You are on page 1of 36

i

ማውጫ
ክፍል አንድ ................................................................................................................................................... 1
አጠቃላይ መግቢያ ......................................................................................................................................... 1
1.1 መግቢያ .............................................................................................................................................. 1
1.2 የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥልጣን እና ኃላፊነት ......................................................... 1
1.3 የሥራ መምሪያው ዓላማ .................................................................................................................. 2
1.4 የሥራ መምሪያው የተፈጻሚነት ወሰን............................................................................................. 2
ክፍል ሁለት .................................................................................................................................................. 3
የሰብአዊ መብቶች ክትትል ተግባራት መሠረታዊ ሐሳቦች .......................................................................... 3
2.1 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ትርጓሜ ................................................................................................. 3
2.2 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ዓላማዎች .................................................................................... 3
2.2.1 የሰብአዊ መብቶች ይዘት ሁኔታን መሰነድ እና የአፈጻጸም ደረጃዎችን ማሳየት ..................... 3
2.2.2 የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ መከላከል ................................................................... 3
2.2.3 ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አፋጣኝ እርምት እና ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ............................ 4
2.2.4 ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፍትሔ ማፈላለግ ...................................................................... 4
2.2.5 የሕግ፣ የፖሊሲ እና አሠራር ለውጦች እንዲመጡ ማድረግ ................................................... 4
2.2.6 በሰብአዊ መብቶች ላይ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ............................................................. 4
2.2.7 በሰብአዊ መብቶች ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ............................................................ 4
2.3 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ዓይነቶች ................................................................................................ 5
2.3.1 በተለዩ ሰብአዊ መብቶች ዘርፍ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ ክትትል (Thematic Monitoring) .... 5
2.3.2 በተለዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች መብቶች ላይ የሚደረግ ክትትል (Target Group
Monitoring) .......................................................................................................................................... 5
2.3.3 ሁኔታዎችን/ኹነቶችን መሠረት ያደረገ የሰብአዊ መብቶች ክትትል (Event/Incident based
Monitoring) .......................................................................................................................................... 5
2.3.4 የመልክአ- ምድር ወሰንን መሠረት ያደረገ የሰብአዊ መብቶች ክትትል (Area based
Monitoring) .......................................................................................................................................... 5
2.3.5 የሕጎችን አፈጻጸም መሠረት ያደረገ ክትትል (Legislation Implementation Monitoring) . 6
2.4 በሰብአዊ መብቶች ክትትል እና በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራዎች መካከል ያለው
መስተጋብር ................................................................................................................................................ 6
ክፍል ሦስት .................................................................................................................................................. 7
የሰብአዊ መብቶች የክትትል መርሆች.......................................................................................................... 7

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
ii

3.1 መግቢያ .............................................................................................................................................. 7


3.2 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ዝርዝር መርሆች .................................................................................. 7
3.2.1 ነጻነት፣ ገለልተኝነትን እና ሚዛናዊነትን መጠበቅ (independence, impartiality and
objectivity) ........................................................................................................................................... 7
3.2.2 ተቆርቋሪነትን ማሳየት (solidarity with victims) ................................................................... 7
3.2.3 ግልጽነትን ማስፈን (Transparency) ....................................................................................... 7
3.2.4 ታታሪነት እና ባለሙያነት (commitment and professionalism) ....................................... 8
3.2.5 ጉዳት አለማድረስ (Do No Harm) .......................................................................................... 8
3.2.6 የመንግሥት ሠራተኞች እና ኃላፊዎችን ማክበር (Respect for public servants and
authorities) .......................................................................................................................................... 9
3.2.7 ተዓማኒነትን ማረጋገጥ (Ensuring Credibility)2 ................................................................... 9
3.2.8 ነጻ ፈቃድን ማግኘት (Informed Consent) ............................................................................ 9
3.2.9 ምስጢር መጠበቅ (Confidentiality) ....................................................................................... 10
3.2.10 የደኅንነት ጥንቃቄዎችን መተግበር (Safety and Security) .............................................. 10
3.2.11 አካባቢያዊ አውዶችን በሚገባ መረዳት (Understanding the Context) ........................... 11
3.2.12 የአካታችነት መርሆችን መተግበር (Inclusiveness) ........................................................... 11
3.2.13 የክትትል ሥራው በይፋ እንዲታወቅ ማድረግ (Visibility) .................................................. 12
3.2.14 መብቶችን የሚመለከቱ መስፈርቶችን በሚገባ መረዳት........................................................ 12
3.2.15 አሳታፊነት (participatory) ................................................................................................... 12
ክፍል አራት ................................................................................................................................................ 14
የሰብአዊ መብቶች ክትትል ዘዴ እና ሂደት ................................................................................................ 14
4.1 የቅድመ ክትትል ሂደት ................................................................................................................... 14
4.1.1 የሁኔታ ትንተና (situation analysis) ................................................................................... 14
4.1.2 የክትትል ዝክረ ተግባር (ቢጋር / ToR) ዝግጅት ................................................................... 14
4.1.3 የሕግ ማዕቀፍ ትንታኔ እና የማገናዘቢያ ዝርዝር (checklist) ............................................... 15
4.1.4 የመጠይቆች (Questionnaires) ዝግጅት ................................................................................ 15
4.1.5 የመረጃ ምንጮችን መለየት ..................................................................................................... 15
4.2 የክትትል ሥራ ሂደት፡ መረጃ ማሰባሰብ ......................................................................................... 16
4.2.1 ቃለ-መጠይቅ ............................................................................................................................ 16
4.2.1.1 የቃለ መጠይቅ ዓይነቶች ...................................................................................................... 16

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
iii

4.2.1.2 የቃለ መጠይቅ ዋና ዋና ሂደቶች ......................................................................................... 19


4.2.1.3 ልዩ ጥበቃ/ትኩረት ሊደረግባቸው ከሚገባ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረግ ቃለ
መጠይቅ............................................................................................................................................... 24
4.2.1.4 ኃላፊነት ያለባቸውን የመንግሥት አካላት ቃለ መጠይቅ ማድረግ...................................... 26
4.2.2 የመስክ ጉብኝት ማድረግ (field visits) .................................................................................. 26
4.2.3 ኩነቶችን መታዘብ (observing events) ................................................................................ 27
4.2.4 የቁስ ወይም የፎረንሲክ ማስረጃ .............................................................................................. 27
4.2.5 የሰነድ ማስረጃዎች ................................................................................................................... 27
4.2.6 ከነጻ ምንጮች የተገኙ ማስረጃዎች (Open-Source Information) ...................................... 27
ክፍል አምስት.............................................................................................................................................. 29
የድህረ መስክ/ክትትል ሂደትና ሪፖርት ዝግጅት ....................................................................................... 29
5.1 መረጃን መመርመር እና መተንተን ................................................................................................ 29
5.2 ሪፖርት ማዘጋጀት ........................................................................................................................... 30
5.3 የማሰራጨት እና የውትወታ ተግባራት (Dissemination and Advocacy) ............................... 31
5.4 የመልሶ ክትትል ተግባራት ማከናወን ............................................................................................. 32

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
1

ክፍል አንድ
አጠቃላይ መግቢያ
1.1 መግቢያ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በፌዴራል ሕገ መንግሥት መሠረት ነጻ


ፌዴራላዊ የመንግሥት አካል ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012
እንደተሻሻለው) የተቋቋመ እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ ለሰብአዊ መብቶች
መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የሚሰራ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ነው።

ይህንን ዓላማ ለማስፈጸም ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ መሠረት የተለያዩ ሥልጣን እና ኃላፊነቶች
የተሰጡት ሲሆን ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው ተግባራት
መካከል አንዱ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማድረግ ነው።

የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተካተቱትን ተጨማሪ ተግባራት እና ኃላፊነቶችን እንዲሁም


በመተግበር ላይ የሚገኘውን ተቋማዊ ለውጥ ታሳቢ ባደረገ አግባብ የሰብአዊ መብቶች ክትትል
ሥራን በውጤታማነት ለማከናወን እንዲቻል ከተቋማዊ ማሻሻያው (institutional reform) በፊት
ሲሰራበት የቆየውን የክትትል የአፈጻጸም መመሪያ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተግኝቷል።

ይህ የሥራ መምሪያ የኮሚሽኑ የክትትል ሥራዎች የሚከናወኑበትን ማዕቀፍ የሚያስቀምጥ


ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች የክትትል ሥራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅት መከተል
ያለባቸውን የአሠራር ሥርዓቶችን ይዘረዝራል። በዚህም የክትትል ሥራ ምንነት መሠረታዊ
መርሆች፣ የክትትል ተግባራት ሂደት፣ መረጃ የመሰብሰብ እና መተንተን መርሆዎች ፣ የባለድርሻ
አካላት ሚና እንዲሁም ዝርዝር የክትትል ሥራዎች የሚከናወኑበትን ሁኔታ አካትቶ
ተዘጋጅቷል።

1.2 የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥልጣን እና ኃላፊነት

ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ መሠረት የተለያዩ ሥልጣን እና ኃላፊነቶች የተሰጡት ሲሆን ከነዚህም
መካከል በአዋጁ አንቀፅ 6(1) የተጠቀሰው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ
መንግሥት የተደነገጉ ሰብአዊ መብቶች በማንኛውም ዜጋ፣ በመንግሥት አካላት፣ በፖለቲካ
ድርጅቶች፣ በሌሎች ማህበራት እንዲሁም በባለስልጣኖቻቸው መከበራቸውን ማረጋገጥ
ይገኝበታል።

ይህንን ለማሳካት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማድረግ
ሲሆን ይህም ስልጣን የሚመነጨው ከዚሁ የአዋጁ ድንጋጌ እና ከተቋሙ ዓላማ ነው። በሕገ
መንግሥቱ ከታወቁት ሰብአዊ መብቶች በተጨማሪም የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 9(4)
እንደሚያስቀምጠው ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል
በመሆናቸው እና በአንቀፅ 13 (2) መሠረት በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የሰብአዊ መብቶች
ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ ሰነዶች እና መርሆዎች
ጋር በተጣጣመ ሁኔታ መተርጎም እንዳለባቸው በሚደነግጉት አንቀጾች መሠረት የኮሚሽኑ
የክትትል ሥራዎች ከዓለም አቀፍ እንዲሁም አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ መርሆች
እና ሕጎች አንጻርም የሚከናወኑ ናቸው። በተጨማሪም የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማትን

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
2

ሥልጣን እና ተግባራትን የሚዘረዝረው በተባበሩት መንግሥታት የጸደቁት መርሆች (የፓሪስ


መርሆች) የሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ በብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት
ከሚከናወኑ ቁልፍ ተግባራት አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሰፊ ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት በሁሉም ሰብአዊ


መብቶች ላይ ክትትል በማድረግ ምክረ-ሐሳቦችን የማቅረብ ኃላፊነት አለበት። በተለይም በማረሚያ
ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ይፋዊ ያልሆኑ የእስር ቦታዎች፣ እንዲሁም እንደ ትምህርት
ቤቶች እና የህክምና ተቋማት ያሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና ፋብሪካዎች ወ.ዘ.ተ...
፣ የስደተኞች እና ሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፖች ባሉ ስፍራዎች ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ
ጭምር በመጎብኘት በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል የማድረግ ስልጣን አለው።

ኮሚሽኑ ክስተቶችን ወይም ሁኔታዎችን መሠረት ያደረጉ የክትትል ተግባራትን የማከናወን


ኃላፊነትም አለበት። ከነዚህም ውስጥ በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 6 ላይ እንደተቀመጠው በምርጫ
ወቅት እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሥልጣን እና
ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ) የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ላይ ክትትል የማድረግ ሥልጣን
እና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

1.3 የሥራ መምሪያው ዓላማ

የዚህ የሥራ መምሪያ አጠቃላይ ዓላማ የኮሚሽኑን የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥርዓትን
ማዳበር እንዲሁም የሥራዎቹን ውጤታማነት፤ ሙያዊነት እንዲሁም ዘላቂ ተፅዕኖ (Impact)
ለማሳደግ ሲሆን የሚከተሉት ዝርዝር ዓላማዎች ይኖሩታል፡-

• ደረጃውን የጠበቀ የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ በመሥራት የሀገሪቱን የሰብአዊ


መብቶች አያያዝ ማሳደግ፤
• በሰብአዊ መብት ክትትል ሥራዎች ወጥ የሆነ፣ የተፋጠነ እና ውጤታማ የአሠራር ሂደት
እንዲኖር ማስቻል፤
• የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥርዓትን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ደረጃዎችን
በኮሚሽኑ አሠራሮች ውስጥ በማካተት በሥራ ላይ ማዋል፤
• የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ዘዴዎችን በማሳየት በኮሚሽኑ ውስጥ ለሚገኙ
ባለሙያዎች የተሻለ እውቀት እና ክህሎት በማዳበር ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ ማስቻል፤
• የክትትል ባለሙያዎች የሚያስፈልጓቸውን ሙያዊ ሥነ ምግባርን እንዲያሟሉ ማገዝ
ናቸው።

1.4 የሥራ መምሪያው የተፈጻሚነት ወሰን

ይህ የክትትል የሥራ መምሪያ ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ሥልጣን
እና ኃላፊነትን የመፈፀም ድርሻ ባላቸው የኮሚሸኑ የሥራ ክፍሎች ሁሉ ተፈፃሚ ይሆናል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
3

ክፍል ሁለት
የሰብአዊ መብቶች ክትትል ተግባራት መሠረታዊ ሐሳቦች
2.1 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ትርጓሜ

የሰብአዊ መብቶች ክትትል (human rights monitoring) የሰብአዊ መብቶች አከባበር እና


አጠባበቅ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ተከታታይ እና ወቅታዊ በሆነ መልኩ አስፈላጊ መረጃዎችን
በማሰባሰብ፤ በመሰነድ እና ትንታኔ በማድረግ እንዲሁም ሪፖርት በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው
የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እና ለሕብረተሰቡ የማሳወቅ እና ድክመቶች
እንዲሻሻሉ እና ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ለማስቻል ምክረ -ሐሳብ መስጠትን፣ ግንዛቤ
ማስጨበጥን፣ ለሕግ፤ ፖሊሲ እና አሠራር ለውጥ እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ውትወታ
ማድረግን የሚጨምር ተግባር ነው።

2.2 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ዓላማዎች

የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሚከናወንበት ዋነኛው ዓላማ መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን


የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነቶቹን እንዲወጣ ለማድረግ ነው። ከመንግሥት
በተጨማሪም ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ግዴታ ያለባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት
ኃላፊነቶቻቸውን በተገቢው እንዲወጡ ለማድረግም ያስችላል። የሰብአዊ መብቶች ክትትል
የሚከተሉት ዝርዝር ዓላማዎች አሉት፡-

2.2.1 የሰብአዊ መብቶች ይዘት ሁኔታን መሰነድ እና የአፈጻጸም ደረጃዎችን ማሳየት

ስልታዊ የሆነ እና በየጊዜው የሚደረግ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ የመብቶች ጥበቃ


የሚገኝበትን ሁኔታ እንዲሁም መብቶችን የማስፋፋት እና የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው
የመንግሥት አካላት ወይም ተቋማት ግዴታዎቻቸውን ምን ያህል በመወጣት ላይ እንደሚገኙ፤
የሚስተዋሉ ጠንካራ አፈጻጸሞችን፣ ክፍተቶችን እንዲሁም ጥሰቶችን ወይም የጥሰት አደጋዎችን
ከነመነሻ ምክንያቶቻቸው ለመለየት ያስችላል። በዚህ አግባብ የሚታወቁ ግኝቶች በኮሚሽኑ
በኩል ለሚወሰዱ እርምጃዎች እንደመነሻ ሆነው ያገለግላሉ።

2.2.2 የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ መከላከል

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራዎች የሚከናወኑት የተወሰኑ ሁኔታዎችን/ተቋማትን


ለመከታተል እና በተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ሪፖርት ለማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን፤ የሰብአዊ
መብቶች ጥሰት አደጋዎችን አስቀድሞ በመለየት ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲሁም
ስህተቶች እንዲታረሙ እና ለወደፊቱ ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይፈጠሩ ለመከላከልም ጭምር
ነው። ይህም ኮሚሽኑ በተደራጀ መልክ ሊሠራ ያቀደውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ቅድመ
ማስጠንቀቂያ ሥራ ይደግፋል። በክትትል ሂደት የሚገኙ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ
የሚከናወኑ የውትወታ እና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ሥራዎች ተመሳሳይ የሰብአዊ
መብቶች ጥሰቶች ወደፊት እንዳይከሰቱ ለመከላከልም አስተዋጽዖ ያበረክታሉ።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
4

2.2.3 ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አፋጣኝ እርምት እና ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ

