You are on page 1of 11

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

ንግድ ቢሮ

የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት

የብሎክ ማናጅመንት
(ቀጠና-ተኮር የክትትልና ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት)
አሰራር መመሪያ (ረቂቅ)

መስከረም 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ

ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌ
1. አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ የብሎክ ማናጅመንት (የቀጠና-ተኮር የንግድ ክትትልና ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት) የአሰራር ስርዓት
መመሪያ ቁጥር ----------/2013" ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

1
2. አጠቃላይ ሁኔታዎች

2.1. ስያሜ
ይህ መመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብሎክ ማኔጅመንት የንግድ ክትትልና ቁጥጥር የአሰራር መመሪያ
ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

2.2. የመመሪያው ዓላማ


የዚህ መመሪያ ዓላማ በየደረጃው በሚገኙ የንግድ ጽ/ቤቶች ስር የሚገኙ የንግድ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያዎች
የየእለት የክትትትልና ቁጥጥ ተግባራትን በብሎክ/ቀጠና/ በመከፋፈል በእቅድ እንዲመራ በማስቻልና በከተማችን
የሚስተዋሉ የንግድ ህገ-ወጥነቶች ወጥ በመከላከል ህጋዊና ፍትሃዊ ንግድ እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡

2.3. የመመሪያው ግብ
የዚህ መመሪያ ግብ የአዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር የንግድ አሰራር የንግድ አዋጆችን ደንቦችና የአሰራር
መመሪያዎችን ተከትሎ እንዲከናወን በማስቻል ፍትሃዊ፤ ፈጣን፤ ውጤታማ፤ ጥራትና ምቹነት ያለው አገልግሎትና
የንግድ ክትትልና ቁጥጥር አሰራር ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ደንበኛውን/ተገልጋዩን/ ማርካት ነው፡፡

2.4. የመመሪያ አስፈላጊነት፤

 የንግድ የአሰራር ስርዓቱን ህጋዊነት እንዲላበስ በማስቻል የወጡ አዋጆችን፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና
የአሰራር ማንዋሎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በሁሉም ክ/ከተሞች እና ወረዳዎች ወጥ ለማድረግና
የበለጠ ግልጸኝነትን ይፈጥራል፣
 በባለሙያው፣ በነጋዴውና በሸማቹ ዘንድ የሚታዩ አላስፈላጊ መጉላላት ጊዜንና ንብረትን በአግባቡ
ለመጠቀም ይረዳል፣
 በህገ-ወጦች የንግድ ስራ ተሰማርተው የሚገኙ በሚገኙት ላይ የሚወሰደዉ እርምጃ ፍትሃዊ እና
አስተማሪ እንዲሆን ያስችላል፣
 የንግድ አሰራር ስርዓት ለማስያዝ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው በየደረጀው ለሚገኘው አስፈፃሚ አካላት ግልፀኝነት፣
ተጠያቂነት ለማስፈን ይረዳል፤
 ባለሙያዎች በኃላፊነት በያዙት ብሎክ/ቀጠና/ የሚገኙ ውጤቶችን ለማበረታታትና ለሚፈጠሩ
ክፍተቶች የተጠያቂነት ስርዓትን ለመዘርጋት ያስችላል፤

2.5. የመመሪያው ወሰንና ተጠቃሚዎች


ይህ መመሪያው በንግድ ህጉ፤ በንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ 980/2008 ና 1150/2011፤ በንግድ ምዝገባና ፍቃድ
ደንብ ቁጥር 392/2009፤ በንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ 813/2006 እና ሌሎች ንግድን በሚመለከቱ
ህጎች፣ ደንቦች መመሪያዎችና ማንዋሎች የተካተቱ የህግ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ከማዕከል እስከ ቀጠናና

2
በያንዳንዱ የንግድ ድርጅት የሚዘረጋ የብሎክ ማናጅመንት የንግድ ክትትልና ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት ነው፡፡
ከተጠቃሚነት አንጻር በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ የንግድ ባለሙያዎች፣ ህጋዊ ነጋዴዎች ፣ ሸማቾችና
ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ለተቋሙ ደንበኛ የሆኑ ሁሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

