You are on page 1of 10

የተሸሻለዉ የጤና ባለሙያዎች የዝዉዉርና ምደባ አፈፃፀም መመሪያ

ጤና ጥበቃ ቢሮ
ሚያዚያ/2011 ዓ.ም
ባ/ዳር
መግቢያ
የጤና አገልግሎቱን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ የሰው ሀብት ስራ አማራር ማስፈፀሚያ መመሪያዎች መኖር ወሳኝ ሚና አላቸው
ዝውውር ፣ ቅጥር ፣ የደረጃ እድገት እና ምደባ ለጤና ባለሙያዎች መብትና ጥቅም መከበር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አኳያ ልዩ ስፍራ
ይሰጠዋል፡፡ ትክክለኛ የጤና ባለሙያዎች ስምሪት መኖር የጤና ባለሙያዎች ስራቸውን በተረጋጋና በጥሩ መንፈስ ለማከናወን ያስችላቸዋል፡፡
ከአሁን በፊት የጤና ባለሙያዎች የዝውውርና ምደባ አፈፃፀም መመሪያ ወጦ ተግባራዊ ሲሆን የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጅ
በአፈፃፀም ላይ አንዳንድ ችግር ያለባቸው በመሆኑ እንደገና መከለስ አስፈልጓል፡፡ ከታዩት ችግሮች ዋና ዋናዎቹ መካከል የጤና ባለሙያዎች
የዕርስ በዕርስ ዝውውር የሚፈቅድ አለመሆኑ ፣ ልዩ ድጋፍ የሚሹ የጤና ባለሙያዎች የልዩ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ አለማድረጉ ፣ የስራ ቦታ
ነጥብ አሰጣጥ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አለመሆኑንና ሌሎች የአፈፃፀም ችግሮችን በመለየት የአብክመ ሲቪል ሰርቪስ
ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 253/2010 አንቀጽ 96 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህንን የተሻሻለው የጤና ባለሙያዎች ዝውውርና ምደባ
መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡
ስለሆነም የጤና ባለሙያዎች የዝውውርና ምደባ አፈፃፀም መመሪያ በችሎታ ፣ በብቃት በግልጽነትና ከአድሎ ነፃ በሆነ ውድድር ላይ
እንዲመሰረት በየደረጃው የሚገኙ አካላት በአግባቡ መመሪያውን ተገንዝቦ መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ክፍል አንድ
ጠቅላላ
አንቀፅ 1. አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ የተሸሻለ የጤና ባለሙያዎች የዝዉዉርና ምደባ አፈፃፀም መመሪያ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
አንቀፅ 2. የመመሪያዉ አስፈላጊነት
2.1. የጤና ባለሙያዎች በተመደቡበት ቦታ ተረጋግተዉ የጤና አገልግሎቱን ስራ ለማከናወን እንዲችሉ ለማድረግ
2.2. የጤና ባለሙያዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተዛዉሮ የመስራት መብትን ለማረጋገጥና ሥራን ማዕከል ያደረገ የሰዉ ኃይል ስምሪት ለመፈፀም
2.3. የጤና ባለሙያዎች የጤና አገልግሎቱን ተግባር ውጤታማ በሆነ መንገድ መፈፀም እንዲችሉ ለማነሳሳት
2.4. በክልሉ ውስጥ ያሉ ሰርተፍኬት ፣ ዲፕሎማና ከዚያ በላይ የሙያ ዝግጅት ያላቸውን የጤና ባለሙያዎች ስምሪት ወጥነት ባለው መልኩ
ለመምራት
አንቀፅ 3. ትርጉም
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠዉ ካልሆነ በስተቀር በዚህ የዝዉዉርና ምደባ መመሪያ ዉስጥ፡-
3.1. “ቢሮ” ማለት የአማራ ክልላዊ መንግስት ጤና ጥበቃ ቢሮ ነዉ፡፡
3.2. “ኮሚሽን” ማለት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ማለት ነው፡፡
3.3. “ጤና ተቋም” ማለት በየደረጃዉ የሚገኙ የህክምናና የምርመራ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የሚያጠቃልል ናው፡፡
3.4. “ጤና አመራር ተቋም” ማለት የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ፣ የዞን ጤና መምሪያ ፣ የሜትሮ ፖሊታን ከተማ ጤና መምሪያ እና የወረዳ ጤና
ጥበቃ ጽ/ቤት ማለት ነው፡፡
3.5. “ጤና ሳይንስ ኮሌጅ” ማለት በክልሉ ጤና ቢሮ ስር የመካከለኛ ጤና ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ተቋም ማለት ነዉ፡፡
3.6. የጤና ባለሙያ ማለት እዉቅና ካለዉ ተቋም 10 ኛ እና 12 ኛ ከአጠናቀቁ በኋላ የተገኘ ሰርተፊኬት፣ በዲፕሎማ፣ በከፍተኛ ዲፕሎማ ፣
በዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ተመርቆ በመንግስት ጤና አመራር ተቋማት ወይም በጤና ተቋማት በጤና አገልግሎት ስራ ላይ
የተሰማራ የሰው ሀብት ነዉ፡፡
3.7. “የስራ ልምድ” ማለት በመንግስት መ/ቤቶች ወይም መንግስታዊ ባልሆኑ እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም ህጋዊ አቋምና የተሟላ
የውስጥ አደረጃጀት ባላቸው የግል ድርጅቶች ውስጥ በማንኛውም የስራ አይነት በቋሚነት ወይም በኮንትራት የወር ደመወዝ እየተከፈላቸው
መደበኛ የስራ ሰዓት የመንግስት ግብር እየተከፈለ የተሰራ የስራ ልምድ ማለት ነው፡፡
3.8. “መደበኛ ዝዉዉር” ማለት ጤና ባለሙያዎች በፍላጎታቸዉ በዓመት አንድ ጊዜ በሞሉት ቅፅ በየደረጃው በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ
መሰረት ከየትኛውም ጤና ተቋምና ጤና አመራር ተቋም ወደ የትኛው ጤና ተቋምና ጤና አማራር ተቋም በየደረጃው ባለው የሰው ሀብት
ልማትና አስተዳደር አማካኝነት የሚደረግ ዝውውር አይነት ነው፡፡
3.9. “የክልል ክልል ዝውውር” ማለት ከአማራ ክልል ወደ ሌሎች ክልሎች ወይም ከሌሎች ክልሎች ወደ አማራ ክልል የሚደረግ ዝውውር
ነው፡፡ ዝውውሩ የፌዴራል ተቋማትንና ሌሎች በክልሉ የሚሰሩ ተመሳሳይ ተቋማትንም ያካትታል፡፡
3.10. “የእርስ በእርስ ዝውውር” ማለት ተመሳሳይ የካርየር ደረጃ ፣ተመሳሳይ ሙያ እና አገልግሎት ያላቸው ሁለት ሰራተኞች እርስ በእርስ
ፈቅደው የሚያደርጉት የዝውውር አይነት ነው፡፡
3.11. “በልዩ ሁኔታ የሚፈፀም ዝዉዉር/ምደባ” ማለት በክልሉ የተሿሚዎች መመሪያ መሰረት በተሿሚነት ወይም በህዝብ ተመራጭነት
ምክንያት ከትዳር በመነጣጠል ፣ በህመም ፣ በማህበራዊ ችግር ምክንያት ፣ ዝውውር/ምደባ ሲጠየቅ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ወይም
