You are on page 1of 12

ኦርቶዶክሳዊ መምህር፣ ዕውቀቱ እና ክሂሎቱ

ማስተማር ምንድን ነው?

ጌታችን ሐዋርያትን ሲልካቸው የሰጣቸው የመጨረሻው መመርያ ለመምህራን ሁሉ መሠረት


ነው፡፡ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ እስከ ዓለም ዳርቻ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ» /የሐዋ
1÷8/ ይህ ቃል የአንድ ሐዋርያ ተግባር ፍጻሜ እንደሌለው ያስረዳናል፡፡ ሊቃውንቱ ይህንን
መመርያ በሁለት መንገድ ተርጉመውታል፡፡ (Arch bishop Anthonios Marqos, The
Theology of mission and missionary.)

1/ ከቅርብ እስከ ሩቅ፡- የአንድ ሐዋርያ ተግባር አጠገቡ ካለው ማኅበረሰብ ጀምሮ አይቶት እና
ሰምቶት እስከማያውቀው ሕዝብ ሊደርስ እንደሚችል

2/ ከቀላል ወደ ከባድ፡- ለአገልግሎቱ ቀላል ከሆነው አንሥቶ ውስብስብ እና አስቸጋሪ


ወደሆነው አገልግሎት፤ መሥዋዕትነት ከማይጠይቀው አገልግሎት መሥዋዕትነት እስከ
ሚጠይቀው አገልግሎት እንደሚደርስ ያስረዳል፡፡

በዚህ ተግባሩ የሚፈጽማቸው አገልግሎቶች በሁለት ዋና ዋና ተልዕኮዎች እና በአምስት ዝርዝር


ተልዕኮዎች ይጠቃለላሉ፡፡

ዋና ዋና ተልዕኮዎች

1. ያመኑትን ማጽናት፡- በወንጌል አምነው፣ በቤተ ክርስቲያን በረት ውስጥ ያሉ ምእመናን


በመናፍቃን፣ በከሃድያን እና በኢአማንያን እንዳይነጠቁ መጠበቅ

2. ያላመኑትን ማሳመን፡- ወደ ወንጌል ማዕድ ያልቀረቡ የአዳም ልጆችን ወደ ወንጌል ማዕድ


ቀርበው የመዳንን መንገድ ዐውቀው እንዲጓዙ ማድረግ

1
ዝርዝር ተልዕኮዎች

መመስከር፡- ወንጌልን ማስተማር

መምራት፡- ሕዝቡን በሕይወት፣ በዕውቀት እና በአሠራር አርአያ መሆን

ማሠልጠን፡- ቤተ ክርስቲያንን ሊመሩ፣ ሊያስተዳድሩ፣ ጉባኤያትን ሊያስተምሩ፣ ለሕዝቡ


አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ መሪዎችን ማሠልጠን

ማደራጀት፡- ጉባኤያትን፣ ማኅበራትን፣ ሰንበት ት/ቤቶችን፣ አጥቢያዎችን፣ ማደራጀት

መትከል፡- አጥቢያዎችን፣ ገዳማትን፣ ማሠልጠኛዎችን፣ የአብነት ት/ቤቶችን ወዘተ መትከል

እነዚህ ነገሮች የመምህራን ሥራ መድረክ ላይ ወጥቶ ከማስተማር በላይ መሆኑን ያስረዱናል፡፡


በሐዋርያት ሥራ ላይ የአበው ሐዋርያትን ተግባር ብንመለከት እነዚህን አምስት ተግባራት
በጉዞዎቻቸው ውስጥ እናገኛለን፡፡

አንዳንድ ሊቃውንት አንድ የወንጌል መምህር ሦስት ነገሮች ሊኖሩት ይገባል ይላሉ፡፡ እነዚህም

የማስተማር ቀደምት አበው ጉባኤ ዘርግተው፣ተዘዋውረው አስተምረዋል፡፡ ትምህርቶቻቸው


በዘመኑ የግሪክ ፍልስፍና የሚዋጅ፤ እንደ ዲዮናስዮስ ያሉ የአርዮስፋጎስ ሊቃውንትን የማረከ
ነበር፡፡ ኢየሱስ ከናዝሬት ወደ ገሊላ ሄደ የሚል ሳይሆን አዳዲስ ዕው ቀት በየዕለቱ የሚገኝበት
ነበር፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቁስጥንጥንያ ሐጊያ ሶፍያ ቤተ ክርስቲያን በየዕለቱ የሠርክ
ጉባኤ ነበረው፡፡ ትምህርቶቹን ተከታትለው ይጽፉ የነበሩ ደቀ መዛሙርትም ነበሩት፡፡ እርሱም
ትምህርቶቹን አስቀድሞ ይጽፋቸው ነበር፡፡ ባስልዮስ ዘቂሳርያም በቂሳርያ ከተማ በመሠረተው
ገዳም አያሌ ሕዝብ ያስተምር ነበር፡፡ በተለይም ዓምደኞች እየተባሉ ይጠሩ የነበሩ መምህራን
ሕዝቡን ሌሊትና ቀን ያስተምሩት ነበር፡፡ ስምዖን ዘዓምድ ከቆመበት ዓምድ ሳይወርድ ቀንና
ሌሊት ወደ እርሱ ይመጡ የነበሩትን ሁሉ አስተምሯል፡፡

