You are on page 1of 56

የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል (Community Learning Centers)

ምንነት፣ አመሰራረት እና አስተዳደር

የባለሙያዎች ማሠልጠኛ ማኑዋል

አዘጋጆች፤
የራስወርቅ መገርሳ በዳዳ
ኤርሚያስ ፀሐይ ብርሃኑ

ትዝታ ለማ መልካ
ጥሩወርቅ ዘለዓለም ወርቅነህ

ዐቢይ መንክር ግዛው

የካቲት 2014 ዓ.ም.


ባሕር ዳር

1
2
ምስጋና
ይህ በማኅበረሰብ መማማሪያ ማእከላት ምንነት፣ አመሰራት እና አስተዳደር ዙሪያ የተዘጋጀው
የባለሙያዎች ማሠልጠኛ ማኑዋል እንዲዘጋጅ እና ታትሞ እንዲሰራጭ የሆነው ከእንግሊዝ ሀገር
መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲተገበር በቆየ የቤተሰብ መማማር እና ሀገር-በቀል ዕውቀት
ላይ ባተኮረ ፕሮጀክት አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኢስት አንግሊያ ውስጥ
የሚገኝ ሌላ ትልቅ ፕሮጀክት አካል ሲሆን የዚህ ፕሮጀክት መለያ ቁጥር (ref. EP/T015411/1)
ነው፡፡

ይህንን ማኑዋል ያዘጋጁት መምህራን በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኢስት አንግሊያ በተቋቋመው የጎልማሶች


ትምህርት ለማኅበራዊ ለውጥ የዩኔስኮ ቼር መርኃ-ግብር የሚሳተፉ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ
መምህራን ናቸው፡፡

Acknowledgement
This Training Manual on Community Learning Centres (CLCs) is prepared and duplicated as part
of and as one of the outcome documents of the project entitled "Family Literacy, Indigenous
Learning and Sustainable Development", which is part of a bigger project - Meeting the SDGs:
creating innovative infrastructures and policy solutions to support sustainable development in
Global South communities (GS-DEV) which is the title of University of East Anglia's Global
Research Translation Award (ref. EP/T015411/1). The award is funded by United Kingdom
Research and Innovation (UKRI) through the Global Challenges Research Fund (GCRF), part of
the UK's Official Development Assistance (ODA).

The team members who prepare this training manual are members of the University of East
Anglia's (UEA) UNESCO Chair in Adult Literacy and Learning for Social Transformation in
which Bahir Dar University is a member.

3
4
ማውጫ
ማውጫ ............................................................................................................................. 5

ምዕራፍ አንድ .................................................................................................................... 9

1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል (ማ.መ.ማ.) ጽንሰ-ሀሳብ............................................... 9

1.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል (CLC) ምንነት ..................................................... 9

1.2. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል ዓላማዎች .......................................................... 10

1.3. የማ.መ.ማ. አመጣጥና ዕድገት በኢትዮጵያ ............................................................ 11

1.4. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት አስፈላጊነት ...................................................... 12

1.5. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት (CLC) ጥቅሞች ............................................... 13

1.6. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ሚናዎች .......................................................... 14

ምዕራፍ ሁለት................................................................................................................. 16

2. በማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት የሚከናወኑ ተግባራት ............................................. 16

2.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ዋና ዋና ተግባራት............................................ 16

2.1.1. የትምህርት ተግባራት ................................................................................... 16

2.1.2. የኢኮኖሚያዊ ተግባራት ................................................................................. 17

2.1.3. የመረጃ ግንኙነት ተግባራ .............................................................................. 17

2.1.4. ሌሎች ተግባራት .......................................................................................... 18

ምዕራፍ ሦስት ................................................................................................................. 20

3. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን ማቋቋም .............................................................. 20

3.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን የማቋቋም ሒደት ........................................... 20

3.1.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል ሽፋን ........................................................... 20

3.1.2. በማኅበረሰቡ ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ............................................. 21

3.1.3. በማ. መ.ማ. ምስረታ ሒደት የማኅበረሰቡን ተሳትፎን ማሳደግ ........................ 22

3.1.4. የማ.መ.ማ የአስተዳደር ኮሚቴ ምስረታ .......................................................... 22

3.1.5. የማ.መ.ማ. ቦታ መምረጥ ............................................................................. 23

5
ምዕራፍ አራት ................................................................................................................. 24

4. የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ................................................................................................ 24

4.1. የማኅበረሰብ የፍላጎት ግምገማ.............................................................................. 24

4.2. የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ዘዴዎች ............................................................................. 24

4.2.1. የሰነድ ጥናት /document analysis/ ............................................................. 25

4.2.2. ቃለ መጠይቅ (interview) ............................................................................ 25

4.2.3. የጽሑፍ መጠይቅ (Questionnaire) .............................................................. 25

4.2.4. ውይይት እና ስብሰባ ..................................................................................... 26

4.2.5. አሳታፊ የገጠር ግምገማ /Participatory Rural Appraisal/ ............................. 26

4.3. ፍላጎቶችን ቅደም ተከተል ማስያዝና ተያያዥ ጉዳዮች ............................................ 26

ምዕራፍ አምስት .............................................................................................................. 27

5. የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት (Database) ማቋቋም ......................................................... 27

5.1. የመረጃ ቋት ምንነትና የማደራጀት ሒደት ............................................................ 27

5.2. የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት አስፈላጊነት ................................................................... 28

5.3. የመረጃ አሰባሰብ ሒደት ...................................................................................... 29

ምዕራፍ ስድስት ............................................................................................................... 30

6. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት አደረጃጀትና አስተዳደር............................................ 30

6.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከሎች አስተዳደራዊ መዋቅር ...................................... 30

6.2. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል አስተዳደር .......................................................... 31

6.3. የአስተዳደር አካላት ተግባርና ኃላፊነት .................................................................. 32

6.4. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል ዕቅድ ዝግጅት .................................................... 33

6.4.1. የዕቅድ ዝግጅት ደረጃዎች ............................................................................. 34

6.4.2. የተለመዱ የማ.መ.ማ. ዕቅድ አካላት .............................................................. 36

ምዕራፍ ሰባት .................................................................................................................. 37

7. የማ.መ.ማ፣ ሠራተኞችን ዐቅም መገንባት ................................................................... 37

7.1. የዐቅም ግንባታ ድጋፍ ደረጃዎች .......................................................................... 38

7.2. የዐቅም ግንባታ ዘዴዎች ...................................................................................... 38


6
ምዕራፍ ስምንት .............................................................................................................. 39

8. የማኅበረሰብ ንቅናቄ፣ ተሳትፎና ባለቤትነት ................................................................. 39

8.1. የማኅበረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊነትና ደረጃዎች ........................................................ 39

8.2. የማኅበረሰብ ንቅናቄ አጋሮች ................................................................................ 41

8.3. የማኅበረሰብ ንቅናቄ ዘዴዎች ................................................................................ 41

8.4. የማኅበረሰብ ሀብቶችን ማሰባሰብ እና ማስተዳደር ................................................... 42

8.4.1. የኃብት ማሰባሰብ .......................................................................................... 43

8.4.2. የማ.መ.ማ ኃብት የሚገኝባቸው ምንጮች ....................................................... 43

8.5. የኃብት አጠቃቀም ............................................................................................... 44

ምዕራፍ ዘጠኝ.................................................................................................................. 46

9. ባለድርሻ አካላትን ማቀናጀት፣ ማስተሳሰርና ማገናኘት .................................................. 46

9.1. የባለድርሻ አካላት ቅንጅት .................................................................................... 46

9.2. የባለድርሻ አካላት ግንኙነት .................................................................................. 46

9.3. የማ.መ.ማ. ግንኙነት የሚፈጥርባቸው ተቋማት .................................................... 47

ምዕራፍ አስር .................................................................................................................. 49

10. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ክትትል፣ ግምገማና ቀጣይነትን ማረጋገጥ ............. 49

10.1. ክትትልና ግምገማ ........................................................................................... 49

10.2. የማ.መ.ማ. ተግባራት መሰነድ .......................................................................... 51

10.3. የማ.መ.ማ. ሰነዶች ስርጭት ............................................................................. 52

10.4. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን ዘላቂነትን ማረጋገጥ .................................... 53

10.4.1. ቀጣይነት ያለው የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል መገለጫዎች .................... 55

ዋቢ መፃህፍት ................................................................................................................. 56

7
መግቢያ
ማኅበረሰብን መሰረት ያደረገ ትምህርት ለዘላቂ ልማት እንዲሁም ንቁ ዜጋ ለማፍራት ጠቀሜታው
የጎላ ነው። በፍጥነት እየተቀየረ ባለው የዓለም ሥርዓት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሰዎች
ቀጥተኛና ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል። እንዲሁም ሰዎች ሕይወታቸውን
በዘላቂነት ለማሻሻል አዳዲስ ዕውቀቶችን እና ክህሎቶችን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡

የማ.መ.ማ. የዕድሜ ልክ ትምህርትን በማስፋፋት ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ


ያደርጋሉ፡፡ ማኅበረሰብ ተኮር የትምህርት አቀራረብ ሰዎች እንዲጠይቁ፣ እንዲረዱ፣
እንዲገመግሙ፣ እና የአካባቢ እና ሀገር በቀል ዕውቀትን የበለጠ እንዲያዳብሩ ያግዛል፡፡ ይህም
ማኅበረሰብን መሰረት ያደረገና ሀገር በቀል ዕውቀት ለማግኘትና ለአካባቢያዊ ችግሮች አካባቢያዊ
መፍትሄ ለመፈለግ ይግዛል፡፡ የማ.መ.ማ. ሚና ለማኅበረሰቡ አባላት የመማማሪያ ቦታ፣ የመዝናኛ
እንዲሁም የመገናኛ ማዕከላት በመሆን ለጎልማሶች፣ ለወጣቶችና ህጻናት የዕድሜ ልክ ትምህርት
ተደራሽነትን ማስፋት ነው፡፡

የአንድን ማኅበረሰብ የዕለት ከዕለት ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል እሴት፣ ዕውቀት፣ ክህሎት፣
ጥበብ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ጉልህ ሚና
ይጫወታሉ፡፡ በተለይም ዝቅተኛ የማንበብና የመፃፍ ባሕል ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ
የማኅበረሰቡን የማንበብና የመፃፍ ክህሎት ለማሳደግና የተቀናጀ ተግባር ተኮር የክህሎት
ሥልጠናዎችን ለመስጠት አስተዋጿቸው የላቀ ነው፡፡ በተጨማሪም የማኅበረሰብ መማማሪያ
ማዕከላት ህፃናትና ጎልማሶች በጋራ የሚማሩበት የሚወያዩበትና ቤተሰባዊ መማማርን ተግባራዊ
የሚያደርጉበት ማዕከልም በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡ በመሆኑም የማኅበረሰብ መማማሪያ
ማዕከላትን ማስፋፋትና ዐቅማቸውን ማሳደግ አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ይህ ማንዋል የተዘጋጀውም የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን በመመስረት፣ በማስተዳደር


እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ሥራ የሚሠሩ የዘርፉ ባለሙያዎችን ዐቅም ለማጎልበት ለሚሰጥ
ሥልጠና እንዲያገለግል በማሰብ ሲሆን የዚህ ማንዋል ዋና ተጠቃሚዎች የዐቅም ግንባታ ሥራ
ለሚሠሩና የሚያሰልጥኑ የክልል፣ ዞንና የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት የጎልማሶች ትምህርት
ባለሙያዎች፣ የቅድመ ልጅነትና ህፃናት ዕድገት እንክብካቤና ትምህርት ባለሙያው ናቸው፡፡
በተጨማሪም በልዩ ልዩ ዘርፍ የሚሠሩና ከማኅበረሰብ ልማት ጋር የተያያዘ ሥራ የሚሠሩ
የዕድሜ ልክ ትምህርትና የማኅበረሰብ ልማት ባለሙያዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

ማንዋሉ በአስር ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን ምንነት፣


በማዕከላቱ የሚከናወኑ ተግባራት፣ አመሰራረት፣ የፍላጎት ጥናት፣ መረጃ አያያዝና የአስተዳደር
ሥርዓት፣ የሠራተኞች ዐቅም ግንባታ፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎና የሕዝብ ንቅናቄ፣ የባለድርሻ አካላት
ግንኙነት፣ እንዲሁም የድጋፍና ክትትል አሠራርን በስፋት የሚተነትኑ ይዘቶች ተካተውበታል፡፡

8
ምዕራፍ አንድ
1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል (ማ.መ.ማ.) ጽንሰ-ሀሳብ
የዚህ ምዕራፍ ዓላማዎች

በዚህ ምዕራፍ መጨረሻ ሠልጣኞች፡


 የማ.መ.ማ.ን ምንነትና ታሪካዊ አመጣጥ ይረዳሉ፡፡
 የማ.መ.ማ.ትን አስፈላጊነት በትክክል ይረዳሉ፡፡
 በተጨማሪም የማ.መ.ማ.ት መኖራቸው ለማኅበረሰቡ አባላት ያላቸውን ጥቅሞች
ይዘረዝራሉ፡፡
የመነሻ ጥያቄዎች

1. የማ.መ.ማ. ሲባል ምን ማለት ነው?


2. ማዕከሉን የሚመሰርተውና የሚያስተዳድረው ማን ነው?
3. በዚህ ማዕከል ውስጥስ ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?

1.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል (CLC) ምንነት


የማ.መ.ማ. ከመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ውጭ የሚገኝ የመማሪያ ቦታ ነው። በገጠርም ሆነ
በከተማ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በአካባቢው ሰዎች የሚተዳደርና ለአካባቢው ሰዎች
አገልግሎት የሚሰጥ ነው:: የማ.መ.ማ.ዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ የተመሰረቱ ተቋማት ሲሆኑ
የሚያገለግሉትን ማኅበረሰብ ልዩ ልዩ ፍላጎቶች የሚዳስሱ የትምህርት መርኃ ግብሮችን ለማቅረብ
ጥሩ ቦታ ያላቸው ናቸው። እንደ እሸቱ እና አማኑኤል (2021 እ.ኤ.አ.) እንደገለፁት የማ.መ.ማ.
እንደ አንድ ቦታ ወይም የተለየ ግቢ ሁሉም የአንድ ማኅበረሰብ አባላት፣ በተለያ የዕድሜ ክልል
ያሉ ልጆች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች በአንድ ላይ የክህሎት ማዳበርና የመማማር ዕድሎች እንዲሁም
የኑሮ ማሻሻያ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉበት ቦታ ነው።

የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር፣ (2016 እ.ኤ.አ.) ባወጣው ረቂቅ ስትራተጂ የማ.መ.ማ. ማለት
ማኅበረሰቡን የበለጠ ጠንካራ ለማድረግ በማኅበረሰቡ ውስጥ ላለ ማኛውም ሰው መረጃና ዕድሜ
ልክ የመማር ልምድ የሚያገኝበት ማዕከል ነው ሲል ተርጉሞታል፡፡ ይህ የማ.መ.ማ. አብዛኛውን
ጊዜ በማኅበረሰቡ አባላት ወይም በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በግሉ
ዘርፍ ድጋፍ የሚቋቋሙና የሚተዳደሩ ማኅበረሰብ-ተኮር ተቋማት ናቸው። መረዳት (ሊትሬሲ)፣

9
ድህረ- መረዳት (ፖስት ሊትሬሲ)፣ የገቢ ማስገኛ፣ የሕይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እና ሌሎች
መሰረታዊ ትምህርቶች በማ.መ.ማ. ውስጥ ይሰጣሉ።

የማ.መ.ማ.ዎች አብዛኛውን ጊዜ ከመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ውጪ ሲሆኑ ለማኅበረሰብ


ልማት እና የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተለያዩ የመማር ዕድሎችን ለማቅረብ በአካባቢው
ሰዎች የሚቋቁሙና የሚተዳደሩ ናቸው። የማ.መ.ማ.ዎች የማኅበረሰቡ ንብረት በመሆናቸው
ከሌሎች ተቋማት ይለያሉ፡፡ ስለሆነም የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች በማኅበረሰቡ አባላት የጋራ ተሳትፎ
የሚስችል ዐቅም ይኖራቸዋል።

በገጠርና በከተማ ያሉ የኅብረተሰቡ ችግሮች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡


ለአብነትም መሬት ማጣት፣ሥራ አጥነት፣ በአንድ የሰብል ምርት ጥገኛ መሆን፣ የበሽታ
ተጋላጭነት መጨመር፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ አለመሆን፣ ከፍተኛ የሆነ
የትምህርት ማቋረጥና መደጋገም ብሎም ከትምህርት ቤት ውጭ የሆኑ ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ
መሆን ይገኙበታል፡፡ እነዚያን ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት በማኅበረሰብ ደረጃ ተቀራረቦ
ለመማማርና ሕይወት እንዲቀጥል ለሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍትሄ እርምጃዎች ለመውሰድ
የማ.መ.ማ.ዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከ2003 እስከ 2013 የነበረው የተባበሩት መንግሥታት
ድርጅት የመረዳት አስርት አመታት (ዲኬድ) የማኅበረሰብ ተሳትፎን እንደ ቁልፍ የተግባር
የሚያካትት ሲሆን የማ.መ.ማ.ን መመስረትን የሚያበረታታ ነበር (ዩኔስኮ ኢንስቲትዩት ፎር ላይፍ
ሎንግ ለርኒንግ፣ 2016 እ.ኤ.አ.)፡፡

1.2. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል ዓላማዎች


የማ.መ.ማ. መርኃ ግብር ዓላማዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ያቋረጡትን፣ የመማር ዕድል
ያላገኙትን (ሂድን ሊትሬትስ)፣ የመፃፍ፣ የማንበብና የማስላት ክህሎትን እንደ አዲስ የተማሩትን
በአጠቃላይ መደበኛ ባልሆነ የትምህርት ዘርፍ እንዲሳተፉና የዕድሜ ልክ ትምህርት የመማር
ልምድ እንዲያዳብሩ ለማድረግ ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ በብዙ ሀገሮች ለተለያዩ የልማት ድርጅቶች
የተለያዩ የድጋፍ አገልግሎቶችን ለማኅበረሰቡ አባላት የሚያቀርቡበት መድረክ በመሆንም
ያገለግላል፡፡ በትምህርታዊ ተግባሮቹም ቀጣይነት ያለው የመረዳት አካባቢ (literacy
environment) ለመፍጠር አጋዥ ይሆናል። የማ.መ.ማ.ዎች በተቀናጀ ዕቅድና ትግበራ መረዳትን
(literacy)፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትንና ተከታታይ ትምህርትን ለማስተባበር በጣም ውጤታማ
እና ደጋፊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

10
ለማጠቃለል የማ.መ.ማ. ዓላማዎች፡-
 የአካባቢው ሰዎች በራሳቸው እንዲተማመኑ ለማድረግ
 የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል
 የማኅበረሰብ ልማትን ለማነቃቃት
 የኅብረተሰቡን የተለያዩ ፍላጎቶች ለመለየትና መፍትሄ መስጠት
 የማኅበረሰቡን ሰብአዊና ቁሳዊ ኃብት ለይቶ ለመጠቀምና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወዘተ.
ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡

