You are on page 1of 2

የቴኃላን ንግድና ኢንቨትመንት አክሲዮን ማህበር አጭር ማስተዋወቂያ

1. መግቢያ

ከኢትዮጵያ የንግድ ህግ አንዱ ዓላማ ለንግዱ ማህበረሰብ አማራጭ የንግድ አደረጃጀትን ማቅረብ ሲሆን ግቡም የንግድ ማህበረሰቡ ወዶ
እና ፈቅዶ እንደ ልዩ ፍላጎቱ፣ እንደ ካፒታል አቅሙ፣የሽሪኮቹን አቀራረብና የሃላፊነት ወሰኑን መሰረት በማድረግ በመደራጀት የንግድ ስራ
እንዲከውኑ ለማድረግ ሲሆን ይህንንም ለማድረግ ይቻል ዘንድ የንግድ ህጉ 7 የተለያዩ የንግድ ማህበራት አይነቶችን አስቀምጧል።
ከነዚህም ማሀከል የአክሲዮን ካምፓኒ (ማህበር) አንዱ ነው፡፡ (የንግድ ህግ አንቀጽ 212፡፡) የአክሲዮን ማህበራት በሃገራችን መበራከት
ሀገራዊ እና ግለሰባዊ ፋይዳ አለው፡፡ ሀገራዊ ፋይዳውን ስናይ አክሲዮን ማህበር ትልልቅና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቁ የንግድ
ዘርፎች (ለምሳሌ ባንክ፣መድን ድርጅት፣በግብርና ዘርፍ፣በቤቶች ግንባታ፤የንግድና ሁለገብ ገበያ ማእከላት ግንባታ ወዘተ) ላይ ለመሰማራት
የሚረዳ የማህበር አይነት በመሆኑ የእነዚህ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በሃገራችን መፈጠር ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ
ለመሰለፍ እያደረገች ያለውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል፡፡ በሌላ በኩል አክሲዮን ማህበር የግለሰቦችን ስራ ፈጣሪነት በማበረታታት
በግለሰብ ደረጃ ለመተግበር ከባድ የሆኑና ተለቅ ያለ ካፒታል የሚጠቁ የንግድና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በተባባረ ክንድ ለመተግበር
ዕድል ይሰጣል። በመሆኑም ግለሰቦች የገቢ አቅማቸውን ከመጨመር ጀምሮ የሀገርን ኢኮኖሚ እድገት ሊያፋጥን የሚችል የንግድ ሃሳብ
አመንጭተው ካፒታል ከአባላት በመሰብሰብ ለመስራት የሚያስችል በመሆኑ ለማህበሩ ካፒታል ያዋጡ አባላት ማህበሩ የሚያስገኘውን
ትርፍ የድርሻቸውን በመውሰድ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ያስችላል፡፡

2. የቴኃላን ንግድና ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማህበር (ቴኃላን)