የመጻፍ በሐዋርያውያን አበው እና ከእነርሱ በኋላ በተነሡ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ዘንድ
እነዚህን ሦስቱን ነገሮች እናገኛለን፡፡ ዛሬ በየድርሳኖቻቸው እና በሃይማኖተ አበው
የምናገኛቸውን ጽሑፎች እና መጻሕፍት ጽፈዋል፡፡ ትርጓሜያትን አዘጋጅተዋል፡፡ እንዲያውም
በሃይማኖተ አበው ላይ የምናገኛቸውን ድርሰቶቻቸውን ስናይ አበው እርስ በርሳቸው
በመልእክት ትምህርት ይለዋወጡ እንደ ነበር፣ጥያቄ ይጠያየቁ እንደነበር እንረዳለን፡፡

2
ከትምህርት መጻሕፍት በተጨማሪ እስከ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰጡ
የጸሎት፣ቅዳሴ፣የመዝሙር፣የሥርዓት መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል፡፡ ያዕቆብ ዘሥሩግ፣ ባስልዮስ፣
ዲዮስቆሮስ፣ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እና ሌሎች ቅዳሴ አዘጋጅተዋል፡፡ እነ አባ ሄሮኒመስ እና
ዮሐንስ አፈወርቅ ትርጓሜ ጽፈዋል፡፡ እነ ሄሬኔዎስ እና አቡሊዲስ ዘሮም ለዘመኑ መናፍቃን
ምላሽ ጽፈዋል፡፡ እነ ባስልዮስ እና አባ ኤፍሬም የጸሎት መጻሕፍት ደርሰዋል፡፡ እነ አውሳብዮስ
ዘቂሳርያ፣ ሶቅራጥስ እና ሩፊኖስ ታሪከን አደራጅተዋል፡፡ እነ አውግስጢኖስ የሕይወት
ታሪካቸውን ጽፈዋል፡፡ እነ ቅዱስ አትናቴ ዎስ የነገረ ሃይማኖት መጻሕፍትን እና የአበውን
ታሪክ ጽፈዋል፡፡

የመመራመር ተሰጥኦ ቀደምት አበው ዘመናቸውን ለመዋጀት ይችሉ ዘንድ የግሪክን እና


የሮምን ፍልስፍናዎች፣ የብሉይ ኪዳንን ትምህርቶች እና ባህሎች፣ የዘመን አቆጣጠር እና
የመልክዐ ምድራዊ ሥራዎች መርምረዋል፡፡ አቡሊዲስ ዘሮም ለብሉይ ኪዳን እንደ ዋና
መክፈቻ ቁልፍ የሚነገረውን የዘመን አቆጣጠር ትንተና አቅርቧል፡፡ ኤጲፋንዮስ ስለ ሥነ
ፍጥረት አክሲማሮስ የተሰኘ መጽሐፍ አቅርቦልናል፡፡ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ የመጽሐፍ ቅዱስን
መልክዐ ምድር አጥንቷል፡፡

የዕውቀት ምንጮች

አንድ መምህር ሊያስተምራቸው የሚችሉ ነገሮችን የሚያገኝባቸው ምንጮች በሁለት


ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም

መሠረታውያን እና ተጨማሪዎች ይባላሉ

የዕውቀት መሠረታውያን

የዕውቀት መሠረታውያን የምንላቸው የምእመናንን ሕይወት እና እምነት፣ የቤተ ክርስቲያንን


አካሄድ እና አሠራር የሚወስኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ምንጮች የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ
ለመመስከር እና ለማረጋገጥ የምናውላቸው ናቸው፡፡

የጌታችን ትምህርቶች ወደ ኋላ ሄደን ብሉይን ፣ወደፊት ተጉዘን ሐዲስን የምንተረጉመው


የቤተ ክርስቲያን መሠረቷ የሆነው ጌታችን በሰጠን መሠረት ላይ ሆነን ነው፡፡

3
የሐዋርያት ትምህርቶች፡ በወንጌል ተጽፎ የምናገኘው የጌታችን ትምህርት ለቤተ ክርስቲያን
መሠረቷ ነው፡፡ጌታችን ከዋለበት ውለው ካደረበት አድረው፣ ትምህርት ተአምራት
ሳይከፈልባቸው የተማሩ፣ የመጀመርያዋን ቤተ ክርስቲያን የመሠረቱ፣ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ
በልዩ ሁኔታ የተጠሩ ሐዋርያት ለቤተ ክርስቲያን ያስቀመ ጧቸው ትምህሮች፣ ሥርዓቶች እና
አሠራሮች የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እና አካሄድ ይወስናሉ፡

የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርቶች፡ ከሐዋርያት የተቀበሉትን ትምህርት፣ሕይወት እና


ሥርዓት ለቤተ ክርስቲያን አደራጅተው እና አብራርተው፣ያስረከቡ አበው ለቤተ ክርስቲያን
ትምህርት እና ጉዞ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ አንድን አባት የቤተ
ክርስቲያን አባት የሚያደርገው አራት ነገሮችን ሲያሟላ ነው፡፡

1. ርቱዕ የሆነውን ኦርቶዶክሳዊ እምነት አምኖ ሲያስተምር

2. ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የሚረዳ መጽሐፍ ሲጽፍ እና

3. ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለመፈጸም ሲችል

4. ለሌሎች አርአያ የሚሆን የቅድስና ሕይወትን ሲኖር (H.G. Bishop Moussa, The
Characteristics of Orthodox Teaching. P ,85)

አንድ ኦርቶዶክሳዊ መምህር የቤተ ክርስቲያን አባቶችን በተመለከተ ሊከተላቸው የሚገቡት


መርሖች አሉ፡

1. የአባቶችን ሕይወት ማጥናት

የአባቶችን ሕይወት ማጥናት ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት የሚያበረታ፣ የሚያተጋ እና


የሚያበረታታ ነገር ይገኝበታል፡፡

መንፈሳዊ ልምዳችንን ይጨምርልናል፡፡ ለተለያዩ ችግሮች እና ሁኔታዎች ምን ማድረግ


እንዳለብን ተግባራዊ ልምድ እናገኛለን፡፡

የተለያዩ እሴቶችን እንማርበታለን፡፡ የተለያዩ አበው ልዩ ልዩ ጸጋ፣ ተሰጥኦ እና ደረጃ አላቸው፡፡


የልዩ ልዩ አበውን ሕይወት ስናጠና እነዚህን ነገሮች እናገኛለን፡፡ ከአትናቴዎስ ለሃይማኖት
መጽናትን፣ ከእንጦንስ ራስን መግዛትን፣ ከአርሳንዮስ ትኅትናን፣ ከዲዮስቆሮስ ሃይማኖትን
በድፍረት እና በእውነት መመስከርን፣ ከአባ ቢሾይ ጸሎት እና ፍቅርን፣ እንማራለን፡፡

4
በአማላጅነታቸው እንድንጠቀም ያደርገናል፡፡

2. የአባቶችን ትምህርት እና አባባል ማጥናት

አንዳንዶች ያለፈውን መጥቀስ እና ካለፈው መነሳት ትውፊታዊነት ወይንም ያለፈውን ብቻ


የማድነቅ አባዜ ያደርጉታል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ክርስትና በኛ አልተጀመረም፤ እኛ ለክርስትና
ተቀባዮች እንጂ ጀማሪዎች አይደለንም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ደግሞ ዘመናት
በጨመሩ ቁጥር የቅድስና ሕይወት እየደከመ እንጂ እየበረታ አይሄድም፡፡ ስለዚህም በእምነት
ረገድ ያለፉት ከኛ ይሻላሉ፡፡

በመሆኑም አንድ ኦርቶዶክሳዊ መምህር የአባቶችን ትምህርት አጥንቶ ትምህርቱን በእነርሱ


መሥመር ማድረግና በትምህርቱም እነርሱን መጥቀስ ይኖርበታል፡፡

3. ሕይወቱን እና ትምህርቱን በአባቶች ሕይወት እና ትምህርት መሠረት ማድረግ

እኛ አባቶች ፈጽመው አይሳሳቱም infallible ብለን አናምንም፡፡ ሰው የመሆን ስሕተቶችን


ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የዶግማ እና የሥነ ምግባር ጥፋቶችን አይሠሩም፡፡ በትንታኔያቸው
አና በትርጓሜያቸው አንዱ ከሌላው ሊለዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን በኦርቶዶክሳዊ እምነታቸው እና
ሕይወታቸው አንድ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሊቅነታቸው የምናደንቃቸው ቢሆንም እነዚያን
አራት ነገሮች ካላሟሉ ግን «የቤተ ክርስቲያን አባት» አንላቸውም፡፡ ለምሳሌ አርጌንስ በኑሮው
እና በድርሰቱ የሚደነቅ ቢሆንም ክርስትናን ከግሪክ ፍልስፍና በመቀላቀሉ «የቤተ ክርስቲያን
አባት» አይባልም፡፡

እንዴት እናንባቸው?