1.3. የማ.መ.ማ. አመጣጥና ዕድገት በኢትዮጵያ


እንደ ኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት አራተኛው ትምህርት ሴክተር ልማት መርኃ ግብር
(ESDP IV) እና የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP1) የጎልማሶችን
የመማር ዕድል በማስፋት የመማር ዕድል ያላገኙ ጎልማሶች (illiterate adults) ቁጥር እንዲቀንስ
ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ነገር ግን ዲቪቪ ኢንተርናሽናል የተባለ ግብረሰናይ ድረጅት
የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በቂ እንዳልሆነ በመረዳት ክፍተቱን ለመሙላት የተቀናጀ
ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መርኃ ግብርን መደገፍ ጀመረ (እሸቱ እና አማኑኤል፣ 2021
እ.ኤ.አ.)፡፡ ይህም የማ.መ.ማ.ትን ለማቋቋምና አራት ቁልፍ የግንባታ መሰረቶችን ለመጣል
ማለትም፤ (1) ተቋማዊ አደረጃጀትን፣ (2) ዐቅም ግንባታን፣ (3) የአመራር ሒደት፣ እንዲሁም
(4) የተቋማትን ትስስርን) እና የሙከራ ትግበራ ለመጀመር አግዞታል፡፡

በመቀጠልም በ2016 እ.ኤ.አ. በሞሮኮ በተካሄደው የተቋሙ የልምድ ልውውጥ መርኃ ግብር ላይ
የተገኙ ተሞከሮዎችን በማዳበር ዲቪቪ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የማ.መ.ማ
ፅንሰ ሃሳብን ለማስተዋወቅ ችሏል፡፡ በመቀጠልም በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔሮች፣
ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች ከየክልሎቹ የትምህርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር የማ.መ.ማ.
የሙከራ ፕሮጀክቶችን ሲሠራ የቆየ ሲሆን በሒደትም ወደአዲስ አበባና ትግራይም ለማስፋት
ችሏል፡፡ ከ2016 እ.ኤ.አ. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዲቪቪ ኢንተርናሽናል በመላ ሀገሪቱ ባለ 11
ወረዳዎች የማ.መ.ማ በመገንባትና ወደ ሥራ በማስገባት በየደረጃው ካሉ የመንግሥት ተቋማት
ጋር ተባብሮ እየሠራ ይገኛል፡፡

በመንግሥት ደረጃ የማ.መ.ማ ስትራቴጅ ረቂቅ (የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር፣ 2016 እ.ኤ.አ.)
የተዘጋጀ ቢሆንም እስካሁን ወደ ተግባር አልገባም፡፡

11
በመንግሥት በኩል የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራም ትግበራ ትኩረት
ተሰጥቶት በመሠራቱ ምክንያት በርካታ ጎልማሶች ማንበብና መፃፍ ችለዋል፡፡ ነገር ግን እነዚያ
ማንበብና መጻፍ የቻሉ ጎልማሶች የሁለት ዓመት መርኃ ግብር ካጠናቀቁ በኋላ በተለያየ ዘርፍ
ትምህርታቸውን ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ጠይቀዋል። አንዳንዶቹ በየአካባቢያቸው የንባብ
ማዕከላት እንዲኖራቸው ሲፈልጉ ሌሎች ደግሞ ወደ መደበኛው ትምህርት ቤት መግባት
ይፈልጋሉ፡፡ አሁንም አብዛኞቹ ተመራቂ ጎልማሶች ኑሮአቸውን መሰረት አድርገው የተለያዩ
ዓይነት ክህሎት የሚማሩበት የማ.መ.ማ. እንዲቋቋም ጠይቀዋል።

ከላይ የተገለጹትን የተመራቂ ጎልማሶችን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሁሉም ክልሎች
እና ከተማ አስተዳደሮች የማ.መ.ማ. እንዲቋቋም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተቀባይነት ያገኘ
ሲሆን ይህም ስትራቴጂ ተጀምሮ የማስፈጸሚያ ሰነዶች እየተዘጋጀ ነው።

በአጠቃላይ የማ.መ.ማ. ጽንሰ-ሀሳብ በኢትዮጵያ በአንጻራዊነት አዲስ ነው። ነገር ግን በሀገሪቱ


ውስጥ ላለው ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ሁኔታ በጣም አስፈላጊ እና ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም
በ2025 ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት
ሰዎች ዐቅም እንዲኖራቸው ለመርዳት አዲሱ የማ.መ.ማ. ስትራቴጂ በኢትዮጵያ ይፋ መደረጉ
ወቅታዊ እና ተገቢ ነው።

1.4. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት አስፈላጊነት


የማነቃቂያ ጥያቄዎች
1. የማ.መ.ማ. አስፈላጊትም ምን ምን ናቸው?
2. ለማንበብ፣ ለመፃፍና ለማስላት የማ.መ.ማ.ላት ያላቸውን ሚና ምንድን ነው?

የማ.መ.ማ. የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና የማንበብ፣ የመፃፍና የማስላት ክህሎትን


ለማዳበር የሚተገበር አዲስ መርኃ ግብር ነው። የማ.መ.ማዕከሎች ለግለሰብ እና ለማኅበረሰብ
ልማት ሁለገብ ድጋፍና አገልግሎት ይሰጣሉ። ብዙውን ጊዜ የማኅበረሰቡ አባላት በራስ
መተማመንን እንዲያዳብሩ፣ የኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻል እና የሰዎች በተለያዩ የልማት ተቋማት
መካከል ትስስር እንዲፈጠር ይረዳሉ፡፡ በተጨማሪም የማ.መ.ማ.ዎች በትምህርት ብቻ ሳይሆን
በኑሮ ዘዴ፣ በጤናና በሥነ-ምግብ አፋጣኝ የአካባቢ ፍላጎቶችን ለማሟላት ያግዛሉ፡፡ በተጨማሪም
የማ.መ.ማ.ዎች ሁሉንም ዕድሜ ክልል የሚያካትት የመማሪያ አካባቢ ይፈጥራሉ፡፡

12
1.5. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት (CLC) ጥቅሞች
የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር (2016 እ.ኤ.አ.) ባዘጋጀው ረቂቅ እስትራቴጅ እንደተገለፀው
የማ.መ.ማ. የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሏቸው፡፡

 የማ.መ.ማ. የአከባቢውን ሕዝብ ፍላጎት የሚያሟሉ የማኅበረሰብ መማማሪያና የልማት


ሥራዎች የሚከናወኑበት ቦታ በመሆን ያገለግላል፡፡
 የማ.መ.ማ. በትምህርት፣ በገቢ ማስገኛ፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሃይማኖት፣ በኪነጥበብ
እና በባሕል የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው
ቀጣይነት ያለው ትምህርት ለኅብረተሰቡ ይሰጣሉ።
 የማ.መ.ማ. በማኅበረሰቡ አባላት መካከል በራስ መተማመንን ይፈጥራል፡፡ በዚህም
ለኅብረተሰቡ ዘላቂ ልማት እና በመጨረሻም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅዖ
ያደርጋሉ።

በተጨማሪም የማ.መ.ማ. መርኃ ግብር በተተገበረባቸው የተለያዩ ሀገራት የሚከተሉት ለውጦች


ታይተዋል (ዩኔስኮ ኢንስቲትዩት ፎር ላይፍ ሎንግ ለርኒንግ፣ 2016 እ.ኤ.አ.)፡፡

 የተሻሻለ የግል ገቢ፡ የማ.መ.ማ.ዎች በሚሰሩባቸው ማኅበረሰቦች ሰዎች የራሳቸውን ንግድ


ለመጀመር የሚያስችሉ አዳዲስ ክህሎቶችን ስለሚጠቀሙ የሥራ አጥነት መጠን እየቀነሰ
መጥቷል፡፡
 የተሻሻለ የማኅበረሰብ ንግድ ክህሎት፡ በማ.መ.ማ የሚሰጡ ሥልጠናዎች በሀገር ውስጥ
ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያለውን ውጤታማነት ለማሳደግ አግዟል።
 የተገለሉ ቡድኖችን ማጎልበት፡ የማ.መ.ማ. የተፅዕኖ ግምገማዎች እንደሚያሳዩት የሥራ
አጥ ወጣቶችና የቤት እመቤቶች የማኅበራዊና ትምህርታዊ እንቅስቃሴ እንዲጨምርና
እንዲሁም የህዳጣን ተሳትፎ እንዲሻሻል የማ.መ.ማ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
 ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም፡ እንደ ኮምፒውተር፣ የእጅ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣
ዘመናዊ የማምረቻ ቴክኖሎጅዎችና ማሽነሪዎችን በዕለት ከዕለት ህይወታቸው የመጠቀም
ልምድ እያደገ መጥቷል፡፡
 በጤናና በንጽህና ላይ የተሻሻለ ዕውቀት፡ የማ.መ.ማ. ተሳታፊ ሰዎች ቤተሰብ ምጣኔን
ጨምሮ ስለ ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ፣ ስለተላላፊ በሽታዎችና ስርአተ-ምግብ ያላቸው ዕውቀት
ጨምሯል፡፡

13
 የአመለካከትን ማዘመን፡- አንዳንድ ማ.መ.ማ.ዎች የአካባቢውን ሕዝቦች ለሌሎች ብሄር
ብሄረሰቦች እና ብሄረሰቦች መቻቻል ያዳበሩ እና የበለጠ ሰላማዊ አብሮ መኖር ያስገኙ
እንደሆኑም ይታወቃል። በተጨማሪም በማ.መ.ማ. ሥልጠና የብዙ ሴቶችን ማብቃት
በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ላይ የበለጠ የዳበረ አረዳድ አስገኝተዋል፡፡
 በአካባቢ አስተዳደር ውስጥ መሳተፍ፡ የዴሞክራሲ ሒደቶችን ማሳደግ፣ ትኩረት
የተነፈጋቸው ሰዎችን ከማብቃት ጎን ለጎን በአካባቢ አስተዳደር መዋቅሮችና በአካባቢ ውሳኔ
አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲኖር አድርጓል።

1.6. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ሚናዎች


የማ.መ.ማ. ከሚጫወቱት ዋና ዋና ሚናዎች መካከል የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር (2016
እ.ኤ.አ.) ዩኔስኮ ባንኮክን በመጥቀስ የሚከተሉትን አስቀምጧል፡፡

1. ለዕድሜ ልክ ትምህርት፡- በማዕከሉ የሚሳተፉ ማኅበረሰቦች ከተለያዩ ምንጮች ማለትም


ከመምህራን፣ ከአሠልጣኞች፣ ከልዩ ድጋፍ ከሚሰጡ የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣
ከጓደኞቻቸው፣ የአጎራባች ማኅበረሰቦችን በመመልከት ወይም በጥናታዊ ጉብኝት መማር
ይችላሉ።
2. የሥራ ክህሎት፡- ተሳታፊዎች ከሀገር በቀል የጥበብ ምንጮች፣ ከልዩ ልዩ አሰልጣኖች
ከተለያዩ የትምህርት ሚዲያዎች እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ በተግባር ሥራ በመማር
የሥራ ክህሎታቸውን ማሻሻል ይችላሉ። እነዚህ ችሎታዎች ሰዎች መሠረታዊ
ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሻሽሉ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል።
3. የመረጃ አገልግሎት፡- በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ሰዎች በፈለጉት ጊዜ ዕድሜ ልክ
የትምህርት ተግባራትን ማከናወን ይችላሉ። ይህ ተግባር ከቤተ-መጻህፍት መጽሃፎችን
ማንበብ፣ ኤግዚቢሽኖችንና ትርኢቶችን መመልከት፣ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን ማዳመጥ፣
የሳተላይት ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መመልከት ወይም መረጃ ለማግኘት ኢንተርኔት
በመጠቀም ሊሆን ይችላል፡፡
4. መዝናኛ፡- የአካባቢ ማኅበረሰቦች አእምሯቸውንና አካላቸውን ለማነቃቃት በተለያዩ
የጨዋታ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ይችላሉ። ተግባራቱም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣
የስፖርት ውድድር፣ የዳንስ፣ የዘፈን፣ የድራማ፣ ስዕልን የሚያጠቃልል ሲሆን እነዚህ
እንቅስቃሴዎች ዓላማቸውም በማኅበረሰቡ አባላት መካከልና በአቅራቢያ ካሉ ማኅበረሰቦች
ጋር አንድነትን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡

14
5. ጤና እና ንፅህና፡- የማኅበረሰቡ አባላት ጤናማ ሆነው በመቆየት የማኅበረሰብን ደህንነት
ማጠናከር ይችላሉ። ስለዚህ የማ.መ.ማ. ሰዎች ስለ በሽታ መከላከል፣ መሰረታዊ ንፅህና
እና የተሻለ የአመጋገብ ሥርዓት የሚማሩበት ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡
6. የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፡- አንዳንድ የማኅበረሰቡ አባላት የራሳቸውን ልዩ ፍላጎት የሚጠቅም
ዕውቀትን ለማግኘት ራሳቸውን በትናንሽ ቡድኖች ማደራጀት ይችላሉ። እነዚህ ቡድኖች
ሴት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ይገኙበታል። እነዚህ ቡድኖች የቡድኑን
አባላት የኑሮ ሁኔታ በሚያሻስሉ ተግባራት ላይ ለመሰማራት አማራጭ ሃሳቦች የሚገኙበት
በመሆን ያገለግላሉ፡፡
7. የሀይማኖት እና የአካባቢ ባሕል፡- በማኅበረሰቡ የሚገኙ ጥበበኛና አስተዋይ አረጋውያን
ልዩ ዕውቀታቸውን፣ ጥበባቸውን፣ እሴታቸውን፣ ለአዲሱ (ለቀጣዩ) ትውልድ ማስተላለፍ
ይችላሉ። ይህ ተግባር በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ዕውቀት በመጠቀም ሁሉም ሰው
በአስተሳሰብ ፣በውሳኔ እና በድርጊት የመሳተፍ ዕድል ስላለው የማኅበረሰቡ የመጨረሻ ግብ
ማኅበረሰብ አቀፍ ዐቅም ግንባታ ላይ ለመድረስ የሚያስችል የሕይወት ዘመን ትምህርት
እንዲኖር የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

15
ምዕራፍ ሁለት
2. በማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት የሚከናወኑ ተግባራት
የማነቃቂያ ጥያቄ

1. በማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት ዘርዝሩ?


2. እያንዳንዱ የተዘረዘሩት ተግባራት ስር የሚከናወኑ ነገሮችን አብራሩ?

ዓላማ

ውድ ሰልጣኖች ይህ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ፡

 በማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ውስጥ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ይዘረዝራሉ፡



 የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ላይ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራ ስር ያሉ ንዕስ
ተግባራትን ይገልፃሉ፡፡

2.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ዋና ዋና ተግባራት


የሚከተሉት የማ.መ.ማ. ዋና ዋና ተግባራት ናቸው።

2.1.1. የትምህርት ተግባራት


 የመረዳት (ሊትሬሲ) ትምህርቶችን ማደራጀት፣
 የአቻነት መርኃ ግብሮች (ልዩ ፍላጎት ላላቸውና ለህዳጣን)፣
 ድህረ መረዳት (ፖስት ሊትሬሲ) መርኃ ግብሮችን ማደራጀት፣
 የመዋለ ሕጻናት ትምህርት መርኃ ግብር ማዘጋጀት፣
 የሕይወት ክህሎት ትምህርት መርኃ ግብር ማዘጋጀት፣
 አካባቢያዊ የመማማሪያ ቁሳቁሶችን ማምረት

የማ.መ.ማ. አስተዳደር ኮሚቴ የትምህርት ተግባራትን አፈፃፀምና የማዕከሉን አገልግሎት አሰጣጥ


ውጤታማነት እና ቅልጥፍናን ለመጨመር የተለያ ግንኙነቶችን (networks) መፍጠር ይችላል።
ለምሳሌ፡-

 በዲስትሪክቱ ውስጥ ካሉ ሁሉም የማ.መ.ማ./ሎች ጋር የቁሳቁስ እና የሥልጠና ልውውጥ


ማድረግ፣
 ለማ.መ.ማ. ሰልጣኖች (ተሳታፊዎች) ቀጣይነት ያለው ትምህርት እንዲኖር ከአካባቢው
መደበኛ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች ጋር መገናኘት፣

16
 የማ.መ.ማ. እንቅስቃሴዎችን በማደራጀት እና በመተግበር ረገድ ድጋፍ ለማግኘት
ከመንግሥት መስሪያቤቶችና ከአካባቢ ልማት አጋሮች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ ዋና
ዋናዎቹ ናቸው፡፡

2.1.2. የኢኮኖሚያዊ ተግባራት


የማ.መ.ማ. የአስተዳደር ኮሚቴ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት የክህሎት ሥልጠናዎችን
ለማዘጋጀት የአዋጭነትና የፍላጎት ጥናት ማካሄድ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም የማ.መ.ማ.
የአስተዳደር ኮሚቴ ሌሎች ብዙ የኢኮኖሚ ተግባራትን ማደራጀት ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡-

 በገቢ ማስገኛ ተግባራት ላይ መጽሃፎችንና መመሪያዎችን ማሰባሰብ፣


 የቢዝነስ ድርጅት ልማት ሥልጠና ኮርሶችን ማደራጀት፣
 የብድር ድጋፍን ማደራጀትና መስጠት፣
 ከሌሎች የብድር ፕሮግራሞች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣
 ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ፣
 ለምርቶች ግብይት ትስስር መፍጠር፣ወዘተ.. ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

2.1.3. የመረጃ ግንኙነት ተግባራ


የማ.መ.ማ. አስተዳደር ኮሚቴ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞችን እንደ
የኅብረተሰብ ጤና፣ የህጻናት ጤና፣ ንፅህና፣ ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል፣ የኮሮና ወረርሽኝ፣
ግብርና፣ አነስተኛ ኢንዱስትሪ፣ የሴቶች ማብቃት፣ የባንክና ብድር፣ ስርአተ-ጾታ፣ ባሕል፣ ሰላም፣
ስነምግባር እና ስነ ዜጋ ወዘተ የመሳሰሉ የተለያዩ የልማት መርኃ ግብሮችን መሰብሰብ፣ ማከማቸት
እንዲሁም ማሰራጨት ሌላኛው ተግባሩ ነው፡፡ ይህ የመርኃ ግብሮች ስብስብና ክምችትና ስርጭት
ተሳታፊ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን መላውን ማኅበረሰብም ይጠቅማል፡፡ በመሆኑም የማ.መ.ማ.
የአስተዳደር ኮሚቴ በማኅበረሰቡ ውስጥ ውጤታማ የመረጃ ልውውጥን ለማመቻቸት ብዙ
እንቅስቃሴዎችን ሊጀምር ይችላል፣ ለምሳሌ፡-

 የሀገር ውስጥ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የኤክስቴንሽን


መምሪያዎች (የጤና፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣---) እንቅስቃሴ መረጃ የሚከማችበት
ማኅበረሰብን መሰረት ያደረገ የመረጃ ማዕከል መፍጠር፣
 በሀገር ውስጥ ጋዜጦች፣ በመጽሔቶች፣ በማስታወቂያ ሰሌዳ ወዘተ የመረጃ ልውውጥን
ማሳለጥ።
 በወረዳ፣ ዘቦንና በክልል ደረጃ የማ.መ.ማ. የግንኙነት መረብ ማቋቋም፣