መመደብ ማለት ነው፡፡
3.12. “ማህበራዊ ችግር” ማለት ባለሙያው አሁን ባለበት አካባቢ ሆኖ ስራን በአግባቡ ለመስራት የማያስችለው ችግር ሲፈጠርና ይህንኑ
ችግር የሚያስረዳ ህጋዊ ማስረጃ ከፍርድ ቤት ፣ ከፖሊስ ጽ/ቤት እና በየደረጃው ካለው አስተዳደር አስተዳዳሪ /ከንቲባ/ አሳማኝ ማስረጃ
የሚያቀርብ የጤና ባለሙያ ነው፡፡
3.13. “የህክምና ቦርድ ማስረጃ” ማለት በመንግስት ሪፈራል ሆስፒታል ደረጃ በሀኪሞች ሜዲካል ቦርድ ታማሚው ያለበትን የጤና ሁኔታና
ምን ሊደረግለት/ሊታገዝ እንደሚገባ የሚገልፅ የህክምና ማስረጃ ማለት ነው፡፡
3.14. “ተሿሚ” ማለት በየትኛውም የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ላይ በክልሉ ምክር ቤት ፣ በብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ምክር ቤቶች ወይም
በክልል ርዕሰ መስተዳድር ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሁም በወረዳ እና በቀበሌ ምክር ቤቶች እንዲሁም የመሾም ስልጣን በተሰጠው
አካል በሹመት የሚመደብ ሰው ማለት ነው፡፡
3.15. “የስራ ቦታ ምድብ ደረጃ” ማለት በአየር ጠባይ ተስማሚ አለመሆን ወይም በመሰረተ ልማት ኋላቀርነት የሚታይበት ፣ ከክልል ርዕሰ
ከተማ ፣ ከዞን ዋና ከተማ ያለው ርቀትና በሌሎች መስፈርቶች የተሰጠ የቦታ ደረጃ ማለት ነው፡፡
3.16. “የጋብቻ ማስረጃ” ማለት በማዘጋጃ ቤት ወይም በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ክፍል ወይም በሀይማኖት ተቋማት ወይም በባህላዊ የጋብቻ
/የአገር ሽማግሌ/ የሚሰጥ የምስክር ወረቀት ነዉ፡፡
3.17. “ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት” ማለት ዞን ጤና ጥበቃ መምሪያዎች ፣ ሜትሮፖሊታን ከተማ ጤና መምሪያዎች ፣
ሆስፒታሎች ፣ ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ፣ ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ደም ባንክ አገልግሎት
ጽ/ቤቶችን ያጠቃልላል፡፡
3.18. “ለዞን ጤና መምሪያ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት” ማለት በዞኑ ውስጥ ያሉት ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤቶች ማለት ነው፡፡ ጤና ጣቢያዎች እና
ጤና ኬላዎችን አያካትትም፡፡
3.19. “ለወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ተጠሪ የሆኑ ተቋማት” ማለት በወረዳው ውስጥ ያሉ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ማለት ነው፡፡
3.20. “ምደባ” ማለት በተለያዩ የጤና ዘርፎች ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ፣ በአብክመ ጤና ጥበቃ ቢሮ ስር ካሉ ጤና ሳይንስ ኮሌጆች
ተመርቀው የሚመጡ አዲስ ባለሙያዎች ፣ ከሹመት የሚነሱ ሰራተኞች እና በድልድል ወቅት ተንሳፋፊ ለሆኑ ሰራተኞች ከሙያና ትምህርት
ዝግጅት አኳያ ታይቶ የሚደረግ የስራ ምደባ ማለት ነው፡፡
3.21. “የኬርየር ደረጃ” ማለት ጤና ባለሙያዎች በካርየር አፈፃፀም መመሪያ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት (የቆይታ ጊዜ እና ስራ አፈፃፀም
ዋዘተ) ሲያሟሉ የሚሰጣቸው የካርየር ደረጃ ማለት ነው፡፡
3.22. “የፓናል ደረጃ” ማለት ባለሙያዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመደቡ ወይም ትምህርታቸውን አሻሽለው ሲመጡ የሚሰጣቸውን
የሙያ ፈቃድ ስያሜ መሰረት በማድረግ በክልሉ የጤና ጥበቃ ቢሮ የሰው ሀብት አስተዳደር የሚሰጥ ደረጃ ማለት ነው፡፡
3.23. “የአካል ጉዳተኛ” ማለት ለዚህ መመሪያ አፈፃፀም በደረሰበት የአከል ፣ የአእምሮ ወይም የስሜት ህዋሳት ጉዳትን ተከትሎ በሚመጣ
የኢኮኖሚ የስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ መድሎ ሳቢያ በስራ ስምሪት የእኩል እድል ተጠቃሚ ያልሆነ ሰው ሲሆን አንድ ሰው የአካል ጉዳተኛ
ተደርጐ የሚወሰደው ሙሉ በሙሉ አይነ ስውር ወይም ሙሉ በሙሉ መስማት የተሳነው ወይም በተጨማሪ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ወይም
በተጨማሪ ድጋፍ ባይንቀሳቀስም በግልፅ በሚታይ ሁኔታ በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት ባጋጠመው ጉዳት የተነሳ የእንቅስቃሴ
ችግር ያለበት ሰው ማለት ነው፡፡
ክፍል ሁለት
የተፈፃሚነት ወሰንና ስምሪቱ የሚመለከታቸዉ ጉዳዮች
አንቀፅ 4፡- የመመሪያዉ የተፈፃሚነት ወሰን
4.1. ጤና ጥበቃ ቢሮ ፣ የዞን ጤና መምሪያዎች ፣ ሜትሮፖሊታን ከተሞች ፣ በተለያዩ ደረጃ በሚገኙ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽ/ቤቶች
፣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤቶች ፣ ሆስፒታሎች ፣ የህብረተሰብ ጤና ምርምር ኢንስቲቲዩት ፣ ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ፣ ኦክስጅን ማምረቻና
ማከፋፈያ ድርጅት ፣ ጤና ጣቢያዎች እና ደም ባንክ አገልግሎት ጽ/ቤቶችን ያጠቃልላል፡፡
አንቀፅ 5፡- ዝውውር ከመፈፀሙ በፊት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች፣
5.1. የተፈቀደ ክፍት የስራ መደብ እና በጀት መኖሩን ማረጋገጥ፤
5.2. አላግባብ የሰው ሀይል ስብስብ የማይፈጥር መሆኑን ማረጋገጥ፤
5.3. የስምሪት ማስታወቂያው ለሁሉም ተወዳዳሪዎች እኩል መድረሱን ማረጋገት፣
5.4. ለስምሪት የተጠየቀው መረጃ በአግባቡ እና በጥንቃቄ ተሞልቶ በወቅቱ በየደረጃው ለሚገኙ አስፈፃሚ አካላት መድረስ ይኖርበታል፡፡
ሆኖም በወቅቱ ባልደረሰ የዝውውር መረጃ ዝውውር መስራት የማይቻል ሲሆን መረጃውን ያዘገየ ባለሙያ /ሃላፊ/ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
አንቀፅ 6፡- የዝዉዉር አይነቶች
6.1. መደበኛ ዝዉዉር
6.2. የዉስጥ ዝዉዉር
6.3. የውጭ ዝውውር
6.4. የእርስ በእርስ ዝውውር
6.5. በልዩ ሁኔታ የሚፈፀም ዝዉዉር
6.6. የክልል ክልል ዝዉዉር

