You are on page 1of 1

ውድ የኢትዮ ቴሌኮም ቤተሰቦች!

ሰላም ለእናንተ ይሁን!


የኩባንያችንን የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም እና የ2016 በጀት ዓመት እቅድን ታሳቢ ያደረገ አመታዊ
የደመወዝ ጭማሪ መወሰኑን ስናበስራችሁ በታላቅ ደስታ ነው፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ኩባንያችን በመጀመሪያው የውድድር አመት ያቀዳቸውን ዘርፈ ብዙ ግቦችና ዒላማዎችን ለማሳካት የነደፈውን
ስትራቴጂ አመራሩና ሰራተኛው በመገባባትና ተቀናጅተው ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ያስቀመጥናቸውን ግቦች በአመርቂ ሁኔታ
ማሳካት ችለናል፡፡ በተጨማሪም ኩባንያችን ሀገራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት አኳያ በርካታ አመርቂ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን
በተለይም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እያደረጋቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ከወዲሁ ውጤት አበረታችና ተስፋ
የሚሰጡ ውጤቶችን ማሳየት ጀምረዋል፡፡ ለዚህም ለኩባንያችን ማኔጅመንትና ሠራተኞች ላቅ ያለ ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ
እወዳለሁ፡፡

የኩባንያችንን ዘላቂ ዕድገትና ትርፋማነትን እንዲሁም ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ በበጀት አመቱ የነበሩትን ውስጣዊና ውጫዊ
ተግዳሮቶችን በመቋቋም፣ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሁም አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኛው በማቅረብ የተሻለ የደንበኛ
እርካታ ለመፍጠርና ተሞክሮ ለማሻሻል በየደረጃው ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ
በቴሌብር አገልግሎት ከፍተኛ ደንበኛ ማፍራት የተቻለበት፣ የክላውድ ሰርቪስ እና የመሰረተ ልማት ማጋራት ስራዎችን በከፍተኛ
ትኩረት በመከወን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ስራ የተሰራበት አመትም ነበር፡፡ የውስጥ አሰራርን በማሻሻል፣
የወጪ አስተዳደርና የሀብት አጠቃቀም ባህልን በሁሉም ደረጃ ቀደም ሲል ከነበረው ጊዜ በማሳደግ ወደላቀ ውጤታማነት
የተጀመረው እንቅስቃሴ በጣም አበረታች ውጤት አስመዝግቧል፡፡

የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት ተከትሎ የበጀት አመቱን የስራ አፈፃጸም መሰረት በማድረግ አመታዊ የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ
በህብረት ስምምነቱ መሰረት የሰራተኛ ማህበሩ የስራ አስፈፃሚ አባላት ከማኔጅመንት ተወካዮች ጋር ድርድር ያካሄዱ ሲሆን ድርድሩ
በመግባባትና የጋራ አላማን መሰረት አድርጎ የተከናወነ ነበር። ድርድሩ የኩባንያውንና የሰራተኛውን ፍላጎት ያጣጣመ፣ የተቋሙን
የመክፈል አቅም እንዲሁም የኩባንያውን የገንዘብ ፍሰትና የውድድር ገበያን ታሳቢ በማድረግ የተከናወነ በመሆኑ የኢትዮ ቴሌኮም
የስራ አመራር ቦርድ የድርድር ውጤቱን ገምግሞ 25 በመቶ አመታዊ ጭማሪ እንዲሰጥ ወስኗል፡፡

ተቋማችን በበጀት አመቱ ላስመዘገበው ውጤት ሁሉም የቴሌኮም ቤተሰቦች ላደረጋችሁት አስተዋፅኦ ከልብ እያመሰገንኩ ተደራዳሪ
አካላት ላደረጉት ውጤታማ ድርድር ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ዓመታዊ የደሞዝ ጭማሪው ዝርዝር አፈፃጸም በሰው ኃብት
ዲቪዥን በኩል ሁሉም ሰራተኛ ከህዳር ወር ደመወዝ ጋር እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡

ኩባንያችን በቴሌኮም የውድድር ገበያ ባቀደው ልክ መሪነቱን ለማስቀጠል የተነደፈውን ስትራቴጂና ግቦችን አመራሩ እና የሰራተኛው
ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት በመስጠት ምርታማነቱን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ፣ በተሰጠው ኃላፊነት የኩባንያውን ሀብት
በአግባቡ የመጠቀም ባህልን በይበልጥ በማሳደግ፣ የኩባንያውን ቀጣይነት ያለው ትርፋማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ
ዘርፈ ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ የሰው ኃይላችንን ውጤታማነት ለማሳደግ በሚወሰዱት የለውጥ እርምጃዎች ረገድ
ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት ይጠበቅበታል።

በመጨረሻም ተቋማችን ያስቀመጠውን የLead እድገት ስትራቴጂ በመፈጸም በውድድር ገበያው የመሪነት ሚናውን በማረጋገጥ የላቀ
ውጤት እንዲያስመዘግብ ተባብረንና ተጋግዘን፣ ተቋማዊ እሴቶቻችንን ጠብቀን በአንድነት ለአንድ ዓላማ በመስራት ሁሉም የተቋሙ
ማህበረሰብ በአብሮነት የስኬቱ ተካፋይ እንዲሆን ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ!

ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን! እንዲሁም የእጆቻችንን ስራ ይባርክ!


በብዙ ፍቅርና አክብሮት!
ፍሬሕይወት ታምሩ
ዋና ስራ እስፈፃሚ

You might also like