You are on page 1of 8

የኦሰተንና አካባቢው የመረዳጃ እድር

መተዳደሪያ ደንብ

መግቢያ :- የእድሩ አስፈላጊነትና ትኩረት

የዚህ እድር አስፈላጊነትና ሙሉ ትኩረት በአባል ወይም በአባል ቤተሰብ ላይ በሞት ምክንያት ሐዘን ሲደርስ የችግሩ ተካፋይ
በመሆን በተለይም ለቀብር ስነ-ሥርዓት ማስፈጸሚያ ወይም አስከሬን መላኪያ ለሚያስፈልገው ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ጫናን
በመቀነሰ ረገድ ለመረዳዳትና ለመተጋገዝዝ ነው። በመሆኑም ይህ እድር ከማንኛውም የሃይማኖት ተቋምና ፖለቲካ ቡድን ገለልተኛ
እንዲሁም ከዘር፣ከብሄር፣ከክልል ወይም ከጐሳ ልዩነት አመለካከት ነፃ ነው። ይህ ማህበር በኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ ዘንድ
በባህላዊ ተለምዶ አጠራር እድር ተብሎ የሚታወቀው ሲሆን የራሱን አባላት የሚያገለግል የመረዳጃ ማህበር ነው:: እድሩ አትራፊ
ያልሆነ ድርጅት ሆኖ በቴክሳስ ስቴት ውስጥ በህጋዊ ደረጃ የሚቋቋም ነው::

1. ሰለ እድሩ መቋቋምና ሰያሜ

1.1. የእድሩ መስራች ጠቅላላ ጉባኤ በ Sunday July 20, 2014 ባካሄደው ስብሰባ ረቂቅ መተዳደሪያ ደንቡን አጽድቆ እና ደንቡ
እንዲዳብር የወስነባቸው ማሻሻያዎች እንዲጨመርበትና እንዲስተካከል አዝዞ ይህን ማኅበር በዚያው እለት በይፋ
አቋቁሟል::
1.2. የማኅበሩ ስም “የኦሰተንና አካባቢው የመረዳጃ እድር” በመባል ይጠራል። ከዚህ በኋላ እድር ወይም እድሩ እየተባለ
ይጠቀሳል።
1.3. ይህ ደንብ የኦሰተንና አካባቢው የመረዳጃ እድር መተዳደሪያ ደንብ (እንደተሻሻለ October 2014) ተብሎ ሊጠቀስ
ይችላል::

2. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ ደንብ ውስጥ፤

2.1. “አባል” ማለት በግለሰብ ደረጃ ወይም በቤተሰብ ሥር የተመዘገበ እና ይህን መተዳደሪያ ደንብ ተቀብሎ የአባልነቱን ግዴታ
እየፈፀመ ያለ ማለት ነው።
2.2. “ቤተሰብ” ማለት ባል፣ሚስት እንዲሁም/ወይም በአባል ስር የሚተዳደር/ሩ ልጅ/ልጆች ማለት ሲሆን፤ በአባል መኖሪያ ቤት
ውስጥ አብረው የሚኖሩ አባትና እናትን ይጨምራል።
2.3. “ልጅ” ማለት በቤተሰብ ሥር የተመዘገበ ሆኖ ሀ)ዕድሜው ከ18 ዓመት በታችና የአባል የሥጋ፣ የእንጀራ ወይም
የጉዲፈቻ(ማደጐ) ልጅ ሲሆን አስመዝጋቢ አባሉ (አባት ወይም እናት) ላይ በህግ መሰረት የአሳዳጊነት ኃላፊነት (legal
guardianship) የተጣለበትን ማንኛውንም ልጅ የሚያካትት ሲሆን ፤ እንዲሁም ለ) ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ
የአባል የሥጋ፣ የእንጀራ ወይም የጉዲፈቻ ልጅን ይጨምራል::
2.4. “የእድር መመዝገቢያ” ማለት ማንኛውም በግለስብ ደረጃ ወይም ከነቤተሰቡ በአዲስ መልክ የእድሩ አባል ለመሆን
ማመልከቻ ያስገባ ሁሉ የእድሩ ሙሉ አባል ለመሆን እንዲያስችለው በቅድሚያ የሚያዋጣው የአንድ ጊዜ የአባልነት
መመዝገቢያ ክፍያ ነው::
2.5. “የእድር ክፍያ” ማለት አባል ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ሲረጋገጥ እድሩ በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሟቹ የአባልነት
መመዝገቢያ ቅጹ ላይ በቅድሚያ በወኪልነት ላስመዘገበው ተጠሪ ግለሰብ የሚሰጠው የገንዘብ ክፍያ ወይም ጥቅም ነው::
2.6. “የእድር መዋጮ” ማለት አባል ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ ጊዜ በእድሩ ወጪ የተደረገውን የእድር ክፍያ በወቅቱ መልሶ
ለመተካት እንዲያስችል እያንዳንዱ አባል የሚያደርገው የገንዘብ መዋጮ ነው::
2.7. “ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ መዋጮ” ማለት እያንዳንዱ በአባልነት የተመዘገበ ግለሰብ እድሩ አስተዳደራዊ ወጪዎችን
ለመሸፈን እንዲያስችለው በዓመት አንድ ጊዜ በ January ወር የሚከፈልው መዋጮ ነው::
2.8. “ወኪል/ተወካይ” ማለት እያንዳንዱ አባል በግለሰብ ደረጃ ወይም በቤተሰብ ሥር ለአባልነት ሲመዘገብ የመመዝገቢያ ቅጹ
ላይ በቅድሚያ ያስመዘገበው እና አባሉ ሞት ቢያጋጥመው ከእድሩ የሚሰጠውን የእድር ክፍያ እንዲረከብ ውክልና
የተሰጠው ተጠሪ ግለሰብ ማለት ነው::
1|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::
2.9. “ኦስተንና አካባቢው” ማለት ኦስተን ከተማን አካበው የሚገኙትን ካውንቲዎች (Counties) ማለትም ትራቪስ፣ዊልያምሰን፣
ባስትሮፕ፣ሄይስ፣ካልድዌል፣ብላንኮ፣እና በርነት ካውንቲዎችን ይጨምራል::
2.10. ማናቸውም በዚህ ደንብ በወንድ ፆታ የተገለጸው አነጋገር ሴትንም ይጨምራል፡፡

