You are on page 1of 28

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የከተማ ልማትና

ቤቶች ሚኒስቴር

የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ

የመስሪያና መሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት የቦታ ዝግጅት፣ ዲዛይን፣ ግንባታ እና አስተዳዳር ሞዴል መመሪያ ቁጥር ------/2010 ዓ.ም

(ተሻሽሎ የቀረበ)

ግንቦት/2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መግቢያ

በጥቃቅን አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ መሰረት የማምረቻና መሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት
ልማት፣አጠቃቀምና አስተዳዳር የኢንተርፕራይዞችን የደረጃ ዕድገት እና የተሻሻለውን የኤጀንሲውን ተልዕኮ ታሳቢ
ያደረገ ወጥነት ያለው ሞዴል መመሪያ ማዘጋጀት በማስፈለጉ፣

በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ እና ከአቅም ውስንነት የተነሳ ለሁሉም
ኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልገውን የማምረቻና መሸጫ ሽድናየገበያ ማዕከላት ሙሉ በሙሉ ለማቅረብ የማይቻል
በመሆኑ ያለውን ውስን ሃብትና አቅርቦት ከኢንተርፕራይዞቹ የስራ መስክና ቁጥር አንጻር በማጣጣም ሳይባክንና
ተገቢ ላልሆነ ተግባር ሳይውል በጥንቃቄና በቁጠባ መጠቀም ስለሚገባ፣

በፌዴራል ደረጃ የተዘጋጀውን ይህን ሞዴል መመሪያ መነሻ በማድረግ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከራሳቸው
ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ፣ አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ የሆነ ሞዴል መመሪያ
ለማዘጋጀት እንዲችሉ በኤጀንሲው የማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 374/2008 አንቀጽ 14 መሠረት ይህ የማምረቻና
የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት የቦታ ዝግጅት፣ ዲዛይን፣ ግንባታ፣ አጠቃቀም እና አስተዳዳር ሞዴል መመሪያ
ተዘጋጅቷል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1. አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ “የተሻሻለ የማምረቻና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት የቦታ ዝግጅት፣ ዲዛይን፣ ግንባታ፣
አጠቃቀም እና አስተዳደር ሞዴል መመሪያ ቁጥር ---------2010›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
1
2. ትርጓሜ

የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው እስካልሆነ ድረስ በዚህ መመሪያ ውስጥ፣

1) “ኤጀንሲ” ማለት በፌደራል ደረጃ የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ስራዎችን
እንዲያስተባብር እንዲደግፍና እንዲከታታል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 374/2008 መሰረት
የተቋቋመ መንግሽታ ተቋም ነው::

2) "የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ" ማለት የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሕጋዊነትን
ለማስፈን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ የመንግስታዊ
ድጋፎችና አገልግሎቶች በተቀናጀ መልኩ ከአንድ ስፍራ በአንድ አስተባባሪ አካል ሥር ካሉ አካላት
የሚያገኙበት አደረጃጀት ነው፡፡

3) “ከተማ” ማለት ማዘጋጃ ቤት የተቋቋመበት ወይም ሁለት ሺህ እና ከዚህ በላይ የሕዝብ ቁጥር ያለውና ከዚህ
ውስጥ ሃምሳ በመቶ የሚሆነው የነዋሪው ሕዝብ ከግብርና ውጭ በሆነ ሥራ የተሰማራ ሆኖ የሚኖርበት
አካባቢ ነው፡፡

4) “የክልል ኤጀንሲ“ ማለት በየክልሉ የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ስራዎችን የሚመራ
መንግስታዊ ተቋም ማለት ነው::

5) “የክልል ቢሮ“ ማለት በየክልሉ የከተሞች ልማትና ቤቶች ስራዎችን የሚደግፍና የሚያስተባብር መንግስታዊ
ተቋም ማለት ነው::

6) “የገበያ ማእከል” ማለት በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና በሌሎች አምራችና አገልግሎት ሰጪዎች
ምርቶቻቸውና አገልግሎታቸው በብዛት ለሽያጭ የሚቀርቡበት የመገበያያ ህንፃ ነው፡፡

7) “ሼድ” ማለት እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በተዘጋጀው ዲዛይን መሰረት የሚሰራና በቋሚነት ወይም
ለተወሰነ ጊዜ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምርት ማምረቻና መሸጫ የሚያገለግል ግንባታ ነው፡፡

8) “የኢንዱስትሪ ዞን” ማለት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከክላስተር ማዕከላቱ የቆይታ ጊዜያቸውን
አጠናቀው ሲወጡ በሊዝ መነሻ ዋጋ መሬት ወስደው በዘላቂነት የራሳቸውን ግንባታ በማካሄድ የሚጠቀሙበት
በመንግሥት መሰረተ ልማት ለምቶ የሚተላለፍ ቦታ ነው፡፡

9) “የኢንዱስትሪ ብክለት” ማለት በማምረትና አገልግሎት በመስጠት ሂደት ጥቃቅንና አነስተኛ


ኢንተርፕራይዞች በክላስተር ማዕከላቱ አካባቢ ለሰው ልጅ አመቺ ያልሆነና ለጤና ጠንቅ የሆነ ቆሻሻን
መፍጠር ነው፡፡

2
10) ”ጠቅላላ ካፒታል” ማለት ህንፃን ሳይጨምር ከኢንተርፕራይዙ ጠቅላላ የቢዝነሱ ሀብት ላይ ዕዳው ተቀንሶ
የሚገኝው ካፒታል ማለት ነው፡፡

11) ”ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ” ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞች
ጨምሮ እስከ አምስት ሰዎች ቀጥሮ የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር
በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50,000 (ሃምሳ ሺህ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100,000 (አንድ መቶ ሺህ)
ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው:፡

12) ”አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ” ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፣የቤተሰቡን አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞችን


ጨምሮ ከ 6 እስከ 30 ሰዎች የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታል መጠን ሕንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ
ከብር 50,001 (ሃምሳ ሺህ አንድ) እስከ 500,000 (አምስት መቶ ሽህ) ወይም በከተማ ግብርና፣ በባህላዊ
ማዕድን ማምረትና በግንባታ ዘርፍ ከብር 100,001 (አንድ መቶ ሺህ አንድ) እስከ 1.5 ሚሊዮን ያልበለጠ
ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡

13) “የኢንተርፕራይዝ ደረጃ ሽግግር” ማለት አንድ የኢንተርፕራይዝ ባለቤት የዕድገት ደረጃ የሚሰጠውን ድጋፍ
ተጠቅሞ በገበያ ላይ በዋጋ፣ በጥራትና በአቅርቦት ተወዳዳሪ ሆኖ የቀጣይ የዕድገት ደረጃ የሽግግር
መስፈርቶቹን በማሟላት መሸጋገር ሲችል ነው::

14) “የምሥረታ/ጀማሪ ደረጃ” ማለት ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመመሥረት ፍላጎት ያላቸው
ሰዎች እና ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በየደረጃው የሚጠበቅባቸውን ትምህርት በማጠናቀቅና በንግድ ህጉ
መሰረት ተደራጅተው የራሳቸውን ቁጠባና ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ብድር በመውሰድ ወደ ሥራ
የገቡትን የሚያካትት ነው:: የምሥረታ /ጀማሪ ደረጃ ኢንተርፕራይዝ ሕጋዊ አቋም ይዞ የማምረትና
አገልግሎት የመስጠት ተግባር የሚጀምርበት ነው::

15) “የታዳጊ/መስፋፋት ደረጃ” ማለት አንድ ኢንተርፕራይዝ የሚሰጠውን ድጋፍ ተጠቅሞ በገበያ ላይ በዋጋ፣
በጥራትና በአቅርቦት ተወዳዳሪ ሲሆንና ትርፋማነቱ በቀጣይነት ሲረጋገጥ ነው:: በዚህ ደረጃ ያለ
ኢንተርፕራይዝ በምሥረታ ደረጃ ከነበረው ቀጥሮ የሚያሠራው የሰው ኃይል ቁጥርና የጠቅላላ ሀብት መጠን
ዕድገት ይኖረዋል:: በተጨማሪም ኢንተርፕራይዙ የሂሳብ አያያዝ ሥርዓት የሚጠቀም ይሆናል::

16) “የመብቃት ደረጃ” ማለት አንድ ኢንተርፕራይዝ የሚሰጠውን ድጋፍ ተጠቅሞ በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና
ትርፋማ ሆኖ የገበያ ድርሻውን ለማሳደግ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በሥራ ላይ ካዋለና ለዘርፉ የተቀመጠውን
ትርጓሜ መሥፈርት ሲያሟላና ወደ ታዳጊ መካከለኛ ሲሸጋገር ወይንም በአለበት ደረጃ ጥቃቅን እና አነስተኛ
ኢንተርፕራይዝ በመሆን በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና ትርፋማ ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን ነው::

17) “ታዳጊ መካከለኛ ደረጃ” ማለት ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተቀመጠውን የሰው ሃይልና ጠቅላላ ካፒታል
መጠን የመብቃት የዕድገት ደረጃ በማለፍ ወደ ኩባንያ ደረጃ የተሸጋገረ የኢንተርፕራይዝ የዕድገት ደረጃ ነው::

3
3. የተፈጻሚነት ወሰን

ይህ ሞዴል መመሪያ በኢትዮጵያ ከተሞች በሚገኙ የከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ


ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

4. ዓላማ

የጥቃቅንና እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ምቹ የሆኑ የማምረቻና የመሸጫ


ሼዶችን እና የገበያ ማዕከላት በመገንባት እንደየእድገት ደረጃቸው በተመጣጣኝ ኪራይ በማቅረብ፣
የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን አጠቃቀም ወጥ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት በማዘጋጀት
ኢንተርፕራይዞች በገበያ ላይ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

5. መርሆዎች

1) የመስሪያና መሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ግንባታ የኢንተርፕራይዞቹን ፍላጎትና የገበያ ሁኔታ የተከተለ
መሆኑን ማረጋገጥ፣

2) የመስሪያና መሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ግንባታ ደረጃውን የጠበቀ፣ለስራ አመቺና ከብክለት ነጻ የሆነ
አካባቢ መፍጠር፣

3) የማምረቻ፣ የመሸጫና የገበያ ማዕከላቱን ግልጽነትንና ተጠያቂነትን እንዲሁም የተጠቃሚዎችን ተሳትፎ


ባረጋገጠ መልኩ ማስተላለፍ፣

4) የማምረቻ፣የመሸጫና የገበያ ማዕከላቱን በተመጣጣኝ የኪራይ ዋጋ ማቅረብ፣

5) የማምረቻ፣የመሸጫና የገበያ የድጋፍ አገልግሎት አሰጣጡ ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ለተሰማሩ
ኢንተርፕራይዞች እና የእድገት ደረጃቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማቅረብ፣