17
 የስኬት ታሪኮችና የፈጠራ ሥራዎች የልምድ ልውውጥና ስርጭት፣
 የገበያ መረጃን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን ለማሳየት በማ.መ.ማ. ውስጥ የማስታወቂያ
ሰሌዳን ማዘጋጀት፣
 ለመረጃ ማከማቻና ስርጭት ኮምፒተር መጠቀም እንዲሁም ለመቅዳት፣ ለማሳየትና መረጃ
ለመለዋወጥ ግንኙነት ሌሎች የአይሲቲ መሳሪያዎችን መጠቀም ወዘተ… ያካትታል፡፡

2.1.4. ሌሎች ተግባራት


እንደ ማኅበረሰቡ ፍላጎትና ዐቅም (ቴክኒካዊ በጀታዊ) በማ.መ.ማ. ሌሎች በርካታ ተግባራትን
ማደራጀት ይችላል፡ ለምሳሌ፡-

 የማኅበረሰቡን ዐቅም የሚገነቡ የልማት ሠራተኞችንና ሌሎች ሰዎችን ወደ መማማሪያ


ማዕከሉ መጋበዝ፣
 ለማ.መ.ማ. ተጠቃሚዎች ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ የልማት ዕቅዶችን መረጃ እና
ቁሳቁሶችን መሰብሰብ እና ማሰራጨት፣
 የግልና የቡድን ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ የሚፈልጉ የመንደሩን
ነዋሪዎች ከመረጃና ከድጋፍ አቅራቢዎች ጋር ማገናኘትና፣
 በማኅበረሰቡ እንደ አዲስ የማንበብና የመፃፍ ክህሎት የተማሩ ሰዎችን ፎርም እንዲሞሉ
መርዳትና ወደ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ፣የልማት አጋር ፅህፈት ቤቶች፣ ባንኮችና
ኤጀንሲዎች ሲሄዱ ክህሎታቸውን እንዲጠቀሙበት ማበረታታትና መገዝ፣
 ወደ ሞዴል የማ.መ.ማ. የመስክ ጉብኝቶችን ማዘጋጀት፣
 በተለያዩ ክፍሎችና ተቋማት ለሚካሄደው የክህሎት ሥልጠናዎች የማ.መ.ማ.
ተሳታፊዎችን ማዘጋጀትና መላክ፣
 የቅስቀሳ ዘመቻዎችን በማደራጀት መረዳትን (ሊትሬሲን) ቀጣይነት ያለው የመማማር
መርኃ ግብር አካል እንዲሆን ማድረግ፣
 የማ.መ.ማ. አባላትን በወጣት ክበቦች፣ በማኅበራዊ ድርጅቶች፣ በእድር፣ እቁብ ወይም
በኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ እንዲገቡና እንዲመዘገቡ ማገዝ፣
 የማ.መ.ማ. ተጠቃሚዎች ባላቸው ፍላጎት መሰረት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የማሳያ ክፍለ
ጊዜዎችን (demonstration) ማደራጀት፣
 ለወጣቶችና ለጎልማሶች (ወንዶችና ለሴቶች) ተስማሚ የሆኑ ስፖርቶችንና ጨዋታዎችን
ማዘጋጀት፣

18
 እንደ ማንበብ፣ መጻፍ፣ ሙዚቃ፣ ጥበብ ወዘተ ያሉ የተለያዩ ውድድሮችን ማዘጋጀት፣
 በተለያዩ አጋጣሚዎች የአካባቢና ሀገር በቀል ባሕላዊ ሁነቶችን ማዘጋጀ፣
 የመጽሐፍ ኤግዚቢሽኖችን እንዲሁም የመጽሃፍ ልውውጥ መርኃ ግብሮችን ከሌሎች
ተቋማትና የማ.መ.ማ. ጋር ማደራጀት፣
 ባሕላዊ ውዝዋዜዎችን፣ ባሕላዊ ጥበቦችንና ባሕላዊ ዘፈኖችን ያደራጁ፣

እነዚህን አጠቃላይ ግቦች በግልፅ ግምት ውስጥ በማስገባት የማ.መ.ማ. አስተባባሪዎች ከማኅበረሰቡ
አባላት ጋር የሚከተሉትን የማ.መ.ማ. ዕቅድ እና አስተዳደር ባህሪያትን ግምት ውስጥ ማስገባት
አለባቸው፡-

1. ድርጅታዊ መዋቅር፣
2. በዕቅድ እና በአስተዳደር ዑደት ውስጥ የተወሰኑ ተግባራት፣
3. የኃብት ልማት ስልቶች፣ እና
4. የኃብት ማሰባሰብ እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር መገናኘት ።

በአጠቃላይ በማ.መ.ማ. ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነትም፡

 የጎልማሶች ትምህርትና ድህረ መረዳት (Post Literacy) ሥልጠና አገልግሎት፣


 የክህሎት ሥልጠናና የገቢ ማስገኛ ተግባራ፣
 የቤተመፃህፍት አገልግሎት፣
 የመረጃ አቅርቦት፣
 የመሠረታዊ የጤና አገልግሎት አቅርቦት፣
 የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣
 ባሕላዊ የግጭት አፈታት፣
 ማኅበረሰብ አቀፍ መዝናኛ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን፣
 አነስተኛ ቁጠባዎችንና የብድር አገልግሎት፣
 የቅድመ ትምህርት ቤት፣
 የህጻናት እንክብካቤ እና መዋለ ህፃናት አገልግሎቶችን ያጠቃልላል (እሸቱ እና አማኑኤል፣
2017 አ.ኤ.አ.)።

19
ምዕራፍ ሦስት
3. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን ማቋቋም

የማነቃቂያ ጥያቄዎች

1. የማ.መ.ማ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

ዓላማ

ውድ ሠልጣኝ በዚህ ምዕራፍ መጨረሻ፡

 የማ.መ.ማ. ለመቋቋም ምቹ አካባቢዎችን መለየት ይችላሉ፡፡


 የማ.መ.ማ. ሲቋቋሙ የማኅበረሰብ ንቅናቄ ለምን እንደሚስፈልግ ይረዳሉ፡፡

3.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን የማቋቋም ሒደት


የማ.መ.ማ. ና ተጠቃሚዎች ለትምህርት አነስተኛ ዕድሎች ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ
ከትምህርት ቤት ውጪ ያሉ ህጻናት፣ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ወጣቶችና ጎልማሶች፣ ሴቶች
እና አዛውንቶችን የማ.መ.ማ. ተጠቃሚዎች ናቸው። የማ.መ.ማ. ለማቋቋም የግድ አዲስ መሠረተ
ልማት አያስፈልገውም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በፊት ማኅበረሰቡ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ተቋማት
ማለትም ጤና ጣቢያ፣ ቤተ-መፅሃፍ፣ ቤተ-ክርስቲያን፣ መስጊድ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ቤት ወይም ሌላ ተስማሚ ቦታ ላይ መጀመር ይችላል። የማ.መ.ማ. በማኅበረሰቡ ፍላጎት በሚመራ
ተነሳሽነት የሚሰራ መርኃ ግብር ነው። የማኅበረሰብ መሪዎች ወይም የማ.መ.ማ. ተጠቃሚዎች
የማ.መ.ማ. በማኅበረሰባቸው ውስጥ ለመጀመር ተነሳሽነት መውሰድ አለባቸው። የማ.መ.ማ.
ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወይም ከማንኛውም የልማት አጋር ጋር
በመተባበር ሊቋቋም ይችላል። የማ.መ.ማ.ን ለማቋቋም የሚከተሉትን ደረጃዎች መከተል አስፈላጊ
ነው፡፡

3.1.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል ሽፋን


አንድ የማ.መ.ማ. ሰፊ አካባቢ ላሉ ሰዎች ድጋፍ መስጠት አይችልም። በሰዎች ፍላጎት እና
በመልክዓ ምድራዊ ባህሪያት ላይ በመመስረት የማ.መ.ማ. የሚሸፍነው ቦታ ወይም የሚያሳትፈው
የሰው ኃይል መወሰን አለበት፡፡ የማ.መ.ማ. ሽፋን በሚወስኑበት ጊዜ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን
ማማከር ይችላሉ።

20
3.1.2. በማኅበረሰቡ ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ
በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ በትክክል መሥራት ከመጀመሩ በፊት የማኅበረሰቡ አባላት ስለ
ማ.መ.ማ. ዓላማ እና ግብ እንዲያውቁ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። የኅብረተሰቡን ተሳትፎ
ለማረጋገጥ የማኅበረሰቡን ነዋሪዎች ማ.መ.ማ ደጋፊና ተጠቃሚ ማወቅ ወሳኝ ነው። የት/ቤት
መምህራን፣ የማኅበረሰቡ መሪዎች፣ መነኮሳት እና የአካባቢ መንግሥት ተወካዮች ለማ.መ.ማ.
ድጋፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ላይ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላሉ። የመንደር ስብሰባዎችን
ማካሄድ፣ የባሕል ፕሮግራሞችን ማደራጀት፣ በሃይማኖት ተቋማት መልዕክት ማስተላለፍ፣
በትምህርት ቤትና በገበያ ቦታዎች ሕዝባዊ ቅስቀሳ ማካሄድ ስለማ.መ.ማ. ሰዎችን ለማሳወቅ
ውጤታማ ዘዴዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

የማኅበረሰቡ ነዋሪዎች፣ ተማሪዎችና መምህራን፣ የአካባቢው መንግሥታዊና መንግሥታዊ


ያልሆኑ ድርጅቶች ጽሕፈት ቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ላይ ለማ.መ.ማ. አዘጋጆች ድጋፍ
ሊሰጡ ይችላሉ። በኅብረተሰቡ ውስጥ የተሳካ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ለማደራጀት ሁሉንም
ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ዕቅድ ማዘጋጀት አለብን። በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች
ስለ አካባቢያዊ ሁኔታዎች፣ ስለ ባሕልና ወግ፣ ስለሚሰቃዩበት የማኅበረሰቡ ችግሮች፣ እንዲሁም
ጋራ ፍላጎቶች ይጋራሉ። ሰዎች ስለ ማኅበረሰቡ ችግሮች እና ፍላጎቶች በማሰብና በመወያየት
እንዲሁም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንገዶችን በማፈላለግ ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። የማ.መ.ማ.
በማኅበረሰብ ደረጃ የተደራጀ፣ የሚተዳደር እና በማኅበረሰብ ሰዎች የተያዘ ተቋም ነው።
የማ.መ.ማ.ዎች የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች እና ችግሮችን ለመፍታት እንቅስቃሴዎችን
የምንጀምርበት እና ለማኅበረሰቡ ነዋሪዎች የኑሮ ማሻሻያ እርምጃዎችን የምንወስድበት መድረክ
ሆነው ያገለግላሉ።

ለማ.መ.ማ. ትግበራ ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ድጋፍ እንፈልጋለን። በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ


ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ኃብትን ለማሰባሰብና የማኅበረሰብ ልማት አገልግሎት አቅርቦትን ለመደገፍ
የሚፈልጉ ግለሰቦች አሉ። ምንም ዓይነት ካሳ ሳይከፈላቸው ነገር ግን ለራሳቸው እርካታ ሲሉ
በኅብረተሰቡ ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ የሚፈልጉ አሉ። በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ውስጥ
በተለያዩ የማኅበረሰብ ልማት ጉዳዮች ላይ ልምድና ዕውቀት ያላቸውና ልምዳቸውን ለማካፈል
እና ለሌሎች ለማዳረስ ለማኅበረሰቡ መልካም ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች ይገኛሉ። እነዚህን
አጠቃላይ የማኅበረሰቡ አባላት የማ.መ.ማ. ለመደራጀት ልንጠቀምባቸው ይገባል።

21
3.1.3. በማ. መ.ማ. ምስረታ ሒደት የማኅበረሰቡን ተሳትፎን ማሳደግ
የማኅበረሰቡን ሰዎች ለማ.መ.ማ. ሥራዎች ለማነሳሳት፣ ስለማ.መ.ማ. ሚና፣ እንቅስቃሴዎቹ እና
ውጤቶቹ ጠቃሚነቱን እንዲያውቁ እና እሱን እንዴት መደገፍ እንደሚችሉ እንዲያውቁ ግንዛቤ
መፍጠር አለብን። ስለዚህ ሁሉንም ሰዎችን የማ.መ.ማ. ገጽታዎች በሚመለከት ዕውቀትና መረጃ
ማስታጠቅ አስፈላጊ ነው። የማኅበረሰቡ ሰዎች በማ.መ.ማ.ተግባራት ፍላጎቶቻቸው እና
ስጋቶቻቸው እየተስተናገዱ መሆኑን ሲመለከቱ በማ.መ.ማ.እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ ፍላጎት
ይኖራቸዋል።

የማ.መ.ማ.ተግባራትን መንደፍ እና ቅድሚያ መስጠት ሁል ጊዜ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚኖሩ


የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አፋጣኝ ፍላጎቶች ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህም
ሁሉም ሰው ከማ.መ.ማ. እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ ይሆናል። ሰዎች በእያንዳንዱ የእንቅስቃሴው
ደረጃ ላይ በመሳተፍ ስለሁኔታው መወያየት እንዲሁም ስሜታቸውን መግለፅ ይወዳሉ። ስለዚህ
የማ.መ.ማ. ትግበራ ሥራዎችንና ስትራቴጂዎችን ለመወሰን አሳታፊ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደት
በመከተል የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ማረጋገጥ በጣም ውጤታማ ያደርጋል። በማኅበረሰቡ አባላት
የላቀ ተሳትፎን ለማረጋገጥ በማ.መ.ማ. ውስጥ ሁሉም ሰው እንዲሳተፍና ነፃነት ተሰምቶት
እንዲንቀሳቀስ ምቹ የውይይትና የተሳትፎ ሜዳ ልንፈጥር ይገባናል፡፡

በማኅበረሰብ ሥራዎች የሰዎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ አንዱ ምርጥ ስልት የብዙ ሰዎችን
መስተጋብር እና ድርጊት የሚጠይቁ ተግባራትን መንደፍ ነው። የማኅበረሰብ ልማት እውነተኛ
ተሳትፎ በእያንዳንዱ አባል ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው። በገንዘብ እጥረት ምክንያት ብዙ
የማኅበረሰቡ አባላት ለማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አይችሉም፡፡ ነገር
ግን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ዕድል ከተሰጣቸው በጥበባቸው፣ በተሞክሮአቸውና በሙያቸው
ጠንካራ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሰዎችን ለማነሳሳት ቁሳዊ ሽልማቶች ሁልጊዜ አስፈላጊ
እንዳልሆኑ ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ተሳታፊወቹ ጎልማሶች
እንደመሆናቸው መጠን ውስጣዊ ተነሳሽነት ከቁሳዊ ሽልማት የላቀ ያበረታታቸዋል፡፡ እውቅና
መስጠት ከሽልማት የበለጠ ውጤታማ ነው። ሰዎች በውስጣቸው የሚያሳድጉት ተነሳሽነት
በእምነታቸው ላይ የተመሰረተና የበለጠ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው::

3.1.4. የማ.መ.ማ የአስተዳደር ኮሚቴ ምስረታ


የአስተዳደር ኮሚቴ ለማ.መ.ማ. ስኬት ቁልፍ ነው። ችሎታ ያላቸውና ተነሳሽነት ያላቸው ሰዎች
ወደ ማ.መ.ማ. ተግባራት ለማሰማራት እንዲሁም ለመዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የማ.መ.ማ.

22
አስተዳደር ኮሚቴ አባላት መምረጥ ያስፈልጋል። የማ.መ.ማ. ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ፣
አባላትና ቋሚ ጸሃፊ ያሉት ሆኖ ሊደራጅ ይችላል፡፡ ነገር ግን በማኅበረሰቡ አባላት ድጋፍ መመረጥ
አለባቸው፡፡ እንደ ማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ዓይነትና ተፈጥሮ የሚከናወኑ ተግባራትን
የሚያግዙ ልዩ ልዩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን ማደራጀትም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

3.1.5. የማ.መ.ማ. ቦታ መምረጥ


የማኅበረሰቡ አባላት በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ማ.መ.ማዕከላት በማኅበረሰቡ አማካይ ቦታ ላይ
መቀመጥ አለበት። የማ.መ.ማ. ቦታ በሚመርጡበት ጊዜ የልጃገረዶችና ለሴቶች ተሳትፎ ልዩ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: በኅብረተሰቡ ውስጥ ተስማሚ ቦታ ከሌለ የማ.መ.ማ. አዲስ ግንባታ
ከማኅበረሰቡ አባላት ወይም ሌሎች ተቋማት ድጋፍ መደረግ አለበት:: የማ.መ.ማ. አስተዳደር
ኮሚቴ ለማ.መ.ማ. ግንባታ ኃብት ማሰባሰብ አለበት። የማ.መ.ማ.ን ለማቋቋም የቦታዎች ምርጫ
በሚከተሉት መመዘኛዎች ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል።

 ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልገው ወይም የተቸገረ ማኅበረሰብ ያለበት


 የማንበብና የመጻፍ ልምድ ባልዳበረበት ወይም ዝቅተኛ በሆነበት ማኅበረሰብ፣
 ማኅበረሰቡን በጋራ ሊያወያይ የሚችል የአርሶ-አደሮች ማሰልጠኛ ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣
አዳራሽ ያለበትና ለሁሉም የማኅበረሰቡ አባላት ተደራሽ የሆነ ቦታ ያለው ማኅበረሰብ፣
 የማ.መ.ማ. ህንፃ ቢያንስ ሁለት ክፍሎች ቢኖሩት ይመረጣል፡፡

23
ምዕራፍ አራት
4. የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት
የማነቃቂያ ጥያቄዎች

1. የማ.መ.ማ ምስረታ የፍላጎት ጥናት እንዴት ይካሄዳል?


2. የፍላጎት ሳሰሳ ጥናት ውስጥ የምንጠቀማቸው የመረዳ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች
ምን ምንድን ናቸው?