3. የእድሩ ዓላማ

3.1. የአባልነት ግዴታውን በሙሉ ያሟላና የእድሩ አባል የሆነ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ለቀብር ስነሥርአት ማስፈጸሚያ ወይም
አስከሬኑን ወደ ሌላ ቦታ ለመላክ የሚሆን የእድር ክፍያ ለማድረግ፤
3.2. የቀብር ስነ-ሥርዓት ለማከናወን ወይም አስከሬን ለማጓጓዝ የሚያስፈልጉ እና የሚያግዙ ወቅታዊ መረጃዎችን ማሰባስብ ፣
ማዘጋጀት እንዲሁም ሲጠየቅ ለሟች ቤተሰብ ማቅረብ፤
3.3. አባል ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ በተቻለ መጠን የእድሩ አባላት ስለደረሰው ኅዘን እንዲያውቁት (inform) ማድረግ።
3.4. ይህ እድር በዚህ ደንብ ከተጠቀሱት የእድሩ ዓላማዎች ውጪ የሆኑትን ማለትም እንደ ፖለቲካና ሃይማኖት ነክ ተግባራት ላይ
ጣልቃ አይገባም፣ በማንኛዉም ሁኔታ አያስተናግድም::

4. አባልነት

4.1. የእድሩን ደንብ የተቀበለ ማንኛውም ግለሰብ፤


4.2. እንደአባልነቱ ሀ) የእድር መመዝገቢያን፣ ለ)የእድር መዋጮ እና ሐ) ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ መዋጮን በወቅቱ የሚከፍል፤
4.3. በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ የሚሆን እና፤
4.4. በኦስተንና አካባቢው የሚኖር አባል መሆን ይችላል።
4.5. አንድ ግለስብ ለእድሩ አባልነት መመዝገብ የሚችለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው::

5. የአባል መብትና ግዴታ

5.1. የመምረጥና የመመረጥ ፤


5.2. ደንቡ የሚፈቅደውን ጥቅም የማግኘት፤
5.3. የእድር ክፍያን መዋጮ እና ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ መዋጮን አሟልቶ በወቅቱ የመክፈል
5.4. እድሩ ተጨማሪ ገንዘብ ቢያስፈልገው የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ በሚያቀርበው መሰረት የእድሩ ምክር ቤት የወሰነውን
የሚከፍል ፤ እና
5.5. ስለራሱና ቤተሰቡ ትክክለኛ መረጃ የመስጠት፤ የቤተሰቡ ሁኔታ ላይ ለውጥ ሲኖር የመመዝገቢያ ቅጹ ላይ ቀደም ብሎ
የሞላውን መረጃ የማስተካከል፤ እንዲሁም የአድራሻ፣ስልክ ወይም ኢሜል ቢቀይር/ሩ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴን የማሳወቅ
ናቸው።
5.6. ቤተሰቡን ያስመዘገበ አባል ከ18 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ልጆች ካሉት በሕግ የተሰጠው የአሳዳጊነት ኃላፊነቱን ምርኩዝ
በማድረግ በማንኛውም የእድሩ ጉዳዩች ላይ የልጆቹ ሙሉ ተጠሪ ነው::
5.7. ቤተሰቡን ያስመዘገበ አባል ከ18 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ልጆች ካሉት እነሱን በመወከል የእድር ጉዳዮችን በተመለከተ
ድምጽ የመስጠት መብት ይኖረዋል::

6. የአባልነት መዋጮ

6.1. እያንዳንዱ ግለሰብ የእድሩ ሙሉ አባል ለመሆን ሲያመለክት ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚከፍለው የእድር መመዝገቢያ በነጠላ $75
ይሆናል።
6.2. አባል የሆነ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እድሩ በዚህ ደንብ መሰረት የከፈለውን ገንዘብ መልሶ ለመተካት እንዲችል እያንዳንዱ
አባል የሚፈለግበትን በግለስብ $25 የእድር መዋጮን በወቅቱ የመክፈል ግዴታ አለበት::
6.3. ማንኛውም ግለስብ በአባልነት ሲመዘገብ ሙሉ ክፍያ ይከፍላል::
6.4. ከነቤተሰቡ አባል ለመሆን የሚፈልግና የእድር መመዝገቢያውን ባንዴ መክፈል ለማይችል የመላ ቤተሰቡ የመመዝገቢያ
ክፍያው ተሰልቶ 1/3ኛውን ብቻ የቅድሚያ ክፍያ አድርጐ ቀሪውን 2/3ኛ አጠናቆ ለመጨረስ ግን የ90 ቀን የእፎይታ ጊዜ
ይሰጠዋል::

