You are on page 1of 2

“እንወቅ፤ እናዉቀዉም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፡፡”

ሆሴዕ 6÷3
በዚህ መፅሐፍ (ትንቢተ ሆሴዕ) እግዚአብሔር በወደዳት፣ በጭቃ ከተለወሰችበት መሬት
አንስቶ ደሟን በማጠብ ከኃጢያትዋ ባነጻት፣ አይታ የማታዉቀዉን ደግሞም የማይገባትን ወግ
ማዕረግ ባሳያት፣ ከግልሙትናዋ ባላቀቃት፣ የኃጢያትዋንና የባርነቷን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ከባርነት
ባወጣት...፣ ከምንም በላይ ደግሞ ማንም ዳግም ሊያፈቅራት በማይችለዉ ታላቅ ፍቅር ያፈቀራት
እና የሚንሰፈሰፍላት "እስራኤል" ከእርሱ እዉነተኛ ፍቅር ይልቅ ሌላዉን፣ ተድላን፣ ምቾትን፣
በሚገርም ሁኔታ ደግሞ የቀድሞ ግልሙትናዋንም ጭምር በመምረጧ የመጨረሻዉን ፍርድ በእርሷ
ላይ ከማሳለፉ በፊት እና እንዳትጠፋበትም ካለዉ ታላቅ ርህራሄ የተነሣ አንጀቱ እንደሚላወስበት
አባት እና ልቡም እንደሚቃጠልበት አፍቃሪ ፍቅሩን ለማደስ እና እርሷን ወደራሱ ለመመለስ
የሚያደርገዉን በፍቅርና በቁጣ የተሞላዉን የመጨረሻ የሚመስል ትግሉን ያሳየናል፡፡ ይህንንም፡-
“እስራኤል ሆይ! እንዴት እጥልሃለሁ? እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? ለአንተ ያለኝ
ፍቅር ይህን ሁሉ እናዳደርግ አይፈቅድልኝም እኔኮ እንደ ሰዉ አይደለሁም!”(11÷8)
በሚል የፍቅር ቃል ይገልፅላታል፡፡ ነገር ግን እስራኤል ይህንን የፍቅር ጥሪ የምትመልሰዉ
“እንወቅ፤ እናዉቀዉም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፡፡”(6÷3) በሚል የእዉነት እና
ፍፁም የፀፀት ቃል መሣይ ነገር ግን ከልብ ባልሆነ የስላቅ እና የማስመሰል መልስ ነዉ፡፡
እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሕዝብ “አንቺን ማግኘቴ እኮ የወይንን ፍሬ÷በምድረበዳ
የማግኘት ያህል ነበር፤ አባቶቻችሁንም ማግኘቴ አንድ ገበሬ የመጀመሪያዉን የበለስ
ፍሬ ሲያይ የሚሰማዉን አይነት ነበር”(9÷10) እያለ ሲነግራት፣ ሲያባብላት፣ ሊመልሳት
ሲጥር እርሷ ግን ከእርሱ ይልቅ አሁንም ሌላ አምላክን፣ ከክብሯ ይልቅ ዉርደትን፣ ከሕይወት
ይልቅ ሞትን መርጣ ከዳችዉ፤ ሲታይ ተስፋ ሰጪ የሚመስለዉን ለእርሱ ያላትን ፍቅርም
ሲገልጸዉ ማለዳ ላይ ምድርን ሁሉ ሸፍኖ እና ከድኖ እንደሚታይ የማለዳ ጉም
እንዲሁም ምድርን ሁሉ አረስርሶ ጨርሶ ተርፎት የሚተፋ በሚመስለዉ የጠዋት ጤዛ
ነዉ፡፡(6÷4) የእስራኤልማ ክህደት፣ በእግዚአብሔር ላይ ያሳየችዉ ንቀት፣ የኃጢያትዋ ብዛት፣
የድፍረቷ ትልቀት፣ የልብዋ ጥንካሬ፣ በእግዚአብሔር ላይ ላለመታመን ያላት ትልቅ እምነት፣ ኸረ
ምኑ ቅጡ÷ የቱ ተዘርዝሮ የቱ ይተዋል???