የክትትል ሥራዎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሲከሰቱ አስፈላጊው አፋጣኝ ምላሽ እና ድጋፍ
ለማሰጠት ጠቀሜታ ይኖራቸዋል። ለምሳሌ ሰዎች በቁጥጥር ስር በሚውሉበት ጊዜ በቁጥጥር
ስር ሆነው ኢ-ሰብአዊ አያያዝ በሚደርስባቸው ወቅት ወይም ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች
መከሰታቸውን በክትትል ከተደረሰበት፤ ወዲያውኑ አስፈላጊው አፋጣኝ ምላሽ በመንግሥትም
ሆነ በሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲሰጥ ለማድረግ ያስችላል። ለምሳሌ ያለአግባብ
የታሰሩ ከሆነ እንዲፈቱ፣ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ከሆነ በአፋጣኝ እንዲቀርቡ፤ የሕክምና
አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ አስተዋጽዖ ያደርጋል።

2.2.4 ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፍትሔ ማፈላለግ

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ሌላው ዓላማ ለተከሰቱ የመብት ጥሰቶች መፍትሔ ማፈላለግ
ነው። የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መከታተል እና መሰነድ ከሚያስፈልግባቸው ዋና ዋና
ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የመብት ጥሰቶች በሚገባ እንዲታወቁ እና ለተጎጂዎች ፍትህን፣
እንደየሁኔታው ሕክምናን፣ የመልሶ ማገገሚያን እና ካሳን በሚያካትት መልኩ የተሟላ
መፍትሔ እንዲያገኙ ለማገዝ እንዲሁም አጥፊዎች እንዲለዩ እና የሕግ ተጠያቂነት እንዲኖር
ለማስቻል ነው።

2.2.5 የሕግ፣ የፖሊሲ እና አሠራር ለውጦች እንዲመጡ ማድረግ

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶች የመብት ጥሰቶች የመነጩት ከሕገ መንግሥቱ፣ ከዓለም
አቀፍ፣ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕግ እና መርሆች ጋር ከማይጣጣሙ ሀገራዊ ሕጎች፣
ፖሊሲዎች ወይም አሠራሮች መሆኑን በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚሁ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና
አሠራሮች እንዲሻሻሉ እና እንዲለወጡ ግፊት ማድረግን ያስችላሉ። በዚህም ምክንያት
መንግሥት በተለያዩ የዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የገባቸውን
ግዴታዎችን እንዲወጣ የሚያግዝም ይሆናል።

2.2.6 በሰብአዊ መብቶች ላይ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ከሚከናወንባቸው ዓላማዎች አንዱ ሰዎች በተለይም የመንግሥት


ኃላፊዎች በሰብአዊ መብቶች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ፣ አመለካከት እንዲሁም ድርጊት (ተግባር)
እንዲለወጥ ማስቻል ነው። በክትትል ሒደት የተሰነዱ ተዓማኒ እና ትክክለኛ መረጃዎችን
መሠረት በማድረግ የተለዩ ግኝቶች በተለያዩ የመንግሥት የሥልጣን እርከን ያሉ ኃላፊዎች
ምክረ ሃሳቦችን እንዲቀበሉ እና እንዲፈጽሙ ለሚደረጉ ጥረቶች ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ።

2.2.7 በሰብአዊ መብቶች ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶችን በይፋ ማሳወቅ በሕብረተሰቡ ዘንድ ስለ ሰብአዊ መብቶች
ያለውን አመለካከት እና ግንዛቤ በማሳደግ መብትና ግዴታውን አክባሪ እና ለመብቶቹም ቀናዒ
የሆነ ሕብረተሰብ እንዲኖር፤ በዚህም የመብት ጥሰቶች እንዲቀንሱ የራሱን አስተዋጽዖ ያደርጋል
። ይህ የግንዛቤ ማስፋፋት ሥራ የሲቪል ማኅበራት፣ ሚዲያ እና የሕዝብ ተወካዮች ላይም በጎ
ተፅዕኖ በማሳደር በሰብአዊ መብቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
5

2.3 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ዓይነቶች

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎች በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች
አፈጻጸም በተለዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ሰብአዊ መብቶች፣ የተመረጡ ኩነቶች ወይም ተቋሞች
በአንድ የተወሰነ አካባቢ ላይ ትኩረት አድርገው ሊከናወኑ ይችላሉ። በተጨማሪም የሕጎችን፣
ፖሊሲዎች ወይም አሠራሮች አፈጻጸም ደረጃ ለመፈተሽ ሊከናወኑ ይችላሉ። እነዚህ የክትትል
ዓይነቶች ብዙውን ጊዜ አንዱ ከሌላው ጋር ተወራራሽነት እና ተመጋጋቢነት ባለው መልኩ
የሚከናወኑ ናቸው።

2.3.1 በተለዩ ሰብአዊ መብቶች ዘርፍ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ ክትትል (Thematic


Monitoring)

የሰብአዊ መብቶች ክትትል አንድን የሰብአዊ መብት አይነት ወይም ዓይነቶች ላይ ትኩረት
በማድረግ ሊከናወን ይችላል። ወሰኑም በዚያው ልክ የሚሰፋ ወይም የሚጠብ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ የሰብአዊ መብቶች ክትትል የጤና ወይም የትምህርት መብቶች ላይ ብቻ አተኩሮ
ሊከናወን የሚችል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ላይ አትኩሮ
በአንጻራዊ ስፋት ሊከናወን ይችላል።

2.3.2 በተለዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች መብቶች ላይ የሚደረግ ክትትል


(Target Group Monitoring)

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ በሰፊው ሆኖ መላው የሕብረተሰብ ክፍልን ታሳቢ በማድረግ


ሊካሄድ የሚችል ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወሰኑን ጠበብ በማድረግ በተወሰኑ የሕብረተሰብ
ክፍሎች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ሊከናወን ይችላል። ለምሳሌ ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣
አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ ስደተኞችን ወይም የእስረኞችን
የሰብአዊ መብቶች አተገባበር ሁኔታን መሠረት በማድረግ ሊከናወን የሚችል ሲሆን በሰፊው
ደግሞ አጠቃላይ ሕብረተሰቡን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊከናወን ይችላል።

2.3.3 ሁኔታዎችን/ኹነቶችን መሠረት ያደረገ የሰብአዊ መብቶች ክትትል


(Event/Incident based Monitoring)

በተመረጡ ሁኔታዎች ወይም ኩነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የሰብአዊ መብቶች ክትትል


ሊከናወን ይችላል። ለምሳሌ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 6 ላይ እንደተመለከተው በምርጫ
ወቅት እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሥልጣን እና
ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ) የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ላይ ክትትል ሊከናወን ይችላል።

2.3.4 የመልክአ- ምድር ወሰንን መሠረት ያደረገ የሰብአዊ መብቶች ክትትል (Area
based Monitoring)

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ በመልክአ-ምድራዊ ወሰን ተገድቦም ሊከናወን ይችላል።


አንዳንድ የክትትል ሥራዎች አጠቃላይ ሀገር አቀፍ (ለምሳሌ ሀገር አቀፍ ምርጫን ሲመለከት)
ሽፋን በመስጠት ሊከናወኑ የሚችሉ ሲሆን፤ ሌሎች የክትትል ዓይነቶች ደግሞ በተወሰነ ክልል

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
6

ወይም አካባቢዎች ላይ ብቻ ለምሳሌ የተወሰነ ክልል(ዞን) የሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ወይም


በዚሁ አካባቢ በተከሰተ ግጭት ወይም ድርቅ ላይ ተወስነው ሊተገበሩ ይችላሉ።

2.3.5 የሕጎችን አፈጻጸም መሠረት ያደረገ ክትትል (Legislation Implementation


Monitoring)

የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተወሰኑ ወይም የተለዩ ሕጎችን አተገባበር መሠረት በማድረግ
ሊከናወን ይችላል። ይህም ለምሳሌ የአንድን አዋጅ አተገባበር ወይም አፈጻጸም ተግባራዊ መሆን
አለመሆን በሚቀመጡ መሠረታዊ መረጃዎች በመመልከት የተወሰዱ እርምጃዎች፣ በአዋጁ
የመጡ ውጤቶችን፣ የፍርድ ቤት የዳኝነት ሂደትን መከታተል (Trial Monitoring)፣ የአንድ
ተቋም አሰራር የሕግና የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ መሆኑን፣ ወ.ዘ.ተ… መከታተልን ሊያጠቃልል
ይችላል።

2.4 በሰብአዊ መብቶች ክትትል እና በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራዎች መካከል ያለው
መስተጋብር

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ (monitoring) እና የሰብአዊ መብቶች ምርምራ (investigation)


ከፍተኛ ተዛማጅነት ያላቸው ሥራዎች ናቸው። ሆኖም በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በአግባቡ
መገንዘብ ያስፈልጋል። የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ በዋናነት የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን
ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች ላይ በቅርበት ክትትል ማድረግን የሚያካትት ነው። ክትትል
መደረጉ በራሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መኖራቸውን የሚያመላክት አይደለም። የሰብአዊ
መብቶች ክትትል ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችን ፣ አሠራሮችን፣ ሥርዓቶችን እና አፈጻጸሞችን በቅርበት
በመፈተሽ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመለየት የሚከናወን ነው።

የሰብአዊ መብቶች ምርምራ በአንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ አቤቱታ በቀረበባቸው ጥቆማ
ወይም መረጃ በተገኘባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽሞበታል በተባለ ጉዳይ ላይ አትኩሮ
ጥሰቱ መፈጸም ወይም አለመፈጸሙን ለማረጋገጥ፤ የተፈጸመውን የመብት ጥሰት ዓይነት
ለመለየት የሚደረግ የምርመራ ሥራ ነው።

የሰብአዊ መብቶች ምርመራ እና ክትትል ሥራዎች የቅርብ ቁርኝት ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር
አንዳንድ ጊዜ በአንድ ላይ ሊከናወኑ የሚችሉበት ወይም አንዱ ለሌላው መነሻ የሚሆኑበት
አጋጣሚም አለ። ለምሳሌ የክትትል ሥራ በማከናወን ላይ የሚገኙ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች
በክትትሉ ሂደት አንድ የተለየ የመብት ጥሰት መፈጸሙን ካመኑ ምርመራ እንዲከናወን ምክረ
ሃሳብ ሊያቀርቡ ወይም ራሳቸው ምርመራ ሊያከናወኑ ይችላሉ። በተመሳሳይ በምርመራ የታዩ
ጉዳዮች ዙሪያ ወደፊት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል ክትትል ሊደረግ ይችላል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
7

ክፍል ሦስት
የሰብአዊ መብቶች የክትትል መርሆች
3.1 መግቢያ

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎች የታሰበላቸውን አላማ ከግብ እንዲያደርሱ፤ ውጤታማ እና


ተአማኒ እንዲሆኑ መሠረታዊ የሆኑ መርሆችን ተከትለው መከናወን አለባቸው።

3.2 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ዝርዝር መርሆች

የሰብአዊ መብቶች ክትትል በሚከተሉት እርስ በእርሳቸው ተደጋጋፊ የሆኑ ዋና ዋና መርሆች


ይመራል።

3.2.1 ነጻነት፣ ገለልተኝነትን እና ሚዛናዊነትን መጠበቅ (independence, impartiality


and objectivity)

የክትትል ባለመያዎች ኮሚሽኑ ነጻ እና ገለልተኛ ተቋም መሆኑን እንዲሁም በሥራቸው ላይ


ሁል ጊዜ ምክንያታዊ ትክክለኝነትን መጠበቅ ያለባቸው መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። መረጃ
የመሰብሰብ፣ የመሰነድ እንዲሁም የመተንተን ሁሉም ሥራዎች የተቋሙን ስልጣን እና ኃላፊነትን
እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች መሠረታዊ መርሆችን ብቻ መሠረት በማድረግ መከናወን
ይኖርባቸዋል። የክትትል ባለሙያዎች ሁል ጊዜ ሚዛናዊነትን መጠበቅ ይገባቸዋል። ለአንድ ወገን
ያደሉ መሆን ወይም መስለው መታየት የለባቸውም። በተጨማሪም የክትትል ባለሙያዎች የግል
እምነታቸው እና ሃሳባቸው በሚገባ መገንዘብ እና በሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራቸው ላይ
ተጽዕኖ እንዳያሳድር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

3.2.2 ተቆርቋሪነትን ማሳየት (solidarity with victims)

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ባለሙያዎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጎጂ የሆኑ ሰዎችን
በሚያነጋግሩበት ወቅት የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጉዳት፣ በደል እና ስቃይ በሚገባ መረዳት
እና ተቆርቋሪነት እና ርህራሄ ማሳየት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ከጉዳት ተጋላጭነት ጋር
ስለሚኖር የማኅበረ ሥነ ልቦና ጉዳት (trauma) በሚገባ ግንዛቤ መውስድ ይኖርባቸዋል።
በሚጠቀሟቸው ቃላትም ሆነ በአካላዊ ሁኔታቸው በተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ላይ አሉታዊ
እና የተዛባ አመለካከትን፣ ሚዛናዊነትን ወይም ገለልተኛነትን በሚጎዳ መልኩ እንዳይተረጎሙ
ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

3.2.3 ግልጽነትን ማስፈን (Transparency)

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎችን አስመልክቶ ሁኔታው በፈቀደ መጠን ሁሉ


ለሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ግልጽነትን ማስፈን ይገባል። ይህም
እንደየአግባብነቱ የፌዴራል፣ የክልል፣ በተዋረድ የሚገኙ የመንግሥት አካላት፣ ሲቪል ማህበረሰብ
እና የአካባቢው ነዋሪዎች የክትትል ሥራ የሚከናወን መሆኑን እንዲያውቁ ማድረግን እንዲሁም
በተለይ ተጎጂዎች እና ተባባሪ ሰዎች የክትትል ሥራው የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው እንዲያውቁ
ማድረግን ያካትታል። ግልጽነትን ማስፈን ከሌሎች አጋር ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ለምሳሌ

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
8

ከመንግሥት ኃላፊዎች፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ጋር ባላቸው


ግንኙነት እና ትብብር ላይ ትልቅ በጎ ሚና የሚጫወት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ሆኖም ግልጸኝነትን የማስፈን መርህ ከመረጃ ሰጪዎች ጥበቃ፣ የደኅንነት ሁኔታዎችን


ከማክበር፣ ሚስጥር ከመጠበቅ እና ጉዳት ካለማድረስ መርሆዎች እንዲሁም ኮሚሽኑ አስቀድሞ
ሳያሳውቅ ክትትል የሚያደርግባቸው አሠራሮች ጋር በተጣጣመ መልኩ ሊተገበር ይገባል።

3.2.4 ታታሪነት እና ባለሙያነት (commitment and professionalism)

ውጤታማ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ክትትል በርካታ መረጃዎችን እና ሰነዶችን ማሰባሰብን፣


መተንተንን፣ መሰነድን እንዲሁም ምላሽ መስጠትን የሚያጠቃልል በመሆኑ ረጅም እና አስቸጋሪ
ሥራ ሊሆን ይችላል። መረጃዎቹ ከተለያዩ ምንጮች በተከታታይነት እና ወጥነት ባለው መልኩ
ከተለያዩ አካላት መሰብሰብ የሚኖርባቸው ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ ሊሆን
ይችላል።

ሁሉን አቀፍ መረጃ ተሰብስቦ እስኪያልቅ ስለሁኔታው ግልጽ እና የተሟላ ግንዛቤ እስኪያዝ ድረስ
የክትትል ባለሙያዎች ረዘም ላለ ጊዜ ሥራቸውን የሚቀጥሉ ይሆናሉ። በተለይም የመንግሥት
አካላትን እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን በተከታታይ መወትወት ሊያስፈልግ
ይችላል። በመሆኑም ባለሙያዎች ያለመሰልቸት እና ተስፋ ባለመቁረጥ፣ ታታሪ በመሆን፣
በትዕግስት እና በጽናት ሥራዎቻቸውን ማከናወን ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም የክትትል ሥራ የሚያከናውኑ ባለሙያዎች በማንኛውም ጊዜ እና በማንኛውም


ሁኔታ ውስጥ በጥሩ ባለሙያነትና በጥሩ የማመዛዘን ችሎታን ተግባራዊ ማድረግን መለማመድ
ይኖርባቸዋል።

3.2.5 ጉዳት አለማድረስ (Do No Harm)

በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ በሰብአዊ መብቶች የክትትል ሂደት ተጎጂዎች እንዲሁም መረጃ
የሚሰጡ ሰዎች በክትትሉ ሂደት ባላቸው ተሳትፎ ምክንያት የሕይወት፤ የአካል እና የስነ ልቦና
ጉዳት(ጥቃት) እንዳይደርስባቸው አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የክትትል
ባለሙያዎች መረጃ ከሚሰጡ ሰዎች ጋር ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት በዚህ ግንኙነት
ምክንያት በሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መሆን አለመሆኑን በሚገባ መመዘን
ይኖርባቸዋል። ባለሙያዎቹ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ወይም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት
ዓይነት እና መጠን መገመት የማይችሉ ከሆነ፤ ከመረጃ ሰጪው ጋር ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ
ወይም አማራጭ ዘዴዎችን መሞከር አለባቸው። ለምሳሌ የመረጃ ምንጮቹን ለብቻ በሚስጥር
ማነጋገር ወይም እንደየሁኔታው ከሌሎች ሰዎች ተለይተው ትኩረት ውስጥ ሊገቡ በማይችሉበት
ሁኔታ ቃለመጠይቅ ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል። የሰብአዊ መብቶች የክትትል ባለሙያው
ድርጊትም ሆነ የሚጠበቅበትን ባለማድረግ በተጎጂዎች፣ መረጃ ሰጪዎች ወይም ሌሎች በክትትሉ
ተባባሪ በሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ አይገባም።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
9