2|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::
6.5. ከላይ በአንቀጽ 6.4 መሰረት ቤተሰቡን የሚያስመዘግብ ግለስብ 1/3ኛውን የቅድሚያ ክፍያ አድርጐ ቀሪውን በተሰጠው
የ90 ቀን ውስጥ ከፍሎ ሳያጠናቅቅ ቢቀር ለእድሩ በቅድሚያ የከፈለው ገንዘብ አይመለስለትም::
6.6. ማንኛውም ከነቤተሰቡ አባል ለመሆን የሚመዘገብ ግለስብ ቤተሰቡን ጨምሮ አባል ለመሆን የሚፈለግበትን የመመዝገቢያ
ሙሉ ክፍያ ከፍሎ ካላጠናቀቀ የእድሩ አባል ሆኖ አይቆጠርም፤ የእድሩን የገንዘብ ጥቅም አያገኝም::
6.7. እያንዳንዱ አባል በዓመት አንድ ጊዜ በ January ወር የሚከፈል በግለሰብ $10 ለእድሩ የሥራ ማስኬጃ መዋጮ ያደርጋል::
የ January ወር ከመድረሱ በፊት በመሃል ባሉ ወራቶች የተመዘገበ አዲስ አባል የከፈለው ክፍያ እስከ Decmber 31st
ላሉት ወራቶች ብቻ እንደሆነ ይቆጠራል::

7. የእድር ክፍያ ሁኔታና መጠን

7.1. እድሩ ለአባላቱ በአስተማማኝ ሁኔታ የእድር ክፍያ ለማድረግ እንዲያመቸው ከአባላት ከሚሰበሰበው የእድር መመዝገቢያ
ለሦስት የሞት አደጋ ለመክፈል የሚያበቃ ቋሚ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲኖረው ይደረጋል::
7.2. የእድሩ አባል የሆነ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የእድር ክፍያ ለማግኘት የሚያስችለው
የአባልነት ግዴታውን ካሟላ በቅድሚያ በወኪልነት ለተመዘገበ የአባል ተጠሪ $10,000.00 ይሰጣል።
7.3. ከላይ በአንቀጽ 7.2 ላይ የተጠቀስው የእድር ክፍያ የሚጀምረው እድሩ ከአባላት ለመመዝገቢያ የሚሰበሰብው መዋጮ ሦስት
የሞት አደጋ ለመክፈል የሚያበቃ ቋሚ ተቀማጭ ገንዘብ ሲኖሩት ብቻ ነው:: በዚህ መሰረት እድሩ ለአባላት የሚሰጠው
የእድር ክፍያ በአቅም ደረጃ ሦስት የሞት አደጋን መሽፈን እስኪችል ድረስ በሥራ ላይ አይውልም::
7.4. ከላይ በአንቀጽ 7.2 ላይ የተጠቀስው የእድር ክፍያ ለአባላት በኦፊሴል መሰጠት የሚጀመረው እድሩ በአቅም ደረጃ ሦስት
የሞት አደጋን መሽፈን የሚያስችል ተቀማጭ ገንዘብ ሲኖረው እና ምክር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አባላትን ለማሰባሰብና
ለመመዝገብ በሚሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሙሉ አባል ሆነው ለተመዘገቡ ይሆናል::
7.5. ምክር ቤቱ ለመመዝገቢያ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተመዘገበ ነገር ግን ዘግይቶ የእድር አባል ለመሆን የሚፈልግ
ማንኛውም ግለሰብ የእድር ክፍያውን ጥቅም ማግኘት የሚጀምረው የእድር መመዝገቢያውን አጠናቆ ከጨረሰበት ቀን
ጀምሮ ለ 6 ወር አባል ሆኖ ከቆየ በኋላ ይሆናል:: በዚህ መሰረት ምክር ቤቱ ከሰጠው የመመዝገቢያ ቀናት ካለቀ በኋላ
የተመዘገበ አንድ አባል በአባልነት 6 ወር ካልሞላው የእድር ክፍያ አያገኝም::
7.6. አባል ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እድሩ በደንቡ መሰረት የእድር ክፍያውን ለመፈጸም እንዲችል የአባሉ ተወካይ የኦፊሴል
ሙት ሰርትፊኬት ወይም ከ funeral homes የኦፊሴላዊ ማስረጃ እንዲያቀርብ ይጠበቅበታል:: እድሩ በአባል ላይ የሞት
አደጋ መድረሱን በፅሁፍ ከተገለጸለት ቀን ጀምሮ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ በቅድሚያ በወኪልነት ለተመዘገበ የአባል ተጠሪ
የእድር ክፍያውን ይፈጽማል።