2.6. የሚጠበቅ ውጤት፤


ቢሮው ያስቀመጣቸው ግቦች፣ የግብ መለኪያዎችና ዝርዝር ተግባራት በተቀመጠላቸው የጥራት፣ የጊዜና የወጭ
መለኪያ መሠረት የያዛቸውን እቅዶች እንዲያከናውን በማድረግ በከተማ አስተዳደሩ የንግድ ህጋዊነት በማስከበር
እንዲሁም ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት በማስፈን ከንግድ ህገ-ወጥነት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ
የህጋዊ ነጋዴውንና የነዋሪውን እርጋታ ማረጋገጥ ነው፡፡

ክፍል ሁለት

2. የቃላትና የጽንሰ ሃሳቦች ማብራሪያ፤


2.1. ብሎክ ማናጅመት ማለት የንግድ ስራ ተግባራት የሚከናወኑት በሚመለከተው አካል በወጡ ህጎችና አሰራሮች
መሰረት ስለመሆኑ የንግድ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያዎች ቀጠናን መሠረት በማድረግ የክትትልና ቁጥጥር
ስራ የሚሰሩበትና በተመደቡበት ቀጠና ለሚገኙ ውጤቶችና ለሚፈጠሩ ውድቀቶች ኃላፊነትን
የሚወስዱበት አሠራር ነው፡፡
2.2 . ኦርጅናል የንግድ ስራ ፈቃድ ማለት በበጀት አመቱ የታደሰ ወይም በበጀት አመት በህጋዊ መንገድ የወጣ የንግድ
ስራ ፈቃድ ማለት ነው፣
2.3 . ዋጋ ዝርዝር ማለት ነጋዴው ለሸቀጦችና አገልግሎቶች ያስቀመጠው የመሸጫ ዋጋ ማለት ነው፡፡
2.4 . ህጋዊ ደረሰኝ ማለት ነጋዴው የገዛበት ወይም የሚሸጥበት በገቢዎችና ጉምርክ ባለስልጣን ፈቃድ የታተመ
የሽያጭ/የግዥ ደረሰኝ ማለት ነው፤
2.5 . የመስፈሪያ መሳሪያ፡- ማለት የክብደት፤ የርዝመትና የይዘት ልኬት መሣሪያ ነው፡፡

3
2.6 . የመለኪያ መሣሪያን ትክክለኝነት ማረጋገጥ /verfiction/፡- ማለት የመለኪያ መሣሪያ በሕግና በአስገዳጅ የኢትዩጵያ
ደረጃዎች የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላቱን ለማረጋገጥ የሚደረግ ምርመራን ፈትሸን ምልክት ማድረግንና የትክክለኛነት
ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መስጠትን የሚጨምር ተግባር ነው
2.7 “የንግድ ሕግ”፡- ማለት በኢትዮጵያ የወጣ የንግድ ህግ ማለት ነው