ዓላማ

ውድ ተሳታፊዎች በዚህ ምዕራፍ ማብቂያ ላይ፡


1. የፍላጎት ዳሰሳ ጥናትን ምንነት ይረዳሉ፡፡
2. የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በማኅበረሰብ ውስጥ ስንሰራ ምንምን የመረጃ መሰብሰቢያ
ዘዴዎችን እንደት መጠቀም እንደሚችሉ ያብራራሉ፡፡

4.1. የማኅበረሰብ የፍላጎት ግምገማ


የማኅበረሰብ ፍላጎቶች ግምገማ ማለት ስለሰዎች ችግርና ፍላጎት የማወቅ ሒደት ነው። ብዙ
ሰዎች በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ይኖራሉ ነገር ግን በሙያ፣ በገቢ፣ በእምነት፣ በልምድ እና
በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ይለያያሉ። ይህ ልዩነት ፍላጎታቸውና ምርጫቸው እንዲለያይ
ያደርገዋል፡፡ ውጤታማ የማ.መ.ማ. መርኃ ግብር ማስኬድ የማኅበረሰቡን አባላት ፍላጎቶትና
ምርጫ በምንፈታበት መንገድ ላይ ይመሰረታል። በፍላጎት ግምገማ ሒደት ስለ ማኅበረሰቡ
ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንዲሁም ስለአሁንና የወደፊት ፍላጎቶቻቸው ግልጽ የሆነ ግንዛቤ
ማግኘት እንችላለን። በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸው
ሰዎች አሉ። የእነዚህን ሰዎች ልዩ ፍላጎቶች ማወቅ አለብን። በተጨማሪም ተጋላጭ የኅብረተሰብ
ክፍሎችንና የህዳጣን ቡድኖችን ልዩ ፍላጎቶች ማወቅ አለብን፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ የፍላጎት ዳሰሳ
ጥናት ማካሄድ ስለሕዝቡ እና ማኅበረሰቡ ዝርዝር መረጃ ለማወቅ ውጤታማ መንገድ ነው።

4.2. የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ዘዴዎች


የማኅበረሰብ ፍላጎት ግምገማ በተለያዩ መንገዶች ሊከናወን ይችላል። የማኅበረሰብ ፍላጎቶችን
ለመገምገም ሊተገበሩ የሚችሉ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። በመጀመሪያ ምን ዓይነት መረጃ መሰብሰብ
እንዳለብን መወሰን አለብን፡፡ ከዚያም እነዚያን መረጃዎች እንዴት እንደምናገኝ መወሰን አለብን።
መረጃ ለማግኘት የተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችንና መሳሪያዎችን (tools) መጠቀም

24
ይቻላል፡፡ አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን እና መሳሪያዎችን በአግባቡ
መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው:: የፍላጎት መመዘኛ ዘዴዎችን እና መሳሪያዎችን መምረጥ እና
መጠቀም ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከትምህርት ቤት
መምህራን ድጋፍ ማግኘት እንችላለን። ፍላጎቶችን ለመገምገም አንድ ወይም ብዙ ዘዴዎችን እና
ተስማሚ የሆኑትን መሳሪያዎች መምረጥ እንችላለን:: የበርካታ ዘዴዎች እና መሳሪያዎች
ምሳሌዎች ከዚህ በታች ተብራርተዋል (የካምቦዲያ ትምህርት ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)፡፡

4.2.1. የሰነድ ጥናት /document analysis/


የሰነድ ጥናት ስለ አንድ ማኅበረሰብ መረጃ ለመሰብሰብ ጠቃሚ ዘዴ ነው፡፡ ስለ አካባቢው አስፈላጊ
መረጃ በሰነዶች መልክ አብዛኛውን ጊዜ በአካባቢያዊ ተቋማት ማለትም በመንግሥት ቢሮዎች፣
በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎችና በሌሎች የአከባቢ መስተዳድር እና መንግሥታዊ ያልሆኑ
ድርጅቶች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡ አስፈላጊውን መረጃ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች መሰብሰብ
በተደራጀ መልኩ በየጊዜው እንዲዘምን (update) ማድረግ አለብን። በሰነድ ጥናት እንደሚከተሉት
ያሉ መረጃዎችን መሰብሰብ አለብን።
 የአካባቢ ታሪክ፣ ባሕልና ወጎች  የአካባቢ ሀብቶች (ሰው እና አካላዊ)
 የማኅበረሰቡ ጂኦግራፊ  የሕዝብ ብዛት
 የሀገር ውስጥ ተቋማት እና አገልግሎቶቻቸው  የማንበብ ደረጃ
 የመንግሥት ኤጀንሲዎች፣ ስምና አገልግሎቶቻቸው  የኢኮኖሚ ሁኔታዎች
 የልማት አጋሮች ስም እና አገልግሎቶቻቸው  የአካባቢ ካርታዎች ወዘተ.

4.2.2. ቃለ መጠይቅ (interview)


ከተለመዱት የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች አንዱ ቃለ መጠይቅ ነው። ምን ዓይነት መረጃ
ማግኘት እንደምንፈልግ እና ለዚያ የተለየ መረጃ ምላሽ ሰጪዎች እነማን እንደሆኑ መወሰን
አለብን። ውጤታማ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ብዙ ልምድ ያስፈልገዋል። በቃለ መጠይቁ ወቅት
መልሱን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ስለ ሰው አስተያየትም ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ ከሰዎች ጋር
ለመወያየትና ሀሳባቸውን ለማግኘት ቀደም ብለው ቤተሰቦችን በመጎብኘት ወይም እንደ ክበቦችና
ሻይ ቤቶ ባሉ የሕዝብ መገለገያ ቦታዎች ላይ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንችላለን።

4.2.3. የጽሑፍ መጠይቅ (Questionnaire)


የፅሁፍ መጠይቅን በተመረጡ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለማግኘት ለሰዎች በአካል በመስጠት
ወይም በፖስታ በመላክ መረጃ መሰብሰብ የሚቻልበት ዘዴ ነው፡፡ የግል መረጃ ሊጠየቁ ስለሚችሉ

25
ግላዊ መረጃቸውን ለመጠበቅ ምላሻቸው እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ለጠያቂው ግልጽ
ማድረግ አለብን። መጠይቆችን ካስሞላን በኋላ ሁሉንም መረጃዎች በማሰባሰብ መተንተን
ይገባናል፡፡ ፡

4.2.4. ውይይት እና ስብሰባ


ውይይቶችና ስብሰባዎች ሃሳቦችን ለማፍለቅ፣ መፍትሄዎችን ለመፈተሽና በማኅበረሰቡ ውስጥ
ያሉ ሰዎችን ውሳኝ እንዲሆኑ ለማድረግ ይጠቅማሉ። የተተነተነውን የፅሁፍ መጠይቅ፣ የቃለ-
መጠይቅና የሰነድ ትንተና ሪፖረት በስብሰባ ለውይይት በማቅረብ እንዲዳብር ማድረግ ይቻላል፡፡
ይመከራልም፡፡ የማኅበረሰብ አባላት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እና ከማኅበረሰብ ጉዳዮች ጋር
የተያያዙ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ መደበኛ ስብሰባዎች ሊዘጋጁ ይችላሉ። በአመቻቾች እርዳታ
በነጻነት ጉዳዮችን ለመወያየት መደበኛ ያልሆነ የቡድን ውይይቶችም ማዘጋጀት ይቻላል። መደበኛ
ባልሆኑ ስብሰባዎች ላይ አንድ ሰው እንዲያዳምጥና እንዲከታተል እንዲሁም የውይይቱን ዋና
ዋና ነጥቦች እንዲያጠቃልል መመደብ አለበት። ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው በርካታ የውይይት
ቴክኒኮች አሉ። ለምሳሌ በዝ ቡድን (Buzz Group፣ የፊት ለፊት ውይይት፣ የትኩረት ቡድን
ውይይት (ኤፍ.ጂ.ዲ.)፣ የአዕምሮ ማሟሸት (Brain storming)፣ወዘተ… ናቸው፡፡

4.2.5. አሳታፊ የገጠር ግምገማ /Participatory Rural Appraisal/


የማኅበረሰቡን ፍላጎትና ችግር ለመለየት የማኅበረሰቡን ዕውቀትና ልምድ ለመለየት
የምንጠቀምባቸው ሌሎች በርካታ ዘዴዎች አሉ። አሳታፊ የገጠር ግምገማ (PRA) የአካባቢ
ዕውቀት ላይ አፅንዖት የሚሰጥ እና የአካባቢው ሰዎች የራሳቸውን ግምገማ እንዲያደርጉ፣
እንዲተነትኑ እና ዕቅድ እንዲያወጡ የሚያስችል አሳታፊ አካሄድ ነው።

4.3. ፍላጎቶችን ቅደም ተከተል ማስያዝና ተያያዥ ጉዳዮች


ከፍላጎት ግምገማ በኋላ ለፍላጎቶች ቅድሚያ ለመስጠት የማ.መ.ማ. የአስተዳደር ኮሚቴ በፍላጎት
ዳሰሳ ጥናት ላይ ከተሳተፉ የማኅበረሰቡ አባላት ጋር ተከታታይ ስብሰባዎችን ማዘጋጀት አለበት።
ይህ በስሜታቸው እንድንረዳ ይረዳል፡፡ ስለ ግምገማው ሒደት፣ ከዚህ በፊት ስለተገኙ ልምዶች፣
ስለአካባቢያዊ ፀጋዎች፣ ድጋፍ ሊያደርጉልን ስለሚችሉ ግለሰቦችና አጋር አካላት፣ እንዲሁም
ማኅበረሰቡን በሚመለከቱ ሁሉም መረጃዎችና ችግሮች ላይ ዝርዝር ውይይት መደረግ አለበት፡፡
በመጨረሻም በውይይቶች ላይ በመመስረት የድርጊት መርኃ ግብር ለማውጣት ለፍላጎቶች ቅደም
ተከተል መስጠት አለብን፡፡

26
ምዕራፍ አምስት
5. የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት (Database) ማቋቋም
ዓላማ፡

በዚህ ምዕራፍ መጨረሻ ተሳታፊዎች፡

 የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት ምንነትን መግለፅ ይችላሉ፡፡


 የማኅበረሰብ የመረጃ ቋትን አስፈላጊነት ያስረዳሉ፡፡
 የማኅበረሰብ የመረጃ ቋትን ጠቀሜታ ያደንቃሉ፡፡

የማነቃቂያ ጥያቄዎች

1. የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት ስንል ምን ማለት ነው?


2. የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት ውስጥ የምንዳስሳቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

5.1. የመረጃ ቋት ምንነትና የማደራጀት ሒደት


የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት ለማቀድ፣ ለውሳኔ ለመስጠትና ችግሮችን ለመፍታት በጣም ጠቃሚ
ነው። በሁሉም የማኅበረሰቡ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን መሰብሰብ
አለብን። ከነዚህም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

 ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ
 የማኅበረሰቡ ታሪክ
 የተፈጥሮ ኃብት፣
 ከሕዝብ ጋር የተያያዙ መረጃች (ቁጥር/ብዛት፣ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በኑሮ ደረጃ፣ በሥራ
መስክ፣ ወዘተ.)
 የሚገኙ ተቋማት (ትምህርት ቤት፣ ኮሌጅ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ክሊኒኮች፣ የማኅበረሰብ
አዳራሾች፣ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ ወዘተ…)
 የኢኮኖሚ ሁኔታ (ሙያ፣ ሥራ፣ የኢኮኖሚ ፀጋዎች፣ የድህነት ደረጃ፣ ወዘተ)፣
 የአመራር ዘይቤ
 የመኖሪያ ቤት ንድፍ;
 የመንገድ ግንኙነት

27
 የመብራት፣ የሚዲያ እና የኢንተርኔት አገልግሎት
 አገልግሎት ሰጭ ኤጀንሲዎች እና አገልግሎቶቻቸውን በተመለከተ
 የትምህርት ሁኔታ (የትምህርት ደረጃ፣ በዕድሜ፣ በፆታ፣ እንዲሁም ድምር መረጃ)
 የፋይናንስ ተቋማት
 የጤና እና የንፅህና አጠባበቅ ሁኔታ
 የማኅበረሰብ መሠረተ ልማት
 የሀገር ውስጥ ድርጅቶች፣ ማኅበራት፣ ክለቦች ወዘተ
 የማኅበረሰቡ ችግሮች እና ተግዳሮቶች
 በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ግብዓቶች
 የመንግሥት የሚቀርቡ የድጋፍ ዓይነቶች
 ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ጥበቦች
 የኅብረተሰቡ ጥንካሬ እና ድክመቶች፣
 የልማት አጋጣሚዎችና ስጋቶች፣ ወዘተ…

ከላይ የተጠቀሱት ቦታዎች አጠቃላይ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እንደማኅበረሰቡ ዓውድ እና ነባራዊ


ሁኔታ ሌላ መረጃ መሰብሰብ ያስፈልገን ይሆናል፡፡ የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት በየጊዜው መገመገምና
ከወቅታዊ መረጃዎች ጋር አብሮ መዘመን አለበት፡፡ ለምሳሌ፡- በመጀመሪያ ማኅበረሰቡ የመብራት
አቅርቦት የለውም የሚል መረጃ በመረጃ ቋታችን መዝግበን ከአንድ ዓመት በኋላ የመብራት
አገልግሎት ቢጀምር መረጃው አብሮ መሻሻል አለበት፡፡

5.2. የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት አስፈላጊነት


የማኅበረሰቡን መረጃ መሰብሰብ የማኅበረሰቡንና የሕዝቡን አጠቃላይ ሁኔታ ለመረዳት ይረዳናል።
የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት ስለማኅበረሰቡ ኃብቶች እንድናውቅ እና ስለማኅበረሰቡ ፍላጎቶች፣
ችግሮችና ዕምቅ ፀጋዎች የበለጠ ለማወቅ ይረዳናል። በማኅበረሰብ የመረጃ ቋት በኩል
ስለመንግሥት አገልግሎቶችና ሌሎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለሚሰጡ አገልግሎቶች ወቅታዊ
መረጃ ማግኘት እንችላለን። ይህ የመረጃ ቋት ውሳኔ ለመወሰንና የማ.መ.ማ ዕቅድ ለማውጣት
በጣም ጠቃሚ ነው። የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለበት፣ ስለዚህም
ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

28
5.3. የመረጃ አሰባሰብ ሒደት
ከመንግሥታዊ ምንጮችና ሰነዶች መረጃ ማግኘት እንችላለን፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች
እና የማኅበረሰብ ድርጅቶች ጠቃሚ መረጃ ሊሰጡ ይችላሉ። በማኅበረሰብ የምክክር ስብሰባዎች፣
ቃለ-መጠይቆችን በማካሄድ ወይም የትኩረት ቡድን ውይይቶች የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት
ለማዘጋጀት መረጃ ማግኘት እንችላለን። እንደ መጠይቆች፣ ፎርማት፣ ቼክ ሊስት ወዘተ የመሳሰሉ
መረጃዎችን ለመሰብሰብ ተገቢ መሳሪያዎች መዘጋጀት አለባቸው። የመንግሥት ባለሥልጣናት፣
የትምህርት ቤት መምህራንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች መረጃ ለመሰብሰብ
ተገቢ መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ሊረዱን ይችላሉ። የማኅበረሰብ የመረጃ ቋት ለማ.መ.ማ. ዕቅድ
ማውጣት እና ውሳኔ መስጠት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ሁሉም መረጃዎች ተጠብቀው በማ.መ.ማ.
ውስጥ መታየት እና በየጊዜው መዘመን አለባቸው።

ኮምፒዩተር ካለ ዝግጁ ሆኖ በኮምፒዩተር ውስጥ መቀመጥ አለበት። የማ.መ.ማ. አስተዳደር


ኮሚቴ ሁሉንም መረጃዎች በራሱ መሰብሰብ ላይሆን ይችላል። ስለ ማኅበረሰቡ ተጨባጭ
ችግሮችና ተግዳሮቶች ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የማኅበረሰቡ አባላት የራሳቸውን የማኅበረሰብ
መረጃ በመሰብሰብ ላይ እንዲሳተፉ ዕድሎችን መስጠት አለብን። መረጃ ስንሰበስብ ከሚከተሉት
አካላት ዕርዳታ ማግኘት እንችላለን (የካምቦዲያ ትምህርት ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)፤

 የማ.መ.ማ (CLC) ተሳታፊዎች/ተማሪዎች


 የትምህርት ቤት እና የኮሌጅ መምህራን
 የትምህርት ቤት እና የኮሌጅ ተማሪዎች
 የአካባቢው የመንግሥት ባለስልጣናት
 የአካባቢው መሪዎች
 የሀገር ውስጥ ክለብ እና የባሕል ተቋማት አባላት
 ፍላጎት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች
 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎች ወዘተ.

29
ምዕራፍ ስድስት
6. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት አደረጃጀትና አስተዳደር
ዓላማ

ውድ ተሳታፊዎች ከዚህ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ፡

1. የማህረሰብ መማማሪያ ማዕከል ድርጅታዊ መዋቅር ምን መምሰል እንዳለበት ይረዳሉ፡፡


2. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ላይ በአስተዳደር ደረጃ የሚሳተፉ አካላትን ይለያሉ፡፡

የማነቃቂያ ጥያቄዎች (ተሳታፊዎች በቡድን ሆነው የሚወያዩት)

1. የማህረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ድርጅታዊ መዋቅር ምን መምሰል አለበት ብላችሁ


ታስባላችሁ?
2. በእያንዳንዱ መዋቅር ውስጥ ያሉትስ አካላት ሀላፊነት እና ግዴታዎች ምን ምን ቢሆኑ
ብላችሁ ታስባላችሁ

6.1. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከሎች አስተዳደራዊ መዋቅር


ድርጅታዊ መዋቅር እንደ ተግባር ድልድል፣ ቅንጅት እና ቁጥጥር ያሉ ተግባራት የድርጅቱን
ዓላማ ለማሳካት እንዴት እንደሚመራ ይገልጻል። ድርጅታዊ መዋቅር በድርጅታዊ ድርጊቶች ላይ
ተጽእኖ ያሳድራል፤ እንዲሁም መደበኛ የአሠራር ሒደቶችና የዕለት ተዕለት ሥራዎች
የሚያርፉበትን መሰረት ይጥላል፡፡ የትኞቹ ግለሰቦች በየትኛው የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች
እንደሚሳተፉ እና የእነሱ አመለካከቶች የድርጅቱን ተግባራት ምን ያህል እንደሚቀርፁ ይወስናል።
ድርጅታዊ መዋቅር ግለሰቦች ድርጅታቸውንና የድርጅቱን ሁኔታ የሚያዩበት መስታወት ወይም
ዕይታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ለማ.መ.ማች ውጤታማ ዕቅድ ማውጣትና ማስተዳደር ተገቢ የሆነ የድርጅት መዋቅር መፍጠር
አስፈላጊ ነው። ይህ መዋቅር ከማኅበረሰቡ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የአካባቢ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ-
ባሕላዊ ባህሪያት ጋር የሚስማማ እና ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት፡፡ የማኅበረሰብ መማማሪያ
ማዕከላትን በየጊዜው ማጠናከር እና አስተዳደሩን ማሻሻል አለበት፡፡ እሸቱ እና አማኑኤል (2017
እ.ኤ.አ.) እንደገለፁት ለትልቅ የማ.መ.ማ. ተስማሚ ሊሆን የሚችል የድርጅታዊ መዋቅር ዓይነተኛ
ምሳሌ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

30
የወረዳ ትምህርና ስልጠና ቦርድ

የቀበሌ ትምህርና ስልጠና ቦርድ

የማ.መ.ማ የአስተዳደር ኮሚቴ

የማ.መ.ማ. አስተባባሪ ጸሐፊ

የክህሎት ሥልጠና የህዝብ ተሳትፎ


ንብረት ክፍል
አስተባባሪ አስተባባሪ

አመቻች

ምስል 1 የማኅበረሰብ መመማሪያ ማዕከል ድርጅታዊ መዋቅር

6.2. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል አስተዳደር


የማ.መ.ማ. የሚባለው ህንፃው አይደለም፡፡ በተቋሙ የሚመደቡ ባለሙያዎች ለማ.መ.ማ.
ውጤታማነት ጉልህ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን ለውጥ ለማማጣ የኮሚቴ
አባላትና የማ.መ.ማ. አስተባባሪዎች ፈጣንና ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ የማ.መ.ማ የአጠቃለይ
ማኅበረሰቡን ተሳትፎ የሚጠይቁ በመሆናቸው የሚመሰቡ አስተባባሪዎችና የኮሚቴ አባላት ሕዝብ
የማስተባበር ዐቅም፣ ብቃትና ልምድ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡

በማኔጅመንት ሳይንስ እንደሚገለፀው የሚከተሉት የአመራር ሒደት ትራንስፎርሜሽናል መሆን


አለበት፡፡ ይህም ማለት ለለውጥ የተዘጋጁና የሚመሯቸውን ሰዎች ማነሳሳት የሚችሉ የእነሱን
ተነሳሽነት በሌሎች ላይ የሚያጋቡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሰዎች ፈርተዋቸው እንዲታዘዙ ሳይሆን
ወደዋቸው እንዲከተሏቸው የማድረግ ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

