” ማለት ሰው በሚኖርበት አካባቢ የሚገኝበአካላዊ እድገት፣ በጤና ወይም በአኗኗር
ዘይቤ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል የሚችል ማንኛውም ለጤና አስጊ የሆነ ነገር ነው፤
17) “ሥራ ነክ ጤና አጠባበቅ” ማለት በሥራ አካባቢ የሚከሰቱ ወይም ከሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸው
ኬሚካላዊ፣ፊዚካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ጎጂ ንጥረ ነገሮች በመከላከልና በመቆጣጠር ሠራተኞች ለአደጋ እንዳይጋለጡ
በማድረግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አስተዳደራዊ ዘዴዎችን በመጠቀም የሠራተኞችን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስችል
አሰራር ማለት ነው፤
18) “ለይቶ ማቆየት” ማለት ለድንገተኛ ተላላፊ በሽታ ተጋልጠዋል ወይም በበሽታው ተይዘዋል ተብለው የሚጠረጠሩ
ሰዎች፣ ዕቃዎች ወይም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ነገሮች ላይ ተላላፊ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን
አለመኖራቸው እስኪረጋገጥ ድረስ ለብቻቸው ተገልለው እንዲቆዩ የማድረግ አሰራር ነው፤
19) “ኢንስፔክተር” ማለት የዚህ አዋጅ አስፈጻሚ አካላት የየራሳቸውን ስልጣን እና ተግባራት
ለማስፈጸም የሚመድቡት ባለሙያ ነው፤
20) “አስፈጻሚ አካል” ማለት በዚህ አዋጅ መሰረት የተሰጡ ተግባራትን ለማከናወን ሀላፊነት የተሰጣቸው አካላት
ሲሆኑ እንደአግባቡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን፣ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ወይም
የክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካልን የሚወክል ነው፤
21) “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት አንቀጽ 47
የተመለከተው ማንኛውም ክልል ሲሆን የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን
ይጨምራል፤
22) “አግባብ ያለው አካል” ማለት እንደ አግባቡ በዚህ አዋጅ ላይ የተጠቀሱ ተግባራት
በሚከናወኑበት ጊዜ ድርሻ ያላቸውና በህግ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ናቸው፤
23) “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤
24) ማንኛውም በወንድ ጾታ የተገለጸ አገላለጽ ሴትንም ይጨምራል፡፡

3
3. የተፈፃሚነት ወሰን

1) ይህ አዋጅ የጤና እና የጤና ነክ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ተቋማት፤ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም በሀይጅን፣ አካባቢ
ጤና አጠባበቅ እና ተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥርን በሚመለከት በመላው ሀገሪቱ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
2) የዚህ አንቀጽ ንዑስ-ቁጥር (1) እንደተጠበቀ ሆኖ፤
ሀ) በመግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚካሄድ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር እና ለይቶ
የማቆየት ተግባር፤
ለ) ውጭ ሀገር ተምረው የሚመጡ ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎችን የመጀመሪያ ምዝገባና ፈቃድ፤
ሐ) የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው የጤና ባለሙያዎች ምዝገባና ፈቃድ በፌደራል ደረጃ የሚከናወን
ይሆናል፡፡
3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 2 (ለ) የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ቀጣይ የፈቃድ ማደስ ተግባራት በክልሎች
የሚከናወን ይሆናል፡፡
4) በዚህ አንቀጽ ንዑስ-ቁጥር (2) መሰረት በፌደራል መንግስት ደረጃ ተፈጻሚ ከሚሆኑ ተግባራት ውጭ
ያሉት የቁጥጥር ስራዎች በክልል መንግስት ተቆጣጣሪ አካላት የሚፈጸሙ ይሆናሉ፡፡

ክፍል ሁለት

የጤና አገልግሎት እና የጤና ባለሙያ አስተዳደር


ንዑስ-ክፍል አንድ
የጤና አገልግሎት አስተዳደር

4. ጠቅላላ

1) ማንኛውም የጤና ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ተፈጻሚነት ያለውን የጥራትና ደህንነት መስፈርቶች ያሟላ መሆን
አለበት፤
2) ማንኛውም የጤና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ለህብረተሰቡ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነቱ
የተጠበቀ መሆኑን የማረጋገጥ ሀላፊነት አለበት፤
3) ማንኛውም የጤና ተቋም እና የጤና ባለሙያ ምዝገባ፤ ፈቃድ እና ቁጥጥር ተቋሙ ወይም ባለሙያው በሚገኝበት
የክልል ተቆጣጣሪ አካል ይሆናል፤
4) ማንኛውም የጤና ተቋም በስሩ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ የጤና ባለሙያ የተመዘገበ እና የታደሰ የሙያ ፈቃድ
ያለው መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፤

4
5) ማንኛውም የጤና አገልግሎት ተቋም የአካባቢ ጤና አጠባበቁ የተጠበቀ፣ ከተለያዩ የበሽታ አምጪ ተህዋሲያንና
ሌሎች በካይ ነገሮች፤ የታካሚዎች፣ ሰራተኞች፣ አስታማሚዎችንና በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ደህንነት ከሚያጓድሉ
ሁኔታዎች የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡
6) የጤና አገልግሎት ተቋም የህንፃ ዲዛይን፣ አሰራር እና የቦታ አቀማመጥ በጤና ተቋሙ የሚሰጥ አገልግሎትን
ደህንነቱ በተሟላ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችል እንዲሁም የታካሚን ደህንነት ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡
7) ማንኛውም የጤና አገልግሎት ተቋም ፈቃድ ለሚያገኝበት የጤና አገልግሎት ተፈጻሚ መስፈርቶችን የሚያሟላ
የህክምና መሳሪያ ሊኖረው ይገባል፡፡
8) ማንኛውም በቴሌኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ አማካኝነት ወይም መሰል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚሰጥ የጤና
አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ የተሰጠው የጤና ተቋም እና የጤና ባለሙያ አገልግሎቱ ተፈጻሚነት ያለውን ደረጃ
ወይም መስፈርት ማሟላቱን የማረጋገጥ ሀላፊነት አለበት፡፡

5. የጤና ተቋም ምዝገባና ፈቃድ

1) ማንኛውም የጤና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም በክልል የጤና ተቆጣጣሪ የተመዘገበና ፈቃድ ያለው መሆን አለበት፤
2) የጤና ተቋም ምዝገባ ፈቃድ የክልል የጤና ተቆጣጣሪ በሚያወጣው የጊዜ ገደብ መሰረት በወቅቱ መታደስ
አለበት፤
3) ማንኛውም የጤና ተቋም ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት ያለበት አስገዳጅ ሀገራዊ ደረጃና የፍቃድ አሰጣጥ ሂደት ይህን
አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ ሌላ ህግ ይወሰናል፡፡

5
6. የጤና አገልግሎት ተቋም ደረጃ

1) ማንኛውም የጤና ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ተፈጻሚነት ያለውን አስገዳጅ ሀገራዊ ደረጃ ያሟላ እና ፈቃድ
ባወጣበት የጤና አገልግሎት ዓይነትና ደረጃ መሰረት መሆን አለበት፡፡
2) የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ደረጃ እንዲሁም የጤና ተቋማት ደረጃ አመዳደብና አሰራር አግባብ ያለው አካል
በሚያወጣው አስገዳጅ ሀገራዊ ደረጃ መሰረት ይወሰናል፡፡

7. የውስጥ ጥራት ቁጥጥር ስርዓት ስለመዘርጋት

ማንኛውም የጤና ተቋም የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የውስጥ የጥራት ቁጥጥር ስርዓት
የመዘርጋት ሀላፊነት አለበት፡፡

8. ስለ ታካሚዎች መብት

1) ማንኛውም የጤና ተቋም የታካሚን ወይም የተገልጋይን ክብርና መብት በጠበቀ መልኩ አገልግሎት መስጠት
አለበት፡፡
2) ማንኛውም የጤና ተቋም እና የጤና ባለሙያ ተፈጻሚነት ያለውን የታካሚ ወይም የተገልጋይን መሰረታዊ መብትና
ግዴታ ለታካሚ በሚታይ ሁኔታ በጤና ተቋሙ የመለጠፍ፤ የማሳወቅና መፈፀሙን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፡፡
3) ማንኛውም የጤና ባለሙያ የታካሚውን የበሽታ ምንነት፣ የህክምና ሂደት፣ አማራጭ እና የሚገኘውን ውጤት
የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡
4) በማንኛውም ሁኔታ በህሙማን ወይም ቤተሰብ ጥያቄ ወይም በህክምና ባለሙያ ምክር ወይም እርዳታ ህይወት
የማቋረጥ ተግባር የተከለከለ ነው፤
5) የዚህ አንቀጽ ዝርዝር አፈጻጸም በሌላ ህግ ይወሰናል፡፡