ታዲያ መፅሐፉም “የጠቢብ ሰዉ አይኖች በራሱ ላይ ናቸዉ”(መክ 2÷14) እንዲል


መፅሐፉም የተፃፈልን ለትምህርታችን ነዉና እኔም እስራኤልን መዉቀሱን ትቼ ራሴንና ዘመኔን
መታዘብ ጀመርኩ እናም ዛሬም በእኛ ዘመን በብዙዎቻችን ላይ የሚታየዉ ችግር ይሄ ይመስለኛል÷
ሁላችንም በአንደበቶቻችን ስለ እግዚአብሔር ማንነት፣ ለእኛ ስላለዉ ፍቅር፣ ስለ ቤ/ክ ስርዓት፣ ስለ
ሕይወት ጥራት ወ.ዘ.ተ... ስናወራ አፍ እስክናስከፍት ድረስ እናስደምማለን፤ ነገር ግን የምናወራዉ
እና የምንሰብከዉ ሕይወት ሁሉ ለራሳችን እንኳን እንግዳ ነገር እስኪሆንብን (እስኪመስለን) ድረስ
አዲስ እንሆናለን፡፡ እግዚአብሔር፣ ኢየሱስ፣ መስቀሉ፣ የክርስቶስ ደም፣ ከሞት መነሳቱ፣ ወደ አብ
ማረጉ፣ መንፈስ ቅዱስን መቀበላችን፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ-መቅደስ ብሎም የእግዚአብሔር
ልጆች መሆናችን ጠልቆ አይሰማንም፤ አንዳንዴማ እዉነትም መስሎ እንኳን አይታየንም፡፡ ከሁሉ
የሚገርመዉ ደግሞ ይህንን ሁሉ ስናስብ አይሞቀን፣ አይበርደን፣ አይፀፅተን፣ ምን ሆነን ነዉ???
ብለን እንኳን አንጠይቅም፡፡ አንድ ወዳጄ እንደሚለዉ ሰይጣን የደረበልንን የድንዛዜ ብርድ ልብስ
ማለትም (ሚዲያ፣ የመዝናኛ እና የተለያዩ ፕሮግራሞች /ቻናሎች/፣ የአለም ሁኔታ፣ ምድራዊ
ኑሮዋችን፣ ወ.ዘ.ተ...) ደራርበን ላንሰማ ላንለማ ጥልቅ እንቅልፍ ዉስጥ ገብተናል፤ ታዲያ ከዚህ
እንቅልፍ ዉስጥ ለመዉጣት እና ለመንቃት የአዳኛችንን እና የታዳጊያችንን ማንነት (ኢየሱስ
ክርስቶስን) ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ማናችንም ብንሆን ራሱን ካልገለጠልን
በስተቀር በራሳችን ጥረት እና ግረት እግዚአብሔርን ልናዉቀዉ እናደማንችል ቁርጣችንን ነግሮናል÷
ደስ የሚለዉ ነገር ግን ወደ እዉነት ሁሉ ምንጭ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራን ደግሞም
ማንነቱን የሚገልጥልን መንፈስ ቅዱስ በዉስጣችን መኖሩ ነዉ፡፡ ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ
የእግዚአብሔር ሚስጥር የሆነዉን ክርስቶስን እንዲገልጥልን መፀለይ ደግሞም ከእርሱ ጋር መጣበቅ
አለብን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ሲገልጥልን ግን ቅዱስ ቃሉ እንደሚለዉ እርሱን በማወቅ፣
ያወቅነዉን በመኖር፣ በምንደክምበትም ጊዜ በሚያስፈልገን ሁሉ ሊረዳን የሚችለዉን
ጸጋ በመደገፍ በይበልጥ የእምነታችን ጀማሪና ፈፃሚ የሆነዉን ክርስቶስን
እየተመለከትን ከፊታችን ያለዉን ሩጫ (ያዉ ምንም ያህል ፈተናና መሰናክል ቢበዛበትም)
በትዕግስት እንሮጣለን፡፡(ዕብ12÷1-2) ያኔ በማስመሰል ሳይሆን ከልባችን “ኑ! እግዚአብሔርን
እንወቅ÷ሳናወላዉልም እንከተለዉ...”እንላለን፡፡ እርሱም እንደ ንጋት ብርሐንና ምድርን
እንደሚያረካ የበልግ ዝናም ሊያረሰርሰን በእርግጥ ወደእኛ ይመጣል፡፡(6÷3)

ኢሣያስ አያሌዉ
06/10/2010 E.C

You might also like