8. የእድሩ አስተዳደር

8.1. የእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ


8.1.1. ጠቅላላ ጉባኤ የእድሩ አባላት የሚገኙበት ጠቅላላ ስብስባ ሲሆን የእድሩ ከፍተኛው የበላይ አካል ነው።
8.1.2. የአባላት መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በየሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ይጠራል፤
8.1.3. በየሁለት ዓመት የሚደረገው የመላው አባላት ጠቅላላ ስብሰባ በጃንዋሪ የመጨረሻው እሁድ ከሰአት በኋላ
ይሆናል፤
8.1.4. ከግማሽ በላይ(51% ወይም ከዚያ በላይ) የእድሩ አባላት የተገኙበት ጠቅላላ ስብሰባ ምልአተ ጉባኤ ይሆናል።
ከግማሽ በላይ አባላት ሳይገኙ ቀርተው ምልአተ ጉባኤው አለመሙላቱ ሲረጋገጥ የተገኙት ጉባኤተኞች ሳይበተኑ
ምክር ቤቱ ወዲያውኑ ተሰብስቦ ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ 2/3ኛው በእለቱ የተገኘው ተሰብሳቢ ቁጥር
እንደምልአተ ጉባኤ ሆኖ ሰብስባው እንዲቀጥል ከተስማማ የእድሩ ጠቅላላ ሰብስባ ሊካሄድ ይችላል::
8.1.5. ምክር ቤቱ ካልተስማማ ግን ሁሉም የእድሩ አባላት በይፋ የተጠሩበት ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ተዘጋጅቶ በእለቱ
በተገኘው የአባላት ቁጥር የምልአተ ጉባኤ ሆኖ ስብሰባው ይቀጥላል::

8.2. የጠቅላላ ጉባኤ ሥልጣንና ተግባር

8.2.1. ይህ እድር የሚመራው በጠቅላላ ጉባኤው በተመረጠ ምክር ቤት እና በምክር ቤቱ በሚመረጥ የሥራ አስኪያጅ
ኮሚቴ ነው።

3|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::
8.2.2. እድሩን የሚመራና የእድሩን አጠቃላይ ሥራ የሚቆጣጠር አንድ ምክር ቤት ይመርጣል፤ ይህ ምክር ቤት ቢያንስ
20 አባላት የሚኖሩት ሲሆን የምክር ቤቱ አባላት ብዛት የሚሰላው አንድ ተመራጭ አባል ለ20 የእድር አባላት
ሆኖ ሊዋቀር ይችላል::
8.2.3. የእድሩ ምክር ቤት በሚያቀርበው ሃሳብ መሰረት የእድሩን መተዳደሪያ ደንብ ያጸድቃል፣ያሻሽላል፤ የማሻሻያ ሃሳቡን
ከጠቅላላ ጉባኤው 2/3ኛው ደግፎ ካጸደቀው ደንቡ ይሻሻላል::
8.2.4. ምክር ቤቱ ለጠቅላላ ጉባኤ በሚያቀርበው የአፈፃፅም ሪፖርትና በሌሎች አጀንዳዎች የጉባኤው ተሳታፊዎች ሃሳብና
አስተያየት መስጠት ይችላሉ፤
8.2.5. ጠቅላላ ጉባኤው የእድሩን ሂሳብ የሚመረምር የውጭ ኦዲተር ወይም ደግሞ ከእድሩ አባላት ውስጥ ይመርጣል።
በዓመታዊ ስብሰባው ላይ በውጭ ኦዲተሩ ወይም ከእድሩ አባላት ውስጥ የተመረጡት የሂሳብ መርማሪ ኦዲተሮች
በሚያቀረቡት ሪፖረት ላይ ይወያያል። የውጭ ኦዲተሩ ወይም ከአባላት ውስጥ የሚመረጡ ኦዲተሮች
ተጠሪነታቸው ለጠቅላላ ጉባኤው ይሆናል፤
8.2.6. በምክር ቤቱ አቅራቢነት ልዩ ስብሰባ ሲጠራ ጠቅላላ ጉባኤው በቀረበው ጉዳይ ላይ ተወያይቶ መመሪያ ወይም
ውሳኔ ይሰጣል፤
8.2.7. በምክር ቤቱ አቅራቢነት የጎደሉ የምክር ቤት አባላትን ይመርጣል።