6) የሴቶችን፣ ወጣቶችን እና አካል ጉዳተኞች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡

ክፍል ሁለት

የማምረቻ፣መሸጫና የገበያ ማዕከላት የቦታ ዝግጅት፣ ዲዛይንና ግንባታ ስታንዳርድ

6. የማምረቻና መሸጫ የሼድ ክላስተር የቦታ ዝግጅት

1) በከተማው ውስጥ የከተማውን ነባራዊ ሁኔታ እና ፕላን መሰረት የሳይት መረጣ ይከናወናል፡፡

ሀ) በከተማው ፕላን መሠረት ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎች መመላከታቸውን
ማረጋገጥ፤
ለ) ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተመላከተው የማምረቻና የመሸጫ ቦታ የኢንተርፕራይዞችን የወደፊት
ዕድገት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ማረጋገጥ፤

4
ሐ) በከተማው ፕላን መሠረት ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከተመደበው የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ምን ያህሉ
ለዚሁ ተግባር በጥቅም ላይ እንደዋለና ቀሪው ቦታ በቂ መሆኑን ማረጋገጥ፤
መ) በከተማው ፕላን መሠረት ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከተመደበው የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ውስጥ
ቅድሚያ ግንባታ የሚደረግባቸውን መለየት፡፡
ረ) የገበያና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ምቹነት ከመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚመጋገቡ፣ ትስስርና ቁርኝት
ሊፈጥር የሚችሉበት ቦታ በኢንዱስትሪ ዞን አካባቢ ይመረጣል፡፡
ሰ) በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና የመሸጫ ቦታ በኢንዱስትሪ ዞን መካከል ያለውን ርቀትና የመሠረተ
ልማት አቅርቦት የተሟላ መሆኑን ማረጋገጥ፤
ሸ) የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች ውስጥ የሚገቡ ኢንተርፕራይዞች በኢንዱስትሪ ዞን
ውስጥ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ስብጥርና ዓይነት ጋር መመጋገቡንና መተሳሰሩን ማረጋገጥ፡፡

2) የሚመረጠው ቦታ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ አመቺ የሆነና የረዥም ጊዜ ዕቅድና የማስፋፊያ

ግንባታዎችን ታሳቢ ማድረግ፤

ሀ) የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችና የገበያ ማእከላት በክልልና በፌደራል ደረጃ
ከሚገነቡ ከፍተኛ የባቡርና የዋና ዋና መንገዶች ግንባታዎች ጋር ያለውን ትስስር በዝርዝር ማመላከት፤
ለ) የኢንተርፕራይዞች የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች እና የገበያ ማዕከላት በከተማ ፕላኑ የተከለለው ቦታ በከተማው
ውስጥ ለሌሎች አገልግሎቶች ከሚውሉ ቦታዎች ጋር ያለውን ትስስርና ተመጋጋቢነት በውል መለየትና ማስቀመጥ፤
ሐ) ለኢንተርፕራይዞች የማምረት ተግባር የሚሆን በቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ አቅርቦት በአካባቢው
መኖሩን ማረጋገጥ፤

3) የቦታው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትናን ስራዎች እንዲመራ በተቋቋመ ተቋም
ስም ተዘጋጅቶ ይሰጣል፡፡

7. የማምረቻና መሸጫ ሼዶች ዲዛይንና ስታንዳርድ

1) የማምረቻና መሸጫ ሼዶች ወጥና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀውን ስታንዳርድ ዲዛይን መነሻ ያደረገ ዲዛይን በክልሉ
የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ይዘጋጃል፡፡

ሀ) የከተማው የመሬት አስተዳደርና የምህንድስና ባለሙያዎች ሰለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ዓይነት፣


ስብጥርና የምርት ሂደት ግንዛቤ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
ለ) በከተሞች የሚገነቡ የማምረቻና መሸጫ ሼዶች ዲዛይን የኢንተርፕራይዞችን የምርት ሂደትና የመሣሪያዎች
አቀማመጥ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡
ሐ) የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ/የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን የሚመራ ተቋም ከተሞች በሀገር አቀፍ
ደረጃ በሚዘጋጀው ሞዴል ስታንዳርድ ዲዛይን መሠረት የማምረቻና መሸጫ ሼዶች እንዲከተሉ ድጋፍ ማድረግ፤

2) የማዕከሉ ዲዛይንና ስታንዳርድ የማምረቻ ወርክሾፖችን፣ የሰራተኞች ንፅህና መጠበቂያ ክፍሎች፣ የህፃናት ማቆያ፣
ማስተባበርያ ቢሮ፣ የጥሬ እቃ ማከማቻ መጋዘኖች፣ ምርት ማሳያና መሸጫ ክፍሎችን፣ ፓርኪንግ፣ መረጃ ማዕከል፣

5
የስልጠና ቦታ፣ የምግብና መዝናኛ አገልግሎት ክፍሎች፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ፣ ፓወር ሃውስና የመሳሰሉትን
በዋነኝነት የያዘና የስራ ዘርፎችን ባህርያት ታሳቢ ያደረገ አንድ ወጥ የሆነ ዲዛይን ማዘጋጀት፤

3) የሚዘጋጁ ዲዛይኖች የከተሞችን የእድገት ደረጃ ታሳቢ ያደረጉ ይሆናል፣

4) የክላስተር አደረጃጀት ዲዛይን ሊያሟላቸው የሚገቡ የጋራ መገልገያዎች እንደ መብራት፣ ውሀ፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን
ቴክኖሎጂ አመቺነት ታሳቢ በማድረግ ይዘጋጃል፣

5) የመሰረተ ልማት አውታሮች ዲዛይን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ ይዘጋጃሉ፡፡

ሀ) ለሼዶች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዲዛይን ሲዘጋጅ ምርትና ጥሬ ዕቃ ለመጫንና ለማራገፍ የሚያመች ስፋት እና
የግንባታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ይዘጋጃል፤
ለ) የኤሌክትሪክ፣ የውኃና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ዲዛይን በሼዶች ውስጥ የሚገቡ ኢንተርፕራይዞችን የምርት
ሂደትን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ይደረጋል፤

6) የግንባታ ሰፔስፊኬሽን ሲዘጋጅ የስራ ዘርፉን ባህሪና የአካባቢውን ማቴሪያል ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት ያደረገ ይሆናል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ የሥራ ዘርፎች የምርቶችን በቀላሉ የመበላሸት ባህሪይ (ለምግብ ማቀነባበር የሚሆን ግንባታ ግድግዳው
ብሎኬት የሆነ፣ ለእንጨትና ብረታ ብረት ግድግዳው ቆርቆሮ ሆኖ ከአናቱ በቂ አየር ማስገቢያ ያለው…..) ታሳቢ ያደረገ
የማቴሪያል ስፔስፊኬሽን መዘጋጀቱን ማረጋገጥ፡፡

8. የገበያ ማዕከላት የቦታ ዝግጅት

1) በከተማው ፕላን መሰረት የከተማውን የዕድገት ደረጃ ታሳቢ፣ ያደረገ ለገበያ ምቹ እና ለተጠቃሚው ህብረተሰብ
ተደራሽ የሆኑ ቦታዎችን መምረጥ፤ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቦታ እንደምርቶቻቸውና አገልግሎታቸው
ዓይነት የሚመረጠው የገበያ ማዕከላት ቦታ ከሌሎች የከተማው የመኖሪያ፣ የንግድና የኢንዱስትሪ አካባቢዎች ጋር ተያያዥነት
እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

ሀ) ለገበያ ማዕከላት የሚመረጡት ቦታዎች ለሸማቹ ለትራንስፖርት አመቺ የሆኑና ከከተማው የዕድገት ማዕከል ቢያንስ
ከሁለተኛ መስመር ያልራቁ መሆኑን ማረጋገጥ፤
ለ) የገበያ ማዕከላቱ የቦታ ስፋት ብዛት ያላቸውን የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሊይዝ እንደሚችል ማረጋገጥ፤

2) እንደ ከተሞች እድገት ደረጃ ከተማውን ያማከሉ ከአንድ በላይ የገበያ ማእከላት ግንባታ ቦታ
ሊዘጋጅ ይችላል፣
ሀ) ከአንድ በላይ የገበያ ማዕከላት ግንባታ ቦታ ሲዘጋጅ በቂ የግብይት እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚችል ማረጋገጥና በገበያ
ቦታዎቹ መካከል ትስስርና መመጋገብ መኖሩን ማረጋገጥ፣
ለ) የከተማውን የእድገት ማዕከላት ታሳቢ በማድረግ በቅርብ ርቀት የገበያ ማዕከላቱን ቦታ ማዘጋጀት፣

3) የቦታው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ስም ተዘጋጅቶ ይሰጣል፡፡

4) ሰፋፊ ቦታ ለሚያስፈልጋቸው ከጤንነትና ደህነት ጋር የተያያዙ ምርቶችንና አገልግሎቶቸን

6
ለሚሰጡ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ማዕከላት ለማደረጀት

አስፈላጊ ቦታዎችን

ሀ) በከተማው አማካይ ቦታ ላይ በቁጥር ብዛት ያላቸውን ቦታዎች ለአትክልትና ፍራፍሬ፣ ለስጋ፣ ለዓሳ መሸጫ
የሚሆኑ ቦታዎችን ይለያል፣
ለ) በከተማው አማካይ ቦታ ላይ በቁጥር ብዛት ያላቸውን ቦታዎች የእህልና የጥራጥሬ እንዲሁም እሴት
የተጨመረባቸው የደረቅ ምግቦች የሚሆኑ ቦታዎች ይለያሉ፤

5) በክላስተር መሰባሰብ የማይችሉና ለዕለት ከዕለት ፍጆታ የሚሆኑ ምርትና አገልግሎቶች የሚያቀርቡ በጋራ
የመኖሪያ ቤቶች አካባቢዎች የመሸጫ ቦታዎችን ይዘጋጃል፤

6) በማህበር፣ በግል እና የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ሲሰሩ የምርትና አገልግሎቶች የሚቀርብባቸው ሱቆች፣ ሱፐር
ማርኬት፣ የውበት ሳሎኖች፣ የልብስ ንጽሕና መስጫ፣ የጽሕፈት መሣሪያ መደብሮች፣ የባልትና ሱቆች፣ ዳቦ
ቤቶች፣ ግሮሰሪዎች፣ ፎቶ ስቱዲዎች፣ የመድኃኒት መደብር እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎቶችን
ታሳቢ ያደረገ ቦታ ይዘጋጃል፡፡