6.1 መደበኛ ዝዉዉር

6.1.1 አዳዲስ ምሩቃን ወደ ጤና ተቋም ከመቀላቀላቸዉ በፊት ነባና ጤና ባለሙያዎች በውድድር ከነበሩበት ከጤና ጥበቃ ቢሮ ፣ ዞን ጤና
መምሪያ፣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት፣ ከተማ አስተዳድር ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት፣ ጤና ተቋም ፣ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ወይም የህብረተሰብ ጤና
ኢንስቲቲዩት ፣ ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ወደ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ወይም ወደ ሌላ ዞን ፣ ወረዳ ፣ የጤና ተቋም ፣ ጤና
ሳይንስ ኮሌጅ የዝውውር ፎርም በመሙላት መዘዋወር ይችላሉ፡፡

6.1.2 ከዞን ዞን የተዛወሩ የጤና ባለሙያዎች በተዛወሩበት ዞን ውስጥ ክፍት ቦታዎች ካሉ በዚያው ዞን ውስጥ ዝውውር ከሞሉ የጤና
ባለሙያዎች ጋር እኩል የመወዳደር መብት ያላቸው ሲሆን ተወዳድረው በተመደቡበት ቦታ የመስራት ግዴታ አለባቸው፡፡
6.1.3 ባልና ሚስት የዝውውር ጥያቄ ፎርም ሲሞሉ የጋብቻ ማስረጃ ከሁለቱም ሰራተኞች የግል ማህደር ላይ ከስድስት ወር በፊት የተያያዘ
መሆን አለበት፡፡ በአንድ ላይ የሚኖሩ ባለትዳሮች ተነጣጥለው መዛወር የማይፈልጉ ከሆነ ይህው ጉዳይ በማሳሰቢያ ይገለፅ፣ ከሁለት አንዱ
በዝውውሩ የማያሸንፉ ከሆነ በወድድሩ ያሸነፈው ተወዳዳሪ ተሰርዞ ቀጥለው ያሉ ሌሎች ተወዳዳሪዎች እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
6.1.4 ባል ወይም ሚስት የመንግስት ሰራተኛ ቢሆኑም ባይሆኑም የጋብቻ ማስረጃው በአንቀጽ 6.1.3 መሰረት ከፋይላቸው ጋር የተያያዘና
የመንግስት ሰራተኛ ከሆኑ ከሚሰሩበት መ/ቤት የመንግስት ሰራተኛ ካልሆኑ ደግሞ ከሚኖሩበት ቀበሌ የኗሪነት ማረጋገጫ ማቅረብ
ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ወደ አወዳዳሪው ተቋም መላክ አለበት፡፡
6.1.5 ባል ወደ ሚስት ወይም ሚስት ወደ ባል ለመዛወር ሲጠይቁ ለተወዳዳሪው የባልና ሚስት የሁለቱ አገልግሎት ተደምሮ ሲካፈል
በሚገኘው አማካይ የአገልግሎት ውጤት ተይዞ ይወዳደራሉ፡፡ የባልን ወይም የሚስትን አገልግሎት ብቻ በመያዝ መወዳደር አይቻልም፡፡
6.1.6 ባል ወይም ሚስት በዝውውር መተየቂያ ቅጽ ላይ መረጃውን በትክክል መሙላት ይገባቸዋል፡፡ ሳይሞሉ ቀርተው ዝውውሩ በተናጠል
ከታየ በኋላ የሚቀርብ የዝውውር ጥያቄ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
6.1.7 የጤና ባለሙያዎች ዝውውር ሲሞሉ 3 ቦታዎችን በቅደም ተከተል መሙላት ይችላሉ፡፡

የመደበኛ ዝውውር መስፈርት


6.1.8 ዝውውር ጠያቂ ጤና ባለሙያ ዝውውር ከመሙላቱ በፊት በሚሰራበት ቦታ አንድ አመት እና ከዚያ በላይ ማገልገል አለበት፡፡
6.1.9 ለመዛወር የዝውውር ፎርም በጊዜ ገደቡ ውስጥ መሙላት ግዴታ ነው
6.1.10 ለዝውውር ማወዳደሪያነት የሚያገለግለው የአገልግሎት ዘመን ሲሆን የአገልግሎት ዘመን የሚሰላው ባለሙያው በሚሰራበት ቦታ
በተሰጠው የቦታ ነጥብ መሰረት ይሆናል፡፡
6.1.11 ህጋዊ ጋብቻ ማስረጃ የሚያቀርቡ ባለትዳሮች ዝውውር የሚጠይቁት አንድ ላይ ለመኖር ወይም ለመቀራረብ ሲሉ ይሆናል፡፡ የጋብቻ
ማስረጃው ተቀባይነት ሲያገኝ ለትዳር 4 ነጥብ ፣ ለሴት ተወዳዳሪዎች ለፆታ 3 ነጥብ ፣ ለአካል ጉዳተኞች ለሴት 4 ለወንድ አካል ጉዳተኛ 3
ነጥብ ይሰጣል፣ ከአንድ በላይ የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚሆን ባለሙያ ሲኖር የተሻለውን ነጥብ ይወሰዳል ፤ አንድ ላይ ያሉ ባለትዳሮች ከትዳር
አጋሩ/ሯ/ ከሚኖሩበት ቦታ ውጭ ለመዛወር ከፈለጉ ለትዳር የተቀመጠውን ነጥብ አያገኙም፡፡

ተወዳዳሪዎች ያመጡት ውጤት እኩል ከሆነ ቅድሚያ ለሴት አካል ጉዳተኛ ይሰጣል ይህ ከሌለ ለወንድ አካል ጉዳተኛ ይሰጣል እነዚህ
በሌሉበት ለሴት ቅደሚያ ይሰጣል ሆኖም ተመሳሳይ ፆታ ከሆኑ በእጣ ይለያሉ፡፡
በአንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 6.2 እና 6.3 የተገለፀው የውስጥና የውጭ ዝውውር አፈፃፀም መመሪያ በመንግስት ሰራተኞች ምልመላና መረጣ
መመሪያ መሰረት ተፈፃሚ የሚሆን ይሆናል፡፡
6.4 የእርስ በእርስ ዝውውር
6.4.1 የእርስ በእርስ ዝውውር ተመሳሳይ የካርየር ደረጃ ፣ ተመሳሳይ ሙያና አገልግሎት ያላቸው ሁለት ሰራተኞች እርስ በእርስ ዝውውር
ማካሄድ ይችላሉ፡፡
6.4.2 የእርስ በእርስ ዝውውር በአንድ ወረዳ ውስጥ በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች በሚሰሩ ባለሙያዎች መካከል ከሆኑ ሁለቱም አሰሪ መ/ቤቱ
ደብዳቤያቸውን ለወረዳው ሲቪል ሰርቪስ ያቀርባሉ ፤ ዝውውሩም በዚያው ወረዳ ይፈፀማል፡፡
6.4.3 የእርስ በእርስ ዝውውሩ በአንድ ዞን ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች በሚሰሩ ባለሙያዎች መካከል ከሆነ ሁለቱም ከየወረዳቸው ያመጡትን
የስምምነት ደብዳቤያቸውን ለዞኑ ሲቪል ሰርቪስ ያቀርባሉ ፣ ዝውወሩም በዚያው ዞን ይፈፀማል፡፡
6.4.4 የእርስ በእርስ ዝውውሩ በተለያዩ ዞኖች መካከል ከሆነ ሁለቱም ከየወረዳቸው ያመጡትን የስምምነት ደብዳቤ ለየዞናቸው ያቀርባሉ፤
በሁለቱ ዞኖች ስምምነት ከተገኘ በዚያው ይፈፀማል፡፡
6.4.5 የእርስ በእርስ ዝውውሩ በአማራ ክልልና በሌላ ክልል መካከል ከሆነ ዝውውር ተያቂው ካለበት ተቋም ስምምነት አፅፎ ለክልል ጤና
ጥበቃ ቢሮ ያቀርባል ፤ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮም በዝውውሩ ካመነበት ለሌለኛው ክልል የትብብር ደብዳቤ ይፅፋል፡፡ ስምምነት ከተገኘ
እንዲዛወሩ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ዝውውሩ በአንድ ወር ውስጥ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ወቅት ባለመጠናቀቁ ለሚፈጠር ችግር ኃላፊነቱ
ተዘዋዋሪው ባለሙያና ዝውውሩን ያጓተተው ተቋም ሀላፊነቱን ይወስዳል፡፡
6.4.6 ከአንቀጽ 6.4.1 እስከ 6.4.5 የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኑ የእርስ በእርስ የዝውውር ተጠቃሚ ለመሆን ቢያንስ በተመደቡበት
ጤና ተቋም አንድ አመት ያገለገለ መሆን አለበት፡፡

6.5 በልዩ ሁኔታ የሚፈፀም ዝውውር


6.5.1 የጤና ባለሙያዎች በልዩ ሁኔታ የሚዘዋወረው በጤና ችግር ምክንያት ከሆነ እና ስለመሆናቸው እንዲሁም በሚሰሩበት ቦታ የህክምና
አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት የማይችሉ መሆኑን በቀላሉ ማግኘት የማይችሉ መሆኑን ማስረጃ የሚያቀርቡ ሠራተኞች ዝቅተኛ ተፈላጊ
ችሎታውን እስካሟሉ ድረስ ከማንኛውም ዝውውር ፈላጊ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከኤች አይ.ቪ/ኤድስ ህሙማን ውስጥ
ባለትዳሮች ካሉ ቅድሚያ የሚሰጥ ሲሆን ያለው የስራ ቦታ ውስን ከሆነ ባላቸው የውድድር ውጤት ይለያሉ፤ ይህም ሆኖ እኩል ከመጡ
ቅድሚያ ለሴት ይሰጣል፡፡ ተመሳሳይ ፆታ ካላቸው በእጣ ይለያሉ፡፡