9. የጤና አጠባበቅ ትምህርት እና ምክር አገልግሎት

ማንኛውም የጤና ተቋምና በተቋሙ የሚሰራ የጤና ባለሙያ የህክምና ደረጃውን እና የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት
መሰረት በማድረግ ስለሚሰጠው አገልግሎትና የጤና አጠባበቅ ትምህርት አግባብነት ያለውን ወቅታዊ መረጃ እና
የምክር አገልግሎት ለተገልጋዩ የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡

10. የታካሚን ሙሉ ፈቃድ ስለማግኘት

6
1) ማንኛውም የጤና ተቋም ወይም የጤና ባለሙያ የታካሚን ወይም እንደሁኔታው የአሳዳጊ ወይም ሌላ ህጋዊ ወኪል
በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ፈቃድ ሳያገኝ የህክምና አገልግሎት መስጠት የለበትም፡፡
2) የዚህ አንቀፅ ንዑስ-አንቀፅ (1) እንደተጠበቀ ሆኖ የተገልጋዩ ሙሉ ፈቃድ ሳይገኝ የጤና ክብካቤን መስጠት
የሚቻለው፡-
ሀ) ተገልጋዩ ሙሉ ፈቃድ መስጠት የማይችል ሲሆን እና ፈቃዱ በተገልጋዩ ወላጆች ፣ አሳዳጊ፣ የትዳር ጓደኛ፣
ልጆች፣ ወንድም፣ እህት ወይም ህጋዊ ወኪል ሲሰጥ፤
ለ) ለተገልጋዩ የጤና ክብካቤ አለመስጠት የህብረተሰብ ጤና አደጋ የሚያስከትል ሆኖ ሲገኝ፤ ወይም
ሐ) ተገልጋዩ በግልጽ ወይም በማንኛውም መልኩ የጤና ክብካቤውን እንደማይፈልግ ካላሳወቀና የጤና ክብካቤውን
ማዘግየት በተገልጋዩ ጤንነት ወይም አካል ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን ነው፡፡
3) ማንኛውም የጤና ተቋም ወይም የጤና ባለሙያ የተገልጋዩን ሙሉ ፈቃድ ለማግኘት ታካሚው ካገልግሎቱ ሊያገኝ
የሚችለው ጥቅምና አገልግሎት ባለማግኘቱ ሊያጋጥመው የሚችለውን ጉዳቱን እና የህክምና አማራጭ ማሳወቅ
አለበት፡፡
4) የዚህ አንቀጽ ዝርዝር አፈጻጸም በሌላ ህግ ይወሰናል፡፡

11. የአምቡላንስ ጤና አገልግሎት

1) ማንኛውም ከጤና ተቋም ውጪ የአምቡላንስ ጤና አገልግሎት መስጠት የሚፈልግ ሰው አግባብ ካለው አስፈጻሚ
አካል ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡
2) ማንኛውም የአምቡላንስ ጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋም አምቡላንሱ በደረጃው መሰረት ለመጀመሪያ ሕክምና
እርዳታ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የጤና ባለሙያ፤ መድኃኒት እና የህክምና መሳሪያ ሊኖረው ይገባል፡፡
3) ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም “የአምቡላንስ ጤና አግልግሎት” ማለት የድንተኛ ህክምና ወይም በቅብብሎሽ ሂደት
ወይም ተጨማሪ የሕክምና አግልግሎት የሚፈልግ ሰው የመጀመሪያ ወይም ጊዜያዊ የሕክምና እርዳታ አገልግሎት
መስጠት እንዲችል ተብሎ በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀና ለዚሁ አግልግሎት በሚውሉ አስፈላጊ የሰውና የቁሳቁስ
ግብአቶች የተሟሉለት የየብስ፣ የአየር ወይም የውሃ ተንቀሳቃሽ መጓጓዣ ነው፡፡
4) ማንኛውም አምቡላንስ ማሟላት ያለበት መስፈርት ይህንን አዋጅ መሰረት በማድረግ በሚወጣ ሌላ ህግ
ይወሰናል፡፡

12. ድንገተኛ ህክምና

1) ማንኛውም የጤና ተቋም በጤና ተቋሙ ደረጃ መሰረት ሊሰጥ የሚችል የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ያለ ቅድመ
ሁኔታ የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡

7
2) የድንገተኛ ህክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ታካሚ ወደ ጤና ተቋም ሲመጣ እና ታካሚው ወደ ሌላ ከፍተኛ
የጤና ተቋም የህክምና የቅብብሎሽ ስርአቱን በመከተል መላክ ካለበት ተቋሙ ታካሚውን ከመላኩ በፊት እንደ
አግባቡ የታካሚውን የጤና ሁኔታ እንዳይባባስ የመቆጣጠር ስራ መስራት አለበት፡፡
3) ታካሚው ከገባበት የጤና ተቋም ደረጃ በላይ የሆነ የጤና እክል የገጠመው እንደሆነ ወደ ሌላ ከፍተኛ የጤና
ተቋም የቅብብሎሽ ስርአቱን በመከተል መላክ እንዳለበት ያመነ ማንኛውም የጤና ባለሙያ ታካሚዉን ሲልክ
ይህንኑ ምክንያት ከታካሚው መላኪያ ቅጽ ላይ ማስፈር አለበት፡፡
4) የድንገተኛ ህክምና እርዳታ አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመሆን አደጋና ወረርሽኝ በተከሰተበት ቦታ ሁሉ ሊሰጥ
ይችላል፡፡
5) ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም “የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት” ማለት አጣዳፊ እና ህይወትን ወይም አካልን አደጋ ላይ
የሚጥል ወይም ዘላቂ የጤና ችግር የሚያመጣ በሸታ ወይም ጉዳት ላጋጠመው ሕመምተኛ በጤና ተቋማትና
በአምቡላንስ ውስጥ በጤና ባለሙያ የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ነው፡፡

8
13. የህሙማን ምርመራ፣ ሕክምና እና ክትትል

1) ማንኛውም የጤና ተቋም የተገልጋይን የጤና ችግር ወይም ህመም ተገቢውን የህክምና ምርመራ ስርአት በመከተል
መለየት፣ ደረጃው በሚፈቅደው መሰረት የማከምና ክትትል የማድረግ ሀላፊነት አለበት፡፡
2) ማንኛውም የጤና ተቋምና በተቋሙ ውሰጥ የሚሰራ የጤና ባለሙያ በግድየለሽነት ወይም የማይገባ ጥቅም
ለማግኘት ሲባል አላስፈላጊ የህክምና ምርመራ ማዘዝ ወይም መጠቀምን የሚከለክል አሰራር የመዘርጋት እና
የመተግበር ግዴታ አለበት፡፡
3) ማንኛውም የህክምና አገልግሎት ተፈጻሚነት ባለው የአገልግሎት ደረጃ መሰረት እና የክልል የጤና ተቆጣጣሪ
ፈቃድ ሲሰጥ ከጤና ተቋም በተጨማሪ በሌሎች መሰል ቦታዎች ሊሰጥ ይችላል፡፡

14. የታካሚ ቅብብሎሽ ስርአት

1) ማንኛውም የጤና ተቋም አግባብ ባለው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ መሰረት የሚጠበቅበትን የድንገተኛና መደበኛ
ጤና አገልግሎት ለታካሚዎች የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡
2) ማንኛውም የጤና ተቋም እና የጤና ባለሙያ በደረጃው መሠረት ተገቢውን የድንገተኛ እና መደበኛ ሕክምና
አገልግሎት ለታካሚው መስጠት ያልቻለ እንደሆነ ተፈላጊውን አገልግሎት ሊያገኝ ወደሚችልበት አግባብ ያለው
የጤና ተቋም የቅብብሎሽ ስርአቱን በመከተል ከተሟላ መረጃ ጋር ወዲያውኑ ማስተላለፍ አለበት፡፡
3) ማንኛውም የጤና ተቋም ለድንገተኛ ህክምና ታካሚውን ወደ ሌላ የጤና ተቋም ከመላኩ በፊት ተቀባዩ የጤና
ተቋም ታካሚውን መቀበል ስለመቻሉ የማረጋገጥ ሀላፊነት አለበት፡፡
4) ማንኛውም የጤና ተቋም የህክምና የቅብብሎሽ ስርአቱን ተከትሎ የመጣለትን ታካሚ የመቀበልና ስለታካሚው
ሁኔታ ለላኪው የጤና ተቋም ግብረ መልስ የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡

9
15. የህክምና ምስክር ወረቀት ስለመስጠት

1) ማንኛውም የጤና ተቋም ታካሚው ወይም ሌላ አግባብ ያለው አካል ታካሚው በጤና ተቋሙ ውስጥ ስለተሰጠው
አገልግሎትና ተያያዥ የሆኑ ህጋዊ መረጃዎች ሲጠየቅ የህክምና ምስክር ወረቀት የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡
2) ማንኛውም የጤና ተቋም በስሩ ህክምና ሲከታተሉ የነበሩ ታካሚዎችን የህክምና ሂደት፣ የጤና መረጃዎች እና
የህክምና ምስክር ወረቀት በሚስጥር መጠበቅ አለበት፡፡
3) የዚህ አንቀፅ ንዑስ-አንቀፅ (2) አገላለጽ እንደተጠበቀ ሆኖ የምስክር ወረቀቱ የታካሚውን ሙሉ ስም፣ የህክምና
ሪከርድ ወይም ካርድ ቁጥር፣ እድሜና አድራሻ፣ የምርመራውን ውጤትና ለታካሚው የተደረግለትን ህክምናና
እንደሁኔታው የተሰጠውን እረፍትና የቦርድ ውሳኔ፣ የህክምና ማስረጃ የተሰጠበት ቀን፣ የምስክር ወረቀቱን የሰጠው
ባለሙያ ሙሉ ስም ፊርማ እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች መያዝ አለበት፡፡
4) በዚህ አንቀጽ መሰረት የሚሰጥ የህክምና የምስክር ወረቀት በሪከርድ ክፍል በተያዘ የጤና መረጃ የተደገፈ እና
ትክክለኛ ስለመሆኑ የማረጋገጥ ሀላፊነት እንደ አግባቡ የምስክር ወረቀቱን የሰጠው ጤና ባለሙያው ወይም የጤና
ተቋሙ ይሆናል፡፡
5) ማንኛውም አካል ህጋዊ የሆኑ ጤና ተቋማት የሚሰጡትን የምስክር ወረቀት የመቀበል ሀላፊነት አለበት፡፡
6) ማንኛውም የጤና ተቋም ወይም ጤና ባለሙያ ለሚሰጠው የህክምና ምስክር ወረቀት የህግ ሀላፊነት ይወስዳል፡፡

16. የህልፈተ ህይወት ምርመራ

1) የህልፈተ ህይወት መንስኤ ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ አግባብ ባለው የጤና ተቋም መከናወን አለበት፡፡
2) የአስከሬን ወይም መሞቱ በባለሙያ የተረጋገጠ የሟቹ የአካል ክፍል ምርመራ የሚከናወነው የሟች የትዳር ጓዳኛ፣
ለአካለ መጠን የደረሰ ልጅ፣ ወላጅ፣ ሞግዚት፣ አሳዲጊው፣ የህግ አስከባሪ አካል ወይም ሌላ አግባብነት ያለው
ሰው የሞቱን ምክንያት ለማወቅ ሲጠይቅ ይሆናል፡፡
3) የዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀፅ (2) ድንጋጌ ቢኖርም ሟቹ በህይወቱ እያለ ፈቃዱን በጽሁፍ ከሰጠ ወይም ሟች
በህይወት ዘመኑ ክልከላ ካላደረገ እና የሟቹ ቤተሰብ ፈቃድ ከተገኘ የትምህርት ወይም የምርምር ተቋም በሟች
አስከሬን ላይ ምርመራ ማድረግ ይቻላል፡፡
4) የዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (3) ቢኖርም ለህብረተሰብ ደህንነትና ጤንነት አደጋ የሚሆን አዲስ የተከሰተ በሽታ
ምንነት፣ መንስኤ ወይም ህክምና እና መከላከያ ለማወቅ የሚረዳ ሆኖ ሲገኝ አግባብ ያለው አስፈጻሚው አካል
በልዩ ሁኔታ በአስክሬኑ ላይ የምርምር ስራ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል፡፡
5) ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም “ህልፈተ ህይወት” ማለት ብቃት ባለው የጤና ባለሙያ የሰው የአንጎል፣ የልብና የመተንፈሻ
አካላት የአሰራር ስርአትን መሰረት ባደረገ ምርመራ በህይወት እንደሚገኝ ምንም አይነት ምልክቶች
እንደማይታይበት ሲረጋገጥ ነው፡፡
6) የዚህ አንቀጽ ዝርዝር አፈጻጸም በሌላ ህግ ይወሰናል፡፡

10
17. በህክምና ቴክኖሎጂ የታገዘ የተዋልዶ አገልግሎት

1) በህክምና ቴክኖሎጂ የታገዘ የተዋልዶ አገልግሎት መስጠት የሚቻለው አግባብ ካለው አስፈጻሚ አካል ይህንን
አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ባገኘ የጤና ተቋም ብቻ መሆን አለበት፡፡
2) በህክምና ቴክኖሎጂ የታገዘ ተዋልዶ አገልግሎት ለማካሄድ ማህፀን ማከራየትም ሆነ መከራየት የተከለከለ ነው፡፡
3) ማንኛውም ሰው ወይም የምርምር ተቋም ሰውን በክሎኒንግ ቴክኖሎጂ መፍጠር የተከለከለ ነው፡፡
4) ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም “በህክምና ቴክኖሎጂ የታገዘ የተዋልዶ ህክምና” ማለት የወንድን የዘር ፍሬ በተፈጥሮ
ከሚታወቀው ዘዴ በተለየ መልኩ ወደ ሴቷ ውስጣዊ የመራቢያ አካላት ለወሊድ አላማ ማስገባት ሆኖ የወንድና
የሴት ዘር ጥምረት ውጤትን ዘሯ ከተወሰደው ማህጸን ውስጥ ለማስተላለፍ ከሰውነት አካል ውጪ የወንድና የሴት
ዘርን ማቀላቀልን ይጨምራል፡፡

11
18. ስለ አካል ክፍሎችና ህብረ-ህዋሳት ልገሳና ንቅለ-ተከላ

1) ማንኛውም የጤና ተቋም አግባብ ካለው አስፈጻሚ አካል ልዩ ፈቃድ ካላገኘ በስተቀር የአካል ክፍሎችን ወይም
ህብረ-ህዋሳትን ንቅለ-ተከላ ህክምና አገልግሎት መስጠት፣ መሰብሰብ ወይም ማከማቸት አይችልም፡፡
2) የሰው የአካል ክፍሎች እና ህብረ-ህዋሳት ንቅለ-ተከላ ማከናወን የሚቻለው የተቀባዩን ሕይወት ለማቆየት ወይም
የሰውነት አቋሙን ለማስተካከል ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድ የማይገኝ መሆኑ ተፈጻሚነት ባለው የህክምና
አግባብ በጤና ባለሙያ ወይም በጤና ቡድን ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡
3) የሰው የአካል ክፍሎች እና ህብረ-ህዋሳት ንቅለ-ተከላ ለማካሄድ የለጋሹ ሰው ጤንነትን የማይጎዳ መሆኑን ሲረጋገጥ
ብቻ ነው፤
4) የሰው አካል ክፍሎች እና ህብረ-ህዋሳት ፍላጎት ወይም አቅርቦት ለንግድ ወይም ተመሳሳይ ዓላማ ማዋል እና
ማስተዋወቅ የተከለከለ ነው፡፡
5) የእንስሳትን የአካል ክፍሎችና ህብረ-ህዋሳት ለሰው ንቅለ-ተከላ ማዋል የተከለከለ ነው፡፡
6) ለዚህ አንቀፅ አፈፃፀም ሲባል “ንቅለ-ተከላ” ማለት በቀዶ-ህክምና የህክምና ዘዴ በህይወት ካለ ወይም ህይወቱ
ካለፈ ሰው የተለገሰን የአካል ክፍል ወይም ኅብረ-ህዋስ በመውሰድ የታካሚውን በበሽታ የተጠቃ ወይም በአግባቡ
መደበኛ ተግባሩን የማያከናውን የአካል ክፍል ወይም ኅብረ-ህዋስ መተካት ነው፡፡
7) ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም ሲባል “ሕብረ-ኅዋስ” ማለት የተዋልዶ አካላት የሆኑትን አባላዘር፣ ሴቴ ዘር፣ የሴቴና
የወንዴ ዘር ማመንጫዎች፣ ሽል፣ እንዲሁም በደም ልገሳ ወቅት የሚወሰዱ ደምንና የደም ተዋጾዎችን ሳይጨምር
ከሰውነት የአካል ክፍሎች የሚወሰድ በቅርፅ፣ በይዘትና በተግባር ተመሳሳይ የሆኑ የህዋስ ስብስብ ነው፡፡
8) ስለአካል ክፍሎች እና ህብረ-ህዋሳት ልገሳና ንቅለ-ተከላ ልዩ ፈቃድ መስጠት፤ ስለመሰብሰብ፤ ስለማከማቸትና
ስለመከልከል ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣው ሌላ ህግ መሰረት ይወሰናል፡፡

12
19. ስለማስክተብ ግዴታ

1) ማንኛውም የጤና ተቋም በተቋሙ ደረጃ እና የሚሰጠውን አገልግሎት መሰረት በማድረግ ለህጻናት፣ ልጆች፣
ለነፍሰ ጡር ሴቶች፣ ለእናቶች እና ሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች የመከላከያ ክትባትን የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡
2) የዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (1) እንደተጠበቀ ሆኖ በአስገዳጅ ሁኔታ አግባብ ባለው አካል ሲወሰን የጤና ተቋሙ
የክትባት አገልግሎት የመስጠት ሀላፊነት አለበት፡፡
3) ወላጆች፣ አሳዳጊዎች ወይም ሌሎች በህግ ሀላፊነት ያለባቸው ሰዎች የክትባት አገልግሎት ደረጃ በሚፈቅደው
መሰረት በስራቸው የሚገኙ ህጻናትንና ልጆችን የማስከተብ ሃላፊነት አለባቸው፡፡