31
በዚህ ረገድ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን ተግባራዊ ለማድረግ የተዋቀረው
ቦርድና የቴክኒክ ኮሚቴ የታየበት ዓይነት መፋዘዝና የሥራ መገፋፋት በማ.መ.ማ ሊደገም
አይገባውም፡፡ ሁሉም ባለድርሻ የየድርሻውን ተግባር ቆጥሮ መረከብ ያለበት ሲሆን ወደ ትግበራ
ከመገባቱ በፊትም ሁሉም የማ.መ.ማ የኮሚቴ አባላት፣ አስተባባሪዎች፣ አመቻቾች፣ ንብረት
ክፍል እና ጸሐፊ ማን ምን መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ዝርዘር የሥራ መግለጫ ሊሰጣቸው
ይገባል፡፡

6.3. የአስተዳደር አካላት ተግባርና ኃላፊነት


የማ.መ.ማ. አስፈፃሚ አካላት ማለትም የወረዳ እና የቀበሌ የቦርድ አመራሮች፣ የማ.መ.ማ፣
አስተባባሪዎች፣ የዘርፍ አስተባባሪዎች፣ አመቻቾች፣ እና ሌሎች ፈፃሚዎች ዝርዝር ተግባርና
ኃላፊነታቸው እንደሚቋቋመው የማ.መ.ማ. መጠን በግልፅ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ
የማ.መ.ማ. አንድ አስተባባሪ እና አመቻቾች ብቻ ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የሕዝብ ግንኙነት
ሥራውን ማን እንደሚሠራው የሥልጠና ሒደቱን ማን እንደሚያስተባብረው በመጀመሪያ
ካልተገለፀ የሥራ መገፋፋት ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ሥራን ስለሚያጓትት በበጎ ፈቃድ የሚሠሩ
የማኅበረሰቡ አባላትን ተነሳሽነት እና ሞራል ይጎዳል፡፡ በተዘዋዋሪ ደግሞ የማዕከሉን ሁለንተናዊ
እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ በመጣል የማ.መ.ማ. ዓላማ እንዳይሳካ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ለመነሻ
ይሆን ዘንድ እሸቱ እና አማኑኤል (2017 እ.ኤ.አ.) ያዘጋጁትን የማ.መ.ማ አስተዳደር ኮሚቴንና
የማ.መ.ማ አስተባባሪዎችን ተግባርና ኃላፊነት ዝርዘር እንደሚከተለው ተቀምጧል፡፡

የሥራ መደብ ተግባር እና ኃላፊነት


የማ.መ.ማ. አስተባባሪ  የማ.መ.ማ ሥራውን በሚገባ እያከናወነ መሆኑን ያረጋግጣል፣
 በድርጊት መርኃ ግብሩ መሰረት የተለያዩ ተግባራትን ይመራል ያስተባብራል፣
 ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እንዲሁም
ከማኅበረሰብ ዓቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት ይመሰርታል፤ ይተባበራል፣
 የማ.መ.ማ. መርኃግብሮች ያመቻቻል፣ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣
ይገመግማል፣
 የተግባራትን አፈፃፀምና ሌሎች ሁኔታዎችን መዝግቦ ያስቀምጣል፣
 ሪፖርት ያዘጋጃል ለሚመለከተው ክፍል ያደርሳል፣
 ከማ.መ.ማ. ተሳታፊዎች ጋር በመደበኛው መርኃ ግብር መገናኘቱን ይቀጥላል፣
 የማ.መ.ማ. ኃብት የማሰባሰብ ሒደት ያስተባብራል
የማ.መ.ማ. አስተዳደር  የማ.መ.ማ. መርኃ ግብር ያወጣሉ ያስፈፅማሉ፣
 ድጋፍ ለማግኘት የቅስቀሳ ሥራ ይሰራሉ፣ ኃብት ያሰባስባሉ፣
ኮሚቴ
 የማ.መ.ማ፣ ተግባራትን ይከታተላሉ፣ ይቆጣጠራሉ፣ ይገመግማሉ፣
 ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚደረግን ትስስር ይደግፋሉ ያስተባብራሉ፣
 የማኅበረሰቡን ፍላጎት ያጠናሉ፣
 የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅድ ያዘጋጃሉ
 የማበረሰቡን ተሳትፎ ያረጋግጣሉ፡፡

32
6.4. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል ዕቅድ ዝግጅት
ወጪ ቆጣቢ መሆናቸውንና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ
የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ተግባት በአግባቡ ማቀድና በተደራጀ አግባብ መተግበር እጅግ
አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንም ለማድረግ የማኅበረሰብ መማማሪያ ከመመስረቱ በፊት የማኅበረሰቡ
አጠቃላይ አባላት ስለ መማማሪያ ማዕከሉ ራዕይና ግብ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን
ለማድረግም የማኅበረሰቡን አጠቃላይ ገጽታ እንዲሁም ዐቅም ማወቅ የሚጠይቅ ሲሆን ይህንንም
የማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ውድ ሠልጣኞች ወደ ቀጣይ ክፍል ከመግባታችሁ በፊት ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች መልሱ፡፡

የማነቃቂያ ጥያቄዎች
1. የተለመዱ የማህበረሰብ መማማሪያ ማዕከል የእቅድ ክፍሎች ምን ምን ናቸዉ?
2. በማ.መ.ማ ምን ምን ተግባራት ሊከናወኑ ይችላሉ ብላችሁ ታስባላችሁ?
3. በማ.መ.ማ ውስጥ የማዕከሉን እቅድ የማዉጣት ኃላፊነት የማን ይመስላችኋል?

የማ.መ.ማ.ን ዕቅድ ማዘጋጀት የማዕከሉ አስተዳደር ኮሚቴ ዋና ተግባር ነው፡፡ የማ.መ.ማ. ዕቅድ
ሲዘጋጅ የማኅበረሰቡ ፍላጎት፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ሁኔታ እንዲሁም የማ.መ.ማ. ተሳታፊ
የሚሆኑ ሰዎች የኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም
የሚጠበቀው የማኅበረሰብ ተሳትፎ ደረጃና በፕሮግራም ትግበራ ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ
እንቅፋቶችን ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡፡

የማ.መ.ማ. (የCLC) ፕሮግራሞች የማኅበረሰቡ ፕሮግራም ስለሆኑ ስኬታማነታቸውም


በማኅበረሰቡ አባላት ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ነው። በጠቅላላው የዕቅድ ሒደት ውስጥ
የማኅበረሰብ ተሳትፎ ውጤታማና ቀልጣፋ የፕሮግራም ዲዛይን ለማድረግ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡
ይህም በመጨረሻ ወደ ፕሮግራሙ ስኬት ይመራል።

የማ.መ.ማ. ዕቅድ ሲዘጋጅ የማዕከሉ የአስተዳደር ኮሚቴ፡ (1) የአካባቢውን የመንግሥት


መስሪያቤቶች፣ (2) መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ እና (3) የልማት አጋሮችን ማማከርና
ድጋፋቸውን ማግኘት ይኖርበታል፡፡ የማ.መ.ማ. ዕቅድ በተናጥል መዘጋጀት የለበትም፡፡ የተቀናጀ
ዕቅድ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጥንካሬ እና አገልግሎት ግምት ውስጥ በማስገባት ለማዕከሉና
ለተጠቃሚዎቹ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አካባቢያዊ ፀጋዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀምና ሀገር

33
በቀል ዕውቀትን ከፍ ለማድረግ የማዕከሉን ዕቅድ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ማቀናጀት
ያስፈልጋል።

የማ.መ.ማ. ዕቅድ ሲያዘጋጅ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የህዳጣን ቡድኖችን


ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታቸውን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም እንደሌሎቹ ተመሳሳይ መብቶች
እና ልዩ መብቶችን ለማግኘት እንዲችሉ ልዩ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ማ.መ.ማ.
ለተገለሉ ቡድኖች ልዩ ፍላጎቶቻቸውን፣ ልምዶቻቸውን፣ ችሎታቸውን፣ ምኞታቸውን፣
ባሕላቸውን እንዲሁም ነባር ልምዶቻቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መርኃ ግብሮችን ማቀድ
አለበት።

6.4.1. የዕቅድ ዝግጅት ደረጃዎች


የማ.መ.ማ. ዕቅድ በሚዘጋጁበት ጊዜ የሚከተሉት የዕቅድ ደረጃዎች ግምት ውስጥ መግባት
አለባቸው።

1. የማ.መ.ማ. መርኃ ግብር ግብና ዓላማ ማውጣት፡ የማ.መ.ማ. መርኃ ግብር ፕሮግራሞች
ግብና ዓላማ ከማኅበረሰቡ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በተገኘ መረጃ መሰረት መቀረፅ አለባቸው።
2. የመርኃ ግብር አተገባበር አጠቃላይ ስልቶችን መወሰን፡ ጥንካሬዎችን፣ ድክመቶችን፣
ዕድሎችን ስጋቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የማ.መ.ማ. ኮሚቴ አባላት የማ.መ.ማ.
መርኃ ግብር አተገባበር አጠቃላይ ስትራቴጂዎችን በመወሰን በተገኘው መንገድ ተፈላጊ
ውጤቶችን ማግኘት አለባቸው። የማ.መ.ማ. ዋና ዋና መርኃ ግብሮች እንዴት ተግባራዊ
እንደሚያደርግ መወሰን አለበት።

ለምሳሌ የሚከተሉትን ስልቶች መከተል ይችላል፡፡

 የማመማ መርኃ ግብር በመንደፍና በመተግበር ላይ የመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ


ድርጅቶች እና የልማት አጋሮችን ማካተት፣
 ሴቶችን፣ አናሳ (ህዳጣን) ብሔረሰቦችን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች፣ ማንበብና መጻፍ
የማይችሉ፣ አካል ጉዳተኞች ወዘተ. የማመማ ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች አድርጎ መምረጥ
 ለመርሃ ግብሩ ዘላቂነት የረጅም ጊዜ ኮርፖሬት የገንዘብ ድጋፍን ማበረታታት፣
 የገቢ ማስገኛ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት የማመማን ካፒታል ማሳደግ።

3. ከተሞክሮ መማር፡ የማ.መ.ማ. መርኃ ግብሮች ዕቅድ ከመጀመራችን በፊት ቀደም ሲል


በማ.መ.ማ. ወይም በወረዳው ውስጥ ባሉ ሌሎች ማ.መ.ማ.ቶች የተተገበሩ ተመሳሳይ

34
መርኃ ግብሮችን ውድቀቶችና ስኬቶች መገምገም የተሻለ ነው። ካለፈው ልምድ የተገኙ
ትምህርቶችን መተንተንና መመርመር እንዲሁም የተከተሉትን ስትራቴጂዎች
ውጤታማነት ማረጋገጥ በጣም ውጤታማ ነው። እነዚህ ግንዛቤዎች ስህተቶችን
ለማስወገድ እና ተገቢ የአተገባበር ስልቶችን ለመለየት ይረዱናል.
4. የተወሰኑ የአተገባበር ስልቶችን መወሰን፡ እያንዳንዱ ፕሮግራም የራሱ ባህሪያት አሉት።
በእያንዳንዱ መርኃ ግብር ዓላማዎችና ተግባራት ላይ በመመስረት, ልዩ የትግበራ ስልቶች
መወሰን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ፡ የማ.መ.ማ. የአስተዳደር ኮሚቴዎች ተሳታፊዎችን
በማ.መ.ማ. ለማሰልጠን በማ.መ.ማ. የክህሎት ሥልጠናዎችን ከማደራጀት ይልቅ
በአካባቢው ካለ የክህሎት ማሰልጠኛ ተቋም (ቴክኒክና ሙያ) ጋር ግንኙነት መፍጠር
አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡
5. ከሀገራዊ ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ጋር መጣጣም፡ የማ.መ.ማ. መርኃ ግብሮች ከሀገራዊና
ከአካባቢያዊ ልማት ዕቅዶች ጋር ወጥነት ባለው መልኩ መቀረጽ አለባቸው። ሌሎች
ባለድርሻ አካላት የማይሠሩባቸውን ተግባራት ማቀድ እንችላለን። በዚህ ረገድ ከመንግሥት
አካላት እና ከአካባቢው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
6. ዋና እና ንዑስ ተግባራትን መወሰን፡ መርኃ ግብሩን ለመተግበር የተለያዩ ተግባራትን
ማከናወን ያስፈልጋል። የማ.መ.ማ. አስተዳደር ኮሚቴ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ
የተካተቱ ተግባራትንና ንዑስ ተግባራትን መወሰን አለበት።
7. የሰው ኃብት ዕቅድ ማውጣት፡- ለማንኛውም መርኃ ግብር ትግበራ የሰው ኃይል በጣም
አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የመረዳት (ሊትሬሲ) ማሰልጠኛ መርኃ ግብር ለመጀመር
በማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከሉ ምን ያህል አመቻቾችና አሠልጣኞች ለምን ያህል ጊዜ
እንደሚያስፈልጉ መወሰን አለበት። እንዲሁም የትምህርት ብቃታቸውና ዕውቀታቸው ምን
እንደሚሆን፣ እንዴት እንደሚቀጠሩና ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ወዘተ…
መወሰን አለበት፡፡
8. የበጀትና የግብአት ዕቅድ ማዘጋጀት፡- ለማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ምን ዓይነት
የበጀት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ፣ ከየትኞቹ ምንጮች እንደሚገኝ እንዲሁም ገንዘቡ እንዴት
እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚውል በግልፅ መታቀድ አለበት።
9. የሰው ኃይል ልማት ዕቅድ ማውጣት፡ ዋና ዋና ተግባራትን የሚያከናውኑ እንዲሁም
የድጋፍ ሥርዓቱን የሚመሩ ሰዎች ተለይተው ሊሠለጥኑ ይገባል። የፈፃሚዎችና የድጋፍ
ሰጪ ባለሙያዎች ሥልጠና በዝርዝር ሊታቀድ ይገባል፡፡

35
10. የድርጊት መርኃ ግብር ማዘጋጀት፡- የድርጊት መርኃ ግብሩን ለማስፈጸም የሚከናወኑ
ተግባራትን በዝርዝር ይገልፃል፡ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ መተግበር ያለባቸው ዋና ዋና
ተግባራት ምን ምን እንደሆኑ፣ እነዚህ ተግባራት መቼ እንደሚከናወኑ እና እነዚህን
ተግባራት ለማከናወን ኃላፊነቱን የሚወስደው ማን እንደሆነ የሚገልፅ ዝርዝር የድርጊት
መርኃ ግብር ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
11. አስተዳደራዊ ስልቶችን (Management strategies) ማዘጋጀት፡- ዕቅድ ስናወጣ አጠቃላይ
የመርኃ ግብሩን አፈፃፀም ሒደት እንዴት እንደምንቆጣጠርና እንደምንመራ መወሰን
አለብን። የማ.መ.ማ. መርኃ ግብሮችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ
በተለያዩ ኤጀንሲዎች መካከል ትክክለኛ ቅንጅትና ትስስር ዘዴዎች መወሰንና በዕቅዱ
ውስጥ ማካተት አስፈላጊ ነው።
12. የመርኃ ግብሩን ዘላቂነት ማቀድ፡- ዘላቂነት ያለው ዕቅድ ለፕሮግራሙ የመጨረሻ ስኬት
በጣም አስፈላጊ ነው። የማ.መ.ማ. የማኔጅመንት ኮሚቴ የመርኃ ግብሮቹን ዘላቂነት
የሚያረጋግጡ ስልቶች መቀየስ አለበት።
13. የግምገማ ዕቅድ ማዘጋጀት፡- በዚህ የዕቅድ ደረጃ የተግባር ክንውኖች ስኬትና ግስጋሴን
እንዴት እንደምንከታተል፣ እንደምንቆጣጠር እንዲሁም መቼ ምን ዓይነት የማስተካከያ
እርምጃዎች እንደምንወስድ እና የመርኃ ግብሮቹ ተፅዕኖዎች መቼና እንዴት
እንደሚገመገሙ መወሰን አለብን። ተግባራት ከመጀመራቸው በፊት የክትትል፣ የግምገማ
እና የሪፖርት አቀራረብ ሒደት መነደፍ አለበት።

6.4.2. የተለመዱ የማ.መ.ማ. ዕቅድ አካላት


የአብዛኞቹ የማ.መ.ማ. እቅዶች የሚከተሉትን ጉዳዮች ያካተቱ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡

1. የመርኃ ግብሩ ስም 9. የትግበራ ስልቶች


2. የመርኃ ግብሩ አስፈላጊነት 10. አስፈላጊ የገንዘብ ምንጭ
3. የመርኃ ግብሩ ግብ 11. የሚፈለግ የሰው ኃይል
4. የመርኃ ግብሩ ዓላማዎች 12. አስፈላጊ የሠራተኞች ሥልጠና
5. የመርኃ ግብሩ ቦታ 13. በጀት
6. የመርኃ ግብሩ የትግበራ ጊዜ 14. የትግብራ ዕቅድ
7. የመርኃ ግብሩ ተጠቃሚዎች 15. ቁጥጥር፣ ክትትልና ግምገማ ዕቅድ
8. የመርኃ ግብሩ ተግባራ

36
ምዕራፍ ሰባት
7. የማ.መ.ማ፣ ሠራተኞችን ዐቅም መገንባት
የማነቃቂያ ጥያቄ

1. የዐቅም ግንባታ ዘዴዎችን ዘርዝሩ?


2. የማ.መ.መ የዐቅም ግንባታ ዘዴዎች በማን ይዘጋጃሉ?