3.2.6 የመንግሥት ሠራተኞች እና ኃላፊዎችን ማክበር (Respect for public


servants and authorities)

ከሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎች ዓላማዎች ውስጥ አንዱ የመንግሥት ሠራተኞች እና


ኃላፊዎች ሥራቸውን በሚገባ እንዲወጡ ወይም አሰራራቸውን (አመለካከታቸውን) እንዲያሻሽሉ
ማገዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎች የሚከናወኑት
ዋነኛውን የመንግሥት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የመጠበቅ እና የሟሟላት ኃላፊነትን
ለመተካት ሳይሆን የመንግሥት አካላት እነዚህን ኃላፊነቶቻቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል
ክፍተቶችን በማሳየት እና የሚሻሻሉበትን ሁኔታ በመጠቆም በዚህም አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች
አያያዝ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ነው። በመሆኑም በክትትል ወቅት የመንግሥት
ሠራተኞች እና ኃላፊዎችን ሥራ አለማደናቀፍ ይልቁንም ማክበር አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም
ከመንግሥት ሠራተኞች እና ኃላፊዎች ጋር ሙያዊ መከባበር ያለበት ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ
ነው።

የመንግሥት ሠራተኞች እና ኃላፊዎች ከሰብአዊ መብቶች የክትትል ባለሙያዎች ጋር በመከባበር


ላይ የተመሠረተ ግንኙነት የሌላቸው ከሆነ፤ ከክትትል ሂደቱ ጋር ባለመተባበር አሉታዊ ተጽእኖ
ሊፈጠርም ይችላል። የክትትል ባለሙያዎች በሥራ የሚያገኟቸውን ሁሉንም ወገኖች
ከማግኘታቸው በፊት ተገቢውን ሙያዊ ዝግጅት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ከመረጃ
ሰጪዎች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች እና ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በተለይ
ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያደርጉት መስተጋብር በጥንቃቄ መከናወን ይኖርበታል። የክትትል
ባለሙያዎች ኮሚሽኑን የሥራውን ወሰን እና የራሳቸውን ሚና በሚገባ በማስተዋወቅ ከሌሎች
ባለድርሻዎች ጋር ለሚኖር የሥራ ግንኙነት ውጤታማነት የበኩላቸውን ማበርከት ይገባቸዋል።

3.2.7 ተዓማኒነትን ማረጋገጥ (Ensuring Credibility)2

የክትትል ባለሙያዎች የኮሚሽኑን ተቀባይነት እና ተዓማኒነት በሚያስጠብቅ መልኩ


ተግባራቸውን ማከናወን አለባቸው። ይህም ማለት የኮሚሽኑን እሴቶች እና የሥነ ምግባር ደንቦች
አክብሮ እና በሕግ በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት ብቻ ተወስኖ ኃላፊነትን መወጣት ማለት
ሲሆን ለምሳሌ የክትትል ባለሙያዎች ሊተገበሩት የማይችሉትን ወይም በኮሚሽኑ ሥልጣን ሥር
ያልሆነን ድርጊት እፈጽማለሁ ወይም ኮሚሽኑ ይፈጽማል በማለት የተስፋ ቃልን መስጠት
የለባቸውም።

3.2.8 ነጻ ፈቃድን ማግኘት (Informed Consent)

ከመረጃ ሰጪዎች ጋር በሚደረግ የቃለ መጠይቅ ወይም ሌላ ማናቸውም የመረጃ ማሰባሰብ ወቅት
የክትትል ባለሙያዎች መረጃዎችን ለመቀበል፣ ለመጠቀምም ሆነ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ለማጋራት
ሁል ጊዜ የመረጃ ሰጪዎችን ነጻ ፈቃድ በግልጽ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህም ማለት የምስጢር
መጠበቅ መርሆችን የሚሰበሰበው መረጃ ለምን አገልግሎት ሊውል እንደታሰበ እንዲሁም
መረጃዎቹ እንዴት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ማስረዳትን ይጨምራል። መረጃው በጥቅም ላይ
በሚውልበት ወቅት በመረጃ ሰጪዎች ደኅንነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ወይም የጉዳት ስጋቶች
ሊፈጥር የሚችል ከሆነ መረጃ ሰጪዎች በራሳቸው ይህንን ሊያውቁ ወይም ሊገምቱ ያልቻሉ
ቢሆንም እንኳ የክትትል ባለሙያዎች ይህንኑ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው። የክትትል ባለሙያው

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
10

መረጃ ሰጪው የሚሰጠው ነጻ ፈቃድ መረጃው በኮሚሽኑ ጥቅም ላይ በመዋሉ እና/ወይም


ለሦስተኛ ወገኖች ተላልፎ በመሰጠቱ ሊመጣ ስለሚችለው የደኅንነት ሥጋት የጠራ ግንዛቤ ይዞ
መሰጠቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

3.2.9 ምስጢር መጠበቅ (Confidentiality)

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ባለሙያዎች የመረጃ ምንጭ ለሚሆኑ ሰዎች በሙሉ ማንነታቸው
እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የተለየ ስምምነት እስካልተሰጠ ድረስ የተሰጠው መረጃ በምስጢር
እንደሚያዝ እና እንደሚጠበቅ ማረጋገጥ አለባቸው። የምስጢር መጠበቅ መርህ ከጉዳት
አለማድረስ መርህ ጋር ተያያዥነት ያለው መርህ ሲሆን፤ የክትትል ባለሙያዎች የመረጃ
ሰጪዎቹን ማንነት በምስጢር የመጠበቅ ግዴታን የሚያመላክት ነው።

የዚህ ምስጢር መጠበቅ መርህ መጣስ በተጎጂዎች ላይ እንዲሁም መረጃ ሰጪዎች እና ሌሎች
ተባባሪ አካላት፤ በባለሙያዎቹ ተዓማኒነት እና ደኅንነት ፤ ተቋሙ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው
ተቀባይነት እና ተዓማኒነት፤ እንዲሁም በአጠቃላይ በሥራው ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ የሆነ
አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻል።

ስለሆነም የመረጃ ምንጭ የሆኑ ሰዎች ፈቃዳቸውን በግልጽ ካልሰጡ በስተቀር ሚስጥራዊነቱ
የሚጠበቅ መሆኑን የክትትል ባሙያዎች በሚገባ ማስረዳት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም
የክትትል ባለሙያዎች ግልጽ ፈቃድ የተሰጣቸው ቢሆንም እንኳ መረጃ ሰጪዎች እና ሌሎች
አካላት ላይ (ለምሳሌ በቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ) ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በሚገባ በመመዘን
አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ የማድረግ እና አደጋውን ሊያስወግድ በሚችል መልኩ ሥራዎችን
የማከናወን ኃላፊነት አለባቸው። የመረጃ ሰጪዎች እንዲሁም ሌሎች ተባባሪ አካላት ደኅንነት
የክትትል ባለሙያዎች ዋነኛ ትኩረት ሊያደርጉበት የሚገባ እና ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ቅድሚያ
የሚሰጠው ጉዳይ መሆን ይኖርበታል።

በዚህ መሠረት የተሰበሰቡ መረጃዎች በተለይም የመረጃ ሰጪዎችን ማንነት ሊያሳውቁ የሚችሉ
መረጃዎች (personally identifiable data) በከፍተኛ ጥንቃቄ መጠበቅ እና መቀመጥ
ይኖርባቸዋል። ይህም የጥንቃቄ ሂደት የተሰበሰቡትን መረጃዎች በሙሉ፤ የሚሰነዱበት
(የሚቀመጡበት) እንዲሁም ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ሁኔታዎች ሁሉ ይመለከታል።

3.2.10 የደኅንነት ጥንቃቄዎችን መተግበር (Safety and Security)

ይህ መርህ የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎችን የሚያከናውኑ ባለሙያዎችንም ሆኑ ከነሱ


ጋር የሥራ ትስስር ያላቸው ሌሎች ሰዎችን ደኅንነት ይጨምራል። የክትትል ባለሙያዎች
የራሳቸው እና የተቋሙን ደኅንነት ለማስጠበቅ መሠረታዊ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ
ይጠበቅባቸዋል። የክትትል ባለሙያዎች ለሥራ የሚንቀሳቀሱባቸውን አካባቢዎች የደኅንነት ሁኔታ
መከታተል እና ተገቢ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሁሉ መተግበር አለባቸው። የደኅንነት ሁኔታዎችን
የማክበር መርህ፣ ጉዳት አለማድረስ፣ ምስጢር ከመጠበቅ እና ነፃ ፈቃድ መርሆች ጋር በተያያዘ
እና በተናበበ መልኩ መታየት የሚኖርበት ሲሆን፤ የክትትል ባለሙያዎች ከራሳቸው ወይም
ከተቋሙ ደኅንነት በተጨማሪ ለሚተባበሩ ሰዎችም ደኅንነት ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል።
የክትትል ባለሙያዎች ለክትትል ሥራው ተባባሪ ለሆኑ ሰዎች ሊተገብሩት የማይችሉትን
የደኅንነት ማረጋገጫ (ዋስትና) ከመስጠት መቆጠብም ይኖርባቸዋል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
11

3.2.11 አካባቢያዊ አውዶችን በሚገባ መረዳት (Understanding the Context)

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎችን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች የክትትል ሥራዎችን


የሚሰሩበትን አካባቢ(ክልል) አካባቢያዊ ሁኔታ (አውድ) በሚገባ መረዳት ይኖርባቸዋል። በተለይም
የሥነ ሕዝብ ሁኔታ (demography)፣ ታሪክ ፣ ኢኮኖሚ፣ መንግሥታዊ አደረጃጀት፣ የማሕበራዊ
እና ባህላዊ እንዲሁም ሌሎች መስተጋብሮችን በሚገባ መረዳት ይኖርባቸዋል። የክትትል
ባለሙያዎች የአካባቢ ሁኔታዎችን መረዳት፤ ለሚያደርጉት ክትትል ከመሠረቱ ለመረዳት እና
መፍትሔዎችን ለመጠቆም የሚያግዛቸው ከመሆኑም በላይ ከሚከታተሏቸው አካላት እንዲሁም
ከአካባቢው ማሕበረሰብ ቀና ትብብርን ለማግኘት ይጠቅማቸዋል። በሌላ በኩል የክትትል
ባለሙያዎች ባሕልን መረዳት አለባቸው ቢባልም ባሐልን ወይንም አካባቢያዊ ሁኔታዎችን
መሠረት ያደረጉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መቀበል ወይም አመክንዮ በመስጠት ማለፍ
አለባቸው ማለት አይደለም። ይልቁንም በባሕል ወይም በልማዳዊ አሠራር የሚፈጸሙ የሰብአዊ
መብቶች ጥሰቶችን ለይቶ በማውጣት እንዲለወጡና እንዲሻሻሉ ማድረግ ይገባል። የክትትል
ባለሙያዎች ሁል ጊዜም ቢሆን የሰብአዊ መብቶች መርሆችን እና መመዘኛዎችን ለሥራቸው
መርህ አድረገው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

3.2.12 የአካታችነት መርሆችን መተግበር (Inclusiveness)

ሀ. ሥርዓተ- ፆታን ማካተት

የሰብአዊ መብቶች ክትትል በሚከናወንበት ወቅት የሥርዓተ ፆታ ማካተት መርህን መተግበር


በጣም አስፈላጊ ነው። ይህም በተለያዩ የክትትል ሂደቱ ደረጃዎች እና ግምገማዎች ላይ ሁሉ
የፆታ አመላካቾችን መጠቀምን እንዲሁም መብቶቹን ከሥርዓተ ፆታ አንጻር በመመልከት
መረጃዎችን መሰብሰብን እና መተንተንን የሚያጠቃልል ይሆናል። ክትትል ብሚደረግበት ወቅት
ሥርዓተ ፆታን ማካተት ክትትል የሚደረግበት የመብት ዓይነት አተገባበሩ ወንዶችን እና ሴቶች
(ወንድ እና ሴት ሕፃናትን ጨምሮ) እንዴት እና በምን ሁኔታ በተለያየ መልኩ እንደሚነካ ወይም
እንደሚጎዳ መለየትን ይጠይቃል። በተጨማሪም በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አመለካከቶች እና
እሴቶች እንዲሁም በተቋማት ውስጥ ያሉ አሠራሮች በመብቱ አተገባበር (አከባበር፣ ጥሰቶች
እንዲሁም ተጠቃሚነት) ላይ የሚኖራቸውን ተጽእኖ መገምገምን እንዲሁም የውትወታ ሥራዎች
በሚከናወኑበት ወቅት የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች በሚገባ ተካትተው እንዲተገበሩ ማድረግ
ያስፈልጋል።1

ለ. ሕፃናትን፣ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን ማካተት

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ በሚታቀድበት፣ በሚተገበርበት አንዲሁም ሪፖርት


በሚጠናቀርበት ወቅት ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ማካተት ሊተገበር የሚገባው
አንዱ የማካተት መርህ ነው። ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች የሰብአዊ መብቶች ጥሰት
ያላቸው ተጋላጭነት ከተቀረው የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ ከፍ ያለ በመሆኑ ራሱን ችሎ ሊታይ
የሚገባው ጉዳይ ነው። አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ክትትሉ በሚከናወንበት ወቅት አካል

1
በኮሚሽኑ ጸድቆ በስራ ላይ ያለውን የሥርዓተ ፆታ አካታችነት ማንዋልን (2013) በተለይም የክትትል ሥራዎችን በሚመለከት የተዘረዘሩትን ተግባራትን በሚገባ
መገንዘብ እና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
12

ጉዳተኞችን ከማካተትም ባሻገር በተፈጠሩ ልዩ ልዩ ክስተቶች ምክንያት ለአዲስ የአካል ጉዳት


ዓይነት የተጋለጡ ሰዎችንም ማካተት ያስፈልጋል።

የሕፃናት፣ አረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ማካተት፤ ክትትል የሚደረግባቸውን ሰብአዊ


መብቶች ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለየ
በምን መልኩ ለመብት ጥሰት እንደሚጋለጡ መለየትን ይጠይቃል። እነዚህን ሕብረተሰብ
ክፍሎችን የሚመለከቱ ሕጎችን አተገባበር መገምገምን እንዲሁም በአንጻራዊነት ከተቀረው
የኅበረተሰብ ክፍል በተለየ ሁኔታ የሕፃናትት፣ አረጋውያንን እና የአካል ጉዳተኞችን የሰብአዊ
መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ መተንተንን እና በመጨረሻም በሚሰጡ ማጠቃለያዎች፣ ምክረሐሳቦች
እና የክትትል ሥራውን ተከትሎ በሚሰሩ የውትወታ እና ሌሎች ተከታታይ ሥራዎች ላይ
መጠነኛ ማመቻቸት በማድረግ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን አካቶ መሥራትን
የሚያጠቃልል ሲሆን ለምሳሌ በክትትል ሥራው ላይ አካል ጉዳተኛ ባለሞያዎች እንዲሳተፉ
ማድረግም አንዱ የማካተት መገለጫ ነው።

3.2.13 የክትትል ሥራው በይፋ እንዲታወቅ ማድረግ (Visibility)

በአንዳንድ ሁኔታዎች የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራዎችን ይፋ ማድረግ (ማሳወቅ) ሌሎች


የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ሊከላከል ይችላል። ሆኖም እንደሁኔታው አንዳንድ ጊዜ
ደግሞ እይታን መቀነስ (low profile) ወይም የክትትል ባለሙያዎች እራሳቸውን ከዕይታ ውጪ
በማድረግ (እንደአስፈላጊነቱ በምስጢር በመንቀሳቀስ) ሥራዎችን መከወን ሊያስፈልግ እንደሚችል
መረዳት ያስፈልጋል። በመሆኑም የክትትል ሥራው እንዲታይ የማድረግን መርህ አግባብነት
ባለው ጊዜ ብቻ ከሌሎች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ነው።

3.2.14 መብቶችን የሚመለከቱ መስፈርቶችን በሚገባ መረዳት

የሰብአዊ መብት የክትትል ሥራን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮ እና


ከሚከታተሉት ሁኔታ ጋር የሚዛመዱ ሀገር አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ
መብቶች መስፈርቶችን ወይም ደረጃዎችን በሚገባ መረዳት አለባቸው። ይህም ክትትል
የሚደረግበትን መብት፣ የሕግ ማዕቀፉን፣ አጠቃላይ ይዘቱን፣ አመላካቾቹን፣ ወሰኖቹን እንዲሁም
ገደቦች ካሉ በሚገባ መረዳት ለክትትል ሥራው አስፈላጊ ነው።