9. የገበያ ማእከላት ዲዛይንና ስታንዳርድ

1) የማእከላት ዲዛይን የከተማውን የእድገት ደረጃ ታሳቢ አድርጎ ከ G+0 ጀምሮ የሚዘጋጅ ይሆናል፣

2) ማእከሉ በውስጡ የሚይዛቸው አገልግሎቶች የመጸዳጃ ቤቶች፣ የኢንተርኔት ካፌ፣ፓርኪንግ ቦታ፣ ቢሮ እና የህፃናት ማቆያ
የሚያጠቃልል መሆን ይኖርበታል፣

3) የገበያ ማእከል ዲዛይን ሲዘጋጅ ቦታ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ታሳቢ መሆን አለበት፡፡ ሆኖም ሰፋፊ የመሸጫ

ቦታ ለሚጠይቁ የንግድ አይነቶች በክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ/የክልሉን የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን በሚመራ
ተቋም በተለየ ሁኔታ ይወሰናል፤

4) ለገበያ አመቺ ባልሆኑና ከከተማ ወጣ ባለ ሥፍራ የማምረቻ ክላስተሮች ምርቶችን በመረከብ በቅብብሎሸ

የሚሰሩ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው የሚሰሩበት የገበያ ማእከላት ይዘጋጃሉ፡፡ እነዚህ ማዕከላት በአንድ ሥፍራ ወይንም
እንደ አስፈላጊነቱ ተጠቃሚው በቀላሉ ሊገለገልባቸው ይችላል ተብሎ በሚታመንባቸው ከአንድ በላይ ቦታዎች ላይ ሊገነቡ
የሚያስችል ዲዛይንና ስታንዳርድ ይዘጋጃል፡፡

10. የማምረቻና የመሸጫ ገበያ ማዕከላት ግንባታ

1) ለማምረቻና መሸጫና ገበያ ማዕከላት ግንባታ የሚያስፈልገውን በጀት ከክልል መንግስት፤ለከተማው

በሚመደብ ወይም ከአንቀሳቃሾች፣ከቤተሰቦቻቸው እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚገኝ ይሆናል፤

7
ሀ) በከተሞች ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል የማምረቻ፣ የመሸጫና ገበያ ማዕከላት ልማት ግንባታን በማካተት
ትኩረት በመስጠት መገንባት፤
ለ) የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ/የክልሉን የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን የሚመራ ተቋም የማምረቻ፣ የመሸጫና
የገበያ ማዕከላት ግንባታ ዝርዝር ወጪ በማዘጋጀት በየዓመቱ ለግንባታ የሚውል በጀት በክልልና በከተሞች በመለየት
ስለሚሸፈንበት አሠራር ይዘረጋል፤
ሐ) የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ/የክልሉን የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን የሚመራ ተቋም በየዓመቱ በክልል እና
በከተሞች ለማዕከላቱ ግንባታ የሚያዘውን በጀት በማቀድ በየዓመቱ መጀመሪያ በየደረጃው እንዲያዝ ያደረጋል፤
መ) በየዓመቱ ለግንባታ የሚመደበው በጀት ከተጠቃሚዎች ከሚሰበሰብ ኪራይ፣ ከማዘጋጃ ቤቶች በጀት፣ ከአንቀሳቃሽ
ቤተሰቦች ከሌሎች ምንጮች የሚሰባሰብ ይሆናል፡፡

2) የማምረቻና መሸጫ የገበያ ማዕከላት ግንባታ በከተማው ባለቤትነት ግንባታው ይከናወናል፤

ሀ) በተለዩና በስቶክ በተያዙ ቦታዎች ላይ በቅደም ተከተል የማምረቻናየመሽጫ የገበያ ማዕከላት ግንባታ ይከናወናሉ፤
ለ) ከተማው የጨረታ ሰነድ በማዘጋጀት የግንባታ ጨረታ ያወጣል፤
ሐ) ከተማው ግንባታውን ከሚያከናወኑ በጨረታ ከተመረጡ ሥራ ተቋራጮች ጋር ውል ይዋዋላል፤
መ) ከተማው የዕለት ተዕለት የግንባታ ሥራውን የሚከታተል ሲሆን የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የሥራውን አፈፃፀም
ይገመግማል፤
ሠ) ግንባታቸው የተጠናቀቁ የማምረቻና መሸጫ የገበያ ማዕከላት በአንድ ማዕከል አገልግሎት በሥራ ላይ እንዲውሉ
ይደረጋል፡፡

3) ለገበያ ማእከል የሚሆኑ ህንጻዎችና ሼዶች ግንባታ ወጪ ቆጣቢ አሰራሮችን መጠቀም አለበት፣

ሀ) በፌደራል ደረጃ የሚዘጋጁ ወጪ ቆጣቢ ዲዛይኖችንና አሠራሮችን ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የክልሉ
ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ከተማው ሥራ ላይ ያውላል፤
ለ) ወጪ ቆጣቢ አሠራሮችን በመጠቀም የተገኘውን የወጪ ቅነሳ ዶክዩመንት በማድረግ በሌሎች ተመሳሳይ የግንባታ ሥራዎች
ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፤
ሐ) ከተሞች የወጪ ቆጣቢ አሠራሮች በሥራ ላይ ሲውሉ ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት ከነማሻሻያ ሀሳቦች ለክልሉ የከተማ
ልማትና ቤቶች ቢሮ ያስተላልፋል፡፡

4) የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ/የግንባታውን ሂደት፣ጥራትና ዲዛይን በበላይነት ይከታተላል፣ይቆጣጠራል፡፡

ሀ) የማዕከላቱ ግንባታ በየከተሞቹ ሲካሄድ በተዘጋጀው ዲዛይንና ስፔስፊኬሽን መሠረት የግንባታ ጥራት ቁጥጥር በየደረጃው
መካሄዱን መከታተል አለበት፤
ለ) በየከተሞቹ የማዕከላቱ ግንባታ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቃቸውን ያረጋግጣል፡፡

8
11. የመሰረተ ልማት አቅርቦት

ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አገልግሎት የሚገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት ደረጃውን የጠበቀ የመሰረተ ልማት
ማለትም የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የመንገድ እና የቴሌ የመሰረተ ልማቶች በዲዛይኑ ተካተው በሚመለከታቸው ተቋማት በወቅቱ
እንዲያሟሉ በጋራ ማቀድና አፈጻጻሙን በጋራ እየተገመገመ መመራት ይኖርበታል፡፡

9
ክፍል ሶስት

የተጠቃሚዎች የመመልመያ መስፈርት፣ የምልመላ ሂደት፣ የቦታ መጠን፣ የክፍያና የገቢ አሰባሰብ ሁኔታ

12. የተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች መመልመያ መስፈርት

1) በማምረቻና መሸጫ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት የሚካተቱ የስራ ዘርፎችና መስኮች

ሀ) በጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ፡-ጨርቃ ጨርቅና ስፌት (ልብስ ስፌት፣ ሽመና፣ ሹራብ ሥራ፣ የጥልፍና
ሙካሽ ሥራ፣ ማቅለምና ህትመት፣ የመሳሰሉት)፤ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች (ጫማ፣ የቆዳ አልባሳት፣
የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች፣ የመሳሰሉት)፤ የብረታ ብረትና የኢንጂነሪንግ ምርቶች (በርና መስኮት ሥራ፣
የኤሌክትሪክና ብየዳ ሥራ፣ የሽት ሜታል ሥራ፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች፣ የተሻሻሉ
ማምረቻ መሣሪያዎች፣የመሳሰሉት)፤ የእንጨት ስራዎች (የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የትምህርት መርጃ
መሣሪያዎች፣ የቀርከሃ ምርት ውጤቶች፣ ለግብርና አገልግሎት የሚወሉ ግብአቶች፣የመሳሰሉት)፤ባህላዊ
የዕደ ጥበብና የጌጣጌጥ ሥራዎች (የቀርከሃና ሰሌን፣ የከበሩ ድንጋዮችና የብር፣ የነሐስ ጌጣጌጥ ሥራ፣
የቀንድና የሽክላ ሥራ፣ የአሻንጉሊት ሥራዎች፣የመሳሰሉት)፤ በአግሮፕሮሰሲግ ስራዎች (ምግብ
ማቀነባባር፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበር ፣ ለደረቅ ምግብና የባልትና ውጤቶች)፡፡
ለ) በከተማ ግብርና ስራዎች (ዶሮ እርባታ፣ ንብ ማነብ፣ እንጉዳይ ማምረት፣ እንስሳት ማድለብ ፣ የወተት ላም
እርባታ፣ አነስተኛ አትክልት ልማት ፣ችግኝ ማፍላት)፤
ሐ) በኮንስትራክሽን ዘርፍ፡- የግንብ ድጋይ ስራ፣ ለአሸዋ ምርት፣ ለጠጠር ምርት፣ ለኮብል ስቶን ስራ፣ የደለል
ወርቅ ስራ፣ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ፣የኤሌክተሪክ ኢንስታሌሽን እና ሳኒተሪ ስራ የመሳሰሉት)፤

2) የገበያ ማዕከላት ውስጥ የሚገቡ የስራ መስኮች

በገበያ ማዕከላት ውስጥ በዋነኛነት የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎት


የሚቀርቡበት ሆኖ ለህብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች የሀገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች በተጓዳኝ
የሚቀርቡበት ይሆናል፡፡ ለአትክልትና ፍራፍሬ የሚዘጋጀው የገበያ ማዕከል ከሌሎች ምርቶች በተለየ ሥፍራ
በየአካባቢው ራሱን ችሎ የሚደራጅ ይሆናል፡፡በገበያ ማዕከላቱ የሚቀርቡ ዋና እና ንዑስ ዘርፎች የሚከተሉት
ናቸው፡፡