ቴኃላን ዋና መሰረቱን ዳሎቻ በማድረግ ዝቅተኛና መካከለኛ የገንዘብ አቅም ያላቸውን ወጣቶች፣ ነጋዴዎችና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ
ግለሰቦችን በማቀፍ ትላልቅ ግቦችን አልሞ በምስረታ ላይ የሚገኝ የንግድና ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማህበር ነው። እንዳሚታወቀው ዳሎቻ
ከተማ ትልቅ ታሪክ ያላትና ከስልጤ ዞን ቀዳሚዋ ከተማ ስትሆን ከዚህ ቀደም በነበራት የክልሉ ትልቅ ገበያ መገኛ መሆኗ፣ የተለያዩ ማህበራዊና
ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በጥራትና በብቃት አቅራቢ የነበረች መሆኑ ብሎም በህዝቡ አቃፊነትና ተግባቢ ማህበራዊ እሴት ባለቤት መሆኗ
ለበርካታ ጉዳዮች ተመራጭ ከተማ የነበረች ናት። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ዳሎቻ ድሮ በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በንግድ፣ በከተሜነት ጥራት፣
በአገልግሎቶች አቅርቦት ወዘተ ቀድሞ የነበራትን የፊት መሪነት በዙሪያዋ ለሚገኙ አዳዲስ ከተሞች መልቀቅ ወደኋላ እየቀረች መታዘብና
መቆጨት የአብዛኛው ወጣቶች፣ የአመራሩ ና ልማት ወዳድ ነዋሪዎች ከሆነ ቆይቷል።
በመሆኑም በከተማዋ ያሉትን የልማት ችግሮች በተባበረ ክንድ የመቅረፍ እሳቤ ላይ በባለድርሻ አካላት ዘንድ የጋራ መግባባት የተፈጠረና በአሁኑ
ወቅት ያለዉ መንግስታዊ መዋቅርም 'ዳሎቻ በኛ ሲዝን (ጊዜ) መልማት አለባት' የሚል ቁርጠኛ አቋም ስለያዘና የከተማዋ ወጣቶችም ዘወትር
በከተማዋ ጉዳይ ከመቆጨትና ከጠያቂነት ባለፈ በአቅማቸው ተሳትፎ ማድረግና ተጠቃሚ መሆን የሚችለበትን ዕድል መፍጠር ዓላማ ያደረገ
ተግባር አስፈላጊ ነውና ይህንን ለማሳካት በዳሎቻ ከተማ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ጥራትና ውበት ደረጃዉን የጠበቀ ሁለገብ ገበያ ማዕከል
ለመገንባትና በተለያዩ ዘርፎች የሚሰማራ በአብላጫው ወጣቶችን ያቀፈ --- አባላት ያሉት የንግድ ማህበር (ቴኃላን) አስቀድሞ በተከፈለ 10
ሚሊዮን ብር ካፒታል በመመሰረት ላይ ነው።
3. የአክሲዮን ማህበር ምንነት
አክሲዮን ማህበር ማለት ቢያንስ በአምስት ሰዎች መካከል የሚቋቋም፣የህግ ሰውነት ያለው፣ካፒታሉ አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዮኖች የተከፋፈለ
እና የአባላቱ ኃላፊነት ለኩባንያው ካፒታል ባዋጡት ወይም በሚያዋጡት መጠን የተወሰነ የንግድ ማህበር ማለት ነው፡፡ (የንግድ ህግ አንቀጽ 210
(2), 304, 307 (1))፡፡ በንግድ ህጉ እንደተቀመጠው አክሲዮን ማህበር 4 መሠረታዊ ባህሪያት አሉት፦

ሀ. የአባላቱ ብዛት ከአምስት ሰዎች የማያንስ መሆኑ

አንድ የአክሲዮን ማህበር ሲመሰረት ዝቅተኛ የመስራች አባላት ብዛት አምስት ሰዎች የሚያስፈልጉት ሲሆን ከፍተኛው የአባላት ብዛት ጣሪያው
ያልተገደበ ነው፡፡

ለ. ካፒታሉ አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዬኖች የተከፋፈለ መሆኑ

የአክሲዮን ማህበሩ ካፒታል አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዬን የተከፋፈለ ነው። ይህም ማለት የአክሲዮን ማህበሩ ምስረታ ተግባር የሚጀምረው
ካፒታሉን፣የአንድ አክሲዮን አቻ ዋጋ እና ካፒታሉ በስንት አክሲዮን እንደሚከፋፈል በመወሰን ቢሆንም የካፒታሉ መነሻ ደግሞ ከ 50 ሺህ ብር
ማነስ የለበትም፡፡፡