2.8 . "ሰው" ማለት ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡
2.9 . አዋጅ ፡-ማለት እንደ ሁኔታው የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 እና የንግድ ውድድርና ሸማች
ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ማለት ነው፡፡
2.10 “የንግድ ዕቃዎች”፡- ማለት ገንዘብና ገንዘብነት ካላቸው ሰነዱች በስተቀር ማናቸውም የሚገዙ
ወይም የሚሸጡ ወይም የሚከራዩ ወይም በሌላ ሁኔታ በሰዎች መካከል የንግድ ስራ የሚከናወንባቸው የሚንቀሳቀሱ እቃዎች
ማለት ነው፡፡
2.11 የፀና የንግድ ሥራ ፈቃድ” ማለት በበጀት አመቱ የተሰጠ ወይም የታደሰ ወይም በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር
980/2008 አንቀጽ 27 መሰረት ያለቅጣት የሚታደሰበት ጊዜ ያላለፈበት የንግድ ሰራ ፈቃድ ነው፤
2.12 ነጋዴ፡- ማለት ንግድን የሙያ ሥራው አድርጐ ጥቅም ለማግኘት ሲል በንግድ ሕጉ ላይ የተዘረዘሩትን ሥራዎች የሚሠራ
ወይም አገልግሎት የሚሰጥ ወይም የንግድ ሥራ ነው ተብሎ በህግ የሚወሰነውን ሥራ የሚሠራ ማንኛውም ሰው ነው፤
2.13 ሸማች፡-ማለት ለማምረት ስራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሰው የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ
ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፍጥሮ ሰው ነው፤
2.14 ተገቢ ያልሆነ የንግድ ሥራ፡- ማለት ንግድን የሚመለከት የሕግ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ማንኛውም ድርጊት ነው፣
2.15 የውጭ ኢንስፔክሽን፡- ማለት በንግድ ምዝገባና ፈቃድ እንዲሁም በንግድ አሰራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ድንጋጌ
መሰረት በንግድ መደብር /ድርጀት/ በር ለበር መጎብኘት/ኢንስፔከት ማድረግ ማለት ነው፤
2.16 የንግድ ድርጅት፡- ማለት ለንግድ ሥራ መስሪያ ለማዋል በንግድ ዋና ምዝገባ በግልጽ ተመዝግቦ የሚታወቅ የንግድ
መደብር ነው፤
2.17 የንግድ ድርጅት ጉብኝትና የፍተሻ ሰዓት፡- ማለት በውጭ ኢንስፔክሽን የንግድ ድርጅቶች የፍተሻና የጉብኝት የሚደረግብት
የመንግስት ሥራ ሰዓት ሲሆን እንዳስፈላጊነቱ በኃላፊ በሚሰጥ ፍቃድ ከመንግስት ስራ ሰዓት ውጪ የሚካሄድበትን ጊዜ
ያመለክታል፣
2.18 የንግድ ድርጅት ማሸግ/መዝጋት ማለት፡-የንግድ ሥራው የሚፈጽምበትን መደብር ሥራውን ለማስቆም መስኰቶችንና
በሮቹን በባለ ድርጅቱ እንዲዘጋ አድርጐ መቆለፉን በማረጋገጥ የመስሪያ ቤቱ ማህተም ባለበት ስለመታሸጉ የሚገልጽ ደብዳቤ
በማጣበቂያ በበሩ/ በመስኮቱ መክፈቻ ወይም መገጣጠሚያ ላይ እንደተዘጋ መለጠፍ ነው፤
2.19 ቢሮ ማለት ይህን መመሪያ ለማስፈፀም ከንግድ ቢሮ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኝ የክፍለ ከተማና ወረዳ የንግድ ጽ/ቤት
ያጠቃልላል፤
2.20 የንግድ ድርጅት ማገድ፡- ማለት የንግድ ድርጅቱ በሮችና መስኮቶች ሳይታሽጉ /ሳይዘጉ ነጋዴው ሥራውን እንዲያቆም
ፈቃዱ ለጊዜው የታገደ መሆኑን በደብዳቤ/ በጽሁፍ መግለጽ ማለት ነው፤