አበውን በአጠቃላይ ማንበብ አለብን፡፡ ምክንያቱም አንዱ በሌላው ይሟላሉና፡፡ ሃሳባቸውን፣


የተነሡበትን ምክንያትና ሌሎች ነገሮችን ተተን አንድን ሃሳብ ብቻ ለራሳችን መደገፊያ
መጠቀም የለብንም፡፡ በርግጥ እንደ ተሰጥኦዋቸው ልዩነት ቢኖርም የሁሉም አንድ ማዕከላዊ
ነገር ግን ኦርቶዶክሳዊ እምነት እና ሕይወት ነው፡፡

የነበሩበትን ዘመን፣ ሁኔታ እና ለነማን እንደ ጻፉት መረዳት አለብን፡፡ መጀመርያ የተጻፈበትን
ቋንቋ፤ በዘመናቸው የነበረውን የሃይማኖት እና የሥነ ምግባር ችግር ማጤን አለብን፡፡

የቤተ ክርስቲያን አባቶችን በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ ይህ አከፋፈል በአብዛኞቹ


ሊቃውንት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ እንደ መክፈያ ዘመን የሚጠቀሙትም የመጀመርያውን
ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ የሆነውን ኒቂያን ነው፡፡

5
1. ቅድመ ኒቂያውያን /pre Nicene /

እነዚህ አባቶች በአብዛኛው ከፈላስፎች እና ከግኖስቲኮች ጋር የተከራከሩ፤ የመጀመርያዎቹ


አበው ናቸው፡፡ ጽሑፎቻቸውም በአብዛኛው አልተገኙም፡፡ ዮስጢኖስ ሰማዕት፣ ሄሬኔዎስ፣
ሄርማን፣ ታትያን፣ አቴናጎራስ፣ ቀሌምንጦስ ዘሮም፣ ፓፒያን፣ዲዮናስዮስ፣አግናጥዮስ ምጥው
ለአንበሳ፣ወዘተ

2. ድኅረ ኒቂያውያን /post Nicene/


እነዚህኞቹ አበው ከመናፍቃን ጋር የተከራከሩ ናቸው፡፡ በተለይም አርዮሳውያንን፣
ንስጥሮሳውያንን፣ አቡሊናርዮሳውያንን ተከራክረዋል፡፡ በአብዛኛው ካለፉት በተሻለ
ጽሑፎቻቸውን እናገኛለን፡፡ አውግስጢኖስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አትናቴዎስ፣ ጎርጎርዮስ
ዘኑሲስ፣ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ ባስልዮስ፣ ቄርሎስ፣ ኤፍሬም ሶርያዊ፣ ዲዮስቆሮስ፣ ወዘተ
ናቸው፡፡

ከዘመናቸውም በተጨማሪ በጻፉበት እና ባስተማሩበት ቋንቋ ምክንያትም በሁለት ይከፈላሉ፡፡


እነዚሀም

1. በግሪክ ቋንቋ የጻፉ፡ በአብዛኛው በግብጽ፣ ቁስጥንጥንያ፣ ሶርያ፣ አርመንያ፣ አንጾኪያ


የነበሩ

2. በላቲን ቋንቋ የጻፉ፡ በአብዛኛው በምዕራብ አውሮፓና በሰሜን አፍሪካ የነበሩ፡፡

በሌላም በኩል ባስተማሩበት ሀገርም ይከፈላሉ፡

 ሮማውያን፡ በሮም እና የሮም ሀገረ ስብከት በነበሩት ቦታዎች ያስተማሩና የጻፉ፡፡ እነ


አውግስጢኖስ፣ ዲዮናስዮስ፣ ቀሌምንጦስ ዘሮም፣ ሄሮኒመስ፣ ወዘተ

 ግብፃውያን፡ በግብጽ እና በሀገረ ስብከቷ የጻፉ፣ ያስተማሩ፡፡ ለምሳሌ አትናቴዎስ፣


ዲዮናስዮስ፣ ዲዮስቆሮስ፣ ቄርሎስ፣ ወዘተ

 አንጾኪያውያን/ቀጰዶቅያውያን/፡ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ ባስልዮስ፣


ወዘተ

 አርመናውያን፡ ለምሳሌ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ

6
 ሶርያውያን፡ ለምሳሌ ኤፍሬም ሶርያዊ

 ኢትዮጵያውያን፡ ቅዱስ ያሬድ፣አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ ርቱዐ ሃይማኖት፣ ወዘተ