3.2.15 አሳታፊነት (participatory)

የአሳታፊነት መርህ የመብቶች ባለቤቶችን በበቂ ሁኔታ ማሳተፍን እና ማማከርን ያመለክታል።


እንዲሁም የክትትል ሥራ በሚከናወንበት ወቅት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚደረጉ
ምክክሮች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። በክትትሉ ሂደት ሁሉንም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሕብረተሰብ
ክፍሎች በተለይም ለመብት ጥሰት ልዩ ተጋላጭነት የሚያጋጥማቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን
ማሳተፍ እና ለተሳትፎ የሚያስፈልጋቸውን መጠነኛ ማመቻቸት ማድረግ ተገቢ ነው። በዚህም
ረገድ ዕድሜን፣ ጾታን፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ የጥቃት ተጎጂነትን፣ቋንቋና ባህልን ሌሎችን
ሁኔታዎች ከግምት ያስገባ የተሳትፎ ሂደትን ማመቻቸት አስፈላጊ ይሆናል። በተጨማሪም ሌሎች
ተመሳሳይ ሥራዎችን ከሚያከናውኑ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር
የሚኖር ቅንጅት እና ምክክር አላስፈላጊ የሥራ ድግግሞሽን ወይም የሚጋጭ ውጤቶች

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
13

እንዳይከሰቱ ለመከላከል ያግዛል። የአሳታፊነት መርህ በኮሚሽኑ ውስጥ ከሚገኙ ልዩ ልዩ የሥራ


ክፍሎች ጋርም የሚኖርን መመካከር እና ቅንጅትን የሚያጠቃልል ነው።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
14

ክፍል አራት
የሰብአዊ መብቶች ክትትል ዘዴ እና ሂደት

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሂደት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ማለትም የቅድመ ክትትል


ሂደት፤ የክትትል ሂደት እና የድህረ ክትትል ሂደትን ያካትታል።

4.1 የቅድመ ክትትል ሂደት

በቅድመ- ክትትል ሂደት ውስጥ ከሚካተቱ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሁኔታ ትንተና፣


የክትትል ቢጋሮች፣ የሕግ ትንታኔ እና የቼክሊስቶች ዝግጅት እንዲሁም የመጠይቆች ዝግጅት
ናቸው።

4.1.1 የሁኔታ ትንተና (situation analysis)

ማንኛውንም የክትትል ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ክትትሉ በሚካሔድበት አካባቢ አግባብነት


ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ተቋማዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም ከጸጥታ እና
የክትትል ቡድኑ አባላት ደኅንነት ጋር በተያያዘ ታሳቢ ሊደረጉ የሚገቡ አጠቃላይ መረጃዎችን
ያካተተ የሁኔታ ትንተና ሰነድ መዘጋጀት ይኖርበታል።

4.1.2 የክትትል ዝክረ ተግባር (ቢጋር / ToR) ዝግጅት

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራው ከመጀመሩ አስቀድሞ የሚከተሉትን ያካተተ ዝክረ ተግባር
(ቢጋር /ToR) ይዘጋጃል፦
• የክትትሉ ዳራ (ከሁኔታ ትንተና የሚወሰድ)
• የክትትሉን ጥቅል እና ዝርዝር ዓላማዎች እና ወሰን
• የክትትሉ ስልት
• ከክትትሉ የሚጠበቁ ውጤቶች (Deliverables/Outputs)
• አስፈላጊ የሠው ሃይል ብዛት፣ የፆታና የብዝሃነት ስብጥር እና የተለያዩ ባለሙያዎች
ሚና
• ክትትሉን ለማጠናቀቅ የሚፈጀውን ጊዜ
• አስፈላጊ የሎጂስቲክስ ጉዳዮችን እና
• ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ወጪ እና የበጀት ምንጭ ማመላከት ይኖርበታል።

ዝክረ ተግባሩ (ቢጋሩ) በሚመለከተው ኃላፊ ከመጽደቁ በፊት በሥራው የሚካፈሉ ሌሎች የተቋሙ
የሥራ ክፍሎች ካሉ ተገቢው ውይይት ተደርጎበት እና ግብዓቶች ተካትተው ሊዘጋጅ ይገባል።
በተጨማሪም ክትትሉን ለማካሄድ የተመረጠው ሥነ ዘዴ ወይም ስልት ስለተመረጠበት
ምክንያት፣ ቃለ መጠይቅ ይደረጋሉ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ብዛት ግምት እና የሚገኙበት
አካባቢ የመሰሉ መረጃዎች እና ማብራሪያዎች መገለጽ ይኖርበታል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
15

4.1.3 የሕግ ማዕቀፍ ትንታኔ እና የማገናዘቢያ ዝርዝር (checklist)

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ክትትል የሚካሔድበትን መብት በተመለከተ ዓለም አቀፍ እና


አህጉራዊ ስምምነቶችን እና መመዘኛዎችን እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ አግባብነት
ያላቸውን ብሔራዊ ሕጎች በመለየት በተግባር ያለውን አፈጻጸም ከሕግ ማዕቀፎች እና
መመዘኛዎች አንጻር ለመለካት የሚያስችል የሕግ ትንታኔ እንዲሁም ዝርዝር የማገናዘቢያ
ዝርዝር (checklist)መዘጋጀት ይኖርበታል። የማገናዘቢያ ዝርዝሮች (checklist) ክትትል
በሚካሔድበት የመብት ርዕሰ ጉዳይ ላይ መረጃ ሊሰበሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦችን በዝርዝር
የሚያመላክቱ መሆን አለባቸው።

አንድ ወጥ አሠራርን ለማረጋገጥ እንዲቻል በተደጋጋሚ የሰብአዊ መብቶች ክትትል


የሚካሔድባቸው መብቶች ወይም ተቋማትን በተመለከተ በኮሚሽኑ የሚገኙ የሥራ ክፍሎች
ከዚህ የሥራ መምሪያ ጋር የተጣጣሙ የማገናዘቢያ ዝርዝሮችን አዘጋጅተው ያፀድቃሉ።
የማገናዘቢያ ዝርዝርሮቹ (checklist) በየጊዜው ከሚኖሩ የሕግ ማዕቀፍ እና የመመዘኛዎች ላይ
ከሚደረጉ ማሻሻያዎች ፣ ከሚለዋወጡ ነባራዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በእያንዳንዱ የክትትል ሥራ
ወቅት ከሚኖራቸው ወሰን እንዲሁም አግባብነት አንጻር ክለሳ ሊደረግባቸው ይችላል።

4.1.4 የመጠይቆች (Questionnaires) ዝግጅት

በክትትል ሂደት በሰፊው ጥቅም ላይ ከሚውሉ የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች አንዱ መጠይቅ
ነው። መጠይቆች በሕግ ትንታኔ እና የማገናዘቢያ ዝርዝሮች መሠረት የሚዘጋጁ ሲሆን በቅድሚያ
አጠቃላይ መረጃዎችን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በማስቀደም በሂደት ወደ ዝርዝር ጥያቄዎች
እንዲገቡ ሆነው መቀረጽ ይኖርባቸዋል። ጥያቄዎች ክፍት (open ended) ወይም ሰፊ ምላሽን
ለማሳጠር የተወሰኑ መልሶችን ብቻ የሚጋብዙ (ውስን) ሆነው ወይም የሁለቱንም ዓይነት
ጥያቄዎች ያቀናጁ ሆነው ሊዘጋጁ ይችላሉ። መጠይቆች በተቻለ መጠን ግልጽ እና አጭር ሆነው
የሚከተሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች መያዝ ይኖርባቸዋል:-
• መግቢያ (የተቋሙን ስም፣ የተቋሙ ምንነት፣ የክትትሉን ዓላማ የሚያመላክት አጠቃላይ
መግቢያ)፤
• በመረጃ ሰጪዋ/ው ፍቃደኛነት የሚሞላ የተጠያቂው የግል መረጃ (ለምሳሌ ጾታ፣ ዕድሜ፣
አካል ጉዳት ሁኔታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ሥራ፣ ትምህርት፣ ወ.ዘ.ተ…)፤
• መረጃ ሰጪዋ/ው የሚሰጣቸውን መረጃዎች መጠቀምን ሆነ ለሦስተኛ ወገን ማጋራትን
በተመለከተ ነፃ ፍቃድ የሰጠ/ች ስለመሆኑ፤
• ጥያቄዎች፤
• መረጃ ሰጪዋ/ውን በተመለከተ ያለው የደኅንነት ሥጋት ዓይነት፤
• በመጠይቁ በመሳተፋቸው የሚቀርብ ምስጋና::

4.1.5 የመረጃ ምንጮችን መለየት

የክትትል ሥራን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ከመንቀሳቀሳቸው አስቀድሞ ተፈላጊ


መረጃዎችን ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎችን እና ተቋማትን መለየት ይኖርባቸዋል። የመረጃ
ሰጪዎችን የመለየት ሥራው በጉዳዩ ላይ ሊሰሙ የሚገባቸው ሁሉንም ወገኖችን፣ ለመብት

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
16

ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እንዲሁም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የመረጃ
ምንጮችን ባካተተ መልኩ ሊከናወን ይችላል። ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የመረጃ ምንጮች
የመብት ባለቤቶች፣ ተጎጂዎች፣ መብቱን የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸው
የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወ.ዘ.ተ... የሚሰጧቸው መረጃዎችን ፣ የሰነድ
ማስረጃዎችን፣ የመንግሥት ይፋዊ ሪፖርቶችን፣ የባለሙያዎች ትንታኔ፣ የሲቪል ማህበራት
(ሀገር በቀልም ሆነ የውጭ አገሮችን ጨምሮ) እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናቶችን እና
ሪፖርቶችን፣ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫዎችን፣ ከማህበራዊ
ትስስር ገጾች የተገኙ መረጃዎችን፣ የቀረቡ አቤቱታዎች(ቅሬታዎችን)፣ የፍርድ ቤት መዝገቦችን፣
የፖሊስ የምርመራ መዝገቦችን እና የመስክ ምልከታዎችን ያካትታሉ።

4.2 የክትትል ሥራ ሂደት፡ መረጃ ማሰባሰብ

የክትትል ባለሙያዎች አስቀድመው በተለዩ የመረጃ ምንጮች እና በመስክ በሚለዩ ተጨማሪ


ምንጮች መሠረት መረጃዎች ወደሚገኙባቸው ስፍራዎች በመንቀሳቀስ ተገቢውን መረጃ
ለመሰብሰብ ሁል ጊዜ ዝግጁ መሆን አለባቸው።

በሰብአዊ መብቶች ክትትል ሂደት በጥንቃቄ የተዘጋጀ የመረጃ መሰብሰቢያ ስርዓትን በመዘርጋት
እውነተኛ እና ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን መሰብሰብ ያስፈልጋል። የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ ከዚህ
በታች የተጠቀሱትን አንዱን፣ የተወሰኑትን ወይንም ሁሉንም በጥቅም ላይ በማዋል ሊከናወን
ይችላል።

4.2.1 ቃለ-መጠይቅ

ቃለ መጠይቆች ማድረግ በሰብአዊ መብቶች አከባበር የክትትል ሥራዎች ላይ ዋነኛ የመረጃ


ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ።

4.2.1.1 የቃለ መጠይቅ ዓይነቶች

በሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሂደት የሚከተሉት የቃለ መጠይቅ ዓይነቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ
ይችላሉ። ለሕፃናትን ቃለ-መጠይቅ በልዩ ሁኔታ የሚዘጋጅ ይሆናል።

ሀ. በከፊል በጥያቄዎች መዘርዝር ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ቀጥታ ቃለ መጠይቅ (Semi-


structured interview)

በከፊል በጥያቄዎች መዘርዝር ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ቀጥታ ቃለ መጠይቅ በጣም የተለመደው


እንዲሁም ውጤታማ ተብሎ የተለየው የመረጃ ማሰባሰብ ዘዴ ነው። በዚህ ሂደት የክትትል
ባለሙያው እንደ መጠይቁ ሁኔታ እና ዓላማ ቀድሞ በተዘጋጀ በጥያቄዎች መዘርዝር መሠረት
የሚከናወን ቃለ መጠይቅ ነው። የክትትል ባለሙያው (መረጃ ሰብሳቢው) የሚጠየቁትን ጥያቄዎች
እና ቅደም ተከተላቸውን የሚወስን ሲሆን በመጠይቁ የተመለከቱ ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ
እንዲያገኙ በቀረበው መዘርዝር መሠረት የሚከናወን ይሆናል። ነገር ግን የመዘርዝሩን ቅደም
ተከተል ሁል ጊዜ መከተል የማይቻል ወይም የማይመከር ይሆናል። በዚህም ሂደት የክትትል
ባለሙያው ዋነኛ ሚና የቀረቡት ጥያቄዎች እንዳይታለፉ ወይም ሳይመለሱ እንዳይቀሩ ማድረግ

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
17

ይሆናል። በዚህ ሂደት ሌሎች በቃለ መጠይቁ ወቅት የሚነሱ ጉዳዮችን መመዝገብ እንደ ሁኔታው
አስፈላጊ ይሆናል።

ይህ የቃለ- መጠይቅ ሂደት በሌሎች ዘዴዎች የተገኙ መረጃዎችን ለማመሳከር እንዲሁም ዝርዝር
(አሃዛዊ ያልሆኑ) መረጃዎችን ለማግኘት የሚጠቅም ነው።
ለ. ሙሉ በሙሉ በጥያቄዎች መዘርዝር ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ቀጥታ ቃለ- መጠይቅ
(structured interview)

ይህ የቃለ መጠይቅ ዓይነት መዘርዝሩን ሙሉ በሙሉ በዝርዝር በመከተል የሚከናወን ሲሆን


በዋነኝነትም የክትትል ባለሙያው ስለ ሁኔታው በቂ መረጃዎችን ካገናዘበ እና ጥያቄዎቹን
በተገቢው ዝርዝር ከቀመረ በኋላ የሚከናወን ነው። የሚዘጋጁት ጥያቄዎች የክትትሉ ሂደት
በሚታቀድበት ወቅት ለመመለስ የተነሳበትን ዓላማ የሚያሳኩ፤ እንዲሁም ሁሉም ጥያቄዎች
ቀድመው የተዘጋጁ እና በሚገባ የተቀመሩ መሆን ይኖርባቸዋል። በዚህ የቃለ መጠይቅ ዓይነት
ከማብራሪያ ውጪ በመዘርዝሩ የሌሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ አያስፈልግም።

ሐ. አስቀድሞ ያልተደራጀ ቃለ መጠይቅ (unstructured interview)

ይህ ዓይነት ቃለ መጠይቅ የክትትል ሥራውን የሚያከናውነው አካል ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ


የሌለው እና ክትትል በሚደረግበት ጉዳይ ላይ አጠቃላይ መረጃዎችን በማሰባሰብ ግንዛቤን
ለማስፋት እና ዝርዝር መረጃዎችን ለማስገኘት የሚያስችል መረጃ የሚሰጡ አካላትን ለመለየት
የሚረዳ ሂደት ነው።

በዚህ ሂደት የጥያቄዎች መዘርዝር ማዘጋጀት ሳያስፈልግ አጠቃላይ አቅጣጫን ሊያሳዩ የሚችሉ
መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችሉ ዘዴዎችን በመከተል ብቻ የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ሂደት
በዝርዝር የሚዘጋጅ የጥያቄዎች መዘርዝር አይኖርም። በሌላ በኩል ግን በጥልቀት ሊጠኑ
የሚገባቸውን ጉዳዮች ለመለየት ከፍተኛ ጥቅም የሚኖረው ሂደት በመሆኑ በጥንቃቄ መከናወን
አለበት። የመረጃ ምንጮቹም በጠቅላላው አመላካች የሆኑ መረጃዎችን ሊሰጡ የሚችሉ አካላትን
በማካተት የሚካሄድ እና ተጎጂዎችወይም ቀጥተኛ መረጃ ሰጪዎች ላይ ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆን
ስለ ጉዳዩ አጠቃላይ መረጃ እና ማስረጃ የሚኖራቸውን አካላት ሁሉ በማነጋገር መረጃ የሚገኝበት
ሂደት ነው።

መ. ጥልቅ የቡድን ውይይቶች (Focus group discussion)

ይህ ዘዴ የተመረጡ ሰዎችን (በተቻለ መጠን ከ 6 ያላነሱ እና ከ 10 ያልበለጡ ተሳታፊዎችን)