8.3. የእድር ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር

8.3.1. የእድሩ ምክር ቤት ተጠሪነቱ ወይም ተጠያቂነቱ ለእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ነው።
8.3.2. የምክር ቤቱ አባላት ከመካከላቸው በድምፅ፡ብልጫ የሚመርጧቸው ፕሬዚደንት፣ም/ፕሬዚደንት እና የምክር ቤቱ
ፀሐፊ ይኖራቸዋል፤የሚያገለግሉት ለአራት ዓመት ይሆናል። የአገልግሎት ዘመናቸውን ሲጨርሱ እንደገና አንዴ
ሊመረጡ ይችላሉ፤
8.3.3. የምክር ቤቱ አባላት የአገልግሎት ዘመን አራት ዓመት ነው፤ አባላቱ በተከታታይ ለሁለት ጊዜ መመረጥ ይችላሉ፤
የምክር ቤቱ ምልአተ ጉባኤ ከግማሽ በላይ(51% ወይም ከዚያ በላይ) አባላት ሲገኙ ይሆናል።
8.3.4. ምክር ቤቱ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ስብሰባ ያደርጋል፤
8.3.5. ምክር ቤቱ በዓመታዊ ስብሰባው ላይ በእድሩ የገንዘብ አጠቃቀምና እንቅስቃሴ እንዲሁም ሂሳብ አያያዝ
በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ እንዳስፈላጊነቱ መመሪያ ይሰጣል፤
8.3.6. ምክር ቤቱ የእድሩን ስራና እንቅስቃሴ በቅርብ የሚከታተልና የሚቆጣጠር አንድ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ
ይመሰርታል፤ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል በድምፅ ብልጫ ሹማሙንቱን መርጦ ይሰይማል፤
8.3.7. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው የእድሩን ሥራ ለማካሄድ የሚያወጣቸውን የአፈጻጸም፡ስርዓቶችን ይመረምራል፣ከደንቡ
ጋር የማይፃረር ከሆነ ያጸድቃል፤
8.3.8. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴውን ዓመታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት ያዳምጣል፣ይመረምራል፤
8.3.9. በቀረበለት ዓመታዊ ሪፖርትና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል እንዲሁም የሥራ አስኪያጅ
ኮሚቴው ውሳኔዎችን በተግባር እንዲያውል መመሪያ ይስጣል፣መፈጸማቸውን ይከታተላል፤
8.3.10. ምክር ቤቱ በሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው የእድሩን የአባላት መጠንና የገንዘብ ገቢውን ሁኔታ ግንዛቤ ያስገባ ግምገማና
ጥናት ሲቀርብለት እንዳስፈላጊነቱ እየተመለከተ የእድር ክፍያ ጥቅም አከፉፈሉን ወይም የእድር መዋጮውን
ሁኔታ መርምሮ ሊያሻሻል ይችላል::
8.3.11. ማንኛውም የምክር ቤት አባል በሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባ ተገኝቶ ማዳመጥ ይችላል

8.4. የእድሩ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሥልጣንና ተግባር

8.4.1. የእድሩ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ወይም ተጠያቂነቱ ለእድሩ ምክር ቤት ይሆናል፣
8.4.2. የእድሩ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሰባት አባላት ይኖሩታል፤ እነርሱም ሊቀ መንበር፣ም/ሊቀመንበር፣ የኮሚቴው ጸሃፊ፣
አቃቤ ነዋይ፣ሂሳብ ሹም፣ የውስጥ ኦዲተርና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ናቸው።
8.4.3. የኮሚቴ አባላት የአገልግሎት ዘመን ሁለት አመት ነው፤ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ስብሰባ ምልአተ ጉባኤ አምስት
አባላት ሲገኙ ነው፤
8.4.4. ከሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት መካከል ሦስት አባላት በቅድሚያ ቀሪዎቹ አራቱ ደግሞ ተከትልው በአመቱ
የአገልግሎት ዘመናቸውን ይጨርሳሉ፤ የኮሚቴ አባላቱ በተከታታይ ለሁለት ጊዜ መመረጥ ይችላሉ፤
8.4.5. ኮሚቴው የእድሩን መተዳደሪያ ደንብ የማስከበር፣የማስፈጸምና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለው፤ እንዲሁም የጠቅላላ
ጉባኤውንና የምክር ቤቱን ውሳኔ በመከታተል ሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፤

4|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::
8.4.6. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ የእድሩን የአባላት መጠንና የገንዘብ ገቢውን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት
እንዳስፈላጊነቱ እየገመገመና እያጠና የእድር ክፍያ ጥቅም አከፉፈልን ወይም የእድር መዋጮውን ሁኔታ
አስመልክቶ ለእድሩ ምክር ቤት የማሻሻያ ሃሳብ ሊያቀርብ ይችላል::
8.4.7. የሂሳብ ሹሙ ለኮሚቴው የሚያቀረበውን አመታዊ የሂሳብ ሪፖርት ያዳምጣል፣ይመረምራል፤ አዘጋጅቶ
የሚያቀረበውን የእድሩን የሚቀጥለው ዓመት በጀት መርምሮ ያሻሽላል፣ያጸድቃል፤
8.4.8. ኮሚቴው ለስራው ክንውን የሚረዱ የስራ አፈጻጽም ስርዓቶች የእድሩን ደንብ በማይጻረር፡መልኩ ያሰናዳል።
በእድሩ ምክር ቤት ሲጽድቅም በሥራ ላይ ያውላል፤
8.4.9. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ለምክር ቤቱ ዓመታዊ የሥራ ክንውን/አፈጻጽም ረፖርቱን በዝርዝር ያቀርባል፤
8.4.10. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ማንኛውም ለአባላት የሚስጡ ክፍያዎችን በደንቡ መሠረት እያጣራ እንዲከፈል
ያደርጋል።
8.4.11. ኮሚቴው ማንኛውም የአስተዳደር ነክ ወጭዎችን ተገቢነታቸውን እየተመለከተ ወጪ እንዲደረጉ ይፈቅዳል።
ለምክር ቤቱ በሚያቀርበው ጠቅላላ ሪፖርት ውስጥ አካትቶ ስለ ወጪዎቹ ያስረዳል።