ሀ) የንግድ ሥራ፡- የሀገር ውስጥ ምርቶች ጅምላ ሽያጭ፣የሀገር ውስጥ ምርቶች ችርቻሮ ንግድ፣ ለጥቃቅንና
አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች፤
ለ) የአገልግሎት ዘርፍ፡- ካፌና ሬስቶራንቶች፤የቱሪስት አገልግሎት፤የውበት ሳሎን ስራዎች፤ የልብስ ንጽህና
አጠባበቅ አገልግሎት፤የኤሌክትሮኒክስና ሶፍት ዌር ልማት፤ የኢንተርኔት ካፌ፤ የጀበና ቡና ዝግጅት፤
የማከማቻ አገልግሎት፤የስራ አመራር አገልግሎት እና የጥገና ስራዎች
(1) ለዩንቨርስቲና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ቅድሚያ ይመቻችላቸዋል፤
10
(2) በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚመረቱ የምርት ውጤቶችን የሚሸጡ፤
(3) ህጋዊ ሰውነት ወይም የንግድ ፈቃድ ያላቸው፣
(4) የመንቀሳቀሻ ካፒታል ያላቸው፤
(5) የሴቶችን፣ የወጣቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ የሚከናወን ሆኖ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ
ይመቻችላቸዋል፤፡
(6) ኢነርጂና ቦታ ቆጣቢ መሣሪያዎችን በግላቸው ወይንም በጋራ በራሳቸው ገንዘብ ወይንም በብድር ገዝተው
ለመጠቀም ፈቃደኛ የሆኑ፣
(7) በብድር አመላለስ፣ በግብር አከፋፈል፣ በመልካም የንግድ ሥነ-ምግባር የሚታወቁ እና ለሌሎች አርአያ መሆን
የሚችሉ፡፡
(8) ነባር ኢንተርፕራይዞች የሂሳብ አያያዝ ስርዓት የዘረጉ (ወጪና ገቢ በአግባቡ መዝግበው የያዙ)፣
(9) የመስሪያና መሸጫ ቦታ ችግር ያለበት ፣
(10) በመመልመያ መስፈርት መሠረት ሞዴል ሆነው የተመረጡ ኢንተርፕራይዞች፡፡

13. ወደ የመስሪያ/መሸጫ ሼድ/የገበያ ማዕከላት የሚገቡ ኢንተርፕራይዞች የምልመላ ሂደት

1) የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ፈላጊ ኢንተርፕራይዞች ጥያቂያቸውን ለዚህ አላማ በተዘጋጀው የማመልከቻ ቅጽ መሰረት
በሚኖሩበት የአስተዳዳር ክልል ውስጥ ለሚገኝ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ያቀርባሉ፤

2) የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች የመስሪያ/መሸጫ ቦታ ማመልከቻ ካቀረቡ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ
መስፈርቱን የሚያሟሉትን በመለየት በደብዳቤ ለከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋሰትና ጽ/ቤት ወይም
በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናውን ስራ ለሚሰራ ተቋም በማመልከቻ በአንድ ሳምንት ውስጥ
ያሳውቃሉ፡፡

3) የከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋሰትና ጽ/ቤት ወይም በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ስራ
የሚሰራ ተቋም ከአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ የቀረበለትን የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ፈላጊ ኢንተርፕራይዞችን
ዝርዝር መረጃ የሚመለከታቸውን አካላት ባሳተፈ መልኩ በማጣራት መስፈርቱን የሚያሟሉትን ስም ዝርዝር በህዝብ
ማስታወቂያ ቦርድ ላይ ለ 5 ተከታታይ የመንግስት የስራ ቀናት አስተያየት እንዲሰጥበት ያደርጋል፡፡

4) ከላይ በአንቀፅ 14 ንውስ ቁጥር 3) መሰረት ለሚቀርብ ቅሬታ ከ 5 የስራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምላሽ መሰጠት
አለበት

5) ከላይ በአንቀፅ 14 ንውስ ቁጥር 3) እና 4) መሰረት የመስሪያ ወይም የመሸጫ ሼድ ወይም ገበያ ማዕከላት እንዲያገኙ
የተመለመሉ ኢንተርፕራይዞች በቅደም ተከተል ተለይተው በመጀመሪያ ወደ አመለከቱበት የአንድ ማዕከል አገልግሎት
መስጫ ጣቢዎች የቅሬታ ማጣሪያ ጊዜው እንዳለቀ በ 3 የስራ ቀናት ውስጥ በደብዳቤ ይላካል፡፡

6) የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ከላይ በአንቀፅ 14 ንዑስ ቁጥር 5) መሰረት በቅድም ተከተል ተመልምለው
ለሚላኩላቸው ኢንተርፕራይዞች ውል በመዋዋል ለኢንተርፕራይዞች የማስተላላፍ ስራ ይሰራሉ፡፡

11
14. ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው የመስሪያና መሸጫ ቦታ መጠን

1) ለኢንተርፕራይዞቹ የሚሰጠው የማምረቻ ወይም የመሸጫ ሼድ/የገበያ ማዕከላት የቦታ መጠን ኢንተርፕራዞቹ
እንደየተሰማሩበት የስራ መስክ፣ የስራ ስፋት፣ የአባላት ብዛት ፣የዕድገት ደረጃቸው እንደክልሎችና ከተሞች ተጨባጭ
ሁኔታ የሚለያይ ይሆናል፡፡

2) የሃብት ክፍፍሉን ፍትሃዊነት ለሚያረጋግጥ የከተማ አመራሩ በሚላከው የአሰራር ማኑዋል መሰረት መስፈርቶቸን
ለሚያሟሉ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለመስሪያና የመሸጫ አገልግሎት ከተገነቡ ሼዶች/የገበያ
ማዕከላት የሚያስፈልጋቸውን የቦታ መጠን በበጀት አመቱ መጀመሪያ ወስኖ ለከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ
እና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት/ወይም በከተማው የስራ ዕድልንና የምግብ ዋስትናን ስራ ለሚሰራ ተቋም
በደብዳቤ ያሳውቃል፡፡

3) የከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት/ወይም በከተማው የስራ ዕድልና የምግብ
ዋስትናን ስራ የሚመራው ተቋም በከተማው አመራር ለየስራ መስኮች የተወሰነውን የቦታ መጠን በስሩ
ለሚገኙት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች በደብዳቤ እንዲደርሳቸው እና የተሟላ ግንዛቤ
እንዲያዝበት ያደርጋል፡፡

4) ምንም አይነት ግንባታ መገንባት ከማይጠይቁ የስራ መስኮች ውጭ ለሚሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች
እራሳቸው ገንብተው እንዲጠቀሙበት ባዶ ቦታ በማንኛውም መንገድ አይሰጥም፤

5) ግንባታ በማይጠይቁ የስራ መስኮች ለምሳሌ በከተማ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች
በሚሰጣቸው ባዶ ቦታ ላይ ቋሚ አትክልት መትከል አይችሉም፡፡

15. የአነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ እና የታዳጊ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና መሸጫ ቦታ ድጋፍ ፍላጎት

1) በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ እና ከበቃ ጥቃቅን ወደ አነስተኛ ጀማሪ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች


በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ድጋፍ የሚደረግላቸው ይሆናል፤
2) ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጪ ከበቃ አነስተኛ ወደ ታዳጊ መካከለኛ የሚሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ወደ
ማኑፋክቸሪግ ዘርፍ በመሸጋገር በኢንዱስትሪ መንደር ወይንም በተመጣጣኝ ዋጋ በሊዝ በሚወስዱት ቦታ ላይ
በዘላቂነት የራሳቸውን ግንባታ ገንብተው መስራት የሚችሉ መሆኑን የማስገንዘብ ስራ ይሰራል፡፡
3) ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጪ ከበቃ አነስተኛ ወደ ታዳጊ መካከለኛ የሚሸጋገሩ ነገር ግን ዘርፋቸውን መቀየር
የማይፈልጉ ኢንተርፕራይዞች በአገሪቱ የንግድ አዋጅና እና ኢንቨስትመንት ህግ በሚፈቅደው መሰረት
የሚያስተናገዱ መሆኑን የማስገንዘብ ስራ ይሰራል፡፡

16. የሼድና የገበያ ማዕከላት የአገልገሎት ክፍያ አፈፃጸምና የገቢ አሰባሰብ

1) የሼድ/የገበያ ማዕከላት የቦታ ኪራይ ዋጋ መወሰኛ መሰረታዊ መስፈርቶች

12
ሀ) በእያንዳንዱ ከተማ የሚኖረው የቦታ ኪራይ ክፍያ መጠን የእያንዳንዱን ከተማ ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ በከተማ
አስተዳደሮች የውሳኔ ሀሳብ ቀርቦ የክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ወይም በክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን
የሚመራ ተቋም በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን ይሆናል፡፡
ለ) የሚወሰነው የቦታ ኪራይ መጠን የህንፃውን ጥገና፣ የመሠረት ልማት፣ የንጽሕና ወጪ፤ የወጪ መጋራት እና የወቅቱን
የአካባቢ ኪራይ ዋጋ ሁኔታ ግምት ታሳቢ ያደረገ ይሆናል፡፡
ሐ) ከላይ በሀ) እና ለ) የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ የቦታ ኪራይ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት መስፈርቶች
ይወሰናል፤-
(1).በክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ወይም በክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን የሚመራ ተቋም በክልሉ
ለከተሞች የተሰጠው የልማትና የከተማ ደረጃ፤
(2) የመሥሪያ ቦታው ከከተማው እምብርት ያለው ርቀትና በቀላሉ ለመገበያየት ያለው አመቺ ሁኔታ፣
(3) በማዕከላቱ ያሉት መሠረተ ልማቶች የመሟላት ደረጃ፣
(4) በአካባቢው ለሚሰማሩ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራዞች የትራንስፖርት አገልግሎት በቀላሉ
የማግኘት ሁኔታ፡፡

2) የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር

ሀ) የማምረቻና መሸጫ ሼድ/የገበያ ማእከላት ግንባታ በተካሄደባቸው ከተሞች ክልሉ እንደ አካባቢው
ተጨባጭ ሁኔታ አጥንቶ እያንዳንዱ የሼድ/የገበያ ማዕከል ክላስተር ያለበትን ደረጃ ሊያወጣ ይችላል፤
ለ) በአንቀጽ.14 ንዑስ አንቀጽ 1) በተቀመጡ መመዘኛዎች መሠረት ክልሉ የከተሞችን ደረጃ ለእያንዳንዱ
የከተማ ክላስተር ዝቅተኛና ከፍተኛ የኪራይ ተመን ሊያወጣ ይችላል፤
ሐ) ከተሞች እንደየ ክላስተሩ ማእከላት ተጨባጭ ሁኔታ የኪራይ ተመን አጥንቶ በማዘጋጀት ለክልሉ ከተማ
ልማትና ቤቶች ቢሮ ወይም በክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን የሚመራ ተቋም ለውሳኔ ያቀርባሉ፤
መ) የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ወይም በክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን የሚመራ ተቋም የእያንዳንዱ
ከተማ የማምረቻ፣ መሸጫና ገበያ ማዕከላት የፀደቀውን የኪራይ ተመን በየደረጃው ለሚገኙ ፋይናንስና
ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ/ጽ/ቤት ያሳውቃል፡፡