የአበውን ትምህርቶች ለማጥናት እንድንችል ጽሑፎቻቸውን በይዘታቸው መከፋፈልም


ይቻላል፡

• ትርጓሜያት /Exegetics/ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመተርጎም የተጻፉ

• የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት መጠበቅ /Apologetics/ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት


ለማስረዳትና ከብረዛ ለመጠበቅ የተጻፉ

• ትምህርቶች /Sermons and Essays/ ስለ ሕይወት፣ስለ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ስለ


ሥነ ምግባር፣ስለ ልዩ ልዩ በዓላት፣ወዘተ የሚያብራሩ ጽሑፎች

• መልእክታት/Epistles/ ወደ ልዩ ልዩ ቦታዎች የተላኩ መልእክታት

• ቅዳሴያት/liturgies/

• መዝሙራት እና ጸሎቶች/ Poetry and Hymns of Praise/

• ክርክሮች /Dialogues/ በልዩ ልዩ ጊዜ ስለ ሃይማት ጉዳዮች የተደረጉ ክርክሮች

• ምናኔያውያን / Ascetics/ ስለ ምንኩስና፣ብሕትውና እና የምናኔ ሕይወት የተጻፉ

• ሕግጋት እና ሥርዓታት/Church Law/ ቤተ ክርስቲያን የምትመራባቸውን ልዩ ልዩ


ሥርዓቶች እና አሠራሮች የደነገጉባቸው ጽሑፎች

የታሪክ መጻሕፍት/Ecclesiastical history/ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በተመለከተ የተጻፉ


(Fr.Tadros Yacoub Malaty. An Introduction of Patrology.)

ኢትዮጵያውያን አባቶች

7
ለቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት፣ የመዝሙር፣ የቅኔ፣ የቅዳሴ እና የሥርዓተ መጻሕፍትን የጻፉ
ኢትዮጵያውያን አበው «ኢትዮጵያውያን አበው» ይባላሉ፡፡

እነዚህ አባቶች በሦስት ይከፈላሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና የቤተ ክርስቲያን መምህራን

1. የቤተ ክርስቲያን አባቶች፡ የምንላቸው ከፍ ብለን ያየናቸውን አራቱን መመዘኛዎች


ያሟሉትን ነው፡፡እነዚህ አበው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ገብተው ቅዱሳን ተብለዋል፡፡
እነርሱም ቅዱስ ያሬድ፣ ርቱዐ ሃይማኖት፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣እነ አባ ጽጌ
ድንግል፣እጨጌ ዕንባቆም፣ ወዘተ ናቸው

2. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፡ የምንላቸው በሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው ቅዱሳን


ለመባል ግን የቤተ ክርስቲያንን ውሳኔ ያላገኙትን ነው፡፡ ከጥንቶቹ የመልክዐ ሥላሴን
ደራሲ መምህር ስብሐት ለአብን፣ እነ መምህር ኤስድሮስን፤ እነ መምህር አካለ
ወልድን፣ ወዘተ፣ ከአሁኖቹ እነ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን ያካትታል፡፡

3. የቤተ ክርስቲያን መምህራን በየቤተ ክርስቲያን መምህራን የምንላቸው በማስተማር


እና በድርሰት በርትተው በሕይወታቸው ምክንያት የቅድስና ማዕረግ ያላገኙትን ነው፡፡
እነ ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ፣ እነ ንግሥት ዕሌኒ፣ እነ ዐፄ ናዖድ፣ ፡በትምህርት፣በድርሰት አና
በልዩ ልዩ አገልግሎት ቢበረቱም በኑሮ ዐንቅፋት ገጥሟቸዋል፡፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት፡ ሁሉም ነገር በመጽሐፍ አልተጻፈም፤ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት
ውስጥ በጸሎቱ፣ በማኅሌቱ፣ በቅዳሴው፣ወዘተ የምናገኛቸው ትምህርቶች እና ሥርዓቶች ለቤተ
ክርስቲያን ርቱዐዊ ጉዞ አስፈላጊ ናቸው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ውሳኔዎችበየዘመናቱ የተነሡ መናፍቃንን፣ በየጊዜው የተፈጠሩ
ችግሮችን፣ በየሁኔታው የገጠሙ ፈተናዎችን ለመፍታት በጉባኤያት ተሰብስበው አበው
የደነገጓቸው ድንጋጌዎች ቤተ ክርስቲያን ከማዕበል ወጥታ ወደ ጸጥታ ወደብ እንድታመራ
ያደረጉ፤ የቤተ ክርስቲያንንም አንድነት ያጸኑ ዋልታዎች ናቸው፡፡