4
ክፍል ሶስት

የብሎክ ማናጅመን አሰራር ስርዓት

3.1 ነጋዴዉን በአድራሻዉ በብሎክ/በቀጣና/ ስርዓት መከፋፈል መረጃውን አደራጅቶ መያዝ


ሀ. ነጋዴዉ በአካባቢዉ በቀጠናዉ (በብሎክ) እንዲከፋፈልና በግልጽ እንዲለይ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ለ. በየብሎኩ የሚገኘዉ ነጋዴ ማንነት፣ ብዛት፣በአድራሻ፣ በንግድ ዘርፉ፣ በንግድ መስኩ፣ በንግድ ምዝገባና ንግድ
ፈቃዱ፣ በግብር ከፋይ መለያ ቁጥሩ መዝግቦ ለድጋፍና ክትትል ስራዎቻችን ምቹ በሚሆን መንገድ
እንዲደራጅ ይደረጋል፡
ሐ. በእያንዳንዱ ብሎክ የሚገኘዉ ነጋዴ በዚህ አግባብ ከተለየ በኋላ ከንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ቢያንስ 2
(ሁለት) ቢበዛ 3 (ሶስት) ባለሙያዎች በቋሚነት በአንድ ቀጠና ለድጋፍና ክትትል ስራዎች ባለቤት
ይመደባል፡፡
መ. ህጋዊና ህገወጥ ነጋዴዎችን የመለየት ስራ ይሰራል፤
ሠ. ህገወጥ ነጋዴዎችን እንደየጥፋታቸው በህችና በአሰራር መመሪያው መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃ
የመውሰድ እንዲሁም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከተው አካል መረጃ የማደራጀት ስራ ይሰራል፤
ረ. በብሎኩ ህጋዊ የሆኑና ለንግድ ፍትሃዊነት የበኩላቸውን አስተዋፆ የሚደርጉት ግንባር ቀደም ነጋዴዎችን
እንዲፈጠሩ ይደረጋል፣

ክፍል አራት

5
የቢሮው ተግባርና ኃላፊነት

4.1. የማዕከል ቁጥጥር ባለሙያ ተግባርና ኃላፊነት

 የብሎክ ማናጅመት የአሰራር መመሪያን የማዘጋጀት ስራ ይሰራል፤


 በመመሪያው ዙሪያ ለተመረጡ ክፍለ ከተማና ለማዕከል ባለሙያዎች ስልጠና ይሰጣል፣
 ለክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የድጋፍና ክትትል ስራ ይሰራል፣
 የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን ክፍለ ከተሞች በመለየት አሰራራቸው በማስፋት በሌሎች እንዲተገበር
ያደርጋል፤ ወደ ኋላ የቀሩ ወረዳዎችን ተከታታይ በሆነ መልኩ ይደግፋል፤ በቂ እድገት በማያሳዩት ላይ
በየደረጃው ማስተካከያ እንዲደረግ መረጃ ያስተላልፋል፤
 በብሎክ ማኔጅመንት አፈጻጸም የተሸለ ውጤት ላስመዘገቡ ባለሙያዎች እውቅና ይሰጣል፤
 የከተማ አስተዳደሩን የነጋዴ መረጃ አደራጅቶ ይይዛል፤

4.2. የክፍለ ከተማ ቁጥጥር ባለሙያ ተግባርና ኃላፊነት

 በመመሪያው ዙሪያ ለወረዳና ለክፍለ ከተማ ባለሙዎች ስልጠና ይሰጣል፣


 በወረዳና በቀጠናዎች በመገኘት የድጋፍና ክትትል ስራ በመስራት የብሎክ ማኔጅመንት ተግባር
በመመሪያው መሰረት እየተፈጸመ መሆኑን ያረጋግጣል፤
 የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን ወረዳዎች በመለየት አሰራራቸው እንዲሰፋ እና ወደ ኋላ የቀሩ ወረዳዎችን
ተከታታይ በሆነ መልኩ ይደግፋል፤ በቂ እድገት በማያሳዩት ላይ በየደረጃው ማስተካከያ እንዲደረግ መረጃ
ያስተላልፋል፤
 በክፍለ ከተማው ውስጥ ብሎክ ማኔጅመንት አፈጻጸም የተሸለ ውጤት ላስመዘገቡ ባለሙያዎች እውቅና
ይሰጣል፤
 በየ 1 ወሩ በክፍለ ከተማ ደረጃ የአካል ግምገማ ስራ ይሰራል፣
 የክፍለ ከተማውን የነጋዴ መረጃ አደራጅቶ የመያዝ
4.3 . የወረዳ ቁጥጥር ባለሙያ ተግባርና ኃላፊነት
 የነጋዴዉን መረጃ በልዩ መለያ ኮድ ለይቶ የተደራጀ መረጃ በመያዝ በየብሎኩ የክትልና ቁጥጥር ስራ
ይሰራል፤