ሐ. የአባላቱ ሃላፊነት የተወሰነ መሆኑ


የአክሲዮን ማህበር ሌላኛው ገፅታ ደግሞ ማህበሩ ከሦስተኛ ወገኖች ማለትም ከአበዳሪዎች፣ከደንበኞቹ እና ከሠራተኞቹ ወ.ዘ.ተ ጋር በሚያደርገው
ግንኙነት ጉዳት ሊያደርሥ ይችላል። በዚህ ወቅት የማህበሩ አባላት (ባለአክሲዮኖች) ሃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለውን ለመረዳት
በንግድ ህጋችን አንቀፅ 304(2) መሰረት የማህበሩ አባላት ሃላፊነት ለማህበሩ ካፒታል ባዋጡት ወይም በሚያዋጡት መጠን እንደሚሆኑ
ይደነግጋል:: ይህም ማለት አባላቱ ማህበሩ ሲመሠረት ወይም ከተመሰረተ በኋላ ለሽያጭ ከቀረበው የአክሲዮን ድርሻ ውስጥ በገዙት የአክሲዮን
መጠን ብቻ ተጠያቂ የሚሆኑ ሲሆን የአክሲዮን ማህበሩ ሃብት ጉዳቱን ለመካስ በቂ ሆኖ ባይገኝ ወደ ባለአክሲዮኖቹ ንብረት መሄድ አይቻልም፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የአባላቱ የግል እዳ ከኩባንያው ሃብት አይከፈልም፡፡
የአባላቱ ሃላፊነት መወሰን ግለሰባዊ እና ሃገራዊ አላማዎችን ለማሳካት ነው፡፡ ግለሰባዊ አላማውን ስናይ ሰዎች ሃላፊነትን ፈርተው ገንዘባቸውን
ቀብረው እንዳይቀሩ እና አውጥተው ለንግድ እንዲያውሉት ለማበረታታት ነው፡፡፡ የሀላፊነት መወሰን ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ሃገራዊ ሲሆን
ይህም ሀላፊነት ካልተወሰነ ሰው ወደ ንግድ እንቅስቃሴ ለመግባት ፋቃደኛ ስለማይሆን አገልግሎት አይስፋፋም፣የስራ እድል
አይፈጠርም፣ለመንግስት ግብር የሚሆን ገቢ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም ለሀገር ጥቅም ወይም ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ሲባል የአክሲዮን
ማህበሩ አባላት ሀላፊነት በገዙት አክሲዮን ልክ የተወሰነ ይሆናል፡፡

መ. የህግ ሰውነት
በንግድ ህጉ ውስጥ ከአሽሙር ሽርክና ማኅበር በሥተቀር የንግድ ማህበራት የህግ ሰውነት እንደሚኖራቸው በአንቀጽ 210(2) በግልፅ
ተደንግጓል፡፡ የህግ ሰውነት ዋና አላማ አንድ ግዑዝነት የሌለው ተቋም ከአባላቱ በተለየ የራሱ ህልውና (ህይወት) እንዳለው በመቁጠር የራሱ
መብት፣ንብረት፣ግዴታ ወዘተ ባለቤት በማድረግ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑበት ማህበር በአንድ ስያሜና በአንድ ውክልና እንዲሠራ ማስቻል ነው፡፡

4. የአክሲዮን ማህበር አመሰራረትና አይነቶች


4.1. አመሰራረት
አንድ አክሲዮን ማህበር እንደማንኛውም ድርጅት ጥንስሱ የሚጀምረው በአንድ ሰው ወይም በጥቂት ሰዎች አዕምሮ ነው፡፡ የሀሳቡ ባለቤት ሃሳቡን
ለሌሎቹ አካፍሎ የሚተባበሩትን ካገኘ በኋላ ለአክሲዮን ማህበሩ አስፈላጊ የሆኑ የህግ ቅድመ ሁኔታዎች ለማሟላት አብረው ይሰራሉ፡፡ ከቅድመ
ሁኔታዎቹ ውስጥ የካፒታሉን መጠን ስንት መሆን እንዳለበት፣ የአንድ አክሲዮን አቻ ዋጋ እና ካፒታሉ በስንት አክሲዮን እንደሚከፋፈል
ይወስናሉ። ይህ ከተደረገ በኋላ በአባላቱ መካከል አክስዮኖቹ ይከፋፈላሉ፡፡
በመስራች አባለቱ ከተወሰነው ካፒታል ላይ ቢያንስ እሩቡ ወይም ሃያ አምስት በመቶ ከተከፈለና በዝግ ሂሳብ ከተቀመጠ ለማህበሩ ምስረታ በቂ
እንደሆነ እና ምዝገባውም በአንድ አመት ውስጥ ካልተፈፀመ በዝግ ሂሳቡ ውስጥ የተቀመጠው ገንዘብ ለአዋጡት ተመላሽ እንደሚደረግ በአንቀፅ
312 በግልፅ ተደንግጓል፡፡ አክሲዮን ማህበሩ እነዚህን ቅደመ ሁኔታዎች ካሟላ በኋላ በንግድ ሚኒስቴር በሚተዳደር አገር አቀፍ የንግድ መዝገብ
ውስጥ መመዝገብ ይኖርበታል፡፡