በማ.መ.ማ. ውስጥ ብቃት ያላቸውና የሰለጠኑ ሠራተኞችንና በጎ ፈቃደኞችን እንዲኖሩ ለማድረግ


ቀጣይነት ያለው የዐቅም ግንባታ መርኃ ግብር መዘርጋት አስፈላጊ ነው። ዐቅምን ማሳደግ
ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን፣ ድርጅቶችን፣ ትስስሮችንና ተቋማትን አፈጻጸማቸውን ለማሻሻል
የማጠናከር አካሄድ ነው። እንደ ዩኔስኮ ኢንስቲትዩት ፎር ላይፍ ሎንግ ለርኒንግ (2017 እ.ኤ.አ.)
ከሆነ ብዙውን ጊዜ የትምህርትና ሥልጠና ዕድል ለአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት መሰጠት
እንዳለበት የሚታሰብ ቢሆንም፣ የማ.መ.ማ ስኬታማ እንዲሆንና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ
የፖሊሲ አውጪዎችን፣ የማኅበረሰብ ድርጅቶች ሠራተኞችን፣ የማኅበረሰብ ትምህርት
ባለሙያዎች፣ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ዐቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ በርካታ
ጥናቶች ያሳያሉ።

የማ.መ.ማ. ሠራተኞችን ዐቅም በማሳደግ የማኅበረሰቡን ሰዎች ችግር የመለየት እና ተገቢውን


የድጋፍ ስልቶችን የመወሰን አቅማቸውን ማጠናከር እንችላለን። በተጨማሪም የዐቅም ግንባታ
መርኃ ግብር የተሳታፊዎች በራሳቸው እንዲተማመኑ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ለራሳቸው፣
ለቤተሰባቸው እና ለማኅበረሰባቸው ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ የማድረግ ኃይልን ይሰጣል።
የዐቅም ግንባታ ዕቅድ ስናዘጋጅ የሚከተሉትን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን (የካምቦዲያ
ትምህርት ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)

 የዐቅም ግንባታ ሥራ ቀጣይነት ያለው ሒደት እንጅ አንዴ የሚከናወን አይደለም፣


 የዐቅም ግምገማ እንደ የዐቅም ግንባታ የመጀመሪያ ደረጃ ነው፣
 ያለፈ ልምድንና ዕውቀትን እውቅና መስጠትና ከሱ መነሳት አስፈላጊ ነው፣
 ከዐቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ ተግባራትን ከማኅበረሰቡ፣ ከድርጅቶች፣ ወይም ከግለሰቦች
ፍላጎት ጋር ማዛመድ፣
 የልምድ አጠቃቀም ስልትን ከፍ ማድረግ፣
 ድርጅታዊና የመርኃ ግብር ዘላቂነት የዐቅም ግንባታ መሪ መርህ ነው፡፡

37
 ከዐቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ ተግባራትን በየጊዜው መከታተልና መገምገም አስፈላጊ ነው።

7.1. የዐቅም ግንባታ ድጋፍ ደረጃዎች


1. የዐቅም ክፍተትን መተንተንና መወሰን
2. መርኃ ግብር መንደፍ
3. መርኃ ግብሩን ማካሄድ
4. መርኃ ግብሩን ግምገማ

7.2. የዐቅም ግንባታ ዘዴዎች


የማ.መ.ማ ዕቅድ አውጪዎችና አዘጋጆች በቂ ግብአት እና ዕውቀት ካላቸው የዐቅም ግንባታ
ድጋፎችን በራሳቸው ማዘጋጀት ይችላሉ። ሌላው የዐቅም ግንባታ ድጋፎችን የሚቆጣጠርበት
መንገድ የልማት አጋሮችን ማነጋገር እና ለዐቅም ግንባታ ተመሳሳይ ተግባራት መኖራቸውን
ማረጋገጥ ነው። በዚህ ጊዜ የማ.መ.ማ. የማኔጅመንት ኮሚቴ ለዐቅም ግንባታ ሰዎችን ወደ ሌላ
ድርጅት መላክ ይችላል። ለዐቅም ግንባታ ሥልጠና ማደራጀት በጣም የተለመደ ዘዴ ነው። የ
ማ.መ.ማ. ሠራተኞችን ዐቅም ለማዳበር ሌሎች ብዙ ቴክኒኮችን መጠቀም እንችላለን። ለዐቅም
ግንባታ ጠቃሚ ቴክኒኮች ዝርዝር የሚከተለው ነው።

 ሥልጠና  ተግባራዊ ጥናትና ምርምር

 ወርክሾፕ  ምልከታና ተሳትፎ

 ስብሰባ  ትብብር፣ ትስስርና አጋርነት

 ማማከር (ሜንተሪንግ)  የአቻ ትምህርት

 ትምህርታዊ ጉብኝት  የሚዲያ ትምህርት

 ውይይት  የሚነበቡ ሰነዶችን ማዘጋጀት

የዐቅም ግንባታ ተግባራትን ተፅእኖ በማሳደግ በማኅበረሰብ ደረጃ የዐቅም ማጎልበቻ ተግባራትን
ውጤታማነት ለማሳደግ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ቴክኒኮች አሉ (የካምቦዲያ ትምህርት
ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)። እነዚህም፡-

 ያለፉትን የዐቅም ማጎልበቻ ተግባራት ገምግሞ ትምህርት መውሰድ፣


 አዳዲስ ድጋፎችን ለመንደፍ የማኅበረሰቡ አባላት ቀድመው የሚያውቁትን ነገር እውቅና
መስጠት፣
 አዳዲስ ክህሎቶችንና አቅሞችን ለመለማመድ ዕድል መስጠት፣
 ውጤታማነቱን ለማወቅ የዐቅም ማጠናከሪያ ሥራዎችን መከታተል እና መገምገም
38
ምዕራፍ ስምንት
8. የማኅበረሰብ ንቅናቄ፣ ተሳትፎና ባለቤትነት
ውድ ሰልጣኖች በዚህ ምዕራፍ ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ለማሳካት ሰፋ ያለ ትንታኔ የያዙ
ጽሑፎችን አቅርበንላችኋል፡፡ በዚህም በመጀመሪያው ክፍል ስለማኅበረሰብ ተሳትፎ ምንነትና
ደረጃዎች፣ በመቀጠል ስለ ማኅበረሰብ ንቅናቄ እንዲሁም በመጨረሻ ስለ ኃብት ማሰባሰብና ኃብት
አስተዳደር በዝርዝር አቅርበንላችኋል፡፡

የምዕራፉ ዋና አላማ፡

ሰልጣኞች ይህን ምዕራፍ እንዳጠናቀቁ፡-

1. በማ.መ.ማ. የህዝብ ተሳትፎ ደረጃዎችን ይለያሉ፡፡


2. የማ.መ.ማ. ውጤታማነት የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር የሚቻልባቸውን ዘዴዎች
ይገነዘባሉ፡፡
3. የማ.መ.ማ. ኃብት ማመንጨት የሚቻልባቸውን ዘዴዎች ይረዳሉ፡፡
4. ወጭ ቆጣቢ የኃብት አስተዳደር ሥርአት በማ.መ.ማ እንዴት እንደሚተገበር
ይገነዘባሉ፡፡

የማነቃቂያ ጥያቄዎች

1. የማኅበረሰብ ንቅናቄ ማለት ምን ማለት ነው?


2. የማኅበረሰብ ንቅናቄ በሚሠራበት ሰዓት እነማን መሳታፍ አለባቸው?
3. የማኅበረሰብ ንቅናቄ መፍጠሪያ ዘዴዎች ምን ምን ናቸው?

8.1. የማኅበረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊነትና ደረጃዎች


የማ.መ.ማ. በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኝና የኅብረተሰቡን ሰዎች የሚያገለግል ተቋም ነው (እሸቱ
እና አማኑኤል፣ 2017 እ.ኤ.አ.)። የማኅበረሰቡን ሙሉ ባለቤትነት ማረጋገጥ ደግሞ የማ.መ.ማ.ን
ቀጣይነት (sustainability)1 ለማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው።

1
የማመማ ቀጣይነትን በተመለከተ በመጨረሻዉ ምዕራፍ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

39
እንደ እሸቱ እና አማኑኤል (2017 እ.ኤ.አ.) ገለፃ በማኅበረሰብ አቀፍ እንቅስቃሴዎች ውስጥ
የማኅበረሰቡ አባላት የተሳትፎ ደረጃ በሦስት ይከፈላል፡፡ እነዚህ የተሳትፎ ደረጃዎችም
እንደሚከተለው ተብራርተው ቀርበዋል፡፡

1. የማኅበረሰቡ ተግባራት በውጭ ሰዎች ወይም በማኅበረሰቡ መሪዎች ሲጀመር የማኅበረሰቡ


አባላት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የማኅበረሰብ ሰዎች እንቅስቃሴዎቹን እንዲቀላቀሉ
ተጋብዘው ወይም ለማ.መ.ማ. አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ተጠይቀው የሚሳተፉበት የተሳትፎ
ደረጃ ነው። ይህ በተለይ አዳዲስ ሀሳቦችና ተግባራት ወደ ማኅበረሰቡ ሲመጡ የተለመደ
ነው። የማ.መ.ማ. አስተባባሪዎች የማኅበረሰቡን አባላት ስለአዲሱ ሃሳብና ተግባር
እንዲያውቁና ለመሳተፍ ፍላጎት እንዲኖራቸው ለማድረግ የተለያዩ ቴክኒኮችን (ምሳሌ፡-
የጅምላ ስብሰባ እና ዘመቻዎች) በመጠቀም ማነቃነቅ አለባቸው፡፡ ስለማ.መ.ማ. እና
ስለሚከናውኗቸው ተግባራት ጠቃሚነት ሰዎችን ለማሳመን የአዳዲስ ክህሎቶችና
ችሎታዎች ሠርቶ ማሳያ አስፈላጊ ነው። የማኅበረሰብ ንቅናቄ ቀጣይነት እንዲኖረው
ያስፈልጋል። በዚህ ደረጃ የማኅበረሰቡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል የሚባሉት በስብሰባዎች ላይ
በመገኘታቸው ብቻ ነው።
2. የማኅበረሰቡ አባላት በነጻነት ይሳተፋሉ፡፡ የማኅበረሰብ ነዋሪዎች በማ.መ.ማ.
እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይበልጥ እየተሳተፉ ሲሄዱ ግንዛቤያቸው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ቀስ
በቀስ መሳተፍ የሚፈልጉባቸውን ተግባራት መምረጥ ይጀምራሉ። የማ.መ.ማ.
አስተባባሪዎች ተገቢውን መረጃ ሊሰጡና ሰዎች ስለሌላ የተሻለ ተግባር እንዲያስቡ
ሊያበረታቱ ይችላል። ማድረግም ይፈልጋሉ። ይህ በማ.መ.ማ. እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ
በማድረግ የማኅበረሰቡ አባላት በነፃነት ውሳኔዎችን ማስተላለፍ የሚችሉበት የተሳትፎ
ደረጃ ነው፡፡
3. የማኅበረሰቡ አባላት በራሳቸው ተነሳሽነት ተግባራትን ማቀድና ትግበራውን መወሰን
ሲጀምሩ የማ.መ.ማ. በማኅበረሰቡ ባለቤትነት መመራት ጀምሯል ማለት እንችላለን።
የማ.መ.ማ. የአስተዳደር ሥራ በአደራጁ ከተመደበው ሥራ አስኪያጅ ወደ አመቻች
(የማኅበረሰቡን ተግባራት ወደ ሚያስተባብር) ሊሸጋገር ይችላል። በዚህ ደረጃ ተሳትፎ
የሚያደርጉ የማኅበረሰቡ አባላት የማ.መ.ማ.ን ስኬት ብቻ ሳይሆን የወደፊት ተግባራትን
በተሻለ ሁኔታ ለማቀድና ለማስተዳደር ማንኛውንም ችግሮችና ውድቀቶችን የመፍታት
ሃላፊነት ይወስዳሉ።

40
የማ.መ.ማ. አስተባባሪዎች ስለእነዚህ የተለያዩ የተሳትፎ ደረጃዎች ማወቅና ሁሉም በማኅበረሰቡ
ውስጥ ያሉ ሰዎች በመጨረሻ የውሳኔ አሰጣጡ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ መሞከር አለባቸው
(እሸቱ እና አማኑኤል, 2017 እ.ኤ.አ.)።

8.2. የማኅበረሰብ ንቅናቄ አጋሮች


ማኅበረሰቡን ማሰባሰብ ቀላል ሥራ አይደለም። የማ.መ.ማ. አስተዳደር ኮሚቴ ብቻውን ማድረግ
አይችልም። ማኅበረሰቡን በማስተባበር ሌሎች አጋር አካላትን ማሳተፍ አለብን። ለአብነትም፡-

የሀይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች፣


የአካባቢው የበጎ ፈቃድ ማኅበራ (ካሉ)፣
የአካባቢ ባለስልጣናትና የመንግሥት ተቋማት፣
የመንግሥት የኤክስቴንሽን ሠራተኞች (ጤና፣ ግብርና፣ ወ.ዘ.ተ.)፣
በአካባቢው ያሉ የትምህርት ተቋማት ኃላፊዎችና ተማሪዎች፣
ሃይማኖት ተቋማት፣
የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባላቶቹ፣
የባሕል ቡድኖች፣
የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማኅበረሰብ
ንቅናቄ ሥራዎች ማሳተፍ ለኅብረተሰቡ የተቀናጀ የልማት ዕቅድ ለማዘጋጀትም ይረዳናል።
እንዲሁም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለማ.መ.ማ. መርኃ ግብሮች ድጋፍ
እንዲያደርጉና እንዲሰሩ ለማሳመን እንደ ግፊት ቡድን ሆነው ሊያገለግሉም ይችላሉ።

8.3. የማኅበረሰብ ንቅናቄ ዘዴዎች


በተለያዩ ዝግጅቶች የማኅበረሰቡ አባላት አብረው እንዲሰሩ ማድረግ ስለማ.መ.ማ. ግቦች፣
ዓላማዎች፣ እና ተግባራት እንዲያውቁ ለማድረግ ሰፊ ዕድል ሊፈጠር ይችላል። እያንዳንዱ
ማኅበረሰብ የየራሱ ባህሎች እና ወጎች አሉት። ያለውን ባሕልና ልምድ በማክበር የሚከተሉትን
ዝግጅቶች በማዘጋጀት የማኅበረሰብ ንቅናቄ መፍጠር እንችላለን።

 የተለያዩ ትርኢቶች፣  ጥያቄና መልስ ውድድሮች፣

 ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣  በማስታወቂያ ሰሌዳ፣ ፖስተሮችና

 የፊልም ፌስቲቫሎች፣ ባነሮች ማሳየት፣

 ክርክሮች፣  የግድግዳ ጽሑፎችና ሥዕሎች፣

41
 የቤት ለቤት ዘመቻዎች፣  የእግር ጉዞዎች እና ሒደቶች፣
 የሬዲዮ ማስታወቂያዎች፣  የመንገድ ዳር ጨዋታዎች፣
 የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣  በራሪ ወረቀቶች ስርጭት ወዘተ…

 የዘፈን፣ የሥዕል፣ የታሪክ፣ የስነ- ግጥም፣ ፉከራ፣ ሽለላ፣ ውዝዋዜ፣ ወዘተ. ዓይነት
ውድድሮች፣

ከላይ የተጠቀሱትን ዝግጅቶችና ተግባራት ለማደራጀት የተለያዩ ኮሚቴዎችን ማቋቋም እንችላለን።


ለማኅበረሰብ ንቅናቄ መርኃ ግብሮች ስኬት የአካባቢው ወጣቶችና ንቁ የሆኑ የማኅበረሰብ አባላት
በኮሚቴዎች ውስጥ መሳተፍ ወሳኝ ነው። ለማኅበረሰቡ ንቅናቄ ዕቅድ ስናዘጋጅ የሚከተሉትን
ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡-

 የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የማኅበረሰብ ንቅናቄ ቀጣይነት ያለው ሒደት ነው።


 የንቅናቄ እንቅስቃሴዎች ተደጋጋሚ ሳይሆን የተለያዩ መሆን አለባቸው።

8.4. የማኅበረሰብ ሀብቶችን ማሰባሰብ እና ማስተዳደር


አንድን ማኅበረሰብ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎችን ለማቀድና ለመፈፀም የተዘጋጀና ንቁ ማድረግ
የማኅበረሰብ ንቅናቄ ይባላል (የካምቦዲያ ትምህርት ሚኒሰቴር፣ 2014)። ኅብረተሰቡ በአግባቡ
ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር ለማንኛውም ተነሳሽነትና ተግባር ስኬት ወሳኝ የሆነውን የማኅበረሰቡን
ሙሉ ድጋፍ፣ ተሳትፎና የባለቤትነት ስሜት ማግኘት አንችልም። በማኅበረሰብ ንቅናቄ በጣም
አስፈላጊ የሆኑትን የሰው፣ የቁሳቁስና የበጀት ምንጮችን ማዘጋጀት እንችላለን። ለማ.መ.ማ.
ውጤታማነት የሰው ኃብትን ጨምሮ ሌሎችንም ኃብቶች፤ የጥሬ ገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ መሬትና
የሰው ኃብት ማፈላለግ ይኖርብናል (እሸቱ እና አማኑኤል, 2017 እ.ኤ.አ.)፡፡ የገንዘብ ማሰባሰብ
ያለማቋረጥ መከናወን አለበት። የማኅበረሰብ ንቅናቄ ዓላማ መላው ማኅበረሰብ ስለማ.መ.ማ.
አስፈላጊነት እንዲሁም ለማ.መ.ማ ያላቸውን ቁርጠኝነትና ባለቤትነት የሚያዳብሩበትን ሁኔታ
ለመፍጠር ነው። በማኅበረሰብ ቅስቀሳ ማኅበረሰቡ በራሱ ችግሮች ለመፍታትና የኑሮ ሁኔታውን
ለማሻሻል የጋራ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የግንዛቤ ማሳደግ ሥራ መሥራት እንችላለን።
የማኅበረሰብ ንቅናቄ በማካሄድ የሚከሉትን ጉዳዮች ማሳካት እንችላለን (የካምቦዲያ ትምህርት
ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)፡፡

 የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣


 የጋራ ቁርጠኝነትን መፍጠርና ለኅብረተሰቡ ልማት አስተዋፅኦ ማጎልበት፣
 አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የጋራ መድረክ መፍጠር፣

42
 ማኅበረሰቡን በራሳቸው ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ ማበረታታት፣
 በማኅበረሰብ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎና ባለቤትነትን ማረጋገጥ፣
 የአካባቢ ፀጋዎችን መለየትና መጠቀም፣
 በማ.መ.ማ. እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ የአካባቢውን ሰዎች ዐቅም
ማጎልበትና ማበረታታት፣
 የማኅበረሰብ ባለቤትነትን ማዳበር፣
 የማኅበረሰብ ልማት ተነሳሽነቶችን እና ተግባራትን ማስቀጠል።

8.4.1. የኃብት ማሰባሰብ


የማ.መ.ማ. ተግባራትን ለመተግበር የሰው ኃብት ማለትም ዕውቀትና ጥበብ፣ እንዲሁም ባለፉት
ጊዜያት ለዓመታት የተሰበሰበው የማኅበረሰቡ ችሎታና ልምድ ያስፈልገናል። ከዚህ በተጨማሪም
የቢሮ እቃዎች፣ ልዩ ልዩ ግብአቶች፣ የልማት መሳሪያዎች፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች
ወዘተ... ዓይነት ቁሳዊ ሀብቶች እንዲሁም የበጀት ምንጮች እንደ ጥሬ ገንዘብ፣ የተለያዩ ዓይነት
ቦንዶች፣ ወዘተ የመሳሰሉት ሀብቶች ሁልጊዜ በቀላሉ ሊገኙ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ኃብት ማሰባሰብ
አለብን። አካባቢያዊ የሆኑ ኃብቶችን ማሰባሰብ በጣም ተስማሚና ዘላቂ ኃብትን የማስተዳደሪያ
ዘዴ ነው። የማኅበረሰብ ባለቤትነትን ያሳድጋል፣ የውጭ ጥገኝነትንም ይቀንሳል፡፡ የማኅበረሰቡ
አባላት ግብአቶችን ለማቅረብ ፍቃደኞች ሆነው እንኳን አንዳንድ አስፈላጊ ግብአቶች በማኅበረሰቡ
ውስጥ ላይገኙ ይችላሉ። ስለዚህ ከመንግሥት ድርጅቶች፣ ከሀገር አቀፍ እና ከዓለም አቀፍ
የእርዳታ ድርጅቶችና ከሌሎች ኤጀንሲዎች ጋር መተባበር በጣም አስፈላጊ ነው። የማ.መ.ማ
አስተዳደር ኮሚቴ ከማኅበረሰቡ ውጭ ኃብት ለማሰባሰብ ባለድርሻ አካላትንና የልማት አጋሮችን
ማነጋገር ይችላል። ሁልጊዜ በውጫዊ ድጋፍ ላይ ጥገኛ መሆን ግን የለብንም፡፡ ከማኅበረሰቡ
የተገኘ ፈንድ ማሰባሰብና ከውጭ ፈንድ ጋር ማዛመድ የውጭ ኤጀንሲዎችን እምነት ይጨምራል።
የውጭ ትብብርን ለማስቀጠል የማ.መ.ማ አስተዳደር ኮሚቴ በመ.መ.ማ. የተከናወኑ ተግባራትና
ስኬቶች መረጃን መዝግቦ ለመንግሥት ኤጀንሲዎች፣ለጋሾች እና ሌሎች ድርጅቶች ማድረስ
አለበት።