8
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁለት ዓይነት ጉባኤያት ተደርገዋል፡፡
1. ዓለም ዐቀፍ ጉባኤያት፡ እነዚህ ጉባኤያት በወቅቱ የነበሩ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት
የተሳተፉባቸው፣ የቤተ ክርስቲያንንም ጉዞ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ጉባኤያት
ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በ325 ዓም የተደረገውን ጉባኤ ኒቂያ፣ በ381 ዓም
የተደረገውን ጉባኤ ቁስጥንጥንያ እና በ431 የተደረገውን ጉባኤ ኤፌሶን ትቀበላለች፡፡
ለሌሎቹ ግን ርቱዓን ናቸው ብላ ዕውቅና አትሰጥም፡፡
2. አካባቢያዊ ጉባኤያት እነዚህ ጉባኤያት በአንድ አካባቢ የተነሡ ችግሮችን ለመፍታት
በአካባቢው የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት የሠሯቸው ጉባኤያት ናቸው፡፡ የእስክንድርያ፣
የጋንግራ፣ የዕንቆራ፣ የካርታጎ ወዘተ እየተባሉ የሚጠሩ ጉባኤያት ናቸው፡፡ በሀገራችንም
በ14ኛው መክዘ የተደረገውን የደብረ ምጥማቅ ጉባኤ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንድ የቤተ
ክርስቲያን መምህር በእነዚህ በሁለቱ ዓይነት ጉባኤያት የተወሰኑ ውሳኔዎችን ማወቅ
አለበት፡፡

ተጨማሪ ዕውቀቶች
አንድ አስተማሪ ቅዱሳት መጻሕፍትን ስላወቀ ብቻ ሊያስተምር አይችልም፡፡ ዘመኑንም ማወቅ
አለበት፡፡ ዘመኑን ማወቅ ማለት ደግሞ፡
 የዘመኑን አስተሳሰብ ማወቅ
 የዘመኑን ችግሮች ማወቅ
 የዘመኑን ጥያቄዎች ማወቅ
 የዘመኑን የአኗኗር ሁኔታ ማወቅ
 የዘመኑን ሥርዓተ ማኅበር ማወቅ ማለት ነው፡፡
እነዚሀን ነገሮች ለማወቅ ደግሞ ሚዲያዎችን መከታተል፣ የዘመኑን ወሳኝ መጻሕፍት
ማንበብ እና አካባቢን ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ሃብታም እና
ድኻ፣ ጋብቻ፣ ወዘተ መጻሕፍቱን ስናነብ ሊቁ ዘመኑን እንዴት እንደተረዳው እናውቃለን፡፡
የግሪክን ፈላስፎች፣ የዘመኑን ዜናዎች፣ የወቅቱን የአኗኗር ባህል በውስጡ ይተነትናቸዋል፡፡
ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የጻፈውን የሙሴ ሕይወት ስናነብ የግሪክ ፈላስፎችን አመለካከት እንዴት
እንዳፈረሰ እናያለን፡፡
አንድ አስተማሪ ከላይ ያሉትን ምንጮች መጠቀም የሚያስችሉት ሦስት መሣርያዎች አሉ፡፡
እነርሱም
 የማንበብ ልምድ
 መረጃ የማሰባሰብ ልምድ እና
 የቋንቋ ችሎታ ናቸው፡፡
9
1. የማንበብ ልምድ፡
የማያነብ ሰባኪ ባያስተምር ይመረጣል፡፡ ከሚደርቅ ምንጭ የሚያረካ ውኃ አይገኝምና፡፡
ማንበብ ደግሞ ከመጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ተንቀሳቃሽ መጻሕፍት ከሆኑት ሊቃውንት
መማርም ነው፡፡ ከቀደሙት አበውም ሆነ ከማንደርስበት የዕውቀት ምንጭ መማር የምንችለው
በማንበብ ነው፡፡ ስለዚህም ሰባኪው የማነበብ እና የማጣጣም ልምድ ሊያዳብር ይገባዋል፡፡
ወስኖ፣ ጊዜ እና ገንዘብ መድቦ ማንበብ ልምድ መሆን አለበት፡፡ የምናነባቸው መጻሕፍት እንደ
በያይነቱ ምግብ ከሁሉም አቅጣጫ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ የሕክምና ሰዎች ልዩ ልዩ ዓይነት
ምግብ የሚመገብ ሰው የተለያዩ ቫይታሚኖች፣ ማዐድኖች እና ገንቢ ነገሮች የማግኘት ዕድሉ
ይሰፋል እንደሚሉት ሁሉ ልዩ ልዩ ዓይነት መጻሕፍትን ማንበብም እንደዚሁ ነው፡፡
2. የማሰባሰብ ልምድ፡
የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት በቀላሉ አይገኙም፡፡ በየገዳማቱ እና በየሊቃውንቱ፤ በየቤተ
መጻሕፍቱ እና በየሙዝየሙ ተበትነዋል፡፡ እነዚሀን ለማገኘት ትእግሥት እና ጥረት
ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎችን በኮፒ፣ በድምጽ፣ በማስታወሻ፣ በኣካል እና በአእምሮ የማሰባሰብ
ልምድ ያስፈልጋል፡፡
3. የቋንቋ ችሎታ፡
ግእዝን፣ ዐረብኛን፣ ዕብራይስጥን እና ግሪክን የመሳሰሉ ቋንቋዎች የጥንት ጽሑፎችን
ለመመርመር፤ እንግሊዝኛ ደግሞ በዘመኑ የተጻፉትንም ሆነ የተተረጎሙትን ለማግኘት
አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ዐቅማችን የፈቀደውን ያህል ብናውቃቸው በሩ ወለል ብሎ
ይከፈትልናል፡፡