20. ጤና ሙያ ትምህርት ላይ ስላሉ ተማሪዎች ስለመከታተል

1) ማንኛውም የጤና ተቋም ጤና ሙያ ትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ የመተባበር


ግዴታ አለበት፤
2) ማንኛውም የጤና ተቋም ጤና ሙያ ትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ሲፈቅድ
ተማሪዎቹ የሚሰሩትን የህክምና ልምምድ ስራዎች የመከታተል ሀላፊነት አለበት፡፡
3) ማንኛውም የጤና ተቋም ጤና ሙያ ትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርግ ሲፈቅድ
በክትትል ጉድለት በታካሚው ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ተማሪው እና ክትትል የሚያደርገው የጤና ተቋም በተናጠል
እና በጋራ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

21. ስለ ተላለፊ በሽታ መከላከል፣ መቆጣጠር እና ቆሻሻ አወጋገድ

1) ማንኛውም የጤና ተቋም እና በተቋሙ ውስጥ የሚሰራ ጤና ባለሙያ ከባለሙያው ወደ ተገልጋይ፣ ከተገልጋይ ወደ
ተገልጋይ ወይም ከተገልጋይ ወደ ጤና ባለሙያ በሽታ እንዳይተላለፍ የሚቀመጡ የደህንነት ድንጋጌዎች የመተግበር
ሀላፊነት አለበት፡፡
2) ማንኛውም የጤና ተቋም ከጤና ተቋም የሚወጣ ቆሻሻ በጤና ላይ ለሚያደርሰው የጤና ደህንነት እና በሽታ
የማስተላለፍ ስጋት በአግባቡ የመለየት፣ የመያዝና የማስወገድ ሀላፊነት አለበት፡፡
3) በጤና ተቋማት ውስጥ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት መከላከል፣ የሚወጡ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ እና
ተቋማቱ ይህንን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ይህንን አዋጅ መሰረት አድርጎ
በሚወጣ ሌላ ህግ ይወሰናል፡፡

22. የጤና አገልግሎትን ስለማቋረጥ

13
1) ማንኛውም የጤና ተቋም ስራውን ሲያቋርጥ ቀጣይ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ታካሚዎች በመለየት አግባብ
ላለው አስፈጻሚ አካል በማሳወቅ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ለሚገኝ የጤና ተቋም የማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡
2) ማንኛውም የጤና ተቋም ሥራውን ሲያቋርጥ በይዞታው ስለሚገኝ መድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያ፣ ኢንቮይስ፣
መዝገብ እና ማዘዣ ወረቀት በሚመለከት አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል ባወጣው መመሪያ መሠረት
አስፈላጊውን መፈጸም አለበት፡፡

23. ስለመረጃ አያያዝና ሪፖርት ስለማድረግ

1) ማንኛውም የጤና ተቋም የህክምና አገልግሎት መረጃ አያያዝ እና ሪፖርት አደራረግን በተመለከተ ተፈጻሚነት
ያለውን አሰራር ወይም ህግ መተግበር አለበት፡፡
2) ማንኛውም የጤና ተቋም ሙያዊ ስህተት ሲከሰት ይህንኑ የመለየት እና አግባብ ላለው ተቆጣጣሪ አካል ሪፖርት
የማድረግ አሰራር መተግበር አለበት፡፡
3) ማንኛውም የጤና ተቋም ሪፖርት መደረግ አለባቸው ተብለው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወይም በኢትዮጵያ
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተለዩ ተላላፊ በሽታዎች መኖራቸውን ባወቀ ወይም በጠረጠረ ጊዜ ባፋጣኝ
አግባብ ላለው አስፈጻሚ አካል ማሳወቅ አለበት፡፡
4) ማንኛውም የጤና ተቋም ሪፖርት መደረግ አለባቸው ተብለው አግባብ ባለው አካል የተለዩ የወሳኝ ኩነቶች መረጃ
ለሚመለከተው አካል በወቅቱ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

14
ንዑስ-ክፍል ሁለት
የጤና ባለሙያዎች አስተዳደር

24. ትምህርትና ስልጠና


1) ማንኛወም የጤና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች የሚዘጋጁት ሚኒስቴሩ በሚያወጣው የሙያ ደረጃና
የብቃት መስፈርት መሰረት መሆን አለበት፤
2) አዳዲስ የጤና ሙያ ዘርፍ ትምህርት ፕሮግራሞች ከመጀመራቸው በፊት በጤናው ዘርፍ ፍላጎት ላይ
ሰለመመስረታቸው ከሚኒስቴሩ ማረጋገጫ ማግኘት አለበት፤
3) ማንኛውም የክልኒካል ጤና ሙያ ትምህርቶችን በርቀት፣ በተከታታይ ወይም በኦንላይን የስልጠና ዘዴ መስጠት
የተከለከለ ነው፡፡

25. የብቃት ምዘና


1) የብቃት ምዘና እንዲወስዱ የሚገደዱ የጤና ሙያ ዘርፎች በሚኒስቴሩ ይወሰናሉ፤
2) በጤና ዘርፍ ስልጠናቸውን የጨረሱ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት በሚኒስቴሩ የሚሰጠውን
የብቃት ምዘና ፈተና ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፤
3) የብቃት ምዘና ላለፉ ባለሙያዎች ሚኒስቴሩ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ይሰጣል፤
4) የብቃት ምዘና ፈተና አዘገጃጀት፣ አሰጣጥ እና ውጤት አገላለፅ ላይ ሚኒስቴሩ ተጨማሪ ደንብና መመሪያ ሊያወጣ
ይችላል፤

26. የሙያ ፈቃድ


1) ጠቅላላ
ሀ. ማንኛውም ሰው እንደ ጤና ባለሙያ ለመስራት በሙያው ተመዝግቦ ፈቃድ ሊኖረው ይገባል፤
ለ. የሙያ ፍቃድ ለማውጣት ወይም ለማደስ የሚያመለክት የጤና ባለሙያ በአካል በመቅረብ ማመልከት አለበት፤
ሐ. ከአንድ በላይ የጤና ሙያ ያለው ሰው አስፈላጊውን መስፈርት እስካሟላ እና በሙያዎቹ እስከሰራበት ድረስ
በሁሉም ሙያዎች መስራት የሚያስችለው የሙያ ሥራ ፈቃድ ማግኘት ይችላል፤
መ. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 (ሐ) የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሙያዎች
የሙያ ምዝገባ ፈቃድ ያገኘ ባለሙያ በራሱ ስም የጤና ተቋም ከፍቶ መስራት የሚችለው በአንዱ ሙያ ብቻ
ሊሆን ይገባል፡፡
ሠ. የሙያ ፈቃድ አዲስ ለማውጣትና ለማደስ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችና የፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ይህን አዋጅ
ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ ይወሰናል፤
ረ. የጤና ባለሙዎች የሙያ ምዝገባ ፈቃድ ዕድሳት በየአምስት ዓመት ይከናወናል፤

15
ሰ. ማንኛውም የጤና ባለሙያ ትምህርት በመውሰድ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም ሁኔታ ለተከታታይ
ሁለት ዓመታት እና ከዚያ በላይ በሙያው አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቶ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሳያሟላ
እንደ ጤና ባለሙያ አገልግሎት መስጠት አይችልም፡፡

2) ስለ ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና ስለመውሰድ

ሀ. ማንኛውም የጤና ባለሙያ የሙያ ምዝገባ ፈቃድ ለማደስ ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና መውሰድ
አለበት፤
ለ. የተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና ዝርዝርና ይዘት እንዲሁም የአሰጣጥ ሂደት በተመለከተ ይህን አዋጅ
ለማስፈጸም በሚወጣ ደንብ ወይም መመሪያ ይወሰናል፡፡

3) በውጭ ሀገር የሰለጠነ የጤና ባለሙያ

ሀ. ማንኛውም በውጭ ሀገር ተምሮ የሚመጣ የጤና ባለሙያ በሀገር ውስጥ ለመስራት የሙያ ምዝገባ እና ፈቃድ
ማግኘት አለበት፤
ለ. የዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀፅ (1) ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ እውቅና ባለው የውጭ ተቋም ስልጠና ወስዶ ለሙያ
ምዝገባ እና ፈቃድ ጥያቄ የሚያቀርብ ሰው አግባብ ባለው አካል የተሰጠ የትምህርት ማስረጃ አቻ ግምት
ማረጋገጫ የማቅረብ ግዴታ አለበት፤