6.5.2 በአንቀጽ 6.5.1 ላይ ያለው እንደተጠበቀ ሆኖ የኤች አይ.ቪ/ኤድስ ህሙማን ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ያቀረቡ ዝውውር ፈላጊዎች
እስከሌሉ ድረስ በጤና ችግር ምክንያት ከመንግስት ሪፈራል ሆስፒታል በሀኪሞች ሜዲካል ቦርድ የተረጋገጠ የህክምና ማስረጃ ለሚያቀርቡ
እና አሁን በሚሰሩበት ተቋም ለመስራት የተቸገሩ መሆኑን በሀኪሞች ቦርድ የህክምና ማስረጃ ለሚያቀርቡ ጤና ባለሙያዎች ቅድሚያ
ይሰጣል፡፡ የህክምና ማስረጃው ተቀባይነት የሚኖረው ዝውውሩ ከመታየቱ በፊት አንድ አመት ያልሞላው መሆኑን አለበት፡፡

6.5.3 ከላይ በተራ ቁጥር 6.5.2 ላይ የተመለከቱት ዝውውር ጠያቂዎች በሌሉበት ሁኔታ ለአካል ጉዳተኛ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ቅድሚያ
የሚሰጣቸው ሙሉ በሙሉ አይነ ስውር ወይም ሙሉ በሙሉ መስማት የተሳናቸው ወይም የአካል ክፍሎቻቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው
በተጨማሪ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ወይም በተጨማሪ ድጋፍ ባይንቀሳቀሱ በግልፅ የሚታይ እንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው ከሆኑ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም
ለሚዛወሩበት ስራ መደብ ዝቅተኛ ተፈላጊ ችሎታውን ማሟላት ይኖርባቸዋል፡፡

6.5.4 በሹመት ምክንያት ከትዳራቸው የተለያዩ ከሆነ ክፍት የስራ ቦታና በጀት መኖሩ ተረጋግጦ በላኪና በተቀባይ መ/ቤት ስምምነት
ዝውውሩ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ሆኖም የስራ መደቡንም ዝቅተኛ ተፈላጊ ችሎታ መሟላት ይኖርበታል፡፡

6.5.5 ከአንቀጽ 6.5.1 እስከ አንቀጽ 6.5.4 የተጠቀሱት የልዩ ዝውውር ፈላጊዎች እስከ ሌሉ ድረስ የማህበራዊ ችግር ያለባቸው የጤና
ባለሙያዎች የማህበራዊ ችግር ያለባቸው ስለመሆኑ ከሚሰሩበት ተቋም ፣ በአካባቢው ባለው ፍ/ቤት እና ፖሊስ ጽ/ቤት ማስረጃ እስካቀረቡና
በየደረጃው ካለው አስተዳደር አስተዳዳሪ/ከንቲባ/አሳማኝ ማስረጃ እስካቀረበ ድረስ የልዩ ዝውውር ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ዝውውሩ
የሚከናወነው የጤና ባለሙያው ሲሰራ በነበረበት ተቋም /ቦታ/ ጋር ተመሳሳይ በሆነ የቦታ ደረጃ መሰረት ዝውውሩ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

6.5.6 በልዩ ሁኔታ የሚፈፀም ዝውውር እናት መ/ቤታቸውን ሳይጠይቁ ማስታወቂያ ማውጣት ሳያስፈልግ በተቀባይና በላኪ ተቋማት
ስምምነት መሰረት የሚፈፀም ይሆናል፡፡
6.5.7 የልዩ ዝውውር ተጠቃሚ የጤና ባለሙያዎች ለአንድ የስራ መደብ ከአንድ በላይ ተወዳዳሪዎች በሚቀርቡበት ጊዜ የተለያየ ፆታ
ያላቸው ከሆነ ለሴት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ተመሳሳይ ፆታ ካላቸው በዕጣ ይለያሉ፡፡
6.5.8 በልዩ ሁኔታ የሚፈፀም ዝውውር የመደበኛ የዝውውር ጊዜን ብቻ ሳይጠበቅ በክፍት የስራ መደብ ዝውውሩ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
ዝውውሩም የጤና ቢሮው በግልባጭ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡
6.6 የክልል ክልል ዝውውር
6.6.1 ከሌላ ክልል ወደ አማራ ክልል ተዛውረው ለመስራት የሚፈልጉ ባለሙያዎች ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡት ለሚቀበላቸው ጤና አመራር
ተቋማት ሲሆን ተቀባዩ መስሪያ ቤትም የሚስማማ ከሆነ ለጤና ጥበቃ ቢሮ ስምምነቱን ማሳወቅ አለበት፡፡ ይሁንና በቢሮው ባሉ ክፍት የስራ
መደቦች ውስጥ ብቻ ለመስራት የሚፈልጉ ባለሙያዎች ጥያቄውን የሚያቀርቡት ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ይሆናል፡፡ ቢሮውም በዝውውሩ
የሚስማማ ከሆነ ዝውውር ጠያቂው ለሚሰራበት ክልል የድጋፍ ደብዳቤ በመስጠት እንዲዛወሩ ያደርጋል፡፡ ሆኖም ዝውውሩ የተፈቀደላቸው
ባለሙያዎች በ 30 ተከታታይ የስራ ቀናት ውስጥ በተዛወሩበት የስራ ቦታ ሪፖርት ካላቀረቡ ዝውውሩ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የድጋፍ
ደብዳቤ የሰጠው ተቋምም ለ 30 ተከታታይ ቀናት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ሆኖም በተገለፀው የዝውወሩ ጊዜካልተፈፀመ የጤና ተቋሙ
የመቀበል ግዴታ የለበትም፡፡
6.6.2 በአንቀጽ 6.6.1 የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ ከዞን እስከ ጤና ጣቢያ ባለው መዋቅር የሚሰሩ ባለሙያዎች የድጋፍ ደብዳቤ
የሚሰጠው በየደረጃው ካለው የጤና መምሪያ ወይም ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ጋር በመነጋገርና መረጃ በመያዝ ነው፡፡
6.6.3 ከአማራ ክልል ወደ ሌሎች ክልሎች በዝውውር መሄድ ለሚፈልጉ ባለሙያዎች በክልሉ ቢያንስ አንድ አመትና ከዚያ በላይ መስራት
የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህን የቆይታ ጊዜ ያጠናቀቁ ለሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት አቅርበው ሲፈቀድላቸው በጤና ጥበቃ ቢሮ
በኩል ለሚዛወሩበት ክልል የድጋፍ ደብዳቤ በመስጠት እንዲዛወሩ ይደረጋል፡፡ የጤና ባለሙያው የውል ግዴታውን እስካላጠናቀቀ ድረስ አሰሪ
መ/ቤቱ የባለሙያ እጥረት አለብኝ ካለዝውውር የድጋፍ ደብዳቤ ለመስጠት አይገደድም፡፡
6.6.4 ከላይ በአንቀጽ 6.6.3 የተገለፀ ቢሆንም ከአማራ ክልል ወደ ሌሎች ክልሎች በዝውውር መሄድ ለሚፈልግ የጤና ባለሙያ በክልሉ
ውስጥ 1 /አንድ/ ዓመት ባያገለግልም በልዩ ሁኔታ የማህበራዊ ችግር ካጋጠመው እና ለዚህ በቂ ማስረጃ ካቀረበና ቢሮው ካመነበት ወደ ሌላ
ክልል በሚገኝ የመንግስት ጤና ተቋም ሊዛወር ይችላል፡፡

6.6.5 ከላይ በአንቀጽ 6.6.3 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ዝውውር ጠያቂው የተማረበትን የኮስት ሸሪንግ ውል ወይም ክልሉ ያስተማረው
ከሆነ የገባውን የውል ግዴታ ከተወጣ ተቋማት ዝውውር የመከልከል መብት የላቸውም፡፡
6.6.6 ሆስፒታሎች ፣ የደም ባንኮችና የህብረተሰብ ጤና ምርምር ኢንስቲቲት ከክልል ክልል በዝውውር ለመቀበልም ሆነ ለመላክ ከተቋሞቹ
ኃላፊዎች የተፈረመ የድጋፍ ደብዳቤ ለክልል ጤና ቢሮ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ አፈፃፀሙም በአንቀፅ 6.6.1 መሰረት ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ክፍል ሶስት
አንቀጽ 7. የቋሚ ቅጥር ምደባ