9. የእድሩ ምክር ቤት ሹማምንት ሥራ ድርሻና ሐላፊነት

9.1. የምክር ቤቱ ፕረዚዳንት


9.1.1. ፕረዚዳንቱ የአባላት ጠቅላላ ጉባኤንና የእድሩን ምክር ቤት አመታዊና አስቸኳይ ስብሰባዎችን ይመራል፣
ያስተባብራል፤
9.1.2. ፕረዚዳንቱ ድምጸ-አልቦ ሆኖ አልፎ አልፎ በሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ስብሰባዎች ላይ እየተገኘ የእድሩን ሂደት
የበላይ ሆኖ ይመለከታል፤
9.1.3. የአባላትን ስሞታ ሰምቶ ለሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ያስተላልፋል።

9.2. የምክር ቤቱ ም/ፕረዚዳንት


9.2.1. ም/ፕረዚዳንቱ ፕረዚዳንቱ በሌለበት ጊዜ ብቻ ተክቶ ስራውን ይሠራል።
9.2.2. ፕረዚዳንቱ በሚጠይቀው መሰረት ይረዳዋል።
9.2.3. በባንክ ሰነዶች ላይ ከሚፈርሙት አንዱ ነው።

9.3. የምክር ቤት ፀሃፊ


9.3.1. የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ እና የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ቃለ ጉባኤና ውሳኔዎች በሥርአት ቅደም ተከተል ቁጥር
በመስጠት በመዝገብ ይይዛል፤
9.3.2. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ የአባላትን ስምና የአገልግሎት ዘመን በመዝገብ ይይዛል።

9.4. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር


9.4.1. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴን ስብሰባን በተገቢ ሁኔታ ይመራል፣ያስተባብራል፣ይቆጣጠራል፣
9.4.2. እድሩን የሚመለከቱ ተግባራትና ጉዳዮችን በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት እንዲከናወኑ ያቅዳል ፣ ይመራል፤
ያስተባብራል፣ ይቆጣጠራል፣ ይፈጽማል፤
9.4.3. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባዎችን በተወሰኑ ጊዜያት እንዳስፈላጊነቱ ይጠራል፣
9.4.4. የእድሩን አጠቃላይ ሁኔታን አስመልክቶ የሥራ ክንውን/አፈጻጽም ሪፖርት ለመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው እንዲሁም
ለእደሩ ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባዎች ያቀረባል፤
9.4.5. የኮሚቴ አባላት ስለስብሰባው ቀደም ብለው መስማታቸውንም ያረጋግጣል።

9.5. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ም/ሊቀመንበር


9.5.1. ሊቀመንበሩ በሚጠይቀው መሠረት ይረዳዋል፣
9.5.2. ሊቀ መንበሩ በሌለበት ጊዜ የእርሱን ሥራ ይሠራል፣
9.5.3. በምክር ቤቱ ሲጠየቅ የአባላት መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎችን ያዘጋጃል
9.5.4. አባላት የሞሉትን ፎርሞቹንና ሌሎች ሰነዶችን በሥርአት ያስቀምጣል፤
9.5.5. በባንክ ሰነዶች ላይ ከሚፈርሙት አንዱ ነው።

5|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::
9.6. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ፀሐፊ
9.6.1. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባዎችን በሥርአት ቅደም ተከተል ቁጥር በመስጠት ይመዘግባል፣
9.6.2. የስብሰባዎችን ዉሳኔዎች ባጭሩ ጽፎ ለምክር ቤቱ አባላት በኢሜይል አለዚያም በየአድራሻቸው እንዲደርስ
ያደርጋል፤
9.6.3. የኮሚቴው ስብሰባዎች የውስጥ አጀንዳ ያዘጋጃል፤ቃለ-ጉባኤ ይይዛል፤
9.6.4. በባንክ ሰነዶች ላይ ከሚፈርሙት አንዱ ነው፤
9.6.5. ሌሎች የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ስራ ያከናውናል፤
9.6.6. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴን ውሳኔ ለሚመለከተው በጽሑፍ፡ያስታውቃል፤
9.6.7. የአባላትን ስምና አድራሻ በሥርዓት ይይዛል።

9.7. አቃቤ ነዋይ


9.7.1. ከአባላት በደረሰኝ የተሰበሰበው ገንዘብ ባንክ መግባቱን ይቆጣጠራል፣በአባሉ ስም መመዝገቡንም ያረጋግጣል፣
9.7.2. በደንቡ መሰረት አባላት መክፈል አለመክፈላቸውን ያረጋግጣል፣
9.7.3. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ለአባላት በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት የእድር ክፍያ እንዲከፈል ሲወስን የወጪ
አከፋፈል ሥርዓቱን በመከተል ይፈጽማል፣
9.7.4. ከአባላት በደረሰኝ ገንዘብ ይቀበላል፣ የተቀበለውን ገንዘብ ባንክ ያስገባል፣
9.7.5. አባላት መዋጮአቸውን በቀጥታ ባንክ ሲያስገቡ በሚደርሰው መረጃ መሠረት ደረሰኝ ይልክላቸዋል፤
9.7.6. የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ማንኛውም ለአባላት ወይም አካላት የሚስጡ ክፍያዎች ላይ ውሳኔ ሲያሳልፍ ወጪው
በቼክ ተፈርሞ በደንቡ መሠረት መሰጠቱን ተከታትሎ ይፈጽማል፤
9.7.7. በባንክ ሰነዶች ላይ ከሚፈርሙት አንዱ ነው።
9.7.8. ቼኮች በሦስት ሰዎች መፈረማቸውን ያረጋግጣል።