6
 በቀጠናው የሚገኝ የነጋዴ ብዛት በመለየት በቋሚ በባህር በመመዝገብ በየእለቱ እያንዳንዱ የበር ከበር
የክትልና ቁጥጥር ስራ በመስራት በእለት መመዝገቢያ ቅፅ ይመዘግባል፤
 በየእለቱ በሚፈጽመው የክትትልና ቁጥጥር ተግባር በንግድ ህጎችና አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና
ማንዋሎች ውስጥ የተቀመጡ የነጋዴ ግዴታዎች በተገቢው መከበራቸውን ያረጋግጣል፡፡
 በእየለቱ የራሱን እቅድ በማዘጋጀት በሚፈጽመው ተግባር በኃላፊነት በያዘው ብሎክ/ቀጠና ለሚፈጠር
የተባባሰ የንግድ ህገ-ወጥነት ኃላፊነት ይወስዳል፡፡
4.4 መብትና ግዴታ
4.4.1 ቁጥጥር ባለሙያ ግዴታ

በኃላፊነት በሚከታተለው ብሎክ ውስጥ

 የሚገኙ ነጋዴዎች መረጃ በልዩ መለያ ኮድ ለይቶ የተደራጀ መረጃ መያዝ፤


 ያለንግድ ስራ ፍቃድ/ባልጸና ንግድ ስራ ፍቃድ የንግድ ስራ የሚያካሂድ ነጋዴ እንዳይኖር የማድረግ፣
 የንግድ ድርጅቶች የመሸጫ ዋጋ በንግድ መደበር ላይ በሚታይ ቦታ እንዲለጠፍ የማድረግ
 ግብይቶች በደረሰኝ እንዲካሄዱ የማድረግ፣
 በጣት አሻራ የተረጋገጠ የግብር ከፋይ መለያ ስለመኖሩ ማረጋገጥ፣
 የንግድ ምዝገባና ንግድ ስራ ፍቃድ ሰርተፊኬት በሚታይ ቦታ እንዲሰቀል ማደረግ፣
 የንግድ ድርጅቱ ፈቃድ ባወጣበት ቦታ( አድራሻ) እና ባስመዘገበው የንግድ ስራ መስክ መሰረት የንግድ ስራ

እንዲከናውን የማድረግ፣
 በንግድ ስራ ፈቃድና በንግድ ምዝገባ ላይ ባስመዘገበው የንግድ ስም መሰረት በንግድ ድርጅቱ መጠሪያና
በንግድ መደበሩ የሚለጠፈው (የሚፃፈው) ስም ተመሳሳይ እንዲሆን የማድረግ፣
 በተለያዩ የንግድ አዋጆችና የአሰራር መመሪያ ውጭ የንግድ እቃዎች እንዳይከማቹ የማድረግ
 ማንኛውም ነጋዴ ትክለኛነቱ በተረጋገጠ ሚዛንና የመስፈሪያ መሳሪያ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ፤
 በመሰረታዊ ሸቀጥ መመሪያው የተቀመጡ የድጎማ ምርቶች ስርጭት አሰራሮች እየተከበሩ መሆኑን
ማረጋገጥ፤

4.4.2. ቁጥጥር ባለሙያ መብት


 ለብሎክ ማናጅመንት የሚስፈልጉ ቁሳቁሶች እንዲሟሉለት የመጠየቅ፣ ስልጠናና ድጋፍ ማግኘት፣
4.4.3 . የነጋዴ ግዴታ

7
 ማንኛውም ነጋዴ የመሸጫ ዋጋ በንግድ መደበር ላይ በሚታይ ቦታ የዋጋ ዝርዝር የመለጠፍ፣
 ማንኛውም ነጋዴ የገዙበትና የሚሸጥበት ደረሰኝ የመያዝና የመስጠት ፣
 ማንኛውም ነጋዴ በጣት አሻራ የተረጋገጠ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የመያዝ፣
 ማንኛውም ነጋዴ በንግድ ምዝገባ ሰርተፊኬት የመያዝ፣
 ማንኛውም ነጋዴ ለተሰማራበት የንግድ ስራ መስክ የፀና የንግድ ስራ ፈቃድ የመያዝ፣