7.1 ቋሚ ምደባ ከመከናወኑ በፊት መደረግ ያለባቸዉ ተግባራት


7.1.1 በየደረጃው ያሉ ጤና ተቋማት ክፍት ስራ መደቦችን በሙያ አይነትና ብዛት በመለየት በጀት መያዙን መረጋገጥ አለበት፤
7.1.2 ለተመዳቢዎች ምደባው መቼ እንደሚከናወን ፣ ባለትዳር ከሆኑ የትዳር ማስረጃቸውንና ይህም ማስረጃ ከትዳር አጋራቸው ፋይል
ውስጥ ከስድስት ወርና በፊት ስለመያያዙ የትዳር አጋሯ/ሩ ከሚሰሩበት መ/ቤት ዕጣው ከሚወጣበት ቀን በፊት ማቅረብ እንዳለባቸው
በማስታወቂያ መገለፅ ይኖርበታል፡፡
7.1.3 የአዲስ ምሩቃን የጤና ባለሙያዎች ቋሚ ምደባ ከመከናወኑ በፊት ነባር ባለሙያዎች ዝውውር መጠናቀቅ ይኖርበታል፣ ሆኖም
መደበኛ ዝውውሩ ከመሰራቱ በፊት የአዲስ ምሩቃን ከመጡ በእጣ በጊዜያዊ ተመደበው ይቆያሉ፡፡ በመደበኛ ዝውውር ወቅት በጊዜያዊነት
ተመድበው የነበሩ አዲስ ምሩቃን የጤና ባለሙያዎች ባይገኙም በተገኙት ተመዳቢዎች አማካኝነት ዕጣ ወጦላቸው በቋሚነት ምደባ
እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡
7.2. የምደባዉ አፈፃፀም ስርዓት
7.2.1 በምደባዉ እለት የጤና ተቋም ለተመዳቢዎች ያሉ ክፍት መደቦች በሙያ አይነትና ብዛት ፣ ስለተቋሙ አጠቃላይ ሁኔታና ስለሙያ ስነ-
ምግባር ፣ መብትና ግዴታ ፣ ወቅታዊ አጀንዳዎችና መሰል ጉዳዬች ግንዛቤ መፍጠር አለበት፡፡
7.2.2 በልዩ ልዩ ምክንያት ልዩ ምደባ ሊሰጣቸው የሚገቡና መረጃዎች ተጣርቶ ተቀባይነት ያገኙ ባለሙያዎችን ከእጣ መቀነስና መረጃውንም
ለተመዳቢዎች በግልፅ ማስታወቂያ ይፋ ማድረግ፡፡

7.2.3 በጤና ችግር ምክንያት ከመንግስት ሪፈራል ሆስፒታል በ 3 ሐኪም የተረጋገጠ የህክምና ቦርድ ማስረጃ ለሚያቀርቡ የጤና
ባለሙያቸው በጀት ያለው ክፍት የስራ መደብ መኖሩ ተረጋግጦ ወይም ከተዘጋጀው እጣ ተቀንሶ በቅድሚያ በቦርድ ወረቀቱ በተሰጠው
አስተያየት መሰረት ይመደባሉ፡፡ ይህም በማስታወቂያ እንዲታወቅ ይደረጋል፡፡
7.2.4 ተመዳቢ የተሿሚ የትዳር አጋር ከሆኑ የባለቤታቸውን የሹመት ደብዳቤ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ምደባውም በተቻለ መጠን
ወደ ትዳር አጋራቸው በሚኖርበት አካባቢ ባለ የጤና ተቋም ክፍት የስራ መደብና በጀት መኖሩ ተረጋግጦ ምደባ ይሰጣል፡፡ ክፍት ስራ መደቡ
ውስን ከሆነ ሴትና ወንድ ተመዳቢዎች ቢያቀርቡ ቅድሚያ ለሴት ተመዳቢ ይሰጣል፡፡ ተመሳሳይ ፆታ ከሆኑ በእጣ ይለያሉ፡፡
7.2.5 የሙያ ማሻሻያ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚመለሱ ባለሙያዎች ቢቻል በመጡበት ተቋም ወይም በሚቀርባቸው አካባቢ ክፍት
የስራ መደብ ካለ ይመደባሉ፡፡ ሆኖም ግን ክፍት ስራ መደብ ከታጣ በሌሎች የጤና ተቋማት በአገልግሎት ዘመናቸው መሰረት ምደባ
ይሰጣል፡፡ ሆኖም ግን የእነዚህ ባለሙያዎች ዋነኛው የምደባ ትኩረት ሙያቸው የሚፈለግበት ቦታ/ተቋም/ በመሆኑ ለስራው ቅድሚያ
ይለያል፡፡
7.2.6 የአዲስ ምሩቃን የጤና ባለሙያዎች በምደባው እለት ያልተገኙ ተመዳቢዎች ቢኖሩ እጣቸው ሌሎች ተመዳቢዎች በተገኙበት ወጥቶና
በቃለ ጉባኤ ተይዞ በሚመጡበት ጊዜ የምደባ ደብዳቤያቸው ይሰጣቸዋል፡፡
7.2.7 የምደባ ደብዳቤ ከመሰጠቱ በፊት ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች የምደባ ቦታቸውን እርስ በስርስ ለመለዋወጥ በሚያቀርቡት
ማመልከቻና ማንነታቸውን ከሚገልፅ መታወቂያ ወይም ማስረጃ ጋር አያይዘው ሲቀርቡ በጠየቁት ስምምነት መሰረት እጣው በወጣ በሁለት
ቀን ውስጥ ልውውጡ ተከናውኖ ደብዳቤው ይሰጣቸዋል፡፡