4.2. የአክሲዮን ማህበራት አይነቶች

በንግድ ህጋችን አንቀጽ 316 እና 317 መሠረት አንድን የአክሲዮን ማህበር በሁለት አይነት መንገድ ማቋቋም ይቻላል፡፡ እነዚህም፡-

U. በመሥራቾች መካከል የሚመሰረት መቋቋም

የአክሲዮን ማህበር ለህዝብ አክሲዮን ሳይሸጥ ከአምስት በማያንሱ መስራቾች መካከል ሲቋቋም በአደራጆች መካከል ተቋቋመ ይባላል፡፡ በንግድ
ህጋችን አንቀጽ 316 መሰረት አንድ አክሲዮን ማህበር በአደራጆች ወይም በመስራቾች መካከል ለማቋቋም አራት መሠረታዊ ነገሮችን አደራጆች
በመመስረቻ ፅሁፍ ውስጥ ማሳየት ይጠበቅባቸዋለ፡-

 ሁሉም አክሲዮኖች የተያዙ መሆናቸውን


 በአንቀጽ 312(1)(ለ) መሠረት የካፒታሉ አንድ አራተኛ ተከፍሎ በዝግ ሂሳብ በባንክ መቀመጡን
 በአይነት የተደረገ መዋጮ በባለ አክሲዮኖች ተገምቶ ግምቱ መገለጽ አለበት( አዋጅ ቁጥር 376/2003 አንቀፅ 5(11))
 የተለያዩ የኩባንያው አስተዳደር አካላት ለምሳሌ የማህበሩ የቦርድ አባላት፣ኦዲተሮች እና ሥራ አስኪያጅ መሾሙን መገለፅ አለበት

ለ. አክሲዮን ለህዝብ በመሸጥ የሚቋቋም


በንግድ ህጋችን አንቀጽ 317 መሠረት የንግድ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች በመሀከላቸው ማህበሩን ማቋቋም ካልቻሉ ለህዝብ አክሲዮን በመሸጥ
ማህበሩን ማቋቋም ይችላሉ፡፡ የንግድ ሀሳቡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ከሆነ ገንዘቡን ትንሽ ሠዎችን በማሣመን መሠብሠብ
ስለሚያሥቸግር ለሕዝብ አክሲዮን በመሸጥ አክሲዮን ማህበሩን ማቋቋም ይችላሉ፡፡

5. ማጠቃለያ
አክሲዮን ማህበራት በሃገራችን አንቨስትምንትን እና ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠራቸው በተጨማሪ ዜጎች እንደ አቅማቸው የተለያየ መደብ
ያለቸውን አክሲዮኖች በመግዛት ማህበሩ በዓመት ከሚያስገኘው ትርፍ በመቀበል የተለያየ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ
ያስችላቸዋል፡፡ እንግዲህ የአክሲዮን ማህበራትን ፋይዳ፣ ባህርያት እና መቋቋም በዚህ ልክ በአጭሩ ከተመለከትን የቴኃላን አክሲዮን ማህበርን
በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች ከመመስረቻ ሰነዱና መተዳደሪያ ደንብ በቂ ግንዛቤ ወስዳችሁ የማህበሩ አባል እንድትሆኑ ጥሪ እናደጋለን::

ምንጭ፡-

በስራ ላይ የዋለው የኢትዮጵያ የንግድ ህግ /2012

You might also like