ሐ. ከውጪ ሀገር ለአጭር ጊዜ በሚቆይ የእርዳታ ስራ፣ ለአደጋ ጊዜ የሰብአዊ እርዳታ ወይም ለሌሎች ጤና
አገልግሎቶች ለሚመጡ ባለሙያዎች ጊዜያዊ የሙያ ስራ ፈቃድ የሚሰጥበትን ሁኔታ አግባብ ያለው
አስፈፃሚ አካል ይወስናል፤
መ. የጤና ባለሙያውን በጊዜያዊነት ያስመጣው ተቋም በባለሙያው ለሚፈፀም ማንኛውም የሥነምግባርና
ከተቀመጠው የሙያ ደረጃ በላይ በመስራት ለሚደርስ ችግር ሀላፊነቱን ይወስዳል፡፡
ሠ. የጤና ባለሙያውን በጊዜያዊነት ያስመጣው ተቋም ባለሙያው ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ ወዲያውኑ ፈቃዱን
ለሰጠ አካል የማሳወቅና ፈቃዱ እንዲመለስ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
ረ. ማንኛውም በውጭ ሀገር በጠቅላላ ህክምና ተምሮ የሚመጣ ባለሙያ የአንድ ዓመት የኢንተርንሽፕ ስልጠና
መከታተል አለበት፤

27. የሙያ ስራ ኃላፊነትና ወሰን


1) ማንኛውም የጤና ባለሙያ የጤና አገልግሎት የሚሰጠው ተፈጻሚነት ባለው የአገልግሎት ደረጃና የሙያ ወሰን
መሠረት ብቻ ነው፤

16
2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (1) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በልዩ ሁኔታ ሲጠየቅና አስፈላጊ የሆነውን ስልጠና
ማግኘቱ ሲረጋገጥ አግባብ ያለው የጤና ባለሙያ ተቆጣጣሪ አካል ባለሙያው ከተመዘገበበት የሙያ ወሰን ውጪ
አገልግሎት የሚሰጥበትን ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል፡፡

28. የሙያ ሥነ-ምግባር


1) ማንኛውም የጤና ባለሙያ ሙያው የሚመራበትን የሥነ-ምግባር መርሆዎች መሠረት በማድረግ ኃላፊነቱን
መወጣት አለበት፤
2) ማንኛውም የጤና ተቋም እና ባለሙያ በተቋሙ ውስጥ የሙያ ስነ-ምግባር ግድፈት በሚከሰትበት ጊዜ ለተቆጣጣሪ
አካል የማሳወቅ ግዴታ አለበት፤
3) የሙያ ፈቃዳቸው የታገደባቸው ወይም የተሰረዘባቸውን የጤና ባለሙያዎች በተመለከተ አግባብ ያለው አስፈፃሚ
አካል መረጃውን ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፤
4) የጤና ባለሙያዎች አጠቃላይ የስነ-ምግባር መስፈርቶች ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ የጤና ባለሙያዎች
የስነ-ምግባር መመሪያ ይወሰናል፤
5) ማንኛውም የክልል አስፈፃሚ አካል በክልሉ የሚፈፀሙ የጤና ባለሙያዎች ስነምግባር ጉዳዮችን የሚያይ ኮሚቴ
ያቋቁማል፤ጉዳዮችን በማየት ውሳኔ ይሰጣል፤
6) የጤና ባለሙያዎች የስነ-ምግባር ግድፈት በሚከሰትበት ጊዜ የሚካሄደው የምርመራና እርምጃ አወሳሰድ ሁኔታ
ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ ይወሰናል፡፡

29. የጤና ባለሙያዎች መማክርት ጉባኤ ስለማቋቋም


1) የጤና ባለሙያዎች ትምህርትና ሥልጠና፤የብቃት ምዘና፣ የስራ ወሰን፣ምዝገባና ፈቃድ፣ እና የሙያ ስነ-ምግባር
አፈፃፀም በአግባቡ መተግበራቸውን የሚከታተል ለሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነ የጤና ባለሙያዎች መማክርት ጉባኤ
ይቋቋማል፤
2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (1) እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ የመማክርት ጉባኤ እንደአስፈላጊነቱ በክልል ደረጃም
ሊቋቋም ይችላል፤
3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (1) መሰረት የሚቋቋም የጤና ባለሙያዎች ጉባኤ ስልጣንና ኃላፊነት እንዲሁም
አደረጃጀት ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ ደንብ የሚወሰን ይወሰናል፡፡

30. የህሙማን ምርመራ፣ ሕክምና እና ክትትል


ማንኛውም የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የጤና ባለሙያ፡-

1) የተገልጋይ የጤና ችግር ወይም ህመም ተገቢውን የህክምና የምርመራ ሥርአት በመከተል የመመርምር፣ የማከምና
ክትትል የማድረግ ግዴታ አለበት፤

17
2) በግድየለሽነት ወይም የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ አላስፈላጊ የህክምና ምርመራ ማዘዝ ወይም መጠቀም
የለበትም፡፡

31. ስለመረጃ አያያዝና ሪፖርት ስለማድረግ


ማንኛውም የጤና ባለሙያ፡-

1) የህክምና አገልግሎት መረጃ አያያዝ እና ሪፖርት አደራረግ በተመለከተ የወጡ አሰራሮችን መከተል አለበት፡፡
2) ሙያዊ ስህተት መፈጸሙን ያወቀ እንደሆነ አግባብ ላለው የጤና ባለሙያ ተቆጣጣሪ አካል ሪፖርት ማድረግ
አለበት፡፡
3) ሙያዊ ስህተት መፈጸሙን ወይም ችግር መኖሩን ያወቀ የጤና ተቋም ወይም ተቆጣጣሪ አካል የሙያ ፈቃዱ
ስለመያዙ ፈቃዱን ለሰጠ አካል የማሳወቅ ግዴታ አለበት፤
4) ሪፖርት መደረግ አለባቸው ተብለው በአስፈጻሚው አካል የተለዩ ተላላፊ በሽታዎች መኖራቸውን ባወቀ
ወይም በጠረጠረ ጊዜ ባፋጣኝ አግባብ ላለው አካል ማሳወቅ አለበት፡፡

ክፍል ሦስት
የሐይጅን፣ አካባቢ ጤና አጠባበቅና ተላላፊ በሽታ ቁጥጥር

32. ጠቅላላ
1) ማንኛውም ወደ ሀገር የሚገባ ወይም ከሀገር የሚወጣ መንገደኛ ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የጤና
አጠባበቅ መስፈርቶች መሠረት ለዓለም አቀፍ መንገደኞች የሚጠየቀውን ክትባት የመውሰድ፣ በመግቢያና መውጫ
ኬላ ላይ ሲጠየቅ የክትባት ደብተሩን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሚመድበው ባለሙያ
የማሳየትና በተላላፊ በሽታ ሲጠረጠርም ለምርመራ የመተባበር እና አስፈላጊ የጤና መረጃ የመስጠት ግዴታ
አለበት፡፡
2) ማንኛውም ሰው በወረርሽኝ መልኩ በሚተላለፉ በሽታ የተጠቃ ከሆነ ወይም በዚሁ በሽታ መያዙ ከተጠረጠረ
ወይም በሽታው ከተከሰተበት አካባቢ ከመጣ በሽታውን ለመከላከል ሲባል ለሚደረግ ቁጥጥር የመተባበርና
አስፈላጊ የጤና መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
3) የጤና የምስክር ወረቀት ሳይዝና መከላከያ ሳይደረግ እንስሳትን ከመንገደኞች ጋር ማጓጓዝ የተከለከለ ነው፡፡
4) ጤና ነክ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ተቋማት ተገቢውን የሃይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ፣ የስራ አካባቢ ጤንነትና
ደህንነት መስፈርቶች ማሟላታቸውን አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል ያረጋግጣል፤ መስፈርቶቹ ሳይሟሉ ሲቀሩ
አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል፡፡

18
33. በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ስለሚደረግ የተላላፊ በሽታ ቁጥጥር
1) ማንኛውም በተላላፊ በሽታ የተጠረጠረ ሰው ወዲያውኑ ኳራንታይን ተደርጎ ተላላፊ በሽታው ከተገኘበት
አስፈላጊውን ክትባትና ህክምና እንዲወስድ ወይም ወደ መጣበት ሀገር እንዲመለስ ሊደረግ ይችላል፡፡
2) አግባብነት ያለው የጤና ማስረጃ ያልያዘ ወይም በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጣ የሚችል ወረርሽኝ
ካለበት ቦታ የመጣ ሰው ወደ ሀገር አንዳይገባ ሊታገድ ይችላል፡፡
3) ማንኛውም ሰው በመግቢያ ወይም በመውጫ ኬላ ላይ በአለም አቀፍ የጤና ቁጥጥር ደንብ መሰረት ቁጥጥር
በሚደረግበት በሽታ የተጠረጠረ ሰው ሲያጋጥም ወዲያውኑ በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቋም ወይም አግባብ
ላለው የሚመለከተው አካል የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡
4) ደም፣ የደም ውጤቶች፣ የሰው አካላት፣ ሽንት ወይም ዓይነምድር ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ወይም ከሀገር
ማስወጣት የሚቻለው በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፈቃድ መሰረት ብቻ ነው፡፡
5) ማንኛውም ተላላፊ በሽታ ያስተላልፋል ተብሎ የሚጠረጠር ገቢ ወይም ወጪ ማጓጓዣ ወይም ጭነት ወደ ሀገር
ውስጥ የሚገባው ወይም ከሀገር የሚወጣው ተባይና ሌሎች ቆርጣሚ እንስሳት ለማጥፋት የሚረጨው ኬሚካል
ርጭትን ጨምሮ ተገቢው የጤና አጠባበቅ ቁጥጥር ተደርጎበት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ፈቃድ ሲያገኝ ይሆናል፡፡