የማስተማር ዓላማ
ኦርቶዶክሳዊ የማስተማር ዐላማው ማስደነቅ፣ ማስደመም፣ ማዝናናት፣ ማሳወቅ፣
ማስጨብጨብ፣ ወዘተ አይደለም፡፡ ማዳን ነው፡፡ (Tadros The Syrian, Orthodox
Teaching. P 35) ሰዎች እግዚአብሔርን ዐውቀው፣ በክርስትና ሕይወት ኖረው፣ መንግሥተ
ሰማያትን እንዲወርሱ ማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያዊው ሄሬኔዎስ በጻፈው «መድፍነ መናፍቃን»
በተሰኘው መጽሐፉ መግቢያ ላይ ማርቅያኖስ የተባለውን ልጁን ሲመክረው «ይህንን
የምጽፍልህ ከጥቂቱ ነገር ብዙ ዐውቀህ፣ የእውነትንም ልዩ ልዩ ክፍሎች ተረድተህ፣
የእግዚአብሔር የሆኑትን ነገሮችም ተገንዝበህ፣ የመዳንን ፍሬ እንድታፈራ ነው» ብሏል፡፡ ለዚህ
ደግሞ ማሳመን፣ ማሳተፍ እና ማስቀጠል ወሳኞቹ ናቸው፡፡ (Irnaeus, On The apostolic
preaching. P 29)

10
 ማሳመን፡ ማለት አንድን ሰው በበቂ ኦርቶዶክሳዊ ዕውቀት ማስታጠቅ ነው፡፡
እንዳይናወጽ እና እንዳይወድቅ አድርጎ መትከል ነው፡፡ ነገ መምህሩ እንኳን ባይኖር
ተማሪው በራሱ ሊኖር እንዲችል አድርጎ መገንባት ነው፡፡
 ማሳተፍ ደግሞ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡
 ማስቀጠል ደግሞ እየጾመ፣ እየጸለየ፣ አሥራት እያወጣ፣ ሰንበቴ እየጠጣ፣ እየተማረ፣
እያስተማረ፣ እየጻፈ፣ እየቀደሰ፣ እያስቀደሰ፣ ወዘተ በአገልግሎት እንዲቀጥል ማድረግ
ነው፡፡
በዚህ ጉዞ ውስጥ ሰባኪው ምእመናን በሦስት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ጽናት መለካት አለበት

1. በዕውቀት የታነጹ እንዲሆኑ፡ ኦርቶዶክሳዊውን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ሕግ፣ የአበው


ታሪክ፣ ወዘተ በሚገባ ማወቃቸውንና ለመመስከር በሚያበቃ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን
ማረጋጥ
2. በክርስቲያናዊ ኑሮ የታነጹ እንዲሆኑ፡ ክርስቲያኖች በሦስቱ መሠረታውያን እሴቶች
ማለትም በጾም ፣ጸሎት እና ምጽዋት፤ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚሳተፉ እንዲሆኑ፤
በጎ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እና ከነቀፋ የጸዱ እንዲሆኑ መከታተል
3. በልዩ ልዩ ግንኙነቶች ርቱዓን እንዲሆኑ፡ ከማኅበረሰቡ፣ ከትዳር አጋሮቻቸው፣
ከቤተሰባቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከንግድ አጋሮቻቸው ወዘተ ጋር በእምነት
የተቃኘ፣ በሥነ ምግባር የተጎበኘ አቀራረብ እና አኗኗር እንዲኖራቸው፡፡
በአሁን ዘመን ያሉ ሰባክያን የሚያስፈልጓቸው አምስት ነገሮች
1. የውይይት እና የዕውቀት መገበያያ መርሐ ግብሮች
ሰባክያን ያገኟቸውን ዕውቀቶች፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች እና ያቀዷቸውን ሃሳቦች
የሚመካከሩባቸው የዕውቀት ጉባኤያት ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ጉባኤያት ጥናቶችን፣
ትምህርቶችን፣ ውይይቶችን እና የልምድ ልውውጦችን ማካተት አለባቸው፡፡ ይህን የመሰሉ
መድረኮች በሀገር አቀፍም ሆነ በአካባቢ ደረጃ ሊመሠረቱ ይችላሉ፡፡