3) የክፍያ መፈጸሚያ ወቅት

ሀ) ማንኛውም ክፍያ በአንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ 2) በተዘረዘረው ተመን መሠረት በየወሩ የመጀመሪያዎቹ 5
ቀናት ብቻ ያለቅጣት ይፈጸማል፡፡
ለ) በ 5 ቀናት ውስጥ ክፍያ ያልከፈለ በእያንዳንዱ ቀን ለዘገየበት የወርሃዊ ክፍያ ቅጣት በውሉ መሠረት
ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

4) የክፍያ ሁኔታ

13
ሀ) የማምረቻና የመሸጫ ማእከላት የኪራይ ክፍያ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ተሻለ
የእድገት ደረጃ እንዲሸጋገሩ በጊዜ ገደብ የተወሰነ ተመጣጣኝ የኪራይ መጠን ይተመንላቸዋል፡፡
ለ) የኪራይ ተመኑ ለኢንተርፕራይዞች በማዕከሉ ቆይታ የሚወሰን ሲሆን በመጀመሪያ አመት 25%፣ በሁለተኛ
አመት 50%፣ በሶስተኛ አመት 75% እና በአራተኛና አምስተኛ አመት ሙሉ የኪራይ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡

5) የክፍያ አሰባሰብ

ሀ) የወሩ ኪራይ አሰባሰብ የፋይናንስ ስርአትን የተከተለ ይሆናል፡፡


ለ) የማእከላት ወርሀዊ ኪራይ በከተማው ገቢዎች ጽ/ቤት አማካይነት ይሰበሰባል፡፡

ክፍል አራት
የማምረቻና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት አስተዳደር

17. የማዕከሉ የሰው ሀይል እና የተጠሪነት ሁኔታ

1) የማምረቻ፣ መሸጫና ገበያ ክላስተር ማዕከላት ተጠሪነት ለአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ይሆናል፡፡

2) ስለማእከላቱ አጠቃቀምና አስተዳደር ድጋፍ የሚሰጡ፤ የኪራይ ክፍያ በወቅቱ መከፈሉን የሚከታተሉና
የተጠቃሚዎችን የአገልግሎት ፍላጎትና ጥያቄዎችን የሚያስተባብሩና የሚያስፈጽሙ ባለሙያዎች
ይመደባሉ፡፡ እንደ ከተማው ደረጃ እየታየ በኤጀንሲው ስር ማዕከላቱን የሚከታተልና የሚያስተዳደር የስራ ሂደት
ሊያደራጁ ይችላሉ፡፡ ዝርዝሩም ኤጀንሲው በሚያወጣው መመሪያ ይፈፀማል፡፡

3) በእያንዳንዱ ማእከላት የሚገቡ ተጠቃሚዎችን መጀመሪያ ሲገቡ የነበራቸው አጠቃላይ መረጃና ፕሮፋይል
በዳታ ቤዝ ተመዝግቦ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡

4) የማምረቻና የመሸጫ ማዕከላቱ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው እንዲሆኑ የሚደረግ ቢሆንም


ኢንተርፕራይዞቹም የጋራ መገልገያዎች እንዲደራጁና በማዕከሉ አስተዳዳር ውስጥ እንዲሳተፉ ድጋፍ
ይሰጣቸዋል፡፡

5) በማዕከላቱ ውስጥ የሚሰጡ የጋራ አገልግሎቶች ጥበቃ፣ጽዳትና ውበት እና የመሳሰሉትን በተመከለተ በጋራ በሚያቋቁሙት
ኮሚቴ አስተባባሪነት ይከናወናል፡፡

14
18. በማዕከሉ ውስጥ ለሚሰሩ ኢንተርፕራይዞች የድጋፍ ሁኔታ

በማዕከላቱ የሚስተናገዱ ኢንተርፕራይዞች ተመሳሳይና ተያያዥነት ባላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች


የተደራጁ እስከ 5 አመት ብቃት አግኝተው ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ እንዲሸጋገሩ የሚረዱ ድጋፎችና
አገልግሎቶች እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡እነዚህም ድጋፎች

1) በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማትና በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ባለሙያዎች አማካኝነት
ኢንተርፕራይዞች ከሚያገኙት ገቢ እንዲቆጥቡና ለስራቸውም በቂ የሆነ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ
ይደረጋል፡፡ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት በክላስተር ውስጥ ቢሮ በመክፈት የቁጠባ፣ የብድር እና የምክር
አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ የተሻለ የቁጠባ ዝግጅት ያላቸው ኢንተርፕራይዞች የብድር አገልግሎት
ቅድሚያ የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል፤
2) የንግድ ልማት አገልግሎት (BDS) እንዲያገኙና የምርትና የአገልግሎት ብቃታቸው እንዲጎለብትም
በአንድ ማዕከል አገልግሎት ጣቢያ ባለሙያዎች ድጋፍ ይመቻቻል፤
3) የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የተሟላ፣ የተቀናጀ፣ ችግር ፈቺና ለተወዳዳሪነት
የሚያበቃ የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን አገልግሎቶች እንዲሰጣቸው በማድረግ ብቃታቸው እንዲያሳድጉ
ይደረጋል፤
4) በዋነኛነት ገበያን በራሳቸው አፈላልገው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የግብይት ክህሎታቸውን ማሳደግና
አስፈላጊውን መረጃ መስጠት እንዲሁም በመንግስት ግዥዎችም ተጠቃሚ የሚሆኑበት በጨረታ
የሚሳተፈበት ምርትና አገልግሎቶቻቸውን በጥራት በዋጋና በጊዜ ተወዳዳሪ ሆነው የሚያቀርቡበት
ድጋፎች ይሰጣቸዋል፤
5) ኢንተርፕራይዞቹ T°ŸL~” በማስተዳደር የጋራ ጥሬ ዕቃዎች ግዥ በማካሄድ ማምረቻ መሳሪያዎችን
በማደራጀት ገበያን በማፈላለግና የንዑስ ተቋራጭነት ተሳታፊና ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆኑ
ይደረጋል፡፡

19. የጋራ አገልግሎት ፍጆታ ክፍያ በተመለከተ

1) መብራትን በተመለከተ በተለይ ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚጠቀሙ በየግላቸው ቆጣሪ


የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ የመብራት ፍጆታ ኢንተርፕራይዞቹ በራሳቸው እንዲከፍሉ
ይደረጋል፡፡

2) ውሀን በተመለከተ በየብሎኩ ለሚገኙ የስራ ዘርፍ የከተማ አስተዳደሩ የሚያስገባ ሲሆን የፍጆታ
ሂሳቡን ኢንተርፕራይዞቹ ራሳቸው መክፈል ይኖርባችዋል፣

3) ጥበቃን በተመለከተ ሁሉም የማእከሉ ተጠቃሚዎች በጋራ ወጪ ይሸፈናል፣

4) የስልክ ወጪ እያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ እንደ አጠቃቀሙ ይከፍላል፣

15
20. የማዕከሉ ተጠቃሚዎች መብት

1) በማዕከሉ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎት የመጠቀም፣

2) በማዕከሉ ውስጥ የጽዳትና ውበት፣ጥበቃ ሌሎች የጋራ አገልግሎቶችን የሚያስተባብሩ አመራር አካላት /ኮሚቴዎችን/
ዲሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ የመምረጥና ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሳይወጡ ሲቀሩ የማውረድ፣

3) የጋራ መገልገያ መሣሪያዎችን በፕሮግራምና ሥርዓት ባለው መንገድ የመጠቀም፡፡

21. የማዕከሉ ተጠቃሚዎች ግዴታ

1) ማንኛውንም በግልም ሆነ በጋራ ለተጠቀሙባቸው አገልግሎቶች የኪራይ ክፍያ በወቅቱ የመፈጸም፣

2) ማዕከላቱን ለታለመለት ዓላማ ብቻ መጠቀም ማለትም ያላሳማኝ ምክንያት እና ከሚመለከታው አካል ፍቃድ ሳያገኝ
ዘርፍ አለመቀየር፣ ያለስራ ዘግቶ አለማስቀመጥ ፣ በማንኛውም መንገድ ለሌላ ወገን አሳልፎ አለመስጠት፤

3) ዘመናዊ የሂሳብ መዝገብ መጠቀም፣ በአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋም ቁጠባ ማስቀመጥ፣ በማንኛውም ወቅት
ኦዲት ማድረግ የሚያስችል ተገቢውን የሂሳብ ሪፖርት የማቅረብ፣

4) የሚሠሩበትን ሕንፃና አካባቢውን እንዲሁም የጋራ መገልገያ መሳሪያዎች የመጠበቅና በንጽህና የመያዝ፣

5) ማንኛውም የክላስተር ተጠቃሚ ማዕከሉን ለቆ እንዲወጣ ከተወሰነበት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለቆ መውጣት፣

6) በማዕከላቱ ይዞታ ውስጥ ምንም ዓይነት የማስፋፊያ ግንባታ ያለመገንባት፣

7) እሳትን ሊያስነሱና የተገልጋዮችን ጤና ሊያውኩ የሚችሉ ተቀጣጣይ ነገሮች ያለማከማቸትና አነስተኛ የእሳት አደጋ
መከላከያ ገዝቶ ማስቀመጥ፣

8) ማንኛውም ኢንተርፕራይዝ የክላስተር ማእከሉን ሲለቅ ከማዕከሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዕዳዎች ነፃ ስለመሆኑ
ማረጋገጫ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

9) ከላይ የተዘረዘሩትን ግዴታዎች ታሳቢ ያደረገ የጋራ መጠቀሚያ መተዳደሪያና ውስጠ ደንብ ማዘጋጀት
ይኖርባቸዋል፡፡

10) በማዕከላቱ ውስጥ ያሉ ኢንተርፕራይዞች በራሳቸው ለንብረታቸው የመድህን ዋስትና እንዲገቡ ይበረታታሉ፤

11) ከላይ የተዘረዘሩት ግዴታዎች ተጥሰው ሲገኙ በመተዳደሪያ ደንቡ እና ውስጠ ደንባቸውና በውለታቸው መሰረት
አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል፡፡

22. በኢንተርፕራይዞች ስለሚቋቋሙ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች

1) ማዕከሉን ለማስተዳደር የሚሰየም ኮሚቴ

ሀ) ማዕከላቱ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲያስችላቸው አጠቃላይ የማእከላቱን የንብረትና የግቢ አስተዳደርን
እንዲሁም ገበያን ጨምሮ ድጋፎችን ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ በክላስተር ማእከሉ አባላት የሚመረጥ ይሆናል፡፡

16
እንደ ክላስተር ማእከላት ስፋት ከ 3 እስከ 7 የሚደርሱ አባላት ይኖሩታል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሊቀመንበር፣ ጸሀፊና
ገንዘብ ያዥ ይኖሩታል፤