34. በሀገር ውስጥ ስለሚካሄድ የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር


1) ማንኛውም የጤና ባለሙያ በወረርሽኝ መልክ ተላላፊ በሽታ መግባቱን ወይም በሽታው ስለመከሰቱ ካወቀ ወይም
ሪፖርት ከደረሰው ወዲያውኑ በቅርቡ ላለው የጤና አገልግሎት ተቋም የማሳወቅ ግዴታ ያለበት ሆኖ የጤና
አገልግሎት ተቋሙ መረጃው እንደደረሰው እርምጃ እየወሰደ ለኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ወይም አግባብ ላለው ሌላ አካል ወዲያውኑ ማሳወቅ አለበት፡፡
2) በወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ለምርመራ፣ ለሕክምና ወይም ለክትባት ፈቃደኛ መሆንና
አስፈላጊ የጤና መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
3) ማንኛውም የጤና አገልግሎት ተቋም በወረርሽኝ መልክ ለሚከሰቱ በሽታዎች በደረጃው ተገቢውን አገልግሎት
የመስጠትና ከአቅሙ በላይ ከሆነ አስፈላጊ መረጃ በመስጠት ህክምና ማግኘት ወደሚችልበት ጤና ተቋም በወቅቱ
የመላክ ግዴታ አለበት፡፡
4) ማንኛውም የጤና አገልግሎት ተቋም ተላላፊ በሽታን አስመልክቶ በየጊዜው የሚወጡ የመከላከልና የመቆጣጠሪያ
መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡

35. ከእንስሳት ወደ ሰው ስለሚተላለፍ በሽታ


1) ማንኛውም ሰው በወረርሽኝ መልኩ ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታ የተጠቃ ከሆነ ወይም በዚሁ በሽታ
መያዙ ከተጠረጠረ ወይም በሽታው ከተከሰተበት አካባቢ ከመጣ በሽታውን ለመከላከል ሲባል ለሚደረግ ቁጥጥር
የመተባበርና አስፈላጊ የጤና መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

19
2) ማንኛውም የጤና አገልግሎት ተቋም ከእንስሳት ወደ ሰው ለሚተላለፉ በሽታዎች በደረጃው ተገቢውን አገልግሎት
የመስጠት እና ከአቅሙ በላይ ከሆነ አስፈላጊ መረጃ በመስጠት ህክምና ማግኘት ወደሚችልበት ጤና ተቋም
በወቅቱ የመላክ ግዴታ አለበት፡፡
3) ማንኛውም የጤና አገልግሎት ተቋም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን አስመልክቶ በየጊዜው
የሚወጡ የመከላከልና የመቆጣጠሪያ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡

36. የአስክሬን እና የሰው አካል ክፍል አያያዝና ዝውውር


1) የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ካልፈቀደ በስተቀር የሰው አካል ክፍልን፣ አስክሬንን ወይም
አጽምን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ወይም ከሀገር እንዲወጣ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
2) በአለም አቀፍ የጤና ቁጥጥር ደንብ መሰረት ቁጥጥር የሚደረግበት ተላላፊ በሽታ ያለበትን አስክሬንን ተፈጻሚነት
ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ማዘዋወር የተከለከለ ነው፡፡
3) በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተላላፊ በሽታ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ አስክሬን አግባብነት ያለው
አካል ሲፈቅድ ለጤና ሙያ ትምህርትና ምርምር እንዲውል ማድረግ ይቻላል፡፡
4) ማንኛውም ሰው ከሞተ ሰባት ዓመት ያልሞላውን የሰው አካል ክፍልን፣ አስክሬንን ወይም አጽምን ለማዘዋወር፣
ለመቅበር ወይም ቆፍሮ ማውጣት የለበትም፡፡ ሆኖም በፍትህ አካላት ሲታዘዝ መቅበር ወይም ቆፍሮ ማውጣት
ይቻላል፤
5) ሰባት አመት የሞላውን የሰው አካል ክፍልን፣ አስክሬንን ወይም አጽምን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ወይም ከሀገር
ማስወጣትን ወይም ቆፍሮ ማውጣትን በተመለከተ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዝርዝር
መመሪያ ያወጣል፡፡

37. የሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት


1) አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል በሚቆጣጠረው ጤና ነክ ቁጥጥር በሚካሄድበት ተቋም ላይ የሥራ ነክ ጤና
አጠባበቅ አገልግሎት ለሰራተኞች መቅረቡን ይቆጣጠራል፡፡
2) አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል ስለ ሥራ ነክ ጤና አጠባበቅ እና መሳሪያ አጠቃቀም በተመለከተ ከሚመለከታቸው
አካላት ጋር በመሆን ሌላ ህግ ያወጣል፡፡

38. የመጸዳጃ ቤት እንዲኖር ስለማድረግ


1) ማንኛውም መኖሪያ ቤት ንፅህናው የተጠበቀ እና በቂ መፀዳጃ ቤት ሊኖረው ይገባል፤
2) ማንኛውም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ንጽህናው እና ደረጃው የተጠበቀ በቂ የመጸዳጃ ቤት የማዘጋጀትና
ለደንበኞች ክፍት የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
3) ማንኛውም የከተማ ወይም የገጠር አስተዳደር የሕዝብ መጸዳጃ ቤት እንዲኖርና ንጽህናውም ሁልጊዜ የተጠበቀ
እንዲሆን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

20
39. የመታጠቢያ ስፍራና የመዋኛ ገንዳዎችን ስለመቆጣጠር
1) የሕዝብ መታጠቢያ ስፍራ፣ መዋኛ ገንዳ፣ የተፈጥሮ እንፋሎት ወይም የፍል ውኃ መታጠቢያ አዘጋጅቶ ለሕዝብ
አገልግሎት የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው የክልል ጤና ተቆጣጣሪ ያወጣውን መስፈርት ማሟላት አለበት፡፡
2) የሕዝብ መታጠቢያ ወይም የመዋኛ ቦታ አዘጋጅቶ አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም ሰው አገልግሎቱን የሚታይ
ወይም ግልጽ የሆነ የቆዳ ሕመም ወይም ቁስል ላለባቸው ሰዎች መስጠት የለበትም፡፡
3) ማንኛውንም የሕዝብ መታጠቢያ ስፍራ፣ መዋኛ ገንዳ፣ የተፈጥሮ እንፋሎት ወይም የፍል ውኃ መታጠቢያን
ከታለመለት አላማ ውጪ መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡

40. ስለ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ


1) ማንኛውም ሰው ደረቅ፣ ፍሳሽ እና ሌላ ቆሻሻን አካባቢን በሚበክል እና በጤንነት ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ
ማከማቸት፣ማጓጓዝ እና ማስወገድ የለበትም፡፡
2) ከጤና ወይም ምርምር ተቋም የሚወጣ ደረቅ፣ ፍሳሽ ወይም ሌላ ቆሻሻ በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ እና መወገድ
አለበት፡፡
3) ከፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ከማስረጊያና ከኢንዱስትሪ የሚወጣን ጤና የሚጎዳ ያልታከመ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ
አካባቢ፣ ወደ ውኃ አካላት ወይም ወደ ውኃ አካላት መገናኛ መልቀቅ የተከለከለ ነው፡፡
4) ማንኛውም የቆሻሻ መሰብሰብ፤ ማጓጓዝ፤ ማከማቸት፤ ማስወገድ ወይም እንደገና ጥቅም ላይ የማዋል ተግባር ላይ
የሚሰማራ ሰው ስራውን ሊሰራ የሚችለው የአካባቢ ጤናንና ደህንነትን በጠበቀ መልኩ ሆኖ ለዚህም አግባብ
ካለው አስፈጻሚ አካል ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡
5) ማንኛውም ፈሳሽ ቆሻሻ ወደ አካበቢ ሊለቀቅ የሚችለው አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል ያወጣውን መስፈርት
ሲያሟላ ነው፡፡

41. የጤና ነክ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ተቋማት


1) ጤና ነክ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ተቋማት ተገቢውን የሃይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ እና ተያያዥ መሰፈርት
ማሟላታቸውን አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል ያረጋግጣል፤ እንደ አስፈላጊነቱም እርምጃም ይወስዳል፡፡
2) በዚህ አዋጅ መሰረት የጤና ነክ ቁጥጥር የሚደረግበት ተቋም ሀላፊ ወይም ሌላ አግባብ ያለው ሰራተኛ ተፈጻሚነት
ያላቸው መስፈርቶች መሟላታቸውን የመከታተል ሀላፊነት አለበት፡፡

42. የድምጽና የአየር ብክለት


1) ማንኛውም ሰው የህብረተሰብ ጤናን ለመጠበቅ የድምጽና የአየር ብክለትን ለመከላከል በሃገር አቀፍ ደረጃ
የሚወጣን መስፈርት ማክበር አለበት፡፡