2. ተተኪዎችን ማፍራት
ፍላጎት እና ተነሣሽነት ያላቸውን ማሳወቅ እንጂ የሚያውቁትን ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረግ
ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም ጥረት፣ ትጋት እና ፍላጎት ያላቸውን መርጦ በግል፣ በቡድን እና
በማኅበር በማሠልጠን ማሠማራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን እንደምናደርገው ሲንቀሳቀሱ
የማይታዩትን ለማንቀሳቀስ ከመሞከር፤ የሚንቀሳቀሱትን የሰሉ የበቁ እንዲሆኑ ማድረግ
ይሻላል፡፡

11
3. ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም
ቪዲዮ፣ መቅረጸ ድምፅ፣ ኮምፒውተር ወዘተ የመሳሰሉትን መሣርያዎችን በበቂ ሁኔታ
መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተለየም ሰባክያን የኢንተርኔትን አጠቃቀም አውቀው ብሎ ጎችን
በመክፈት፣ ዌብሳይቶችን በማዘጋጀት፣ የኢሜይል ትምህርቶችን በመላክ ወዘተ እንዲሳተፉ
መደረግ አለበት፡፡
4. መንፈሳዊ ድፍረት እና ንቃት
ዛሬ ዛሬ መድረኮቻችን ዕውቀት እና ሕይወት በሌላቸው ሰባክያን እየተሞሉ ይመስላል፡፡
እነዚህ ሰባክያን ያላቸው አንድ ነገር ቢኖር ድቅድቅ ድፍረት ነው፡፡ ሌሎች በትኅትና ዝም ሲሉ
እነርሱ በድፍረት ያልሆኑትን ነን ብለው ወጡ፡፡ ስለዚህም ያልተማሩትንም፣ የማያምኑበትንም
ያስተምራሉ፡፡ አሁን ከእውነተኞቹ መምህራን መንፈሳዊ ድፍረት እና አካላዊ እና ሥነ ልቡናዊ
ንቃት ያስፈልጋል፡፡ ራሳችሁን በዕውቀት እና በአተያይ አዘምኑ፡፡
የምታውቁትን ሁሉ «እናውቃለን፤ ግን አይጠቅምም ብለን ተውነው» ለማለት ማቻል
አለባችሁ፡፡
የትምህርት ደረጃዎቻችንንም እናሻሽል፡፡ ወደፊት ከአብነት ትምህርት ቤት የሚመጡት
እያነሡ፤ ከዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የሚመጡት እየበዙ ነው የሚሄዱት፡፡ ስለሆነም
አብረናቸው ማደግ ይኖርብናል፡፡ ካልሆነም በማንበብ እና በመከታተል ራሳችንን ማብቃት
አለብን፡፡
5. በመዋቅር መሥራት ነገር ግን ያለ መዋቅር ማሰብ
ሥራን በአደረጃጀት፣ በመዋቅር እና በተቋማዊ መንገድ መሥራት መልካም ነው፡፡ ሃሳብን ግን
በመዋቅር ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ መዋቅሮች ይረዱናል፤ ያግዙናል እንጂ አይተኩንም፡፡
ስለሆነም ለማንበብም፣ ለመጻፍም፣ ለማስተማርም፣ ለመማርም፣ ለማደግም፣ ለመሻሻልም፣
ወንጌልን ለማስፋፋትም፣ ለማሠልጠንም መዋቅርን እና መዋቅርን ብቻ መጠበቅ የለብንም፡፡
አንዳንዶቻችን በኮሚቴ፣ በማኅበር፣ በቡድን፣ በጽዋ ካልተሰበሰብን ሥራ መሥራት የምንችል
አይመስለንም፡፡ እነዚህ ሁሉ ለሥራ መልካም ሊሆኑ ይችላሉ ለማሰብ ግን መሰብሰብ
አያስፈልግም፤ መጸለይ እና መጨነቅ እንጂ፡፡ ከመዋቀራችን በፊት ሰው ነበርን፡፡ ስለሆነም
መጀመርያ የሰውነታችንን ሥራ እንሥራ፡፡ በጀት ፈልገን፣ ሰው አስተባብረን ለመሥራት
እንሞክር እንጂ ሁሉን በዕቅድ እና በበጀት፣ በመመርያ እና በስብሰባ አናድርገው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

12

You might also like