ለ) የኮሚቴ አባላት ስብጥር በክላስተር ውስጥ የታቀፉን ዘርፎች እንዲወክሉ ተደርጎ ይዋቀራል፣ የሴቶች፣
ወጣቶችና አካልጉዳተኞችን ተሳትፎ ያማከለ ይሆናል፡፡

2) የኮሚቴው ሥልጣንና ተግባር፣

ሀ) በዚህ መመሪያ ውስጥ የተዘረዘሩት የአባላት መብትና ግዴታ በአግባቡ መተግበሩን በቅርበት ይከታተላል፣

ለ) በተገልጋዮች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በቅርበት ይፈታል፣ ከአቅሙ በላይ ሆኖ ሲገኝም


በሚመለከታቸው አካላት እንዲፈታ ያደርጋል፣

ሐ) መተዳደሪያ ደንብ የተላለፉ ኢንተርፕራይዞች በደንቡ መሰረት ቅጣት እንዲወሰንባቸው ክትትል


በማድረግ ያስወስናል፣

መ) የማዕከሉ ተጠቃሚዎቸ ቋሚ ቁጠባ እንዲኖራቸው፣ ብድር እንዲያገኙ፣ ብድራቸውን በወቅቱ


እንዲመልሱና ማነኛውንም የመንግሥት ክፍያዎች በወቅቱ እንዲከፈሉ ክትትል ያደርጋል፣

ሠ) ጥበቃና ጽዳት በአግባቡ እንዲከናወን ያደረጋል፤

ረ) ኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልጋቸውን ግብአቶች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ስልጠና፣ የሂሳብና የኦዲት


አገልግሎት፣ የጋራ መገልገያዎችና የገበያ ትስስር የሚገኙበት ሁኔታዎችን ያመቻቻል፣

ሰ) የክላስተር ማእከሉ ተጠቃሚዎች የሚያወጡትን የጋራ የውስጥ መተደደሪያ ደንብ ተፈፃሚ ያደርጋሉ፣

ሸ) የክላስተሩን አባላት የጋራ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ከመንግስትና ከሌሎች አካላት ጋር ግንኙነት ያደርጋል፣
ይደራደራል፣ ያስፈፅማል፣

ቀ) የገበያ አቅርቦትና የግዥ ፍላጎትን በማጥናት የጋራ ግዥና ሽያጭ እንዲፈፀም ሁኔታዎችን ያመቻቻል፣

በ) ክላስተሩ እየተጠናከረ ሲሄድ የማእከሉ አስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችንና የጋራ መገልገያ


መሳሪያዎችን የጋራ ክፍያዎችንና የመሳሰሉትን በተገቢው መንገድ በመምራት የኢንተርፕራይዞችን
የግቢና ንብረት አስተዳደር ኮሚቴ የዕለት ተዕለት ስራዎችን ተክቶ የሚሰራ አንድ ስራ አስኪያጅ
በኢንተርፕራይዞች ኮሚቴ አማካኝነት የሚቀጠር ይሆናል፣

ተ) ቅጥሩንም በተመለከተ ለማዕከላቱ አዋጭነት በማዕከሉ ውስጥ በሚገኙ ኢንተርፕራዞች ሲታመን


የሚቀጠር ሲሆን ተግባርና ሃላፊነቱም የሚከተለው ይሆናል፣

ቀ) የማዕከሉ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶችና አካልጉዳተኞች ፍትሐዊ ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣

17
3) የክላስተር ማዕከል ስራ አስኪያጅ ተግባርና ኃላፊነት

ሀ) ለፅዳት ጥበቃና ግቢ ውበት ሰራተኞች የማእከሉን ስፋት ታሳቢ በማድረግ ከኢንተርፕራይዞች ኮሚቴ ጋር
በመመካከር ይቀጥራል፣

ለ) ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣

ሐ) የመብራት፣ የውሃ፣ የቦታ ኪራይና ሌሎች ክፍያዎችን በወቅቱ ለሚመለከታቸው መከፈሉን በመከታተል
ያስፈፅማል፣

መ) አጠቃላይ አስተዳደራዊ ስራዎችን በተመለከተ ለኢንተርፕራይዞች ክላስተር ኮሚቴ ሪፖርት ያቀርባል፣

ሠ) በክላስተር ኮሚቴ በሚሠጠው አቅጣጫ መሰረት የገበያ ትስስርና የግዥ ፍላጎትን በማጥናት የጋራ ግዥና
ሽያጭ እንዲፈፀም ሁኔታዎችን ያመቻቻል፣

ረ) የክላስተር ማዕከሉ የጋራ ንብረትና መገልገያዎችን ያስተዳድራል፣

ሰ) የኢንተርፕራይዞች ክላስተር ኮሚቴ የሚሰጠውን ተግባር ያከናውናል፡፡

4) በማዕከላቱ የኢንተርፕራይዞች የቆይታ ጊዜ

ሀ) ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በማዕከላቱ የሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ ጣሪያ 5 ዓመት

ሆኖ በሚገቡት ውል መሠረት ተፈፃሚ ይሆናል፤

ለ) ይህ የኢንተርፕራይዞች የክላስተር ማዕከሉ ቆይታ የማዕከሉን ደንብ ባለማክበር በጥፋት እንዲወጡ የሚደረጉትን
አይመለከትም፤

ሐ) በዚህ መመሪያ መሠረት መስፈርቶችን አሟልተው ከሚገቡ ኢንተርፕራይዞች በፊት በማዕከላቱ እየተገለገሉ የቆዩ
ኢንተርፕራይዞችን በተመለከተ እያንዳንዱ ከተማ አስተዳደር ኢንተርፕራይዙ ያለበትን ደረጃ በመገምገም አዲስ የቆይታ
ውል እንዲገቡ ያደረጋል፡፡

23. ከማዕከሉ የሚመረቁ ኢንተርፕራይዞች የመውጫ ስትራቴጂ

በማዕከሉ የሚኖረው የቆይታ ጊዜ በተራ ቁጥር 4.5.4 ንኡስ ቁጥር 1 ላይ በተጠቀሰው መሰረት ይሆናል፡፡ ተጠቃሚዎች
በግላቸው በመረጡት መንገድ የመሥሪያ ቦታቸውን በዘላቂነት ማመቻቸቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለቀጣይ ኢንቨስትመንት
አገልግሎት የሚሆን ከገቢያቸው ቢያንስ 30% የቆጠቡ እና የተመረቁ ለመሆናቸው ተገቢውን ሠርተፊኬት ያገኙ
ኢንተርፕራይዞች በተራ ቁጥር 3.5 መሰረት የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ይመቻችላቸዋል፡፡

18
1) ዋና ዋና የመመረቂያ መስፈርቶች፣

ሀ) በጥቃቅን እና አነሰተኛ ኢንተርፕራይዝ ትርጓሜ መሠረት መስፈርቱን የሚያሟሉና ወደ ታዳጊ መካከለኛ


ኢንተርፕራይዝነት ይሸጋገራሉ፡፡

ለ) በአንጻራዊ ከሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ሲወዳደር በቂ የክህሎትና የፋይናንስ አቅም የፈጠሩና


ተገቢውን ሥራ ለመስራት የሚያስችል የማምረቻ መሳሪያ ያላቸው፣

ሐ) በግል ወይም በጋራ የራሳቸው የሆነ ወይም በኪራይ የመስሪያ ቦታ ያዘጋጁ ፣

መ) ከተደራጁ በኋላ ለ 5 /አምስት/ ዓመታት ተከታታይ ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ፡፡

ሀ) ማንኛውም ኢንተርፕራይዝ ከታች የተዘረዘሩት መስፈርቶችን ቀድሞ ማሟላቱ ከተረጋገጠ 5

ዓመቱን ሳይጨርስ መመረቅ ይችላል፡፡

2) ወደ ታዳጊ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ እድገት ያልተሸጋገሩ ቀጣይ ድጋፍ

ሀ) በማምረቻና መሸጫ ክላስተር ማእከላት ለተከታታይ አምስት ዓመታት የማምረቻና መሸጫ ማእከል ተሰጥቶዋቸው
የመመረቂያ መመዘኛ መስፈርት ማሟላት ባለመቻላቸው ያልተመረቁ ኢንተርፕራይዞች በማንኛውም መንገድ በቀጣይ
የማምረቻና መሸጫ ማእከላት አይሰጣቸውም፡፡

ለ) ወደ ታዳጊ መካከለኛ እድገት ደረጃ ያልተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ሌሎች ድጋፎችን ማለትም የንግድ ምክር እና መረጃ
አገልግሎት፣ የብድር አገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን አገልግሎት እና የገበያ ትስስር ድጋፍ እስከ ቀጣይ 2 ዓመታት
ሊሰጣቸው ይችላል፡፡

3) በማዕከላቱ አካባቢ ተጓዳኝ የሆኑ አገልግሎቶችን ስለማደራጀት

በማዕከላቱ አካባቢ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የአገልግሎት ስራዎች (መረጃ ማዕከል፣ ጤና ኬላ፣
የህፃናት ማቆያ እና የስብሰባ አደራሽ የመሳሰሉት) እንዲደራጁ ይደረጋል፡፡

ክፍል አምስት

የፈፃሚና የባለ ድርሻ አካላት ተግባርና ኃላፊነት

24. የከተማ ልማትና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር

1) የማምረቻና የመሸጫ ክላስተር ማዕከላት ግንባታ፣ አጠቃቀምና አስተዳደር ስርዓት በሁሉም


19
የአገሪቱ ከተሞች እንዲዘረጋና እንዲጠናከር ይደግፋል፣ ይከታታላል ያስተባባራል፣
2) ለዘርፉ ልማት ለመስሪያና የመሸጫ ሼድ /ማከላት ልማት የሚውል የለማ ቦታ ከተሞች በከተማ ፕላናቸው
እንዲያካትቱ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፣
3) የማምረቻና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ዲዛይን እና ግንባታ ወጭና ቦታ ቆጣቢ በሆነ መልኩ
መዘጋጀቱን ይከታታላል፣ ይደግፋል ያስተባብራል፣
4) ከተሞች ለሼድና የገበያ ማዕከላት ልማት ቅድሚያ በጀት እንዲይዙ ድጋፍ እና ክትትል
ያደርጋል፣
5) የማምረቻና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ልማት የደረሰበትን ደረጃ እና ያጋጠሙ ችግሮችን
በየወሩ እና በሩብ አመቱ በጂቲፒ መድረክ ፣ በስድስት ወሩ በሴክተር ጉባኤ እና በዘርፉ ምክር ቤት ትኩረት
ተሰጥቶት እንዲገመገምና ላጋጠሙ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡

25. የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ

1) የማምረቻ እና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማእከላት ውስጥ የሚሰጡ የድጋፍ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና
በሂደት በጥናት ላይ በመመስረት እንዲሻሻሉ ማድረግ፣