8.4.2. የማ.መ.ማ ኃብት የሚገኝባቸው ምንጮች


ማ.መ.ማ ከተለያዩ ምንጮች ኃብት ማሰባሰብ ይችላል። በአንድ ምንጭ ላይ ከመተማመን ይልቅ
የማ.መ.ማ አስተዳደር ኮሚቴ ከተለያዩ ምንጮች ገንዘብ ለማሰባሰብ እኩል ትኩረት መስጠት
አለበት። የማ.መ.ማ አስተዳደር ኮሚቴ በገንዘብ ማሰባሰብ ሒደት ውስጥ ያለው ሚና በጣም

43
አስፈላጊ ነው። የሰዎችን ፍላጎትና ዐቅም ግምት ውስጥ በማስገባት የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባራትን
በማ.መ.ማ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት መካከል ሊከፋፈሉ ይችላሉ። ከማ.መ.ማ አስተዳደር ኮሚቴ
አባላት በተጨማሪ የአካባቢው አስተዳደር እና የልማት አጋሮች ለማ.መ.ማ. ሀብቶችን በማሰባሰብ
ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላሉ። የማ.መ.ማ አስተዳደር ኮሚቴ ኃብት ማሰባሰብ
የሚችልባቸው አንዳንድ ምንጮች የሚከተሉት ናቸው።

 ተቋማዊ ለጋሾች  የአገልግሎት ክፍያ (ከተሳታፊዎች)


 ሐይማኖታዊ ድርጅቶች  የግለሰብ ለጋሾች
 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች  በቤተሰብ አባላት የተመሰረቱ
 የኢንዶውመንት ስጦታ ፋውንዴሽኖች
 ከማ.መ.ማ የገቢ ማስገኛ ንግድና ሌሎጅ ዝግጅቶች የድርጅት ለጋሾችን ለመሳብ ሌላው
ጠቃሚ የገንዘብ ማሰባሰብያ መንገድ ነው።

ለጋሽ ድረጅቶችን እና የንግድ ሰዎችን በብዙ መንገዶች ማነጋገር እንችላለን፡-

 የንግድ ድርጅት ላላቸው የኮርፖሬት አጋሮች የተለያዩ ግብአቶችን ለማ.መ.ማ በማቅረብ


አብረው እንዲሰሩ ዕድሎችን ልንሰጣቸው እንችላለን፣
 በአንድ ጊዜ የኮርፖሬት ድጎማዎች ፋንታ የረጅም ጊዜ የኮርፖሬት ሽርክና የምንፈጥርበትን
ዕድል ማመቻቸት አለብን፣
 ጠቅላላ የመርኃ ግብሩን ወጪ ሊሰጡን ካልቻሉ ወጭዎችን በመከፋፈል (ሀ) የካፒታል
ወጪዎችን፣ (ለ) መደበኛ የፕሮግራም ወጪዎችን፣እና (ሐ) የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን
ብለን በመከፋፈል ለጋሾች እንዲያዋጡ መጠየቅ እንችላለን ።
 እንደ ፍላጎታቸው እና አቅማቸው መዋጮ ማድረግ እንዲችሉ ለመለገስ ብዙ አማራጮችን
ማቅረብ።

8.5. የኃብት አጠቃቀም


ከማኅበረሰቡ ንቅናቄ እና ኃብት ማፍራት ጎን ለጎን ኃብትን እንዴት በብቃት ማስተዳደር እንዳለብን
ማወቅ አለብን። ሀብቶችን ማስተዳደር ሁልጊዜ ወጪ ቆጣቢ መሆን አለበት። ልምድ ያላቸው
ሰዎች በተወሰኑ ሀብቶች ውስጥ እንቅስቃሴዎችን እንዴት ማደራጀት እና ማስተዳደር እንደሚችሉ
ያውቃሉ። ኃብትን በብቃት መጠቀም ከፍተኛውን ውጤት ሊሰጠን ይችላል። ስለዚህ ሀብቶችን
ስንጠቀም መጠንቀቅ አለብን። ኃብትን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን
እንችላለን።

44
 የማ.መ.ማ. መርኃ ግብሮችን ተግባራት በማስተባበርና ኃብት በ፣ስተዳደር በንቃት
ለሚሳተፉ ሰዎች ሥልጠና መስጠት፣
 በጣም ተስማሚ መሳሪያዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን ብቻ መግዛትና መጠቀም፣
 የማኅበረሰቡ አባላት ውሳኔ እንዲወስኑና ለራሳቸው መርኃ ግብሮች ኃላፊነት እንዲወስዱ
ዕድሎችን መስጠት፣
 ያጋጠሙ ወጪዎችን ለመከታተል ትክክለኛውን የሂሳብ አያያዝና የኦዲት ሒደቶችን
መጠቀም፣
 የማ.መ.ማ ተግባራትን እና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎችን በመምራት በውጫዊ ዕውቀት
ላይ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ በአካባቢው ያሉ ባለሙያዎችንና ጥበባቸውን ጥቅም ላይ
ማዋል፣
 ያሉትን ሀብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እና ለወደፊት ጥቅም ላይ የሚውሉ
መሆናቸውን ለማረጋገጥ ህገ ደንብ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ፣
 የአካባቢው ሰዎች ለማ.መ.ማ. እና ለማኅበረሰቡ ዕድገት አስፈላጊ ናቸው ብለው
የሚሏቸውን ሀብቶች እንዲቆጣጠሩና የአካባቢ ሀብቶችን እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት
መስጠት፣
 ሁሉም ሰው እንዲያየው የማ.መ.ማ የውስጥ በጀት ማጠቃለያ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ
መለጠፍ። ይህ የማ.መ.ማ. መርኃ ግብር ተግባራትና የፋይናንስ ግልጽነት እንዲኖራቸው
ያደርጋል፣
 የማ.መ.ማ እንቅስቃሴዎችን በተለይም ሂሳብ አያያዝ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ክትትልና
ግምገማ ማካሄድና ውጤቱን በማ.መ.ማ. ውስጥ ማሳየትና ውጤቱን ለመርኃ ግብሩ
ሥራዎችን ለማሻሻል ዓላማ መጠቀም፡፡

ከላይ ያሉት አቀራረቦች ሀብቶችን በብቃት ለማስተዳደር ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው አንዳንድ


የተለመዱ አቀራረቦች ናቸው። እንደ ፕሮጀክቱ ዓይነትና ባህሪያት ሌላ አካሄድ መከተል
እንችላለን። በአስፈላጊ ሁኔታ፣ የማ.መ.ማ ኃላፊና ሠራተኞች ሀብቶችን በአግባቡ እና በብቃት
ለማንቀሳቀስ እና ለማስተዳደር ጥሩ አቀራረብን ለመምረጥ ፈጠራ የታከለበት ሥራ መሥራት
የሚችሉ መሆን አለባቸው።

45
ምዕራፍ ዘጠኝ
9. ባለድርሻ አካላትን ማቀናጀት፣ ማስተሳሰርና ማገናኘት
የምዕራፉ ዓላማ፡-

ይህ ምዕራፍ ሲያጠናቅቁ ሠልጣኞች፡-

 የባለድርሻ አካላት ቅንጅት፣ ግንኙነትና ትስስር አስፈላጊነትን ይረዳሉ፡፡


 የማ.መ.ማ. ባለድርሻ አካላትን ለማቀናጀትና ለማስተሳሰር ሊደረጉ የሚገባቸውን ተግባራት
ይረዳሉ፡፡

9.1. የባለድርሻ አካላት ቅንጅት


ተመሳሳይ ዓላማና ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ሰፋ ባለ አመለካከት በጋራ
ለመሥራት የጋር መድረክ ሲፈጥሩ ትስስር (ኔትወርክ) ይባላል። ተደጋጋፊ የሥራ አካባቢ
ለመፍጠር በባህሪያቸው ተመሳሳይ በሆኑ የማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ትስስር ይመሰረታል።
ከኅብረተሰቡ ርቀው ከሚገኙ ነገር ግን አገልግሎቶችን ለመስጠትና ሀብቶችን ለማጋራት ዝግጁ
ከሆኑ ድርጅቶችና ኤጀንሲዎች ጋር ትስስር ሊመሰረት ይችላል። ትስስር መፍጠር (ኔትዎርኪንግ)
በማኅበረሰቡ ውስጥ፣ በድርጅቶችና በማኅበረሰቦች፣ እነረዲሁም በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል
ጠቃሚ ትስስሮችን በመፍጠር አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በጋራ በማሰባሰብ የጋራ ግቦችን ማሳካት
ነው (የካምቦዲያ ትምህርት ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)።

ከሌሎች ተቋማት ጋር የግንኙነት መስመር መዘርጋት እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመገናኘት


ሀብቶችን ማሰባሰብ ይቻላል፡፡ የማኅበረሰቡን ዘርፈ ብዙ ፍላጎት ለማሟላት ሥራ አስኪያጆች
ከሌሎች የማ.መ.ማ. ድርጅቶች እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና የአካባቢ አስተዳደር
ተቋማት ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠርና ለማስቀጠል ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ አለባቸው
(እሸቱ እና አማኑኤል, 2017 እ.ኤ.አ.)።

9.2. የባለድርሻ አካላት ግንኙነት


በሌላ በኩል በማ.መ.ማ. አስተዳደር ኮሚቴ፣ በአገልግሎት ሰጪ እና በማኅበረሰቡ አባላት መካከል
ያለው መስተጋብር ግንኙነት (ሊንኬጅ) ተብሎ ሊጠራ ይችላል። አገልግሎት ሰጪው የመንግሥት
ክፍል፣ የአካባቢው አስተዳደር፣ የግል ድርጅት፣ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ወይም ነጋዴ
ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ጥቂት ሰዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞቻቸውን
ለመጀመር የብድር ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። የማ.መ.ማ. አስተዳደር ኮሚቴ እነዚያን ሰዎች

46
የማይክሮ ፋይናንስ ብድር ከሚሰጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ሊያገናኝ (ሊንኬጅ
ሊፈጥር) ይችላል።

9.3. የማ.መ.ማ. ግንኙነት የሚፈጥርባቸው ተቋማት


የመረጃ ፍሰትንና የሀሳብ አንድነትን በማጠናከር የጋራ ግቦችን ለማሳካት ከማኅበረሰቡ ጋር
ከሚሠሩ ሌሎች አካላትና የማኅበረሰብ ልማት ድርጅቶች ጋር ግንኙነት (ሊንኬጅ) መፍጠር
ይኖርብናል፡፡ እነዚህ ድርጅቶችም፡-

 የአካባቢ ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች ፣  የአካባቢ ክበቦችና የሴቶች ማኅበራት፣

 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣  የአካባቢ የትምህርት ተቋማት ፣

 የአካባቢ ንግድ ድርጅቶች፣  የኤክስቴንሽን ሠራተኞች ፣

 የሙያ ማኅበራት፣  ሌሎች የማ.መ.ማ.

 የአካባቢው የጤና ባለሙያዎች፣  የልማት ድርጅቶች ፣

 የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በማህበረሰቡ ውስጥ ማንበብና መጻፍ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የትምህርት እንቅስቃሴን ውጤታማ
ለማድረግ የማ.መ.ማ አስፈላጊ መሳሪያወች ቢሆኑም አገልግሎታቸው በእነዚህ ተግባራት ብቻ መገደብ
የለበትም። የማ.መ.ማ. የመማርያና የማህበረሰቡን ጉዳዮች መወያያ ቦታ ተብሎ የሚታወቅበት ስለሆነ
ተግባራቶቹንና አገልግሎቶቹን በማስፋፋት በሌሎች በርካታ መንገዶች ለማህበረሰቡ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል።
ነገር ግን ይህ እንዲሆን ማ.መ.ማ.ን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ አስፈላጊውን እውቀት፣ ግንኙነትና
ግብዓቶች ያላቸዉን አጋሮችና ተባባሪዎች መለየት አስፈላጊ ነው። ስለሆነም ከአጋሮች ጋር ትስስር
መፍጠርና እንደዚህ አይነት ትስስሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የማ.መ.ማ. ማህበረሰቡን ለማገልገል፣
ችግሮቹን ለመፍታት እና ፍላጎቶቹን ለማሟላት ትክክለኛ የመማማሪያ ማዕከላትና የተለያዩ ተግባራትን
ለማከናወን የተግባራት ሁሉ የስበት ማዕከል (ማግኔት) ማድረግ ያስፈልጋል።

47
በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ውስጥ የጋራ ዓላማ ያላቸው እና እንደ ማ.መ.ማ. ተመሳሳይ ተጠቃሚዎች
ያላቸው የመንግሥት ክፍሎች፣ ተቋማት፣ ኤጀንሲዎች እና ድርጅቶች አሉ። የማ.መ.ማ.
አስተዳደር ኮሚቴ መርኃ ግብሮችን በመንደፍና በመተግበር ሒደት ላይ ሙሉ በሙሉ ወይም
በከፊል ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉትን የሌሎች ተቋማትን ሀብቶች ግምት ውስጥ በማስገባት
ማቀድና መሥራት አለበት፡፡

ሰፊ ኔትወርኮች ያላቸው የማ.መ.ማዕከሎች ለኅብረተሰቡ ብዙና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ


ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ ግልፅነትን በመጨማር ተአማኒነቱንና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ
ያለውን ተቀባይነት ያሳድጋል። እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የማኅበረሰብ ቡድኖች ባሉ
ተመሳሳይ ተቋማት መካከል ሽርክና የተለመደ ቢሆንም መንግሥታት ባልተለመዱ አጋሮች
መካከል እንደ ዩኒቨርሲቲዎችና የማኅበረሰብ ቡድኖች፣ የምርምር ተቋማት እና መንግሥታዊ
ካልሆኑ ኤጀንሲዎች እና ከግሉ ሴክተር ጋር ሽርክና መፍጠር ይችላሉ (ዩኔስኮ ኢንስቲትዩት ፎር
ላይፍ ሎንግ ለርኒንግ፣ 2017 እ.ኤ.አ.)።

በኔትወርክ፣ ትምህርቶችን፣ ልምዶችን እና ዕውቀትን በተደራጀ መንገድ ለመካፈል እድላችንን


ልናሰፋው እንችላለን።

ዩኔስኮ (2007 አ.ኤ.አ.) ባወጣው ሪፖርት የሚከተለውን አስፍሯል፡፡

የትስስር ግንኙነቶች በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ትስስር የሚከተሉትን ማድረግ
ይችላል (የካምቦዲያ ትምህርት ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)፡፡

 የተለዩና በሌላ መንገድ መስተጋብር የማይፈጥሩ ቡድኖችን ወይም ሰዎችን ያገናኛሉ፣


 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ማኅበረሰብ አቀፍ ድርጅቶችን ዐቅም የማጠናከርና
የመጠቀም ዕድል ይፈጥራሉ፣
 ለቅስቀሳና ለማስተዋወቅ ሥራ የተሸለ ክብደት ያስገኛሉ፣
 ዐቅምን ለመቆጠብና ለመጋራት (Reduce duplication of Effort)
 በተለያዩ ደረጃዎች ትብብርንና አንድነትን ማሳደግ ፣
 የጋራ ተግባራትን ማሳደግና መቀራረብን (synergy) ይፈጥራሉ፣
 የአካባቢና ሀገር በቀል ልምዶችንና ባሕልን ማረጋገጥ ዕድል ይፈጥራሉ፣
 ከመንግሥት ድርጅቶች፣ ከልማት ኤጀንሲዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና
ሌሎች ጋር ሰፊ ግንኙነት ይፈጥራሉ።

48
ምዕራፍ አስር
10. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት ክትትል፣ ግምገማና
ቀጣይነትን ማረጋገጥ
10.1. ክትትልና ግምገማ
ክትትልና ግምገማ ልምድና ችሎታ የሚጠይቅ ሙያዊ ሥራ ነው። በማ.መ.ማ ውስጥ የመርኃ
ግብሩን ተጠቃሚዎች በማሳተፍ አሳታፊ ክትትልና ግምገማ ማድረግ እንችላለን። ይህንን
ለማድረግ የክትትልና ግምገማ አመልካቾችን መለየትና መረጃና ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ
ተስማሚ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን (data collection tools) ማዘጋጀት አለብን:: በዚህ
ሒደት ከመንግሥት ኃላፊዎችና ከልማት አጋሮች ድጋፍ ማግኘት እንችላለን፡፡

ክትትልን ከመጀመራችን በፊት የሚከተሉትን ጉዳዮች ያካተተ የክትትል ዕቅድ ማዘጋጀት አለብን።

 የክትትል ዓላማዎች
 ክትትል ሊደረግባቸው የሚገቡ ተግባራት
 ለክትትል ጥቅም ላይ የሚውል ጊዜ
 ክትትልየሚደረግባቸው የፕሮጀክቱ ተግባራትና የሚጠበቁ ውጤቶች
 የሚሰበሰበው መረጃ
 የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎች
 የክትትል ቡድን
 የክትትል ድግግሞሽ (በወር ወይም በዓመት)

የማ.መ.ማ. እንቅስቃሴዎችን ለመከታተልና ለመገምገም መረጃን ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ በርካታ


ዘዴዎች አሉ። ከክትትልና የግምገማ ዓላማዎች ጋር የሚስማማውን ዘዴ መምረጥ አለብን
የግምገማ ቡድኑ ኃላፊነት ነው። በአጠቃላይ አንድን ዓላማ ለማሳካት ማንኛውንም ዘዴ
በምንመርጥበት ጊዜ የሚከተሉትን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡

መረጃን በመሰብሰብ እና በመተርጎም ላይ የመርኃ ግብሩ ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ


ማድረግ፣
ዘዴውን ተግባራዊ ለማድረግ ተገቢ ጊዜ፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ ዕውቀት እና ችሎታ መኖሩን
ማረጋገጥ፣
ግልጽና አስተማማኝ መረጃ የማግኘት ዕድልና የመረጃ ትንተና ወሰንን ማወቅ፣

49
ዘዴው ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነና እሱን ለመጠቀም ምን ያህል ጊዜ እና ዕውቀት
እንደሚያስፈልግ ለማረጋገጥ የክትትልና የግምገማ ዘዴዎች አስቀድመው መሞከር
አለባቸው።

የማ.መ.ማ. ተግባራት ስንገመግም የማ.መ.ማ መርኃ ግብር ዓላማዎች በጊዜ ሒደት ምን ያህል
እንደተሳኩ ማወቅ አለብን። በግምገማ የፕሮጀክቶቹን ወጪ ቆጣቢነት እና ለታለመላቸው
ተሳታፊዎች የሚጠበቀውን ለውጥ ስለማምጣታቸው መረጃ ማግኘት እንችላለን። በግምገማው
ውጤት መሰረት፣ የማ.መ.ማ የማኔጅመንት ኮሚቴ የማ.መ.ማ ተግባራትን መቀጠል ወይም
ማሻሻልን በተመለከተ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል። የሚከተለው ለዓላማ ተኮር ግምገማ ሊሰበሰቡ
የሚችሉ የመረጃ ዓይነቶች ናሙና ነው። እንደ አውዱ ጥያቄዎችን ማከል ወይም መቀነስ
እንችላለን።

1. የማንኛውም ፕሮጀክት ተግባራት ዓላማዎች ለመገምገም


 ፕሮጀክቱ ይዟቸው የተነሳቸው ዓላማዎች እውነተኛና የማኅበረሰቡን ፍላጎት
የሚያሟሉ ነበሩ?
2. የማንኛውም ፕሮጀክት ተግባራት በጀት ለመገምገም
 በጀቱ ዓላማዎቹን ለማሳካት በቂ፣ በጣም ትንሽ ወይስ በጣም ትልቅ ነበር? ከሆነ
ይህ በፕሮጀክት ትግበራ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ?
3. የማንኛውም ፕሮጀክት ተግባራት አፈፃፀም ለመገምገም
 መርኃግብሩ በእቅዱ መሰረት ስልታዊ በሆነ መንገድ ተተግብሯል?
 የመርኃ ግብሩ ተሳታፊዎች የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸዋል?
4. የማንኛውም ፕሮጀክት ተግባራት አስተዳደር ለመገምገም
 የፕሮጀክቱ ዓላማዎች በተያዘለት መርኃ ግብር ተሳክተዋል? ካልሆነ ለምን?
 የፕሮጀክቱ ጊዜ በጣም የተጣበበ ነበር፣ የተለጠጠ ወይስ ትክክል?
 የፕሮጀክቱ ተግባራት በታቀደው በጀት ተከናውነዋል? ካልሆነ ለምን?
 ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች የተደረገው ድጋፍ በቂ ነበር?
 ለፕሮጀክት አስተዳደር ምን ማሻሻያ ያስፈልጋል?
 በተለይ ምን ሰርቷል?
5. የማንኛውም ፕሮጀክት ተግባራት ተጽዕኖ ለመገምገም
 በሰዎች ዕውቀት ላይ ምን ለውጦች መጥተዋል?
 በሰዎች ችሎታ ላይ ምን ለውጦች መጥተዋል?