ክፍል አራት
አንቀፅ 8፡ የወረዳዎች አመዳደብና ነጥብ አሰጣጥ
8.1 የስራ ቦታ ምድብ ደረጃ
8.1.1 ምድብ አንድ
 የክልሉን ርዕሰ ከተማ ባህርዳርን ጨምሮ ሌሎች የዞን ከተሞች
8.1.2 ምድብ ሁለት
 የገንዳ ውኃ እና የዋግህምራ ዞን ርእሰ ከተማ ጨምሮ ከዞን ከተሞች ውጭ የሆኑ ሌሎች ወረዳዎች
8.1.3 ምድብ ሦስት
 በረኸት፣ ጃን አሞራ፣ መሃል ሳይንት፣ አርጎባ፣ ዳዉንት፣ አበርገሌ፣ ዳዋ ሃርዌ ፣ ሚዳ ወረሞ ፣ ወቀት ፣ ጅሌ ጥሙጋ
8.1.4 ምድብ አራት
 በየዳ፣ ጠለምት፣ ዳህና፣ ግሸራቤል
8.1.5 ምድብ አምስት
 ቋራ፣ ጃዊ፣ ታች አርማጭሆ፣ ጠገዴ ፣ አድአርቃይ ፣ አበርገሌ
8.1.6 ምድብ ስድስት
 መተማ፣ ም/አርማጭሆ ፣ አብደራፊከተማ አስተዳደር ፣ አብራጅራ ከተማ አስተዳደር ፣ ዝቋላ ፣ ሰሀላ ፣ ምዕ/በለሳ
8.2 የስራ ቦታ ምድብ ደረጃ ነጥብ አሰጣጥ
8.2.1 በምድብ አንድ ለሰራበት አንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጠዉ ነጥብ 1.0 ይሆናል
8.2.2 በምድብ ሁለት ለሰራበት አንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጠዉ ነጥብ 1.1 ይሆናል
8.2.3 በምድብ ሦስት ለሰራበት አንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጠዉ ነጥብ 1.2 ይሆናል
8.2.4 በምድብ አራት ለሰራበት አንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጠዉ ነጥብ 1.3 ይሆናል
8.2.5 በምድብ አምስት ለሰራበት አንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጠዉ ነጥብ 1.4 ይሆናል
8.2.6 በምድብ ስድስት ለሰራበት አንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጠዉ ነጥብ 1.5 ይሆናል
ክፍል አምስት
አንቀፅ 9 የጤና ባለሙያዎች ስምሪት የአስፈፃሚ አካላት ተግባርና ኃላፊነት
9.1 የክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ተግባርና ኃላፊነት፣
9.1.1 ወደ ጤና ጥበቃ ቢሮ እና በስሩ ባሉ በሁሉም ተጠሪ ተቋማት የሚደረገው መደበኛ ዝውውርና ምደባ የሚፈፀመው በክልሉ ጤና
ጥበቃ ቢሮ ይሆናል፡፡
9.1.2 የመደበኛ ዝውውር ፎርም በማዘጋጀት የጤና ባለሙያዎች በተወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የዝውውር ፎርም ተሞልቶ እንዲመጣ
ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፡፡
9.1.3 ተጠሪ ተቋማት የሚያስፈልጋቸዉን የሰዉ ኃይል በመጠንና በሙያ ዓይነት ከበጀት ጋር በማገናዘብ ለቢሮው እንዲያሳውቁ ክትትል
በማድረግ መረጃው እንዲጠናቀር ያደርጋል፡፡
9.1.4 ዝዉዉሩ በተቀመጠዉ የጊዜ ሰሌዳና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በተዘጋጀዉ መስፈርት መሰረት እንዲፈፀም ያደርጋል፡፡
9.1.5 ከጤና ጥበቃ ሚኒስቲርና ከመንግስት የጤና ሳይንስ ኮሌጆች ተመርቀዉ ወደ ቢሮዉ የሚላኩ የጤና ባለሙያዎችን የጥሪ ማስታወቂያ
ወጥቶላቸው በእጣ ይመደባል፡፡
9.1.6 ከግሉ የጤናው ሴክተር ተመርቀው የሚወጡ እና ወደ መንግስት ተቋማት ለመቀጠር የሚፈልጉ የጤና ባለሙያዎችን የቅጥር
ማስታወቂያ በማውጣት ባለው ክፍት የስራ ቦታ በውድድር ይቀጥራል፡፡
9.1.7 በጤናው ሴክተር ውስጥ ያለውን የሰው ሀይል ስምሪት ይከታተላል፣ ይደግፋል ፣ ይቆጣጠራል ህግ በሚፈቅደው መሰረት የማስተካከያ
እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
9.1.8 ለሴክተሩ የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል በሙያ አይነትና መጠን በመተንተን ያቅዳል ፣ ከሚመለከተው አካል ጋር በመመካከር
እንዲሟላ ያረጋል፡፡
9.2 የዞን ጤና ጥበቃ መምሪያ ተግባርና ኃላፊነት
9.2.1 በዞኑ እና በስሩ ባሉ ወረዳዎች የሚሰሩ ጤና ባለሙያዎች የዝውውር ፎርም በወቅቱ ሞልቶ እንዲላክለት በማድረግ እና ትክክለኛነቱን
በማረጋገጥ ዝውውሩን ለመፈፀም በሚያስችል መልኩ ለሁሉም ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤቶች እና ለዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ እንዲደርስ
ያደርጋል፡፡
9.2.2 የክልሉ የጤና ባለሙያዎች የመደበኛ ዝውውር በተቀመተው የጊዜ ሰሌዳ ተግባራዊ እንዲሆን የውድድር መስፈርቱን መሰረት
በማድረግ ለዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ እና ለወረዳዎች ጤና ጽ/ቤት ቴክኒካል ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙም አፋጣኝ
መፍትሔ ይሰጣል፡፡
9.2.3 በዞኑ ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ የተሰራዉን ስምሪት ይከታተላል፡፡
9.2.4 ከዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ የሚፈለግ መረጃ ሲኖር መረጃውን ለጤና ጥበቃ ቢሮ ያስተላልፋል፡፡
9.2.5 ለዞንና ለዞን ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ማለትም የወረዳ ጤና ጽ/ቤቶች የሰው ሃይል ስምሪት ይከታተላል፤ ይደግፋል ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ
የመፍትሔ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
9.2.6 ለዞንና ለተጠሪ ተቋማት የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል እቅድ ያዘጋጃል ፤ የተፈቀዱ መደቦች በሰው ሀይል መሟላታቸውን ይከታተላል
፣ በሰው ሀይል ያልተሟሉ መደቦች በጀት እንዲፈቀድላቸው ድጋፍ ያደርጋል፡፡
9.2.7 በዞን ውስጥ የሚፈፀመውን የሰው ሀይል ስምሪት በመመሪያው መሰረት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ መተግበሩን ይከታተላል፡፡
9.2.8 ስራውን የሚከታተል ባለሙያ (focal person) ይመድባል
9.3 የወረዳ ጤና ጽ/ቤት ተግባርና ኃላፊነት
9.3.1 በወረዳው እና በስሩ ባሉ ጤና ተቋማት የሚሰሩ ጤና ባለሙያዎች የዝውውር ፎርም በወቅቱ አስሞልቶ ለወረዳው ለሲቪል ሰርቪስ
ጽ/ቤት ይልካል፡፡
9.3.2 መደበኛ ዝውውሩ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲፈፀም ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ቴክኒካል
ችግሮች ሲያጋጥመው አፋጣኝ አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጣል፡፡
9.3.3 በወረዳው ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት የተሰራውን ስምሪት ይከታተላል፡፡ የተደራጀ የሰው ሀብት መረጃ በወረዳው ውስጥ እንዲኖር
ያደርጋል፡፡
9.3.4 ለወረዳው ተጠሪ ተቋማት የሚፈፀመው የሰው ሀይል ስምሪት ይከታተላል ይደግፋል፡፡
9.3.5 ከሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ጋር አብሮ የሚሰራ አንድ ሰራተኛ (focal person) ይወክላል፡፡
9.4 ሆስፒታሎች ፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፣ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ደም ባንክ አገልግሎት ጽ/ቤቶች ተግባርና ሃላፊነት
9.4.1 በተቋማቸው የሚሰሩ ጤና ባለሙያዎችን የመደበኛ ዝውውሩ ፎርም በጥንቃቄ በማስሞላት በተወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለጤና
ጥበቃ ቢሮ የሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይረክቶሬት እንዲደርስ ያደርጋሉ፡፡
9.4.2 ከጤና ጥበቃ ቢሮ የሚላኩ የጤና ባለሙያዎችን ለመመደብ እንዲቻል በጤና ተቋሙ የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል መጠን እና በሙያ
አይነት ከበጀት ጋር በመለየት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለጤና ጠበቃ ቢሮ የሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይረክተሮት እንዲደርስ
ያደርጋሉ፡፡