9.8. ሂሳብ ሹም
9.8.1. የእድሩን ዓመታዊ በጀት ያዘጋጃል፣ለሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ በማቅረብ ያጸድቃል፤
9.8.2. እያንዳንዱ አባል የሚከፍለውን በሥርአት ይመዘግባል፣ የያንዳንዱን አባል ክፍያዎች በስንጠርዥ (በExcel)
መመዝገብ አለበት፣
9.8.3. አባላት በደንቡ መሰረት መክፈል የሚገባቸውን ያስተጓጎሉትን ለህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በወቅቱ ያሳውቀዋል፣
9.8.4. ገቢና ወጪዎችን በሚገባ መዝግቦ በየወሩ ለሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሪፖርት ያቀርባል፣
9.8.5. የእድሩን የባንክ ሂሳብ ይይዛል፤ አመታዊ የሂሳብ ሪፖርትም ያዘጋጃል፣
9.8.6. ለመንግስት ተቋማት የሚቀርብ የሂሳብ ሪፖርትም ያዘጋጃል።

9.9. የውስጥ ኦዲትር


9.9.1. በሂሳብ ሹሙ የተዘጋጀውን ሂሳብ ይመረምራል፣
9.9.2. የእድሩን የሂሳብ አጠቃላይ ወጪና ገቢዎችንም በወቅቱ ይመረምራል፣ ይቆጣጠራል፣መረጃና ሰነዶችን
ይመለከታል።
9.9.3. ከኮሚቴው የእድሩን መዝገቦችና ሰነዶችን በመረከብ በሥርአትና በአግባብ መያዘቸውን፣መርምሮ ለአባላት ጠቅላላ
ጉባኤና ለእደሩ ምክር ቤት በመረጃ የተደገፈ ሪፖርት በስብሰባው ወቅት ያቅረባል።

9.10. የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ


9.10.1. እድሩን የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል፣ የእድር አባላት እንዲበዙ ለማድረግ ይጥራል፣ እንዲሁም የተለያዩ የ
ማስተዋወቅ (promotion) ዘዴዎችን እየተጠቀመ የአባላት ብዛት እንዲጨምር ይተጋል፣ ያስተባብራል፤
9.10.2. አዲስ አባላትን ፎርም ያስሞላል፣ ይቀበላል፤ የተሞላው ፎርም በደንቡ መሰረት መሟላቱን ያረጋግጣል::
9.10.3. አባላት የሚጠበቅባቸውን የእድር መመዝገቢያ፣ የእድር መዋጮ እና ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ መዋጮ ቅጣት
ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በወቅቱ እንዲከፍሉ ማስታወሻ ይልካል። ለያንዳንዱ አባል የተላከው ማስታወሻ
እንደኦፊሴላዊ ማስረጃ ሰለሚቆጠር መረጃው በተገቢው መያዙን/መቀመጡን ይከታተላል፣ያረጋግጣል ::
9.10.4. በማንኛውም የእድሩ ጉዳዩችን በተመላከተ አስፈላውን መረጃ ለአባላት ያስተላልፋል ወይም መተላለፉን
ይከታተላል፣ ያረጋግጣል::

10. የእድሩ ገንዘብ አያያዝ ሥርዓት

6|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::
10.1. እድሩ የሚተዳደረው ከአባላት ከሚሰበሰብ መዋጮ ነው፤
10.2. ኦስተን እድር በሚል ስም የባንክ ሂሳብ ይኖራል፤
10.3. ማንኛውም መዋጮ ባንክ ሂሳብ መግባት አለበት፤ አባላት የእድር መመዝገቢያ፣ የእድር መዋጮ እና ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ
መዋጮአቸውን ለመፈጸም በቀጥታ ወደ ባንክ ሊልኩ ይችላሉ፤ ለማስገባታቸው መረጃ ለጽህፈት ቤቱ ሲያቀርቡ ደረሰኝ
ይሰጣቸዋል፤
10.4. ባንክ ሂሳብ የሚንቀሳቀሰው ከአራት ፈራሚዎች በሶስት ስዎች ፊርማ ነው፤ ፈራሚዎቹ የምክር ቤቱ ም/ፕረዚዳንት፣ የሥራ
አስኪያጅ ኮሚቴ ም/ሊቀመንበሩ፣የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ጸሃፊና አቃቤ ነዋይ ናቸው፤
10.5. የውስጥ ኦዲተሩና ሂሳብ ሹሙ በቼክ ላይ የፈረሙት ከላይ በአንቀጽ 10.4 ላይ ከተጠቀሱት/ከተመደቡት ፈራሚዎች
መካከል መሆኑን ያረጋግጣሉ፣ይቆጣጠራሉ፤
10.6. ትንሽም ሆነ ትልቅ ወጪዎች ሁሉ የሚንቀሳቀሱት በቼክ ከባንክ ነው። የለት ተለት ወጪዎችን ለመሸፈን እንዲያሰችል የሥራ
አስኪያጅ ኮሚቴ የፔቲ ካሽ ፈንድ ይኖራል:: የፔቲ ካሹ መጠን በማንኛውም ጊዜ ከ $500 አይበልጥም::

11. ስነ ሥርአትና መቀጮ

11.1. የአባላት ትልቁ ሥነ-ሥርአት በአንቀጽ 6 የተመለከቱትን ክፍያዎችንና የመዋጮ ግዴታዎችን በጊዜው መክፈልና ማጠናቀቅ
ነው፤