50
 ሰዎች አዲሱን ዕውቀትና ችሎታ እንዴት እየተጠቀሙበት ነው?
 አመለካከታቸው ተለውጧል ወይ?
 እነዚህ ለውጦች በሰዎች ሕይወት ላይ ምን ተጽእኖ አምጥተዋል?

10.2. የማ.መ.ማ. ተግባራት መሰነድ


ዶክመንቴሽን የተለያዩ ዓይነት መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት መዝገቦችን
የማቆየት ስልታዊ ዘዴ ነው። የማ.መ.ማ. ተግባራትን መመዝገብ የማ.መ.ማ ፈጻሚዎች
ያለፉባቸውን ሒደቶችና የማ.መ.ማ. መርኃ ግብሮች እንዲሁም ተግባራትን ስንፈፅም ያገኘናቸውን
ልምዶች ያስገኘናል። ከማ.መ.ማ. ሥራዎች ጋር የተያያዙ የሁሉም መርኃ ግብሮችና ተግባራት
ሒደት እና ውጤቶችን መመዝገብ እንችላለን። የማ.መ.ማ ሠራተኞች ሪፖርቶችን፣ መዝገቦችን፣
ጋዜጣዎችን፣ ብሮሹሮችን፣ የተሰራጩ ዜናዎችን ወዘተ በማዘጋጀት ሁሉንም አስፈላጊ ነገሮች
መመዝገብና በመረጃ ቋት2 መቀመጥ አለባቸው። የማ.መ.ማ ቀጣይነት ያለው ተግባራትን እና
የስኬት ታሪኮችን በድምጽ እና በምስል መልክ ሊመዘግብ ይችላል። ፎቶግራፍ ሌላ እውነተኛ
ዕድገትን እና ችግሮችን የመመዝገቢያ መንገድ ነው፡፡ የማ.መ.ማ ማኔጅመንት ኮሚቴ ምን
እንደሚመዘግቡ፣ እንዴትና እነ ማን እንደሚመዘግቡ መወሰን አለበት።

የሚከተሉት ጉዳዮች እንደ የሰነድ ተዘጋጅተው መቀመጥና ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ


መደረግ አለባቸው፡፡

 የማ.መ.ማ. የልማት ዕቅድ፣


 የመርኃ ግብር እንቅስቃሴዎች የተፃፉባቸው ሪፖርቶች፣
 የማ.መ.ማ. ማኔጅመንት ኮሚቴ እና የሌሎች ስብሰባዎች ቃለ ጉባኤዎች፣
 በማ.መ.ማ. እንቅስቃሴ ላይ የክትትል እና ግምገማ ሪፖርቶች፣
 የተለያዩ መርኃ ግብሮች ተግባራት የፎቶግራፍና የቪዲዮዎች ማስረጃዎች፣
 በማ.መ.ማ ተግባራት ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ሰልጣኖች ስለነበራቸው ተሳትፎና
አፈፃፀማቸው የሚገልፅ መዝገቦች፣
 የስኬት ታሪኮች፣
 የሥልጠና መመሪያዎች፣
 የተለያዩ አሃዛዊ (ስታቲስቲክሳዊ) መረጃዎች፣
 የማኅበረሰብ መገለጫ እና የማኅበረሰብ መረጃ፣

2
ስለመረጃ ቋት ዝግጅትና አጠቃቀም በምዕራፍ አምስት በዝርዝር ተገልጿል፡፡

51
 አስፈላጊ የደብዳቤ ልውውጦች፣
 የሚዲያ ዘገባዎች፣
 የቃለ መጠይቅ መዝገቦች፣
 በማ.መ.ማ. ተሳታፊዎች (ሰልጣኖች) የተሰሩ ቁሳቁሶች ናሙናዎች፣
 በጋዜጣና በመጽሔት ላይ ስለማ.መ.ማ. እንቅስቃሴዎች የታተሙ ጽሑፎች፣ እና
 የተማሪዎችን የቃለ መጠይቅና የመማር ግኝቶች፡፡

ሰነዶች በተገኙት ልምዶች ላይ ተመስርተው ተግባራትን በተሻለ ጥራትና ብቃት ለመፈፃም


የማ.መ.ማ. ሠራተኞችን ቅልጥፍና ይጨምራል። ከዚህ በፊት ከነበሩ ስህተቶችም እንድንርቅ
ይረዳናል። ሰነዶች ለማ.መ.ማ. በጣም አስፈላጊ ናቸው ምክንያቱም ሰነዶች ማ.መ.ማ. ጥንካሬን
እና ድክመቶችን፣ ስኬቶችንና ውድቀቶችን ለሌሎች ባለድርሻ አካላትና ለጋሾች ለማሳየት ይረዳሉ
(የካምቦዲያ ትምህርት ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.አ.አ.)። በዚህ መንገድ ሰነዶች የማ.መ.ማ. ለሌሎች
ለማስተዋወቅ ይረዳል። ወደፊት መውሰድ ስላለብን እርምጃ ውሳኔ የማ.መ.ማ. ጠቃሚ
መረጃዎችን መዝግቦ መያዝ ይረዳናል። የክትትል ውጤቶችን መመዝገብ የማ.መ.ማ. መርኃ
ግብሮችን ስኬትና ችግሮችን ለመከታተልና ተገቢውን እርምጃ እንድንወስድም ይረዳናል።

የማ.መ.ማ.ተግባራትን የምንመዘግበው፡

1. የማ.መ.ማ. ተግባራትን ስኬት ለማኅበረሰቡ አባላት ለማቅረብና ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ


ለማነሳሳት፣
2. ውጤታማነታቸውን በመገምገም የማ.መ.ማ. ተግባራትን ለማሻሻል ለማሳደግ፣
3. የማ.መ.ማ. ተግባራተን ስኬት ለማረጋገጥና የማ.መ.ማ. ተግባራትን የስኬት ተሞክሮ ወደ
ሌላ ቦታ ለማስፋት እንዲሁም ለሌሎች የማ.መ.ማ. ለማካፈል፣
4. የገንዘብ ድጋፍ ስንፈልግ የማ.መ.ማ. መረጃ ለለጋሾች ማቅረብ ስላለብን፣

10.3. የማ.መ.ማ. ሰነዶች ስርጭት


ሰነዶች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉበት ቅጽ ለታለመላቸው ታዳሚዎች መሰራጨት አለባቸው።
የበይነመረብ ግንኙነትን በመጠቀም የማ.መ.ማ. መረጃን ለብዙ ተቀባዮች በአንድ ጊዜ ማሰራጨት
እንችላለን። ያለ መረጃ ስርጭት ለማ.መ.ማ. ጥሩ ድጋፍ ማድረግ አንችልም። ለተለያዩ ባለድርሻ
አካላት መረጃን መላክ እንችላለን ወይም መረጃ በማ.መ.ማ. ውስጥ በመለጠፍ ማሳየት እንችላለን።
መረጃን በማሰራጨት ለልማት አጋሮቻችን መረጃ መስጠት እና ማዘመን እንችላለን። በየጊዜው
መረጃን ማሰራጨት ተጨማሪ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍን ለማግኘት ይረዳናል።

52
መረጃዎቻችንን (ሰነዶቹን) በሚከተሉት መንገዶች ማሰራጨት እንችላለን (የካምቦዲያ ትምህርት
ሚኒሰቴር፣ 2014 እ.ኤ.አ.)።

 ሳምንታዊ፣ ወርሃዊ፣ ዓመታዊ ስብሰባ፣ እና ወርክሾፖች በማዘጋጀት፣


 የማ.መ.ማ. እንዲጎበኝ ለማድረግ ጉብኝቶችን በማዘጋጀት፣
 እንደ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ መጽሔት ወይም ጋዜጣ ባሉ ታዋቂ ሚዲያዎች ውስጥ
ጽሑፎችን እና ዜናዎችን በማሰራጨት፣
 በማ.መ.ማ. በእንቅስቃሴዎቹ ዙሪያ የድምፅና የምስል ይዘቶችን በማዘጋጀት፣
 ፍሊፕ ቻርት በማዘጋጀት፣
 በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት፣
 የጥናት ሪፖረት በማዘጋጀት፣
 የመማማሪያ ቁሳቁስ በማዘጋጀት፣ ወዘተ፡፡

10.4. የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከላትን ዘላቂነትን ማረጋገጥ


ለብዙ የማኅበረሰብ ልማት ድርጅቶች እና የመንግሥት ተቋማት የማ.መ.ማ.ን መመስረት ዋነኛው
ችግር አይደለም። ይልቁንም የማ.መ.ማ.ዎችን ዘላቂነት ማረጋገጥ ትልቅ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ
ትምህርት ሚኒስቴር (2016 እ.ኤ.አ.) ባወጣው የማ.መ.ማ. ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ እንደገለጸው
የዘላቂነት ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል፡ (1) መርኃ ግብሩ ለተሳታፊዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ፣ እና
(2) የማ.መ.ማ እራሱን የሚችል ተቋም መሆን መቻሉ መሆኑን ገለጿል።

የማ.መ.ማ.ን መርኃ ግብረ ቀጣይነት ለማረጋገት የማ.መ.ማ.ን ማኔጅመንት ኮመኪቴ


የሚከተሉትን ጉዳዮች ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡

 የማ.መ.ማ.ን መርኃ ግብሮችን ዘላቂ ለማድረግ በርካታ የኃብት ማሰባሰብ ስልቶችን


መተግበር አለበት፣
 የማ.መ.ማ.ን መርኃ ግብሮች ለማኅበረሰቡ ፍላጎት፣ እሴትና ባሕል ምላሽ ሰጭ በመሆን
የበለጠ የማኅበረሰብ ተሳትፎ መሳብ አለባቸው፣
 የማ.መ.ማ.ን መርኃ ግብር አወጣጥና አተገባበር ሒደት ማናቸውንም ለውጦች ማስተናገድ
እንዲችሉ ተማጭና ተለዋዋጭ መሆን አለበት፣
 በውጭ ሰዎች መዋጮና ድጋፍ ላይ ጥገኝነትን ለመቀነስ ከጥገኝነት የመውጫ ስትራቴጂ
ሊኖረው ይገባል፣

53
 የማ.መ.ማ.ን መርኃ ግብሮችን በመተግበር ላይ ለማኅበረሰቡ ተሳትፎ ተጨማሪ ቦታ
መስጠትና የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጥሩ ማድረግ ያስፈልጋል፣
 በባለድርሻ አካላትና በልማት አጋሮች መካከል የተሳትፎ፣ ትብብርና የኃብት መጋራት
ዕድሎችን መፍጠር፣
 ተአማኒ የሆነ የመርኃ ግብር በጀት ማዘጋጀት፣
 የገቢ ማስገኛ መርኃ ግብሮችን በማዘጋጀትና የተሳታፊዎችን የአገልግሎት ክፍያ
በመሰብሰብ የበጀት ዘላቂነት ማረጋገጥ፣
 ከታማኝ ተቋማት የትብብርና የአጋርነት ድጋፍ ማግኘት፣
 የአካባቢ አስተዳደር፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና በማኅበረሰቡ
ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች ድጋፍ ማግኘት፣
 በተቻለ መጠን ቁርጠኛ የሆኑ በጎ ፈቃደኞችን መመልመልና የአካባውን ሰዎች
በሠራተኝነት መቅጠር፣
 ራሳቸውን ችለው እንዲቀጥሉ የማ.መ.ማ ሠራተኞችን ዐቅም መገንባትና ማብቃት፣
 የማኅበረሰቡን ጥበብ ለመጠቀምና ሀብቶቹን ለማንቀሳቀስ የማኅበረሰቡን ዐቅም ማጎልበትና
ግንኙነትን ማሳደግ፣
 የአካባቢያዊ ሁኔታን የመረዳትና አዊዳዊ ተግባራትን ለመጠቀም ከማኅበረሰቡ ውጭ
የሚመጡ የመርኃ ግብሩ ፈፃሚዎችን ዐቅም ማጎልበትና የመረዳ ክፍተትን መቀነስ፣
 የማ.መ.ማ.ን መርኃ ግብሮች በማኅበረሰቡ አባላት የመታየት ወይም የመጎብኘት ዕድል
እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እሸቱ እና አማኑኤል (2021) በዲቪቪ ኢንተርናሽናል የማ.መ.ማ. ማንዋል ላይ


እንዳሰፈሩት በኢትዮጵያ የማ.መ.ማ.ን ዘላቂነት ለማረጋገጥ፡-

 የማ.መ.ማ.ዎች በኢኮኖሚያዊ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ለማድረግ የአጭር እና


የረዥም ጊዜ እቅዶችን ከሰፊ ተልዕኮ ጋር ያዘጋጁ።
 የአካባቢው የመንግሥት አስተዳደር የማ.መ.ማ. የበለጠ ትርጉም ያለው ድጋፍ የሚሰጥበት
ሥርዓት ይፍጠሩ።
 ያልተቋረጠ የዕለት ከለት ድጋፍና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ማኅበረሰቡ
የማ.መ.ማ.ን በቁሳቁስና በገንዘብ በንቃት እንዲደግፍ ማበረታታት፡፡ ይህ መዋጮ በሎተሪ፣
በጨረታ፣ በዓመታዊ መዋጮ ወዘተ… ሊሆን ይችላል።

54
 የማ.መ.ማ. የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ፣እና ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተገቢ የሆነ
ቴክኒካዊ ድጋፍ በወረዳ አስተዳደር፣በቀበሌ አመራር፣በማእከል አስተዳደር ኮሚቴዎች፣
በመንግሥት ሴክተር ተቋማት እና ሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲቀጥል ማድረግ።

በአጠቃላይ የማ.መ.ማ.ት ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፡- (1) የማኅበረሰብ ተሳትፎን


ማሻሻል፣ (2) ጠንካራ አመራር መገንባት፣ (3) የማይቋረፅ ቋሚ ገቢ ማፈላለግ፣ (4) ጠንካራ
የክትትልና ግምገማ ሥርዓት መገንባት፣ (5) ቁርጠኛ የፕሮግራም አስተባባሪ መመደብ፣ (6) እና
ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት ተገቢ ነው።

10.4.1. ቀጣይነት ያለው የማኅበረሰብ መማማሪያ ማዕከል መገለጫዎች


የሚከተሉት ቀጣይነት ያለው የማ.መ.ማ. ባህሪያት ናቸው፡፡

 መንግሥት የማ.መ.ማ.ን እንደ መደበኛ ያልሆነ ትምህርት መስጫ መድረኮች አድርጎ


በመመልከት መዋቅራቸውን ያዳብራል፣ ያጠናክራል።
 የታቀዱ ተግባራት በመንግሥት ከፍተኛ ድጋፍና በማኅበረሰቡ አባላት በተለያየ መንገድ
ሊተገበሩ ይችላሉ።
 በመንግሥት፣ በግል፣ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል መደበኛ ግንኙነት
እና ትብብር አለ።
 የማ.መ.ማ. የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት በራሳቸው ተነሳሽነት የወደፊት ተግባራት ዕቅድ
ያወጣሉ፡፡
 በማ.መ.ማ. ተግባራት ውስጥ ሰፊ የማኅበረሰብ ተሳትፎ አለ፡፡
 የአስተዳደር ቡድኑ የአካባቢ ችግሮችን ያውቃል፣ የአካባቢ መፍትሄዎችን ለማፍለቅም
ፈቃደኛ ነው፡፡
 ተግባራቶቹ የተከናወኑት ከማኅበረሰቡ ውስጥ በሚመነጩ ሀብቶች ነው።
 አባላቱ የአካባቢ ፀጋዎችን ለመጠቀም ማቀድ ይችላሉ።

55
ዋቢ መፃህፍት
እሸቱ አባተ፣ እና አማኑኤል ሃደራ. (2017). Manual for CLC Establishment and
Implementation.
እሸቱ አባተ፣ እና አማኑኤል ሃደራ. (2021). Expanding Community Learning Centres in
Ethiopia. Asqual.

የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር. (2016). National Strategy on Community Learning


Centers (CLCs) in Ethiopia (first draft document ) (Draft).
የካምቦዲያ ትምህርት ሚኒሰቴር. (2014). Manual for Management of Community
Learning Center (CLC).
ዩኔስኮ. (2007). Strengthening Community Learning Centres through Linkages and
Networks: A Synthesis of Six Country Reports.
https://unesdoc.unesco.org/in/documentViewer.xhtml?v=2.1.196&id=p::usmarcde
f_0000152157&file=/in/rest/annotationSVC/DownloadWatermarkedAttachment/att
ach_import_529bdc98-a134-4e73-9464-
c704b76c8feb%3F_%3D152157eng.pdf&locale=en&multi=true&ark=/ark:/48223/
p

ዩኔስኮ ኢንስቲትዩት ፎር ላይፍ ሎንግ ለርኒንግ. (2016). Synthesis Report on the State
of Community Learning Centres in Six Asian Countries Bangladesh, Indonesia,
Mongolia, Republic of Korea, Thailand and Viet Nam (Issue December 2016).
https://uil.unesco.org/literacy/community-learning/synthesis-report-state-
community-learning-centres-six-asian-countries

ዩኔስኮ ኢንስቲትዩት ፎር ላይፍ ሎንግ ለርኒንግ. (2017). Community-based learning for


sustainable development (No. 8; UIL/2017/PI/H/6, Issue 8).
https://uil.unesco.org/library

56

You might also like