በሚያሳትፍ ቃለ-መጠይቅና ጥልቅ የቡድን ውይይት መረጃዎችን የመሰብሰብ ሂደት ነው። የቡድን
ውይይቱ ተሳታፊዎች እና ውይይት የሚደረግበት ርዕሰ ጉዳይ ሲመረጥ እንዲሁም ውይይቱ
ሲከናወን የአካባቢውን ባህል፣ ልምድ፣ ሕግ እና አሠራር ግምት ውስጥ እንዲገባ መደረግ
ይኖርበታል። በተጨማሪም በውይይቱ የሚሳተፉ መረጃ ሰጪዎች መካከል ለመብት ጥሰት
ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተገቢው መወከላቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የቡድን ውይይቱን የሚመራው የክትትል ባለሙያ ሲሆን በዋነኝነት በተዘጋጁ የጥያቄ መዘርዝሮች
መሠረት ጥያቄዎችን በማንሳት መረጃ የመሰብሰብ ሥራ ነው። የጥልቅ ቡድን ውይይት በሰብአዊ
መብቶች ክትትል በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ሊከናወን የሚችል ሲሆን፤ የቡድኑ አባላት እንዲሁም

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
18

የጥያቄዎቹ ይዘት እንደ ጉዳዩ እና የክትትሉ ሂደት ደረጃ የሚወሰኑ ይሆናል። አጠቃላይ
መረጃዎችን ለመሰብሰብ የታሰበ ከሆነ የቡድን ውይይቱ ላይ የሚሳተፉት ሰዎችም ከተለያዩ
መስኮች እንዲውጣጡ ለማድረግ የሚቻል ሲሆን ዝርዝር ጉዳዮች ለመጠየቅ እና ለክትትሉ
ቀጥተኛ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት የታሰበ ከሆነ ደግሞ የቡድን ውይይቱ
ተሳታፊዎች አስቀድሞ በተዘጋጁ ዝርዝር መስፈርቶች መሠረት የተመረጡ መሆን እና
ውይይቱም አስቀድመው በተዘጋጁ መጠይቆች መሠረት መከናወን ይኖርበታል። በተጨማሪም
የቡድን ውይይት በሌሎች የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች የተገኙ መረጃዎችን ለማረጋገጥ እንዲሁም
በተዘጋጀ ሪፖርት ላይ ተጨማሪ ግብዓት ለማግኘት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

የቡድን ውይይት በተቻለ መጠን ምቹ በሆነ እና ፀጥታ ባለው ስፍራ መከናወን ያለበት ሲሆን
ከሁለት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ይመከራል። የቡድን ውይይቱን የሚመራው
የክትትል ባለሙያ ሁሉም ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ እድል መስጠት አለበት። በዚህ
ሂደት አንዳንድ ሂደቱን የሚቆጣጠሩ (dominant) የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በሚነሱ ሃሳቦች
ምክንያት በተሳታፊዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ባለሙያው በሚገባ መምራት
(ማመቻቸት) እና ሁሉም አስተያየቶች እና አመለካከቶች በነጻነት እንዲንሸራሸሩ የሚያስችል
ሁኔታን መፍጠር ይጠበቅበታል። የቡድን ውይይት ዕድሜን ፣ጾታን፣ አካል ጉዳትን እና ሉሎች
የብዝኃነት እና አከታችነት መርሆችን በተከተለ መልኩ መመቻቸት እና መመራት አለበት።
ሕፃናትን በተመለከተም የሕፃናት ተሳትፎ መመሪያዎች ልብ ሊባሉና በአግባቡ ሊተገበሩ ይገባል።

የቡድን ውይይቱ በቅድሚያ የእርስ በእርስ ትውውቅ በማድረግ የሚጀመር ሲሆን ሂደቱን
የሚመራው ባለሙያ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ማንሳት ይኖርበታል፡-
• ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት እንዲሁም ለመሳተፍ ፈቃደኛ በመሆናቸው
ማመስገን፤
• የውይይቱን አጀንዳ እንዲሁም ዓላማ ማስተዋወቅ፤
• ውይይቱ የሚካሄድበትን ደንብ፣ ሕግ፣አሠራር ማስተዋወቅ (የሌሎችን ሃሳብ ማክበርን፤
በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ብቻ እንዲናገር፤ ስህተት ተብሎ የሚጣል ሃሳብ የሌለ መሆኑን
እንዲሁም ሁሉም ሃሳቦች የራሳቸው ጠቀሜታ እና ዋጋ እንዳላቸው ወ.ዘ.ተ...)

• ተሳታፊዎቹ እራሳቸውን እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ያላቸውን ዝምድና(ትስስር)


እንዲያስተዋውቁ እድል መስጠት ወ.ዘ.ተ።

በመጀመሪያ የሚነሱት ጥያቄዎች ስለአጠቃላይ ስለ ሁኔታው መረጃ የሚሰጡና ግንዛቤን


የሚፈጥሩ መሆን አለባቸው። በቀጣይ የሚነሱት ጥያቄዎች ዝርዝር እየሆኑ የሚሄዱ ሲሆን
በውይይቱ ሂደት የሚነሱ ሌሎች ጉዳዮችን (ጥያቄዎችንም) በማካተት መረጃዎችን መሰብሰብ
አስፈላጊ ነው። በዚህ ሂደት የጥያቄዎቹን ቅደም ተከተል ሁል ጊዜ መከተል የማይቻል ወይም
የማያስፈልግ ሲሆን እንደ ውይይቱ አቅጣጫ ጥያቄዎችን ማስኬድ አስፈላጊ ይሆናል። ሆኖም
በማመላከቻው ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ጥያቄዎች መነሳታቸውን ወይም ምላሽ ማግኘታቸውን
ማረጋገጥ ከባለሙያው ይጠበቃል።

የቡድን ውይይቶች ላይ በተቻለ መጠን ሁለት ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል። አንደኛው ባለሙያ
ጥያቄዎችን በማንሳት እና እድል በመስጠት ውይይቱን ሲመራ ሌላኛው ባለሙያ ማስታወሻ
የመያዝ እና ፍቃድ በተገኘ ጊዜ ድምጽ ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል የመቅዳት ኃላፊነት እንዲሁም

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
19

ውይይቱን የሚመራው ባለሙያ መነሳት ያለባቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ማንሳቱን የመከታተል ሚና


ይኖረዋል። የቡድን ውይይቶች ላይ የተሳታፊዎችን ነጻ ፈቃድ ማግኘት በተቻለ ጊዜ በመቅረጸ
ድምጽ ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል መቅዳት አስፈላጊ ነው።

4.2.1.2 የቃለ መጠይቅ ዋና ዋና ሂደቶች

ሀ) ቃለ መጠይቅ የሚደረግላቸው አካላትን መለየት

የክትትል ሥራው ከመጀመሩ አስቀድሞ የተለዩ ቃለመጠይቅ የሚደረግላቸው መረጃ ሰጪዎች


እንደተጠበቁ ሆነው የክትትል ባለሙያዎች በመስክ ላይ መረጃዎችን በሚያሰባስቡበት ወቅት
ተጨማሪ ቃለመጠይቅ ሊደረጉላቸው የሚገቡ የመረጃ ምንጮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይህንኑ ታሳቢ
ማድረግ ያስፈልጋል።

ለ) የቃለ መጠይቅ ቅድመ ዝግጅት

ቃለ መጠይቁን የሚመራው ባለሙያ ቃለመጠይቁ ከመካሄዱ በፊት የተዘጋጀውን የሁኔታ ትንተና


እንዲሁም መረጃ ስለሚሰጠው ወይም ቃለመጠይቅ ስለሚደረግለት ሰው አስፈላጊውን መረጃ
በማገናዘብ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል። በተጨማሪም የቃለመጠይቁን ዓይነት አስቀድሞ
መወሰን እና እንደአስፈላጊነቱ የጥያቄዎች መዝርዝር ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።

ሐ) ቃለ መጠይቁን የሚያከናውን ቡድን መለየት

አብዛኛውን ጊዜ ሁለት ባለሙያዎች መጠይቁን ቢያደርጉ ይመከራል። በዚህም አንደኛው ባለሙያ


ጥያቄዎቹን ሲያቀርብ እና ከምስክሩ ጋር ሲነጋገር፤ ሌላኛው ባለሙያ መልሶቹን መመዝገብ
እንዲሁም የተዘለሉ ጥያቄዎች ካሉ እነሱን በማንሳት ሂደቱን ማገዝ ያስችላል። ነገር ግን ሁል
ጊዜ ሁለት ባለሙያዎች ላይኖሩ የሚችልበት ሁኔታ ሲኖር በአንድ ባለሙያም መጠይቆችን
ማድረግ ይቻላል።

መ) ቋንቋ እና አስተርጓሚዎች

ክትትሉን የሚያከናውነው ቡድን በሚዋቀርበት ወቅት የአካባቢውን ቋንቋ የሚችሉ ባለሙያዎች


ቢኖሩበት ለሥራው በጎ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ይህንን ለማድረግ በማይቻልበት ጊዜ
አስተርጓሚዎችን ለመጠቀም አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይ መስማት
ለተሳናቸው መረጃ ሰጪዎች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው።

አስተርጓሚዎቹ በሚገባ የተመረጡ እና ለሥራው የሚያስፈልገውን ብቃትና ሥነምግባር


ማሟላታቸው በሚገባ ማጣራት ያስፈልጋል። ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች አካላት የተለየ
ወገንተኝነት የሌላቸው ለመረጃ ሰጪዎች የደኅንነት ሥጋት የማይፈጥሩ እንዲሁም የቋንቋውን
አካባቢያዊ ዘዬ (dialect) የሚረዱ እና በሚገባ መግባባት የሚችሉ መሆናቸውን ማጣራት
ያስፈልጋል።

ቃለመጠይቁን የሚያከናውነው ባለሙያ አስተርጓሚውን ስለ ትርጉም ሥራው አጠቃላይ


የሚከተሉትን መርሆች እና መመሪያዎች ማስረዳት ይጠበቅበታል፡-

• ጥብቅ የሆነ የሚስጥር ጠባቂነት ግዴታ ያለባቸው መሆኑን

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
20

• አስተርጓሚዎች ቃለመጠይቁ ሁል ጊዜም በክትትል ባለሙያው እና በመረጃ ሰጪው


መካከል መሆኑን እና የአስተርጓሚዎች ሚና የሚጠየቁ ጥያቄዎችን እና የሚሰጡ
ምላሾችን ማስተርጎም ብቻ መሆኑን፤
• አስተርጓሚዎች የሚጠየቁትን ጥያቄዎች በተቻለ መጠን ቃል በቃል በአጭሩ እና በግልጽ
ሊተረጉሙ እንደሚገባ እንዲሁም መረጃ ሰጪው ጥያቄውን ያልተረዳ ከሆነ
አስተርጓሚዎች ቃለ መጠይቁን ለሚያከናውነው ባለሙያ በማስረዳት ባለሙያው
ጥያቄውን በድጋሚ በሌላ አገላለጽ እንዲያቀርብ ማሳወቅ ያለባቸው መሆኑን ማሳወቅ
ያስፈልጋል።

በዚህ ሂደት መጠይቁን የሚያከናውነው ባለሙያ ጥያቄዎቹን ለትርጉም እንዲመቹ በግልጽ እና


አጭር አቀማመጥ ማቅረብ ይኖርበታል። እንዲሁም ጥያቄዎችን ሲጠይቅ አስተርጓሚውን ሳይሆን
መረጃ ሰጪውን መመልከት ይኖርበታል።

ሠ) ባህላዊ ሁኔታዎችን መገንዘብ

ቃለ መጠይቁን በሚያከናውነው ባለሙያ እና በመረጃ ሰጪው መካከል ጉልህ የሆነ የባህል ልዩነት
ካለ መግባባት ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያደርስ ይችላል። እነዚህ የባህል ልዩነቶች በሥርዓተ
ጾታ አረዳድ ላይ፤ የደረሰ ጉዳት እና የጥሰት አይነት እንዲሁም በሚነሱ ርዕሶች ላይ ጎልተው
ሊወጡ ይችላሉ። ሌሎች ጉዳዮች ለምሳሌ አለባበስ፣ የአካል ንክኪ፣ የአይን ግንኙነት (eye
contact) ወ.ዘ.ተ… የራሳቸው የሆነ አለመግባባት ሊፈጥሩ ይችላሉ። መጠይቁን የሚያከናውነው
ባለሙያ እነዚህ የባሕል ልዩነቶች በሚገባ መረዳት እና በታጋሽነት መጠይቁን ማከናወን እንዲሁም
ስለ ባሕሎቹ የበለጠ ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።

ከባህላዊ ሁኔታዎች በተጨማሪ የተጠያቂው በአንድ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም ተዛማጅ


ጉዳይ አስተሳሰብ ጠንካራ ድጋፍ ወይም ተቃውሞ ወይም አቋም ሊኖረው ይችላል። በቃለ
መጠይቁ ወቅትም በግልጽ ይህን ሃሳቡን፣ እምነቱን ወይም አቋሙን ሊያንጸባርቅ ይችላል። በዚህ
ወቅት ቃለ መጠይቁን የሚያደርገው ባለሙያ በተጠያቂው እምነት ወይም አስተያየት
የማይስማማ ቢሆንም እንኳ በዋናው ጉዳይ የሚሰጠውን መረጃ እና ማስረጃዎችን በሚገባ
መመዝገብ ይኖርበታል።

ረ) የቃለ መጠይቅ ማድረጊያው ስፍራ እና የደኅንነት ጉዳዮች

ክትትል የሚደረግበት የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በባህሪው ቃለመጠይቅ የሚደረግላቸውን ሰዎች


ለጥቃት ወይም ሌላ የደኅንነት ሥጋት ሊዳርግ የሚችል በሆነ ጊዜ ሁሉ ከመረጃ ሰጪዎች ጋር
የሚደረግ ቃለ መጠይቅ ለብቻ የሚከናወንበት ደህንነቱ የተጠበቀ ስፍራ እና ሌሎች ሰዎች በድብቅ
ሊሰሙ በማይችሉበት ሁኔታ መደረግ አለበት።

የደኅንነት ሥጋት ባለባቸው ሁኔታዎች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች የሚደረግ ቃለ


መጠይቅ ባልተፈለገ መልኩ ምስጢር የሚሰማበት ሁኔታን እንዲሁም በድብቅ የሚቀረጽበትን
(Surveillance) እድል የሚያሰፋ በመሆኑ አደገኛ ይሆናል። በመሆኑም ቃለ መጠይቁ
የሚከናወንበት ስፍራ በተቻለ መጠን ተሳታፊዎቹ ሲገቡ እና ሲወጡ እንዲሁም ሲነጋገሩ
የማያሳይ/የማያሰማ ስፍራ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ስፍራው ቃለ መጠይቁ ግልጽ
ንግግርን የሚጋብዝ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች(የንግግር መቆራረጥ)ረብሻ የየሌለበት

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
21

መሆን ይኖርበታል። ስፍራውን ለመምረጥ መረጃ ሰጪዎችን ወይም አካባቢውን የሚያውቁ


ገለልተኛ ወይም የታመኑ ሰዎችን መጠየቅ አስፈላጊ ነው።

ጉዳት ያለማድረስ መርህን ተግባራዊ ለማድረግ የክትትል ባለሙያዎች መረጃዎችን በሚሰበስቡበት


ወቅት ግንዛቤ ማስገባት የሚኖርባቸው ጉዳይ አንደኛው የመረጃ ሰጪዎች ደኅንነት ጥበቃ ነው።
በዚህ ረገድ የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል።