9.4.3 ከጤና ጥበቃ ቢሮ የሚመደብላቸውን ባለሙያዎች በተገቢው የስራ መደብ ላይ በመመደብ አገልግሎቱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው
እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡
9.4.4 ባለሙያዎች ማግኘት ያላባቸውን ጥቅማጥቅም ማግኘት እንዲችሉ የባለሙያዎችን አገልግሎትና ማሟላት ያለበትን መረጃ በተሟላ
መንገድ ይይዛሉ ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለጤና ጥበቃ ቢሮ ያሳውቃሉ፡፡
9.4.5 በተቋማቸው ውስጥ በጀት ያለው ክፍት የስራ መደብ ሲኖር ከቢሮው ጋር በመመካከር በመመሪያው መሰረት በዝውውር ፣ በደረጃ
እድገት ወይም በቅጥር ያለውን ክፍት የስራ መደብ ያሟላሉ፡፡ ማሟላት ያልቻሉትን ክፍት የስራ መደብ የሰው ሀይል እንዲሟላላቸው ለጤና
ጥበቃ ቢሮ ያሳውቃል፡፡
9.5 የጤና ጣቢያ ተግባርና ኃላፊነት
9.5.1 በጤና ጣቢያው ውስጥ የሚሰሩ ጤና ባለሙያዎችን የዝውውር ፎርም በጥንቃቄ በማስሞላት በተወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በወቅቱ
ለወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት እና ለጤና ጥበቃ ጽ/ቤት እንዲደርስ ያደርጋል፡፡
9.5.2 ለተቋሙ የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል በመጠንና በሙያ አይነት በመለየት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለወረዳ ጤና ጥበቃ
ጽ/ቤት እንዲደርስ ያደርጋል፡፡
9.5.3 የጤና ባለሙያውን የሰው ሀይል መረጃ በአግባቡ በማደረጃት መረጃ ሲፈለግ ለወረዳ ጤና ጥበቃ እና ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት
ያቀርባል፡፡
9.6 የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ተግባርና ኃላፊነት
9.6.1 ከክልል ጤና ቢሮ እስከ ወረዳ የሚደረጉ መደበኛ ዝውውር የሚፈፀመውን ስምሪት ድጋፍ ፣ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡
9.6.2 በዚህ መመሪያ አፈፃፀም ዙሪያ ቤደረጃው ያልተፈቱ ቅሬታዎች ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እየቀረቡ የሚታይ ይሆናል፡፡
9.7 የዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ተግባርና ኃላፊነት
9.7.1 ከክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ተዘጋጅቶ በሚደርሰው የዝውውር ፎርም መሰረት ከዞን ዞን የሚጠይቁ የጤና ባለሙያዎችን መረጃ
በማጠናቀር በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲላክ ክትትል በማድረግ እና ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ በወቅቱ ለጤና ጥበቃ ቢሮው
ያስተላልፋል፡፡ በዞን ደረጃ የሚሰራውን ዝውውር አደራጅቶ ይይዛል፡፡
9.7.2 በዞኑና በስሩ ባሉ ወረዳዎች የጤና ባለሙያዎች የዝውውር ፎርም በወቅቱ ተሞልቶ እንዲላክለት በማድረግ እና ትክክለኛነቱን
በማረጋገጥ ዝውውሩን ለመፈፀም በሚያስችል መልኩ እንዲዘጋጅ ያደርጋል፡፡ ችግሮች ካጋጠሙ በዞኑ ጤና መምሪያ ጋር በመተባበር መፍትሔ
ያፈላልጋል፡፡
9.7.3 በተቀመጠው የማወዳደሪያ መስፈርት መሰረት በመደበኛ ዝውውር ጊዜ ከዞን ዞን የተዛወሩ ተወዳዳሪዎች በማካተት ዝውውሩን
በማከናወን ለተወዳዳሪዎች ውጤቱን ይፋ ያደርጋሉ፡፡
9.7.4 ከዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ የሚፈለግ መረጃ ሲኖር መረጃውን ለጤና ጥበቃ ቢሮ ያስተላልፋል፡፡
9.7.5 ለዞን ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ማለትም የወረዳ ጤና ጽ/ቤቶች የሰው ሀይል ስምሪት ይከታተላል ፣ ይደግፋል ፣ ይቆጣጠራል ፣ ችግሮች
ሲያጋጥሙ የመፍትሔ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
9.7.6 በዞን ውስጥ የሚፈፀመውን የጤና ባለሙያዎች የዝውውርና ምደባ መመሪያ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ መተግበሩን ይከታተላል
ይቆጣጠራል፡፡
9.8 የወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ተግባርና ኃላፊነት
9.8.1 በወረዳውና በስሩ ባሉ ጤና ተቋማት የሚሰሩ ጤና ባለሙያዎች የዝውውር ፎርም በወቅቱ ተሞልቶ እንዲላክለት በማድረግ እና
ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ ዝውውሩን ለመፈፀም በሚያስችል መልኩ እንዲዘጋጅ ያደርጋል፡፡ ችግሮች ካጋጠሙ ከወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት
ጋር በመተባበር መፍትሄ ያፈላልጋል፡፡
9.8.2 በተቀመጠው የማወዳደሪያ መስፈርት መሰረት በመደበኛ ዝውውር ጊዜ ከወረዳ ወደ ወረዳ የተዛወሩ ተወዳዳሪዎች በማካተት በወረዳ
ደረጃ የሚሰራውን ዝውውር በማከናወን ለተወዳዳሪዎችም ውጤቱን ይፋ ያደርጋሉ፡፡
9.8.3 የጤና ባለሙያዎችን የዝውውር እና ምደባ መረጃ ይይዛል አዲስ ምሩቅ የጤና ባለሙያዎችን ከጤና ጽ/ቤቱ ጋር በመነጋገር
ይመድባል፡፡ በወቅቱ እንዲጀምሩም ክትትል ያደርጋል፡፡
9.8.4 በዝውውር ፎርም መሰረት ከወረዳ ወረዳ ዝውውር የሚጠይቁ ጤና ባለሙያዎች መረጃ በማጠናቀር እና ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ
በወቅቱ ለዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ያስተላልፋል፡፡
9.9 የአማራ ክልል ጤና ባለሙያዎች ማህበር ተግባርና ኃላፊነት
9.9.1 በየደረጃው ያሉ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ምደባና ዝውውር ፣ ደረጃ እድገትና ቅጥር ፣ ሲከናወን በታዛቢነት ይሳተፋል፤
9.9.2 በጤና ባለሙያዎች የዝውውር ፣ ደረጃ እድገትና ቅጥር አፈፃፀም ላይ ችግረሮች ካጋጠሙ ከሂደቱ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር
መፍትሔ ያፈላልጋል
9.9.3 በተቀመጠው የማወዳደሪያ መስፈርት መሰረት ዝውውሩ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ አልተከናወነም ብሎ ሲያምን ችግሩን ለሚመለከተው
አካል በማሳወቅ መፍትሔ እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡
10 በየደረጃው መረጃ የሚሰባሰብበትንና ዝውውር የሚካሄድበት ጊዜ
10.1 በጤና ጣቢያ የዝውውር ፎርም የሚሞላው ከጥር 15 እስከ ጥር 30 ሆኖ ዝውውር ፈላጊዎች ይሞላሉ፡፡ በበጀት የተደገፈ ክፍት የስራ
መደብ ለወረዳ ሲቪል ሰርቪስ የሚላክበት ጊዜ ከየካቱት 1 እስከ የካቲት 10 ይሆናል፡፡
10.2 በወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ደረጃ ከየጤና ጣብያው ተሞልቶ የተላከው የዝውውር ፎርም እና በበጀት የተደገፈ ክፍት የስራ መደብ ከየካቲት
11 እስከ የካቲት 16 ድረስ ተጠናክሮ ለዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ይላካል፡፡
10.3 ለጤና ጥበቃ ቢሮው ተጠሪ የሆኑ የጤና ተቋማት የዝውውር ፎርም የሚሞላው እና በበጀት የተደገፈ ክፍት የስራ መደብ ተጠናቅሮ
ለጤና ጥበቃ ቢሮ የሚላክበት ጊዜ ከየካቲት 17 እስከ መጋቢት 10 ይሆናል፡፡
10.4 በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ በኩል ዝውውር የሚታይበት ጊዜ ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዚያ 5 ተሰርቶ ውጤቱ በይፋ በማስታወቂያ
ይገለፃል፡፡ በተሰራው ውጤት ላይ ቅሬታ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ወይም ተቋማት ቅሬታቸውን ከሚያዚያ 5 እስከ ሚያዚያ 15 ያቀርባሉ፡፡
የቀረበው ቅሬታ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ተስተካክሎ የመጨረሻ ውጤቱ ከሚያዚያ 16 እስከ ሚያዚያ 30 ለተቋማት ይገለፃል፡፡ በቅሬታ
ወቅት ሳይቀርብ የቀረ ቅሬታ በማንኛውም ምክንያት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በዝውውሩ ያለፉ ሰራተኞች ወደ ተዛወሩበት ቦታ ክሊራንስ
በመያዝ መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡
10.5 በተጠቀሰው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መሟላት ያለበት የዝውውር መረጃ ተሞልቶ ለሚመለከተው ተቋም ያልደረሰ መረጃ ተቀባይነት
አይኖረውም፡፡ ይህን ያልፈፀመ ፈፃሚ /ኃላፊ/ በሲቪል ሰርቪስ የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡
10.6 የዞን ሲቪል ሰርቪስ ከክልሉ የደረሰውንና እራሱንም አጠናቅሮ የያዘውን ከግንቦት 1 እስከ ግንቦት 11 ይሰራል፤ ውጤቱን ግንቦት 12
ያሳውቃል፡፡ በተሰራው ውጤት ላይ ቅሬታ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ወይም ተቋማት ቅሬታቸውን ግንቦት 13 እስከ 20 ያቀርባሉ፡፡ በየቀረበው
ቅሬታ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ተስተካክሎ የመጨረሻ ውጤቱ ግንቦት 21 እስከ ሰኔ 28 ለተቋማት ይገለፃል፡፡ በቅሬታ ወቅት ሳይቀርብ የቀረ
ቅሬታ በማንኛውም ምክንያት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በዝውውሩ ያለፉ ሰራተኞች ወደ ተዛወሩበት ቦታ ክሊራንስ በመያዝ መሄድ
ይኖርባቸዋል፡፡
10.7 የወረዳው ሲቪል ሰርቪስ ከዞኑ የደረሰውንና እራሱም አጠናቅሮ የያዘውን ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 9 ይሰራል ፣ ውጤቱን ሰኔ 10
ያሳውቃል፡፡ በተሰራው ውጤት ላይ ቅሬታ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ወይም ተቋማት ቅሬታቸውን ከሰኔ 11 እስከ ሰኔ 19 ያቀርባሉ፡፡ የቀረበው
ቅሬታ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ተስተካክሎ የመጨረሻ ውጤቱ ሰኔ 20 ለተቋማት ይገለፃል፡፡ በቅሬታ ወቅት ሳይቀርብ የቀረ ቅሬታ
በማንኛውም ምክንያት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በዝውውሩ ያለፉ ሰራተኞች ወደተዛወሩበት ቦታ ክሊራንስ በመያዝ በ 7 የስራ ቀናት ውስጥ
መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡
10.8 የዝውውር ፎርም የሚሞላበት ጊዜ እና ውጤት ይፋ የሚደረግበት ጊዜ የስራ ቀናትን ታሳቢ በማድረግ ሲሆን ውጤቱ ይፋ የሚሆንበት
የበዓል ቀን ከሆነ በሚቀጥለው የስራ ቀናት ይሆናል፡፡
ክፍል ስድስት
አንቀጽ 11 ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች፤
11.1 በመደበኛ ወይም በውጭ ወይም በውስጥ ዝውውር እና በቅጥር ለማሟላት የማይቻልበት ሁኔታ ሲኖርና ቦታው የግድ መሟላት
ካለበት በትውስት የስራ መደቡን ሸፍኖ ለጊዜው ማሰራት ይቻላል፡፡
11.2 በማንኛውም ደረጃ ዝውውር የተሰራለት የጤና ባለሙያ በመንግስት እውቅና በክረምት ተከታታይ ትምህርት /ኮርስ/ ወይም የርቀት
ትምህርት ፕሮግራም ወይም ተመሳሳይ ስልጠና በመጀመራቸው ምክንያት ወደ ተዛወረበት ቦታ እንዳይሄዱ ሊከለከሉ አይችሉም፡፡
11.3 በአንቀጽ 11.2 የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ በስልጠና ላያ ያሉ ጤና ባለሙያዎች ወደ ተዛወሩበት የጤና ተቋማት በስልጠና ላይ
መሆናቸውና ውል የገቡበትን ሰነድ ወይም ስልጠናውን ያጠናቀቁ ከሆነም በገቡት የስልጠና መመሪያ ውል መሰረት ምን ያህል ጊዜ
እንደቀራቸው ላይ ሊገለጽ ይገባል፡፡
11.4 ወደ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚደረግ ዝውውር በኮሌጆች ተፈላጊ ችሎታ መስፈርት መሰረት በማስታወቂያ በውድድር ይፈፀማል፡፡
ከማንኛውም የጤና ተቋም ወደ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚዛወሩ ባለሙያዎች የደመወዝ አከፋፈል በኮሌጅ ስኬል መሰረት ሲሆን ከጤና ሳይንስ
ኮሌጅ ወደ ማንኛውም ጤና ተቋም የሚዛወሩ ጤና ባለሙያዎች የደመወዝ አከፋፈል በሙያ ስያሜና ደረጃ (ፓናል) ጓደኞቹ በደረሱበት
መሰረት ይሆናል፡፡
11.5 አንድ ዝውውር ጠያቂ ፎርም ሞልቶ ከላከ በኋላ ሀሳቡን ከቀየረ ዝውውሩ ይፋ ከመሆኑ ከ 15 ቀን በፊት መሰረዝ ይችላል፡፡ ሆኖም
ዝውውሩ ተቀባይነት አግኝቶ ከተወሰነ በኋላ የዝውውር ጥያቄውን መሰረዝ አይቻልም፡፡ ሆኖም ዝውውሩ ተሰርቶለት ወደ ተዛወረበት ቦታ
የማይሄድ ባለሙያ አሳማኝ ማስረጃ እስከ አላማጣና ይህንም በተቋሙ ኃላፊ ተቀባይነት እስካላገኘ ድረስ ወደ ተዛወረበት ቦታ ሄዶ የመስራት
ግዴታ አለበት፡፡
11.6 በየትኛውም ደረጃ ተሞልቶ የተላከ የዝውውር ጥያቄ የሚያገለግለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
11.7 ማንኛውም ስምሪት ሲሰጥ የውስጥ ዝውውር ፣ ደረጃ እድገት ፣ የውጭ ዝውውር እና ቅጥር ፣ መሆኑን አውቆ በቅደም ተከተላቸው
ማካሄድ አለበት፡፡ ሆኖም የጤና ተቋም ማኔጅመንት ካመነበት በልዩ ሁኔታ አዲስ ምሩቅ የጤና ባለሙያዎችን ቅደም ተከተሉን ሳይጠብቅ
ቅጥር መፈፀም ይቻላል፡፡
11.8 በዚህ መመሪያ ያልተካተቱ የጤና ባለሙያዎች ስምሪት በአብክመ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መመሪያ መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
አንቀጽ 12. ተጠያቂነት
12.1 የጤና ባለሙያዎች የዝውውር ቅጽ መሙያ ጊዜን የተቋማት ኃላፊዎች /ባለሙያዎች/ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው ፣ የጤና ባለሙያዎች
ሳያሳውቁ የዝውውር ጊዜው ቢያልፍባቸው የጤና ተቋማትና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሰው ሀይል ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡
12.2 ማንኛውም የጤና ባለሙያ ህጋዊ ባልሆነ /በተጭበረበረ/ ሐሰተኛ/ ማስረጃ ጋብቻ እንደፈጸመ በማድግ ወይም የህክምና ማስረጃ ወይም
በሌላ ምክንያት ዝውውር እንዲታይለት ወይም እንዲዛወር ያደረገ ወይም ያቀረበ መሆኑ ሲረጋገጥ በዲሲፕሊን ስነ-ስርዓት አፈፃፀም መመሪያ
መሰረት ይጠየቃል ፣ ሆኖም ጉዳዩ በህግ የሚያስጠይቀው ሆኖ ከተገኘ አግባብ ባለው በወንጀል ይጠየቃል፡፡ የተፈፀመው ስምሪትም
ይሰረዛል፡፡
12.3 ይህን የዝውውር መመሪያ በተዛባ መልኩ ወይም ያላግባብ የሚፈፀም ወይም ማስረጃ ሳይቀርብ እንደቀረበ አድርጐ ወይም የቀረበውን
እንዳልቀረበ አድርጐ ዝውውር የፈፀመ ወይም ያስፈፀመ ባለሙያ ወይም ኃላፊ በዲስፕሊን ስነ-ስርዓት አፈፃፀም መመሪያ መሰረት ይጠየቃል፣
ሆኖም ጉዳዩ በወንጀል የሚያስጠይቀው ሆኖ ከተገኘ አግባብ ባለው ህግ ይጠየቃል፡፡ የተፈፀመው ስምሪትም ይሰረዛል፡፡
12.4 በየደረጃው ተሞልቶ ለሚመለከታቸው አካላት በሚላከው የጤና ባለሙያዎች የግል መረጃ ላይ አላግባብ ተሞልቶ ለሚፈጠረው ችግር
መረጃውን የሞላው ባለሙያ /ኃላፊ/ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
አንቀጽ 13 የቅሬታ አቀራረብ
13.1 አግባብ ያልሆነ የጤና ባለሙያዎች የዝውውርና ምደባ አፈፃፀም መመሪ ተፈጽሟል ተብሎ ሲገመት ለሚመለከተው አካል ቅሬታ ወይም
አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል፡፡
13.2 የጤና ባለሙያዎች የዝውውርና ምደባ አፈፃፀም መመሪያ ሂደት ላይ የሚቀርቡ ጥቆማዎችና ቅሬታዎች በመንግስት ሰራተኞች የቅሬታ
አቀራረብና አፈፃፀም ስነ-ስርዓት ደንብ መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
አንቀጽ 14 በዚህ መመሪያ ያልተሸፈኑ ጉዳዬችን በተመለከተ
14.1 የሰው ሀብት አስተዳደርን በተመለከተ በዚህ መመሪያ ያልተሸፈኑ አዳዲስ ጉዳዬች ሲያጋጥሙ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በተናጠል
አይቶ የመወሰን ስልጣን አለመው፡፡
አንቀጽ 15 የተሻሩና ተፈፃሚነት ስለማይኖራቸው ጉዳዮች
15.1 ከዚህ በፊት ሚያዚያ 1/2006 ዓ.ም ወጥቶ ስራ ላይ የነበረው የጤና ባለሙያዎች የዝውውርና ምደባ አፈፃፀም መመሪያ እና ይህን
ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሰርኩላሮችና ማብራሪያዎች በዚህ መመሪያ ተተክተዋል፡፡
አንቀጽ 16 መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ
ይህ መመሪያ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

You might also like