21
2) ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም በሆስፒታል፣ በትምህርት ቤት፣ በመንግሥት መስሪያ ቤት እና መኖሪያ አካባቢን
ጨምሮ በሌሎች የህዝብ መገልገያ አካባቢዎች የድምጽ ሁከት የሚያስከትል ጡሩንባ፣ ድምጽ ማጉያ ወይም
በሚጮሁ መሣሪያ ከተፈቀደው መጠን በላይ መጠቀም የለበትም፡፡
3) ከኢንዱስትሪ ወይም ከሌላ የሥራ ቦታ የሚወጣ ማንኛውም ዓይነት ጋዝ፣ ኬሚካላዊ ትነት፣ ጭስ፣ አቧራ፣ ወይም
ሌላ አየር በካይ ንጥረ ነገር ለሠራተኛውም ሆነ ለአካባቢው ነዋሪ የጤና አደጋ ወይም ብክለት በማይፈጥርበት
ሁኔታ መወገድ አለበት፡፡
4) ማንም ሰው አግባብ ካለው አካል ፈቃድ ውጭ ከባቢ አየርን ሊበክል የሚችል ቁፋሮዎችን፤ የቆሻሻ ማቃጠል
ሥራ፣ ከባድ ጥቁር ጭስ አውጭ መሣሪያዎች ወይም ሞተሮችን መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡
5) የዚህ አንቀጽ ዝርዝር በሌላ ህግ የሚወሰን ይሆናል፡፡

43. የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ቅኝት


አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል ለሰው ጤና ጠቃሚ የሆኑ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ቅኝት ከሚመለከተታቸው አካላት
ጋር በመሆን ያካሂዳል፤ በግኝቱም ጉድለቶች መስተካከላቸውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይቆጣጠራል፡፡

44. ጤናማ ስለሆነ የመኖሪያ እና የስራ ህንጻ


1) አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል ቁጥጥር በሚያደርግበት ተቋም የህንጻ ደረጃ ከጤና አንጻር ያለውን ተስማሚነት
ይቆጣጠራል፤ ደረጃውን ሳያሟላ ሲቀር እርምጃ ይወስዳል፡፡
2) አግባብ ያለው አስፈጻሚ አካል አገር አቀፍ ለጤና ተስማሚ የሆነ የመኖሪያ ቤት ደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት
ጋር በመሆን ያዘጋጃል፤ መተግበሩንም ይከታተላል፡፡

22
ክፍል አራት
ስለ ኢንስፔክተሮች እና ተያያዥ የህግ ማስከበር እርምጃዎች

45. ስለ ኢንስፔክተር ስልጣንና ተግባር

1) በዚህ አዋጅ እና ተፈጻሚነት ባላቸው ሌሎች ህጎች መሰረት የተሰጣቸውን ስልጣን እና ተግባር ለማስፈጸም
አስፈጻሚ አካሎች ኢንስፔክተሮች ብቃታቸውን እና ስነ-ምግባራቸውን በማረጋገጥ ይመድባሉ፡፡
2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (1) መሰረት የተመደበ ኢንስፔክተር በሚሰራበት ተቋም ስልጣን እና ተግባር መሰረት
እንደ አግባቡ የሚከተሉት ስልጣን እና ተግባር ይኖረዋል፡-
ሀ) ቁጥጥር በሚደግባቸው የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች እና
ጤናና ጤና ነክ አገልግሎት በማንኛውም ክፍት በሆኑበት ሰዓት በመግባት የመቆጣጠር፤
ለ) በመግቢያ እና መውጫ በሮች ላይ ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመንገደኞች ክትባት ሰርተፊኬቶችን፣
አስክሬኖችን፣ አውሮፕላኖችን፣ ባቡሮችና በሌሎች ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ የቁጥጥር ሥራዎችን የማከናወን፤
ሐ) የህብረተሰብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ስለመኖሩ የሚገልጽ በቂ ምክንያት ሲኖር ያለ ፍርድ ቤት
ትእዛዝ ቁጥጥር በሚካሄድበት ግቢ ወይም ህንጻ ውስጥ የመግባት እና የመፈተሽ፤ ግቢው ወይም ህንጻው
የመኖሪያ ቤት ብቻ ከሆነ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መሰረት የመግባት እና የመፈተሽ፤
መ) ቁጥጥር የሚደረግባቸው ተቋማት ውስጥ ያለን የጤና መረጃ፣ የፎቶግራፍ ወይም ቪዲዮ ምስል እና
ሰነዶችን ኮፒ የመውሰድ፤
ሠ) ኢኒስፔክተሩ ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ህጋዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ ሊይዝ ይችላል ብሎ ያመነበትን
ማንኛውም ሰነዶች፣ ማስታወሻዎች፣ ደረሰኞችን፣ መዝገቦች፣ ኤሌክትሮኒክ መዝገቦችን ወይም ሌሎች
መዛግብትን ጨምሮ የመመርመር እና ኮፒ የማድረግ፤
ረ) የህግ ጥሰት መኖር አለመኖሩን ለመወሰን የሚረዳ ሆኖ ከተገኘ ማንኛውንም ሰው ቃለ መጠይቅ የማድረግ፤ እና
ሰ) ለአስፈጻሚ አካሉ የተሰጡትን ስልጣን እና ኃላፊነቶች በብቃት እና በቅልጥፍና ለማስተዳደር አግባብነት ያለው
ወይም ምክንያታዊ የሆነ ሌላ ማንኛውም እርምጃ የመውሰድ፡፡
46. የኢኒስፔክተር ግዴታ

ማንኛውም ኢንስፔክተር፡-
1) ስራውን ከማከናወኑ በፊት ማንነቱንና የመጣበትን መስሪያ ቤት፣ ለምን እንደመጣ፣
ቁጥጥር ወደ ሚደረግባቸው ተቋም ገብተው የመመርመር ስልጣን እንዳለው በመግለፅ
የኢኒስፔክተር መታወቂያ የማሳየት ግዴታ አለበት፡፡

23
2) ቁጥጥር የሚደረግበት ተቋም ወይም ምርት እንደ አስፈላጊነቱ ናሙናዎችን፣
ልኬቶችን፣ የሰነዶች ኮፒ፣ የቪዲዮ ቅጂ እና የመዝገብ ኮፒን ጨምሮ ተቀባይነት
ያላቸውን ሌሎች ማስረጃዎች የመያዝ፣ የመሰብሰብ እና አግባብ ላለው አካል
የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡
3) የተሰጠውን ስልጣን የሚተገብረው የተቆጣጣሪ አካሉን ዓላማ ለማሳካት በህግ
በተሰጠው ወሰን ውስጥ እና ሎሎች አግባብነት ያላቸው የአገሪቱን ህጎችና የስነ-ምግባር
ኮዶች ባከበረ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መሆን አለበት፡፡
4) በትጋት፣ በታማኝነት፣ በጥንቃቄ እና በተቻለ ፍጥነት ስራውን መፈፀም እና የበላይ
ሀላፊን ትዕዛዝ በማክበር የመስራት ግዴታ አለበት፡፡
5) የመስሪያ ቤቱን ሀላፊነት በተቻለ ፍጥነት መወጣት እንዲችል አስፈጻሚ አካሉ
በሚያመጣው ተቀባይነት ያለው አዳዲስ የአሰራር ስርአቶችን ተቀብሎ የመፈፀም
ግዴታ አለበት፡፡

47. አስተዳደራዊ እርምጃ


1) ቁጥጥር የሚደረግበት አገልግሎት ወይም ፈቃድ የያዘ ሰው ይህንን አዋጅ ወይም ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም
የሚወጡ ህጎችን ጥሶ ከተገኘ እንደ ህግ መተላለፉ መጠን ከማስጠንቀቂያ እስከ ምዝገባ ወይም ፍቃድ መሰረዝን
ጨምሮ የገንዘብ ቅጣት አግባብ ባለው አስፈጻሚ አካል ይወሰድበታል፡፡
2) የዚህ አንቀፅ ንዑስ-አንቀፅ( 1) ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ አግባቡ አስፈጻሚው አካል የፈቃድ የዕገዳ ወይም
የስረዛ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደበትን ቁጥጥር የሚደረግበትን ሰው የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ሲባል
መረጃውን ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡
3) በዚህ አዋጅ መሰረት ቁጥጥር ከሚደረግበት አገልግሎት ጋር በቀጥታ በሚገናኝ ስራ ምክንያት በወንጀል ተጠርጥሮ
በፍርድ ቤት ጥፋተኛነቱ የተረጋገጠን ሰው አስፈጻሚው አካል ይህን ሰው ቁጥጥር በሚያደርግበት ስራ ላይ
እንዳይሰራ ሊያግድ ይችላል፡፡
4) የጤና ቁጥጥር ህግን መተላለፉ በወንጀል የሚያስጠይቅ ከሆነ አስፈጻሚ አካሉ ወዲያውኑ መረጃዎችን በማጠናከር
አግባብነት ላለው የህግ አካል ሪፖርት የማድረግ እና በህግ አፈፃፀም ወቅት በጋራ የመስራት ሀላፊነት አለበት፡፡
5) ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ ደንብ ወይም ሌላ አግባብ ባለው ህግ መሰረት አስፈጻሚ አካሉ ከሌላ
አስተዳደራዊ እርምጃ ጋር ወይም በተናጠል የገንዘብ ቅጣት ሊጥል ይችላል፡፡