• በቃለ መጠይቁ ሂደት ላይ የሚሳተፉ መረጃ ሰጪዎችን አላስፈላጊ ትኩረት


እንዲደረግባቸው የሚያደርጉ ሁኔታዎችን መረዳት እና ማስወገድ። ለምሳሌ ከዋናው መረጃ
ሰጪ በተጨማሪ ሌሎች በርከት ያሉ ሰዎችን ቃለመጠይቅ በማድረግ በመረጃ ሰጪው
ላይ የሚኖር ትኩረትን ወይም የደኅንነት ሥጋትን መቀነስ ይቻላል።
• ቃለ መጠይቅ የሚያደርጉ ባለሙያዎች ሌሎች መረጃ ሰጪዎችን በሚያነጋግሩበት ወቅት
ቀድሞ መጠይቅ የተደረገለት መረጃ ሰጪ የገለጸውን መረጃ በቀጥታ ማንሳት አይገባም።
ይህም ሁኔታ የመጀመሪያውን መረጃ ሰጪ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ሲሆን ሌላኛውን
መረጃ ሰጪ ደግሞ የምስጢር አጠባበቅ ሁኔታውን በመገንዘብ መረጃዎችን ከመስጠት
እንዲቆጠብ ሊያደርገው ይችላል። በተጨማሪም የመረጃ ሰጪዎች ማንነት ደኅንነታቸውን
በሚገባ ለማረጋገጥ ካልተቻለ በስተቀር በፍጹም መግለጽ አይቻልም።
• ቃለ መጠይቁን የሚያቀርበው ባለሙያ መረጃ ሰጪው አደጋ ላይ መሆን አለመሆኑን
መጠየቅ እንዲሁም ይህን አደጋ ለማስወገድ መወሰድ ስለሚገባቸው ጉዳዮች መረጃ
ሰጪውን መጠየቅ ይኖርበታል።
• ቃለ መጠይቁ ከመካሄዱ በፊት እንዲሁም ከመጠይቁ በኋላ በሰፊው መረጃ ሰጪው ቃሉን
በመስጠቱ ሊደርስበት የሚችል አደጋ ካለ አስቀድሞ ለመከላከል ሊወሰዱ ስለሚገባቸው
እርምጃዎች መጠየቅ ይኖርበታል። የክትትል ባለሙያው የመረጃ ሰጪውን ደኅንነት
ለማስጠበቅ ያለው አቅም ውሱን መሆኑን መግለጽ ይኖርበታል።
• የመረጃ ሰጪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲቻል የተሰበሰቡ ሁሉም
መረጃዎች/ማስረጃዎች በሙሉ ሁል ጊዜ በሚገባ በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ለምሳሌ ማህደሮች ከሰዎች ስሞች ይልቅ በቁጥር ወይም በኮድ ቢሰነዱ እና የሚስጥር
ኮዱ ወይም ልዩ ምልክቶች ለብቻው ቢያዝ ተጨማሪ ጥንቃቄ ሊሆን ይችላል።
እንደአስፈላጊነቱ የመረጃ ሰጪውን ማንነት የሚገልጹ ጉዳዮችን (ስም፣ ስልክ፣ አድራሻ
እና ሥራ የመሳሰሉ መረጃዎች) በምስክርነት ከተሰጠው ቃል ለይቶ በሌላ ሰነድ
በማደራጀት የተሻለ ጥበቃ ማድረግ ይቻላል። ተጨማሪ መረጃዎች ሲገኙም በምስክሩ ስም
ፋንታ በፋይል ቁጥሩ ማመላከት ያስፈልጋል። በተጨማሪም የሁሉም መረጃዎች ኮፒ
በሚገባ ጥበቃ በሚደረግበት ሁኔታ መሰነድ ይኖርበታል።
• የክትትል ሥራ በሚከናወንበት ወቅት ለመረጃ ሰጪዎች ክፍያ መፈጸም በፍጹም ተገቢ
አይደለም። ነገር ግን እንደነገሩ ሁኔታ እና በተጨባጭ አሳማኝ ምክንያት የመረጃ ሰጪው
የረዥም ጉዞ የትራንስፖርት እና ተመሳሳይ ወጪዎችን መሸፈን አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

ሰ) ቃለ መጠይቁን መቅዳት/መቅረጽ/ፎቶ ማንሳት

ሰ. 1 በመቅረጸ ድምጽ መቅዳት

ቃለ መጠይቆችን በመቅረጸ ድምጽ መቅዳት በተጠያቂዎቹ ደኅንነት ላይ አደጋ ሊያስከስት የሚችል


በመሆኑ ሁል ጊዜ መጠቀም ላያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን የደኅንነት ሁኔታው ምቹ ከሆነ፤ ቃለ

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
22

መጠይቁን በመቅረጸ-ድምጽ መቅዳት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። መቅረጸ-ድምጽ መጠቀም


የሚቻለው የመረጃ ሰጪዋ/ው ፈቃድ በግልጽ ከተገኘ በኋላ ብቻ ሲሆን ጥቅም ላይ ለማዋልም
መጀመሪያውኑ የመረጃ ሰጪዋ/ውን ስምምነት እና ፈቃድ ማግኘት አስፈላጊ ነው። በመቅረፀ-
ድምጽ መቅዳት መረጃ ሰብሳቢው አንድ ባለሙያ ብቻ በሆነበት ሁኔታ በተለየ መልኩ ጠቀሜታ
ይኖረዋል። በተጨማሪም ማስተርጎም የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሲኖር በኋላ በድጋሚ በመመለስ
እንደገና ለማዳመጥ እድል የሚሰጥ ስለሆነ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ቃለ መጠይቅ አድራጊው የቃለ መጠይቁን ዓላማ እንዲሁም ምስጢር የሚጠበቅ መሆኑን


በመግለጥ የተጠያቂዋ/ውን ሙሉ ፈቃድ ሳያገኝ መቅረጸ-ድምጽ መሳሪያው መጠቀም መጀመር
የለበትም። ስምምነት ተገኝቶ መቅረጸ-ድምጹ እንደተጀመረ ግን በቅድሚያ ስምምነት ላይ
ስለመደረሱ በድጋሚ በመግለጽ እና በማረጋገጥ እንዲቀረጽ ተደርጎ ቃለ መጠይቁ ይቀጥላል።
ተጠያቂው መቅረጸ-ድምጹ ጥቅም ላይ የመዋሉን አስፈላጊነት እንዲረዳ ማድረግ የሚያስፈልግ
ሲሆን በዋነኝነትም የተናገራቸው ጉዳዮች እንዳይረሱ በሚገባ ለመመዝገብ መሆኑን በማስረዳት
ፍቃዱን እንዲሰጥ ሊጠየቅ ይገባል። በምንም መልኩ ቢሆን መቅረጸ-ድምጽን በድብቅ ጥቅም ላይ
ማዋል አይገባም።
ለመረጃ ሰጪዋ/ው ደኅንነት ጥበቃ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በድምጽ የተቀዳው ወይም የተቀረጸው
ሰነድ የመረጃ ሰጪውን ስም ወይም ማንነት መያዝ የለበትም። የመረጃ ሰጪው ማንነት በሌላ
ቦታ እና ሰነድ ተመዝግቦ መያዝ የሚኖርበት ሲሆን ከተቀረጸው ድምጽ እና ምስክሩ መካከል
ቀጥተኛ ትስስር እንዳይኖር አስፈላጊው ጥረት መደረግ አለበት። በተጨማሪም የተቀረጸው ድምጽ
(ቴፕ፣ ካሴት፣ ሲዲ ወይም ፍላሽ) በቀላሉ በብርበራ ተገኝቶ በሌሎች አካላት እጅ እንዳይገባ
ወይም ምስክሩን እንዳያጋልጥ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ መደረግ አለበት።

ሰ. 2 የፎቶግራፍ መረጃዎች

የፎቶግራፍ መረጃዎች መውሰድ ከድምጽ በበለጠ አደጋ ወይም ችግር ሊፈጥር የሚችል ነው።
መረጃ ሰጪዎችን ፎቶግራፍ ከማንሳት በፊት ሊደርስባቸው የሚችልን ጥቃት በሚገባ ግንዛቤ
ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። አንዳንድ መረጃ ሰጪዎች (ተጎጂዎች) የደረሰባቸውን ጉዳት
(ቁስል፣ ጠባሳ ወ.ዘ.ተ…) ለማሳየት ሲፈልጉ፤ ማንነትን በማያመላክት መልኩ (ፊትን እና ሌሎች
ልዩ መለያዎችን ሳይታይ) ፎቶግራፉን ማንሳት ያስፈልጋል።

ፎቶግራፍ ለመነሳት የመረጃ ሰጪዋ/ው ፈቃድ የተገኘ እንደሆነ ምስሉን በህትመት (ይፋዊ
ሪፖርቶች) ላይ ለመጠቀም ወይም ለማሰራጨት ፈቃደኛ መሆኑንም በተጨማሪነት መጠየቅ እና
ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ሰ.3 ተንቀሳቃሽ ምስሎች (የቪዲዮ ምስሎች)

የደኅንነት ሥጋት ባለባቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራዎች የሚከናወኑ ቃለመጠይቆችን


በቪዲዮ ምስሎች መቅረጽ የበለጠ አደገኛ ነው። ይህም መረጃ ለመስጠት የሚተባበሩ ሰዎችን
በብዛት የማግኘት ዕድልን የሚያጣብብ ከመሆኑም በላይ የተቀረጸው መረጃ ተገቢ ባልሆነ አካል
ቢወሰድ መረጃ ሰጪውን ለከፍተኛ አደጋ ሊያጋልጥ የሚችል ነው።

ከዚህ በላይ ስለ ድምጽ መቅረጽ እና ፎቶግራፍ ማንሳት የተገለጹት መርሆች እንደየአግባብነታቸው


እንደተጠበቁ ሆነው የክትትል ባለሙያዎች ተንቀሳቃሽ ምስል ለመቅረጽ በሕግ ወይም በአሠራር

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
23

ክልከላ በሌለባቸው አካባቢዎች የሚያደርጉትን የመስክ ምልከታ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ


ወይም አጠቃላይ ሁኔታዎችን የሚመለከቱ ኩነቶችን በተንቀሳቃሽ ምስል ሊቀርጹ ይችላሉ። እንደ
ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ይፋዊ ያልሆኑ የተጠርጣሪ ማቆያ ሥፍራዎች ወ.ዘ.ተ...
ያሉ ሥፍራዎችን ፎቶግራፍም ሆነ በተንቀሳቃሽ ምስሎች ከመቅረጽ በፊት የሚመለከታቸው
የመንግሥት አካላት ፍቃድ መጠየቅ ያስፈልጋል።

ሸ) ቃለ መጠይቁን ማከናወን

ከቡድን ውይይት ውጪ የሚከናወኑ ቃለመጠይቆች ሁሉ በተቻለ መጠን በአንድ ጊዜ ከአንድ


መረጃ ሰጪ ጋር ብቻ መከናወን ይኖርባቸዋል። የክትትል ባለሙያው ቃለመጠይቁን በሚጀምርበት
ወቅት አጠቃላይ ሁኔታን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በማስቀደም በሂደት ወደ ዝርዝር ጥያቄዎች
መሄድ ይኖርበታል። ቃለ መጠይቅ ሰጪው ክትትል ከሚደረግበት ጉዳይ ጋር ያለውን ቅርበት
እና የሚሰጣቸውን መረጃዎች እንዴት ሊያውቃቸው እንደቻለ በቃለ መጠይቁ መግቢያ ላይ ግልጽ
እንዲያደርግ መጠየቅ ያስፈልጋል።

መረጃ ሰጪው በድካም፣ በስሜታዊነት ወይም በሌላ ምክንያት መረጃዎችን ለመስጠት በተቸገረ
ጊዜ ሁሉ እረፍት እንዲያደርግ እና መንፈሱን ለማረጋገት እንዲችል የክትትል ባለሙያው ማገዝ
ይኖርበታል። ይህንንም ከጥቃት ተጎጂነት፣ ከዕድሜ፣ ከጾታ፣ አካል ጉዳት እና ሌሎች ሁኔታዎች
በማገናዘብ ልዩ ትኩረት መስጠት ያሻል።

መረጃ ሰጪው በቃለ መጠይቁ ሂደት ሃሳቡ ሳይቆራረጥ ለመናገር የሚችልበትን እድል መስጠት
እንዲሁም ከተገቢው በላይ በሌሎች ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ማቋረጥ አያስፈልግም። መረጃ
ሰጪው ግልጽ ያልሆኑ፣ የተጋነኑ ወይም እውነት ያልሆኑ፡ የማይመስሉ መረጃዎች ቢሰጥም
እንኳ የክትትል ባለሙያው በፊት ገጹ፣ በድርጊቱም ሆነ በቃላቱ መረጃ ሰጪውን መጠራጠሩን
ወይም ያለማመኑን ማመላከት የለበትም። እንዲህ ያሉ መረጃዎች ሲሰጡ መረጃ ሰጪው ሃሳቡን
እንዲጨርስ እድል ከተሰጠ በኋላ በማጣሪያ ጥያቄ መልክ በድጋሚ እንዲብራራ መጠየቅ ተገቢ
ነው።

በተጨማሪም አስተርጓሚዎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ ከስር ከስር ለመተርጎም እንዲችሉ


መረጃ ሰጪዎች ሃሳባቸውን በአጭር በአጭሩ ጋብ በማድረግ እና ለትርጉም እድል በመስጠት
እንዲተባበሩ መጠየቅ ያስፈልጋል።

ቀ) ቃለ መጠይቁን ማጠናቀቅ እና አድራሻ መስጠት

ቃለ መጠይቁን የሚያከናውነው ባለሙያ መረጃ ሰጪው ጥያቄዎች ካሉት እንዲጠይቅ


ሊያበረታታው ይገባል። መረጃ ሰጪው የሰጠው መረጃ ምስጢር የሚጠበቅ መሆኑን በድጋሚ
በሚገባ ማስረዳት ይኖርበታል። በተጨማሪም ባለሙያው ከቃለመጠይቁ ቀጥሎ በኮሚሽኑ በኩል
የሚከናወኑ ተግባራትን (ለምሳሌ ይፋዊ ሪፖርት ሊወጣ የሚችል መሆኑን፤ ግኝቶችን መሠረት
ያደረጉ ምክረ ሃሳቦች እንደሚቀርቡ እና ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ ውትወታ የሚደረግ
ስለመሆኑ ወዘተ) ማሳወቅ ያለበት ሲሆን በምንም ዓይነት መልኩ ሊያደርግ የማይችለውን ነገር
ቃል መግባት ግን የለበትም።

በተጨማሪም ባለሙያው ለወደፊቱ ስለሚኖር ደኅንነቱን የጠበቀ የግንኙነት መስመር ስልክ፣


ኢሜይል ወይም ሌላ ዘዴዎች መኖራቸውን ለመረጃ ሰጪው መግለጽ ይኖርበታል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
24

በ) የቃለ መጠይቅ ማስታወሻ ሪፖርት ማዘጋጀት

ቃለ መጠይቁ እንደተጠናቀቀ ቃለ መጠይቁን ያከናወኑት ባለሙያዎች በቃለ መጠይቁ ወቅት


የመዘገቧቸውን ማስታወሻዎች መሠረት በማድረግ ወዲያውኑ የተጠቃለለ ማስታወሻ ሪፖርት
ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ይህ ማስታወሻ ቀድሞ በተዘጋጀ ዝርዝር የማስታወሻ ቅርጽን መሠረት
በማድረግ ሊዘጋጅ ይችላል። ይህ ሂደት በቃለ መጠይቁ ወቅት የተገኙትን መረጃዎች በሚገባ
የሚያመላከት እና ምን እንደተከሰተ፣ ኹነቱ ለምን እና እንዴት እንደተከሰተ ማስረዳት የሚችል
መሆን ይኖርበታል።

4.2.1.3 ልዩ ጥበቃ/ትኩረት ሊደረግባቸው ከሚገባ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር


የሚደረግ ቃለ መጠይቅ

የክትትል ባለሙያዎች የተለያዩ መረጃ ሰጪዎች ለምሳሌ በእድሜ ወይም የማኅበረ ሥነ ልቦና
ጉዳት (trauma) ሰለባ በመሆናቸው ምክንያት የየራሳቸው ልዩ ባሕርይ ስለሚኖራቸው እነዚህን
ሰዎች ቃለ መጠይቅ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። በመሆኑም
ልዩ ትኩረት ሊደረግላቸው የሚገባ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቃለ-መጠይቅ በሚደረጉበት ወቅት
እንደየሁኔታው ለየት ያለ አቀራረብ እና ዘዴ መከተል አስፈላጊ ይሆናል። ለዚህም የበለጠ ዝግጅት
እና ትዕግስት አስፈላጊ ነው።

ሀ) የማሰቃየት እና የጭካኔ ተግባር ተጎጂዎች

የማሰቃየት እና የጭካኔ ተግባር ተጎጂዎችን መጠይቅ ማድረግ እጅግ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ
ሥራ ነው። መጠይቁን የሚያከናውን ባለሙያ የስቃይ ተጎጂዎች የሚኖርባቸውን የማኅበረ ሥነ
ልቦና ጉዳት (trauma) በሚገባ በመረዳት ቃለ መጠይቁን በሚያደርጉበት ወቅት በድጋሚ ለሌላ
የማኅበረ ሥነ ልቦና ጉዳት (secondary trauma) የማያጋልጥ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል።
የክትትል ባለሙያዎች ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ቀድመው መዘጋጀት እንዲሁም ተጎጂዎቹም
ሆኑ መረጃ ሰጪዎች በሚናገሩበት ወቅት ማበረታታት፤ እረፍት ከፈለጉ ቃለ መጠይቁን
ማቆምን፤ ስሜታዊ ሲሆኑ ደጋፊ እና ተቆርቋሪ መሆን ወ.ዘ.ተ… ይኖርባቸዋል። ነገር ግን
የክትትል ባለሙያዎች የሰለጠኑ የስነልቦና ባለሙያዎች ስላልሆኑ፤ ሥራቸው ሕክምና ወይም
የሥነ ልቦና ድጋፍ ለመስጠት እንዳልሆነ መገንዘብ እና እንዲሁም በአቅራቢያ የሚገኙ የሥነ
ልቦና ሕክምና አገልግሎች ሰጪ ተቋማት እና ባለሙያዎችን በማጣራት መረጃውን ለተጎጂዎች
ማድረስ አለባቸው። የሚቻል ከሆነ የክትትል ቡድኑ አባል አግባብ ያለው የሕክምና እና የሥነ
ልቦና ባለሙያዎች ማካትተ አስፈላጊ ነው። የሕክምና ባለሙያው የምስክሩን የበፊት የሕክምና
ሪከርዶችን በመመልከት እና አሁን ካለው ጋር በማመሳከር የሙያ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል።