11.2. እያንዳንዱ አባል እድሩ በዚህ ደንብ መሰረት ወጪ ያደረገውን የእድር ክፍያ ተመልሶ እንዲተካ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው
በይፉ ካሳወቀው ቀን ጀምሮ የሚፈለግበትን መዋጮ በአንድ ወር የጊዜ ገደብ ዉስጥ የመክፈል ግዴታ አለበት:: በተሰጠው
የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ባንክ ያላገባ ወይም ሳይከፍል የቀረ ሰው መቀጫ ይከፍላል፤ መቀጫው በየወሩ በአባል $5.00
ነው::
11.3. ማንኛውም አባል እድሩ በዚህ ደንብ መሰረት ወጪ ያደረገውን የእድር ክፍያ ተመልሶ እንዲተካ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው
በይፉ ካሳወቀው ቀን ጀምሮ የሚፈለግበትን መዋጮ በዘጠና (90) ቀን የጊዜ ገደብ ዉስጥ ባንክ ያላገባ ወይም ሳይከፍል
የቀረና ለመክፈሉ ማስረጃ ማቅረብ ያልቻለ እራሱን ከእድሩ እንዳስወጣ ተቆጥሮ አባልነቱ ይሰረዛል::
11.4. አባሉ የተጠየቀውን የእድር ክፍያን በተሰጠው የዘጠና (90) ቀን የጊዜ ገደብ ዉስጥ ሳይከፍል ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ
ከእድሩ የሚፈለግበት ውዝፉ መዋጮ ከእድር ክፍያው ተቀንሶ በቅድሚያ በወኪልነት ለተመዘገበ ተጠሪው ይከፈላል::
11.5. እያንዳንዱ አባል ለእድሩ የሥራ ማስኬጃ መዋጮ በዓመት አንድ ጊዜ የሚከፍለውን $10 በየዓመቱ በ January ወር ውስጥ
ከፍሎ የማጠናቀቅ ግዴታ አለበት:: አባሉ የእድሩ ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ መዋጮውን በወቅቱ ካልከፈለ ግን በየስድስት
(6) ወሩ የ $5 መቀጫ ይከፍላል::

12. ተመልሶ በአባልነት እንደገና ስለመቀጠል

12.1 ማንኛውም ግለሰብ የሚጠበቅበትን የእድር ክፍያ በዘጠና (90) ቀን የጊዜ ገደብ ዉስጥ ሳይከፍል ቀርቶ ከአባልነቱ
ከተሰረዘ በኋላ ተመልሶ አባል ለመሆን ቢጠይቅ ከመሰናበቱ በፊት ያልከፈለውን ውዝፉ ከፍሎ እንደአዲስ አባል የእድር
መመዝገቢያውን ጭምር በመክፈል እንደገና መመዝገብ ይችላል፣

13. ተጨማሪ ጉዳዮች

13.1. እድርተኛው ኦስተንን ወይም አካባቢዋን ለቆ ቢሄድ እና አባልነቱን መቀጠል ከፈለገ መቀጠል ይችላል። ነገር ግን የእደሩን
ጥቅም የሚያገኝው በሚለቅበት ጊዜ ተመዝግበው ላሉ ቤተሰቦቹ ብቻ ነው፤ሌላ መጨመር አይችልም።
13.2. ማንኛውም አባል ከእድሩ በፈቃደኝነት ወይም በሌላ ሁኔታ አባልነቱን ቢሰርዝ ያዋጣው ገንዘብ አይመለስለትም።
13.3. እድሩ ቢፈርስ በምክር ቤቱ አቅራቢነት የጠቅላላ ጉባኤው በሚወስነው መሠረት ንብረቱ በሕግ ለተመዘገበ የበጎ አድራጎት
ድርጅት ይሰጣል።

14. ደንቡ ሰለሚፀናነት ጊዜ

7|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::
14.1 ይህ ደንብ በ July 20, 2014 በተካሄደው የእድሩ መሥራች ጠቅላላ ጉባኤ ባፀደቀውና እንዲሻሻል በወሰነው
መሰረት ተዘጋጅቶ ከ October 19, 2014 ጀምሮ የፀና ይሆናል::

15. ሕጋዊነት

15.1 የቴክሳስ ሕግ በሚያዘው መሰረት ህልውናውም ሆነ የሥራ እንቅስቃሴው ህጋዊነቱን የጠበቀ ነው:: እድሩ አትራፊ
ያለሆነ ድርጅት ሰለሆነ በአባላቱ ላይ የሞት ሃዘን ሲደርስ እርስበርስ የመተባባር እና የመደጋገፍ ልዩ የበጐ መንፈስ ባህላችንን
ለማጠናከር ብቻ የሚሰራ ሕጋዊነት ያለው ድርጅት ነው::

16 ስለደንቡ መሻሻል

16.1 ይህ ደንብ በአባላት ጠቅላላ ጉባኤው በአንቀጽ 8.2.3 ላይ በሚያዘው መሰረት በማንኛውም ጊዜ ሊሻሻል ይችላል::
________________________________________________

8|Page
በ July 20, 2014 ጸድቆ በ October 19, 2014 ተሻሻለ::

You might also like