48. በአስተዳደራዊ እርምጃዎች ላይ ስለሚቀርብ ቅሬታ


1) ቁጥጥር በሚደረግበት ተቋም ወይም ሰው ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደበት ወይም በዚህ አዋጅ ላይ
የተቀመጡን አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን የተነፈገ ማንኛውም ሰው እርምጃው አግባብነት የለውም፣ ተመጣጣኝ

24
ያልሆነ ወይም ህገ-ወጥ ነው ብሎ ካመነ ቅሬታውን በዚህ አንቀጽ መሰረት አስፈጻሚ አካሉ ለሚቋቋም የቅሬታ
ሰሚ አካል በማቅረብ እንደገና እንዲታይለት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
2) በዚህ አንቀጽ መሰረት የሚቋቋም የቅሬታ ሰሚ አካል የመደመጥ መብትን ጨምሮ የአስተዳደር ፍትህ ሂደት
መርሆዎችን በተከተለ መልኩ የሚሰራ ይሆናል፡፡
3) በዚህ አንቀጽ መሰረት የሚቀርብ ቅሬታ አስፈጻሚ አካሉ የመጨረሻ ውሳኔ ከሰጠበት ቀን ጀምሮ በ 30 ተከታታይ
ቀናት ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል፡፡
4) በዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (1) መሰረት ቅሬታን የተቀበለ የቅሬታ ሰሚ አካል ቅሬታውን ከተቀበለበት ቀን ጀምሮ
ባሉት 30 ተከታታይ ቀናት ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል፡፡
5) በዚህ አንቀጽ መሰረት በቅሬታ ሰሚ አካል ወይም በአስፈጻሚ አካሉ የሚሰጥ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ከፍሬ ነገር
በስተቀር አግባብ ወዳለው መደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊባልበት ይችላል፡፡

49. ቅጣት
በወንጀል ሕጉ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር፡-
1) ማንኛውም ሰው ይህን አዋጅ በመቃረን ኢኒስፔክተሮችች የተሰጣቸውን ስልጣን እና ተግባር እንዳያከናውኑ
ከከለከለ፣ እንቅፋት የፈጠረ እንደሆነ ወይም በማንኛውም መንገድ ማስረጃ እንዳይወስድ እክል ከፈጠረ፤ የህግ
መተላለፉን የሚመለከቱ ማስረጃዎችን ወይም ፍሬ ነገሮች ከኢኒስፔክተሮች የሸሸገ፣ ያሸሸ፣ ያጠፋ፤ የሀሰት
ማስረጃ፣ የሀሰት ቃል ወይም የተጭበረበረ ሰነድ የሰጠ ወይም እነዚህን ተግባራ ለመፈጸም የሞከረ ከሆነ ከአንድ
ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከብር 10 ሺ በማያንስና ከብር 50 ሺ
በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤
2) በዚህ አዋጅ መሰረት የተሰየመን ኢኒስፔክትር የተሰጠውን ስልጣን በሚተገብርበት ወቅት በስብእናው ወይም
በአካሉ ላይ ወይም በሚጠቀምበት ማንኛውም ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከአንድ ዓመት
በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከብር 10 ሺ በማያንስና ከብር 50 ሺ በማይበልጥ
መቀጮ ይቀጣል፤
3) ማንኛውም ኢኒስፔክትር በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በመተላለፍ ሆነ ብሎ መደለያ በመቀበል ወይም
በዝምድና ወይም አግባብ ባልሆነ ሌላ ግንኙነት የጤና ወይም ጤና ቁጥጥር የሚደረግበት ተቋም የምዝገባ ፈቃድ
ወይም የሙያ ስራ ፈቃድ እንዲያገኝ ወይም እንዲታደስ ያደረገ እና በዚህ ምክንያት ማህበረሰቡ ላይ የጤና ጉዳት
እንዲደርስ ያደረገ ወይም ህብረተሰቡ ላይ የጤና ጉዳት ሊደርስ የሚችል በቂ ምክንያት እንዲኖር ያደረገ እንደሆነ
ከሰባት ዓመት በማያንስና ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና ከብር 30 ሺ በማያንስና ከብር
50 ሺ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤
4) ማንኛውም ኢኒስፔክትር አግባብ ያለውን ፍሬነገር ወይም መረጃ ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት ለአስፈጻሚው
አካሉ ባለማሳወቁ ምክንያት ማህበረሰቡ ላይ የጤና ጉዳት እንዲደርስ ያደረገ ወይም ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሊደርስ

25
የሚችል በቂ ምክንያት እንዲኖር ያደረገ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም ከብር 10 ሺ በማያንስና ከብር 30 ሺ
በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤
5) ማንኛውም ኢኒስፔክትር ተቆጣጣሪ በህግ የተሰጠውን ተግባር በማከናወን ቁጥጥር የተደረገበትን ተቋም
በሚመለከት ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት የተሳሳተ ሪፖርት ለአስፈሚው አካል ማድረጉ ከተረጋገጠ፣ እርምጃ
መውስድ እያለበት አለመውሰዱ ከተረጋገጠ ወይም ያለ በቂ ምክንያት የወሰደው እርምጃ ህጉ ከሚፈቅደው በእጅጉ
ያነሰ ከሆነ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከብር 10 ሺህ የማይንስ
እና ከብር 20 ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤
6) ይህን አዋጅ በመተላለፍ ደረጃና ወሰኑን ሆን ብሎ በመተላላፍ የጤና አገልግሎት የሰጠ ማንኛውም የጤና ባለሙያ
ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከብር 5 ሺ በማያንስና ከብር 10 ሺ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤
7) የዚህን አዋጅ ድንጋጌ በመተላለፍ ያለሙያ ፈቃድ ወይም በሐሰተኛ መንገድ ወይም በማጭበርበር በተገኘ የሙያ
ፈቃድ ሲሰራ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከአምስት አመት በማይበልጥና ከሰባት አመት በማያንስ ፅኑ እስራት ወይም
ከብር 100 ሺ በማያንስና ከብር 500 ሺ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፤
8) የዚህን አዋጅ ድንጋጌ በመተላለፍ በሀሰተኛ መንገድ የህክምና ምስክር ወረቀት የሰጠ የጤና ባለሙያ ከሶስት ወር
በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከብር 5 ሺ በማያንስና ከብር 10 ሺ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤
9) በዚህ አዋጅ የተደነገገውን ሪፖርት የማድረግ ግዴታ የተላለፈ ማንኛውም የጤና ባለሙያ ከሶስት ወር በማያንስ
ቀላል እስራት ወይም ከብር 5 ሺህ በማያንስና ከብር 10 ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤
10) ማንኛውም ሰው የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች በመተላለፍ ሌሎች ወንጀሎችን የፈጸመ እንደሆነ አግባብ ባላቸው
የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች መሰረት ይቀጣል፡፡

ክፍል አምስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

50. ስለ መተባበር ግዴታ

አስፈጻሚ አካሉ በዚህ አዋጅ ውስጥ የተቀመጡ ኃላፊነት እና ግዴታዎችን መወጣት እንዲችሉ የሚመለከታቸው የፌዴራል
እና የክልል መንግስታት ከአስፈጻሚ አካሉ ጋር የመተባበር ግዴታ አለባቸው፡፡

51. ስለ ማስታወቂያ

1) በብዙሃን መገናኛ ወይም በሌላ ዘዴ የሚተላለፍ ቁጥጥር የሚደረግባቸው የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ይህንን
አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ መመሪያ መሰረት ይሆናል፡፡

26
2) ማንኛውም ብዙሀን መገናኛ ወይም ማስታወቂያ የሚሰራ አካል በዚህ አዋጅ መሰረት የሚወጣውን መመሪያ
የማክበር ግዴታ አለበት፡፡

52. ስለተሻሩ እና ተፈጻሚነት የሌላቸው ህጎች

1) በዚህ አዋጅ መሰረት የተደነገጉ ጉዳዮችን በሚመለከት አዋጅ ቁጥር 661/2002 ተሽሯል፡፡
2) በዚህ አዋጅ ከተደነገጉ ጉዳዬች ጋር የሚቃረን ማንኛውም ህግ፣ ልማድ ወይም አሰራር ተፈፃሚነት
አይኖረውም፡፡

53. ደንብና መመሪያን ሰለማውጣት

1) ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡


2) ክልሎች ስልጣን እና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የራሳቸውን አዋጅ፣ ደንብ ወይም መመሪያ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡
3) አስፈጻሚ አካላት ለዚህ አዋጅ እና በዚህ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ (1) መሰረት ለሚወጣ ደንብ ማስፈጸሚያ
መመሪያዎች ሊያወጡ ይችላሉ፡፡

54. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ


የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

27

You might also like