የፎቶግራፍ መረጃዎችን ለመሰብሰብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፤ የምስክሩን ሙሉ ፈቃድ በማግኘት፤


የተመረጠ ተጎጂውን የማያሳፍር (የማያዋርድ) መሆኑን በማረጋገጥ እና እንደአስፈላጊነቱ የተወሰነ
የሰውነት ክፍልን ለይቶ በማንሳት ማንነታቸውን ላለማሳወቅ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ
ይኖርበታል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
25

ለ) የጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎች

ሴቶችም ሆኑ ወንዶች፣ ሕፃናትም ሆኑ ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች ስለደረሰባቸው ጾታዊ እና


ወሲባዊ ጥቃት በሕብረተሰብ ሊደርስባቸው ከሚችል መገለል እና መድልዎ ምክንያት ስለጥቃቱ
መናገር ላይፈልጉ ይችላሉ። ከእነዚህ ተጎጂዎች ጋር የቀረበ መተማመን ለመፍጠር ተጨማሪ
ጥረቶች ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም መረጃዎቹ በምስጢር የሚያዙ መሆኑን እና በእነርሱ
ፈቃድ እና ፍላጎት መሰረት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆኑ እንዲረዱ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

መረጃ በሚሰበሰብበት ወቅት እውነታውን ለመረዳት አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችን ሁሉ (ማን፣


መቼ፣ የት፣ እንዴት፣ ወ.ዘ.ተ…) ማንሳት አስፈላጊ ሲሆን፤ እውነታው በማስረጃ ከተረጋገጠ
በኋላ ግን ስለጥቃቱ ደጋግሞ ማንሳት አስፈላጊ አይሆንም። በሴቶች ላይ የተፈጸመ ጥቃት ሲሆን
በተቻለ መጠን የክትትል ሥራውን ሴት ባለሙያዎች እንዲሳተፉበት ጥረት መደረግ ይኖርበታል።
በተመሳሳይ፤አተርጓሚዎችን መጠቀም አስፈላጊ ሲሆንም በተቻለ መጠን ሴት አስተርጓሚዎችን
መጠቀም ይመከራል።

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው የጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃት
ተጎጂዎችን ቃለመጠይቅ ማድረግ በራሱ ለተደራራቢ የሥነ ልቦና ጉዳት የሚዳርግ በመሆኑ
ቃለመጠይቁ ከመደረጉ አስቀድሞ በተቻለ መጠን የማህበረ ሥነ ልቦና (psycho-social) እና
የሕክምና (medical) አገልግሎቶችን ማመቻቸት ተገቢ ነው።

ሐ) ስደተኞች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች

እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ችግር እና እንግልት ውስጥ ያለፉ እንደዚሁም የኢኮኖሚ
ችግሮች ያሉባቸው በመሆኑ የክትትል ባለሙያዎች ይህንኑ መረዳት እና ተቆርቋሪነትን ማሳየት
እንዲሁም ጥያቄዎችን ከስደተኝነት ወይም ሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጋር ግንኙነት ካላቸው ሕጎች
እና ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ሰነዶች ጋር በተናበበ መልኩ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል።

መ) ሕፃናት

ሕፃናት ነገሮችን የሚረዱበት እና የሚመለከቱበት እይታ አካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች የተለየ
ሊሆን ይችላል። ቃለ-መጠይቁን የሚያደርገው ባለሙያ ይህንን በሚገባ በመረዳት መጠይቁ
የሕፃናትን እድሜ፣ ብስለት እና ግንዛቤ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ማከናወን ይኖርበታል።
ቀላል ቃላትን በመጠቀም ከሕፃናቱ ጋር ቅርርብ እና መተማመንን ለማስፈን ረዘም ያለ ጊዜ
ሊወስድ እንደሚችል በመገንዘብ በትዕግስት መሥራት ያስፈልጋል። በተጨማሪም መረጃዎችን
ለማግኘትም ሆነ የተሰበሰበውን መረጃ ለማመሳከር ይረዳ ዘንድ የሕፃናቱን ወላጆች (አሳዳጊዎች)
ወይም የቤተሰብ አባላት፣ መምህራን፣ ወይም ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችን እንደሁኔታው
ማነጋገር አስፈላጊ ይሆናል።

ሠ) አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን

በሁሉም የክትትል ሥራዎች የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ሁኔታ ሊካተት ይገባል። አካል
ጉዳተኞች እና አረጋውያን መረጃ ለመስጠት ተነሳሽነት ላይኖራቸው ወይም ላያስታውሱ ወይም
በአካባቢው ማኅበረሰብ የተገለሉ ሊሆኑ ይችላል። ስለሆነም እነዚህን ሰዎች አግኝቶ ለማነጋገር
የተለየ ጥረት ማድረግ በተጨማሪም በማኅበሮቻቸው በኩል ማሳተፍ አስፈላጊ ነው። ጥያቄዎቹም

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
26

የእነሱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ከእድሜያቸው መግፋት


ምክንያት የምናቀርብላቸውን ጥያቄ በአግባቡ ለመረዳት የሚያዳግታቸው ወይም ትክክለኛውን
መልስ ከመስጠታቸው በፊት በርካታ የተለያዩ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ጉዳዮች
ሊነግሩን የሚችሉ አረጋውያንን በትእግስት እና ጥሞና ማድመጥ አስፈላጊ ነው። መስማት
የተሳናቸውን ሰዎች ለማነጋገር አስቀድሞ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ማዘጋጀት እንዲሁም
የአዕምሮ እድገት ውስንነት ካለባቸው ሰዎች መረጃን ለማግኘት ስእል እና ምልክቶችን ጨምሮ
እንደነገሩ ሁኔታ የተለያዩ ስልቶችን መጠቀም ያስፈልጋል።

4.2.1.4 ኃላፊነት ያለባቸውን የመንግሥት አካላት ቃለ መጠይቅ ማድረግ

ከተጎጂዎች፣ ምስክሮች እና ሌሎች አካላት መረጃዎች ከተሰባሰቡ በኋላ ግዴታ ካለባቸው አካላት
በተገኙት መረጃዎች ላይ ያላቸውን ምላሽ መጠየቅ እና ማካተት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም
ክትትል በሚደረግበት ጉዳይ ዙሪያ ተገቢነት ያላቸው የበላይ ኃላፊዎችን ቃለመጠይቅ ማድረግ
ይገባል። ለምሳሌ ክትትሉ የሚደረገው በፖሊስ ጣቢያ ወይም ማረሚያ ቤት ከሆነ የፖሊስ
ጣቢያውን አዛዥ ወይም የማረሚያ ቤቱን የበላይ ኃላፊ ወይም እነዚህ ሊገኙ ባልቻሉ ጊዜ
ተወካዮቻቸውን በማነጋገር ምላሾቻቸውን በአግባቡ መመዝገብ ያስፈልጋል።

ከመንግሥት አካላት ጋር የሚደረጉ ቃለ መጠይቆች የሰብአዊ መብቶች ክትትሎችን የስህተት


ፍለጋ እንዳያስመስሉት ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም ቃለመጠይቆች ሙያዊ እና መከባበር
የተሞላባቸው እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። የክትትል ባለሙያው ያሰባሰባቸውን መረጃዎች
በሚገባ በመተንተን እና በመመዘን በቂ ዝግጅት አድርጎ መገኘት፤ ጥያቄዎቹንም በሚያነሳበት
ጊዜም በጨዋነት እና ለመረዳት ዝግጁ በሆነ አስተሳሰብ (Open-minded) መሆን ይኖርበታል።
የጥያቄዎች ዝርዝር እንደ ሁኔታው እና የመንግሥት ሰራተኛው ወይም ኃላፊው የሚሰጠው
መልስ ላይ ተንተርሶ ተከታይ ጥያቄዎችን ማቅረብ ሊያስፈልግ የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ
ሆኖ ጥያቄዎች የሚጠየቁበትን ቅደም ተከተል ጨምሮ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል።

ቃለ መጠይቅ የሚደረግለት ሰው በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ የተሳተፈ ሊሆንም የሚችል


መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚያስፈልግ ሲሆን ከነዚህ ሰዎችም ቢሆን የሚሰጠውን
መረጃ በሚገባ መመዝገብ እና መሰነድ ያስፈልጋል።

4.2.2 የመስክ ጉብኝት ማድረግ (field visits)

የዚህ መረጃ የማሰባሰቢያ ዘዴ በተለይም ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች፣ ማረሚያ ቤቶች፣


የፖሊስ ተጠርጣሪዎች ማቆያ/ማረፊያ ቤቶች፣ ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናት ማሳደጊያዎች፣
የስደተኞች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ካምፖች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሰፋፊ
የሆኑ የእርሻ ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎች ወ.ዘ.ተ… ላይ በሚደረግ የክትትል ሂደት ላይ ጠቃሚ እና
አስፈላጊ ይሆናል።

በዚህ የመረጃ የማሰባሰብ ዘዴ የሚከወን የክትትል ሥራ በቅድሚያ በሚዘጋጅ የምልከታ መረጃ


መሰብሰቢያ ቼክ ሊስት መመራት ይኖርበታል። ይህም የሚሰበሰበው መረጃ ተመሳሳይ ቅርጽ
እንዲኖረው ለትንታኔም አመቺ እንዲሆን ያደርጋል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
27

4.2.3 ኩነቶችን መታዘብ (observing events)

ይህ የክትትል ዘዴ በተለይ የሀገር ውስጥ የምርጫ ሂደቶችን፣ ሰላማዊ ሰልፎችን ፣ የችሎት


(የፍርድ) ሂደቶችን ወ.ዘ.ተ… የመከታተያ እና መረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ ሆኖ ጥቅም ላይ ሊውል
ይችላል። በዚህም የራሱ ዝርዝር የመከታተያ ሰነድ ተዘጋጅቶለት በኩነቶች ላይ ያተኮረ የክትትል
ሥራ መረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ ነው።

4.2.4 የቁስ ወይም የፎረንሲክ ማስረጃ

ማንኛውም በወንጀል የሚያስጠይቅ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸሙን የሚያሳዩ የቁስ ወይም
የፎረንሲክ ማስረጃዎችን በክትትል ሂደት መነካካትም ሆነ ከስፍራቸው ማንሳት ተገቢ አይደለም።
ነገር ግን በሥራቸው ምክንያት የክትትል ባለሙያዎች እነዚህን መረጃዎች እና ማስረጃዎች ያገኙ
እንደሆነ ወዲያውኑ ለሚመለከተው የወንጀል ምርመራ አካል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ፖሊስ
መረጃዎችን በቅርበት ተገኝቶ መሰብሰብ ባለመቻሉ እና ሌሎች አማራጮች በሌሉ ጊዜ ጉዳዩ
የሚመለከተው የመንግሥት የወንጀል ምርመራ አካላት በሚሰጡት ፍቃድ እና ሙያዊ ምክር
መሠረት የክትትል ባለሙያው ማስረጃዎቹ በሚገባ እንዲሰበሰቡ (እንዲቀመጡ) በተገቢው ምልክት
እንዲደረግባቸው እና እንዲታሸጉ በማድረግ ከመጥፋት እና በንኪኪ ከመበላሸት እንዲጠበቁ
ማድረግ ይቻላል። ማስረጃዎችን በጥንቃቄ ፎቶግራፍ ማንሳት ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል መቅረጽ
ይችላሉ። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ የቁሶችን መጠን በትክክል ለመለየት እንዲቻል ለማነጻጸሪያነት
የሚያገልግሉ በተለምዶ የሚገኙ ዕቃዎችን (ለምሳሌ ማስመሪያ፣ እስክሪብቶ፣ ማስታወሻ ደብተር
ወ.ዘ.ተ...) የወንጀል ሥፍራውን በማይረብሽ አግባብ ከቁስ ማስረጃዎች አጠገብ በማስቀመጥ
ፎቶግራፍ ማንሳት ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል ለመቅረጽ ይቻላል።

4.2.5 የሰነድ ማስረጃዎች

በቃል የተሰጠን ማስረጃ በሌሎች ሰነድ ማስረጃዎች ማጠናከር ሁል ጊዜ ጠቃሚ ይሆናል።


የክትትል ባለሙያዎች በቀጥታ ከመረጃ ሰጪ ተቋማት ለኮሚሽኑ ከሚጻፉ ደብዳቤዎች እና አባሪ
ሰነዶች በስተቀር የሰነድ ማስረጃዎችን ዋና ቅጂ (ኦሪጅናል) መሰብሰብ የለባቸውም። ሆኖም
የሚፈለጉት የሰነድ ማስረጃዎች ከመንግሥት ወይም ከግል ተቋማት የተገኙ ከሆኑ ፎቶ ኮፒው
ላይ ተዓማኒነታቸውን ለማሳደግ እንዲቻል የመረጃ ምንጭ የሆነው ተቋም ማህተም እንዲያርፍበት
ማድረግ ይመከራል።

4.2.6 ከነጻ ምንጮች የተገኙ ማስረጃዎች (Open-Source Information)

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከቴክኖሎጂ እድገት በተለይም የስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮች
መስፋፋት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ለመከወን ከነጻ ምንጮች (Open
Source) የሚገኙ መረጃዎች የመጠቀም አስፈላጊነት እያደገ መጥቷል።

ከነጻ ምንጮች የሚገኙ መረጃዎች ስንል በማንኛውም ሰው በነጻ ወይም በግዥ ሊገኙ የሚችሉ
እና መረጃዎችን ለማግኘት ልዩ ሕጋዊ መብት ወይም ፍቃድን የማይጠይቁ በአብዛኛው ለብዙ
ሰዎች ተደራሽ ሆነው በተለይ በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ጭምር ሊገኙ የሚችሉ መረጃዎችን ማለት
ነው። ከነዚህ ምንጮች ዋንኛው በመረጃ መረብ የሚገኙ መረጃዎች ሲሆኑ በድረ ገጾች፣ ማኅበራዊ
ሚዲያዎች (ፌስ ቡክ፣ ትዊተር፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም ወ.ዘ.ተ...) የሚገኙ የጽሁፍ፣
የፎቶግራፍ፣ የቪዲዮ እና የድምጽ መረጃዎችን ያካትታሉ። በተጨማሪም የሰብአዊ መብቶች

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
28

ክትትል ባለሙያዎች ክትትል በሚያደርጉባቸው የመብት ርዕሶች እና አካባቢዎች ላይ ተጨባጭ


መረጃ ያላቸውን ሰዎች እና ተቋማት ድረ-ገጾች እና ማኅበራዊ ድረ-ገጾች በየጊዜው መከታተል
ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ለመለየት እንዲሁም ክትትል በሚከናወንበት ወቅት ሊታዩ
የሚገባቸውን የመብት ጥሰት ጉዳዮች እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎችን
በተመለከተ ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘት ያስችላል።

በሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ከነጻ ምንጮች የሚገኙ መረጃዎች እና ማስረጃዎች በቅድመ


ክትትል የሁኔታ ትንተና ዝግጅት ሂደት እንዲሁም በመረጃ ማሰባሰብ ሂደት ሊገኙ ይችላሉ።
በተለይ ከፍ ያሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የሚያሳዩ የነጻ ምንጭ መረጃዎች በአግባቡ ከየት፣
መቼ እና በምን ሁኔታ እንደተገኙ እንዲሁም ከተሰበሰቡ በኋላ ያለፉበትን የማስረጃ ሰነድ
ቅብብሎሽ (chain of custody) በመመዝገብ እና ከባቢያዊ መረጃዎችን በማከል ቴክኒካዊ የሆነ
ምርምራ እንዲደረግባቸው ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች ወዲያውኑ ማሳወቅ ያስፈልጋል። በተለይ
ከመረጃ መረብ ወይም ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚገኙ ነጻ ምንጭ መረጃዎች እና ማስረጃዎች
ለስህተት/manipulation የተጋለጡ በመሆናቸው የምንጮችን ተዓማኒነት እና የመረጃዎችን
ትክክለኛነት በጥንቃቄ መመዘን፤ በተቻለ ጊዜ ሁሉ በዚህ መልኩ የሚገኙ መረጃዎችን እና
ማስረጃዎችን በሌሎች ዓይነት መረጃዎች ማጣራት እና ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
29

ክፍል አምስት
የድህረ መስክ/ክትትል ሂደትና ሪፖርት ዝግጅት
5.1 መረጃን መመርመር እና መተንተን

በሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ ትክክለኛ እና ተዓማኒ የሆነ መረጃ መሰብሰብ በጣም አስፈላጊ
ነው። የተሰበሰቡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የሚከናወኑ ትንታኔዎች እና ድምዳሜዎች
ለምክረ ሃሳቦች መነሻ ሆነው ያገለግላሉ፤ ከመንግሥት አካላትም ሆነ ከሌሎች ግዴታ ያለባቸው
አካላት ጋር ለሚከናወኑ የውትወታ ሥራዎች መነሻ ይሆናሉ።