 ማንኛውም ነጋዴ አድራሻ እና ባስመዘገበው የንግድ ስራ መስክ መሰረት የንግድ ስራ ማከናወን፣


 ማንኛውም ነጋዴ የፀና የንግድ ሰራ ፈቃዱን በንግድ መደበሩ ኦሪጅናል በንግድ መደበሩ በሚታይ ቦታ
የመስቀል፣
 ማንኛውም ነጋዴ ከንግድ አዋጆችና የአሰራር መመሪያ ውጭ የንግድ እቃዎች ያለማከማቸት
 ትክለኛነቱ በተረጋገጠ ሚዛን አገልግሎት የመስጠት፣
4.4.4 የነጋዴ መብት
 የንግድ አዋጅና መመሪያ አስካሟላ ድረስ የንግድ ምዝገባ፣ የንግድ ስራ ፈቃድ ሰርቲፊኬት የማግኘት፣ፈቃዱን
የማደስ፣ ፈቃዱን እንዲሰረዝለት የመጠየቅ፣ምትክ የማግኘት መብት ይኖረዋል፣
4.5 በብሎክ ማናጅመት የአሰራር ስርዓት ህጋዊ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የንግድ አዋጅና መመሪያን ተጥሷል
የሚባለውና በአዋጅ ቁጥር 980/2008 ፣1150/2011 መሰረት የሚወሰድ የእርምጃ፣
4.5.1 የጥፋት አይነት
ሀ. የፀና የንግድ ስራ ፈቃድ ሳይኖረው በንግድ ስራ ተሰማርቶ ከተገኘ፣
ለ. ሀሰተኛ መረጃ በማቅረብ በንግድ ምዝገባ የተመዘገበ ወይም የንግድ ስሙን ያስመዘገበ ወይም የንግድ
ፍቃድ የምስክር ወረቀት ያወጣ ወይም የንግድ ምዝገባውን ወይም የንግድ ፍቃዱን የምስክር ወረቀት
ያሳደሰ እንደሆነ፣
ሐ. የሕጉን፣አዋጅን ወይም ደንቡን ድንጋጌዎች ወይም ሚኒስትሩ የሚያወጣውን የህዝብ ማስታወቂያ
ተላልፎ የተገኘ እንደሆነ፣
መ. ከአስመዘገበው የንግድ ስራ ፈቃድ አድራሻና መስክ ሲነግድ ካልተገኘ፣
ሠ. የገዛበትና የሚሸጥበት ህጋዊ ደረሰኝ የማይዝና የማሰጥ ከሆነ፣
ረ. ትክለኛ ባልሆነ የሚዛንና መስፈሪያ መሳሪያዎች አገልግሎት ሲሰጥ ከተገኘ፣
ሰ. ከንግድ ህግና መመሪያ ውጭ ምርት አከማችቶ (ከዝኖ) ከተገኘ፣
ሸ. የንግድ ድርጅቱን መለያ ኮድ በሚታይ ቦታ ለጥፎ ካልተገኘ፣
ቀ. የሚሸጥበት የዋጋ ዝርዝር በሚታይ ቦታ ለጥፎ ካልተገኘ፣
ተ. በብሎክ ተለይቶ የተሰጠው የቁጥጥር ባለሙያ በተመደበበት ብሎክ የፀና የንግድ ስራ ፈቃድ ሳይኖረው በንግድ
ስራ ተሰማርቶ ህገወጥ ነጋዴ ከተገኘበት፣ከአድራሻ ውጭ፣ ከመስክ ውጭ፣ዋጋ ዝርዝር ሳይለጥፍ፣ የገዛበት