2) የሀገር አቀፍ የሼድና የገበያ ማዕከላት መነሻ አማጭ ስታንዳርድርና ዲዛይን በማዘጋጀት ክልሎች በነሻነት
እንዲጠቀሙባቸው ድጋፍና ክትል ማድረግ፤

3) ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ቦታና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ የሼድና የገበያ ማዕከላት ልማት ምርጥ
ተሞክሮዎችን ቀምሮ በየክልል እንዲስፋፋ ማድረግ፡

4) በማምረቻ እና መሸጫ ሼድና የገበያ ማእከላት ግንባታ፣ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ላይ የክልሎች
ወይም ከተማ አስተዳደሮች አቅም መገንባት፤

5) በመስሪያና የመሸቻ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት አቅርቦት፣ አጠቃቀምና አስተዳርን የሚመለከት የተደራጀ
ሪፖርት ለሚኒስቴር መስሪያቤቱና ለዘርፉ ምክር ቤት በማቅረብ በጉድለቶች ላይ የማስተካካያ አቅጣጫ
እንዲሰጥበት ማድረግ

26. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

1) ለዘርፉ ልማት ለሚገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያቀርባል፣

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ አቅዶ ይሰራል፤

2) ለተገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያቀርባል፤

3) በዘርፉ የምክር ቤት ጉባኤ በመገኝት የዘርፉ ልማት አፈጻጻም ይገመግማል

20
27. የክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ/በክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ስራን እንዲመራ የተቋቋመ ተቋም

1) የማምረቻና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ቦታ ዝግጅት፣ ግንባታ፣ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ
የፌዴራሉን መነሻ በማድረግ ያዘጋጃል፣

2) ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሚውል የለማ ቦታ በከተሞች ፕላን እንዲኖር


ያስተባብራል፣ ይከታተላል፣ ይደግፋል፣ ይገመግማል፡፡

3) የማምረቻ እና መሸጫ ሼድና የገበያ ማእከላት አማራጭ ዲዛይን የፌዴራሉን መነሻ በማድረግ ከክልሉ
ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዘጋጀት ከተሞች እንዲጠቀሙበት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡

4) ለሼዶችና የገበያ ማዕከላት ግንባታ የሚሆን በጀት ከተሞች በበጀት አመቱ መጀመሪያ ቅድሚያ ሰጥተው
እንዲመድቡ ያስተባብራል፤ ይደግፋል፤ ይከታተላል ይገመግማል፤

5) ለሚገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት ከፍተኛና ዝቅተኛ የኪራይ መጠን በካሬ በመወሰን ከተሞች
ተግባራዊ እንዲያደርገት ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፤

6) የማምረቻ እና መሸጫ ሼድና የገበያ ማእከላት ግንባታየጥራት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ትኩረት
ሰጥቶ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣ ይገመግማል፣

7) የማምረቻ፣ የመሸጫና ገበያ ክላስተር ማእከላት ግንባታና መሰረተ ልማት አገልግሎት የሚውል በጀት
በክልል መንግስት እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲመደብ ያደረጋል፡፡

28. የክልል የከተማ የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ስራዎችን የሚመራ ተቋም

1) የመስሪያና የመሸጫ ሼድ እና የገበያ ማዕከላት የቦታ ዝግጅት፣ ዲዛይን፣ ግንባታ፣ አጠቃቀምና አስተዳደር
መመሪያ የፌዴራሉን መነሻ በማድረግ በማዘጋጀት ለቢሮው አቅርቦ ያስፀድቃል፣

2) ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የመስሪያና የመሸጫ አገልግሎት የሚሆን ቦታ በከተሞች ፕላን


እንዲመላከት ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል

3) የማምረቻ፣ የመሸጫና ሼዶችና የገበያ ማዕከላት ዲዛይን የፌዴራሉን መነሻ እንደክልሉ ነባራዊ ሁኔታ
እንዲዘጋጅና ተግባራዊ እንዲሆን ክትትል እና ድጋፍ ያደርጋል ፡፡

4) በመስሪያና መሸጫ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት የሚገቡ ኢንተርፕራይዞች በተዘጋጀው መመልመያ


መስፈርት መሰረት እንዲከናወን ያስተባብራል፣ ይደግፋል፣ ከታተላል ገመግማል፤

5) የማምረቻ እና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት አስተዳደርን በተመለከተ በበላይነት ይመራል፣


ኢንተርፕራይዞቹ አስፈላጊውን የጋራ መገልገያ መሳሪያዎች እንዲያደራጁ ያመቻቻል፣
21
6) የማምረቻ እና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የእድገት ሽግግራቸውን
ማፋጠን እንዲችሉ አስፈላጊውን የድጋፍ አገልግሎቶች በአግባቡ ማግኘታቸውን ይከታተላል፣ ሥራውን
በበላይነት ይመራል፣

7) የማምረቻ እና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መረጃ ይሰበስባል፣ ያጠናቅራል፣
ያሰራጫል፣

8) የተገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት ማዕከላት ተገቢውን አገልግሎት መስጠታቸውን፣ በማዕከላቱ የገቡ
ተጠቃሚዎችም ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ማግኘታቸውን፣ በእያንዳንዱ ከተማ ኢንተርፕራይዞች ኪራይ
መክፈላቸውን ይከታተላል፣ ይገመግማል፡፡

9) የተሰጣቸውን ሼድና የገበያ ማዕከላትን ከአሰራር ውጭ በሚጠቀሙ ኢንተርፕራይዞች ላይ ወቅታዊና


አሰራርን የተከተለ የማስተካካያ እርምጃ እንዲወሰድ ያስተባብራል፣ ደግፋል፣ ይከታተላል፣ ገመግማል፡፡

10) ከመስሪያና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት አቅርቦት አጠቃቀምና አስተዳዳር የሚመለከት የተደራጀ
ሪፖርት ለዘርፉ ም/ቤት በማቅረብ አቅጣጫ እንዲሰጥበት ያደርጋል፡፡

29. የከተማ የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስት ስራዎችን የሚመራ ተቋም

1) የማምረቻ እና መሸጫ ሼድና የገበያ ማእከላት መገንቢያ የሚሆን መሬት በከተማው ፕላን እንዲሰጠው
ክትትል ያደርጋል፣

2) በከተማው ፕላን ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የተመላከተውን መሬት በፅ/ቤቱ ስም


ከከተማው የመሬት አስተዳዳር የስራ ክፍል ይረከባል፣

3) ለሼድና ለገበያ ማዕከላት መገንቢያ በቂ በጀት ከተማው እንዲመድብ ያስተባብራል ይከታታላል፣

4) የሼድና የገበያ ማዕከላት ዲዛይን የክልሉን መነሻ በማድረግ በሚመለከተው የስራ ክፍል ከከተማው ተጨባጭ
ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ እንዲዘጋጅ ክትትል ያደርጋል

5) የሼድና የገበያ ማዕከላቱ ግንባታ በተያዘው በጀትና በተዘጋጀው ዲዛይን መሰረት በወቅቱ ጥራቱን ጠብቆ
እንዲገነባ ከግንባታ ክትትልና ቁጥጥር የስራ ክፍል ጋር በመሆን ክትትል ያደርጋል፣

6) ለሚገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት መሰረተ ልማቶች (መንገድ፣መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ የጥበቃ
ቤት) እንዲሟላላቸው ያስተባብራል አፈጻጻሙን ይከታታላል፣

7) የሼድና የገበያ ማዕከላቱ ግንባታ ሲጠናቀቁ በሚመለከተው በውሌታው መሰረት መሆኑ እንዲረጋገጥ
በማድረግ ግንባታውን ካከናወነው ተቋም የግንባታ ሕጉን በተከተለ አግባብ ይረከባል፣

8) የተረከባቸውን የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችንና የገበያ ማዕከላትን በከተማው ለሚገኙ የአንድ ማዕከል
አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ውል ይዘው እንዲያስተላልፏቸው ያስረክባል

22
9) በመስፈርቱ መሰረት ከአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች በመመልመያ መስፈርቶች መሰረት
ተመልምለው የተላኩለትን ኢንተርፕራይዞች በማጣራት የመስሪያና የመሸጫ ቦታ የሚሰጣቸውን በቅደም
ተከተል በስም ዝርዝር በመለየት በደብዳቤ ለየጣቢያዎቹ ያተላልፋል፣

10) የመስሪያና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላትን ድጋፍ የሚያመቻችና የሚከታታል ባለሙያ በከተማ እና
በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስቻ ጣቢያዎች ይመድባል፣ የድጋፍ አሰጣጣቸውን ብቃት በተገቢው
ይገመግማል፣ ለባለሙያዎቹም ግብረ-መልስ ይሰጣል፣

11) ወደ መስሪያና መሸጫ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት የሚገቡ ኢንተርፕራይዞች በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች
ህጋዊ ውል ተዋውለው ስለመግባታቸው ይከታተላል ይገመግማል ግብረ መልስ ይሰጣል፣

12) የመስሪያና የመሸጫ ሼና የገበያ ማዕከላት ተጠቃሚ ኢንተርፕራዞች በገቡት ውል መሰረት ተሰጣቸውን ድጋፍ ለታለመለት
አላማ ማዋላቸውንና ወራዊ ኪራይ በወቅቱ መክፈላቸውን ክትትል ያደርጋል፣

13) ኢንተርፕራይዞች የቆይታ ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ እንደሚወጡ በተከታታይነት ያስገነዝባል፣

14) የተሰጣቸውን ሼድና የገበያ ማዕከላት ከአሰራር ውጭ የሚጠቀሙ ኢንተርፕራይዞች ዝርዝር መረጃ ከአንድ ማዕከል
አገልግሎት መስቻ ጣቢያዎች ሲደርሰው አጣርቶ ወቅታዊና ህጋዊ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል

15) የኢንተርፕራይዞቹ አጠቃላይ መረጃዎችን በተገቢው በማደራጀት የተሻለ አፈፃጸም ያሳዩትን እንዲበረታቱ ያደርጋል፣

16) የማዕከሉ ማህበረሰብ በተለይ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ ከመስሪያ ቦታና ከሠራተኛ ደህንነት እና ተግባር ተኮር የጎልማሶች
ትምህርት ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ይሰራል፣

17) የመስሪያና የመሸጫ ሼድ እና የገበያ ማዕከላት አቅርቦት አጠቃቀምና አስተዳዳርን በተመለከተ የተደራጀ ሪፖርት ለዘርፉ
ም/ቤት በማቅረብ ባጋጠሙ ችግሮች ላይ አቅጣቻ እንዲሰጥበት ያደርጋል፡፡

30. ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ/ተቋም

1) በክላስተር ማእከላት ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የክህሎት ክፍተት እየለየ የቴክኒክና የንግድ ስራ አመራር ስልጠና
ፕሮግራም በማውጣት ይሰጣል፣

2) የማምረቻ መሳሪያዎችን ምርታማነት ለማሳደግ የምክር አገልግሎት፣እንዲሁም ምርታማነታቸው የተረጋገጡ የቴክኖሎጂ


ውጤቶች መረጃ በመስጠት ድጋፍ ይሰጣል፣

3) የድጋፉ ተጠቃሚ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች ፕሮቶታይፕ በመስራት የቴክኖሎጂ ሽግግር ያካሄዳል፣

4) የድጋፉ ተጠቃሚ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሂሳብ መስመር ዝርጋታ ድጋፍ ይሰጣል፣

5) አራቱንም ፓኬጆች ያሟላ የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለሼድና የገበያ ማዕከላት ተጠቃሚ
ኢንተርፕራይዞች ይሰጣል፡፡
23
31. የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት

1) የሼድና የገበያ ማዕከላት ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች በፋይናንስ ድጋፍ አሰጣጥ መመሪያው ላይ የግንዛቤ
ማስጨበጫ ስልጠና ይሰታል

2) የብድር አገልግሎት ለሚፈልጉ የመስሪያና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች ቅድመ ብድር
መስፈርቶችን ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የብድር አገልግሎት ይሰታል

3) የብድር ተጠቃሚ የሆኑ ኢንተርፕራዞች የወሰዱትን ብድር ለታለመለት አላማ እንዲያውሉት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል

4) የፋይናንስ ድጋፍ ( የቁጠባ፣ የብድር እና አመላላስ) ተጠቃሚ ኢንተርፕራዞችን መረጃ በማደራጀት ለከተማው የስራ
ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በወቅቱ ሪፖርት ያደርጋል

5) የወሰዱትን ብድር የማይመልሱ ኢንተርፕራዞችን ዝርዝር መረጃ በማደራጀት በብድር አስመላሽ ኮሚቴ እንዲመለስ
ተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፣

32. በከተማ የከተማ ልማትና ቤቶች ስራዎችን የሚመራ ተቋም

1) ለማምረቻ፣መሸጫና ገበያ ማእከላት የሚሆኑ ቦታዎችን በቦታ ዝግጅት፣ መረጣ መስፈርትና ከተሞች እድገትና ፕላን
መሰረት አዘጋጅቶ ያቀርባል፣

2) ለማምረቻና መሸጫ አገልግሎት እንዲውሉ ለተመረጡ ቦታዎች አስፈላጊውን መሰረተ ልማት ከሚመለከታቸው ተቋማት
ጋር በመቀናጀት ያሟላል፣

3) በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ በተዘጋጀው ስታንዳርድና ዲዛይን መሰረት ከተማው ለዘርፉ ልማት የተመረጠውን ቦታ
ታሳቢ ያደረገ ዲዛይንና ስፔስፊኬሽን ያዘጋጃል፣

4) የማምረቻና መሸጫ ሸድና የገበያ ማእከላት ቦታ ሳይት ፕላን አዘጋጅቶ ለከተማው የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና
ጽ/ቤት ያስረክባል፣

5) የማምረቻ እና መሸጫ ሼድና ገበያ ማዕከላት ግንባታ ወጭ ቆጣቢ አሰራሮችን በተከተለ መልኩ ህንፃዎችንና
ሼዶችን ይገነባል፣

ረ) የማምረቻ እና መሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት የህንጻ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለከተማው የስራ እድል ፈጠራና የምግብ
ዋስትና ጽ/ቤት ያስረክባል፣

ሰ) ለማምረቻና መሸጫ ሼድና የገበያ ማእከላት ግንባታ ክልሉ ከሚመድበው በተጨማሪ ቅድሚያ ሰጥቶ በጀት ይመድባል፣

33. የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ

1).የመስሪያና የመሸጫ ሼድና ገበያ ማእከል ፈላጊ ኢንተርፕራይዞችን ማመልከቻ በማስሞላት ይመዘግባሉ፣

24
2) ከተመዘገቡት ሼድና የገበያ ማዕከላት ፈላጊ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ የመመልመያ መስፈርቱን የሚያሟሉትን በመለየት
ለከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ወይም በከተማው የስራ እድል ፈጠራ እና የምድብ ዋስትናን
ስራ ለሚመራ ተቋም በደብዳቤ ያስተላልፋሉ፣

3) ከከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ወይም በከተማው የስራ እድል ፈጠራ እና የምድብ ዋስትናን
ስራ በሚመራ ተቋም ተመልምለው በደብዳቤ ለሚላኩለት ኢንተርፕራይዞች እንደቅደም ተከተላቸው ውል በማዋዋል
የማስተላላፍ ስራ ይሰራል

4) የመስሪያና የመሸጫ ሼድ እና ገበያ ማዕከላት በውል የወሰዱ ኢንተርፕራይዞች በተወሰነ የጊዜ ገደብ በወቀጣ የእድገት
ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ ያመቻቻል

5) የመስሪያና የመሸጫ ሼድና የገበያ ማዕከላት ተጠቃሚ የሆኑ ኢንተርፕራዞች የሚሰጣቸውን ድጋፍ ለታለመለት አላማ
ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው ተከታታይነት ያለው የምክር ድጋፍ ይሰታል

6) የተሰጣቸውን የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ከታለመለት አላማ ውጭ የሚጠቀሙ ኢንተርፕራይዞችን በስም ዝርዝር ለይቶ
እንዲያስተካክሉ የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፣

7) የተሰጣቸውን የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ከአሰራር ውጭ በመጠቀማቸው በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መስተካካል


ያልቻሉትን በመለየት የማስተካካያ እርምጃ እንዲወሰድ ለከተማው የስራ ዕድልና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በደብዳቤ
ያሳውቃል፣

8) በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት መስተካካል ያልቻሉትን ውል
በማቋረጥ የህግ አስከባሪ ተቋማ ያሳውቃል፡፡

34. የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት

1) ለዘርፉ ልማት ለሚገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት የውሃ መስመር በመዘርጋት የውሃ አገልግሎት ለመስጠት
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ያቅዳል፤

2) ለተገነቡ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት የውሃ አገልግሎት ያቀርባል፤

3) በዘርፉ የምክር ቤት ጉባኤ በመገኝት የዘርፉ ልማት አፈጻጻም ይገመግማል

35. የከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ጉዳይ ጽ/ቤት

1) ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የለማ ቦታ እንዲዘጋጅ በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ስራ ከሚመራ
ተቋም ጋር አቅዶ በዕቅድ ይሰራል፣

2) የወጣቶችን የመስሪያና የመሸጫ የቦታ አቅርቦች ችግር ሊቀርፍ የሚችል በቂ በጀት ከተማው እንዲመድብ ግፊት ያደርጋል፣

3) በሚገነቡ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት ተጠቃሚዎች ምልመላ ላይ በንቃት ይሳተፋል፣

25
4) የመስሪያና የመሸጫ ሼድና ገበያ ማዕከላት ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች ድጋፉን ለታለመለት አላማ እንዲያውሉ ድጋፍና ክትትል
ያደርጋሉ ፣

36. የከተማ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤጾች

1) ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የለማ ቦታ እንዲዘጋጅ በከተማው የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ስራ ከሚመራ
ተቋም ጋር አቅዶ በዕቅድ ይሰራል፣

2) የሴቶችን የመስሪያና የመሸጫ የቦታ አቅርቦች ችግር ሊቀርፍ የሚችል በቂ በጀት ከተማው እንዲመድብ ግፊት ያደርጋል፣

3) በሚገነቡ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችና የገበያ ማዕከላት ተጠቃሚዎች ምልመላ ላይ በንቃት ይሳተፋል፣

4) የመስሪያና የመሸጫ ሼድና ገበያ ማዕከላት ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ድጋፉን ለታለመለት አላማ እንዲያውሉ ድጋፍና ክትትል
ያደርጋሉ፣

ክፍል ስድስት

37. የድጋፍ፣ ክትትል እና ግምገማ ስርዓት

1) ለማንኛውም ኢንተርፕራይዝ በየደረጃው የተደረጉ ድጋፎች፣ በየጊዜው የተገኙ መሻሻሎችና ለውጦች እንዲሁም አጠቃላይ
ንብረት መጠንና የእድገት ደረጃ በየስድስት ወሩ በእያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ በተከፈተ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በስራ
እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ይመዘገባል፡፡

2) ኢንተርፕራይዙ በራሳቸው ነፃነት መንቀሳቀሳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ተመርቀው እስኪ ወጡ ድረስ አጠቃላይ የገንዘብ
አጠቃቀማቸውን በተመለከተ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፡፡

3) በየጊዜው በገንዘብና ንብረት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ካሉ ወቅታዊ የማስተካከያ ድጋፎች ይደረጋል፡፡

4) ከክላስተር ማእከሉ እሰከ ቢሮ/ኤጀንሲ K¡ƒƒM“ l ጥጥ` ›S ቺነት ይኖረው ዘንድ የተቀናጀ የመረጃ ፍሰት
እንዲኖር ይደረጋል፡፡

5) በክላስተር ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች በመጀመሪያ የነበሩበት ሁኔታና የተገኙ ለውጦችን በሚያሳይ
መልኩ ፕሮፋይል ይዘጋጃል፡፡

6) የክላስተር ማዕከላት ውጤታማነት የኤጀንሲው ወይም ቢሮ በየ 3 ወር፣ ከተሞች በየወሩ የክትትልና ግምገማ
ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን በማዕከሉ ያሉ የተለያዩ ኮሚቴዎች በሳምንት አንድ ጊዜ የማእከሉ የጋራ
መገልገያዎችና አሰራሮች ዙሪያ ግምገማ ማከናወን አለባቸው፡፡

7) የግምገማ ሂደቱ በመስክ ጉብኝት በማከናወን የተከሰቱ ችግሮች አፈጣኝ ምላሽ በመስጠትና የታዩ ጉድለቶች
ለባለ ድርሻ አካላት በግብረ መልስ እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡

26
ክፍል ሰባት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

38. ሞዴል መመሪያውን ስለማሻሻል

ይህ ሞዴል መመሪያ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር


ለማጣጣም መሰረታዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንደ አስፈላጊነቱ በክልሉ/ከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ወይም በፌዴራል
ከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አማካኝነት ሊሻሻል ይችላል፡፡

39. መመሪያው የሚጸናበት ጊዜ

ይህ ሞዴል መመሪያው ከፀደቀበት ከ------------------ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

ጃንጥራር ዓባይ
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር

27

You might also like