በቃለ መጠይቅ የተገኘ መረጃን ትክክለኛነት እና ተዓማኒነት ለማረጋገጥ በዋናነት የመረጃ


ሰጪውን ሰው ተዓማኒነት እና የመረጃውን ትክክለኛነት በሁለት ደረጃ ከፍሎ መመዘን
ያስፈልጋል።

የመረጃ ምንጮች ተዓማኒነት የመረጃ ሰጪዎችን የግል አስተያየት እና በጉዳዩ ላይ ያላቸው


አቋም (personal bias)፣ የሥራ ድርሻ፣ ፖለቲካዊ አቋም ወ.ዘ.ተ... ታሳቢ በማድረግ
ይከናወናል። የክትትሉ ግኝቶች አንድን ወገን በጥሩ ወይም በመጥፎ አፈጻጸም ደረጃ ላይ
እንደሚገኝ እንዲያሳዩ ሊያነሳሱ የሚችሉ ፍላጎቶች ወይም አነሳሽ ምክንያቶች ካሏቸው መረጃ
ሰጪዎች የሚገኙ መረጃዎችን በጥንቃቄ መመዘን እና ጥሩ የማገናዘብ ችሎታን መጠቀም
ያስፈልጋል።

የመረጃ ትክክለኛነት በሁለት መልኩ ይመዘናል። የመጀመሪያው የተሰጠው መረጃ እርስ በእርሱ
የማይጋጭ ውስጣዊ ወጥነት (internal consistency) ያለው መሆኑን መመዘን ነው። ከአንድ
መረጃ ሰጪ የተገኘ ውስጣዊ ወጥነት ያለው መረጃ ይበልጥ ተዓማኒ ሊሆን ይችላል። ሆኖም
በተለይ መረጃ ሰጪው የቋንቋ ችግር፣ የእድሜው መግፋት ወይም ማነስ፣ በደረሰበት የመብት
ጥሰት ሳቢያ የተከሰተ የማኅበረ ሥነ ልቦና ጉዳት፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ወ.ዘ.ተ... ያሉበት
ከሆነ በሚሰጠው መረጃ ውስጣዊ ወጥነት ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል
መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት እና በመረጃው ትክክለኛነት ምዘና ላይ ታሳቢ ማድረግ
ያስፈልጋል።

ሁለተኛው በቃለ መጠይቅ የተገኘ መረጃን ትክክለኛነት የመመዘኛ ዘዴ መረጃውን ከሌሎች


በቃለመጠይቅ፣ በሠነድ፣ በመስክ ምልከታ ወይም ነጻ ከሆኑ ምንጮች ከተገኙ መረጃዎች ጋር
ያለውን ተመሳሳይነት/ተመጋጋቢነት (external consistency) መፈተሽ ነው። በተመሳሳይ አካባቢ
በአንድ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች የተገኙ መረጃዎች በአብዛኛው ተመሳሳይ ይሆናሉ፤
የሚሰበሰቡ መረጃዎችም ይህንኑ ያመላክታሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በአንድ አካባቢም ቢሆን
በባህል፣ ማኅበራዊ ደረጃ ወይም በሌሎች ምክንያቶች በማኅበረሰቡ ክትትል በሚደረግበት አካባቢ
ወይም ተቋም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ለየት ባለ መልኩ ተጎጂ ሊሆኑ ስለሚችሉ
የተለየ መረጃ ሊሰጡ እንደሚችሉ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል። ለምሳሌ በአንድ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ
ሙሉ አካላዊ ጤና ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ስለመሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት የሚሰጡት
መረጃ የአካል ጉዳት ያለባቸው መረጃ ሰጪዎች ከሚሰጡት መረጃ የተለየ ሊሆን ይችላል። እንዲህ
ያሉ የመረጃ ልዩነቶች ተዓማኒነትን ከመቀነስ ይልቅ በክትትል ሥራው የሁሉንም የሕብረተሰብ
ክፍሎች የመብት ሁኔታ ለመፈተሽ ጠቃሚ ሆኖ የሚያገለግል ነው።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
30

ቀጥተኛ ከሆኑ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች ቀጥተኛ ካልሆኑ ምንጮች የተሻለ አስተማማኝነት
(ተአማኒነት) እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። ሆኖም ቀጥተኛ መረጃ ምንጭ የሆኑ ሰዎች በሰጧቸው
መረጃዎች ውስጥም ቢሆን ከግል አመለካከት ወይም (personal bias) የሚመነጩ መረጃዎችን፣
እራሳቸው ካዩት፣ ከሰሙት እና ካሳለፉት ልምድ ውጪ የሆኑ መረጃዎችን ለይቶ ማውጣት
አስፈላጊ ነው።

5.2 ሪፖርት ማዘጋጀት

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሪፖርት የክትትሉን ዓላማ፣ የመረጃ ማሰባሰቢያ ስልት፣ የክትትል
ሥራውን ወሰን፣ የሕግ እና የሁኔታ ትንተና፣ በክትትሉ ከሁሉም ወገኖች የተገኙ መረጃዎች፣
ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሁኔታ (ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን
እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ) በግኝቶች እና ምክረ- ሃሳቦች ማካተት አለበት።

የሰብአዊ መብት ክትትል ሪፖርት የትክክለኛነት እና የተዓማኒነት መመዘኛዎችን በማለፍ አሳማኝ


(Prima Facie) የተረጋገጡ መረጃዎችን ብቻ ይዞ መዘጋጀት ይኖርበታል። ያልተረጋገጡ ወይም
ጥረት ተደርጎ ለማረጋገጥ ያልተቻሉ መረጃዎችን በሪፖርቱ ውስጥ መግለጽ የግድ አስፈላጊ ሲሆን
መረጃዎቹ በኮሚሽኑ ያልተረጋገጡ መሆኑን በግልጽ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው።

በተለይ ለሕዝብ ይፋ የሚደረጉ ሪፖርቶች በሚዘጋጁበት ወቅት አንባቢው የሕግ ወይም የሰብአዊ
መብቶች ባለሙያ እንደማይሆን ታሳቢ በማድረግ ሪፖርቱ በአጠቃላይ ለአንባቢ በቀላሉ እንዲረዳ
ወይም ተደራሽ እንዲሆን የሚከተሉትን ነጥቦች መሠረት በማድረግ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፦

• ውስብስብ ያልሆኑ ቀላል አነጋገሮችን መጠቀም፤


• ሙያዊ የሆኑ አገላለጾችን መጠቀም፤
• ትርጓሜ የሚፈልጉ ወይም ለመረዳት የሚከብዱ ቃላትን አለመጠቀም (Avoid Jargons
and abbreviations)፤
• በመረጃ አቀራረብ እና በትንታኔ መካከል ልዩነትን በሚገባ ማስቀመጥ፤ ሁል ጊዜ በመረጃ
(በተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች ወይም እውነታዎች (Facts) መጀመር፤
• በተቻለ መጠን የውጪ ቋንቋ አገላለጾችን አለመጠቀም፤
• ስሜታዊ የሆኑ አገላለጾችን አለመጠቀም፤
• አጠቃላይ እና ግልጽነት የጎደላቸው ድምዳሜዎችን የሚያመላክቱ አገላለጾችን
አለመጠቀም።

ጥሩ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት አንጻራዊ በሆነ መልኩ አጭር ግልጽ እና መረዳት
የሚያስችል እንዲሁም መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አመክንዮን እንዲሁም መረጃዎቹ ላይ
በተገቢው መጠን አጠር ያለ ትንታኔ መስጠት የሚችል መሆን ይኖርበታል። የተወሰኑት
አንባቢዎች ብዙ ገጾችን ለማንበብ ጊዜ የሌላቸው መሆኑን በመገንዘብም፤ አጭር መልዕክቱን
ለማወቅ ለሚፈልጉ አንባቢዎች የሚረዳ አንኳር ክፍል ማዘጋጀትም አስፈላጊ ነው። ጥሩ ሪፖርት
አንድ ሃሳብን በፍጥነት እና በአጭር ጊዜ መረዳት በሚያስችል መልኩ ማቅረብ መቻልን
ይጠይቃል። በአንድ ጉዳይ ላይ የተሰበሰበ መረጃን ወይም የሚታወቅ ጉዳይን ሁሉ ከሚያስፈልገው
መጠን በላይ መዘርዘር አስፈላጊ አይሆንም።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
31

ሁሉም የሰብአዊ መብት ክትትል ሪፖርቶችን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ላያስፈልግ ይችላል።


የክትትሉ ግኝቶች ከፍ ያሉ የመብት ጥሰቶችን የማያሳዩ ሲሆኑ፤ ከፍተኛ ትኩረት ያገኙ ወቅታዊ
ሀገራዊ ጉዳዮችን የማይመለከቱ ሲሆኑ፤ የመብት ጥሰቶች ወይም የአፈጻጸም ክፍተቶች በአጭር
ጊዜ ለማስተካከል ከሚያስቸግሩ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ጋር የተሳሰሩ ሲሆኑ ወይም
ከሚመለከተው ተቋም ጋር በሚደረግ ውይይት ብቻ ምክረ ሃሳቦች ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ
በታመነ ጊዜ የክትትሉን ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች ብቻ የሚያመላክቱ ደብዳቤዎችን
ለሚመለከተው ፈጻሚ ተቋም እና ለሚመለከታቸው ሌሎች የመንግሥት ወይም ሌሎች
የሚመለከታቸው አካላት በመላክ፤ ውይይት በማድረግ እና በመወትወት ሊከናወን ይችላል።
እንደነገሩ ሁኔታ አስፈላጊ የሚሆነው አቅጣጫ የሥራ ክፍሉን በሚመሩ ኮሚሽነሮች እና
ዳይሬክተሮች ውይይት የሚወሰን ይሆናል። ሆኖም እነዚህ መረጃዎች በኮሚሽኑ የተለያዩ ዓመታዊ
ወይም ወቅታዊ የክትትል ሪፖርቶች ውስጥ ተካትተው ይፋ ሊደረጉ ይችላሉ። በሪፖርቶች
ይዘት፣ ቅርጽ እና ስርጭት ስልት ላይ ሁል ጊዜም ከኮሚሽኑ የሕግ እና ፖሊሲ እንዲሁም
ኮሙኒኬሽን የሥራ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረግ ተገቢ ነው።

የክትትል ሪፖርት የመጀመሪያ ረቂቅ ሁል ጊዜም ክትትሉን ባካሔደው ባለሙያ ወይም


የባለሙያዎች ቡድን መዘጋጀት አለበት። ክትትሉን ያከናወኑት ባለሙያዎች በየደረጃው ከሚገኙ
ኃላፊዎች ወይም ሌሎች ባለሙያዎች ይልቅ መረጃዎችን እና አውዶችን ይገነዘባሉ። በተጨማሪም
ረቂቅ ሪፖርቱን ሌሎች የኮሚሽኑ የሥራ ክፍሎች እንዲመለከቱት እና እንደየሥራ መስካቸው
እና ሙያዊ ዘርፋቸው አግባብነት ያላቸው የሪፖርቱን ክፍሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው አስተያየት
እንዲሰጡ ማድረግ እና ይህንኑ ማካተት ያስፈልጋል።

በክትትል ሪፖርት ላይ የሚካተቱ ምክረ ሃሳቦች ቀረጻ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው።
የክትትል ሪፖርት ላይ የሚካተቱ ምክረ ሃሳቦች የሚከተሉትን መስፈርቶች ታሳቢ በማድረግ
ሊቀረጹ ይገባል፦

• በቁጥር ውሱን መሆን፤ በጣም ጠቃሚ የሆኑትን እና አግባብነት ያላቸውን ብቻ መለየት፤


• ምክረ ሃሳቡን የመፈጸም ኃላፊነት ያለበትን ተቋም በግልጽ ማመላከት፤
• የሚፈለገውን ውጤት ወይም እየተጠየቀ ያለውን እርምጃ በግልጽ ማመላከት፤
• አጭር እና ግልጽ መሆን፤ ሰፊ መንደርደሪያዎችን እና ትንተናዎችን ማስቀረት፤
• አላስፈላጊ ወቀሳን ማስቀረት፤ ፈጻሚዎች የሰብአዊ መብት አከባበርን እንዲያሻሽሉ በማገዝ
ገንቢ መንፈስ መቅረጽ፤
• ከክትትሉ ግኝቶች ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ መሆን፤
• ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ መሆን፤
• እንዲመጣ ለሚፈለገው ለውጥ በቀጥታ አግባብነት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ፤ እና
• በጊዜ የተገደቡ መሆን።

5.3 የማሰራጨት እና የውትወታ ተግባራት2 (Dissemination and Advocacy)

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሪፖርት የታሰበለትን ውጤት ለማሳካት ያስችለው ዘንድ እንዲሁም
አስፈላጊ እርምጃዎች ይወሰዱ ዘንድ፤ ለታለመለት አካል እንዲደርስ እና ግንዛቤ እንዲወሰድበት
ማድረግ አስፈላጊ ነው።

2
ይህ ስራ የኮሚሽኑን የውትወታ እና ቪሲቢሊቲ ስትራቴጂን ታሳቢ በማድረግ መከናወን ይኖርበታል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ
32

የተለየዩ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት በክትትል ግኝቶቻቸው ላይ በመመስረት እንዲሁም በሪፖርቱ


ላይ የተመላከቱ ምክረ ሃሳቦችን አፈጻጸም ለመከታተል የተለያዩ የውትወታ ስትራቴጂዎችን
ነድፈው ይተገብራሉ። የክትትል ሥራን መሰረት በማድረግ የሚወጡ ሪፖርቶች በሚመለከታቸው
ባለድርሻ (ግዴታ ያለባቸው) አካላት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ
ሌሎች ውትወታዎች፤ የሰብአዊ መብቶች ምክር መስጠት፤ አስቸኳይ ደብዳቤ መጻፍ፤ የጋዜጣዊ
መግለጫዎች ማውጣት፤ የሕዝብ ንቅናቄ መፍጠር እንዲሁም ከባለመብቶችና ሌሎች አጋሮች
ጋር በጋራ የሚደረግ ውትወታ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

ለዚህም ስልቶችበመንደፍ የጊዜ ገደብ እና አፈጻጸም መከታተያ ስልት በመቀየስ በቅድሚያ


የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በተጨማሪም የውትወታ ሥራው የሚከተሉትን
ጉዳዮችን ሊያካትት ይገባል:-

• የሚመለከታቸውን አካላትን መለየት፤


• የሚወሰዱ እርምጃዎችን ማቀናጀት፤
• የሚተላለፉ መልዕክቶችን ማዘጋጀት፤
• መልክቶቹ የሚተላለፉበትን አውድ መለየት፤
• ስብሰባዎች፣ ዎርክሾፖችን እና የምክክር መድረኮችን ማካሄድ፤
• ውጤቱን መገምገም፤
• አማራጭ ስትራቴጂዎችን መመልከት።

የውትወታ ሥራ እራሱን የቻለ አሠራር ሥርዓት እና ስልት ያሉት ስለሆነ ለብቻው ዝርዝር
ስትራቴጂ ዕቅድ በማዘጋጀት የሚከናወን አስፈላጊ ሥራ ነው።

5.4 የመልሶ ክትትል ተግባራት ማከናወን

የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ በአንድ ጊዜ ብቻ ተከናውኖ የሚያበቃ ሳይሆን በተከታታይነት


የሚደረግ በክትትል ሂደት የታዩ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ለውጦችን የመመዝገብ ሥራን
ያጠቃልላል። የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ቢሆኑ የሰብአዊ መብቶች የክትትል ሥራ፤
አንድ ጊዜ ብቻ ተከናውነው ሪፖርቱ ከተዘጋጀ በኋላ የሚያበቃ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም
ተከታታይነት ላለው ክትትል እና ውትወታ መንገድ የሚከፍት መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ
ያስፈልጋል። በዚህም መሠረት የክትትል ሪፖርቱ የደረሱት ጥሰቶች ምላሽ እንዲያገኙ ወደፊት
ደግሞ ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ተከታታይነት ያለው ጫና (ተጽእኖ) የሚያደርግ መሆኑን
ግንዛቤ መውሰድ ይገባል።

የክትትል ባለሙያዎች ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ


አካሎች ጋር ቅርበት ያለው መልካም የሥራ ግንኙነት ሊኖራችው ይገባል። ከእነዚህ የመንግሥት
ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካሎች ጋር የሚኖር መልካም ግንኙነት የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ
መፍትሔ ለመስጠት ሊያግዝ ይችላል። በተጨማሪም የክትትል ሥራን የሚያከናውኑ
ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን በተከታታይ፡ በመደበኛነት
መጎብኘት እና መከታተል ይጠበቅባቸዋል። ከእነዚሀም ውስጥ ማረሚያ እና ማረፊያ ቤቶች፣
ሆስፒታሎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የስደተኞች መጠለያዎች ይገኙበታል።

www.ehrc.org የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የሥራ መምሪያ

You might also like