8
ደረሰኝ ሳይዝ፣ደረሰኝ መስጠት የሚጠበቅበት ሆኖ ሳለ ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ፣ ኦሬጅናል የንግድ ስራ
ፈቃድ ሳይሰቅል ከተገኘ፣መለያ ኮድ ሳይለጥፍ የተገኘ ከሆነ፣
4.5.2 እርምጃ አወሳሰድ በተመለከተ
ሀ. በተራ ቁጥር 4.5.1 ከሀ እስከ ቀ ድርሰ የተጠቀሱትን የጥፋት አይነቶች ፣
 ጥፋት የፈፀመ ማንኛውም ነጋዴ በንግድ አዋጅ ቁጥር 980/2008፣ በንግድ ምዝገና ፈቃድ ማሻሻ አዋጅ ቁጥር
1150 /2011፣ በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006፣ በመሰረታዊ ሸቀጥ ስርጭት መመሪያ
እንዲሁም በንግድ ስርዓት ማስከበር የአሰራር ማንዋል 2011 ዓ.ም ላይ የተቀመጡ አስተዳደራዊ የእርምጃ ተፈፃሚ
ይሆናል፣
 እንደ አስፈላጊነቱና የጥፋቱ መጠን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ስራ ይሰራል፤
ለ. በብሎክ ተለይቶ የተሰጠው የቁጥጥር ባለሙያ በተመደበበት ብሎክ በተራ ቁጥጥር 4.5.1 ተ
የተጠቀሱ ጥፋቶች ሲገኙ
 ለመጀመሪያ ጊዜ በተመደበበት ቀጠና የተባባሰ የንግድ ህገ-ወጥነት የተገኘበት ባለሙያ በፅ/ቤት ኃላፊው

ባለበት በክትትልና ቁጥጥር ሂደት ጥፋቱን ያገኘው አካል ቃለ-ጉባኤ አስይዞ እንዲገመገም በማድረግ

የቃል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤

 በተመደበበት ቀጠና የተባባሰ ህገ-ወጥነት የሚገኝበት ባለሙያ ሁኔታው ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ የመጀመሪያ

ጊዜ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣

 በተመደበበት ቀጠና የተባባሰ ህገ-ወጥነት የሚታይበት ባለሙያ ሁኔታው ለሶስተኛ ጊዜ ከሆነ በዲስፕሊን
እንዲጠየቅ ይደረጋል፡፡

4.6 በተወሰደው እርምጃ ቅሬታ ስለማቅረብ

ሀ. በዚህ መመሪያ በሚሸፈን ማናቸውም ጉዳይ በሚሰጡ ውሳኔዎች ቅሬታ ያለው ማንኛውም አካል ቅሬታውን
በ 10 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል፡፡

ለ. የበየደረጃው በሚገኝ የንግድ የንግድ ተቋም የበላይ ኃላፊ የቀረበውን አቤቱታ ሰምቶ በ 7 ቀናት ውስጥ
ውሳኔውን ለአመልካቹ በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፤

9
ክፍል አምስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

5.1 ቅጣት
ይህን መመሪያ የጣሰ ማንኛዉም ግለሰብ ወይም ድርጅት በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008
እና በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ተከልክለው በሚገኙ ጉዳዮች በወንጅል
ተጠያቂ ይሆናል፡፡
5.2 የመተባበር ግዴታ
ማንኛውም ሰዉ ሆነ ድርጅት ይህንን መመሪያ በማክበርና በማስከበር ረገድ የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡
5.3 መመሪያዉን ስለማሻሻል
ይህንን መመሪያ ቢሮዉ እንደአስፈላጊነቱ ሊያሻሽለዉ ይችላል፡፡
5.4 መመሪያዉ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ ረቂቅ መመሪያ በቢሮው ከፀደቀ ቀን ጀምሮ የሚፀና ይሆናል፡፡

10
1

You might also like