You are on page 1of 4

የሰበር መ/ቁ 50291

የካቲት 26 ቀን 2002 ዓ.ም

ዳኞች፡- መንበረፀሐይ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

ብርሃኑ አመነው

አልማው ወሌ

ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡- ጄ ሰቨን ንግድና ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር

ተጠሪ፡- እነ አቶ ነሲቡ ጀማል (52 ሰዎች)

መዝገቡን መርምረን የሚከተውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍርድ

ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 80158 ነሐሴ 26

ቀን 2001 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ

እንዲታረምልኝ በማለት ህዳር 1 ቀን 2002 ዓ.ም በማመልከቱ ነው፡፡ ክርክሩ በመጀመሪያ የታየው

በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ተጠሪዎች አመልካች የከሰረ በመምሰል በሠራተኛ ቅነሳ

በሚል ከሥራ ያሰናበታቸው በመሆኑ ስንብቱ ሕገ ወጥ በመሆኑ ካሣ፣ የስንብት ካሣ፣ ጫማና ቱታ

የዓመት እረፍት በገንዘብ ተቀይሮና የጡረታ መብታችን እንዲጠበቅ ውሣኔ ይሰጥልን በማለት

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ አቀርበዋል፡፡ አልካች በበኩሉ በተከሳሽነት ቀርቦ ተጠሪዎች

ከሥራ የተሰናበቱት ድርጅቱ ሕጉን መሠረት በማድረግ ባከናወነው የሠራተኛ ቅነሳ ነው፡፡ ስለዚህ ውሉ

በመቋረጡ የምንከፍለው ካሣ የለም፡፡ የሥራ ስንብት ካሣ የማስጠንቀቂያ ክፍያ የሁለት ወር የአመት

እረፈት ክፍያ ተከፍሏቸዋል፡፡ ጫማና ቱታ ለሥራ የሚሰጥ በመሆኑ ሊጠይቁን አይገባም የሚል መልስ

ሰጥቷል፡፡

1
የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ከሥራ የተሰናበቱት በህገወጥ መንገድ መሆኑን

አላስረዱም አመልካች አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 29 መሠረት ባከናወነው

የሠራተኛ ቅነሳ ተጠሪዎች ከሥራ የተሰናበቱ በመሆኑ በህገወጥ መንገድ የሥራ ውሉ በመቋረጡ ካሣ

እንዲከፈላቸው ያቀረበት ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡ አመልካች የአመት እረፍት ክፍያ የሁለት ወር

ደመወዝ የማስጠንቀቂያ ክፍያና ካሣ የከፈለ መሆኑ በጽሑፍ ማስረጃ አስረድቷል፡፡ ተጠሪዎች የሶሶት

ወር የማስጠንቀቂያ ክፍያ እንዲከፈላቸው የጠየቁ ቢሆንም ክፍያው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ

35(መ) መሠረት የተከናወነ ስለሆነ በህጉ መሠረት የተፈፀመ ነው፡፡ ጫማና ቱታ ለከሳሾች

(ተጠሪዎች) በገንዘብ ተለውጦ ይሰጣቸው፡፡ አመልካች ካሣ የከፈለ መሆኑ ቢረጋገጥም ካሣው በአዋጅ

ቁጥር 377/96 አንቀጽ 40(3) መሠረት በማድረግ አስልቶ አልከፈላቸውም በማለት ልዩነቱን በህጉ

መሠረት አስልቶ አመልካች ለተጠሪዎች እንዲከፍል ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ የጡረታ መብት

ለሚመለከተው አካል ያቅርቡ በማለት ወስኗል፡፡ ተጠሪዎች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ

ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ

ማስጠንቀቂያ ሣይሰጥ የሥራ ውላቸው መቋረጡ ተጠሪዎች ከሥራ የተሰናበቱት በህገ ወጥ መንገድ

መሆኑን ያረጋግጣል በማለት አመልካች ለተጠሪዎች በሕገወጥ መንገድ የሥራ ውል በማቋረጡ

ሊከፍል የሚገባውን ካሣ በአንቀጽ 43(4)ሀ የሁለት ወር የማስጠንቀቂያ ደመወዝ ክፍያ በአዋጅ ቁጥር

377/96 አንቀጽ 41 አንቀጽ 77(5) አንቀጽ 39(1)ሐ) እና 40(2)(3) መሠረት እንዲከፍል የጡረታ

መብት ፎርሟሊቲ አሟልቶ ለማህበራዊ ዋስትና ባለሥልጣን እንዲልክ በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

አመልካች በሰበር አቤቱታው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ክስ ሲያቀርቡ ያልጠየቁትን

ክፍያ በራሱ አነሳሽነት በማንሣት እንድንከፍል ወስኗል ለጉዳዩ አግባብነት የሌላቸውን ድንጋጌዎነች

ለመጥቀስ የአዋጁን አንቀጽ 41 እና ሌሎችንም አግባብነት የሌላቸውን ድንጋጌዎች በመጥቀስ

ተገቢነት የሌለው ክፍያ እንድንከፍል ወስኗል፡፡ ክፍያ የፈፀምን መሆኑን በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ

ቤት አረጋጦ ውሣኔ የሰጠባቸውን ክፍያዎች ያለበቂ ምክንያትና ማስረጃ በድጋሚ ለተጠሪዎች

እንድንከፍል በመወሰን መሠረታዊ የህግ ስህተት የፈፀመ መሆኑ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት

2
አመልክቷል፡፡ ተጠሪዎች በበኩላቸው አመልካች የሥር ዋስትናችንን በማሣጣት በህጉ መሠረት

ሊከፍለን የሚገባውን ክፍያ ሣይከፍል ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ያሰናበተን በመሆኑ የከፍተኛው ፍርድ

ቤት ስንብቱ ህገወጥ ነው በማለት አመልካች በአዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎች መሠረት የለያዩ

ክፍያዎነችን እንድንከፍል የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ

ሰጥተዋል፡፡

ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ጉዳዩን

መርምረናል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች ተጠሪዎችን ከሥራ ያሰናበታቸው በአዋጅ ቁጥር

377/96 አንቀጽ 29 ድንጋጌ ተከትሎ ባከናወነው የሰራተኛ ቅነሳ መሆኑን የከፍተኛው ፍርድ ቤት

በሰጠው ውሣኔ ሶስተኛው ገጽ በሁለተኛው ፖራግራፍ ገልፆለታል፡፡ አመልካች ተጠሪዎች በህገ ወጥ

መንገድ ያሰናበታቸው ስለመሆኑ የሚያስረዳ ማስረጃ ተጠሪዎች እንዳላቀረቡና በአንፃሩ አመልካች

ተጠሪዎችን ከሥራ መቀነሱን ያረጋገጠ መሆኑ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በውሣኔው ገልፆል፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤትም ሆነ የከፍተኛው ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪዎችን ከሥራ

ያሰናበታቸው በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 29 መሠረት ባከናወነው የሠራተኛ ቅነሣ መሠረት

መሆኑን በውሣኔአቸው ያረጋገጡ ፍሬ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

የከፍተኛው ፍርድ ቤት አመልካች የፈፀመው የሥራ ስንብት ህገወጥ ነው ከሚለው

መደምደሚያ ላይ የደረሰው አመልካች ተጠሪዎችን ከሥራ ስቀንስ ማስጠንቀቂያ አልሰጣቸውም

በሚል ምክንያት መሆኑን ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ከዚህ አንፃር

ስንመለከተው የከፍተኛው ፍርድ ቤት አመልካች ተጠሪዎችን ከሥራ ያሰናበተው በአዋጅ ቁጥር

377/96 አንቀጽ 29 የተደነገጉ መስፈርቶች አሟልቶ መሆኑን በውሣኔው ካረጋገጠ በኋላ ከሥራ

ስትቀንስ ማስጠንቀቂያ አልሰጠኃቸውም በማለት አመልካች የተጠሪዎችን የሣምንት አማካኝ

ደመወዘ በአንድ መቶ ሰማኒያ ቀናት በማባዛት የመክፈል ሀላፊነት አለበት በማለት የአዋጅ ቁጥር

377/96 አንቀጽ 43(4)(ሀ) በመጥቀስና ለድንጋጌው የተዛባ ትርጉም በመስጠት የሰጠው ውሣኔ ተገቢ

ሆኖ አላገኘውም፡፡ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አመልካች ለተጠሪዎች የከፈለ

3
መሆኑን በሰነድ ማስረጃ ያረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ ውሣኔው የሰጠባቸውን የሁለት ወር

የማስጠንቀቂያ ክፍያ የአመት እረፍትና የሥራ ስንብት ክፍያ የከፍተኛው ፍርድ ቤት አመልካች

ለተጠሪዎች በድጋሚ እንዲከፍል የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 29 መሠረት የሠራተኛ ቅነሳ በሚደረግበት ጊዜ

ተጠቃሽና ተፈፃሚ የማይሆነውን የአዋጁን አንቀጽ 41 በመጥቀስ የሰጠው ውሣኔ ተገቢ ሆኖ

አላገኘውም፡፡ በአጠቃላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በይግባኝ ሊወስነው የሚገባውን ጭብጥ በአግባቡ

በመለየትና በመያዝ ጭብጡን ለመፍታት አግባብነት ያላቸውን የፍሬ ጉዳይ እና የህግ ነጥቦች በመለየት

ሣይሆን አግባብነት በሌለው ሁኔታ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ የሻረው መሆኑን

ተገንዝበናል፡፡ ስለሆነም ከላይ በዝርዝር የገለጽናቸው ምክንያቶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት የአዋጅ ቁጥር

377/96 የተለያዩ ድንጋጌዎች በመጥቀስና በመተርጐም የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት

አለበት በማለት ወስነናል፡፡

ውሣኔ

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተሻሽሏል፡፡

2. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ፀንቷል፡፡

3. በዚህ ፍርድ ቤት የወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ ይኸ ፍርድ በፌዴራል

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሙሉ ድምጽ ተሰጠ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ፀ/መ

You might also like